የብሉይ ኪዳን መጽሐፍ ቅዱስ ጥናት

የትንቢተ ዘካርያስ ታሪካዊ ሥረ-መሠረት

አይሁድ በ539 ዓ.ዓ. ከምርኮ በተመለሱ ጊዜ ከፍተኛ መነቃቃትና ደስታ ተሰማቸው። ከሰባ ዓመታት በኋላ ከምርኮ እንደሚመለሱ እግዚአብሔር ለኤርምያስ የሰጣቸው ትንቢቶች እየተፈጸሙ ነበር። እግዚአብሔር በኢሳይያስ፥ በኤርምያስና በሕዝቅኤል የሰጣቸው ሌሎች ትንቢቶችም በቶሎ እንደሚፈጸሙ ያምኑ ነበር (ለምሳሌ፡- ኤርምያስ 30-33፤ ሕዝቅኤል 36-39)። እነዚህ ትንቢተች አይሁድ ወደገዛ ምድራቸው እንደሚመለሱ፥ መሢሑ እንደሚመጣ፥ በአሕዛብ አገዛዝ ሥር መኖራቸው እንደሚያከትም፥ ታላቁ ቤተ መቅደስ እንደገና እንደሚሠራ፥ የእግዚአብሔር መንግሥት እንደሚጀምርና ስራቸው እንደሚያበቃ የሚናገሩ ነበሩ። ስለዚህ በታላቅ ደስታ የሚመጣውን በረከት በሚጠባበቅ ልብ ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሰው፥ እግዚአብሔርን ለማምለክ መሠዊያ ከማቆማቸውም የቤተ መቅደሱን ሥራ ጀመሩ። ነገር ግን እነዚህ ተስፋዎች አለመፈጸማቸውን ለማወቅ ብዙ ጊዜ አልወሰደባቸውም። የቤተ መቅደሱን ሥራ እንደጀመሩ በተለይ ከሳምራውያን በኩል ተቃውሞ ገጠማቸው። ሳምራውያን ከፊል አይሁዳውያን ከፊል አሕዛብ የሆኑ በጥንታዊቷ የእስራኤል ምድር ይኖሩ የነበሩ ናቸው። አይሁድ የቤተ መቅደሱን ሥራ ወዲያውኑ ለማቆም ተገደዱ። ይህም አይሁድ ከአሕዛብ ተጽዕኖ ነጻ እንዳልሆኑና አገራቸው ከቁጥር የማትገባ የፋርስ ንጉሠ ነገሥት ግዛት ክፍለ ሀገር እንደነበረች አረጋገጠላቸው። አይሁድ በየስፍራው የሚመለከቱት ከ50 ዓመታት በፊት ባቢሎን ኢየሩሳሌምን በደመሰሰች ጊዜ የተረፉትን ፍርስራሾች ነበር። የቤተ መቅደሱ፥ የኢየሩሳሌም ቅጥርና በውስጧ የሚገኙ ቤቶች ፍርስራሽ በአካባቢው ነበር። አይሁድ የቤተ መቅደሱን ሥራ ለማቆም ስለተገደሉ የየራሳቸውን ቤቶች መሥራት ጀመሩ። የእግዚአብሔርን ነገሮች ረስተው፥ ለራሳቸው ፍላጎት ብቻ የሚጠነቀቁ ራስ ወዳዶች ሆኑ። ወዲያውኑ ሁሉን ነገር የሚያጥላሉ ሆኑና እግዚአብሔር የሰጠውን ተስፋ ይፈጽም ይሆንን? የሚል ጥያቄ አቀረቡ። ሌሎች ደግሞ ተስፋ መቁረጥ ጀመሩ። ደግሞም የተመለሱት አይሁድ ቁጥር ጥቂት ስለነበረ ብዙ ሕዝብ አልነበረም፡፡ ድርቅና ራብ አከታትሉ ያጠቃቸው ነበር። የእግዚአብሔር ተስፋዎች የታሉ? እግዚአብሔር በተስፋዪቱ ምድር እንደሚባርካቸው አምነው መመለሳቸው ስሕተት ነበርን? በዚህ ሁኔታ ዓመታት እየተቀጠሩ ሲሄዱ ሕዝቡ የበለጠ ተስፋ እየቆረጡና ለመንፈሳዊ ነገሮች ያላቸው ፍላጎት እየቀነሰ ይሄድ ነበር። በመካከሉ እግዚአብሔር ሁለት ነቢያትን ጠራ፡፡ በመጀመሪያ ሐጌ እግዚአብሔር ሕዝቡን ያልባረከው በራስ ወዳድነት ተይዘው የየራሳቸውን ፍላጎት ብቻ ለማሟላት ይጥሩ ስለነበር እንደሆነ ነገራቸው። ንስሐ በመግባትና ቤተ መቅደሱን በመሥራት ለእግዚአብሔር መታዘዝ ነበረባቸው። ሁለተኛ፥ ከሁለት ወራት በኋላ እግዚአብሔር ዘካርያስ የተባለ ሌላ ነቢይ ጠራ። አይሁድ ቤተ መቅደሱን መሥራት ከጀመሩ አምስት ወር አልፏቸው ነበር። በዚያኑ ወቅት ተንትናይ የተባለና ሌሎች የፋርስ ባለ ሥልጣናት አይሁድ ቤተ መቅደሱን በመሥራታቸው በፋርስ መንግሥት ላይ በእርግጥ ዓምፀው እንደሆነ ለመመርመር መጡ። እነርሱም የመሪዎችን ስም ጻፉና ወደ ዳርዮስ ደብዳቤ ላኩ። አይሁድ የግንባታውን ሥራ የቀጠሉ ቢሆንም ሥራውን መቀጠል የሚችሉት እስከመቼ እንደሆነ በማሰብ ሳይደነቁ አልቀሩም። ከዚህ ቀደም እንደሆነው ጠላታችን ያስቆሙን ይሆን? ብለው መሥጋታቸው አልቀረም። ስለዚህ ተስፋ መቁረጥ ጀመሩ። እግዚአብሔር ዘካርያስን የጠራው እዚህን ተስፋ የቆረጡ ሕዝብ እንዲያገለግል ነበር። አገልግሎቱ የሕዝቡን መንፈሳዊ ሕይወት እንደገና ማደስ ነበር። ዘካርያስ እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር የገባውን ቃል ኪዳን በማፍረሳቸው ተጠያቂዎች እንደሆኑ በመንገር ሕዝቡን ያስጠነቅቃቸዋል። ሕዝቡ ንስሐ እንዲገቡና ወደ እግዚአብሔር እንዲመለሱ ይነግራቸዋል። እግዚአብሔር የሚባርካቸው ይህ ሲሆን ብቻ ነበር። እግዚአብሔር ከእነርሱና ከመሪዎቻቸው ከዘሩባቤልና ከኢያሱ ጋር እንደሆነ የሰጣቸውም ተስፋ እንደሚፈጸም በመናገር ሕዝቡን ያበረታታል። የቤተ መቅደሱ ሥራ ይጠናቀቃል፤ እግዚአብሔር ሕዝቡን ይጠብቃል፡፡ በመሲሁም መምጣት የእግዚአብሔር ተስፋዎች ይፈጸማሉ፡፡ የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) በዚያን ዘመን አይሁድ የነበራቸው ዝንባሌ ዛሬ ብዙ ክርስቲያኖች ካላቸው ዝንባሌ ጋር የሚመሳሰለው እንዴት ነው? ለ) በዘካርያስ ዘመን የእግዚአብሔርን በረከት ለማግኘት የሚያስችሉት ቅድመ-ሁኔታዎች ከዛሬዎቹ ጋር አንድ ዓይነት የሚሆኑት በምን መንገድ ነው? ሐ) እግዚአብሔር ወደፊት ስለሚያደርገው ነገር እኛም እንደ ዘካርያስ በመናገር ክርስቲያኖችን እንዴት ማበረታታት እንችላለን? ዘካርያስ አገልግሎቱን ለብዙ ዓመታት ቀጥሉ ነበር። ዘካርያስ የአይሁድ ሕዝብ መንፈሳዊ ተሐድሶ በተካሄደና ቤተ መቅደሱ እንደገና በተሠራ ጊዜ ታላቅ ድርሻ እንዳበረከተ ከመጽሐፈ ዕዝራ እናነባለን (ዕዝራ 5፡2)። የቤተ መቅደሱ ሥራ በ516 ዓ.ዓ. ሊጠናቀቅ ዘካርያስ ምስክር እንደነበር አንጠራጠርም። አገልግሎቱን በሚጀምርበት ጊዜ ወጣት የነበረ ይመስላል (ዘካርያስ 2፡4)። ስለዚህ አስቴርን እስካገባው ንጉሥ እስከ ቀዳማዊ አርጤክስስ ዘመነ መንግሥት ድረስ ሳይኖር አልቀረም (465-424 ዓ.ዓ.)። የውይይት ጥያቄ፥ ስለ ዘካርያስ ከመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት አንብብ። በመዝገበ ቃላት ውስጥ የምታገኛቸውን ጠቃሚ ትምህርቶች ዘርዝር፡ (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡) የመመዘኛ ጥያቄዎችን ለማግኘት ከታች ያለውን ሊንክ (መስፈንጠሪያ) ይጫኑ፡፡

የትንቢተ ዘካርያስ ታሪካዊ ሥረ-መሠረት Read More »

የትንቢተ ዘካርያስ መግቢያ

ትንቢተ ሐጌ ያተኮረው እግዚአብሔር የሚመለክበትን ቤተ መቅደስ በመሥራት ላይ ነበር። ዳሩ ግን አንድን ሕንጻ ለቤተ መቅደስነት መሥራት ትክክለኛ የሆነ አምልኮ ለመካሄዱ ዋስትና አይደለም። ብሉይ ኪዳን ለእውነተኛ አምልኮ ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ አስፈላጊ መሆኑን በተደጋጋሚ ይናገራል (ለምሳሌ፡- 1ኛ ሳሙኤል 15፡22-24፤ መዝሙር (51)፡16-17)። ከነቢዩ ሐጌ በኋላ ሁለት ወር ዘግይቶ አገልግሎቱን የጀመረው ነቢዩ ዘካርያስ ተገቢና ትክክለኛ በሆነ አምልኮ አስፈላጊነት ላይ ያተኩራል። ዘካርያስ ንስሐ እንዲገቡና መንፈሳዊ ተሐድሶ እንዲኖራቸው ለሕዝቡ ጥሪ አደረገ፡፡ የእግዚአብሔር ሕዝብ በንጹሕ ልብና እግዚአብሔርን ለማምለክ በሚፈልግ ዝንባሌ ወደ እግዚአብሔር በሚቀርብበት ጊዜ ከሁሉም የበለጠ ለአምልኮ የሚያስፈልገውን ነገር አሟልተዋል ማለት ነው። አምልኮ የሚፈልገው ሕንጻን ሳይሆን በሚገባ የተዘጋ ልብን ነው፡፡ ስለዚህ ዘካርያስ የቤተ መቅደሱ ሥራ በሚጠናቀቅበት ጊዜ ሕዝቡ እግዚአብሔርን በሚገባ እንዲያመልኩ በቅድሚያ የሕዝቡን ልብ ለማዘጋጀት ጥሯል። የውይይት ጥያቄ፦ ሀ) ብዙ ክርስቲያኖች ለአምልኮ የሚሆን ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ሳይኖራቸው፥ የአምልኮ ሥርዓትን ብቻ በመፈጸም እግዚአብሔር የማይቀበለውን አምልኮ የሚያቀርቡት እንዴት ነው? ለ) ክርስቲያኖች ራሳቸውን ለትክክለኛና ለእውነተኛ አምልኮ ማዘጋጀት እንዴት ይችላሉ? ሐ) የቤተ ክርስቲያን መሪዎች አባሎቻቸው በየእሑዱ ለሚያካሄዱት የአምልኮ ፕሮግራም ራሳቸውን እንዲያዘጋጁ ለመርዳት ምን ማድረግ ይችላሉ? የትንቢተ ዘካርያስ ጸሐፊ ዘካርያስ 1፡1 «የእግዚአብሔር ቃል ወደ ዘካርያስ እንዲህ ሲል መጣ» በሚል ዓረፍተ ነገር ስለሚጀምር ቃሉ የመጣው ወደ ዘካርያስ እንደሆነ እንመለከታለን። ስለዚህ የትንቢተ ዘካርያስ ጸሐፊ ዘካርያስ እንደሆነ ለመገመት እንችላለን። ዘካርያስ ልክ እንደ ኤርምያስና ሕዝቅኤል ነቢይ ብቻ ሳይሆን፥ ካህንም ነበር፡፡ ዘካርያስ የተወለደው ከሌዊ ነገድ ከአሮን የዘር ግንድ ነበር። የተወለደውም በባቢሎን አገር በምርኮ ዘመን ሳይሆን አይቀርም። ሆኖም በ538 ዓ.ዓ. አይሁድ ወደ አገራቸው በተመለሱ ጊዜ ከአያቱ ከዒዶ ጋር አብሮ የተመለሰ ይመስላል። የዘካርያስ አያት ዒዶ ወደ ኢየሩሳሌም ከተመለሱት ዐበይት ካህናት ኣንዱ ነበር (ነህ. 12፡4 ተመልከት)። በኋላ ኢያሱ ሊቀ ካህን በነበረ ጊዜ ስለ ዘካርያስ አባት ምንም ነገር ስለማንሰማ እርሱ ሞቶ ዘካርያስ የቤተሰቡን የክህነት ሥራ ተክቶ ሳይሠራ አልቀረም (ነህምያ 12፡16)። የዘካርያስ አባት በራክዩ በመጽሐፈ ዕዝራና ነህምያ ውስጥ ስላልተጠቀሰ ብዙ ሰዎች ዘካርያስ ገና ወጣት ሳለ አባቱ በመሞቱ፥ ያደገው በአያቱ በዒዶ እጅ እንደሆነ ይስማማሉ። ዘካርያስ የነቢይነት አገልግሎቱን የጀመረው ሐጌ ማገልገል ከጀመረ ከሁለት ወራት በኋላ ስለነበር፥ ሁለቱም በኣንድነት አገልግለዋል (ዕዝራ 5፡1፤ 6፡14 ተመልከት)። ይህ ማለት ዘካርያስ አገልግሎቱን የጀመረው በ520 ዓ.ዓ. ነበር ማለት ነው። ይሁን እንጂ የዘካርያስ አገልግሎት ከሐጌ ኣገልግሎት ለበለጠ ጊዜ ቆይቷል። የመጨረሻው ትንቢቱ በ518 የተናገረው ነበር። ዳሩ ግን ዘካርያስ 9-12 የተጻፈው በዘካርያስ ሕይወት መጨረሻ ገደማ ነበር። መጽሐፉ በአጠቃላይ በዘካርያስ ብቻ ወይም በሌሎች ሁለትና ሦስት ሰዎች ስለ መጻፉ ምሁራን ክርክር ይገጥማሉ። ብዙዎቹ ሊቃውንት ዘካርያስ 1-8 የተጻፈው ቤተ መቅደሱ ከመጠናቀቁ በፊት ከ520-518 ዓ.ዓ. በነበረው ጊዜ ውስጥ በዘካርያስ እንደሆነ ይስማማሉ። ክርክሩ የሚካሄደው ከዘካርያስ 9-14 ባለው ክፍል ላይ ነው። አንዳንድ ምሁራን ዘካርያስ 9-11 የተጻፈው ባልታወቀ ሁለተኛ ሰው ሲሆን፥ ዘካርያስ 12-14 ደግሞ በሌላ ሦስተኛ ሰው እንደ ተጻፈ ያምናሉ። ሌሎች ምሁራን ደግሞ ዘካርያስ 9-14 የተጻፈው በሌላ ሁለተኛ ሰው ነው ይላሉ። እነዚህ ምሁራን የዘካርያስ የመጨረሻ ክፍል የተጻፈው ከ300-100 ዓ.ዓ. ነው ይላሉ። አንዳንድ ምሁራን ትንቢተ ዘካርያስን ቢያንስ ሁለት ሰዎች እንደጻፉትና የመጨረሻው ክፍል ዘግይቶ እንደተጻፈ የሚያምኑት ለምንድን ነው? በመጀመሪያ ደረጃ የትንቢተ ዘካርያስ የመጨረሻ ክፍል ከመጀመሪያዎቹ ስምንት ምዕራፎች ጋር ሲወዳደር በአጻጻፍ ስልቱና በሥነ-መለኮት ትምህርቱ ከፍተኛ ልዩነት ማሳየቱ በሌላ ጸሐፊ መጻፉን የሚያመለክት ነው ይላሉ። ሁለተኛ፥ ዘካርያስ “አፖሊፕቲክ” ተብሎ የሚጠራ የሥነ-ጽሑፍ ዓይነት ክፍል እንደሆነ ይናገራሉ። አፖካሊፕቲክ ሥነ-ጽሑፍ በአብዛኛው ስለ መላእክት፥ ስለ ሕልሞችና ራዕዮች ስለፍርዶችና የእግዚአብሔር ልጆች ባልተለመዱ መንገዶች ስለዳኑበት ሁኔታ የሚተርክ ነው። እነዚህ ምሁራን የዚህ ዓይነቱ የአጻጻፍ ስልት የተጀመረው ከ300 ዓ.ዓ. በኋላ ነው ይላሉ። ስለዚህ ዘካርያስ ይኖር ከነበረበት ከብዙ ዓመታት በኋላ በአንድ ሌላ ሰው ተጽፎ በትንቢተ ዘካርያስ ላይ እንደተጨመረ ያስባሉ። ወግ አጥባቂ ከሆኑ ምሁራን ግን ይህንን መጽሐፍ በአጠቃላይ የጻፈው ዘካርያስ ነው ብለው ያምናሉ። የአጻጻፍ ስልት ልዩነት የመኖሩ ምክንያት ዘካርያስ የተለያዩ ዓይነት የአጻጻፍ ስልቶችና ጽሑፎችን መጠቀሙ ነው። ዘካርያስ ቀዳሚዎቹን ስምንት ምዕራፎች የነቢይነት አገልግሎቱን በጀመረበት የመጀመሪያው የወጣትነት ዘመኑ የጻፋቸው ሲሆን፥ የመጨረሻዎቹን አራት ምዕራፎች ደግሞ በሕይወቱ ዘመኑ መጨረሻ ገደማ እግዚአብሔር ወደፊት ስለሚሆነው ነገር ከሰጠው ራእይ በኋላ የጻፋቸው ናቸው ብለው ያስባሉ። መጽሐፉ የተጠቃለለው ከ500-470 ዓ.ዓ. ነው ብለው ያስባሉ። ሁለት ወይም ከሁለት በላይ የሆኑ ጸሐፊዎች እንደ ጻፉት የሚጠቁም ምንም መረጃ ስለሌለ መጽሐፉን በሙሉ የጻፈው ዘካርያስ እንደሆነ መቀበል የተሻለ አማራጭ ነው። (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡) የመመዘኛ ጥያቄዎችን ለማግኘት ከታች ያለውን ሊንክ (መስፈንጠሪያ) ይጫኑ፡፡

የትንቢተ ዘካርያስ መግቢያ Read More »

የትንቢተ ሐጌ ዓላማ፣ አስተዋጽኦ እና ዐበይት ትምሕርቶች

የትንቢተ ሐጌ ዓላማ እግዚአብሔር ሐጌን የጠራው ለአንድ ግልጽ ዓላማ ነበር። ይኸውም ወደ ኢየሩሳሌምና ወደ ይሁዳ የተመለሱት አይሁድ ከ70 ዓመታት በፊት የተደመሰሰውን ቤተ መቅደስ በመሥራት ለእግዚአብሔር ያላቸውን ፍቅር እንዲገልጡ ማበረታታት ነበር። ትንቢተ ሐጌ አይሁድ ቤተ መቅደሱን ለመሥራት ያላቸውን ዕድልና ያለባቸውን ኃላፊነት የሚያሳስቡ አራት መልእክቶችን ይዟል። የእግዚአብሔር የቃል ኪዳኑ ሕዝብ በመሆናቸው የራሳቸውን አኗኗር ከማሻሻላቸው በፊት፥ እግዚአብሔርን ለማምለክ የሚጠቀሙበትን ቤተ መቅደስ መሥራት ግዴታቸው ነበር። እንዲሁም ሐጌ ለእስራኤል ሕዝብ ሙሉ በረከት ይዞ ስለሚመጣው መሢሕ ለአይሁድ አስታወሳቸው። አሁን ያሉበትን ሁኔታ ሳይሆን፥ የወደፊቱን የእግዚአብሔር ሥራ በማየት ሊበረታቱ ይገባ ነበር። ትንቢተ ሐጌ መሪዎች የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የሆነችውን ቤተ ክርስቲያንን ለመጠበቅ ማድረግ ስላለባቸው ነገሮች ስለሚያስተምር ዛሬም አስፈላጊነቱ የጐላ ነው። የሰዎች መንፈሳዊ ሕይወት ሲበላሽና ሲጠፋ መልሶ ማስተካከል እንዴት እንደሚቻል ያስተምራል። በዚያን ጊዜ እንደነበሩ አይሁድ፥ እኛም በራሳችን የእግዚአብሔርን ነገሮች ከራሳችን ፍላጎትና ጥቅም ለማስቀደም መቻል አለብን። ምን ያህል ገንዘብ እንደምናገኝ፣ ምን ያህል ትምህርት እንዳለን፥ በምን ዓይነት ቤት ውስጥ እንደምንኖር ወዘተ. ከማሰብ ይልቅ፥ የበለጠ ሊገደን የሚያስፈልገው ከእግዚአብሔር ጋር ስላለን ግንኙነትና ለእርሱ ስላለን መታዘዝ መሆን አለበት። የውይይት ጥያቄ፦ ሀ) የቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ግድግዳዎች ሊደመሰሱና እንደገና ሊሠሩ የሚያስፈልግበትን ሁኔታ የሚገልጽ ምሳሌ ስጥ። ለ) የቤተ ክርስቲያን መሪዎችን ጨምሮ ክርስቲያኖች ከእግዚአብሔር ነገሮች ይልቅ ለግል ምቾቶቻቸው ማሰብ የሚቀልላቸው እንዴት ነው? ሐ) ይህ ነገር ለቤተ ክርስቲያን አደገኛ የሚሆነው ለምንድን ነው? መ) የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ይህንን ለመዋጋት ምን ማድረግ ይችላሉ? የትንቢተ ሐጌ አስተዋጽኦ  1. 1ኛ መልእክት፡- ሕዝቡ ቤተ መቅደሱን እንዲሠሩ መጠራታቸውና የሰጡት ምላሽ (ሐጌ 1)፥  2. 2ኛ መልእክት፡- ቤተ መቅደሱ በእግዚአብሔር ክብር እንደሚሞላ የተነገረ ትንቢት (ሐጌ 2፡1-9)፥  3. 3ኛ መልእክት፡- ሕዝቡ ከነጹና ቤተ መቅደሱን መሥራት ከቀጠሉ እግዚአብሔር ይባርካቸዋል (ሐጌ 2፡10-19)፡  4. 4ኛ መልእክት፡- እግዚአብሔር ዘሩባቤልን እንደ ራሱ ቀለበት ማተሚያ አድርጎ መረጠው (ሐጌ 2፡20-23)።  የትንቢተ ሐጌ ዐበይት ትምህርቶች 1. መታዘዝ በረከትን አለመታዘዝ ደግሞ ቅጣትን ያመጣል፡- ዛሬ ብዙዎቻችን እንደምናስበው ሁሉ አይሁዶችም፥ በሕይወታቸው ዘመን በሚፈልጉአቸው ነገሮች ላይ እስካተኲሩ ድረስ እንደሚያገኙአቸው ያምኑ ነበር። በሕይወት ውስጥ ከሁሉ የላቀውና ተፈላጊው ነገር ሊያገኙት የሚችሉት ሥጋዊ በረከት እንደሆነ ያምኑ ነበር። ስለዚህ ጠንክረው በመሥራት ቁሳዊ በረከቶችን አገኙ። ጥሩ ቤቶች፥ ጥሩ ሥራ፥ ወዘተ. ነበራቸው። ግን አንድ ነገር ደኅና አልነበረም፤ የእህል ምርታቸው የተጠበቀውን ያህል የሚያረካ አልነበረም፤ ድርቅ ከምድሪቱ በፍጹም የሚለቅ አይመስልም። ትንቢተ ሐጌ የሚያስተምረው፥ በሕይወት ውስጥ እውነተኛ በረከትን ለማግኘት፥ ማለትም ሥጋዊ ብቻ ሳይሆን መንፈሳዊ በረከት ጨምሮ እንዲኖር፥ እግዚአብሔር እንድንሠራው የሚፈልገውን ነገር በተቀዳሚ የመሥራት ፍላጎት መኖር እንዳለበት ነው። እግዚአብሔርን መታዘዝ ያስፈልጋል። ከግል ፍላጎት በላይ ለእግዚአብሔር ጉዳይ ቅድሚያ የመስጠት ፍላጎት መኖር አለበት። ሐጌ የድርቁ ምክንያት ሕዝቡ እግዚአብሔርንና ጽድቁን አለመፈለጋቸው እንደነበር ይናገራል። ስለዚህ የእግዚአብሔርን ፍጹም በረከት መቀበል ቢፈልጉ ኖሮ እግዚአብሔርን ማስቀደም ነበረባቸው። የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ መሥራትና ለእግዚአብሔር በንጽሕናና በመታዘዝ መኖር አስፈላጊያቸው ነበር። በእርግጥ እግዚአብሔር በቁሳዊ ነገሮች የሚባርካቸው በዚህ ጊዜ ነበር። እግዚአብሔር በሥጋዊ በረከቶች ሊባርካቸው ይችላል። ከዚህ የሚበልጠው ግን እግዚአብሔር በመካከላቸው በመኖር፥ ከእነርሱ ጋር ኅብረት በማድረግ፥ በመጠበቅ የልብ ሰላምና የሕይወት ደስታን በመስጠት ይባርካቸው ነበር። ለክርስቲያኖች፥ እግዚአብሔርን ከታዘዝን ሥጋዊ በረከቶችን እንደምናገኝ የተገባልን ቃል ኪዳን የለም፡፡ ይህ ምድራዊ ሕይወት በሥቃይ፥ በስደትና በሞት የታጀበ እንደሆነ ተነግሮናል። ክርስቲያኖች የተገባልን ተስፋ ወይም ቃል ኪዳን ለእግዚአብሔርና ለክብሩ ከኖርን፥ እግዚአብሔርን ከታዘዝንና የእርሱን ነገር ካስቀደምን በሕይወታችን ከሁሉ የላቀውን በረከት እንደምናገኝ ነው። እግዚአብሔር በውስጣችን በመኖር ከእኛ ጋር ኅብረት ያደርጋል። ውጫዊ ሁኔታዎች ምንም ዓይነት ይሁኑ ሰላምና ደስታ ይኖረናል። እግዚአብሔር መጠጊያችን በመሆን በሕይወታችን ዘመን የሚያስፈልጉንን ነገሮች ሁሉ ይሰጠናል። የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ብዙ ክርስቲያኖች እምነት ካላቸው፥ ሁልጊዜ ሥጋዊ በረከቶችን እንደሚያገኙ የሚመስላቸው ለምንድን ነው? ለ) ይህ እውነት ነውን? ከሆነ ለምን? ካልሆነስ ለምን? ሐ) ከቁሳዊ በረከቶች ይልቅ መንፈሳዊ በረከቶች የበለጠ አስፈላጊ የሚሆኑት በምን መንገድ ነው? መ) ከላይ የተመለከትነው እውነት በሕይወትህ ሲረጋገጥ ያየኸው እንዴት ነው? 2. የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ፡- መጽሐፍ ቅዱስ ለቤተ መቅደስ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ይናገራል። ሙሴ የመጨረሻ ቃሎቹን ለእስራኤላውያን በሚናገርበት ጊዜ አንድ ቀን እግዚአብሔር ስሙን የሚያጸናበት የአምልኮ ስፍራ እንደሚመሠርት ጠቁሟል (ዘዳግም 14፡23-25)። በኋላም እስራኤላውያን ወደ ተስፋዪቱ ምድር እንደገቡ በሴሎ የመገናኛውን ድንኳን ተከሉ (ኢያሱ 18፡1)። ይህም ስፍራ በመጨረሻ ተደመሰሰ። ቀጥሎም ዳዊትና ሰሎሞን ቋሚ የሆነ እግዚአብሔር የሚመለክበት ቦታ ሠሩ። ታላቁ ቤተ መቅደስ ከሰባት ዓመታት በኋላ ተሠርቶ ሲያልቅ፥ በእግዚአብሔር ክብር ተሞላ (1ኛ ነገሥት 8)።  እግዚአብሔር ለአይሁዶች ያለው አሳብ የቤተ መቅደሱ ሕንጻ ሥራ መጠናቀቅ በራሱ እንደ ተልዕኳቸው ማብቂያ እንዲታይ አልነበረም፤ ነገር ግን ሕንጻው እግዚአብሔር በመካከላቸው መኖሩን እንዲያውቁ የሚያሳይ ምልክት እንዲሆን ነበር። ከእግዚአብሔር ጋር ልዩ የሆነ ግንኙነት እንዳላቸው፥ ለቃል ኪዳኑ በመታዘዝ እግዚአብሔርን እንዲያከብሩትና ሕያው የሆነውን እውነተኛውን አምላክ ከልባቸው እንዲያመልኩት ለማስታወስ ነበር። ይሁን እንጂ በኤርምያስ ጊዜ አይሁድ ውጫዊውን ሕንጻ እንደ አንድ የአስማት ሐውልት ይመለከቱት ነበር። የቤተ መቅደሱን ሕንጻ ከጠላቶቻቸው የሚጠብቃቸው ዋስትና አድርገው ይቆጥሩት ነበር። ለእግዚአብሔር ከሚሰጡት ትኩረት ይልቅ፥ ከውጭ ለሚታየው ሕንጻ የሚሰጡት ትኩረት የላቀ ነበር። በኋላም በሕዝቅኤል ራእይ የእግዚአብሔር ክብር ቤተ መቅደሱን ትቶ ሲሄድ ታየ፤ ይህም እግዚአብሔር በሕዝቡ ጣዖት አምላኪነትና አለመታዘዝ ማዘኑን የሚያሳይ ነበር። የቤተ መቅደሱ ሕንጻ ከዚያ በኋላ ለተወሰነ ጊዜ ቢቆይም እንኳ እግዚአብሔር ግን በውስጡ አልነበረም። ዳሩ ግን እግዚአብሔር ቤተ መቅደሱን ለማጥፋት ወሰነ (ኤርምያስ 7፡1-15)። ሕዝቡ በቤተ መቅደሱ ውስጥ አምልኮ መፈጸማቸውን የቀጠሉ ቢሆንም፥ ይህን የሚያደርጉት በባዶ ሕንጻ ውስጥ ነበር። በመጨረሻ በ587 ዓ.ዓ. ናቡከደነፆር ባዶውን የቤተ መቅደስ ሕንጻ ደመሰሰው። የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ዛሬ ብዙ ክርስቲያኖች ውጫዊ የሆነውን የቤተ ክርስቲያን ሕንጻ የእግዚአብሔር በረከቶችን የማግኘት ዋስትና አድርገው የሚቆጥሩት እንዴት ነው? ለ) ብዙ ክርስቲያኖች ለቤተ ክርስቲያን ሕንጻ ሥራ ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጡት ለምንድን ነው? የእነዚህ ክርስቲያኖች ዝንባሌ በኤርምያስ ጊዜ ከነበሩት አይሁዳውያን ጋር ተመሳሳይ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው? ሰባ ዓመት ያህል ካለፈ በኋላ እግዚአብሔር ቤተ መቅደሱን ይሠሩ ዘንድ ሕዝቡን አነቃቃቸው። ለእርሱ በመታዘዝ ከተመላለሱ ይሰጣቸው ዘንድ ቃል የገባላቸውን በረከት እንደ ገና እንደሚያፈስስላቸው ተስፋ ሰጠ። ቤተ መቅደሱ አሁንም ቢሆን ከሁሉ የላቀና የተሻለ ነገር አልነበረም። ነገር ግን እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር እንዳለና በመካከላቸው እንደሚኖር ያመለክት ነበር። ስለዚህ በእርሱ ፊት እንደ ቃል ኪዳን ሕዝብ መመላለስ ነበረባቸው። ቤተ መቅደሱ ለእግዚአብሔር በጣም አስፈላጊ የሆነውና አይሁድ እንዲሠሩት የታዘዙት ለምን ነበር? እግዚአብሔር ቤተ መቅደሱ አይሁድ ሁሉ የሚያመልኩበት ስፍራ እንዲሆን ይፈልግ ነበር። አይሁድ ቤተ መቅደሱን በተመለከቱና በዚያ አምልኮን ባቀረቡ ቁጥር እግዚአብሔር በመካከላቸው እንዳለ መገንዘብ አስፈላጊያቸው ነበር። ይህም የእግዚአብሔር የቃል ኪዳኑ ሕዝብ እንደሆኑና እንደ ቃል ኪዳን ሕዝቡም ለእግዚአብሔር በመታዘዝ መኖር እንዳለባቸው ያስታውሳቸው ነበር። ነገር ግን የሚያሳዝነው አይሁድ ልክ እንደቀደሙት አባቶቻቸው ፈጥነው የቤተ መቅደሱን መኖር ለእግዚአብሔር በረከት መኖር ማረጋገጥ አድርገው ቆጠሩት። ለእውነተኛው የእግዚአብሔር አምልኮ ወይም እግዚአብሔርን መታዘዝ ጉዳይ ብዙ ትኩረት አይሰጡም ነበር። ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረ ጊዜ አይሁድ ከእግዚአብሔር ይልቅ ቤተ መቅደሱን ያከብሩ ነበር። ኢየሱስም እንደ ኤርምያስ ስለ ቤተ መቅደሱ መደምሰስ ተነበየ (ሉቃስ 21፡5-6)። በዓይን የሚታየው ግዑዝ ሕንጻ አስፈላጊ እንዳልሆነ፥ ዳሩ ግን እግዚአብሔር በሰው ልብ ቅንነትና በልብ ውስጥ በሚፈጸም ንጹሕ አምልኮ እንደሚደሰት ለሳምራዊትዋ ሴት ተናግሯል። “በእውነትና በመንፈስ” እስከሆነ ድረስ ሰው የትም ቦታ እግዚአብሔርን ሊያመልከው ይችላል (ዮሐንስ 4፡21-24)። በኋላም ሐዋርያው ጳውሎስ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ በዓይን የምናየው ውጫዊ ሕንጻ እንዳልሆነ አስተምሯል። ይልቁንም ኢየሱስ የሚኖርበት የእያንዳንዱ ክርስቲያን ልብ ቤተ መቅደስ ነው (1ኛ ቆሮ. 6፡19)። በተጨማሪም እግዚአብሔር በመካከላቸው ስለሚኖር ማናቸውም ክርስቲያኖች የተሰበሰቡበት ቦታ

የትንቢተ ሐጌ ዓላማ፣ አስተዋጽኦ እና ዐበይት ትምሕርቶች Read More »

ትንቢተ ሐጌ መግቢያ

የውይይት ጥያቄ ማቴዎስ 6፡33 አንብብ። ሀ) ከሁሉ አብልጠን ልንፈልጋቸው የሚገቡ ነገሮች ምንድን ናቸው? ለ) «ይህም ሁሉ» ምንን ያመለክታል? ሐ) ይህን ጥቅስ በሕይወትህ የተጠቀምህበት እንዴት ነው? ምናልባት በሕይወታችን እጅግ አስቸጋሪ የሆነውና ክርስቲያኖች እንደመሆናችን ለይጣን ብዙ ጊዜ እኛን የሚያሸንፍበት መንገድ ለክርስቶስ ኢየሱስ ያለንን ፍቅር በሌላ ፍቅር እንድንተካ ማድረጉ ነው። ይህም ሌላ ፍቅር ቤተሰባችን፥ ቁሳዊ ሀብታችን ወይም ንብረታችን፥ በሌሉች ዘንድ ያለን ታዋቂነት፥ ትምህርት፥ ወዘተ. ላይ ያተኩረ ሊሆን ይችላል። ሰዎችን ወይም የተለያዩ ነገሮችን ከእግዚአብሔር በላይ መውደድ ስንጀምር ሕይወታችንም መለወጥ ይጀምራል። ለእግዚአብሔር ነገሮች ያለን ጥልቅ ስሜት ይጠፋል። እግዚአብሔር የሚፈልጋቸውን ነገሮች ከመፈለግና ከማድረግ ይልቅ በራሳችን ፍላጎቶች ላይ የበለጠ ማተኮር እንጀምራለን። ሐጌ በይሁዳ ባገለገለበት ጊዜ፥ የእስራኤል ሕዝብ ከምርኮ ተመልሰው በኢየሩሳሌምና በአካባቢዋ ይኖሩ ነበር። እግዚአብሔርን ይወዱት ነበርና መጀመሪያ ወደ ኢየሩሳሌም በተመለሱ ጊዜ በቅድሚያ ያደረጉት ነገር እግዚአብሔርን በማክበር እርሱን ማምላክ የሚችሉበትን ቤተ መቅደስ መሥራት መጀመር ነበር። ዳሩ ግን ይህ ብዙ አልቆየም። የገጠማቸው ተቃውሞና የራሳቸውን ኑሮ ለማሻሻል የነበራቸው ፍላጎት የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ መሥራታቸውን እንዲያቆሙና ለራሳቸው ጥሩ ጥሩ ቤቶችን እንዲሠሩ አደረጋቸው። የራሳቸውን ነገር በማስቀደም የእግዚአብሔርን ነገር የመጨረሻ አደረጉ። በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር አይሁድ የእርሱን በረከት የሚፈልጉ ከሆነ ከራሳቸው የግል ፍላጎት ይልቅ የእግዚአብሔርን ነገር ማስቀደም እንደነበረባቸው ያስታውሳቸው ዘንድ ነቢዩ ሐጌን ጠራው። ያንን ካደረጉና የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ከሰሩ እግዚአብሔር ሊያከብራቸውና ሊባርካቸው ቃል ገብቶ ነበር። የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ዛሬ ክርስቲያኖች ብዙ ጊዜ የራሳቸውን ፍላጎት ከእግዚአብሔር ፍላጎት የሚያስቀድሙባቸውን መንገዶች ዘርዝር። ለ) ለእግዚአብሔር ነገር ቅድሚያ ሰጥተን የራሳችንን ፍላጎት የመጨረሻ ማድረግ ብዙ ጊዜ የሚከብደን ለምንድን ነው? የትንቢተ ሐጌ ጸሐፊ አይሁድ በ539 ዓ.ዓ. ከምርኮ ከተመለሱ በኋላ በይሁዳ ካገለገሉት ሦስት ነቢያት (ሐጌ፥ ዘካርያስና ሚልክያስ መካከል አንዱ ሐጌ ነበር። ሐጌ ያገለገለው ዘካርያስ ባገለገለበት ዘመን ነበር። በሐጌ 1፡1 የእግዚአብሔር ቃል በሐጌ በኩል እንደመጣ የእስራኤል ሕዝብ መሪዎች ለነበሩት ለዘሩባበልና ለኢያሱ ተጽፏል። ስለዚህ ትንቢተ ሐጌን የጻፈው ሐጌ ነው ማለት ትክክል ነው። ስለ ሐጌ የምናውቀው ተጨማሪ ነገር በጣም ጥቂት ነው። አንዳንዶች ሐጌ ቀድሞ በኢየሩሳሌም የነበረውን ቤተ መቅደስ ያየ፥ አሁን እድሜው ከ70 ዓመት በላይ የሆነ ሽማግሌ ነው ይላሉ። ሐጌ በሽባዛር መሪነት መጀመሪያ ከምርኮ ከተመለሱት መካከል የነበረ ሰው ሳይሆን አይቀርም። ይሁን እንጂ በዕዝራ 1-2 ከተዘረዘሩት ከምርኮ ከተመለሱት ውስጥ አልተመዘገበም። አንዳንዶች ስለ ተቀደሰ የአምልኮ ሥርዓት ስለሚያስተምር (ሐጌ 2፡11-14) ካህን ነበር ብለው ያስባሉ። ስለ ሐጌ የምናውቀው ጥቂት ቢሆንም እንኳ ትንቢት የተነበየው መቼ እንደነበር በትክል እናውቃለን። ሐጌ ትንቢቱን መቼ እንደተናገረ በጥንቃቄ መዝግቧል። አራቱም መልእክቶቹ የፋርሱ ንጉሥ ዳርዮስ በነገሠ በሁለተኛው ዓመት በአራት ወራት የተሰጡ ነበሩ። የመጀመሪያው ትንቢት ነሐሴ 22 ቀን 520 ዓ.ዓ. የተነገረ ሲሆን፥ የመጨረሻው ደግሞ ታኅሣሥ 18 ቀን 520 ዓ.ዓ. ነበር። ሐጌ አገልግሎቱን የጀመረው ከዘካርያስ ሁለት ወር ቀድሞ ነው። ትንቢተ ሐጌ የተጻፈው ወዲያውኑ ትንቢቱ እንደተነገረ መሆን አለበት። ምክንያቱም የቤተ መቅደሱ ሥራ ማለቁን የሚጠቁም ምንም ነገር በመልእክቱ ውስጥ አልተገኘም። እግዚአብሔር ሐጌን የጠራው ለአንድ ግልጽ ዓላማ ነበር። አገልግሎቱ ረጅም ስላልነበረ ስለ ሕይወቱ ብዙ አናውቅም። ዳሩ ግን እግዚአብሔር ሊጠራው ሐጌ በታማኝነትና በድፍረት የእግዚአብሔርን ቃል አስተምሯል። እግዚአብሔር ሕዝቡ እንዲነጹና የቤተ መቅደሱን ሥራ እንዲፈጽሙ ይፈልግ ስለነበር በሐጌ በኩል አነቃቃቸው። ሐጌ ተከናወነለት፤ ከአራት ወራት አገልግሎት በኋላ የነቢይነት ተግባሩ ተጠናቀቀ። ቤተ መቅደሱን እንዲሠሩ ሕዝቡን አነቃቃ። ሕዝቡም የቤተ መቅደሱን ሥራ ጀምረው ከአምስት ዓመታት በኋላ ተጠናቀቀ። እግዚአብሔር በተለያየ መንገድ በሰዎች እንዴት እንደሚጠቀም ማስተዋል የሚያስገርም ነው። እግዚአብሔር አንዳንድ ሰዎችን ይጠራና የረጅም ጊዜ አገልግሎት ይሰጣቸዋል። ኤርምያስ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ነው። ይሁን እንጂ እንደ ሐጌ ላሉ ሌሎች ደግሞ አንድ የተለየ አገልግሎት ዐቅዶላቸው ነበር። እግዚአብሔር ሰዎችን ይጠራል እነርሱም የተጠሩበትን አገልግሉት ፈጽመው ወደ ቀድሞው ሥራቸው ይመለሳሉ። ይህ ነገር መሪዎችን ሁሉ የሚያስታውሰን አገልግሎታችን ለምን ያህል ጊዜ እንደሚቆይ የሚወስን እግዚአብሔር ብቻ መሆኑን ነው። እንዴት እንደሚከናወንልንና በዘመናችን ሁሉ ጥቂት ፍሬ እያፈራን እንደምናገለግል ወይም ቤተ ክርስቲያንን በከፍተኛ ደረጃ የሚለውጥ አንድ ስብከት ብቻ እንደምናቀርብ የሚወስነው እርሱ ነው። መሪዎችን የሚጠራ፥ የአገልግሎታቸውን ዘመንና የስኬታማነታቸውን መጠን የሚወስን እግዚአብሔር እንደሆነ ልብ በል። የእኛ ኃላፊነት ለእግዚአብሔር ታማኞች መሆንና የቀረውን ነገር ለእርሱ ሉዓላዊ ሥልጣን መተው ነው። እግዚአብሔር ከእኛ ይልቅ ሌላውን ሰው የበለጠ በሚታይ መንገድ ቢጠቀምበት መቅናት ጨርሶ አይገባንም። የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) እግዚአብሔር ሌላውን ሰው ሲጠራ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ከሥልጣናቸው መውረድ የሚከብዳቸው ለምንድን ነው? ለ) እንዲህ የሚያደርጉ ከሆነ፥ ስለ አገልግሎት ያላቸው አመለካከት ምንድን ነው? ) በርካታ መሪዎች ከእነርሱ በተሻለ ሁኔታ ውጤታማና ታዋቂ በሆኑ ሌሎች መሪዎች የሚቀኑት ለምንድን ነው? የትንቢተ ሐጌ ታሪካዊ ሥረ-መሠረት የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ኤርምያስ 25፡1-14 አንብብ። ኤርምያስ የእስራኤል የምርኮ ዘመን ምን ያህል ይሆናል ብሎ ነበር? ለ) ዕዝራ 1፡1-8 አንብብ። ምርኮኞቹን የለቀቀው የፋርስ ንጉሥ ስም ማን ነበር? ሐ) የአይሁድን ሕዝብ ከምርኮ ይዞ የተመለሰው የመጀመሪያ መሪ ማን ነበር? እግዚአብሔር ለበርካታ ዘመናት በይሁዳ የነበሩትን የአይሁድ ሕዝብ ንስሐ ካልገቡና እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር ላደረገው ቃል ኪዳን ካልታዘዙ ወደ ምርኮ እንደሚልካቸው በነቢያት መልእክት አስጠንቅቆአቸው ነበር። በመጨረሻም እግዚአብሔር በሙሴ በኩል ለአይሁድ ቃል ኪዳን በሰጣቸው ጊዜ እንዳስጠነቀቃቸው (ዘዳግም 28)፥ በ586 ዓ.ዓ. ከ50 ዓመታት በላይ በስደት ወደቆዩበት ወደ ባቢሎን አስማረካቸው። (ማስታወሻ፡- በኤርምያስ የተተነበየው 70 ዓመት፥ አይሁድ መጀመሪያ ወደ ምርኮ ከሄዱበት ከ605 ዓ.ዓ. ጀምሮ እስከተመለሱበት እስከ 538 ዓ.ዓ. ድረስ የነበረው ጊዜ ነው። አንዳንዶች ይህን ምርኮ ቤተ መቅደሱ ከተደመሰሰበት ከ586 ዓ.ዓ. ድረስ እንደገና እስከተሠራበት እስከ 516 ዓ.ዓ. ያለውን ጊዜ የሚያካትት ነው ይላሉ)። አይሁድ የተማረኩት እንዲጠፉ ላይሆን፥ ከኃጢአታቸው እንዲነጹና ወደ እግዚአብሔር ተመልሰው ለቃል ኪዳኑ ታዛዦች እንዲሆኑ ለማበረታታት ነበር። እግዚአብሔር ለሜዶንና ለፋርስ መንግሥት ሥልጣን ከሰጠ በኋላ አይሁድና ሌሎች ሕዝቦች ወደ ገዛ ምድራቸው እንዲመለሱ የሚደነግግ አዋጅ ያወጣ ዘንድ የንጉሥ ቂሮስን ልብ አነሣሣ። በ538 ዓ.ዓ. ቂሮስ ኣይሁድ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ፈቀደ። የሚያስገርመው ግን ብዙዎቹ አይሁድ ወደ ጳለስጢና ለመመለስ ፈቃደኞች አለመሆናቸው ነው። ጥሩ ኑሮ በሚኖሩበት በባቢሎንና በሌሎች አሕዛብ አገሮች መኖርን መረጡ። በሽሽባደር መሪነት ቁጥራቸው ኀምሳ ሺህ የሚደርሱ አይሁድ ወደ አገራቸው ተመለሱ። ሸሽባደር የይሁዳ መስፍንና የአይሁድ ማኅበረሰብ የመጀመሪያ ገዥ ነበር። ሰራያ የዘሩባቤል ሌላው ስሙ ሳይሆን አይቀርም። አይሁድ ወደ ኢየሩሳሌም ለመመለስ ብዙ ወራት ከተጓዙ በኋላ ኢየሩሳሌም እንደደረሱ ወዲያውኑ ቤተ መቅደሱን መሥራት ጀመሩ። በታላቅ ደስታ የቤተ መቅደሱን መሠረት ጣሉ፡፡ ዳሩ ግን ወዲያውኑ ተቃውሞ ተነሳና የቤተ መቅደሱ ሥራ ቆመ። ከዚያ በኋላ አይሁድ የራሳቸውን ኑር ወደማሻሻል ዞር አሉ። ንግድና የእርሻ ሥራ ጀመሩ። አንዳንዶች በጣም ሀብታሞች በመሆን ያማሩ ቤቶችን ይሠሩ ጀመር። ወዲያውኑ ለለ መንፈሳዊ ሕይወታቸው የማይገዳቸው ሆኑና ቤተ መቅደሱን ለመሥራት የነበራቸው ፍላጎት ጠፋ። ድርቅና ራብ ወደ ይሁዳ መጣ። እነርሱ አሁንም በፋርስ ቁጥጥር ሥር ነበሩ፤ እንደ ኤርምያስና ሕዝቅኤል ባሉ ነቢያት አማካይነት የተሰጡ ተስፋዎች አልተፈጸሙም ነበር። ስለዚህ ሕዝቡ ተስፋ ቆረጡ። የቤተ መቅደሱ መሠረት ተጥሎ ምንም ሳይሠራ 18 ዓመት ያህል አለፈ። የፋርስ ንጉሥ ቂሮስ በ529 ዓ.ዓ. ሞተ። ለሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት በትረ መንግሥቱን ለመጨበጥ ከፍተኛ ትግል ተካሂዶ ነበር፤ በመጨረሻ በ521 ዓ.ዓ. በትረ መንግሥቱን የጨበጠው ቀዳማዊ ዳርዮስ ከ521-486 ዓ.ዓ. በሥልጣን ላይ ቆየ። ዳርዮስ በመላው ግዛቱ ውስጥ በነበሩት ሃይማኖቶች ደስ ተሰኝቶ ነበር። በዚሁ ጊዜ አካባቢ ማለት በ520 ዓ.ዓ. አይሁድ የቤተ መቅደሱን ሥራ ከፍጻሜ ያደርሱ ዘንድ ለማበረታታት የሚሆን መልእክት ያደርስ ዘንድ እዚአብሔር ነቢዩ ሐጌን ጠራው። በዚህ ጊዜ የሕዝቡ መሪዎች አዲሱ ገዥ ዘሩባቤል እና ካህኑ ኢያሱ ነበሩ። ከካርያስ ጋር በመሆን የቤተ መቅደሱን ሥራ

ትንቢተ ሐጌ መግቢያ Read More »

የትንቢተ ሶፎንያስ ዓላማ እና ዐብይ ትምሕርት

የትንቢተ ሶፎንያስ ዓላማ ከይሁዳ ውድቀት በፊት እግዚአብሔር የመጨረሻ መልእክተኞች ካደረጋቸው ቃል አቀባዮቹ አንዱ ሶፎንያስ ነበር። ሶፎንያስ በእግዚአብሔር የተላከው በክፋታቸው ምክንያት በቅርብ ጊዜ ስለሚፈጸምባቸው ፍርድ በመናገር የይሁዳን ሕዝብ ለማስጠንቀቅ ነበር። ሕዝቡ ንስሐ ካልገቡና አኗኗራቸውን ካልለወጡ ሊመጣባቸው ስላለው ፍርድ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ለማቅረብ እግዚአብሔር ተጠቀመበት። በመሆኑም ሊመጣ ስላለው «የጌታ ቀን» ተናገረ። ይህ ቀን አብዛኛው ሕዝብ እንደሚጠብቀው የደስታና የበረከት ቀን አይሆንም። ይልቁንም ከበረከቱ ጊዜ በፊት በኃጢአተኞች ሁሉ ላይ ከፍተኛ የፍርድ ጊዜ ይኖራል። ፍርዱ የሚጀምረው በኢየሩሳሌም በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ ነው። ነገር ግን ክፉና ኃጢአተኛ በሆኑ ሰዎች ሁሉ ላይም ይፈጸማል። ትሑታን የሆኑና ወደ እግዚአብሔር ለመመለስ የሚፈልጉ ሰዎች ንስሐ እንዲገቡና የእግዚአብሔርን ምሕረት እንዲፈልጉ ተጠርተው ነበር። ሶፎንያስ የይሁዳ ሕዝብ ተማርከው ወደ ባቢሎን እንደሚወሰዱ በግልጽ ባያመለክትም፥ በይሁዳ ላይ ስለሚመጣ ትልቅ ጥፋትና ከምርኮ ስለ መመለሷም ተናግሮ ነበር (ሶፎንያስ 3፡20)። ዛሬ ለሰዎች መስበክ ያለብን ወንጌል ሶፎንያስ ከብዙ ዓመታት በፊት ካስተላለፈው መልእክት ጋር ተመሳሳይ ነው። በአንድ በኩል ንስሐ ለሚገቡና ለእግዚአብሔር ወደ መታዘዝ ዞር ለሚሉ ሰዎች የደስታ፥ የሰላምና የመንፈሳዊ በረከት ተስፋ እንዳላቸው ልንነግራቸው እንችላለን። በሌላ በኩል ደግሞ ለእግዚአብሔር አለመታዘዝ የሚያስከትላቸውን ነገሮች ለሰዎች ማሳየት አስፈላጊ ነው። ወንጌል በኢየሱስ ክርስቶስ የማያምኑ ሰዎች የዘላለም ሥቃይ እንደሚያገኛቸው የሚናገር መልእክትም አለው። ልክ አይሁዶች ያስቡት እንደነበረው፥ ሰዎች መልካም ሆኑ ክፉ እግዚአብሔር ግድ እንደሌለው አድርገው እንዲያስቡ መፍቀድ የለብንም። ንስሐ ገብተው፥ በኢየሱስ ማመንና ለእግዚአብሔር በመታዘዝ መራመድ እንዳለባቸው። አለበለዚያ ግን የእግዚአብሔር ፍርድ እንደሚጠብቃቸው ልናሳስባቸው ይገባል። የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) በአዲስ ኪዳን ውስጥ ሰዎች ንስሐ ባይገቡ በእግዚአብሔር እንደሚፈረድባቸው በመናገር የሚያስጠነቅቁትን ጥቅሶች ዘርዝር። ለ) እነዚህ ጥቅሶች ለማያምኑ ሰዎች ልንነግራቸው የሚገባው የወንጌል ክፍል የሚሆኑት እንዴት ነው? ሐ) ክርስቲያኖችን ሳይቀር ስለሚመጣው ፍርድ በመናገር የሚያስጠነቅቁ ጥቅሶች የትኞቹ ናቸው? የትንቢተ ሶፎንያስ ዓቢይ ትምህርት እንደ አብዛኛዎቹ ሌሎች ነቢያት፥ ሶፎንያስም ሊመጣ ባለው «የጌታ ቀን» ላይ በማተኮር ይናገራል። ሶፎንያስ ስለ ጌታ ቀን የሚያስተምራቸው ትምህርቶች በአንድ ክፍለ ጊዜ ውስጥ መድቦ ለመግለጽ የሚያስቸግሩ ናቸው። ሶፎንያስ ስለ ጌታ ቀን የሚናገረው ሰፋ ያለ አሳብ በሚገልጡ ቃላት ነው። በመሆኑም በዚያኑ ዘመን በይሁዳና በአሕዛብ ሁሉ ላይ በሚመጣው የጌታ ቀንና በመጨረሻው ዘመን በሚመጣው የጌታ ቀን መካከል ብዙ ልዩነት አላደረገም። በትንቢተ ሶፎንያስ ውስጥ የጌታ ቀን የተገለጸው በታሪክ ውስጥ የሚከሰት አንድ የተወሰነ ቀን ወይም ጊዜ ተደርጎ ሳይሆን፥ የማያቋርጥ የታሪክ ሂደት ሆኖ ነው። እግዚአብሔር በፍርድ ወይም በበረከት ፈቃዱን የፈጸመበት ማንኛውም ቀን የጌታ ቀን ተብሎ ሊጠራ ይችል ነበር። ያ የጌታ ቀን ሰዎችንና ነገሮችን ሁሉ የሚነካ ነው። በጌታ ቀን የሚሆኑትን የሚከተሉትን ነገሮች አስተውል፡- 1. ለይሁዳ፥ የጌታ ቀን ሶፎንያስ ከነበረበት ዘመን ጋር የሚቀራረቡ ውጤቶች ነበሩት። የጌታ ቀን አይሁድ እጅግ ከባድ በሆነ ሁኔታ የእግዚአብሔርን ፍርድ የሚቀበሉበት ቀን ነው። ይህ ቀን ተማርኮ ወደ ባቢሎን መሄድንም እንደሚያጠቃልል እናውቃለን። በተጨማሪም ያ የባቢሎን ምርኮ በዘመን መጨረሻ ኢየሱስ ለመግዛት ከመምጣቱ በፊት ይሁዳ የምትጋፈጠውን ከፍተኛ ጥፋት የሚያመለክት ተምሳሌት ነው። ስለዚህ ይህ ቀን በዘሩባቤል፥ በዕዝራና በነህምያ መሪነት አይሁድ ከምርኮ የሚመለሱበትን ጊዜ ስለሚጨምር የበረከት ጊዜም ነበር። እንደዚሁም በዘመናት መጨረሻ የእስራኤል ሕዝብ ሁሉ በአካል ወደ ምድራቸው ተመልሰው፥ ከመንጻታቸው የተነሣ በረከቶችን የሚቋደሱበትና አይሁድ ሁሉ እግዚአብሔርን በእውነት የሚያመልኩበትን ታላቁን የጌታ ቀን የሚያመለክት ነበር።  2. አሕዛብም የጌታን ቀን ምንነት ያውቃሉ። አሦርና ሌሎች አሕዛብ እግዚአብሔር ፍርድን አምጥቶባቸዋልና በታሪክ ያንን የፍርድ ቀን ያውቃሉ። በዚህ ዓይነት አሦር በባቢሎን ተደመሰሰች፤ ፍልስጥኤም፥ ሞዓብ፥ አሞንና ኩሽም ጠፉ። እነዚህ ጥፋቶች አሕዛብ ሁሉ የእግዚአብሔርን ፍርድ የሚቀበሉበት የመጨረሻው ታላቁ የጌታ ቀን ምሳሌዎች ነበሩ።  ያ ቀን ለአይሁድ እንደሆነው ሁሉ ለአሕዛብም የበረከት ቀን ይሆናል። እግዚአብሔርን ለማክበር የሚመለሱ አሕዛብም በረከትን ያገኛሉ።  3. ፍጥረታት ሁሉ የጌታን ቀን ያውቃሉ። እንስሳት፥ ከዋክብት፥ ፀሐይ ወዘተ. ሁሉም እግዚአብሔር በፍርድ በሚሠራበት ቀን የፍርዱ ተካፋዮች ይሆናሉ። ይህም ምድርን በተለያዩ ጊዜያት በሚመቱ የተፈጥሮ አደጋዎች በከፊል ታይቷል። ይሁን እንጂ በተለይ የሚታየው በዘመናት ፍጻሜ ነው። የዮሐንስ ራእይ ፍጥረታት በተለያየ ሁኔታ የሚመቱባቸዉን መንገዶች በግልጽ ያሳያል። ያ ቀን የሚያበቃው እግዚአብሔር አሁን ያሉትን ሰማይና ምድርን በእሳት ሲያጠፋና አዲስ ሰማይና ምድር ሲፈጥር ይሆናል (2ኛ ጴጥሮስ 3፡10፤ ራእይ 21፡1)። የውይይት ጥያቄ፥ 2ኛ ጴጥሮስ 3፡10-13 አንብብ። ሀ) ስለ ጌታ ቀን የሚኖረን ግልጽ ግንዛቤ፥ ዛሬ የምንኖረውን ኑሮ መለወጥ የሚገባው በምን መንገዶች ነው? ለ) ስለ ጌታ ቀንና በዚህም ምክንያት እንዴት መኖር እንዳለባቸው የቤተ ክርስቲያንህን አባላት ለማስተማር ዐቅድ።  የውይይት ጥያቄ፥ ሶፎንያስ 1-3 አንብብ። ሀ) እግዚአብሔር ይሁዳ ይፈረድባታል ያለው ለምንድን ነው? ለ) በጌታ ቀን የሚፈጸሙ ሁኔታዎች የሚነኳቸውን ነገሮች ዝርዝር። ሐ) በጌታ ቀን እንደሚሆኑ ተስፋ የተሰጡ በረከተች ምንድን ናቸው?  1. በሁሉም ላይ ስለሚደርስ ፍርድ የተነገረ አጠቃላይ መልእክት (ሶፎንያስ 1፡1-3) የሶፎንያስ መልእክት ጠንከር ያለና አስደንጋጭ ነበር። ሶፎንያስ በምድር ላይ ስለሚሆነው ታላቅ ጥፋት በመናገሩ፥ ሰዎች ራሳቸውን በመመርመር በእግዚአብሔር ፊት ትክክለኛ መሆናቸውን ለማረጋገጥ ይጥራሉ የሚል እምነት አድሮበት ነበር። በራሳቸው ረክተው በመኖራቸው እንዲደነግጡና ካሉበት ሁኔታ እንዲወጡ ለማድረግ አስቦ ነበር። ሶፎንያስ የዘመን መጨረሻን አሻግሮ በማየት ነገሮች ሁሉ እንዴት በእግዚአብሔር እንደሚዳኙ ሰፋ አድርጎ አሳይቷል።  2. በጌታ ቀን በይሁዳ ላይ የሚመጣው ፍርድ (ሶፎንያስ 1፡4-18) ቀጥሎ ሶፎንያስ ወደ ይሁዳ ዞረ። የእግዚአብሔርን ፍርድ ሊያመጣባቸው ወዳለው ወደ ይሁዳ ኃጢአት አመለከተ። የጣዖት አምልኮ በእጅጉ ተንሰራፍተ ነበር። ሕዝቡ እግዚአብሔርን አልፈለጉም፤ ወይም ከኃጢአታቸው ንስሐ አልገቡም። መሪዎች በኃጢአት ይኖሩ ነበር። ስለዚህ እግዚአብሔር ፍርድ እንደሚያመጣና የይሁዳ ምድር እንደምትደምሰስ ተናገረ። ይህም ከ40 ዓመታት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ በባቢሎናውያን አማካይነት ተፈጸመ።  3. በጌታ ቀን በአሕዛብ ሁሉ ላይ የሚመጣው ፍርድ (ሶፎንያስ 2፡1-3፡8) እግዚአብሔር ንስሐ እንዲገቡ ዕድል ሳይሰጥ በሰዎች ላይ አይፈርድም። ሶፎንያስ ወደ እግዚአብሔር እንዲመለሱና በዚያን ቀን ከሚገለጠው ቁጣ እንዲያመልጡ ሕዝቡን፥ በተለይም አይሁድን አጥብቆ ጠይቆአቸው ነበር። ሶፎንያስ በዙሪያው ያሉትን አንዳንድ አሕዛብና መንግሥታት በመመልከት፥ እግዚአብሔር በእነርሱም ላይ እንደሚፈርድ አመለከተ። እነዚህ የአሕዛብ መንግሥታት በይሁዳ ላይ ችግር የፈጠሩ ነበሩ። መደምሰስና መጥፋት ብቻ ሳይሆን አንድ ቀን የእነዚህን አሕዛብ ምድር አይሁድ ይወርሱታል። 4. በጌታ ቀን የሚመጡ በረከቶች (ሶፎንያስ 3፡9-20) የነቢያት መልእክት ብዙ ጊዜ የሚጠቃለለው፥ በፍርድ ሳይሆን በማበረታቻ ወይም በማጽናኛ ቃል ነበር። ሶፎንያስ ስለ መጪው የጌታ ቀን በድጋሚ ይናገራል። በዚህ ጊዜ ግን የሰዎች ክፋት አንድ ቀን እንደሚወገድ ይናገራል። ከናፍርት ለአምልኮ ይነጻሉ። ሰዎች ለእግዚአብሔር ይታዘዛሉ። በተበተኑት አይሁድ መካከል ትሑታን የነበሩትና በእግዚአብሔር የሚያምኑት ሰዎች ወደ አገራቸው ይመለሳሉ። እግዚአብሔር በእነርሱ ደስ ይለዋል። እነርሱም በሁሉ ይከበራሉ። የውይይት ጥያቄ፦ ሀ) በትንቢተ ሶፎንያስ ውስጥ የሚገኙትን ጠቃሚ የሆኑ መንፈሳዊ ትምህርቶች ዘርዝር ለ) የቤተ ክርስቲያን አባሎች በሙሉ እነዚህን ትምህርቶች ማወቅ የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው? (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡) የመመዘኛ ጥያቄዎችን ለማግኘት ከታች ያለውን ሊንክ (መስፈንጠሪያ) ይጫኑ፡፡

የትንቢተ ሶፎንያስ ዓላማ እና ዐብይ ትምሕርት Read More »

ትንቢተ ሶፎንያስ መግቢያ

የውይይት ጥያቄ፥ ሶፎንያስ 1፡12 አንብብ። ሀ) እግዚአብሔር እቀጣለሁ ያለው ምን ዓይነት ሰዎችን ነበር? ለ) ሰዎች ስለ እግዚአብሔር የነበራቸው የተሳሳተ አመለካከት ምን ነበር? ለእግዚአብሔር ሕዝብ እጅግ አደገኛ ከሆኑ ነገሮች ዋናው በእግዚአብሔር ላይ በግልጽ ማመፅ አይደለም። ወደ ሐሰት ትምህርቶች ወይም ሃይማኖቶች መለወጥም አይደለም። የእግዚአብሔር ሰዎች በራሳቸው መርካታቸው እንጂ። ሶፎንያስ ባገለገለበት ዘመን በይሁዳ ላይ ችግር ከፈጠሩት ኃጢአቶች አንዱ ይህ ነበር። በዮሐንስ ራእይ፥ እግዚአብሔር የሉዶቅያን ቤተ ክርስቲያን፥ ባላት መንፈሳዊ ሕይወት በመርካቷና በራድ ወይም ትኩስ ባለመሆኗ ሲገሥጻት እንመለከታለን (ራእይ 3፡14-20)። ቤተ ክርስቲያን ወይም ክርስቲያን ለብ የሚለውና በራሱ የሚረካው ለምንድን ነው? በርካታ ምክንያቶች አሉ፡- በመጀመሪያ፥ ቤተ ክርስቲያን ለብ የምትለው በግል ወይም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በሚደረግ አምልኮ ሁልጊዜ አዲስና ሕያው በሆነ መንገድ ከማምለክ ይልቅ የአምልኮ ሥርዓቶችን ብቻ የመከተል አዝማሚያ ሲኖር ነው። ሁለተኛ፥ ቤተ ክርስቲያን በራሷ የረካች የምትሆነው እርስዋ ወይም ክርስቲያን እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ሌሎች ሰዎች ከመድረስ ይልቅ፥ ለራሳቸው ፍላጎትና ምቾት አጥብቀው ማሰብ ሲጀምሩ ነው። በቤተ ክርስቲያን ወይም በእያንዳንዱ ክርስቲያን ሕይወት ውስጥ ራስ ወዳድነት ሲንሰራፋ በመንፈሳዊ ሕይወት ረገድ በራስ መርካትን ያስከትላል። ሦስተኛ፥ የጠፉትን የመፈለግና በወንጌል የመድረስ ፍላጎት ሲጠፋ ነው። ይህ የወንጌላውያን እንጂ የእኛ ሥራ አይደለም ብሎ ማሰብ ቀላል ነው። ወይም በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ ልንመለከታቸው የሚገቡን ብዙ ችግሮች ስላሉ፥ የጠፉትን ለመፈለግም ሆነ ለመድረስ ጊዜና ገንዘብ የለንም ብሉ ማሰብ ቀላል ነው። አራተኛ፥ በመንፈሳዊ ሕይወታችን በመልካም ሁኔታ ላይ እንደምንገኝ በማሰብ ስለ እግዚአብሔር ባለን እውቀት ያለማቋረጥ ማደግ እንደማያስፈልገን ስናስብ በራስ መርካት ይመጣል። ቤተ ክርስቲያን ወይም ክርስቲያን በራሱ መርካት ሲጀምር፥ በመንፈሳዊ ሕይወቱ ምውት ወደ መሆን ያዘግማል። ምክንያቱም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ መንፈሳዊ ሕይወት ስለማይኖር ሰዎች ወደ ሌላ ቤተ ክርስቲያን ወይም እምነታቸውን ትተው ወደ ሌላ ሃይማኖት ይሄዳሉ። በራስ ከመርካት የተነሣ ክርስቲያን እግዚአብሔር አንድ ቀን እንደሚፈርድበት ይረሳል። ወዲያውኑ በኃጢአት ወጥመድ ይያዝና ከዚያ በማምለጥ ለእግዚአብሔር እንደገና መኖር በጣም አስቸጋሪ ከሚሆንበት ሁኔታ ውስጥ ይገባል። የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ክርስቲያን ወይም ቤተ ክርስቲያን በራሳቸው ወደ መርካት ሊመጡ የሚችሉባቸውን ሌሎች ምክንያቶች ዘርዝር። ለ) በራስ የመርካት ሌሎች ውጤቶችን ዘርዝር። ሐ) ይህ ነገር በሕይወትህ፥ በሌላ ሰው ሕይወት ወይም በቤተ ክርስቲያን እንዴት እንደተፈጸመ አንዳንድ ምሳሌዎችን ስጥ። መ) በመንፈሳዊ ረገድ በራስ መርካትን በሚመለከት ፈውስ የሚሆኑ አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው? የይሁዳ ሕዝብ በራስ ከመርካት የተነሣ ቀስ በቀስ በኃጢአት ወደቁ። አይሁድ እግዚአብሔር ለረጅም ጊዜ ስለታገሣቸውና ፈጥኖ ስላልፈረደባቸው እነርሱ ስለሚያደርጉት ነገር እግዚአብሔር ይገደው እንደሆነ መጠየቅ ጀመሩ። እግዚአብሔር ሕዝቡን ለማስጠንቀቅ መልእክተኞቹን ነቢያትን በትዕግሥት ይልካቸው ነበር። ይሁን እንጂ ሕዝቡ አንዳንድ ጊዜ ድርጊታቸውን ለጊዜው ለመለወጥ ፈቃደኞች ቢሆኑም፥ ልባቸውን ለመለወጥ አልፈለጉም ነበር። እገዳው እንደተነሣላቸው ፈጥነው ወደ ጣዖት አምልኮ ይመለሱ ነበር። በመጨረሻ እግዚአብሔር ሶፎንያስን ጠራ። ሶፎንያስ የእግዚአብሔር የፍርድ ጊዜ ደርሶአል ሲል አወጀ። እግዚአብሔር ሕዝቡ በራሳቸው በመርካታቸውና በኃጢአታቸው ምክንያት እንደሚቀጣቸው ተናገረ።  የትንቢተ ሶፎንያስ ጸሐፊ በሶፎንያስ 1፡1 የእግዚአብሔር ቃል ወደ ሶፎንያስ እንደመጣ ተጽፏል። ይህ ማለት የትንቢተ ሶፎንያስ ጸሐፊ ሶፎንያስ ነው ማለት ነው። ስለ ሶፎንያስ የምናውቀው ነገር ብዙ ባይሆንም፥ አመጣጡ ከንጉሣዊ ዘር ይመስላል። በሶፎንያስ 1፡1 የተጠቀሰው ሕዝቅያስ የተባለው ሰው ንጉሥ ሕዝቅያስ ከሆነ፥ ሶፎንያስ የንጉሥ ሕዝቅያስ የልጅ ልጅ ልጅ ነው ማለት ነው። ይህም ማለት ሶፎንያስ ባገለገለበት ዘመን በይሁዳ ነግሦ ከነበረው ከንጉሥ ኢዮስያስ ጋርም ይዛመዳል ማለት ነው። ሶፎንያስ ያደገው በኢየሩሳሌም ሳይሆን አይቀርም። በሰው ሁሉ ዘንድ የተከበረ ያደረገውም የንጉሥ ዘር መሆኑ ይሆናል። በሚገባ የተማረና በይሁዳ ከሚኖሩ ሁሉ የተሻለ ቤተሰብ ውስጥ የነበረ ሰው ነው። ይህ ማለት ግን ሶፎንያስ ስለ ሕዝቡ ወይም ዘመዶቹ ስለሆኑት ንጉሣውያን ቤተሰብ ኃጢአት ግድ አልነበረውም ማለት አይደለም። የሕዝቡን ኃጢአት በመቃወም በድፍረት ይናገር ነበር። በድጋሚ የምንመለከተው እግዚአብሔር በሁሉም ዓይነት ሰዎች እንደሚጠቀም ነው። እንደ ሚክያስና አሞጽ ባሉ ተራ ሰዎች ይጠቀም ነበር። እንደ ሶፎንያስ ባሉ ሀብታምና የተማሩ ሰዎችም ተጠቅሟል። ሶፎንያስ ያገለገለው በኢዮስያስ ዘመነ መንግሥት እንደ ነበረ ይነገራል (640-609 ዓ.ዓ.)። ኢዮስያስ ሥልጣን የጨበጠው ከክፉዎቹ ነገሥታት ከምናሴና ከአሞን ቀጥሎ ገና የስምንት ዓመት ልጅ እያለ ነበር። ኢዮስያስ ከስምንት ዓመት በኋላ የአሥራ ስድስት ዓመት ልጅ ሲሆን፥ የሕዝቡን ሃይማኖት ማደስ ጀመረ። ሶፎንያስ ያገለገለው በኢዮስያስ ዘመነ መንግሥት የመጀመሪያዎቹ ዓመታት ሳይሆን አይቀርም። ኢዮስያስ በነገሠበት ዘመን ሁለት የተሐድሶ እንቅስቃሴዎች ተካሂደዋል። አንዱ በ632 ዓ.ዓ. አካባቢ የነበረው ሲሆን፥ ሌላው ደግሞ በ622 ዓ.ዓ. ገደማ የነበረው ነው። ሶፎንያስ ከእነዚህ ሁለት የተሐድሶ ጊዜያት በአንዱ ሳይሠራ አልቀረም። ነገር ግን ዋና የአገልግሎት ዘመኑ 627 ዓ.ዓ. አካባቢ ሳይሆን አይቀርም። ሶፎንያስ በንጉሥ ኢዮስያስ ሕይወት ላይ አዎንታዊ ተጽዕኖ በማሳደር ባካሄደው ተሐድሶ ረድቶት እንደሆነ የምናውቀው ነገር የለም። በሥልጣኑና ከንጉሡ ጋር በነበረው ግንኙነት ረድቶት ሊሆን ይችላል። የሚያሳዝነው ግን የሕዝቡ ንስሐ ውጫዊ ስለነበረ ንጉሥ ኢዮስያስ እንደሞተ ወደ ክፉ ሥራቸው ተመለሱ። በዚህ ጊዜ በይሁዳ ያገለግል የነበረው ነቢይ ሶፎንያስ ብቻ አልነበረም። ኤርምያስ፣ ናሆምና ምናልባት ዕንባቆምም አገልግለዋል። ምርኮው ከመፈጸሙ አስቀድሞ በነበረው ጊዜ እግዚአብሔር ብዙ ነቢያትን በመላክ የኃጢአታቸውን ውጤቶች በመንገር ሕዝቡን እንዲያስጠነቅቋቸው አድርጎ ነበር። ሕዝቡን ለመለወጥና እግዚአብሔር የተናገረውን ፍርድ ለማስለወጥ ግን አልቻሉም።  የትንቢተ ሶፎንያስ ታሪካዊ ሥረ-መሠረት  ሶፎንያስ ይኖር የነበረው የአሦር መንግሥት እየከሰመ የባቢሎን መንግሥት ግን እያቆጠቆጠ ባለበት የሽግግር ወቅት ነበር። ከጥቂት ዓመታት በኋላ የይሁዳ ሕዝብ በባቢሎን ቁጥጥር ሥር በመውደቅ፥ በመጨረሻ በ586 ዓ.ዓ. ሊደመሰሱ ተዘጋጅተው ነበር። የአሦር መንግሥት በመካከለኛው ምሥራቅ ፖለቲካዊ ገጽታ ላይ የበላይነት ተጽዕኖን በማሳደር ለብዙ ዓመታት ቆይቷል። በዚያን ጊዜ የነበሩት መሪዎች ግን ብርቱዎች ስላልነበሩ በመንግሥቱ ሁሉ ውስጥ እየተባባሰ የሚሄድ ዓመፅ ነበር። የመጨረሻው የአሦር ዋና ንጉሥ አሱርባኒፓል ከሞተ በኋላ የአሦር መንግሥት መፈረካከስ ጀመረ። ባቢሎን ከአሦር ነፃ መውጣቷን አወጀች። በኋላም ባቢሎን ሜዶንን ከመሳሰሉ ሌሎች አገሮች ጋር በመተባበር አሦርን ማጥቃትና ማውደም ጀመረች። ይህ ከመሆኑ አስቀድሞ ሶፎንያስ የአሦርን ውድቀት አመልክቶ ነበር (ሶፎንያስ 2፡13-15)። ለጥቂት ዓመታት ይሁዳ ከውጭ መንግሥታት አንጻራዊ ሰላም አግኝታ ነበር። ባቢሎን በሰሜን በኩል ግዛቷን እያስፋፋችና ተጽዕኖዋን እያሳደገች ብትሄድም፥ እስካሁን ድረስ ወደ ከነዓን አልመጣችም ነበር። በዚህ በተገኘው ሰላም ንጉሥ ኢዮስያስ በይሁዳ ሕዝብ መካከል መንፈሳዊ ተሐድሶ ለማካሄድ ችሎ ነበር። የንጉሥ ኢዮስያስ አያት የነበረው ንጉሥ ምናሴ በይሁዳ ከገዙት እጅግ ክፉ መሪዎች አንዱ የነበረ ሲሆን፥ ከ50 ዓመታት በላይ ነግሦአል (697-642 ዓ.ዓ.)። ምናሴ ወደ ኢየሩሳሌም አዳዲስ የጣዖት አምልኮ አመጣ። በውስጡ ጣዖትን በማኖር ቤተ መቅደሱን አረከሰ። የገዛ ልጁንም ለጣዖት መሥዋዕት አድርጎ አቀረበ። ይህ ክፉ ንጉሥ በነገሠባቸው 50 ዓመታት ይሁዳን ልታንሰራራ ወደማትችልበት መንፈሳዊ አዘቅት ውስጥ ከቷት ነበር። በእርሱ ዘመነ መንግሥት የነበረው ትውልድ በአጠቃላይ የሚያውቀው ነገር ቢኖር የተደባለቀውን የበአልና የእግዚአብሔር አምልኮ ነበር። በዘመነ መንግሥቱ መጨረሻ ገደማ ምናሴ ተማርኮ ወደ አሦር ተወሰደና ሳይለቀቅ ለጥቂት ዓመታት ኖረ። በአሦር እያለ ልቡ ተለወጠና ወደ ጌታ ተመለሰ። ምናሴ ንስሐ ቢገባም እንኳ የይሁዳን ሕዝብ መንፈሳዊ ሕይወት ለመለወጥ ፈጽሞ አልቻለም። እርሱ ሲሞት ልጁ አሞን በምትኩ ነገሠ። አሞን ምናሴ ከነገሠባቸው የመጀመሪያ ዓመታት እንደነበረው በክፋት ሄደ። በልጅነቱ የአባቱን ክፋት ተመልክቶ ስለነበር እግዚአብሔርን ለማክበር አልቻለም። ስለሆነም፥ እግዚአብሔር እንዲነግሥ የፈቀደለት ለሁለት ዓመታት ብቻ ነበር። አሞን ተገደለና ትንሽ ልጁ ኢዮስያስ ነገሠ። የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ወላጆች በልጆቻቸው ላይ የሚያሳድሩት ተጽዕኖ ልጆች በሚያድጉ ጊዜም የሚቀጥለው በምን መንገድ ነው? ለ) ክርስቲያን ወላጆች ልጆቻቸው ትልልቆች እስኪሆኑ ድረስ ከመጠበቅ ይልቅ፥ ገና ትንንሾች እያሉ እግዚአብሔርን እንዲፈሩና ለእርሱ እንዲታዘዙ ማስተማር የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው? ኢዮስያስ በይሁዳ ሕዝብ መንፈሳዊ ሕይወት ለውጦችን ለማምጣት የሞከረ ቢሆንም፥ አብዛኛዎቹ ለውጦች ውጫዊ እንጂ ውስጣዊ አልነበሩም። በእርሱ ተጽዕኖ ሕዝቡ ጣዖታትን ለማጥፋትና

ትንቢተ ሶፎንያስ መግቢያ Read More »

የትንቢተ ዕንባቆም ዓላማ እና ዋና ዋና ትምሕርቶች

የትንቢተ ዕንባቆም ዓላማ ትንቢተ ዕንባቆም እግዚአብሔር በባቢሎናውያን አማካይነት በይሁዳ ላይ ስለሚያመጣው ቅጣት የሚተነብይ ቢሆንም፥ ዓላማው የእግዚአብሔርን ቅንና ትክክለኛ ፍርድ መመርመር ነው። ትንቢተ ዕንባቆም የእግዚአብሔርን መንገድ ለሕዝቡ እንደሚገልጡ የጥበብ መጻሕፍት ዓይነት ነው። ትንቢተ ዕንባቆም ከመጽሐፈ ኢዮብ የሚመሳሰልም የሚለያይም ነው። የመጽሐፈ ኢዮብ ዋና የፍልስፍና ጥያቄ «ጻድቅ መከራን በሚቀበልበት ጊዜ የእግዚአብሔር ትክክለኛ ፍርድ አለን?» የሚል ነው። በዚያ ስፍራ የተሰጠው መልስ፥ ሰይጣን ጻድቃንን እንዲፈትን እግዚአብሔር ይፈቅዳል የሚል ነበር። ጻድቃን የተከበረውን የእግዚአብሔር ኃይልና ከእግዚአብሔር ጋር ሲወዳደሩ የቱን ያህል ኢምንት እንደሆኑ በማስታወስ በፈተናቸው በእግዚአብሔር መታመን አለባቸው። በትንቢተ ዕንባቆም ውስጥ ሁለት የፍልስፍና ጥያቄዎች ተመልሰዋል፡- 1. «ሕዝቦችና መንግሥታት በክፋት ሲሞሉና ክፉ ሰዎች ሲበለጽጉ የእግዚአብሔር ቅንና ትክክለኛ ፍርድ አለን?» እግዚአብሔር ለዚህ ጥያቄ የሰጠው መልስ፡- እርሱ በራሱ ጊዜና በራሱ መንገድ በአሕዛብ መንግሥታት ላይ ይፈርዳል። ይሁዳ ቅጣት የሚፈጸምባት በባቢሎን ነው የሚል ነበር።  2. «ጻድቁ እግዚአብሔር ከይሁዳ ይልቅ ክፉና ጠማማ የሆነውን ሕዝብ እንዴት ለቅጣት መሣሪያ አድርጎ ይመርጣል?»  እግዚአብሔር ለዚህ ጥያቄ የሰጠው መልስ ሁለት ክፍሎች አሉት፡- ሀ. እግዚአብሔር ታላቅና ኃይለኛ ነው። ሰው ስለ እግዚአብሔር የአሠራር መንገዶች የመጠየቅ መብት የለውም። ይልቁንም ጻድቅ ግራ በተጋባና እርግጠኛ ባልሆነበት ጊዜ በእግዚአብሔር ላይ ያለውን እምነት እንኳ መጠበቅ አለበት። ጻድቅ ሰው የእግዚአብሔርን መንገዶች ምንነት በማይረዳበት ጊዜም እንኳ የታማኝነትና የጽናት ሕይወቱን ይጠብቃል። ለ. እግዚአብሔር ኃጢአተኞችን በራሱ ጊዜ ለመቅጣት ሌሎችን ይጠቀማል። እግዚአብሔር ይሁዳን ለመቅጣት በባቢሎን መንግሥትና ሕዝብ ከተጠቀመ በኋላ በተራቸው ይቀጣቸዋል። እግዚአብሔር ሕዝቡን ለመቅጣት የተጠቀመበት ሰው ወይም መንግሥት መልካም ነው ማለት አይደለም። በእግዚአብሔር እጅ እንዳሉ መሣሪያዎች ናቸው። ስለዚህ ከተጠቀመባቸው በኋላ ሊጥላቸው ወይም እንደየአስፈላጊነቱ እነርሱን ደግሞ ሊቀጣቸው ይችላል። የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ክርስቲያኖች እነዚህን እውነቶች ማወቅና መጠቀም የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው? ለ) በዚህ ዘመን የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች እግዚአብሔርን ዘወትር የሚጠይቁባቸውን ነገሮች ዝርዝር። ሐ) እነዚህ እውነቶች እንዴት ይረዷቸዋል? ዕንባቆም ተገቢውን ትምህርት እንዳገኘ ከመጨረሻ ጸሎቱ እንረዳለን። ባይረዳውም እንኳ የእግዚአብሔርን መንገድ ተቀብሏል። የእግዚአብሔርን ትክክለኛ ፍርድ መጠራጠሩን አቁሞ ነበር። በዚህ ፈንታ እግዚአብሔር ክፉዎችን እንደሚቀጣና ጻድቃንን እንደሚባርክ በሰጠው ዋስትና ላይ አርፎ ነበር። እግዚአብሔር ኃጢአተኞችን መቼና እንዴት መቅጣት እንዳለበት መወሰን የዕንባቆምም ሆነ የእኛ ኃላፊነት አይደለም። የዕንባቆምም ጸሎት ሊመጣ ካለው መዓት አንጻር የተጸለየ አስደናቂ የእምነት ጸሎት ነው። እግዚአብሔር በሕዝቡ ላይ በሚፈርድበት ጊዜ ምሕረቱን ከቶ እንደማይረሳ ጸለየ። በተጨማሪ በእጁ የሚገኘው ማንኛውም ሥጋዊ በረከት ሁሉ ቢወሰድ እንኳ፥ በእግዚአብሔር ብርታት ላይ መደገፉንና በእርሱም መታመኑን ለመቀጠል መወሰኑን ገለጸ።  የትንቢተ ዕንባቆም ዋና ዋና ትምህርቶች 1. እግዚአብሔር ክፉዎችን በኃጢአታቸው ምክንያት ይቀጣቸዋል። ብዙውን ጊዜ ግን ክፉዎች በኃጢአታቸው የማይቀጡ ይመስላል። እንዲያውም በኃጢአታቸው ምክንያት ሲበለጽጉና ሲከናወንላቸው ስለሚታዩ በኃጢአታቸው የተባረኩ ይመስላሉ። ክፉዎችና ኃጢአተኞች ሲሳካላቸው፥ ከእግዚአብሔር ሕዝብ አብዛኛዎቹ መከራ ይቀበላሉ። ይህም ለመበልጸግ ሲሉ ኃጢአተኞች የሚጠቀሙባቸውን መንገዶች ክርስቲያኖችም እንዲጠቀሙበት ይገፋፋቸዋል። ይህን ሲያደርጉ ግን እግዚአብሔር ክፉዎችን እንደሚቀጣ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረውን ትምህርት ዘንግተዋል ማለት ነው። ቅጣቱ እኛ በምንፈልገው ፍጥነትና መንገድ ቢይሆንም፥ ዳሩ ግን እግዚአብሔር ኃጢአተኞችን በኃጢአታቸው ምክንያት እንደሚቀጣ ቃል ይገባል። ስለዚህ ኃጢአተኞች አሁን ስላልተቀጡ እኛም ብንሆን አንቀጣም ብለን በማሰብ፥ እንደ እነርሱ ለመሆን መፈተንና ለፈተናው መንገድ መክፈት የለብንም። የእግዚአብሔር ትክክለኛ ፍርድ ብዙ ጊዜ ቢዘገይም መፈጸሙ ግን የማይቀር ነው። የይሁዳና የአሦር መንግሥታት እግዚአብሔር በእነርሱ ላይ ከመፍረዱ በፊት ለብዙ ዘመናት ቆይተዋል። ባቢሎናውያን ግን በእግዚአብሔር ሳይቀጡ የቆዩት ለ70 ዓመታት ብቻ ነው። የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) አንዳንድ ክርስቲያኖች፥ የማያምኑ ሰዎች ስለ ኃጢአታቸው ባለመቀጣታቸው ምክንያት እነርሱም እንደማይቀጡ በማሰብ፥ በኃጢአት የሚወድቁት እንዴት እንደሆነ ግለጽ። ለ) ይህን በሚያደርጉበት ጊዜ የዘነጉት ነገር ምንድን ነው? የዕንባቆም ትምህርት ማስጠንቀቂያ ሊሆናቸው የሚችለው እንዴት ነው? 2. ክፉዎችና ኃጢአተኞች ሲበለጽጉ ወይም ጻድቃን መከራ ሲቀበሉ፥ በታማኝነት ጸንቶ መኖር የጻድቃን ኃላፊነት ነው። እጅግ ታዋቂ ከሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች አንዱ ዕንባቆም 2፡4 ነው። ይህም በአዲስ ኪዳን እግዚአብሔር ሰውን የሚያጸድቀው በሥራ ሳይሆን በእግዚአብሔር ላይ ባለው እምነት መሆኑን ለመገልጥ በተደጋጋሚ ተጠቅሶ እናያለን (ሮሜ 1፡ 17፥ ገላትያ፤ 3፡11፤ ዕብራውያን 10፡38)። ይሁን እንጂ በትንቢተ ዕንባቆም የተሰጠው ትኩረት በጣም የተለየ ነው። ዕንባቆም የእግዚአብሔር ምርጦች የሆኑት ጻድቃን በምንም ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ቢሆኑ፥ በእግዚአብሔር መታመን እንዳለባቸው ያስተምራል። ክፋትና ኃጢአት ሲስፋፉ፥ ምን ክፉዎች ከመቀጣት ይልቅ እየበለጸጉ የሄዱ ሲመስሉ፥ ጻድቃን ሊያስታውሱት የሚገባው የተጠሩት በእግዚአብሔር ፊት የጽድቅና የቅድስና ሕይወት ለመኖር እንደ ሆነ ነው። ስለሆነም የቅድስና አካሄዳቸውን መጠበቅ አለባቸው። እግዚአብሔር አንድ ቀን ኃጢአተኞችንና ጠማሞችን እንደሚቀጣ ማስታወስ አለባቸው። ይህ ቅጣት በምድር እያሉ ሊደርስባቸው ወይም ላይደርስባቸው ቢችልም በመጨረሻው ዘመን ግን የማይቀር ነው። ደግሞም ጻድቃን አንዳችም ነገር ሳያጠፉ መከራ በሚቀበሉበት ጊዜ በእግዚአብሔር ላይ ያላቸውን እምነት መጠበቅ አለባቸው። እግዚአብሔር ይሁዳን ለመቅጣት ባቢሎንን በተጠቀመ ጊዜ በይሁዳ በርካታ ጻድቃን ሰዎች ነበሩ፤ ዕንባቆም፥ ኤርምያስ፥ ሶፎንያስና ሌሎችም ብዙዎች ነበሩ። ቅጣቱ በሚፈጸምበት ጊዜ መከራቸውን ያዩ ነበር፡፡ በእግዚአብሔር ላይ ማጉረምረም ለእነርሱ ቀላል ነበር። «ለእግዚአብሔር ታማኝ ሆኜ እያለሁ መከራን ከተቀበልሁ፥ በእርሱ ላይ ያለኝን እምነት እክዳለሁ» ብሎ ማሰብ ቀላል ነበር። ዳሩ ግን ዕንባቆም የሚያስተምረን እምነታችን በእግዚአብሔር እንጂ በዙሪያችን ባሉ ሁኔታዎች ላይ መመሥረት እንደሌለበት ነው። ብዙ ክርስቲያኖች በእግዚአብሔር ለመታመን ፈቃደኞች የሚሆኑት ገንዘብ እስካገኙ፥ ፈውስ እስከተሰጣቸውና የተለያዩ ሥጋዊ በረከቶችን እስከተቀበሉ ድረስ ብቻ ነው። የሚያሳዝነው ደግሞ በእግዚአብሔር ካመንን ሁልጊዜ ባለጸጎች እንሆናለን ወይም ከበሽታችን እንፈወሳለን በማለት የሐሰት ትምህርት የሚያስተምሩ ብዙ ክርስቲያኖች መኖራቸው ነው። ኢዮብ ከፍ ያለ ሥቃይ ቢደርስበትም እንኳ በእግዚአብሔር ላይ የነበረውን እምነቱን ጠብቋል። ዕንባቆም ደግሞ መንጋውንና የእርሻ ፍሬውን ሁሉ በማጣት፥ ረሃብ ምናልባትም ሞት እንደሚያጋጥመው ቢያውቅም እንኳ እምነቱ በእግዚአብሔር ላይ ነበር። ሐሤት የሚያደርገው በእግዚአብሔር ላይ እንጂ በሁኔታዎች ላይ አልነበረም። በሁኔታዎቹ ሁሉ ውስጥ ማለፍ እንዲችል ደግሞ እግዚአብሔር ኃይሉን ያድስለት ነበር። የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) አንዳንድ ክርስቲያኖች ሰው እውነተኛ እምነት ካለው ሀብታም ይሆናል ወይም አይታመምም እያሉ ሲያስተምሩ ሰምተሃልን? ለዚህ ትምህርት የሚጠቀሙባቸው ጥቅሶች የትኞቹ ናቸው? ለ) ትንቢተ ዕንባቆምን በመጠቀም መልስ የምትሰጣቸው እንዴት ነው? ሐ) ብዙ ክርስቲያኖች እግዚአብሔር እስከባረካቸው ድረስ ብቻ በእርሱ እያመኑ፥ መከራ ወይም ችግር በሚገጥማቸው ጊዜ ግን የሚክዱት ለምንድን ነው? መ) «ጻድቅ በእምነት ይኖራል» የሚለው ትምህርት ክርስቲያኖች ሊያስታውሱት የሚገባ እጅግ ጠቃሚ የሆነው እንዴት ነው? 3. እግዚአብሔር መንግሥታትን ስለ ክፉ ድርጊታቸው ይቀጣቸዋል። ከትንቢተ ዕንባቆም በግልጽ እንደምንመለከተው፥ እግዚአብሔር መልካምም ሆነ ክፉ መንግሥታትን ላደረጉት ነገር ተጠያቂዎች ያደርጋቸዋል። እግዚአብሔር የይሁዳን ሕዝብ ተጠያቂ አድርጎ ነበር። ኃጢአታቸው እጅግ ከፍተኛ ደረጃ ላይ በደረሰ ጊዜ ፍርዱን አመጣባቸው። እግዚአብሔር ስለ ክፋታቸው በአሦርና በባቢሎንም ላይ ፈርዷል። ማንኛውም ሰው ሆነ ሕዝብ ወይም መንግሥት ከእግዚአብሔር ፍርድ ማምለጥ አይችልም። ግለሰቦችም ሆኑ ሕዝቦች በብሔራዊ ደረጃ ለሚያደርጉት ድርጊት ተጠያቂዎች ናቸው። እግዚአብሔር ለእኛም ሆነ ለመንግሥታት የመምረጥ ነፃነት ሰጥቶናል። በዚህ ነፃ ምርጫችን ስለምንወስደው እርምጃ ሁሉ ግን እግዚአብሔር ይጠይቀናል። ልንቆጣጠር የምንችለው ምርጫችንን እንጂ ምርጣችን የሚያስከትላቸውን ነገሮች ወይም ውጤቶች አይደለም። የምርጫችን ውጤቶች በእግዚአብሔር እጅ ናቸው። መልካም ነገሮችን ከመረጥን (ከዘራን) መልካም ነገሮችን እናጭዳለን። ክፉ ነገሮችን ከመረጥን (ከዘራን) የክፉ ምርጫዎቻችንን ውጤቶች እናጭዳለን (ምሳሌ 11፡18፤ 22፡8፤ ገላትያ 6፡7-8)። በመጨረሻ ሁላችንም በሚፈርድብን በእግዚአብሔር ፊት እንቆማለን፤ እርሱም እንደየድርጊታችን ዋጋችንን ይሰጠናል ወይም ይቀጣናል።  የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ይህን የመጨረሻ ትምህርት ማስታወስ ለእኛ ጠቃሚ የሚሆነው ለምንድን ነው? ለ) ሰዎች ስለሚያደርጉአቸው ምርጫዎች ሁሉ እግዚአብሔር ተጠያቂዎች እንደሚያደርጋቸው ቢያስታውሱ የበለጠ ጥንቃቄ የተሞላ ምርጫ የሚያደርጉት እንዴት ነው? የውይይት ጥያቄ፥ ዕንባቆም 1-3 አንብብ። ሀ) ዕንባቆም የጠየቃቸው ሁለት ጥያቄዎች ምን ነበሩ? ለ) እግዚአብሔር የዕንባቆምን ጥያቄዎች የመለሰው እንዴት ነበር? ሐ) የዕንባቆም ጸሎት ዛሬ እኛም ብንጸልየው መልካም

የትንቢተ ዕንባቆም ዓላማ እና ዋና ዋና ትምሕርቶች Read More »

ትንቢተ ዕንባቆም መግቢያ

የውይይት ጥያቄ፥ የምትመለከተው ክፉ ተግባር ከመብዛቱ የተነሣ እጅግ ታክተህ እግዚአብሔር ይህንን ተግባር የፈጸመውን ሰው ወይም ሰዎች የማይቀጣው ለምን እንደሆነ ተደንቀህ ታውቃለህን? ሁኔታውን አብራራ። ምናልባት ሁላችንም በአንድ ወይም በሌላ ወቅት በጣም ብዙ ክፋት ተመልክተን በመደነቅ እግዚአብሔር ይህንን ነገር ለምን እንደማይቀጣው ጠይቀን ይሆናል። ዙሪያችንን ስንቃኝና ሰዎች ኃጢአት ሲሠሩ፥ ድሆች መጠቀሚያ ሲደረጉ ትክክለኛ ፍርድን በጉቦ የሚያጣምሙ ሰዎች ያለምንም ቅጣት ተዝናንተው ሊኖሩ መመልከት፥ ልባችንን በኃዘን ይሞላል። ዓለም በቅን ፍርድና በጽድቅ የምትሞላበትን ጊዜ በልባችን እንናፍቃለን። ክፋት እስካልተቀጣ ድረስ ይህ ቀን ሊመጣ እንደማይችልም እንገነዘባለን። በዚህ አንጻር እግዚአብሔር ክፋትን ለምን እንደማይቀጣና ለእግዚአብሔር ለመኖር አጥብቀው የሚፈልጉትን ሰዎች ለምን እንደማይባርክ በማሰብ እንደነቃለን። ነቢዩ ዕንባቆምም ከዚህ ጉዳይ ጋር ግብግብ ገጥሟል። የደም መፍሰስና ክፋት ያለ ቅጣት በዙሪያው ተንሰራፍቶ መመልከት ሰልችቶት ነበር። በመሆኑም ክፋትን በመቅጣት ጽድቁን እንዲገልጥ ወደ እግዚአብሔር ይጮህ ነበር፤ እግዚአብሔር የሚሰጠውን መልስ ግን አልጠበቀም ነበር። ትንቢተ ዕንባቆም የእግዚአብሔርን የጽድቅና የቅን ፍርድ ባሕርይ በሚመለከትበት ጊዜ ሊረዳ ያልቻላቸውን ነገሮች በሚመለከት ያቀረባቸውን የተለያዩ ጥያቄዎች የምናገኝበት ነው። ትንቢተ ዕንባቆም ከታናናሽ ነቢያት መጻሕፍት አንጻር ሲታይ ልዩ መጽሐፍ ነው። በመጽሐፉ ውስጥ አንዳንድ ትንቢቶች በመኖራቸው ከነቢያት መጻሕፍት ቢመደብም የበለጠ የሚመሳሰለው ከጥበብ መጻሕፍት ጋር ነው። ከመጽሐፈ ኢዮብ ጋር የሚመሳሰለው የእግዚአብሔርን ቅንና ትክክለኛ ፍርድ በዓለም ውስጥ ከሚገኙ ክፉ ነገሮች አንጻር የሚመለከት ስለሆነ ነው። የትንቢተ ዕንባቆም ጸሐፊ የዚህ መጽሐፍ ጸሐፊ ዕንባቆም ነው። እንደ ናሆም ሁሉ ስለ ዕንባቆምም የምናውቀው ነገር የለም። መጽሐፉ በዚህ ዘመን የነበሩት ነገሥታት እነማን እንደነበሩ አይገልጽም። ዕንባቆም የት ይኖር እንደነበር አልተጻፈም። ከአዋልድ መጻሕፍት መካከል አንዱ በሆነው «ቤልና ድራጎን» በተባለው (በአልና ክንፍ ያለውና እሳት የሚተፋ ፍጡር) መጽሐፍ ውስጥ ዕንባቆም በአንበሶች ጉድጓድ ውስጥ ተጥሉ ሳለ ዳንኤልን እንዴት እንደረዳው የሚናገር ታሪክ ብናገኝም፥ ታሪኩ እውነት አይመስልም። መጽሐፉ መቼ እንደተጻፈ ለማወቅ፥ አሁንም መጠቀም የምንችለው በመጽሐፉ ውስጥ ባለው መረጃ ነው። ትንቢተ ዕንባቆም የተጻፈበትን ጊዜ በሚመለከት ሁለት ዐበይት አመለካከቶች አሉ፡- 1. ትንቢተ ዕንባቆም የተጻፈው ባቢሎን ኢየሩሳሌምን በ605 ዓ.ዓ. ለመጀመሪያ ጊዜ ከማጥቃቷ በፊት ከ609-605 ዓ.ዓ. ነው። ይህም በንጉሥ ኢዮአቄም ዘመነ መንግሥት የመጀመሪያዎቹ ዓመታት ገደማ ነበር።  2. ትንቢተ ዕንባቆም የተጻፈው ከ640-626 ዓ.ዓ. ነው። ትንቢተ ዕንባቆም የባቢሎን የዓለም ኃያል መንግሥት መሆን ጨርሶ ያልተጠበቀ ነገር እንደነበር የሚያሳይ ይመስላል። የባቢሎን መንግሥት ገናና መሆን የጀመረው ባቢሎን ከአሦር ተለይታ ነጻ በሆነችበት በ626 ዓ.ዓ. ነበር። ስለዚህ ትንቢተ ዕንባቆም የተጻፈው ከዚህ ጊዜ በፊት ይመስላል። ይህ መጽሐፍ የተጻፈበት ነው ሊባል የሚችለው የመጨረሻው ጊዜ 615 ዓ.ዓ. ነው። ምክንያቱም የአሦር መንግሥት በባቢሎን ሙሉ በሙሉ የተሸነፈው በ612 ዓ.ዓ. ነበርና ከዚህ በኋላ ይህ ትንቢት ለዕንባቆም ምንም ትርጉም የሌለው ይሆናል።  ዕንባቆም ትንቢት የተናገረው ኢዮስያስ በይሁዳ ተሐድሶ ከመጀመሩ በፊት በነበረው የመጀመሪያው ዘመነ መንግሥቱ ገደማ እንደሆነ ዘመኑ ከሁሉም የሚሻል ይመስላል። ኢዮስያስ ገና በልጅነቱ ሆኖ የነገሠው በ640 ዓ.ዓ. ነበር። ያም በይሁዳ ፍትሕ ያልነበረበት ክፉ ጊዜ ነበር። የንጉሥ ኢዮስያስ ተሐድሶ የይሁዳን ሕዝብ መለወጥ የጀመረው ቆይታ በ626 ዓ.ዓ. ገደማ ነበር። ስለዚህ ዕንባቆም የኖረውና በአካባቢው ከነበረው የፍትሕ መዛባት ጋር የታገለው በንጉሥ ኢዮስያስ ዘመነ መንግሥት መጀመሪያ ገደማ ይመስላል። ምናልባት እርሱም የተሳተፈበት የንጉሥ ኢዮስያስ ተሐድሶ ሕዝቡን መለወጥ ሲጀምር እጅግ ሳይደሰት አልቀረም። ነገር ግን እግዚአብሔር ይሁዳን በእርሱ ዘመነ መንግሥት እንደሚደመስስ መናገሩን ያውቅ ነበር። ስለዚህ ሸክም በተጫጫነው ልብ የባቢሎንን ምጥቀት ከመመልከቱም፥ ኢየሩሳሌምም ስትደመሰስ ምስክር እንድነበረ አይጠረጠርም። ዕንባቆም ባገለገለበት ዘመን ሶፎንያስና ኤርምያስም አገልግለዋል።  የትንቢተ ዕንባቆም ሥረ መሠረት  የምናሴ ዘመነ መንግሥት (697-642 ዓ.ዓ.) የይሁዳ ሕዝብ በመንፈሳዊ ሕይወቱ ወደ መጨረሻው ዓዘቅት የወረደበት ጊዜ ነበር። ምናሴ ሕዝቅያስ ያካሄደውን ተሐድሶ ሁሉ ከመቅጽበት አበላሸ። የጣዖት አምልኮ እጅግ ተስፋፋ። ለጣዖት አምልኮ የሚሆን መሠዊያ አሠርቶ በቤተ መቅደሱ ውስጥ በማኖር የራሱን ልጅ መሥዋዕት አድርጎ አቀረበ። በሃይማኖታዊ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን፥ በሥነ-ምግባርና በማኅበራዊ ጉዳዮችም ሕዝቡ ፊታቸውን ከእግዚአብሔር በመመለሳቸው ማኅበራዊ ክፋት እጅግ የተለመደ ነገር ሆነ። ምናሴ ለመስበክና ሕዝቡን ስለ እግዚአብሔር ፍርድ ለማስጠንቀቅ የፈለጉትን ነቢያት ሁሉ አስገደለ። ይህም እግዚአብሔር በይሁዳ ላይ ፍርድ ለማምጣት እንዲወሰን አደረገው። ምናሴ በአሦር ላይ ለማመፅ በሞከረ ጊዜ፥ ተማርኮ ወደ አሦር ተወሰደ። በምርኮ ምድር ንስሐ ገባና ልቡ ተለወጠ፤ ከምርኮ ተለቆ ወደ ይሁዳ በተመለሰ ጊዜ ቀድሞ የፈጸማቸውን ክፉ ተግባራት ለማሻሻል ቢሞክርም አልቻለም። ከምናሴ ሞት በኋላ ልጁ አሞን ነግሦ ሁለት ዓመት ከገዛ በኋላ ተገደለ። የአሞን ልጅ ኢዮስያስ ግን ከአባቱ በተለየ መንገድ እግዚአብሔርን ተከተለ። ሥልጣን በያዘ ጊዜ ገና የስምንት ዓመት ልጅ ነበር። በይሁዳ መንፈሳዊ ተሐድሶን ለማምጣት የወሰነውና ርምጃ የወሰደው ከነገሠ ከአሥራ ስምንት ዓመት በኋላ በሃያ ስድስት ዓመቱ ነበር። ዕንባቆም ትንቢቱን የተቀበለው ይህ መንፈሳዊ ተሐድሶ ከመካሄዱ በፊት ሳይሆን አይቀርም። ኢዮስያስ ያመጣው መንፈሳዊ ተሐድሶ በሕዝቡ መንፈሳዊ፥  ሥነ ምግባራዊና ማኅበረሰባዊ ሕይወት ላይ ለውጥ ከማምጣቱ በፊት በጦርነት ሞተ። ልጆቹም በጥቂት ዓመታት ውስጥ ከእግዚአብሔር ዞር አሉ። ዕንባቆም ስለ ባቢሎን ምርኮ የተናገረው ትንቢት በ586 ዓ.ዓ. ተፈጸመ። ራቅ ብሉ በስተሰሜን ምሥራቅ ይገኝ የነበረውና ለብዙ ምዕተ ዓመታት ኃያል የነበረው የአሦር መንግሥት በእርስ በርስ ጦርነት ይፈራርስ ጀመር። ባቢሎን በ627 ዓ.ዓ. በአሦር መንግሥት ላይ ያካሄደችው ዓመፅ ተሳካላት። በ612 ደግሞ የአሦርን ዋና ከተማ ነነዌን አሸነፈች። የአሦር ጦር እስከ 609 ዓ.ዓ. ድረስ ውጊያውን ሳያቋርጥ ቢታገልም፥ የቁጥጥሩ ኃይሉ ተንኮታኩቶ ነበር። ከለዳውያን በመባል የሚታወቁት ባቢሎናውያን ኃይላቸው እንደገና እየገነነ ሄደ፡፡ ይሁዳ በተከታታይ ለማመፅ የሞከረች ቢሆንም፥ ባቢሎን በ605 ዓ.ዓ. ኢየሩሳሌምን ደመሰሰቻት። በዚህም የዕንባቆም ትንቢት ይፈጸም ጀመር። የባቢሎን ኃያል መንግሥት ለ70 ዓመታት ብቻ ቆየና በ539 ዓ.ዓ. በሜዶንና በፋርስ መንግሥት ተደመሰሰ። እግዚአብሔር ከ100 ዓመታት በፊት በዕንባቆም በኩል እንደተናገረው ባቢሎንን ስለ ኃጢአትዋ ቀጣት። የውይይት ጥያቄ፥ ስለ ዕንባቆም ከመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት አንብብና ያገኘሃቸውን ዋና ዋና እውነቶች ዘርዝር። የትንቢተ ዕንባቆም አስተዋጽኦ  1. ዕንባቆም ለእግዚአብሔር ያቀረበው የመጀመሪያ ጥያቄ፡- እግዚአብሔር በይሁዳ የሚታየውን ክፋት ለምን አይቀጣም? (ዕንባቆም 1፡1-4) 2. የእግዚአብሔር የመጀመሪያ መልስ፡- እግዚአብሔር ይሁዳን ለመቅጣት ባቢሎናውያንን ይልካል (ዕንባቆም 1፡5-11)። 3. ዕንባቆም ለእግዚአብሔር ያቀረበው ሁለተኛ ጥያቄ፡- ጻድቅና ትክክለኛ ፈራጅ የሆነው እግዚአብሔር ጥቂት ክፋት ያለባትን ይሁዳን እጅግ ክፉ በሆኑት ባቢሎናውያን እንዴት ይቀጣል? (ዕንባቆም 1፡12-2፡1)።  4. የእግዚአብሔር ሁለተኛ መልስ፡-  ሀ. ጻድቅ ግን በእምነቱ በሕይወት ይኖራል (ዕንባቆም 2፡2-5)፣ ለ. ባቢሎናውያንም ይቀጣሉ (ዕንባቆም 2፡6-20)።  5. የዕንባቆም ጸሎት፡- ፍርድን በምታመጣበት ጊዜ ምሕረትህን አስብ (ዕንባቆም 3፡1-19)። (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡) የመመዘኛ ጥያቄዎችን ለማግኘት ከታች ያለውን ሊንክ (መስፈንጠሪያ) ይጫኑ፡፡

ትንቢተ ዕንባቆም መግቢያ Read More »

የትንቢተ ናሆም ዓላማ እና ዋና ዋና ትምርቶች

የትንቢተ ናሆም ዓላማ ናሆም ብቸኛ ዓላማው የነነዌን ውድቀት ማመልከት ነበር። እንደ ዮናስ ወደ ነነዌ በመሄድ መልእክቱን አላቀረበም። መልእክቱን ያቀረበው በይሁዳ ሆኖ ነበር። የናሆም መልእክት አሦርን ስለሚመጣባት ሽንፈት ለማስጠንቀቅ የተሰጠ አልነበረም፤ ነገር ግን የእግዚአብሔር ሕዝብ ለነበሩት ለአይሁድ የተሰጠ የማበረታቻ መልእክት ነበር። ለብዙ ዓመታት በአሦር መንግሥት ቁጥጥር ሥር ነበሩ። አሁን ግን ነነዌ የምትደመሰስበት ጊዜ እንደደረሰ እግዚአብሔር ይነግራቸዋል። እግዚአብሔር የአሦርን የአገዛዝ ዘመን ወደ ፍጻሜ ያመጣዋል። ከመቶ ዓመታት ለበለጠ ጊዜ በአሕዛብ ላይ ገዥ የነበሩትን አሦራውያንን ይቀጣል። እግዚአብሔር በመንግሥታት ሁሉ ላይ ሉዓላዊ ሥልጣን አለው። እርሱ ጻድቅና ትክክለኛ ፈራጅ ስለሆነ ነነዌ ፍርድ የምትቀበልበት ዘመን ደረሰ።  የትንቢተ ናሆም ዋና ዋና ትምህርቶች  1. የእግዚአብሔር ባሕርይ ሀ. የእግዚአብሔር ትዕግሥትና ምሕረት፡- የትንቢተ ናሆም አብዛኛው ክፍል በእግዚአብሔርና በባሕርዩ ላይ የሚያተኩር ነው። በአንድ በኩል እግዚአብሔር ለቁጣ የዘገየና በመከራ ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች መሸሽጊያ እንደሆነ ተገልጿል (ናሆም 1፡3፡ 7)። እግዚአብሔር በነነዌ ላይ፥ በተለይም ደግሞ የዮናስን መልእክት ሰምተው ንስሐ ከገቡ በኋላ፥ ሳይፈርድ የዘገየው በዚህ ባሕርዩ ምክንያት ነበር። ለ. የእግዚአብሔር ቁጣና ፍርድ፡- እግዚአብሔር ቸርና መሐሪ ብቻ አይደለም። ነገር ግን የቁጣ አምላክም ነው። እንደሚቀጣው በተናገረው ኃጢአት ላይ ቁጣውን ይገልጻል (ሮሜ 11፡22 ተመልከት)። እግዚአብሔር በትንቢተ ናሆም የተገለጸው ታላቅና ኃያል ሆኖ ነው። እግዚአብሔር ፍርዱ ቢዘገይም እንኳ፥ «… በደለኛውን ንጹሕ ነህ አይልም» (ናሆም 1፡3)። የእግዚአብሔር የቅጣት ኃይል በዚህ ስፍራ ከወጀብና ከዐውሎ ነፋስ፥ ከምድር መንቀጥቀጥም ጋር ተዛምዷል። ኃይሉ እጅግ ታላቅ ከመሆኑ የተነሣ ታላላቅ ወንዞችን ማድረቅ ይችላል። እኛ ክርስቲያኖች በእግዚአብሔር የፍቅር፥ ምህረትና በጎነት ባሕርይ ላይ ከሚገባ በላይ በማተኮር፥ እርሱ የቁጣ፥ የመዓት፥ የፍርድና የበቀል አምላክ መሆኑን እንዳንዘነጋ መጠንቀቅ ይገባናል። የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) እግዚአብሔር ለቁጣ የዘገየ፥ የፍቅርና የምሕረት አምላክ መሆኑ የሚያበረታታን እንዴት ነው? ለ) የእግዚአብሔርን የቁጣና የፍርድ ባሕርይ ስንዘነጋ ምን ይሆናል? ሐ) እግዚአብሔር ጥፋተኛውን ለመቅጣት ያለውን ውሳኔ፥ ቁጣውንና ትክክለኛ ፍርዱን ብናስታውስ ድርጊታችን እንዴት ሊለወጥ ይችላል? ሐ. እግዚአብሔር በመንግሥታትና በሕዝቦች ላይ ያለው የበላይ ተቆጣጣሪነት፡- ምንም እንኳ ዓለም የነነዌን ውድቀት በመመልከት፥ ይህ የሆነው በባቢሎን ገናናነትና በአሦር መሪዎች ደካማነት ነው ቢልም፥ መጽሐፍ ቅዱስ ግን እግዚአብሔር በነነዌ ላይ ለመፍረድና እርሷን ለማጥፋት በመወሰኑ እንደሆነ ያስተምራል። እግዚአብሔር አሦርን የእስራኤል መቅጫ በትር አድርጎ ተጠቀመባት። አሁን ፍርድን መቀበል የአሦር ተራ ነበርና እግዚአብሔር በእርሷ ላይ ለመፍረድ ባቢሎንን ተጠቀመ።  2. የእግዚአብሔር ፍርድ በአሕዛብና በመንግሥታት ሁሉ ላይ፡- እግዚአብሔር የሚፈርደው በግለሰቦች ብቻ ሳይሆን፥ በመንግሥታትም ላይ እንደሆነ ብዙ ጊዜ ተመልክተናል። እግዚአብሔር መንግሥታትን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተጻፉ ሕግጋት ብቻ ሳይሆን፥ በልባቸው በጻፈውም ሕግ መሠረት መኖር አለመኖራቸውን በሚመለከት ተጠያቂዎች ያደርጋቸዋል (ሮሜ 1፡18-29)። መንግሥታትና የመንግሥታት መሪዎች የእግዚአብሔርን ሕግ በግልጽ እየተቃወሙና እየጣሱ ሲኖሩ ለጊዜው ከእግዚአብሔር ፍርድ ሊያመልጡ ይችሉ ይሆናል። እግዚአብሔር ለቁጣ የዘገየ ስለሆነ ሰዎች ሁሉ ንስሐ እንዲገቡና ተመልሰው የእርሱን በረከት እንዲያገኙ ይፈልጋል (2ኛ ጴጥሮስ 3፡8-9)። ነገር ግን የእግዚአብሔርን በረከት እንዲያገኙ ትክክለኛና ቅን ፍርድ ማለት፥ የአሕዛብን ኃጢአት ሳይቀጣ አያልፍም ማለት ነው። እግዚአብሔር በራሱ ጊዜ በአሕዛብ ላይ ቅጣትን ያመጣል። በአጠቃላይ ታሪክን ያየን እንደሆነ የመንግሥታትና የሕዝቦች መውደቅና መነሣት ምክንያት ተፈጥሮአዊ ክስተት ብቻ ሳይሆን፥ እግዚአብሔር በእያንዳንዳቸው ላይ ፍርድን ለማምጣት የሚሠራው ሥራ ጭምር ነው።  በክፋትና በጭቆና ላይ የሚመሠረት ማንኛውም መንግሥት በመጨረሻ መውደቁ አይቀርም። እግዚአብሔር በሌሎች ላይ ባሳየችው የጭካኔና የአረመኔነት ተግባር አሦርን ተጠያቂ አድርጎ እርምጃ ሊወስድባት ተቃርቦ ነበር። በጥንት ታሪክ፥ በጭካኔያቸው ከሚጠቀሱ መንግሥታት ዋናዋ የአሦር መንግሥት ነበረች። ሰዎች እጅግ ይፈሩአት ነበር። አሦራውያን ማንኛውም ሕዝብ እንዳያምፅባቸው ለማድረግ ይህንን ጭካኔ ይጠቀሙበት ነበር። ማንኛውም የዓመፅ ተግባር ምልክት ወዲያውኑ ይቀጣ ነበር። ጠላቶቻቸውን በሕይወት እያሉ ያቃጥሏቸው፥ በአሰቃቂ ሁኔታ ይገርፏቸውና አካለ ጐደሉ ለማድረግ የሰውነት ክፍሎቻቸውን ይቀራርጡ፥ ወዘተ። ነበር። ሌሎች ሕዝቦችና መንግሥታትም የዚህ ዓይነቱን እጅግ አሠቃቂ ቅጣት ከመቀበል ይልቅ መገዛትን ይመርጡ ነበር። ነገር ግን እግዚአብሔር ይህንን ክፋት ይቆጥር ስለነበር፥ የፍርዱ ቀን ደርሶ ነነዌ በሌሎች ላይ የፈጸመችውን ክፋት በሙሉ ተቀበለች። ዛሬ የነነዌ ከተማ በዓለም ላይ የለችም። እግዚአብሔር እንደወሰነና በናሆም አስቀድሞ እንደተናገረ፥ ነነዌ እንደገና በማታንሰራራበት ሁኔታ ጠፋች። የውይይት ጥያቄ፥ ) ይህ እውነት በታሪክ ውስጥ የቀረበው እንዴት ነው? ወይም አንተ ለዓለም ታሪክ ባለህ ግንዛቤ መሠረት የተመለከትከው እንዴት ነው? ለ) ክርስቲያኖች እነዚህን ትምህርቶች ማስታወስ የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው?  የውይይት ጥያቄ፥ ናሆም 1-3 አንብብ። ሀ) ነነዌ የፈጸመቻቸውን የተለያዩ ኃጢአተች ዘርዝር። ) ናሆም በነነዌ ላይ የተነበያቸውን የተለያዩ የቅጣት ትንቢቶች ዘርዝር። 1. ፈራጅ ስለሆነው እግዚአብሔር የቀረበ መግለጫ (ናሆም 1፡1-8) ትንቢተ ናሆም ስለ እግዚአብሔር የተለያዩ መግለጫዎችን ይሰጣል። በክፉ ሕዝብ፥ በተለይም በነነዌ ላይ ሊፈርድ የተነሣውን የእግዚአብሔርን ሥዕላዊ መግለጫ እንመለከታለን። ጽድቅን የተሞላው የእግዚአብሔር ቁጣና ኃጢአትን ለመቅጣት የነበረው ውሳኔ ኃይሉን ለማሳየት በዚህ መልኩ ተገልጾአል። እግዚአብሔር ለቁጣ የዘገየ ቢሆንም እንኳ ቁጣው ገንፍሎ የሚመጣበት ጊዜ አለ። በዚያን ጊዜ «በቁጣው ፊት የሚቆም ማን ነው?» ዳሩ ግን ዓለምን መምሰል ለማይፈልጉና ለእግዚአብሔር በጽድቅና በመታዘዝ ለመኖር ለወሰኑ ሰዎች እግዚአብሔር መልካም ነው። በመከራ ቀንም መሸሸጊያ ነው።  2. ስለ ነነዌ መደምሰስ የተነገረ ትንቢት (ናሆም 1፡9-14) ምንም እንኳ ነነዌ በእግዚአብሔር ላይ በማሤር በክፉ መንገዷ መጓዝ ብትቀጥልም እግዚአብሔር የእርስዎን መደምሰስ ወስኖ ነበር፡፡ የነነዌ ተባባሪዎች ሁሉ ሊያድኗት አይችሉም ነበር። ነነዌና የአሦር ሕዝብ ተማርከው ይሄዳሉ። ከዝርያቸው ማንም አይቀርም፤ አማልክቶቻቸው ይደመሰሳሉ፤ ልክ እንደሞተ ሰው አሦር ልትቀበር ተዘጋጅታ ነበር።  3. የይሁዳ ነፃ መውጣት (ናሆም 1፡15) የነነዌ ውድቀት ለአሦር ሕዝብ ክፉ ወሬ ቢሆንም፥ ረዘም ላለ ጊዜ በከባድ ሁኔታ በአሦራውያን ሲሠቃዩ ለነበሩት የይሁዳ ሰዎች ግን መልካም ወሬ ነበር። ስለዚህ የአሦርን ውድቀት የሚያመለክተውን የምሥራች ይዞ የመጣው መልእክተኛ የተባረከ ነበር። አሁን ይሁዳ አሦርን ሳትፈራ እግዚአብሔርን ማምለክ ትችላለች። 4. ስለ ነነዌ ውድቀት የቀረበ ገለጻ (ናሆም 2-3) የትንቢተ ናሆም የመጨረሻ ሁለት ምዕራፎች በተለያዩ መንገዶች የነነዌን ውድቀት ይገልጻሉ። የነነዌ መወረርና መበዝበዝ ተገልጿል። ነነዌ ኀፍረተ ሥጋዋ በሰው ሁሉ ፊት ከተገለጠ ጋለሞታ ጋር ተወዳድራ ቀርባለች። የነነዌ ኃጢአት በዝርዝር ተገልጿል። ነነዌ እጅግ ታላቅ ከተማ ብትሆንም፥ በመጨረሻ አንድም ሰው በነነዌ አይቀርም። የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ከትንቢተ ናሆም የተማርሃቸውን አንዳንድ ጠቃሚ ትምህርቶች ግለጽ። ለ) አንተ ባለህበት ቤተ ክርስቲያን ለሚገኙ ክርስቲያኖች እነዚህን ትምህርቶች ማስተማር ጠቃሚ የሚሆነው ለምንድን ነው? (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡) የመመዘኛ ጥያቄዎችን ለማግኘት ከታች ያለውን ሊንክ (መስፈንጠሪያ) ይጫኑ፡፡

የትንቢተ ናሆም ዓላማ እና ዋና ዋና ትምርቶች Read More »

ትንቢተ ናሆም መግቢያ

የእግዚአብሔር ፍትሐዊ ወፍጮ የሚፈጨው በዝግታ ቢሆንም ጥሩ አድርጎ ይፈፃል የሚል አባባል አለ። ይህ ማለት በሰብአአዊ አመለካከት የእግዚአብሔር ፍትሕ በምድር ላይ የሚሠራ አይመስልም ማለት ነው። በሁሉም ስፍራ ጦርነት፥ ድኅነት፣ ፍትሕ-አልበኝነትና ክፋት አለ። ኃጢአተኞች እንዲሳካላቸውና ኑሮ እንዲሰምርላቸው ጉቦን፥ ዛቻንና ሰውን ማሠቃየትን ይጠቀማሉ። ብዙውን ጊዜ የእግዚአብሔርን ሕግጋት በግልጽ ከሚጥሱ ሰዎች ይልቅ ጻድቃን የበለጠ ሥቃይ የሚቀበሉ ይመስላሉ። እንዲህ ባሉ ጊዜያት እግዚአብሔር ቅን ፈራጅ በመሆኑ፥ እያንዳንዱን ሰው ወይም አገር እንደየሥራው ይቀጣዋል ወይም ይሸልመዋል የሚለውን አሳብ የማጣጣል ፈተና ይጋጥመናል። ታዲያ “የእግዚአብሔርን ሕግጋት መከትል ለምን ይጠቅማል?” ሌላው ሰው የእግዚአብሔርን ሕግ ሳይጠብቅ መበልጸጉን ከቀጠለ ለምን እንደ እርሱ አልሆንም? የተሻለ ነገር ለማግኘት ለምን ጉቦ አልሰጥም? በትምህርት ቤት ለምንስ አላጭበረብርም? የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) እንደዚህ ለማሰብ እንዴት እንደተፈተንህ ግለጽ። ለ) ብዙ ክርስቲያኖች በማታለል፥ ጉቦን በመቀበል ወይም ሌሎችን የእግዚአብሔር ሕግጋት ባለመጠበቅ እየተመላለሱና በሰይጣን ወጥመድ ውስጥ እየገቡ ያለው እንዴት ነው? ሐ) አማኞች እንደዚህ ለማሰብ በሚፈተኑበት ጊዜ እንዴት ትመክራቸዋለህ?  ትንቢተ ናሆም እግዚአብሔር ክፋትን ለመቅጣት ቢዘገይም፥ መቅጣቱ ግን እንደማይቀር ያስተምረናል። እርሱ ጻድቅና ቅን ፍርድ የሚያደርግ አምላክ ስለሆነ እኛም ሆንን ሌሎች የሚያደርጓቸው ነገሮች በቸልታ አይታለፉም። ቅጣቱን እኛው ራሳችን እንቀበላለን ወይም እግዚአብሔርን ይቅርታ በመጠየቅ ኢየሱስ ክርስቶስ ቅጣታችንን በመስቀል ላይ እንዲሸከምልን እናደርጋለን። ትንቢተ ዮናስን ስናጠና፥ እግዚአብሔር ዮናስን የአሦር መንግሥት ዋና ከተማ ወደሆነችው ወደ ነነዌ እንደላከውና የምትጠፋ መሆንዋን እንዳመለከተ አይተናል። ዳሩ ግን ሕዝቡ ንስሐ በገቡ ጊዜ እግዚአብሔር ፍርዱን ለሌላ ጊዜ አስተላለፈው። በትንቢተ ዮናስ የተመለከትነው፥ ሕዝቡ በንስሐ ወደ እርሱ በሚመለሱበት ጊዜ እግዚአብሔር ምን ያህል መሐሪ እንደሆነ ነበር፡፡ ትንቢተ ናሆም የተጻፈው ከ100 ዓመታት በኋላ ነው። አሁን ግን የንስሐ ጊዜ አልፎ ነበር። የእግዚአብሔር ትዕግሥትና ቻይነት ወደ ፍጻሜ ደርሶ ነበር። ትንቢተ ናሆም ነነዌ ሙሉ በሙሉ እንደምትጠፋ ይናገራል። ብዙ ሳይቆይ የናሆም ትንቢት በመፈጸሙ፥ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ነነዌ በባቢሎን መንግሥት ተደመሰሰች። የውይይት ጥያቄ፥- የሚከተሉትን ጥቅሶች ተመልከት፡- ማቴዎል 12፡35-37፤ ሮሜ 2:4-11፤ 14፡12። 2ኛ ቆሮንቶስ 5፡10። ሀ) በእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ የሚገኘው ማስጠንቀቂያ ምንድን ነው? ለ) ዓለምን እንመስልና የእግዚአብሔርን ሕግጋት እንጥስ ዘንድ ስንፈተን ይህን እውነት ማስታወስ የሚጠቅመን ለምንድን ነው? የትንቢተ ናሆም፥ አብድዩና ዮናስ መልእክቶች ተቀዳሚ ትኩረት በአሕዛብ መንግሥታት ላይ ትንቢት መናገር ነበር። ናሆም በአሦር መንግሥት ላይ የተነገረ ትንቢት ነው።  የትንቢተ ናሆም ጸሐፊ  ትንቢተ ናሆም የተጻፈው በናሆም ነበር፡፡ እንደ አብዛኛዎቹ የታናናሽ ነቢያት መጻሕፍት ስለ ናሆም ያለን መረጃ ጥቂት ነው። ናሆም ከኤልቆሻ ከተማ እንደነበር እናውቃለን። አንዳንድ ምሁራን ኤልቆሻ በደቡብ ይሁዳ የሚገኝ ቦታ ነው ቢሉም፥ ከተማው የነበረበትን ቦታ አናውቅም። ናሆም ከይሁዳ የነበረ ሳይሆን አይቀርም። እርሱ ባገለገለበት ዘመን የነበሩ የይሁዳና የእስራኤል ነገሥታት እነማን እንደነበሩ አልተጠቀሰም። ስለዚህ የተጻፈበትን ጊዜ ለመወሰን፥ በመጽሐፉ ውስጥ የሚገኙትን መረጃዎች መመልከት አለብን። ትንቢተ ናሆም የተጻፈው ከነነዌ ውድቀት በፊት ስለሆነ፥ ነነዌ በባቢሎን ከተያዘችበት ከ612 ዓ.ዓ. አስቀድሞ ነው ማለት ነው። ትንቢተ ናሆም የተጻፈው የግብፅ ከተማ ከሆነችው ከኖእ አሞን መደምሰስ በኋላ መሆኑንም እናውቃለን (ናሆም 3፡8)። ይህ የሆነው አሦራውያን ወደ ግብፅ ዘልቀው ገብተው ከተማይቱን በያዙበት በ663 ዓ.ዓ. ነበር። ስለዚህ ትንቢተ ናሆም የተጻፈው ከ663-612 ዓ.ዓ. ባለው ጊዜ ነበር። በ650 ዓ.ዓ. አሦራውያን ከግብፅ ተባረው ወጡና ኖእ አሞን ከተማ እንደገና ተቆረቆረች። ስለዚህ ናሆም ያገለገለው በክፉው ንጉሥ በምናሴ ዘመነ መንግሥት (609-642 ዓ.ዓ.) ወይም በኢዮስያስ ዘመነ መንግሥት (640-609 ዓ.ዓ.) ነው ማለት ነው። ብዙ ምሁራን ይህ መጽሐፍ የተጻፈው በምናሴ ዘመነ መንግሥት መጨረሻ ገደማ ምናልባትም ከ655-650 ዓ.ዓ. ባለው ጊዜ እንደሆነ ይገምታሉ። የትንቢተ ኢሳይያስና ናሆም የአጻጻፍ ሥልት መመሳሰሉን መመልከት አስገራሚ ነው (ናሆም 1፡15 ና ኢሳይያስ 52፡7 አወዳድር)። ናሆም ምናልባት ትንቢተ ኢሳይያስን አንብቦት ይሆናል።  የትንቢተ ናሆም ታሪካዊ ሥረ መሠረት  አሦር ለብዙ መቶ ዓመታት በመካከለኛው ምሥራቅ የምትገኝ ኃያል አገር ነበረች። እግዚአብሔር በሰሜኑ የእስራኤል መንግሥት የሚገኙትን ሕዝቡን ለመቅጣት የተጠቀመው በአሦራውያን ነበር (722 ዓ.ዓ.)። አሦራውያን የእስራኤልን ሕዝብ በክፋትና በተንኮል ማርከው ወሰዱአቸው። አሦር የታወቀችው በጭካኔዋና ሌሉች ሕዝቦችን በቁጥጥር ሥር በምታውልበት የማስፈራሪያ ኃይሏ ነበር። በአሦር ላይ ለማመፅ የሚደረግ ማንኛውም ሙከራ ምልክት የሕዝቡ ሁሉ ተነቅሉ መበተን፥ መሠቃየትና መቀጣት ነበር። ይሁዳ በአሦር ባትያዝም እንኳ ለብዙ ዓመታት በእርስዋ ቁጥጥር ሥር ሆና አንድ ቅኝ መንግሥት መከፈል የሚገባውን ግብርና ቀረጥ ትከፍል ነበር። በሕዝቅያስ ዘመነ መንግሥት፥ አሦር ይሁዳን አጥቅታ ከኢየሩሳሌም በስተቀር የቀሩትን ክፍሎች በሙሉ ይዛ ነበር። ኢየሩሳሌምም የዳነችው እግዚአብሔር በጉዳዩ ውስጥ ጣልቃ በመግባቱና የአሦር ሠራዊት በመደምሰሱ ነበር (2ኛ ነገሥት 19፡35-36)። ንጉሥ ምናሴ የአሦርን ጣዖት ለማምለክ ወደ አሦር ሄዶ ነበር። የአሦርን የጣዖት አምልኮ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ይሁዳ ያመጣ እርሱ ነው። በኋላም በአሦር ላይ ዓመፀና በምርኮ ተወሰደ። በመጨረሻም ከምርኮ ተለቆ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ። እግዚአብሔር ናሆምን ለነቢይነት በጠራው ጊዜ አሦር እጅግ ገናናና ኃያል በመሆኗ፤ ማንም ሊያሸንፋት የማይችል ትመስል ነበር። ንጉሥ አሱርባኒፓል በትረ ሥልጣኑን ይዞ ባደረጋቸው በርካታ ጦርነቶች መንግሥቱን እስከ ግብፅ ድረስ እንኳ ዘልቆ አስፋፍቶ ነበር። ነነዌ ጨርሶ ልትነካ በማትችልበት ሁኔታ ላይ የምትገኝ ትመስል ነበር። ታሪክን ሁሉ የሚቆጣጠረው እግዚአብሔር ግን የሚደርስባትን ነገር ያውቅ ነበር። ከአሱርባኒፓል ሞት በኋላ የአሦር መንግሥት በፍጥነት ማሽቆልቆል ጀመረ (ከ669-627 ዓ.ዓ.)። የተለያዩ ገዥዎች ሥልጣን ለመጨበጥ በሚያደርጉት ጥረት በአገሪቱ የእርስ በርስ ጦርነት ይካሄድ ጀመር። ከዚያም በ627 ዓ.ዓ. የባቢሎን ከተማ ከአሦር ነፃ ሆና ራሷን ቻለች። የባቢሎን መንግሥት በ612 ዓ.ዓ. ከሜዶን ሠራዊት ጋር በመተባበር የአሦርን መንግሥት አሸንፋ ተቆጣጠረች። በጥንት ታሪክ ውስጥ ከባቢሎን ቀጥላ በሁለተኛ ደረጃ እጅግ ገናና የነበረችው፥ ታላቅ ግንቦች፥ የመናፈሻ ቦታዎች፥ ሙዝናኛዎች፥ የእንስሳት መጠበቂያዎች ወዘተ. የነበሯት ታላቋ የነነዌ ከተማ ተደመሰሰች። ከዚያ በኋላ በዓለም ኃያል መንግሥት ሆና ከቶ አልተነሣችም አትነሣምም፡፡ እግዚአብሔር በነነዌ ላይ ያወጀው ፍርድ ተፈጸመ። የውይይት ጥያቄ፥ በነነዌ ላይ ተነግሮ ከነበረው ትንቢት ፍጻሜ ስለ እግዚአብሔርና ስለ ቃሉ ኃይል ምን እንማራለን? ናሆም ያገለገለው ሶፎንያስ ባገለገለበትና በመጀመሪያዎቹ የኤርምያስ የአገልግሎት ዘመናት ነበር።  የትንቢተ ናሆም አስተዋጽኦ  1. ስለ ፈራጁ እግዚአብሔር የተሰጠ መግለጫ (ናሆም 1፡1-8)።  2. ስለ ነዌ መደምሰስ የተነገሩ ትንቢቶች (ናሆም 1፡9-14)፥  3. የይሁዳ ነፃ መውጣት (ናሆም 1፡15)፥ 4. የነነዌ ውድቀት መግለጫ (ናሆም 2-3)። የውይይት ጥያቄ፥ ስለ ናሆም ከመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ተመልከት። በዚያም ስለ ናሆም የተጠቀሱትን አንዳንድ ጠቃሚ እውነተች ዘርዝር። (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡) የመመዘኛ ጥያቄዎችን ለማግኘት ከታች ያለውን ሊንክ (መስፈንጠሪያ) ይጫኑ፡፡

ትንቢተ ናሆም መግቢያ Read More »