የደቀ-መዝሙር ትምሕርት

በርካታ ሰዎች፣ የክርስቶስን አዳኝነት በተቀበሉ ሰአት ከእግዚአብሔር ጋር የጀመሩት ጉዞ እዛው ላይ እንደሚያበቃ ያስባሉ፡፡ ይህ ከእውነታው እጅግ የራቀ ነው። እርግጥ ነው ጌታን የመቀበል ውሳኔ የዘላለም አድራሻችንን እስከወዲያኛው ይለውጣል! ይህ ውሳኔ በሕይወታችን ከወሰነው ውሳኔ ሁሉ ታላቁና ወሳኙ ነወ። በዚህ ውሳኔያችን አማካኝነት እንዲያው በጸጋው ከመንፈሳዊው ዘር ተወልደናልና የእግዚአብሔር ልጆች እንሆን ዘንድ ስልጣንን አግኝተናል። እናም የዘላለም ሕይወት አለን!! ነገር ግን፣ በምድር በሚኖረን ቀሪ የሕይወት ዘመን እግዚአብሔር ከእያንዳንዳችን ጋር ሊያደርገው የሚወዳቸው በርካታ መንፈሳዊ ጉዳዮች አሉ፡፡ የዚህ ትምሕርት ዋነኛው ጉዳይም ከድነታችን በኋላ ባለው ቀሪው የምድራዊ ሕይወታችን ዘመን እግዚአብሔር ከኛ የሚሻውን ነገር ማሳወቅ ነው።

እግዚአብሔር በአስተሳሰብህ፣ በቅደመ ሁኔታዎችህ፣ በትምህርትህ፣ በመዝናኛዎችህ፣ በፍቅር ሕይወትህ፣ በወደፊት ሕይወትህ፣ በገንዘብህ፣ በጊዜ አጠቃቀምህ፣ በእቅዶችህ፣ እንዲሁም በማናቸውም የሕይወት ጉዳዮችህ ውስጥ እጁን ማስገባትና ዋነኛ ተዋናይ መሆን ይፈልጋል፡፡ እግዚአብሔር በሕይወትህ ጉዳዮች ሁሉ ከአንተ ጋር ‹‹አንድ›› በመሆን እርሱ የሚያፈቅራቸውንና የሚሻቸውን ነገሮች ሁሉ አንተም በሙሉ ልብህ እንድታፈቅራቸውና እንድትሻቸው ይፈልጋል፡፡ ለአንተና የአንተ የሆነውን ሁሉ ማላቅና ማሳደግ ይሻል፣ ደግሞም ፈጣሪህ እንደመሆኑ ይህንን እንዴት መከወን እንዳለበትም ጠንቅቆ ያውቃል!

ከመፀነስህ ዘመን አንስቶና ከዚያም በፊት እግዚአብሔር ሁለት ፈረጅ ያለው አላማ ለሕይወትህ ሰንቆልሃል፡-

  1. አንደኛው፣ ለዘላለም ከእርሱ ተለይተህ እናዳትኖር አንተን መታደግ ሲሆን (የዘላለም ሕይወት/ድነት መስጠት)
  2. ሁለተኛው ደግሞ፣ ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስን እንድትመስል ማድረግ ነው (የክርስቶስ ደቀ-መዝሙር ማድረግ)

የመጀመሪያው አላማ (አላማ #1) ጌታን በተቀበልክ ቅፅበት ተግባራዊ የሚሆን ሲሆን ሁለተኛው አላማ (አላማ #2) ግን የሕይወት ዘመን ጉዞህን የሚጠይቅ ነው፡፡ ይህ ጉዞ በመንፈሳዊ ልደትህ ወቅት ተጀምሮ የሚቀጥል ሂደት ሲሆን ሂደቱም ኢየሱስ በሰው አካል በምድር ላይ ሲመላለስ በነበረበት ወቅት ወደ ነበረበት ፍፁምነት እስክትደርስ ድረስ ወይም ከዚህ አለም በሞት ተለይተህ በሰማይ እርሱን ለመገናኘት እስከምትሄድበት ጊዜ ድረስ የሚቀጥል ነው፡፡

እስካሁን በዚህች ምድር ላይ ወደዚህ ፍፅምና የደረሰ ፍጡር የለም ሊኖርም አይችልም፡፡ ነገር ግን ይህ ጉዳይ ተስፋ ሊያስቆርጥህ አይገባም! በመንፈሳዊ የብስለት ጎዳና ባደግህ መጠን፣ እግዚአብሔር ለአንተ ያሰበውን ‹‹የተትረፈረፈ›› ሕይወት ለመለማመድ ትችላለህ (ዮሐንስ 10፡10)፡፡ በመንፈስ በጎለመስክ ቁጥር፣ መገኘቱን፣ የባርኮት እጆቹን፣ በውሳኔዎችህ ውስጥ ደግሞ የእርሱን ምሪት ይበልጥ እየተለማመድክ ትሄዳለህ፡፡ ለእርሱ ያለህ ጠቀሜታ ባደገ ቁጥር ደግሞ፣ ደስታህና የመኖር አላማህ ጥልቅ እየሆነ ይመጣል፡፡ መኖርህንም ትወደዋልህ። መልካሙን ለማድረግና ክፉውንም ለመጸየፍ ያለህ ፍላጎት እየጨመረ ይሄዳል፡፡ ለእርሱና ለሌሎች ያለህ ፍቅር ንጹህ እየሆነም ይሄዳል፡፡ በሕይወትህ ለነገሮች የምትሰጠው የቅደም ተከተል ተርታዎች ከእርሱ ቅደም ተከተሎች አንጻር የሰመሩ ግቡብ ይሆናሉ፡፡ ስለ እግዚአብሔር መንግስት እውነታ ያለህ ምልከታ ይጠራል፡፡ የእግዚአብሔር የእድገት መለኪያ እንደሆነው እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ ማየት፣ ማድረግና ለነገሮች ምላሽ መስጠት ትጀምራለህ፡፡

ይህን ጉዞ ለመጀመር ተዘጋጅተሃል (ተዘጋጅተሻል)? እንግዲያው ከዚህ በታች የቀረበው ባለ 48 ክፍለ-ትምሕርት የጥናት ኮርስ የዚህ ጉዞህ(ሽ) አጋዥ መሳሪያ ይሆናል፡፡ የደቀመዝሙር ማስልጠኛ መጽሐፉ በአንድሪው ዋማክ ተዘጋጅቶ በጸሃፊው ሙሉ ፈቃድ በ የሕይወት እንጀራ አገልግሎት የተተረጎመ ሲሆን መጽሐፉ እያንዳንዱ አማኝ በእግዚአብሔር ቃል እውነት ሥር እንዲሰድና ፍሬያማ የክርስቶስ ደቀ መዝሙር እንዲሆን በታልቅ ጥንቃቄ የተዘጋጀ ነው፡፡ ከዚህ የሚከተለውን ሊንክ በመጫን መጽሐፉን በ ፒ.ዲ.ኤፍ ፋይል በማውረድ አልያም እዚሁ (ኦንላይን) ላይ በማንበብ ጥናትዎን ይቀጥሉ፡- የደቀ መዝሙር ማሰልጠኛ