ዘካርያስ 1-14
ብዙ ሰዎች እግዚአብሔር ትንቢትን የሰጠው ወደፊት ምን እንደሚሆን እንድናውቅ ነው ብለው ያስባሉ። ስለዚህ የትንቢትን መጻሕፍት የሚያጠኑት በከፍተኛ ጉጉት ነው። ወደፊት በመካከለኛው ምሥራቅ ምን እንደሚሆን ለማወቅ፥ ወይም ሩስያ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተጠቅሳ እንደሆነ ወይም በመጨረሻዎቹ ቀናት ከእስራኤል ጋር የሚዋጉት አገሮች የትኞቹ እንደሆኑ ለማወቅ በመጓጓት ያጠናሉ። የውይይት ጥያቄ፥ አንዳንድ ክርስቲያኖች ትንቢትን በተመለከተ የዚህ ዓይነት አመለካከት ሲጠቀሙ ያየኸው እንዴት ነው? እግዚአብሔር የትንቢት መጻሕፍትን መልእክት የሰጠን ወደፊት ምን እንደሚሆን የማወቅ ፍላጎታችንን ለማርካት አይደለም። ትንቢት የተሰጠው የእግዚአብሔርን ሕዝቦች በተለይም ደግሞ በስደት ውስጥ የሚኖሩትን እግዚአብሔር የበላይ ተቆጣጣሪ መሆኑን በማስተማር ለማበረታታት ነው። እግዚአብሔር ስለመጪው ጊዜ ዕቅድ አለው። ይህ ዕቅድ ጦርነቶችንና ፍርድን የሚጨምር ነው። ይህም ቢሆን በእግዚአብሔር ቁጥጥር ሥር የሚፈጸም ነው። ይህ ዕቅድ በሚጠቃለልበት ጊዜ እግዚአብሔር ፍጹም በሆነው ምድር ይነግሣል። ኃጢአትና ሞት ይደመሰሳሉ። ክርስቲያኖች በእምነታችን ምክንያት በምንሰደድበት ጊዜ ወይም ብዙ ችግሮች ሲያጋጥሙን ፍጻሜያችን መልካም መሆኑን በማስታወስ ልብ ገዝተን ልንኖርና በእምነታችን ልንጸና እንችላለን። ወደፊት እግዚአብሔር ምን ሊያደርግ እንዳለው በእምነት መመልከት እንችላለን። በትንቢተ ዘካርያስ ውስጥ ዘካርያስ ተስፋ የቆረጡትን አይሁድ የሚያበረታታበት ዋና መንገድ የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን መምጣትና እርሱም የሚያመጣውን በረከት በማሳየት እግዚአብሔር የሁሉ ነገር የበላይ ተቆጣጣሪ መሆንን በማረጋገጥ ነበር። የውይይት ጥያቄ፥ ዘካርያስ 1-14 አንብብ። ሀ) ዘካርያስ ያያቸውን የተለያዩ ራእዮች ዘርዝር። የእነዚህ ራእዮች ትርጉም ምን ይመስልሃል? ለ) በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ወደፊት ስለሚሆኑ ነገሮች የተጠቀሱትን የተለያዩ ትንቢቶች ዘርዝር። ሐ) ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የተጠቀሱትን የተለያዩ ትንቢቶች ዘርዝር። ክፍል 1፥ አይሁድ ቤተ መቅደሱን በመሥራት ላይ ሳሉ የመጡላቸው መልእክቶች (ዘካርያስ 1-8) 1. ዘካርያስ ንስሐ እንዲገቡ ለሕዝቡ ጥሪ አደረገ (ዘካርያስ 1፡1-6) አይሁድ ለእግዚአብሔር ታዝዘው ቤተ መቅደሱን እየሠሩ ቢሆኑም እንኳ በሕይወታቸው አሁንም ኃጢአት ነበር። ስለዚህ ትንቢተ ዘካርያስ የሚጀምረው አይሁድን ስለ ኃጢአታቸው በመውቀስና ንስሐ እንዲገቡ ጥሪ በማድረግ ነው። ለእግዚአብሔር አንድ ነገር ከምናደርግለት ይልቅ ብንቀደስለት ይመረጣል። እግዚአብሔር የምናደርግለትን ነገር የሚቀበለው ከኃጢአታችን ንስሐ ስንገባ ብቻ ነው። አይሁድ የዘካርያስን መልእክት ከሰሙ በኋላ ንስሐ ገቡ። እግዚአብሔርም ይባርካቸው ዘንድ ከሚችልበት ሁኔታ ላይ ደረሱ። የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) በዚህ ዘመን ብዙ ክርስቲያኖች ቅዱሳን ከመሆን ይልቅ የእግዚአብሔርን ነገር ማከናወን የሚቀላቸው ለምንድን ነው? ለ) ይህ ነገር ሲፈጸም እንዴት እንደተመለከትህ የሚያስረዱ ሥዕላዊ መግለጫዎችን ዘርዝር። ሐ) እግዚአብሔር ለእርሱ ምንም ነገር ከማድረጋችን በፊት እንቀደስ ዘንድ በእጅጉ አበክሮ የሚናገረው ለምን ይመስልሃል? 2. ዘካርያስ በሌሊት ያያቸው ስምንት ራእዮች (ዘካርያስ 1፡7-6፡8) ሕዝቡ ከእግዚአብሔር ጋር ትክክለኛ ግንኙነት እንዲኖራቸው ካደረገው መልእክቱ ቀጥሎ፥ ዘካርያስ በአንድ ሌሊት ያያቸውን ስምንት ራእዮች ያቀርባል። እነዚህ ራእዮች በአሕዛብ እንደተጨቆኑ በመቁጠር ኃዘን የተሰማቸውንና ለእግዚአብሔር በሚሠሩት ሥራ ተስፋ ቆርጠው የነበሩትን አይሁዶች የሚያበረታቱ ነበሩ፤ እያንዳንዳቸው እግዚአብሔር ለአይሁዶች የሰጠውን ግልጽ የሆነ ልዩ የማበረታቻ መልእክት የያዙ ነበሩ። ሀ. የመጀመሪያው ራእይ – በዛፎች መካከል ቆሞ የነበረው ፈረሰኛ (ዘካርያስ 1፡7-17) አይሁድ ወደ አገራቸው ቢመለሱም፥ ገና በአሕዛብ ቁጥጥር ሥር ነበሩ። አሕዛብ በምቾት ሲዝናኑ እነርሱ ግን በመከራ ውስጥ ነበሩ። ነገር ግን እግዚአብሔር ነገሮችን ተቀጣጥሮ ነበር። ፈረሰኛው በዓለም ሁሉ ተዘዋውሮ ሰላምን እንዳገኘ ሁሉ እግዚአብሔርም ቤተ መቅደሱ እንደሚሠራና የእስራኤል ሕዝብ በሰላም እንደሚኖር ለአይሁድ ተስፋ ሰጠ። ሰላም እየመጣ ነበር፤ ዳሩ ግን እግዚአብሔር በእነርሱ ምትክ ሆኖ እስኪሠራና የይሁዳን ምድር እስኪያድስ ድረስ መጠበቅ ነበረባቸው። ለ. ሁለተኛው ራእይ – አራት ቀንዶችና አራት ጠራቢዎች (ዘካርያስ 1፡18-21) ለአይሁድ ቀንድ የብርታትና የኃይል ምልክት ነበር። እነዚህ ቀንዶች እስራኤልን የበተኑትን መንግሥታት ወይም በአሕዛብ ላይ የነገሡትን ነገሥታት ሊያመለክቱ ይችላሉ። ቀንዶቹ እስራኤልን የበተኑና አይሁድን ወደ ምርኮ የወሰዱትን መንግሥታት የሚወክሉ ነበሩ። በዚህ ስፍራ የቀንዶቹ አራት መሆን አራት የተለያዩ መንግሥታትን የሚወክል ይሆናል የሚለው አሳብ ምሁራንን ያከራክራቸዋል። አንዳንዶች እነዚህ አራት መንግሥታት ባቢሎን፥ ሜዶንና ፋርስ፥ ግሪክና ሮም ናቸው ሲሉ፥ ሌሎች ደግሞ አሦር፥ ግብፅ፥ ባቢሎንና እንዲሁም ሜዶንና ፋርስ ናቸው ይላሉ። አራቱ ጠራቢዎች የሚወክሉት ደግሞ ለአይሁድ መበተን ምክንያት የሆኑት የአሕዛብ መንግሥታት የሚቀጡባቸውን የእግዚአብሔርን የፍርድ መሣሪያዎች ነው። እስራኤልን የወጉ ሁሉ በተራቸው ይደመሰሳሉ። አንዳንድ ምሁራን እነዚህ አራት ጠራቢዎች ባቢሎንን የደመሰሰው ሜዶንና ፋርስ፥ ሜዶንና ፋርስን የደመሰሰው ግሪክ፣ ግሪክን የደመሰሰው ሮም፥ በመጨረሻ ላይ የሮምን መንግሥት የሚደመስሰው መሢሑ ነው ብለው ያምናሉ። ዋናው ትምህርት የእስራኤልን ጠላቶች እግዚአብሔር በራሱ ጊዜ ይደመስሳቸዋል የሚለው ነው። እግዚአብሔር ጠላቶቹን የሚደመስስባቸው የተለያዩ ዓይነት ጠራቢዎች አሉት። ሐ. ሦስተኛው ራእይ – የመለኪያ ገመድ የያዘው ሰው (ዘካርያስ 2) በዘካርያስ ዘመን የኢየሩሳሌም ቅጥሮችና የከተማው አብዛኛው ክፍል ተደምስሶ ነበር። ነህምያ ከአይሁድ ጋር ቅጥሩን ለመሥራት የሚመጣው ገና ከብዙ ዓመታት በኋላ ነበር። በጥንት ጊዜያት አንድ ከተማ ቅጥር ከሌለው፥ የማይረባና ጥቃት መፈጸም ለሚፈልግ ጠላት ሁሉ የተጋለጠ ነበር። በዚህ ራእይ ዘካርያስ የኢየሩሳሌምን ከተማ ለመለካት የመለኪያ ገመድ የያዘ ሰው ይመለከታል። ዳሩ ግን በኢየሩሳሌም ከተማ የሚኖረው ሕዝብ እጅግ ብዙ ስለነበር ለመለካት ጨርሶ የማይቻል ነበር። እግዚአብሔር አንድ ቀን የኢየሩሳሌም ከተማ ቅጥር ሊኖራት እስከማይችል ድረስ እጅግ ታላቅ ትሆናለች የሚል ተስፋ ሰጠ። እግዚአብሔር ራሱ በከተማዋ ውስጥ ስለሚኖርና የእሳት ቅጥር ስለሚሆናት ለጥበቃ የሚሆን ምንም ዓይነት ቅጥር የማያስፈልግበት ጊዜ ይመጣል። ከአይሁድ መካከል ከምርኮ የተመለሱት ጥቂቶች ብቻ ነበሩ። ብዙዎቹ በባቢሎንና በሌሎች አሕዛብ መካከል በምቾት መኖርን መረጡ። ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲመለሱ ጥሪ አደረገላቸው። አንድ ቀን አይሁድን ሁሉ ከዓለም ዙሪያ በመሰብሰብ ወደ ኢየሩሳሌም እንደሚያመጣቸው ተናገረ። በዚያም ከእነርሱ ጋር ከሚተባበሩ ሌሎች ሕዝቦች ጋር እግዚአብሔር አብሮአቸው ይሆንና ይባርካቸዋል። መ. አራተኛ ራእይ – ለታላቁ ካህን ለኢያሱ የተሰጡ ንጹሕ አልባሳት (ዘካርያስ 3) ኢያሱ የእስራኤል ሊቀ ካህን ነበር። ይሁን እንጂ የሚሠራበት ቤተ መቅደስና ከእርሱ አስቀድሞ የነበሩ ካህናት ይለብሱአቸው የነበሩት ዓይነት ንጹሕና ጌጠኛ አልባሳት አልነበሩትም። ታዲያ እርሱ በእርግጥ የሕዝቡ መንፈሳዊ መሪ ነበርን? እግዚአብሔር አገልግሎቱን ተቀብሏልን? ኢያሱ በእግዚአብሔር የተመረጠ መሣሪያ መሆኑን ለሕዝቡ ለማሳየት እግዚአብሔር ለዘካርያስ ራእይ ሰጠው። በዚያ ራእይ ሰይጣን ንጹሕ አይደለም በማለት ኢያሱን በእግዚአብሔር ፊት ሲከሰው እንመለከታለን። (እድፋም ልብስ የመንፈሳዊ ንጽሕና ጉድለት ምልክት ነበር።) እግዚአብሔር ግን ኢያሱን የመረጠው እርሱ እንደሆነና በፊቱ ንጹሕ እንደሆነ ለሰይጣን ያረጋግጥለታል። (ጥሩ ልብስና ንጹሕ ጥምጥም ተደረገለት።) ሊቀ ካህን መሆን እንደሚገባው ለማረጋገጥ እግዚአብሔር ለኢያሱ የሊቀ ካህን ልብስ ሰጠው። ካህን እንዲሆን የተጠራው ኢያሱ የእስራኤል ሕዝብ ተምሳሌትም ነበር (ዘጸአት 19፡5-6)። ሰይጣን ኢያሱን እንደከሰሰ የእግዚአብሔር ምርጥ ሕዝብ የሆኑትን እስራኤልንም ንጹሕ አይደላችሁም በማለት ከሰሳቸው። ዳሩ ግን እግዚአብሔር አንጽቶ እንደገና የእርሱ ካህናት ይሆኑ ዘንድ ጠራቸው። የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ሰይጣን ኃጢአተኛ ነህ በማለት ለሚከሰው ክርስቲያን እግዚአብሔር ስለሚሰጠው መልስ ይህ ራእይ ጥሩ መግለጫ የሚሆነው እንዴት ነው? ለ) ኃጢአታችን የተሸፈነው በምንድን ነው? በዚህ ራእይ ስለ ኢየሱስ የሚናገር አሳብ እናገኛለን፤ እርሱም ቅርንጫፍ ተብሏል። ይህም በኢሳይያስ 4፡2 እና በሌሎችም የብሉይ ኪዳን ክፍሎች ከዳዊት ሥር የሚመጣውን መሢሕ ለማመልከት የተጠቀሰ ተምሳሌታዊ አገላለጽ ነው። ይህ ትንቢት ሙሉ በሙሉ የሚፈጸመው በእርሱ ብቻ ነው። የሰዎችን ኃጢአት ለመሸፈንና አይሁድን ለማዳን በመስቀል ላይ በተፈጸመው የክርስቶስ የሞቱ ሥራ አንድ ቀን ኃጢአት ከምድሪቱ ፍጹም ይወገዳል፤ ሰላምም ይኖራል። ሠ. አምስተኛ ራእይ – የወርቅ መቅረዝና ሁለት የወይራ ዛፎች (ዘካርያስ 4) የቤተ መቅደሱ ሥራ መጓተት ብዙዎቹን አይሁድ ተስፋ አስቆርጦ ነበር። የሰሎሞንን ቤተ መቅደስ ያህል ትልቅ እንዳልነበር አወቁ። ስለሆነም ምናልባት በዘሩባቤልና በኢያሱ ላይ ማጉረምረም ሳይጀምሩ አልቀሩም። እግዚአብሔር የእስራኤል ሕዝብ የፖለቲካ መሪ የነበረውን ዘሩባቤልንና መንፈሳዊ መሪ የነበረውን ኢያሱን በመንፈሱ እንዳበረታቸው ለሕዝቡ የሚያስረዳ አምስተኛ ራእይ ለዘካርያስ ሰጠው። በዚህ ራእይ ዘካርያስ ሰባት መብራቶች የነበሩበትን አንድ የወርቅ መቅረዝ አየ። በወርቅ መቅረዙ ላይ የዘይት ማሰሮ ነበር። በወርቅ መቅረዙ አጠገብ በማሰሮው ግራና ቀኝ
