የብሉይ ኪዳን መጽሐፍ ቅዱስ ጥናት

በትንቢተ ዮናስ ውስጥ ዐበይት መንፈሳዊ ትምህርቶች

ትንቢተ ዮናስ እጅግ ጠቃሚ በሆኑ መንፈሳዊ እውነቶችና ከሕይወታችን ጋር ሊዛመዱ በሚችሉ ቁም ነገሮች የተሞላ ነው። ከዚህ መጽሐፍ ልንማራቸው ከምንችል ትምህርቶች አንዳንዶቹ ቀጥሉ ተዘርዝረዋል፡- 1. የእግዚአብሔር ባሕርይ ሀ. እግዚአብሔር ፈቃዱን ለመፈጻም ነገሮችን ሁሉ የሚቆጣጠርበትን ኃይል እንመለከታለን። እግዚአብሔር ማዕበሉን፥ ዓሣ ነባሪውን፥ ትሉን ሳይቀር ሲቆጣጠር እንመለከታለን። ሁሉም እርሱ የሚፈልገውን ነገር አድርገዋል። ለ. የእግዚአብሔርን ታላቅ ርኅራኄ መመልከት እንችላለን። እግዚአብሔር የነዌ ሰዎች እንዲሞቱ አልፈለገም ነበር። ዳሩ ግን ንስሐ የሚገቡበትን ዕድል እንዲያገኙ ፈለገ። እግዚአብሔር የነነዌ ሰዎች ባሳዩት አነስተኛ የንስሐ ምልክት በእነርሱ ላይ ተዘርግቶ የነበረውን የፍርድ እጁን አነሣ።  ሐ. ጽድቅ የሆነውን የእግዚአብሔር ቁጣ እንመለከታለን። እግዚአብሔር ክፋትን ስለሚጠላ ኃጢአትን ይቀጣል። እግዚአብሔር ለቁጣ የዘገየ ነው (ዮናስ 4፡2)። እግዚአብሔር መራራቱን የሚተውበትንና የሚፈርድበትን ጊዜ ይወስናል። መ. ትንቢተ ዮናስ መሠረታዊ የሥነ-መለኮት ጥያቄ ያነሣል። «እግዚአብሔር ክፉዎችንና ኃጢአተኞችን የማይቀጣው ለምንድን ነው?» (ዮናስ 4፡4፥9)። ብዙ ጊዜ ከፉና ኃጢአተኛ የሚበለጽግ፥ ጻድቅ ደግሞ መከራን የሚቀበል ይመስላል። ክርስቲያኖች ዘወትር የሚፈልጉት እግዚአብሔር ክፉና ኃጢአተኛ የሆ፥ ጠላቶቻቸውን ፈጥኖ እንዲቀጣላቸው ነው። እግዚአብሔር እነርሱ በሚፈልጉት ፍጥነት ይህን ሳያደርግ ሲቀር ግራ ይጋባሉ። ትንቢተ ዮናስ እግዚአብሔር ይቅር ለማለት ወይም ለመቅጣት መብት እንዳለው ይናገራል። እግዚአብሔር ክፉዎችና ኃጢአተኞች የሆኑትን ሰዎች ፈጥኖ ለመቅጣት ወይም የፍርድ እጆቹን ሳይሰነዝር ለዘላለም ለመቆየት አይገደድም። መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር ኃጢአተኞችንና ክፉዎችን እንደሚቀጣ ያስተምረናል። ፍርዱ በኃጢአት ላይ ይፈጸማል (ኤርምያስ 13፡14)። ዳሩ ግን መቼ መፈጸም እንዳለበት የመወሰን መብት ያለው እግዚአብሔር ራሱ ነው፤ በዚህ ሕይወት ወይም በዘላለማዊነት ሊሆን ይችላል። 2. የእግዚአብሔር ሕዝብ ባሕርይ  ዮናስ የእግዚአብሔር ሕዝብ ምሳሌ ነው። እኛ ብዙውን ጊዜ ልክ እንደ ዮናስ ነን። ሀ. የተረጋገጠ ማስረጃ ሳይኖረን እንደ ዮናስ በሌሉች ላይ መጥፎ አስተያየት የምንሰነዝር ሰዎች ነን። ከሌሎች ነገዶች የሆኑ ሰዎችን በመጥላት ወንጌል እንዲደርሳቸው ባለመፈለግ የዘር መድልዎ የምናሳይ ሰዎች ነን። ከዳኑ በኋላም ቢሆን በየቤተ ክርቲያኖቻችን ሙሉ በሙሉ አንቀበላቸውም። ከእነርሱ ጋር ጋብቻ አንመሠርትም። በኢኮኖሚ ዓቅማቸው ከእኛ ጋር የማይመጣጠኑትን ሰዎች አድልዎ በማድረግ እናገላቸዋለን። ሀብታሞች ከሆንን ከሀብታሞች ጋር ብቻ ኅብረት በማድረግ ድሆችን እንንቃለን። ድሆች ከሆንን ደግሞ፥ ከድሆች ጋር ብቻ ኅብረት በማድረግ ከሀብታሞቹ ይልቅ መንፈሳዊ የሆንንን ይመስለናል። ወንዶች ከሴቶች ይልቅ የተሻሉ እንደሆኑና በእግዚአብሔር ዘንድ ተፈላጊነት እንዳላቸው የሚያስቡበት የጾታ ልዩነትም አለ። እግዚአብሔር እነዚህን ሁሉ ይጠላል። እነዚህ ሁሉ መንፈሳዊ ብስለት የሌለንና ከእግዚአብሔር የራቅን መሆናችንን የሚያሳዩ ምልክቶች ናቸው። አዲስ ኪዳን የመለያየትና የአድልዎ ግድግዳዎች ሁሉ በክርስቶስ አካል የፈራረሱ መሆናቸውን ያስተምረናል (ገላትያ 3፡28፤ ቈላስይስ 3፡11 ተመልከት)። ለ. የእግዚአብሔር ሕዝብ እርሱ ለሕይወታቸው ካለው ዓላማና ፈቃድ ብዙ ጊዜ ይሸሻሉ። የእግዚአብሔር ፈቃድ ከባድ ወይም የማይወዱት እንደሆነ ያስባሉ። ስለዚህ በራሳቸው ውሳኔ በመሸሽ ሌላ ነገር ያደርጋሉ። በዚህም ማድረግ የሚችሉት ከሁሉ የላቀ ነገር እንደሚያመልጣቸው አይገነዘቡም። እውነተኛ ደስታ ለማግኘት የምንችለው እግዚአብሔር የሚፈልገውን ነገር ስናደርግ ብቻ ነው። ከእግዚአብሔር መሸሽ አደገኛ ነው። ጉዳቱ ለእኛ ብቻ አይደለም፤ በሌሎች ሰዎች ሕይወት ላይም አደጋ ሊያመጣ ይችላል። ምንም በማያውቁ የመርከብ ላይ መንገደኞች፥ በሚስቶቻችን፥ በልጆቻችን፥ ወዘተ. ሠራተኞች አደጋ ሊያስከትል ይችላል።  ሐ. የእግዚአብሔር ሕዝብ ብዙውን ጊዜ ለሌሎች ወንጌልን የማዳረስ አስፈላጊነት ዘንግተው በራሳቸው ጉዳዮች ላይ ብቻ ያተኩራሉ። ብዙ ክርስቲያኖች የሚጐዳኙትና አብረው የሚውሉት ከክርስቲያኖች ጋር ብቻ ነው። የዓለም ብርሃን ይሆኑ ዘንድ እግዚአብሔር እንደጠራቸው ይዘነጋሉ። ዮናስ ከሕዝቡ ይልቅ ለቅሏ እንዳዘነ፥ እኛም በየቀኑ ያለ ክርስቶስ እየሞቱ ወደ ገሃነም ከሚሄዱት ከብዙ ሺህ ሰዎች ይልቅ፥ ለሥልጣናችን ወይም ለቁሳዊ ሀብታችንና ለምቾት ኑሮአችን ልንጨነቅ እንችላለን።  3. እግዚአብሔር ከሕዝቡ ጋር ያለው ግንኙነት ትንቢተ ዮናስ እግዚአብሔር ከሕዝቡ ጋር ስላለው ግንኙነት በርካታ ትምህርቶችን ይሰጠናል። ሀ. እግዚአብሔር ሕዝቡን ወደ ፈቃዱ ለመመለስ በትጋት ሲሠራ እንመለከታለን።  ለ. የቀድሞ ስሕተቶቻቸውን እየረሳ ሰዎችን እንደገና ለመጠቀም የሚያስችለውን የእግዚአብሔር ጸጋ እናያለን።  ሐ. እግዚአብሔር በፈቃዱ ውስጥ ባይሆኑም እንኳ በከፍተኛ ደረጃ በሰዎች ለመጠቀም ያለውን ችሎታ እንመለከታለን። ዮናስ ከእግዚአብሔር ሸሽቶ በመሄድ ላይ ነበር፤ እግዚአብሔር ግን ለመርከበኞቹም ኃይሉን ለማሳየት ተጠቀመበት። ዮናስ በእግዚአብሔር ላይ ተቆጥቶ ነበር፤ እግዚአብሔር ግን አንዲት ትልቅ ከተማን ለማዳን ተጠቀመበት። የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) እነዚህን እውነቶች በራስህ ሕይወት ወይም በሌሎች ሕይወት ያየህባቸውን መንገዶች ዘርዝር። ለ) እነዚህ እውነቶች ለክርስቲያኖች የሚያስፈልጓቸው ለምንድን ነው? በአዲስ ኪዳን ውስጥ የዮናስ ታሪክ የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ሆኖ እናያለን። ዮናስ ለነነዌ ሰዎች ምልክት እንደነበር፥ ኢየሱስም ለአይሁድ ምልክት ነበር (ሉቃስ 11፡30)። ዮናስ በዓሣ ነባሪ ሆድ ውስጥ ለሦስት ቀንና ሌሊት እንደነበር፥ ኢየሱስም በመቃብር ውስጥ ለሦስት ቀንና ሌሊት ነበር (ማቴዎስ 12፡39-41)። ኢየሱስ «የዮናስ ምልክት» በማለት በማቴዎስ 16፡4 የተናገረው፥ ልክ ዮናስ በዓሣ ነባሪው ሆድ ውስጥ ከነበረበት ተምሳሌታዊ ሞት እንደተነሣ ክርስቶስም መነሣቱን የሚያሳይ ነው። የውይይት ጥያቄ፥ ዮናስ 1-4 አንብብ። ሀ) ዮናስ ከእግዚአብሔር ጋር የነበረውን ግንኙነት ግለጽ። ለ) እግዚአብሔር ካልዳኑ ሰዎች ጋር ያለውን ግንኙነት ግለጽ። ዮናስ በእስራኤል ሕዝብ መካከል የሚኖር የእግዚአብሔር ነቢይ ነበር። ምናልባት እግዚአብሔር በኃይል ተጠቅሞበት ይሆናል። ነገር ግን እግዚአብሔር ለዮናስ ሌሎች ዕቅዶች ነበሩት። የአሦር ዋና ከተማ ወደሆነችው ወደ ነነዌ እንዲሄድ ፈልጎ ነበር። እግዚአብሔር በዮናስ በኩል ለነነዌ ያስተላለፈው መልእክት የፍርድ መልእክት ነበር። ምናልባት ዮናስ ለባዕዳን እጅግ ጨካኞች የነበሩትን አሦራውያንን ፈርቶ ይሆናል። ነገር ግን የፈራው ሌላው ነገር ወደ አሦር ከሄደና ከሰበከላቸው፥ ንስሐ ይገቡና እግዚአብሔር ይቅር ይላቸዋል የሚለውን አሳብ ይመስላል። ዮናስ አሦራውያን በንስሐ ተመልሰው እንዲኖሩ ሳይሆን፥ እንዲጠፉ ፈልጎ ነበር። አሦር የምትገኘው ከእስራኤል በስተሰሜን ምሥራቅ 1200 ኬሎ ሜትሮች ያህል ርቃ ነበር። ወደዚያ ለመድረስ ብዙ ወራቶችን ይወስድ ነበር። ዮናስ ግን ወደ ምዕራብ ሄደ። በምዕራብ ከሚገኙና ከሚያውቋቸው ከተሞች ራቅ ብላ ወደምትገኘው ወደ ጠርሴስ የሚሄድ መርከብ አገኘ። ጠርሴስ በስፔይን ውስጥ የምትገኝ ሳትሆን አትቀርም።  ዮናስ ከእግዚአብሔር ሸሽቶ ለማምለጥ የሚችል መስሉት ነበር። እግዚአብሔር ግን ለዮናስ ዓላማ ነበረው። በታላቅ ትዕግሥት ዮናስን ለማስተማርና እንዲታዘዝ ለማድረግ ጣረ። አውሎ ነፋስን፥ ዓሣ ነባሪን፥ ቅልንና ትልን በመጠቀም እግዚአብሔር ዓላማውን ፈጸመ። የእግዚአብሔር ዓላማዎች በአንድ ነገር ብቻ የተወሰኑ አለመሆናቸውን መመልከቱ አስደናቂ ነው። እግዚአብሔር ጉዳይ ያለው ከነነዌ ሰዎች ጋር ብቻ ሳይሆን በመርከቡ ላይ ከተሳፈሩት ሰዎች ጋርም ነበር። እግዚአብሔር ከአሕዛብ ጋር ጉዳይ ያለው ቢሆንም፥ በዚህ አጋጣሚ ዮናስም እንዲያድግ ይፈልግ ነበር። እግዚአብሔር አውሎ ነፋስን በመጠቀም፥ በመርከቡ ውስጥ የነበሩ ሠራተኞች ዮናስን ወደ ባሕሩ እንዲጥሉት አደረገ። እግዚአብሔር ዓሣ ነባሪን በማዘጋጀት ዮናስን እንዲውጥና መልሶ ወደ ባሕር ዳርቻ እንዲወስደው አደረገ። ዮናስም በዓሳው ሆድ ውስጥ ሆኖ ወደ ነነዌ ተጓዘ። እግዚአብሔር የዮናስን መልእክት ይሰሙ ዘንድ አሦራውያንን አዘጋጅቶ ስለነበር መልእክቱን ሰሙና ፈጥነው ንስሐ ገቡ። ዮናስ አሁንም ቢሆን የሚፈልገው አሦራውያን ሲጠፉ ማየት ነበረና ወደ ተራራማ ስፍራ በመሄድ በከተማይቱ ላይ የሚሆነውን መጠባበቅ ጀመረ። እግዚአብሔር የነነዌን ሰዎች ባለመቅጣቱ እጅግ ተቆጣ። እግዚአብሔር ቅልና ትንሽ ትልን በመጠቀም ሰዎች ከሌሎች ቁሳዊ ነገሮች የላቁና የተሻሉ መሆናቸውንና ከሕዝቡ ሥጋዊ ምቾት ይልቅ የአሕዛብ ንስሐ መግባት እንደሚገደው ለዮናስ አስተማረው። የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ከትንቢተ ዮናስ የተማርሃቸውን አንዳንድ መንፈሳዊ ትምህርቶች ዘርዝር። ለ) እነዚህን ትምህርቶች በቤተ ክርስቲያንህ ለሚገኙ ለሌሉች ሰዎች ለማስተማር ዐቅድ። (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡) የመመዘኛ ጥያቄዎችን ለማግኘት ከታች ያለውን ሊንክ (መስፈንጠሪያ) ይጫኑ፡፡

በትንቢተ ዮናስ ውስጥ ዐበይት መንፈሳዊ ትምህርቶች Read More »

የትንቢተ ዮናስ ዓላማ

ትንቢተ ዮናስ ትንቢትን የያዘ ባይሆንም እንኳ አመዳደቡ ከትንቢት መጻሕፍት ውስጥ ነው። አይሁዶች ይህንን ያደረጉት ለምድን ነው? የዮናስ ታሪክ የተጻፈው ለአሦራውያን ጥቅም ሳይሆን፥ ለአይሁድ ነበር። እግዚአብሔር ለእነርሱ ስላለው ዓላማና ፍላጎት በርካታ የሆኑ ጠቃሚ ትምህርቶችን እንዲማሩ ከእግዚአብሔር የተሰጠ ነበር። ዮናስ ራሱ መማር የነበረበትን ትምህርት የእስራኤል ሕዝብ መማር ነበረባቸው፡፡  1. እግዚአብሔር አይሁድን ሲጠራ ለራሳቸው ጥቅም ብቻ በስግብግብነት በመኖር በእግዚአብሔር በረከት ብቻቸውን ደስ እንዲሰኙ ሳይሆን ለአሕዛብም በማዳረስ የእግዚአብሔር መሣሪያዎች እንዲሆኑ ነበር። «የካህናት መንግሥት» ነበሩ (ዘጸአት 19፡6)። ለአሕዛብ ብርሃን መሆን ይጠበቅባቸው ነበር (ኢሳያያስ 42፡6፤ 49፡6)። አሕዛብ የሚባረኩት በእነርሱ በኩል ነበር (ዘፍጥረት 12፡3)። እስራኤላውያን ግን ይህንን በመዘንጋት እግዚአብሔር መባረክ ያለበት እነርሱን ብቻ እንደሆነና አሕዛብ መረገምና መደምሰስ እንዳለባቸው አሰቡ። እግዚአብሔር የዮናስን ሕይወት እስራኤላውያን የተመረጡበትን ዓላማ ለማስታወስ ተጠቀመበት። በዮናስና በእስራኤላውያን ታሪክ ውስጥ የሚከተሉትን ተመሳሳይ ነገሮች ተመልከት፡- – ለአሕዛብ ወንጌል ይሰብኩ ዘንድ እግዚአብሔር ዮናስንና እስራኤልን ጠራቸው።  – ዮናስና እስራኤል ግን ከእግዚአብሔር የተሰጣቸውን ተልእኮ ለመታዘዝ ሳይፈቅዱ ቀሩ።  – ዮናስ በባሕር ውስጥ በመጣል፥ እስራኤል ደግሞ በአሕዛብ መካከል በመበትን ተቀጡ። (በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ባሕር ብዙ ጊዜ የአሕዛብ ምሳሌ ነው።)  – እግዚአብሔር ዮናስን በዓሣ ነባሪ ሆድ ውስጥ እንደጠበቀው፥ የእስራኤልንም ሕዝብ ይጠብቃል።  – ዮናስ ንስሐ ገብቶ ተመለሰ። አንድ ቀን እስራኤልም ንስሐ ገብታ ትመለሳለች። ዮናስ በመጨረሻ ለእግዚአብሔር እንደታዘዘ፥ እስራኤልም አንድ ቀን ለእግዚአብሔር በመታዘዝ የዓለም ብርሃን ትሆናለች። የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) የእስራኤልና የቤተ ክርስቲያን ጥሪ ተመሳሳይ የሆነው እንዴት ነው? ለ) ዮናስ ለነነዌ የነበረው አመለካከት ብዙ ክርስቲያኖች በዚህ ዘመን በሌሎች ነገዶች ደኅንነት ላይ ካላቸው አመለካከት ጋር የሚመሳሰለው እንዴት ነው? ሐ) የአንተ ቤተ ክርስቲያን እንደ እስራኤልና ዮናስ የመሆን አደጋ ይገጥማታል ብለህ ታስባለህ? መልስህን አብራራ። 2. በአንዳንድ ምሁራን አስተሳሰብ የመጽሐፉ ዓላማ፥ እግዚአብሔር – አሕዛብ ለነበሩት ለነነዌ ሰዎች እንደራራ፥ እስራኤልም በዙሪያዋ ላሉት አሕዛብ በመራራት ይቅር እንድትል ማስተማር ነው (ማቴዎስ 5፡44 ተመልከት)። 3. ሌሎች ምሁራን ደግሞ የዚህ መጽሐፍ ትኩረት በእግዚአብሔርና በባሕርዩ እንዲሁም ከሰው ጋር ባለው ግንኙነት ላይ ነው ይላሉ። የመጽሐፉ ትኩረትና ዐቢይ ትምህርት እግዚአብሔር ለመረጠው ሕዝብ ቸር ለመሆን ያለውን ችሎታና መብት ማሳየት በመግለጽ፥ እግዚአብሔር በማን ላይ መፍረድና ማንን ይቅር ማለት እንዳለበት መወሰን የሰዎች መብት አይደለም። እግዚአብሔር ሰዎችን ይቅር ለማለትና ሁለተኛ ዕድል ለመስጠት ያለውን ፍላጎት የሚናገር መጽሐፍ ነው። ዮናስና ነነዌ ተመሳሳይ ነበሩ። ሁለቱም ለእግዚአብሔር ባለመታዘዝ ይኖሩ ነበር። ይህ አለመታዘዛቸው ወደ እግዚአብሔር ፍርድ መራቸው። ሁለቱም ከነበሩበት ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ በራሳቸው ኃይል ለመውጣት አልቻሉም ነበር። በመጨረሻ ሁለቱም የነበሩበትን ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ አስተዋሉና በንስሐ ወደ እግዚአብሔር ተመለሱ። እግዚአብሔር ሁለቱንም ያዳናቸውና የታደጋቸው በጸጋው ነው። ሰዎች ኃጢአት ከበዛበት መንገዳቸው ወደርሱ ሲመለሱ፥ እግዚአብሔር ጸጋውን ለማሳየት ይወዳል። ለሰዎች ሁለተኛ ዕድል መስጠት ይወዳል። ነነዌ ከእግዚአብሔር ፍርድ ራስዋን ማዳን አትችልም ነበር። ለሕዝቦቿ ብቸኛው ዕድላቸው ወደ እግዚአብሔር በንስሐ መመለስ ነበር። ይህም በመሆኑ፥ እግዚአብሔር በትክክለኛ አቅጣጫ የጀመሩትን ርምጃ በማክበር በእነርሱ ላይ ሊያመጣ የነበረውን ፍርድ ለጊዜው አስተላለፈው። የነነዌ ሰዎች ብዙ ሳይቆዩ ወደ ቀድሞው ኃጢአታቸው ስለተመለሱ ንስሐቸው በጣም የላላ ነበርና እግዚአብሔርን በእውነት አምነው ነበር ለማለት አይቻልም። በጥቂት ዓመታት ውስጥ እስራኤልን ይወጋሉ፤ ፈጽመውም ያጠፏታል፤ ሕዝቡንም ይማርካሉ። ቆይተን በትንቢተ ናሆም ውስጥ እንደምናየው እግዚአብሔር በነነዌ ላይ ያስተላለፈው ፍርድ ሊለወጥ የማይችል ነበር። ነነዌና ዮናስ ለእስራኤል ሕዝብ ትምህርት ሰጪዎች ነበሩ። ስለዚህ ትንቢተ ዮናስ ለእስራኤል ሕዝብ ማስጠንቀቂያ ነበር። ዮናስ መጻሕፍት ካዘጋጁት ከመጀመሪያዎቹ ነቢያት አንዱ ነበር። ከእርሱ በኋላ የተነሡ ነቢያት ሁሉ የእስራኤል ሕዝብ እንደሚጠፉ አመልክተዋል። በትንቢተ ዮናስ ግን እስራኤላውያን እንደ ነነዌ ሕዝብ እንደነበሩ በመጥቀስ ያስጠነቅቃቸዋል። በኃጢአታቸው ምክንያት ሊፈረድባቸውና ሊጠፉ ይገባቸው ነበር። እስራኤላውያን የእግዚአብሔርን ጥበቃ የመጠየቅ መብት እንደሌላቸው አለመታዘዛቸውን ያመለክት ነበር። እግዚአብሔር ግን ጸጋውን ሊያሳያቸው ፈለገ። ስለዚህ ንስሐ ሲገቡና ከክፋታቸው ቢመለሱ እግዚአብሔር የፍርድ እጁን ከእነርሱ ላይ ሊያነሣ ደስታው ነበር። የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ከዚህ መጽሐፍ ስለ እግዚአብሔር ባሕርይ ምን እንማራለን? ለ) ስለ ንስሐና ደኅንነት ምን እንማራለን? ሐ) ከዚህ ውስጥ ስለ እውነተኛ ንስሐና ስለ ሐሰተኛ ንስሐ ምን እንማራለን? (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡) የመመዘኛ ጥያቄዎችን ለማግኘት ከታች ያለውን ሊንክ (መስፈንጠሪያ) ይጫኑ፡፡

የትንቢተ ዮናስ ዓላማ Read More »

ትንቢተ ዮናስ መግቢያ

አንድ ሰባኪ ወይም አገልጋይ እግዚአብሔር እንደሚፈልገው ባይመላለስ ያንን ሰው እግዚአብሔር ሊጠቀምበት ይችላልን? እግዚአብሔር ብዙዎችን ወደ ራሱ ለማምጣት ዓለማዊነት በሚያጠቃው ወንጌላዊ ሊጠቀም ይችላልን? አንድ ክርስቲያን እርሱ ሳይባረክ፥ እግዚአብሔር ሌሎችን ለመባረክ ሊጠቀምበት ይችላልን? የውይይት ጥያቄ፥ እነዚህን ጥያቄዎች እንዴት ትመልሳቸዋለህ? መልስህን አብራራ። ትንቢተ ዮናስ ዓለም እስካሁን ካየቻቸው የተሳካላቸው ሰባኪዎች መካከል አንዱ ስለሆነው ሰው ታሪከ ይገልጣል። በመልእክቱ ንጉሡን ጨምሮ የአንዲት ከተማ ሕዝብ በሙሉ ንስሐ እንዲገቡ አደረገ። ይሁን እንጂ የዮናስ ልብ በእግዚአብሔር ፊት ትክክል አልነበረም። ለአገልግሎቱ የነበረው ዝንባሌ እጅግ መጥፎ ነበር። ስለዚህ ራሱ ሊያገኝ የሚችለውን በረከት አጣ። ትንቢተ ዮናስ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ለሆንን ሰዎች ከባድ ማስጠንቀቂያ ይዟል። ሕይወታችንን በሙሉ በእግዚአብሔር ቤት አገልግሎት ልናሳልፍ፥ እግዚአብሔር በኃይል ሊጠቀምብንና ለሌሎች በረከት ልንሆን እንችላለን። ነገር ግን እግዚአብሔር የሚፈልገን ዓይነት ሰዎች ላንሆን፥ አገልግሎትን በሚመለከት የተሳሳተ ዝንባሌ ሊኖረንና እግዚአብሔር የሚሰጠንን በረከት ልናጣ እንችላለን።  የትንቢተ ዮናስ ጸሐፊ ከታናናሽ ነቢያት ሁሉ ላቅ ብሉ የታወቀው ዮናስ ነው። ታሪኩን ሁላችንም የምናውቀው ነው። ትንቢተ ዮናስ ከታናናሽ ነቢያት የሚመደብ ቢሆንም፥ ከሌሉች የትንቢት መጻሕፍት ሁሉ ፍጹም የተለየ ነው። የትንቢት መጻሕፍት በሙሉ ነቢያት ለሕዝቡ የተናገሯቸው መልእክቶች የተጻፉባቸው ናቸው። ትንቢተ ዮናስ ግን ነነዌ በጥቂት ቀናት ውስጥ እንደምትጠፋ የሚገልጽ መልእክት ከመያዙ ሌላ ምንም ዓይነት ትንቢት አልያዘም። ይልቁንም መጽሐፉ ከነቢያት አንዱ የሆነውን የዮናስን ታሪክ የያዘ ነው። ትንቢተ ዮናስ የተሰየመው የመጽሐፉ ዋና ባለታሪክ በሆነው በዮናስ ስም ነው። መጽሐፉን ዮናስ እንደጻፈው የሚገልጽ አሳብ በመጽሐፉ ውስጥ ስለሌለና የተጻፈው በሦስተኛ ሰው ስለሆነ፥ ማን እንደጻፈው ማረጋገጥ አንችልም። በግምት ግን የዚህ መጽሐፍ ጸሐፊ ዮናስ ሳይሆን አይቀርም። እንዲሁም የዮናስን ታሪክ በሚያውቅ በሌላ ሰውም ተጽፎ ሊሆን ይችላል። እንደ አብዛኛዎቹ ታናናሽ ነቢያት፥ ስለ ዮናስ የምናውቀው ነገር በጣም ጥቂት ነው። ዮናስ ነቢይ እንደሆነ በ2ኛ ነገሥት 14፡25 ተጠቅሷል። በእስራኤል ይኖር የነበረና በዳግማዊ ኢዮርብዓም ዘመነ መንግሥት የነበረ ነቢይ ነው። ለእስራኤል ሕዝብ ለማስተላለፍ የፈለገው መልእክት ምን እንደ ነበረ አናውቅም። ስለ እርሱ የምናውቀው ነገር ቢኖር፥ እግዚአብሔር የአሦር ዋና ከተማ ወደነበረችው ወደ ነነዌ የፍርድ መልእክት እንዲያደርስ በላከው ጊዜ ከእግዚአብሔር ጋር የነበረውን ግንኙነት ብቻ ነው። በትንቢተ ዮናስ ከተመዘገበው ታሪክ ቀጥሎ ምን እንደተፈጸመ የምናውቀው ነገር የለም። ዮናስ ከኃጢአቱ በንስሐ ተመልሶ ይሆን?  ካሳለፈው የሕይወት ልምድ ተምሮ ይሆን? ወደ እስራኤል የተመለሰው በንስሐ በተለወጠ ልብ ካልሆነ በቀር መጽሐፉን አይጽፍም ነበር የሚል እምነት ስላለን፥ ለእነዚህ ጥያቄዎች ልንሰጥ የምንችለው ምላሽ ቢኖር አዎንታዊ ግምት ብቻ ነው።  የትንቢተ ዮናስ መጽሐፍ  የትንቢተ ዮናስ ታሪክ እውነተኛነት በብዙ ምሁራን ዘንድ አጠያያቂ ሆኖአል። ዮናስ በዓሣ ነባሪ ሆድ ውስጥ ለሦስት ቀናት እንዴት በሕይወት ሊቆይ ይችላል? ጥላ የሆነችው ቅል እንዴት በፍጥነት ልታድግ ቻለች? ይህ ሊሆን የሚችል ነገር አይደለም በማለት ምሁራን መጽሐፉን በተለያዩ መንገዶች ይተረጉማሉ።  1. ተምሳሌታዊ አተረጓጐም፡- የመጽሐፉ ታሪክ እያንዳንዱ ክፍል አንድን እውነት የሚወክል ነው። ታሪኩንም ሆነ ለታሪኩ የሚሰጠውን ትርጉም በቁሙ (በቀጥታ) ልንረዳው አይገባም። 2. ምሳሌያዊ አተረጓጐም፡- አንዳንዶች ደግሞ ይህ ታሪክ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ከተናገራቸው ምሳሌዎች ጋር ተመሳሳይ ነው ይላሉ። (ለምሳሌ፡- የመልካሙ ሳምራዊ ታሪክ)። ይህ ታሪክ እውነተኛ አይደለም። ነገር ግን የሥነ-ምግባር ትምህርት ለማስተማር የተዘጋጀ የፈጠራ ታሪክ ነው ይላሉ። የዚህ ዓይነቱ ታሪክ ልጆች እውነትን በሚገባ እንዲረዱ ለማድረግ የሚነገር እውነተኛ ያልሆነ ታሪክ የሚመስል ነው)።  3. እውነትን ለማስተማር ተጋንኖ የቀረበ ታሪክ፡- አንዳንዶች የዚህ ታሪክ የተወሰነ ክፍል እውነተኛ ነው ይላሉ። ወደ ነነዌ የሄደ ዮናስ የሚባል ሰው ነበር። ይሁን እንጂ በታሪኩ ውስጥ የተጠቀሱት ዝርዝር ጉዳዮች ታሪኩን የበለጠ ልብ የሚነካ ለማድረግ ተጋንነው የቀረቡ ናቸው። ይህም የተመለከትነውን አደጋ ለመግለጥ ወይም የሠራነውን ታላቅ ሥራ ለማስረዳት በማጋነን እንደምንናገራቸው ነገሮች ያለ ነው። የተመሠረተው በእውነተኛ ታሪክ ላይ ቢሆንም፥ ይበልጥ ሕይወት እንዲኖረው ለማድረግ በዝርዝር ጉዳዮች ላይ ተጨማሪ ነገሮችን እናክላለን።  4. በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደተጻፈው በቀጥታ በዮናስ ሕይወት የተፈጸም ታሪክ ነው። መጽሐፉን የምንረዳበት ከሁሉም የተሻለው መንገድ ተአምራቱን ጨምሮ የተጻፈው ሁሉ እንዳለ የተፈጸመ እውነተኛ ታሪክ መሆኑን ማመን ነው። ኢየሱስ በዚህ ታሪክ እንዳመነና ዮናስ በዓሣ ነባሪ ሆድ ውስጥ ለሦስት ቀንና ሌሊት የቆየበትን ታሪክ የሞቱና የትንሣኤው መግለጫ አድርጎ እንደተጠቀመባት ግልጽ ነው (ማቴዎስ 12፡40-41)። በዓሣ ነባሪ ሆድ ውስጥ በርካታ ቀናት የቆዩና ዓሣ ነባሪው ተይዞ ከውስጡ ሲወጡ በሕይወት የተገኙ የሌሎች ሰዎች ታሪኮች አሉ።  ታሪካዊ ሥረ መሠረት ዮናስ የኖረው በዳግማዊ ኢዮርብዓም ዘመነ መንግሥት ነው (782-753 ዓ.ዓ.)። ኢዮርብዓም እግዚአብሔርን የማያመልክ ክፉና ኃጢአተኛ ቢሆንም፥ ኃይለኛ ንጉሥ እንደነበር የሚታወስ ነው። የእስራኤልን ድንበር በዳዊትና በሰሎሞን ዘመነ መንግሥት ወደነበረበት ስፍራ ሊመልስ ችሎ ነበር። ይህ የሆነበት አንዱ ምክንያት በዚያ ዘመን ከነዓንን የሚቆጣጠር ኃያል መንግሥት አለመኖር ነው። ወደ ሰሜን ምሥራቅ ርቃ ትገኝ የነበረችውና ሶርያን ያሸነፈችው አሦርም ደካማ ነበረች። ይህም ለእስራኤል ሕዝብ ታላቅ ሰላምንና ብልጥግናን አስገኝቶ ነበር። እስራኤል ታላቅ አገር በሆነች ጊዜ በብርታትዋ ትታበይ ጀመር። ኃይሏንና ብልጥግናዋን ያገኘችው የእግዚአብሔር ምርጥ በመሆኗ መሰላት፡፡ በውስጧ የነበረውን የጣዖት አምልኮ እያወቀች ካለማስወገዷም ንስሐ ለመግባት አልፈለገችም። እስራኤላውያን የእግዚአብሔር ሕዝብ ስለሆኑ እግዚአብሔር ለሌሎች አሕዛብ፥ በተለይም በጭካኔያቸው አንድ ጊዜ ለታውቁ ሕዝቦች ግድ የለውም የሚል እምነት ነበራቸው። አሦር ኃያል አገር እንደሆነችና በማንኛውም ጊዜ የእነርሱ ጠላት ልትሆን እንደምትችል እስራኤላውያን ያውቁ ነበር። ነቢዩ አሞጽ በኋላም ሆሴዕ በኃጢአታቸው ምክንያት እግዚአብሔር ከደማስቆ ባሻገር (አሞጽ 5፡27) ትገኝ ወደነበረችው ወደ አሦር (ሆሴዕ 9፡3) እንደሚያስማርካቸው ለእስራኤል ሕዝብ መናገር ጀምረው ነበር፡፡ እግዚአብሔር የእስራኤልን ሕዝብ የሚቀጣው በአሦር አማካይነት እንደሆነ ዮናስ ያውቅ እንደነበረ መገመት ይቻላል። አሦራውያን ለጠላቶቻቸው ከፍ ያለ ጭካኔን በማሳየት ቀድሞውኑ እውቅናን ያተረፉ ነበሩ። አንዳንድ ጊዜ ጠላቶቻቸውን ከነሕይወታቸው ይቀብሩ፥ ቆዳቸውን ይገፍፉና ምላሳቸውን ጎልጉለው በማውጣት ይቆርጡ ነበር። ዮናስ ወደ ነነዌ ሰዎች ሄዶ ለመስበክ ያልፈለገባቸው ምክንያቶች እነዚህ ነበሩ። እግዚአብሔር በዮናስ በኩል ለሚያመጣው መልእክት አሦራውያንን አዘጋጅቶአቸው ነበር ማለት ይቻላል። በ765ና በ759 ዓ.ዓ. አሦርን የመቱ ሁለት ከባድ መቅሠፍቶች ወርደው ነበር። በ763 ዓ.ዓ. ደግሞ የጥንት ሰዎች ብዙ ጊዜ የእግዚአብሔር ፍርድ ምልክት ነው ብለው የሚያምኑት የፀሐይ ግርዶሽ ተከስቶ ነበር። አንዳንዶች ደግሞ የመሬት መንቀጥቀጥ ሳይፈጸም አልቀረም ይላሉ። ዮናስ ራሱ ያልተለመደ ምልክት ነበር ማለት ይቻላል። ዮናስ በዓሣ ነባሪ ሆድ ውስጥ ለሦስት ቀናት ስለቆየ፥ የዓሣ ነባሪው የጨጓራ አሲድ ፀጉሩንና ቆዳውን ወደ ነጭነት ቀይሮት ይሆናል። አሦራውያን ዮናስ ላመጣው መልእክት ፈጣን ምላሽ የሰጡት በእነዚህ ሁሉ ምክንያቶች ሳይሆን አይቀርም።  የትንቢተ ዮናስ አስተዋጽኦ  1. ዮናስ ለአሦራውያን እንዲሰብክ ከተሰጠው ተልእኮ ሸሸ (ዮናስ 1-2)፤  2. ዮናስ ለአሦራውያን እንዲሰብክ የተሰጠውን ተልእኮ ፈጸመ (ዮናስ 3-4)፤  ሀ. የሕዝቡ በንስሐ መመለስ (ዮናስ 3)፥  ለ. ለእግዚአብሔር ምሕረት ዮናስ የሰጠው ምላሽ (ዮናስ 4)፥  (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡) የመመዘኛ ጥያቄዎችን ለማግኘት ከታች ያለውን ሊንክ (መስፈንጠሪያ) ይጫኑ፡፡

ትንቢተ ዮናስ መግቢያ Read More »

የትንቢተ አብድዩ ዓላማ እና ዋና ዋና ትምሕርት

የትንቢተ አብድዩ ዓላማ ነቢያት በኤዶም ላይ ከተናገሯቸው በርካታ ትንቢቶች መካከል ትንቢተ አብድዩ አንደኛው ነው (ኢሳይያስ 21፡11-12፤ 34፡5-17፤ ኤርምያስ 49፡7-22፤ ሕዝቅኤል 25፡12-14፤ አሞጽ 1፡11-12)። ትንቢተ አብድዩ ሁለት ዐበይት ዓላማዎች አሉት፡- ሀ. የኤዶማውያንን ኃጢአት ማውገዝ ወይም መኮነን ነው። እነዚህ ኃጢአቶች ኤዶማውያን በጥበባቸውና የሚደርስባቸውን ጥቃት ለመቋቋም በመቻላቸው ትምክሕት ስላደረባቸው በአይሁድ ላይ መጨከናቸውና ኢየሩሳሌም በወደቀች ጊዜ በአይሁድ ላይ በደል መፈጸማቸው ነበሩ (አብድዩ 2-9)።  ለ. እግዚአብሔር በጌታ ቀን በክፉ ሕዝቦችና አገሮች ሁሉ ላይ ድል እንደሚነሣ ለአይሁድ ቅሬታዎች ለማስታወስ ነው (አብድዩ 17-21)።  የትንቢተ አብድዩ ዋና ትምህርት የውይይት ጥያቄ አብድዩ 15-16 አንብብ። በእነዚህ ቁጥሮች ውስጥ የሚገኘው መንፈሳዊ መመሪያ ምንድን ነው? ትንቢተ አብድዩ እግዚአብሔር ሕዝቦችና መንግሥታት የሚያደርጉትን ነገር ሁሉ እንደሚመለከትና እንደሚቆጣጠር ለድርጊታቸውም ሁሉ ተጠያቂ እንደሚያደርጋቸው የሚያስጠነቅቅ ነው። እግዚአብሔር በአሕዛብ ሁሉ ላይ በሉዓላዊነት ይገዛል። ጽድቅና ቅን ፍርድ የጎደለው ድርጊታቸውን ሁሉ ይመለከታል ያስታውሳቸዋልም። እግዚአብሔር ሰዎችንና መንግሥታትን ሁሉ ስለ ድርጊታቸው እንደሚቀጣቸው ይናገራል። እግዚአብሔር ሰዎችን ሲቀጣ ብዙውን ጊዜ የሚጠቀምበት መንገድ እነዚያ ሰዎች ሌሎችን ለመቅጣት የተጠቀሙበት መንገድ ከቅን ፍርድና ከጽድቅ የራቀ ነበር፡፡ ጨካኞች ከሆኑ ጭካኔ ይገጥማቸዋል። (አብድዩ 15-16፤ መዝሙር 7፡15-16፤ ምሳሌ 26፡27፥ ገላ. 6፡7-10 ተመልከት)። አሦር እስራኤልን እንደመታች ሁሉ እርስዋም በተራዋ በባቢሎን ተመታች።  አገሮች ወይም ሕዝቦች ቅን ፍርድን በማዛባት ጽድቅ የጎደለው ተግባር እየፈጸሙ ከፍርድ ያመለጡ ቢመስሉም፥ ክፉና ኃጢአተኛ የሆኑ ሰዎች በእግዚአብሔር ፊት በመቆም የኃጢአታቸውን ዋጋ የሚቀበሉበት የመጨረሻ የፍርድ ቀን ግን አለ። በክርስቶስ ደም እስካልተሸፈነ ድረስ ሳይቀጣ የሚቀር ኃጢአትና ክፉ ተግባር አይኖርም። በተቃራኒ ትንቢተ አብድዩ በአድልዎ ግፍ ለሚፈጸምባቸው ክርስቲያኖች ማበረታቻ ሊሆን ይገባል። አንድ ቀን እግዚአብሔር ክፉና ኃጢአተኞች ሰዎችን በመቅጣት አማኞችን ስለ ጽድቅ ሥራቸው እንደሚሸልማቸው ሊያስታውሱ ያስፈልጋል። እግዚአብሔር በሕዝቡ ላይ በጽድቅ ይገዛል። የውይይት ጥያቄ፥ የትንቢተ አብድዩን ዋና ትምህርት መረዳት አስፈላጊ የሚሆነው ለምንድን ነው? «በሌሎች ላይ ያደረግኸው በአንተም ላይ ይደረግብሃል። ድርጊትህ በራስህ ላይ ይመለስብሃል» የሚለው መንፈሳዊ መርሕ ሲሠራ ያየኸውና እውነት መሆኑን ያረጋገጥኸው እንዴት ነው?  የውይይት ጥያቄ፥ ትንቢተ አብድዩን አንብብ። ሀ) እግዚአብሔር ኤዶምን እንደሚቀጣ የወሰነባቸውን ምክንያቶች ዘርዝር። ለ) በኤዶም ላይ እንደሚፈጸሙ የተነገሩ የፍርድ ትንቢቶች ምን ነበሩ? ሐ) እግዚአብሔር ለሕዝቡ የገባው ተስፋ ምን ነበር? መ) ከዚህ መጽሐፍ የምንማራቸው ጠቃሚ መንፈሳዊ ትምህርተች ምንድን ናቸው? ኤዶማውያን ማንም ሊቋቋማቸው እንደማይችል በማሰብ የሚኩራሩ ትዕቢተኞች ነበሩ። ዋና ከተማቸው ጴጥራ ለጥቃትና ለሽንፈት ፈጽሞ በማትመችበት ሁኔታ ላይ ነበረች። ከተማይቱ በኮረብታዎች ግርጌ የተሠራች ስለነበረች፥ ጥቂት ሰዎች ሊከላከሉት በሚያመች ሁኔታ ላይ ነበረች። ኤዶማውያን በቁጥር ጥቂት ሕዝብ ቢሆኑም በጥንቱ ዓለም በጥበባቸው እጅግ ታዋቂ ሕዝብ ነበሩ። ይህም ወደ ትዕቢት መራቸው። እግዚአብሔር ትዕቢትን ስለሚጠላ ኤዶማውያንን እንደሚያዋርድ ተናገረ።  ኤዶማውያን ጨካኞችም ነበሩ። ከባቢሎናውያን ጋር በመተባበር ይሁዳን ከማጥቃታቸውም ሌላ፥ ከይሁዳ የተሰደዱ ሰዎች መጠጊያ ፍለጋ ወደ እነርሱ ሲሸሹ ይጨፈጭፏቸው ዘንድ ከባቢሎናውያን ጋር ተባበሩ። በኢየሩሳሌም መደምሰስ ታላቅ ደስታ ተሰማቸው። ይህ ሁሉ በአንድነት ተዳምሮ የእግዚአብሔርን ፍርድ አመጣባቸው። እግዚአብሔር በይሁዳ ላይ በፈጸሙት ዓይነት ወንጀል ፍርድ አመጣባቸው። በይሁዳ ላይ የፈጸሙትን በመሰለ ተመሳሳይ ጥፋት እግዚአብሔር እንደሚቀጣቸው ተናገረ። በጌታ ቀን፥ ፍርድ በኤዶም ብቻ ሳይሆን በአሕዛብ ሁሉ ላይ ይሆናል። እግዚአብሔር ግን የጽዮንን ተራራ ኢየሩሳሌምን በመታደግ በምርኮ ለነበሩት እስራኤላውያን በረከትን ያመጣል። በአንድ ወቅት የኤዶም የነበረውን ምድር ሳይቀር ይገዛሉ። የውይይት ጥያቄ፥ ለቤተ ክርስቲያንህ አባላት ልታስተምራቸው የምትችል መንፈሳዊ እውነቶችን ከትንቢተ አብድዩ ዘርዝር። (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡) የመመዘኛ ጥያቄዎችን ለማግኘት ከታች ያለውን ሊንክ (መስፈንጠሪያ) ይጫኑ፡፡

የትንቢተ አብድዩ ዓላማ እና ዋና ዋና ትምሕርት Read More »

ትንቢተ አብድዩ መግቢያ

ከብሉይ ኪዳን መጻሕፍት መካከል ትንሹ አብድዩ ነው። ትንቢተ አብድዩ አንድ ምዕራፍ ብቻ ያለው ሆኖ ስለ ኤዶምና ከእግዚአብሔር ዘንድ ስለሚመጣባት ፍርድ ይናገራል። በአሕዛብ መንግሥታት ላይ ከሚያተኩሩ ሦስት የትንቢት መጻሕፍት መካከል አንዱ አብድዩ ነው። አብድዩ በኤዶም ላይ ሲተነብይ፥ ዮናስና ናሆም ደግሞ በአብዛኛው በአሦር መንገሥት ላይ ተንብየዋል። የውይይት ጥያቄ፥ ስለ አብድዩ ከመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት አንብብ። ስለ መጽሐፉ ያገኘሃቸውን ዐበይት እውነቶችን ዘርዝር። የትንቢተ አብድዩ ጸሐፊ መጽሐፈ አብድዩ ከእግዚአብሔር የተቀበለውን ራእይ የያዘ መጽሐፍ ስለመሆኑ በትንቢተ አብድዩ መጀመሪያ ቁጥር ላይ ተጠቅሷል። በትንቢት መጻሕፍት ውስጥ ይህ «ራእይ» የተሰኘ ቃል መልእክቱ ከእግዚአብሔር ዘንድ በቀጥታ የመጣ መሆኑን ለመግለጽ የሚያገለግል ቃል ነው። ይህም ሲባል፥ መልእክቱ የተገኘው ሌሊት በታየ ሕልም ወይም ራእይ አማካይነት ብቻ መሆኑን ለመግለጽ የሚያገለግል ቃል አይደለም። ከስሙ በቀር ስለ አብድዩ የምናውቀው አንዳችም ነገር የለም። ኢየሩሳሌም በጠላቶችዋ ጥቃት በደረሰባት ጊዜ ኤዶም ላደረገችው ነገር ምላሽ የሚሰጥ በመሆኑ አብድዩ የኖረው በይሁዳ ሳይሆን አይቀርም። አብድዩ የሚለው ስም በጣም የተለመደ አይሁዳዊ ስም ቢሆንም፥ ይኸኛው አብድዩ ግን በመጽሐፈ ነገሥት፥ ዜና መዋዕል፥ ዕዝራና ህምያ የተጠቀሰው ሰው መሆኑ አጠራጣሪ ነው። ትንቢተ አብድዩ ስለ ተጻፈበት ጊዜ ምሁራን የተለያየ አሳብ ይሰነዝራሉ። መጽሐፉ ከ850-400 ዓ.ዓ. ባሉት ጊዜያት መካከል በየትኛውም ወቅት ተጽፎ ሊሆን ይችላል። ከእነዚህ መካከል የበለጠ ድጋፍ ያላቸው ሁለት ጊዜያት አሉ። እነርሱም፡-  ሀ. በኢዮራም ዘመነ መንግሥት (853-841 ዓ.ዓ.)፡- ኢየሩሳሌም በፍልስጥኤማውያንና በዐረቦች በተጠቃች ጊዜ ነበር (2ኛ ነገሥት 8፡20-22)። አብድዩ የኖረው በዚህ ጊዜ ከሆነ፥ መልእክቶቻቸው በመጻሕፍት ከተያዙ ነቢያት መካከል የመጀመሪያው ይሆናል። የኖረውም በኤልሳዕ ዘመን ሊሆን ይችላል ማለት ነው።  ለ. ባቢሎን በኢየሩሳሌም ላይ ጥቃት ባደረሰች ጊዜ (606-586 ዓ.ዓ.)፡- ይህ ከሆነ ደግሞ አብድዩ የኖረው በኤርምያስ ዘመን ነበር ማለት ይሆናል። አብድዩ የተጻፈበት ጊዜ ይህ ሳይሆን አይቀርም።  ታሪካዊ ሥረ- መሠረት የውይይት ጥያቄ፥ ስለ ኤዶም ከመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት አንብብ። ኤዶምና ይሁዳ ይህን ያህል ጠላትነት ለምን እንዳደረባቸው አብራራ። ትንቢተ አብድዩን ለመረዳት፥ የኤዶምንና የይሁዳን ልዩ ልዩ ታሪኮች መመልከት አለብን። ይስሐቅ ሁለት ልጆች እንደነበሩት ታስታውሳለህ። ትልቁ ዔሳው ትንሹ ደግሞ ያዕቆብ ይባሉ ነበር። ያዕቆብ በማታለል የብኩርናን በረከት ከአባቱ ሲያገኝ፥ ከዔሳው ዘንድ ደግሞ ጥላቻን አተረፈ። ይህ ጥላቻ ወደ ዔሳውና ያዕቆብ የልጅ ልጆች ሁሉ ተላለፈ። የዔሳው ዝርያዎች ኤዶማውያን ሲሆኑ፥ የያዕቆብ ዝርያዎች ደግሞ ምርጥ የእግዚአብሔር ሕዝብ የነበሩት እስራኤላውያን ሆኑ። እስራኤላውያን በእግዚአብሔር የተመረጠችውን የተስፋ ምድር ወረሱ። ኤዶማውያን ደግሞ ከእስራኤል በስተደቡብ በሚገኘው በረሃ ኖሩ። እስራኤላውያን እግዚአብሔር ከግብጽ ባርነት ነፃ አውጥቶአቸው ወደ ተስፋይቱ ምድር በሚጓዙበት ጊዘ በኤዶም ምድር ለማለፍ ፈለጉ። ኤዶማውያን ግን ሊያሳልፏቸው ፈቃደኞች ስላልነበሩ፥ እስራኤላውያን በርካታ የሆኑ ተጨማሪ ብዙ ኪሎ ሜትሮች መጓዝ ነበረባቸው (ዘኁልቁ 20፡14-21፤ 21፡14)። አይሁዳውያን ኤዶማውያን ያደረጉባቸውን ነገር ሊረሱ በጭራሽ አልቻሉም ነበር።  በኋላም በዳዊትና በሰሎሞን አመራር እስራኤላውያን ኤዶምን ወርረው በመያዝ ተቆጣጠሯት። ይህ የበላይነት ኤዶማውያን ዓምፀው ነፃነታቸውን እስካገኙበት (2ኛ ነገሥት 8፡20-22) እስከ ኢዮራም ዘመነ መንግሥት ድረስ ቀጠለ (853-841 ዓ.ዓ.)። የተለያዩ የይሁዳ ነገሥታት ኤዶምን ደግመው ለመያዝ ቢሞክሩም የተቈጣጠሩዋት ለጊዜው ብቻ ነበር። በ597 ዓ.ዓ. ባቢሎን ይሁዳን ተቆጣጠረች። በዚህ ጊዜ ኤዶማውያን መንግሥታቸውን በማስፋፋት ከይሁዳ ምድር የተወሰኑ ክፍሎችን ተቆጣጠሩ። ባቢሎን በ586 ዓ.ዓ. ይሁዳን በማጥቃት ስትደመስሳት፥ ኤዶማውያንም ከባቢሎን ጋር በማጥቃቱ ተባበሩ። አይሁድ ተማርከው ሲሄዱም ኤዶማውያን ከይሁዳ ምድር ተጨማሪ ግዛቶችን ያዙ። ይህም በትንቢተ አብድዩ ውስጥ የምናገኘው ጠንከር ያለ ትንቢት በኤዶም ላይ እንዲነገር አደረገ። አብድዩ የኤዶም አገር እንደገና ለማንሰራራት በማይችልበት ሁኔታ ፍጹም እንደሚደመሰስ ተነበየ። የኤዶም አገር በሚልክያስ ዘመን እንዴት ጨርሶ እንደጠፋና መንግሥቱም እንደተደመሰሰ መናገር አስቸጋሪ ነው። (በ450 ዓ.ዓ.) የተለያዩ የዐረብ ነገዶች ኤዶምን በተደጋጋሚ አጥቅተው ሳያጠፏት አልቀሩም። በ312 ዓ.ዓ. የናባቲያን ዐረቦች ኤዶምንና ዋና ከተማዋን ጴጥራን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጠሩ። የኤዶም ሰዎች በኋላ ኤዶማውያን ሆኑ። በአይሁድ ተሸነፉና የእነርሱን ወግ ለመከተል ተገደዱ። (በመሠረቱ ታላቁ ሄሮድስ የኤዶም ሰው ወይም ኤዶማዊ ነበር)። ኤዶማውያን በ70 ዓ.ም. በሮም ላይ በተደረገው ዓመፃ ከእስራኤላውያን ጋር በመተባበራቸው ሙሉ በሙሉ ተደመሰሱ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በታሪክ ስለ እነርሱ ተወስቶ አናገኝም። ዋና ከተማቸው ጴጥራ በ636 ዓ.ም. በሙስሊሞች ተደመሰሰች። እግዚአብሔር አስቀድሞ በአብድዩ በኩል እንደተናገረው፥ ዛሬ የኤዶም ሰዎች ወይም የኤዶም መንግሥት የለችም። የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ለመፈጸም ብዙ ምእተ ዓመት ሊወስዱ ቢችሉም፥ እግዚአብሔር የተናገራቸው የተስፋ ቃሉችና ትንቢቶች እንደሚፈጸሙ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) እግዚአብሔር ተስፋዎቹንና ትንቢቶቹን እንደሚፈጽም ከሚገልጸው እውነታ የምንመለከተው የእግዚአብሔር ባሕርይ ምንድነው? ለ) ይህ ባሕርይ መጽናኛ የሚሆነን ለምንድን ነው? የትንቢተ አብድዩ አስተዋጽኦ 1. በኤዶም ላይ የሚመጣ ፍርድ (አብድዩ 1-14)  2. የጌታ ቀን (አብድዩ 15-21) (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡) የመመዘኛ ጥያቄዎችን ለማግኘት ከታች ያለውን ሊንክ (መስፈንጠሪያ) ይጫኑ፡፡

ትንቢተ አብድዩ መግቢያ Read More »

የትንቢተ ኢዩኤል ዓላማ እና ዐበይት የሥነ መለኮት ትምሕርቶች

የትንቢተ ኢዩኤል ዓላማ ብዙ ጊዜ የነቢያት ዓላማ ወደፊት ስለሚሆኑ ነገሮች መተንበይ እንደሆነ እንገምታለን። ምንም እንኳ የብሉይ ኪዳን ነቢያት ስለ መጪው ጊዚያት የተነበዩ ቢሆኑም፥ የመልእክታቸው አብዛኛው ክፍል በዘመኑ የነበሩትን ሰዎች የሚመለከት ነበር። ነቢያት የእግዚአብሔር ሕዝብ በክፋታቸው ተጸጽተው ወደ እግዚአብሔር እንዲመለሱ የሚለምኑ የእግዚአብሔር ቃል አቀባዮች ነበሩ። ትንቢቶቹ የሚነገሩት ብዙውን ጊዜ የሕዝቡን አደራረግ ውጤቶች ለማመልከት ነበር። የትንቢት ዓላማ ስለ መጪው ጊዜ ብዙ እንድናውቅ ሳይሆን፥ እግዚአብሔር አሁንና ወደፊት በሚያደርጋቸው ነገሮች ምክንያት አሁን ያለውን ኑሮአችንንና አካሄዳችንን እንድንለውጥ ለማድረግ ነው። እግዚአብሔር ነቢዩ ኢዩኤልን ወደ ይሁዳ የላከው፥ ለእግዚአብሔር ባለመታዘዛቸው ምክንያት የሚደርሱባቸውን ነገሮች በመዘርዘር ሊያስጠነቅቃቸው ነበር። የአንበጣው መቅሠፍት እግዚአብሔር በእነርሱ ደስ አለመሰኘቱን የሚያሳይ ምልክት መሆኑን በመጥቀስ አስጠነቀቃቸው። በንስሐ ካልተመለሱ እግዚአብሔር በእነርሱ ላይ ታላቅ መቅሠፍት ለማምጣት፥ በንስሐ ከተመለሱ ግን እንደገና ምድራቸውን ለመባረክ ቃል ገብቶ ነበር። እንዲሁም ኢዩኤል የአንበጣውን መቅሠፍት ይሁዳን ለመውረር የሚመጣ የሌላ ጦር ኃይል ምልክት አድርጎ ተጠቅሞበታል። ይህ ጦር ስለ ባቢሎን ወይም ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ከመመለሱ ጥቂት ቀደም ብሉ ስለሚመጣ ሌላ ጦር የሚናገር ሊሆን ይችላል። በይሁዳ ላይ የሚመጣው ጦር የአንበጣ መንጋን ያህል እጅግ አጥፊና ብዙ ሊሆን ይችላል። እግዚአብሔር ግን ሕዝቡን በመታደግ፥ እነርሱ የማያውቁአቸውን በረከቶች ያመጣላቸዋል። መንፈስ ቅዱስ በሕዝብ ሁሉ ላይ ይወርዳል። ይህ የመጨረሻ ዘመን እግዚአብሔር ምድርን ከክፋት የሚያጠራበትና በአሕዛብ ሁሉ ላይ የሚፈርድበት ስለሆነ የታላቅ ጥፋት ቀንም ይሆናል። የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) እግዚአብሔር ንስሐ እንድንገባ እኛንና አገራችንን በሚያስጠነቅቀን ወቅት በሕይወታችንና በአገራችን ላይ የሚመጣውን የማስጠንቀቂያ ጥፋት መገንዘብ ጠቃሚ የሚሆነው ለምንድን ነው? ለ) ከርስቲያኖች ከፍተኛ ጥፋት የሚደርስበትንና ታላቅ በረከት የሚያመጣውን የመጨረሻውን ዘመን በንቃት መገንዘባችን ጠቃሚ የሚሆነው በምን መንገድ ነው? ሐ) ይህ ነገር በአኗኗራችን ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድረው እንዴት ነው? በትንቢተ ኢዩኤል ውስጥ የሚገኙ ዐበይት የሥነ-መለኮት ትምህርቶች 1) ክርስቲያን ስለተለያዩ አደጋዎች ያለው ግንዛቤ  ሰዎች የተለያዩ አደጋዎችን በሚመለከቱበት ጊዜ በአመዛኙ ምላሻቸው ከሚከተሉት ሦስት አሳቦች አንዱ ይሆናል፡- ሀ) በተለይ በምዕራቡ ዓለም እግዚአብሔር የተለያዩ አደጋዎችን በምንም ዓይነት እንደ ማይቆጣጠራቸው አድርጎ ማሰብ የተለመደ ነው። በሕዝቡ ላይ ያለምንም ዓላማ በድንገት የሚመጡ ነገሮች ስለሆኑ፥ እኛ ማድረግ የምንችለው ነገር ቢኖር እስኪያልፉ ድረስ መታገሥ ብቻ ነው ይላሉ።  ለ) ብዙ ክርስቲያኖች ወይም ሙስሊሞች የተፈጥሮ አደጋዎች በቀጥታ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደሚመጡ ያምናሉ። ነገር ግን እነዚህ ነገሮች የሚከሠቱት ያለምንም ዓላማ ነው የሚል እምነት አላቸው። እግዚአብሔር እነዚህ ሁኔታዎች እንዲከሠቱ የሚያደርግበትን ምክንያት ሰዎች ሊያውቁ እንደማይችሉ ይናገራሉ። ስለዚህ ማድረግ የምንችለው ነገር ቢኖር፥ እነዚህን ነገሮች እግዚአብሔር እንደሚያደርጋቸውና እኛም ምንም የምንለውጠው ነገር ስለሌለ አሜን ብሎ መቀበል ነው ይላሉ።  ሐ) እግዚአብሔር የራሱን ዓላማ ለመፈጸም በሕይወታችንና በአገራችን ላይ የሚደርሱትን ነገሮች ሁሉ እንደሚመራ መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምረናል። ዝናም፥ ፀሐይ፥ ሰብሎች ቁሳዊ ሀብትና የመሳሰሉት መልካም ነገሮች ሁሉ የሚመጡት ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው። ይሁን እንጂ አደጋዎች ወይም ችግሮች የሚመጡት በእርሱ ፈቃድ ነው። የሚመጡትም ያለ ዓላማ ሳይሆን፥ እግዚአብሔር በሚያውቀው ዓላማ ነው። የሁሉ ነገር ኃላፊ እግዚአብሔር ስለሆነ እርሱን ማሰብ ለእኛም ሆነ ለአገራችን እንደሚያስፈልገን ለማሳሰብና ለመርዳት ነው። ስለሚሰጠን በረከቶች እግዚአብሔርን ልናመሰግነውና በችግራችን ጊዜ ልናስበው ይገባናል። ችግሮች እግዚአብሔርን በማወቅና በመንፈሳዊ ባሕርይ እንድናድግ ሊረዱን የሚከሰቱ ናቸው። እግዚአብሔር አደጋ የሚያመጣባቸውን ምክንያቶች ሁሉ ለማወቅ ባንችልም፥ የሚመጡት በእግዚአብሔር ቁጣና ምሕረት የለሽ ፍርድ ሳይሆን፥ በእግዚአብሔር ፍቅርና ምሕረት ጭምር እንደሆነ እናውቃለን። የሚመጣውን በረከትና አደጋ የሚቆጣጠር እግዚአብሔር እንደሆነ ብናውቅም፥ የበረከትን ወይም የአደጋን መኖር እግዚአብሔር በአንድ ሰው ሕይወት ወይም በአንዲት አገር ላይ ፍቅሩ ወይም ፍርዱ እንዲገለጽ የሚጠቀምበት መሣሪያ እንደሆነ ለመወሰን እንዳንጠቀምበት ልንጠነቀቅ ይገባል። እጅግ ሀብታሞች የሆኑ ክፉና ኃጢአተኞች ሰዎች ወይም አገሮች ብዙ ናቸው። በመከራና በችግር ውስጥ የሚያልፉ ብዙ የእግዚአብሔር ሰዎች አሉ። በአንድ ሰው ወይም በአንድ አገር ሕዝብ ክፋት ወይም በጎነት ምክንያት መቅሠፍት ወይም በረከት ይደርሳል ብሎ መወሰኑ የእኛ ድርሻ አይደለም። የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) በእነዚህ ሦስት መንገዶች መቅሠፍት የደረሰባቸው ሰዎች ምን እንዳደረጉ የሚገልጽ ታሪክ በምሳሌነት ጥቀስ። ለ) በሕይወትህ ለገጠሙህ የተለያዩ ችግሮች ምላሽ የሰጠህባቸውን የተለያዩ መንገዶች ጥቀስ። ከእነዚህ ምላሾችህ መካከል ዕድገት ያስገኙልህ የትኞቹ ናቸው? ምንም ዕድገት ያላስገኙትስ? 2. የጌታ ቀን  የውይይት ጥያቄ፥ ኢዩኤል 1፡15፤ 2፡1-2፤ 3፡18 አንብብ። ሀ) የጌታን ቀን የተለያዩ ባሕርያት ግለጽ። ለ) ይህንን ቃል ከመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ውስጥ በመመልከት የጌታ ቀን ምን እንደሆነ የሚገልጽ አጠር ያለ አንቀጽ ጻፍ። የብሉይ ኪዳን ነቢያት በሰፊው ከተጠቀሙባቸው ሐረጎች አንቱ «የጌታ ቀን» የሚለው ነው። አይሁድ አንዳንድ ዐበይት ድርጊቶች የተፈጸሙባቸውን ጊዜያት «ቀን» በማለት ይጠሩአቸው ነበር። ነቢያት «የጌታ ቀን» ብለው የጠሯቸው ቀናት እግዚአብሔር በሰዎች ታሪክ ውስጥ ጣልቃ በመግባት ታላቅና ኃይለኛ ተግባር የፈጸመባቸው ማንኛዎቹም ቀናት ነበሩ። አንዳንድ ጊዜ እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ የፈረደባቸው ቀናት «የጌታ ቀን» ተብለዋል (ሰቆቃወ ኤርምያስ 2፡22)። በሌሉች ጊዜያት ደግሞ እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ ወደፊት የሚፈርድባቸው ጊዜያት «የጌታ ቀን» ተብለዋል (ኢዩኤል 2፡1-11)። እንደዚሁም ይህንን ሐረግ በዓለም ታሪክ መጨረሻ ገደማ የሚፈጸሙትን ታላላቅ ድርጊቶች ለመግለጥ ተጠቅመውባቸዋል። ነቢያት እግዚአብሔር ከዚህ ቀደም አድርጎት የማያውቀውን ነገር የሚያደርግበት ጊዜ እንደሚመጣ ነቢያት አመልክተዋል። አንዳንዴ ይህ ጊዜ የሚያመለክተው ክርስቶስ በመስቀል ላይ ለመሞት የመጣበትን ወቅት ነው። በሌላ ጊዜ ደግሞ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚነግሥበትን ዳግም ምጽአቱን ያመለክታል። ብዙውን ጊዜ እነዚህ ሁለት የክርስቶስ ምጽአቶች በግልጽ ሳይለዩ በአንድነት ተጠቅሰዋል። አንዳንድ ጊዜ ነቢያቱ የእስራኤል ሕዝብ ይለማመዱት የነበረውን ታሪካዊ ድርጊት በማየት፥ በመጨረሻው ዘመን የሚመጣውን ታላቁን የጌታ ቀን እንደሚያመለክት አድርገው ይጠቀሙበታል (ኢሳይያስ 13፡5-10)። ከጌታ ቀን ባሕርያት ውስጥ ጥቂቶቹ እንደሚከተለው ተዘርዝረዋል፡- ሀ. የጌታ ቀን በጨለማ፥ ደብዘዝ ባለ ብርሃንና በፍርድ ባሕርዩ ይታወቃል። (ኢሳይያስ 13፡9-10፤ ማቴዎስ 24፡29)።  ለ. የጌታ ቀን እንደ መሬት መንቀጥቀጥና ረሀብ ባሉ የተፈጥሮ አደጋዎች ይሞላል።  ሐ. የጌታ ቀን የጦርነት ጊዜ ይሆናል፥ ሕዝብ በሕዝብ ላይ፥ በተለይም በእስራኤል ሕዝብ ላይ በመነሣቱ ይታወቃል፡፡  መ. የጌታ ቀን እግዚአብሔር በአሕዛብ ሁሉ ላይ የሚፈርድበት ቀን ይሆናል (ኢዩኤል 3፡19)።  ሠ. የጌታ ቀን የእስራኤል ሕዝብ በብዛት ወደ እግዚአብሔር የሚመለሱበት ቀን ነው። እነዚህ ቅሬታዎች ከእግዚአብሔር ከፍተኛ በረከትን ያገኛሉ (ኢዩኤል 2፡32፤ አሞጽ 9፡11-15)።  ረ. የጌታ ቀን ከዚህ በፊት በጭራሽ ተደርጎ በማያውቅ አኳኋን የእግዚአብሔር መንፈስ በእያንዳንዱ ሰው ሕይወት ውስጥ የሚሠራበት ጊዜ ይሆናል፤ (ኢዩኤል 2፡28)።  ሰ. የጌታ ቀን ምድር በቃል ሊገለጽ የማይችል ታላቅ በረከትና ብልጽግና የምትለማመድበት ጊዜ ይሆናል (ኢዩኤል 3፡18)።  ሸ. የጌታ ቀን ምድር በእሳት ፍርድ የምትጠራበት ጊዜ ይሆናል (2ኛ ጴጥሮስ 3፡10-13)።  ቀ. የጌታ ቀን ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚገለጥበት ጊዜ ይሆናል (1ኛ ቆሮንቶስ 1፡8) የውይይት ጥያቄ፥ ስለ ጌታ ቀን የተሰጠው ትምህርት ታላቅ ማስጠንቀቂያና ክርስቲያኖች በከፍተኛ ሁኔታ የሚጠብቁት ጊዜ የሚሆነው እንዴት ነው?  የውይይት ጥያቄ፥ ኢዩኤል 1-3 አንብብ። ሀ) ኢዩኤል በእስራኤል ሕዝብ ላይ ፈጥኖ እንደሚደርስ የተናገረው ትንቢት ምን ነበር? ለ) ኢዩኤል ንስሐ እንዲገባ የሚያስጠነቅቀው ማንን ነበር? ሐ) ሕዝቡ ንስሐ ከገቡ በኋላ ተስፋ የተሰጣቸው በረከቶች ምን ነበሩ? መ) ለአይሁድ ስለ መጨረሻው ዘመን የተሰጡ የበረከት ተስፋዎች ምንድን ናቸው? 1. ኢዩኤል የጌታን ቀን በአንበጣ መቅሠፍት ተመለከተ (ኢዩኤል ) ትንቢተ ኢዩኤል፥ የእስራኤልን ምድር ሰብል ሙሉ በሙሉ ስላጠፋውና የይሁዳን ሕዝብ ሁሉ ችግር ላይ ስለጣለው የአንበጣ መቅሠፍት በማስረዳት ይጀምራል። ኢዩኤል ይህ የእግዚአብሔር ፍርድ መሆኑን በመገንዘብ፥ ሕዝቡ ሁሉ ንስሐ እንዲገቡ ይጋብዛል።  2. ኢዩኤል ስለሚመጣው የጌታ ቀን ተነበየ (ኢዩኤል 2፡3) የትንቢተ ኢዩኤል የመጨረሻ ግማሽ ክፍል ወደፊት ከረጅም ጊዜ በኋላ ስለሚሆነው ስለ ሌላ የጌታ ቀን ወደ መናገር ይመለሳል። በዚህ የትንቢተ ኢዩኤል ክፍል «ጣምራ ትንቢት»ን የሚያመለከቱ በርካታ መግለጫዎችን እናያለን። ይህም ሲባል እግዚአብሔር አንድን ትንቢት

የትንቢተ ኢዩኤል ዓላማ እና ዐበይት የሥነ መለኮት ትምሕርቶች Read More »

ትንቢተ ኢዩኤል መግቢያ

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ከዚህ ቀደም ያጋጠሙህን ጥፋቶች ወይም አስቸጋሪ ሁኔታዎች ዘርዝር። ለ) ከእነርሱ ምን ተማርህ? ሐ) በኢትዮጵያ ውስጥ ከዚህ በፊት የደረሱትን ጥፋቶች ዘርዝር። መ) ከእነዚህ ጥፋቶች ሰዎች መማር ያለባቸው ትምህርቶች ምንድን ናቸው? መጽሐፍ ቅዱስ፥ እግዚአብሔር በሕይወታችን የሚደርሱትን ክፉና በጎ ነገሮች ሁሉ እንደሚቆጣጠር ያስተምራል። እንደ ፀሐይና ዝናብ ያሉ በረከቶች የሚመጡት ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው (ማቴዎስ 5፡44-45)። ደግሞም እግዚአብሔር ወደ ሕይወታችን የሚመጡትን አደጋዎች ሁሉ ይቆጣጠራል (ኢሳያይስ 45፡5-8 ተመልከት)። እኛ ወይም ከቤተሰቦቻችን አንዱ ሲታመም የምንወዳቸው በሞት ሲለዩን በአገራችን ድርቅ ሲኖር፥ እነዚህ ሁሉ እግዚአብሔር ለእኛ ካለው ፍቅር የተነሣ ሊመጡ ይችላሉ። እግዚአብሔር አደጋዎችን በተለያዩ መንገዶች በመጠቀም በሕይወታችን ምሕረቱን ያሳየናል። አደጋ እግዚአብሔር በኃጢአት ላይ እንደሚፈርድ በማሳየት የከፋ ፍርድ ከመምጣቱ በፊት ወደ እርሱ በንስሐ እንድንመለስ የሚጋብዝ ሊሆን ይችላል። ብዙ ጊዜ ሰዎች ራሳቸውን እንዲመረምሩና ለእግዚአብሔር በመታዘዝ ይሄዱ እንደሆነ በማረጋገጥ ወደ ንስሐ እንዲመጡ ለማድረግ የሚያስጠነቅቅ ነው። አንዳንድ ጊዜ አደጋ እግዚአብሔር በእምነታችን ሊያጠነክረን ማለትም ጽናትን፥ ራስ መግዛትንና ሌሎችንም ጠቃሚ የሕይወት ብቃቶች መፈለጉን የሚያሳይ ምልክት ሊሆን ይችላል (ያዕቆብ 1፡2-4)። በኢዩኤል ዘመን እግዚአብሔር ታላቅ የአንበጣ መንጋ መቅሠፍት በእስራኤል ላይ አፈሰሰ። የምድሪቱ ሰብል ጠፋ። እንስሳት የሚግጡትን ሣር አጡ። ኢዩኤል ይህ የእግዚአብሔር ፍርድ መሆኑን ያውቅ ነበር። ስለዚህ የእግዚአብሔር ሕዝብ በንስሐ በመመለስ፥ በመታዘዝና በመቀደስ እንዲኖሩ ይለምናል። ችግሮችና አደጋዎች በሕይወታችን በሚከሰቱበት ጊዜ የእግዚአብሔር ዓላማ ምን እንደሆነ ለመረዳት ትልቅ ጥበብና የመንፈስ ቅዱስ ምሪት ያስፈልገናል። ይህ የሚሆነው ለግል መንፈሳዊ ዕድገት ኃጢአትን ለመቅጣት ይሁን ወይም በእግዚአብሔር ላይ እንድንደገፍ ሊያስታውሰን በመፈለጉ፥ የምናውቀው እኛ ብቻ ነን። ሌሎች ሰዎች መከራን የሚቀበሉት ለምን እንደሆነ ከመፍረድ መጠንቀቅ አለብን። የእግዚአብሔር ዓላማ የተለያየ ስለሆነ፥ በሌሎች ላይ የምንፈርድ ወይም የመንፈስ ቅዱስን የመውቀስ ሥራ የምንሻማ መሆን የለብንም። ትንቢተ ኢዩኤል ለይሁዳ ከተጻፉ ሦስት አነስተኛ የነቢያት መጻሕፍት አንዱ ነው። ሚክያስና ሶፎንያስ ሁለቱም ለይሁዳ ሕዝብ የተጻፉ ነበሩ።  የትንቢተ ኢዩኤል ጸሐፊ በኢዩኡል 1፡1፥ «ወደ ባቱኤል ልጅ ወደ ኢዩኡል የመጣው ቃል ይህ ነው» ተብሉ በተገለጸው ቃል መሠረት ጸሐፊው ኢዩኤል እንደሆነ ይገመታል። ከዚህ ሌላ ስለ ኢዩኤል ማወቅ አስቸጋሪ ነው። ኢዩኤል በብሉይ ኪዳን ውስጥ የተለመደ ስም ነበር። ቢሆንም በሌሎች ስፍራዎች የምናገኘው ይህ ስም የዚህ መጽሐፍ ጸሐፊ አይመስልም። ኢዩኤል የትና መቼ እንደተወለደና እንደኖረ አናውቅም። አብዛኞቹ ሊቃውንት ኢዩኤል በተደጋጋሚ የሚጠቅሰው ይሁዳንና ኢየሩሳሌምን ስለሆጎ (ኢዩኡል 2፡32፤ 3፡1፥6፥8) ከደቡብ፥ መንግሥት ከይሁዳ ነገድ ሳይሆን እንደማይቀር ይናገራሉ። ትንቢተ ኢዩኤል ከሌሎች የትንቢት መጻሕፍት በተለየ ሁኔታ ኢዩኤል ማገልገሉን አይገልጽም። የይሁዳም ሆነ የእስራኤል ንጉሥ አልተጠቀሱም። የተጠቀሱት ነገሥታት ሳይሆኑ ካህናት ብቻ ነበሩ። ስለዚህ መጽሐፉ የተጻፈው ብቁ የሆነ ንጉሥ ባልነበረበት ጊዜ ይመስላል። ትንቢተ ኢዩኤል መቼ እንደተጻፈ በርግጠኝነት ለመናገር የሚቻልበት መንገድ ጨርሶ የለም። ትንቢተ ኢዩኤል ስለተጻፈበት ጊዜ ምሁራን ሁለት አሳብ አላቸው፡-  1. ትንቢተ ኢዩኤል የተጻፈው ከ 835-830 ዓ.ዓ. ባለው ጊዜ ነበር። በዚህ ጊዜ የዳዊት ንጉሣዊ የዘር ግንድ በክፉዋ ንግሥት በጎቶልያ አማካይነት ጨርሶ ሊጠፋ ደርሶ ነበር። ኢዮአስ ብቻ ተርፎ ነበር። ኢዮአስ የሰባት ዓመት ልጅ በሆነ ጊዜ በዙፋን ላይ ተቀመጠ። ኢዮአስ ንጉሥ ቢሆንም እንኳ ራሱን ችሎ እስኪያስተዳድር ድረስ አገሪቱ በካህናት ትመራ ነበር። እነዚህ ምሁራን ትንቢተ ኢዩኤል የተጻፈው በዚህ ጊዜ ነው ብለው የሚያምኑባቸው ምክንያቶች የሚከተሉት ናቸው፡- ሀ. አይሁድ ትንቢተ ኢዩኤልን ከታናናሽ ነቢያት መጻሕፍት መጀመሪያ አካባቢ ማድረጋቸው ልክ እንደ ትንቢተ ሆሴዕ ከምርኮ በፊት አንደተጻፈ ያምኑ እንደነበር የሚያሳይ ነው።  ለ. የአሦር ወይም የባቢሎን ስም አለመጠቀሱ፥ ታሪኩ ከእነዚህ ሁለት ታላላቅ መንግሥታት በፊት መፈጸሙን የሚያሳይ ነው።  ሐ. ኢዩኤል «የጌታ ቀን» የሚለውን ሐረግ የሚጠቀመው ከምርኮ በፊት ከተጻፉ መጻሐፍት ጋር በሚመሳሰል መንገድ ነው። ይህ አመላካከት እውነት ከሆነ፥ ትንቢተ ኢዩኤል ከመጽሐፍ ቅዱስ የትንቢት መጻሕፍት ሁሉ ቀዳሚ ይሆናል።  2. ሌሎች ምሁራን ደግሞ ትንቢተ ኢዩኤል የተጻፈው አይሁድ ተማርከው ከሄዱና ምርኮው ተፈጽሞ ወደ አገራቸው ከተመለሱ በኋላ ነው ብለው ያምናሉ። ከትንቢተ ሐጌና ዘካርያስ በኋላ ቢሆንም፥ ነገር ግን ከትንቢተ ሚልክያስ በፊት ተጽፏል የሚል አስተሳሰብ አላቸው። ትንቢተ ኢዩኤል የተጻፈበት ጊዜ ከ525-475 ዓ.ዓ. ነው ብለው ይገምታሉ። ይህም በጊዜ ቅደም ተከተል፥ ትንቢተ ኢዩኤልን ከብሉይ ኪዳን የትንቢት መጻሕፍት መካከል ከመጨረሻው መጽሐፍ ብቻ ቀዳሚ ያደርገዋል። ትንቢተ ኢዩኤል በዚህ ጊዜ እንደተጻፈ የሚያምኑ ምሁራን የሚከተሉትን ምክንያቶች ያቀርባሉ፡- ሀ. በትንቢተ ኢዩኤል 3፡1-2 የተጠቀሰው አሳብ፥ የእግዚአብሔር ሕዝብ መበተን ያለፈ ጉዳይ እንጂ ገና የሚመጣ መሆኑን የሚያመለክት አይመስልም።  ለ. ከምርኮ በፊት እጅግ ተደጋግሞ ይታይ የነበረው፥ ከምርኮ በኋላ ግን ያልተከሰተው የጣዖት አምልኮ ኃጢአት አልተጠቀሰም። ሐ. ከምርኮ በፊት በመካከለኛው ምሥራቅ ጨርሶ የማይታወቁ የነበሩት ግሪኮች ተጠቅሰዋል።  መ. የኢዩኤል አጻጻፍ ስልት ከኢየሩሳሌም ውድቀት በኋላ የተጻፉትን የታናናሽ ነቢያት መጻሕፍት እንጂ፥ የመጀመሪያዎቹን የነቢያት መጻሕፍት አይመስልም።  ሁለቱም አመለካከቶች የየራሳቸው የሆኑ ጠንካራ ጎኖች አሏቸው። እርግጥ ኢዩኤል ቀደም ሲል እንደተጻፈ የሚናገረው አመለካከት የተሻለ ቢመስልም፥ መቼ እንደተጻፈ አናውቅም ማለቱ ግን ከሁሉም የሚሻል ነው። ትንቢተ ኢዩኤል መቼ እንደተጻፈ አለማወቃችን ስለ መጽሐፉ የሚኖረንን ግንዛቤ ብዙ አይለውጠውም።  ታሪካዊ ሥረ መሠረት ትንቢተ ኢዩኤል የተጻፈበትን ጊዜ ስለማናውቅ ስለ መጽሐፉ ታሪካዊ ሥረ-መሠረት እርግጠኞች ለመሆን አንችልም። ስለዚህ መጽሐፉን በሚገባ ለመረዳት ሁለቱን የታሪክ ቅደም ተከተሎች መገንዘብ ጠቃሚ ነው።  1. የኢዮአስ ዘመነ መንግሥት (835-796 ዓ.ዓ.)  የውይይት ጥያቄ፥ የዚህን ጊዜ ታሪክ ለመረዳት 2ኛ ነገሥት 11 አንብብ። ሀ) የዳዊት የዘር ግንድ ምን ሊሆን ተቃርቦ ነበር? ለ) ንጉሥ ኢዮአስን ያሳደገው ማን ነው? ሐ) ንግሥት ጎቶልያ ምን ዓይነት ሴት ነበረች? ንጉሥ ኢዮራም ሲሞት ልጁ አካዝያስ ነገሠ። ይህ ሰው በእስራኤል ንጉሥ በኢዩ ከመገደሉ በፊት በሥልጣን ላይ የቆየው ለአንድ ዓመት ብቻ ነበር። ይህንን ሥልጣን ለመጨበጥ የደረሰ ሌላ ልጅ ስላልነበረ የኢዮራም ሚስት ጎቶልያ ዙፋኑን ያዘች። ዙፋኑን የሚወርስ ሌላ ሰው እንዳይኖር ወዲያውኑ የዳዊትን ዝርያዎች በሙሉ ለመግደል ሞከረች። ካህናቱ ኢዮአስ የተባለውን ሕፃን ብቻ አድነው ሰባት ዓመት እስኪሞላው ድረስ በቤተ መቅደስ ውስጥ ደብቀው አሳደጉት። ከዚህ በኋላ በሊቀ ካህኑ በዮዳሄ መሪነት ንግሥት ጎቶልያን ከሥልጣንዋ የማስወገድ ተግባር ተከናወነ። ዮዳሄ በሕይወት እስካለ ድረስ የይሁዳ ዋና የፖለቲካ መሪ ሆኖ አገለገለ። ዮዳሄ በኢዮአስ በመጠቀም መንፈሳዊ መነቃቃት ለማምጣት ቻለ። ዮዳሄ እንደሞተ ግን ኢዮአስ ከጌታ ፊቱን መለሰ። ዮዳሄ ከዙፋኑ በስተኋላ የነበረውን ሥልጣን በሚገባ የተጠቀመበት በንግሥት ጎቶልያ ሞትና በንጉሥ ኢዮአስ መንገሥ መካከል በነበረው ጊዜ ነበር። እግዚአብሔር ነቢዩ ኢዩኤልን በማስነሣት ቃሉን እንዲናገር ያደረገውም በዚህ ጊዜ ነበር። ኢዩኤል ምድሪቱን የመታትን የአንበጣ መቅሠፍት በምሳሌነት በመጠቀም፥ እንደ አንበጣ ምድሪቱን የሚያጠፋ በሰዎች የተገነባ ሌላ የጦር ኃይል እንደሚመጣ ተናገረ።  2. ከምርኮው በኋላ የነበሩት ጊዜያት (500 ዓ.ዓ. ገደማ) የውይይት ጥያቄ፥ ስለ መጽሐፈ ዕዝራ ከመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት አንብብ። በዕዝራ ዘመን የፖለቲካ ሁኔታ ምን ይመስል ነበር? መጽሐፉ የተጻፈው ዕዝራ በነበረበት ዘመን ገደማ ከሆነ የፖለቲካ ሁኔታው የተለየ ነበር ማለት ነው። በይሁዳ ከነበሩት ምርኮኞች አብዛኛዎቹ ወደ ይሁዳ ለመመለስ ሳይሆን በባቢሎን ለመቆየት የመረጡ ቢሆኑም፥ በዘሩባቤል፥ በዕዝራና በነህምያ መሪነት አንዳንድ አይሁዳውያን ተመልሰዋል። በላያቸው የነገሠ ንጉሥ አልነበረም። ይልቁንም በሜዶንና በፋርስ መንግሥት ቁጥጥር ሥር ስለነበሩ በሕዝቡ ላይ የተሾሙ ገዥዎች ነበሩ። እንደ እውነቱ ከሆነ ሕዝቡን የሚመሩት እንደ ዕዝራ ያሉ ካህናት ነበሩ። እነዚህ ካህናት መንፈሳዊ አመራር መስጠት ብቻ ሳይሆን የፖለቲካ መሪዎችም ሆኑ። ይህም የካህናቱን ሕይወት በማበላሸቱ፥ ከአመራር ስለሚያገኙት ሥጋዊ ጥቅም እንጂ፥ ስለ ሕዝቡ መንፈሳዊ ሕይወት የማይገዳቸው ሆኑ። ሕዝቡ በቃላቸው እግዚአብሔርን እንከተላለን እያሉ ቢናገሩም፥ የቅድስና ሕይወት የማይኖሩና የእግዚአብሔርን ሕግጋት በመታዘዝ የማይራመዱ ነበሩ። ኢዩኤል ነቢይ የነበረው በዚህ ዘመን ከሆነ፥ የተጠራው ወደ ምድራቸው የተመለሱት አይሁድ እግዚአብሔርን እንዳይተው፥ ነገር ግን

ትንቢተ ኢዩኤል መግቢያ Read More »

ሚክያስ 1-7

የውይይት ጥያቄ፥ ሚክያስ 1-7 አንብብ። ሀ) ሚክያስ ሕዝቡን የከሰሰባቸውን ኃጢአቶች ዘርዝር። ለ) እግዚአብሔር በሕዝቡ ላይ ምን ዓይነት ፍርድ እንደሚያመጣ ተናገረ? ሐ) ዛሬ ሊያጽናኑን የሚችሉትንና ወደ ፊት ስለሚመጣው ንጉሥና መንግሥት የተነገሩትን ትንቢቶች ዘርዝር። እግዚአብሔር ጻድቅና ቅዱስ አምላክ ነው። ስለዚህ ኃጢአትን በተለይም ደግሞ በሕዝቡ መካከል ያለውን ኃጢአት መቅጣት አለበት፤ ይቀጣልም። ብዙ ጊዜ ሰይጣን ሕዝቡን እግዚአብሔር የሚገደው ለመሥዋዕት ሥነ-ሥርዓት፥ ለአምልኮ ጸሎት፥ ለመዝሙር፥ ለስብከትና ለመሳሰሉት ነው በማለት ያስታቸዋል። በዚህ ምክንያት እነርሱ ይህንን እስካደረጉ ድረስ፥ እግዚአብሔር ደስ የሚሰኝና የሚባርካቸው ይመስላቸዋል። ነገር ግን እነዚህ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች በቀላሉ ባዶና ምንም ዋጋ የሌላቸው ሊሆኑ ይችላሉ። በእግዚአብሔር ሕዝብ መካከል ኃጢአት፥ መለያየት፥ የሥነ-ምግባር ድቀት፥ ጠብ፥ ጥላቻ ቅንዓትና ትዕቢት ወይም ሌላ ዓይነት ኃጢአት ካለ እግዚአብሔር በሕዝቡ ደስ አይሰኝም፡፡ እግዚአብሔር በሕዝቡ ሕይወት ችግር እንዲመጣ ያደርጋል። ሕዝቡን ወደ ራሱ ለመመለስ የስደት ሞት ሳይቀር ሊያመጣ ይችላል። ከሥርዓተ አምልኮ በላቀ ሁኔታ እግዚአብሔር በሁሉም ሕይወታችን ክፍል አግባብ ባለው መንገድ እንድንመላለስ ይፈልጋል። ሕይወታችን ሙሉ በሙሉ ለእግዚአብሔር በምንሰጥበትና ለእርሱ በምንታዘዝበት ጊዜ፥ አምልኮአችን ሁሉ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ይሆንና እርሱም ክብሩንና ኃይሉን ያሳየናል። የውይይት ጥያቄ ሀ) ብዙ ክርስቲያኖች እግዚአብሔር በእሑድ የእርሱን በሚያመልኩበት ጊዜ በሚያደርጉት ድርጊት ብቻ ሳይሆን፥ በአጠቃላይ ስለ ሕይወታቸው የሚገደው መሆኑን የሚዘነጉት ለምንድን ነው? አንተም ሆንህ ቤተ ክርስቲያንህ እነዚህን እውነቶች ማስታወሳችሁ አስፈላጊ የሚሆነው ለምንድን ነው? 1. ሚክያስ በሰማርያና በኢየሩሳሌም ላይ የተናገራቸው ትንቢቶች (ሚክያስ 1) ጻድቅ የሆነው አስፈሪው ዳኛ እግዚአብሔር በሕዝቡ ላይ ለመፍረድ ከሰማይ ሲወርድ ይታያል። ሰማርያና ኢየሩሳሌም ስለ ኃጢአታቸው ተጠያቂዎች ናቸው። ሰማርያ ፈጽማ ልትጠፋ፥ ኢየሩሳሌምም ልትቀጣ ነበር። ስለዚህም፥ ሚክያስ ይህን ትንቢት በተቀበለ ጊዜ በኃዘን ተሞልቶ ነበር። አንድ ወዳጁ ወይም አፍቃሪው የሞተበት ሰው በሚያዝንበት መንገድ ያለቅስና በባዶ እግሩ ዕርቃኑን ይመላለስ ነበር።  2. ሚክያስ በይሁዳ መሪዎች ላይ የተናገራቸው ትንቢቶች (ሚክያስ 2-3)  እግዚአብሔር በይሁዳ ላይ ለመፍረድ የተነሣው ለምን ነበር? በእግዚአብሔር ሕዝብ መካከል በነበረው ኃጢአትና የፍትሕ መዛባት ምክንያት ነበር። ሀብታሞች፣ ጎረቤቶቻቸውንና ድሆችን በማታለል ገንዘባቸውን ይቀሙአቸው ነበር። ሕዝቡ ኃጢአታቸውን ተገንዝበው በንስሐ እንዳይመለሱ የሐሰት ማጽናኛ ቃሎችን ይተነብዩ ነበር። የሚያገለግሉት የእግዚአብሔርን ቃል ለሕዝቡ በማስተማር፣ ሕዝቡ ንስሐ ሲገቡ ለማየት በመናፈቅ ሳይሆን፥ ለገንዘብ ሲሉ ነበር። መሪዎቹ ጉቦ በመቀበልና ኃይላቸውን ያለ አግባብ በመጠቀም ሀብትን ይሰበሰቡ፥ ለድሆች የሚገባውንም ነገር ይነጥቁ ነበር። ሰዎች እነዚህን መሰሎቹ ድርጊቶች በእግዚአብሔር ፊት መልካም እንደሆኑ ቢያስቡም የእግዚአብሔር ፍርድ ግን በደጅ ነበር።  3. ሚክያስ ስለ ጽዮን መመለስ የተናገረው ትንቢት (ሚክያስ 4-5) በይሁዳ መንግሥት ከነበረው ክፋት ጋር ሲነጻጸር በመጨረሻው ዘመን በእግዚአብሔር የሚመሠረት ሌላ መንግሥት እንደሚመጣ ተናገረ። እርሱና የእግዚአብሔር ጻድቅ ሕዝብ የሆነው ቅሬታ የዚህ መንግሥት አካል ይሆናሉ። የእግዚአብሔር ሕዝብ በተለወጠ ልብ እግዚአብሔርን ያመልካሉ። ጦርነትና ክፋት ይወገዳል። ሰዎች በሰላም ይኖራሉ። አሕዛብ ሳይቀሩ እግዚአብሔርን ያመልካሉ። እግዚአብሔር በይሁዳ ሕዝብ ላይ የሚፈርድ ቢሆንም እንኳ አንድ ቀን እንደ ዳዊት ያለ የእግዚአብሔርን ሕዝብ የሚመራ ንጉሥ እንደሚመጣ ተናገረ። በእግዚአብሔር ኃይልና ብርታት ይመጣል፤ ዳሩ ግን ለእግዚአብሔር ሕዝብ ርኅሩኅ እረኛ ይሆናል።  4. ሚክያስ ስለ ይሁዳ ክፋትና ስለሚመጣባት ፍርድ የተናገረው ትንቢት (ሚክያስ 6-7፡6)  እግዚአብሔር ተራሮችንና ኮረብቶችን በምስክርነት በመጥራት በይሁዳ ላይ ክሱን ያቀርባል። እግዚአብሔር ለእነርሱ በቸርነት የተገለጠ ቢሆንም፥ አይሁድ ግን ያለማቋረጥ በእግዚአብሔር ላይ ዓመፁ። የእግዚአብሔርን ሕግጋት ባሕርያት ሊለውጡ በማይችሉ ውጫዊ የሃይማኖት ሥርዓቶች ለወጡ። የጣዖት አምልኮን ለእግዚአብሔር ከሚቀርብ አምልኮ ጋር ቀላቀሉ። ክፋትን በመቃወም የሚናገሩ መልካም ሰዎች እየተገደሉ ከምድሪቱ ይወገዱ ጀመር። ስለዚህ የእግዚአብሔር ፍርድ በእነርሱ ላይ ይመጣል። ፍርድ እንደሚመጣ የተረጋገጠ ነው። ፍርዱ በሚፈጸምበት ጊዜ ታማኝ የሆኑት የእግዚአብሔር ሕዝቦች «እኔ ግን ወደ እግዚአብሔር እመለከታለሁ፥ የመድኃኒቴንም አምላክ ተስፋ አደርጋለሁ፥ አምላኬም ይሰማኛል» (ሚክያስ 7፡7) የሚል ምላሽ ይሰጣሉ።  5. የእስራኤል ቅሬታዎች በወደፊቱ የእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ ስለሚቀበሉት ይቅርታ ሚክያስ የተናገራቸው ትንቢቶች (ሚክያስ 7፡7-20)  ይሁዳ በእግዚአብሔር ፍርድ ምክንያት የሚደርስባት ጥፋት ዘላለማዊ አልነበረም። አንድ ቀን እንደገና በምሕረቱ ሊጎበኛት እግዚአብሔር ቀን ቀጥሮ ነበር። እግዚአብሔር ለሕዝቡ የሚሠራውን ሥራ የምድር አሕዛብ በመደነቅና በአክብሮት ይመለከቱታል። ኢየሩሳሌም እንደገና ትሠራለች። እውነተኛ ይቅርታና ተሐድሶም ይሆናል። ሚክያስ ስለዚህ ነገር እርግጠኛ የሆነው ለምን ነበር? እግዚአብሔር ከአብርሃም ጋር ቃል ኪዳን ስላደረገና ለቃል ኪዳኑም ታማኝ ስለሆነ ነው። የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ከትንቢተ ሚክያስ የተማርካቸውን አንዳንድ መንፈሳዊ ትምህርቶች ዘርዝር። ለ) እነዚህን ትምህርቶች በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ ለሚገኙ የተወሰኑ ቡድኖች ለማስተማር ዐቅድ። (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡) የመመዘኛ ጥያቄዎችን ለማግኘት ከታች ያለውን ሊንክ (መስፈንጠሪያ) ይጫኑ፡፡

ሚክያስ 1-7 Read More »

የትንቢተ ሚክያስ ዓላማ እና ዋና ዋና ትምሕርቶች

የትንቢተ ሚክያስ ዓላማ እግዚአብሔር ስለ ኃጢአታቸውና ንስሐ መግባት እንደሚያስፈልጋቸው በመናገር ይሁዳን እንዲያስጠነቅቅ ሚክያስን ላከው። ሕዝቡ እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር የገባውን ቃል ኪዳን በመተዋቸው በይሁዳ ላይ ስለሚመጣው ቅጣት ተናገረ፡፡ ምንም እንኳ ውጫዊ በሆነው ሥርዓት እግዚአብሔርን ሊያመልኩ ቢችሉም ሕይወታቸው ግን እግዚአብሔርን በመፍራት የሚመራ አልነበረም። ይህም በተለይ ግልጽ ሆኖ የታየው እርስ በርስ በነበራቸው ግንኙነት ውስጥ ነበር። ሀብታሞች ድሆችን ይጨቁኑ ነበር፤ ስለዚህ የእግዚአብሔር ፍርድ በሀብታሞችና በሕዝቡ ሁሉ ላይ ይከሰታል። የእግዚአብሔር ፍርድ ታማኝ ባልሆነችው ይሁዳ ላይ የሚመጣ ቢሆንም፥ እግዚአብሔር ግን ሕዝቡን ሙሉ በሉ አያጠፉም። እግዚአብሔር ለአብርሃምና ለዳዊት የገባውን ቃል ኪዳን ይፈጽል። አንድ ቀን እግዚአብሐር እርሱ በሚፈልገው መንገድ በጽድቅ የሚገዛ ሰው ከዳዊት ዘር ያስነሣል። ይህ ንጉሥ በእግዚአብሔር ሕዝብ ልብ ውስጥ አንዳችም ክፋት የማይኖርበትንና ሕዘቡ ከእውነት ጨርሶ የማይርቁበትን አዲስ ዘመን ያመጣል። ጦርነት ተሽሮ ሰዎች ሁሉ በእውነተኛ ሰላም ይኖራሉ። እስከ ዛሬ ድረስ በፍትሕ መጉደል የሚሠቃዩ ሰዎች በእነዚህ ጥቅሶች ከፍተኛ መጽናናትን ያገኛሉ። አንድ ቀን እግዚአብሐር በዘላለም መንግሥቱ ያስተናግዳቸዋል። የውይይት ጥያቄ፣ በችግር ውስጥ በምትሆንበት ጊዜ ጽድቅና ቅን ፍርድ የሞላበት አስተዳደር የመምጣቱ ተስፋ የሚያበረታታህ በምን መንገድ ነው? የትንቢተ ሚክያስ ዋና ዋና ትምሕርቶች የውይይት ጥያቄ፣ ሚክያስ 6፡6-8 አንብብ። ሀ) ሚክያስ፣ እግዚአብሔር ከእርሱ የማይፈልገው ምንድር ነው አለ? ለ) ሚክያስ እዚአብሔር ከሰው የሚፈልገው ነገር ምንድር ነው አለ፤ ሐ) እነዚህን ጥሶች ከሕይወትህ ጋር የምታዛምድባቸውን መንገዶች ዘርዝር። መ) ሚክያስ 6፡8 በቃልህ አጥና።  1. ጌታ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው? ትንቢተ ሚክያስ በኃጢአት ላይ የሚመጣውን ፍርድ ወደፊት ከሚገለጡ ታላላቅ ዘመናት ጋር በማቀናጀት የሚናገር ነው። በተለይ የሚያተኩረው ድሆችን በሚጨቁኑ ሀብታሞች ኃጢአት ላይ ነው (ሚክያስ 2፡1-2፤ 3፡1-3፥ 9-11)። ሚክያስ የይሁዳን ኃጢአት በሚገልጽበት ክፍል መሀል እጅግ ጠቃሚ የሆኑ ሁለት ጥያቄዎችን ይጠይቃል፤ በመጀመሪያ፥ “ምን ይዤ ወደ እግዚአብሔር ፊት ልምጣና በልዑል አምላክ ፊት ልስገድ? (ሚክያስ 6፡6) የሚል ሲሆን፥ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ “ሰው ሆይ፥ መልካሙን ነግሮሃል እግዚአብሔር ከአንተ ዘንድ የሚሻው ምንድር ነው?» (ሚክያስ 6፡8) የሚል ነው። በዘመናችን ብዙ ክርስቲያኖች እንደሚያደርጉት በሚክያስ ዘመንም ሕዝቡ እግዚአብሔር ከፍተኛ ትኩረት የሚያደርገው በአምልኮ ሥርዓቶች ላይ ነው የሚል እምነት ነበራቸው። ሕዝቡ ወደ ቤተ-መቅደስ ከመጡ፥ መዝሙራትን ከዘመሩና በሙሴ ሕግጋት መሠረት መሥዋዕቶችን ካቀረቡ እግዚአብሔር የሚፈልግባቸውን ነገሮች ሁሉ ያሟሉ ይመስላቸው ነበር። የአምልኮ ሥርዓቶችን በመፈጸም፥ በክፉ ሥራዎቻቸው ምክንያት ከተቆጣው ቁጣ እግዚአብሔርን የሚመልሱት ይመስላቸው ነበር። እግዚአብሔር አምልኮ በሚፈጽሙበት ጊዜ ስለሚያደርጉት ነገር ብቻ እንጂ በቀሩት የሳምንቱ ቀናት ስለሚያደርጉት ነገር ግድ የሌለው ይመስላቸው ነበር።  ነገር ግን ሚክያስ የልብና የአኗኗር ለውጥ እስከሌለ ድረስ፥ እግዚአብሔር ለሃይማኖታዊ ሥርዓት ግድ እንደሌለው አይቷል። ምንም ያህል ሰዎች ቢዘምሩ፥ ቢጸልዩ፥ ቢጾሙና ለሌሎች ሰዎች ቢመሰክሩ ወይም ሌሎች ሰዎች እጅግ አስፈላጊ ናቸው የሚሏቸውን ሃይማኖታዊ ሥርዓተች ቢፈጽሙ፥ በትክክል እግዚአብሔርን የመታዘዝ ሕይወት እስካልኖሩ ድረስ፥ እግዚአብሔር ደስ አይሰኝም። እውነተኛ አምልኮ ሁለንተናችንን የሚጠይቅ ነው። እግዚአብሔር ስንዘምር፥ ስንጸልይ፥ ስንጾምና ለሌሎች ስንመሰክር ደስ የሚለው መላ ሕይወታችንን የሰጠነው እንደሆነ ነው። ሚክያስ እግዚአብሔር በእርግጥ የሚፈልገው ከልብ መታዘዝን እንደሆነ በማስጠንቀቅ ሕዝቡን የሚያስታውሳቸው ለዚህ ነው (1ኛ ሳሙኤል 15፡22 ተመልከት)። ይህ መታዘዝ ሕይወታቸውን በሙሉ ማጠቃለል አለበት። ከእግዚአብሔር ጋር ያላቸውን ግንኙነት ሁሉ የሚያጠቃልል መሆን አለበት («ከእግዚአብሔር ጋር በትሕትና ኑሩ»)፤ እንዲሁም ከሌሎች ጋር ያላቸውን ግንኙነት የሚጨምር መሆንም አለበት። («በጽድቅ ሥሩ ምሕረትንም ውደዱ»)። የውይይት ጥያቄ፥ ሕይወትህን መርምር። ሀ) ለእግዚአብሔር አምልኮ እንዲሆኑ የምታደርጋቸውን ነገሮች ዘርዝር። ለ) እነዚህ ነገሮች ሊፈጸሙ የሚችሉትና በእግዚአብሔር ዘንድ ግን ተቀባይነት የማያገኙት እንዴት ነው? ሐ) በዚህ ሳምንት ያደረግሃቸውን ጽድቅና ምሕረት የሚያመለክቱ ነገሮችን ዘርዝር። መ) ሁለንተናህ ለእግዚአብሔር መታዘዙን ማረጋገጥ የምትችለው እንዴት ነው? ሠ) እነዚህን እውነቶች ለቤተ ክርስቲያንህ ለማስተማር የምትችለው እንዴት ነው? 2. የሚመጣው ንጉሥና የእግዚአብሔር መንግሥት፡- የትንቢተ ሚክያስ አብዛኛው ክፍል በኃጢአት ላይ ስለሚፈጸም ፍርድና ስለሚመጣው ፍርድ የተነገረ ትንቢት ቢሆንም፥ ሚክያስ የፍርድ ትንቢቶችን ከተስፋ ትንቢቶች ጋር አቀናጅቶ ያቀርባል። ትንቢተ ሚክያስ የመጨረሻውን ዘመን ማለት የሁሉ መደምደሚያ የሆነው እረኛ ንጉሥና መሢሕ በዘመኑ ፍጻሜ ላይ በእግዚአብሔር መንግሥት እንደሚገዛ የሚያሳይ ታላቅ ሥዕላዊ ትዕይንት ያቀርባል። በዚያ መንግሥት ጦርነት አይኖርም፤ ሁሉ ነገር ሰላም ይሆናል። እግዚአብሔር ራሱ ሕዝቡን ስለሚያስተምር ምንም ዓይነት የውሸት አምልኮ አይኖርም። የተበተኑት የእስራኤል ቅሬታዎች ወደ እግዚአብሔር በመመለስ፥ በኢየሩሳሌም እግዚአብሔርን ያመልካሉ። እግዚአብሔር ኃጢአታቸውን ይቅር ይላል። የሚመጣው ንጉሥ፥ መሢሑ የዳዊት ከተማ በሆነችው ቤተልሔም ይወለዳል። አመጣጡ ከዳዊት ዘር ነው፤ ነገር ግን ደካሞችና ኃጢአተኞች ከሆኑት ከዳዊት በኩል ከተነሡት ነገሥታት የተለየ ይሆናል። አመጣጡ ከጥንት ዘመን ስለሆነ አምላክ ነው። ምድርን ሁሉ በጽድቅ መግዛት ብቻ ሳይሆን ደግና ርኅሩኅ እረኛ ይሆናል። ማስታወሻ፡- ስለ ክርስቶስ ኢየሱስ የመጀመሪያና ዳግም ምጽአት የተነገሩ ትንቢቶች በታሪክ በተፈጸሙበት አኳኋን ተነጣጥለው ሳይሆን እንዴት ተጣምረው እንደቀረቡ አስተውል። ነቢያት የወደፊቱን ሁኔታ አርቀው በመመልከት ስለ ክርስቶስ መምጣት ሲናገሩ፥ መሚሑ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚመጣው:- መጀመሪያ በቤተልሔም ተወልዶ በመስቀል ላይ ለመሞት፥ ቀጥሎ ደግሞ እንደ ድል ነሺ ንጉሥ እንደሚሆን አላስተዋሉም ነበር። እና ይህን ልዩነት ልንረዳ የቻልነው የምንኖረው ከኢየሱስ ክርስቶስ ልደትና ሞት በኋላ ስለሆነ ብቻ ነው። ይህ አይሁዶች በተለይ ደግሞ ደቀ መዛሙርት ኢየሱስ በምድር ላይ በተመላለሰና በሞተ ጊዜ የተፈጠረባቸውን ግራ የመጋባት ሁኔታ ለመገንዘብ ይረዳናል። ድል በመንሣት ይገዛል ብለው ይጠብቁት የነበረውን መሢሕ ሁኔታ አላሟላላቸውም ነበር። ከእነዚህ ትንቢቶች አብዛኛዎቹ ኢየሱስ ክርስቶስ ተመልሶ የሚገዛበትን የመጨረሻውን ዘመን የሚመለከቱ ናቸው። በእርሱ ዘመነ መንግሥት ጽድቅና ቅን ፍርድ በምድር ላይ ይንሰራፋል። ኃጢአት ይደመሰስና ሰው ሁሉ በተለወጠ ልብ እግዚአብሔርን ያመልካል። የውይይት ጥያቄ ሀ) እነዚህ ጥቅሶች ከምድር ላይ ፍትሕና ጽድቅ በሚጠፉበት ጊዜ ማበረታቻ የሚሆኑን እንዴት ነው? ለ) ክርስቲያኖች ይህንን እውነት በልባቸው መያዝ ያለባቸው ለምንድን ነው? ሐ) እግዚአብሔር በአምልኮአቸው ደስ ይሰኝ ዘንድ እርሱን በሚያስደስተው መንገድ እንዲኖሩ ሰዎችን ለመርዳት ምን ማድረግ ትችላለህ? (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡) የመመዘኛ ጥያቄዎችን ለማግኘት ከታች ያለውን ሊንክ (መስፈንጠሪያ) ይጫኑ፡፡

የትንቢተ ሚክያስ ዓላማ እና ዋና ዋና ትምሕርቶች Read More »

የትንቢተ ሚክያስ መግቢያ

የውይይት ጥያቄ) እግዚአብሔር በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያሉትን ሰዎች በተለያዩ ስጦታዎች፥ ሥልጠናዎችና ሥረ መሠረቶች የተጠቀመባቸውን መንገዶች ግለጽ። ለ) እግዚአብሔር በዚህ መንገድ የሚሠራው ለምንድን ነው ብለህ ታስባለህ? የእግዚአብሔርን አሠራር ልዩ ከሚያደርጉ ነገሮች አንዱ የተለያዩ ባህሎች፥ ስጦታዎች፡ ሥልጠናዎችና ሥረ መሠረቶች ያሏቸውን ሰዎች ወደ አንድ አካል ማምጣቱ ነው። የክርስቶስ አካል የሆነው ያ ቡድንም የእግዚአብሐርን ዓላማዎች ለመፈጸም ጠንካራና ብርቱ ኃይል ይሆናል። በሌላም በኩል ሰዎች ሌሎች ከእነርሱ ጋር ተመሳሳይ እንዲሆኑ ይፈልጋሉ። ሰዎች፥ የተለያዩ ባህሎችና ሥረ መሠረቶች ወይም የተለያዩ ስጦታዎችና ችሎታዎች ካሏቸው ሰዎች፥ ጋር ከመሆን ይልቅ፥ ተመሳሳይ ሥረ-መሠረቶችና ባህሎች፥ እንዲሁም ተመሳሳይ ስጦታዎች ካሏቸው ሰዎች ጋር መሥራትን ይመርጣሉ። ይህ ምርጫ አንድነትን በማምጣት ቤተ ክርስቲያንን የሚያጠናክር ቢመስለንም፥ በመሠረቱ የዚህ ውጤት ደካማ ቤተ ክርስቲያንን መመሥረት ነው። በብሉይ ኪዳን ውስጥ የእግዚአብሔር ቃል አቀባዮች ሆነው ያገለገሉትን ነቢያት ሕይወት ስንመረምር እጅግ የተለያዩ ዓይነት ሰዎች እንደነበሩ እንመለከታለን። እንደ ኤልያስና ኤልሳዕ ያሉት የነቢያት ጉባኤ አባላት ሲሆኑ፥ የነቢይነት ሥራቸውን የሚያከናውኑት ሙሉ ጊዜያቸውን ሰጥተው ነበር። እንደ አሞጽ ያሉት ሌሎች ደግሞ ግብርናን በመሰለ ሌላ ሥራ ላይ ተሰማርተው ነበሩና የነቢይነት ሥራን ለተወሰነ ጊዜ ብቻ የሚሠሩ ነበሩ። እንደ ዳንኤልና ኢሳይያስ ያሉት ደግሞ ከንጉሣዊ ቤተሰብ የመጡ የኅብረተሰቡ ከፍተኛ መደብ አባሎች ነበሩ። እንደ ሚክያስ ያሉት ከድሀ ወይም ከዝቅተኛ መደብ የመጡ ነበሩ። ሌሎች ደግሞ ነቢያት ብቻ ሳይሆን፥ ካህናትም ነበሩ (ለምሳሌ፡- ሕዝቅኤል)። እነዚህ ሁሉ እጅግ የተለያዩ ቢሆኑም እንኳ እግዚአብሔር ሁሉንም የራሱ ቃል አቀባዮች ሆነው እንዲያገለግሉ አድርጎ ነበር። የውይይት ጥያቄ፣ የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን የተለያዩ ስጦታዎች ባሏቸው የተለያዩ ሰዎች የተገነባች መሆኗን ማስታወስ የሚያስፈልገው ለምንድን ነው? ለ) እያንዳንዱ ክርስቲያን የተሰጠውን ስጦታ በማወቅ ቤተ ክርስቲያንን ሲያገለግል ጠቃሚ የሚሆነው ለምንድን ነው? ሐ) ከእኛ የተለዩ ስጦታዎች ወይም ባህሎች ያሏቸውን ሰዎች በአክብሮት ላለማስተናገድ ይህ እውነት ምን ሊያስተምረን ይገባል? መ) እያንዳንዱ አባል የተሰጠውን ስጦታ እንዲያውቅና እንዲጠቀምበት ለመርዳት ቤተ ክርስቲያህ ማድረግ የምትችላቸውን ነገሮች ዘርዝር። የትንቢተ ሚክያስ ጸሐፊ ትንቢተ ሚክያስ የተጻፈው ሚክያስ በተባለ ሰው ነው። ስለ ነቢዩ ሚክያስ የምናውቀው ነገር እጅግ በጣም ጥቂት ነው። ሚክያስ የመጣው አንዳንድ ጊዜ ሞሬሼት ተብላ ትጠራ ከነበረችው ከሞሬሽትጌት ከተማ ነው (ሚክያስ 1፡1፥14)። ይህች ከተማ የምትገኘው ከኢየሩሳሌም ደቡብ ምዕራብ 30 ኪሎ ሜትር ርቃ በሜድትራንያን ባሕርና በኢየሩሳሌም ከተ መመካከል ነበር። በኋላ ቀርነታቸው እጅግ ከሚታወቁት የይሁዳ ክፍሎች አንዱ በመሆንዋ ትታወቅ ነበር፡፡ በዚህች ከተማ ብዙ ድሀ ገበሬዎች ይኖሩ ነበር። ሚክያስ የይሁዳ ሕዝብ በድሆች ላይ ስለፈጽሟቸው ማህበራዊ ኃጢአቶች የፍርድ ቃል በተናገረበት በመጽሐፉ ውስጥ ስለ እነዚህ ድሆች የነበረውን አትኩሮት ልንመለከት እንትላለን፡፡ ሚክያስ በይሁዳ ሕዝብ መካከል የነቢይነት አገልግሎት የሰጠው ከ750-686 ዓ.ዓ. ነበር። ይህም በኢዮአታም፣ በአካዝና በሕዝቅያስ ዘመነ መንግሥት መሆኑ ነው (ሚክያስ 1፡1)። ምናልባት ከትንቢቶቹ አብዛኛው ክፍል የተነገረው በንጉሥ ሕዝቅያስ መሪነት ተካሄዶ ከነበረው መንፈሳዊና ማኅበራዊ ተሐድሶ በፊት ሳይሆን አይቀርም። በዚያን ዘመን ያገለግል የነበረ ነቢይ ሚክያስ ብቻ አልነበረም። ሆሴዕና አሞጽ በእስራኤል ላይ ትንቢት ሲናገሩ፥ በይሁዳ ደግሞ ከሚክያስ ጋር ኢሳይያስም ያገለግል ነበር። በኢሳይያስና በሚክያስ መልእክቶች መካከል ካለው ግልጽ ተመሳሳይነት የተነሣ (ሚክያስ 4፡1-3 ና ኢሳይያስ 2፡1-4)፥ ብዙ ምሁራን ሚክያስ ኢሳያይስን እንደሚያውቅና ምናልባትም የእርሱ ደቀ መዝሙር እንደነበረ ይናገራሉ። የኢሳይያስ አገልግሉት በኢየሩሳሌም ከተማ ውስጥ ሲሆን፥ የሚክያስ አገልግሎት ደግሞ ምናልባት ደግሞ በገጠር የነበረ ሊሆን ይችላል። ሚክያስ በነቢይነቱ በሕዝቡ መካከል የነበረው ምስክርነት መልካም ነበር፤ እንዲሁም ከብዙ ዓመታት በኋላ በኤርምያስ ዘመን፥ ኤርምያስ በኢየሩላሉም ላይ በተናገረው ትንቢት ምክንያት ሕዝቡ ከመገደል የተረፈው የሚክያስን ትንቢት በመመልከታቸው ነበር (ኤር. 26፡15-19 ተመልከት)። እግዚአብሔር በይሁዳ መንፈሳዊ እንቅስቃሴ ለመጀመር፥ እንደ ኢሳያይስ ካሉ ነቢያትና ፈሪሀ እግዚአብሔር ካደረበት ንጉሥ ሕዝቅያስ ጐን ሚክያስንም ተጠቅሞበታል። የእግዚአብሔር ፍርድ ለብዙ ዓመታት ተፈጻሚ ሳይሆን የቆየው በእርሱ ምክንያት ነበር።  የትንቢተ ሚክያስ ታሪካዊ ሥረ መሠረት ሚክያስ የተወለደው ንጉሥ ዖዝያን በይሁዳ ዙፋን ላይ እያለ ነበር። ዖዝያን እግዚአብሔርን የሚፈራ ታላቅ መሪ ነበር። በእርሱ አመራር ወቅት በእስራኤል ፍጹም ሰላምና ብልጽግና ነበረ። ሰዎች የጣዖት አምልኮአቸውን እየተዉ በቤተ መቅደስ እግዚአብሔርን ያመልኩ ነበር። ከፍተኛ የሆነ መንፈሳዊ መነቃቃት የታየበት ጊዜ ነበር። ዳሩ ግን ሀብትና ንግድ ዕድገት እያሳየ በመሄዱ ምክንያት አዲስ ዓይነት ሰዎች በይሁዳ ተነሡ። እነዚህ ነጋዴዎች እጅግ ሀብታሞች ስለሆኑ በይሁዳ እጅግ ይከበሩ ጀመር። የሚያሳዝነው ግን ለሀብት የነበራቸው ስግብግብነት ገበሬዎችንና ድሆችን እንዲጨቁኑና ከታዋቂ ሰዎችና ከመሪዎች ጋር በመሆን በተራው ሕዝብ ላይ የፍትሕ መዛባት እንዲያደርሱ አደረጋቸው። ንጉሥ ዖዝያን በሞተ ጊዜ ነገሮች ቀስ በቀስ መለወጥ ጀመሩ። ልጁ ንጉሥ ኢዮአታም በአባቱ ዘመን የነበረውን ሀብትና ሰላም ለማስጠበቅ ወይም ለማቆየት ችሎ ነበር። ሚክያስ የእግዚአብሔር ነቢይ ሆኖ በይሁዳ ማገልገል የጀመረው በእነዚህ ጊዜያት ነበር። የኢዮአታም ልጅ አካዝ በነገሠ ጊዜ ነገሮች ሁሉ ፈጥነው ተቀየሩ። እግዚአብሔርን የማይፈራ ሰው ስለነበር ሕዝቡን ፈጥኖ ወደ ጣዖት አምልኮ መለሳቸው። በመሆኑም፥ በይሁዳ የነበረው መንፈሳዊና ሥነ ምግባራዊ ሁኔታ እጅግ ተበላሸ። የሰው ልጆች መሥዋዕት ተደርገው የሚቀርቡበት የጣዖት አምልኮ ተስፋፋ። የሃይማኖት መሪዎች የነበሩት ካህናትና ነቢያት የእግዚአብሔርን ቃል ስለመናገርና ማስተማር የማይገባቸው ሆኑ። በዚህ ፋንታ ለገንዘብ መሯሯጥ ጀመሩ። የፖለቲካ መሪዎች፥ ነገሥታትና መሳፍንት ለራሳቸው ደኅንነትና ዋስትና ብቻ በመጨነቅ፥ የድሆችን፥ የመበለቶችንና የሙት ልጆችን ጥሪት የሚነጥቁ ሆኑ። ቤተሰብ መፈራረስ ጀመረ፤ በምድሪቱም ሁሉ አለመተማመን ነገሠ (ሚክያስ 7፡5-6)። የዖዝያንና የኢዮአታም የሰላም ጊዜያት አከተሙ። የእስራኤል ንጉሥ ፋቁሔና የሶርያ ንጉሥ ረኦሶን ይሁዳን ይወጉ ጀመር። በዚህ ምክንያት ንጉሥ አካዝ የአሦርን እርዳታ ለመነ። አሦርም ሶርያን በ732 ዓ.ዓ.፥ እስራኤልን ደግሞ በ722 ዓ.ዓ. አሸነፈች። ሚክያስ የሰማርያን ውድቀት አመለከተ (ሚክያስ 1፡6)። አንድ ቀን ይሁዳ በተመሳሳይ መንገድ በምርኮ እንደምትወሰድ በማወቅ ይህንን ከፍተኛ ኃዘን ይጠባበቅ እንደነበረ ጥርጥር የለውም። የሚክያስ አብዛኛው መልእክት ሥነ-ምግባራዊና መንፈሳዊ ክፋት የነበረበትን ይህን ጊዜ ያመለክታል።  ንጉሥ ሕዝቅያስ ወደ ሥልጣን በመጣና ሁኔታዎች መለዋወጥ በጀመሩ ጊዜ ሚክያስ እጅግ ሳይደሰት አልቀረም። ሕዝቅያስ ሕዝቡን ወደ እግዚአብሔር ለመመለስ የጣረ መልካም ንጉሥ ነበር። በዚህ ተሐድሶ ሚክያስ እንደ ተካፈለ ጥርጥር የለውም። ሕዝቅያስ ይሁዳ ራሷን ከጠላቶችዋ የምትጠብቅበትን መከላከያ አጠንክሮ ነበር። ነገር ግን ምንም አልረዳውም። በ701 ዓ.ዓ. አሦር ይሁዳን በማጥቃት አብዛኛውን የይሁዳ ምድር ያዘች። ኢየሩሳሌም የዳነችው በእግዚአብሔር ጣልቃ ገብነት ብቻ ነበር (2ኛ ነገሥት 18-19)። ሚክያስ ይህ ጥፋት ሕዝቡ በእግዚአብሔር ላይ በሠሩት ኃጢአት ምክንያት አንድ የሚመጣባቸው ምልክት እንደሆነ ተገንዝቦ ነበር። የውይይት ጥያቄ፣ ስለ ሚክያስ ከመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት አንብብ። ስለ ትንቢተ ሚክያስ የተጠቀሱትን ጠቃሚ እውነቶች ዘርዝር። የትንቢተ ሚክያስ አስተዋጽኦ 1. ሚክያስ በሰማርያና በኢየሩሳሌም ላይ የተናገራቸው ትንቢቶች (ሚክያስ 1)፥  2. ሚክያስ በይሁዳ መሪዎች ላይ የተናገራቸው ትንቢቶች (ሚክያስ 2-3)፡  3. ሚክያስ ስለ ጽዮን ተሐድሶ የተናገረው ትንቢት (ሚክያስ 4-5) ሀ. የሚመጣው የእግዚአብሔር መንግሥት (ሚክያስ 4) ለ. ንጉሥና እረኛ ሆኖ የሚመጣው የመንግሥቱ ገዥ (ሚክያስ 5)፡  4. ሚክያስ ስለ ይሁዳ ክፋትና ስለሚመጣበት ፍርድ የተናገረው ትንቢት (ክያስ 6፥7፡6)። 5. ሚክያስ፥ የእስራኤል ቅሬታዎች በወደፊቱ የእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ ስለሚቀበሉት ይቅርታ የተናገራቸው ትንቢቶች (ሚክያስ 7፡7-20)። (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡) የመመዘኛ ጥያቄዎችን ለማግኘት ከታች ያለውን ሊንክ (መስፈንጠሪያ) ይጫኑ፡፡

የትንቢተ ሚክያስ መግቢያ Read More »