የትንቢተ ሐጌ ዓላማ፣ አስተዋጽኦ እና ዐበይት ትምሕርቶች
የትንቢተ ሐጌ ዓላማ እግዚአብሔር ሐጌን የጠራው ለአንድ ግልጽ ዓላማ ነበር። ይኸውም ወደ ኢየሩሳሌምና ወደ ይሁዳ የተመለሱት አይሁድ ከ70 ዓመታት በፊት የተደመሰሰውን ቤተ መቅደስ በመሥራት ለእግዚአብሔር ያላቸውን ፍቅር እንዲገልጡ ማበረታታት ነበር። ትንቢተ ሐጌ አይሁድ ቤተ መቅደሱን ለመሥራት ያላቸውን ዕድልና ያለባቸውን ኃላፊነት የሚያሳስቡ አራት መልእክቶችን ይዟል። የእግዚአብሔር የቃል ኪዳኑ ሕዝብ በመሆናቸው የራሳቸውን አኗኗር ከማሻሻላቸው በፊት፥ እግዚአብሔርን ለማምለክ የሚጠቀሙበትን ቤተ መቅደስ መሥራት ግዴታቸው ነበር። እንዲሁም ሐጌ ለእስራኤል ሕዝብ ሙሉ በረከት ይዞ ስለሚመጣው መሢሕ ለአይሁድ አስታወሳቸው። አሁን ያሉበትን ሁኔታ ሳይሆን፥ የወደፊቱን የእግዚአብሔር ሥራ በማየት ሊበረታቱ ይገባ ነበር። ትንቢተ ሐጌ መሪዎች የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የሆነችውን ቤተ ክርስቲያንን ለመጠበቅ ማድረግ ስላለባቸው ነገሮች ስለሚያስተምር ዛሬም አስፈላጊነቱ የጐላ ነው። የሰዎች መንፈሳዊ ሕይወት ሲበላሽና ሲጠፋ መልሶ ማስተካከል እንዴት እንደሚቻል ያስተምራል። በዚያን ጊዜ እንደነበሩ አይሁድ፥ እኛም በራሳችን የእግዚአብሔርን ነገሮች ከራሳችን ፍላጎትና ጥቅም ለማስቀደም መቻል አለብን። ምን ያህል ገንዘብ እንደምናገኝ፣ ምን ያህል ትምህርት እንዳለን፥ በምን ዓይነት ቤት ውስጥ እንደምንኖር ወዘተ. ከማሰብ ይልቅ፥ የበለጠ ሊገደን የሚያስፈልገው ከእግዚአብሔር ጋር ስላለን ግንኙነትና ለእርሱ ስላለን መታዘዝ መሆን አለበት። የውይይት ጥያቄ፦ ሀ) የቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ግድግዳዎች ሊደመሰሱና እንደገና ሊሠሩ የሚያስፈልግበትን ሁኔታ የሚገልጽ ምሳሌ ስጥ። ለ) የቤተ ክርስቲያን መሪዎችን ጨምሮ ክርስቲያኖች ከእግዚአብሔር ነገሮች ይልቅ ለግል ምቾቶቻቸው ማሰብ የሚቀልላቸው እንዴት ነው? ሐ) ይህ ነገር ለቤተ ክርስቲያን አደገኛ የሚሆነው ለምንድን ነው? መ) የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ይህንን ለመዋጋት ምን ማድረግ ይችላሉ? የትንቢተ ሐጌ አስተዋጽኦ 1. 1ኛ መልእክት፡- ሕዝቡ ቤተ መቅደሱን እንዲሠሩ መጠራታቸውና የሰጡት ምላሽ (ሐጌ 1)፥ 2. 2ኛ መልእክት፡- ቤተ መቅደሱ በእግዚአብሔር ክብር እንደሚሞላ የተነገረ ትንቢት (ሐጌ 2፡1-9)፥ 3. 3ኛ መልእክት፡- ሕዝቡ ከነጹና ቤተ መቅደሱን መሥራት ከቀጠሉ እግዚአብሔር ይባርካቸዋል (ሐጌ 2፡10-19)፡ 4. 4ኛ መልእክት፡- እግዚአብሔር ዘሩባቤልን እንደ ራሱ ቀለበት ማተሚያ አድርጎ መረጠው (ሐጌ 2፡20-23)። የትንቢተ ሐጌ ዐበይት ትምህርቶች 1. መታዘዝ በረከትን አለመታዘዝ ደግሞ ቅጣትን ያመጣል፡- ዛሬ ብዙዎቻችን እንደምናስበው ሁሉ አይሁዶችም፥ በሕይወታቸው ዘመን በሚፈልጉአቸው ነገሮች ላይ እስካተኲሩ ድረስ እንደሚያገኙአቸው ያምኑ ነበር። በሕይወት ውስጥ ከሁሉ የላቀውና ተፈላጊው ነገር ሊያገኙት የሚችሉት ሥጋዊ በረከት እንደሆነ ያምኑ ነበር። ስለዚህ ጠንክረው በመሥራት ቁሳዊ በረከቶችን አገኙ። ጥሩ ቤቶች፥ ጥሩ ሥራ፥ ወዘተ. ነበራቸው። ግን አንድ ነገር ደኅና አልነበረም፤ የእህል ምርታቸው የተጠበቀውን ያህል የሚያረካ አልነበረም፤ ድርቅ ከምድሪቱ በፍጹም የሚለቅ አይመስልም። ትንቢተ ሐጌ የሚያስተምረው፥ በሕይወት ውስጥ እውነተኛ በረከትን ለማግኘት፥ ማለትም ሥጋዊ ብቻ ሳይሆን መንፈሳዊ በረከት ጨምሮ እንዲኖር፥ እግዚአብሔር እንድንሠራው የሚፈልገውን ነገር በተቀዳሚ የመሥራት ፍላጎት መኖር እንዳለበት ነው። እግዚአብሔርን መታዘዝ ያስፈልጋል። ከግል ፍላጎት በላይ ለእግዚአብሔር ጉዳይ ቅድሚያ የመስጠት ፍላጎት መኖር አለበት። ሐጌ የድርቁ ምክንያት ሕዝቡ እግዚአብሔርንና ጽድቁን አለመፈለጋቸው እንደነበር ይናገራል። ስለዚህ የእግዚአብሔርን ፍጹም በረከት መቀበል ቢፈልጉ ኖሮ እግዚአብሔርን ማስቀደም ነበረባቸው። የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ መሥራትና ለእግዚአብሔር በንጽሕናና በመታዘዝ መኖር አስፈላጊያቸው ነበር። በእርግጥ እግዚአብሔር በቁሳዊ ነገሮች የሚባርካቸው በዚህ ጊዜ ነበር። እግዚአብሔር በሥጋዊ በረከቶች ሊባርካቸው ይችላል። ከዚህ የሚበልጠው ግን እግዚአብሔር በመካከላቸው በመኖር፥ ከእነርሱ ጋር ኅብረት በማድረግ፥ በመጠበቅ የልብ ሰላምና የሕይወት ደስታን በመስጠት ይባርካቸው ነበር። ለክርስቲያኖች፥ እግዚአብሔርን ከታዘዝን ሥጋዊ በረከቶችን እንደምናገኝ የተገባልን ቃል ኪዳን የለም፡፡ ይህ ምድራዊ ሕይወት በሥቃይ፥ በስደትና በሞት የታጀበ እንደሆነ ተነግሮናል። ክርስቲያኖች የተገባልን ተስፋ ወይም ቃል ኪዳን ለእግዚአብሔርና ለክብሩ ከኖርን፥ እግዚአብሔርን ከታዘዝንና የእርሱን ነገር ካስቀደምን በሕይወታችን ከሁሉ የላቀውን በረከት እንደምናገኝ ነው። እግዚአብሔር በውስጣችን በመኖር ከእኛ ጋር ኅብረት ያደርጋል። ውጫዊ ሁኔታዎች ምንም ዓይነት ይሁኑ ሰላምና ደስታ ይኖረናል። እግዚአብሔር መጠጊያችን በመሆን በሕይወታችን ዘመን የሚያስፈልጉንን ነገሮች ሁሉ ይሰጠናል። የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ብዙ ክርስቲያኖች እምነት ካላቸው፥ ሁልጊዜ ሥጋዊ በረከቶችን እንደሚያገኙ የሚመስላቸው ለምንድን ነው? ለ) ይህ እውነት ነውን? ከሆነ ለምን? ካልሆነስ ለምን? ሐ) ከቁሳዊ በረከቶች ይልቅ መንፈሳዊ በረከቶች የበለጠ አስፈላጊ የሚሆኑት በምን መንገድ ነው? መ) ከላይ የተመለከትነው እውነት በሕይወትህ ሲረጋገጥ ያየኸው እንዴት ነው? 2. የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ፡- መጽሐፍ ቅዱስ ለቤተ መቅደስ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ይናገራል። ሙሴ የመጨረሻ ቃሎቹን ለእስራኤላውያን በሚናገርበት ጊዜ አንድ ቀን እግዚአብሔር ስሙን የሚያጸናበት የአምልኮ ስፍራ እንደሚመሠርት ጠቁሟል (ዘዳግም 14፡23-25)። በኋላም እስራኤላውያን ወደ ተስፋዪቱ ምድር እንደገቡ በሴሎ የመገናኛውን ድንኳን ተከሉ (ኢያሱ 18፡1)። ይህም ስፍራ በመጨረሻ ተደመሰሰ። ቀጥሎም ዳዊትና ሰሎሞን ቋሚ የሆነ እግዚአብሔር የሚመለክበት ቦታ ሠሩ። ታላቁ ቤተ መቅደስ ከሰባት ዓመታት በኋላ ተሠርቶ ሲያልቅ፥ በእግዚአብሔር ክብር ተሞላ (1ኛ ነገሥት 8)። እግዚአብሔር ለአይሁዶች ያለው አሳብ የቤተ መቅደሱ ሕንጻ ሥራ መጠናቀቅ በራሱ እንደ ተልዕኳቸው ማብቂያ እንዲታይ አልነበረም፤ ነገር ግን ሕንጻው እግዚአብሔር በመካከላቸው መኖሩን እንዲያውቁ የሚያሳይ ምልክት እንዲሆን ነበር። ከእግዚአብሔር ጋር ልዩ የሆነ ግንኙነት እንዳላቸው፥ ለቃል ኪዳኑ በመታዘዝ እግዚአብሔርን እንዲያከብሩትና ሕያው የሆነውን እውነተኛውን አምላክ ከልባቸው እንዲያመልኩት ለማስታወስ ነበር። ይሁን እንጂ በኤርምያስ ጊዜ አይሁድ ውጫዊውን ሕንጻ እንደ አንድ የአስማት ሐውልት ይመለከቱት ነበር። የቤተ መቅደሱን ሕንጻ ከጠላቶቻቸው የሚጠብቃቸው ዋስትና አድርገው ይቆጥሩት ነበር። ለእግዚአብሔር ከሚሰጡት ትኩረት ይልቅ፥ ከውጭ ለሚታየው ሕንጻ የሚሰጡት ትኩረት የላቀ ነበር። በኋላም በሕዝቅኤል ራእይ የእግዚአብሔር ክብር ቤተ መቅደሱን ትቶ ሲሄድ ታየ፤ ይህም እግዚአብሔር በሕዝቡ ጣዖት አምላኪነትና አለመታዘዝ ማዘኑን የሚያሳይ ነበር። የቤተ መቅደሱ ሕንጻ ከዚያ በኋላ ለተወሰነ ጊዜ ቢቆይም እንኳ እግዚአብሔር ግን በውስጡ አልነበረም። ዳሩ ግን እግዚአብሔር ቤተ መቅደሱን ለማጥፋት ወሰነ (ኤርምያስ 7፡1-15)። ሕዝቡ በቤተ መቅደሱ ውስጥ አምልኮ መፈጸማቸውን የቀጠሉ ቢሆንም፥ ይህን የሚያደርጉት በባዶ ሕንጻ ውስጥ ነበር። በመጨረሻ በ587 ዓ.ዓ. ናቡከደነፆር ባዶውን የቤተ መቅደስ ሕንጻ ደመሰሰው። የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ዛሬ ብዙ ክርስቲያኖች ውጫዊ የሆነውን የቤተ ክርስቲያን ሕንጻ የእግዚአብሔር በረከቶችን የማግኘት ዋስትና አድርገው የሚቆጥሩት እንዴት ነው? ለ) ብዙ ክርስቲያኖች ለቤተ ክርስቲያን ሕንጻ ሥራ ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጡት ለምንድን ነው? የእነዚህ ክርስቲያኖች ዝንባሌ በኤርምያስ ጊዜ ከነበሩት አይሁዳውያን ጋር ተመሳሳይ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው? ሰባ ዓመት ያህል ካለፈ በኋላ እግዚአብሔር ቤተ መቅደሱን ይሠሩ ዘንድ ሕዝቡን አነቃቃቸው። ለእርሱ በመታዘዝ ከተመላለሱ ይሰጣቸው ዘንድ ቃል የገባላቸውን በረከት እንደ ገና እንደሚያፈስስላቸው ተስፋ ሰጠ። ቤተ መቅደሱ አሁንም ቢሆን ከሁሉ የላቀና የተሻለ ነገር አልነበረም። ነገር ግን እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር እንዳለና በመካከላቸው እንደሚኖር ያመለክት ነበር። ስለዚህ በእርሱ ፊት እንደ ቃል ኪዳን ሕዝብ መመላለስ ነበረባቸው። ቤተ መቅደሱ ለእግዚአብሔር በጣም አስፈላጊ የሆነውና አይሁድ እንዲሠሩት የታዘዙት ለምን ነበር? እግዚአብሔር ቤተ መቅደሱ አይሁድ ሁሉ የሚያመልኩበት ስፍራ እንዲሆን ይፈልግ ነበር። አይሁድ ቤተ መቅደሱን በተመለከቱና በዚያ አምልኮን ባቀረቡ ቁጥር እግዚአብሔር በመካከላቸው እንዳለ መገንዘብ አስፈላጊያቸው ነበር። ይህም የእግዚአብሔር የቃል ኪዳኑ ሕዝብ እንደሆኑና እንደ ቃል ኪዳን ሕዝቡም ለእግዚአብሔር በመታዘዝ መኖር እንዳለባቸው ያስታውሳቸው ነበር። ነገር ግን የሚያሳዝነው አይሁድ ልክ እንደቀደሙት አባቶቻቸው ፈጥነው የቤተ መቅደሱን መኖር ለእግዚአብሔር በረከት መኖር ማረጋገጥ አድርገው ቆጠሩት። ለእውነተኛው የእግዚአብሔር አምልኮ ወይም እግዚአብሔርን መታዘዝ ጉዳይ ብዙ ትኩረት አይሰጡም ነበር። ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረ ጊዜ አይሁድ ከእግዚአብሔር ይልቅ ቤተ መቅደሱን ያከብሩ ነበር። ኢየሱስም እንደ ኤርምያስ ስለ ቤተ መቅደሱ መደምሰስ ተነበየ (ሉቃስ 21፡5-6)። በዓይን የሚታየው ግዑዝ ሕንጻ አስፈላጊ እንዳልሆነ፥ ዳሩ ግን እግዚአብሔር በሰው ልብ ቅንነትና በልብ ውስጥ በሚፈጸም ንጹሕ አምልኮ እንደሚደሰት ለሳምራዊትዋ ሴት ተናግሯል። “በእውነትና በመንፈስ” እስከሆነ ድረስ ሰው የትም ቦታ እግዚአብሔርን ሊያመልከው ይችላል (ዮሐንስ 4፡21-24)። በኋላም ሐዋርያው ጳውሎስ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ በዓይን የምናየው ውጫዊ ሕንጻ እንዳልሆነ አስተምሯል። ይልቁንም ኢየሱስ የሚኖርበት የእያንዳንዱ ክርስቲያን ልብ ቤተ መቅደስ ነው (1ኛ ቆሮ. 6፡19)። በተጨማሪም እግዚአብሔር በመካከላቸው ስለሚኖር ማናቸውም ክርስቲያኖች የተሰበሰቡበት ቦታ
የትንቢተ ሐጌ ዓላማ፣ አስተዋጽኦ እና ዐበይት ትምሕርቶች Read More »
