ትንቢተ ሶፎንያስ

የትንቢተ ሶፎንያስ ዓላማ እና ዐብይ ትምሕርት

የትንቢተ ሶፎንያስ ዓላማ ከይሁዳ ውድቀት በፊት እግዚአብሔር የመጨረሻ መልእክተኞች ካደረጋቸው ቃል አቀባዮቹ አንዱ ሶፎንያስ ነበር። ሶፎንያስ በእግዚአብሔር የተላከው በክፋታቸው ምክንያት በቅርብ ጊዜ ስለሚፈጸምባቸው ፍርድ በመናገር የይሁዳን ሕዝብ ለማስጠንቀቅ ነበር። ሕዝቡ ንስሐ ካልገቡና አኗኗራቸውን ካልለወጡ ሊመጣባቸው ስላለው ፍርድ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ለማቅረብ እግዚአብሔር ተጠቀመበት። በመሆኑም ሊመጣ ስላለው «የጌታ ቀን» ተናገረ። ይህ ቀን አብዛኛው ሕዝብ እንደሚጠብቀው የደስታና የበረከት ቀን አይሆንም። ይልቁንም ከበረከቱ ጊዜ በፊት በኃጢአተኞች ሁሉ ላይ ከፍተኛ የፍርድ ጊዜ ይኖራል። ፍርዱ የሚጀምረው በኢየሩሳሌም በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ ነው። ነገር ግን ክፉና ኃጢአተኛ በሆኑ ሰዎች ሁሉ ላይም ይፈጸማል። ትሑታን የሆኑና ወደ እግዚአብሔር ለመመለስ የሚፈልጉ ሰዎች ንስሐ እንዲገቡና የእግዚአብሔርን ምሕረት እንዲፈልጉ ተጠርተው ነበር። ሶፎንያስ የይሁዳ ሕዝብ ተማርከው ወደ ባቢሎን እንደሚወሰዱ በግልጽ ባያመለክትም፥ በይሁዳ ላይ ስለሚመጣ ትልቅ ጥፋትና ከምርኮ ስለ መመለሷም ተናግሮ ነበር (ሶፎንያስ 3፡20)። ዛሬ ለሰዎች መስበክ ያለብን ወንጌል ሶፎንያስ ከብዙ ዓመታት በፊት ካስተላለፈው መልእክት ጋር ተመሳሳይ ነው። በአንድ በኩል ንስሐ ለሚገቡና ለእግዚአብሔር ወደ መታዘዝ ዞር ለሚሉ ሰዎች የደስታ፥ የሰላምና የመንፈሳዊ በረከት ተስፋ እንዳላቸው ልንነግራቸው እንችላለን። በሌላ በኩል ደግሞ ለእግዚአብሔር አለመታዘዝ የሚያስከትላቸውን ነገሮች ለሰዎች ማሳየት አስፈላጊ ነው። ወንጌል በኢየሱስ ክርስቶስ የማያምኑ ሰዎች የዘላለም ሥቃይ እንደሚያገኛቸው የሚናገር መልእክትም አለው። ልክ አይሁዶች ያስቡት እንደነበረው፥ ሰዎች መልካም ሆኑ ክፉ እግዚአብሔር ግድ እንደሌለው አድርገው እንዲያስቡ መፍቀድ የለብንም። ንስሐ ገብተው፥ በኢየሱስ ማመንና ለእግዚአብሔር በመታዘዝ መራመድ እንዳለባቸው። አለበለዚያ ግን የእግዚአብሔር ፍርድ እንደሚጠብቃቸው ልናሳስባቸው ይገባል። የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) በአዲስ ኪዳን ውስጥ ሰዎች ንስሐ ባይገቡ በእግዚአብሔር እንደሚፈረድባቸው በመናገር የሚያስጠነቅቁትን ጥቅሶች ዘርዝር። ለ) እነዚህ ጥቅሶች ለማያምኑ ሰዎች ልንነግራቸው የሚገባው የወንጌል ክፍል የሚሆኑት እንዴት ነው? ሐ) ክርስቲያኖችን ሳይቀር ስለሚመጣው ፍርድ በመናገር የሚያስጠነቅቁ ጥቅሶች የትኞቹ ናቸው? የትንቢተ ሶፎንያስ ዓቢይ ትምህርት እንደ አብዛኛዎቹ ሌሎች ነቢያት፥ ሶፎንያስም ሊመጣ ባለው «የጌታ ቀን» ላይ በማተኮር ይናገራል። ሶፎንያስ ስለ ጌታ ቀን የሚያስተምራቸው ትምህርቶች በአንድ ክፍለ ጊዜ ውስጥ መድቦ ለመግለጽ የሚያስቸግሩ ናቸው። ሶፎንያስ ስለ ጌታ ቀን የሚናገረው ሰፋ ያለ አሳብ በሚገልጡ ቃላት ነው። በመሆኑም በዚያኑ ዘመን በይሁዳና በአሕዛብ ሁሉ ላይ በሚመጣው የጌታ ቀንና በመጨረሻው ዘመን በሚመጣው የጌታ ቀን መካከል ብዙ ልዩነት አላደረገም። በትንቢተ ሶፎንያስ ውስጥ የጌታ ቀን የተገለጸው በታሪክ ውስጥ የሚከሰት አንድ የተወሰነ ቀን ወይም ጊዜ ተደርጎ ሳይሆን፥ የማያቋርጥ የታሪክ ሂደት ሆኖ ነው። እግዚአብሔር በፍርድ ወይም በበረከት ፈቃዱን የፈጸመበት ማንኛውም ቀን የጌታ ቀን ተብሎ ሊጠራ ይችል ነበር። ያ የጌታ ቀን ሰዎችንና ነገሮችን ሁሉ የሚነካ ነው። በጌታ ቀን የሚሆኑትን የሚከተሉትን ነገሮች አስተውል፡- 1. ለይሁዳ፥ የጌታ ቀን ሶፎንያስ ከነበረበት ዘመን ጋር የሚቀራረቡ ውጤቶች ነበሩት። የጌታ ቀን አይሁድ እጅግ ከባድ በሆነ ሁኔታ የእግዚአብሔርን ፍርድ የሚቀበሉበት ቀን ነው። ይህ ቀን ተማርኮ ወደ ባቢሎን መሄድንም እንደሚያጠቃልል እናውቃለን። በተጨማሪም ያ የባቢሎን ምርኮ በዘመን መጨረሻ ኢየሱስ ለመግዛት ከመምጣቱ በፊት ይሁዳ የምትጋፈጠውን ከፍተኛ ጥፋት የሚያመለክት ተምሳሌት ነው። ስለዚህ ይህ ቀን በዘሩባቤል፥ በዕዝራና በነህምያ መሪነት አይሁድ ከምርኮ የሚመለሱበትን ጊዜ ስለሚጨምር የበረከት ጊዜም ነበር። እንደዚሁም በዘመናት መጨረሻ የእስራኤል ሕዝብ ሁሉ በአካል ወደ ምድራቸው ተመልሰው፥ ከመንጻታቸው የተነሣ በረከቶችን የሚቋደሱበትና አይሁድ ሁሉ እግዚአብሔርን በእውነት የሚያመልኩበትን ታላቁን የጌታ ቀን የሚያመለክት ነበር።  2. አሕዛብም የጌታን ቀን ምንነት ያውቃሉ። አሦርና ሌሎች አሕዛብ እግዚአብሔር ፍርድን አምጥቶባቸዋልና በታሪክ ያንን የፍርድ ቀን ያውቃሉ። በዚህ ዓይነት አሦር በባቢሎን ተደመሰሰች፤ ፍልስጥኤም፥ ሞዓብ፥ አሞንና ኩሽም ጠፉ። እነዚህ ጥፋቶች አሕዛብ ሁሉ የእግዚአብሔርን ፍርድ የሚቀበሉበት የመጨረሻው ታላቁ የጌታ ቀን ምሳሌዎች ነበሩ።  ያ ቀን ለአይሁድ እንደሆነው ሁሉ ለአሕዛብም የበረከት ቀን ይሆናል። እግዚአብሔርን ለማክበር የሚመለሱ አሕዛብም በረከትን ያገኛሉ።  3. ፍጥረታት ሁሉ የጌታን ቀን ያውቃሉ። እንስሳት፥ ከዋክብት፥ ፀሐይ ወዘተ. ሁሉም እግዚአብሔር በፍርድ በሚሠራበት ቀን የፍርዱ ተካፋዮች ይሆናሉ። ይህም ምድርን በተለያዩ ጊዜያት በሚመቱ የተፈጥሮ አደጋዎች በከፊል ታይቷል። ይሁን እንጂ በተለይ የሚታየው በዘመናት ፍጻሜ ነው። የዮሐንስ ራእይ ፍጥረታት በተለያየ ሁኔታ የሚመቱባቸዉን መንገዶች በግልጽ ያሳያል። ያ ቀን የሚያበቃው እግዚአብሔር አሁን ያሉትን ሰማይና ምድርን በእሳት ሲያጠፋና አዲስ ሰማይና ምድር ሲፈጥር ይሆናል (2ኛ ጴጥሮስ 3፡10፤ ራእይ 21፡1)። የውይይት ጥያቄ፥ 2ኛ ጴጥሮስ 3፡10-13 አንብብ። ሀ) ስለ ጌታ ቀን የሚኖረን ግልጽ ግንዛቤ፥ ዛሬ የምንኖረውን ኑሮ መለወጥ የሚገባው በምን መንገዶች ነው? ለ) ስለ ጌታ ቀንና በዚህም ምክንያት እንዴት መኖር እንዳለባቸው የቤተ ክርስቲያንህን አባላት ለማስተማር ዐቅድ።  የውይይት ጥያቄ፥ ሶፎንያስ 1-3 አንብብ። ሀ) እግዚአብሔር ይሁዳ ይፈረድባታል ያለው ለምንድን ነው? ለ) በጌታ ቀን የሚፈጸሙ ሁኔታዎች የሚነኳቸውን ነገሮች ዝርዝር። ሐ) በጌታ ቀን እንደሚሆኑ ተስፋ የተሰጡ በረከተች ምንድን ናቸው?  1. በሁሉም ላይ ስለሚደርስ ፍርድ የተነገረ አጠቃላይ መልእክት (ሶፎንያስ 1፡1-3) የሶፎንያስ መልእክት ጠንከር ያለና አስደንጋጭ ነበር። ሶፎንያስ በምድር ላይ ስለሚሆነው ታላቅ ጥፋት በመናገሩ፥ ሰዎች ራሳቸውን በመመርመር በእግዚአብሔር ፊት ትክክለኛ መሆናቸውን ለማረጋገጥ ይጥራሉ የሚል እምነት አድሮበት ነበር። በራሳቸው ረክተው በመኖራቸው እንዲደነግጡና ካሉበት ሁኔታ እንዲወጡ ለማድረግ አስቦ ነበር። ሶፎንያስ የዘመን መጨረሻን አሻግሮ በማየት ነገሮች ሁሉ እንዴት በእግዚአብሔር እንደሚዳኙ ሰፋ አድርጎ አሳይቷል።  2. በጌታ ቀን በይሁዳ ላይ የሚመጣው ፍርድ (ሶፎንያስ 1፡4-18) ቀጥሎ ሶፎንያስ ወደ ይሁዳ ዞረ። የእግዚአብሔርን ፍርድ ሊያመጣባቸው ወዳለው ወደ ይሁዳ ኃጢአት አመለከተ። የጣዖት አምልኮ በእጅጉ ተንሰራፍተ ነበር። ሕዝቡ እግዚአብሔርን አልፈለጉም፤ ወይም ከኃጢአታቸው ንስሐ አልገቡም። መሪዎች በኃጢአት ይኖሩ ነበር። ስለዚህ እግዚአብሔር ፍርድ እንደሚያመጣና የይሁዳ ምድር እንደምትደምሰስ ተናገረ። ይህም ከ40 ዓመታት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ በባቢሎናውያን አማካይነት ተፈጸመ።  3. በጌታ ቀን በአሕዛብ ሁሉ ላይ የሚመጣው ፍርድ (ሶፎንያስ 2፡1-3፡8) እግዚአብሔር ንስሐ እንዲገቡ ዕድል ሳይሰጥ በሰዎች ላይ አይፈርድም። ሶፎንያስ ወደ እግዚአብሔር እንዲመለሱና በዚያን ቀን ከሚገለጠው ቁጣ እንዲያመልጡ ሕዝቡን፥ በተለይም አይሁድን አጥብቆ ጠይቆአቸው ነበር። ሶፎንያስ በዙሪያው ያሉትን አንዳንድ አሕዛብና መንግሥታት በመመልከት፥ እግዚአብሔር በእነርሱም ላይ እንደሚፈርድ አመለከተ። እነዚህ የአሕዛብ መንግሥታት በይሁዳ ላይ ችግር የፈጠሩ ነበሩ። መደምሰስና መጥፋት ብቻ ሳይሆን አንድ ቀን የእነዚህን አሕዛብ ምድር አይሁድ ይወርሱታል። 4. በጌታ ቀን የሚመጡ በረከቶች (ሶፎንያስ 3፡9-20) የነቢያት መልእክት ብዙ ጊዜ የሚጠቃለለው፥ በፍርድ ሳይሆን በማበረታቻ ወይም በማጽናኛ ቃል ነበር። ሶፎንያስ ስለ መጪው የጌታ ቀን በድጋሚ ይናገራል። በዚህ ጊዜ ግን የሰዎች ክፋት አንድ ቀን እንደሚወገድ ይናገራል። ከናፍርት ለአምልኮ ይነጻሉ። ሰዎች ለእግዚአብሔር ይታዘዛሉ። በተበተኑት አይሁድ መካከል ትሑታን የነበሩትና በእግዚአብሔር የሚያምኑት ሰዎች ወደ አገራቸው ይመለሳሉ። እግዚአብሔር በእነርሱ ደስ ይለዋል። እነርሱም በሁሉ ይከበራሉ። የውይይት ጥያቄ፦ ሀ) በትንቢተ ሶፎንያስ ውስጥ የሚገኙትን ጠቃሚ የሆኑ መንፈሳዊ ትምህርቶች ዘርዝር ለ) የቤተ ክርስቲያን አባሎች በሙሉ እነዚህን ትምህርቶች ማወቅ የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው? (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡) የመመዘኛ ጥያቄዎችን ለማግኘት ከታች ያለውን ሊንክ (መስፈንጠሪያ) ይጫኑ፡፡

የትንቢተ ሶፎንያስ ዓላማ እና ዐብይ ትምሕርት Read More »

ትንቢተ ሶፎንያስ መግቢያ

የውይይት ጥያቄ፥ ሶፎንያስ 1፡12 አንብብ። ሀ) እግዚአብሔር እቀጣለሁ ያለው ምን ዓይነት ሰዎችን ነበር? ለ) ሰዎች ስለ እግዚአብሔር የነበራቸው የተሳሳተ አመለካከት ምን ነበር? ለእግዚአብሔር ሕዝብ እጅግ አደገኛ ከሆኑ ነገሮች ዋናው በእግዚአብሔር ላይ በግልጽ ማመፅ አይደለም። ወደ ሐሰት ትምህርቶች ወይም ሃይማኖቶች መለወጥም አይደለም። የእግዚአብሔር ሰዎች በራሳቸው መርካታቸው እንጂ። ሶፎንያስ ባገለገለበት ዘመን በይሁዳ ላይ ችግር ከፈጠሩት ኃጢአቶች አንዱ ይህ ነበር። በዮሐንስ ራእይ፥ እግዚአብሔር የሉዶቅያን ቤተ ክርስቲያን፥ ባላት መንፈሳዊ ሕይወት በመርካቷና በራድ ወይም ትኩስ ባለመሆኗ ሲገሥጻት እንመለከታለን (ራእይ 3፡14-20)። ቤተ ክርስቲያን ወይም ክርስቲያን ለብ የሚለውና በራሱ የሚረካው ለምንድን ነው? በርካታ ምክንያቶች አሉ፡- በመጀመሪያ፥ ቤተ ክርስቲያን ለብ የምትለው በግል ወይም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በሚደረግ አምልኮ ሁልጊዜ አዲስና ሕያው በሆነ መንገድ ከማምለክ ይልቅ የአምልኮ ሥርዓቶችን ብቻ የመከተል አዝማሚያ ሲኖር ነው። ሁለተኛ፥ ቤተ ክርስቲያን በራሷ የረካች የምትሆነው እርስዋ ወይም ክርስቲያን እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ሌሎች ሰዎች ከመድረስ ይልቅ፥ ለራሳቸው ፍላጎትና ምቾት አጥብቀው ማሰብ ሲጀምሩ ነው። በቤተ ክርስቲያን ወይም በእያንዳንዱ ክርስቲያን ሕይወት ውስጥ ራስ ወዳድነት ሲንሰራፋ በመንፈሳዊ ሕይወት ረገድ በራስ መርካትን ያስከትላል። ሦስተኛ፥ የጠፉትን የመፈለግና በወንጌል የመድረስ ፍላጎት ሲጠፋ ነው። ይህ የወንጌላውያን እንጂ የእኛ ሥራ አይደለም ብሎ ማሰብ ቀላል ነው። ወይም በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ ልንመለከታቸው የሚገቡን ብዙ ችግሮች ስላሉ፥ የጠፉትን ለመፈለግም ሆነ ለመድረስ ጊዜና ገንዘብ የለንም ብሉ ማሰብ ቀላል ነው። አራተኛ፥ በመንፈሳዊ ሕይወታችን በመልካም ሁኔታ ላይ እንደምንገኝ በማሰብ ስለ እግዚአብሔር ባለን እውቀት ያለማቋረጥ ማደግ እንደማያስፈልገን ስናስብ በራስ መርካት ይመጣል። ቤተ ክርስቲያን ወይም ክርስቲያን በራሱ መርካት ሲጀምር፥ በመንፈሳዊ ሕይወቱ ምውት ወደ መሆን ያዘግማል። ምክንያቱም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ መንፈሳዊ ሕይወት ስለማይኖር ሰዎች ወደ ሌላ ቤተ ክርስቲያን ወይም እምነታቸውን ትተው ወደ ሌላ ሃይማኖት ይሄዳሉ። በራስ ከመርካት የተነሣ ክርስቲያን እግዚአብሔር አንድ ቀን እንደሚፈርድበት ይረሳል። ወዲያውኑ በኃጢአት ወጥመድ ይያዝና ከዚያ በማምለጥ ለእግዚአብሔር እንደገና መኖር በጣም አስቸጋሪ ከሚሆንበት ሁኔታ ውስጥ ይገባል። የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ክርስቲያን ወይም ቤተ ክርስቲያን በራሳቸው ወደ መርካት ሊመጡ የሚችሉባቸውን ሌሎች ምክንያቶች ዘርዝር። ለ) በራስ የመርካት ሌሎች ውጤቶችን ዘርዝር። ሐ) ይህ ነገር በሕይወትህ፥ በሌላ ሰው ሕይወት ወይም በቤተ ክርስቲያን እንዴት እንደተፈጸመ አንዳንድ ምሳሌዎችን ስጥ። መ) በመንፈሳዊ ረገድ በራስ መርካትን በሚመለከት ፈውስ የሚሆኑ አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው? የይሁዳ ሕዝብ በራስ ከመርካት የተነሣ ቀስ በቀስ በኃጢአት ወደቁ። አይሁድ እግዚአብሔር ለረጅም ጊዜ ስለታገሣቸውና ፈጥኖ ስላልፈረደባቸው እነርሱ ስለሚያደርጉት ነገር እግዚአብሔር ይገደው እንደሆነ መጠየቅ ጀመሩ። እግዚአብሔር ሕዝቡን ለማስጠንቀቅ መልእክተኞቹን ነቢያትን በትዕግሥት ይልካቸው ነበር። ይሁን እንጂ ሕዝቡ አንዳንድ ጊዜ ድርጊታቸውን ለጊዜው ለመለወጥ ፈቃደኞች ቢሆኑም፥ ልባቸውን ለመለወጥ አልፈለጉም ነበር። እገዳው እንደተነሣላቸው ፈጥነው ወደ ጣዖት አምልኮ ይመለሱ ነበር። በመጨረሻ እግዚአብሔር ሶፎንያስን ጠራ። ሶፎንያስ የእግዚአብሔር የፍርድ ጊዜ ደርሶአል ሲል አወጀ። እግዚአብሔር ሕዝቡ በራሳቸው በመርካታቸውና በኃጢአታቸው ምክንያት እንደሚቀጣቸው ተናገረ።  የትንቢተ ሶፎንያስ ጸሐፊ በሶፎንያስ 1፡1 የእግዚአብሔር ቃል ወደ ሶፎንያስ እንደመጣ ተጽፏል። ይህ ማለት የትንቢተ ሶፎንያስ ጸሐፊ ሶፎንያስ ነው ማለት ነው። ስለ ሶፎንያስ የምናውቀው ነገር ብዙ ባይሆንም፥ አመጣጡ ከንጉሣዊ ዘር ይመስላል። በሶፎንያስ 1፡1 የተጠቀሰው ሕዝቅያስ የተባለው ሰው ንጉሥ ሕዝቅያስ ከሆነ፥ ሶፎንያስ የንጉሥ ሕዝቅያስ የልጅ ልጅ ልጅ ነው ማለት ነው። ይህም ማለት ሶፎንያስ ባገለገለበት ዘመን በይሁዳ ነግሦ ከነበረው ከንጉሥ ኢዮስያስ ጋርም ይዛመዳል ማለት ነው። ሶፎንያስ ያደገው በኢየሩሳሌም ሳይሆን አይቀርም። በሰው ሁሉ ዘንድ የተከበረ ያደረገውም የንጉሥ ዘር መሆኑ ይሆናል። በሚገባ የተማረና በይሁዳ ከሚኖሩ ሁሉ የተሻለ ቤተሰብ ውስጥ የነበረ ሰው ነው። ይህ ማለት ግን ሶፎንያስ ስለ ሕዝቡ ወይም ዘመዶቹ ስለሆኑት ንጉሣውያን ቤተሰብ ኃጢአት ግድ አልነበረውም ማለት አይደለም። የሕዝቡን ኃጢአት በመቃወም በድፍረት ይናገር ነበር። በድጋሚ የምንመለከተው እግዚአብሔር በሁሉም ዓይነት ሰዎች እንደሚጠቀም ነው። እንደ ሚክያስና አሞጽ ባሉ ተራ ሰዎች ይጠቀም ነበር። እንደ ሶፎንያስ ባሉ ሀብታምና የተማሩ ሰዎችም ተጠቅሟል። ሶፎንያስ ያገለገለው በኢዮስያስ ዘመነ መንግሥት እንደ ነበረ ይነገራል (640-609 ዓ.ዓ.)። ኢዮስያስ ሥልጣን የጨበጠው ከክፉዎቹ ነገሥታት ከምናሴና ከአሞን ቀጥሎ ገና የስምንት ዓመት ልጅ እያለ ነበር። ኢዮስያስ ከስምንት ዓመት በኋላ የአሥራ ስድስት ዓመት ልጅ ሲሆን፥ የሕዝቡን ሃይማኖት ማደስ ጀመረ። ሶፎንያስ ያገለገለው በኢዮስያስ ዘመነ መንግሥት የመጀመሪያዎቹ ዓመታት ሳይሆን አይቀርም። ኢዮስያስ በነገሠበት ዘመን ሁለት የተሐድሶ እንቅስቃሴዎች ተካሂደዋል። አንዱ በ632 ዓ.ዓ. አካባቢ የነበረው ሲሆን፥ ሌላው ደግሞ በ622 ዓ.ዓ. ገደማ የነበረው ነው። ሶፎንያስ ከእነዚህ ሁለት የተሐድሶ ጊዜያት በአንዱ ሳይሠራ አልቀረም። ነገር ግን ዋና የአገልግሎት ዘመኑ 627 ዓ.ዓ. አካባቢ ሳይሆን አይቀርም። ሶፎንያስ በንጉሥ ኢዮስያስ ሕይወት ላይ አዎንታዊ ተጽዕኖ በማሳደር ባካሄደው ተሐድሶ ረድቶት እንደሆነ የምናውቀው ነገር የለም። በሥልጣኑና ከንጉሡ ጋር በነበረው ግንኙነት ረድቶት ሊሆን ይችላል። የሚያሳዝነው ግን የሕዝቡ ንስሐ ውጫዊ ስለነበረ ንጉሥ ኢዮስያስ እንደሞተ ወደ ክፉ ሥራቸው ተመለሱ። በዚህ ጊዜ በይሁዳ ያገለግል የነበረው ነቢይ ሶፎንያስ ብቻ አልነበረም። ኤርምያስ፣ ናሆምና ምናልባት ዕንባቆምም አገልግለዋል። ምርኮው ከመፈጸሙ አስቀድሞ በነበረው ጊዜ እግዚአብሔር ብዙ ነቢያትን በመላክ የኃጢአታቸውን ውጤቶች በመንገር ሕዝቡን እንዲያስጠነቅቋቸው አድርጎ ነበር። ሕዝቡን ለመለወጥና እግዚአብሔር የተናገረውን ፍርድ ለማስለወጥ ግን አልቻሉም።  የትንቢተ ሶፎንያስ ታሪካዊ ሥረ-መሠረት  ሶፎንያስ ይኖር የነበረው የአሦር መንግሥት እየከሰመ የባቢሎን መንግሥት ግን እያቆጠቆጠ ባለበት የሽግግር ወቅት ነበር። ከጥቂት ዓመታት በኋላ የይሁዳ ሕዝብ በባቢሎን ቁጥጥር ሥር በመውደቅ፥ በመጨረሻ በ586 ዓ.ዓ. ሊደመሰሱ ተዘጋጅተው ነበር። የአሦር መንግሥት በመካከለኛው ምሥራቅ ፖለቲካዊ ገጽታ ላይ የበላይነት ተጽዕኖን በማሳደር ለብዙ ዓመታት ቆይቷል። በዚያን ጊዜ የነበሩት መሪዎች ግን ብርቱዎች ስላልነበሩ በመንግሥቱ ሁሉ ውስጥ እየተባባሰ የሚሄድ ዓመፅ ነበር። የመጨረሻው የአሦር ዋና ንጉሥ አሱርባኒፓል ከሞተ በኋላ የአሦር መንግሥት መፈረካከስ ጀመረ። ባቢሎን ከአሦር ነፃ መውጣቷን አወጀች። በኋላም ባቢሎን ሜዶንን ከመሳሰሉ ሌሎች አገሮች ጋር በመተባበር አሦርን ማጥቃትና ማውደም ጀመረች። ይህ ከመሆኑ አስቀድሞ ሶፎንያስ የአሦርን ውድቀት አመልክቶ ነበር (ሶፎንያስ 2፡13-15)። ለጥቂት ዓመታት ይሁዳ ከውጭ መንግሥታት አንጻራዊ ሰላም አግኝታ ነበር። ባቢሎን በሰሜን በኩል ግዛቷን እያስፋፋችና ተጽዕኖዋን እያሳደገች ብትሄድም፥ እስካሁን ድረስ ወደ ከነዓን አልመጣችም ነበር። በዚህ በተገኘው ሰላም ንጉሥ ኢዮስያስ በይሁዳ ሕዝብ መካከል መንፈሳዊ ተሐድሶ ለማካሄድ ችሎ ነበር። የንጉሥ ኢዮስያስ አያት የነበረው ንጉሥ ምናሴ በይሁዳ ከገዙት እጅግ ክፉ መሪዎች አንዱ የነበረ ሲሆን፥ ከ50 ዓመታት በላይ ነግሦአል (697-642 ዓ.ዓ.)። ምናሴ ወደ ኢየሩሳሌም አዳዲስ የጣዖት አምልኮ አመጣ። በውስጡ ጣዖትን በማኖር ቤተ መቅደሱን አረከሰ። የገዛ ልጁንም ለጣዖት መሥዋዕት አድርጎ አቀረበ። ይህ ክፉ ንጉሥ በነገሠባቸው 50 ዓመታት ይሁዳን ልታንሰራራ ወደማትችልበት መንፈሳዊ አዘቅት ውስጥ ከቷት ነበር። በእርሱ ዘመነ መንግሥት የነበረው ትውልድ በአጠቃላይ የሚያውቀው ነገር ቢኖር የተደባለቀውን የበአልና የእግዚአብሔር አምልኮ ነበር። በዘመነ መንግሥቱ መጨረሻ ገደማ ምናሴ ተማርኮ ወደ አሦር ተወሰደና ሳይለቀቅ ለጥቂት ዓመታት ኖረ። በአሦር እያለ ልቡ ተለወጠና ወደ ጌታ ተመለሰ። ምናሴ ንስሐ ቢገባም እንኳ የይሁዳን ሕዝብ መንፈሳዊ ሕይወት ለመለወጥ ፈጽሞ አልቻለም። እርሱ ሲሞት ልጁ አሞን በምትኩ ነገሠ። አሞን ምናሴ ከነገሠባቸው የመጀመሪያ ዓመታት እንደነበረው በክፋት ሄደ። በልጅነቱ የአባቱን ክፋት ተመልክቶ ስለነበር እግዚአብሔርን ለማክበር አልቻለም። ስለሆነም፥ እግዚአብሔር እንዲነግሥ የፈቀደለት ለሁለት ዓመታት ብቻ ነበር። አሞን ተገደለና ትንሽ ልጁ ኢዮስያስ ነገሠ። የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ወላጆች በልጆቻቸው ላይ የሚያሳድሩት ተጽዕኖ ልጆች በሚያድጉ ጊዜም የሚቀጥለው በምን መንገድ ነው? ለ) ክርስቲያን ወላጆች ልጆቻቸው ትልልቆች እስኪሆኑ ድረስ ከመጠበቅ ይልቅ፥ ገና ትንንሾች እያሉ እግዚአብሔርን እንዲፈሩና ለእርሱ እንዲታዘዙ ማስተማር የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው? ኢዮስያስ በይሁዳ ሕዝብ መንፈሳዊ ሕይወት ለውጦችን ለማምጣት የሞከረ ቢሆንም፥ አብዛኛዎቹ ለውጦች ውጫዊ እንጂ ውስጣዊ አልነበሩም። በእርሱ ተጽዕኖ ሕዝቡ ጣዖታትን ለማጥፋትና

ትንቢተ ሶፎንያስ መግቢያ Read More »