ትንቢተ ዕንባቆም

የትንቢተ ዕንባቆም ዓላማ እና ዋና ዋና ትምሕርቶች

የትንቢተ ዕንባቆም ዓላማ ትንቢተ ዕንባቆም እግዚአብሔር በባቢሎናውያን አማካይነት በይሁዳ ላይ ስለሚያመጣው ቅጣት የሚተነብይ ቢሆንም፥ ዓላማው የእግዚአብሔርን ቅንና ትክክለኛ ፍርድ መመርመር ነው። ትንቢተ ዕንባቆም የእግዚአብሔርን መንገድ ለሕዝቡ እንደሚገልጡ የጥበብ መጻሕፍት ዓይነት ነው። ትንቢተ ዕንባቆም ከመጽሐፈ ኢዮብ የሚመሳሰልም የሚለያይም ነው። የመጽሐፈ ኢዮብ ዋና የፍልስፍና ጥያቄ «ጻድቅ መከራን በሚቀበልበት ጊዜ የእግዚአብሔር ትክክለኛ ፍርድ አለን?» የሚል ነው። በዚያ ስፍራ የተሰጠው መልስ፥ ሰይጣን ጻድቃንን እንዲፈትን እግዚአብሔር ይፈቅዳል የሚል ነበር። ጻድቃን የተከበረውን የእግዚአብሔር ኃይልና ከእግዚአብሔር ጋር ሲወዳደሩ የቱን ያህል ኢምንት እንደሆኑ በማስታወስ በፈተናቸው በእግዚአብሔር መታመን አለባቸው። በትንቢተ ዕንባቆም ውስጥ ሁለት የፍልስፍና ጥያቄዎች ተመልሰዋል፡- 1. «ሕዝቦችና መንግሥታት በክፋት ሲሞሉና ክፉ ሰዎች ሲበለጽጉ የእግዚአብሔር ቅንና ትክክለኛ ፍርድ አለን?» እግዚአብሔር ለዚህ ጥያቄ የሰጠው መልስ፡- እርሱ በራሱ ጊዜና በራሱ መንገድ በአሕዛብ መንግሥታት ላይ ይፈርዳል። ይሁዳ ቅጣት የሚፈጸምባት በባቢሎን ነው የሚል ነበር።  2. «ጻድቁ እግዚአብሔር ከይሁዳ ይልቅ ክፉና ጠማማ የሆነውን ሕዝብ እንዴት ለቅጣት መሣሪያ አድርጎ ይመርጣል?»  እግዚአብሔር ለዚህ ጥያቄ የሰጠው መልስ ሁለት ክፍሎች አሉት፡- ሀ. እግዚአብሔር ታላቅና ኃይለኛ ነው። ሰው ስለ እግዚአብሔር የአሠራር መንገዶች የመጠየቅ መብት የለውም። ይልቁንም ጻድቅ ግራ በተጋባና እርግጠኛ ባልሆነበት ጊዜ በእግዚአብሔር ላይ ያለውን እምነት እንኳ መጠበቅ አለበት። ጻድቅ ሰው የእግዚአብሔርን መንገዶች ምንነት በማይረዳበት ጊዜም እንኳ የታማኝነትና የጽናት ሕይወቱን ይጠብቃል። ለ. እግዚአብሔር ኃጢአተኞችን በራሱ ጊዜ ለመቅጣት ሌሎችን ይጠቀማል። እግዚአብሔር ይሁዳን ለመቅጣት በባቢሎን መንግሥትና ሕዝብ ከተጠቀመ በኋላ በተራቸው ይቀጣቸዋል። እግዚአብሔር ሕዝቡን ለመቅጣት የተጠቀመበት ሰው ወይም መንግሥት መልካም ነው ማለት አይደለም። በእግዚአብሔር እጅ እንዳሉ መሣሪያዎች ናቸው። ስለዚህ ከተጠቀመባቸው በኋላ ሊጥላቸው ወይም እንደየአስፈላጊነቱ እነርሱን ደግሞ ሊቀጣቸው ይችላል። የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ክርስቲያኖች እነዚህን እውነቶች ማወቅና መጠቀም የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው? ለ) በዚህ ዘመን የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች እግዚአብሔርን ዘወትር የሚጠይቁባቸውን ነገሮች ዝርዝር። ሐ) እነዚህ እውነቶች እንዴት ይረዷቸዋል? ዕንባቆም ተገቢውን ትምህርት እንዳገኘ ከመጨረሻ ጸሎቱ እንረዳለን። ባይረዳውም እንኳ የእግዚአብሔርን መንገድ ተቀብሏል። የእግዚአብሔርን ትክክለኛ ፍርድ መጠራጠሩን አቁሞ ነበር። በዚህ ፈንታ እግዚአብሔር ክፉዎችን እንደሚቀጣና ጻድቃንን እንደሚባርክ በሰጠው ዋስትና ላይ አርፎ ነበር። እግዚአብሔር ኃጢአተኞችን መቼና እንዴት መቅጣት እንዳለበት መወሰን የዕንባቆምም ሆነ የእኛ ኃላፊነት አይደለም። የዕንባቆምም ጸሎት ሊመጣ ካለው መዓት አንጻር የተጸለየ አስደናቂ የእምነት ጸሎት ነው። እግዚአብሔር በሕዝቡ ላይ በሚፈርድበት ጊዜ ምሕረቱን ከቶ እንደማይረሳ ጸለየ። በተጨማሪ በእጁ የሚገኘው ማንኛውም ሥጋዊ በረከት ሁሉ ቢወሰድ እንኳ፥ በእግዚአብሔር ብርታት ላይ መደገፉንና በእርሱም መታመኑን ለመቀጠል መወሰኑን ገለጸ።  የትንቢተ ዕንባቆም ዋና ዋና ትምህርቶች 1. እግዚአብሔር ክፉዎችን በኃጢአታቸው ምክንያት ይቀጣቸዋል። ብዙውን ጊዜ ግን ክፉዎች በኃጢአታቸው የማይቀጡ ይመስላል። እንዲያውም በኃጢአታቸው ምክንያት ሲበለጽጉና ሲከናወንላቸው ስለሚታዩ በኃጢአታቸው የተባረኩ ይመስላሉ። ክፉዎችና ኃጢአተኞች ሲሳካላቸው፥ ከእግዚአብሔር ሕዝብ አብዛኛዎቹ መከራ ይቀበላሉ። ይህም ለመበልጸግ ሲሉ ኃጢአተኞች የሚጠቀሙባቸውን መንገዶች ክርስቲያኖችም እንዲጠቀሙበት ይገፋፋቸዋል። ይህን ሲያደርጉ ግን እግዚአብሔር ክፉዎችን እንደሚቀጣ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረውን ትምህርት ዘንግተዋል ማለት ነው። ቅጣቱ እኛ በምንፈልገው ፍጥነትና መንገድ ቢይሆንም፥ ዳሩ ግን እግዚአብሔር ኃጢአተኞችን በኃጢአታቸው ምክንያት እንደሚቀጣ ቃል ይገባል። ስለዚህ ኃጢአተኞች አሁን ስላልተቀጡ እኛም ብንሆን አንቀጣም ብለን በማሰብ፥ እንደ እነርሱ ለመሆን መፈተንና ለፈተናው መንገድ መክፈት የለብንም። የእግዚአብሔር ትክክለኛ ፍርድ ብዙ ጊዜ ቢዘገይም መፈጸሙ ግን የማይቀር ነው። የይሁዳና የአሦር መንግሥታት እግዚአብሔር በእነርሱ ላይ ከመፍረዱ በፊት ለብዙ ዘመናት ቆይተዋል። ባቢሎናውያን ግን በእግዚአብሔር ሳይቀጡ የቆዩት ለ70 ዓመታት ብቻ ነው። የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) አንዳንድ ክርስቲያኖች፥ የማያምኑ ሰዎች ስለ ኃጢአታቸው ባለመቀጣታቸው ምክንያት እነርሱም እንደማይቀጡ በማሰብ፥ በኃጢአት የሚወድቁት እንዴት እንደሆነ ግለጽ። ለ) ይህን በሚያደርጉበት ጊዜ የዘነጉት ነገር ምንድን ነው? የዕንባቆም ትምህርት ማስጠንቀቂያ ሊሆናቸው የሚችለው እንዴት ነው? 2. ክፉዎችና ኃጢአተኞች ሲበለጽጉ ወይም ጻድቃን መከራ ሲቀበሉ፥ በታማኝነት ጸንቶ መኖር የጻድቃን ኃላፊነት ነው። እጅግ ታዋቂ ከሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች አንዱ ዕንባቆም 2፡4 ነው። ይህም በአዲስ ኪዳን እግዚአብሔር ሰውን የሚያጸድቀው በሥራ ሳይሆን በእግዚአብሔር ላይ ባለው እምነት መሆኑን ለመገልጥ በተደጋጋሚ ተጠቅሶ እናያለን (ሮሜ 1፡ 17፥ ገላትያ፤ 3፡11፤ ዕብራውያን 10፡38)። ይሁን እንጂ በትንቢተ ዕንባቆም የተሰጠው ትኩረት በጣም የተለየ ነው። ዕንባቆም የእግዚአብሔር ምርጦች የሆኑት ጻድቃን በምንም ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ቢሆኑ፥ በእግዚአብሔር መታመን እንዳለባቸው ያስተምራል። ክፋትና ኃጢአት ሲስፋፉ፥ ምን ክፉዎች ከመቀጣት ይልቅ እየበለጸጉ የሄዱ ሲመስሉ፥ ጻድቃን ሊያስታውሱት የሚገባው የተጠሩት በእግዚአብሔር ፊት የጽድቅና የቅድስና ሕይወት ለመኖር እንደ ሆነ ነው። ስለሆነም የቅድስና አካሄዳቸውን መጠበቅ አለባቸው። እግዚአብሔር አንድ ቀን ኃጢአተኞችንና ጠማሞችን እንደሚቀጣ ማስታወስ አለባቸው። ይህ ቅጣት በምድር እያሉ ሊደርስባቸው ወይም ላይደርስባቸው ቢችልም በመጨረሻው ዘመን ግን የማይቀር ነው። ደግሞም ጻድቃን አንዳችም ነገር ሳያጠፉ መከራ በሚቀበሉበት ጊዜ በእግዚአብሔር ላይ ያላቸውን እምነት መጠበቅ አለባቸው። እግዚአብሔር ይሁዳን ለመቅጣት ባቢሎንን በተጠቀመ ጊዜ በይሁዳ በርካታ ጻድቃን ሰዎች ነበሩ፤ ዕንባቆም፥ ኤርምያስ፥ ሶፎንያስና ሌሎችም ብዙዎች ነበሩ። ቅጣቱ በሚፈጸምበት ጊዜ መከራቸውን ያዩ ነበር፡፡ በእግዚአብሔር ላይ ማጉረምረም ለእነርሱ ቀላል ነበር። «ለእግዚአብሔር ታማኝ ሆኜ እያለሁ መከራን ከተቀበልሁ፥ በእርሱ ላይ ያለኝን እምነት እክዳለሁ» ብሎ ማሰብ ቀላል ነበር። ዳሩ ግን ዕንባቆም የሚያስተምረን እምነታችን በእግዚአብሔር እንጂ በዙሪያችን ባሉ ሁኔታዎች ላይ መመሥረት እንደሌለበት ነው። ብዙ ክርስቲያኖች በእግዚአብሔር ለመታመን ፈቃደኞች የሚሆኑት ገንዘብ እስካገኙ፥ ፈውስ እስከተሰጣቸውና የተለያዩ ሥጋዊ በረከቶችን እስከተቀበሉ ድረስ ብቻ ነው። የሚያሳዝነው ደግሞ በእግዚአብሔር ካመንን ሁልጊዜ ባለጸጎች እንሆናለን ወይም ከበሽታችን እንፈወሳለን በማለት የሐሰት ትምህርት የሚያስተምሩ ብዙ ክርስቲያኖች መኖራቸው ነው። ኢዮብ ከፍ ያለ ሥቃይ ቢደርስበትም እንኳ በእግዚአብሔር ላይ የነበረውን እምነቱን ጠብቋል። ዕንባቆም ደግሞ መንጋውንና የእርሻ ፍሬውን ሁሉ በማጣት፥ ረሃብ ምናልባትም ሞት እንደሚያጋጥመው ቢያውቅም እንኳ እምነቱ በእግዚአብሔር ላይ ነበር። ሐሤት የሚያደርገው በእግዚአብሔር ላይ እንጂ በሁኔታዎች ላይ አልነበረም። በሁኔታዎቹ ሁሉ ውስጥ ማለፍ እንዲችል ደግሞ እግዚአብሔር ኃይሉን ያድስለት ነበር። የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) አንዳንድ ክርስቲያኖች ሰው እውነተኛ እምነት ካለው ሀብታም ይሆናል ወይም አይታመምም እያሉ ሲያስተምሩ ሰምተሃልን? ለዚህ ትምህርት የሚጠቀሙባቸው ጥቅሶች የትኞቹ ናቸው? ለ) ትንቢተ ዕንባቆምን በመጠቀም መልስ የምትሰጣቸው እንዴት ነው? ሐ) ብዙ ክርስቲያኖች እግዚአብሔር እስከባረካቸው ድረስ ብቻ በእርሱ እያመኑ፥ መከራ ወይም ችግር በሚገጥማቸው ጊዜ ግን የሚክዱት ለምንድን ነው? መ) «ጻድቅ በእምነት ይኖራል» የሚለው ትምህርት ክርስቲያኖች ሊያስታውሱት የሚገባ እጅግ ጠቃሚ የሆነው እንዴት ነው? 3. እግዚአብሔር መንግሥታትን ስለ ክፉ ድርጊታቸው ይቀጣቸዋል። ከትንቢተ ዕንባቆም በግልጽ እንደምንመለከተው፥ እግዚአብሔር መልካምም ሆነ ክፉ መንግሥታትን ላደረጉት ነገር ተጠያቂዎች ያደርጋቸዋል። እግዚአብሔር የይሁዳን ሕዝብ ተጠያቂ አድርጎ ነበር። ኃጢአታቸው እጅግ ከፍተኛ ደረጃ ላይ በደረሰ ጊዜ ፍርዱን አመጣባቸው። እግዚአብሔር ስለ ክፋታቸው በአሦርና በባቢሎንም ላይ ፈርዷል። ማንኛውም ሰው ሆነ ሕዝብ ወይም መንግሥት ከእግዚአብሔር ፍርድ ማምለጥ አይችልም። ግለሰቦችም ሆኑ ሕዝቦች በብሔራዊ ደረጃ ለሚያደርጉት ድርጊት ተጠያቂዎች ናቸው። እግዚአብሔር ለእኛም ሆነ ለመንግሥታት የመምረጥ ነፃነት ሰጥቶናል። በዚህ ነፃ ምርጫችን ስለምንወስደው እርምጃ ሁሉ ግን እግዚአብሔር ይጠይቀናል። ልንቆጣጠር የምንችለው ምርጫችንን እንጂ ምርጣችን የሚያስከትላቸውን ነገሮች ወይም ውጤቶች አይደለም። የምርጫችን ውጤቶች በእግዚአብሔር እጅ ናቸው። መልካም ነገሮችን ከመረጥን (ከዘራን) መልካም ነገሮችን እናጭዳለን። ክፉ ነገሮችን ከመረጥን (ከዘራን) የክፉ ምርጫዎቻችንን ውጤቶች እናጭዳለን (ምሳሌ 11፡18፤ 22፡8፤ ገላትያ 6፡7-8)። በመጨረሻ ሁላችንም በሚፈርድብን በእግዚአብሔር ፊት እንቆማለን፤ እርሱም እንደየድርጊታችን ዋጋችንን ይሰጠናል ወይም ይቀጣናል።  የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ይህን የመጨረሻ ትምህርት ማስታወስ ለእኛ ጠቃሚ የሚሆነው ለምንድን ነው? ለ) ሰዎች ስለሚያደርጉአቸው ምርጫዎች ሁሉ እግዚአብሔር ተጠያቂዎች እንደሚያደርጋቸው ቢያስታውሱ የበለጠ ጥንቃቄ የተሞላ ምርጫ የሚያደርጉት እንዴት ነው? የውይይት ጥያቄ፥ ዕንባቆም 1-3 አንብብ። ሀ) ዕንባቆም የጠየቃቸው ሁለት ጥያቄዎች ምን ነበሩ? ለ) እግዚአብሔር የዕንባቆምን ጥያቄዎች የመለሰው እንዴት ነበር? ሐ) የዕንባቆም ጸሎት ዛሬ እኛም ብንጸልየው መልካም

የትንቢተ ዕንባቆም ዓላማ እና ዋና ዋና ትምሕርቶች Read More »

ትንቢተ ዕንባቆም መግቢያ

የውይይት ጥያቄ፥ የምትመለከተው ክፉ ተግባር ከመብዛቱ የተነሣ እጅግ ታክተህ እግዚአብሔር ይህንን ተግባር የፈጸመውን ሰው ወይም ሰዎች የማይቀጣው ለምን እንደሆነ ተደንቀህ ታውቃለህን? ሁኔታውን አብራራ። ምናልባት ሁላችንም በአንድ ወይም በሌላ ወቅት በጣም ብዙ ክፋት ተመልክተን በመደነቅ እግዚአብሔር ይህንን ነገር ለምን እንደማይቀጣው ጠይቀን ይሆናል። ዙሪያችንን ስንቃኝና ሰዎች ኃጢአት ሲሠሩ፥ ድሆች መጠቀሚያ ሲደረጉ ትክክለኛ ፍርድን በጉቦ የሚያጣምሙ ሰዎች ያለምንም ቅጣት ተዝናንተው ሊኖሩ መመልከት፥ ልባችንን በኃዘን ይሞላል። ዓለም በቅን ፍርድና በጽድቅ የምትሞላበትን ጊዜ በልባችን እንናፍቃለን። ክፋት እስካልተቀጣ ድረስ ይህ ቀን ሊመጣ እንደማይችልም እንገነዘባለን። በዚህ አንጻር እግዚአብሔር ክፋትን ለምን እንደማይቀጣና ለእግዚአብሔር ለመኖር አጥብቀው የሚፈልጉትን ሰዎች ለምን እንደማይባርክ በማሰብ እንደነቃለን። ነቢዩ ዕንባቆምም ከዚህ ጉዳይ ጋር ግብግብ ገጥሟል። የደም መፍሰስና ክፋት ያለ ቅጣት በዙሪያው ተንሰራፍቶ መመልከት ሰልችቶት ነበር። በመሆኑም ክፋትን በመቅጣት ጽድቁን እንዲገልጥ ወደ እግዚአብሔር ይጮህ ነበር፤ እግዚአብሔር የሚሰጠውን መልስ ግን አልጠበቀም ነበር። ትንቢተ ዕንባቆም የእግዚአብሔርን የጽድቅና የቅን ፍርድ ባሕርይ በሚመለከትበት ጊዜ ሊረዳ ያልቻላቸውን ነገሮች በሚመለከት ያቀረባቸውን የተለያዩ ጥያቄዎች የምናገኝበት ነው። ትንቢተ ዕንባቆም ከታናናሽ ነቢያት መጻሕፍት አንጻር ሲታይ ልዩ መጽሐፍ ነው። በመጽሐፉ ውስጥ አንዳንድ ትንቢቶች በመኖራቸው ከነቢያት መጻሕፍት ቢመደብም የበለጠ የሚመሳሰለው ከጥበብ መጻሕፍት ጋር ነው። ከመጽሐፈ ኢዮብ ጋር የሚመሳሰለው የእግዚአብሔርን ቅንና ትክክለኛ ፍርድ በዓለም ውስጥ ከሚገኙ ክፉ ነገሮች አንጻር የሚመለከት ስለሆነ ነው። የትንቢተ ዕንባቆም ጸሐፊ የዚህ መጽሐፍ ጸሐፊ ዕንባቆም ነው። እንደ ናሆም ሁሉ ስለ ዕንባቆምም የምናውቀው ነገር የለም። መጽሐፉ በዚህ ዘመን የነበሩት ነገሥታት እነማን እንደነበሩ አይገልጽም። ዕንባቆም የት ይኖር እንደነበር አልተጻፈም። ከአዋልድ መጻሕፍት መካከል አንዱ በሆነው «ቤልና ድራጎን» በተባለው (በአልና ክንፍ ያለውና እሳት የሚተፋ ፍጡር) መጽሐፍ ውስጥ ዕንባቆም በአንበሶች ጉድጓድ ውስጥ ተጥሉ ሳለ ዳንኤልን እንዴት እንደረዳው የሚናገር ታሪክ ብናገኝም፥ ታሪኩ እውነት አይመስልም። መጽሐፉ መቼ እንደተጻፈ ለማወቅ፥ አሁንም መጠቀም የምንችለው በመጽሐፉ ውስጥ ባለው መረጃ ነው። ትንቢተ ዕንባቆም የተጻፈበትን ጊዜ በሚመለከት ሁለት ዐበይት አመለካከቶች አሉ፡- 1. ትንቢተ ዕንባቆም የተጻፈው ባቢሎን ኢየሩሳሌምን በ605 ዓ.ዓ. ለመጀመሪያ ጊዜ ከማጥቃቷ በፊት ከ609-605 ዓ.ዓ. ነው። ይህም በንጉሥ ኢዮአቄም ዘመነ መንግሥት የመጀመሪያዎቹ ዓመታት ገደማ ነበር።  2. ትንቢተ ዕንባቆም የተጻፈው ከ640-626 ዓ.ዓ. ነው። ትንቢተ ዕንባቆም የባቢሎን የዓለም ኃያል መንግሥት መሆን ጨርሶ ያልተጠበቀ ነገር እንደነበር የሚያሳይ ይመስላል። የባቢሎን መንግሥት ገናና መሆን የጀመረው ባቢሎን ከአሦር ተለይታ ነጻ በሆነችበት በ626 ዓ.ዓ. ነበር። ስለዚህ ትንቢተ ዕንባቆም የተጻፈው ከዚህ ጊዜ በፊት ይመስላል። ይህ መጽሐፍ የተጻፈበት ነው ሊባል የሚችለው የመጨረሻው ጊዜ 615 ዓ.ዓ. ነው። ምክንያቱም የአሦር መንግሥት በባቢሎን ሙሉ በሙሉ የተሸነፈው በ612 ዓ.ዓ. ነበርና ከዚህ በኋላ ይህ ትንቢት ለዕንባቆም ምንም ትርጉም የሌለው ይሆናል።  ዕንባቆም ትንቢት የተናገረው ኢዮስያስ በይሁዳ ተሐድሶ ከመጀመሩ በፊት በነበረው የመጀመሪያው ዘመነ መንግሥቱ ገደማ እንደሆነ ዘመኑ ከሁሉም የሚሻል ይመስላል። ኢዮስያስ ገና በልጅነቱ ሆኖ የነገሠው በ640 ዓ.ዓ. ነበር። ያም በይሁዳ ፍትሕ ያልነበረበት ክፉ ጊዜ ነበር። የንጉሥ ኢዮስያስ ተሐድሶ የይሁዳን ሕዝብ መለወጥ የጀመረው ቆይታ በ626 ዓ.ዓ. ገደማ ነበር። ስለዚህ ዕንባቆም የኖረውና በአካባቢው ከነበረው የፍትሕ መዛባት ጋር የታገለው በንጉሥ ኢዮስያስ ዘመነ መንግሥት መጀመሪያ ገደማ ይመስላል። ምናልባት እርሱም የተሳተፈበት የንጉሥ ኢዮስያስ ተሐድሶ ሕዝቡን መለወጥ ሲጀምር እጅግ ሳይደሰት አልቀረም። ነገር ግን እግዚአብሔር ይሁዳን በእርሱ ዘመነ መንግሥት እንደሚደመስስ መናገሩን ያውቅ ነበር። ስለዚህ ሸክም በተጫጫነው ልብ የባቢሎንን ምጥቀት ከመመልከቱም፥ ኢየሩሳሌምም ስትደመሰስ ምስክር እንድነበረ አይጠረጠርም። ዕንባቆም ባገለገለበት ዘመን ሶፎንያስና ኤርምያስም አገልግለዋል።  የትንቢተ ዕንባቆም ሥረ መሠረት  የምናሴ ዘመነ መንግሥት (697-642 ዓ.ዓ.) የይሁዳ ሕዝብ በመንፈሳዊ ሕይወቱ ወደ መጨረሻው ዓዘቅት የወረደበት ጊዜ ነበር። ምናሴ ሕዝቅያስ ያካሄደውን ተሐድሶ ሁሉ ከመቅጽበት አበላሸ። የጣዖት አምልኮ እጅግ ተስፋፋ። ለጣዖት አምልኮ የሚሆን መሠዊያ አሠርቶ በቤተ መቅደሱ ውስጥ በማኖር የራሱን ልጅ መሥዋዕት አድርጎ አቀረበ። በሃይማኖታዊ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን፥ በሥነ-ምግባርና በማኅበራዊ ጉዳዮችም ሕዝቡ ፊታቸውን ከእግዚአብሔር በመመለሳቸው ማኅበራዊ ክፋት እጅግ የተለመደ ነገር ሆነ። ምናሴ ለመስበክና ሕዝቡን ስለ እግዚአብሔር ፍርድ ለማስጠንቀቅ የፈለጉትን ነቢያት ሁሉ አስገደለ። ይህም እግዚአብሔር በይሁዳ ላይ ፍርድ ለማምጣት እንዲወሰን አደረገው። ምናሴ በአሦር ላይ ለማመፅ በሞከረ ጊዜ፥ ተማርኮ ወደ አሦር ተወሰደ። በምርኮ ምድር ንስሐ ገባና ልቡ ተለወጠ፤ ከምርኮ ተለቆ ወደ ይሁዳ በተመለሰ ጊዜ ቀድሞ የፈጸማቸውን ክፉ ተግባራት ለማሻሻል ቢሞክርም አልቻለም። ከምናሴ ሞት በኋላ ልጁ አሞን ነግሦ ሁለት ዓመት ከገዛ በኋላ ተገደለ። የአሞን ልጅ ኢዮስያስ ግን ከአባቱ በተለየ መንገድ እግዚአብሔርን ተከተለ። ሥልጣን በያዘ ጊዜ ገና የስምንት ዓመት ልጅ ነበር። በይሁዳ መንፈሳዊ ተሐድሶን ለማምጣት የወሰነውና ርምጃ የወሰደው ከነገሠ ከአሥራ ስምንት ዓመት በኋላ በሃያ ስድስት ዓመቱ ነበር። ዕንባቆም ትንቢቱን የተቀበለው ይህ መንፈሳዊ ተሐድሶ ከመካሄዱ በፊት ሳይሆን አይቀርም። ኢዮስያስ ያመጣው መንፈሳዊ ተሐድሶ በሕዝቡ መንፈሳዊ፥  ሥነ ምግባራዊና ማኅበረሰባዊ ሕይወት ላይ ለውጥ ከማምጣቱ በፊት በጦርነት ሞተ። ልጆቹም በጥቂት ዓመታት ውስጥ ከእግዚአብሔር ዞር አሉ። ዕንባቆም ስለ ባቢሎን ምርኮ የተናገረው ትንቢት በ586 ዓ.ዓ. ተፈጸመ። ራቅ ብሉ በስተሰሜን ምሥራቅ ይገኝ የነበረውና ለብዙ ምዕተ ዓመታት ኃያል የነበረው የአሦር መንግሥት በእርስ በርስ ጦርነት ይፈራርስ ጀመር። ባቢሎን በ627 ዓ.ዓ. በአሦር መንግሥት ላይ ያካሄደችው ዓመፅ ተሳካላት። በ612 ደግሞ የአሦርን ዋና ከተማ ነነዌን አሸነፈች። የአሦር ጦር እስከ 609 ዓ.ዓ. ድረስ ውጊያውን ሳያቋርጥ ቢታገልም፥ የቁጥጥሩ ኃይሉ ተንኮታኩቶ ነበር። ከለዳውያን በመባል የሚታወቁት ባቢሎናውያን ኃይላቸው እንደገና እየገነነ ሄደ፡፡ ይሁዳ በተከታታይ ለማመፅ የሞከረች ቢሆንም፥ ባቢሎን በ605 ዓ.ዓ. ኢየሩሳሌምን ደመሰሰቻት። በዚህም የዕንባቆም ትንቢት ይፈጸም ጀመር። የባቢሎን ኃያል መንግሥት ለ70 ዓመታት ብቻ ቆየና በ539 ዓ.ዓ. በሜዶንና በፋርስ መንግሥት ተደመሰሰ። እግዚአብሔር ከ100 ዓመታት በፊት በዕንባቆም በኩል እንደተናገረው ባቢሎንን ስለ ኃጢአትዋ ቀጣት። የውይይት ጥያቄ፥ ስለ ዕንባቆም ከመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት አንብብና ያገኘሃቸውን ዋና ዋና እውነቶች ዘርዝር። የትንቢተ ዕንባቆም አስተዋጽኦ  1. ዕንባቆም ለእግዚአብሔር ያቀረበው የመጀመሪያ ጥያቄ፡- እግዚአብሔር በይሁዳ የሚታየውን ክፋት ለምን አይቀጣም? (ዕንባቆም 1፡1-4) 2. የእግዚአብሔር የመጀመሪያ መልስ፡- እግዚአብሔር ይሁዳን ለመቅጣት ባቢሎናውያንን ይልካል (ዕንባቆም 1፡5-11)። 3. ዕንባቆም ለእግዚአብሔር ያቀረበው ሁለተኛ ጥያቄ፡- ጻድቅና ትክክለኛ ፈራጅ የሆነው እግዚአብሔር ጥቂት ክፋት ያለባትን ይሁዳን እጅግ ክፉ በሆኑት ባቢሎናውያን እንዴት ይቀጣል? (ዕንባቆም 1፡12-2፡1)።  4. የእግዚአብሔር ሁለተኛ መልስ፡-  ሀ. ጻድቅ ግን በእምነቱ በሕይወት ይኖራል (ዕንባቆም 2፡2-5)፣ ለ. ባቢሎናውያንም ይቀጣሉ (ዕንባቆም 2፡6-20)።  5. የዕንባቆም ጸሎት፡- ፍርድን በምታመጣበት ጊዜ ምሕረትህን አስብ (ዕንባቆም 3፡1-19)። (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡) የመመዘኛ ጥያቄዎችን ለማግኘት ከታች ያለውን ሊንክ (መስፈንጠሪያ) ይጫኑ፡፡

ትንቢተ ዕንባቆም መግቢያ Read More »