የአዲስ ኪዳን መጽሐፍ ቅዱስ ጥናት

ማቴዎስ 17፡1-27

ኢየሱስ ክብሩን ለጥቂት ደቀ መዛሙርት ገለጠ (ማቴ. 17፡1-13) ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ አንዳንዶቹ ከመሞታቸው በፊት የሰው ልጅ በክብሩ ሲመጣ እንደሚያዩት ተናግሮ ነበር፡፡ ይህ የሆነው መቼ ነው? ሁሉም ደቀ መዛሙርቱ ከክርስቶስ ምጽአት በፊት ስለ ሞቱ፥ ይህ ሌላ ነገር የሚያመለክት መሆን አለበት። ምንም እንኳ አንዳንድ ምሑራን ይህ የክርስቶስን ትንሣኤ ወይም የቤተ ክርስቲያንን ጅማሬ እንደሚያመለክት ቢያምኑም፣ ክርስቶስ ለማለት የፈለገው ከደቀ መዛሙርቱ አንዳንዶቹ የመንግሥቱን ክብር በተራራ ላይ እንደሚመለክቱ ይምስላል ይላሉ። በተራራው ላይ መለኮታዊ ክብሩን አንጸባርቋል። ተመሳሳይ ወንጌላት ሁሉ ክርስቶስ ይህን ከተናገረ በኋላ፥ በተራራው ላይ እንደ ተለወጠ የሚያመለክተውን ታሪክ ጽፈዋል። ይህም ጸሐፊዎቹ ሁሉ ይህን የተስፋ ቃል ፍጻማ እንደ ተመለከቱ የሚያሳይ ይመስላል። ኢየሱስ ከሙሴና ኤልያስ ጋር ለምን ተገናኘ? ለዚህ ምክንያቱ ሙሴና ኤልያስ የብሉይ ኪዳን ልዑካን መሆናቸው ነው። ሙሴ ሕግንና ከዘፍጥረት እስከ ዘዳግም ያሉትን የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ይወክላል። በሲና ተራራ የብሉዩን ቃል ኪዳን እግዚአብሔር የሰጠው ለእርሱ ነበር። ኤልያስ ነቢያትን፥ የተቀሩትን የብሉይ ኪዳን መጻሕፍትና የሁሉንም ነገሮች በሚያድስ አካል ይመሰላል (ሚል. 4፡5-6)። ስለሆነም፥ ክርስቶስ ብሉይ ኪዳን በሙሉ ማለትም ሕግና ነቢያት እንዴት በእርሱ እንደ ተፈጸመ አሳይቷል። ሁሉም ወደ ክርስቶስ ቢያመለክቱም ለእርሱ የሚገዙ ናቸው። የክርስቶስ ሞት በብሉይ ኪዳን እንደ ተተነበየ ሁሉ፥ እነ ሙሴ የተሰባሰቡት መፈጸም በሚኖርበት ሞቱ ላይ ለመነጋገር ነበር፡፡ በዚህ አጋጣሚ ክርስቶስ እጅግ ለሚቀርቡት ሦስት ደቀ መዛሙርቱ ስለ መለኮታዊ ባሕርዩና ስለ መጭው ሞቱ ኣስተምሮአል። ይህ ሁሉ በብሉይ ኪዳን ትንቢቶች የተነገረ ነበር። በዚህ ክፍል ውስጥ የክርስቶስ ሞት ሦስት ጊዜ ተጠቅሷል። ይህ እግዚአብሔር አብ ለሁሉም በሚሰማ ድምፅ ክርስቶስ እርሱ የሚወደው ልጁ እንደሆነ ለሁለተኛ ጊዜ የተናገረበት ወቅት ነበር፡፡ ኢየሱስ አጋንንት የነበሩበትን ልጅ ፈወሰ (ማቴ. 17፡14-23) የክርስትና ሕይወት የተራራና ሸለቆ ገጠመኞችን እንደሚያካትት መግለጽ ይቻላል። አንዳንድ ጊዜ እግዚአብሔር ሕይወታችንን ሁሉ በተራራ ላይ እንድናሳልፍ የሚፈልግ ይመስለናል። ሁልጊዜ እየዘመርን፥ እየጸለይንና እያመለክን እንቆያለን። ከዚህ የበለጠ ምን አለ? ነገር ግን ምንም እንኳ እግዚአብሔር ለልጆቹ አንዳንድ ጊዜ የተራራ ላይ ሕይወት እንዲመሩ ቢያደርጋቸውም፥ እምነታቸው የሚጠናከረውና የሚታየው በሸልቆ ውስጥ ነው። እግዚአብሔርን የምናገለግለው በሸለቆ ስለሆነ፥ እግዚአብሔር ወደ ሸለቆ እንድንመለስ ይፈልጋል። ኢየሱስ፥ ጴጥሮስ፥ ያዕቆብና ዮሐንስ ከተራራው በወረዱ ጊዜ፥ ወዲያው የሕይወት እውነተኛ ገጽታ ታያቸው። የሕይወት ክብደት፥ መንፈሳዊ ውጊያና የእምነት አስፈላጊነት ጠበቃቸው። የተቀሩት ዘጠኝ ደቀ መዛሙርት ከልጁ አጋንንትን ለማስወጣት ሞክረው ነበር፡፡ ቀደም ሲል አጋንንትን ለማስወጣት የቻሉ ሲሆን፥ አሁን ን አልተሳካላቸውም ነበር። ክርስቶስ አጋንንቱን ካወጣ በኋላ፥ አጋጣሚውን ተጠቅሞ ስለ መንፈሳዊ ውጊያ አስተማረ። በዚህ ክፍል ሦስት ዐበይት ትምህርቶች ቀርበዋል። በመጀመሪያ፥ ደቀ መዛሙርት አሁን ከሰይጣን ጋር ለነበራቸው ውጊያ በቀደሙት ድሎች መተማመን አላስፈለጋቸውም። በፊት ማሸነፋችን ለአሁኑ ድል ዋስትና አይሰጠንም። ሁለተኛ፣ ኃይሉ የሚወጣው ከእኛ ሳይሆን ከእግዚአብሔር እንደሆነ ማስታወስ አለብን። ለዚህ ነው ሁሉም መንፈሳዊ ጦርነቶች እግዚአብሔር ላይ ሙሉ በሙሉ ጥገኞች መሆናችንን የሚያሳይ ጸሎት ማካተት ያለባቸው። ሦስተኛ፣ ሁሉ መንፈሳዊ ጦርነቶች ተመሳሳይ አይደሉም። አንዳንዶችን በቀላሉ ማሸነፍ ሲቻል ሌሎች ደሞ ረዥምና አስቸጋሪ ውጊያን ይጠይቃሉ። ጦርነቱ የሚካሄደው በአጋንንት ላይ ብቻ ሳይሆን፥ ሙሉ በሙሉ በእግዚአብሔር ላይ ለመደገፍ ጭምር ነው፡፡ መጾምና በጋራ መጸለይ ልባችንን ከእግዚአብሔር ጋር እንድናስተባብር ይረዳናል። ሙሉ በሙሉ በእርሱ ላይ በምንደፍበት ጊዜ፥ እግዚአብሔር ልናስብ ከምንችለው በበለጠ መንገድ ይሠራል። አሁንም ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ስለ መጭው ሞቱ ነገራቸው። የኢየሱስ አሳብ ሙሉ በሙሉ ባይገባቸውም ኀዘን አጠላባቸው። ኢየሱስ የቤተ መቅደስን ቀረጥ ከፈለ (ማቴ. 17፡24-27) ኢየሱስ ለቤተ መቅደስ ቀረጥ እንደከፈለ የሚያስረዳውን ይህንኑ ታሪክ የጠቀሰው፥ ቀራጩ ማቴዎስ ብቻ ነው። ይህ ከ20 ዓመት በላይ የሆናቸው የአይሁድ ዜጎች ሁሉ የሚጠየቁት ቀረጥ ነበር፡፡ ኢየሱስ፥ ጴጥሮስ አሁን የእግዚአብሔር መንግሥት አካል በመሆኑ ከሌሎች፥ የማያምኑ አይሁዶች እንደሚለይ ገለጸለት። ንጉሥ ወይም የንጉሥ ልጅ ከሌሎች ቀረጥ የመሰብሰብ እንጂ፣ የመክፈል ተግባር እንደማይፈጽሙ ሁሉ፥ የሰማዩ መንግሥት ገዥ የሆነው ክርስቶስ፥ የሰማዩ ንጉሥ ልጆች የሆኑት ጴጥሮስና ሌሎች ደቀ መዛሙርት የቤተ መቅደስ ቀረጥ መክፈል አልነበረባቸውም ነበር። ይህ የማያምኑ አይሁዶች ተግባር መሆን ነበረበት፡፡ ነገር ግን ኢየሱስ ሌላም ነጥብ አስተምሯል። ክርስቲያኖች ስለሚገደዱ ላይሆን ለወንጌሉ አላስፈላጊ ጥላቻ ላለማጣት የሚያደርጓቸው ነገሮች አሉ። ስለሆነም፣ በእግዚአብሔር ተአምር የተገኘውን ገንዘብ ኢየሱስና ጴጥሮስ ለሮማ መንግሥት ቀረጥ ከፍለውታል፡፡ የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ክርስቲያኖችን ስለሚያጋጥማቸው መንፈሳዊ ውጊያ፥ አንዳንድ ምሳሌዎችን ልጥ። በቀደምት ድሎች ወይም በራሳችን ብርታት ላይ በምንደገፍበት ጊዜ፥ በአብዛኛው ልንሸነፍ የምችንለው እንዴት ነው? ከክርስቶስ ጋር ያለንን ተገቢ የጥገኝነት ንኙነት በጸሎትና በጾም አማካኝነት የምናሳየው እንዴት ነው? ለ) ክርስቲያን ማድረግ ሳይኖርበት ሌሎችን ላለማስቀየም የሚፈጽማቸውን ተግባራት ምሳሌዎች ዘርዝር። (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ ስለዚህ አስደናቂ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡)

ማቴዎስ 17፡1-27 Read More »

ማቴዎስ 16፡1-28

ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያን ኢየሱስን ፈተኑት (ማቴ. 16፡1-12) ኢየሱስ በሽተኞችን በመፈወስ፥ አጋንንትን በማውጣት፣ እንዲሁም ሙታንን በማስነሣት ተኣምራዊ ኣገልግሎት አካሂዷል። ይህም ሆኖ፥ የሃይማኖት መሪዎቹ ክርስቶስ መሢሕ አይደለም ብለው ደምድመው ነበር። ሰዎች አስቀድመው ስለ አንድ ነገር በልባቸው ከወሰኑና አዲስ እውነት ለመቀበል አእምሯቸውን ከዘጉ፥ ታላላቅ ተአምራት ቢሠሩ እንኳ ምንም ነገር ወደ እምነት አያመጣቸውም። ምንም እንኳ ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያን ለዓመታት ጠላቶች የነበሩ ቢሆኑም፥ የጋራ ጠላታቸው የነበረውን ኢየሱስን ለማሸነፍ አብረው ይሠሩ ነበር። ለሁለተኛ ጊዜ ወደ እርሱ መጥተው መሢሕነቱን ለማረጋገጥ “ከሰማይ ምልክትን” እንዲያሳያቸው ጠየቁት። የሃይማኖት መሪዎቹ ከኢየሱስ ተአምራት በቂ ማረጋገጫ ስላገኙ፥ የማመን ፍላጎት ቢኖራቸው ኖሮ፥ ይህንኑ ያደረጉ ነበር። እነርሱ ግን የማመን ፍላጎት አልነበራቸውም። ኢየሱስም ለመታየት ብሎ ተአምራት አልሠራም። ስለሆነም፥ ኢየሱስ «ከዮናስ ምልክት» ማለትም ከሞቱ፥ ከመቀበሩና ከመነሣቱ ተአምር በቀር ሌላ ነገር ሊያሳያቸው እንደማይፈልግ በድጋሚ ኣስገነዘባቸው። ከዚያ በኋላ ኢየሱስ የሃይማኖት መሪዎችን ገሠጻቸው። ተራ ሰዎች የኣየሩንና የጸሐዩን ሁኔታ ተመልክተው የዝናብን መምጣት ወይም አለመምጣት ሊተነብዩ ይችላሉ። የሃይማኖት መሪዎቹ ግን የኢየሱስን መሢሕነት የሚያመለክቱ እነዚያ ሁሉ ማረጋገጫዎች እያሉ፥ የብሉይ ኪዳንን ትንቢቶች ሊረዱ ኣልቻሉም ነበር። ብዙዎቻችን እንደ ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያን የመሆን ዝንባሌ ማሳየታችን ኢየሱስን አሳስቦታል፡ በውጫዊ ሕግጋት ላይ እያተኮሩ የእግዚአብሔር እጅ ታላላቅ ነገሮችን ሲሠራ ለማየት ባለመፈለጋቸው፥ ኢየሱስ ግብዝታቸውንና መንፈሳዊ ትዕቢታቸውን «የፈሪሳውያንና ሰዱቃውያን እርሾ» ሲል ጠርቷል። ስለሆነም ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱ ከእነዚህ አመለካከቶች ሙሉ በሙሉ እንዲጠበቁ አስጠንቅቋል። እንዲህ ዓይነቱ እርሾ በሰው ሕይወት ውስጥ ካደገ በኋላ ያጠፋዋልና፡፡ የውይይት ጥያቄ:- ሀ) ከላይ የተገለጹት ዝንባሌዎች ብዙውን ጊዜ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚታዩት እንዴት ነው? ለ) የዚህ አይነት እርሾ በልብህ ውስጥ እንዳይኖር ምን እያደረግህ ነው? ኢየሱስ ስለ እርሾ ሊናገር፥ ደቀ መዛሙርቱ ምግብ ላይዙ በመምጣታቸው ጌታ የሚገስጻቸው መሰላቸው መንፈሳዊ እውነትን ለመረዳት አለመቻላቸው ኢየሱስን አሳዘነው እርሱ ከእነርሱ ጋር እያለ እንዴት ለሥጋዊ ምግብ ይጨነቃሉ? በትንሽ ምግብ አምስት ሺህ፥ በኋላም አራት ሺህ ሰዎችን ሲመግብ እይተዋል። ኢየሱስ ፍላጎቶቻቸውን ስለሚያሟላ፣ ደቀ መዛሙርቱ ለመሠረታዊ ነገሮች መጨነቅ አልነበረውም። ጴጥሮስ የክርስቶስን መሢሕነት መሰከረ (ማቴ 16፡13-20) የማቴዎስ መጽሐፍ ማዕከል ጴጥሮስ ስለ ኢየሱስ የለጠው ምስክርነት ነው። ማቴዎስ የኢየሱስን ተአምራትና ትምህርቶች በማቅረብ እርሱ አይሁዶች ሊያምኑበት የሚገባ መሢሕ መሆኑን መስክሯል አሁን ምርጫው የራሳቸው ነበር፡፡ ያ ሁሉ ማረጋገጫ እያለ በኢየሱስ ላለማመን እንደ ወሰኑት ፈሪሳውያን ሊሆኑ ይሻሉ? ወይስ የሃይማኖት ምሁር ባይሆንም እንኳ ኢየሱስ መለኮታዊ መሢሕና “የሕያው እግዚአብሔር ልጅ” እንደሆነ በግል ሊመለከት እንደቻለው እንዲ ጴጥሮስ ሊሆኑ ይሻሉ? ይህ የጴጥሮስ ምስክርነት የመጽሐፉ ማእከላዊ ነጥብ ነው። ከዚያ በኋላ፥ ማቴዎስ በመጪው የኢየሱስ ሞት ላይ ያተኩራል። ኢየሱስ ራሱ ለደቀ መዛሙርቱ ስለ ሞቱና ትንሣኤው አስተምሯል። ኢየሱስ “ቤተ ክርስቲያን” የሚለውን ቃል ሁለት ጊዜ ብቻ ጠቅሷል። ይህ ቤተ ክርስቲያን የተባለ የአማኞች የአንድነት አካል መጀመሩን የሚያሳይ ቀዳሚ ቃል ነው (ማቴ 18፡17 አንብብ።) በግሪክ ቋንቋ፥ ቤተ ክርስቲያን የሚለው ቃል “ተጠርተው የወጡ የክርስቶስ ተከታዮች ስብስብ” የሚል ፍች ይሰጣል፡ በኣዲስ ኪዳን ይህ ቃል የሚያመለክተው፥ የቤተ ክርስቲያንን ሕንጻ ሳይሆን፥ የክርስቲያኖችን ቡድኖች ነው። እነዚህም በአንድ ቤት ውስጥ የሚሰባሰቡትን ወይም ከኣንድ የቤት ቤተ ክርስቲያን የሚበልጡ ወገኖች የሚካተቱበትን የአንዲት ከተማ ወይም በየትኛውም ስፍራ የሚገኙትን ክርስቲያኖች ሁሉ የሚያመለክት ሊሆን ይችላል። ይህ በኢትዮጵያ ቃሉ በቀዳሚነት ክርስቲያኖች የሚሰባሰቡበትን ሕንጻ ከሚያመለክትበት ሁኔታ የተለየ ነው፡፡ በዚህ ክፍል ምሑራን የሚከራከሩባቸው ሁለት ዐበይት ጥያቄዎች አሉ። በመጀመሪያ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያኑን የሚሠራበት ዓለት ምንድን ነው? ሁለተኛ ለጴጥሮስ የተሰጠው ሥልጣን ምንን ያመለክታል? 1 የቤተ ክርስቲያን መሠረት የሆነው ዓለት ምንድን ነው? ለዚህ ጥያቄ የሚቀርቡ አራት ዐበይት ትርጉሞች አሉ። ሀ. አንዳንዶች ዓለቱ ጴጥሮስ እንደሆነ ያምናሉ። ክርስቶስ ስሙን “ዓለት” የሚል ፍቺ ወደሚሰጠው ጴጥሮስ የለወጠው ለዚሁ ነው ይላል። የሮም ካቶሊኮች ይህ ቃል ጴጥሮስና ከእርሱ በኋላ የሚሾሙት ሊቀ ጳጳሳት መንፈሳዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ ለእግዚአብሔር፥ የክርስቶስን ያህል ሥልጣን እንዳላቸው የሚያሳይ መሆኑን ያምናሉ። ሊቀ ጳጳሱና ካህናቱ የአማኙን መዳን ወይም አለመዳን የመወሰን መብት እንዳላቸው ያምናሉ። ይህ አተረጓጎምና ለሊቀ ጳጳሱ የተሰጠው ሥልጣን ሊሆን የማይችል ነው፡፡ ክርስቶስ ለጴጥሮስ ይህን ሥልጣን ቢሰጠው እንኳ፥ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የጴጥሮስ ሥልጣን ወደ ሌሎች የቤተ ክርስቲያን መሪዎች እንደሚተላለፍ የሚያመለክት አሳብ የለም። እግዚአብሔር ጴጥሮስ የመጀመሪያውን ስብከት በበዓለ ኀምላ እንዲያቀርብ በማድረጉ፥ በአይሁዶች መካክል ቤተ ክርስቲያን ተወልዳለች (የሐዋ. 2:38-41)። እግዚአብሔር ሰማርያውያን እውነተኛ አማኞች መሆናቸውን እንዲመሰክርና መንፈስ ቅዱስን እንዲቀበሉ ተጠቅሞበታል (የሐዋ. 8፡14-17)። እንዲሁም፥ ጴጥሮስ ለቆርኔሌዎስ በመመስከር አሕዛብን ወደ እግዚአብሔር መንግሥት እንዲያመጣ ተጠቅሞበታል (የሐዋ. 10፡27-48)። ለ. ሌሎች ደግሞ ጴጥሮስ የሌሎች ሐዋርያት እንደራሴ እንደሆነ ያስባሉ። በኤፌ. 2፡20 ጳውሎስ ሁሉም ሐዋርያት የቤተ ክርስቲያን መሠረት እንደሆኑ ገልጾአል። እነዚህ ሐዋርያት ወንጌልን የመስበክ ብቻ ሳይሆን፥ በዓለም ሁሉ የማሰራጨት ኃላፊነት ተሰጥቷቸው ነበር። በተጨማሪም፥ ለቤተ ክርስቲያን የእግዚአብሔር ፈቃድ ምን እንደ ሆነ፥ እውነተኛው ዶክትሪን የትኛው እንደሆነ፥ ክርስቶስ ማን እንደ ነበረ የመመስከር ሥልጣን ነበራቸው። በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ፥ ሐዋርያት የቀድሞይቱን ቤተ ክርስቲያን ሊመሩና አስተምህሮቷን መልክ ሲያስይዙ እንመለከታለን። ሐ. ዓለቱ ኢየሱስ ነው። ኢየሱስ በዚህ ስፍራ ለዓለት ሁለት ቃላት ተጠቅሟል። ስምዖን የሚለውን ስም ወደ ጴጥሮስ በለወጠበት ጊዜ የተጠቀመው ቃል «ትንሽ ዓለት» የሚል ፍች ይሰጣል። ስለሆነም፥ ክርስቶስ ስምዖን ጴጥርስ (ትንሽ ዓለት) ሲሆን፥ በዚህ “ትልቅ ዓለት” ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ ብሏል። ትልቁ ዓለት ማን ነው? ሰዎች የሚሰናከሉበትና የእግዚአብሔር አዲስ ዕቅድ የማዕዘን ራስ የሆነው የተተወው ዓለት ማን ነው? እርሱ ክርስቶስ እንደሆነ ግልጽ ነው (ማቴ. 21፡42-44 አንብብ።) የቤተ ክርስቲያን መሠረት የሆነው ክርስቶስ ነው። (1ኛ ቆሮ. 3፡11 አንብብ።) ከሞተ፥ ከተቀበረና ሞትን አሸንፎ ከተነሣ በኋላ፥ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን ለመመሥረት መንፈስ ቅዱስን ላከ። የቤተ ክርስቲያን ራስ እንደ መሆኑ መጠን፥ ክርስቶስ ገዥ ነው። መ. ዓለቱ ጴጥሮስ የሰጠው ምስክርነት ነው። አንድ ሰው ለመዳንና የቤተ ክርስቲያን አካል ለመሆን ማንን ማመን አለበት? ማመን ያለበት ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ የሆነ መሢሕ መሆኑን ነው። ይህ መሠረታዊ የአስተምህሮ ሐቅ አንድ ሰው ደኅንነትን ለማግኘትና የእግዚአብሔር ቤተሰብ አባል ለመሆን ሊያሟላው የሚገባው መሠረታዊ እውነት ነው። 2 ክርስቶስ ለጴጥሮስ የመንግሥተ ሰማይን ቁልፎች እንደ ሰጠ ሲናገር ምን ማለቱ ነው? በማቴዎስ 18፡18፣ ለሁሉም ደቀ መዛሙርት ተመሳሳይ ሥልጣን ተሰጥቷል። አሁንም ምሑራን በዚህ ጉዳይ ላይ በመስራከር የተለያዩ ኣተረጓጎሞችን ይሰጣሉ። ሀ. የሮም ካቶሊክ ክርስቲያኖች ይህን ጥቅስ የሚጠቀሙት የሊቀ ጳጳሱን ሥልጣን ለማረጋገጥ ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ክርስቶስ ለጴጥሮስ ታላቅ ሥልጣን እንደ ሰጠው ያምናሉ፡ ካቶሊኮች ጴጥሮስ በምእመናን ላይ መንፈሳዊ ሥልጣን (ቁልፍ) እንዳለውና በእርሱ ውሳኔ የዘላለምን ሕይወት ሊያገኙ ወይም ወደ ሲኦል ሊወርዱ እንደሚችሉ ያስባሉ፡፡ ከዚህ በመነሣት፥ በአሁኑ ዘመን የሚያገለግለው ሊቀ ጳጳስ የጴጥሮስ ቀጥተኛ ተተኪ እንደሆነና ይህንኑ ተመላላይ ሥልጣን እንደ ተቀበለ ያስተምራሉ። ነገር ግን እነዚህ ምንባቦች ለጴጥሮስ ይህን ያህል ያልተገደበ ሥልጣን መስጠታቸው አጠራጣሪ ከመሆኑም በላይ፣ አዲስ ኪዳን ውስጥ ይህ ሥልጣን ወደ ሌሎች የቤተ ክርስቲያን መሪዎች እንደሚተላለፍ የሚያመለክት አሳብ አለመጠቀሱ ሊጤን ይገባል። ስለሆነም ይህ ትክክለኛ አተረጓጎም እንዳልሆነ እንረዳለን። ለ. ሌሎች ክርስቲያኖች እነዚህ ምንባቦች ለጴጥሮስ ከፍተኛ ሥልጣን እንደተሰጠው የሚያመለክቱ መሆናቸውን ይሰማሉ። ይህ ግን ጴጥሮስ «አንተን ወደ መንግሥተ ሰማይ አስገባሃለሁ እላስገባህም?» የሚልበት ኃጢአትን ይቅር የማለትና ያለማላት ሥልጣን እንልሆነ ያስረዳሉ። ይህ ግን በእግዚአብሔር የተስፋ ቃሉችና በግለሰቡ እምነት ላይ ተመሥርቶ ጴጥሮስ የእግዚአብሔር መንግሥት አካል መሆኑን የሚያውጅበት ሥልጣን ነው። በግሪኩ መጽሐፍ ቅዱስ ለጴጥሮስ የተሰጠው ሥልጣን «የመንግሥተ ሰማይን ቁልፎች እሰጥሃለሁ፤ በምድር ላይ ያሰርከው ሁሉ ቀደም ሲል በሰማይ የታሰረ ነው በምድር የፈታከው ሁሉ ቀደም ሲል በሰማይ የተፈታ ነው።” ተብሎ ሊነበብ ይችላል፡፡ እነዚህ ምሑራን ጴጥሮስ በክርስቶስ ያመኑት እንደዳኑና ያላመኑት ግን ጥሩ አይሁዶች ቢሆኑም

ማቴዎስ 16፡1-28 Read More »

ማቴዎስ 15፡1-39

ማቴዎስ በክርስቶስና የሃይማኖት መሪዎች መካከል ወደነበረው ግጭት እየተመላለሰ ይናገራል። ቀደም ሲል ሰንበትን በመጠበቁ ጉዳዩ ላይ የተጋጩ ሲሆን፥ አሁን ደግሞ ስለ ሥርዓታዊ ንጽሕና ተከራከሩ። የብሉይ ኪዳን ካህናት ለእግዚአብሔር መሥዋዕቶችን ከማቅረባቸው በፊት እጆቻቸውን የመታጠብ ግዴታ ስለነበረባቸው (ዘጸ 30፡17-20)፥ ፈሪሳውያን አይሁዶች ሁሉ ከየትኛውም ሃይማኖታዊ ተግባር በፊት መታጠብ እንዳለባቸው አስተማሩ። ይህም ለምግብ ከመጸለይና ከመመገብ በፊት እጅ መታጠብን ይጨምር ነበር። ፈሪሳውያን፥ አይሁዶች እግዚአብሔርን ለምግቡ አመስግነው መብላት ከመጀመራቸው በፊት በተወሰነ መንገድ መታጠብ እንዳለባቸው ያስተምሩ ነበር። የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያልተጠቀሱትንና ክርስቲያኖች ለእውነተኛ መንፈሳዊነት ጠቃሚዎች ናቸው የሚሏቸውን አንዳንድ ልምምዶች ዘርዝር። ለምላሉ፥ በጸሎት ጊዜ ዓይንን መጨፈን፥ ፊልም አለማየት የመሳሰሉትን። ለ) ምንም እንኳ እነዚህ ባሕላዊ ልምምዶች ቢሆኑም፥ ክርስቲያኖች ከእግዚአብሔር ቃል እኩል ሊያዩዋቸው የሚችሉባቸውን መንገዶች ዓለጽ፡፡ ፈሪሳውያን ደቀ መዛሙርት እነዚህን የመታጠብ ባሕሎች እያከበሩ ኣለመሆናቸውን ሲገልጹ፥ ክርስቶስ ደግሞ ለሕዝቡ ስለ እውነተኛ መንፈሳዊ ንጽሕና አስተማረ፥ እንዲሁም ክርስቶስ ለፈሪሳውያን በሚከተለው መንገድ ምላሽ ሰጥቷል። ሀ. በሰው ሠራሽ ደንቦች ላይ በማተኮር፥ ፈሪሳውያን ብዙውን ጊዜ እውነተኞቹን የእግዚአብሔር ሕግጋት ይተላለፉ ነበር። የራሳቸውን የራስ ወዳድነት ዓላማዎች ለማሳካት፥ ሕጉን በመሣሪያነት ይጠቀሙ ነበር። ለምሳሌ፥ ለቤተሰቦቻቸው ገንዘብ ላለመስጠት ገንዘባቸው «ቁርባን» እንደሆነ ይናገሩ ነበር። ይህም “ለእዚአብሔር ሊሰጥ የተለየ” የሚል ፍች ያለው የኣይሁዶች ቃል ነበር። ይህን ማለታቸው ግን ገንዘብን ለራሳቸው ፍላጎት ከመጠቀም አላገዳቸውም ነበር። ነገር ገን ለሌሎች፥ በተለይም ለወላጆቻቸው ገንዘብ ላለመስጠት ማመኻኛ ሆኗቸዋል። ሊ ሰዎችን መንፈሳዊ በሚያስመስሉ ደንቦች ላይ ማተኮሩ፥ እጅግ መንፈሳዊ የሆነውን ነገር ከእግዚአብሔር ጋር የሚኖራቸውን ቀንኙነትና ሌሎችን መውደድ እንዳይመለከቱ ዓይኖቻቸውን አሳውሮታል። ሰዎች መንፈሳዊነትንና ከእግዚአብሔር ጋር ግንኙነት ማድረግን እንደ ማበረታታት፥ በውጫዊ ተግባራት ላይ ትኩረት አድርገዋል። ሒ በእግዚአብሔር ዓይኖች ፊት አንድን ሰው የሚያረክሰው ከአፉ የሚወጣው ነው። የምንበላው ምግብ እያረከሰንም፡፡ በልባችን ውስጥ ያለውና በአፋችን በኩል የሚወጣው ግን ሰውን በእግዚአብሔር ፊት ያረክሰዋል። የኃጢአት ምንጩ ሰዎች የሚለብሱት፥ የሚበሉት ወይም የሚጠጡት ነገር አይደለም። የኃጢአት ምንጭ ክፉ ልብ ነው። የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚቃረኑ ውጫዊ ነገሮች ሁሉ የሚመነጩት፥ ከክፉ ልብ ነው። ይህም የምንበላው ምግብ (ለምሳሌ፥ የሙስሊሞች ምግብ) እንደማያረክሰን ያሳያል።ይህ ባሕላችን ይህ ጥሩ ነው ያ መጥፎ ነው ብሎ በሚያስተምረን ሁኔታ ላይ የተመሠረተ ነው። መ. ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱ ሕዝቡን ወደ ተሳሳተ አቅጣጫ የሚመሩትን ወገኖች ለመቃወም እንዳይፈሩ አስጠንቅቋቸዋል። ክርስቶስ ለኃጢአተኞች ስሜት ይጠነቀቅ ነበር። ነገር ግን ፈሪሳውያን ብዙ ሰዎችን ወደ ኃጢአትና የሐሰት ሃይማኖት እየመሩ በመሆናቸው፥ ክርስቶስ በግልጽ ለመናገር ፈለገ። ደቀ መዛሙርቱ ፈሪሳውያን በቃሉ እንደ ተቀየሙ ሲነግሩት፥ ሰዎች ሰምተው ይማሩ ዘንድ አንዳንድ ጊዜ በግልጽ መናገሩ አስፈላጊ እንደሆነ ገለፁላቸዋል። ፈሪሳውያን እግዚኣብሔር ፈጥኖ ሊነቅላቸው የሚገባ አረሞች ነበሩ። የደኅንነትን መንገድ የሚያውቁ ቢመስሉም፥ ለራሳቸው ዕውሮች ሆነው ሳለ፥ ሌሎች መንፈሳዊ ዕውራንን ለመምራት ይፈልጉ ነበር። ውጤቱ ግን እነርሱም ሆኑ የሚመሯቸው ሰዎች ወደ ሐሰት ትምህርትና የእግዚአብሔር ፍርድ ጉድጓድ መውደቃቸው ነበር። (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ ስለዚህ አስደናቂ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡)

ማቴዎስ 15፡1-39 Read More »

ማቴዎስ 14፡1-36

ማቴዎስ  14፥ የክርስቶስ አገልግሎት ረዥሙ ዕለት በመባል ይታወቃል። በአንድ ቀን ክርስቶስ ታላላቅ ተቃውሞዎችና ፈተናዎች እጋጥመውታል። የአክስቱ ልጅና የመንሥቱ ኣገልጋይ የነበረው መጥምቁ ዮሐንስ ተገደለ። ክርስቶስ ምንም እንኳ ድካም ቢሰማውና ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ብቻ ለመሆን ቢፈልግም፥ ብዙ ሰዎች ስለሚከተሉት ለራሱ ጊዜ አላገኘም፤ አምስት ሺህ ሰው መገበ። ከዚያ በኋላ ግን ደቀ መዛሙርቱ ማዕበል በበረታባቸው ጊዜ በእርሱ አለማመናቸውን ታዘበ። ከዚያም አሳዛኝ ነገሮች ደረሱበት። ነገር ግን ክርስቶስ የአባቱን ድምፅ ይሰማ ስለነበር፥ እነዚህን ነገሮች የእግዚአብሔርን ፍላጎት ለማሟላቱ ተግባር እውሏቸዋል። ይህ ብዙውን ጊዜ በቤተ ክርስቲያን መሪዎች ላይ ይደርሳል። ሰዎች ሲሞቱ፥ በኃጢአት ሲወድቁ ወይም እምነታቸውን ሊተዉ በከፍተኛ ደረጃ እንከፋለን። የራሳችን ዕቅዶች ቢኖሩንም፥ በጊዜ ሰሌዳቸው መሠረት አይከናወኑም። የቤተ ክርስቲያን መሪዎች በዚህ ምክንያት ሊቆጡ ወይም ተስፋ ሊቆርጡ ይችላሉ። ነገር ግን በእያንዳንዱ ተስፋ መቁረጥና ችግር ውስጥ የእግዚአብሔርን እጅ ማየቱ ከሁሉም የበለጠ ነው። የመጥምቁ ዮሐንስ አንገት በሰይፍ ተቀላ (ማቴ. 14፡1-12) የብሉይ ኪዳን የመጨረሻው ታላቅ ነቢይ የነበረው መጥምቁ ዮሐንስ፥ ለረዥም ጊዜ ታስሮ ቆየ። ከዚያም በንጉሥ ሄሮድስ ቤተሰብ ተንኮል ምክንያት ሞት ተፈረደበት። ዮሐንስ የታሰረው የእግዚአብሔርን ቃል እየተናገረ የባለሥልጣናትን ሰላም እንዳይነሣ በማሰብ ነበር። ለእምነቱ መከራ ተቀብሎ ሞተ። ይህ ሁኔታ ክርስቶስን በከፍተኛ ደረጃ ሳያሳዝነው አልቀረም። ይህ ድርጊት የእግዚአብሔርን ሕዝብ ኃጢኣት ተቃውመው የተናገሩትን ነቢያት ከገደሉት የብሉይ ኪዳን አይሁዶች የተለየ አልነበረም። ይህንኑ የመሰለ የጭካኔ ተግባር ከኣንድ ዓመት በኋላ በክርስቶስ ላይ ሊደርስ ነው። ይህ ሁኔታ ክርስቶስን ለመከተል በሚመርጡ ሰዎች ላይም ስለሚደርሰው አደጋ የሚያስተላልፈው መልእክት አለው። እግዚአብሔር አንዳንድ ጊዜ ሕዝቡን ከሞት ቢያድንም (የሐዋ. 12፡6-11)፥ ስለዚህ በሌሎች ጊዜያት መከራ ተቀብለው እንዲሞቱ የሚፈቅድበት ጊዜ አለ (የሐዋ. 7፡54-60)። ክርስቶስ አምስት ሺህ ሰዎችን መገበ (ማቴ. 14፡13-21) ክርስቶስ የአክስቱ ልጅ በሆነው መጥምቁ ዮሐንስ ላይ ስለደረሰው የሞት አደጋ ከሰማ በኋላ፥ ለመጸለይና ለማሰላሰል የተወሰነ ጊዜ ፈለገ። ነገር ግን በጀልባ ለጥ ወዳለ ስፍራ ለመሄድ በፈለገ ጊዜ፥ ከአምስት ሺህ በላይ የሆኑ ሰዎች (ማለትም ተጨማሪ አምስት ሺህ ሴቶችና ልጆች) ይከተሉት ጀመር። ክርስቶስ ለግል ጊዜው አክብሮት ባለመስጠታቸው ወይም ራስ ወዳድ በመሆናቸው ሊቆጣቸው ይችል ነበር። ማቴዎስ እንደሚነግረን ግን፥ ክርስቶስ የግል ሥቃይ ቢኖርበትም ለሕዝቡ ከመራራት አልታቀበም። ስለሆነም፥ ቃሉን በማስተማር፥ የታመሙትን በመፈወሰ፥ እንዲሁም ረሃብተኞችን በመመገብ ረዳቸው። (ክርስቶስ አምስት ሺህ ሕዝብ የመገበበት ተአምር በአራቱም ወንጌላት ውስጥ ከተመዘገቡት ጥቂት ተአምራቶች አንዱ ነው።) ነገር ግን ክርስቶስ እንክብካቤውን ያሳየው ለሕዝቡ ብቻ አልነበረም። ለደቀ መዛሙርቱም እነርሱንና ያላቸውን ጥቂት ሀብት በመጠቀም፥ የሰዎችን ፍላጎት ሊያሟላ እንደሚችል አስተምሯቸዋል። ክርስቶስ ይህ በራሳቸው ሊወጡ የማይችሉት ተግባር መሆኑን እያወቀ ደቀ መዛሙርቱ ሕዝቡን እንዲመግቡ ነገራቸው። ይህን የተናገረው የማይቻል ነገር ሊያደርጉ እንደሚችሉ ለማስተማር ነበር። ወደ እርሱ ከተመለሱ እነርሱንና ሀብታቸውን በመጠቀም ከችሎታቸው የላቀ ተግባር ሊያከናውን ይችል ነበር። ከዚህ ክፍል የሚከተሉትን እውነቶች ልንመለከት እንችላለን። ሀ. ደቀ መዛሙርቱ ሕዝቡን እንዲመግቡ የተናገረው ክርስቶስ ነበር። በዚህም ክርስቶስ ፍላጎታቸውን እንዲያሟላ እያስገደዱት አልነበሩም። ሰዎች የማይቻል ተግባር ለመፈጸም የሚሞክሩባቸው ሁለት አማራጮች አሉ። በመጀመሪያ፥ የእግዚአብሔር ልጆች አንድ ታላቅ ነገር (ለምሳሌ፥ አዲስ የቤተ ክርስቲያን ሕንጻ) የሚፈልጉባቸው ጊዜያት አሉ። ነገር ግን ብዙውን ጊዜ እነሣሽ ምክንያታቸው በራስ ወዳድነት ስሜት የጎደፈ ነው። ለምሳሌ ያህል ትልቅ ቤተ ክርስቲያን በመገንባት ለራሳችንና ለቤተ ክርስቲያናችን የበለጠ ክብር እንደምናመጣ ልናስብ እንችላለን። እግዚኣብሔርን ሳይጠይቁ ወይም እምነታቸውን የሚፈትነው እግዚአብሔር መሆኑን ሳያረጋግጡ ክርስቲያኖች የሕንጻውን ሥራ ይጀምሩና እግዚአብሔር ፍላጎታቸውን እንዲያሟላላቸው ይጠይቃሉ። ብዙውን ጊዜ የዚህ ዓይነቱ እምነት ለሰዎቹም ሆነ ለእግዚአብሔር ስም ኃፍረትን ያስከትላል። ሁለተኛ፥ እግዚአብሔር ሰዎች አንድን የማይቻል ተግባር እንዲፈጽሙ በግልጽ የሚናገርባቸው ጊዜያት አሉ። ይህ በእግዚአብሔር ተማምነን እርሱ ሊሠራ የሚችለውን የምንመለከትበት መልካም አጋጣሚ ነው። ለ. በማይቻሉ ሁኔታዎች ውስጥ እግዚአብሔር የራሱን ታላቅነት እንድንረዳ ለማገዝ ይፈልጋል። በራሳችን ሀብት የምንችለውን ብቻ የምናደርግ ከሆንን፥ የእግዚአብሔርን እገዛ እንፈልግም። እምነታችንም አይፈተንም። የእግዚአብሔርን እጅ በሥራ ላይ ልንመለከት የምንችለው እግዚአብሔር የማይቻለውን እንድናደርግ በሚጠይቀን ጊዜ ብቻ ነው። አንድ ሰው እንደተናገረው፥ እግዚኣብሔር የማይቻል ነገር የሌለበትን ተግባር ለእርሱ እንድንፈጽም አይጠይቀንም። በዚህ ጊዜ ብቻ ነው ውጤቱ የእግዚአብሔር እንጂ የእኛ የማይሆነው። ሐ. እግዚአብሔር አንድን ታላቅ ነገር እንድንሠራ በሚጠይቀን ጊዜ፥ ካለን ነገር ይጀምራል። እግዚአብሔር ብዙውን ጊዜ ከባዶ አይጀምርም። ክርስቶስ የማይቻለውን አምስት ሺህ ሰዎችን የመገበው በደቀ መዛሙርቱ እጅ በነበረው ጥቂት እንጀራና ዓሣ አማካኝነት ነበር፡፡ በመጀመሪያ ደቀ መዛሙርቱ ያላቸውን ለእርሱ መስጠት ነበረባቸው። እግዚአብሔር በራስ ወዳድነት ሀብታችንን የሙጥኝ ብለን፥ «እግዚአብሔር ሆይ፥ አንተው አድርገው» በምንልበት ጊዜ ለመሥራት አይፈልግም። እግዚአብሔር ሕዝቡ ያለውን እንዲሠዋ ይሻል። ከዚያም የመፍትሔው አካል እንድንሆን ይፈቅድልናል። ነገር ግን፥ «ይህ የማይቻል ነገር መሆኑ ግልጽ ነው። ስለሆነም፥ የምችለውን አደርጋለሁ፥ ላደርገው የምችለውም ይህንኑ ብቻ ነው» ከሚል አመለካከት መቆጠብ አለብን። ያለንን ከሰጠን በኋላ እግዚአብሔር እንዴት እንደሚሠራ መጠባበቅ አለብን። መ. እግዚአብሔር የልጆቹን ፍላጎት የሚያሟላው በሚያገለግሉበት ወቅት ነው። ብዙውን ጊዜ ግን ሥራውን ከመጀመራቸው በፊት ፍላጎታቸውን አያሟላላቸውም። ደቀ መዛሙርቱም ተርበው ነበር። ምግብ ስጠንና ከበላን በኋላ የተረፈውን ለሰዎች እንሰጣለን ሊሉ ይችሉ ነበር። ክርስቶስ ግን ለደቀ መዛሙርቱ የሰጣቸው ለሰዎች ከሰጡ በኋላ ነበር። ደቀ መዛሙርቱ እያንዳንዳቸው አንድ ቅርጫት ምግብ ያገኙት (12 ቅርጫት ምግብ ስለ ተረፈ) የሕዝቡን ፍላጎት ለማሟላት ከሰጡ በኋላ ነበር። የውይይት ጥያቄ፣ ሀ) ክርስቲያኖች የእግዚአብሔርን ፈቃድ ሳይጠይቁ ወይም በራስ ወዳድነት ምክንያቶች አንድን ነገር ሊጀምሩ የሚችሉባቸውን መንገዶች ግለጽ። ለ) እግዚአብሔር አንድ የማይቻል ተግባር እንድትፈጽም ከጠየቀህ በኋላ በታዘዝኸው ጊዜ እንዴት ፍላጎትህን እንዳሟላ የሚያስረዱትን ምሳሌዎች ዘርዝር። ሐ) ከዚህ ስለ መታዘዝና የእግዚአብሔር ቸርነት የምንማራቸው ሌሎች ትምህርቶች ምንድን ናቸው? ማቴዎስ ክርስቶስ እንደ መሢሕና ፈጣሪ የሕዝቡን ሥጋዊ ፍላጎቶች እንዳሟላ ገልጾአል። እግዚአብሔር በምድረ በዳ ውስጥ በሙሴ አማካኝነት ለሕዝቡ ምግብን እንደ ሰጣቸው ሁሉ፥ ክርስቶስም በተአምር የሕዝቡን ፍላጎቶች ለማሟላት ችሏል። በተጨማሪም ማቴዎስ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ስለሚበሉት ምግብ መጨነቅ እንደሌለባቸው ተናግሯል። ክርስቶስ የደቀ መዛሙርቱን ፍላጎት ያሟላል። ክርስቶስና ጴጥሮስ በውኃ ላይ ተራመዱ (ማቴ. 14፡22-36) ክርስቶስ ኅዘን በደረሰበት ጊዜ ሳይቀር ተግባሩን ለመቀጠል ኃይልን ከየት አገኘ? ይህን ኃይል ያገኘው ከእግዚአብሔር ጋር ካሳለፈው የግል የጸሎት ጊዜ ነበር። ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን ይወዳቸው የነበረ ቢሆንም፥ በተለይም ብዙ ሠርቶ በደከመና ችግር በደረሰበት ወቅት ከእግዚአብሔር ጋር የግል ጊዜ የማሳለፉን ጠቀሜታ ተገንዝቦ ነበር። ስለሆነም፤ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን በጀልባ ከሰደዳቸው በኋላ፥ ለብቻው ወደሚጸልይበት ስፍራ ሄደ። ከሌሎች ሰዎች ጋር መጸለይ መልካም ነው። ነገር ግን የግል ጊዜ ወስደን እግዚአብሔር በቃሉ ሲናገር ካላዳመጥንና ወደ እርሱ ካልጸለይን፥ ፍሬያማ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ልንሆን እንደማንችል ከክርስቶስ ምሳሌነት እንማራለን፡፡ ነገር ግን ደቀ መዛሙርቱን በጀልባ የላከበት ሌላም ምክንያት ነበር። ክርስቶስ በእርሱ ላይ የነበራቸውን እምነት ለመፈተን ፈልጎ ነው። ክርስቶስ ማዕበሉ እንደሚነሳ ቢያውቅም፣ ደቀ መዛሙርቱን ወደዚያው ላካቸው። ሕይወት ዘመናቸውን በሙሉ በውኃ ላይ ቢያሳልፉም፥ ክርስቶስ ዓሣ አጥማጆቹ ከማዕበሉ የማያመልጡበትን ሁኔታ አደረገ። ቀደም ሲል እርሱ በማዕበል ውስጥ አብሯቸው ነበር። በዚህ ጊዜ በማዕበል ውልጥ ብቻችንን ነን ብለው ያስቡ ነበር። በማዕበሉ መካከል ክርስቶስ እየተራመደ ወደ ደቀ መዛሙርቱ መጣ። ጴጥሮስ ክርስቶስ በውኃ ላይ ሲራመድ ባየ ጊዜ፥ እንደ እርሱ ለማድረግ ፈለገ። ክርስቶስም ጴጥሮስ በውኃ ላይ እየተራመደ ወደ እርሱ እንዲመጣ ጠራው። ጴጥሮስ ክርስቶስን እየተመለከተ በውኃው ላይ ከተራመደ በኋላ፥ ማዕበሉንና ነፋሱን ሲያይ መስመጥ ጀመረ። ክርስቶስ ግን በፍጥነት ኣዳነው። ክርስቶስ ወደ ጀልባይቱም ሲገባ ማዕበሉ ጸጥ አለ። ማቴዎስ ይህን ታሪክ የጨመረው ለምንድን ነው? በመጀመሪያ፥ ታሪኩ የክርስቶስን ኃይል ያሳያል። ክርስቶስ በውኃ ላይ በመጓዙና ማዕበሉን ጸጥ በማሰኘቱ፥ በተፈጥሮ ላይ ሙሉ ሥልጣን እንዳለው አሳይቷል። እንዲህ ዓይነት ኃይል ያለው እግዚአብሔር ብቻ በመሆኑ፥ ኣይሁዶች ስለ ክርስቶስ ኃይል ማወቅ ያስፈልጋቸው

ማቴዎስ 14፡1-36 Read More »

ክርስቶስ በምሳሌዎች አማካኝነት ስለ እግዚአብሔር መንግሥት አስተማረ (ማቴዎስ 13:1-58)

ክርስቶስ ካስተማረባቸው ዘዴዎች አንዱ በምሳሌዎች መጠቀም ነበር። (አንዳንድ ምሑራን ከ60 በላይ ምሳሌዎች ወይም ምሳሌ መሰል አባባሎች እንዳሉ ይናገራሉ። ይህም ከክርስቶስ ጠቅላላ ትምህርት ሲሶው ያህል ነው።) ምሳሌዎችን በትክክል ለመተርጎም ይቻለን ዘንድ፥ የምሳሌዎችን ምንነትና እንዴት ልንረዳቸው እንደሚገባን ማወቅ አለብን። ምሳሌዎች ስውር መልእክት የሚያስተላልፉ እንቆቅልሾች (allegories) አይደሉም። እያንዳንዱ የታሪኩ ዝርዝር መንፈሳዊ ትርጉም እንዲሰጥ ሆኖ የተዘጋጀ ልብወለዳዊ ታሪክም አይደለም። ነገር ግን ምሳሌዎች አንድ ዐቢይ መንፈሳዊ እውነት ለማብራራት የሚቀርቡ ቀላል ታሪኮች ናቸው። ክርስቶስ አንዳንድ ምሳሌዎችን የተረጎመ ቢሆንም፡ አብዛኞቹ ምሳሌዎቹ አልተተረጎሙም። ስለሆነም፥ ምሳሌዎችን በምንተረጉምበት ጊዜ፥ የሚከተሉትን የትርጉም ሂደቶች መከተል አለብን፡፡ ሀ. ጠቅላላውን ታሪክ ክርስቶስ ምሳሌውን ከተናገረው የአይሁድ ባሕል አንጻር መረዳት አለብን። ለ. ከዚያም፥ «በዚህ ታሪክ እየተብራራ ያለው ዐቢይ መንፈሳዊ እውነት ምንድን ነው?» ብለን መጠየቅ ኣለብን። ሐ. በመጨረሻም፥ «ይህ መንፈሳዊ እውነት ዛሬ ከእኛ ሕይወት ጋር እንዴት ይዛመዳል?» ብለን እንጠይቃለን። ክርስቶስ በተአምራት አማካኝነት በማስተማር ሁለት ነገሮችን አከናውኗል። በመጀመሪያ፥ ለምትህርቱ ልባቸውን ለከፈቱት ሰዎች፥ እነዚህ ምሳሌዎች ጥልቅ መንፈሳዊ እውነቶችን ለማብራራት እንደ መልካም የማስተማሪያ መሣሪያዎች አገልግለዋል። ክርስቶስ ብዙ ሰዎች ንድፈ አሳባዊ እውነቶችን ለመረዳትና ከሕይወታቸው ጋር ለማዛመድ እንደሚቸገሩ ስለሚያውቅ፥ መንፈሳዊ እውነቶችን ለማብራራት በእነዚህ ምሳሌዎች ተጠቅሟል። ሁለተኛ፡ ለመንፈሳዊ እውነቶች ልባቸውን ላልከፈቱ ሰዎች፥ እነዚህ ምሳሌዎች የወንጌሉን እውነት ስለሚደብቁ የእግዚአብሔርን ፍርድ ያመለክታሉ። ማቴዎስ ከክርስቶስ ምሳሌዎች ብዙዎችን ሰብስቦ በዚህ ምዕራፍ ውስጥ ያሰፈረ ይመስላል። ክርስቶስ የጀመረውን የመንግሥተ ሰማይ ምሥጢራት የሚያብራሩ ሰባት ምሳሌዎች ቀርበዋል። ሀ. የአራት ዓይነት መሬቶች ምሳሌ (ማቴ. 3፡1-23)። ክርስቶስ የመጣው ወንጌልን እየሰበከ ነበር። ከዚያም ደቀ መዛሙርቱና እኛም መልካሙን የምሥራች ወደ ሰዎች ሁሉ እንድናደርስ አዝዞናል። ነገር ግን ሰዎች ለምስክርነታችን የምንፈልገውን ዓይነት ምላሽ በማይሰጡበት ጊዜ፥ እንዳንደነቅ ወይም ተስፋ እንዳንቆርጥ፥ ክርስቶስ አራት የተለያዩ ነገሮች ስላጋጠሙት ስለ ግብርና የሚያስረዳ ምሳሌ ተናግሯል። አንዳንድ ዘሮች በፍጹም አይጎነቁሉም። ይህ ወንጌሉን ከሰሙ በኋላ ለማመን ከመወሰናቸው በፊት፥ ሰይጣን ዘሩን በመውሰዱ ምክንያት ምላሽ ከመስጠት የሚታቀቡትን ሰዎች የሚያመላክት ነው። ሌሎች ዘሮች በድንጋያማ መሬት ላይ ይወድቃሉ። እነዚህ ሰዎች ወንጌሉን ሰምተው ማመናችውን ይናገራሉ። ነገር ግን ያልተጠበቁ ነገሮች፣ ችግሮች ወይም ስደት ስለሚደርስባቸው፥ ለወንጌሉ ጀርባቸውን ሰጥተው ወደ ዓለም ይመለሳሉ። በአረሞች መካከል የሚወድቁ ዘሮች ይታነቃሉ። እነዚህ ወንጌሉን ሰምተው በክርስቶስ የሚያምኑ ሰዎች ናቸው። ነገር ገን የዓለም ነገሮች (ገንዘብ፥ ሥራ፥ ትምህርት፥ ቤተሰብ፥ ወዘተ…) እምነታቸውን አንቆ ስለሚገድልና ወደ ዓለም እንዲመለሱ ስለሚያደርግ፥ ልባቸው የተከፋፈለ ይሆናል። አንዳንድ ዘሮች በመልካም መሬት ላይ ይወድቃሉ። እነዚህ ወንጌሉን ሰምተው በሚያምኑትና እምነታቸውም በመንፈሳዊ ፍሬዎች የሚታዩ ናቸው። የውይይት ጥያቄ፡- እነዚህ አራት ምላሾች ለወንጌሉ ሲሰጡ የተመለከትክበትን ሁኔታ ግለጽ። ደቀ መዛሙርቱ ክርስቶስ በማቴ. 5-7 ካቀረባቸው ዓይነት ግልጽ ስብከቶች፥ ስውር ትርጉም ወዳላቸው ምሳሌዎች በመዛወር፥ የማስተማር ዘዴ መቀየሩን ተመልክተዋል። ምክንያቱን በጠየቁት ጊዜ፥ እንደ ደቀ መዛሙርቱ ስለ እግዚአብሔር መንግሥት የመማር ዕድል እንደነበራቸው ገልጾአል። በክርቶስ ማመናቸውን ስላሳዩ፥ የበለጠ እውነት ጨምሮላቸዋል። ነገር ግን ሌሎች፥ በተለይም የሃይማኖት መሪዎች ክርስቶስን የመቃወም አቋም ስለወሰዱ፥ የመገንዘብ ዕድል አልነበራቸውም። ተቃውሟቸው ድንገተኛ ክስተት አልነበረም። በኢሳይያስ ዘመን ብቻ ሳይሆን፥ በክርስቶስም ዘመን የሚኖሩትን ሰዎች የገለጸውን የኢሳይያስ 6፡9-10 ትንቢት ፈጽሟል። ደቀ መዛሙርቱ ዕድለኞች ነበሩ። ምንም እንኳ የብሉይ ኪዳን ነቢያት የክርስቶስን መምጣት ሲናፍቁም፥ እርሱንም ሆነ የትንቢታቸውን ፍጻሜ ለመመልከት አልታደሉም ነበር። ለ. የአረሞች ምሳሌ ማቴ. 13፡24-30)። አይሁዶች የመሢሑ መንግሥት፥ ጠላቶቻቸውን እንደሚያወድምና በክፉዎች ላይ እንደሚፈርድ አስበው ነበር፡፡ ክርስቶስ ግን መንግሥቱ የዚያን ዓይነት መንገድ እንደማይከተል ገልጾላቸዋል። የመንግሥቱን ዘገምተኛ ዕድገት ከሁለት ሰዎች ጋር አነጻጸረ። ገበሬው ስንዴ ሲዘራ ጠላቱ ከስንዴው ጋር የሚመሳሰል እንክርዳድ ጨመረበት። ሠራተኞቹ እንክርዳዱን ለመንቀል ሲፈልጉ፥ ገበሬው ስንዴውና እንክርዳዱ አድገው በቀላሉ እስከሚለዩበት ጊዜ ድረስ እንዲታገሡ ነገራቸው። ክርስቶስ የምሳሌዎቹን ትርጉም በማቴ. 3፡36-43 ኣብራርቷል። ገበሬው ክርስቶስ፣ እርሻው ዓለም፥ ስንዴው እማኛችን ይወክላሉ። ጠላት የተባለው ሰይጣን ሲሆን፥ አረሞቹ የክርስቶስ ተከታዮች ነን የሚሉ የሰይጣን «ልጆች። ናቸው። ክርስቶስ መንግሥቱ ቀስ እያለች ስታድግ በክርስቶስና በሰይጣን መንግሥታት መካከል የማያቋርጥ ትግል እንደሚካሄድ አስረድቷል። ከዚህ ትግል ውስጥ የተወሰነው በእያንዳንዱ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ስለሚካሄድ የተሰወረ ይሆናል። ለዚህም ምክንያቱ የሰይጣንና የክርስቶስ መንግሥት ተከታዮች መኖራቸው ነው። ማን እውነተኛ፡ ማን ደግሞ ሐሰተኛ አማኝ እንደሆነ ለመረዳት ያስቸግራል። አንዳንድ ጊዜ ክርስቲያኖች፥ ክርስቲያኖች እንዳልሆኑት፥ ክርስቲያኖች ያልሆኑት ደግሞ እንደ ክርስቲያኖች ሊመላለሱ ይችላሉ። የክርስቶስ እውነተኛ ተከታዮች ያልሆኑ ሰዎች፥ ክርስቶስን «ጌታ ሆይ» ብለው ሊጠሩትና ተአምራትን ሳይቀር ሊፈጽሙ እንደሚችሉ ቀደም ብለን ተመልክተናል። እውነተኛ ክርስቲያኖችን ከሐሰተኞቹ መለየት የቤተ ክርስቲያን መሪዎችና አገልጋዮች ኃላፊነት አይደለም። የመጨረሻው ዘመን በመጣበት ጊዜ ክርስቲያኖች ባልሆኑት ላይ ፍርድ ይሰጣል። በዚያን ጊዜ በስንዴ ተምሳሌትነት የተገለጹት የእግዚአብሔር ልጆች በከፍተኛ ደረጃ ይባረካሉ። ንጹሕ ቤተ ክርስቲያን ብንሻም፣ ይህ በዘመናችን የሚሳካ አይሆንም። ሁልጊዜም ክርስቲያኖች ነን ብለው የሚገበዙና የሐሰት አስተማሪዎች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ይኖራሉ። ስለዚህ ከስንዴው ወገን ነን ወይስ ከእንክርዳዱ ብለን ራሳችንን ልንጠይቅ ይገባል። የውይይት ጥያቄ፡- ይህን እሳት በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ ያየኽው እንዴት ነው? ሐ. የሰናፍጭ ንጣትና ያእርሾ ምሳሌዎች (ማቴ 13፡31-35)። ክርስቶስ መንግሥቱ ከትንሽ ብትጀምርም እንኳ እያደገች በመሄድ ታላቅ እንደምትሆን ተናግሯል። ክርስቶስ ተመሳሳይ ፍች ያላቸውን ሁለት ምሳሌዎች ተናገረ፡፡ የሰናፍጭ ቅንጣት በአይሁዶች ዘንድ ከታወቁ ትናንሽ የተክል ዘርች አንዱ ነው፡ ነገር ግን ይህ አነስተኛ ዘር በከፍተኛ ደረጃ በማደግ የወፎች መኖሪያ እስከ መሆን ድረስ ይደርሳል፡፡ ብዙ ሑራን ይህ የወፎች ማረፊያነት ምሳሌ፥ ከዳን. 4፡20-21 እንደ መጣ ያስባሉ። ይህ ምሳሌ የክርስቶስ መንግሥት በ12 ደቀ መዛሙርት አማካኝነት በአነስተኛ ደረጃ እንደሚጀምር ያሳያል፡ ነገር ግን በምድር ላይ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አማኞች እስኪኖሩት ድረስ ማደጉን ይቀጥላል። መንግሥቱ ከፍጻሜ በሚደርስበት ጊዜ፥ ክርስቶስ በሚሊዮኖች በሚቆጠሩ ሰዎች ልብ ውስጥ ይገዛል። ይኽው መንግሥት ክርስቶስ በምድር ነገሥታት ሁሉ ላይ እስከሚቆጣጠርበት ጊዜ ድረስ ማደጉን ይቀጥላል። እርሾም በጣም አነስተኛ ነገር ነው። ነገር ቀን ትንሽ እርሾ ብዙ ሊጥ ሊያቦካ ይችላል፡፡ ብዙውን ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ እርሾን የጥፋት ተምሳሌት አድርጎ ይጠቀማል ማቴ 16፡6፤ 1ኛ ቆሮ. 5፡6-8)። እዚህ ላይ ግን እንደ ስናፍጭ ቅንጣት ሁሉ እርሾ የክርስቶስን መንግሥት መስፋፋት ያመለክታል፡፡ ከአይሁድ ሕዝብ ወይም ከርመ ሠራዊት ሲነጻጸሩ፥ ክርስቶስና ደቀ መዛሙርቱ ከቁም ነገር የማይቆጠሩ ሊመስሉ ቢችሉም፣ ከጊዜ በኋላ በአለም ሁሉ ይስፋፋሉ። የውይይት ጥያቄ፡- የእግዚአብሔር መንግሥት (ቤተ ክርስቲያንን ከአነስተኛ ጀምሮ ወደ ታነት ሊያድ የተመለከትንው እንዴት ነው? መ. የተሰወረች መዝገብና የዕንቁ ምሳሌዎች (ማቴ 13፡44-46)። የእግዚአብሔር መንግሥት ምን ያህል ገንዘብ ያመጣል? አንድ ሰው ይህን መንግሥት ለማግኘት ምን ማድረግ ይኖርበታል? የእግዚአብሔር መንግሥት ለሰው ሕይወት እጅ አስፈላጊ መሆኑንና ይህን መንግሥት ለማግኘት ሌሎች ሀብቶቻችንን መተው እንዳለብን ለማሳየት፥ ክርስቶስ እነዚህን ሁለት ምሳሌዎች ተናግሯል። አንድ ሰው ብዙ ሀብት ያለውን መሬት ለመግዛት ንብረቱን ሁሉ መሸጥ ነበረበት። እንዲሁም አንድ ነጋዴ ከፍተኛ ዋጋ ያለውን ዕንቁ ለመግዛት ትናንሽ ጌጣጌጦቹን ሁሉ ሸጠ። በዚህ መሠረት የእግዚአብሔር ዘላለማዊ መንግሥት አባል ለመሆንና እጅግ የላቀ በረከት ለመቋደስ የሚፈልጉ ሰዎች ሁሉ፥ የሚወዷቸውን ሌሎች ነገሮች ትተው መንግሥቱን መሻት ይኖርባቸዋል። የእግዚአብሔርን መንግሥት ለማግኘት፥ እያንዳንዳችን ራሳችንን የሰጠን የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት መሆን አለብን። የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ብዙ ሰዎች የሚወዷቸውን ነገሮች መተው እንዳለባቸው ሳያስቡ ክርስቲያኖች ይሆናሉ። እነዚህ ምሳሌዎች ስለ እነዚህ ሰዎች ምን ያስተምራሉ? ለ) ዛሬ ክርስቲያኖች የክርስቶስን ዘላለማዊ መንግሥት ለማግኘት ከልባቸው ከፈለጉ ሊተዉአቸው የሚገቧቸው ነገሮች ምንድን ናቸው? ሠ. የመረብና ዓሣ ምሳሌ (ማቴ. 13፡47-50)። የስንዴና እንክርዳድ ምሳሌ፥ የክርስቶስን መንግሥት ዕድገት ረዥም ሂደትና እስከ መጨረሻው ዘመን ድረስ ክርስቲያኖችና ዓለማውያን ጎን ለጎን እንደሚጓዙ ሲያመለክት፥ ይህ ምሳሌ መጭውን ፍርድ ያሳያል። ከደቀ መዛሙርቱ ብዙዎቹ ዓሣ አጥማጆች ስለነበሩ፥ ክርስቶስ ይህንን ሙያ በምሳሌነት ተጠቅሟል። ዓሣ አጥማጆቹ ከሚጠቀሙባቸው መረቦች አንዱ

ክርስቶስ በምሳሌዎች አማካኝነት ስለ እግዚአብሔር መንግሥት አስተማረ (ማቴዎስ 13:1-58) Read More »

ክርስቶስ ከሃይማኖት መሪዎች ጋር ተጋጨ (ማቴዎስ 12:1-50)

ጸጋዬ ከወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት የአንዱ መሪ ነበር። ጸጋዬ መጠነኛ የሥነ መለኮት ትምህርት ስለተከታተለ፥ የቤተ ክርስቲያኒቱ መሪዎች መጋቢያቸው አድርገው መረጡት። ጸጋዬ ከእነርሱ የበለጠ ሥልጠና ስለነበረው፥ ቤተ ክርስቲያኒቱን በመቆጣጠር የሽማግሌዎችን ቦርድ ተጫነ፡፡ ብዙም ሳይቆይ አምባገነን ሆነ። ሰዎችን «እንዲህ አድርጉ፥ አታድርጉ» እያለ ያዝዝ ጀመር። እርሱ ግን ትእዛዙን ለመፈጸም ደፋ ቀና ሲሉ አይረዳቸውም ነበር። ብዙውን ጊዜ የሰዎችን ኃጢአት እያጋለጠና በፀያፍ ቃላት እየተጠቀመ ይሰብክ ነበር። ጸጋዬ ቁጡ፥ ቁጥጥሩ ጠንካራ፥ እና በትምህርቱና በሥልጣኑ ይኩራራ የነበረ ሰው ነበር። የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) የጸጋዬ አመለካከት ከክርስቶስ የሚለየው እንዴት ነው? ለ) ማቴ. 12-13ን አንብብ። ስለ ክርስቶስና ከሃይማኖት መሪዎች ጋር ስለነበረው ግንኙነት ምን እንማራለን? ሐ) ይህ ስለ ደቀ መዝሙርነት ምን ይነግረናል? ክርስቶስ ከሃይማኖት መሪዎች ጋር ተጋጨ (ማቴ. 12) ክርስቶስ የዋህና ትሑት ቢሆንም፥ ቅን ያልሆኑ ሰዎችንና ክፋትን መቃወሙ አልቀረም። በአዲስ ኪዳን ሁሉ፥ ክርስቶስ የተራ ሰዎችን ኃጢአት አጥብቆ እንዳልተቃወመ እንመለከታለን። የሮምን መንግሥት ክፋት ያን ያህል አልተቃወመም። እርሱ አጥብቆ የተቃወመው እንደ ጸጋዬ ያሉትን የሃይማኖት መሪዎች ክፋት ነበር። ትዕቢተኞችን፥ ድሆችን የሚበድሉ፥ የእነርሱን የመንፈሳዊነት ግንዛቤ የማይከተሉትን ሰዎችና ነገሮችን ሁሉ የሚቃወሙ የሃይማኖት መሪዎችን ኃጢአት ይጠላ ነበር። ክርስቶስ የሃይማኖት መሪዎችን ኃይል የሚገድብ፥ ፍጹም የተለየ የመንፈሳዊነትና የአመራር አቅጣጫ እያስተማረ ስለነበር፥ ከፈሪሳውያን ጋር መጋጨቱ አልቀረም ነበር። ማቴዎስ በ12ኛው ምዕራፉ፥ የሃይማኖት መሪዎች ክርስቶስን ለምን እንደጠሉትና እንዲሰቀልም ለምን እንደፈለጉ ለአይሁዶች ይገልጻል። ይህ ክፍል የቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ሥልጣን ለተሰጠን ሰዎች ጠንካራ ማስጠንቀቂያ ነው። ዛሬ ክርስቶስ በኢትዮጵያ ከተሞች ውስጥ እየተመላለሰ ቢሆን፥ በእኛም ላይ ጠንካራ ቃላት ይሰነዝር ይሆን? በዚህ ክፍል፥ ማቴዎስ ክርስቶስ ከሃይማኖት መሪዎች ጋር እንዴት እንደተጋጨ ምሳሌዎችን ይሰጠናል። በዚህም ማቴዎስ ክርስቶስ በሰው ሠራሽ ሕጎች ላይ ሥልጣን እንዳለው በማሳየት፥ ወደፊት የሚነሡ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች በሕግጋት ላይ ሳይሆን፥ ከእግዚአብሔር ጋር ግላዊ ግንኙነት በማድረጉ ላይ እንዲያተኩሩ አሳስቧል። ሀ. በሰንበት እሸትን በመቅጠፍ የተነሣ ክርስቶስ ከፈሪሳውያን ጋር ተጋጨ (ማቴ. 12፡1-8)። ቀደም ብለን እንደተመለከትነው፥ ፈሪሳውያን እግዚአብሔርን ለማስደሰት ብዙ የተለያዩ ሕግጋት የሚጠብቁ አጥባቂ ሃይማኖተኞች ነበሩ። እነርሱም የአይሁዶች የአምልኮ ቀን ስለሆነው ሰንበት ብዙ ሕግጋት አውጥተው ነበር። ብሉይ ኪዳን አይሁዶች ሰንበትን የዕረፍት ቀን አድርገው እንዲጠብቁ አስጠንቅቋቸው ነበር (ዘጸ. 31፡14–17ን አንብብ)። በብሉይና በአዲስ ኪዳን መካከል በነበረው ዘመን ሰንበትን መጠበቅ እግዚአብሔርን ማስደሰት ከሚቻልባቸው ዐበይት መንገዶች አንዱ ተደርጎ ይወሰድ ነበር (ነህ. 13፡15-22ን አንብብ)። ስለሆነም፥ የሃይማኖት መሪዎች የተለያዩ ደንቦችን፥ (በ39 ምድቦች የሚከፈሉ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሕግጋት አውጥተው ነበር)። እነዚህ ሰዎች ብዙ ሕግጋትን መጠበቅ አንድ ሰው እግዚአብሔርን ደስ በሚያሰኝ መንገድ ሰንበትን እንደሚያከብር ያሳያል ብለው ያስቡ ነበር። ስለሆነም፥ ፈሪሳውያን የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት በሰንበት እሸት ሲቀጥፉ ሳሉ ክርስቶስ ሳይከለክላቸው ስለቀረ፥ ቁጣቸውን ገለጹ። ክርስቶስ ግን ያደረገው የእነርሱን ተቃራኒ ነበር። ክርስቶስ ያከበረው እግዚአብሔር ሰንበትን ቅዱስ አድርጎ የለየበትን መንፈስ ነበር። ሰው ሠራሽ ደንቦች ከመንፈሳዊነትና አንድ ሰው ከእግዚአብሔር ጋር ከሚያደርገው ግንኙነት ጋር የሚገናኙ ባለመሆናቸው፥ እነርሱን ያለመጠበቅ ነጻነት ነበረው። እንዲያውም፥ አዲስ የተጨመሩት የሃይማኖት መሪዎች ሕግጋት፥ ሰዎች «ከእግዚአብሔር ጋር እንደ አብርሃም ሕያውና ግላዊ ግንኙነት የማደርገው እንዴት ነው?» ብለው እንዳይጠይቁ ስለከለከሏቸው፥ እግዚአብሔር የፈለገውን መልእክት እንዳስተጓጎሉ ያውቅ ነበር። ሕዝቡ የተጨመሩትን ሕግጋት ለመፈጸም ይታገል ነበር። በተመሳሳይ ሁኔታ፥ የቤተ ክርስቲያን ሕግጋት መልካሞች ሊሆኑ ቢችሉም፥ ሰዎች ከሁሉም በላይ አስፈላጊ የሆነውን ከእግዚአብሔር ጋር የሚደረግ ግንኙነት አቋርጠው በሕግጋቱ ላይ እንዲያተኩሩ ካደረጉ፥ አደገኞች ናቸው። ክርስቶስ ከፈሪሳውያን ክስ ምላሽ የሰጠው በአራት የተለያዩ መንገዶች ነበር፦ እግዚአብሔር ሕጉን ከመከተሉ በላይ የሚያሳስበው የግለሰብ የልብ አመለካከት ነው። ስለሆነም፥ እግዚአብሔር አንዳንድ ጊዜ ለበለጠ ዓላማ ሕጎች እንዲጣሱ ይፈቅዳል። ክርስቶስ አይሁዶች ጀግናቸው አድርገው ስለሚመለከቱትና የእግዚአብሔር የልብ ወዳጅ ስለነበረው ዳዊት፥ አንድ እውነት አሳሰባቸው። ይህም ምንም እንኳ ለካህናት ብቻ የተፈቀደውን ኅብስት በቤተ መቅደስ ውስጥ መብላት የተከለከለ ቢሆንም፥ እግዚአብሔር ዳዊት ኅብስቱን ስለበላ እንዳልቀጣው ነበር። ዳዊት ይህን ሕግ እንዲጥስ የተፈቀደለት፥ ከእግዚአብሔር ጋር ከነበረው ግንኙነትና እግዚአብሔርም ከዚያ የበለጠ ችግር እንደደረሰበት በመገንዘቡ ነበር። ከእግዚአብሔር ጋር የነበረው ግንኙነት ከሕግ ፊደል በላይ አስፈላጊ የሆነ ነበር። በየሰንበቱ ካህናት የሰንበትን ሕግ ለመተላለፍ ይገደዱ ነበር። ሕጉ «ማንም እንዳይሠራ» ቢደነግግም፥ ካህናት የግድ መሥዋዕቶችን ማቅረብና ቤተ መቅደሱን መንከባከብ ያስፈልጋቸው ነበር። ይህም እግዚአብሔር ሰዎች በሰንበት ቀን እንዲሠሩ እንደፈቀደ ያሳያል። ካህናት እርሱን በማገልገል ላይ በመሆናቸው፥ ክርስቶስ ሕጉን እንዲጥሱ ፈቅዶላቸዋል። ክርስቶስ ግን ከካህናት በላይ በመሆኑ፥ ሰው ሠራሽ ደንቦችን በጣሰ ነበር። አንድ ሰው ከክርስቶስ ጋር የሚያደርገው ግንኙነት፥ ሰዎች እግዚአብሔርን ለማምለክ ከሠሯቸው ደንቦች ሁሉ ከመከተል ይበልጣል። የሃይማኖት መሪዎች ሕግጋትን በመጠበቁ ላይ፥ ከመጠን በላይ በማተኮራቸው፥ ብሉይ ኪዳን ስለ አምልኮ ምን እንደሚያስተምር ዘንግተው ነበር። እግዚአብሔር ከሕግጋትና ደንቦች ይልቅ በግንኙነቶች ላይ የሚያተኩር አምላክ ነው። በመሆኑም በብሉይ ኪዳን ሁሉ የአምልኮ አመለካከት (ለምሳሌ፦ መታዘዝ [1ኛ ሳሙ. 15፡22]) እና አንድ ሰው ከሌሎች ጋር ያለው ግንኙነት (ለምሳሌ፥ ምሕረት [ሆሴዕ 6፡6]) ለእግዚአብሔር ከውጫዊ የሕግ ተገዥነትና ሰው ሠራሽ የአምልኮ ሥርዓቶች ይበልጣል። የሃይማኖት መሪዎች በሕግጋት ላይ በማተኮራቸው እግዚአብሔር ከእርሱና ከሌሎችም ጋር የፍቅር ግንኙነት እንዲመሠርቱ መፈለጉን ዘንግተው ነበር። እግዚአብሔር የሰንበትን ቀን የለየው ሰዎች እርሱን እንዲያመልኩና እርስ በርሳቸው እንዲተጋገዙ ለማበረታታት ነበር። ይህ ካልሆነ ሰዎች በየዕለት ሥራዎቻቸው ተጠምደው እርሱን ለማምለክና የተቸገሩትን ሰዎች ለመርዳት ጊዜ እንደማያገኝ ያውቅ ነበር። አምላክ የሆነው መሢሕ ራሱ በመካከላቸው ነበር። ስለሆነም፥ ስለ ሰንበት ሕግጋት የእግዚአብሔርን ልብ ስለሚያውቅ፥ የብሉይ ኪዳን ሕግጋትን የመበየንና የመተርጎም ሥልጣን ነበረው። ለ. በሰንበት ዕለት ሰው በመፈወሱ ምክንያት ከፈሪሳውያን ጋር መጋጨቱ (ማቴ. 12፡9-14)። ማቴዎስ በሌላ ክስተት ተጠቅሞ አይሁዶች ክርስቶስን ለምን አጥብቀው እንደጠሉት አብራርቷል። በሰንበት ቀን ሰው ስለፈወሰ ሊገድሉት ቆርጠው ተነሡ። ክርስቶስ በሰንበት ቀን በመፈወሱ፥ እግዚአብሔር ከሃይማኖታዊ ተግባራት በላይ ምሕረትን እንደሚወድ አሳይቷል። ክርስቶስ ፈሪሳውያን እየተከታተሉት እንደሆነ ቢያውቅም፥ ስለ ሕጉ ከነበራቸው የተሳሳተ ግንዛቤ ሊመልሳቸው ፈለገ። ስለሆነም፥ ፈሪሳውያኑን ቅድሚያ ሊሰጣቸው ስለሚገባቸው ነገሮች ለማስተማር እጁ የሰለለችውን ሰው ፈወሰ። ክርስቶስ ሰው ሠራሽ ሕግጋት ሰዎች ሰዎችን እንዳይረዱ በሚከለክሉበት ጊዜ፥ እነዚህን ሕግጋት ማስወገድ እንደሚገባ አስተምሯል። ራሳቸው የሃይማኖት መሪዎች እንኳ የበግ ከጉድጓድ ውስጥ መውደቅ ዓይነት ድንገተኛ አደጋ በሚያጋጥምበት ጊዜ፥ ሰዎች የሰንበትን ሕግጋት እንዲያፈርሱ ይፈቅዱላቸው ነበር። ነገር ግን ድንገተኛ አደጋ በማይኖርበት ጊዜ (ግለሰቡ እስከ ነገ በሕይወት ሊቆይ ካልቻለ በቀር)፤ እርዳታ ማድረጉ እንደ ኃጢአት ይቆጠር ነበር። ሰው ለእግዚአብሔር ከእንስሳ በላይ ጠቃሚ ስለሆነ እርዳታ ማድረጉ እንስሳትን ከመሠዋት፥ ከመዘመር፥ ከመጸለይ እኩል እግዚአብሔርን የሚያስከብር ተግባር ነበር። የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ዛሬ ክርስቲያኖች የሚከተሏቸውና ከእግዚአብሔር ይልቅ በሕግጋት ላይ እንዲያተኩሩ የሚያደርጓቸው ሰው ሠራሽ ደንቦች ምንድን ናቸው? ለ) ሰዎች ከእግዚአብሔር ጋር ሕያው ግንኙነት ከማድረግና ለሌሎች ከፍቅርና ርኅራኄ የመነጨ እገዛ ከመስጠት ይልቅ በአምልኮ ተግባራት ላይ ሊያተኩሩ የሚችሉባቸው መንገዶች ምንድን ናቸው? ሐ. የክርስቶስ ተግባራትና ባሕርያት የብሉይ ኪዳን ትንቢቶችን ይፈጽማሉ (ማቴ. 12፡15-21)። ማቴዎስ በክርስቶስና በሃይማኖት መሪዎች መካከል ስለተከሰተው ሌላ የግጭት ምሳሌ ከመግለጹ በፊት፥ ክርስቶስ በኢሳ. 42፡1-4 ስለ መሢሑ ከተነገሩት እጅግ ጠቃሚ ትንቢቶች አንዱን እንደፈጸመ አመልክቷል። ፈውሱ፥ ትምህርቱና አመለካከቱ ሁሉ ኢሳይያስ የተነበየለት የእግዚአብሔር ባሪያ መሆኑን አሳይቷል። ክርስቶስ ከሃይማኖት መሪዎች ጋር ባካሄደው ግብግብ ለፍትሕና ለሰዎች ሁሉ ትክክል ስለሆነው ጉዳይ ተሟግቷል። ነገር ግን ለሰዎች የነበረው አመለካከት የሃይማኖት መሪዎች ወይም የሮም ባለሥልጣናት የሚያራምዱት ዓይነት አልነበረም። ሰዎችን አልገፋም፥ አልገፈተረም። ከማላቱ በላይ በተግባሩ የእግዚአብሔርን ባሕርያት እያሳያቸው በዝምታ ተመላልሷል። የሰዎችን ትኩረት ወደ ራሱ ለመሳብ አልሞከረም። ለዚህ ነበር ክርስቶስ ሰዎች ስለ ተአምራቱ እንዳይናገሩ ያስጠነቀቃቸው (ማቴ. 12:16)። መሢሕ ቢሆንም ክርስቶስ እጅግ ገር በመሆኑ፥ «የተቀጠቀጠን ሸንበቆ» አይሰብርም። ይህም የሰዎችን የተጎዳና የተዳከመ አኗኗር የሚያመለክት አገላለጽ ነበር። የዓለም ፈጣሪ ቢሆንም፥

ክርስቶስ ከሃይማኖት መሪዎች ጋር ተጋጨ (ማቴዎስ 12:1-50) Read More »

ማቴዎስ 11፡1-30

የውይይት ጥያቄ፡– ስለ እምነትህ የተጠራጠርህበትን ጊዜ ግለጽ። የተጠራጠርኸው ምን ነበር? በክርስቶስ ላይ ያለህን እምነት መልሰህ እንድትቀዳጅ የረዳህ ምን ነበር? በአንድ ወይም በሌላ ጊዜ ሁሉም ክርስቲያኖች ጥርጣሬዎች ይኖሯቸዋል። ለጸሎትህ መልስ ስትጠብቅ አይመጣም፤ ደግሞም እግዚአብሔር በዚህ መንገድ ይሠራል ብለህ የማታስበው አንድ ነገር ይከሰታል። የመኪና አደጋ ደርሶ ለአገልግሎት የወጣ ጠንካራ ክርስቲያን ወንድም ሽባ ይሆናል። በእንዲህ ዓይነት ጊዜያት እግዚአብሔርን ልንጠራጠር እንችላለን። መጥምቁ ዮሐንስ ለተወሰነ ጊዜ ታስሮ ቆይቶ ነበር። ደቀ መዛሙርቱ ክርስቶስ ስለሚያከናውናቸው ተግባራት ቢገልጹለትም፥ ለዮሐንስ ስሜት አልሰጠውም። የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀትና የእሳት ፍርድ የታሉ? ክርስቶስ ክፉዎችን አጥፍቶ የጽድቅ መንግሥቱን የሚጀምረው መቼ ነው? ክርስቶስ የመጣው እርሱ ከጠበቀው መንገድ ሙሉ በሙሉ በተለየ ሁኔታ በመሆኑ፥ ዮሐንስ ግራ ተጋባ። እግዚአብሔር የክርስቶስን መሢሕነት ለእርሱ መግለጹ ስሕተት ይሆን? ስለሆነም፥ ዮሐንስ «የክርስቶስን መሢሕነት ወይም ሌላ መጠበቅ እንዳለባቸው» ለማረጋገጥ ደቀ መዛሙርቱን ወደ ክርስቶስ ላከ። ክርስቶስ ወደ ተአምራቱ በማመልከት፥ «እግዚአብሔር በእኔ በኩል ያደረገውን ሄዳችሁ ንገሩት። እነዚህ ለመሢሕነቴ በቂ ማረጋገጫዎች ናቸው፤ አትጠራጠር በሉት» አላቸው። ማቴዎስ ተመሳሳይ ጥርጣሬ ለነበራቸው አይሁዶችም ይህንኑ ምላሽ ሰጥቷቸዋል። አይሁዶች መሢሕ ድል ነሺ ንጉሥ እንደሚሆን ጠብቀው ነበር። ማቴዎስ በመጽሐፉ «ክርስቶስ ያደረጋቸውን ተአምራት ተመልከቱ። እነዚህን ተአምራት እንዳደረገ ታውቃላችሁ፤ እነርሱም የመሢሕነቱ ማረጋገጫዎች ናቸው። ሌላ ሰው አትፈልጉ» ሲል አስረድቷል። ለጥርጣሬዎች ምላሽ ለመስጠት የእግዚአብሔርን ቃል እውነት እንጠቀማለን። ክርስቶስም የመጥምቁ ዮሐንስን ዓይኖች ለእግዚአብሔር እውነቶች አብርቷል። ክርስቶስ በዚህ ጊዜ ለሕዝቡ ስለ ዮሐንስና ከመጪው እግዚአብሔር መንግሥት ጋር ስላለው ግንኙነት አስተምሯል። ባማረ ልብስ ባያጌጥና ተአምራት ባይሠራም፥ ዮሐንስ ለመሢሑ መንገድ እንዲጠርግ የተላከ ክቡር ነቢይ ነበር። ስለሆነም፥ ዮሐንስ ታላቅ አገልጋይ ነበር። ከዚያ በኋላ ክርስቶስ ለመረዳት የሚያስቸግር አሳብ ሰንዝሯል። ዮሐንስ ታላቅ ቢሆንም፥ በመንግሥተ ሰማይ እጅግ አነስተኛ የሆነው ሰው ይበልጠዋል። ክርስቶስ ይህን ሲል ምን ማለቱ ነው? በክርስቶስ መምጣት አዲስ የዘመን ምዕራፍ ተከፍቷል። የብሉይ ኪዳን ዘመን አብቅቶ የአዲስ ኪዳን ዘመን እየተጀመረ ነበር። ዮሐንስ ታላቅ ነቢይ ቢሆንም፥ የብሉይ ኪዳን ዘመን አካል ነበር። መሢሑን ለዓለም የማስተዋወቅን ልዩ ዕድል ስላገኘ፥ የአሮጌው ዘመን ታላቅ ነቢይ ነበር። ነገር ግን የክርስቶስን ሞትና ትንሣኤ ለማየት አልታደለም ነበር፤ የቤተ ክርስቲያን አባል አልሆነም ነበር። አዲሱ ዘመን ከብሉይ ኪዳን ዘመን ስለሚልቅ፥ የአዲሱ ዘመን ተራ አባል ከአሮጌው ዘመን ታላቅ ሰው ይበልጣል። ክርስቶስ በተጨማሪም፥ «ከመጥምቁም ከዮሐንስ ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ መንግሥተ ሰማይ ትገፋለች፤ ግፈኞችም ይናጠቋታል» ብሏል። ይህም ለመረዳት የሚያስቸግር አሳብ ነው። አንዳንድ ምሑራን ከማቴዎስ 10 ዐውድ በመረዳት፥ ስደትን እንደሚያመለክት ይገልጻሉ። በአንድ በኩል፥ የእግዚአብሔር መንግሥት መስፋፋት ጠላትን እያሸነፈ ነበር። ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያኑን እንደሚመሠርትና የገሃነም ደጆች እንደማይቋቋሟት ገልጾታል። ከመጥምቁ ዮሐንስ ዘመን ጀምሮ፥ ይህ ሁኔታ በመካሄድ ላይ ቆይቷል። በተመሳሳይ ጊዜ፥ የእግዚአብሔርን መንግሥት መስፋፋት የሚቃወሙ ሰዎች ነበሩ። ስደት የቤተ ክርስቲያን የማይቋረጥ ሂደት ነው። መጥምቁ ዮሐንስ የታሰረ ሲሆን፥ ክርስቶስ ደግሞ ተሰቅሏል። በታሪክ ሁሉ፥ ቤተ ክርስቲያን ስደትን ስትጋፈጥ ቆይታለች። መጥምቁ ዮሐንስና አይሁዶች የመሢሑ መንግሥት ከመቅጽበት መጥቶ አሕዛብን ወይም የክፋት ኃይሎችን ሁሉ እንደማያስወግድ መገንዘብ ነበረባቸው። የእግዚአብሔር መንግሥት ቀስ በቀስ እያደገ ሲሄድ፥ የክፉ ሰዎች ተቃውሞ አይለየውም። ምሑራን የክርስቶስን አሳብ የሚረዱበት ሌላው መንገድ የእግዚአብሔር መንግሥት አካል ለመሆን ጥረትን እንደሚጠይቅ ነው። አንድ ሰው የክርስቶስ ተከታይ ሆኖ ካለመወለዱም በላይ፥ ምርጫውም ቀላል አይደለም። የመንግሥቱ አካል መሆንን፥ አንድ ሰው ከምንም ነገር በላይ ሊሻው ይገባል። ሁልጊዜም ስደት ስለሚኖር፥ ብርታት፥ ኃይልና ቁርጥ ውሳኔ አስፈላጊዎች ይሆናሉ። ከዚያም ክርስቶስ አይሁዶች የእግዚአብሔርን አሠራር ለመገንዘብ ባለመቻላቸውና በሌሎች ላይ በመፍረዳቸው ገሥጿቸዋል። መጥምቁ ዮሐንስ ቆዳ ለብሶ ጠንካራ የፍርድ መልእክት እየሰበከ ሲመጣ፥ «ወግ አጥባቂ ነው» አሉት። ይህም በጋኔን ቁጥጥር እንደሚሠራ የመግለጽ ያህል ነበር። ክርስቶስ ደግሞ ከሰዎች ጋር በመብላትና በመጠጣት የቅርብ ወዳጃቸው ሆነ። ከኃጢአተኞች ጋር ወዳጅነትን በመመሥረቱ፥ ብዙውን ጊዜ ይጋብዙት ነበር። አይሁዶች ግን ይህን ባሕርዩን በመጥላት ቀለል ያለ በላተኛና ጠጪ እንደሆነ ተናገሩ። በቂ መንፈሳዊነት እንደሌለውና የቀራጮችና ኃጢአተኞች ወዳጅ በመሆን የተሳሳተ ዝምድና እንዳፈራ ገለጹ። የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ክርስቶስ ከሴተኛ አዳሪዎች፥ ከጎዳና ተዳዳሪዎችና ዱርዬዎች ጋር ወዳጅነትን እየጠበቀ በቤተ ክርስቲያንህ ቢያገለግል፥ ምን ዓይነት ስም የሚሰጠው ይመስልሃል? በሽማግሌዎች የሚወደድ ይመስልሃል? ለምን? ለ) ክርስቶስ በዚህ ተግባሩ የማይወደድ ከሆነ፥ ይህ ክርስቶስን መምሰልን አስመልክቶ የተሳሳተ አመለካከት መያዛችንን የሚያሳየው እንዴት ነው? ክርስቶስ ሰዎች ንስሐ ባልገቡባቸው ከተሞች ላይ ፍርድን ማወጁ እና ለሚያምኑበት ዕረፍትን እንደሚሰጣቸው መግለጡ (ማቴ. 11፡20-30) ብዙ ከተሰጠው ብዙ እንደሚጠበቅ የሚያመለክት መጽሐፍ ቅዱሳዊ መርሕ አለ (ሉቃስ 12፡48)። ይህም ገንዘብ፥ ትምህርት፥ የክርስቶስ እውቀትና መንፈሳዊ ስጦታ ላላቸው የሚሠራ ነው። እግዚአብሔር ለእያንዳንዳችን ይህን ስጦታ የሰጠን ለክብሩ እንደምንጠቀምበት በመገንዘብ ሲሆን፥ እንዴት እንደተጠቀምንበት ይጠይቀናል። የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) እግዚአብሔር እንደ በረከት የሰጠህን አንዳንድ ነገሮች ዘርዝር። ለ) እነዚህን ነገሮች እግዚአብሔርን በሚያስከብር መንገድ የምትጠቀምባቸው እንዴት ነው? የኮራዚንና የቤተሳይዳ ከተሞች፥ ክርስቶስ አብዛኞቹን ተአምራት ባደረገበት በገሊላ ውስጥ የሚገኙ ስፍራዎች ነበሩ። በዚያ ዘመን እነዚህ ከተሞች ከሌሎች ከተሞች ሁሉ በላይ ተባርከው እንደነበር ታሪካቸው ይመሰክራል። ክርስቶስን በሥጋ ማየታቸውና ተአምራቱን መመልከታቸው ኃላፊነትን የሚያስከትል በረከት ነው። ክርስቶስ ተአምራቱን እየተመለከቱ ያላመኑበት ሰዎች በመሢሕነቱ ሊያምኑ እንደሚገባቸው አስጠንቅቋቸዋል፤ ክርስቶስ ሊዶናና ጢሮስ የተባሉት የአሕዛብ ከተሞች እነዚህን ተአምራት ቢመለከቱ ኖሮ፥ በእርሱ ያምኑ እንደነበር ተናግሯልና። ነገር ግን አይሁዶች እርሱን ባለመቀበላቸው የእግዚአብሔርን ልጅ ካላዩት ሰዎች ይልቅ ጥፋተኞች መሆናቸውን አሳይተዋል። ሰዶምና ገሞራ የአይሁዶችን ያህል ግልጽ ምስክርነት አላገኙም ነበር። ስለሆነም በአይሁዶች ላይ ፍርድ ይሰጣል። በ70 ዓ.ም. ብዙ ከተሞቿ በመደምሰሳቸው ገሊላ ፍርዱን የተቀበለች ስትሆን፥ ሌሎች አይሁዶች በመጨረሻው ዘመን ፍርድን ያገኛሉ። ማቴዎስ በዚህ መልእክቱ በዘመኑ የነበሩትን አይሁዶችና በየትኛውም ዘመን የሚኖሩትን ሰዎች እያስጠነቀቀ ነበር። ወንጌሉ ተጨማሪ ተጠያቂነትን ያስከትላል። ወንጌሉን ከሰሙና የመንፈስ ቅዱስን ሥራ ከተመለከቱ በኋላ፥ በክርስቶስ ለማመን የማይፈልጉ ሰዎች ስለ ክርስቶስ ሰምቶ ከማያውቅ ሰው የከፋ ቅጣት ይጠብቃቸዋል። ክርስቶስ ለሚያምኑበት ዕረፍትን እንደሚሰጣቸው ቃል ገባ (ማቴ. 11፡25-30) ወንጌሉ ሁልጊዜም የሚያምኑትን ሰዎች ከማያምኑት ይለያል። ክርስቶስ አብዛኛው ሰው በእርሱ ባለማመኑ ተስፋ ሳይቆርጥ፥ በዘመናት ሁሉ እውነት የሆነውን ምሥጢር ለመመልከት ችሏል። በአጠቃላይ፥ እንደ ፈሪሳውያንና የዩኒቨርሲቲ መምህራን ምድራዊ ዕውቀት የነበራቸው ሰዎች ወንጌሉን ከሞኝነት ስለቆጠሩት ወንጌሉን አልተቀበሉም ነበር። እንደ ሊቀ ካህናትና የሮም ገዥዎች ያሉት ሀብታሞችና ባለሥልጣናትም ልባቸውን በሌሎች ነገሮች ስላጣበቡ፥ ወንጌሉን ለመቀበል አልፈለጉም። ዓለም የናቃቸው ድሆች ግን በክርስቶስ አመኑ። አብዛኞቹ የቀድሞይቱ ቤተ ክርስቲያን አባላት፥ ባሮችና ድሆች የነበሩ ሲሆን፥ ይኸው ሁኔታ በታሪክ ሂደት ውስጥ ሁሉ ቀጥሏል። የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) 1ኛ ቆሮ. 1፡18–31ን አንብብ። ጳውሎስ ይህን የወንጌል ምሥጢር ያብራራው እንዴት ነው? ለ) አንዳንድ ጊዜ ጠቢባንን፥ ሀብታሞችንና ኃይለኞችን ለመማረክ እየሞከርንና ድሆችንና የተናቁትን እየተውን ይህንን ምሥጢር ችላ የምንለው እንዴት ነው? ክርስቶስ ሊከተሉት የሚፈልጉት ተራ ሰዎች መሆናቸውን በመገንዘቡ፥ እግዚአብሔርን ለሚሠራበት መንገድ አመሰገነው። ክርስቶስ፥ ደኅንነት የሰው ሥራ ሳይሆን የእግዚአብሔር ሥራ መሆኑን ገልጾታል። እግዚአብሔር የመንግሥቱን ምሥጢራት ለልጁ ለኢየሱስ ክርስቶስ ሰጥቷል። ክርስቶስም የወንጌሉን ምሥጢራት ገልጾ ለመረጣቸው ሰዎች ሰጥቷል። ይህ በሲኖፕቲክ ወንጌላት ውስጥ ከቀረቡት የክርስቶስን አምላክነት ከሚያስረዱትና ከእግዚአብሔር አብ ጋር ያለውን ልዩ ግንኙነት ከሚያሳዩት ግልጽ መግለጫዎች አንዱ ነው። ክርስቶስ አንድ ሰው እርሱን ለመከተልና ለመዳን የሚያጋጥመውን ስደት ከገለጸ በኋላ፥ አሁን ደግሞ ሌላኛውን የወንጌሉን ምሥጢር ገጽታ ያሳያል። ክርስቶስ፥ የሕይወት ውጥረትና ሸክም ያደከማቸው ሰዎች ወደ እርሱ እንዲመጡ ጋብዟል። ፈሪሳውያንና ሌሎች የሃይማኖት መሪዎች ብዙ ሕጎቻቸውን በሰዎች ላይ ሲጭኑ፥ ክርስቶስ ከባድ ነገር እንደማይጠይቃቸው ተናግሯል። የምንፈልገውን አግኝተን ውስጣዊ ሰላም የምናገኘው በክርስቶስ ብቻ ነው። ነገር ግን ሌሎች ሰዎች የደቀ መዝሙርነትን መንገድ ይከተሉ ዘንድ፥ ሕይወታችን ከክርስቶስ ጋር እንዲጣመር (ልክ ሁለት በሬዎች በአንድ ቀንበር እንደሚጣመሩ) ልናደርግ ይገባል። ልባችንንና ሕይወታችንን

ማቴዎስ 11፡1-30 Read More »

የዐሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት መላክ (ማቴዎስ 10:1-42)

ክርስቶስ ታላቁ መምህርና ፈዋሽ ብቻ ሳይሆን፥ ዋና አሠልጣኝም ነበር። ብዙውን ጊዜ ስለ ትምህርት ስናስብ፥ በትምህርት ቤት የተወሰኑ እውነቶችን ተምሮ ቤተ ክርስቲያንን ስለ መምራት እናስባለን። ይህን ዓይነቱን ሥልጠና ካገኘን በኋላ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለማገልገል ብቁዎች ነን ብለን እናስባለን። የዚህ ዓይነቱ የአመራር ሥልጠና ዓይነት የቤተ ክርስቲያንን ፍላጎቶች ለማሟላት አልቻለም። በትምህርት ቤት ውስጥ መማር የክርስቶስ ሥልጠና ተቃራኒ ነው። ክርስቶስ መጽሐፍ ቅዱስ ያልነበረው ከመሆኑም በላይ ቁጭ ብሎ ንድፈ አሳቦችን (ቲዎሪ) አላስተማረም። በአንድም ጊዜ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን አላስተማረም። ለክርስቶስ አገልግሎት ውጤታማነት ከሚጠቀሱት ዐበይት ነገሮች አንዱ፥ ደቀ መዛሙርቱን ያማከለበት ሁኔታ ነው። ደቀ መዛሙርቱን ደህና አድርጎ ባያሠለጥናቸው ኖሮ፥ ክርስቶስ ወደ ሰማይ እንደ አረገ ቤተ ክርስቲያን ትሞት ነበር። ነገር ግን ደቀ መዛሙርቱ እንደ ክርስቶስ ለመሆን በመብቃታቸው፥ ቤተ ክርስቲያን ጠቅላላውን የሮም ግዛት በአንድ ትውልድ እስክታጥለቀልቅ ድረስ አደገች። እንግዲህ፥ ከክርስቶስ ሥልጠና ውስጥ ልንመለከታቸውና ዓለምን የሚለውጡ መሪዎችን ለማፍራት የምንጠቀምባቸው ቁልፍ አሳቦች ምንድን ናቸው? ክርስቶስ የሕያው እምነትና ከእርሱ ጋር የተጋጋለ ግንኙነት የማድረግን ሁኔታ አሳይቷል። ደቀ መዛሙርቱ ሁሉ ከክርስቶስ ጋር ኖረው ለሦስት ዓመታት ያህል ሲመለከቱት ቆይተዋል። በዚህም ከቃላቱ ይልቅ ከምሳሌው የበለጠ ተምረዋል። ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱ እንዴት እንደሚያስተዳድሩ፥ እንደሚሰብኩና እንዴት ተአምራትን እንደሚፈጽሙ ሳይሆን፥ እንዴት የተለወጠ ባሕርይ ሊኖራቸው እንደሚችል አስተምሯቸዋል። ብዙውን ጊዜ አንድ ሰው አንድን ተግባር እንዴት እንደሚያከናውን ማሳየቱ ቀላል ነው። ነገር ግን ባሕርዩን ወደ መንፈሳዊ መሪነት መለወጡ የበለጠ አስቸጋሪ ነው። ብዙ እውቀት ኖሮት የመንፈሳዊ አመራር ባሕርይ የሌለው ሰው፥ ሰይጣን ቤተ ክርስቲያንን ለማውደም የሚጠቀምበት መሣሪያ ነው። ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱ ትክክል ነው ብለው ያሰቡትን የዓለምን የአመራር ሁኔታ በጥብቅ ተቃውሟል። ደቀ መዛሙርቱ ኃይልን፥ ሥልጣንንና የመሪነትን ጥቅሞች ለማግኘት ሲፈልጉ፥ ክርስቶስ ግን መሪነት አገልግሎት እንደሆነ ገልጾላቸዋል። ይህንንም እግራቸውን በማጠብ አርአያነቱን ያሳያቸው ሲሆን፥ የዚህ ዓይነቱ አመራር አገልግሎት መሆኑን አስተምሯቸዋል። ክርስቶስ በመንግሥቱ ውስጥ ታላቁ የተባለ ሰው የሌሎችን ፍላጎቶች ከራሱ የሚያስቀድምና ዝቅ የሚልና የሚያገለግል እንደሆነ በመግለጽ አስተማራቸው። ዛሬ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚታየው ትልቁ ችግር ብዙ መሪዎች አሁንም የዓለምን የአመራር አመለካከት የሚያንጸባርቁ መሆናቸው ነው። ክርስቶስ እንዴት በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ማገልገል እንደሚቻል አሳይቷል። እንዴት ማስተማር፥ መስበክ፥ መፈወስ፥ መጸለይ እንደሚቻል በራሱ ምሳሌነት አስተምሯቸዋል። ከክርስቶስ ዕርገት በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ያደረጉት ሁሉ እርሱ ሲያደርግ የተመለከቱት ነበር። የክርስቶስ ትምህርት እውነትን ከሕይወት ጋር የማዛመድ ተግባር ነበር። ክርስቶስ ያስተማረው ስለ እግዚአብሔር እውነትን ወይም በንድፈ አሳባዊ መንገድ መመስከርን አልነበረም። ክርስቶስ የተመላለሰውና ያስተማረው ምሳሌዎችንና የዕለት ተዕለት ሁኔታዎችን ተጠቅሞ ለደቀ መዛሙርቱ መንፈሳዊ እውነቶችን በመግለጽ ነበር። ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱ እርሱ እየተመለከታቸው እንዲያገለግሉ በማድረግ ሲያጠፉ አርሟቸዋል (ይህንን በዛሬው ትምህርታችን እንመለከተዋለን)። ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱ አገልግሎታቸውን በሚያካሂዱበት ጊዜ፥ መንፈስ ቅዱስ እንዲያድጉ እንደሚረዳቸው ተማምኗል (ዮሐ. 14፡26)። እርሱ ያስተማረበት ጊዜ፥ የትምህርት መጨረሻ ሳይሆን መጀመሪያ ነበር። ለራሳቸው እንዴት እንደሚማሩ በማሳየት፥ መማራቸውን እንዲቀጥሉ አበረታቷቸዋል። የውይይት ጥያቄ፡- የአመራር የሥልጠና ፕሮግራሞቻችንን የክርስቶስን ምሳሌነት ተከትለን ብናዋቅር፥ ምን ምን ነገሮችን መለወጥ ይኖርብናል? የውይይት ጥያቄ፡- ማቴዎስ 10–11ን አንብብ። ሀ) ከዚህ ክፍል ስለ ክርስቶስ ምን እንማራለን? ለ) ስለ ደቀ መዝሙርነትና አመራር የምንማራቸው ነገሮች ምንድን ናቸው? ደቀ መዛሙርቱ እግዚአብሔር ብዙ ትክክለኛ መሪዎችን ያስነሣ ዘንድ እንዲጸልዩ ከነገራቸው በኋላ፥ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱ የሰዎችን ፍላጎቶች እንዲያሟሉና ስለ መጪው የእግዚአብሔር መንግሥት እንዲያስተምሩ ላካቸው። እነዚህ ደቀ መዛሙርት ሌላ ሰው ለችግሩ የእግዚአብሔር መፍትሔ እንዲሆን ከመጸለይ አልፈው ራሳቸው በትጋት በአገልግሎቱ ውስጥ ይሳተፉ ነበር። ክርስቶስ አሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርት መርጦ ለአገልግሎት አሰማራቸው (ማቴ. 10) ክርስቶስን በደቀ መዝሙርነት የሚከተሉት ብዙ ሰዎች ነበሩ። ክርስቶስ እነዚህን ሁሉ ደቀ መዛሙርት በእኩል ደረጃ ካለመመልከቱም በላይ፥ በተለያየ ብቃት ደረጃ አሠልጥኗቸዋል። የመጀመሪያ ደረጃ ደቀ መዛሙርት በብዛት የሚከተሉት ነበሩ። በክርስቶስ ዕርገት ጊዜ፥ ቢያንስ 120 ደቀ መዛሙርት እንደነበሩ ሲታወቅ፥ ቁጥራቸው ከዚህ እንደሚበልጥ የሚያጠራጥር አይሆንም (1ኛ ቆሮ. 15፡6)። ሁለተኛ፥ የሰባ ደቀ መዛሙርት ቡድን ነበር፤ ክርስቶስ እነዚህንም ለአገልግሎት አሰማርቷቸዋል (ሉቃስ 10፡1)። ሦስተኛ፥ 12ቱ ደቀ መዛሙርት ነበሩ። ማቴዎስ ክርስቶስ እነዚህን ደቀ መዛሙርት እንዴት እንደመረጣቸው በመግለጽ፥ ስማቸውን ዘርዝሯል። እነዚህ ሰዎች በጥልቀት የሠለጠኑ ሲሆን፥ የሐዋርያነት ኃላፊነት ተሰጥቷቸው ነበር። እነዚህ ሰዎች በቀድሞይቱ ቤተ ክርስቲያን፥ የክርስቶስን ሥልጣን ይዘው በእንደራሴነት አገልግለዋል። በመጨረሻም፥ ከክักษቶስ ጋር እጅግ ቀርበው የሚሠሩ ሦስት ደቀ መዛሙርት ነበሩ። በልዩ አጋጣሚዎች ክርስቶስ ጴጥሮስን፥ ዮሐንስንና ያዕቆብን በመውሰድ አንዳንድ እውነቶችን ገልጦላቸው ነበር (ለምሳሌ፥ ማቴ. 17፡1)። ክርስቶስ አንድ ከሁሉም በላይ የቀረበ ወዳጅ እንደነበረው የሚያሳዩ ፍንጮች አሉ። ዮሐንስ ራሱን የገለጸው «ክርስቶስ ይወደው የነበረው ደቀ መዝሙር» በማለት ነበር (ዮሐ. 20፡2)። ክርስቶስ ከሁሉም ደቀ መዛሙርት ጋር እኩል ዝምድና አልነበረውም። ክርስቶስ ዓለምን ለመለወጥ ጥቂት ሰዎችን በብቃት አሠልጥኗል። ዛሬ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች የክርስቶስን አብነት ተከትለው ብዙ ሰዎች ከማሠልጠን ሊቆጠቡና ጥቂቶችን ደህና አድርጎ በማሠልጠኑ ላይ ሊያተኩሩ ይገባል ትላለህ? ማቴዎስ 10 ክርስቶስ 12ቱ ደቀ መዛሙርት በአንድ የአገልግሎት ጉዞ እንዲያከናውኑ የሚፈልገውን መስፈርት የቀድሞይቱ ቤተ ክርስቲያን መሪዎች የ12ቱን ደቀ መዛሙርት ምሳሌነት ተከትለው ወንጌልን በዓለም ሁሉ በሚመሰክሩበት ጊዜ ሊጠብቁ ከሚገባቸው ገጠመኞች ጋር የሚያዋህድ በመሆኑ፥ አስገራሚ የወንጌል ክፍል ነው። ማቴዎስ የ12ቱን ደቀ መዛሙርት ለአገልግሎት መላክ ተጠቅሞ፥ ከሁሉም የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ምን እንደሚጠበቅ አስተምሯል። በምኵራብ መደብደብን የመሳሰሉት ብዙዎቹ ነገሮች ክርስቶስ በምድር ላይ በነበረ ጊዜ ባይከሰቱም፥ ክርስቶስ ካረገ በኋላ በአይሁድ ክርስቲያኖች ላይ ደርሰዋል። ከዚህ ክፍል የሚከተሉትን ነገሮች እንመለከታለን፦ ሀ. መጀመሪያ ክርስቶስ 12ቱ ደቀ መዛሙርቱ አሕዛብን ወይም ሰማርያውያንን ሳይሆን አይሁዶችን እንዲያገለግሉ አዝዟቸዋል። በኋላ ግን ክርስቶስ ይህንን አመለካከት ለውጧል። በማቴዎስ 28፡19-20 እና በየሐዋ. 1፡8 ክርስቶስ እነዚህ አገልጋዮች ወደ ሰዎች ሁሉ እንዲሄዱ አዟቸዋል። ምናልባትም ማቴዎስ የቀድሞይቱ ቤተ ክርስቲያን የአገልግሎት አሠራር እያሳየ ይሆናል። እንደ ጳውሎስ ከአይሁዶች ይጀምሩና ወንጌሉን በፍጥነት ወደ አሕዛብ ይወስዱ ነበር (የሐዋ. 13፡44-48ን አንብብ)። ለ. ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ የጠራ መልእክት ሰጥቷቸዋል። ይኸውም ስለ መንግሥተ ሰማይ እንዲያስተምሩ ነበር። ያስተላለፉት መጥምቁ ዮሐንስና ክርስቶስ ያስተማሩትን ተመሳሳይ መልእክት ነበር። የክርስቶስ ተከታዮች አዳዲስ እውነቶችን ከመሻት ይልቅ መልእክታቸውን ቀለል አድርገው ማቅረብ ነበረባቸው። ሐ. ደቀ መዛሙርቱ የክርስቶስን ዓይነት አገልግሎት በማካሄድ፥ ሊፈውሱ፥ ሙታንን ሊያስነሡና አጋንንትን ሊያስወጡ ይገባቸው ነበር። በኋላም እነዚህ 12ቱ ደቀ መዛሙርት፥ «ሐዋርያት» ተብለው ተጠርተዋል። ለዚህም ምክንያቱ መልእክቱን ለማወጅና ተግባራቱን ለማከናወን በክርስቶስ ሥልጣን የተላኩ መሆናቸው ነው። መ. ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱ ገንዘብና ተጨማሪ ልብስ በመውሰድ ራሳቸውን ከሚንከባከቡ ይልቅ በሰዎች እንግዳ ተቀባይነት ላይ እንዲደገፉ ነግሯቸዋል። ብዙውን ጊዜ አንድ ሰው ወደ አዲስ አካባቢ በሚሄድበት ጊዜ፥ ለምግብና መኝታ የሚከፍለውን ገንዘብ፥ ተጨማሪ ልብስ ይይዛል። ክርስቶስ ለዚህ የደቀ መዛሙርት የጉዞ አገልግሎት የሰጠው መመሪያ ጊዜያዊ ነበር። የክርስቶስ ትእዛዝ ሌሎችን ለእግዚአብሔር መንግሥት የማዘጋጀቱ ተግባር አጣዳፊ እንደሆነ ያሳያል። እርሱም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ለመቆየት ብዙ ጊዜ አልቀረውም። ይህ ትእዛዝ ጊዜያዊ በመሆኑ፥ ክርስቶስ በኋላ ለውጦታል (ሉቃስ 22፡35-37)። ክርስቶስ ካረገ በኋላ፥ ሐዋርያት ለረዥም ጊዜ አገልግሎት የሚስማማ ሌላ አሠራር ተከተለዋል። ደቀ መዛሙርቱ ወደ አንዲት ከተማ በሚደርሱበት ጊዜ፥ እግዚአብሔር ወደ ቤቱ ወስዶ የሚንከባክባቸውን ሰው ያዘጋጅላቸው ነበር። ባለቤቱና የከተማይቱ ነዋሪዎች የክርስቶስ መልእክተኞች አድርገው ሲቀበሏቸው፥ በእነርሱ ላይ የእግዚአብሔርን ሰላም የማወጅ ሥልጣን ተሰጥቷቸው ነበር። ነገር ግን ሕዝቡ የክርስቶስን ደቀ መዛሙርት ለመቀበል ካልፈለጉ፥ ደቀ መዛሙርቱ የእግራቸውን ትቢያ ማራገፍ ነበረባቸው። ይህም አይሁዶች ከከተማይቱ ምንም ነገር እንዳልወሰዱና እግዚአብሔር በከተማይቱ እንደሚፈርድ ለማመልከት የሚጠቀሙበት ተምሳሌት ነበር። ሕዝቡ ወንጌሉን ሰምተው ሊቀበሉ የሚችሉበት ዕድል ነበራቸው፤ ይህን ለማድረግ ባለመፈለጋቸው፥ እግዚአብሔር በአብርሃም ዘመን ካጠፋቸው የሰዶምና ገሞራ ከተሞች በላይ፥ ኃጢአተኞች ይሆናሉ (ዘፍጥ. 19)። ስለሆነም፥ በፍርድ ቀን በእግዚአብሔር ይኮነናሉ። ማቴዎስ፥ ለክርስቶስ የሚሰጠው አገልግሎት

የዐሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት መላክ (ማቴዎስ 10:1-42) Read More »

ክርስቶስ የፈጸማቸውን የተለያዩ ተአምራት ማቴዎስ 8:1-9:38

የውይይት ጥያቄ፡- ማቴ. 8-9ን አንብብ። ሀ) ክርስቶስ የፈጸማቸውን የተለያዩ ተአምራት ዘርዝርና እያንዳንዳቸው ስለ ክርስቶስ ምን እንደሚያስተምሩ ግለጽ። ለ) ከእነዚህ ምዕራፎች ስለ ደቀ መዝሙርነት ምን እንማራለን? ሐ) የክርስቶስ ፈውስ ዛሬ ብዙ አገልጋዮች ከሚያካሂዱት ፈውስ ጋር በምን እንደሚመሳሰልና እንደሚለያይ ግለጽ። ማቴዎስ የክርስቶስን የሕይወት ታሪክ የጻፈው፥ እውነተኛ መሢሕ መሆኑን ለአይሁዶች ለማሳመንና ለክርስቲያኖች ደግሞ የክርስቶስ ተከታይ መሆን ማለት ምን ማለት እንደሆነ ለማመልከት መሆኑን ተመልክተናል። ማቴዎስ ክርስቶስ ስለፈጸማቸው አሥር ተአምራት የገለጸበት ሁኔታም እነዚህኑ ጭብጦች ያሳየናል። ማቴዎስን ከሌሎች ሁለት የወንጌል መመሳሰል (ማመሳከሪያዎች) ጋር በምናነጻጽርበት ጊዜ፥ 1) ማቴዎስ እነዚህን ታሪኮች በጊዜ ቅደም ተከተል እንደማይተርክ እንመለከታለን። ከእነዚህ ተአምራት ውስጥ አንዳንዶቹ ከተራራው ስብከት በፊት የተፈጸሙ ሲሆኑ፥ የተቀሩት ግን ከዚያ በኋላ የተፈጸሙ ሳይሆኑ አይቀሩም። ማቴዎስ ግን ክርስቶስ የፈጸማቸውን የተአምራት ዓይነቶች ለማብራራት ተጠቅሞባቸዋል። 2) ማቴዎስ በክርስቶስ ትምህርት ላይ በማተኮሩ ምክንያት፥ ስለ እነዚህ ተአምራት ከማርቆስና ከሉቃስ ያነሰ ማብራሪያ ይሰጣል። የለምጻሙ ሰው መፈወስ ተአምር (ማቴ. 8፡1-4) በአይሁዶች አመለካከት እንደ ለምጽ ያለ አስከፊ በሽታ አልነበረም። አይሁዶች በአያሌ ምክንያቶች ለምጽን ይጠሉ ነበር። በመጀመሪያ፥ በሽታው ሊፈወስ የማይችልና የግለሰቡን መልክ የሚያበላሽ ነው ብለው ስለሚገምቱ ነበር። ሁለተኛ፥ በአይሁድ እምነት ለምጻም ሰው ርኩስ በመሆኑ፥ ከቤተሰቡና ከኅብረተሰቡ ተለይቶ ሌሎች የማይፈለጉ ሰዎች ከሚኖሩበት ወጣ ያለ አካባቢ ለመኖር ይገደድ ስለነበረ ነው። ለምጻሙ ሰው ክርስቶስ እንዲፈውሰው በጠየቀው ጊዜ፥ ክርስቶስ አንድ ቃል በመናገርና በመዳሰስ ፈወሰው። ክርስቶስ ለምጻሙን በመንካቱ በሽታውን አለመፍራቱንና ለበሽተኛው ርኅራኄ እንዳለው አሳይቷል። የክርስቶስ ዳሰሳ ከማርከስ ይልቅ በሽተኛውን ከለምጹ አነጻው። ክርስቶስ ግለሰቡ እንደገና ከማኅበረሰቡ ለመቀላቀል የብሉይ ኪዳንን መስፈርቶች እንዲያሟላ በማዘዙ፥ ለሕጉ የነበረውን አክብሮት አሳይቷል (ዘሌዋ. 13-14)። ከዚያም ለምጻሙ ስለ ተአምሩ ለማንም እንዳይናገር አስጠነቀቀው። ለምን? ለዚህ በምክንያትነት የሚጠቀሱ አያሌ አሳቦች አሉ። በመጀመሪያ፥ ክርስቶስ በተአምር አድራጊነት ለመታወቅ አልፈለገም ነበር። ስለሆነም የተአምራት ሠሪነቱ ዜና እንዲሰራጭ አልፈቀደም። ሁለተኛ፥ ክርስቶስ አገልግሎቱ ሚዛናዊነትን እንዲያጣ አልፈለገም። ፍላጎቱ በሰዎች ሕይወት ውስጥ ዘላቂ ፍሬና ለውጥ ሊያስከትል በሚችለው የማስተማር አገልግሎቱ ላይ ለማተኮር ነበር። በፈውስ አገልግሎቱ ላይ ማተኮር፥ የሰዎችን አሳብ ይበልጥ በመሳብ፥ አስፈላጊ ከሆነው ጉዳይ ለማስተማሪያ የሚፈልገውን ጊዜ ይሻማበት ነበር። ሦስተኛ፥ ሕዝቡ ለመንፈሳዊ ለውጦች ትኩረትን ሳይሰጥ ሥጋዊ ፍላጎታቸውን የሚያሟላ ዓይነት መሢሕ አድርገው እንዲረዱት አልፈለገም ነበር። ማቴዎስ ይህን የመጀመሪያ ተአምር የጠቀሰው፥ ለአያሌ ምክንያቶች ነበር። በመጀመሪያ፥ አይሁዶች በመሢሑ የአገዛዝ ዘመን ለምጽ እንደማይኖር ያምኑ ነበር። ስለሆነም ክርስቶስ እንደ መሢሕ ለምጽን የማስወገድ ኃይል እንዳለው ለማሳየት ፈለገ። ሁለተኛው፥ ማቴዎስም ኢየሱስ በየትኛውም ዓይነት በሽታ ላይ ኃይል እንዳለው አሳየ። በዚህ ረገድ ኢየሱስ ለምጽን መፈወስ ከቻለ የትኛውንም ዓይነት በሽታ ሊፈውስ ይችላል ማለት ነው። የክርስቶስ ተከታዮች የሆንን ሁላችን ክርስቶስ ከበሽታ ሊፈውስ እንደሚችል ማመን አለብን። ነገር ግን ክርስቶስ በሽታዎችን ሁሉ የመፈወስ ኃይል ቢኖረውም፥ የሚሠራው እንደ ፈቃዱ ስለሆነ፥ የተገዥነት መንፈስ ሊኖረን ይገባል። ዛሬ ብዙ ሰዎች የፈውስ አገልግሎት ይዘው ወደ ተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት ይሄዳሉ። የፈውስ አገልጋይ ሁሉ ከእግዚአብሔር እንዳልሆነ ግልጽ ነው (2ኛ ተሰ. 2፡9፤ ራእይ 13፡13-14፤ 19፡20ን አንብብ።) አንድ የፈውስ አገልጋይ እግዚአብሔርን መወከል አለመወከሉን እንዴት እናውቃለን? ባለፈው ሳምንት እንደተመለክተነው፥ ቀዳሚው መንገድ የግለሰቡን ባሕርይ መፈተን ነው። ግለሰቡ በማቴዎስ 5፡3-12 ላይ የተጠቀሱት ባሕርያት አሉት? ከዛሬው ታሪክ የምንመለከታቸው ሌሎች ፍንጮች አሉ። ግለሰቡ የክርስቶስን የፈውስ አገልግሎት ምሳሌ ይከተላል? የክርስቶስን የፈውስ አገልግሎት በምንመለከትበት ጊዜ፥ ሰዎች ሁሉ ብድግ ብለው በመቆም ፈውሳቸውን እንዲቀበሉ እንዳላዘዘና «አጠቃላይ» ፈውስ እንዳልሰጠ እንመለከታለን። ከሕዝቡ መካከል ሳይሆን፥ ከሚፈውሰው ግለሰብ ጋር በግል ይገናኝ ነበር። በተጨማሪም፥ ሰዎች እንደ ተአምራት ሠሪ እንዲረዱትና ወደ እርሱ እንዲሳቡ የማድረግ ፍላጎት አልነበረውም። ስለዚህ ሕዝቡ ስለ ተአምራቱ እንዳያወሩ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት ያደርግ ነበር። ክርስቶስ ሰዎች ከእርሱ ጋር ግንኙነት እንዲመሠርቱና እግዚአብሔርን በሚያስከብር መንገድ እንዲኖሩ ማስተማር ከፈውስ እንደሚበልጥ ያውቅ ነበር። በዚህም እንዲሁም የክርስቶስ ፈውስ ቅጽበታዊና የተሟላ እንደሆነ እንመለከታለን። ከፊል ፈውስ (ለምሳሌ፥ የሽባው ወደ ማነከስ ደረጃ መሻሻል) ወይም በሽታው ዳግም ያገረሸበት ሁኔታ አልነበረም። የውይይት ጥያቄ፡- ዛሬ የምንመለከታቸው አብዛኞቹ የፈውስ አገልግሎቶች ከነዚህ መመዘኛዎች አንጻር እንዴት ይታያሉ? المቶ አለቃው ባሪያ ፈውስ (ማቴ. 8፡5-13) ምንም እንኳ ማቴዎስ ወንጌሉን የጻፈው ለአይሁዶች ቢሆንም፥ ክርስቶስ ለአሕዛብም ትኩረትን እንደሰጠ አመልክቷል። ስለሆነም፥ ማቴዎስ የመቶ አለቃውን ባሪያ የፈውስ ታሪክ አካትቷል። የመቶ አለቃው የ100 ሰዎች (ወታደሮች) ሹም የሮም ጦር መኮንን ነበር። ይህ የመቶ አለቃ ዋነኛ የንግድ መተላለፊያ በሆነችው በቅፍርናሆም ይኖር ነበር። ምንም እንኳ የሮም ወታደሮች በአይሁዶች የተጠሉ ቢሆኑም፥ ይህ የመቶ አለቃ በጣም የተከበረ መሆኑን ሉቃስ (7፡1-5) ይናገራል። ይህን ሰው ራሳቸው አይሁዶች ነበሩ ወደ ክርስቶስ አምጥተው እንዲፈውሰው የለመኑት። ማቴዎስ የዚህን መቶ አለቃ አስደናቂ እምነትና ስለ ክርስቶስ ኃይል የነበረውን ግንዛቤ ገልጾታል። ሰውየው አሕዛብ ቢሆንም፥ እምነቱና ለክርስቶስ የሰጠው እውቅና ከአብዛኞቹ አይሁዶች የላቀ ነበር። አይሁዶች እንረክሳለን ብለው ስለሚፈሩ፥ ወደ አሕዛብ ቤት አይሄዱም ነበር። ነገር ግን ክርስቶስ ለዚህ ዓይነት ግርጃ ስለማይገዛ ወደ ግለሰቡ ቤት ለመሄድ ፈለገ። የመቶ አለቃው ግን ከለከለው። ይህን ያደረገው ክርስቶስ እንዳይረክስ ስለፈለገ ነበር ወይስ፥ ኃጢአተኛ በመሆኑ ክርስቶስን በቤቱ የማስተናገድ ብቃት እንዳልነበረው በመገንዘብ? መልሱን አናውቅም። ከግለሰቡ ምላሽ የምንረዳው ነገር ቢኖር፥ በክርስቶስ ኃይል ላይ ሙሉ እምነት እንደነበረው ነው። የመቶ አለቃው የክርስቶስን ኃይል ከራሱ ሥልጣን ጋር አነጻጸረ። ሮማውያን ሁሉም ሥልጣን ከንጉሡ እንደሚመነጭ ያምኑ ነበር። ያ ሥልጣን በተዋረድ እስከ ተራው ወታደር ይደርሳል። በየትኛውም የተዋረደ ደረጃ ላይ «አልታዘዝም» ማለት ንጉሡን ካለመታዘዝ እኩል ይቆጠር ነበር። ተግባራቱም የሚፈጸሙት በቃል ትእዛዝ ነበር። እንደ መቶ አለቃ፥ ሥራውን ራሱ የማከናወን ግዴታ አልነበረበትም፤ ሥልጣን ማለት ሌሎችን እያዘዙ ማሠራት ማለት ነበር። የመቶ አለቃው ይህንኑ ግንዛቤውን ከክርስቶስ ጋር አዛምዷል። ሁሉም አጠቃላይ ሥልጣን ከእግዚአብሔር እንደሚመነጭና እንደ እግዚአብሔር ወኪል የክርስቶስ ቃላት የእግዚአብሔርን ሥልጣን እንደሚያንጸባርቁ ተገነዘበ። የመቶ አለቃው ክርስቶስ ታላቅ ኃይል እንዳለውና ራሱ ወደ ቤቱ መምጣት እንደማያስፈልገው አመነ። የአፉ ቃል ብቻ ፈውስን ያመጣል ብሎ አሰበ። የክርስቶስ ንግግር እግዚአብሔርን ስለሚወክል፥ የአፉ ቃል እንደሚፈውስ አመነ። የዚህን ግለሰብ እምነት ታላቅነት የምንገነዘበው ስለ ክርስቶስ ኃይልና ከእግዚአብሔር ጋር ስላለው ግንኙነት ከማወቁ ላይ ብቻ ሳይሆን፥ ክርስቶስ ከበሽተኛው አጠገብ ርቆ ቢገኝም እንኳ ሊፈውስ እንደሚችል በማመኑ ነው። እስከዚህ ጊዜ ድረስ፥ ክርስቶስ ይህንን አላደረገም ነበር። ክርስቶስ በመቶ አለቃው እምነትና ግንዛቤ ተደነቀ። ኢየሱስ ለአይሁዶችና ለደቀ መዛሙርት ብዙ አሕዛብ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት እንደሚጨመሩ በመግለጽ አስጠነቀቀ። ሥጋዊ ዝርያቸው የእግዚአብሔር ቤተሰብ አካል ያደርገናል ብለው የሚያስቡ ብዙ አይሁዶች ደግሞ ከመንግሥቱ ውጭ ቀርተው የዘላለምን ፍርድ ይቀበላሉ። ኢየሱስ የጴጥሮስን አማትና ሌሎች ሰዎችን ፈወሰ (ማቴ. 8፡14-17) ማቴዎስ የክርስቶስን የፈውስ አገልግሎት ማብራራቱን ቀጥሏል። የጴጥሮስ አማትና ሌሎችም የከተማይቱ ነዋሪዎች ተፈወሱ። በተጨማሪም፥ ክርስቶስ አጋንንትን ከሰዎች አስወጣ። ነገር ግን ማቴዎስ በዚህ ታሪክ ውስጥ አጽንኦት የሰጠው ለተአምሩ ሳይሆን፥ ለብሉይ ኪዳን ትንቢት ፍጻሜ ነበር። ክርስቶስ በሁሉም ዓይነት በሽታዎች ላይ ኃይል እንዳለው በማሳየቱ፥ በኢሳይያስ 53፡4 እንደተተነበየው፥ መሢሑ የእግዚአብሔር ባሪያ መሆኑን አረጋግጧል። እነዚህ ሦስት ተአምራት ሁሉ፥ ማቴዎስ በዓለም የማይጠቅሙ ተደርገው የሚታሰቡትን ሰዎች መምረጡ አስገራሚ ነው። የመጀመሪያው ከበሽታው የተነሣ ከኅብረተሰቡ የተገለለ ለምጻም ሲሆን፥ ሁለተኛው በብዙ ምክንያት የተናቀ አሕዛብ ነበር። ሦስተኛዋ በጾታዋ ምክንያት ዝቅተኛ ግምት የሚሰጣት ሴት ነበረች። ምናልባትም ማቴዎስ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዓለም ለናቃቸው ሰዎች የሚያስብ መሆኑን ለማሳየት የፈለገ ይመስላል። ማንም ለእርሱ አላስፈላጊ አይደለም፤ እርሱ ሰዎችን በእኩል ደረጃ ያያል። ክርስቶስ ደቀ መዝሙርነት ስለሚያስከፍለው ዋጋ አብራራ (ማቴ. 8፡18-22) ማቴዎስ የክርስቶስ ደቀ መዝሙር ለመሆን ስለፈለገ አንድ ሰው በመግለጽ፥ የተአምራት ትረካውን ገትቷል። በዚህም ማቴዎስ ዋናኛው ጉዳይ ደቀ መዝሙርነት እንጂ ተአምር እንዳልሆነ አሳይቷል። ክርስቶስን መከተል ማለት ምን

ክርስቶስ የፈጸማቸውን የተለያዩ ተአምራት ማቴዎስ 8:1-9:38 Read More »

የኢየሱስ ተከታዮች ሊከተሏቸው የሚገቡ መሠረታዊ መርሖዎች (ማቴ. 6፡19-7፡29)

አንዳንድ ጊዜ ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ግንኙነት እናወሳስበዋለን። የተለያዩ ክርስቲያን መሪዎች እንደ ክርስቲያን ፍሬያማ መሆን ማለት ምን ማለት እንደሆነ ብዙ አሳቦችንና ደንቦችን ያስተምራሉ። ይህ ደግሞ ክርስቲያኖች ተስፋ እንዲቆርጡና የበደለኛነት ስሜት እንዲሰማቸው ከማድረጉም በላይ በኋላ ሰዎችን ለማስደሰት ከመጣር በቀር ከእግዚአብሔር ጋር መልካም ግንኙነት እንዲኖረን አያደርግም። ኢየሱስ በቀጣዩ የተራራው ላይ ስብከቱ የመንፈሳዊ ሕይወትን መሠረታዊ መርሖዎች ቀለል አድርጎ አቅርቧል። እነዚህን መርሖዎች ከግል ሕይወታችን ጋር ብናዛምድ፥ በመንፈሳዊ ሕይወታችን አድገን የክርስቶስ በሳል ደቀ መዛሙርት ለመሆን እንችላለን። የውይይት ጥያቄ፡- ማቴ. 6፡19-7፡29ን አንብብ። ሀ) ክርስቶስ የሰጣቸውን መሠረታዊ ትምህርቶች ዘርዝር። ለ) የክርስቶስ ተከታይ መሆን ማለት ምን ማለት እንደሆነ ለመረዳት እነዚህን መርሖዎች መገንዘብ የሚያስፈልገን እንዴት ነው? መርሕ አንድ፦ በግል ሕይወትህ ላይ ሳይሆን፥ በዘላለሙ መንግሥት ላይ ትኩረት አድርግ። ክርስቲያኖችን ከሚያጋጥሙ ዐበይት ፈተናዎች አንዱ፥ የገንዘብ ጉዳይ ነው። ሁላችንም ለመተዳደሪያ የምንፈልገው ነገር በመሆኑ ገንዘብ በራሱ መጥፎ አይደለም። በዛሬው ዓለም ውስጥ ገንዘብ ከሌለን፥ ምግብ ለመመገብ፥ ልብስ ለመግዛት፥ የመኖሪያ ቤት ለመከራየት አንችልም። ነገር ግን ከዚህ አልፈን ገንዘብን በልባችን ውስጥ ከዐበይት ፍላጎቶቻችን አንዱ እንዲሆን በቀላሉ እናደርጋለን። ብዙ ገንዘብ ካገኘን ደስታችን የሚጨምር ይመስለናል። አዳዲስ ልብሶችን ልንገዛ፥ የተሻለ ምግብ ልንመገብ፥ በምርጥ ቤት ውስጥ ልንኖር እንችላለን። ይህም ብዙዎቻችን ተጨማሪ ገንዘብን እንድናገኝና ገንዘቡ የሚያስገኘውን ተጽዕኖና ደኅንነት እንድናሳድድ ያደርገናል። ገንዘብ ሕይወታችንን እንዲቆጣጠር የምንፈቅድበት ዋንኛው ምክንያት፥ የተሳሳቱ ነገሮችን መመልከታችን እንደሆነ ኢየሱስ ራሱ ገልጾታል። ሥጋዊና መንፈሳዊ ዓይኖቻችን ለራሳችን የተመቻቸ ሕይወትን በማዘጋጀት ላይ ካተኮሩ፥ ልባችን በመንፈሳዊ ጽልመት ይሞላል። ነገር ግን መንፈሳዊ ዓይኖቻችን በመንፈሳዊ ነገሮችና በዘላለማዊ ጉዳዮች ላይ ካተኮሩ፥ ከሁሉም የሚልቀው ምን እንደሆነ በመገንዘብ ለዘላለም ሕይወታችን የሚጠቅም አኗኗርን እንከተላለን። ሥጋዊ ዓይኖቻችን መንገድ አይተን እንድንሄድ እንደሚረዱን ሁሉ፥ መንፈሳዊ ዓይኖቻችንም መንፈሳዊ እውነቶችን ተረድተን በመንፈሳዊ አኳኋን እንድንመላለስ ይረዱናል። የዓለም ነገሮች መንፈሳዊ ዓይኖቻችንን እንዲያሳውሩ ከፈቀድናቸው መንገዳችን በጨለማ ተደናቅፎ ከእግዚአብሔር እውነት እንርቃለን። ከዚያ በኋላ ክርስቶስን ልንከተል አንችልም። (ይህ የምንመለከታቸውን ቪዲዮዎችና የምናነባቸውን መጻሕፍት በጥንቃቄ መምረጥ እንዳለብን ያስጠነቅቀናል። የምንመለከታቸው ቪዲዮዎች፥ የምናነባቸው መጻሕፍትና መጽሔቶች በአስተሳሰባችንና በተግባራችን ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖን ያስከትላሉ።) ኢየሱስ አንድ ልብ ከአንድ ጌታ የበለጠ ሊያስተናግድ እንደማይችል ገልጾታል። ይህም ክርስቶስ ወይም እንደ ገንዘብ ያለ ሌላ ነገር ሊሆን ይችላል። አንድ ሰው ገንዘብን ወይም ሌላ ማንኛውንም ሥጋዊ ነገር የሕይወቱ ቀዳሚ ትኩረት እያደረገ «የክርስቶስ ተከታይ ነኝ» ሊል አይችልም። ብዙም ሳይቆይ የገንዘብ ፍቅሩ ከምድርና ከሰማይ መርሖዎች አንዱን እንዲመርጥ ስለሚያስገድደው፥ ምድርንና ጊዜያዊ በረከቶቿን መምረጡ አይቀርም። የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ዛሬ ሰዎች እጅግ የሚፈልጓቸውና እነርሱን ለማግኘት ሲሉ በክርስቶስ ላይ ያላቸውን እምነት የሚያመቻምቹላቸው ነገሮች ምንድን ናቸው? ለ) እነዚህ ሰዎች ዓይኖቻቸውን ከዘላለማዊ ነገሮች ላይ ያነሡት እንዴት ነው? መርሕ ሁለት፦ ስለ ማንኛውም ነገር አትጨነቅ፥ ለሁሉም በእግዚአብሔር ተማመን (ማቴ. 6፡25-34)። በዕብ. 11፡6 ላይ፥ ያለ እምነት እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት እንደማይቻል ይናገራል። በአንድ ደቀ መዝሙር ሕይወት ውስጥ እጅግ መሠረታዊ የሆነው መርሕ በነገር ሁሉ በእግዚአብሔር የመታመን መርሕ ነው። በምንጨነቅበት ጊዜ ሁሉ፥ እግዚአብሔር ፍላጎታችንን ስለ ማሟላቱ መጠራጠራችን ነው። ሰዎች የሚጨነቁባቸው መሠረታዊ ነገሮች ምንድን ናቸው? ምግብና ልብስ ናቸው። ክርስቶስ ግን ለእነዚህም መጨነቅ እንደማያስፈልግ አስተምሯል። ገንዘብ የሚያስቀምጡባቸው ባንኮች ወይም ምግብ የሚገዙባቸው የገበያ አዳራሾች ባይኖሯቸውም፥ እግዚአብሔር የምድር ፍጥረታትን ሁሉ ይመግባል። እነዚህ ፍጥረታት ምግብ አጥተው አይራቡም። እግዚአብሔር ሰዎች ከአዕዋፋትና ከእንስሳት እንደሚበልጡ ገልጾታል። ስለሆነም እግዚአብሔር አነስተኛ አስፈላጊነት ያላቸውን እንስሳት ከመገበ፥ የሰዎችን ብቻ ሳይሆን የመንፈሳዊ ልጆቹን ፍላጎቶች እንደሚያሟላ እንገነዘባለን። ክርስቶስ የንጉሥ ሰሎሞንን ውብ ልብሶች ከአበቦች ጋር አነጻጽሯል። እግዚአብሔር ትናንሽ ተክሎችን እንደ ሰሎሞን ካሉት እጅግ ሀብታሞች የበለጠ አድምቆ ያላብሳቸዋል። እነዚህ አበቦች ከጥቂት ቀናት ወይም ሳምንታት የበለጠ ዕድሜ የላቸውም፤ ወዲያው ጠውልገው በእሳት ይቃጠላሉ። ሰዎች፥ በተለይም የእግዚአብሔር መንፈሳዊ ልጆች፥ ለእግዚአብሔር ከአበቦችና ከተክሎች በላይ አስፈላጊዎች ናቸው። ስለሆነም ያለጥርጥር የምንፈልገውን ልብስ ያለብሰናል። የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) የምትጨነቀው ምን ለማግኘት ነው? ለ) ጭንቀት በእግዚአብሔር አለመታመንህን የሚያሳየው እንዴት ነው? የጭንቀት ተቃራኒ ምንድን ነው? ከጭንቀት ለመገላገል የሚረዳን ምንድን ነው? በሕይወት የተሳሳቱ እሴቶችን ከመያዝ የሚጠብቀን ምንድን ነው? ክርስቶስ ተከታዮቹ በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ከፍተኛ ትኩረት እንዲያደርጉ አሳስቧቸዋል። ዓይኖቻቸውን በእግዚአብሔር ዘላለማዊ ነገሮች ላይ ልንጥል ይገባል። ክርስቶስ ሀ) በእርሱ አገዛዝና ለእርሱ አስፈላጊ በሆኑት ነገሮችና ለ) ከእርሱ ጋር ካለን ግንኙነት በሚመጣው ጽድቅ ላይ ብናተኩር፥ ጭንቀታችን እንደሚወገድ ገልጾታል። ይህም ጽድቅ በታዛዥነትና በትክክለኛ መንገድ በመመላለስ ራሱን ይገልጻል። ጠቃሚዎቻችን ናቸው የምንላቸው ነገሮች ከእግዚአብሔር መንገዶች ጋር የሚስማሙ ሲሆኑ፥ እንደ ገንዘብና ትምህርት ያሉ ሌሎች ጌቶች እንዲቆጣጠሩን አንፈቅድም። ይህም ሲሆን እግዚአብሔር ብዙውን ጊዜ የሚያስጨንቁንን መሠረታዊ ፍላጎቶቻችንን ያሟላል። የውይይት ጥያቄ፡- ማቴ. 6፡33ን በቃልህ አጥና። ሀ) የክርስቶስን መንግሥትና ጽድቅ በትጋት የምትሻባቸውን መንገዶች ዘርዝር። ለ) ጭንቀት በዘላለማዊ ነገሮች ላይ አለማተኮራችንን የሚያመለክተው እንዴት ነው? በመጨረሻም ክርስቶስ ስለ ወደፊቱ ዘመን መጨነቁ ሞኝነት እንደሆነ አብራርቷል። ምንም ያህል ብንጨነቅ የነገን ክስተቶች መለወጥ አን can’t። ጭንቀት የሚያስከትለው ነገር ቢኖር ኀዘን፥ ሽበትና የጨጓራ ሕመም ብቻ ነው። አባታችን የወደፊቱን ዘመን እንደሚቆጣጠርና እርሱ ያልወሰነው ነገር እንደማይደርስብን እርግጠኞች ልንሆን ይገባል። በእርሱ ላይ ዓይኖቻችንን ተክለን በታዛዥነት የምንመላለስ ከሆን፥ እግዚአብሔር ወደፊት የሚመጣውን የትኛውንም ችግር ለመቋቋም የሚያስችል ብርታት ይሰጠናል። ችግሩ የሚመጣው መፍትሔውን ከራሳችን ለማመንጨት በምንታገልበት ጊዜ ነው። መርሕ ሦስት፦ ከሰዎች ጋር ባለህ ግንኙነት የፈራጅነትን አመለካከት አታንጸባርቅ (ማቴ. 7:1-6)። «የሆነ ምሥጢራዊ ነገር ስላለ ተጠንቀቅ። ልታታልልህ እየሞከረች ነው። አፏ የሚናገረው ቃል ከልቧ የፈለቀ አይደለም።» «ይህንን ለምን እንዳደረገች አውቃለሁ፤ ስለማትወደኝ ልትጎዳኝ ትፈልጋለች።» «ከእኔ ለመቅደም ስለሚፈልግ፥ ከእኔ ጋር አይስማማም። ይህን ያደረገው እርሱ የሌላ ጎሳ አባል ስለሆነና የእኛን ጎሳ ስለማይወድ ነው።» «ሊፕስቲክ መቀባቷ መንፈሳዊት ሴት አለመሆኗን ያሳየናል።» የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት ምሳሌዎች ክርስቶስ በማቴ. 7፡1-6 ላይ ካስተማረው አሳብ ጋር የማይስማሙት እንዴት ነው? ለ) የሌሎች ሰዎችን አነሣሽ ምክንያቶች ለመፍረድ የምንሞክርባቸው ሌሎች መንገዶች ምንድን ናቸው? የክርስቶስ ተከታዮችን ከሚያጋጥማቸው ታላላቅ ችግሮች አንዱ፥ ከሌሎች ክርስቲያኖች ጋር መልካም ግንኙነት አለማድረግ ነው። የችግሩም መንሥዔ በጎሳዎች፣ በመሪዎችና በግለሰቦች መካከል ጥርጣሬ የሚከሰትባቸውን ዐበይት ምክንያቶች አለመገንዘባችን ነው። ከግለሰቡ ተግባር ባሻገር ዘልቀን፥ ልቡን የምንመረምርበት የተለየ ዓይን ያለን ይመስለናል። ይህ ግን ስሕተት ነው። የሰውን ልብ የሚያውቀው እግዚአብሔር ብቻ ነው። ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱ ከዚህ የሰዎች ዝንባሌ እንዲታቀቡ «አትፍረዱ» ሲል አጥብቆ አስጠንቅቋቸዋል። «መፍረድ» የሚለው ቃል ሁለት ፍካሬያዊ ትርጉሞች አሏቸው። በመጀመሪያ፥ ክርስቲያኖች ሊያደርጉ የሚገቧቸውን ነገሮች መገምገምን ሊያመለክት ይችላል። ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱ የሰዎችን፥ በተለይም የሐሰተኛ አስተማሪዎችን ሕይወት በመገምገም እውነተኛ ደቀ መዛሙርት መሆን አለመሆናቸውን እንዲለዩ ነግሯቸዋል (ማቴ. 7፡15-20)። ግምገማው የሚካሄደው ግን በግልጽ መረጃዎች እንጂ በስውር አነሣሽ ምክንያቶች አይደለም። ሁለተኛው፥ መፍረድ የሌሎችን አነሣሽ ምክንያቶች በንቀት መመልከትን ሊያመለክት ይችላል። ይህንን በምናደርግበት ጊዜ አመለካከታችን፥ «እኛ ከእነርሱ እንሻላለን» የሚል ነው። ከተግባራቸው አልፈን ልባቸውን ለማየት የምንችል ይመስለናል። ክርስቶስ በዚህ መንገድ መፍረድ እንደሌለብን ተናግሯል። ብዙውን ጊዜ ሌሎችን ስንተች የራሳችንን ልብ በኃጢአት መቆሸሽ ከምንም አንቆጥርም። ኢየሱስ በዓይኑ የእንጨት ግንድ (ምሰሶ) ስላለበት ሰው በሚናገር አስገራሚ ምሳሌ ተጠቅሟል። ይህ ሰው በዓይኑ ጉድፍ ያለበት ሰው ሲያጋጥመው ለመርዳት ይሽቀዳደማል። በራሱ ዓይን ውስጥ ያለው ግንድ ግን ይህን ከማድረግ ይከለክለዋል። በተመሳሳይ መንገድ፥ የሌላውን ሰው የባሕርይ ችግር ወይም ድብቅ ኃጢአት ማየቱ ቀላል ነው። ነገር ግን ብዙዎቻችን ራሳችንን አጥርተን አንመለከትም። ለዚህ መፍትሔው የሌላውን ሰው ችግር ለማቃለል አለመሞከር አይደለም፤ ችግር ያለበትን ሰው መርዳቱ ተገቢ ነው። በመጀመሪያ ግን የራሳችንን ሕይወት አይተን ሌሎች ሕይወታችንን ለመመርመር እንዲረዱን ልንጠይቃቸው ይገባል። መጀመሪያ ሕይወታችን ከእግዚአብሔር ጋር እንዲስተካከል ካደረግን በኋላ፥ ሌላው ሰው በእግዚአብሔር ቃል ብርሃን ሕይወቱን እንዲመረምር በትሕትና ልንረዳው

የኢየሱስ ተከታዮች ሊከተሏቸው የሚገቡ መሠረታዊ መርሖዎች (ማቴ. 6፡19-7፡29) Read More »