1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች

ክርስቲያን በዓለም ውስጥ እንጂ ከዓለም አይደለም (1ኛ ቆሮ. 5:1-13)። 

ምንም እንኳ ክርስቲያን በእግዚአብሔር ጸጋ ከዓለም ርኩሰት የዳነ ቢሆንም በዓለም እስካለ ድረስ አልፎ አልፎ ዓለማዊ ጸባይ ማሳየቱ አይቀርም። የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች የዓለማዊ ፀባይ የሆነ የዝሙት ሥራ በመካከላቸው ተነሥቶ ነበር። ነገር ግን ክርስቲያን በኃጢአት ሥር ስለማይኖር በንስሐ ከውድቀቱ ተመልሶ ይነሣል። ጻድቅ ሰባት ጊዜ ይወድቃል ግን ደግሞ ሰባት ጊዜ ይነሣል! በዚህ ተስፋ እንጽናና።  1ኛ ቆሮንቶስ 5ን አንብብ።  ጥያቄ 15. ከቁጥር 1 እስከ 2 ባለው ክፍል ውስጥ «ታብያችኋል ይልቅስ እንድታዝኑ አይገባችሁምን?» ሲል ከጠቀሰው የዝሙት ሥራ ጋር ትዕቢታቸው ምን ግንኙነት አለው?  ጥያቄ 16. ከቁጥር 3 እስከ 5 ያለውን ክፍል ከማቴ.18፡15-20 ጋር በማወዳደር መግለጫ ጻፍ።  ጥያቄ 17. ከቁጥር 6-8 ላይ ስለ እርሾ የተናገረውን አብራራ።  ጥያቁ 18. ከቁጥር 9-13ን በጥንቃቄ በማጥናት የሚከተለውን ጥያቄ መልስ። ክርስቲያን ከዓለማውያን ራሱን መለየት የለበትም፤ ግን ክርስቲያን ነኝ እያለ በኃጢአት ውስጥ ከሚኖር ሰው መለየት አለበት። ለምን? መልስህ ያለው ይሁን።  የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በመካከላቸው ታላቅ ኃጢአት ሲካሄድ እንደማዘንና እርምጃ እንደመውሰድ በዓለማዊ ጥበብ እየተመኩ ተቀምጠዋል። በመካከላቸው የነበረውም በደል እንኳን በምእመናን መካከል ቀርቶ በማያምኑት መካከል እንኳ ተቀባይነት የለውም። ከአባሎቹ አንዱ ከእንጀራ እናቱ ጋር በሥጋ ፍትወት ይኖር ነበር። ስለዚህ በደል ብዙም ዝርዝር አይሰጥም። ግን ቤተ ክርስቲያኒቱ ዝም ማለቷ በጣም ደካማ መሆኗን ያስረዳል።  «ይህን የሠራ ከመካከላችሁ ይወገድ»። ሐዋርያው ቤተ ክርስቲያኒቱ ማድረግ የሚገባትን በገልጽና በአጭሩ ይናገራል። እንዴት ከመካከላቸው እንደሚያስወግዱት መመሪያ ይሰጣል፡፡ ምእመናን በአንድነት በክርስቶስ ስምና ሥልጣን ተሰብስበው ይህን በደለኛ ከመካከላቸው ማስወገድ አለባቸው። በዚህ ስብሰባቸው ላይ ጌታ ኢየሱስ በሥልጣኑና በኃይሉ ከመካከላቸው ይገኛል። ስለዚህ የቤተ ክርስቲያኑ ውሣኔ የሰዎች ውሣኔ ሳይሆን የክርስቶስ ውሣኔ ነው! (ማቴ.18፡15-20)፡፡  በማቴ.18፡15-20 ላይ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚገኝ አንድ ሰው ያልተናዘዘው ኃጢአት ካለው ምን ዓይነት እርምጃዎችን መውሰድ እንደሚገባን ያሳየናል። በመጀመሪያ፡- ክርስቲያን የሆነ አንድ ሰው ኃጢአተኛውን ሰውዬ መውቀስ ይገባዋል። ሁለተኛ፡- ሰውዬው መናዘዝ ካልፈለገ ግን በሁለት ወይም በሦስት የክርስቲያን ምስክሮች ፊት ይወስደዋል። ሦስተኛ:- አሁንም ሰውዬው አልናዘዝም ብሎ ከወሰነ፥ ለቤተ ክርስቲያን ይነገራትና ኃጢአተኛው ሰውዬ ከቤተ ክርስቲያን ጋር ያለው ሕብረት እንዲቋረጥ ይደረጋል። ጳውሎስ የቆሮንቶስን ቤተ ክርስቲያን ሰዎች የሚያሳስበው ይህንን የመጨረሻ እርምጃ እንዲወስዱ ነበር።  ጥያቄ 19. አንደዚህ ዓይነት እርምጃ በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ ተወስዶ ያውቃል? እንዴት ተፈጸመ? በእግዚአብሔር ቃል መሠረት ሦስቱም ደረጃዎች ተፈጸሙ?  በቁጥር 5 ላይ ሐዋርያው ትርጉሙን ለመረዳት የሚያስቸግር ቃል ይናገራል፤ «ለሥጋው ጥፋት ለሰይጣን እንዲሰጥ ፍርዴ ነው»። ምን ማለቱ ነው? ከቤተ ክርስቲያን ጉያ መውጣት ከክርስቶስ ቤት ተባሮ ሰይጣን በነገሠበት በዚህ ዓለም ውስጥ መጣል ነው፤ ቆላስያስ 1:13፤ 1ኛ ዮሐ.5፡19 ተመልከት። «ለሥጋው ጥፋት» የሚለውም በቤተ ክርስቲያን መወገዝና ክርስቶስን ማስቀየም የሥጋ መቅሰፍት ሊያስከትል መቻሉን ማስታወሱ ነው፤ ( 1ኛ ቆር.11:30፤ የሐዋ.13:8-11)። እንግዲህ የጳውሎስ ዓላማ አጥፊው በጌታ እጅ ከተገሠጸ አዝኖ ንስሐ ይገባና ነፍሱ ትድናለች ማለቱ ነው እንጂ ያለንስሐ ወደ ዓለም በመጣሉና በዓለም መከራ በመቀበሉ ብቻ ነፍሱ ትድናለች ማለቱ አይደለም፡፡  ቁጥር 6 ላይ እንደገና ስለ ትዕቢታቸው ይናገራል። በውጭ በትዕቢት ሲራመዱ በውስጣቸው ግን ኃጢአት እንደ እርሾ እየበላቸው ነው። እርሾ በመጽሐፍ ቅዱስ የኃጢአት ምሳሌ ነው፤ (ማቴ. 13:33፤ ገላ.5፡9)።  ከቁጥር 7-8 ከብሉይ ኪዳን የእርሾን ምሳሌ ያቀርባል። በአይሁዶች የፋሲካ በዓል ቂጣ እንጂ እርሾ ያለበት ነገር አይበላም። ይህም የግብፅን ባርነት ትተው በነፃነት እንዳሉ አዲስ ሕይወታቸውን የሚያስረዳ ነው።  አሁንም ክርስቲያኖች የዓለምን መጥፎ ሥራዎች ማስወገድ አለባቸው። «ፋሲካችን ክርስቶስ ታርዷልና ስለዚህ በቅንነትና በእውነት ቂጣ በዓልን እናድርግ እንጂ በአሮጌ እርሾ በክፋትና በግፍ እርሾም አይደለም»። ክርስቲያን በክርስቶስ ሞት ከኃጢአት ባርነት ነፃ የወጣ ስለሆነ እንደገና ወደ ባርነት ለኃጢአት ሥራ ራሱን መሸጥ የለበትም፤ (ሮሜ 6፡12-14)።  ከቁጥር 9-13 ባለው ክፍል ውስጥ ከዚህ በፊት የጻፈላቸውን መልእክት በደንብ እንዳልተረዱና አሁን እንደገና ሊያስረዳቸው እንደሚሞክር እንገነዘባለን። የትምህርቱ ዋና ፍሬ ነገር በቁጥር 12ና 13 ላይ ይገኛል። “በውስጥ ባሉ ሰዎች ላይ አትፈርዱምን? በውጭ ባሉቱ ግን አግዚአብሔር ይፈርዳል። ክፉውን ከመካከላችሁ አውጡት”። ክርስቲያን በዓለም እንጂ ከዓለም አይደል፤ (ዮሐ.17:15 እና 16)። ስለዚህ በጣዖት አምልኮአቸው እስካልተጠላለፈ ድረስ ክርስቲያን ከዓለም ሰዎች ጋር አብሮ መኖር አለበት። ነገር ግን ክርስቲያን ነኝ እያለ በእግዚአብሔር መንገድ የማይመላለስ ከሆነ እንደዚህ ካለው ጋር እንኳን ለአባልነት በቤተ ክርስቲያን መቀበል ቀርቶ በጉርብትና እንኳ መወዳጃት ክልክል ነው። አንድ አማኝ ከቤተ ክርስቲያን በቅጣት ከአባልነት ከተወገዘ በኋላ ከእርሱ ጋር አባሎች በውጭ መወዳጀት የላባቸውም። እንዲህ ካደረጉ የቤተ ክርስቲያኒቱን ተግሣጽ በማክሸፍ ይበርዙታል። በቤተ ክርስቲያን የእርሱን መመገድ ደግፈው ዞር ብለው ግን በውጭ ጓደኝነታቸውን ቢቀጥሉ ወላዋይና መንታ ምላስ ያላቸው ቀላማጆች መሆናቸው ነው። የተገሰጸውም ሰው የተገሣጹን ትልቅነት ባለመረዳት ንስሐ እንዳይገባ እንቅፋት ይሆኑበታል። ስለዚህ ይህን የሐዋርያውን ቃል በጥንቃቄ እንገንዘብ፡ ጥያቄ 20. ክርስቲያን ነኝ እያለ ግን በኃጢአት ውስጥ ለሚኖረው ሰው ሕብረታችንን ማቋረጣችንን የምንገልጸው እንዴት ነው? በምሳሌ ግለጽ። (ምንጭ፤ በትምህርተ መለኮት ማስፋፊያ (ትመማ) መልክ የተዘጋጀ ጽሑፍ፡- በቄስ ኃይሉ መኮንን)

ክርስቲያን በዓለም ውስጥ እንጂ ከዓለም አይደለም (1ኛ ቆሮ. 5:1-13)።  Read More »

የክርስቶስ ሐዋርያት (1ኛ ቆሮ. 4:1-21)

ለወንጌል ሥራ ቅንዓት ያላቸው አብያተ ክርስቲያናት ብዙውን ጊዜ ለወንጌል አገልጋዮች በቂ እንክብካቤ አያሳዩም። መጽሐፍ ቅዱስ ግን ወንጌላውያንን እንድንከባከብ አጥብቆ ያስተምረናል። በዚህ ምዕራፍ ውስጥ ሐዋርያው ጳውሎስ የቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ተገቢውን እንክብካቤ ስላላደረገችለት የወቀሳ ደብዳቤ ይጽፍላቸዋል። የእኛስ ቤተ ክርስቲያን ለወንጌላውያን ያላት እንክብካቤ እንዴት ነው? የዓለም ጥበብ የሚታየው ለሰዎች ወይም ለአንድ ሰው በሚሰጠው ክብር ነው። የእግዚአብሔር ጥበብ ግን ክብርን የሚሰጠው ለእግዚአብሔር ብቻ ነው።  1ኛ ቆሮንቶስ 4ን አንብብ።  ጥያቄ 8. «ሎሌ» በሚለው ቃልና ‹መጋቢ» በሚለው ቃል መካከል ያለውን ልዩነት ግለጽ።  ጥያቄ 9. በቁጥር 4 ላይ በዚህ አልጸድቅም እኔን የሚፈርድ ጌታ ነው» ሲል ሐዋርያው ምን ማለቱ ነው?  ጥያቄ 10. በቁጥር 6 ላይ ‹ስል አንዱ በአንዱ ላይ አንዳችሁም እንዳይታበዩ (እንዳትታበዩ)» ማለቱ ምን ማለቱ ነው?  ጥያቄ 11. ከቁጥር 8 እስከ 13 ያለው ክፍል በግልጽ የሮሮ አፃፃፍ ነው። የጽሑፉን ጠቅላላ ሀሳብ በአጭሩ ግለጽ።  ጥያቄ 12. በቁጥር 15ና 16 ላይ በወንጌል ወልጄአችኋለሁና እንግዲህ እኔን የምትመስሉ ሁኑ” ሲል በምን እርሱን እንዲመስሉ ነው የሚጠይቃቸው?  ከቁጥር 1-5 ያለው ክፍል ከላይ የጠቀሳቸውን ነጥቦች ይከተላል፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስና ባልደረቦቹ በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ሲያገለግሉ ተጠሪነታቸው ለሰው ሳይሆን ለእግዚአብሔር መሆኑን ይገልጻል፡፡ ስለሆነም በምንፈሳዊ ሠራተኛች ዘንድ ታማኝ ሆና መገኘት አስፈላጊ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ በራሱ ላይ እንኳ መፍረድ እንደማይችል ይናገራል፡፡ ጳውሎስ ሰው እንደመሆኑ ሊታለል እንደሚችል ያውቅ ነበር። ስለዚህም እንኳን በሰዎች ላይ ቀርቶ በራሱ ላይ ለመፍረድ የማይችል መሆኑን ተረድቶ ነበር። የቆሮንቶስም ክርስቲያና በሠራተኞች ላይ ከመፍረድ እንዲጠበቁ ያስጠነቅቃቸዋል።  ጳውሎስ ስለራሱና ስላባልደረቦቹ የእግዚአብሔር ሎሌና የእግዚአብሔር መጋቢ የሚሉትን ቃላት ይናገራል። በመጽሐፉ ሎሌ የሚባለው ተራ አሽከር ሲሆን መጋቢ ደግሞ በሎሌዎች ላይ የተሾመ የሎሌዎች ተቆጣጣሪ አሽከር ነው፡፡ ስለዚህ ሎሌም ሆነ መጋቢ ሁለቱም የእግዚአብሔር ባሮች እንጂ ባለቤቶች ስላልሆኑ ባንዱም መመካት የለብንም። ለቀጠራቸው ለእግዚአብሔር መልስ የሚሰጡ ተጠሪነታቸውም ለእግዚአብሔር የሆነ አገልጋዮች ናቸው።  በቁጥር 6 ላይ የአማርኛ ስህተት አለ፤ ‹እንዳይታበዩ» የሚለው «እንዳትታበዩ» ብሎ መነበብ አለበት። በቁጥር 6 እና 7 ላይ ሐዋርያው ክርስቲያኖች በሠራተኞች ላይ መመካት እንደሌለባቸው ይናገራል። የጠቀሰው ምሳሌ «ከተጻፈው አትለፍ» የሚለው ጥቅስ በብሉይ ኪዳን የትም ቦታ ተጽፎ አይገኝም፤ ምናልባት በዘመኑ በኅብረተሰቡ የታወቀ ምሳሌ ሊሆን ይችላል። አገልጋዮች እግዚአብሔር በሰጣቸው ስጦታ ስለሚያገለገሉ ተገልጋዮች በአገልጋዮች ችሎታ መመካት የለባቸውም።  ጥያቁ 13. አንዳንድ ሰዎች ወይም አገልጋዮች በችሎታቸው የሚመኩ አሉ? መመካታቸውን የሚገልጹት እንዴት ነው?  ከቁጥር 8-13 ያለው ክፍል በአሽሙር መልክ የቀረበ የጳውሎስ ወቀሳ ነው። ሀሳቡን በዝርዝር ለማግኘት እንድንችል ቁጥር በቁጥር እንመለከተዋለን።  ቁጥር 8፡- የቆሮንቶስ ክርስቲያናት በዓለማዊ አስተሳሰብ ውስጥ ስላሉ በወንጌል ምክንያት እየተሰደዱ የሚናቁትን የወንጌልን አገልጋዮች ይንቁ ስለነበር ጳውሎስ «ነገሣችኋል» በማለት ያሸሟጥጣቸዋል። በእርግጥ የነገሡ ከሆነ ከወንጌል አገልጋዮች ጋር አብረው በነገሡ፤ ማለት አሁን ለክርስቶስ ወንጌል ታማኝ ሆነው ከአገልጋዮች ጋር በመሰለፍ በዓለማውያን ቢናቁና በኋላ በወቅቱ ከወንጌል አገልጋዮች ጋር አብረው ቢነገሡ ይሻላል ይላቸዋል።  ቁጥር 9፡- ሐዋርያት የወንጌል ሥራ ቀደምተኞች ስለሆኑ ዓለም በስደትና በማንቋሸሽም ቀደምት አድርጋቸዋለች፡፡ በዘመኑ የሞት ፍርድ የተፈረደባቸው ወደ ሞታቸው ሲነዱ በሰልፍ ታጅበው ሟቾቹ ከሰልፉ መጨረሻ ተደርገው በሕዝብ ይንጓጠጡ ነበር። ሐዋርያው ያን ምሳሌ ወስዶ ሐዋርያት በዓለም ብቻ ሳይሆን በመላእክት እንኳ እየታዩ በውርደት ቦታ እግዚአብሔር እንዳስቀመጣቸው ይናገራል (መላእክት የሰዎችን ሕይወት ታዛቢ ለመሆናቸው የሚያስረዱ የሚከተሉትን ጥቅሶቶ ተመልከት፤ (1ኛ ቆሮ.11:10፤ 1ኛ ጢሞ.3:16፤ 5፡21፤ 1ኛ ጴጥ.1:12)። እንግዲህ የአሸሙሩ አቅጣጫ ይግባን። መንፈሳዊ አባቶች የሆኑት ሐዋርያት እንዲህ ተዋርደው ሳሉ ምእመናኑ ግን በትዕቢት ተነፍተው አገልጋዮችን ቢያንገዋልሉ ምን ያህል መጥፎ ነገር እንደሆነ ለቀሮንቶስ ክርስቲያኖች ያስረዳቸዋል፡፡ ከቁጥር 10-13፡- የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በኩራት አገልጋዮችን ሲያንገዋልሉ አገልጋዮች ግን ለክርስቲያኖች ሲሉ በብዙ ውርደትና መከራ ውስጥ አሉ። ይህ ክፍል ቤተ ክርስቲያንን ለወንጌል አገልጋዮች ተገቢ እንክብካቤ እንድታደርግ በጥብቅ ተግሣጽ ይናገራታል፡፡ ቤተ ክርስቲያንም ይህን ተግሣጽ መስማትና ወንጌላውያንን እንደቃሉ መሠረት ልትንከባከብ ይገባታል።  ቁጥር 14፡- ሐዋርያው ነገሩን ለማለሳለስ በፍቅር ብቻ ተገዶ ይህን ወቀሳ እንዳቀረበላቸው ያሳስባቸዋል።  ቁጥር 15፡- ለመጀመሪያ ጊዜ ወንጌልን የሰበከላቸው ጳውሎስ ስለሆነ በክርስቶስ አባታቸው መሆኑን ያስታውሳቸዋል፤ ስለሆነም በግልጽ ሊወቅሳቸው ይችላል። እንዲያውም ከሱ በኋላ መጥተው ካገለገሏቸው ሞግዚቶች ይልቅ ይቀርባቸዋል። ይህ አነጋገሩ በተለይ እርሱን አንፈልግም ያሉትን ክርስቲያናት በጣም ሊገስጻቸው ይገባል።  ቁጥር 16፡- ልጅ አባቱን መምሰል እንደሚገባው የእርሱን ምሳሌ እንጂ የዓለምን ምሳሌ መምሰል የለባቸውም፤ 1ኛ ቆሮ.1:1 1ኛ ተሰ.1:6፤ ሮሜ 12:1 እና 2። የጳውሎስን የክርስትና አኗኗር በሚገባ ተረድተው እርሱን እንዲመስሉ ስለ እርሱ ሕይወት የሚያውቀውን ጢሞቴዎስን ይልክላቸዋል። ጳውሎስ በስብከት ብቻ ሳይሆን በኑሮውም ያስተምር ስለነበር እኛም የዘመኑ ወንጌላውያን አርአያ የሆነ ሕይወት ሊኖረን ይገባል።  ከቁጥር 18-21:- ጳውሎስ በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ተቃዋሚዎች በተነሡበት ጊዜ አፍር ወይም በመቀየም አኩርፎ ከቤተ ክርስቲያኑ የማይቀር መሆኑን በግልጽ ያውጃል። የጌታ አገልጋይ ነገሮች በጠራ መንገድ እንዲታዩ መጣር አለበት።  ጥያቄ 14. በአሁኑ ዘመን ቤተ ክርስቲያን ለአገልጋዮችዋ ትክክለኛ እንክብካቤ ምን እያደረገች ነው? (ምንጭ፤ በትምህርተ መለኮት ማስፋፊያ (ትመማ) መልክ የተዘጋጀ ጽሑፍ፡- በቄስ ኃይሉ መኮንን)

የክርስቶስ ሐዋርያት (1ኛ ቆሮ. 4:1-21) Read More »

መንፈሳዊ ጉልምስና ( 1ኛ ቆሮ. 3:1-23) 

1ኛ ቆሮንቶስ ምዕራፍ 3 ስላ መንፈሳዊ ጉልምስና በሰፊው ያስተምራል። በመንፈስ የመዳን ዋናው ምልክት ክርስቲያን ሕይወቱን ለእግዚአብሔር አገልግሎት መስጠቱ ነው። በቁጥር 9 ላይ «ከእርሱ ጋር አብረን የምንሠራ ነንና» ይላል። ክርስቲያን እግዚአብሔርን ለማገልገል ታጥቆ ሲነሣ ከእርሱ ጋር አብሮት የሚሠራው እግዚአብሔር እንደሆነ ተረድቶ በእምነት መሠማራት አለበት፡፡ እኛም የእግዚአብሔር አገልጋዮች መሆናችንን ብቻ ሳይሆን በአገልግሎታችን ተባባሪ ሆኖ ኃይል የሚሰጠን እግዚአብሔር ራሱ መሆኑን መገንዘብ አለብን፡፡ 1ኛ ቆሮንቶስ 3ን አንብብ።  ጥያቄ 1. ከቁጥር 1-4 ያለውን ክፍል በጥንቃቄ ተመልክተህ በሥጋዊነትና በዓለማዊነት መካከል ያለውን መወራረስ (ተመሳሳይ ባሕሪይ) አስረዳ። ጥያቄ 2. ከቁጥር 5-9 ባለው ክፍል ውስጥ ሁለት ሠራተኛች ተጠቅሰዋል፤ እነማን ናቸው?  ጥያቄ 3. ቁጥር 10-15ን በመመልከት «የማንም ሥራ የተቃጠለበት ቢሆን ይጕዳበታል፤ እርሱ ራሱ ግን ይድናል ነገር ግን በእሳት አንደ ሚድን ይሆናል» የሚለውን በራስህ አማርኛ በአጭሩ ገልጸህ አስረዳ።  ጥያቄ 4. ቁጥር 15ንና 1ኛ ቆሮንቶስ 6:9ና 10ን አስተያይተህ በሁለቱ መካከል ያለውን ተቃራኒ የሚመስል ሃሳብ አስታርቅ፡፡ መንፈሳዊ ጉልምስና የሚከተሉትን ያሳያል  1ኛ. ሥጋዊነትን ያስወግዳል ( 1-4)  2ኛ. አገልግሎት ምን እንደሆነ ይገነዘባል፤ ( 5-9)  3ኛ. የአገልግሎቱን ድካም በእግዚአብሔር ሚዛን ላይ ያስቀምጣል፤ ( 10-17)  4ኛ. በሰው ጥበብ ሳይሆን በእግዚአብሔር ጥበብ ያገለገላል፤ ( 18-23)  ከላይ ከ1-4 የተዘረዘሩትን ነጥቦች በየተራ እንመልከታቸው፡፡ 1ኛ . መንፈሳዊ ጉልምስና ሥጋዊነትን ያስወግዳል ( 1-4)  በመሠረቱ ሕፃንነት በራሱ አስነቃፊ አይደለም፤ ነገር ግን ሰው በሕፃንነት ሲሰነብት የጤንነት አለመሆኑ ግልጽ ነው። በመንፈሳዊ ደረጃ ነገሩ የከፋ ነው። በመንፈሳዊ ሕይወቱ የማያድግ ክርስቲያን ባለበት አይቆምም፤ ወደ ኋላ በማፈግፈግ ወደ ሥጋዊነት እያዘነበለ ይመጣል፡፡ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ጽኑ ምግብ በመመገቢያቸው ወቅት ወተት መጋት ነበረባቸው። ይህ ሕፃንነት ግን ኃጢአትንም አስከተለ፤ «ገና ጽኑ መብል ለመብላት አትችሉም ነበርና ወተት ጋትኋችሁ፤ ገና ሥጋውያን ናችሁና እስከ አሁን ድረስ ገና አትችሉም። ቅናትና ክርክር ስለሚገኝባችሁ ሥጋውያን መሆናችሁ አይደለምን?» (ቁጥር 2ና 3)፡፡  በቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በኩል ሥጋዊነታቸው የተገለጠው እርስ በርስ ባለመስማማት ነበር፤ በእኛስ በኩል ሥጋዊነታችን በምን ይገለጣል? አለመጎልመስ እስካለ ድረስ ሥጋዊነትም አብሮ እንዳለ መገንዘብ አለብን። ግን የሥጋዊነት መግለጫ ሊለያይ ይችላል። መለያየትና መከራከር አለመቀራረብ፥ ለመንፈሳዊ ነገር ቅድሚያ አለመስጠት፥ ገድየለሽነት የመሳሰሉት የሥጋዊነት መግለጫዎች ናቸው፡፡  ጥያቄ 5. ሀ/ በሕይወትህ መንፈሳዊ ጎልማሳ ነህ? መሆንህን ወይስ አለመሆንህን በምን አወቅህ? ለ/ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ብዙ ሰዎች መንፈሳዊ ሕፃናት ናቸውን? አለመጎልምሣቸውን በምን ያሳያሉ?  2ኛ. መንፈሳዊ ጉልምስና አገልገሎት ምን እንደሆነ ይገነዘባል፤ (5-9)  ሥጋውያን ክርስቲያኖች እርስ በርሳቸው ከመለያየታቸውም በላይ በአገልጋዮች መካከልም የመለያየት ምክንያት ይሆናሉ፤ (ለምሳሌ ያህል ማርቆስ በጳውሎስና በባርናባስ መካከል መለያየትን ፈጠረ፤ የሐዋ.15:36-41)። ይህንም የሚያደርጉት የአገልግሉት ነገር ገና ስላልገባቸው ነው፤ (ቁጥር 6-8)፡፡  ሰው የእግዚአብሔር መሆኑን ከተገዘበ «የእከሌ ተከታይ ነኝ» ከሚለው የሕፃን ጭቅጭቅ ውስጥ አይገባም። የእግዚአብሔር ከሆነ አገልጋዮቹ በሙሉ የርሱ ናቸው እንጂ አንዱ ወይም ሁለቱ ብቻ አይደሉም።  የእግዚአብሔር ሀብት መሆናችሁን የተገነዘባችሁ ስንቶች ናችሁ? የእግዚአብሔር ከሆናችሁ በሕይወታችሁ እግዚአብሔርን ለማስቀደም ምን ያህል ጥረት ይታይባችኋል? ለምትወስኑት ውሣኔ «ይህ እግዚአብሔርን በበለጠ እንዳገለግል ይረዳኛል» ብላችሁ ከራሳችሁ ጋር ትነጋገራላችሁ ወይ? ወይስ ጭራሽ የእግዚአብሔር ነገር ከውሣኔአችሁ ውስጥ አይገባም? ለአንዳንድ ክርስቲያን ነን ባዮች በእግዚአብሔር ማመን እንደ ጌጥ ትርፍ ነገር እንጂ የሕይወታቸው መነሻና መድረሻ አይደለም። “የእግዚአብሔር እርሻ ናችሁ፤ የእግዚአብሔር ሕንፃ ናችሁ” የሚለው ቃል በሕይወታቸው ውስጥ ቦታ ያለው አይመስልም። አንግዲያስ አንድ ሰው ይህን ካልተገነዘበ የመንፈሳዊ አገልግሎት ትርጉሙ በፍጹም ገና አልገባውም። ይህም ከሆነ መንፈሳዊ ሕፃንነቱ ሥር ከመስደዱ የተነሣ አስተሳሰቡ ዓለማዊ ነው።  በእግዚአብሔር ሥራ ውስጥ እግዚአብሔር ለተለያየ ሥራ የተለያዩ መሪዎችን ይጠቀማል። እንደ ጳውሎስ ያሉ ወንጌላውያን ወንጌልን ለሌሎች ያዳርሳሉ፤ እንደ አጵሎስ መጋቢና መምህራን የሚሆኑ ደግሞ ያመኑትን በእምነታቸው እንዲያድጉ ይረዱአቸዋል። ሁሉም የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ለበለጠ ዓላማና ግብ በሕብረት መሥራት ይገባቸዋል። ይህም ግብ የቤተ ክርስቲያንን ዕድገት በየጊዜው በመገምገም የእግዚአብሔር ሕዝብ በእምነቱ ሲያድግ ማየት ነው፤ (ኤፌ.4:11-13)። ሁላችንም ብንሆን የምናገለግለው መንፈሳዊ እድገት ሊሰጠን የሚችለውን አንዱን ኢየሱስ ክርስቶስን በመሆኑ በልባችን ከእኛ ጋር ከሚያገለገሉት ከሌሎቹ የበለበ ክብር የመፈለግ ምኞት ሊኖረን አይገባም።  ጥያቄ 6. ሀ/ በተለያየ መልክ በመሪነት በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ የሚያገለግሉትን ሰዎች ስም ዝርዝር ጻፍ። እግዚአብሔር ለቤተ ክርስቲያንህ ያለውን ዓላማ ተግባራዊ ለማድረግ አብረው በሕብረት የሚሠሩት አንዴት ነው? ለ/ አንዳንዴ ሰይጣን በመካከላቸው የምቀኝነትን ሃሳብ በማምጣት የእግዚአብሔርን ሥራ የሚያደናቅፍባቸውን መንገዶች ገልፅ።  በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አገልግሎታችንን ከአገልጋዮች ወይም ከሽማግሌዎች አንፃር ሳይሆን ከእግዚአብሔር አንፃር ካላየነው አገልጋዮችን እንደ ጣዖት ተደግፈናቸዋል ማለት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “በጌታ የሚታመን አያፍርም” ይላል። ስለዚህ ከጌታ በስተቀር በሌላ የሚተማመን እንደሚያፍር ግልጽ ነው።  3ኛ. መንፈሳዊ ጉልምስና የአገልግሉቱን ድካም በእግዚአብሔር ሚዛን ላይ ያስቀጣል፤ ( 10-17)  ሰውን የሚያይ፥ መንፈሳዊ አገልግሎቱን በሰው መሠዊያ (ገበታ) ላይ የሚያስቀምጥ የእግዚአብሔርን ሚዛን አያይም። እርምጃው ሁሉ ሰውን ለማስደሰትና ሰው በእርሱ እንዲደሰት ነው። ይህ ሳይሳካ ሲቀር ይሰባበራል። የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች እኔ የእከሌ ነኝ በማለት በመከራከር ላይ ሳሉ ለራሳቸውና ለአገልጋዮቻቸው የተዘረጋውን የእግዚአብሔርን ሚዛን ረሱ። የአገልጋዮችን ሕይወትና ድካም መዛኝ እግዚአብሔር እንደሆነ ጳውሎስ ያስረዳል።  ሆኖም ይህን ሲል አገልጋይ በኃጢአት ሲመላለስ አይገሠጽ ማለቱ አይለም። ኃጢአትን መገሠጽ እንዳለብን መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምራል (1ኛ ቆር. 5፡1-2 እና 11-13)። በዚህ ክፍል ውስጥ የሚናገረው ስለ አገልገሎት ድካም መዛኙ እግዚአብሔር መሆኑን ለማስረዳት ብቻ ነው። ስንቶች ነን «በመጨረሻ ግዜ እግዚአብሔር ሥራዬን ገልጦ የሚመዝንበት ጊዜ ስለሚመጣ አሁን ሰውን ሳልመለከት እግዚአብሔርን በትጋት ላገልግል የምንል?» ደግሞም ሰው ይህን ካላለ አግዚአብሔርን ማገልገል አይችልም።  በዚህ ነገር ሰው ካልተጠነቀቀ በሰው ተሰናክሎ የእግዚአብሔርን ቤት ወደ ማፍረስ ይደርሳል (16ና 17)። ያ ከሆነ ያገልግሉት ሽልማት ብቻ የማጣት ነገር ሳይሆን (14ና 15) ጠቅላላ ሕይወቱ በእግዚአብሔር ፍርድ ውስጥ ይወድቃል። ስለዚህ ሰውን ሳይመለከቱ ማገልገል በድካም እንዳንዝል ከማድረጉም በላይ በእግዚአብሔር ፍርድ ውስጥ እንዳንወድቅ ይረዳናል።  ጥያቄ 7. እኛ ስለ እግዚአብሔር ሚዛን ብናስብ ኖሮ የእኛ ወይም የሌሎች አገልግሎት እንዴት ነበር የሚለወጠው?  እግዚአብሔርን ማገልገሉ ብቻ በቂ አይደለም፤ እንዴት እንደምናገለግለው ማጤኑም ተገቢ ነው። የምንሠራው ሥራ ከንጹሕ ልብ የመነጨ መሆን ይገባዋል። ሥራው የእግዚአብሔር ቤት በሆነው በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ዘላቂ የሆነ ለውጥን ማስገኘት አለበት። በእግዚአብሔር የፍርድ እሳት ውስጥ ለእርሱ ክብር ያልሆነ ወይም ከንጹሕ ልብ ሆነን ያልሠራነው ነገር ሁሉ (እንደ እንጨት፥ ሣርና አገዳ) ምንም ጥቅም እንዳሌለው ይታያል። ምንም እንኳ የእግዚአብሔር ልጆች ብንሆንና ብንድንም ለሠራነው ሥራ ምንም ሽልማት አይኖረንም። በትክክልኛ ንጹሕ መንፈስ ተነሣሥተን ለእግዚአብሔር ክብርና ቤተ ክርስቲያን ጥሩ የሆነ ሥራ ከሠራን ሥራችን ዘላቂ (እንደ ብር፥ ወርቅና የከበረ ድንጋይ) ይሆናል። በተጨማሪም ከእግዚአብሔር ሽልማት እናገኛለን። በእግዚአብሔር ሚዛን ሲለካ ሥራችን የሚያሸልም እንዲሆን እስቲ ሁላችንም ሥራችንንና ልቦናችንን እንመርምር።  1ኛቆሮ. 3፡15፣ የአማኞች ሥራ እንዴት እንደሚፈተን ነው የሚናገረው። እግዚአብሔር ስለ ኃጢአታቸው እንደገና በአማኞች ላይ እንደማይፈርድባቸው ቃል ገብቷል። ኢየሱስ ክርስቶስ አስቀድሞ ለአማኞች ቅጣቱን ከፍሎላቸዋል (ዮሐ.5፡24)። እውነተኛ አማኝ የእግዚአብሔርን ሥራ ሳይሠራ ወደ መንግሥተ ሰማይ ሊገባ ይችላል፤ ቢሆንም ይህ ሰው አሁንም የእግዚአብሔር ቤተሰብ አባል ነው። 1ኛቆሮ.6፡9-10 ግን የሚናገረው የእግዚአብሔርን የዘላለም ሕይወት ስጦታ ስላልተቀበሉና ዝም ብለው በኃጢአት ኑሮ ውስጥ ያለማቋረጥ ስለሚኖሩ ሰዎች ነው።  4ኛ መንፈሳዊ ጉልምስና በሰው ጥበብ ሳይሆን በእግዚአብሔር ጥበብ እንድናገለግል ይረዳናል፤ (18-25)  አንዳንድ ጊዜ በሰው ፊት ተወዳጅ ሆኖ ለመቅረብ ሰው ብዙ ዓለማዊ ጥበብ ይጠቀማል። ግን ይህ በእግዚአብሔር ፊት ምንም ዋጋ የለውም። “ጌታ የጥበበኞችን አሳብ ከንቱ እንደሆነ ያውቃል”። ሰውን ማታለል ይቻላል፤ እግዚአብሔር ግን ስለማይታለል በእግዚአብሔር ቤት የዓለምን ጥበብ ማስወገድ አለብን።  ሕይወታችንን በጥንቃቄ እንጠብቅ። በእግዚአብሔር እንደምንመዘን ሳንዘነጋ በሕይወታችን እግዚአብሔርን ከማገልገል አንቦዝን። ሕይወታችን ለራስ መደሰቻ ሳይሆን እግዚአብሔርን ማክበሪያ ነውና በሕይወታችን እግዚአብሔርን እናክብር። «የእግዚአብሔር እርሻ

መንፈሳዊ ጉልምስና ( 1ኛ ቆሮ. 3:1-23)  Read More »

አገልግሉት በሰው ጥበብ ሳይሆን በእግዚአብሔር ጥበብ መሆን አለበት (1ኛ ቆሮ. 2:1-16) 

እግዚአብሔር በጠቢባን ሳይሆን በደካሞች ይጠቀማል ሲባል ያገኘነውን እውቀት እግዚአብሔር አገልገሎት ላይ አናውለው ማለት አይደለም፤ ወይም ደግሞ ለእግዚአብሔር አገልገሎት በቂ ዝገጅትና ትጋት አናሳይ ማለት አይደለም። ግን ሁሉንም ካደረግን በኋላ መንፈስ ቅዱስ ካልተጠቀምበት የእኛ ጥረት ብቻውን ከንቱ መሆኑን መገንዘብ ማለት ነው።  1ኛ ቆሮንቶስ ምዕራፍ 2ን አንብብ።  ጥያቄ 1. የሐዋርያው ስብከት «መንፈስንና ኃይልን በመግለጥ ነበር» ሲል ምን ማለቱ ነው? ይህ ሊሆን የቻለው ጳውሎስ ማንን ስለሰበከ ነው?  ጥያቄ 2. በቁጥር 7 ላይ ተሰውሮ የነበረውን የእግዚአብሔርን ጥበብ «በምሥጢር እንናገራለን» ሲል ምን ማለቱ ነው?  ጥያቄ 3. አማኞች ስውር የሆነውን የእግዚአብሔርን ጥበብ እንዴት ሊያውቁት ቻሉ?  ሐዋርያው ወንጌልን በቃልና በጥበብ ብልጫ አልሰበከም፤ ይህም ማለት ወንጌልን ለቆሮንቶስ ሰዎች በሰበከ ጊዜ የቆሮንቶስ ሰዎች በሚያደንቁት በግሪኮች ፍልስፍናና የንግግር ዘይቤ (ርሂቶሪክ) በመጠቀም አልነበረም። ነገር ግን አዋቂ ነን የሚሉ በሚንቁት በክርስቶስ ወንጌል ተመክቶ ነበር፡፡ በዚያም አላፈረም፤ የእግዚአብሔር የማዳን ኃይል በወንጌል በኩል ተገልጿልና፤  (ሮሜ 1:16ና 17)።  ይህን ነጥብ በደንብ ልንገነዘበው ይገባናል። በማያምኑ ሰዎች ፊት የክርስትናን እምነት ተቀባይነት ለማስገኘት ብለን ወንጌልን በተለያየ የሳይንስና የፍልስፍና ቅመም ብናጅለው እናበላሸዋለን። ለዓለማውያን አንዲዋጥላቸው እናደርግ ይሆናል፤ ግን ወንጌልን ሳይሆን የሰውን ጥበብ የእምነታቸው መሠረት አደረግን ማለት ነው። ጳውሎስም የፈራው ይህንኑ በር፤ (ቁጥር 4 እና 5)  ጥያቄ 4. አንዳንድ ሰዎች ወንጌልን ለውጠው በሰው ጥበብ ሲሰብኩ ያየህበት ጊዜ አለ? ካየህ ወንጌሉን የለወጡት እንዴት ነበር?  «በበሰሉት መካከል ጥበብን እንናገራለን» (ቁጥር 6)። የበሰሉት ማለቱ በመንፈስ ቅዱስ አስተማሪነት የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገር የተረዱትን ማለቱ ነው። የእግዚአብሔር ጥልቅ ነገር የመስቀሉ ቃል ነው። ያልበሰሉት ሥጋውያን ወይም ዓለማውያን ይህንን ነገር ሊገነዘቡት አይችሉም። «ያልበሰሉት» የተባሉት በመንፈስ ያላደጉት ክርስቲያኖች ሳይሆኑ ፍጹም ወንጌልን ያልተቀበሉትን ዓለማውያን ናቸው፡፡ ይህ ለመሆኑ ማስረጃው ቁጥር 14-16 ነው።  ወንጌል «እግዚአብሔር አስቀድሞ ከዘመናት በፊት ለክብራችን የወሰነውን ተሰውሮም የነበረውን የእግዚአብሔርን ጥበብ በምሥጢር» ይገልጣል፤ (ቁጥር 7)። በምስጢር መገለጥ ማለትም ሰው በሚሰጠው መመራመር የተገኘ ሳይሆን እግዚአብሔር የገልጠው ብቻ ነው ማለት ነው፡፡ ይህ እውቀት የሳይንስ እውቀት አይደለም፤ ምክንያቱም ለተመራመረና ላጠና ሁሉ የሳይንስ ጥበብ ክፍት ነው፤ ይህ ግን ክፍትነቱ እግዚአብሔር ለገለጠላቸው ብቻ ነው፡፡  ይህ የወንጌል ምስጢር ከጊዜ በኋላ የታሰበ ትኩስ ነገር አይደለም፤ አስቀድዋ ከዘመናት በፊት በእግዚአብሔር ታስቦ ነበር። ደግሞም ይህ በእግዚአብሔር ብቻ እንጂ ከሰዎች በማንም አእምሮ ውስጥ ያደረ አልነበረም! (ቁጥር 9)።  እኛ ማለት አማኞች ይህን ምስጢር አንዲት ልናውቀው ቻልን? “ለእኛ እግዚአብሔር በመንፈሱ በኩል ገለጠው” (ቁጥር 10)። ይህም ለእኛ የተሰጠበት ምክንያት በእኛ ውስጥ ሊያሰጠን የሚችል ነገር ተገኝቶብን ሳይሆን “እንዲያው” ነው የተሰጠን፤ (ቁጥር 12)። ስለዚህ ወንጌልን የምናምነውም የምናስተምረውም በመንፈስ ቅዱስ ረዳትነት ብቻ መሆኑን መገንዘብ አለብን። በወንጌል ላይ የሰውን ጥበብ በማንኛውም ደረጃ ላይ ከጨመርንበት እንበርዘዋለን።  ነገር ግን ለእኛ የእግዚአብሔር ጥበብ የተገለጸልን እንዴት ነው? የተገለጸው በመጽሐፍ ቅዱስ ነው። በቃሉ ውስጥ የተገለጸውን የእግዚአብሔርን ጥበብ መንፈስ ቅዱስ ይወስድና ለእኛ እንደሚገባን አድርጎ በምንገኝበት ሁኔታ ውስጥ ተግባራዊነቱን ይገልጽልናል። ትምህርታችንና አመለካከታችን በይበልጥ በእግዚአብሔር ቃል ላይ በተደገፈ ቁጥር መንፈስ ቅዱስ ደግሞ ቃሉን እንደ ጥበብ በእኛና በሌሎች ሕይወት ውስጥ እንድንጠቀምበት ያደርገናል።  ጥያቄ 5. ላልዳኑት ግልፅ ያልሆነውን ነገር መንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔርን ቃል በመጠቀም እንዴት አድርጎ ነው ግልፅ ያደረገልህ?  እኛ እንዲህ የምናደንቀው ወንጌል ለማያምኑት ምኝነት የሆነበት ምክንያት ምስጢሩ ሳይገባቸው ስለቀረ ነው፤ (ቁጥር 14-15)። ወንጌል ቀርቶ በወንጌል የሚያምኑት ራሳቸው ለማያምን ሰው አስተሳሰባቸው አይገባቸውም፤ ስለዚህ የማያምኑት አማኞችን በከንቱ ሲቃወሟቸውና በድንቁርና ተመርኩዘው እምነታቸውንና ለሕይወታቸው ከንቱ ስያሜና ስድብ ሲሰጡ ይታያሉ። ክርስቶስን የማያውቅ የአማኝንም አስተሳሰብ ሊያውቀው አይችልም (ቁጥር 16)። (ምንጭ፤ በትምህርተ መለኮት ማስፋፊያ (ትመማ) መልክ የተዘጋጀ ጽሑፍ፡- በቄስ ኃይሉ መኮንን)

አገልግሉት በሰው ጥበብ ሳይሆን በእግዚአብሔር ጥበብ መሆን አለበት (1ኛ ቆሮ. 2:1-16)  Read More »

የዓለም ጥበብና የእግዚአብሔር ጥበብ (1ኛ ቆሮ. 1:18-31) 

( 1ኛ ቆሮንቶስ 1:18-31ን) አንብብ።  ጥያቄ 1. የመስቀሉ ቃል ሞኝነት ነው ሲል እንዴት የእግዚአብሔር ነገር ሞኝነት ሊሆን እንደቻለ አስረዳ።  ጥያቄ 2. እግዚአብሔር ራሱ የሰውን አእምሮ የፈጠረ ሲሆን ለምን የሰውን ጥበብ መልሶ ይቃወማል?  ጥያቄ 3. ለአይሁድና ለግሪኮች ለእያንዳንዳቸው የወንጌሉ ቃል እንዴት መሰናክል ሊሆን ቻለ?  ጥያቄ 4. እግዚአብሔር የዓለምን ጥበብ ለመቃወም ሁለት እርምጃዎችን ወሰደ፤ እነዚህ እርምጃዎች ምንና ምን ናቸው? (ለዚህ ጥያቄ መልስ በተለይ ቁጥር 18ና 26ን ተመልከት)።  የመስቀሉ ቃል ሞኝነት የሆነው በራሱ በእውነትም ሞኝነት ሆኖ ሳይሆን በዓለማውያን ዘንድ ሞኝነት ሆኖ ተቀጠረ ማለት ነው። አናጺዎች የጣሉት ጽንጋይ የማዕዘን ራስ ሆነ ከሚለው ቃል ጋራ አብሮ የሚሄጽ ቃል ነው፡፡ «ለሚጠፉት ሞኝነት ነው ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነው»፡፡ ዓለማመን የእግዚአብሔርን የማዳን ኃይል ወደ ሞኝነት ቀየረባቸው። ግን ይህ የናቁት «ሞኝ» ነገር አንድ ቀን በፍርድ ያፋጥጣቸዋል፤ (የሐዋ.17:30-31፤ ሮሜ 2:16፤ ራዕይ 6፡16 እና 17)።  እግዚአብሔር የሰውን ጥበብ ቢፈጥርም ሰው እግዚአብሔር የሰጠውን ጥበብ አዙሮ እግዚአብሔርን መዋጊያ ስላደረገው እግዚአብሔር የሰውን ጥበብ ከንቱ እንዲሆን አድርጓል። ይህም የሆነው ዓለም ሞኝ በምትለውና በምትንቀው በመስቀል ቃል የደህንነትን መንገድ በማቅረብ ነው። ስለዚህ የዓለም መርማሪም ሆነ ተራ ያልተማረው ራሱን ከንቱ አድርጎ ወደ እግዚአብሔር መቅረብ አለበት፤ (ቁጥር 21)።  እግዚአብሔር የዓለምን ጥበብ በሁለት መንገድ ከንቱ አደረገ፤ ሞኝነት በተባለው በመስቀል በኩል ደህንነትን ማዘጋጀቱና የዓለምን ተራ ሰዎች የመንግሥቱ ወራሾች አድርጎ መምረጡ ነው። የዓለም ተራ ነገር የተመረጠበት ምክንያት ያ ተራው ነገር እውነትም ከከበረው ነገር ተመራጭ ሆና ስለተገኘ ሳይሆን በራሱ የሚመካበት ስለሌለውና ባዶነቱን በቶሎ ስለሚገነዘብ ብቻ  ነው፡፡ «የሚመካ በእግዚአብሔር ይመካ» የተባለው ቃል የሰው ሁሉ መመሪያ መሆን ይገባዋል፤ ነገር ግን የዓለም አዋቂዎች በጥበባቸው እየተመኩ በመስቀሉ ቃል ይሰናከላሉ፤ (ቁጥር 25-31 ተመልከት)። ስለዚህ መስቀሉ ጥበበኞችን በትዕቢታቸው ስላጠመዳቸው ሞኝነት መሆኑ ቀርቶ ሰው በጥበቡ ሊደርስበት የማይችል ረቂቅ የእግዚአብሔር ጥበብ ነው፤ (ቁጥር 24)፡፡ ይህን ሀሳብ ሐዋርያው በአግቦ አነጋገር ሲገልጽ እንዲህ ይላል፤ «ከሰው ይልቅ የእግዚአብሔር ሞኝነት ይጠበባልና»፡፡ ይህ ማለት ከሰው ጥበብ ይልቅ የእግዚአብሔር ሞኝነት የበለጠ ጥበብን ያሳያል።  የእግዚአብሔር ጥበብ የተገለጸው የእግዚአብሔር ጥበብ በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ ነው። የእግዚአብሔር ጥበብና ኃይል የተገለጸው በኢየሱስ ምጽዓትና ሞት ነው። ምንም እንኳን የእግዚአብሔር ልጅ ቢሆንም ምድር ላይ መጥቶ የኖረው በታላቅ ኃይልና ክብር አልነበረም። እንዲያውም አንደ አገልጋይ ሆኖ ነበር የመጣው። የመጣውም ለኃጢአታችን ሲል ለመሞትና በዚህም ሞቱ የደህንነትን መንገድ እንዲከፍትልን ነበር። ላልዳኑት ይህ የደህንነት መንገድ ሞኝነት ነው። አይሁዳውያን ይጠብቁ የነበረው ከጠላቶቻቸው እጅ ነፃ የሚያወጣቸውን ታላቅና ድል አድራጊ ንጉሥ ነበር። እንደማንኛውም ተራ ነፍሰ ገዳይ የሚሰቀል መሢህ አልነበረም የሚጠብቁት። አሕዛቦችም፥ በተለይ ግሪኮች ታላቁን የእግዚአብሔር የደህንነት ዓላማ ሊረዱ አልቻሉም። ነገር ግን የድል ምልክት የሆነው መስቀል በእግዚአብሔር ዓላማ ውስጥ ዋነኛውን ሥፍራ ይዟል፡፡ በዚህ መስቀል አማካኝነት፡- ሀ. ሰይጣን ተሸንፏል።  ለ. በቅዱሱ እግዚአብሔርና በኃጢአተኛው ሰው መካከል የእርቅ መንገድ ተከፍቷል።  ሐ. እንደ እግዚአብሔር ልጆች የቅድስናና የጽድቅ ኑሮ እንድንኖር ኃይሉ ተሰጥቶናል።  የእግዚአብሔር ዓላማና ጥበብ ከሰው የተለየ መሆኑን የምናረጋግጠው፥ እግዚአብሔር በዓለም የተናቀውን ነገር ወደ ራሱ አምጥቶ ለክብሩ ሲጠቀምበት በማየታችን ነው፡፡  ጥያቄ 5. ሀ/ ይህንን ከላይ የተጠቀሰውን የእግዚአብሔርን ጥበብ የመናቅን ጉዳይ ለሰዎች በምትመሰክርበት ጊዜ በምን መልኩ ነው ያየኸው? ለ/ እግዚአብሔር በዓለም ዓይን የተናቀውን ሰው መርጦ በታላቅ ኃይል ለእርሱ አገልግሎት ሲያዘጋጃው ያየኽው ሰው ካለ እንዴት አድርጎ ይህንን ሰው ተጠቀመበት? (ምንጭ፤ በትምህርተ መለኮት ማስፋፊያ (ትመማ) መልክ የተዘጋጀ ጽሑፍ፡- በቄስ ኃይሉ መኮንን)

የዓለም ጥበብና የእግዚአብሔር ጥበብ (1ኛ ቆሮ. 1:18-31)  Read More »

መለያየት በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ (1ኛ ቆሮ. 1:4-17)

1ኛ ቆሮንቶስ 1:4-17ን በጥንቃቄ በመመልከት የሚከተሉትን ጥያቄዎች መልስ።  ጥያቄ 1. ጳውሎስ «ለክርስቶስ መመስከሬ በእናንተ ዘንድ እንደጸና» ሲል ምን ማለቱ ነው?  ጥያቄ 2. በቁጥር 9 ላይ ሐዋርያው ክርስቲያኖች ስለ አንድ ነገር እርግጠኛ እንዲሆኑ ይነገራቸዋል፤ ያ ነገር ምንድነው? ጥያቄ 3. ጳውሎስ፣ “ሁላችሁ አንድ ንግግር እንድትናገሩ በአንድ ልብና በአንድ አሳብም የተባበራችሁ እንድትሆኑ ” (ቁጥር 10) ሲል ሰዎች ሁሉ ተመሳሳይ ሃሳብ እንዲይዙ መፈለጉን ያሳያል? ጥያቄ 4. በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የመለያየት መነሻ የሆናቸው ነገር ምን ነበር? (ቁጥር 12ን ተመልከት።)  ጥያቄ 5. በውኃ ጥምቀትና በወንጌል መስበክ መካከል ያለውን ልዩነት በማጤን በአጭሩ መግለጫ ስጥ።  ጥያቄ 6. ሀ) በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ ያሉትን ችግሮች ዘርዝር። ለ) በእነዚህ ችግሮች ላይ ማተኮር ተስፋ መቁረጥን ወይም ፍራቻን እንዴት ሊያስከትል እንደሚችል ግለጽ። ሐ) እግዚአብሔር በግለሰቦችና አብያተ ክርስቲያናት ሕይወት በመሥራት ስሙን ሊያስከብር በመቻሉ ላይ ብናተኩር አመለካከታችን እንዴት ይቀየራል? ምንም እንኳ የቆሮንቶስ ምእመናን በድካማቸው ሐዋርያውን ቢያደክሙትም በመጀመሪያ የሰበከላቸው ወንጌል በእነርሱ ዘንድ ሥር ሰዶ መገኘቱ እግዚአብሔርን ስለ እነርሱ እንዲያመሰግን ረድቶታል፤ «ለክርስቶስ መመስከሬ በእናንተ ዘንድ እንደጸና» ይላልና። ይህ ጽናትም በመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች ተመስክሮአል፤ «በነገር ሁሉ በቃልም በእርሱ ባለጠጎች እንድትሆኑ ተደርጋችኋል»፡፡  በክርስቶስ ጸንተው እስከቆዩ ድረስ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ እየበዛላቸው እንጂ እያነሰባቸው አይሄድም፤ «የጌታችንን መምጣት ስትጠባበቁ አንድ የጸጋ ስጦታ እንኳ አይጎድልባችሁም»፡፡ የጌታን መምጣት መጠባበቅ ማለትም በክርስትና ሕይወት ታማኝ ሆኖ መኖር ማለት ነው። ይህ በክርስትና ሕይወት ታማኝ ሆኖ መኖር ራሱ በጸጋው የሚሰጠን እንጂ በራሳችን ጥረት የምናሳየው አይደደም፤ «እርሱም ያለ ነቀፋ እንድትሆኑ እስከፍጻሜ ድረስ ያጸናችኋል»፡፡ በሚገጥሙን ነገሮች ሁሌ ታማኝ ሆነን ስንገኝ በነገር ሁሉ እግዚአብሔር ታማኝ ሆኖ እንደሚረዳን እርግጠኞች መሆን እንችላለን።  ይህ ጽናት የሚመጣው:- 1ኛ. አገልጋዮች በእግዚአብሔር ቃል መሠረት ተገልጋዮችን ሲረዱ፤ 2ኛ. ተገልጋዮች የተነገራቸውን ጉድለት በእግዚአብሔር ቃል መሠረት ሲያርሙ ነው። ይህንንም አገልገሉት ሐዋርያው በ1:10-13 ባለው ውስጥ ያቀርብላቸዋል። እንግዲህ አንደ ተስፋ ቃሉ መሠረት እስከፍጻሜ ጸንተው ለመቆየት ይህን የማይገባ መከፋፈላቸውን ማረም ይኖርባቸዋል።  ሐዋርያው «ለማጥመቅ ክርስቶስ አልላከኝምና ወንጌልን ልሰብክ እንጂ » ሲል ጥምቀትና ወንጌል የተለያዩ መሆናቸውን ያሳያል፡፡ ጥምቀት ምልክት ብቻ እንጂ የማዳን ኃይል የለውም፡፡ ወንጌል ግን ፍጹም የማዳን ኃይል ነው፤ (ሮሜ 1:16 እና 17 ተመልከት)፡፡ ስለዚህ ጥምቀት ያድናል ብለው የሚያምኑ በዚህ ሐዋርያዊ ቃል ሃሳባቸውን ማረም ይገባቸዋል።  በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ መለያየትን የፈጠረው ክርስቲያኖቹ ዓይናቸውን ከክርስቶስ ላይ አንሥተው በሰው ወይም ሰው ሰራሽ በሆኑ ሥጋውያን ሥርዓቶች መደገፍ ስለጀመሩ ነው። ይህም በክርስቶስ ላይ ሳይሆን በአገልጋዮቻቸው ላይ መደገፍና እንዲሁም በወንጌል ቃል ሳይሆን በጥምቀት መመካታቸው ነው።  የጳውሎስ ምኞት የቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን በአንድ መንፈስና በአንድ ልብ እንድትዋሃድ ነበር። እነርሱ ግን እውነተኛ ደህንነት በሚገኝበት በመስቀሉና በኢየሱስ ላይ ዓይናቸውን ከማድረግ ፋንታ በሰዎች ላይ ነበር የታመኑት። በተጨማሪም አንዳንዶች የአይሁድ ቤተ ክርስቲያን መሪ የሆነው የኬፋ (ለጴጥሮስ የተሰጠ ሌላ ስም) ተከታይ ነኝ እያሉ ፥ ሌሎች ደግሞ የአሕዛብ ቤተ ክርስቲያን መሪ የሆነው የጳውሎስ ተከታይ ነኝ እያሉ፣ በመጨረሻም ዳግሞ ሌሎች ጳውሎስ የቆሮንቶስን ቤተ ክርስቲያን መሥርቶ ከሄደ በኋላ እዚያ ድረስ መጥቶ የሰበከውና ያስተማረው የአጵሎስ ተከታይ ነን በማለት እርስ በርሳቸው ተከፋፍለው ነበር። (የሐዋ. 18፡24-19:1 ተመልከት)፡፡ ከዚህም በላይ አንዳንዶች ከትዕቢት የተነሣ የእኛ ከሌሎች ይሻላል በማለት ራሳቸውን «እውነተኛቹ የክርስቶስ ተከታዮች» በማለት ሰይመዋል።  አማኞች በሙሉ እምነታቸው የተመሠረተው በኢየሱስ ክርስቶስና በመስቀሉ ላይ ነው። ደህንነታቸውንም የሚያገኙት ለኃጢአታቸው በሞተው በክርስቶስ በማመን ነው። ያኔ ምንም መከፋፈል በሌለበት በክርስቶስ ቤተሰብ ውስጥ ይጠመቃሉ፡፡ ስለዚህም መከፋፈልና መደባደብ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ምንም ቦታ አይኖረውም። ምንም እንኳ የተለያዩ ቤተ ክርስቲያናት በተለያየ ሃሳብ ቢመሩም፥ እምነታችን በዚህ ላይ አይደለም፡፡ እምነታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እስከሆነና የእርሱን ቃል በታዛዥነት እስከጠበቅን ድረስ የተለያየ ሃሳብም ቢኖረን እንኳን አብረን ልናመልክ እንችላለን። (ምንጭ፤ በትምህርተ መለኮት ማስፋፊያ (ትመማ) መልክ የተዘጋጀ ጽሑፍ፡- በቄስ ኃይሉ መኮንን)

መለያየት በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ (1ኛ ቆሮ. 1:4-17) Read More »

ሰላምታ (1ኛቆሮ.1:1-3) 

ሐዋርያው ጳውሎስ ደብዳቤ ለመጻፍ የተነሣሣው ችግሮች መነሣታቸው አስገድደውት ቢሆንም ደብዳቤውን ሲጀምር ችግርን በመጥቀስ ሳይሆን የችግራችን ሁሉ መፍትሔ የሆነውን የእግዚአብሔርን ጸጋ በመተረክ ነው። ይህን ለግል ክርስቲያን ኑሮአችንም ሆነ ለአገልገሎታችን መመሪያ ማድረግ አለብን። ችግር ሲያጋጥመን ማተኮር ያለብን ለችግራችን መፍትሄ በሆነው በእግዚአብሔር ጸጋ ላይ እንጂ በችግራችን ትልቅነት ላይ መሆን የለበትም። ይህንን ክፍል ስናጠና የሐዋርያውን ምሳሌ እንከተል!  1ኛ ቆሮንቶስ 1:1-3ን አንብብና ለሚከተሉት ጥያቄዎች መልስ ስጥ።  ጥያቀ 1. «ሐዋርያ» ማለት ምን ማለት ነው? (የሚከተሉትን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች በመመልከት መልስህን አዘጋጅ፤ በተጨማሪም ኮሜንታሪ ወይም የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ለመመልከት ሞክር፤ (ሉቃስ 6፡12-16፣ የሐዋ.1፡21-22፤ 1ኛቆሮ. 9፡1-2 ገላ.1፡1-2)።  ጥያቄ 2. «በቆሮንቶስ ላለች ቤተ ክርስቲያን» ሲል የሚያመላክተው ወደ ሕንፃው ነው ወይስ ወደ ሕዝቡ? (ለመልስህ እንዲረዱህ የሚከተሉትን ጥቅሶች ተመልከት፤ ሮሜ 16፡5፤ ፊልሞና 2)፡፡ ጥያቄ 3. በቆሮንቶስ የነበሩ ክርስቲያኖች ብዙ መንፈሳዊ ድካሞች ሲገኙባቸው እንዴት ጳውሎስ «ቅዱሳን» ወይም «በክርስቶስ ኢየሱስ ለተቀደሱት» ይላቸዋል? (ለመልስህ ሃሳብ ከ1ኛ ቆሮ. 6፡9-11 ላይ ተመልከት)።  ሐዋርያው ጳውሎስ መልእክቱን ሲከፍት ሐዋርያነቱን በመናገር ይከፍታል። ይህም ገና ሲጀምር ደብዳቤው የግል ሳይሆን በሐዋርያነት ደረጃ የጻፈላቸው መሆኑን ያስረዳቸዋል። የሐዋርያን መመሪያ አለመቀበል የአንድ ተራ ሰውን መመሪያ አለመቀበል አይደለም። የሐዋርያ ቃል የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል፣ የእግዚአብሔር ቃል ነበርና! ( 1ኛቆሮ.14:37)። አንድ ሰው ሐዋርያ ሊባል የሚችለው በኢየሱስ ለሐዋርያነት ሲመረጥና ከሞት የተነሣውን ኢየሱስን በዓይኑ ካየ ነው። ኢየሱስ ካረገ በኋላ ሐዋርያት የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ነበሩ።  «በቆሮንቶስ ያለች የእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን» ሲል በጳውሎስና በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ሰዎች መካከል እግዚአብሔር ያለ መሆኑን ያስገነዝባል። የእግዚአብሔር መሆናቸው በ3፡9 ላይና በ3:16 ላይ በሰፊው ተገልጿል። እነዚህን ጥቅሶች ተመልከታቸው፡፡ቤተ ክርስቲያን በእጅ የተሠራ ሕንፃ ሳይሆን እግዚአብሔር ያዳናቸውና ከኃጢአት ያነፃቸው የእግዚአብሔር ልጆች የሆኑ ሕዝቦችን ያመለክታል።  «በክርስቶስ ኢየሱስ ለተቀደሱት» ክርስቲያን ማለት በእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ የታጠበና የተቀደሰ ነው። በ1ኛ ጴጥ.1:1 እና 2 ላይ በክርስቶስ ደምና በመንፈስ ቅዱስ የተቀድስን መሆናችንን ያስረዳል፡፡በኤፌሶን 5:25-27 ላይ ደግሞ ክርስቲያን በመንፈስ ቅዱስና በቃሉ የተቀደሰ እንደሆነ ተጽፏል።  ጥያቄ 4. ክርስቶስን እንደ ግል መድኃኒት አድርገህ ተቀብለህ የተቀደስከው መቼ ነበረ? በየዕለቱስ ቅድስናህን የምታሳየው እንዴት ነው?  ክርስቲያን ገና ዕለት በዕለት ከሚሠራቸው ኃጢአቶች ነፃ ያልሆነ ሲሆን እንዴት ቅዱስ ሊባል ይችላል? መልሱ ይህ ቅድስና በእግዚአብሔር ፊት ያለውን አቋማችንን የሚገልጽ እንጂ በራሳችን ሙሉ ቅድስናን ያልተቀዳጀን መሆናችንን አይክድም፡፡ የቆሮንቶስ ክርስቲያና፥ በዕለት ኑሮአቸው ብዙ መንፈሳዊ ጉድለቶች ሲታዩባቸው በእግዚአብሔር ፊት ግን ፍጹም ቅዱሳን ነበሩ፤ (6፡11ን በጥንቃቄ ተመልከት)።  «የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ስም በየሥፍራው ከሚጠሩት ሁሉ ጋር» ይህ ዐረፍተ ነገር ሁለት ሐሳቦችን በአንድ ጊዜ ያሳስበናል፡- 1ኛ . ቤተ ክርስቲያን በዓለም ዙሪያ የተስፋፋች እንጂ በአንድ ቦታ ብቻ የምትገኝ አለመሆንዋን ሲያስረዳ፤  2ኛ . እውነተኛ ምእመናን ደግሞ በየሥፍራው እርስ በርስ የሚሰበሰቡ መሆናቸውን ያስረዳል።  «ጸጋና ሰላም» በዘመኑ ይሰጥ የነበረ የሰላምታ ቃል ሲሆን ጳውሎስ ሐሳቡን ወደ ክርስቲያን ለውጦ «ጸጋና ሰላምን ከእግዚአብሔር የሚሰጡ በረከቶች መሆናቸውን ያስተምራል። (ምንጭ፤ በትምህርተ መለኮት ማስፋፊያ (ትመማ) መልክ የተዘጋጀ ጽሑፍ፡- በቄስ ኃይሉ መኮንን)

ሰላምታ (1ኛቆሮ.1:1-3)  Read More »

የ 1ኛ ቆሮንቶስ የመደብ ክፍፍል (Outline) 

ጥያቄ 6. ከዚህ በታች የተሰጠውን የመደብ ክፍፍል ከመመልከትህ በፊት 1ኛ ቆሮንቶስ መጽሐፍን በጥንቃቄ በመመልከት መጽሐፉን በመደብ ከፋፍል። ከዚያ በኋላ ከዚህ በታች ከተሰጠው የመደብ ክፍፍል ጋር አንተ ያወጣከውን አስተያይ።  ምንም እንኳ በዚህ ጥናት ውስጥ ለአንድ ቀን የሚሆን ሐተታ ባይሰጥም 1ኛ ቆሮንቶስን በመደብ መከፋፈል ብዙ ጥረትና ጊዜ የሚወስድ መሆኑን አስታውስ! በተቻለ መጠን ንባብህን በአንድ ጊዜ ለመፈጸም ሞክር።  ሰላምታ፤ (1:1-3)  ስለ ክርስቲያን ሕብረት፤ (ከምዕሪና 1:4 እስከ ምዕራፍ 4)  ክርስቲያን በዓለም ውስጥ እንጂ ከዓለም አይደለም፤ (ምዕራፍ 5)  የምእመናን የእርስ በርስ መካሰስ፤ (6፡1-11)  የአማኝ አካልና ዝሙት፤ (6፡12-20)  ስላ ጋብቻ ምክር፤ (ምዕራፍ 7)  ጣዖትና ነጻነት፤ (ከምዕራፍ 8 እስከ ምዕራፍ 10)  በቤተ ክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የነበሩ ቶርች፤ (ከምዕራፍ 11 እስከ ምዕራፍ 14)  – የሴቶች መከናነብና አለመከናነብ፤ 11:1-16  – ስለ ቅዱስ ቁርባን፤ 11:17-30  – ስለ መንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች፤ ምዕራፍ 12  – የተሻለው መንገድ፤ ምዕራፍ 13  – ስለ ልሳን ስጦታ መምሪያ፤ ምዕራፍ 14  ስለ ሙታን ትንሣኤ፤ (ምዕራፍ 15)  የመሰነባበቻ ሃሳቦች፤ (ምዕራፍ 16) (ምንጭ፤ በትምህርተ መለኮት ማስፋፊያ (ትመማ) መልክ የተዘጋጀ ጽሑፍ፡- በቄስ ኃይሉ መኮንን)

የ 1ኛ ቆሮንቶስ የመደብ ክፍፍል (Outline)  Read More »

የ1ኛ ቆሮንቶስ መግቢያ 

1ኛ ቆሮንቶስ የተጻፈው በሐዋርያው ጳውሎስ ነው! ( 1ኛ ቀር.1፡1)። የቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን የተመሠረተችው ሐዋርያው ጳውሎስ በቆሮንቶስ ከተማ ለአሥራ ስምንት ወር በተቀመጠበት ጊዜ ነበር፤ (የሐዋ.18፡1-11) አንብብ። በዚህ በቆሮንቶስ ከተማ የተለያዩ የሕዝብ ዘሮች ይኖሩ ነበር። በቤተ ክርስቲያንም ውስጥ እንዲሁ የተቀላቀሉ ወገኖች ይገኙ ነበር፤ ለምሳሌ አህዛብና አይሁዶች ነበሩ። ይህን ዓይነት የዘር ልዩነት በዘመናችን በየቤተ ክርስቲያኑ እናገኛለን። ይህንን የዘር ልዩነት በዚያን ጊዜ የመከፋፈል ዝንባሌ እንደፈጠረ አሁንም ያው ችግር ሊነሣ ይችላልና መፍትሔውን በጥንቃቄ ከቃሉ እንመልከት።  የቆሮንቶስ ሰዎች በንግድ በጣም የተራመዱ ስለነበሩ ሀብታሞች ነበሩ። ደግሞም የቆሮንቶስ ከተማ ሰዎች በኃጢአት በጣም የከፋ ከመሆናቸው የተነሣ «እንደ ቆሮንቶስ ሰው ኑር» የተሰኘ ምሳሌያዊ አነጋገርን አትርፈው ነበር፡፡ በዚህ ሕዝብ መካከል እግዚአብሔር ለራሱ ወገንን መረጠ፤ ( 1ኛቆሮ.6፡9-11)። የኃጢአት ብዛት እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያኑን ከመትከል አላገደውም!!  ጳውሎስ ይህን ጸብዳቤ ለመጻፍ የተነሣሣበት ሁለት ምክንያቶች ነበሩት፡ 1ኛ / ስለ ቤተ ክርስቲያኒቱ ደስ የማይል ሪፖርት ሰምቶ ስለነበር፤ (1:11፤ 5:1) ተመልከት።  2ኛ / የቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ሰዎች ጳውሎስን የተለያዩ ጥያቄዎች ጠይቀውት ለጥያቄዎቻቸው መልስ ለመስጠት በበር፤  (7:1 ተመልከት)።  ስለ ቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ከሰማቸው ሪፖርቶች ውስጥ አምስቱ የሚከተሉት ናቸው፡፡ በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ መከፋፈል ነበር (3፡1-4)።  ከአባሎቹ ውስጥ አንዱ በክፉ ዝሙት ይኖር ነበር፤ (5:1)።  በአማኞች መካከል በፍርድ ቤት መካሰስ ነበር፤ ( 6፡6-8)።  በክርስቲያን ነፃነት እያሳበቡ የሚፈጸሙ ስሕተቶች ነበሩ፤ (10:23-33)።  በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ብዙ ከሥነ ሥርዓት ውጭ የሆኑ ድርጊቶች ነበሩ። ከእነዚህም ውስጥ አንዱ የጌታ እራት አፈጻፀም ሥርዓት ነበር፤ (11:27-30)።  የቆሮንቶስ ሰዎች ለጠየቁት ጥያቄዎች ሐዋርያው መልስ የሰጠባቸው ነጥቦች የሚከተሉት ናቸው።  ስለ ጋብቻ ጥያቄዎች፤ (ምዕራፍ 7)።  ለጣዖት ስለተሠዋ ሥጋ (10:14-22)።  በጉባኤ ውስጥ ስለ ሴቶች መከናነብ (11፡1-16)።  ስለ መንፈሳዊ ስጦታዎች (ከምዕራፍ 12-14)።  ስለ ሙታን ትንሣኤ፤ (ምዕራፍ 15)።  ለእነዚህ ጥያቄዎች በሚሰጣቸው መልሶች በዚያን ጊዜ ስለነበሩት አብያተ ክርስቲያናት ጠባዮች ብዙ ነገሮችን እንረዳለን። በአሁኑ ጊዜ ቤተ ክርስቲያንን በሚገጥሟት ችግሮችና በዚያን ጊዜ የቆሮንቶስን ቤተ ክርስቲያን በገጠሟት ችግሮች መካከል ብዙ መመሳሰል ስላለ ይህ መጽሐፍ ለእኛም አብያተ ክርስቲያናት በቃሚ የሆኑ መመሪያዎችን ይሰጣል። በሚከተሉት ትምህርቶች ውስጥ እዚህን ነጥቦች በዝርዝር እንመለከታቸዋለን።  ጥያቄ 1. የሐዋ. 18፡1-11ን በጥንቃቄ በመመልከት የቆሮንቶስን ቤተ ክርስቲያን አመሠራረትን ተርክ።  ጥያቄ 2. ይህን ደብዳቤ ለመጻፍ ያነሣሡት ሁለት ምክንያቶች ነበሩ፤ ለእያንዳንዱ ምክንያት የተሰጡትን ጥቅሶች በመመልከት ምክንያቶቹን ጥቀስ፡፡ ጥያቄ 3. በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ ያሉ ችግሮች በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ከነበሩት ችግሮች ጋር እንዴት ይመሳሰላሉ? (ምንጭ፤ በትምህርተ መለኮት ማስፋፊያ (ትመማ) መልክ የተዘጋጀ ጽሑፍ፡- በቄስ ኃይሉ መኮንን)

የ1ኛ ቆሮንቶስ መግቢያ  Read More »

ለቅዱሳን የተደረገ የገንዘብ መዋጮ እና የሐዋርያው ጳውሎስ ዕቅድ (1ኛ ቆሮ. 16፡1-24)

የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች አይተዋቸው ለማያውቋቸውና በኢየሩሳሌም ለሚኖሩ አይሁዳውያን ክርስቲያኖች ገንዘብ መስጠት ያለባቸው ለምንድን ነው? (1ኛ ቆሮ. 6፡1-4) የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች የጠየቁት የመጨረሻው ጉዳይ በኢየሩሳሌም ለሚገኙ አይሁዳውያን አማኞች ገንዘብ መዋጣትን የሚመለከት ነበር። ጳውሎስ በቅርቡ ክርስቲያኖች በድህነት ወደሚሠቃዩባት ወደ ኢየሩሳሌም እንደሚሄድ ለአሕዛብ አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ የተናገረ ይመስላል። ስለሆነም የአሕዛብ ክርስቲያኖች ለአይሁድ ክርስቲያኖች ፍቅራቸውንና ወንጌሉን ለማካፈላቸው ምስጋናቸውን የሚገልጹበትን ዕድል ሰጣቸው። ጳውሎስ አሕዛብ ክርስቲያኖች በየሳምንቱ ምጽዋት እንዲሰበስቡና እርሱ በሚመጣበት ጊዜ በተወሰኑ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች አማካኝነት ገንዘቡን ወደ ኢየሩሳሌም እንዲልኩ መከራቸው። (ጳውሎስ እንደገና በ2ኛ ቆሮ. 8-9 ስለዚህ ጉዳይ ያነሣል።) ከዚህ ክፍል አያሌ ጠቃሚ እውነቶችን ልንማር እንችላለን። ሀ. ክርስቲያኖች ሁሉ ሁልጊዜም ለእግዚአብሔር ሥራና ለእግዚአብሔር ሕዝብ ገንዘባቸውን መስጠት አለባቸው። ጳውሎስ በየእሑዱ ምጽዋት እንዲሰበስቡ ነግሯቸዋል። ለ. አማኞች ለራሳቸውና ለማኅበረ ምእመኖቻቸው ብቻ ሳይሆን በዓለም ሁሉ ለተበተኑት ወንድሞችና እኅቶች ፍላጎት ሊያስቡ ይገባል። ሐ. ክርስቲያን መሪዎች ከገንዘብ ጋር በተያያዘ ዝናቸው እንዳይጎድፍ መጠንቀቅ አለባቸው። ጳውሎስ ገንዘቡን ለማድረስ ሌሎች የቤተ ክርስቲያኒቱ መሪዎች አብረውት እንዲሄዱ ጠይቋል። ጳውሎስ ይህን ያደረገው በራሱ ታማኝነት ላይ ጥርጣሬ ስላደረበት ሳይሆን፥ ታማኝነቱን የሚጠራጠሩ ሰዎች ወሬ እንዳያዛምቱበት ነበር። የመሪዎች ስም ከሚጎድፍባቸው ዐበይት መንገዶች አንዱ የተሳሳተ የገንዘብ አያያዝ ወይም ሌሎች ሰዎች የሚጠራጠሩበትን በር መክፈት ነው። የውይይት ጥያቄ፡– ሀ) የተሳሳተ የገንዘብ አጠቃቀም የአንድን ቤተ ክርስቲያን መሪ ስም ሲያጎድፍ ያየኸው እንዴት ነው? መሪዎች ስማቸውን ለመጠበቅ ምን የተለየ ነገር ማድረግ አለባቸው? ለ) ብዙ ክርስቲያኖች አሥራትን የሚሰጡ ይመስልሃል? ካልሆነ ለምን? ሐ) የአንድ ቤተ ክርስቲያን የገንዘብ አጠቃቀም፤ የራስን ጥቅም ከመፈለግና ከራስ ወዳድነት ወይም ደግሞ ከቤተ ክርስቲያን ውጪ ክርስቲያን ያልሆኑትን ለመርዳት እንደዋለ የሚታወቀው እንዴት ነው? መደምደሚያ (1ኛ ቆሮ. 16፡5-24) ጳውሎስ ተጨማሪ ግላዊ መረጃ በመስጠት ይህን መልእክት ደምድሟል። በኤፌሶን ለጥቂት ወራት ከተቀመጠ በኋላ በመቄዶንያ በኩል ወደ ቆሮንቶስ ተጉዞ አያሌ ወራት እንደሚቆይ ይነግራቸዋል። ጢሞቴዎስ ሊጎበኛቸው ስለሚመጣ መልካም አቀባበል እንዲያደርጉለት ያሳስባቸዋል። በተጨማሪም፥ ጳውሎስ አጵሎስ ሄዶ እንዲያገለግላቸው መፈለጉንና አጵሎስ ግን በወቅቱ ይህንኑ ሊያደርግ አለመቻሉን ገልጾአል። አጵሎስ ከጳውሎስ የበለጠ የመናገር ስጦታ የነበረው ቢመስልም ጳውሎስ አልቀናበትም ነበር። ጳውሎስ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በመንፈሳዊ ሕይወታቸው እንዲያድጉ ስለሚፈልግ፥ አጵሎስ ከመንፈሳዊ ለጋነታቸውና ከችግሮቻቸው አልፈው እንዲሄዱ ይረዳቸው ዘንድ ወደደ፡፡ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ አማኞች ሰላምታንና በሦስት ተወካዮቻቸው (እስጢፋኖስ፥ ፈርዶናጥስና አካይቆስ) አማካኝነት ስለላኩለት ስጦታ ምስጋና በማቅረብ መልእክቱን ደምድሟል። ከእስያ ክርስቲያኖች በተለይም ከአቂላና ከጵርስቅላ ሰላምታ አቅርቦላቸዋል። አቂላና ጵርስቅላ በቆሮንቶስ ከተማ ስለኖሩ የአገሪቱ ክርስቲያኖች ያውቋቸው ነበር። ምሁራን ጳውሎስ የዓይን ሕመም ስለነበረበት መልእክቱን ራሱ ለመጻፍ ሳይሳነው እንዳልቀረ ያስባሉ። በመሆኑም፥ ለሮሜ መጽሐፍ እንዳደረገው በሌላ ጸሐፊ ተጠቅሟል (ሮሜ 16፡22)። ነገር ግን መልእክቱ የሌላ ሰው ሳይሆን የራሱ እንደሆነ ለማሳየት በደብዳቤው ላይ ፈርሞበታል። ጳውሎስ ይህንን መልእክት የፈጸመው ክርስቶስን የማይወዱትን በማስጠንቀቅ ነበር። ጳውሎስ የክርስቶስን ምጽአት ቢናፍቅም፥ ምጽአቱ ክርስቶስን በሕይወታቸው ባላከበሩት ሰዎች ላይ ፍርድን እንደሚያስከትል አልዘነጋም። እኛም ልባችንን ሁልጊዜ ልንመረምር ይገባል። ልባችን «ማራናታ» ወይም «ጌታ ኢየሱስ ሆይ ና» እያለ ቢጮህ፥ ለፍርዱ በፊቱ ለመቆም ልባችንን መመርመር አለብን። ለክርስቶስ ምጽአት ዝግጁዎች ነን? የውይይት ጥያቄ፡- ከ1ኛ ቆሮንቶስ ጥናታችን የተማርሃቸው አንዳንድ ቁልፍ ትምህርቶች ምን ምንድን ናቸው? (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ለቅዱሳን የተደረገ የገንዘብ መዋጮ እና የሐዋርያው ጳውሎስ ዕቅድ (1ኛ ቆሮ. 16፡1-24) Read More »