1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች

አማኝ ከሞተ በኋላ ሥጋው ምን ይሆናል? (1ኛ ቆሮ. 15፡1-58)

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ሞት የሰዎችን እምነት ጭምር የሚያናጋ አስፈሪ ነገር መሆኑን በተለያዩ መንገዶች አብራራ። ለ) ለክርስቲያኖች ከሞቱ በኋላ ስለሚደርስባቸው ነገር ግልጽ ግንዛቤ ማግኘት አስፈላጊ የሚሆነው ለምንድን ነው? በዓለም ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ሁሉ ሞትን ይፈራሉ። ከሞት ለማምለጥ ያላቸውን ሀብት ሁሉ ለመሠዋት ፈቃደኞች ናቸው። ከሞት በኋላ የሚሆነውን ነገር በፍጹም አያውቁትም። አንድ መልካም ነገር ይመጣል ብለው ተስፋ ቢያደርጉም አያውቁትም። ስለሆነም፥ ሞት በተስፋ ቢስ ለቅሶና ፍርሃት የተሞላ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ግን ከሞት በኋላ በክርስቲያን ላይ ስለሚሆነው ነገር በግልጽ ያብራራል። ይህም እውቀት በሽታንና ሞትን ሳንፈራ በእርጋታ ክርስቶስን እንድንከተል ያደርገናል። ለክርስቲያን ሞት ሥቃይ፥ መከራ ወይም ሞት ወደሌለበት ስፍራ የሚመራን በር ማለት ነው። በዚያ ከክርስቶስ ጋር ለዘላለም እንኖራለን። የውይይት ጥያቄ፡- 1ኛ ቆሮ. 15ን አንብብ። ሀ) ጳውሎስ ስለ ሙታን ትንሣኤ የገለጻቸውን እውነቶች ዘርዝር። ለ) እነዚህን እውነቶች ክርስቲያኖች ሁሉ በግልጽ ማወቃቸውና ማመናቸው ለምን ይጠቅማል? ችግሩ፡- ብዙ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች የሙታን ትንሣኤ መኖሩን የተጠራጠሩ ይመስላል። ግሪኮች በሥጋ ትንሣኤ አያምኑም ነበር። ለዚህ ነበር የአቴና ሰዎች ጳውሎስ ወንጌሉን ሲመሰክርላቸው የቀለዱበት። (የሐዋ. 17፡32 አንብብ።) እንደ ሰውነት ያሉ የተፈጠሩ ነገሮች ተራና በራሳቸው ክፉ ናቸው የሚል እምነት ነበር። ስለሆነም፥ እግዚአብሔር ተራ የሆነውን ነገር ወደ መንግሥቱ እንዲገባ ስለማይፈቅድ መንፈስ እንጂ ሥጋ ከሞት እንዲነሣ አያደርግም የሚል አሳብ ነበራቸው። የቆሮንቶስ ክርስቲያኖችም ከሞት መነሣትን በተመለከተ ጳውሎስ ማብራሪያ እንዲሰጣቸው ደብዳቤ ጽፈው ጠየቁት። የጳውሎስ መልስ፡ ፩. የክርስቶስ ትንሣኤ እኛም ከሞት እንደምንነሣ ያረጋግጣል (1ኛ ቆሮ. 15፡1-34) ሀ. ወንጌሉ ክርስቶስ ለኃጢአት መሞቱን ብቻ ሳይሆን በሥጋ ከሞት መነሣቱንም ያስተምራል። የእርሱ ትንሣኤ መንፈሳዊ ብቻ አልነበረም። የክርስቶስ መነሣት በብዙ ሰዎች ተረጋግጧል። ራሱ ጳውሎስም ከሞት የተነሣውን ክርስቶስን አይቶታል። ጳውሎስ ከዕርገት በኋላ ከሞት የተነሣውን ጌታ ማየቱ ክርስቶስ ወደ ሰማይ ከሄደ በኋላም ቢሆን የትንሣኤ አካሉን ይዞ እንደሚገኝ ያመለክታል። ስለሆነም፥ የምናመልከው ክርስቶስ እንደ መንፈስ ብቻ ሳይሆን በትንሣኤ አካልም ይኖራል። ለ. አካላዊ ትንሣኤን መካድ ማለት ክርስቶስ ራሱ ከሞት አልተነሣም እንደ ማለት ነበር። ይህ ማለት ደግሞ ጳውሎስ ስለ ክርስቶስ ትንሣኤ የሚያስተምረው ትምህርት ብቻ ሳይሆን ጠቅላላው ክርስትና ውሸት ነው እንደ ማለት ነበር። ቀደም ሲል የሞቱት ክርስቲያኖችም እንደ ዓለማውያን ሁሉ ያለ ተስፋ ጠፍተዋል እንደ ማለት ይሆናል። ለወደፊቱ የትንሣኤ ተስፋ ከሌላቸው ደግሞ ክርስቲያኖችም እንደ ዓለማውያን ሁሉ ያለ ተስፋ ጠፍተዋል ማለት ነበር። ለወደፊቱ የትንሣኤ ተስፋ ከሌላቸው ደግሞ ክርስቲያኖች ለእግዚአብሔር መኖራቸውን አቁመው ለራሳቸው መኖር ይኖርባቸዋል። ምቾትን በመከተል በሕይወት መደሰት አለብን። እንዲሁም፥ ከሞት በኋላ ሕይወት ከሌለ ፋይዳ ሊሰጥ ከማይችል ስደት መሽሽ አለብን ማለት ነው። ሐ. ክርስቶስ ከሞት የተነሣ ሲሆን፥ ለተከታዮቹ የትንሣኤ ምሳሌ ነው። ጳውሎስ የክርስቶስ ትንሣኤ የሁሉም ክርስቲያኖች ትንሣኤ ምሳሌ መሆኑን ለማሳየት ሁለት ማብራሪያዎችን ተጠቅሟል። በመጀመሪያ፥ ክርስቶስ የሚሞቱት ክርስቲያኖች ሁሉ «በኩር» መሆኑን ገልጾአል። በብሉይ ኪዳን አዝመራ በሚደርስበት ጊዜ አይሁዶች ከእህል አነስተኛውን ክፍል ወደ ቤተ መቅደስ ወስደው ለእግዚአብሔር ያቀርቡ ነበር (ዘሌ. 23፡10-11፥ 17፥20)። ይህንንም የሚያደርጉት እግዚአብሔር አዝመራውን እንደሰጣቸው ለመግለጽና ለስጦታውም ምስጋናቸውን ለማቅረብ ነበር። አንድ ሰው ከእህሉ የተወሰነውን ለእግዚአብሔር በሚሰጥበት ጊዜ የቀረውን ለእግዚአብሔር ክብር እንደሚያውል መግለጹ ነበር። ክርስቶስም እንዲሁ ከሞት የተነሡት ሰዎች ታላቅ አዝመራ በኩራት ነው። የክርስቶስ ተከታዮች እንደ ክርስቶስ ሁሉ ከሞት ይነሣሉ። ሁለተኛ፥ ኢየሱስ ሁለተኛው «አዳም» ነው። የመጀመሪያው አዳም በኃጢአቱ ምክንያት በሰዎች ሁሉ ላይ ሥጋዊና መንፈሳዊ ሞት አስከትሏል። ሁለተኛው አዳም ግን ከሞት በመነሣቱ ለክርስቲያኖች መንፈሳዊና ሥጋዊ ትንሣኤ ሕይወት አስገኝቶላቸዋል። መ. የክርስቶስ ትንሣኤ በዘላለማዊነት የሚፈጸም የታላቅ ሂደት ጅማሬ ነው። ክርስቶስ «የትንሣኤዎች መከር» መጀመሪያ በመሆኑ፥ የትንሣኤን ሂደት በአዲስ አካል ጀምሯል። ሁለተኛ፥ የብሉይም ሆነ የአዲስ ኪዳን ቅዱሳን ትንሣኤ ይከተላል። ሦስተኛ፥ ክርስቶስ አገዛዙን በሰዎች ሁሉ ላይ ከመሠረተና ክፋትን ሁሉ ካወደመ በኋላ፥ መንግሥቱን ለእግዚአብሔር አብ አሳልፎ ይሰጣል። ከሚጠፉት የመጨረሻ ክፋቶች አንዱ ሞት ነው። ፪. የትንሣኤው አካል አሁን ካለን አካል ጋር ቢመሳሰልም የተለየ ይሆናል (1ኛ ቆሮ. 15፡35-58)። አሁን ያለን አካል በኃጢአት የተበላሸ ስለሆነ፥ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ምን ዓይነት የትንሣኤ አካል እንደሚኖራቸው እያሰቡ ነበር። ጳውሎስ ከትንሣኤ በኋላ ስለሚኖረው ሁኔታ የተለያዩ ገለጻዎችን ያቀርባል። ሀ. ጳውሎስ የሰው ካልሆኑት ሦስት የተለያዩ አካላት ጋር በማነጻጸር ማብራሪያውን ይጀምራል። በመጀመሪያ፥ የትንሣኤ ሕይወት የተክልን ሕይወት ይመስላል። የስንዴ ዘር መሬት ውስጥ ተቀብሮ ከበሰበሰ በኋላ በእግዚአብሔር ኃይል አዲስ ተመሳሳይ ተክል ያስገኛል። ሁለተኛ፣ እግዚአብሔር ለተለያዩ እንስሳትና ዓሦች የተለያዩ አካላትን ይሰጣል። ሦስተኛ፥ ፀሐይ ከጨረቃ የበለጠ ክብር እንዳላት ሁሉ እግዚአብሔር የተለያዩ የክብር ደረጃ ዎችን ይሰጣል። ጳውሎስ ከእነዚህ ማብራሪያዎች በመነሣት የሚከተለውን አስተምሯል። እንደ ተክል ሁሉ የትንሣኤ አካላችን ከቀድሞው አካላችን ጋር የሚመሳሰል ቢሆንም አዲስና የተለየ ይሆናል። ከእንግዲህ ሞትና መበስበስ የማይነካን ዘላለማውያን እንሆናለን። የትንሣኤው አካል ተፈጥሯዊ ብቻ ሳይሆን ለዘላለም ከእግዚአብሔር ጋር ለመኖር የሚያስችል መንፈሳዊ ብቃት ያለው አዲስ አካል ነው። እንደ ተለያዩ አካላት ሁሉ፥ የትንሣኤ ተጨባጭ ትንሣኤ ይሆናል። ነገር ግን የተለየ ዓይነት አካል ይኖረናል። የፀሐይና የጨረቃ ክብር የተለያየ እንደሆነ ሁሉ፥ አሁን ያሉን አካላት ብዙ ክብር የላቸውም። ከትንሣኤ በኋላ ግን አካላችን አዲስ ክብርና ኃይል ይኖረዋል። ለ. ጳውሎስ አዳምንና ክርስቶስን (ሁለተኛ አዳም) ያነጻጽራል። አዳም የተፈጠረው ከምድር አፈር ነበር። የእኛም ቁሳዊና ኃጢአተኛ አካላት የእርሱን ይመስላሉ። ክርስቶስ ግን ከሰማይ ስለመጣ ከመጀመሪያው አዳም ይበልጣል። ክርስቶስ ከሞት ከተነሣ በኋላ አዲሱን «መንፈሳዊ» አካል መሥርቷል። ይህም ከሞት በተነሣን ጊዜ የምናገኘው ነው። ጳውሎስ መንፈሳዊ አካል የሚለው እንደ መላእክት ያለውን ዓይነት አይደለም። ነገር ግን በመንፈሳዊ ስፍራ ለመኖር የሚያስችል አካል ማለቱ ነው፡፡ የክርስቶስ ተከታዮች ከትንሣኤው በኋላ ሊዳስሱትና ሊያዩት እንደቻሉት ዓይነት ተጨባጭ ይሆናል። ነገር ግን የትንሣኤ አካላችን የማይጠፋ፣ ኃጢአት እልባና ለዘላለም ከእግዚአብሔር ጋር ለመኖር የሚችል በመሆኑ ከምድራዊ አካል የተለየ ነው። ሰውነታችን የክርስቶስን የትንሣኤ አካል ይመስላል። ሐ. የጳውሎስ ድምዳሜ፡- የትንሣኤ አካላችን ምን እንደሚመስል ሙሉ በሙሉ ግልጽ ባይሆንም፥ የክርስቶስን የትንሣኤ አካል እንደሚመስል አያጠራጥርም። ልናውቅ የምንችላቸው አንዳንድ ነገሮች አሉ። በመጀመሪያ፥ ሥጋና ደም የሆነው የአሁኑ አካላችን በዘላለማዊ የእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ ለመኖር ስለማይስማማ፥ የግድ ለውጥ መደረግ አለበት። የአሁኑ ሰውነታችን በሆነ መንገድ ተለውጦ የማይበሰብስ ይሆናል፡፡ ሁለተኛ፥ እግዚአብሔር ለጳውሎስ በብሉይ ኪዳን ያልታወቀውን «ምሥጢር» ገልጦለታል። ያም ምሥጢር በመጨረሻው ዘመን የእግዚአብሔር ልጆች ምን እንደሚሆኑ የሚያሳይ ነው። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሚመለስበት ጊዜ ነገሮች ከመቅጽበት ይለወጣሉ። ለውጡ የሚጀምረው «በክርስቶስ በሞቱት » ይሆናል። ይህም በሥጋ የሞቱትን ክርስቲያኖች የሚያሳይ ነው። ሥጋዊ ሰውነታቸው በትል ተበልቶ ቢጠፋም፥ የማይጠፋና የማይሞት የትንሣኤ አካል ከመቅጽበት ይቀበላሉ። ከዚያም በምድር ላይ በሕይወት ያሉት ሰዎች ሟች አካል በማይሞት፥ በማይጠፋና በትንሣኤ አካል ይተካል። ከዚያ በኋላ በእምነት ስንጠባበቅ በቆየነው በእግዚአብሔር ዘላለማዊ መንግሥት ውስጥ ለመኖር ዝግጁዎች እንሆናለን። ስለሆነም፥ ክርስቲያኖች ሞትን ወይም ከመቃብር በኋላ የሚመጣውን ያልታወቀ ክስተት መፍራት የለባቸውም። ምንም እንኳ የምንወዳቸው ሰዎች በሞት በሚለዩን ጊዜ ማዘናችን ባይቀርም፥ እንደ ሌሎች ሰዎች ተስፋ-ቢሶች አይደለንም። ምክንያቱም እያንዳንዱ የእግዚአብሔር ልጅ አዲስን አካል እንደሚቀበል እናውቃለን። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲመለስና እኛም ዘላለማዊ አካላችንን ተቀብለን ከሌሎች አማኞች ጋር ለዘላለም በምንኖርበት ጊዜ የመለያየቱ ሥቃይ ሳይቀር ይወገዳል። ይህ እውነት ክርስቲያኖችን ሁልጊዜም ሊያጽናናቸው ይገባል። ከመቃብር በኋላ ለዘላለም ከክርስቶስ ጋር እንደምንኖር በመረዳት በልበሙሉነት እየተመላለስን እግዚአብሔርን ልናገለግል እንችላለን። ይህ ለማያምኑ ወይም እምነታቸውን ለተዉትም ማስጠንቀቂያ ነው። ሞተው በሚነሡበት ጊዜ ከሌሎች አማኞች ጋር አብሮ የመኖር ዕድል ሳያገኙ ወደ ዘላለማዊ ሲዖል ይወርዳሉ። (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

አማኝ ከሞተ በኋላ ሥጋው ምን ይሆናል? (1ኛ ቆሮ. 15፡1-58) Read More »

ለጉባኤ አምልኮ የተሰጡ መሠረታዊ መመሪያዎች (1ኛ ቆሮ. 14፡26-40)።

ጳውሎስ ለጉባኤ አምልኮ አንዳንድ መመሪያዎችን በሚሰጥበት ጊዜ ለማስተላለፍ የሚፈልገውን መልእክት ለመረዳት ቤተ ክርስቲያኒቱ ምን ትመስል እንደነበረ ማስታወሱ አስፈላጊ ነው። ዛሬ እንደምናደርገው ቤተ ክርስቲያኒቱ በትልቅ የስብሰባ አዳራሽ ውስጥ አትሰባሰብም ነበር። አማኞች የሚሰባሰቡት በግለሰቦች ቤት ውስጥ በመሆኑ የሰዎቹ ቁጥር ከ50 ወይም 60 አይበልጥም ነበር። ስለሆነም ቤተ ክርስቲያኒቷ የኅብረት ጸሎት ወይም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚካሄድባት እንጂ በግዙፍ ሕንጻ ውስጥ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት የሚካሄድበት ዓይነት ቤተ ክርስቲያን አልነበረችም። የሰዎቹ ቁጥር ጥቂት ስለሆነ መዝሙር ለመምረጥ፥ ቃል ለማካፈል፥ በአስተርጓሚ አማካኝነት በልሳን ለመናገር፥ ወዘተ. ብዙ ነጻነት ነበራቸው። ጳውሎስ የሚከተሉትን መመሪያዎች ሰጥቷል። አምልኮ እንደ መሪዎች ወይም ኳዬርና ሰባኪ ያሉ ጥቂት ሰዎች ሁሉንም ተግባር የሚፈጽሙበትና ሌሎች በትዝብት የሚመለከቱበት ሳይሆን ምእመናን በሙሉ የሚሳተፉበት ነው። ጳውሎስም ሁሉም ትምህርት፥ ልሳን፥ ትንቢት፥ ወዘተ በማቅረብ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ እንዳለ አመልክቷል። ጳውሎስ ይህን ሲል ሁሉም ሰው ሁሉንም ነገር ማድረግ አለበት ማለቱ ሳይሆን ሁሉም ሰው ለመሳተፍ እንደሚችል መግለጹ ነበር። አምልኮው ሁሉ ለምእመናን በሙሉ ጠቃሚ መሆን አለበት። አስተርጓሚ ሳይኖር በልሳን መናገሩ ለሌሎች መንፈሳዊ ጥቅም የማያስገኝ በመሆኑ ተከልክሏል። ሰዎች የሚነገረውን አሳብ ተረድተው «አሜን» (እስማማለሁ) ሊሉ አይችሉም ነበር። የጉባኤ አምልኮ የሁሉም ስለሆነ፥ የሁሉም መረዳት ወሳኝ ነው። መልእክቱ በሚገባቸው ቋንቋ ሊተላለፍና ፕሮግራሙም እምነታቸውን የሚያንጹትን ነገሮች ሊያካትት ይገባል። (ይህ አንድ ሰው ለቡድኑ እንዲጸልይ በሚጠየቅበት ጊዜ ለራሱ መጸለይ ወይም በልሳን መናገሩ ትክክል እንዳልሆነ የሚያመለክት ይመስላል። ሁሉም የግለሰቡን ጸሎት ካልሰሙ ጥያቄውን ማጽደቃቸውን ለማሳየት «አሜን» ሊሉ አይችሉም። የጉባኤ አምልኮ ዓላማ የግል ጸሎት፥ ጥያቄ ወይም በረከት ሳይሆን፥ የሁሉም በአንድነት መሳተፍ ነው።) ነገሮች በሥርዓትና በአግባቡ ሊከናወኑ ይገባል። ሰዎች በራስ ወዳድነት ስጦታዎቻቸውን ለማሳየት በመፈለጋቸው ምክንያት የቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን በሁከት ሳትሞላ አትቀርም። ጉባኤው ብዙ ሰዎች በአንድ ጊዜ በሚናገሯቸው የልሳንና የትንቢት መልእክቶች፥ እንዲሁም በሴቶች ጫጫታ ይታወክ ነበር። ነገር ግን አምልኮ ሥርዓትን የተከተለና አግባብነት ያለው ሊሆን ይገባል። በሌላ አገላለጽ፥ አምልኮ ለሕዝቡ ባሕል በሚስማማ፥ በሚጥም፥ ሕዝቡን ደስ በሚያሰኝ መንገድ መካሄድ አለበት። ስለሆነም፥ ጳውሎስ ለቤተ ክርስቲያን አምልኮ የሚያገለግሉ መመሪያዎችን ሰጥቷል። ሀ. ሰዎች በልሳን ለመናገር ከፈለጉ ሊፈቀድላቸው ይገባል። ነገር ግን ተራ በተራ መናገር ይኖርባቸዋል። በልሳን በሚናገሩበት ጊዜ ደግሞ መልእክቱ መተርጎም አለበት። ተርጓሚ ከሌለ ዝም ብለው በልባቸው መጸለይ አለባቸው። በአንድ የአምልኮ ጊዜ ሁለት ወይም ሦስት ሰዎች ብቻ በዚሁ መንገድ መናገር ይኖርባቸዋል። ለ. ሰዎች ትንቢት መናገር ቢፈልጉ ተፈቅዶላቸው ነበር። ተራ በተራ ትንቢት መናገር ይቻላል። ትንቢትም ሆነ ልሳን በመንፈስ ቅዱስ ቁጥጥር እንጂ ራስን በመሳት (in a trance) ሊነገር አይገባም። መንፈስ ቅዱስ እንደ ሰይጣን ሰዎች ከአእምሯቸው ውጭ እንዲሆኑ አያደርግም። ግለሰቡ አእምሮውን ሳይስት መንፈስ ቅዱስንና እርሱ የሚናገረውን ይሰማል። ትንቢት የሚነገርበት ዓላማ ግለሰቡ የተሰማውን እንዲናገርና ለሌሎች መልእክት የማካፈል ዕድል እንዲያገኝ ሳይሆን፥ የእግዚአብሔርን መልእክት ለሕዝቡ ለማስተላለፍ ነው። ስለሆነም፥ እርሱ እየተናገረ ሳለ እግዚአብሔር ተጨማሪ ማብራሪያ ለመስጠት በሌላ ሰው አማካኝነት የትንቢትን ቃል ከላከ፥ የመጀመሪያው ተናጋሪ ተራ ሊለቅለት ይገባል። በመጨረሻም፥ እንደ ልሳን ሁሉ በአንድ ጉባኤ ሁለት ወይም ሦስት ሰዎች ብቻ ትንቢትን እንዲናገሩ ተፈቅዷል። ከቡሉይ ኪዳን በተለየ መልኩ፥ የአዲስ ኪዳን ትንቢት እግዚአብሔር ራሱ የሚናገረውን ያህል ጠንካራ ሥልጣን ያለው አይመስልም። አንድም የአዲስ ኪዳን ነቢይ፥ «እግዚአብሔር እንዲህ ይላል» እያለ ሲናገር አንመለከትም። ክርስቲያኖችም ትንቢትን በሁለት መንገዶች እንዲመረምሩ ተነግሯቸዋል። በመጀመሪያ፥ ቃላቱ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር መስማማታቸውን ለመመርመር ትንቢትን እንፈትናለን። እግዚአብሔር ሊዋሽ ስለማይችል በአንድ በኩል (በሰው ወይም በመጽሐፍ ቅዱስ) የተናገረውን መልእክት አይቃረንም። ስለሆነም የተነገረው ትንቢት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በግልጽ ከተጻፈው ወይም ከመጽሐፍ ቅዱስ ዐበይት መርሆች ጋር የሚጻረር ከሆነ ትንቢቱን መቀበል አያስፈልግም። ሁለተኛ፥ ትንቢቱ ለሁሉም ሰው የሚጠቅም መሆኑን መመርመር አለብን። ለሕዝቡ ሁሉ የማያገለግልና ቤተ ክርስቲያንን የማያንጽ ከሆነ፥ ትንቢቱን መቀበል አያስፈልግም። ወይም ጉዳዩ ለሚመለከታቸው ብቻ ማካፈል ያሻል። ሐ. ሴቶች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ዝም ሊሉ ይገባል። ይህ ምንባብ በክርስቲያኖች መካከል ብዙ ውይይቶችንና የተለያዩ አመለካከቶችን አስከትሏል። በሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ያልተደገፉ የሚመስሉ ሁለት የተራራቁ አመለካከቶች አሉ። በመጀመሪያ፥ አንዳንድ ክርስቲያኖች ሴት በፍጹም በጉባኤ ላይ መናገር የለባትም ይላሉ። እነዚህ ወገኖች ሴቶች ማስተማር፥ መስበክ፥ ማካፈል፥ መጸለይ፥ ወዘተ… እንደማይችሉ ይናገራሉ። ሁለተኛ፥ ሌሎች ክርስቲያኖች እነዚህ የጳውሎስ ትእዛዛት ከእኛ ጋር እንደማይዛመዱ ያስረዳሉ። እነዚህ ትእዛዛት የተሰጡት ወንዶች ሴቶችን በሚንቁበት ዘመንና የሴት የቤተ ክርስቲያን ውስጥ መናገር የተሳሳተ ወይም የዓመፅ ምልክት ተደርጎ በሚወሰድበት ባሕል ውስጥ ለነበሩት ሰዎች እንደሆነ ያስረዳሉ። ጊዜው ስለተቀየረና ዘመናዊ ባሕሎች የሴቶችን እኩልነት ስለተገነዘቡ፥ ሴቶች የወንዶችን ያህል እኩል ድርሻና ሥልጣን ይይዛሉ። ተገቢው መጽሐፍ ቅዱሳዊ አመለካከት የሚውለው በእነዚህ ሁለት የተራራቁ አመለካከቶች መሀል ይመስላል። የትኛውንም አመለካከት ብንከተል፥ ጳውሎስ ቀደም ሲል በ1ኛ ቆሮንቶስ 11፡2-16 የተናገረውን ማስታወስ ይኖርብናል። በዚህ ክፍል ጳውሎስ ሴቶች የመጸለይና ትንቢት የመናገር ፈቃድ እንዳላቸው በማሰብ፥ ይህንኑ አገልግሎት በሚሰጡበት ጊዜ ከባሕላቸው ጋር ላለመቃረን ራሳቸውን መሸፈን እንዳለባቸው ገልጾአል። በኢዩኤል 2፡28-32 የተሰጠውና በሐዋርያት ሥራ 2፡17-21 የተጠቀሰው የመንፈስ ቅዱስ የተስፋ ቃል ወንዶችን ብቻ ሳይሆን ሴቶችንም ይጨምራል። ስለሆነም፥ የአዲስ ኪዳን ሴቶች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሊናገሩና ሊያገለግሉ እንደሚችሉ በግልጽ ያሳያል። ክርስቲያኖች ከሚይዟቸው የተለያዩ አተረጓጎሞች አንዳንዶቹ ከዚህ በታች ተዘርዝረዋል። እንደ እግዚአብሔር ቃል ተማሪ፥ አንተና ቤተ ክርስቲያንህ ይህን ክፍል በምታዛምዱበት ሁኔታ ላይ መንፈስ ቅዱስ እንዲመራችሁ በጸሎት ጠይቁ። አንዳንድ ምሁራን ጳውሎስ እግዚአብሔር የአስተዳደርና የሥልጣን ደረጃ ዎችን ስለወሰነ ሴቶች በቤትም ሆነ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለባሎቻቸው እንዲገዙ ለማስረዳት መፈለጉን ይገልጻሉ። ስለሆነም፥ ሴቶች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከመናገር ይልቅ ያልተገነዘቧቸውን ነገሮች ወደቤታቸው ከተመለሱ በኋላ ከባሎቻቸው በመጠየቅ አክብሮታቸውን ማሳየት ያስፈልጋቸው ነበር። ሌሎች ምሁራን ጳውሎስ የተጋፈጠው ችግር ስለ መጽሐፍ ቅዱስ በቂ እውቀት ያልነበራቸውና በክርስትና እምነት ከወንዶች ጋር እኩል በመሆናቸው ምክንያት ባገኙት አዲስ ነጻነት የተደሰቱት ሴቶች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የፈጠሩት ሁከት እንደነበረ ይናገራሉ። እነዚህ ሴቶች ስለ ትንቢት አተረጓጎም፥ ወዘተ. እየተንጫጩ ይከራከሩ ነበር። ስለሆነም፥ ጳውሎስ እነዚህ ሴቶች ቤት ውስጥ ከባሎቻቸው ጋር እንዲወያዩና ቤተ ክርስቲያን ውስጥ መከራከራቸውን እንዲያቆሙ አዟል ይላሉ። ነገር ግን ጳውሎስ በክርክሩ ውስጥ ስለሚሳተፉት ወንዶች ምንም ሳይናገር ለምን ሴቶችን ብቻ እንደኮነነ መረዳቱ አስቸጋሪ ነው። ሴቶች መቼ መናገር እንዳለባቸው የሚያመለክት ተጨማሪ መመሪያ ሳይሰጥ በደፈናው ዝም እንዲሉ ያዘዛቸው ለምንድን ነው? ሌሎች ደግሞ የጳውሎስ ትልቁ ግዳጅ አማኞች ለሌሎችና ለእግዚአብሔር አክብሮት በሚያሳይ መልኩ የጸጋ ስጦታዎቻቸውን በመጠቀም ቤተ ክርስቲያንን ማነጻቸው ነው ይላሉ። ለሌሎች ሰዎች አክብሮትን ማሳየት ከሚቻልባቸው መንገዶች አንዱ ለሴቶች ተገቢ የሆነውን ባሕላዊ ግንዛቤ መጠበቅ ነበር። የጥንቱ ባሕል ሴቶች በሕዝብ ፊት እንዳይናገሩ ስለሚከለክል፥ ሴቶች ባሕሉን በማክበር በቤተ ክርስቲያንም ይህንኑ ተግባር ከመፈጸም መታቀብ ነበረባቸው። ጳውሎስ ሴቶች በሕዝብ ፊት ሊጸልዩና ትንቢትን ሊናገሩ የሚችሉባቸው ጊዜያት እንዳሉ ቢናገርም። ጉዳዩ ባሕላዊ ጫና እንዳለው ግልጽ ነው። በአጠቃላይ መልኩ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ተገቢው ነገር የሴቶች በጉባኤ ዝም ማለት ነበር። በዘመናችን ባሕሉ ተለውጦ የሴቶች በጉባኤ ላይ መናገር ግራ መጋባትንና ነውረኝነትን የማያስከትል ከሆነ፥ ሴቶች እንዲናገሩ ሊፈቅድላቸው ይገባል። በመጨረሻም፥ ስለ ትንቢትና ልሳን በሚናገሩ አሳቦች ላይ በማተኮር አስተያየታቸውን የሚሰጡ ወገኖች አሉ። ጳውሎስ ቤተ ክርስቲያን ትንቢቶችን በጥንቃቄ ስለምትመዝንበት ሁኔታ እያስተማረ ነበር። ሴቶችም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ትንቢት ሊናገሩ እንደሚችሉ ተፈቅዶላቸው ነበር። ነገር ግን ቤተ ክርስቲያን ትንቢቶችን መዝና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ወይም ከእግዚአብሔር መሆን አለመሆናቸውን በምትወስንበት ሂደት ውስጥ ሴቶች ዝም ማለት ነበረባቸው፡፡ ወንዶች ስለ ትንቢት እንዲወያዩ በመፍቀድ በመጽሐፍ ቅዱስ መርሆ መሠረት ለወንዶች የተሰጠውን ሥልጣን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያንጸባርቁ ነበር። ሴቶች የተወሰነ አመለካከት ስለተወሰደበት ምክንያት ጥያቄ ቢኖራቸው በቤታቸው ውስጥ ባሎቻቸውን መጠየቅ ይኖርባቸዋል። ጳውሎስ ሴቶች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እውቅና በተሰጠው የማስተማር

ለጉባኤ አምልኮ የተሰጡ መሠረታዊ መመሪያዎች (1ኛ ቆሮ. 14፡26-40)። Read More »

የመንፈሳዊ ስጦታዎች በተለይም በልሳን የመናገር ዓላማ ምንድን ነው? (1ኛ ቆሮ. 12፡1-14፡25)

አንዳንድ አማኞች፣ «ደካማ የምንሆንበት ምክንያት በቂ መንፈሳዊ ስጦታዎች ስለሌሉን ነው። ሁሉም ክርስቲያኖች ሊያገኙት የሚገባው እጅግ ጠቃሚ ስጦታ በልሳን መናገር ነው። መንፈስ ቅዱስ በክርስቲያኑ ውስጥ እንዳለ የሚታወቀው በልሳን ሲናገር ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ሰዎች በልሳን ስለሚናገሩና ብዙ ተአምራት ስለሚፈጸሙ መነቃቃትን እንዳገኘን እናውቃለን።» ይላሉ። ለመሆኑ እንዲህ ዓይነት አባባሎች እውነት ናቸው? መንፈሳዊ ስጦታዎች ጠቃሚዎች ናቸው። ጳውሎስ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ስለ መንፈሳዊ ስጦታዎች እንዲያውቁ የፈለገውም ለዚህ ነው (1ኛ ቆሮ. 12፡1)። ነገር ግን መንፈሳዊ ስጦታዎች አንድ ግለሰብ ወይም ቤተ ክርስቲያን በሳል መሆናቸውን አያሳዩም። ጳውሎስ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ምንም የጸጋ ስጦታ እንዳልጎዳላቸው ቢናገርም፥ መንፈሳዊ ብስለት እንዳልነበራቸው ገልጾአል (1ኛ ቆሮ. 3፡1-4)። ክፍፍል፥ ቅንዓትና ሌሎችም ኃጢአቶች ቤተ ክርስቲያኒቱን አጨናንቀው ነበር። እንዲያውም ጳውሎስ ስለ መንፈሳዊ ስጦታዎች ይህን ረዥም ትምህርት ያቀረበው የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በመንፈሳዊ ስጦታዎች ላይ በነበሯቸው የተሳሳቱ ግዛቤዎች ሳቢያ ይከፋፈሉ ስለነበረ ነው። የተቀረውን የአዲስ ኪዳን ክፍል በጥንቃቄ ብንመረምር፥ መንፈሳዊ ስጦታዎች በሌሎች ጥቂት ስፍራዎች ብቻ እንደተዘረዘሩ እንረዳለን (ሮሜ 12፡4-7፤ ኤፌ. 4፡11-13፤ 1ኛ ጴጥ. 4፡10-11)። ይህም መንፈሳዊ ስጦታዎች የአዲስ ኪዳን ቀዳሚ ትኩረቶች እንዳልሆኑ ያስረዳናል። በአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ሁሉ ውስጥ በአጽንኦት የተገለጸው የመንፈስ ፍሬ ነው (ገላ. 5፡22-23)። ይህም ፍቅር፥ ደስታ፥ ሰላም፥ እንድነት፥ ተስፋ፥ ትዕግሥት፥ የመሳሰሉት የሚገኙበት ነው። ይህም እውነተኛ መንፈሳዊነት በቀዳሚነት ራሱን የሚገልጸው በመንፈሳዊ ስጦታዎች ሳይሆን በመንፈሳዊ ባሕርያት እንደሆነ ያሳያል። የውይይት ጥያቄ፡- አንዳንድ ሰዎች በኢትዮጵያ ውስጥ መንፈሳዊ መነቃቃት እንዳለ ይናገራሉ። አስደሳች አምልኮ፥ የልሳን ስጦታና አስደናቂ ተአምራት ከወትሮው በበለጠ እንደሚታዩ ያስረዳሉ። ሀ) ይህ ሰዎች ከበፊት ይልቅ መንፈሳዊ ብስለትን እንደተላበሱ የሚያሳይ ይመስልሃል? መልስህን አብራራ። ለ) የመንፈስ ፍሬ (ገላ. 5፡22-23ን አንብብ።) ከበፊት የበለጠ የሚታይ ይመስልሃል ? መልስህን አብራራ። የውይይት ጥያቄ፡- 1ኛ ቆሮ 12ን አንብብ። ሀ) ጳውሎስ በዚህ ክፍል ያተኮረባቸውን የመንፈሳዊ ስጦታዎች መርሆዎች ዘርዝሩ። ለ) ከእነዚህ መርሆዎች ዛሬ አንዳንድ ሰዎች ስለ መንፈሳዊ ስጦታዎች ከሚያስቡት እሳብ ጋር የሚጋጩት የትኞቹ ናቸው? ችግሩ፡- የቆሮንቶስ አማኞች በአንዳንድ የጸጋ ስጦታዎች፥ በተለይም በልሳን አጠቃቀም ላይ በአሳብ የተከፋፈሉ ይመስላል። አንዳንድ ክርስቲያኖች በልሳን መናገር እጅግ በጣም ጠቃሚ ስጦታ ነው ብለው አሰቡ። እንዳንድ ክርስቲያኖች፥ «እውነተኛ ሰዎች ሁሉ በልሳን ይናገራሉ። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ብዙ ሰዎች በልሳን መናገራቸው የሌሎችን አምልኮ ቢረብሽም እንኳ የተሻለ ነው» ይሉ ነበር። እነዚህ ሰዎች ጳውሎስ ክርስቲያኖች ሁሉ በልሳን እንዲናገሩ ያበረታታላቸው ዘንድ ፈለጉ። ሌሎች ክርስቲያኖች ደግሞ ብዙ ሕዝብ በሚያመልክበት ስፍራ በልሳን መናገሩ አስፈላጊ እንዳልሆነ በመግለጽ እጥብቀው ተቃወሙ። በልሳን የሚናገሩ ሰዎች ጉባኤውን ከሚያውኩ በቀር ምንም ጥቅም እንደሌለው አስረዱ። ስለሆነም፥ ጳውሎስ በልሳን የሚናገሩትን ሰዎች እንዲከለክል ፈለጉ። «የመንፈሳዊ ስጦታዎች ዓላማ ምንድን ነው? ብዙ ሕዝብ በተሰበሰበበት አምልኮ ውስጥ (በተለይ ልሳንን) እንዴት ልንጠቀም ይገባል?» ሲሉ ጠየቁት። ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በሰጠው ምላሽ ስለ መንፈሳዊ ስጦታዎች ብቻ ሳይሆን፥ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሊኖር ስለሚገባው ፍቅር፥ አንድነትና መተሳሰብ ጠቃሚ ትምህርት ሰጥቷል። መፍትሔው፡- ምንም እንኳ ጳውሎስ ብዙ ሕዝብ በሚገኝበት አምልኮ ውስጥ ልሳንን እንዴት መጠቀም እንደሚቻል ዝርዝር መመሪያዎችን ባይሰጥም (1ኛ ቆሮ. 14)፥ መንፈሳዊ ስጦታዎችን መጠቀም ስለሚያስፈልግባቸው ምክንያቶችና ስጦታዎቹን በምንጠቀምበት ጊዜ ሊኖረን ስለሚገቡ አመለካከቶች አጽንኦት ሰጥቶ አብራርቷል። ቀጣዩ ጳውሎስ የሰጠው ትምህርት ጭማቂ ነው። ሀ. በልሳን መናገር የአንድን ሰው መንፈሳዊነት አያረጋግጥም (1ኛ ቆሮ. 12፡1-3)። በዚህ ክፍል የጳውሎስን ምክንያት መረዳቱ አስቸጋሪ ነው። ነገር ግን ጳውሎስ በልሳን ከሚናገሩ ሰዎች አንዳንዶቹ አረማውያን በነበሩ ጊዜ (በተለይ ጠንቋዮቹ) በልሳን ይናገሩ እንደነበረ እያስታወሳቸው ይሆናል። ስለሆነም በልሳን መናገር በራሱ የመንፈሳዊነት ምልክት ሊሆን አይችልም። ክርስቲያን የሆኑትም ያልሆኑትም በልሳን ሊናገሩ ይችላሉ። እንግዲህ፥ የአንድ ሰው ልሳን ከእግዚአብሔር ወይም ከሰይጣን መሆኑን እንዴት እናውቃለን? ጳውሎስ የክርስቶስን ጌትነት በልቡ የሚያምንና በሕይወቱ የሚያረጋግጥ ማንኛውም ክርስቲያን በሰይጣን ቁጥጥር ሊናገር እንደማይችል ገልጾአል። ይህን መፈተኛ ለመረዳት፥ የጳውሎስን ዘመን ባሕል መረዳት አለብን። ዛሬ ሰዎች ስለ ትርጉሙ ብዙም ሳያውቁ መስቀልን የውበት ትምህርት አድርገው ይጠቀማሉ። ከእግዚአብሔር ጋር ግንኙነት የሌላቸው ሰዎች ሳይቀሩ ኢየሱስ ጌታ ነው ሊሉ ይችላሉ። በጳውሎስ ዘመን ግን አንድ አይሁዳዊ የሆነ ሰው ኢየሱስ የብሉይ ኪዳን አምላክ የሆነው ያህዌ ነው ቢል፥ አይሁዶች ለፈጸመው የስድብ ኃጢአት በድንጋይ ወግረው ይገድሉት ነበር። አንድ አሕዛብ ኢየሱስ ጌታ ነው ቢል፥ ማኅበረሰቡ የተሰቀለው ኢየሱስ ጌታ ነው በማለቱ ከማኅበራቸው ያስወጡት ነበር። ዛሬ ለሙስሊሞች በክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅነት ማመን የሚከብደውን ያህል ያን ጊዜ ለሰዎች በክርስቶስ ማመኑ አስቸጋሪ ነበር። ስለሆነም፥ በክርስቶስ ላይ ላላቸው እምነት ለመሞት የሚመርጡ ሰዎች እግዚአብሔር በልባቸው ውስጥ ለውጥ ያመጣባቸው ብቻ መሆናቸውን ገልጾአል። እንደነዚህ ዓይነት አማኞች በልሳን በሚናገሩበት ጊዜ የስጦታው ምንጭ መንፈስ ቅዱስ ለመሆኑ እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። ጳውሎስ አጽንኦት የሰጠው በሚናገራቸው ቃላት ላይ ሳይሆን፥ ግለሰቡ በሕይወቱ ክፍሎች ሁሉ በክርስቶስ አገዛዝ ሥር ስለመኖሩ ነው። ግለሰቡ ለክርስቶስ የማይገዛና ፍቅርን የማያሳይ ከሆነ፥ በልሳን የመናገርን ኃይል የሰጠው ሰይጣን ሊሆን እንደሚችል የመጠራጠር መብት አለን። የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) አኗኗራቸው ክርስቶስ የሕይወታቸው ጌታ መሆኑን የሚመሰክርላቸው ክርስቲያኖች በልሳን ሲናገሩ ሰምተሃል? ለክርስቶስ እንደሚገዙ በምን ታውቃለህ? የዚህ ዓይነቱ ልሳን ምንጭ ማን ነው? ለ) ለክርስቶስ ተገዝተውና ታዘው እንደሚኖሩ ሕይወታቸው የማይመሰክርላቸው ክርስቲያኖች በልሳን ሲናገሩ ሰምተሃል? ለክርስቶስ አለመገዛታቸውን እንዴት ታረጋግጣለህ? የልሳናቸው ምንጭ ማን ነው? ለ. ከአንዱ አሀዱ–ሥሉስ አምላክ የሚመጡ የተለያዩ ስጦታዎች (አገልግሎቶችና አሠራሮችም ተብለዋል) አሉ (1ኛ ቆሮ. 12፡4-6)። ጳውሎስ እንዴት በሁለት ቃላቶች ላይ እንደሚያተኩር አጢን። ጳውሎስ «ልዩ ልዩ» በሚለው ሐረግ ላይ በማተኮር የተለያዩ ስጦታዎች መኖራቸውን ያሳያል። ይህም እንደ ልሳን ካለው አንድ ስጦታ ይልቅ እግዚአብሔር በሚሰጣቸው ስጦታዎች ሁሉ ላይ አጽንኦት መስጠት እንዳለብን ያመለክታል። እንዲሁም፥ እነዚህ የተለያዩ ስጦታዎች ከእግዚአብሔር (ከአንድ ምንጭ) እንደሚመጡ ለማሳየት «አንድ» በሚል ቃል ላይ ትኩረት አድርጓል። ስለሆነም፤ በልሳን የመናገር ስጦታ ያለው ሰው ሌላ ዓይነት ስጦታ ካለው ሰው ይልቅ መንፈስ ቅዱስ በበለጠ ሁኔታ ይኖርበታል ማለት አይደለም። ሐ. እያንዳንዱ ክርስቲያን የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ለጋራ ጥቅም ይሰጠዋል። ይህም በክርስቲያኑ ሕይወት ውስጥ መንፈስ ቅዱስ እንዳለ ያሳያል (1ኛ ቆሮ. 12፡7)። የእያንዳንዱ መንፈሳዊ ስጦታ ዓላማ የጋራ ጥቅም ነው። ስጦታው የሚሰጠው ለግለሰቡ የግል ጥቅም ሳይሆን፥ ለቤተ ክርስቲያን ነው። መንፈሳዊ ስጦታ መንፈስ ቅዱስ እያንዳንዱ ክርስቲያን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንዲያገለግል የሚሰጠው ችሎታ ነው። መ. መንፈስ ቅዱስ ለተለያዩ ሰዎች የተለያዩ ስጦታዎችን ይሰጣል (1ኛ ቆሮ. 12፡8-10)። አንዳንድ ክርስቲያኖች የተወሰኑ መንፈሳዊ ስጦታዎች ብቻ እንዳሉ ቢያስቡም፥ በአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ውስጥ የተገለጹት የመንፈሳዊ ስጦታዎች ዝርዝሮች አንድ ዓይነት አይደሉም። ይህም መንፈስ ቅዱስ ሊሰጥ የሚችላቸው የተለያዩ ስጦታዎች እንዳሉ ያሳያል። መንፈስ ቅዱስ በልሳን መናገርን ለሁሉም አማኞች አይሰጥም። ይህ አንድ ስጦታ ብቻ ሲሆን፥ መንፈስ ቅዱስ ለተለያዩ ሰዎች የሚሰጣቸው የተለያዩ ስጦታዎች አሉ። ሠ. ማን የትኛውን ስጦታ እንደሚቀበል የሚወስነው መንፈስ ቅዱስ ነው (1ኛ ቆሮ. 12፡1)። መንፈሳዊ ስጦታን የሚሰጠን መንፈስ ቅዱስ ስለሆነ፥ ሌሎች ከእኛ ይበልጥ አስደናቂ ስጦታ የተቀበሉ በሚመስልበት ጊዜ የመቅናት መብት የለንም። እንደ እኛ አስደናቂ የሆኑ ስጦታዎች የሌላቸውንም ቁልቁል ልንመለከትና ልንንቃቸው አይገባም። ስጦታውን የሚወስነው ተቀባዩ ሳይሆን፥ እንደ ዓላማውና እንደ ምርጫው የሚሰጠው መንፈስ ቅዱስ ነው። ረ. ሰውነት አብረው ከሚሠሩ የተለያዩ የሰውነት ክፍሎች እንደተዋቀረ ሁሉ፥ ቤተ ክርስቲያንም ለክርስቶስ አካል ጥቅም በሚሠሩ የተለያዩ ስጦታዎች ባሏቸው ሰዎች ተዋቅራለች (1ኛ ቆሮ. 12፡12-26)። ይህ አሳብ ብዙ ጠቃሚ ትምህርቶችን ያስተምራል። በመጀመሪያ፥ እያንዳንዱ ክርስቲያን ስጦታውን በሚገባ ካልተጠቀመ ቤተ ክርስቲያን ትዳከማለች። ሁለተኛ፥ እያንዳንዱ መንፈሳዊ ስጦታ ዋጋ ሊሰጠው እንደሚገባና አንዱ መንፈሳዊ ስጦታ ከሌላው እንደሚበልጥ ሁሉ ከፍ ከፍ መደረግ እንደሌለበት ያሳያል። ሦስተኛ፥ እጅግ አስደናቂ ያልሆኑ ወይም ጎልተው የማይታዩ ስጦታዎች መከበር እንዳለባቸው ያሳያል። ሰ. የበለጠ ጠቀሜታ ያላቸው አንዳንድ መንፈሳዊ ስጦታዎች አሉ።

የመንፈሳዊ ስጦታዎች በተለይም በልሳን የመናገር ዓላማ ምንድን ነው? (1ኛ ቆሮ. 12፡1-14፡25) Read More »

በጌታ እራት ጊዜ ትክክለኛው ባሕርይ ምንድን ነው? (1ኛ ቆሮ. 11፡17-34)።

«አሁን የጌታን እራት እንወስዳለን» ሲባል ጉባኤው በዝምታ ይዋጣል። ንግግርና ጭውውት አብቅቶ ጉባኤው ያረምማል። ይህ እጅግ የተቀደሰ የአምልኮ ጊዜ ነው። ብዙ አብያተ ክርስቲያናት የተጠመቁ አባሎቻቸው ብቻ የጌታን እራት እንዲወስዱ ያደርጋሉ። ንስሐ ስላልገቡባቸው ኃጢአቶች ጠንካራ ማስጠንቀቂያ ይሰጣቸዋል። ዛሬ ስለ የጌታ እራት በጥብቅ የሚያሳስበን ነገር አለ። ይኽውም የጌታን እራት አለአግባብ ልንጠቀም የምንችለው እንዴት ነው? የሚል ነው። የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) የጌታ እራት ለአንተ ልዩ የሚሆነው ለምንድን ነው? ለ) 1ኛ ቆሮ. 11፡17-34 አንብብ። በጌታ እራት ጊዜ የተከሰተውንና ጳውሎስ የተቃወመውን ችግር ግለጽ። ሐ) ስለ የጌታ እራት ሊያስተካክል የፈለገው የተሳሳተ አመለካከት ምን ነበር? መ) ጳውሎስ ስለ ጌታ እራት የሰጠውና ዛሬ ከእኛ ጋር የሚዛመደውን መመሪያ ዘርዝር። ችግሩ፡- የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች የተቸገሩበት ሁለተኛው የአምልኮ ክፍል በጌታ እራት ጊዜ ትክክለኛው ባሕርይ ምን ዓይነት ነው? የሚል ነበር፡፡ ችግሩን ለመረዳት እንችል ዘንድ የቀድሞዪቱ ቤተ ክርስቲያን የጌታን እራት ስለምትወስድበት ሁኔታ ማወቅ አለብን። የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን የጌታን እራት የምትወስድበት ሁኔታ በተለያዩ መንገዶች ከዛሬው ዘመን የተለየ ነበር። በመጀመሪያ፥ ክርስቲያኖች ሁሉ በጌታ እራት ተካፋይ ነበሩ። የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ሰዎችን ወዲያውኑ እንዳመኑ ታጠምቃቸው ስለነበር፥ አንድ ሰው በሚያምንበትና የጌታን እራት በሚወስድበት መካከል ብዙ የጊዜ ርቀት አልነበረም። በአባሎችና እንዲሁ ለመካፈል በመጡት ሰዎች መካከልም ልዩነት አልነበረም። ሁለተኛ፥ ዛሬ በአብዛኞቹ አብያተ ክርስቲያናት በወር አንድ ጊዜ እንደሚሰጠው ሳይሆን፥ በጥንቷ ቤተ ክርስቲያን የጌታ እራት በየአምልኮ ፕሮግራሙ ላይ ይደረግ ነበር። ሦስተኛ፥ የጌታ እራት ሰዎች የዳቦ ቁራሽና አነስተኛ መጠጥ የሚጠጡበት ሥርዓት ብቻ አልነበረም። ነገር ግን ምእመናኑ በአምልኮው ሰዓት መጨረሻ ላይ አብረው የሚበሉት ምግብ ነበር። የጌታ እራት ዳቦና መጠጥ የሚቀርበው ከምግቡ በኋላ ነበር። በቆሮንቶስ እያንዳንዱ ቤተሰብ ምግቡን አምጥቶ በጋራ ይመገብ የነበረ ይመስላል። ምእመናኑ ያመጡትን ምግብ አብረው ከበሉ በኋላ የጌታን እራት ሥርዓት ያካሄዳሉ። ነገር ግን ሰይጣን ይህን መልካም ልማድ ወደ ራስ ወዳድነት ተግባር ለወጠው። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሀብታምና ድሀ ክርስቲያኖች ነበሩ። ሀብታም ክርስቲያኖች ብዙ ጥሩ ጥሩ ምግቦች (እንደ እንጀራና ወጥ ያለ) ይዘው ሲመጡ፥ ድሆቹ ግን ምንም ወይም ደከም ያለ (እንደ ንፍሮ ዓይነት) ምግብ ያመጡ ነበር። ሀብታም ክርስቲያኖች ጥሩ ምግባቸውን በልተውና ወይናቸውን ጠጥተው ሲሰክሩ፥ ድሆቹ ጥሩ ምግብ ለመብላት አልቻሉም ነበር። ድሆቹ ሀብታሞቹ የሚበሉትን እየጓጉ ከመመልከት ያለፈ ሚና አልነበራቸውም። ወደ ቤተ ክርስቲያን ብዙ ምግብ ይዘው ሊመጡ ስለማይችሉ ዝቅተኛነት ይሰማቸው ነበር። ስለሆነም፥ የጌታ እራት የፍቅርና የአንድነት መዘከሪያ ከመሆን ይልቅ የመከፋፈልና የራስ ወዳድነት መገለጫ ሆኖ ተገኘ። ጳውሎስ ክፍፍልና ራስ ወዳድነት እያሉ የጌታን እራት በአግባቡ ማካሄድ እንደማይቻል አመልክቷል። ጳውሎስ በዚህ ክፍል የተቃወመውም ይህንኑ ክፍፍልና ራስ ወዳድነትን ነው። መርሁ፡- እግዚአብሔር የሚቀበለው አምልኮና የጌታ እራት በአንድነት፥ በፍቅርና ለሌሎች በማሰብ ሊካሄድ ይገባል። ራስ ወዳድነትና ከፍፍል ካሉ የአምልኮ፥ የዝማሬ፥ የአሥራት፥ የስብከትና የጌታ እራት ሥርዓት ማካሄዱ ለእኛም ሆነ ለሌሎች የሚያበረክተው ፋይዳ አይኖርም። ትእዛዛት፡ ጳውሎስ መፍትሔ መስጠት የጀመረው ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ስለ የጌታ እራት ዓለማ በማስታወስ ነው። ትኩረት ሊሰጥ የሚገባው በሚበሉት ምግብ ላይ ሳይሆን፥ ስለ እነርሱ የሞተውን ክርስቶስን በማስታወሱ ላይ ነበር። ስለሆነም ከራባቸው በቤታቸው እንዲበሉና ሰይጣን የኢኮኖሚ ልዩነታቸውን ለማጉላት የሚጠቀምበትን ብዙ ምግብ ይዞ የመምጣት ተግባራቸውን እንዲያቆሙ መክሯቸዋል። የጌታ እራት ዓላማ ሰዎች ክርስቶስ ስለ እኛ በመስቀል ላይ መሞቱን እንዲያስታውሱ ማገዝ ነው፡፡ ክርስቶስ ብዙውን ጊዜ በተለያዩ ነገሮች ስለምንጣደፍ ይህ የእምነታችን መሠረታዊ እውነት እንደሚዘነጋ ያውቅ ነበር። በመጀመሪያ፥ የጌታ እራት ከኃጢአት መዳናችንን፥ መንፈስ ቅዱስ መቀበላችንን፥ የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን የዘላለም ሕይወት ማግኘታችንን ጨምሮ፥ ደስ የምንሰኝባቸውን በረከቶች ሁሉ እንድናስታውስ ይረዳናል። እነዚህ በረከቶች ሁሉ የተገኙት ክርስቶስ ለኃጢአታችን በመሞቱ ምክንያት ነው። ሁለተኛ፥ የጌታ እራት ክርስቲያኑ ማኅበረሰብ እምነቱና ተስፋው በክርስቶስ የመስቀል ላይ ሞት እንዳረፈ የሚመሰክርበት ነው። በአማኞች ማኅበረሰብ የጌታ እራት በከፍተኛ ጥንቃቄ ሊወስድ ይገባል። በግለሰብም ሆነ በአማኞች አካል ደረጃ ልባችንን በመመርመር ኃጢአታችንን ልንናዘዝ ይገባል። በመካከላችን ክፍፍልና ራስ ወዳድነት፥ እንዲሁም ሌሎች ያልተናዘዝናቸው ኃጢአቶች እያሉ የጌታን እራት መውሰድ በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ላይ ማላገጥ ይሆናል። ክርስቶስ የሞተው ለኃጢአታችን ስለሆነ ንስሐ ሳንገባ የጌታ እራት የምንወስድ ከሆነ፥ ክርስቶስ ለኃጢአታችን እጅግ ተሠቃይቶ በደሙ እኛን ስለ መግዛቱ ግድ የለንም ማለት ነው። አሁንም በዓመፀኛነታችን እንቀጥላለን ማለት ነው። ጳውሎስ አንዳንድ ክርስቲያኖች ለጌታ እራት እንዲህ ዓይነት የግድየለሽነት አመለካከት በማሳየታቸው በሞት እንደተቀጡ ገልጾአል። አንዳንዶች በሕመም ሌሎች ደግሞ በሞት ተቀጥተዋል (አንቀላፍተዋል)። አሁንም ሆነ የኋላ ኋላ የእግዚአብሔርን ፍርድ ከመቀበል ይልቅ ሕይወታችንን መመርመር፥ ኃጢአታችንን መናዘዝና በኅብረት መብላቱ ጠቃሚ ይሆናል። የጌታ እራት ልዩነቶችንና የራስ ወዳድነትን ሁኔታ ከማሳየት ይልቅ ፍቅርንና አንድነትን ሊያንጸባርቅ ይገባል። አማኞች እርስ በርሳቸው ተጠባብቀው አንድ ላይ እንዲመገቡ ተነግሯቸዋል። የጌታ እራቱ በክርስቶስ ሞት እንጂ በምግባቸው ላይ ሊያተኩር አይገባም ነበር። የተራበ ሰው ቢኖር ወደ ቤተ ክርስቲያን ከመምጣቱ በፊት መብላት አለበት። የውይይት ጥያቄ፡– ሀ) ብዙ ጊዜ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የመከፋፈል ወይም ሌሎች ኃጢአቶች ቢኖሩም ክርስቲያኖች የጌታን እራት መውሰዳቸውን ይቀጥላሉ። ጳውሎስ ስለዚህ ጉዳይ ምን የሚል ይመስልሃል? ለ) የጌታን እራት ፍች በትክክል ብንረዳ፥ ይህ ቤተ ክርስቲያንን ሊያነጻ የሚችለው እንዴት ነው? (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

በጌታ እራት ጊዜ ትክክለኛው ባሕርይ ምንድን ነው? (1ኛ ቆሮ. 11፡17-34)። Read More »

ሕዝብ በሚሰበሰብበት ይፋዊ አምልኮ ላይ የሴቶችና ወንዶች ትክክለኛ አለባበስ ምን ዓይነት መሆን አለበት? (1ኛ ቆሮ. 11፡2-16)።

1ኛ ቆሮንቶስ 11-14 ብዙ ሕዝብ ስለሚካፈልበት ይፋዊ አምልኮ ይናገራል። በመጀመሪያ፥ ጳውሎስ በአምልኮ ጊዜ ተገቢውን የአለባበስና የባሕርይ ሥርዓት መከተል እንደሚያስፈልግ ያስረዳል (1ኛ ቆሮ. 11፡2-16)። ሁለተኛ፥ በጌታ እራት ላይ የሚከሰቱትን ችግሮች ለማረም ይፈልጋል (1ኛ ቆሮ. 11፡17-34)። ሦስተኛ ጳውሎስ ስለ መንፈሳዊ ስጦታዎች፥ በተለይም በልሳን ስለመናገር ክርስቲያኖች የነበሯቸውን የተሳሳቱ ግንዛቤዎች ለማረም ይፈልጋል (1ኛ ቆሮ. 12፡14)። የውይይት ጥያቄ፡- 1ኛ ቆሮ. 11፡2-16 አንብብ፡፡ ሀ) እግዚአብሔር የመሠረተውን የሥልጣን ቅደም ተከተል ዘርዝር። ለ) ስለ ወንዶችና የአለባበስ ሥርዓት የተሰጠውን ድንጋጌ ግለጽ። ሐ) ስለ ሴቶችና የአለባበስ ሥርዓት የተሰጠውን ድንጋጌ ግለጽ። 1ኛ ቆሮንቶስ 11፡2-16 ዛሬ እንዴት ተግባራዊ ሊሆን ይገባል? የሚለው ጥያቄ በምሁራን መካከል ከፍተኛ ክርክሮችን አስከትሏል። ጳውሎስ ሴቶች ራሳቸውን እንዲሸፍኑና ወንዶች ጸጉራቸውን እንዲያሳጥሩ የሰጠው ሕግ ዛሬም ይሠራል? ወይስ ይህ በጳውሎስ ዘመን የነበረ ባሕላዊ ጉዳይ በመሆኑ ዛሬ ዝርዝር ደንቦቹን ሳይሆን መርሆዎቹን ብቻ ተግባራዊ የምናደርግበት ነው? ጳውሎስ ሴቶች ፀጉራቸውን እንዲሸፋፈኑ በማዘዝ የሰጠው ድንጋጌ እርሱ የነበረበትን ዘመን እንጂ የእኛን ዘመን የማይመለከት ከሆነ፥ ወንድ ከሴት የመብለጡም ጉዳይ ባሕላዊ መሠረት ያለውና ተመሳሳይ ግንዛቤ የሚያሻው ነው? ይህንን ምዕራፍ አስቸጋሪ የሚያደርገው ስለ ጥንት ሰዎች ባሕልና ጳውሎስ ይህን ጉዳይ ለማንሣት የተገደደበትን ምክንያት አለማወቃችን ነው። ጳውሎስ በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንደነበሩ የሰማቸውን ችግሮችና ቤተ ክርስቲያኒቱ ያነሣቻቸውን ጥያቄዎች ለመመለስ ጥረት በማድረግ ላይ ነበር። ስለሆነም፥ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በአምልኮ ወቅት ሊለበሱ ስለሚገባቸው ተገቢ ልብሶች የጠየቁት ይመስላል። እንደ ሌሎች ምንባቦች ሁሉ፥ የዛሬውን ዘመን አለባበስ ሳይሆን የጥንቱን ዘመን ባሕላዊ ልምምዶች ለመረዳት መሞከር ይኖርብናል። በጥንት ጊዜ ሰዎች ቦላሌ ሱሪዎችን፥ ሸሚዞችን፥ ጫማዎችን፥ ቀሚሶችን፥ ወዘተ አይለብሱም ነበር። በጳውሎስ ዘመን ለሴቶች ተለምዷዊ አለባበስ ሁለት ባሕላዊ መመዘኛዎች ነበሩ። (በእስያና መካከለኛው ምሥራቅ) ሴቶች በአደባባይ ወይም ከእንግዶች ጋር በሚሆኑበት ጊዜ ፊታቸውን የመሸፋፈን ልማድ ነበራቸው (ዘፍጥ. 24፡65)። በግሪክ ግን ሴቶች የራስ መሸፋፈኛ አልነበራቸውም። ምሁራን በ1ኛ ቆሮንቶስ ውስጥ የተገለጸው የራስ መሸፈኛ ጭንብልን ወይም ረዥም ፀጉርን ስለማመልከቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ተመራማሪዎች ይከራከራሉ። በተጨማሪም፥ ምሁራን የዚህ ምዕራፍ ዋነኛ ጉዳይ ሴቶች ራሳቸውን ሳይሸፋፈኑ ወደ ቤተ ክርስቲያን መሄዳቸው ይሆን? ወይስ ፀጉራቸውን ሸብ አድርገው ሳያስሩ ከትከሻቸው ላይ ማዘናፈላቸው ይሆን? በሚለውም አሳብ ላይ ይከራከራሉ። ጳውሎስ የሚናገረው ረዥም ፀጉር ስላላቸው ምዕራባውያን ሴቶች እንጂ ስለ አፍሪካውያን ሴቶች አልነበረም። ፀጉራቸውን ሳያስይዙ ማዘናፈል በጥንት ባሕል አንድም የአልቃሽነት ወይም የዘማዊነት ምልክት ነበር። የትኛውንም አመለካከት ብንቀበል፥ ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ ነጻነትና አክብሮት ያገኙት አንዳንድ የቆሮንቶስ ሴቶች ከባሕላቸው ያፈነገጡ ይመስላል። ቤተ ክርስቲያን ከእንግዲህ «ወንድ፥ ሴት፥ ባሪያ ወይም ነፃ ሰው» የለም፥ ሁሉም በክርስቶስ አንድ ሰው ናቸው ብላ ታስተምር ነበር (ገላ. 3፡28 አንብብ።) የራስ መሸፈኛ ማድረግን ወይም ፀጉራቸውን ማስያዝ አቆሙ። ይህ ደግሞ በዘመኑ ባሕል ተቀባይነት አልነበረውም። ስለሆነም ጳውሎስ ሴቶች አዲሱን ነጻነታቸውን ባሕላቸው በማይፈቅደው መንገድ መጠቀም እንደሌለባቸው ያስረዳል። ጳውሎስ ባሕላቸውን አክብረው ሊለብሱና በአደባባይ ከመናገር ሊቆጠቡ እንደሚገባቸው ገለጻ (1ኛ ቆሮ. 14፡34)። ይህን ምንባብ በጥንቃቄ በምናጠናበት ጊዜ የሚከተሉትን ነገሮች እንረዳለን። እግዚአብሔር የሥልጣንን ቅደም ተከተልና አስተዳደር አዋቅሯል። ከሁሉም የሚበልጠው ባለሥልጣን እግዚአብሔር አብ ሲሆን፥ ከእርሱ ቀጥሎ ከርስቶስ ነው። (እዚህ ባይጠቀስም፥ ቀጣዩ መንፈስ ቅዱስ መሆኑን ከሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች እንረዳለን።) ቀጣዩ ወንድ ሲሆን፥ ሴት የመጨረሻውን ስፍራ ትይዛለች። ጳውሎስ ይህን የሥልጣን ቅደም ተከተል «ራስ» ይለዋል። አንዳንድ ምሁራን «ራስ» ከበላይ ያለ አካልን ማክበርን የሚያመለክት ነው ይላሉ። ስለሆነም፥ ሴት ወንድን፥ ወንድ ክርስቶስን፥ ክርስቶስ ደግሞ እግዚአብሔር አብን ማክበር አለበት ይላሉ። ሌሎች ራስ የሚለው ቃል ሥልጣንን እንደሚያመለክት ይናገራሉ። ስለሆነም፥ የእግዚአብሔር የሥርዓት ቅደም ተከተል ከእግዚአብሔር አብ ወደ ክርስቶስ ከዚያ ወደ ወንድና ብሎም ወደ ሴት እንደሚተላለፍ ያስረዳሉ። ይህ የሥልጣን ቅደም ተከተል በአምልኮ ውስጥ በተለያዩ ባሕሎች ሊገለጥ የሚችለው እንዴት ነበር? ይህ ወንዶች ባርኔጣቸውን በማውለቅና ፀጉራቸውን በአጭሩ በመቆረጥ እግዚአብሔርን ማክበር እንደነበረባቸው ያመለክታል። ሴቶች በአምልኮ ሰዓት ራሳቸውን በሻሽ፥ መጎናጸፊያ አልያም በረጅም ፀጉር መሸፈን እንደነበረባቸው ያመለክታል። ስለዚህ ምንባብ የትኛውንም እመለካከት ብንከተል፥ ጳውሎስ ሴቶች ከወንዶች ያንሳሉ ማለቱ እንዳልሆነ መገንዘብ ይኖርብናል። በተቃራኒው ግን ስለ እግዚአብሔር የአስተዳደር ሥርዓት መግለጹ ነበር። ክርስቶስ ከእግዚአብሔር አብ ጋር በባሕርይና በኃይል የሚስተካከል ፍጹም አምላክ ሆኖ እያለ በሥልጣን ተዋረድ ከእግዚአብሔር አብ በታች እንዳለ ሁሉ፥ ሴቶችም በባሕርይና በጠቀሜታቸው ከወንዶች እኩል ናቸው። ነገር ግን ሴቶች በወንዶች አስተዳደር ሥር ይኖራሉ። ጳውሎስ የወንዶችና የሴቶች ግንኙነት በእግዚአብሔር አብና በእግዚአብሔር ወልድ መካከል ባለው ግንኙነት ምሳሌነት የተዘጋጀ መሆኑን አመልክቷል። የቤተ ክርስቲያን አምልኮ የአካባቢውን ባሕል ያንጸባርቃል። ትክክለኛ ያልሆነ አለባበስና ባሕርይ ወንጌሉን በማሰደብ ሰዎች ስለ ክርስትና የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ስለሚያደርግ፥ ክርስቲያኖች ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የማይቃረኑትን ባሕላዊ መመዘኛዎች መከተል ይኖርባቸዋል። ስለሆነም፥ አንድ ወንድ ራሱን ተሸፋፍኖ ትንቢት መናገሩ ባሕሉ ለወንድ ተገቢ እንደሆነ ከሚገልጸው ድርጊት ያፈነገጠ በመሆኑ ትክክል አይሆንም። በጳውሎስ ዘመን ወንዶች ለእግዚአብሔር ያላቸውን አክብሮት ለማሳየት ባርኔጣቸውን ማንሣትና ራሳቸውን አለመሸፈን የሚጠበቅባቸው ይመስላል። ከሴቶች ይልቅ ፀጉራቸውን ማሳጠር ይኖርባቸዋል። ይህንን ማድረግ ቢያቆሙ ግን በውጪ ባሉት ዘንድ ለእግዚአብሔር ተገቢውን ክብር እንደማይሰጡ ያስቆጥርባቸዋል። በሌላ በኩል፥ ሴት ራሷን ሳትሸፋፈን ትንቢት ብትናገር፥ ባሕሉ ትክክል ነው ብሎ ከሚያስበው ግንዛቤ መውጣቷ ነበር። የጠበቀ ሥነ ምግባራዊ አኗኗር የማይከተሉ ሴቶች ፀጉራቸውን አይሸፋፈኑም ነበርና። ይህ ለዝሙት ወይም ጋለሞታነት የሚሰጠውን ፀጉርን የመላጨት ተግባርን ያህል አሳፋሪ ነበር። በተጨማሪም፥ ይህ ሴቶች የባሎቻቸውን ሥልጣን ባለመቀበል ያሻቸውን እንደሚያደርጉ የሚያሳይ ድርጊት ነበር። (ጳውሎስ ሴት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ትንቢት ልትናገር እንደምትችል ይናገራል።) ስለሆነም፥ ጳውሎስ ሴቶች በአምልኮ ወቅት ባሕላቸው በሚፈቅደው መሠረት ባሎቻቸውን ማክበራቸውን እንዲያሳዩ ይጠይቃል። በቆሮንቶስ ይህ ማለት የሴቶች በአምልኮ ሰዓት ራሳቸውን መሸፋፈን ነበር። ይህም ሚስት ባሏንና እግዚአብሔርን ማክበሯን የሚያሳይ ሲሆን፥ የእግዚአብሔር ልጆች የሚያከናውኑትን ተግባር ለሚመለከቱት መላእክት መልካም ምስክርነት ነው። በእግዚአብሔር ዓይኖች ፊት ወንድና ሴት፥ ባሎችና ሚስቶች እኩልና አንዳቸው ያለ ሌላቸው ሊኖሩ የማይችሉ ናቸው። ጳውሎስ ይህ ትምህርት ከመጠን በላይ እንዲለጠጥና ወንዶች ሴቶችን የመቆጣጠር፥ የመግዛትና የመጨቆን ሥልጣን አለን ብለው እንዲያስቡ አይፈልግም። ወንዶች ለሴቶች እንደሚያስፈልጓቸው ሁሉ፥ ሴቶችም ለወንዶች ያስፈልጓቸዋል። እግዚአብሔር መጀመሪያ ሰውን ወንድና ሴት አድርጎ በአምሳሉ እንደፈጠረ አስታውስ (ዘፍጥ. 1፡27)። ይህ ክፍል ከዛሬዪቱ ቤተ ክርስቲያን ጋር ስለሚዛመድበት ሁኔታ ክርስቲያኖች ቢያንስ ሦስት አመለካከቶች አሏቸው። ሀ. እነዚህ በሁሉም ዘመን ለሚሠሩ ክርስቲያኖች ሁሉ የተሰጡ ትእዛዛት ናቸው። ይህን አመለካከት የሚቀበሉ ሰዎች ሴቶች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በሚሆኑበት ጊዜ ሁሉ በራሳቸው ላይ አንድ ነገር ማድረግ እንዳለባቸው ያስተምራሉ። መንፈስ ቅዱስ በታሪክ ሁሉ እግዚአብሔርን የሚፈሩ ክርስቲያኖች እነዚህ ትእዛዛት ለሁሉም ባሕሎች የተሰጡ ናቸው ብለው እንዳያስቡ ያደረገው ባሕላዊ መሠረት ስላላቸው ሳይሆን አይቀርም። ለ. በዛሬው ዘመን ትክክለኛ በሆነው ጉዳይ ላይ የተለያዩ ባሕላዊ ግንዛቤዎች ስላሉ፥ የጳውሎስን ዝርዝር ትእዛዛት መከተል አያስፈልግም። ነገር ግን ሚስቶች ለባሎቻቸው በመገዛት አክብሮታቸውን ማሳየት እንዳለባቸው የሚያመለክተው የጳውሎስ አስተምህሮ በሁሉም ዘመን በሁሉም ባሕሎች ውስጥ ለሚኖሩ ሰዎች የሚሠራ ዐቢይ መርሆ ነው። ዋናው ነገር የአለባበስ ጉዳይ ሳይሆን እግዚአብሔርን እየፈሩ በተገዢነት መኖር ነው። ከሕይወታችን ጋር ልናዛምደው የሚገባን መርህ በባሕላችን ውስጥ ዓመፀኝነትን ሳይሆን ለእግዚአብሔር ጨዋነትንና አክብሮትን በሚያሳይ መልኩ መልበስ እንዳለብን ነው። ሐ. ጳውሎስ ወንዶች ፀጉራቸውን በአጭሩ እንዲቆረጡና እንዳይሸፋፈኑ ሴቶች ረዥም ፀጉር እንዳያሳድጉና እንዲሸፋፈኑ፥ ወንዶች በሴቶች ላይ ሥልጣን እንዲኖራቸው ያዘዘው ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ብቻ ነው። በ1ኛ ቆሮ. 11፡11-12 ጳውሎስ የወንዶችንና የሴቶችን እኩልነትና አንዳቸው የሌላቸው ጥገኛ መሆናቸውን ገልጾአል። ይህ ዛሬ ተግባራዊ ልናደርገው የሚገባን እውነት ነው። ጳውሎስ ስለ እግዚአብሔር አብና ወልድ የሥልጣን ደረጃ መናገሩ ባል በሚስቱ ላይ አስተዳደራዊ ሥልጣን እንዳለው ሊያመለክት ይችላል። ነገር ግን ይህ ወንዶችና ሴቶች አንዳቸው ለሌላቸው ስለሚገዙበት ሁኔታ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ከሚናገሩት

ሕዝብ በሚሰበሰብበት ይፋዊ አምልኮ ላይ የሴቶችና ወንዶች ትክክለኛ አለባበስ ምን ዓይነት መሆን አለበት? (1ኛ ቆሮ. 11፡2-16)። Read More »

ክርስቲያን ለጣዖት የተሠዋ ሥጋ መብላት አለበት? (1ኛ ቆሮ. 8፡1-11፡1)

የውይይት ጥያቄ፡- 1ኛ ቆሮ. 8-10 አንብብ። ሀ) የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ያሳሰባቸው ጉዳይ ምን ነበር? ለ) ጳውሎስ ለጣዖት የተሠዋን ሥጋ ስለ መብላት ወይም ስላለመብላት የሰጣቸውን መርሆች ዘርዝር። ሐ) ዛሬ ክርስቲያኖች በአመለካከት የሚለያዩባቸውንና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በግልጽ ያልተጠቀሱትን ልምምዶች ዘርዝር። የጳውሎስ መርሆች ከእነዚህ የተለያዩ ግንዛቤዎች ጋር የሚዛመዱት እንዴት ነው? ሁልጊዜም ክርስቲያኖች በአመለካከት የሚለያዩባቸው የተለያዩ ልምምዶች አሉ። ክርስቲያኖች አልኮል ሊጠጡ፥ ከንፈራቸውንና ጥፍራቸውን ቀለም ሊቀቡ፥ የፋሽን ልብስ ሊለብሱ፥ ፊልም ሊያዩ፥ የዓሣማ ሥጋ ሊበሉ፥ ወዘተ.. ይችላሉ? ከኦርቶዶክስ እምነት የመጡ ክርስቲያኖች አንገታቸው ላይ የነበረውን ክር ሊበጥሱ ይገባል? ክርስቲያኖች በእነዚህ ጉዳዮች በአሳብ አይስማሙም። እንግዲህ፥ ክርስቲያኖች መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ በማይከለክላቸው ጉዳዮች ላይ በአሳብ በሚለያዩበት ጊዜ ምን ማድረግ ይኖርብናል? በእነዚህ ምዕራፎች ውስጥ በእግዚአብሔር ቤተሰብ ውስጥ ልዩነቶችን አቻችሎ ስለመኖር ጠቃሚ መርሆዎች ቀርበዋል። ሀ. በቆሮንቶስ የነበረው ሁኔታ፤ በቆሮንቶስ ከተማ ብዙ ጣዖታትና ጥቂት ክርስቲያኖች እንደነበሩ ቀደም ብለን ተመልክተናል። በቆሮንቶስ ከተማ ከጣዖት አምልኮ ጋር የሚዛመዱ ብዙ ነገሮች ነበሩ። የቆሮንቶስ ሰዎች በክርስቶስ ካመኑ በኋላ፥ «ከቀድሞ ሕይወታችን ልንተወውና ይዘን ልንቀጥል የሚገባን ምንድን ነው? እያሉ ይጠይቁ ነበር። ሁለተኛው ጥያቄ ደግሞ፥ «ቀደም ሲል ሃይማኖታዊ አስከትሎቶችን ያስተናገዱትንና በራሳቸው ክፉዎች ያልሆኑትን ነገሮች እንዴት ልናስተናግዳቸው ይገባል?» የሚል ነበር። በቆሮንቶስ ክርስቲያን በገበያ ላይ የሚሸጥ ሥጋ ሊበላ ይገባል ወይ? በሚለው ጥያቄ ዙሪያ የተጧጧፈ ክርክር ይካሄድ ነበር። አንድ ሰው ለጣዖት ለመሠዋት በሚፈልግበት ጊዜ እንስሳውን ወደ ቤተ ጣዖት ይወስዳል። እንስሳው ታርዶ ከፊሉ ለጣዖት ከተሠዋ በኋላ፥ ከቀረው ሥጋ የተወሰነውን ለካህኑ ሲሰጥ፥ የተወሰነውን ደግሞ ቤቱ ወስዶ ከወዳጆቹ ጋር ሊመገብ ወይም ገበያ ላይ ሊሸጥ ይችል ነበር። ገበያ ላይ የሚሸጠው ሥጋ በአብዛኛው ለጣዖት የተሠዋ ነበር። ስለሆነም፥ የቆሮንቶስ አማኞች፥ «ክርስቲያኖች ከገበያ ላይ ሥጋ ገዝተው ሊበሉ ይችላሉ? ከዓለማዊ ሰው ቤት ሲጋበዙስ የሚቀርብላቸውን ሥጋ ሊበሉ ይገባል? ይህ ሥጋ ለጣዖት የተሠዋ ሊሆን ይችላልና» የሚል ጥያቄ አነሡ። ይህ እንዳንድ ክርስቲያኖች ከሙስሊም ሉካንዳ ወይም በተገቢው የኦርቶዶክስ ክርስቲያን ያልታረደ ሥጋ ለመብላት ከሚቸገሩበት ሁኔታ ጋር ተመሳሳይ ሊሆን ይችላል። ጳውሎስ ለዚህ ጥያቄ «እንዲህ አድርጉ/ እንዲህ አታድርጉ» የሚል ቀላል ምላሽ አልሰጠም። እንደነዚህ ዓይነት ጥያቄዎች ሁልጊዜም ሥር የሰደዱ ጉዳዮችን እንደሚያካትቱ ተገንዝቦ ነበር። መርሆዎች፡- ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ከሰጣቸው መልሶች ለሁላችንም ጠቃሚ የሆኑትን መርሆዎች እናገኛለን። እንደሚከተለው ቀርበዋል። ሀ. አንድ ነገር ስሕተት አለመሆኑን ማወቃችን በፍቅርና ለሌሎች ከማሰባችን ጋር ሊጣጣም ይገባል (1ኛ ቆሮ. 8፡1-3)። ፍቅር ያልታከለበት እውቀት ኩሩና አጥፊ ነው። ለምሳሌ፥ ወደ ፊልም ቤት መሄድ ስሕተት አለመሆኑን ባውቅና ሌሎች ክርስቲያኖች ግን ስሕተት ነው ብለው ቢያስቡ፥ የእኔ ወደ ፊልም ቤት መሄድ የእነርሱን እምነት ከመጉዳትና የእኔን ምስክርነት ከማበላሸት የተሻለ ጥቅም አይኖረውም። ‹እውቀቴን ጉዳትን እንጂ ጥቅምን አላስከተለም። ሰዎች ተጨማሪ ትምህርት ከተከታተሉ በኋላ ተመልሰው የቤተ ክርስቲያናቸው መሪ በሚሆኑበት ጊዜ ይኩራራሉ። እውቀታቸው ከሌሎች ሰዎች የሚያስበልጣቸው ይመስላቸዋል። ይህ የኩራት እውቀት እነዚህ ሰዎች ስለ መንፈሳዊ ነገሮች ብዙም እንደማያውቁ ያሳያል። ለ. ከእውቀት አንጻር፥ ሰብአዊ ጣዖት (ወይም ሌላ ሃይማኖት) ሰው ሠራሽ እንጂ አምላክ እንዳልሆነ በሳል ክርስቲያኖች ያውቃሉ (1ኛ ቆሮ. 8፡4-7)። አንዱ እውነተኛ አምላክ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጠው ብቻ ነው። ብቸኛው አምላክና ጌታ በዓለም ውስጥ ሁሉንም ነገር የፈጠረው እግዚአብሔር አብ፥ የፍጥረት ሥራ ሁሉ ወኪል የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስና ሕይወት ሰጭ የሆነው መንፈስ ቅዱስ ነው። ስለሆነም፥ ሕይወትና ኃይል ለሌላቸው ሰው ሠራሽና ሙት ጣዖታት የተሠዋን ሥጋ መብላት ምንም ማለት እንዳልሆነና ሊበላ እንደሚችል በሳል (ጠንካራ) ክርስቲያኖች ይገነዘባሉ። ሒ. ሌሎች ቢያደርጉትም እንኳ ትክክል ነው ብለህ ያላመንኸውን ነገር ማድረጉ ኃጢአት ነው። ጣዖት ሲያመልኩ የኖሩና በእምነታቸው ያልበሰሉ አንዳንድ ክርስቲያኖች ሥጋውን መብላት በጣዖት አምልኮ ውስጥ መሳተፍ ነው ከሚል ድምዳሜ ላይ ደረሱ። ይህም ድነትን (ደኅንነትን) ባገኙ ጊዜ የተዉት ልምምድ ነበር። ስለሆነም፥ ሌሎች ክርስቲያኖች ይህን ሥጋ ሲበሉ አይተው ከኃፍረት የተነሣ አብረው በሚበሉበት ጊዜ፥ ሕሊናቸው ስለሚቆሽሽ ኃጢአትን ይሠራሉ። የሚያደርጉት ነገር በእግዚአብሔር የተፈቀደ ነው ብለው እስካላመኑ ድረስ (ጳውሎስ «በእምነት ካልሆነ» እንዳለው)፥ ሌሎች የሚያደርጉትን መከተል አያስፈልጋቸውም ነበር። መ. ለጣዖት የተሠዋ ሥጋ መብላትም ሆነ አለመብላት ምንም ዓይነት መንፈሳዊ እሴት የለውም። አንድን ሰው ወደ እግዚአብሔር አያቀርበውም ወይም ከእግዚአብሔር አያርቀውም (1ኛ ቆሮ. 8፡8)። አዲስ ኪዳን ሁሉም ነገር በጸሎት የተባረከ ስለሆነ ልንበላ እንደምንችል ያስረዳል። በእምነት እስካደረግነው ድረስ በእግዚአብሔር የተፈቀደ ነው (ማር. 7፡14-19፤ የሐዋ 10፡9-16)። ሠ. አንድ ተግባር በእግዚአብሔር የተፈቀደ ነው ብለን ብናምን እንኳ ፍቅር ከግለሰባዊ ነጻነት ይልቃል (1ኛ ቆሮ. 8፡9–9፡27)። ስለሆነም፥ ሥጋን መብላት ምንም ችግር የለውም የሚል እምነት ያላቸው (ወይም በመጽሐፍ ቅዱስ ያልተከለከለውን ተግባር የሚፈጽሙ) ሰዎች የተለየ አመለካከት የሚከተሉትን ወገኖች ላለመጉዳት ሲሉ ነጻነታቸውን መገደብ አለባቸው። (ጳውሎስ «ደካማ» እና «ጠንካራ» ክርስቲያኖች እንዳሉ ገልጾአል። ጳውሎስ ይህን ሲል ስለ መንፈሳዊ ብስለት ወይም መንፈሳዊነት መናገሩ አይደለም። እርሱ ያተኮረው አንድ ሰው በያዘው የግንዛቤ ደረጃ ላይ ነው። ስለሆነም፥ አንድ ክርስቲያን የዓሣማ ሥጋ በመብላቱ በኩል «ጠንካራ» ሊሆንና የፋሽን ልብስ በመልበሱ ረገድ «ደካማ» ሊሆን ይችላል። ሌላው ክርስቲያን ደግሞ ሥጋ ለመብላት ሊቸገርና የፋሽን ልብስ ለመልበስ ሊደፍር ይችላል።) ጠንካራ ክርስቲያኖች ደካማ ክርስቲያኖችን ላለማሰናከል ሲሉ ተግባሮቻቸውንና ነጻነቶቻቸውን መገደብ አለባቸው። ከሁሉም የሚበልጠው ፍቅር ነው። ፍቅር ደግሞ ሥጋን መብላት ወይም የተወሰኑ ልብሶችን መልበስ ሌላውን ክርስቲያን የሚጎዳው ከሆነ፥ ከዚህ ተግባር መቆጠብ እንዳለብን ይመክረናል። የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ክርስቲያኖች የተለያዩ አመለካከቶችን ስለሚይዙባቸው ነገሮች ያቀረብኸውን ዝርዝር ከልስ። ወይም ሌሎች ምሳሌዎችን ጨምርበት። ጠንካራውና ደካማው የትኛው እርምጃ እንደሆነ ግለጽ። ለ) ፍቅር አልባ እውቀት ያለው ሰው በእነዚህ ልምምዶች ሁሉ ወቅት ምን እንደሚያደርግ ግለጽ። ሐ) ፍቅር ያለው ሰው በእነዚህ ልምምዶች ወቅት ምን እንደሚያደርግ ግለጽ። ማብራሪያ፡ ለሌሎች ባለን ፍቅር የግል መብቶችንና ነጻነቶችን ስለመተው ጳውሎስ ከራሱ ሕይወት ምሳሌ ሰጥቷል (1ኛ ቆሮ. 9)። ጳውሎስ ሐዋርያ ቢሆንም፥ ለወንጌሉ ሲል ብዙ ጊዜ መብቶቹን ትቷል። ለምሳሌ፥ ሀ. ጳውሎስ የማግባት መብት ቢኖረውም ለወንጌሉ ሲል አላደረገውም። ለ. ጳውሎስ ለሐዋርያዊ አገልግሎቱ ገንዘብ የመቀበል መብት ቢኖረውም፥ ሰዎች ለራስ ወዳድነት ምክንያቶች ያስተምረናል ብለው እንዳያስቡ ትቷል። ቆሮንቶሶችና አዳዲስ ክርስቲያኖች ለወንጌል ስርጭቱ ዓላማ ጥርጣሬ እንዳይኖራቸው በማሰብ፥ ጳውሎስ ክፍያ ላለመቀበል ወስኗል። ስለሆነም፥ ከበሳል አብያተ ክርስቲያናት በሚያገኘው ስጦታ ወይም ራሱ ሠርቶ በሚያገኘው ገንዘብ (በቆሮንቶስ ሳለ ድንኳን ይሰፋ እንደነበረ የሐዋ. 18፡3 አንብብ።) ራሱን ይደግፍ ነበር። በፊልጵስዩስ 1፡5 እና 4፡14–18 ጳውሎስ የፊልጵስዩስ ቤተ ክርስቲያን እንዴት አገልግሎቱን በገንዘብ እንደደገፈች ገልጾአል። ስለሆነም፥ ጳውሎስ ከወንጌል ስብከት ገንዘብ ለማግኘት ካልፈለገ ምን ይሆን የፈለገው? ጳውሎስ ገንዘብ ቢከፈለውም ሳይከፈለውም ከእግዚአብሔር ዘንድ ወንጌልን የመስበክ ግዴታ እንደተጣለበት ያውቅ ነበር። በግሉ የተሸላሚነት ስሜት የሚሰማው ገንዘብ ሳይጠይቅ ለጠፉት ወንጌልን በሚሰብክበት ጊዜ ነበር። (ጳውሎስ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚያገለግሉ፥ በተለይም ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ብለው የገቢ ማግኛቸውን የሚተዉ ሰዎች ደመወዝ ሊከፈላቸው እንደሚገባ የሚያስረዳውን የመጽሐፍ ቅዱስ መርህ አጽንዖት ሰጥቶ ገልጾአል። ለሚያገለግሏት ሰዎች የማትከፍል ወይም ነፃ የውጭ ወንጌላውያን ሥራዎቿን እንዲያካሄዱላት የምትፈልግ ቤተ ክርስቲያን ከእግዚአብሔር ፈቃድ እንዳፈነገጠች ግልጽ ነው።) ሐ. ከመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል እስካልወጣ ድረስ ጳውሎስ እንደፈለገ የመኖርና የመሥራት ነጻነት ነበረው። ነገር ግን በተቻለ መጠን ብዙዎችን ያድን ዘንድ ነጻነቱን ገድቦታል። አይሁዶችን በሚያገለግልበት ጊዜ ወንጌሉን ሊያካፍላቸው እንዲችል የተወሰኑ ምግቦችን የመመገብ፥ በተወሰኑ መንገዶች የመልበስና የማምለክ ነጻነቱን በመገደብ ባሕሉን ቀይሯል። አሕዛብን በሚያገለግልበት ጊዜ የቋንቋ አጠቃቀሙን፥ የአለባበስና የአምልኮ ሁኔታውን በመቀየር ከባሕላቸው ጋር ተግባብቶ ወንጌሉን ሰብኮላቸዋል። ጳውሎስ በእምነታቸው ደካሞች ሆነው እግዚአብሔር እንዳልከለከለ የሚያውቃቸውን ነገሮች ለማድረግ የማይፈልጉ ሰዎች በሚያጋጥሙት ጊዜ፥ እንደነርሱው «ደካማ» ሆኗል። ጳውሎስ ለግል ነጻነቱና መብቱ ብዙም ትኩረት አይሰጥም ነበር። ለጳውሎስ ዋናው የሰዎች መዳን ነበር። ስለሆነም፥ ሰዎች እንዳይድኑ የሚያደናቅፉትን

ክርስቲያን ለጣዖት የተሠዋ ሥጋ መብላት አለበት? (1ኛ ቆሮ. 8፡1-11፡1) Read More »

ጋብቻን በተመለከተ ለተነሱ ጥያቄዎች ጳውሎስ የሰጠው መልስ (1ኛ ቆሮ. 7፡1-40)

እያንዳንዱ ባሕል በጋብቻና ወሲባዊ ግንኙነቶች ላይ የተለያየ አመለካከት አለው። የምዕራባውያን ባሕል በወሲባዊ ፍቅር ስለሚደመደም፥ ይህንኑ ወሲባዊ ፍቅር ከሁሉም እንደ ላቀ ደስታ ይቆጥረዋል። ለምዕራባውያን ወሲባዊ ፍቅር የሚያተኩረው ራስን በማስደሰት ላይ ነው። የአፍሪካ ባሕል ጋብቻንና ወሲባዊ ግንኙነቶችን ልጆችን ለመውለዱ ዓላማ ይጠቀማል። ብዙ ልጆች ለመወለድ ሲባል ብዙ ሚስቶች ማግባትንም የሚፈቅዱ አንዳንድ ባሕሎች አሉ። ከጳውሎስ ዘመን ጀምሮ እስከ መካከለኛው ዘመን ድረስ ወሲባዊ ግንኙነቶችና ጋብቻ ትክክል አለመሆናቸውን የሚያስረዱ አመለካከቶች ተንጸባርቀዋል። መንፈሳዊ የሆነ ሰው ብቻውን ወይም በገዳማት ከወሲባዊ ግንኙነቶች ርቆ መኖር እንዳለበት ይታሰባል። ይህ ወሲባዊ ግንኙነት መጥፎ ነው የሚለው አመለካከት በዓለም ውስጥ በብዙ ባሕሎች ውስጥ ይታያል። ስለ ወሲባዊ ፍቅር ሚዛናዊ አመለካከት ለማግኘት መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረውን መመልከት ይኖርብናል። ጥሩና መጥፎ ስለሆነው ነገር መመሪያዎችን የሚሰጠው ሰዎችንና ወሲባዊ ግንኙነቶችን የፈጠረው እግዚአብሔር ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚከተሉትን ነገሮች እንመለከታለን። እግዚአብሔር ሰውን ወንድና ሴት አድርጎ በአምሳሉ ፈጥሯል። ሔዋንን ለአዳም እንደ እኩል አጋሩ አድርጎ ሰጥቷል። እኩልነታቸውንና ፍቅራቸውን ይገልጹ ዘንድ ወሲባዊ ፍቅርን ሰጥቷቸዋል። ይህንንም ሁሉ «መልካም ነው» ብሏል። ስለሆነም፥ የእግዚአብሔርን የፍጥረት አሠራር ከተከተልን ወሲባዊ ፍቅር መልካም ነው (ዘፍጥ. 1-2)። የመኃልየ መኃልይ መጽሐፍ እግዚአብሔር በባልና ሚስት መካከል ያለውን ፍቅር እንደሚቀበል ያሳያል። ሌላው እግዚአብሔር ወሲባዊ ፍቅርን የሰጠበት ምክንያት ሰዎች እንዲበዙ ነበር። ሰዎች ልጆችን በመውለድ እግዚአብሔር ያዘጋጀላቸውን ምድር እንዲሞሉ ታዘዋል (ዘፍጥ. 1፡22)። ወሲባዊ ግንኙነት በባልና በሚስት መካከል ብቻ መፈጸም ይኖርበታል። ሰዎች ከመጋባታቸው በፊትም ሆነ የትዳር ጓደኞቻቸው ካልሆኑት ሰዎች ጋር የሚፈጽሙት የትኛውም ዓይነት ከጋብቻ ውጭ የሆነ ወሲብ እግዚአብሔር ያልፈቀደው ነው። የጋብቻ ግንኙነት እስከ ሞት ድረስ የጸና መሆን አለበት። ስለሆነም፥ በምዕራቡ ዓለም ተስፋፍቶ የሚታየው ፍች ኃጢአት ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ፍች ሊካሄድ የሚችለው የማያምን የትዳር ጓደኛ ያመነውን ትቶ ሲሄድ ወይም ከተጋቢዎቹ አንዱ የማያቋርጥ ዝሙት ከሌላ ሰው ጋር የሚፈጽም እንደሆነ ብቻ ነው (ማቴ. 5፡31-32)። የተሻከሩ ባልና ሚስት በይቅርታ ታድሰው ትዳራቸውን ሊቀጥሉ ስለሚችሉ ዝሙት የግድ እንዲፋቱ ማድረግ የለበትም። የእግዚአብሔር የጋብቻ ዓላማ አንድ ወንድ ከአንዲት ሴት፥ አንዲት ሴት ከአንድ ወንድ ጋር እንዲጋቡ ነው። ለዚህም ነው እግዚአብሔር አዳምን ለሔዋን ሔዋንን ደግሞ ለአዳም የፈጠረው። ስለሆነም፥ የአንድ ወንድ ብዙ ሴቶችን ማግባትም ሆነ በአንዳንድ ባሕሎች እንደሚታየው የአንዲት ሴት ብዙ ወንዶችን ማግባት ትክክል አይደለም። እግዚአብሔር ወሲባዊ ፍቅርን እንደ ውብ፥ አስደሳችና ጠቃሚ የጋብቻ አካል አድርጎ ስለፈጠረ፥ ሰይጣን ሁልጊዜም ሊያበላሸው ይሞክራል። ይህንንም የሚያደርገው በብዙ የተለያዩ መንገዶች ነው። ሰይጣን ያገቡም ሆነ ያላገቡ ሰዎች ከሌሎች ሰዎች ጋር ወሲብን እንዲፈጽሙ ያበረታታቸዋል። ወንዶች ብዙ ሚስቶችን ማግባታቸውንም ያበረታታል። ወንዶች ሴቶች እኛን ለማርካት የተፈጠሩ መሣሪያዎች ናቸው ብለው እንዲያስቡ ወይም ወሲባዊ ፍቅር ክፉ ነው እንዲሉ ይገፋፋቸዋል። የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ብዙ ኢትዮጵያውያን እግዚአብሔር በጋብቻ ውስጥ ያስቀመጠውን ወሲባዊ ፍቅር ያበላሹባቸውን መንገዶች ግለጽ። ለ) ምን ያህል ክርስቲያኖች ስለ ጋብቻና ወሲባዊ ፍቅር የተሳሳተ ግንዛቤ እንዳላቸው ግለጽ። ጳውሎስ በ1ኛ ቆሮንቶስ 1-16 እርሱን ሊጎበኙ የመጡት የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ለነገሩት ችግሮች መልስ መስጠቱን አቁሞ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በደብዳቤ የጠየቁትን ጥያቄዎች ወደ መመለሱ ይሻገራል። (1ኛ ቆሮ. 7፡1 አንብብ።) ጳውሎስ እየተናገረ ያለውን አሳብ ለመረዳት የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች የተጋፈጧቸውንና የጳውሎስን ማብራሪያ የጠየቁባቸውን ጉዳዮች መመልከቱ ጠቃሚ ይሆናል። አንዳንዶቹ ጉዳዮች ግልጽ ሲሆኑ፥ ሌሎቹ ግን ግልጽ አይደሉም። እንዲሁም ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ውስን ጉዳዮች ከሰጣቸው መልሶች ምን ያህሉን ከዛሬው ሁኔታችን ጋር ማዛመድ እንዳለብን በመግለጹ ረገድ ክርስቲያኖች በአሳብ ይለያያሉ። ከነዚህም መካከል ዝርዝር ጉዳዮችን ሳይሆን ከጳውሎስ ትእዛዛት በስተጀርባ የሚገኙትን የተወሰኑ መርሆች መከተል አለብን የሚሉ አሉ። የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) 1ኛ ቆሮ. 7ን አንብብ። በዚህ ምዕራፍ ውስጥ ስለ ጋብቻ የተጠቀሱትን የተለያዩ መርሆች ዘርዝር። ለ) ጳውሎስ በላጤነት መኖር መልካም ስለመሆኑ የሰጣቸውን ምክንያቶች ዘርዝር። ጳውሎስ ስለ ወሲባዊ ርኩሰት እየገለጸ በመሆኑ፥ አቅጣጫውን ቀይሮ ስለ ክርስቲያናዊ ጋብቻ ማስተማሩ ተገቢ ነበር። ቆሮንቶሶች ለጳውሎስ ሁለት ጥያቄዎችን ያቀረቡለት ይመስላል። በመጀመሪያ፥ መበለቶች፥ ወንደ ላጤዎችና ሴተ ላጤዎች ክርስቲያኖች ማግባት ወይም ሳያገቡ መኖር እንዳለባቸው ጠይቀዋል (1ኛ ቆሮ. 7፡1)። ሁለተኛ፥ ልጃገረድ ሴቶች (ደናግልት) ማግባት ወይም በላጤነት መኖር እንዳለባቸው ጠይቀዋል (1ኛ ቆሮ. 7፡25-26)። የጳውሎስን ዝርዝር ትእዛዛት ከመመልከታችን በፊት ጳውሎስና ሌሎችም በአዲስ ኪዳን ውስጥ የጻፉትን መረዳት ይኖርብናል። ጳውሎስ ጋብቻን እንደማይቃወምና ዝቅ አድርጎ እንደማይመለከት ግልጽ ነው። በኤፌሶን 5፡22-33 ጳውሎስ በባልና ሚስት መካከል ያለው ጋብቻና ፍቅር ክርስቶስ ለቤተ ክርስቲያን ያሳየውን ፍቅር በምሳሌነት እንደሚያብራራ አስረድቷል። እንዲያውም ጋብቻን መከልከል የተሳሳተ የመጨረሻው ዘመን ምልክት እንደሆነ አስረድቷል (1ኛ ጢሞ. 4፡1-3 አንብብ።) ዕብራውያን 13፡4 ጋብቻን እንድናከብር ያስተምረናል። ይህም ጳውሎስም ሆነ ሌሎች የአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎች ጋብቻን እንደማይቃወሙ ያሳያል። በ1ኛ ቆሮንቶስ 7፥ ጳውሎስ ጋብቻንም ላጤነትንም ያከብራል። ከዚህ በታች የክርክር አሳቡ ጠቅለል ብሎ ቀርቧል። ሀ. ሰው ሳያገባ በእግዚአብሔር ፊት ንጹሕ ሆኖ ቢኖር መልካም ነው። ይህም የወንድና ሴት መበለቶች፥ እንዲሁም ገና ያላገቡትንና ደናግሎችን ይመለክታል። ጳውሎስ ስላላገባ ራሱን በምሳሌነት አቅርቧል። አንድ ሰው ከተቻለ ሳያገባ መኖር ያለበት ለሦስት ምክንያቶች ነው። በመጀመሪያ፡ ከጊዜው «ችግር» የተነሣ በላጤነት መቆየት ከብዙ የልብ ስብራት ያድናል (1ኛ ቆሮ. 7፡26)። ጳውሎስ ስለ የትኛው ችግር እንደሚናገር አናውቅም። ምናልባትም ጳውሎስ የሮም መንግሥት በክርስቲያኖች ላይ እንደሚያመጣ ስለሚጠባበቀው ስደት መናገሩ ይሆናል። ወይም ጳውሎስ ብዙውን ጊዜ ክርስቲያኖች እየታሰሩና እየተገደሉ ለስደት ስለሚዳረጉ፥ ሳያገቡ መኖሩ ባል፥ ሚስት ወይም ልጆች በሚለዩዋቸው ጊዜ በኃዘን ከመጎሳቆል እንደሚያድናቸው መናገሩ ይሆናል። ሁለተኛ፥ ጳውሎስ ክርስቶስ በቶሎ ስለሚመለስ የእግዚአብሔርን አገልግሎት ለማካሄድ ብዙ ጊዜ እንደማይኖር አስረድቷል። ስለሆነም፥ ክርስቲያኖች እየተጋቡ በምድር ላይ የተለመደ ሕይወት ለመምራት ከመሞከር ይልቅ እግዚአብሔርን በማገልገሉ ተግባር ላይ ሊያተኩሩ ይገባል። በቀድሞዪቱ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንደነበሩት አብዛኞቹ ሰዎች ጳውሎስም ክርስቶስ በጥቂት ዓመታት ውስጥ እንደሚመለስ ተስፋ አድርጎ ነበር። ስለሆነም፥ ከዚህ ዓለም ሕይወት ይልቅ በመጭው የክርስቶስ መንግሥት ላይ አጽንኦት ሰጥቶ ነበር። ሦስተኛው፥ ከጋብቻ በኋላ በባልና ሚስት ላይ ብዙ ኃላፊነቶች ይወድቃሉ። ይህም የአገልግሎት ጊዜያቸውን ስለሚሻማ ላጤነቱ ተመራጭ ይሆናል። ላጤነት እግዚአብሔር ለአንዳንድ ሰዎች የሚሰጣቸው ስጦታ ነው (1ኛ ቆሮ. 7፡7)። ያላገባ ሰው ብዙ ጊዜውን እግዚአብሔርን በማገልገሉ ተግባር ላይ ሲያውል፥ ያገባው ግን ሌሎች ኃላፊነቶች ይኖሩታል። እግዚአብሔርን ለማስደሰትና ለማገልገል ቢፈልጉም፥ ጊዜያቸውና ትኩረታቸው እግዚአብሔርንና ቤተሰቦቻቸውን በማገልገሉ መካከል ይከፋፈላል። ያገቡ ሰዎች ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ለመደገፍ ጥሩ ሥራ መያዝ ይኖርባቸዋል። ቤት፥ የልጆች ትምህርት፥ ወዘተ… እግዚአብሔርን የሚያገለግሉበትን ጊዜ ይወስድባቸዋል። በታሪክ ሁሉ እግዚአብሔር ብዙ ሰዎችን፣ ላጤ ሚሲዮናውያንንም፥ ሳያገቡ እንዲኖሩ ጠርቷቸዋል። እነዚህ ሰዎች ባልተከፈለው ልባቸው አብዛኞቹ ያገቡ ሰዎች በማይችሏቸው መንገዶች ለቤተ ክርስቲያንና ለወንጌሉ መስፋፋት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል። የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) እግዚአብሔር ለዚህ እንደጠራው በማወቅ ሳያገባ የኖረ ሰው ታውቃለህ? ለ) ይህ ሰው አሳብን ከሚሰርቁ ተጨማሪ ኃላፊነቶች ርቆ ከአብዛኞቹ ባለትዳሮች በላቀ መንገድ እግዚአብሔርን ለማገልገል የቻለበትን ሁኔታ ግለጽ። ለ. አብዛኞቹ ክርስቲያኖች ማግባት ይፈልጋሉ። ለዚህም አንዱ ምክንያት ከዝሙት ራሳቸውን ለመጠበቅ ነው። በጋብቻ ሁለቱ አንድ ስለሆኑ፥ እያንዳንዱ አጋር ለገዛ ሰውነቱ መብት አይኖረውም። የባል ሰውነት ሚስቱ ትደሰትበት ዘንድ የራሷ ሰውነት ይሆናል። የሚስት ሰውነት ባል ይደሰትበት ዘንድ የራሱ ሰውነት ይሆናል። በጸሎት ላይ ለማተኮር በጋራ ተስማምተው ለተወሰነ ጊዜ ወሲባዊ ግንኙነቶችን እስካላቋረጡ ድረስ፥ ወሲባዊ ፍቅር ሁልጊዜም ሊቀጥል የሚገባውና ለሁለቱም እርካታ የሚበጅ ነው። ባል ወይም ሚስት ወሲባዊ ግንኙነት ለመፈጸም የማይፈቅድ ከሆነ ሰይጣን በግንኙነታቸውና በትዳራቸው ላይ ጥቃት እንዲሰነዝር መፍቀዳቸው ነው። ሐ. ከተቻለ፥ ሁሉም እግዚአብሔር ድነትን (ደኅንነትን) ባገኙ ጊዜ በጠራቸው ሁኔታ ሊኖሩ ይገባል። ካላገቡና ወሲባዊ ፍላጎት ካላየለባቸው ሳያገቡ መኖር አለባቸው። ያገቡ ሰዎች ግን መለያየትም ሆነ መፋታት የለባቸውም። በዚህ ክፍል፥ ጳውሎስ እግዚአብሔር በግልጽ የተናገረውን (ይህን ጌታ እንጂ እኔ

ጋብቻን በተመለከተ ለተነሱ ጥያቄዎች ጳውሎስ የሰጠው መልስ (1ኛ ቆሮ. 7፡1-40) Read More »

ጳውሎስ ስለ ዝሙት ተጨማሪ ትምህርት ሰጠ (1ኛ ቆሮ. 6፡9-20)

ጳውሎስ በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ስለተከሰተው የዝሙት ኃጢአት ያቀረበውን ገለጻ ከፈጸመ በኋላ፥ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የትኛውንም ዓይነት ወሲባዊ ኃጢአት ማድረግ ስሕተት የሆነባቸውን ምክንያቶች ያብራራል። ሀ. በማያቋርጥ ወሲባዊ ኃጢአት የሚኖሩ ሰዎች እውነተኛ የእግዚአብሔር ልጆች አለመሆናቸውን ስለሚያሳዩ፥ ወደ ዘላለማዊ የእግዚአብሔር መንግሥት ሊገቡ አይችሉም። በክርስቶስ በምናምንበት ጊዜ አሮጌው ሕይወታችን ተለውጦ አዲስ ሕይወት እንጀምራለን። ወሲባዊ ሕይወታችን ስለሚለወጥ ዝሙት፥ ሴተኛ አዳሪነትና ግብረ ሰዶማዊነት ከመፈጸም እንቆጠባለን። አምልኳችን ስለሚለወጥ እንደ ቀድሞው ጣዖት አናመልክም። (በሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ከእግዚአብሔር በላይ የምንወደው ነገር ሁሉ ጣዖታችን እንደሆነ ተገልጾአል። ቆላ. 3፡5 አንብብ።) ከሌሎች ሰዎች ጋር ያለን ግንኙነት ይለወጣል። ሌሎች ሰዎችን በመስረቅ ወይም በማታለል (በመንጠቅ) ለመክበር አንፈልግም። በተጨማሪም፥ ሌሎችን ከመርዳት ይልቅ ነገሮችን ለራስ ማግበስበሱ የራስ ወዳድነት ኃጢአት ነው። የሰዎችን ስም በማጉደፍ ዝናቸውን ለማክሰም አንፈልግም። ከራሳችን ጋር ያለ ግንኙነትም ስለሚለወጥ ከእንግዲህ የመጠጥ ባሪያዎች አንሆንም። ምንም እንኳ ከማመናቸው በፊት በዚህ ዓይነት ላይኖሩ ቢችሉም፥ ጳውሎስ የቀድሞው አኗኗር እንዳበቃ ገልጾላቸዋል። በክርስቶስ ባመኑበት ወቅት የክርስቶስ ደም ከእነዚህ ኃጢአቶች አጥቧቸዋል። እናም በደሙ ተዋጅተዋል። ደሙ ለአዲስ ሕይወት ለይቷቸዋል (ቀድሷቸዋል)። ጥፋተኛ አይደላችሁም ተብለዋል፣ ጸድቀዋል)። እነዚህ ሦስቱ የክርስቶስና የመንፈስ ቅዱስ ሥራዎች ሕይወታቸውን ሙሉ በሙሉ ለውጠዋል። ለ. ኃጢአትን የሚፈጽሙ ሰዎች ስለሚቆጣጠራቸው ነገር የተለያየ አመለካከት ይኖራቸዋል። ምናልባትም ጳውሎስ በኃጢአት እየተመላለሱ «ሁሉም ተፈቅዶልኛል» የሚሉትን አንዳንድ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች አባባል ጠቅሶ እየተናገረ ይሆናል። «እኛ በክርስቶስ ነፃ ነን። ከሕግ በታች ስላልሆንን እንደፈለግን ልንኖር እንችላለን» ሲሉ ተሟገቱ። ጳውሎስ ለዚህ ክርክር በተለያዩ መንገዶች ምላሽ ሰጥቷል። መጠየቅ ያለብን ጥያቄ «የተፈቀደልኝ ምንድን ነው?» የሚል ሳይሆን የሚጠቅመው የቱ ነው የሚለውን ነው። በሙያዊ ይዘታቸው ኃጢአት ያልሆኑና ለእኛ የማይጠቅሙ ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ። ስለሆነም፥ ለእኛ መልካም ያልሆኑትንና ክርስቲያናዊ ምስክርነታችንን የሚያጠፉትን ነገሮች ከመፈጸም መቆጠብ ይኖርብናል። እንደ ክርስቲያኖች እንድናድግ በሚረዱንና ለክርስቶስ ክብርን በሚያመጡ ነገሮች ነጻነታችን ሊገደብ ይገባል። ምንም ነገር ሰውነታችንን እንዲቆጣጠር መፍቀድ የለብንም። ሰውነታችን ለእግዚአብሔር ክብር የተሠራ መሆኑን መገንዘብ አለብን። በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ በመተባበራችን ከሥጋ ፍላጎት ቁጥጥር ነፃ ወጥተናል። ስለሆነም፥ እነዚህ ክፉ ፍላጎቶች ሊቆጣጠሩን አይገባም። ሆዳምነት (የምግብ ፍቅር)፥ ወሲብ፥ ዕፅ፥ መጠጥ፥ ገንዘብ፥ ትምህርትን በመሳሰሉት ቁጥጥር ሥር መዋሉ ትክክል አይደለም። ከእነዚህ ነገሮች አንዱም እንኳ ቢቆጣጠረን ኃጢአት ነው። አንድ ቀን ሰውነታችን ፈርሶ ሌላ አካል ይሰጠናል። ስለሆነም፥ ወደ ኃጢአት የሚመሩ ወይም እግዚአብሔርን የማያስከብሩ ነገሮችን በማድረግ ለጊዜው ፍላጎቶቻችንን ከምናሟላ ይልቅ ዘላለማዊ ጠቀሜታ ያላቸውን ነገሮች ልንፈጽም ይገባል። ክርስቲያኖች የክርስቶስ አካል የራሱ ከፍሎች ናቸው። ስለሆነም፥ አንድን ተግባር በምንፈጽምባት ጊዜ ክርስቶስንም የዚያ ድርጊት ተሳታፊ እናደርገዋለን። ለእግዚአብሔር ምስጋናን ስንዘምር፥ ይህ ክርስቶስ ለእግዚአብሔር ምስጋናን የሚዘምርበት ዓይነት ነው። ስንመሰክር ክርስቶስ እንደሚመሰክር ነው፥ ለድሀ ስንመጸውት ይህ ክርስቶስ ለድሃ እንደሚመጸውት ያህል ነው። ጳውሎስ እንደሚለው፥ ከክርስቶስ ጋር ስለተባበርን የምናደርገው ክፉም ሆነ ደግ ተግባር ክርስቶስን ያሳትፈዋል (በሐዋርያት ሥራ 9፡4 ክርስቶስ ክርስቲያኖችን ማሳደድ እርሱን እንደ ማሳደድ መሆኑን በገለጸበት መልኩ ይህንኑ እውነት እንመለከታለን።) ጳውሎስ ወሲባዊ ኃጢአት ለፈጻሚው እንደ ውሸት ካሉት ሌሎች ኃጢአቶች የከፋ መዘዝ እንደሚያስከትል አመልክቷል። ጳውሎስ ይህን ሲል ምን ማለቱ እንደሆነ እርግጠኞች አይደለንም። ምናልባትም ወሲባዊ ኃጢአት ከሌሎች ኃጢአቶች በበለጠ ባሕሪያችንን፥ ቤተሰባችንና ጤንነታችንን እንደሚጎዳ መግለጹ ይሆናል። ዛሬ ሰዎችን የሚያሠቃዩ እንደ ኤድስ ያሉ በሽታዎች የወሲባዊ ኃጢአት ውጤቶች ናቸው። ወሲባዊ ኃጢአት የመንፈስ ቅዱስን ቤተ መቅደስ ያረክሰዋል። በቆሮንቶስ አረማዊ አምልኮ ወሲባዊ ኃጢአት የጣዖት አምልኮ አካል ነበር። ለክርስቲያኖች ግን እውነቱ የተገላቢጦሽ ነበር። እግዚአብሔር በብሉይ ኪዳን ዘመን በመገናኛው ድንኳንና በቤተ መቅደስ ውስጥ ይኖር እንደነበረ ሁሉ፥ መንፈስ ቅዱስ በእኛ ውስጥ እንደሚኖር እያንዳንዱ አማኝ መገንዘብ አለበት። ክርስቲያኖች ሁሉ ይህንን ሊያውቁ ይገባል። የአማኞች ኅብረት የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ ስለመሆኑ ከሚናገረው 1ኛ ቆሮ. 3፡16 በተለየ መንገድ፥ ይህ ምንባብ እያንዳንዱ አማኝ የመንፈስ ቅዱስ ቤተመቅደስ በመሆኑ ላይ ያተኩራል። ለዚህም ምክንያቱ ኃጢአት ቢሠሩም እንኳ መንፈስ ቅዱስ በክርስቲያኖች ሕይወት ውስጥ የሚኖር መሆኑ ነው። እግዚአብሔር ቅዱስ አምላክ ስለሆነ፥ ማደሪያዎቹ የሆኑት ክርስቲያኖች እንዲቀደሱለት ይፈልጋል። ይህም በብሉይ ኪዳን ዘመን ሕዝቡ በተቀደሰ ሕይወት እንዲያመልከው ከተጠየቀበት ሁኔታ ጋር ተመሳሳይ ነው። ወሲባዊ ኃጢአት የማን መሆናችንን እንድንዘነጋ ያደርጋል። ጳውሎስ እንደሚለው፥ የእግዚአብሔር ልጆች ከሆንን በራሳችን ሕይወት ላይ መብት አይኖረንም። ክርስቶስ በመስቀል ላይ በመሞት ገዝቶናል። ስለሆነም ክርስቶስ በሕይወታችን ላይ መብት ስላለው እርሱ የሚፈልገውን ማድረግ አለብን። ሰውነታችንንና ሰውነታችንን የምንጠቀምበትን ሁኔታ ሊቆጣጠር የሚገባው በባለቤትነት የሚያስተዳድረን ክርስቶስ ነው። የክርስቶስ ትልቁ ፍላጎት እግዚአብሔርን ማስከበር ስለሆነና ሰውነታችንን ለእግዚአብሔር ክብር ለመጠቀም ስለሚፈልግ፥ ተግባራችን ሁሉ ለእግዚአብሔር ክብርን ማምጣት አለበት። ወሲባዊ ኃጢአት እግዚአብሔርን አያስከብርም። ስለሆነም፥ የክርስቶስ የሆነውን ሰውነታችንን እርሱ ለማይፈልገው ተግባር መጠቀሙ ትክክል አይሆንም። የውይይት ጥያቄ፡– ሁለት ወጣቶች ወደ አንተ መጥተው፥ «እርስ በርሳችን እንፋቀራለን» በሚቀጥሉት ሦስት ወራት ውስጥ ጋብቻችንን ስለምንፈጽም አብረን መተኛት ብንጀምር ምን ይመስልሃል? ይሄ ማንንም አይጎዳም» ቢሉህ፥ ጳውሎስ ስለ ወሲባዊ ኃጢአት ካስተማረው በመነሣት ምን ብለህ ትመክራቸዋለህ? (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ጳውሎስ ስለ ዝሙት ተጨማሪ ትምህርት ሰጠ (1ኛ ቆሮ. 6፡9-20) Read More »

ክርስቲያኖች በፍርድ ቤት ይካሰሱ ነበር (1ኛ ቆሮ. 6፡1-8)

ከጳውሎስ ልማዶች አንዱ ስለ አንድ ጉዳይ እየጻፈ ሳለ ሌላ ነገር ሲነገረው ርእሰ ጉዳዩን ወደ አዲሱ መረጃ የማዞር ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ በኤፌሶን 3፡1 ጳውሎስ ለኤፌሶን ክርስቲያኖች ስለ መጸለዩ የሚናገር ይመስላል። ነገር ግን ለአሕዛብ መታሰሩን ማስታወሱ አሳቡን ስላላስለወጠው ለኤፌሶን ክርስቲያኖች ስለ መጸለይ ያነሣውን ጉዳይ ከማብራራቱ በፊት (ኤፌ. 3፡14) ወንጌል ለአሕዛብ ስለ መሰበኩ ብዙ ማብራሪያ ሰጥቷል። በዚህ ስፍራም ጳውሎስ የጀመረውን የዝሙት ጉዳይ አቋርጦ (በ1ኛ ቆሮ. 6፡9-20 የሚቀጥል) ክርስቲያኖች በሌሎች ክርስቲያኖች ላይ በመፍረድ ኃላፊነታቸውን አለመወጣታቸውን ያስረዳል። ጳውሎስ አንዳንድ ክርስቲያኖች በሀብት ጉዳይ ሌሎች ክርስቲያኖችን ፍርድ ቤት እንደሚያቆሟቸው የሰማ ይመስላል። ምናልባት አንድ ክርስቲያን ለሌላው አንድ ንብረት ወይም ከብት ከሸጠለት በኋላ ገዢው የተታለለ መስሎ ሳይሰማው አልቀረም። ስለዚህም እንደ ዓለማውያን ክርክራቸውን በፍርድ ቤት ለመቋጨት ፈለጉ። ክርስቲያኖች ችግሮቻቸውን ለመፍታት ክርስቲያን ባልሆነ ዳኛ ፊት መቆማቸው ጳውሎስን አስቆጣው። ይህ ክርስቲያኖች የመፍረድ ሥልጣናቸውን እንዳልተጠቀሙበት የሚያሳይ ነበር። ጳውሎስ እንዲህ ዓይነቱን ጉዳይ የማያምኑ ሰዎች ወደሚገኙበት ችሎት መውሰድ እንደሌለባቸው በመግለጽ የሚከተለውን ብሏል። ክርክሮችን ወደማያምኑ ዳኞች (ችሎት ወይም የጎሳ ሽማግሌዎች) የሚወስዱ ክርስቲያኖች እግዚአብሔር የሰጠንን ሥልጣን አልተገነዘቡም። በመጨረሻ ከክርስቶስ ጋር በማያምኑ ሰዎች ላይ እንፈርዳለን። (ማቴ. 19፡28፤ 2ኛ ጢሞ 2፡12፤ ራእይ 20፡4 አንብብ።) በመላእክትም ላይ እንፈርዳለን። ይህ ምናልባትም በወደቁትና አሁን የሰይጣን መላእክትና እጋንንት ሆነው በሚሠሩት መላእክት ላይ ክርስቶስ ፍርድ በሚሰጥበት ጊዜ እኛም እንደምንሳተፍ የሚያሳይ ይሆናል። (2ኛ ጴጥ. 2፡4-9፤ ይሁዳ 6 አንብብ።) እግዚአብሔር ወደ ፊት ለክርስቲያኖች እንዲህ ዓይነት ሥልጣን የሚሰጣቸው ከሆነ፥ አሁን እንደ ንብረት ያሉትን ጥቃቅን ጉዳዮች የመዳኘት ሥልጣን እንዳለን ግልጽ ነው። ጳውሎስ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የመዳኘት ሥራ የሚሠሩትን ሰዎች መምረጡ ቀላል እንደሆነ በምፀታዊ ድምፀት ይናገራል። ጳውሎስ ይህን ሲል፥ «ትምህርትና ስጦታ ያላቸውን ሽማግሌዎች ተዉአቸው። ትምህርት የሌላቸውን ሽማግሌዎች ውሰዱ። እነዚህ ሰዎች በኋላ በታላላቅ ጉዳዮች ላይ ፍርድ የሚሰጡ የእግዚአብሔር ልጆች ስለሆኑ ችግሮችን ለማስተካከል ይችላሉ» ማለቱ ነበር። እንዲህ ዓይነቱን ጉዳይ ወደ ፍርድ ቤት መውሰድ በክርስቲያኖች መካከል የሚነሣውን አለመግባባት የሚፈታ አስተዋይ ሰው የለም እንደ ማለት ነበር። ክርስቲያኖች ችግሮቻችንን ወደ ዓለማውያን መውሰዳችን እርስ በርሳችን ለመዳኘት አለመቻላችንን ያሳያል። ይህም ምስክርነታችንን ከማበላሸቱም በላይ የክርስቶስን ስም ያስነቅፋል። ይህም በዋናው ጉዳይ ላይ ሽንፈት እንደገጠመን ያሳያል። ክርስቲያናዊ ስማችንና የክርስቶስ ስም ከየትኛውም የግል ጉዳይ የበለጠ ነው። በጠብና ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት በመውሰድ የክርስቶስንና የክርስቲያኖችን ስም ከማጉደፍ ይልቅ ተበዳዩ ተበድሎም እንኳ ቢሆን ጉዳዩን መተው ነበረበት። የራሳችን ለሆነው ንብረት በመፋለም የክርስቶስንና የቤተ ክርስቲያንን ስም ከማጉደፍ ይልቅ መበደሉ የተሻለ ነው። የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ክርስቲያኖች ችግሮቻቸውን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሊፈቱ ሲችሉ እንዴት ወደ ዓለማውያን እንደሚወስዱ ግለጽ። ለ) ከእነዚህ ልምምዶች የሚመነጩ አሉታዊ ነገሮች ምን ምንድን ናቸው? ሐ) በክርስቲያኖች መካከል ስለተፈጸመ አንድ ክፍፍል ግለጽ። ጳውሎስ ባስተማረው መሠረት እግዚአብሔር ክርስቲያኖች ችግሮቻቸውን እንዴት አድርገው እንዲፈቱ የሚፈልግ ይመስልሃል? (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ክርስቲያኖች በፍርድ ቤት ይካሰሱ ነበር (1ኛ ቆሮ. 6፡1-8) Read More »

በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ምግባረ ብልሹነት ነበር (1ኛ ቆሮ. 5፡1-13)

መሪዎችን ጨምሮ ክርስቲያኖችን በተደጋጋሚ ከሚያውኩ ኃጢአቶች አንዱ ወሲባዊ እርኩሰት ነው። ከጋብቻ ውጭ ወሲብ የሚፈጽም ባል ወይም ሚስት፥ ወንድ ወይም ሴት ወጣት እግዚአብሔርን በጽኑ ያሳዝነዋል። የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ከብዙ ሰዎች ጋር ወሲባዊ ግንኙነት ተቀባይነት ባገኘበት ማኅበረሰብ ውስጥ ይኖሩ ነበር። የቆሮንቶስ ሰዎች ከጋብቻ ውጭ ከሚፈጽሟቸው የወሲብ እርኩሰቶች በተጨማሪ፥ እንደ ግብረ ሰዶማዊነት ያሉትን ያልተለመዱ ወሲባዊ ተግባራት ያከናውኑ ነበር። በዚህ ባሕል ውስጥ የነበሩት የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ይህን ችግር እንዴት መቋቋም እንዳለባቸው አላወቁም ነበር። ስለሆነም አክራሪ ጫፍ ይመዙ ጀመር። አንዳንዶች ሁሉም ወሲባዊ ግንኙነቶች ክፉዎች ስለሆኑ መጋባት ለክርስቲያኖች አስፈላጊ እንዳልሆነ ይናገሩ ጀመረ። ሌሎች ደግሞ ሁሉም ዓይነት ወሲባዊ ግንኙነቶች ተቀባይነት እንዳላቸው አስተማሩ። እነዚህ ወገኖች የእግዚአብሔር ጸጋ ለኃጢአት ይቅርታን የሚያስገኝ ከመሆኑም በላይ በሥጋ የሚሠራው ኃጢአት መንፈሳዊ ሕይወትን እንደማይነካ ገለጹ። ስለሆነም፥ ጳውሎስ እነዚህን ሁለት የተራራቁ አመለካከቶችን በማማከል መናገር ነበረበት። በ1ኛ ቆሮንቶስ 7 ስለ ጋብቻ ይናገራል። በ1ኛ ቆሮንቶስ 5-6፥ ከጋብቻ ውጭ ስለሚካሄዱ ወሲባዊ ግንኙነቶች ክርስቲያኖች የነበራቸውን የተሳሳተ አመለካከት ያብራራል። ሁለተኛውና የቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን መሪዎች ለጳውሎስ ሪፖርት ያደረጉት ችግር ግልጽ የሆነ ወሲባዊ እርኩሰት በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ መከሰቱ ነበር። ጳውሎስን ያስደነቀው ወሲባዊ እርኩሰት መፈጸሙ ሳይሆን የቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ምእመናንና መሪዎች ለዚህ ኃጢአት የነበራቸው አመለካከት ነበር። ሁኔታው (1ኛ ቆሮ. 5፡1)፡- በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ከአባቱ ሚስት ጋር ዝሙት የሚፈጸም ሰው ነበረ። ይህች ሴት እናቱ ሳትሆን የእንጀራ እናቱ ነበረች። ሴቲቱ ለኃጢአቷ መቀጣት እንዳለባት የሚያመለክት አሳብ ስላልተጠቀሰ፥ ሴትዮዋ አማኝ ያልነበረች ይመስላል። ቤተ ክርስቲያን ሥልጣን ያላት በምእመኖቿ ላይ ብቻ ስለሆነ፥ ጳውሎስ የቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን በኃጢአት የሚመላለሱ ምእመኖቿን እንዴት ማረም እንዳለባት ያስረዳል። መሪዎቹ ግለሰቡን ከመገሠጽና የቤተ ክርስቲያን የቅጣት ደረጃዎችን ተከትለው ከመሥራት ይልቅ ሁኔታውን በቸልተኝነት ይመለከቱ ነበር። ለምን? ምክንያቱም ኃጢአት እየቀጠለ እንዲሄድ መፍቀዳቸው ለተፈጸመው ጥፋት ተቃውሞ የሌለበት ምላሽ እንዳላቸው ያሳያል። ጳውሎስ ራሱ ኃጢአት ሲበዛ የእግዚአብሔር ጸጋ ከዚያ በላይ እንደሚገለጥ አስተምሮ የለም? ሊሉ አሰቡ (ሮሜ 5፡20-21)። የጳውሎስ ውሳኔ (1ኛ ቆሮ. 5፡2-5)፡- ሀ) በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚከሰት ኃጢአት አስደሳች ወይም በቀላሉ የሚታይ ሳይሆን ኃዘንን የሚያስከትል ነው። ለ) ይህን ኃጢአት የሚፈጽመው ግለሰብ ከቤተ ክርስቲያን ኅብረት መውጣት አለበት። ጳውሎስ ይህንኑ ግለሰቡን ከቤተ ክርስቲያን ኅብረት የማስወጣት ሂደት ሰውዬውን «ለሰይጣን አሳልፎ መስጠት» ሲል ይጠራዋል። የቀድሞዎቹ ክርስቲያኖች መንፈስ ቅዱስ በአማኞች ስብሰባና ኅብረት ውስጥ ስለሚኖር ስፍራው ድነት (ደኅንነት) የሚገኝበትና ክርስቶስ የሚገዛበት በመሆኑ የሰይጣን ኃይል የተዳከመበት እንደሆነ ያምኑ ነበር። ነገር ግን ከክርስቲያኖች ኅብረት ውጭ ሰይጣን በንጉሥነት እንደሚገዛ ያምኑ ነበር። ስለሆነም አንድን ሰው ከኅብረቱ ማስወጣት ማለት ወደ ሰይጣን ግዛት መመለስ ማለት ነበር። በዚህ ጊዜ ሰይጣን ግለሰቡን በተለያዩ መንገዶች ሊያጠቃው ይችላል። ግለሰቡን ከቤተ ክርስቲያን ማስወጣታቸው ክርስቲያን ወዳለመሆን እንደተመለሰ አያሳይም። ቀዳሚ ዓላማውም ቅጣት አልነበረም። ይህ የግለሰቡ የኃጢአት ባሕርይ እንዲጠፋና መንፈሱ በጌታ ቀን እንድትድን ታስቦ የተደረገ የመማሪያ ገጠመኝ ነበር። ሰውዬው ከሚወዳቸው ምእመናን ተለይቶ ሲወጣ በሚሰማው ኃፍረትና በሚደርስበት የሰይጣን ጥቃት ምክንያት ከኃጢአቱ ንስሐ ገብቶ ወደ ቤተ ክርስቲያን እንዲመለስ ለማድረግ የተወሰደ እርምጃ ነበር። (የዚህን አሳብ ተጨማሪ ማብራሪያ ከ1ኛ ጢሞ. 1፡20 አንብብ።) ጳውሎስ ግለሰቡ በኃጢአቱ እየገፋበት መሆኑንና ይህም በምእመናን ሁሉ ዘንድ መታወቁን ገምቷል። ይህ አንድ ሰው ስለ ሌላው የሚያቀርበው ወቀሳ ወይም ጉምጉምታ ሳይሆን፥ የቤተ ክርስቲያኒቱ መሪዎች ጥናት አድርገው ለጳውሎስ የጻፉት ጉዳይ ነበር። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ኃጢአት በሚኖርበት ጊዜ ሽማግሌዎች በማቴ. 18፡15-17 የተሰጠውን ደረጃ መከተላቸው ጠቃሚ ነው። ይህን ከፍተኛ ቅጣት መስጠት የሚቻለው ከዚያ በኋላ ብቻ ነው። ይህ ከፍተኛ ቅጣት የተሰጠበት ምክንያት (1ኛ ቆሮ. 5፡6-8)፡- ኃጢአትን በትኩረት ተከታትለን የቤተ ክርስቲያን ቅጣት እንዲሰጥበት ካላደረግን ጥቂት እርሾ ጠቅላላውን ሊጥ እንደሚያቦካ ሁሉ፥ ኃጢአት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ መስፋፋቱ የማይቀር ነው። ጳውሎስ ከብሉይ ኪዳን የአይሁዶች የፋሲካ ልምምድ ተነሥቶ ምን ማድረግ እንዳለባቸው ይመክራል። ከፋሲካው በዓል ቀደም ብሎ እያንዳንዱ አይሁዳዊ ቤተሰብ እርሾ ያለበትን ነገር ሁሉ ያስወግድ ነበር። ይህም ክፋትን የማስወገድ ተምሳሌት ነበር። በተመሳሳይ ሁኔታ፥ የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎችም የትኛውንም ዓይነት ያፈጠጠና ንስሐ ያልተገባበትን ኃጢአት ከቤተ ክርስቲያን ለማስወገድ ነቅተው ሊሠሩ ይገባል። ጳውሎስ፥ «በክፋትና በግፍ እርሾም አይደለም» ሲል ለወሲባዊ እርኩሰት ብቻ ሳይሆን፥ በቤተ ክርስቲያን ስላለ ሥነ ሥርዓትም ጭምር ነበር። ስለሆነም፥ ንስሐ ያልተገባበትና የዓመፃ ኃጢአት ሁሉ እልባት ሊሰጠው ይገባል። ጳውሎስ ራሷን በንጽህና የምትጠብቅ ቤተ ክርስቲያንን «የቅንነትና የእውነት ዳቦ» ይላታል። በተጨማሪም፥ ጳውሎስ ፍርዱ በክርስቲያኖች ፊት በይፋ መሰጠት እንዳለበት አመልክቷል። ይህ ኃጢአት ለፈጸመው ግለሰብ ብቻ ሳይሆን ለክርስቲያኖች ሁሉ የመማሪያ ገጠመኝ ይሆናል። ኃጢአት ከፈጸሙ በኋላ ንስሐ በማይገቡት ሰዎች ላይ የሚደርሰውን ቅጣት በመመልከት ክርስቲያኖች በተመሳሳይ ኃጢአት ላለመውደቅ ይጠነቀቃሉ። በማቴዎስ 18፡15-17 የተጠቀሰውን ሂደት ከተከተሉ በኋላ ክፍፍል እንዳይፈጠር ሽማግሌዎች ፍርዱን ለክርስቲያኖች ሁሉ ማሳወቃቸው አስፈላጊ ነው። ይህም መከፋፈል እንዳይፈጠር ያደርጋል። ስለተፈጸመው ኃጢአት ሰዎች ሁሉ ከሰሙ በኋላ ከዋናው ጋር ሲስተያይ የሽማግሌዎችን ውሳኔ በይፋ አለማሳወቁ፥ ሰይጣን የወሬ ጉምጉምታዎችን በመጠቀም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሰዎችን እንዲከፋፍል በር ይከፈታል። በተጨማሪም፥ እነዚህ በማቴዎስ 18፡15-17 የተጠቀሱትን ምስክሮች በምንመርጥበት ጊዜ እድልዎአዊ አቅጣጫ የማይዙትን ሰዎች መጠቀም እንዳለብን ያሳያል። የውይይት ጥያቄ፡– ሀ) በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ ጳውሎስ የሰጠው ዓይነት ፍርድ ሲበየን አይተህ ታውቃለህ? እንደዚህ ከሆነ፥ የተከሰተውን ሁኔታ አብራራ። ለ) ቤተ ክርስቲያን በዓመፃ ኃጢአቶች ላይ ብዙም ይፋዊ ፍርድ የማትሰጠው ለምን ይመስልሃል? ይህ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ኃጢአት እንዲስፋፋ የሚያደርገው እንዴት ነው? ሐ) በሽምግልና ተመርጠህ በምታገለግልበት ጊዜ ሁለት የኳዬር መዘምራን ዝሙት እንደሚፈጽሙ ሰማህ እንበል። ማቴዎስ 18፡15-17 እና በዚህ ክፍል ጳውሎስ ያስተማረውን አሳብ በመከተል፥ ለዚህ ኃጢአት መፍትሔ መጠቆም ያለብህ እንዴት ነው? መ) «እነዚህን ሰዎች ብናጋልጥ እነርሱና ቤተሰቦቻቸው ቤተ ክርስቲያናችንን ጥለው ይወጣሉ። እነዚህ ሰዎች ስለሚጠቅሙን በዚህ መንገድ ልናሳፍራቸው እንችልም?» የሚል አሳብ ለሚያቀርብ ሽማግሌ ምን ምላሽ ትሰጠዋለህ? ጳውሎስ ቀደም ሲል ለቤተ ክርስቲያን የሰጠውን ትእዛዝ አብራራ (1ኛ ቆሮ. 5፡9-11)፡- ጳውሎስ ስለዚህ ወይም ስለ ሌላ ወሲባዊ ኃጢአት ቀደም ሲል የሰማና ክርስቲያኖች ጭፍን ዝሙት ከሚፈጽሙና በእግዚአብሔር ላይ ከሚያምፁ ሰዎች ጋር ኅብረት እንዳያደርጉ የሚያሳስብ መልእክት የጻፈላቸው ይመስላል። የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች የጳውሎስን ትእዛዛት በተሳሳተ መንገድ በመረዳት ከዓለማውያን ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንዳያደርጉ የከለከላቸው መሰላቸው። ጳውሎስ ግን የተቀደሰ አኗኗር ሳይከተሉ እንደ ዓለማውያን ስለሚኖሩ ክርስቲያኖች እየተናገረ መሆኑን ገልጾላቸዋል። አሁንም ጳውሎስ ስለ ወሲባዊ ርኩሰት ብቻ እየተናገረ አለመሆኑን መገንዘብ ጠቃሚ ነው። ስለ ራስ ወዳዶች፥ ነጣቂዎች በክርስቶስ እናምናለን እያሉ የቤተሰቦቻቸውን ወይም የማኅበረሰቡን ፍርድ በመፍራት የድሮ አምልኮአቸውን የሚያካሂዱትን ጭምር ይዘረዝራል። ጳውሎስ ክርስቲያኖች ያፈጠጠ ኃጢአት ከሚፈጸሙ ሰዎች ጋር ምንም ዓይነት ኅብረት እንዳያደርጉ የከለከለው ክፉ መንገዳቸውን አይተው በንስሐ እንዲመለሱ ለማገዝ ነበር። በአንጻሩ ግን ጳውሎስ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በኃጢአት ከሚኖሩት ከዓለማውያን ጋር ኅብረት በማድረግ እንደሚመሰክሩላቸው አሳስቧል። እግዚአብሔር ክርስቲያኖችን የጠራቸው ዓለምን እንዲተዉና ራሳቸውን ከዓለማውያን እንዲለዩ አይደለም። ነገር ግን እርሱ ባስቀመጠን ማኅበረሰብ ውስጥ እየኖርን ንጹሐንና ቅዱሳን እንድንሆን ጠርቶናል። የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ሆን ብለው ኃጢአትን ከሚፈጽሙ ክርስቲያኖች ጋር ያለንን ግንኙነት እምብዛም የማናቋርጠው ለምን ይመስልሃል? ለ) አንዳንድ ክርስቲያኖች በክርስቲያናዊ ድርጅቶች ውስጥ ለመሥራት ሲሉ ሥራቸውን የሚለቁት ወይም ከክርስቲያኖች ጋር ለመጎራበት የሚፈልጉት ለምንድን ነው? ጳውሎስ እንዲህ ያለውን ምክንያት የሚቀበል ይመስልሃል? ጳውሎስ ኃጢአት የሚሠሩትን ክርስቲያኖች እንደ ዓለማውያን ለምን መፍረድ እንደሌለብን ያብራራል (1ኛ ቆሮ. 5፡12-13)። በዓመፀኝነት መንፈስ ግልጽ ኃጢአት የሚፈጽሙትን ክርስቲያኖች መቅጣትና መፍረድ ያለብን እግዚአብሔር ከሰጠን የፈራጅነት ሥልጣን የተነሣ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ልጆች በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ የመፍረድ ሥልጣን እንዳላቸው ይናገራል። (ማቴ. 19፡28 አንብብ።) ስለሆነም አሁን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አንዳችን በሌላችን ላይ የመፍረድ ብቃት አለን። ነገር ግን

በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ምግባረ ብልሹነት ነበር (1ኛ ቆሮ. 5፡1-13) Read More »