1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች

1ኛ ቆሮንቶስ 9፡ 15-18 

ጥያቄ 1. በቁጥር 15 ላይ «እንዲህ እንዲሆንልኝ ይህን አልድፍም» ሲል ምን ማለቱ ነው?  ጥያቄ 2. በቁጥር 15 ላይ «ትምክሕት» የሚለው ምኑን ነው?  ጥያቄ 3. በቁጥር 17 መሠረት ሐዋርያው ወንጌልን ይሰብክ የነበረው በፈቃድ ነበር ወይስ ያለፈቃድ?  ጥያቄ 4. በቁጥር 18 ላይ ወንጌልን የመስበክ ደምወዙ ምንድነው ይላል?  ቁጥር 15:- ከላይ ከዘረዘራቸው መብቶች በአንዱም እንኳ ያልተጠቀመ እንደሆነ ይመሰክራል፡፡ በዚህ ጊዜ በአእምሮው የመጣበት ምናልባት የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች «ይህን ሁሉ አሁን የሚናገረው ደመወዝ ፈልጎ ነው ይሉኝ ይሆናል፤» የሚለው ግምት ነበር። ይህም እንዳልሆነ በከባድ አነጋገር ያረጋግጥላቸዋል። «ማንም ትምክህቴን ከንቱ ከሚያደርገብኝ ሞት ይሻለኛልና።»  ትምክህቱ ወንጌልን በነፃ መስበኩ ነው። ግን አሁን ሃሳቡን ቀይሮ ደመወዝ መቀበል ቢጀምር ያ ትምክህቱ ይቀራል። ትምክህቱ የትዕቢት ሳይሆን ደመወዝ በመቀበል ሊመጣ የነበረውን የወንጌልን እንቅፋት በማስወገዱ ነበር። በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሐዋርያውን የማይወዱ ሐሰተኛና ደምወዝ ወዳድ አስተማሪዎች ተነሥተው ነበርና የሐዋርያው አቋም ለእውነት በጣም አስፈላጊ ነበር። እነዚህም ሐሰተኛ አስተማሪዎች እርሱም ደመወዝን ተቀብሎ ከእርሱ እኩል በመሆን እንዳያሳጣቸው ይፈልጉ ነበር፤ (2ኛ ቆሮ. 11:12)።  ጥያቄ 5. በአንዳንድ ቤተ ክርስቲያን ለደመወዝ ብቻ ብለው የሚያገለገሉ መሪዎች አሉ? ይህ ዓይነት ሃሳብ እንዴት ለወንጌልና ለቤተ ክርስቲያን እንቅፋት ሊሆን ይችላል?  ቁጥር 16፡- «ወንጌልን ብሰብክ እንኳ» የሚለው አነጋገር እንደዚሁ ብሰብክም እንኳ ያንኑ የታዘዝሁትን ፈጸምሁ እንጂ ትርፍ ሥራ የሠራሁ ይመስል ልኮራ አይገባኝም ማለቱ ነው፤ (ሉቃ.17:10)። ወንጌልን መስበክ ግዴታው ስለሆነም ወንጌልን ባይሰብክ “ወዮለት!” ወንጌላዊ ጥሪውን በቀላሉ ሊመለከተው አይገባም።  ጥያቄ 6. ይህን ዓይነት ገዴታ በእኛ ላይ አለ? እንዴት?  ቁጥር 17:- «በፈቃዴ ባደርገው» ማለቱ ክርስቶስ በግድ ባያዘው ኖሮ እርሱ ራሱ በገዛ ምርጫው ቢሰማራ ኖሮ ደመወዝ ይገባው ነበር። ይህ ደመወዝ የሚለው አነጋገር ወንጌላውያን ከወንጌል ሥራ መተዳዳሪያ (ደመወዝ) ይቀበሉ ካለው ሃሳብ የተለየ ነው። ይኸኛው እግዚአብሔርን ለደመወዙ ባለዕዳ ማድረግ ነው፤ (ሮሜ 4:4)። ማንም ሥጋ ለባሽ እግዚአብሔርን ባለዕዳ ማድረግ አይችልም። ወንጌልን የሰበከው “የመጋቢነት አደራ” ስለተሰጠው ነበርና ባሪያ እንጂ በእግዚአብሔር ፊት ባለመብት አይደለም። መጋቢ የሚለው ቃል የባርነትን አደራ ያመልክታል፤ በ1ኛ ቆሮ.4: 1 ላይ የተወያየንበትን ተመልከት።  ቁጥር 18፡- እንግዲህ ሐዋርያው ምንም እንኳ በእግዚአብሔር ፊት ባሪያ ቢሆንም ቤተክርስቲያን ለሥራው ደመወዝ ልትሰጠው መብት እንዳለው በፊት አረጋግጧል። እንግዲህ ይህን ደምወዝ አለመቀበል ሙሉ ትምክህት በሰው ፊት ስለሚሰጠው ይህን ትምክህት አንደደምወዙ ቆጥሮታል።  ጥያቄ 7. ጥሩ ዓይነት ትምክህትና መጥፎ ዓይነት ትምክህት በምን ይለያል? እኛ በምን ላይ በጥሩ ሁኔታ ልንመካ እንችላለን?  (ምንጭ፤ በትምህርተ መለኮት ማስፋፊያ (ትመማ) መልክ የተዘጋጀ ጽሑፍ፡- በቄስ ኃይሉ መኮንን)

1ኛ ቆሮንቶስ 9፡ 15-18  Read More »

የሐዋርያ መብት ( 1ኛ ቆሮ.9:1-14) 

ጥያቄ 15. በቁጥር 1 ላይ «እኔ ነፃ አይደለሁምን?» ሲል ስለምን ዓይነት ነፃነት ነው የሚያወራው?  ጥያቄ 16. በቁጥር 1 እና 2 በጥያቄ መልክ የሚያቀርባቸው የሐዋርያነቱ ማረጋገጫዎች ምን ምን ናቸው?  ጥያቄ 17. በቁጥር 5 የጌታ ወንድሞች የሚላቸው እነማን ናቸው? (ማር.6፡3)  ጥያቂቄ 18. በቁጥር 9 ላይ «እግዚአብሔር ስለ በሬዎች ይገደዋልን?» የሚለውን ከማቴ.6፡26 ጋር በማስተያየት አስታራቂ ሃሳብ ጻፍ።  ጥያቄ 19. ሐዋርያው በመብቱ ቢጠቀም ኖሮ የክርስቶስን ወንጌል ሊከለክል እንደሚችል በቁጥር 12 ላይ ይናገራል፤ ይህ መብት ምን ነበር? አንዴትስ ወንጌልን ይከለክል ነበር?  ስለ ክርስቲያን ነጻነት በምዕራፍ 8 ይናገር ነበር፡፡ ያንኑ ነጥብ ቀጥሎ በምዕራፍ 9 ያብራራዋል። ሌሎች ነፃነታቸውን በፍቅር ለወንድሞች ጥቅም መሰዋት አለባቸው ብሎ ካስተማረ በኋላ የሚያስተምረውን በሥራ ላይ የሚያውል አስተማሪ መሆኑን ያረጋግጥላቸዋል።  ቁጥር 1-3፡- በምዕራፍ 8 ላይ ጳውሎስ ምንም እንኳን የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዝሙር ቢሆንም በእውቀቱ ላይ ሳይሆን በፍቅር ላይ ተመሥርቶ እንደሚኖር ያሳየናል። በመጀመሪያ እርሱ ራሱ ነፃ የሆነ ሰው እንደሆነ ለቆሮንቶስ ሰዎች ያሳያቸዋል፡፡ ከፈለገ ሚስት የማግባትም ሆነ ለሐዋርያዊነት ሥራው ደመወዝ የመቀበል ነፃነት ነበረው። ነገር ግን ለወንጌል እንቅፋት ሳይፈጥር የእግዚአብሔርን ሥራ ለመሥራት ሲል ነው ይህን ነፃነቱን ወደ ኋላ የተወው። በመጀመሪያ ግን ጳውሎስ አንዳንድ ጥያቀቄዎችን በመጠየቅ ሐዋርያነቱን አሳውቆ ነበር። 1ኛ/ «ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን አላየሁትምን?» ጌታን ያላየ ሐዋርያ መሆን አይችልም፤ ምክንያቱም ሐዋርያነት በቤተ ክርስቲያን ሳይሆን በቀጥታ በክርስቶስ የሚሰጥ ሥልጣን ስለሆነ ነው፤ (ገላ.1፡1 እና የሐዋ.9፡10-18)። 2ኛ/ ይህ ሐዋርያነቱን እንዲሁ በአፍ ወሪ ሳይሆን በሥራ የተመሰከረለት ነበር። ይህም ራሳቸው የቆሮንቶስ ሰዎች በጳውሎስ አገልግሎት ወደ እምነት መምጣታቸው የጳውሎስን ሐዋርያነት ያረጋግጣሉ።  ቁጥር 4-7:- በእነዚህ ቁጥሮች ውስጥ ሐዋርያ ስለሆነ የሐዋርያነት መብት እንዳለው ይናገራል። «ልንበላና ልንጠጣ መብት የለንምን?» ይህ መብላትና መጠጣት በምዕራፍ 8 ላይ ያለው ዓይነት መብላትና መጠጣት ሳይሆን፥ ከታች ዝቅ ብሎ እንደዘረዘረው ደመወዝ ወይም አበል ማለቱ ነው።  አንደነጴጥሮስ ያሉት ሐዋርያትና የጌታ ወንድሞች ከቤተ ክርስቲያን ውጪ ሚስቶቻቸውን ይዘው ለወንጌል ሥራ የመዞር መብታቸውን ተጠቅመውበት ነበር። ባርናባስና ጳውሎስ ግን ምንም እንኳ ይህ መብት እንዳላቸው ቢገነዘቡም በመብታቸው አልተጠቀሙም። ራሳቸው በትርፍ ጊዜያቸው በሚሠሩት ነበር ይተዳደሩ የነበረው። ሥራን ትቶ ወንጌልን ብቻ መስበክ ለእነርሱም የተሰጠ መብት ነበር፤ ግን አልተጠቀሙበትም።  ከሕብረተሰቡ ልማድ ምሳሌዎችን በማቅረብ ነገሩን ያረጋገጥላቸዋል። እነዚህም የገበሬና የወታደር ምሳሌዎች ናቸው። ስለዚህ በወንጌል ሥራም የተሰማሩ ከወንጌል መተዳደሪያ መቀበል መብታቸው ነው። በወንጌል የሚገለገሉ ለአገልጋዮቻቸው ደምወዝ ሊከፍሏቸው የተገባ ነው።  «የጌታ ወንድሞች» የሚለው ማሪያም ከዮሴፍ የወለደቻቸው የጌታችን የሥጋ ወንድሞች ናቸው። ማርያም ከጌታችን በኋላ አልወለደችም የሚሉ ማስረጃ ይዘው ሳይሆን የሥጋ ግብር ርኩስ ነው ብለው ስለሚገምቱ ማርያምን ለማክበር አስበው ነው። ግን ይህ አስተሳሰብ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ይጋጫል። በምዕራፍ 7 ላይ ስንመለከት ሐዋርያው በአንድም ቦታ ከሚስት ጋር መተኛት ርኩስ ነው አላለም። አለማግባት ከማግባት ይሻላል ያለውም ለአገልግሎት አመቺ ከመሆኑ አንጻር ነው እንጂ ከሚስት ጋር መተኛት ርኩስ ስለሆነ አልነበረም። እንዲያውም በዕብራውያን 13፡4 ላይ ጋብቻ ክቡርና ንጹሕ እንደሆነ ይናገራል። እንዲሁም እግዚአብሔር የፈጠረው ስለሆነ በምስጋና መቀበል አለብን እንጂ ርኩስ ነው ማለት እግዚአብሔርን መሳደብ መሆኑን መዘንጋት የለብንም። ጋብቻን ማርከስ የአጋንንት ትምህርት መሆኑንም ሐዋርያው ጳውሎስ በ1ኛ ጢሞ.4:1-3 ላይ አስተምሮአል።  ከቁጥር 8-12:- የወንጌል አገልጋዮች በሚገለገሉት ምእመናን ሊረዱ ይገባቸዋል የሚለውን ሃሳብ በሰው ባህል ላይ ያም በገበሬና በወታደር ወግ ላይ ብቻ አልመሠረተም። ከመጽሐፍ ቅዱስም ማስረጃ ያቀርባል። “የሚያበራየውን በሬ አፉን አትሰር” ብሎ ሙሴ እንዳዘዘና ይህ ስለሰዎች እንደሚናገር ያስረዳል፤ (ዘዳ.25፡4)።  “እግዚአብሔር ስለ በሬዎች ይገደዋልን? ይህን የሚለው ፈጽሞ ስለእኛ አይደለምን?” ይህ አነጋገር እግዚአብሔር ለበሬዎች አያስብም ማለት ሳይሆን አነጋገሩ እንዲህ ነው፡፡ “እግዚአብሔር ለበሪዎች አስቦ ይህን ዓይነት ሕግ ካወጣ እኛም ሰዎች ከእንስሳት ስለምንበልጥ እንገዲያስ ሕጉ ከበሬዎች ይልቅ እኛን በበለጠ ይመለከተናል።» ይህን ከማቴዎስ 6፡25-30 ጋር አስተያይ።  ገበሬ የዘራውን ዓይነት ዋጋ መቀበል ከቻለ የወንጌል አገልጋዮች መንፈሳዊ ነገር ዘርተው ሥጋዊ ደመወዝ መቀበላቸው እንደትልቅ ነገር ሊገመት አይገባውም። ይኸውም ሲያንሳቸው ነውና እግዚአብሔር በመንፈሳዊ ክብር በሚመጣውም ዓለም ያከብራቸዋል።  ቁጥር 13 እና 14:- ይህን መብቱን ሐዋርያው አልተጠቀመበትም። ስለዚህ የቆሮንቶስም ክርስቲያኖች ለወንድማቸው ሲሉ ለጣዖት የተሠዋ ሥጋ የመብላት መብታቸውን መልቀቅ አለባቸው። ሐዋርያው የእርሱን መብት የለቀቀው «የክርስቶስ ወንጌል እንዳይከለከል» ስለሆነ እነርሱም ክርስቶስ ለሞተለት ወንድም ሲሉ መብታቸውን መልቀቅ መማር አለባቸው። ይህ የሚያስታብየው የእውቀትና የመብት እርምጃ ሳይሆን የፍቅር እርምጃ ነው።  በአምልኮት አገልግሎት የተሰማሩ ከቤተ መቅደስና ከመሠዊያው ለመካፈል መብት ያላቸው መሆኑን እንኳን ብሉይ ኪዳንን የሚያውቁ ቀርቶ በአህዛብ ወግ እንኳ የተጠበቀ ነበር። ይህንንም የቆሮንቶስ ሰዎች ጣዖት አምላኪዎች ስለነበሩ ያውቁታል። በአረመኔነታቸው ያከብሩት የነበረው አሁን ለክርስቶስ አገልጋዮች ሊነፈጋቸው አይገባም።  «የክርስቶስን ወንጌል እንዳንከለክል በሁሉ እንታገሣለን እንጂ በዚህ መብት አልተጠቀምንም።» ይህን ሲል ከቤተ ክርስቲያን ደመወዝ ቢቀበል ኖሮ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በእምነታቸው ደካሞች ከመሆናቸው የተነሣ «ጳውሎስ ወንጌልን የሚሰብከው ለደመወዙ ሲል ነው» በሚለው በተቃዋሚዎች ነቀፋ ይሰናከሉ ነበር። ስለዚህ የተቃዋሚዎችን አፍ ለማዘጋትና በዚህም የወንጌልን እንቅፋት ለማስወገድ ሐዋርያው በመብቱ አልተጠቀመም ነበር። ይህን በሁሉም ቦታ አላደረገም፤ ለምሳሌ ከፊልጵስዩስ ክርስቲያኖች እርዳታ ይቀበል ነበር። ስለዚህ ጉዳይ የሚከተሉትን ጥቅሶች አንብብ፤ 2ኛ ቆሮ.11:7-12።  ጥያቄ 20. ይህንን መብት በቤተ ክርስቲያንህ የሚጠቀሙበት እነማን ናቸው? የማይጠቀሙበትስ እነማን ናቸው? ለወንጌል ብለን መብታችንን ሳንጠቀምበት የምንሠራው ነገር ምንድነው? (ምንጭ፤ በትምህርተ መለኮት ማስፋፊያ (ትመማ) መልክ የተዘጋጀ ጽሑፍ፡- በቄስ ኃይሉ መኮንን)

የሐዋርያ መብት ( 1ኛ ቆሮ.9:1-14)  Read More »

ለጣዖት የተሠዋ ሥጋ (1ኛ ቆሮ.8:7-13) 

ጥያቄ 9. በቁጥር 7 ላይ በሁሉ ዘንድ አይገኝም የሚለው እውቀት ምን ዓይነት እውቀት ነው?  ጥያቄ 10. በቁጥር 9 ላይ የተጠቀሰው መብት ምንድነው?  ጥያቄ 11. በቁጥር 10 ላይ «ሕሊናው አይታነጽበትምን› ማለቱ ምን ማለቱ ነው?  ቁጥር 7:- «ይህ እውቀት በሁሉ ዘንድ የለም»። ጣዖት ከንቱ አንደሆነ ሁሉ ክርስቲያኖች አያውቁም። በቁጥር 1 ላይ «ሁላችን እናውቃለን» ካለው ጋር ይህ ንገገሩ ሊጋጭ አይገባም። በቁጥር 1 ላይ ይህ እውቀት በቆሮንቶስ ክርስቲያኖች መካከል ብቻ ሳይሆን በሁሉም አገር ክርስቲያኖች ዘንድ ይገኛል ማለቱ ሲሆን በቁጥር 7 ደግሞ ይህ እውቀት በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ባሉ በእያንዳንዳቸው ክርስቲያኖች ዘንድ አይገኝም ማለቱ ነው።  ጣዖት ከንቱ መሆኑን ስላልተገነዘቡና ጣዖትን ለብዙ ገዜ ከማምለክ የተነሣ አእምሮአቸው በጣዖት አምልኮ አስተሳሰብ ስለተጠምደ በጣዖት ነገር በቀላሉ ይረክሳሉ። ጣዖት ከንቱ ነገር መሆኑን የተገነዘበ ሰው ለጣዖት የተሠዋውን ቢበላ ምንም አይሆንም። ግን ጣዖት አንድ ኃይል አለው የሚል ልማድ ያለው ሰው ለጣዖት ከተሰዋው ሥጋ ቢበላ ሕሊናው ይረክሳል።  የሕሊና መርክስ ማለት ለጣዖት የተሠዋውን በሚበላበት ጊዜ ለጣዖት ኃይል መስጠት የለምደ ደካማ አእምሮ ስላለው የተከለከለ ጣዖትን ያመለከ በምስሎት ሕሊናው ይወቅሰዋል፡፡ ይህ የሕሊና ወቀሳ የሕሊና መርከስ ይባላል። ይህ እግዚአብሔርን ያስቀይመዋል እያለ ግን ደፍሮ ያን ሥራ ቢፈጽም በእውነትም እግዚአብሔርን ያስቀይማል። የሕሊና መርከስ እንግዲህ “በእምነት ያልሆነ ሁሉ ኃጢአት ነው” ከሚለው አስተሳሰብ ጋር ይወራረሳል፤ (ሮሜ 14:20): ጥያቄ 12. በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ በአንድ ነገር ላይ ይህ ተፈቅዷል፤ ይህ አልተፈቀደም ብለው በሃሳብ የሚለያዩ ሰዎች አሉን? ካሉስ የሚለያዩበት ሃሳብ ምንድነው? ጥያቄአቸው ከቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ጥያቄ ጋር ይመሳሰላል ወይስ ይለያያል?  ቁጥር 8፡- ጣዖት ከንቱ ስለሆነ ለጣዖት የተሠዋም በራሱ እንዲሁ ተራ ምግብ ከመሆን ሌላ ኃይል የለውም። ምግብም በሃይማኖት በኩል በራሱ ምንም ዋጋ የለውም። ሰው በመብል ወደ እግዚአብሔር ሊቀርብም ከእግዚአብሔር ሊርቅም አይችልም። “ብንበላም ባንበላም ምንም አይተርፈንም”።  ቁጥር 9፡- ስለምንበላው “ይህ እግዚአብሔርን ያስቀይም ይሆን?” አያሉ አለመጨነቅ ትልቅ የክርስቲያን ነፃነት ነው። ነገር ግን እውቀት የጎዳላቸው ክርስቲያኖች ይህን ነፃነት ገና አልተጎናጸፉም። በዚህም ምክንያት “ደካሞች” ተብለዋል። እንግዲህ መብል በራሱ ጉዳትም ጥቅምም ከሌለው፥ በመብልም ምክንያት ወንድም የሚሰናከል ከሆነ አለመብላትን በመምረጥ ነጻነታችንን በፍቅር ማሰር አለብን። ስለዚህ ማየት ያለብን ነፃነታችንን ብቻ ሳይሆን ያ ነፃነታችን በወንድማችን ላይ ሊያስከትል የሚችለውንም ጭምር መሆን አለበት። ይህም በእውቀት ሳይሆን በፍቅር መመላለስ ማለት ነው። «እውቀት ያስታብያል ፍቅር ግን ያንፃል።»  ቁጥር 10፡- በዚህ ቁጥር ላይ አንድ እውቀት ያለው ክርስቲያን እውቀቱን ያለ ፍቅር ሥራ ላይ ካዋለው የሚያደርሰውን በደል ሐዋርያው ይዘረዝራል፡፡ አንድ ሰው «ጣዖት ከንቱ ነው፤ ስለዚህ ለጣዖትም የተሠዋ አንዲሁ ተራ ምግብ ስለሆነ ብበላው ምንም አይጎዳኝም» ብሎ በጣዖት ቤት ቁጭ ብሎ ለጣዖት የተሰዋውን ሥጋ ይበላል። ነገር ግን ይህ እውቀት የሌለው ደካማ አማኝ ደግሞ ይህን አይቶ “አይ ይኸው እከሌ እንኳ በጣዖት ገበታ ይሳተፋል፤ ስለዚህ እኔም ልሳተፍ” ይልና ይሳተፋል፡፡ በቂ እውቀትም ስለሌለው «አይ ከጣዖት ማዕድ በመካፈሌ አምላክን አስቀየምሁ» አያለ የሕሊና ክስ ያስጨንቀዋል። ግን ደግሞ መልሶ «አይ ግድየለም እከሌስ በልቶ የለ?» እያለ በራሱ እምነት ሳይሆን ሰውን ብቻ በማየት በአምላኩ ፊት ይደፍራል፡፡ ይህ እንደዚህ ሕሊናውን መጣሱ እየተደጋገመ ሲመጣ ወደ ሌላም ኃጢአት በመንሸራተት በእምነቱ ይሰናከላል። ለዚህ ሁሉ  መነሻና የመሰናከያ አለት የሆነበት ያ ያለፍቅር በእውቀቱ የተመካው ክርስቲያን ወንድም ነው፡፡ «ሕሊናው አይታነጽበትምን?» ማለት ይህን ለጣዖት የተሠዋ ምግብ በእውቀት ሳይሆን በአምልኮት ለመብላት ይደፍራል ወይም ያን ለማድረግ ይገነባል ማለት ነው። የማይገባውን እርምጃ በድፍረትና በድንቁርና ይወስዳል፡፡ይህን ለማለት “ገነባ” የሚለው ቃል ተመራጭ አይደለም። ይህን ቃል ሐዋርያው የተጠቀመው ምናልባት በአሽሙር መልክ ሳይሆን አይቀርም። ምናልባት የቆሮንቶስ አማኞች ደካሞችን በእውቀት በመገንባት ሳይሆን በእርምጃ ለመገንባት ይሞክሩና የተባለውን ጉዳት በወንድማቸው ላይ አድርሰው ይሆናል። ስለዚህ ሐዋርያው በአጭር አነጋር «አዎ እንዲህ ወንድምህን እያሰናከልህ ትገነባዋለህ፤» ማለቱ ይሆናል።  ቁጥር 11-12:- ፍቅር በሌለው እውቀት ሰው እንዲህ ወንድሙን ሊጎዳ ይችላል። ይህም ወንድም ክርስቶስ የሞተለት ስለሆነ ይህን በደል ያደረሰው ሰው ሰውን ብቻ ሳይሆን ክርስቶስን እንደበደለ ይታያል፡፡ ስለዚህ ሰው እርምጃውን በእውቀት ሚዛን ላይ ብቻ ሳይሆን በፍቅር ሚዛንም ላይ ማስቀመጥ አለበት። ፍቅርም ለሰው ብቻ ሳይሆን ለክርስቶስም የተሰነዘረ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል።  ጥያቄ 13. በዚህ ዘመን በእውቀታችን ብቻ ሳይሆን በፍቅር ሚዛን ላይ መታየት ያለባቸው ነገሮች ምን ዓይነት ናቸው?  በዚህ ክፍል ውስጥ «ይጠፋል» የሚለው ቃል በግሪኩ የወደፊት ግሥ ሳይሆን የአሁን ግሥ ነው። ስለዚህ ጥፋቱ በዘላለም ኩነኔ ሳይሆን በአሁኑ ዘመን የሚደርስበትን ጉዳት ነው የሚያመለክተው፡፡ መጥፋት ማለትም በእምነቱ ተሰነካክሉ የክርስትና ሕይወቱ ይበላሻል ማለቱ ነው እንጂ የዘላለም ኩነኔ ይደርስበታል ማለቱ አይደለም። ሐዋርያው አንድ ክርስቲያን ከዳነ በኋላ የማይጠፋ የደህንነት ዋስትና እንዳለው አስተምሮአል (ፊልጵ.1:6)።  ቁጥር 13፡- ሐዋርያው ክርስቲያኖች ማድረግ ያለባቸውን እርሱም ሊያደርግ የተዘጋጀ መሆኑን ያውጃል። “ወንድሜን እንዳላሰናክል” ማለት የወንድሙን ሕሊና እንዳያረክስ ማለቱ ነው፡፡ እዚህ ላይ ማሰናከል የሚለውን ቃል “ማስቀየም” ወይም “ቅር ማሰኘት” ከሚለው ሃሳብ ጋር ማደባለቅ የለብንም። በወንጌል እምነት የሌሉ ሰዎች ክርስቲያኖች በሚያደርጓቸው አንዳንድ ነገሮች ቅር መሰኘታቸው ወይም መቀየማቸው አይቀርም። ቃሉን በደንብ እንገንዘበው፡፡ 1ኛ / «ወንድምህን» ነው የሚለው፤ 2ኛ / ደካማን ወንድም ወደ ሕሊና ማርከስ አንምራ ነው እንጂ የሚለው በወንጌል ብርሃን መራመድ በማይፈልጉ ሰዎች ድንቁርና ታሰሩ አይደለም የሚለው።  ጥያቂ 14. ላላመኑት የምናሳየው የሕይወታችን ምስክርነት እና የደካማውን አማኝ ሕሊና መጠበቅ በምን ይመሳሰላል? በምንስ ይለያያል? (ምንጭ፤ በትምህርተ መለኮት ማስፋፊያ (ትመማ) መልክ የተዘጋጀ ጽሑፍ፡- በቄስ ኃይሉ መኮንን)

ለጣዖት የተሠዋ ሥጋ (1ኛ ቆሮ.8:7-13)  Read More »

ለጣዖት የተሠዋ ሥጋ (1ኛ ቆሮ.8፡1-6)

በመጀመሪያው መቶ ዓመት ይኖሩ ለነበሩ ክርስቲያኖች የጣዖት ጉዳይ ከባድ ችግር ያስከተለ ነበር፡፡ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ሐዋርያውን ከጠየቁት ጥያቄዎች አንዱ ስለ ጣዖት ነበር። ስለ ጋብቻ ለጠየቁት ጥያቄ በቂ መልስ ከሰጠ በኋላ አሁን ወደ ሁለተኛው ጥያቄያቸው ዘወር ይላል።  ለእነዚህ ክርስቲያኖች ለጣዖት የተሠዋ ሥጋ በሁለት መንገድ ችግር አስከትሉባቸው ነበር፡፡ አንደኛው በየሄዱበት ግብዣ ያጋጥማቸዋል። ይህንንም ግብዣ የሕብረተሰቡ አባል የሆነ ሁሉ መካፈል ነበረበት። ካልተካፈሉ ከሕብረተሰቡ ጋር ከባድ የቅያሜ ግጭት ይደርስባቸው ነበር፡፡  ሁለተኛው ችግር በሥጋ ገበያ ሄደው የሚገዙት ሥጋ አስቀድዋ ለጣዖት የተሠዋ ነበር፡፡ እንደልማዳቸው የሕብረተሰቡ አባሎች ለጣዖት ከሠዉ በኋላ ሲሦው (⅓) ሊሰግዱ ለመጡት ይታደላል፤ ሲሦው ለካህኑ ይሰጣል። ካህኑ የተሰጠውን ስለማይጨርሰው የተረፈውን ገበያ አውጥቶ ይሸጣል። እንግዲህ በገበያ ያለው ሥጋ አስቀድሞ ለጣዖት ተሠውቶ ነበር ማለት ነው።  ለዚህ ችግራቸው መፍትሄ እንዲነገራቸው ሐዋርያውን ይጠይቁታል። በእነዚህ ምዕራፎች ውስጥ ያለው ውይይት ይህን ጥያቄ በመመርኮዝ ነበር፡፡ 1ኛ ቆሮ.4፡1-6ን ካነበብህ በኋላ የሚከተሉትን ጥያቄዎች መልስ።  ጥያቄ 3. በቁጥር 1 ላይ አለን የሚለው እውቀት ምን ዓይነት እውቀት ነው?  ጥያቄ 4. ጣዖት ከንቱ ከሆነ ለጣዖት የተሠዋ ሥጋስ?  ጥያቄ 5. በቁጥር 6 ላይ እንደተጠቀሰው በአብና በወልድ መካከል ያለውን ዝምድና ሰፋ ባለ አነጋገር ግለጽ።  ቁጥር 1:- ለጣዖት ስለተሠዋ ሥጋ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች እውቀት ያላቸው መሆኑን ገልጸውለት ባላቸውም እውቀት የተመኩ ይመስላል። “ለጣዖት ስለተሠዋ ሥጋ ሁላችን እውቀት አለን” በማለት ስለዚህ ነገር እውቀት ያላቸው እነርሱ ብቻ እንዳልሆኑም ይገልጽላቸዋል። ይህ እውቀት ምን እንደሆነ ዝቅ ብሎ ይዘረዝራል፤ (ቁጥር 4)።  አለን የተባለው የእውቀት ፍሬ ነገር ይህ ነው፤ አንድ አምላክ ብቻ ስላለ ጣዖት አምላክ አይዳለም፤ እንዲሁ ከንቱ ነገር ነው። ከንቱ ነገርም ስለሆነ ሰው በዚህ ነገር መጨነቅ አይገባውም። ስለዚህ ሰው ለከንቱ ነገር የተሠዋውን ቢበላ ምንም ጉዳት የለበትም እያሉ ነገሩን ይህን በመሰለ ግምገማ ውስጥ አስቀምጠውት ነበር።  ቁጥር 2፡- ሆኖም በዚህ ግምገማቸው ላይ የዘነጉት ነገር እንዳለ ያስረዳቸዋል። ያም የዘነጉት ነገር ፍቅር ነው። «እውቀት ያስታብያል ፍቅር ግን ያንጻል»። ይህም ማለት ሰው እውቀት አለኝ ብሎ እውቀቱ የመሪውን ነገር ሁሉ ማድረግ አይገባውም። ያ የሚወስደው እርምጃ በሌሎች ላይ ምን ያስከትላል ብሉ ማመዛዘን ይኖርበታል፡፡ ካላመዛዘን ግን በእውቀቱ ትዕቢት አድሮበታል፤ ሥራውም ቤተ ክርስቲያንን የሚገነባ ሳይሆን የሚያፈርሳት ሆኖ ይገኛል።  ቤተ ክርስቲያንን በማይገነባትና በሚያፈርሳት ሥራ መሠማራት አደገኛ እንደሆነ ሐዋርያው ቀደም ሲል ተናግሮአል ( 1ኛ ቆሮ.3፡17)። ነገር ግን ሰው በእውቀት ታብዮ ሳይሆን በፍቅር ተመርቶ ሲራመድ ቤተ ክርስቲያንን ይገነባል፤ «ፍቅር ግን ያንፃል።»  ከዚህ በላይ ምንም እንኳ ሰው ብዙ እውቀት ያለው ቢሆንም ሊታወቅ የሚገባውን ገና አላወቀም፤ ሊያውቅም አይችልም። ስለዚህ የሰው እውቀት ሁልጊዜ ጎዶሎ ስለሆነ በእውቀቱ ላይ መደገፍ የለበትም። የቆሮንቶስ ሰዎች ያላቸው እውቀት በቂ አለመሆኑን ተገንዝበው በትህትናና በፍቅር መራመድ ይኖርባቸዋል፡፡ ትህትናና ፍቅር የሌለበት የእውቀት ምንጭ ከዲያብሎስ አንጂ ከእግዚአብሔር አይደለምና እውቀትን እንዴት እንደምንጠቀምበት ጥንቃቄ እናድግ፤ (ያዕ.3፡15)።  ጥያቄ 6. የዛሬ ዘመን አማኞች በፍቅር ሳይሆን በእውቀት ብቻ ሲሠሩ የምናየው እንዴት ነው? በምሳሌ ግለጽ።  ቁጥር 3፡- የፍቅር መጀመሪያው እግዚአብሔርን ማፍቀር ነው። እግዚአብሔርን ከምውደድ አንፃር እግዚአብሔር የወደዳቸውንም መውደድ እንችላለን፤ (1ኛ ዮሐ.4:20 እና 21)፡፡ የእውቀትም ጉዳይ በእግዚአብሔር መታወቅ ነው። ስለዚህ ሰው ስለ ራሱ ደስ መሰኘት ከወደደ በእግዚአብሔር በመታወቁ ብቻ ሊደሰት ይገባዋል፤ (ሉቃ. 10፡20-22)።  በእግዚአብሔር መታወቅ ማለት ምን ማለት ነው? ከላይ ከሉቃስ ወንጌል እንዳገኘነው የእያንዳንዱ ክርስቲያን ስም በእግዚአብሔር መዝገብ ስለሰፈረ በእግዚአብሔር ታውቋል። ይህም እውቀት የሚንከባከብና የእኔ ነህ የሚል ፍቅር ነው። ቅዱስ ዳዊት ስለዚህ እውቀት ሲጽፍ እንዲህ ይላል፤ «እግዚአብሔር የጻድቃንን መንገድ ያውቃል፤ የኃጢዕን መንገድ ግን ትጠፋለች፤» (መዝ.22፡(23):6)።  ቁጥር 4፡- ስለ ጣዖት አለን የተባለውን እውቀት ይጠቅሳል። ጣዖት ከንቱ እንደሆነ እናውቃለን። ከአንዱ አምላክ በስተቀር ሌላ አምላክ የለም።  ቁጥር 5-6፡- ምንም እንኳ ሰዎች የተለያዩ ነገሮችን አምላክና ጌታ አድርገው ቢሰግዱላቸውና ቢያገለግሏቸውም እኛ ግን አንድ አምላክ ብቻ እንዳለን እናውቃለን። ሌሎቹ ግን ከንቱ ነገሮች ብቻ ናቸው።  ጥያቄ 7. በዛሬ ዘመን አንዳንድ ሰዎች ከእግዚአብሔር ሌላ አምላክ የሚያደርጉት ነገር ምንድነው? ለእኛስ ነገር ሁሉ ከእርሱ የሆነ እኛም ለእርሱ የሆንን አንድ አምላክ አብ አለን። ሁሉ ነገር ከአብ የመነጨ ነው፡፡ከዚያም ቀጥሎ “ነገር ሁሉ በእርሱ በኩል የሆነ እኛ በእርሱ በኩል የሆንን አንድ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አለን”፡፡ በማለት በአብና በወልድ መካከል ያለውን ዝምድና ይገልፃል። ሁሉ ነገር ከአብ ሲሆን፥ ሁሉ ነገር ደግሞ በወልድ በኩል (ወይም አማካይነት) ነው፡፡ ይህም ማለት እግዚአብሔር አብ ሥራውን ሁሉ (የመፍጠርንም የማዳንን ሥራ) የሠራው በእግዚአብሔር ወልድ በኩል ነው ማለት ነው።  ጥያቄ 8. ይህንን እውነት የሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን ነን ለሚሉት እንዴት አንድንመልሳቸው ልንጠቀምበት እንችላለን? (ምንጭ፤ በትምህርተ መለኮት ማስፋፊያ (ትመማ) መልክ የተዘጋጀ ጽሑፍ፡- በቄስ ኃይሉ መኮንን)

ለጣዖት የተሠዋ ሥጋ (1ኛ ቆሮ.8፡1-6) Read More »

ዳግመኛ ለማግባት የሚፈቀደው መቼ ነው? (1ኛ ቆሮ. 7:36-40)

ጥያቄ 1. ዳግመኛ ለማግባት የሚፈቀደው መቼ ነው? (ቁጥር 39ና 40፤ 1ኛ ቆሮ.1:15፤ ማቴ.5፡32)  ቁጥር 36 የተለያየ ትርጉም የተሰጠው ከባድ ጥቅስ ነው። በዚህ ላይ ባደረገሁት ጥናት መሠረት የሚመስለኝን ትርጉም አቅርቤአለሁ፤ ነገር ግን ሙሉ በሙሉ አጥጋቢ የሆነ ትርጉም አላገኘሁም።  አሁን ያለውን የአማርኛውን ትርጉም ቃል በቃል ከግሪኩ ከተተረጎመው ጋር እናስተያየው። ከግሪኩ ቃል በቃል ሲተረጕም እንዲህ ይላል፡- ነገር ግን ሰው የእርሱ ስለሆነችው ድንግል የማይገባውን እንዳደረገ ቢያስብ፥ ድንግሊቱም በዕድሜ እየገፋች ብትሄድ፥ እንዲሁም ለማድረግ ግዴታ ቢኖርበት፥ የሚወደውን የድርግ፤ ኃጢአትን አይሠራም ይጋቡ።  እንግዲህ በዚህ መሠረት ሁለት አተረጓጕሞች ይገኛሉ፤ አንደኛው የተጠቀሰው ሰው የድንግሊቱ አባት ሲሆን ሁለተኛው አማራጭ ደግሞ የተጠቀሰው ሰው የድንግሊቱ እጮኛ ነው። አባቷ ነው የሚሉ ይጋቡ የሚለው ገሥ መተርጉም ያለበት «ያጋባቸው» ብሎ ነው ይላሉ።  የሁለተኛውን አተረጓጉም የሚደግፉ ደግሞ እንዲህ ይላሉ፤ ምንም እንኳ ግሡ ያጋባቸው የሚል ትርጉም ቢኖረውም በዚህ ጥቅስ ላይ ተስማሚው አተረጓጎም ይጋቡ የሚለው ነው ይላሉ። በተጨማሪም በነጠላ ቁጥር ሆኖ ያጋባቸው ሳይሆን በብዙ ቁጥር የተነገረ ስለሆነ «ይጋቡ» ተብሎ መተርጎም አለበት፤ ያም እጮኛሞቹን ነው የሚያመለክተው ይላሉ።  የመጀመሪያው አተረጓጎም ይመረጣል፤ የሚከተሉትም ምክንያቶች ይህንኑ ያረጋግጣሉ።  1ኛ/ ለወጣቶቹ በእጮኝነት መዋዋል በዚያን ጊዜ ባህላቸው አይፈቅድም፤ ነገር ግን አባት ድንግል ሴት ልጁን በጋብቻ መስጠት የተለመደ ነበር። ስለዚህ የጥቅሱ ሃሳብ ይህ ነው፤ አንድ አባት ሴት ልጁን ለጋብቻ ባለመስጠቱ የማይገባውን እንዳደረገ ቢመስለው ያጋባት»፡፡  2ኛ/ በግሪክ ቋንቋ «የእርሱ የሆነችው ድንግሊት» የሚለው አነጋገር ለእጮኛ አይውልም፤ ለአባት ግን ይውላል።  3ኛ/ እጮኛ ብትሆን ኖሮ እጮኛዋ ላለማግባት ከወሰነ ለምን እንደ በደል ይቆጠራል? የማይገባስ ለምን ይሆናል? አላገባም ብሎ ከተዋት አሁን የርሱ አይደለችም። አባት ከሆነ ግን ጋብቻን ከከለከላት «ይህችን ልጅ በደልኳት» ብሉ ትክክለኛ ነገር ማድረግ አለማድረጉ ሊያጠራጥረው ይችላል።  ስለዚህ የጥቅሱ ጠቅላላ አነጋገር ይህ ነው፤ አንድ አባት ወጣት ልጃገረድ ልጅ ኖራው እንዳታገባ አስጠብቋት የማግቢያ ወቅቷ ሲተላልፍባት አይቶ የማይገባውን ያዳረገ ቢመስለውና እንዲያጋባት ገድ ቢሆንበት ለጋብቻ ቢሰጣት ኃጢአት አያደርግም፤ የቀረበላት እጮኛና እርሷ ይጋቡ።  ቁጥር 37:- አሁንም የግሪኩን ቃል በቃል መተርጎም አለብን፤ የአማርኛ ትርጉማችን በቂ አይደለም፡፡ ግን በራሱ ልብ ጸንቶ የቆመ፥ ግዴታ ከሌለበትና፥ በራሱ የመወሰን መብት ካለው፥ የራሱም የሆነችውን ድንግል በድንግልና ለመጠበቅ በራሱ ልብ ወስኖ ከሆነ መልካም አደረገ።  እንግዲህ የጥቅሱ ሃሳብ፥ ይህ አባት ልጃገረድ ልጁን በድንግልና እንድትኖር በራሱ ሳይጠራጠር የወሰነና ይህን ለመወሰን መብት ካለው (የሰው ተገዥ ባሪያ ካልሆነ ወይም አንድ ዓይነት ግዳጅ ከሌለበት ማለት ውል መሳይ ነገር ባያስገድደው) መልካም አጸረገ።  ቁጥር 38፡- ይህ ቁጥር ቃል በቃል ከግሪኩ ሲተረጕም ይህን ይመስላል፤ እንዲሁም ድንግሊቱን በጋብቻ የሰጠ መልካም አደረገ፤ በጋብቻ ያልሰጣትም የተሻለ አደረገ።  ቁጥር 39 እና 40፡- ሰው ዳግመኛ ማግባት የተፈቀደላት ሚስቱ ከሞተች ነው። የጳውሎስ ምክር ግን ያው ከላይ በተዘረዘረው ምክንያት ሳታገባ ብትኖር የተሻለ መሆኑን ይናገራል።  በ1ኛ ቆሮ.7:15 ላይ ደግሞ የማታምነው ከተለየች፣ አማኙ በጋብቻው ያልታሰረ መሆኑን ስለገለጠ እንግዲያስ ዳግመኛ ለማግባትም ተፈቅዷል ማለት ነው። ባሏን ትታ እንደሄደችው አማኝ (ቁጥር 10ና 11) በጋብቻው ስላልታሰረ ሳያገባ እንዲኖር ገዴታ የለበትም፤ «ወንድም ቢሆን ወይም እህት እንዲህ በሚመስል ነገር አይገዙም»። ስለዚህ የማታምን ሚስቱ ጥላው ከሄደች ዳግመኛ የማግባት መብት ስላለው ይህ ዳግመኛ ለማግባት ሁለተኛው የተፈቀደ መንገድ ነው፡፡ ይህ መደረግ ያለበት የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎች አይተውት አማኙ በደለኛ አለመሆኑን ቤተ ክርስቲያን ስትመሰክር ብቻ እንጂ በግል መደረግ ያለበትም። እንደዚህ ከሆነ አማኝ ሚስቱን በግፍ ሊበድላት እንደሚችል መጠራጠር የለብንም።  ጋብቻ ፈርሶ ሌላ ማግባት የሚፈቀድበት ሌላ አንድ ተጨማሪ ምክንያት አለ፤ ያም ዝሙት ነው። ማቴ.5፡32 እና 19፡9። ያለ ዝሙት ምክንያት ሚስቱን ፈትቶ ሌላ ማግባት ስለተከለከለ፣ እንግዲያስ በዝሙት ምክንያት ሚስትን ፈትቶ ሌላ ማግባት ተፈቅዷል ማለት ነው። በዚህ መንገድ ሰው በግሉ ሳይሆን ነገሩ በቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎች ተጠንቶ መረጋገጥ አለበት። ሚስቴ አመንዝራለች ወይም ባሌ አመንዝሮአል በማለት ጋብቻን በግል ማፍረስ ከጌታ ሥርዓት ውጭ መሆን ስለሆነ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። ዝሙት መፈጸሙ እንኳ ቢረጋገጥም በንስሐና በይቅርታ ጋብቻ እንዲጸና ለማድረግ ከፍቺው በፊት ጥብቅ ሙከራ መደረግ አለበት።  ጥያቄ 2. ያንተ ቤተ ክርስቲያን ስለ ፍቺና ስለ ጋብቻ የምታስተምረው ምንድን ነው? እንዴት ነው ከዚህ ትርጓሜ ጋር የሚመሳሰለው? የሚለያየውስ አንዴት ነው? (ምንጭ፤ በትምህርተ መለኮት ማስፋፊያ (ትመማ) መልክ የተዘጋጀ ጽሑፍ፡- በቄስ ኃይሉ መኮንን)

ዳግመኛ ለማግባት የሚፈቀደው መቼ ነው? (1ኛ ቆሮ. 7:36-40) Read More »

1ኛ ቆሮ. 7:25–35

መግቢያ  ሐዋርያው በዚህ ክፍል ውስጥ አለማግባት ለምን ከማገባት እንደሚሻል ሁለት ምክንያቶችን በመስጠት ያስተምራል። እነዚህ ምክንያቶች:- 1ኛ/ በአሁኑ ዘመን ስደት ስላለ በጋብቻ ውስጥ ያሉ በስደት ጊዜ ውስጥ ካላገቡት የበለጠ ስደቱ ይከብዳቸዋል፤ (ቁጥር 28)። 2ኛ/ ጌታን በአንድ ልብ ለማገልገል አለማግባት ከማግባት ይሻል! (ቁጥር 32-33)። ሆኖም ግን አለማግባት ራስን የመግዛት ጸጋ ለተሰጣቸው ብቻ እንጂ ለሁሉ አይሆንም። ይህ ጸጋ ያልተሰጣቸው ባያገቡ ሐዋርያው እንዳላው በስሜት ወደ መቃጠል ይወድቃሉ። እንደዚያ እንዳይሆን ካለማግባት ማገባት ይሻላል፤ (7:1-2)።  ጥያቀ 18. በቁጥር 25 ላይ «የጌታ ትእዛዝ የለኝም» ሲል ምን ማለቱ ነው?  ጥያቄ 19. በቁጥር 28 ላይ «እንዲህ በሚያደርጉ ላይ በሥጋቸው መከራ ይበዛባቸዋል» ሲል ምን ማለቱ እንደሆነ አብራራ። ጥያቄ 20. አለማግባት ከማግባት የተሻለ መሆኑን በሁለት ምክንያቶች ይደግፋል፤ እነዚህን ምክንያቶች ጥቀስ፤ (ቁጥር 29-35)።  ቁጥር 25 «ስለደናግልም የጌታ ትእዛዝ የለኝም» እንደበፊተኛው (ቁጥር 10 እና 11 ጌታ ያስተማረው በወንጌል እንደተጠቀሰው የለኝም ማለቱ ነው እንጂ መንፈስ ቅዱስ ይህንን እንዲናገር አልመራውም ማለት አይደለም። እንዲያውም በቁጥር 40 ላይ ይህን ሲያስተምር የእግዚአብሔር መንፈስ እየመራው እንደሆነ ይናገራል።  «ምክር እመክራለሁ»፡፡ በዚህ ክፍል ውስጥ የሚያስተምራቸው እንደ ትእዛዝ ሳይሆኑ በምርጫ የሚደረጉ ምክሮች ናቸው። ሰው የሚወስደውን የእርምጃውን ውጤት አውቆ ባለው ነፃነት እንዲወስን ሐዋርያው ስለደናግል ጋብቻ ምክር ይሰጣል። የማግባትንም ያለማገባትን ውጤት በየመሥመሩ በማስቀመጥ ውሣኔው የምእመኑ እንደሆነ ያስተምራል። በተጨማሪ ይህ ትምህርት ምእምንን «ምነው ባላገባሁ ኖሮ» ወይም ያላገባው «ምነው ባገባሁ» እያለ ያለበትን ሁኔታ እንዳያማርር ይመክራል፤ (ቁጥር 27)።  ማግባት ወይም አለማግባት የግል ምርጫ ጉዳይ ወይም ለእያንዳንዱ እግዚአብሔር እንደሰጠው በነፃነት የሚወሰድ እርምጃ ነው እንጂ የኃጢአትና የጽድቅ ጉዳይ አይደለም። ማግባትዎ አለማግባትም ተፈቅዷል (ቁጥር 28)። እንዲያውም ጋብቻን መከልከል የዲያብሎስ ትምህርት እንደሆነ ሐዋርያው በሌላ ቦታ ያወግዛል፤ ( 1ኛጢሞ.4:1 እና 2)።  ጥያቄ 21. ለምንድነው አንዳንድ የክርስቲያን ሃይማኖት ቡድኖች መሪዎቻቸው (ቄሶቹ) እንዲያገቡ የማይፈቅዱላቸው? ጠይቃቸውና ምክንያታቸውን ገልጽ፡፡ ከቁጥር 29-31:- በእዚህ ጥቅሶች ውስጥ ያለው ምክር በቁጥር 27 ካለው ምክር ጋር ይስማማል። ሰው በማግባቱ «ምነው ባላገባሁ ናሮ» ወይም ባለማግባቱ «ምነው ባገባሁ» ብሉ መጸጸትና የልብ ሰላም ማጣት የለበትም። ምክንያቱም ጋብቻ የዚህ ዓለም ኑሮ ጉዳይ ብቻ ስለሆነ አንድ ቀን እንዳልነበር የሚሆንበት ወቅት ይመጣል። ጋብቻ ብቻ ሳይሆን በጠቅላላው የአሁኑ ሥርዓት የሚሻርበት ወቅት ስለሚመጣ ክርስቲያን ባለው ተደስቶ በምስጋናና ራስን በመግዛት መኖር አለበት። ከዚህ ሃሳብ ጋር የዮሐንስ ራእይ 21:4ን ተመልከት።  ነገር ግን በጊዜው ችግር ምክንያት አለማግባት ይቀላል በማለት ሐዋርያው የራሱን ምክር ከርህራሄ አንፃር ይሰጣል፤ (ቁጥር 25 እና 32-35)፡፡ ሰው ካገባ ለራሱ ማሰብ ቀርቶ ለሚስቱና ለልጆቹ መጨነቅ ይጀምራል። ይህም በችግር ላይ ችግር ያስከትላል። ስለዚህ መላ ልቡን በጌታ አገልግሎት ላይ ማሰማራት ያስቸግረዋል። እንግዲያስ ሰው ከጋብቻ የሚቆጠበው ለራሱ ምቾትን ፍለጋ ሳይሆን ባልተከፋፈለ አእምሮ ጌታን ማገልገል እንዲችል መሆኑን መዘንጋት የለብንም። ሐዋርያው የራሱን ሕይወት ምሳሌ በማድረግ ሰው ባለማግባት ምን ያህል ለጌታ ሥራ በነፃነት እንደሚሰማራ ይናገራል። ስለዚህ ክማግባት ይልቅ አለማግባትን ይመርጣል።  ጥያቄ 22. ያላገባ ሰው በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሲኖር ብዙ ሰዎች እንዲያገባ ሊያስገድዱ የሚሞክሩት ከምን የተነሣ ነው? ይህ ትክክል ነው?  አሁንም ደግመን መገንዘብ ያለብን፡- 1ኛ / ጋብቻ ኃጢአት የለበትም። 2ኛ / አለማግባት የግል ጥቅምን ፍለጋ መሆን የለበትም፤ ለጌታ ሕይወትን የመሠዋት ጉዳይ ነው እንጂ፤ ማቴ. 19፡12ን እንመልከት። «ስለመንግሥተ ሰማያትም ራሳቸውን የሰለቡ ጃንደረቦች አሉ።» ይህም ማለት ራሳቸውን አንደ ስልብ ቆጥረው በነጠላ ኑሮ ጌታን የሚያገልግሉ ማለት ነው። «ያልተጋባች ሴትና ድንግል በሥጋም በነፍስም እንዲቀሱ የጌታን ነገር ያስባሉ፤ የተጋባች ግን ባሏን እንዴት ደስ እንድታሰኘው የዓለምን ነገር ታስባላች፤» (ቁጥር 34)።  ነገር ግን ይህን የመሥዋዕትነት ኑሮ መቀበል የሚችሉ ራስን መግዛት የተሰጣቸው ብቻ ናቸው እንጂ ሁሉም አይደሉም። ስለዚህ ሐዋርያው “በጠምዳችሁ ብዬ አይደለም” ይላል። «የቆጡን አወርድ ብላ የብብቷን ጣለች» ወይም «አተርፍ ባይ አጉዳይ» እንዳንሆን መጠንቀቅና በአቅማችን ማደር ይኖርብናል። (ምንጭ፤ በትምህርተ መለኮት ማስፋፊያ (ትመማ) መልክ የተዘጋጀ ጽሑፍ፡- በቄስ ኃይሉ መኮንን)

1ኛ ቆሮ. 7:25–35 Read More »

1ኛቆሮንቶስ 7:17-24

ማሳሰቢያ!  በዚህ የተሰጠውን ዝርዝር ጥናት ከመመልከትህ በፊት ቃሉን በራስህ በመመርመር ለቀረቡልህ ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት ሞክር።  ጥያቄ 15. በቁጥር 20 ላይ “እያንዳንዱ በተጠራበት መጠራት እንደዚሁ ይኑር» ሲል ሐዋርያው ምን ማለቱ ነው?  ጥያቄ 16. ባሪያዎች በባርነታቸው እንዳይጨነቁበት ባሉበት ሁኔታ እግዚአብሔርን እንዲያገለግሉ መክሮአቸው ሲያበቃ በቁጥር 23 ላይ «የሰው ባሪያዎች አትሁኑ» ማለቱ ምን ማለቱ ነው?  በዚህ ክፍል ውስጥ ሐዋርያው ስለ ጋብቻ ተወት አድርጎ ስል አጠቃለይ የክርስቲያን ኑር ይናገራል። በቁጥር 17 ላይ እያንዳንዱ ክርስቲያን ጌታን ሲቀበል በነበረው ኑሮ መቀጠል እንጂ ክርስቶስን ከተቀበለ በኋላ ኑሮውን ለመቀየር ክርስትና አያስገድደውም። መቀየር ያለበት የኃጢአት ኑሮን እንጂ የሥራ ስምሪትን መቀየር ግዴታ አይደለም። በማንኛውም ሥራ ብንሠማራ በዚያ ጌታን ማገልገል እንችላለን።  በሚከተሉት ጥቅሶች ውስጥ ሰው ይሰማራባቸው የነበሩትን አንዳንድ የሥራ መስኮች ምሳሌ ይሰጣል፡፡ እነርሱም ባርነትና ጌትነት ናቸው፤ (20-24)። «ባርያ ሆነህ ተጠርተህ እንደሆነ አይገድህም»። ይህም ማለት ባርነት የክርስቶስ አገልጋይ ከመሆን አይከለክልም ማለት ነው። ሆኖም ባርነትን የተመረጠ ኑሮ አድርገህ ተቀበለው ማለቱ አይደለም። ሰው በነጻነት ለመኖር መንገድ ካገኘ ነጻነቱን ይጕናጸፍ፤ ነገር ግን ነጻነት መጐናጸፍ ባይችል ነጻ እስከሚሆን ድረስ በባርነቱ የክርስቶስ አገልጋይ መሆን ይችላል።  እንዲህ በባርነቱ በክርስቶስ የማይደገፍ ሆኖ ነጻነት ስለሌለው ሁልጊዜ ተስፋ ቢስ በመሆን ቢኖር ለሰው ባሪያ መሆኑ የእግዚአብሔር ባሪያ ከመሆን ከልክሎታል ማለት ነው። ይህ ከሆነ የአግዚአብሔር ባሪያ መሆኑ ቀርቶ የሰው ባሪያ ሆነ ማለት ነው፤ «ባሪያ ሆኖ በጌታ የተጠራ የጌታ ነጻ ነውና፤» (ቁጥር 22)።  ችግር ሰውን እግዚአብሔርን ከማገልገል ሊከለክለው አይችልም። ምንም እንኳ ሰው ክፉ በሆነ ባርነት ቢያዝም በዚያ ውስጥ እንኳ በመንፈስ ነጻ የወጣ ነውና አገልግሎቱን ለእግዚአብሔር ሊያደርገው ይቻላል።  ይህ የሐዋርያው ትምህርት «መጽሐፍ ቅዱስ ባርነትን ይደግፍፋል» ለሚለው ጥራዝ ነጠቅ የነቀፋ አስተያየት መነሾ ሆኖአል። ነገር ግን እዚህ ላይ ሐዋርያው ነጻነትን አይቃወም «አርነት ልትወጣ ቢቻልህ ግን አርነትን ተቀበል፤» (ቁጥር 21)።  ሐዋርያው እዚህ ላይ ክርስቲያን በጭቆና ውስጥ ሳለ እንዴት ጭቆናን መቋቋም እንደሚችል መንፈሳዊ መምሪያ መስጠቱ ነው። በተጨማሪም ስለመገረዝና ስለአለመገረዝ ይናገራል፤ “ማንም ተገርዞ ሳለ ተጠርቶ እንደሆነ ወደ አለመገረዝ አይመለስ” (ቁጥር 18)። በሰው ልቦና ውስጥ ሁልጊዜ መጓጓት አለ። እግዚአብሔር በሰጠው ረክቶ በአእምሮ ሰላም እንደመቀመጥና እግዚአብሔርን አንደማገልገል ሁልጊዜ የሌለውን ነገር ወይም ያልሆነውን እያሰበ በማጉረምረም መኖር ለክርስቲያን አይገባውም። «እያንዳንዱ በተጠራበት እንዲሁ ሆኖ በእግዚአብሔር ዘንድ ይኑር፤» (ቁጥር 24)። እንደዚህ ሆኖ በመንፈስ ነጻ ሆኖ በምስጋና ለመኖር ክርስቲያን ከእግዚአብሔር ነጻነት ተሰጥቶታልና በሆነው ባልሆነው እያማረረ መበሳጨት የለበትም። ነገር ግን ክርስቲያን በተሰጠው የኑር ጥሪ በእግዚአብሔር ፊት በምስጋናና በድል መኖር አለበት።  ጥያቄ 17. ይህን ምክር በትምህርታቸው፥ በዘራቸው፥ በኑሮ ደረጃቸው፥ ወዘተ ለማይደሰቱ ሰዎች እንዴት አድርገን ነው እንዲገባቸው ማድረግ የምንችለው? (ምንጭ፤ በትምህርተ መለኮት ማስፋፊያ (ትመማ) መልክ የተዘጋጀ ጽሑፍ፡- በቄስ ኃይሉ መኮንን)

1ኛቆሮንቶስ 7:17-24 Read More »

ስለ ጋብቻ ምክር (1ኛቆሮ.7:1-16) 

ጥያቄ 8. በምን ዓይነት መንገድ ነው ይህ ትምህርት ዛሬ ላሉት ወጣቶች፥ ለተጋቡት፥ ወዘተ ጠቃሚ ሊሆን የሚችለው?  ጥያቄ 9. በቁጥር 1 ላይ «ከሴት ጋር አለመገናኘት ለሰው መልካም ነው» ሲል ሐዋርያው ምን ማለቱ ነው?  ጥያቁ 10. ዝሙትን ለማስወገድ ጋብቻ ተሰጥቷል በማለት ሐዋርያው ሲያስተምር የጋብቻ ዓላማ ለዚህ ብቻ ነው ማለት ነው? ለመልስህ ከመጽሐፍ ቅዱስ ማስረጃ ስጥ፡፡ ጥያቄ 11. በቁጥር 4 ላይ ባል በገዛ ሥጋው ላይ ሥልጣን የለውም» ሲል ምን ማለቱ ነው?  ጥያቄ 12. በቁጥር 6 ላይ “እንደፈቃድ እንጂ እንደ ትእዛዝ አልልም” ሲል ምን ማለቱ ነው?  ጥያቄ 13. ከቁጥር 10-15 ባለው ክፍል ወስጥ «አትለያይ»፥ «አይተዋት» ፥ «አትተወው»፥ «ቢለይ» እያለ ሲናገር ጋብቻንና መፋታትን በመመልከት ለእነዚህ ቃላት ትርጉም ስጥ።  ከዚህ በፊት እንደተጠቀሰው የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ሐዋርያውን ብዙ ጥያቄዎች ጠይቀውታል። ለመጀመሪያው ጥያቄአቸው በዚህ ክፍል መልስ መስጠት ይጀምራል።  ቁጥር 1 እና 2:- በባሕላቸው አለማግባት እንደ ትልቅ ጽድቅ ይቆጠር ስለነበር አለማግባት ወይም “ከሴት ጋር አለመገናኘት” መልካም ነው፤ ብሎ ሙሉ በሙሉ ሳይሆን በመጠኑ በሃሳቡ ይስማማል። ግን ሰው ይህን መልካም ነገር አገኛለሁ ብሎ ራሱን ባለመግዛት በዝሙት እንዳይጠመድ ያስጠነቅቃል።  ሰው እግዚአብሔር የሰጠውን መውጫ ንቆ ቢጠመድ በእግዚአብሔር ፍርድ ሥር ይወድቃል። ያለሚስት ለመኖር ሰው ራስን የመቆጣጠር ችሎታ ከእግዚአብሔር የተሰጠው መሆኑን ማጣራት አለበት፤ (ቁጥር 7 እና ማቴ.19፡11-12 ተመልከት)።  “ለራሱ ሚስት ትኑረው፤ ለራስዋ ባል ይኑራት” ሲል አንድ ወንድ ለአንድ ሴት እንጂ «ለራሱ ሚስቶች ይኑሩት» ባለማለት ከአንድ በላይ ማግባትን ይከለክላል።  ቁጥር 3-4:- «ሚስት በገዛ ሥጋዋ ላይ ሥልጣን የላትም፤ ባል በገዛ ሥጋው ላይ ሥልጣን የለውም»። ይህ አነጋገር በባልና ሚስት መካከል እኩልነት ያለ መሆኑን ያስገነዝበናል። ባል ሚስቱን የራሱ ስሜት ማርኪያ ዕቃ አድርጎ መጠቀም የለበትም። ነገር ግን ራሱን ለሚስቱ እርካታ እንደ አገልግሎት አድርጎ ማቅረብ እንዳለበት ይህ ሐዋርያዊ ቃል ያስተምረናል። ሚስትም ለባልዋ እንዲሁ በማድረግ በጋብቻቸው መተሳሰብን ማሳየት አለባቸው።  ጥያቄ 14. ይህ ነገር እንዴት ነው ዛሪ ስለ ባልና ሚስት ካለው ሃሳብና ባሕል ጋር ሊቃረን የሚችለው?  ቁጥር 5፡- “እግዚአብሔርን አገለግላለሁ” ብሉ ሰው ሚስቱን ቢተው አገልግሎቱ በአግዚአብሔር ፊት ተቀባይነት አይኖረውም። በቃሉ የነገረንን ትእዛዝ በመናቅ እግዚአብሔርን ማገልገል አንችልም። በዚህ ላይ ሐዋርያው ባልና ሚስት መለያየት እንደሌለባቸው ያዛል። መለየት የተፈቀደው ለጾምና ለጸሎት ብቻ ያውም በስምምነትና ለአጭር ጊዜ ብቻ መሆኑን ማስተዋል አለብን። ባልየው ወይም ሚስትየዋ ያሰቡት ሃሳብ ሌላውን ቅር ካሰኘ ሃሳቡ መሰረዝ አለበት።  «ሰይጣን እንዳይፈታተናችሁ» በማለት ሐዋርያው ስለመለያየት ወይም ስለመከላከል ይናገራል። ባል ወይም ሚስት በሆነው ምክንያት እርስ በርስ ቢከለከሉ፥ የተከለከለው ወገን በሰይጣን ፈተና ቢወድቅ የወደቀውም፥ በመከልከል ፈተናውን ያስከተለውም በእግዚአብሔር ፊት ጥፋተኛ ናቸው። ስለዚህ ከላይ በቁጥር 3 እና 4 ላይ የተሰጠውን መምሪያ ባልና ሚስት በጥንቃቄ መከተል አለባቸው።  ቁጥር 6፡- ሐዋርያው ለጾምና ለጸሎት እርስ በርስ መለያየት እንደሚችሉ በቁጥር 5 ላይ ተናግርአል። ይህን ንግግሩን በፈቃዳቸው እንጂ ነገሩን አንደ ትእዛዝ ቆጥረው መጾምና መጸለይ ስላለብን መለያየት አለብን» ብለው የግዴታ እርምጃ መውሰድ እንዳይጀምሩ ቁጥር 6ን ጨምሮ ይጽፋል።  ቁጥር 7ን ከላይ ቁጥር 2ን ስንዘረዝር ጠቅሰነዋል። ሳያገቡ በንጽሕና መኖር ለሁሉ ያልተሰጠ መሆኑን ያስጠነቅቃል። እርሱ ራሱም ይህ ሳያገቡ በንጽሕና የመኖር ስጦታ እንደተሰጠው ይመሰክራል።  ከቁጥር 8-9፡- በዚህ ክፍል ውስጥ ሐዋርያው ላላገቡና ለመበለቶች ምክር ይሰጣል። ሳያገቡ መኖር ተመራጭ ለመሆኑ ጌታችንም በወንጌል ተናግሯል፤ ነገር ግን ይህ ለተሰጣቸው እንጂ ለሁሉ ስላልሆነ ሰው ባለማግባት ራሱን በፈተና ላይ መጣል የለበትም። ማግባት አለበት። ይህ ትምህርት በወንጌል ጌታችን እንዳስተማረው ስለተጠቀሰ ሐዋርያው «እኔ ግን አላዝም ጌታ እንጂ» ይላል። ይህን ሲል በሐዋርያነቱ ለክርስቲያኖች ትእዛዝ ለመስጠት መብት የለውም ማለት አይደለም።  ቁጥር 10 እና 1 1:- ባልና ሚስት መለያየት የለባቸውም። መለያየት ቢመርጡ ግን ሳያገቡ በነጠላ ኑሮ መኖር አለባቸው። «ሚስትም ከባልዋ አትለያይ፤ ባልም ሚስቱን አይተዋት።» ይህ ትእዛዝ ሁለቱም ክርስቲያኖች ለሆኑ ነው የተሰጠው፡፡ ሐዋርያው ይህ ትእዛዝ በጌታችን የተሰጠ መሆኑን ይናገራል። የጌታም ትምህርት በወንጌል ውስጥ ተጽፎ ይገኛል፤ (ማቴ. 5፡32፤ 19፡3-9)። እንግዲህ በዚህ ላይ የምንመለከተው ጋብቻን መተው አንድ ራሱን የቻለ በደል ነው፤ «ሚስትም ከባልዋ አትለያይ፤ ባልም ሚስቱን አይተዋት።» ግን ከዚህ የበለጠው ሁለተኛው ደረጃ በደል አለ፤ ያም እንቢ ብሉ ከተለያዩ በኋላ ሌላ ማገባት ነው። ይህንንም ሐዋርያው «ብትለያይ ግን ሳታገባ ትኑር ወይም ከባልዋ ትታረቅ » ብሎ ይከለክላል።  ስለመፋታት ሊነገር ያለውን ሁሉ ሐዋርያው እዚህ አይዘረዝረውም። ለምሳሌ ጌታችን «ያለ ዝሙት ምክንያት ሚስቱን የሚፈታ» ያለውን ሐዋርያው አይጠቅስም። ያልጠቀሰበትም ምክንያት እዚህ የሚናገረው የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች የጠየቁትን ለመመላስ ብቻ እንጂ ስለ ጋብቻ ዝርዝር ትምህርት ለመስጠት ስላልሆነ ነው። እኛ ግን ያንንም ጨምረን ማየት አለብን።  ከቁጥር 12-16፡- የተቀላቀለ ጋብቻ ማለት ባል ወይም ሚስት ሳያምኑ ሲቀሩ ነው። በመጀመሪያው ሁለቱም አማኞች ሳይሆኑ በኋላ ግን አንደኛው በወንጌል ካመነ ማለቱ ነው እንጂ ክርስቲያን ያላመነችውን በማግባት የተቀላቀለ ጋብቻ ማለቱ ይደለም።  እንዲህ ባለ ጋብቻ ውስጥ የማያምነው ወይም የማታምነው ለመለየት ብትፈልገ አማኝ መጨነቅ የለበትም። “ወንድም ቢሆን ወይም እህት እንዲህ በሚመስል ነገር አይገዙም።” አይገዙም ማለቱ አይታሰሩም፥ ነፃ ናቸው ማለቱ ነው። ይህ ከሆነ አማኙ ሌላ ለማግባት እንደተፈቀደለት እንገነዘባለን። ያም በጌታ የሆነ ጋብቻን ለመመስረት እድል ስለሚሰጥ የማያምን ባለማግባት ዳግምኛ በተመሳሳይ ወጥመድ መውደቅ የለበትም። ይሁን እንጂ አማኝ ለጋብቻው መፍረስ ምክንያት መሆን የለበትም። «ያላመነች ሚስት ከእርሱ ጋር ልትቀመጥ ብትስማማ አይተዋት።» አማኝ “አሁን እኔ አማኝ ነኝ አንቺ ግን አታምኚም፤ ስለዚህ ከአንቺ ጋር በጋብቻ ታስሬ መኖር አልፈልግም” ሊል አይገባውም። እንዲህ ታግሶ መኖር ምናልባት የማያምነውን ወገን ወደ እምነት ሊያመጣ ይችል ይሆናል፤ «አንቺ ሴት ባልሽን ታድኚ እንደሆንስ ምን ታውቂያለሽ?»።  ምናልባት ከማያምን ጋር በጋብቻ ታስሮ መኖር አማኝን የሚያረክስ መስሉ ታይቷቸው ሳይሆን አይቀርም፤ ምክንያቱም ሐዋርያው «ያላመነ ባል በሚስቱ ተቀድሷልና» ይላል። ይህ ዓይነቱ አስተሳሰብ፥ አማኝ ከማያምን መለየት አሁንም በአንዳንዶች ዘንድ እንደሚገኝ ይሰማል። ማንም በመንፈስ ቅዱስ ተመራሁ ብሎ ይህንን የሐዋርያውን ቃል በመናቅ ከማታምን ሚስቱ መለየት የለበትም። ይህ ከፈሪሳውያን የበለጠ ግብዝነትና የዲያብሎስ ትምህርት እንጂ የመንፈስ ቅዱስ ትምህርት አይደለም። አማኝ ከማያምን ባሏ ጋር በጋብቻ ብትኖር የእርሷ ቅድስና እሱን ይባርከዋል እንጂ የእርሱ አለማመን እሷን አያረክሳትም።  ይህ የመቀደስ አነጋገር ከአማኝ ልጆች ቅድስና አንፃር የተነገረ ነው። «ልጆቻችሁ የተቀደሱ ናቸው»። የአማኝ ልጆች በወላጆቻቸው እምነት ምክንያት የእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ወራሾች በመሆናቸው መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል፤ (ዘፍ.17:7)። ስለሆነም እንደ ክርስቲያን በጌታ ትምህርትና ተግሣጽ ሊኮተኮቱ ይገባቸዋል፤ (ኤፌ. 6፡4)፡፡ ሆኖም ይህ ማለት ክርስትና በዘር ይተላለፋል ማለት አይደለም። የአማኝ ልጅ ራሱ ጌታን በግሉ ካልተቀበለ የወላጆቹ እምነት አያድነውም፤ (ሕዝ. 18፡10-13)፡፡ (ምንጭ፤ በትምህርተ መለኮት ማስፋፊያ (ትመማ) መልክ የተዘጋጀ ጽሑፍ፡- በቄስ ኃይሉ መኮንን)

ስለ ጋብቻ ምክር (1ኛቆሮ.7:1-16)  Read More »

የአማኘ አካልና ዝሙት (1ኛ ቆሮ. 6፡12-20) 

ሐዋርያው ጳውሎስ እንደ ሙሴ «አትስረቅ» ፥ «አትገደል» ፥ «አትመኘ» ፥ «አታመንዝር» በማለት ሕግን ብቻ አይደረድርም። ነገር ግን ክርስቲያን ከኃጢአት ለምን መራቅ እንዳለበት በማስረዳት ኃጢአትን ይከለክላል። ስለ ዝሙት ሰፊ ትምህርት በመስጠት ክርስቲያን ከዝሙት መሪቅ ብቻ ሳይሆን ክርስቲያን ለምን ከዝሙት መራቅ እንዳለበት ያስረዳል።  1ኛ ቆሮንቶስ 6፡12-20ን በጥንቃቄ በመመልከት የሚከተሉትን ጥያቄዎች መልስ።  ጥያቄ 1. በቁጥር 12 ሁሉ ተፈቅዶልኛል ሁሉ ግን አይጠቅምም» የሚለውን ሃሳብ አብራራ።  ጥያቄ 2. በቁጥር 12 «ሁሉ ተፈቅዶልኛል በእኔ ላይ ግን አንድ ነገር እንኳ አይሠለጥንብኝም» የሚለውን አብራራ።  ጥያቄ 3. በቁጥር 13 እና 14 ላይ መብል ለሆድ ከሆነ ሥጋ ለዝሙት አለምሆኑን ጳውሎስ እንዴት ያረጋግጣል?  ጥያቄ 4. ከቁጥር 15 እስከ ቁጥር 17 ሁለት ዓይነት “አንድነቶች” ተጠቅሰዋል፤ ምን ምን ናቸው?  ጥያቄ 5. በዚህ ክፍል ውስጥ ሐዋርያው ጳውሎስ ዝሙትን በተለያዩ ምክንያቶች ይከለክላል፤ እነዚህን ምክንያቶች ዘርዘር፤ (ቁጥር 15-20)  ከቁጥር 12-14:- የቆሮንቶስን ምእመናን ጳውሎስ ስለክርስቲያን ነፃነት «ሁሉ ተፈቅዶልኛል» በማለት ሳያስተምራቸው አይቀርም። እነርሱ ግን ይህን ትምህርት አጣመሙ። ሁሉ ከተፈቀደ እንገዲያስ ዝሙትም መከልከል የለበትም ማለት ሳይጀምሩ አይቀሩም። ስለዚህ ጳውሎስ “ሁሉ ተፈቅዶልኛል ሁሉ ግን አይጠቅምም” የሚለውን ሃሳብ መጨመር ነበረበት። በተጨማሪም ሰው በክርስቶስ ያለው ነፃነቱ የጽድቅና የቅድስና አገልጋይ እንዲያደርገው ነው እንጂ የኃጢአት ባሪያ በመሆን ራሱን ለዝሙትና ለመሳሰሉት ኃጢአቶች እንዲሸጥ አይደለም፤ (ሮሜ 6፡13-14)፡፡  ምንም እንኳን በአንዳንድ ነገሮች ላይ ነፃነት እንዳለን ብናውቅም እነዚህን ሁለት ጥያቄዎች መጠየቅ ይገባናል። አንደኛ፡- ይህ የማደርገው ነገር ለሥጋዬ፥ ለመንፈሳዊ ሕይወቴ፥ ለምስክርነቴ፥ ወዘተ የሚጠቅም ነው ወይ? መጽሐፍ ቅዱስን የሚቃወም ማንኛውንም ነገር መተው ይገባናል። ሁለተኛ፡- ይህ ነገር እኔን እየገዛኝ ወይም እየሠለጠነብኝ ነው? ብሎ መጠየቁ ተገቢ ነው። እኛ የክርስቶስ አገልጋዮች እንጂ የሌላ ነገር ተገዢ መሆን አይገባንም። ኃጢአት ሊቆጣጠረን አይገባም። ጥሩ ነው ብለን የምንለው እንደ ምግብ ያለ ነገር እንኳን ሃሳባችንንና ፍላጎታችንን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር የለበትም።  ጥያቄ 6. የትኞቹ መጥፎ ወይም መልካም ነገሮች ናቸው፥ ሰውን በቁጥጥራቸው ሥር አድርገው ለራሱና ለወንጌል እንቅፋት የሚሆኑት?  በቆሮንቶስ ሕዝብ መካከል መብል ለሆድ ነው ሆድም ለመብል ነው» የሚል ምሳሌያዊ አነጋገር ሳይኖር አይቀርም። የቆሮንቶስ አማኞች ይህን ምሳሌ በመመርኮዝ ሥጋ ለዝሙት ነው ዝሙትም ለሥጋ ነው» ሳይሉ አይቀሩም። ይህንን አስተሳሰባቸውን ሐዋርያው ሥጋ ግን ለጌታ ነው እንጂ ለዝሙት አይደላም» ብሉ ይቃወማል፡፡ አሁን ክርስቲያን ስለሆኑ ሥጋ ለዝሙት መሆኑ ቀርቶ ለጌታ ሆኖአል። ስለዚህ አሁን ክርስቲያን በሥጋው እግዚአብሔርን ማክበር አለበት፡፡ የክርስቲያን ሥጋ ለትንሣኤ ክብር ስለታጨ ሥጋችን በክብር ላይ መዋል አለበት። አግዚአብሔር ጌታን ከሞት አንዳሥነሣው ሁሉ የእኛንም ሥጋ ከመቃብር ያነሳል።  ከቁጥር 15-17:- ዝሙት እግዚአብሔር ለጋብቻ የመሠረተውን ባልተፈቀጸ መንገድ በሥራ ላይ ያውላል፡፡ አንድ ወንድ ከሴት ጋር በሥጋ ፍትወት ሲገናኝ ከእርሷ ጋር አንድ አካል ይሆናል። ይህ ዓይነት ኅብረት የተፈቀደው ለጋብቻ ብቻ ነው። እግዚአብሔር የመጀምሪያውን ጋብቻ ሲመሠርት «ሁለቱ አንድ ሥጋ ይሆናሉ» ብሏልና ሚስት ካልሆነች ሴት ጋር በሥጋ መገናኘት ይህን አንድነት በተከለከለ ሁኔታ መመሥረት ነው። ስለዚህ ሐዋርያው «ከዝሙት ሽሹ» ይላል። ክርስቲያን ከክርስቶስ ጋር መንፈሳዊ ኅብረት መሥርቷል። ከጌታ ጋር አንድ መንፈስ ሆኖአል። እንዲህ ከሆነ በዝሙት መሠማራት በእግዚአብሔር የተከለከለ ነው፡፡ ቁጥር 18፡- የዝሙት ኃጢአት ከሌሎቹ ኃጢአቶቹ ሁሉ ኃጢአተኛውን በቀጥታ ይጎዳዋል። ምክንያቱም አካሉን ከጌታ ወስዶ «ከጋለሞታ ጋር› ስለሚያስተባብር ነው። ስለዚህ ሰው የዝሙትን ኃጢአት በጥብቅ ማስወገድ አለበት። ከጋብቻ ውጭ የሚፈጸም የሥጋ ግንኙነት ሁልጊዜ ዝሙት ነውና ዝሙትን በሁሉም መንገድ ክርስቲያን ማስወገድ አለበት።  ከቁጥር 19-20፡- ክርስቲያን ከዝሙት እንዲርቅ ሌላ ተጨማሪ ምክንያት ይሰጠዋል፤ የክርስቲያን አካል የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ ነው። እያንዳንዱ እውነተኛ ክርስቲያን መንፈስ ቅዱስን የተቀበለ ስለሆነ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ሆኖአል። ስለዚህ ትምህርት በተጨማሪ የሚከተሉትን ጥቅሶች ተመልከቱ፤ (1ኛ ቆሮ.3፡16ና 17፤ ሮሜ 8፡9 እና 15፤ ኤፌ.4:30፤ ቲቶ 3፡4-7)።  ከአሥርቱ ትእዛዛት አንዱ «አታመንዝር» የሚለው ነው። አሁን በአዲስ ኪዳን ትእዛዙ መሻር ቀርቶ የትእዛዙ ጥብቅነት በአምስት ምክንያቶች ላይ ተመሥርቷል። እነዚህ አምስት ምክንያቶች እንደሚከተሉት ናቸው፤  1ኛ. የክርስቲያን አካል ከጌታ ጋር ስለተባበረ ሥጋውን በዝሙት ሥራ ማርከስ የለበትም፤ (ቁጥር 13 እና 15)።  2ኛ. የክርስቲያን ሥጋ ለክብር (ለትንሣኤ) ስለታጨ በረከሰ ሥራ ላይ መዋል የለበትም፤ (ቁጥር 14)።  3ኛ. በዝሙት መሠማራት አካልን ከአመንዝራ ጋር ስለሚያስተባብር የዝሙት ሥራ መወገድ አለበት።  4ኛ. ከሌሎች ኃጢአቶች ሁሉ የዝሙት ሥራ ስለሚጎዳ ሰው ከዝሙት መሸሽ አለበት።  5ኛ. ሥጋችን የመንፈስ ቅዱስ ቤት ስለሆነ በሥጋችን እግዚአብሔርን ማክበር አለብን፤ ዝሙት እግዚአብሔርን ያስቀይመዋል እንጂ አያክብረውም፤ (19-20)። ዕብ.13፡4 ጋብቻ ክቡር፥ አመንዝራነት ግን በእግዚአብሔር የተከለከለ መሆኑን ያስተምራል። ስለዚህ ጋብቻ ከመመሥረቱ በፊትም ሆነ በኋላ ከጋብቻ ውጭ የሥጋ ፍትወት መወገድ አለበት።  ጥያቄ 7. ሀ/ በቤተ ክርስቲያን የዝሙት ሥራ እንደዚህ በጣም የበዛው ለምንድነው? ለ/ ከጋብቻ በፊት የግብረ ሥጋ ግንኙነትን እንዳይለማመዱ ወጣቶቻችንን እንዴት አድርገን ነው በተሻለ መንገድ ልናስተምር የምንችለው? (ምንጭ፤ በትምህርተ መለኮት ማስፋፊያ (ትመማ) መልክ የተዘጋጀ ጽሑፍ፡- በቄስ ኃይሉ መኮንን)

የአማኘ አካልና ዝሙት (1ኛ ቆሮ. 6፡12-20)  Read More »

 የምእመናን የእርስ በርስ መካሰስ (1ኛ ቆሮ 6፡1-11) 

ጥያቄ 21. በቁጥር 1 ላይ “በቅዱሳን ፊት መፋረድ” ሲል ቅዱሳን የሚላቸው እነማንን ነው? አመፀኛችስ ያላቸው እነማን ናቸው?  ጥያቄ 22. ከቁጥር 1-8 ውስጥ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች የፈጸሟቸው ስንት ስሕተቶች ተዘርዝረዋል? ምን ምን ናቸው?  ጥያቄ 23. ከቁጥር 9-11 ያለው ከቁጥር 1-8 ካለው ጋር የሃሳብ ዝምድናውን አስረዳ።  ቁጥር 1:- በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን አማኝ ከአማኝ ጋር ይካሰስ ነበር። በተካሰሱ ጊዜ ለዳኝነት አማኞች ዘንድ ሳይሆን እማያምኑት ዘንጽ ይሄዱ ነበር። ይህ እንኳን በክርስቲያን መካከል ቀርቶ በአይሁድ ባሕል እንኳ ተቀባይነት አልነበረውም። ጳውሎስ ይህ በክርስቲያኖች መካከል መደረገ እንደሌለበት ያስተምራል። በዚህ ክፍል ውስጥ አማኞችን ቅዱሳን ሲላቸው የማያምኑትን ደግሞ አመጸኞች ይላቸዋል። አምጸኝነታቸው ለእግዚአብሔር ሕግና በወንጌል በኩል ለቀረበው ለአግዚአብሔር ምሕረት ባለመታዘዛቸው ነው።  ከቁጥር 2–3:- አማኞች በፍርድ ቀን ከክርስቶስ ጋር በመተባበር በዓለም ላይ ይፈርዳሉ፤ (ዳንኤል 7:22፤ ማቴ.19፡28)። እንግዲያስ በአሁኑ ጊዜ በሚነሡ ክሶች ላይ መፍረድ ይችላሉ። ስለ ትዳር ጉዳይ ቀርቶ “በመላእክት እንኳ እንድንፈርድ” እግዚአብሔር ወስኗል። በመላእክት ላይ መፍረድ ማለትም በመላእክት ላይ መሠልጠን ማለት ነው፡፡ ወይም በመላእክት ላይ ሥልጣን መያዝ ማለት ነው። ይህም ሊሆን የሚችለው አማኝ ከክርስቶስ ጋር ስለሚነግሥ ክርስቶስም በመላእክት ላይ ስለነገሠ ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስ ሙሽራ እንደመሆኗ መጠን ይህን ሥልጣን ከክርስቶስ ጋር ትካፈላለች፤ (ሮሜ 8፡17፤ አፌ.1:22)።  ከቁጥር 4-5፡- ቁጥር 4ን አንዳንድ የግሪክ ቋንቋ ሊቃውንት እንዲህ ብለው ይተረጉማሉ፤ «እንግዲህ ስለትዳር ጉዳይ የፍርድ ቤት ቢያስፈልጋችሁ በቤተ ክርስቲያን የተናቁትን ሰዎች ፈራጆች አድርጋችሁ አስቀምጡ።» እንዲህ ከተወሰደ ትርጉሙ ምንም እንኳ ላዳኝነት የሚበቁ አማኞች በመካከላችሁ ባይገኙም ዓለማውያን ፊት ሄዶ ከመፋረድ በቤተ ክርስቲያን ዝቅተኛው አማኝ የተሻለ ፍርድ ይሰጣልና እርሱን ሹሙት” ማለት ይሆናል። ነገር ግን ይህ አተረጓጎም ትክክለኛ አይደለም። ትክክለኛው ትርጉም የአማርኛው ትርጉም ስለሆነ በዚያው እንረጋለን። ጳውሎስ ጥያቄ ነው ያቀረበው፤ «በቤተ ክርስቲያን የተናቁትን ሰዎች ፈራጆች አድርጋችሁ ታስቀምጣላችሁን?»፡፡ ማለት ዓለማውያን በቤተ ክርስቲያን የተናቁና የአማኝን ሕይወት በደንብ የማያውቁ ሰዎች ስለሆኑ በአማኝ ላይ በፍርድ እንዲቀመጡ አማኝ እነርሱ ዘንድ መሄድ የለበትም። በቁጥር 5 ላይ በትዳር ጉዳይ የሚፈርዱ አማኞች የማይጠፋ መሆኑን አጠራጣሪ እንዳልሆነ ያረጋገጣል።  ጥያቄ 24. በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ በሁለት ክርስቲያኖች መካከል ክርክር ቢነሣ የሚታረቁት በምን መንገድ ነው?  ከቁጥር 6-8፡- በዚህ ክፍል ሐዋርያው በመሠረቱ የመካሰስ ነገር በመካከላቸው መነሣት እንደሌለበት ይናገራል። ይህ በመሆኑ በክስ እንኳ ቢረቱ እንደተሸነፉ ያስረዳቸዋል። አማኝ ከክርስቲያን ወንድሙ ጋር በሰላም መኖር አለበት። ቢካሰስ ድካም መሆኑን መገንዘብ አለበት። ግን በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ክስ የተነሣው ወንድም ወንድሙን ስለሚያታልል በር። ይህ መሆን አልነበረበትም፡፡ ስለዚህ በዚህ በመካሰስ ጉዳይ የፈጸሟቸው ስሕተቶች እነዚህ ናቸው፡- 1ኛ/ አማኞች እርስ በርስ መፋቀርና መደጋገፍ ሲገባቸው በውስጣቸው ክስ መኖሩ።  2ኛ/ ክሱም ስለተበደሉ ሳይሆን ወንድሞችን በማታለል ነበር።  3ኛ/ ይህንም ክስ በአማኞች ፊት ሳይሆን በማያምኑ ፊት ያቀርቡ ነበር።  ከቁጥር 9-11:- አማኞች ክሳቸውን በማያምኑ ፊት ያቀረቡት በአማኝና በማያምን መካከል ምን ያህል ትልቅ ልዩነት እንዳለ ባለመረዳት ሊሆን ስለሚችል፥ ያለውን ልዩነት በዝርዝር ያስረዳቸዋል። «አመፀኞች የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም። አመፀኝነታቸው በሁለት መንገድ ነው። 1ኛ/ የእግዚአብሔርን ሕግ በሕይወታቸው አይጠብቁም። 2ኛ/ እግዚአብሔር በክርስቶስ በኩል የቀረበላቸውን ደኅንነት አይቀበሉም። ስለዚህ የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም። ሕጉንም እንዴት እንዳፈረሱ በዝርዝር ጽፎአል፤ (ቁጥር 9 እና 10)። በቁጥር 11 ላይ የክርስቲያንን መለወጥ ያስተምራል። «ከእናንተም አንዳንዶች እንደዚህ ነበራችሁ»። አሁን ግን፡- 1ኛ. ታጥባችኋል፤ ክርስቲያን ከኃጢአቱ እድፍ በክርስቶስ ደምና በመንፈስ ቅዱስ ታጥቧል። ጥምቀት የዚህ የመታጠብ የውጭ ምሳሌ ሆኖ ቀርቧል። ኃጢአት እድፍ ወይም እርኩስ ነው፤ ስለዚህ ሰው በእግዚአብሔር ፊት ተቀባይነት የሚኖረው ከእድፋ ሲታጠብ ብቻ ነው። ይህም በሥራ ሳይሆን እንዲያው በነፃ በክርስቶስ በማመናችን ብቻ ይሰጠናል።  2ኛ. ተቀድሳችኋል፤ መቀደስ ሁለት ደረጃ አለው። የመጀመሪያው ደረጃ አማኝ ክርስቶስን የተቀበለ ዕለት በእግዚአብሔር መንፈስ ታጥቦ የእግዚአብሔር ዕቃ ይሆናል። ቅዱስ ዕቃ ነው፤ (3፡16 እና 17)። ይህ የሚደጋገም ሳይሆን በአማኝ ሕይወት አንድ ጊዜ ስለተፈጸመ አማኝ ቅዱስ ይባላል፤ (1:2፤ 6፡1)። ሌላው የቅድስና ደረጃ በክርስቶስ ዳግም ምጽአት ጊዜ አማኝ ከኃጢአት ነፃ ይሆናል። አሁን አማኝ ከኃጢአቱ ንጹሕ ላለመሆኑ መጽሐፍ ቅዱስም ሕይወቱም ይመሰክራሉ፤ (1ኛ ዮሐ.1:8-10)። ነገር ግን ተቀድሳችኋል ማለቱ የሁለተኛውን ዓይነት ቅድስና ሳይሆን የአንደኛውን ዓይነት ቅድስና ማለቱ ነው።  3ኛ. ጸድቃችኋል፤ ይህ የፍርድ ቤት ቋንቋ ነው። አማኝ በእግዚአብሔር ፍርጽ ዙፋን ፊት ቀርቦ ክሱ ተሰርዞለት የክርስቶስን ጽድቅ በመጎናጸፍ «ጻድቅ» ተብሎ ተፈርዶለታል። ስለዚህ ስለ ኃጢአቱ ወደፊት በፍጹም አይጠየቅም። ይህ ወንጌል የሚሰጠን የምሥራች ነው። ይህን የምሥራች በእምነት የተቀበለ ሁሉ የዚህ ጽድቅ ወራሽ ሆኖአል፡፡ እንግዲህ አማኝ ይህን መሰል ሲሆን የማያምን ደግም የረከሰና በእግዚአብሔር ፍርድ ሥር ያለ ስለሆነ እንዴት አማኝ ለዳኝነት ጉዳይ ወደማያምን ዘንድ ይሂድ? (ምንጭ፤ በትምህርተ መለኮት ማስፋፊያ (ትመማ) መልክ የተዘጋጀ ጽሑፍ፡- በቄስ ኃይሉ መኮንን)

 የምእመናን የእርስ በርስ መካሰስ (1ኛ ቆሮ 6፡1-11)  Read More »