የሕይወት እንጀራ አገልግሎት

ስለ እኔ፦ የአገልግሎቱ ራእይና ጥሪ ሰላም ለእናንተ ይሁን! እኔ አዳነው ዲሮ ዳባ እባላለሁ። ወደዚህ ድረ-ገጽ ስለመጡና የ"የሕይወት እንጀራ" ቤተሰብ ስለሆኑ እጅግ ደስ ብሎኛል። ይህ አገልግሎት የተወለደው በሕይወቴ ውስጥ ካለ አንድ ትልቅ እውነት ነው፤ እርሱም "ሰው በእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም" የሚለው መለኮታዊ ቃል ነው። 📖✨ 📜 ጥሪዬና ማንነቴ እግዚአብሔር በጸጋው በሰጠኝ ዘመን ሁሉ እንደ መጽሐፍ ቅዱስ መምህር፣ ጽሐፊና ተርጓሚ በመሆን ሳገለግል ቆይቻለሁ። ቃሉን መመርመር፣ የተሰወሩ ዕንቁዎችን ማውጣትና ያገኘሁትን መንፈሳዊ ምግብ ለሌሎች ማካፈል የልቤ ትርታ ነው። ✍️ የአገልግሎቴ መሪ ቃል "ኢየሱስ፣ የነፍስ ምግብ" የሚል ሲሆን፣ ዓላማዬም በዕለት ተዕለት ሕይወት ሩጫና ድካም ውስጥ ለሚገኙ ነፍሳት የማይለወጠውንና የማይጠፋውን የክርስቶስን ወንጌል በተለያዩ ትምህርቶች ማድረስ ነው። 🌍 ከየት ወደ የት? በአሁኑ ሰዓት በዩናይትድ ስቴትስ የምኖር ቢሆንም፣ ልቤና ሐሳቤ ግን ሁልጊዜም በኢትዮጵያና በዓለም ዙሪያ ካሉ ወገኖቼ ጋር ነው። በአካል ብንራራቅም፣ በቴክኖሎጂ አማካኝነት ይህንን የወንጌል ድልድይ በመገንባት የጌታን ቃል በየቤታችሁ ለማድረስ እተጋለሁ። በተለይም በሕይወት ታሪኬና በተለያዩ የሥልጠና ጽሑፎቼ አማካኝነት እግዚአብሔር በሕይወቴ ውስጥ የሠራውን ተአምርና ያስተማረኝን ጥልቅ ትምህርቶች ለእናንተ ለማካፈል በዝግጅት ላይ እገኛለሁ። 🌱🕊️ 🤝 አብረን እንጓዝ በዚህ ድረ-ገጽ የምታገኟቸው ትምህርቶች ሁሉ ከጸሎትና ከጥልቅ ጥናት በኋላ የሚቀርቡ "የነፍስ ምግቦች" ናቸው። ዓላማዬ በክርስቶስ እንድታድጉ፣ በመንፈሳዊ ማንነታችሁ እንድትጸኑና የተሰጣችሁን የሰማይ መክሊት እንድትጠቀሙ መርዳት ነው። በዚህ የመንፈሳዊ ጉዞ አብረን እንድንጓዝ፣ እንድንማማርና አብረን እንድንጸልይ በታላቅ አክብሮት እጋብዛችኋለሁ።🙏🌟

ለምን እግዚአብሔር ክፉ ነገር በመልካም ሰዎች ላይ እንዲደርስ ይፈቅዳል?

በስነ-መለኮቱ አለም ከሚነሱ ዋነኛ ጥያቄዎች መካከል አንዱ ለምን እግዚአብሔር ክፉ ነገር በመልካም ሰዎች ላይ እንዲደርስ ይፈቅዳል? የሚለው ነው። እግዚአብሔር መጀመሪያ እና መጨረሻ የለውም፣ ሁሉን ቻይ፣ በሁሉ ስፍራ በአንዴ የሚገኝ እንዲሁም ሁሉን አዋቂ ነው። በተቃራኒው ሰው ደግሞ ፍጡር፣ ውሱን እና በስባሽ ነው። ይህ ፍጡር ትልቁን ፈጣሪ ሙሉ በሙሉ ለመረዳት ሲሞክር ነው እንግዲህ እነኚህን የመሳሰሉ ጥያቄዎች መነሳት የሚጀምሩት። ሰው፣ ፈጣሪውን ሙሉ በሙሉ ሊረዳው እንደሚችል ሊያስብ አይገባውም የሚለውን አጠቃላይ እውቀት ከግንዛቤ ከተን ወደተነሳንበት ርዕሰ ጉዳይ እንመለስ። ለምን እግዚአብሔር ክፉ ነገር በመልካም ሰዎች ላይ እንዲደርስ ይፈቅዳል? ስለዚህ ጉዳይ የኢዮብ መጽሐፍ መጠነኛ ግንዛቤ ይሰጠናል። ሰይጣን ኢዮብን እና የኢዮብ የሆነውን ሁሉ (ከነፍሱ በስተቀር) እንዲያጠፋ ከእግዚአብሔር ፈቃድ አገኘ። ለዚህ የእግዚአብሔር ውሳኔ የኢዮብ ውሳኔ ምን ነበር? ‘‘እነሆ፥ ቢገድለኝ ስንኳ እርሱን በትዕግሥት እጠባበቃለሁ ነገር ግን መንገዴን በፊቱ አጸናለሁ’’ (ኢዮብ 13፡15)። ‘‘ራቁቴን ከእናቴ ማኅፀን ወጥቻለሁ፥ ራቁቴንም ወደዚያ እመለሳለሁ እግዚአብሔር ሰጠ፥ እግዚአብሔርም ነሣ የእግዚአብሔር ስም የተባረከ ይሁን’’ (ኢዮብ 1፡21)። በሕይወቱ ላይ ይህ ክፉ ነገር እንዲደርስ እግዚአብሔር ለምን እንደፈቀደ ኢዮብ ምንም ግንዛቤ አልነበረውም። ነገር ግን እግዚአብሔር መልካም እንደሆነ ስለሚያውቅ እምነቱን በእግዚአብሔር ላይ ጣለ። የነገሩም ዋነኛ ጉዳይ ይኸው ነው – በእንደዚህ አይነት ወቅቶች የእኛም ምላሽ እንዲሁ ሊሆን ይገባል። ለምን ክፉ ነገር በመልካም ሰዎች ላይ ይደርሳል? ለዚህ ጥያቄ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምላሹ – በዚህ ምድር ላይ ምንም አይነት ‘መልካም’ ሰው የለም የሚል ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ሁላችን ከሃጢአት በታች እንደወደቅን፣ በሃጢአት እንደተበከልን በተደጋጋሚ ይነግረናል (መክብብ 7፡20፤ 1ዮሐንስ 1፡8)። በምድር ላይ መልካም ነገር ገንዘቡ የሆነች፣ ኃጢአትንም የማያደርግ ሰው አለመኖሩን ሮሜ 3፡10-18 በግልጽ ያሳየናል፣ ‘‘ጻድቅ የለም አንድ ስንኳ፤ አስተዋይም የለም፤ እግዚአብሔርንም የሚፈልግ የለም፤ ሁሉ ተሳስተዋል፥ በአንድነትም የማይጠቅሙ ሆነዋል፤ ቸርነት የሚያደርግ የለም፥ አንድ ስንኳ የለም። ጕሮሮአቸው እንደ ተከፈተ መቃብር ነው፥ በመላሳቸውም ሸንግለዋል፤ የእባብ መርዝ ከከንፈሮቻቸው በታች አለ፤ አፋቸውም እርግማንና መራርነት ሞልቶበታል፤ እግሮቻቸው ደምን ለማፍሰስ ፈጣኖች ናቸው፤ ጥፋትና ጉስቁልና በመንገዳቸው ይገኛል፥ የሰላምንም መንገድ አያውቁም። በዓይኖቻቸው ፊት እግዚአብሔርን መፍራት የለም።’’ በዚህ ምክንያት በዚህ ምድር ላይ የሚኖር እያንዳንዱ ሰው በአሁኑ ሰአት ሊያገኝ የሚገባው አንድ እና ትክክለኛ ነገር ቢኖር ወደ እቶን እሳት መጣል ብቻ ነው። ከዚህ በተቃራኒው በሆነ መንገድ በዚህ ምድር ላይ የምናሳልፋት እያንዳንዷ መልካም ሰከንድ የእግዚአብሔር ምህረት እና ፀጋ ውጤት ናት እንጂ የተገባን ሆና አይደለም። በዚህች ምድር ላይ የምንቀበለው ትልቁ ክፉ ነገር በሲኦል ልንቀበለው ከነበረው ታላቅ መከራ ጋር ሲተያይ የአግዚአብሔርን ምህረት አሳንሰን እንድናይ ሊያደርገን አይገባም። እናም፣ ጥያቄው ሊሆን ይገባ የነበረው – ‘‘ለክፉዎች ለምን እግዚአብሔር መልካም ነገር እንዲሆንላቸው ፈቀደ?’’ የሚል ነበር። ሮሜ 5፡8 እንዲህ ይላል፣ ‘‘ነገር ግን ገና ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ስለ እኛ ሞቶአልና እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር ያስረዳል’’። እርሱ የእኛ  ክፋት፣ ሃጢአትና ጠማማነት ሳያግደው ልጁን ስለእኛ ሲል ለሞት አሳልፎ እስከመስጠት ድረስ ይወደናል (ሮሜ 6፡23)። ኢየሱስ ክርስቶስን እንደ አዳኝ የምንቀበለው (ዮሐንስ 3፡16፤ ሮሜ 10፡9) ከሆነ፣  ሃጢአታችን ይቅር ይባልልናል፣ በመንግስተ ሰማይም የዘላለም ቤት ይኖረናል (ሮሜ 8፡1)። ይህ የሚገባን ስጦታ አልነበረም። ይገባን የነበረው ገሃነመ እሳት ነበር። ነገር ግን እኛን ስለመውደዱ ምክንያት እምነታቸውን በኢየሱስ ላይ ባደረጉ ሁሉ ላይ ዘላለማዊ ሕይወትን አዟል። የም ሆኖ፣ አንዳንድ ጊዜ ክፉ ነገሮች ሊያገኛው አይገባቸውም በምንላቸው ሰዎች ላይ ሲደርሱ ይታያል። እነዚህ ነገሮች ባንረዳቸውም እንኳ በእግዚአብሔር ዘላለማዊ እቅድ ውስጥ ፋይዳ እንዳላቸው  ልናምን ይገባል። በሕይወታችን ላይ የመጣው ነገር ምንም ሆነ ምን፣ እግዚአብሔር መልካም፣ ፍቅር እና መሃሪ እንደሆነ ልንዘነጋ አይገባም። ልንገነዘባቸው የማንችላቸው ጉዳዮች ሲገጥሙን የእግዚአብሔርን መልካምነት ከመጠራጠር ይልቅ ልንታመንበት ይገባል። ‘‘በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፥ በራስህም ማስተዋል አትደገፍ በመንገድህ ሁሉ እርሱን እወቅ፥ እርሱም ጎዳናህን ያቀናልሃል’’ (ምሳሌ 3፡5-6)።

ለምን እግዚአብሔር ክፉ ነገር በመልካም ሰዎች ላይ እንዲደርስ ይፈቅዳል? Read More »

በውኑ አምላክ ከባድ ኃጢአቶችን ይቅር ይል ይሆን? ነፍሰ ገዳዩንስ ይቅር ይል ይሆን?

ብዙ ሰዎች፣ እግዚአብሔር እንደ ውሸት፣ ቁጣና ከፉ ሀሳብ የመሳሰሉ “ትንንሽ” ኃጢአቶችን ይቅር እንደሚል ያምኑና  ነገር ግን እንደ ግድያ እና ምንዝርና ያሉትን “ትላልቅ” ኃጢአቶች ይቅር እንደሚል ለማመን ይቸገራሉ። ይህ እውነት አይደለም። እግዚአብሔር ይቅር የማይለው “ትልቅ” ኃጢያት የለም። ኢየሱስ በመስቀል ላይ ሲሞት የመላው ዓለምን የኃጢአት ዋጋ ለመክፈል ሞቷል (1ኛ ዮሐንስ 2፡2)። አንድ ሰው ድነትን ለማግኘት በኢየሱስ ክርስቶስ ሲያምን፣ ለሁሉም ኃጥያቶቹ ይቅርታን ያገኛል። ይህም ይቅርታ ያለፈ፣ የአሁን፣ እና የወደፊት “ትልቅም ሆነ ትንሽ” ኃጥያቶቹን ያካትታል። ኢየሱስ የሞተው ለኃጢአቶቻችን ሁሉ ቅጣት ለመቀበል ነው። እናም ኃጢአተኛው ሰው ይቅር ከተባለ ዘንዳ ከሁሉም ኃጢአቶች ይቅርታን ያገኛል ማለት ነው (ቆላስያስ 1፡14; ሐዋርያት ሥራ 10:43)። ሁላችንም በኃጢያታችን ምክንያት በደለኞች ነን (ሮሜ 3፡23)። በበደላችን ምክንያት ደግሞ ዘላለማዊ ቅጣት መቀበል ይገባናል (ሮሜ 6 23)። ነገር ግን፣ መድሃኒታችን ኢየሱስ ቅጣታችንን ተቀብሎ ስለ እኛ ሞቷል (ሮሜ 5፡8)። ማንም ሰው ምንም ዓይነት ኃጢአት ቢሠራም እነኩዋን ለመዳን በኢየሱስ ክርስቶስ ካመነ፣ የኃጥያት የቅርታን ያገኛል (ሮሜ 6 23; ዮሐንስ 3:16)። ነፍሰ ገዳይ ወይም አመንዝራ ከውሸታሙ ሰው ይልቅ ለክፉ ተግባሩ (ህጋዊ፣ ማሀበራዊ፣ ወዘተ) ከባድ ችግሮች ሊደርስበት ይችላል። ነገር ግን ለድነቱ በክርስቶስ እስከታመነ ድረስ ለኃጥያቶቹ ሁሉ እንደማንኛውም ኃጢአተኛ ፍጹምና ዘላለማዊ ይቅርታን ያገኛል። የኃጢያት ይቅርታን ለማግኘት  ወሳኙ ነገር የኃጢአቱ አይነትና መጠን ሳይሆን ለኃጢያት ስርየት በክርስቶስ የተከፈለው የመስዋዕት መጠን ነው። ኃጢያት የሌለበት የእግዚአብሔር በግ (አኢየሱስ ክርስቶስ) የአለሙን ሁሉ ኃጢያት ሊያስወግድ የሚችል ከሆነ፣ ይህ መስዋዕት ሊከድነው የማይችለው የኃጢአት አይነትም ሆነ መጠን ሊኖር አይችልም። መጽሐፍ ቅዱስ “ተፈጸመ” ብሎ ሲናገር፣ የተሟላ ስርየት ተደረገ፤ እግዚአብሔር በመስዋዕቱ ረካ፤ ፍጹም ምህረት ተገኘ፤ ሰላም ተፈጠረ፤ ከኃጢአት ሁሉ መቤዠት ተገኘ ማለቱ ነው። የክርስቶስ መስዋዕት እውን እና የተሟላ ነው። ይህ መስዋዕት የጎደለው ነገር ስለሌለ በላዩ ላይ ማንም ምንም ነገር ሊጨመርበት አይችልም፤ ሊቀለበስውም እንዲሁ። መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የሕይወትዎ ጌታ በማድረግ ቀሪው ዘመንዎን ለመኖር ወስነው ከሆነ፣ ይህንን ሊንክ በመጫን ስምዎንና የኢ-ሜይል አድናሻዎን ይላኩልንና፣ ለመንፈሳዊ ሕይወት እድገትዎ የሚቻለንን ሁሉ እገዛ እናደርግሎታለን።

በውኑ አምላክ ከባድ ኃጢአቶችን ይቅር ይል ይሆን? ነፍሰ ገዳዩንስ ይቅር ይል ይሆን? Read More »