ትንቢተ ሚክያስ

ሚክያስ 1-7

የውይይት ጥያቄ፥ ሚክያስ 1-7 አንብብ። ሀ) ሚክያስ ሕዝቡን የከሰሰባቸውን ኃጢአቶች ዘርዝር። ለ) እግዚአብሔር በሕዝቡ ላይ ምን ዓይነት ፍርድ እንደሚያመጣ ተናገረ? ሐ) ዛሬ ሊያጽናኑን የሚችሉትንና ወደ ፊት ስለሚመጣው ንጉሥና መንግሥት የተነገሩትን ትንቢቶች ዘርዝር። እግዚአብሔር ጻድቅና ቅዱስ አምላክ ነው። ስለዚህ ኃጢአትን በተለይም ደግሞ በሕዝቡ መካከል ያለውን ኃጢአት መቅጣት አለበት፤ ይቀጣልም። ብዙ ጊዜ ሰይጣን ሕዝቡን እግዚአብሔር የሚገደው ለመሥዋዕት ሥነ-ሥርዓት፥ ለአምልኮ ጸሎት፥ ለመዝሙር፥ ለስብከትና ለመሳሰሉት ነው በማለት ያስታቸዋል። በዚህ ምክንያት እነርሱ ይህንን እስካደረጉ ድረስ፥ እግዚአብሔር ደስ የሚሰኝና የሚባርካቸው ይመስላቸዋል። ነገር ግን እነዚህ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች በቀላሉ ባዶና ምንም ዋጋ የሌላቸው ሊሆኑ ይችላሉ። በእግዚአብሔር ሕዝብ መካከል ኃጢአት፥ መለያየት፥ የሥነ-ምግባር ድቀት፥ ጠብ፥ ጥላቻ ቅንዓትና ትዕቢት ወይም ሌላ ዓይነት ኃጢአት ካለ እግዚአብሔር በሕዝቡ ደስ አይሰኝም፡፡ እግዚአብሔር በሕዝቡ ሕይወት ችግር እንዲመጣ ያደርጋል። ሕዝቡን ወደ ራሱ ለመመለስ የስደት ሞት ሳይቀር ሊያመጣ ይችላል። ከሥርዓተ አምልኮ በላቀ ሁኔታ እግዚአብሔር በሁሉም ሕይወታችን ክፍል አግባብ ባለው መንገድ እንድንመላለስ ይፈልጋል። ሕይወታችን ሙሉ በሙሉ ለእግዚአብሔር በምንሰጥበትና ለእርሱ በምንታዘዝበት ጊዜ፥ አምልኮአችን ሁሉ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ይሆንና እርሱም ክብሩንና ኃይሉን ያሳየናል። የውይይት ጥያቄ ሀ) ብዙ ክርስቲያኖች እግዚአብሔር በእሑድ የእርሱን በሚያመልኩበት ጊዜ በሚያደርጉት ድርጊት ብቻ ሳይሆን፥ በአጠቃላይ ስለ ሕይወታቸው የሚገደው መሆኑን የሚዘነጉት ለምንድን ነው? አንተም ሆንህ ቤተ ክርስቲያንህ እነዚህን እውነቶች ማስታወሳችሁ አስፈላጊ የሚሆነው ለምንድን ነው? 1. ሚክያስ በሰማርያና በኢየሩሳሌም ላይ የተናገራቸው ትንቢቶች (ሚክያስ 1) ጻድቅ የሆነው አስፈሪው ዳኛ እግዚአብሔር በሕዝቡ ላይ ለመፍረድ ከሰማይ ሲወርድ ይታያል። ሰማርያና ኢየሩሳሌም ስለ ኃጢአታቸው ተጠያቂዎች ናቸው። ሰማርያ ፈጽማ ልትጠፋ፥ ኢየሩሳሌምም ልትቀጣ ነበር። ስለዚህም፥ ሚክያስ ይህን ትንቢት በተቀበለ ጊዜ በኃዘን ተሞልቶ ነበር። አንድ ወዳጁ ወይም አፍቃሪው የሞተበት ሰው በሚያዝንበት መንገድ ያለቅስና በባዶ እግሩ ዕርቃኑን ይመላለስ ነበር።  2. ሚክያስ በይሁዳ መሪዎች ላይ የተናገራቸው ትንቢቶች (ሚክያስ 2-3)  እግዚአብሔር በይሁዳ ላይ ለመፍረድ የተነሣው ለምን ነበር? በእግዚአብሔር ሕዝብ መካከል በነበረው ኃጢአትና የፍትሕ መዛባት ምክንያት ነበር። ሀብታሞች፣ ጎረቤቶቻቸውንና ድሆችን በማታለል ገንዘባቸውን ይቀሙአቸው ነበር። ሕዝቡ ኃጢአታቸውን ተገንዝበው በንስሐ እንዳይመለሱ የሐሰት ማጽናኛ ቃሎችን ይተነብዩ ነበር። የሚያገለግሉት የእግዚአብሔርን ቃል ለሕዝቡ በማስተማር፣ ሕዝቡ ንስሐ ሲገቡ ለማየት በመናፈቅ ሳይሆን፥ ለገንዘብ ሲሉ ነበር። መሪዎቹ ጉቦ በመቀበልና ኃይላቸውን ያለ አግባብ በመጠቀም ሀብትን ይሰበሰቡ፥ ለድሆች የሚገባውንም ነገር ይነጥቁ ነበር። ሰዎች እነዚህን መሰሎቹ ድርጊቶች በእግዚአብሔር ፊት መልካም እንደሆኑ ቢያስቡም የእግዚአብሔር ፍርድ ግን በደጅ ነበር።  3. ሚክያስ ስለ ጽዮን መመለስ የተናገረው ትንቢት (ሚክያስ 4-5) በይሁዳ መንግሥት ከነበረው ክፋት ጋር ሲነጻጸር በመጨረሻው ዘመን በእግዚአብሔር የሚመሠረት ሌላ መንግሥት እንደሚመጣ ተናገረ። እርሱና የእግዚአብሔር ጻድቅ ሕዝብ የሆነው ቅሬታ የዚህ መንግሥት አካል ይሆናሉ። የእግዚአብሔር ሕዝብ በተለወጠ ልብ እግዚአብሔርን ያመልካሉ። ጦርነትና ክፋት ይወገዳል። ሰዎች በሰላም ይኖራሉ። አሕዛብ ሳይቀሩ እግዚአብሔርን ያመልካሉ። እግዚአብሔር በይሁዳ ሕዝብ ላይ የሚፈርድ ቢሆንም እንኳ አንድ ቀን እንደ ዳዊት ያለ የእግዚአብሔርን ሕዝብ የሚመራ ንጉሥ እንደሚመጣ ተናገረ። በእግዚአብሔር ኃይልና ብርታት ይመጣል፤ ዳሩ ግን ለእግዚአብሔር ሕዝብ ርኅሩኅ እረኛ ይሆናል።  4. ሚክያስ ስለ ይሁዳ ክፋትና ስለሚመጣባት ፍርድ የተናገረው ትንቢት (ሚክያስ 6-7፡6)  እግዚአብሔር ተራሮችንና ኮረብቶችን በምስክርነት በመጥራት በይሁዳ ላይ ክሱን ያቀርባል። እግዚአብሔር ለእነርሱ በቸርነት የተገለጠ ቢሆንም፥ አይሁድ ግን ያለማቋረጥ በእግዚአብሔር ላይ ዓመፁ። የእግዚአብሔርን ሕግጋት ባሕርያት ሊለውጡ በማይችሉ ውጫዊ የሃይማኖት ሥርዓቶች ለወጡ። የጣዖት አምልኮን ለእግዚአብሔር ከሚቀርብ አምልኮ ጋር ቀላቀሉ። ክፋትን በመቃወም የሚናገሩ መልካም ሰዎች እየተገደሉ ከምድሪቱ ይወገዱ ጀመር። ስለዚህ የእግዚአብሔር ፍርድ በእነርሱ ላይ ይመጣል። ፍርድ እንደሚመጣ የተረጋገጠ ነው። ፍርዱ በሚፈጸምበት ጊዜ ታማኝ የሆኑት የእግዚአብሔር ሕዝቦች «እኔ ግን ወደ እግዚአብሔር እመለከታለሁ፥ የመድኃኒቴንም አምላክ ተስፋ አደርጋለሁ፥ አምላኬም ይሰማኛል» (ሚክያስ 7፡7) የሚል ምላሽ ይሰጣሉ።  5. የእስራኤል ቅሬታዎች በወደፊቱ የእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ ስለሚቀበሉት ይቅርታ ሚክያስ የተናገራቸው ትንቢቶች (ሚክያስ 7፡7-20)  ይሁዳ በእግዚአብሔር ፍርድ ምክንያት የሚደርስባት ጥፋት ዘላለማዊ አልነበረም። አንድ ቀን እንደገና በምሕረቱ ሊጎበኛት እግዚአብሔር ቀን ቀጥሮ ነበር። እግዚአብሔር ለሕዝቡ የሚሠራውን ሥራ የምድር አሕዛብ በመደነቅና በአክብሮት ይመለከቱታል። ኢየሩሳሌም እንደገና ትሠራለች። እውነተኛ ይቅርታና ተሐድሶም ይሆናል። ሚክያስ ስለዚህ ነገር እርግጠኛ የሆነው ለምን ነበር? እግዚአብሔር ከአብርሃም ጋር ቃል ኪዳን ስላደረገና ለቃል ኪዳኑም ታማኝ ስለሆነ ነው። የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ከትንቢተ ሚክያስ የተማርካቸውን አንዳንድ መንፈሳዊ ትምህርቶች ዘርዝር። ለ) እነዚህን ትምህርቶች በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ ለሚገኙ የተወሰኑ ቡድኖች ለማስተማር ዐቅድ። (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡) የመመዘኛ ጥያቄዎችን ለማግኘት ከታች ያለውን ሊንክ (መስፈንጠሪያ) ይጫኑ፡፡

ሚክያስ 1-7 Read More »

የትንቢተ ሚክያስ ዓላማ እና ዋና ዋና ትምሕርቶች

የትንቢተ ሚክያስ ዓላማ እግዚአብሔር ስለ ኃጢአታቸውና ንስሐ መግባት እንደሚያስፈልጋቸው በመናገር ይሁዳን እንዲያስጠነቅቅ ሚክያስን ላከው። ሕዝቡ እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር የገባውን ቃል ኪዳን በመተዋቸው በይሁዳ ላይ ስለሚመጣው ቅጣት ተናገረ፡፡ ምንም እንኳ ውጫዊ በሆነው ሥርዓት እግዚአብሔርን ሊያመልኩ ቢችሉም ሕይወታቸው ግን እግዚአብሔርን በመፍራት የሚመራ አልነበረም። ይህም በተለይ ግልጽ ሆኖ የታየው እርስ በርስ በነበራቸው ግንኙነት ውስጥ ነበር። ሀብታሞች ድሆችን ይጨቁኑ ነበር፤ ስለዚህ የእግዚአብሔር ፍርድ በሀብታሞችና በሕዝቡ ሁሉ ላይ ይከሰታል። የእግዚአብሔር ፍርድ ታማኝ ባልሆነችው ይሁዳ ላይ የሚመጣ ቢሆንም፥ እግዚአብሔር ግን ሕዝቡን ሙሉ በሉ አያጠፉም። እግዚአብሔር ለአብርሃምና ለዳዊት የገባውን ቃል ኪዳን ይፈጽል። አንድ ቀን እግዚአብሐር እርሱ በሚፈልገው መንገድ በጽድቅ የሚገዛ ሰው ከዳዊት ዘር ያስነሣል። ይህ ንጉሥ በእግዚአብሔር ሕዝብ ልብ ውስጥ አንዳችም ክፋት የማይኖርበትንና ሕዘቡ ከእውነት ጨርሶ የማይርቁበትን አዲስ ዘመን ያመጣል። ጦርነት ተሽሮ ሰዎች ሁሉ በእውነተኛ ሰላም ይኖራሉ። እስከ ዛሬ ድረስ በፍትሕ መጉደል የሚሠቃዩ ሰዎች በእነዚህ ጥቅሶች ከፍተኛ መጽናናትን ያገኛሉ። አንድ ቀን እግዚአብሐር በዘላለም መንግሥቱ ያስተናግዳቸዋል። የውይይት ጥያቄ፣ በችግር ውስጥ በምትሆንበት ጊዜ ጽድቅና ቅን ፍርድ የሞላበት አስተዳደር የመምጣቱ ተስፋ የሚያበረታታህ በምን መንገድ ነው? የትንቢተ ሚክያስ ዋና ዋና ትምሕርቶች የውይይት ጥያቄ፣ ሚክያስ 6፡6-8 አንብብ። ሀ) ሚክያስ፣ እግዚአብሔር ከእርሱ የማይፈልገው ምንድር ነው አለ? ለ) ሚክያስ እዚአብሔር ከሰው የሚፈልገው ነገር ምንድር ነው አለ፤ ሐ) እነዚህን ጥሶች ከሕይወትህ ጋር የምታዛምድባቸውን መንገዶች ዘርዝር። መ) ሚክያስ 6፡8 በቃልህ አጥና።  1. ጌታ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው? ትንቢተ ሚክያስ በኃጢአት ላይ የሚመጣውን ፍርድ ወደፊት ከሚገለጡ ታላላቅ ዘመናት ጋር በማቀናጀት የሚናገር ነው። በተለይ የሚያተኩረው ድሆችን በሚጨቁኑ ሀብታሞች ኃጢአት ላይ ነው (ሚክያስ 2፡1-2፤ 3፡1-3፥ 9-11)። ሚክያስ የይሁዳን ኃጢአት በሚገልጽበት ክፍል መሀል እጅግ ጠቃሚ የሆኑ ሁለት ጥያቄዎችን ይጠይቃል፤ በመጀመሪያ፥ “ምን ይዤ ወደ እግዚአብሔር ፊት ልምጣና በልዑል አምላክ ፊት ልስገድ? (ሚክያስ 6፡6) የሚል ሲሆን፥ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ “ሰው ሆይ፥ መልካሙን ነግሮሃል እግዚአብሔር ከአንተ ዘንድ የሚሻው ምንድር ነው?» (ሚክያስ 6፡8) የሚል ነው። በዘመናችን ብዙ ክርስቲያኖች እንደሚያደርጉት በሚክያስ ዘመንም ሕዝቡ እግዚአብሔር ከፍተኛ ትኩረት የሚያደርገው በአምልኮ ሥርዓቶች ላይ ነው የሚል እምነት ነበራቸው። ሕዝቡ ወደ ቤተ-መቅደስ ከመጡ፥ መዝሙራትን ከዘመሩና በሙሴ ሕግጋት መሠረት መሥዋዕቶችን ካቀረቡ እግዚአብሔር የሚፈልግባቸውን ነገሮች ሁሉ ያሟሉ ይመስላቸው ነበር። የአምልኮ ሥርዓቶችን በመፈጸም፥ በክፉ ሥራዎቻቸው ምክንያት ከተቆጣው ቁጣ እግዚአብሔርን የሚመልሱት ይመስላቸው ነበር። እግዚአብሔር አምልኮ በሚፈጽሙበት ጊዜ ስለሚያደርጉት ነገር ብቻ እንጂ በቀሩት የሳምንቱ ቀናት ስለሚያደርጉት ነገር ግድ የሌለው ይመስላቸው ነበር።  ነገር ግን ሚክያስ የልብና የአኗኗር ለውጥ እስከሌለ ድረስ፥ እግዚአብሔር ለሃይማኖታዊ ሥርዓት ግድ እንደሌለው አይቷል። ምንም ያህል ሰዎች ቢዘምሩ፥ ቢጸልዩ፥ ቢጾሙና ለሌሎች ሰዎች ቢመሰክሩ ወይም ሌሎች ሰዎች እጅግ አስፈላጊ ናቸው የሚሏቸውን ሃይማኖታዊ ሥርዓተች ቢፈጽሙ፥ በትክክል እግዚአብሔርን የመታዘዝ ሕይወት እስካልኖሩ ድረስ፥ እግዚአብሔር ደስ አይሰኝም። እውነተኛ አምልኮ ሁለንተናችንን የሚጠይቅ ነው። እግዚአብሔር ስንዘምር፥ ስንጸልይ፥ ስንጾምና ለሌሎች ስንመሰክር ደስ የሚለው መላ ሕይወታችንን የሰጠነው እንደሆነ ነው። ሚክያስ እግዚአብሔር በእርግጥ የሚፈልገው ከልብ መታዘዝን እንደሆነ በማስጠንቀቅ ሕዝቡን የሚያስታውሳቸው ለዚህ ነው (1ኛ ሳሙኤል 15፡22 ተመልከት)። ይህ መታዘዝ ሕይወታቸውን በሙሉ ማጠቃለል አለበት። ከእግዚአብሔር ጋር ያላቸውን ግንኙነት ሁሉ የሚያጠቃልል መሆን አለበት («ከእግዚአብሔር ጋር በትሕትና ኑሩ»)፤ እንዲሁም ከሌሎች ጋር ያላቸውን ግንኙነት የሚጨምር መሆንም አለበት። («በጽድቅ ሥሩ ምሕረትንም ውደዱ»)። የውይይት ጥያቄ፥ ሕይወትህን መርምር። ሀ) ለእግዚአብሔር አምልኮ እንዲሆኑ የምታደርጋቸውን ነገሮች ዘርዝር። ለ) እነዚህ ነገሮች ሊፈጸሙ የሚችሉትና በእግዚአብሔር ዘንድ ግን ተቀባይነት የማያገኙት እንዴት ነው? ሐ) በዚህ ሳምንት ያደረግሃቸውን ጽድቅና ምሕረት የሚያመለክቱ ነገሮችን ዘርዝር። መ) ሁለንተናህ ለእግዚአብሔር መታዘዙን ማረጋገጥ የምትችለው እንዴት ነው? ሠ) እነዚህን እውነቶች ለቤተ ክርስቲያንህ ለማስተማር የምትችለው እንዴት ነው? 2. የሚመጣው ንጉሥና የእግዚአብሔር መንግሥት፡- የትንቢተ ሚክያስ አብዛኛው ክፍል በኃጢአት ላይ ስለሚፈጸም ፍርድና ስለሚመጣው ፍርድ የተነገረ ትንቢት ቢሆንም፥ ሚክያስ የፍርድ ትንቢቶችን ከተስፋ ትንቢቶች ጋር አቀናጅቶ ያቀርባል። ትንቢተ ሚክያስ የመጨረሻውን ዘመን ማለት የሁሉ መደምደሚያ የሆነው እረኛ ንጉሥና መሢሕ በዘመኑ ፍጻሜ ላይ በእግዚአብሔር መንግሥት እንደሚገዛ የሚያሳይ ታላቅ ሥዕላዊ ትዕይንት ያቀርባል። በዚያ መንግሥት ጦርነት አይኖርም፤ ሁሉ ነገር ሰላም ይሆናል። እግዚአብሔር ራሱ ሕዝቡን ስለሚያስተምር ምንም ዓይነት የውሸት አምልኮ አይኖርም። የተበተኑት የእስራኤል ቅሬታዎች ወደ እግዚአብሔር በመመለስ፥ በኢየሩሳሌም እግዚአብሔርን ያመልካሉ። እግዚአብሔር ኃጢአታቸውን ይቅር ይላል። የሚመጣው ንጉሥ፥ መሢሑ የዳዊት ከተማ በሆነችው ቤተልሔም ይወለዳል። አመጣጡ ከዳዊት ዘር ነው፤ ነገር ግን ደካሞችና ኃጢአተኞች ከሆኑት ከዳዊት በኩል ከተነሡት ነገሥታት የተለየ ይሆናል። አመጣጡ ከጥንት ዘመን ስለሆነ አምላክ ነው። ምድርን ሁሉ በጽድቅ መግዛት ብቻ ሳይሆን ደግና ርኅሩኅ እረኛ ይሆናል። ማስታወሻ፡- ስለ ክርስቶስ ኢየሱስ የመጀመሪያና ዳግም ምጽአት የተነገሩ ትንቢቶች በታሪክ በተፈጸሙበት አኳኋን ተነጣጥለው ሳይሆን እንዴት ተጣምረው እንደቀረቡ አስተውል። ነቢያት የወደፊቱን ሁኔታ አርቀው በመመልከት ስለ ክርስቶስ መምጣት ሲናገሩ፥ መሚሑ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚመጣው:- መጀመሪያ በቤተልሔም ተወልዶ በመስቀል ላይ ለመሞት፥ ቀጥሎ ደግሞ እንደ ድል ነሺ ንጉሥ እንደሚሆን አላስተዋሉም ነበር። እና ይህን ልዩነት ልንረዳ የቻልነው የምንኖረው ከኢየሱስ ክርስቶስ ልደትና ሞት በኋላ ስለሆነ ብቻ ነው። ይህ አይሁዶች በተለይ ደግሞ ደቀ መዛሙርት ኢየሱስ በምድር ላይ በተመላለሰና በሞተ ጊዜ የተፈጠረባቸውን ግራ የመጋባት ሁኔታ ለመገንዘብ ይረዳናል። ድል በመንሣት ይገዛል ብለው ይጠብቁት የነበረውን መሢሕ ሁኔታ አላሟላላቸውም ነበር። ከእነዚህ ትንቢቶች አብዛኛዎቹ ኢየሱስ ክርስቶስ ተመልሶ የሚገዛበትን የመጨረሻውን ዘመን የሚመለከቱ ናቸው። በእርሱ ዘመነ መንግሥት ጽድቅና ቅን ፍርድ በምድር ላይ ይንሰራፋል። ኃጢአት ይደመሰስና ሰው ሁሉ በተለወጠ ልብ እግዚአብሔርን ያመልካል። የውይይት ጥያቄ ሀ) እነዚህ ጥቅሶች ከምድር ላይ ፍትሕና ጽድቅ በሚጠፉበት ጊዜ ማበረታቻ የሚሆኑን እንዴት ነው? ለ) ክርስቲያኖች ይህንን እውነት በልባቸው መያዝ ያለባቸው ለምንድን ነው? ሐ) እግዚአብሔር በአምልኮአቸው ደስ ይሰኝ ዘንድ እርሱን በሚያስደስተው መንገድ እንዲኖሩ ሰዎችን ለመርዳት ምን ማድረግ ትችላለህ? (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡) የመመዘኛ ጥያቄዎችን ለማግኘት ከታች ያለውን ሊንክ (መስፈንጠሪያ) ይጫኑ፡፡

የትንቢተ ሚክያስ ዓላማ እና ዋና ዋና ትምሕርቶች Read More »

የትንቢተ ሚክያስ መግቢያ

የውይይት ጥያቄ) እግዚአብሔር በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያሉትን ሰዎች በተለያዩ ስጦታዎች፥ ሥልጠናዎችና ሥረ መሠረቶች የተጠቀመባቸውን መንገዶች ግለጽ። ለ) እግዚአብሔር በዚህ መንገድ የሚሠራው ለምንድን ነው ብለህ ታስባለህ? የእግዚአብሔርን አሠራር ልዩ ከሚያደርጉ ነገሮች አንዱ የተለያዩ ባህሎች፥ ስጦታዎች፡ ሥልጠናዎችና ሥረ መሠረቶች ያሏቸውን ሰዎች ወደ አንድ አካል ማምጣቱ ነው። የክርስቶስ አካል የሆነው ያ ቡድንም የእግዚአብሐርን ዓላማዎች ለመፈጸም ጠንካራና ብርቱ ኃይል ይሆናል። በሌላም በኩል ሰዎች ሌሎች ከእነርሱ ጋር ተመሳሳይ እንዲሆኑ ይፈልጋሉ። ሰዎች፥ የተለያዩ ባህሎችና ሥረ መሠረቶች ወይም የተለያዩ ስጦታዎችና ችሎታዎች ካሏቸው ሰዎች፥ ጋር ከመሆን ይልቅ፥ ተመሳሳይ ሥረ-መሠረቶችና ባህሎች፥ እንዲሁም ተመሳሳይ ስጦታዎች ካሏቸው ሰዎች ጋር መሥራትን ይመርጣሉ። ይህ ምርጫ አንድነትን በማምጣት ቤተ ክርስቲያንን የሚያጠናክር ቢመስለንም፥ በመሠረቱ የዚህ ውጤት ደካማ ቤተ ክርስቲያንን መመሥረት ነው። በብሉይ ኪዳን ውስጥ የእግዚአብሔር ቃል አቀባዮች ሆነው ያገለገሉትን ነቢያት ሕይወት ስንመረምር እጅግ የተለያዩ ዓይነት ሰዎች እንደነበሩ እንመለከታለን። እንደ ኤልያስና ኤልሳዕ ያሉት የነቢያት ጉባኤ አባላት ሲሆኑ፥ የነቢይነት ሥራቸውን የሚያከናውኑት ሙሉ ጊዜያቸውን ሰጥተው ነበር። እንደ አሞጽ ያሉት ሌሎች ደግሞ ግብርናን በመሰለ ሌላ ሥራ ላይ ተሰማርተው ነበሩና የነቢይነት ሥራን ለተወሰነ ጊዜ ብቻ የሚሠሩ ነበሩ። እንደ ዳንኤልና ኢሳይያስ ያሉት ደግሞ ከንጉሣዊ ቤተሰብ የመጡ የኅብረተሰቡ ከፍተኛ መደብ አባሎች ነበሩ። እንደ ሚክያስ ያሉት ከድሀ ወይም ከዝቅተኛ መደብ የመጡ ነበሩ። ሌሎች ደግሞ ነቢያት ብቻ ሳይሆን፥ ካህናትም ነበሩ (ለምሳሌ፡- ሕዝቅኤል)። እነዚህ ሁሉ እጅግ የተለያዩ ቢሆኑም እንኳ እግዚአብሔር ሁሉንም የራሱ ቃል አቀባዮች ሆነው እንዲያገለግሉ አድርጎ ነበር። የውይይት ጥያቄ፣ የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን የተለያዩ ስጦታዎች ባሏቸው የተለያዩ ሰዎች የተገነባች መሆኗን ማስታወስ የሚያስፈልገው ለምንድን ነው? ለ) እያንዳንዱ ክርስቲያን የተሰጠውን ስጦታ በማወቅ ቤተ ክርስቲያንን ሲያገለግል ጠቃሚ የሚሆነው ለምንድን ነው? ሐ) ከእኛ የተለዩ ስጦታዎች ወይም ባህሎች ያሏቸውን ሰዎች በአክብሮት ላለማስተናገድ ይህ እውነት ምን ሊያስተምረን ይገባል? መ) እያንዳንዱ አባል የተሰጠውን ስጦታ እንዲያውቅና እንዲጠቀምበት ለመርዳት ቤተ ክርስቲያህ ማድረግ የምትችላቸውን ነገሮች ዘርዝር። የትንቢተ ሚክያስ ጸሐፊ ትንቢተ ሚክያስ የተጻፈው ሚክያስ በተባለ ሰው ነው። ስለ ነቢዩ ሚክያስ የምናውቀው ነገር እጅግ በጣም ጥቂት ነው። ሚክያስ የመጣው አንዳንድ ጊዜ ሞሬሼት ተብላ ትጠራ ከነበረችው ከሞሬሽትጌት ከተማ ነው (ሚክያስ 1፡1፥14)። ይህች ከተማ የምትገኘው ከኢየሩሳሌም ደቡብ ምዕራብ 30 ኪሎ ሜትር ርቃ በሜድትራንያን ባሕርና በኢየሩሳሌም ከተ መመካከል ነበር። በኋላ ቀርነታቸው እጅግ ከሚታወቁት የይሁዳ ክፍሎች አንዱ በመሆንዋ ትታወቅ ነበር፡፡ በዚህች ከተማ ብዙ ድሀ ገበሬዎች ይኖሩ ነበር። ሚክያስ የይሁዳ ሕዝብ በድሆች ላይ ስለፈጽሟቸው ማህበራዊ ኃጢአቶች የፍርድ ቃል በተናገረበት በመጽሐፉ ውስጥ ስለ እነዚህ ድሆች የነበረውን አትኩሮት ልንመለከት እንትላለን፡፡ ሚክያስ በይሁዳ ሕዝብ መካከል የነቢይነት አገልግሎት የሰጠው ከ750-686 ዓ.ዓ. ነበር። ይህም በኢዮአታም፣ በአካዝና በሕዝቅያስ ዘመነ መንግሥት መሆኑ ነው (ሚክያስ 1፡1)። ምናልባት ከትንቢቶቹ አብዛኛው ክፍል የተነገረው በንጉሥ ሕዝቅያስ መሪነት ተካሄዶ ከነበረው መንፈሳዊና ማኅበራዊ ተሐድሶ በፊት ሳይሆን አይቀርም። በዚያን ዘመን ያገለግል የነበረ ነቢይ ሚክያስ ብቻ አልነበረም። ሆሴዕና አሞጽ በእስራኤል ላይ ትንቢት ሲናገሩ፥ በይሁዳ ደግሞ ከሚክያስ ጋር ኢሳይያስም ያገለግል ነበር። በኢሳይያስና በሚክያስ መልእክቶች መካከል ካለው ግልጽ ተመሳሳይነት የተነሣ (ሚክያስ 4፡1-3 ና ኢሳይያስ 2፡1-4)፥ ብዙ ምሁራን ሚክያስ ኢሳያይስን እንደሚያውቅና ምናልባትም የእርሱ ደቀ መዝሙር እንደነበረ ይናገራሉ። የኢሳይያስ አገልግሉት በኢየሩሳሌም ከተማ ውስጥ ሲሆን፥ የሚክያስ አገልግሎት ደግሞ ምናልባት ደግሞ በገጠር የነበረ ሊሆን ይችላል። ሚክያስ በነቢይነቱ በሕዝቡ መካከል የነበረው ምስክርነት መልካም ነበር፤ እንዲሁም ከብዙ ዓመታት በኋላ በኤርምያስ ዘመን፥ ኤርምያስ በኢየሩላሉም ላይ በተናገረው ትንቢት ምክንያት ሕዝቡ ከመገደል የተረፈው የሚክያስን ትንቢት በመመልከታቸው ነበር (ኤር. 26፡15-19 ተመልከት)። እግዚአብሔር በይሁዳ መንፈሳዊ እንቅስቃሴ ለመጀመር፥ እንደ ኢሳያይስ ካሉ ነቢያትና ፈሪሀ እግዚአብሔር ካደረበት ንጉሥ ሕዝቅያስ ጐን ሚክያስንም ተጠቅሞበታል። የእግዚአብሔር ፍርድ ለብዙ ዓመታት ተፈጻሚ ሳይሆን የቆየው በእርሱ ምክንያት ነበር።  የትንቢተ ሚክያስ ታሪካዊ ሥረ መሠረት ሚክያስ የተወለደው ንጉሥ ዖዝያን በይሁዳ ዙፋን ላይ እያለ ነበር። ዖዝያን እግዚአብሔርን የሚፈራ ታላቅ መሪ ነበር። በእርሱ አመራር ወቅት በእስራኤል ፍጹም ሰላምና ብልጽግና ነበረ። ሰዎች የጣዖት አምልኮአቸውን እየተዉ በቤተ መቅደስ እግዚአብሔርን ያመልኩ ነበር። ከፍተኛ የሆነ መንፈሳዊ መነቃቃት የታየበት ጊዜ ነበር። ዳሩ ግን ሀብትና ንግድ ዕድገት እያሳየ በመሄዱ ምክንያት አዲስ ዓይነት ሰዎች በይሁዳ ተነሡ። እነዚህ ነጋዴዎች እጅግ ሀብታሞች ስለሆኑ በይሁዳ እጅግ ይከበሩ ጀመር። የሚያሳዝነው ግን ለሀብት የነበራቸው ስግብግብነት ገበሬዎችንና ድሆችን እንዲጨቁኑና ከታዋቂ ሰዎችና ከመሪዎች ጋር በመሆን በተራው ሕዝብ ላይ የፍትሕ መዛባት እንዲያደርሱ አደረጋቸው። ንጉሥ ዖዝያን በሞተ ጊዜ ነገሮች ቀስ በቀስ መለወጥ ጀመሩ። ልጁ ንጉሥ ኢዮአታም በአባቱ ዘመን የነበረውን ሀብትና ሰላም ለማስጠበቅ ወይም ለማቆየት ችሎ ነበር። ሚክያስ የእግዚአብሔር ነቢይ ሆኖ በይሁዳ ማገልገል የጀመረው በእነዚህ ጊዜያት ነበር። የኢዮአታም ልጅ አካዝ በነገሠ ጊዜ ነገሮች ሁሉ ፈጥነው ተቀየሩ። እግዚአብሔርን የማይፈራ ሰው ስለነበር ሕዝቡን ፈጥኖ ወደ ጣዖት አምልኮ መለሳቸው። በመሆኑም፥ በይሁዳ የነበረው መንፈሳዊና ሥነ ምግባራዊ ሁኔታ እጅግ ተበላሸ። የሰው ልጆች መሥዋዕት ተደርገው የሚቀርቡበት የጣዖት አምልኮ ተስፋፋ። የሃይማኖት መሪዎች የነበሩት ካህናትና ነቢያት የእግዚአብሔርን ቃል ስለመናገርና ማስተማር የማይገባቸው ሆኑ። በዚህ ፋንታ ለገንዘብ መሯሯጥ ጀመሩ። የፖለቲካ መሪዎች፥ ነገሥታትና መሳፍንት ለራሳቸው ደኅንነትና ዋስትና ብቻ በመጨነቅ፥ የድሆችን፥ የመበለቶችንና የሙት ልጆችን ጥሪት የሚነጥቁ ሆኑ። ቤተሰብ መፈራረስ ጀመረ፤ በምድሪቱም ሁሉ አለመተማመን ነገሠ (ሚክያስ 7፡5-6)። የዖዝያንና የኢዮአታም የሰላም ጊዜያት አከተሙ። የእስራኤል ንጉሥ ፋቁሔና የሶርያ ንጉሥ ረኦሶን ይሁዳን ይወጉ ጀመር። በዚህ ምክንያት ንጉሥ አካዝ የአሦርን እርዳታ ለመነ። አሦርም ሶርያን በ732 ዓ.ዓ.፥ እስራኤልን ደግሞ በ722 ዓ.ዓ. አሸነፈች። ሚክያስ የሰማርያን ውድቀት አመለከተ (ሚክያስ 1፡6)። አንድ ቀን ይሁዳ በተመሳሳይ መንገድ በምርኮ እንደምትወሰድ በማወቅ ይህንን ከፍተኛ ኃዘን ይጠባበቅ እንደነበረ ጥርጥር የለውም። የሚክያስ አብዛኛው መልእክት ሥነ-ምግባራዊና መንፈሳዊ ክፋት የነበረበትን ይህን ጊዜ ያመለክታል።  ንጉሥ ሕዝቅያስ ወደ ሥልጣን በመጣና ሁኔታዎች መለዋወጥ በጀመሩ ጊዜ ሚክያስ እጅግ ሳይደሰት አልቀረም። ሕዝቅያስ ሕዝቡን ወደ እግዚአብሔር ለመመለስ የጣረ መልካም ንጉሥ ነበር። በዚህ ተሐድሶ ሚክያስ እንደ ተካፈለ ጥርጥር የለውም። ሕዝቅያስ ይሁዳ ራሷን ከጠላቶችዋ የምትጠብቅበትን መከላከያ አጠንክሮ ነበር። ነገር ግን ምንም አልረዳውም። በ701 ዓ.ዓ. አሦር ይሁዳን በማጥቃት አብዛኛውን የይሁዳ ምድር ያዘች። ኢየሩሳሌም የዳነችው በእግዚአብሔር ጣልቃ ገብነት ብቻ ነበር (2ኛ ነገሥት 18-19)። ሚክያስ ይህ ጥፋት ሕዝቡ በእግዚአብሔር ላይ በሠሩት ኃጢአት ምክንያት አንድ የሚመጣባቸው ምልክት እንደሆነ ተገንዝቦ ነበር። የውይይት ጥያቄ፣ ስለ ሚክያስ ከመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት አንብብ። ስለ ትንቢተ ሚክያስ የተጠቀሱትን ጠቃሚ እውነቶች ዘርዝር። የትንቢተ ሚክያስ አስተዋጽኦ 1. ሚክያስ በሰማርያና በኢየሩሳሌም ላይ የተናገራቸው ትንቢቶች (ሚክያስ 1)፥  2. ሚክያስ በይሁዳ መሪዎች ላይ የተናገራቸው ትንቢቶች (ሚክያስ 2-3)፡  3. ሚክያስ ስለ ጽዮን ተሐድሶ የተናገረው ትንቢት (ሚክያስ 4-5) ሀ. የሚመጣው የእግዚአብሔር መንግሥት (ሚክያስ 4) ለ. ንጉሥና እረኛ ሆኖ የሚመጣው የመንግሥቱ ገዥ (ሚክያስ 5)፡  4. ሚክያስ ስለ ይሁዳ ክፋትና ስለሚመጣበት ፍርድ የተናገረው ትንቢት (ክያስ 6፥7፡6)። 5. ሚክያስ፥ የእስራኤል ቅሬታዎች በወደፊቱ የእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ ስለሚቀበሉት ይቅርታ የተናገራቸው ትንቢቶች (ሚክያስ 7፡7-20)። (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡) የመመዘኛ ጥያቄዎችን ለማግኘት ከታች ያለውን ሊንክ (መስፈንጠሪያ) ይጫኑ፡፡

የትንቢተ ሚክያስ መግቢያ Read More »