የአዲስ ኪዳን መጽሐፍ ቅዱስ ጥናት

1ኛ ቆሮ.15፡1-19

በቆርንቶስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ስለ ምእመናን ሙታን ትንሣኤ የሚክዱ እንዳነበሩ ከአፃፃፉ እንረዳለን፡፡ የምእመናንን ትንሣኤ መካድ የክርስቶስን ትንሣኤ መካድ መሆኑን ያስረዳቸዋል። የክርስቶስንም ትንሣኤ መካድ ጠቅላላ የክርስትናን ሃይማናት መካድ እንደሆነ ያስረዳቸዋል። ስለዚህ ክርስቶስ ተነሥቷል፤ እርሱም ከተነሣ በእርሱ የሚያምኑትም ይነሣሉ!  ጥያቄ 23. ስለ ትንሣኤ ውይይት ሲጀምር በቁጥር 1 እና 2 ላይ ለምን ስል መሠረታዊ ወንጌል ይጠቅሳል?  ጥያቄ 24. ከቁጥር 3-11 ሁለት ዓይነት የክርስቶስ ትንሣኤ ማረጋገጫዎች ይጠቅሳል። ምንና ምን ናቸው?  ጥያቄ 25. ከቁጥር 12-19 ባለው ክፍል ውስጥ የምእመናንን ትንሣኤ በምን ላይ ይመሠርተዋል?  ቁጥር 1 እና 2:- ሐዋርያው ስለ ትንሣኤ ትምህርቱን ሲጀምር ስለ ወንጌል ያስታውሳቸዋል። የሰሙት ወንጌል ስለ ክርስቶስ ትንሣኤ ያበስራል። ለጳውሎስ አንድ ወንጌል ብቻ ነው ያለው፤ ይኸውም የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ነው። ጳውሎስ ይህንን ወንጌል ሲያስተላልፍ የራሱን ሃሳብ ላለመጨመርና አሕዛቦች እንዳያምኑ ሊያደርግ የሚችለውን ነገር ላለማስቀረት ሲል በጣም ይጠነቀቅ ነበር። ጳውሎስ በጥንቃቄ የሰበከው ወንጌል በቆርንቶስ ክርስቲያኖች ዘንድ ተቀባይነት አግኝቷል፡፡ ሙሉ እምነታቸውንም በወንጌሉ ላይ በማድረግ ለመዳን ችለዋል። ይህም ቢሆን፥ ጳውሎስ የሰበከላቸውን ወንጌል አንድም ሳያስቀሩ በእምነታቸው መግፋት እንደሚገባቸው ያሳስባቸዋል። አንዳንድ የቆሮንቶስ ክርስቲያናች ትንሣኤ የለም በማለት ወንጌልን ለመቀየር ሞክረዋል። ጳውሎስም ከወንጌል የሚገኘውን ደህንነት ሙሉ በሙሉ ለማገኘት አንድ ሰው እስከ መጨረሻው በእውነተኛው ወንጌል ማመን እንደሚገባው ይናገራል። ወንጌሉን ለመቀየር የሚደረግ ማንኛውም ሙከራ የሰውዬውን የመጀመሪያ እምነት ውድቅ እንደሚያደርገው አበክሮ አስገንዝቧል።  ጥያቄ 26. አንዳንዶች ዛሬ እውነተኛውን ወንጌል ለመቀየር የሚሞክሩት እንዴት ነው?  ከቁጥር 9-11:- ይህንን አስታኮ ጳውሎስ ወንጌል ምን እንደሆነ ያብራራል። በመጀመሪያ፡- በኢየሱስ ሞት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ኢየሱስ የሞተው ለእኛ ኃጢአት ሲል ነው እንጂ ለራሱ ኃጢአት ሲል አይደለም። ሁለተኛ፡- ኢየሱስ ለመሞቱ ማረጋገጫ የሚሆነን የእርሱ መቀበር ነው። አንዳንዶች ዛሬ እንደሚያስተምሩት ራሱን ስቶ አይደለም በመጨረሻ ላይ የነቃው። ሦስተኛ፡- የኢየሱስ አካል እንዳለ ነው ከሙታን የተነሣው (ከመቃብር ውስጥ ሥጋው እንዳለ ነው የተነሣው)፡፡ ይህ ትንሣኤ መንፈሳዊ ብቻ ሳይሆን አካላዊም ጭምር ነው። ለዚህም ማስረጃ የሚሆነን ሞቶ ሲነሣ ለብዙ ሰዎች መታየቱ ነው።  በዚህ ክፍል ውስጥ ሐዋርያው ስለ ሁለት የክርስቶስ ትንሣኤ ማስረጃዎች ይናገራል። እነርሱም መጽሐፍ ቅዱስና የዓይን ምስክሮች ናቸው። ስለ ክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ አስቀድሞ ብሉይ ኪዳን አስተምሮአል። ስለዚህ ሐዋርያው «መጽሐፍም አንደሚል» እያለ ይናገራል። ጌታችንም ስለዚሁ የተናገረውን ከሉቃስ 24፡44-47 ተመልከት።  ብሉይ ኪዳን ስለክርስቶስ ሞት በመዝሙረ ዳዊት 22 እና በትንቢተ ኢሳይያስ 53 ተናግሮአል። ስለትንሣኤውም ሐዋርያት ከብሉይ እንደጠቀሱ በሐዋ.2:25-28፤ 34 እና 35፤ 13:33ና 34 እናነባለን።  ለትንሣኤው የዓይን ምስክሮችም ሐዋርያትና ከ500 በላይ የሆኑት ምእመናን ናቸው። በስም የተሰበከውንም ወንጌል በልዩ ልዩ ተአምራት እያጀበ ለትንሣኤው መሰከረ። የቆሮንቶስም ክርስቲያኖች ይህንን ወንጌል ወይም የምሥራች ሰምተው አመኑ። ራሳቸው ለትንሣኤው ምስክሮች ሆኑ ማለት ነው። ጳውሎስ ምናልባትም ከሰብዓዊነቱ የተነሣውን ክርስቶስን ያየ የመጨረሻው ሰው ሳይሆን አይቀርም። እስጢፋኖስ በድንጋይ እየተወገረ ሳለ ነበር ኢየሱስን ያየው። ከዚህ ጊዜ በኋላ ነበር ጳውሎስ በደማስቆ መንገድ ኢየሱስን ያየው! (የሐዋ.9)።  ጳውሎስ ኢየሱስ ከመረጣቸው ከ12ቱ ደቀ መዛሙርት እኩል ሥልጣን እንደነበረው ያውቅ ነበር። ይህም ቢሆን በእግዚአብሔር መመረጡን ሲያስብ በጣም ነበር የሚገረመው። እንዲህ የሚገረምበት ምክንያት ቤተ ክርስቲያንን ብዙ ያሠቃየና ለብዙ ክርስቲያናት ሞት መንስኤ በመሆኑ ነው። እግዚአብሔር በጸጋው ወደ ራሱ ጠራው። በዚህም ምክንያት እንደሌሎቹ ደቀ መዛሙርት እርሱም ከሙታን የተነሣውን የጌታ የኢየሱስን ወንጌል መስበክ ጀመረ።  ከቁጥር 12-19፡- ክርስቶስ ከሙታን ከተነሣ እንግዲያስ የአማኛችም ትንሣኤ አለ በማለት የክርስቶስን ትንሣኤ ከአማኞች ትንሣኤ ጋር ያያይዘዋል። የክርስቶስ ትንሣኤ ከሌለ የክርስትና እምነት ራሱ ከንቱ እንዳሆነ ያስረዳል። የክርስትና እምነት ዋና ዋጋው በዚህ ሕይወት ሳይሆን በሚመጣው ሕይወት ስለሆነ ክርስቶስ ካልተነሣ የሚመጣውም ሕይወት አይኖርም፤ እኛም ያን ተስፋ ያደረግን «ከሰው ሁሉ ምስኪኖች ነን»።  እንገዲህ በቆሮንቶስ ያሉ ክርስቲያኖች በክርስቶስ ትንሣኤ በማመን ወንጌልን ተቀብለዋል። ግን የአማኞችን የወደፊት ትንሣኤ ክደው ነበር። ሐዋርያው ግን የክርስቶስን ትንሣኤና የአማኞችን ትንሣኤ መለያየት እንደማይችሉ ያስረዳቸዋል።  ጥያቄ 27. ሀ/ በኢየሱስ ትንሣኤ ማመን ለምን አስፈለገ?  ለ/ ለምን ኢየሱስ ለኃጢአታችን መሞቱን ብቻ አናምንም?  ሐ/ ዛሬ ለእኛ የቅዱሳን ትንሣኤ ለምን ማበረታቻ ሆነ?

1ኛ ቆሮ.15፡1-19 Read More »

1ኛ ቆሮ. 14፡26-40

ጳውሎስ ለጉባኤ አምልኮ አንዳንድ መመሪያዎችን በሚሰጥበት ጊዜ ለማስተላለፍ የሚፈልገውን መልእክት ለመረዳት ቤተ ክርስቲያኒቱ ምን ትመስል እንደነበረ ማስታወሱ አስፈላጊ ነው። ዛሬ እንደምናደርገው ቤተ ክርስቲያኒቱ በትልቅ የስብሰባ አዳራሽ ውስጥ አትሰባሰብም ነበር። አማኞች የሚሰባሰቡት በግለሰቦች ቤት ውስጥ በመሆኑ የሰዎቹ ቁጥር ከ50 ወይም 60 አይበልጥም ነበር። ስለሆነም ቤተ ክርስቲያኒቷ የኅብረት ጸሎት ወይም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚካሄድባት እንጂ በግዙፍ ሕንጻ ውስጥ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት የሚካሄድበት ዓይነት ቤተ ክርስቲያን አልነበረችም። የሰዎቹ ቁጥር ጥቂት ስለሆነ መዝሙር ለመምረጥ፥ ቃል ለማካፈል፥ በአስተርጓሚ አማካኝነት በልሳን ለመናገር፥ ወዘተ. ብዙ ነጻነት ነበራቸው። ጳውሎስ የሚከተሉትን መመሪያዎች ሰጥቷል። አምልኮ እንደ መሪዎች ወይም ኳዬርና ሰባኪ ያሉ ጥቂት ሰዎች ሁሉንም ተግባር የሚፈጽሙበትና ሌሎች በትዝብት የሚመለከቱበት ሳይሆን ምእመናን በሙሉ የሚሳተፉበት ነው። ጳውሎስም ሁሉም ትምህርት፥ ልሳን፥ ትንቢት፥ ወዘተ በማቅረብ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ እንዳለ አመልክቷል። ጳውሎስ ይህን ሲል ሁሉም ሰው ሁሉንም ነገር ማድረግ አለበት ማለቱ ሳይሆን ሁሉም ሰው ለመሳተፍ እንደሚችል መግለጹ ነበር። አምልኮው ሁሉ ለምእመናን በሙሉ ጠቃሚ መሆን አለበት። አስተርጓሚ ሳይኖር በልሳን መናገሩ ለሌሎች መንፈሳዊ ጥቅም የማያስገኝ በመሆኑ ተከልክሏል። ሰዎች የሚነገረውን አሳብ ተረድተው «አሜን» (እስማማለሁ) ሊሉ አይችሉም ነበር። የጉባኤ አምልኮ የሁሉም ስለሆነ፥ የሁሉም መረዳት ወሳኝ ነው። መልእክቱ በሚገባቸው ቋንቋ ሊተላለፍና ፕሮግራሙም እምነታቸውን የሚያንጹትን ነገሮች ሊያካትት ይገባል። (ይህ አንድ ሰው ለቡድኑ እንዲጸልይ በሚጠየቅበት ጊዜ ለራሱ መጸለይ ወይም በልሳን መናገሩ ትክክል እንዳልሆነ የሚያመለክት ይመስላል። ሁሉም የግለሰቡን ጸሎት ካልሰሙ ጥያቄውን ማጽደቃቸውን ለማሳየት «አሜን» ሊሉ አይችሉም። የጉባኤ አምልኮ ዓላማ የግል ጸሎት፥ ጥያቄ ወይም በረከት ሳይሆን፥ የሁሉም በአንድነት መሳተፍ ነው።) ነገሮች በሥርዓትና በአግባቡ ሊከናወኑ ይገባል። ሰዎች በራስ ወዳድነት ስጦታዎቻቸውን ለማሳየት በመፈለጋቸው ምክንያት የቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን በሁከት ሳትሞላ አትቀርም። ጉባኤው ብዙ ሰዎች በአንድ ጊዜ በሚናገሯቸው የልሳንና የትንቢት መልእክቶች፥ እንዲሁም በሴቶች ጫጫታ ይታወክ ነበር። ነገር ግን አምልኮ ሥርዓትን የተከተለና አግባብነት ያለው ሊሆን ይገባል። በሌላ አገላለጽ፥ አምልኮ ለሕዝቡ ባሕል በሚስማማ፥ በሚጥም፥ ሕዝቡን ደስ በሚያሰኝ መንገድ መካሄድ አለበት። ስለሆነም፥ ጳውሎስ ለቤተ ክርስቲያን አምልኮ የሚያገለግሉ መመሪያዎችን ሰጥቷል። ሀ. ሰዎች በልሳን ለመናገር ከፈለጉ ሊፈቀድላቸው ይገባል። ነገር ግን ተራ በተራ መናገር ይኖርባቸዋል። በልሳን በሚናገሩበት ጊዜ ደግሞ መልእክቱ መተርጎም አለበት። ተርጓሚ ከሌለ ዝም ብለው በልባቸው መጸለይ አለባቸው። በአንድ የአምልኮ ጊዜ ሁለት ወይም ሦስት ሰዎች ብቻ በዚሁ መንገድ መናገር ይኖርባቸዋል። ለ. ሰዎች ትንቢት መናገር ቢፈልጉ ተፈቅዶላቸው ነበር። ተራ በተራ ትንቢት መናገር ይቻላል። ትንቢትም ሆነ ልሳን በመንፈስ ቅዱስ ቁጥጥር እንጂ ራስን በመሳት (in a trance) ሊነገር አይገባም። መንፈስ ቅዱስ እንደ ሰይጣን ሰዎች ከአእምሯቸው ውጭ እንዲሆኑ አያደርግም። ግለሰቡ አእምሮውን ሳይስት መንፈስ ቅዱስንና እርሱ የሚናገረውን ይሰማል። ትንቢት የሚነገርበት ዓላማ ግለሰቡ የተሰማውን እንዲናገርና ለሌሎች መልእክት የማካፈል ዕድል እንዲያገኝ ሳይሆን፥ የእግዚአብሔርን መልእክት ለሕዝቡ ለማስተላለፍ ነው። ስለሆነም፥ እርሱ እየተናገረ ሳለ እግዚአብሔር ተጨማሪ ማብራሪያ ለመስጠት በሌላ ሰው አማካኝነት የትንቢትን ቃል ከላከ፥ የመጀመሪያው ተናጋሪ ተራ ሊለቅለት ይገባል። በመጨረሻም፥ እንደ ልሳን ሁሉ በአንድ ጉባኤ ሁለት ወይም ሦስት ሰዎች ብቻ ትንቢትን እንዲናገሩ ተፈቅዷል። ከቡሉይ ኪዳን በተለየ መልኩ፥ የአዲስ ኪዳን ትንቢት እግዚአብሔር ራሱ የሚናገረውን ያህል ጠንካራ ሥልጣን ያለው አይመስልም። አንድም የአዲስ ኪዳን ነቢይ፥ «እግዚአብሔር እንዲህ ይላል» እያለ ሲናገር አንመለከትም። ክርስቲያኖችም ትንቢትን በሁለት መንገዶች እንዲመረምሩ ተነግሯቸዋል። በመጀመሪያ፥ ቃላቱ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር መስማማታቸውን ለመመርመር ትንቢትን እንፈትናለን። እግዚአብሔር ሊዋሽ ስለማይችል በአንድ በኩል (በሰው ወይም በመጽሐፍ ቅዱስ) የተናገረውን መልእክት አይቃረንም። ስለሆነም የተነገረው ትንቢት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በግልጽ ከተጻፈው ወይም ከመጽሐፍ ቅዱስ ዐበይት መርሆች ጋር የሚጻረር ከሆነ ትንቢቱን መቀበል አያስፈልግም። ሁለተኛ፥ ትንቢቱ ለሁሉም ሰው የሚጠቅም መሆኑን መመርመር አለብን። ለሕዝቡ ሁሉ የማያገለግልና ቤተ ክርስቲያንን የማያንጽ ከሆነ፥ ትንቢቱን መቀበል አያስፈልግም። ወይም ጉዳዩ ለሚመለከታቸው ብቻ ማካፈል ያሻል። ሐ. ሴቶች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ዝም ሊሉ ይገባል። ይህ ምንባብ በክርስቲያኖች መካከል ብዙ ውይይቶችንና የተለያዩ አመለካከቶችን አስከትሏል። በሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ያልተደገፉ የሚመስሉ ሁለት የተራራቁ አመለካከቶች አሉ። በመጀመሪያ፥ አንዳንድ ክርስቲያኖች ሴት በፍጹም በጉባኤ ላይ መናገር የለባትም ይላሉ። እነዚህ ወገኖች ሴቶች ማስተማር፥ መስበክ፥ ማካፈል፥ መጸለይ፥ ወዘተ… እንደማይችሉ ይናገራሉ። ሁለተኛ፥ ሌሎች ክርስቲያኖች እነዚህ የጳውሎስ ትእዛዛት ከእኛ ጋር እንደማይዛመዱ ያስረዳሉ። እነዚህ ትእዛዛት የተሰጡት ወንዶች ሴቶችን በሚንቁበት ዘመንና የሴት የቤተ ክርስቲያን ውስጥ መናገር የተሳሳተ ወይም የዓመፅ ምልክት ተደርጎ በሚወሰድበት ባሕል ውስጥ ለነበሩት ሰዎች እንደሆነ ያስረዳሉ። ጊዜው ስለተቀየረና ዘመናዊ ባሕሎች የሴቶችን እኩልነት ስለተገነዘቡ፥ ሴቶች የወንዶችን ያህል እኩል ድርሻና ሥልጣን ይይዛሉ። ተገቢው መጽሐፍ ቅዱሳዊ አመለካከት የሚውለው በእነዚህ ሁለት የተራራቁ አመለካከቶች መሀል ይመስላል። የትኛውንም አመለካከት ብንከተል፥ ጳውሎስ ቀደም ሲል በ1ኛ ቆሮንቶስ 11፡2-16 የተናገረውን ማስታወስ ይኖርብናል። በዚህ ክፍል ጳውሎስ ሴቶች የመጸለይና ትንቢት የመናገር ፈቃድ እንዳላቸው በማሰብ፥ ይህንኑ አገልግሎት በሚሰጡበት ጊዜ ከባሕላቸው ጋር ላለመቃረን ራሳቸውን መሸፈን እንዳለባቸው ገልጾአል። በኢዩኤል 2፡28-32 የተሰጠውና በሐዋርያት ሥራ 2፡17-21 የተጠቀሰው የመንፈስ ቅዱስ የተስፋ ቃል ወንዶችን ብቻ ሳይሆን ሴቶችንም ይጨምራል። ስለሆነም፥ የአዲስ ኪዳን ሴቶች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሊናገሩና ሊያገለግሉ እንደሚችሉ በግልጽ ያሳያል። ክርስቲያኖች ከሚይዟቸው የተለያዩ አተረጓጎሞች አንዳንዶቹ ከዚህ በታች ተዘርዝረዋል። እንደ እግዚአብሔር ቃል ተማሪ፥ አንተና ቤተ ክርስቲያንህ ይህን ክፍል በምታዛምዱበት ሁኔታ ላይ መንፈስ ቅዱስ እንዲመራችሁ በጸሎት ጠይቁ። አንዳንድ ምሁራን ጳውሎስ እግዚአብሔር የአስተዳደርና የሥልጣን ደረጃ ዎችን ስለወሰነ ሴቶች በቤትም ሆነ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለባሎቻቸው እንዲገዙ ለማስረዳት መፈለጉን ይገልጻሉ። ስለሆነም፥ ሴቶች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከመናገር ይልቅ ያልተገነዘቧቸውን ነገሮች ወደቤታቸው ከተመለሱ በኋላ ከባሎቻቸው በመጠየቅ አክብሮታቸውን ማሳየት ያስፈልጋቸው ነበር። ሌሎች ምሁራን ጳውሎስ የተጋፈጠው ችግር ስለ መጽሐፍ ቅዱስ በቂ እውቀት ያልነበራቸውና በክርስትና እምነት ከወንዶች ጋር እኩል በመሆናቸው ምክንያት ባገኙት አዲስ ነጻነት የተደሰቱት ሴቶች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የፈጠሩት ሁከት እንደነበረ ይናገራሉ። እነዚህ ሴቶች ስለ ትንቢት አተረጓጎም፥ ወዘተ. እየተንጫጩ ይከራከሩ ነበር። ስለሆነም፥ ጳውሎስ እነዚህ ሴቶች ቤት ውስጥ ከባሎቻቸው ጋር እንዲወያዩና ቤተ ክርስቲያን ውስጥ መከራከራቸውን እንዲያቆሙ አዟል ይላሉ። ነገር ግን ጳውሎስ በክርክሩ ውስጥ ስለሚሳተፉት ወንዶች ምንም ሳይናገር ለምን ሴቶችን ብቻ እንደኮነነ መረዳቱ አስቸጋሪ ነው። ሴቶች መቼ መናገር እንዳለባቸው የሚያመለክት ተጨማሪ መመሪያ ሳይሰጥ በደፈናው ዝም እንዲሉ ያዘዛቸው ለምንድን ነው? ሌሎች ደግሞ የጳውሎስ ትልቁ ግዳጅ አማኞች ለሌሎችና ለእግዚአብሔር አክብሮት በሚያሳይ መልኩ የጸጋ ስጦታዎቻቸውን በመጠቀም ቤተ ክርስቲያንን ማነጻቸው ነው ይላሉ። ለሌሎች ሰዎች አክብሮትን ማሳየት ከሚቻልባቸው መንገዶች አንዱ ለሴቶች ተገቢ የሆነውን ባሕላዊ ግንዛቤ መጠበቅ ነበር። የጥንቱ ባሕል ሴቶች በሕዝብ ፊት እንዳይናገሩ ስለሚከለክል፥ ሴቶች ባሕሉን በማክበር በቤተ ክርስቲያንም ይህንኑ ተግባር ከመፈጸም መታቀብ ነበረባቸው። ጳውሎስ ሴቶች በሕዝብ ፊት ሊጸልዩና ትንቢትን ሊናገሩ የሚችሉባቸው ጊዜያት እንዳሉ ቢናገርም። ጉዳዩ ባሕላዊ ጫና እንዳለው ግልጽ ነው። በአጠቃላይ መልኩ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ተገቢው ነገር የሴቶች በጉባኤ ዝም ማለት ነበር። በዘመናችን ባሕሉ ተለውጦ የሴቶች በጉባኤ ላይ መናገር ግራ መጋባትንና ነውረኝነትን የማያስከትል ከሆነ፥ ሴቶች እንዲናገሩ ሊፈቅድላቸው ይገባል። በመጨረሻም፥ ስለ ትንቢትና ልሳን በሚናገሩ አሳቦች ላይ በማተኮር አስተያየታቸውን የሚሰጡ ወገኖች አሉ። ጳውሎስ ቤተ ክርስቲያን ትንቢቶችን በጥንቃቄ ስለምትመዝንበት ሁኔታ እያስተማረ ነበር። ሴቶችም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ትንቢት ሊናገሩ እንደሚችሉ ተፈቅዶላቸው ነበር። ነገር ግን ቤተ ክርስቲያን ትንቢቶችን መዝና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ወይም ከእግዚአብሔር መሆን አለመሆናቸውን በምትወስንበት ሂደት ውስጥ ሴቶች ዝም ማለት ነበረባቸው፡፡ ወንዶች ስለ ትንቢት እንዲወያዩ በመፍቀድ በመጽሐፍ ቅዱስ መርሆ መሠረት ለወንዶች የተሰጠውን ሥልጣን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያንጸባርቁ ነበር። ሴቶች የተወሰነ አመለካከት ስለተወሰደበት ምክንያት ጥያቄ ቢኖራቸው በቤታቸው ውስጥ ባሎቻቸውን መጠየቅ ይኖርባቸዋል። ጳውሎስ ሴቶች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እውቅና በተሰጠው የማስተማር

1ኛ ቆሮ. 14፡26-40 Read More »

1ኛ ቆሮ.14፡1-25

ጥያቄ 9. ከቁጥር 1-5 ባለው ክፍል ውስጥ ከልሳን ይልቅ በትንቢት መናገርን የመረጠው ለምንድነው?  ጥያቄ 10. ልሳን ቤተ ክርስቲያንን የማያንጽ የሆነበት ምክንያት ምንድነው?  ጥያቄ 11. ልሳን የሚናገር ሰው ዓላማ ምን መሆን አለበት?  ጥያቄ 12. በቁጥር 22 ላይ ልሳን ለማያምኑ ምልክት ነው እንጂ ለሚያምኑ አይደለም የሚለውን አብራራ።  ዛሬ እንዳሉት ብዙ ቤተ ክርስቲያኖች፥ የቆርንቶስም ቤተ ክርስቲያን በልሳን የመናገርን ሥጦታ በማጋነን ቤተ ክርስቲያኗን ጎድተዋታል። በዚህ ጥናት ጳውሉስ በልሳን ስላመናገር የሰጠውን ተጨማሪ ትምህርት እንመለከታለን።  ቁጥር 1-5:- ከልሳን ይልቅ ትቢት የሚመረጥበት፥ ትንቢት ማህበሩን ስለሚያንጽ ነው። እንደምታስታውሰው ትንቢት ማለት ሁሌ የወደፊቱን ብቻ መናገር ሳይሆን የአግዚአብሔርን መልእክት ለምዕመናኑ ማስተላለፍም እንደሆነ አይተናል። የትንቢት ሥጦታ የነበራቸው ሰዎች በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ የሚገኙትን ቃል ኪዳናት በማካፈል፥ ሌሎችን የማበረታታት፥ የማጽናናትና የመቀስቀስ ችሎታ አላቸው። ልሳን ግን ራስን ብቻ ስለሚጠቅም የፍቅርን መንገድ ይረሳል። በልሳን የሚናገሩ በነገሩ ከመደሰታቸው የተነሣ ሌሎችን የማንገዋለልና ለሌሎች ያለማሰብ ዝንባሌ ይታይባቸው ነበር። እንዲሁም ልሳን የማይናገሩትን አማኞች በመንፈስ አልተሞላችሁም ብሎ ማንገዋለል ያለ ፍቅር መጓዝ መሆኑን እናስተውል።  ጥያቄ 13. ሀ/ ለምንድነው አንዳንድ ክርስቲያኖች በልሳን መናገሩ ለአንድ ክርስቲያን አስፈላጊ ነገር ነው የሚሉት? ለ/ በልሳን ከመናገር ይልቅ ትንቢት መናገሩ የበለጠ አስፈላጊ የሆነበት ምክንያት ምንድነው?  ከቁጥር 6-12:- ልሳን ትርጉሙ ካልታወቀ ምንም ትርጉም የማይሰጥ ጩኸት ይሆናል። ክርስቲያን ከዚህ ትርጉም የለሽ እርምጃ ራሱን መጠበቅ አለበት። እንኳን አእምሮ ያለው ሰው ቀርቶ የሙዚቃ መሣሪያ እንኪ ጩከቱ ትርጉም አለው። ስለዚህ አንድ ክርስቲያን መመሪያው ፍቅር መሆን ስላለበት ሌሎችን ለማነጽ እንዲችል ለተሰጠው ልሳን ትርጉም ደግሞ አንዲሰጠው መጸለይ አለበት እንጂ እሰይ በልሳን ተናገርኩ ብሉ ረክቶ መቀመጥ የለበትም።  እንዲሁም ትርጉሙን ካወቀው በልሳን መናገሩ ቀርቶ በሚታወቀው ቋንቋ መልእክቱን በቀጥታ ጉባኤው በሚያውቀው ቋንቋ ብቻ ያስተላልፋል። እንደ ትንቢት መናገር የመሳሰሉትን በቀጥታ ቤተ ክርስቲያንን የሚያንፁትን ስጦታዎች መመኘቱ ይሻላል።  ጥያቄ 14. ሀ/ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሰዎች ሲናገሩ በልሳን ሰምተህ ታውቃለህ? ለ/ ልሳኑ ተተርጉሞ ነበር? ሐ/ ለምንድነው የተጠቀሙበት? ለማበረታታት፥ ለማጽናናት፥ ወዘተ።  ከቁጥር 13-19፡- “ስለዚህ በልሳን የሚናገር እንዲተረጉም ይጸልይ”። ይህ የፍቅር መንገድ ነው። ደግሞም በአእምር ሕፃን አለመሆንን ያሳያል። በማይጠቅም ነገር ረክቶ የሚቀመጥ ሕፃን ብቻ ነው። ዝቅ ብሎ በቁጥር 20 ላይ ይህንኑ ሃሳብ ይዞ «በአእምሮ ሕፃናት አትሁኑ፤ ለክፋት ነገር ሕፃናት ሁኑ እንጂ» ይላል።  በቅዱስ ቁርባን ሥነ ሥርዓታቸውም ጊዜ እያንዳንዳቸው የራሳቸውን እራት ብቻቸውን በመብላት ሌሎችን መርሳት እንደለመዱ አሁንም በልሳን መናገር የየግል ደስታቸውን እንጂ ወንድሜ እንዴት ይሆን አላሉም። በማይገባው ቋንቋ በወንድሜ ፊት በምናገርበት ጊዜ መንፈሱን እረብሸበት ይሁን ብሎ አለማሰብ የፍቅርን መንገድ መርሳት ነው። ስለዚህ ሐዋርያው በማህበር ውስጥ እልፍ ቃላት በልሳን ከምናገር ይልቅ በሚታወቅ ቋንቋ አምስት ቃላት መናገርን እመርጣለሁ ብሏል። ይህም የሚሰሙትን ለማነጽ ስለሚጠቅም ነው።  ከቁጥር 20-25፡- በልሳን በማህበር በመናገር የማያምኑትንም ማሰናከል አለ። «አብደዋል» እስኪሉ ድረስ መልካሚቱን የጌታን መንገድ በሕፃንነታችን ማሰደብ ተገቢ አይቻልም።  ሐዋርያው ስለ ልሳን ከብሉይ ኪዳን በመጥቀስ ትክክለኛውን ዓላማ ያስተምራል። በቁጥር 22 ላይ “እንግዲያስ በልሳኖች መናገር ለማያምኑ ምልክት ነው» ይላል። ይህ ምን ማለት ነው? በመጀመሪያ ሐዋርያው ኢሳ.28፡11ና 12ን ይጠቅሳል። በዚያ ትንቢት ላይ የልሳን ዓላማ አምጸኞችን ለመቅጣት ነበር። የሚነገራቸው ቃል እንዳይገባቸው ሆኖ ማቅረብ መርገም እንጂ በረከት አልነበረም። እንዲሁም አሁን ልሳን ምልክት ይሁን ከተባለ ምልክትነቱ ለማያምኑ መርገም መሆኑ መዘንጋት የለበትም።  ጥያቄ 15. ለምን ይመስልሃል ብዙ ክርስቲያኖች በተለምዶ ቋንቋ ከመናገር ይልቅ በልሳን መናገርን የሚፈልጉት?

1ኛ ቆሮ.14፡1-25 Read More »

1ኛ ቆሮ. 13፡1-13

ሐዋርያው ስለ መንፈስ ቅዱስ የከፈተውን ውይይት ያቋርጥና ስለ ፍቅር በምዕራፍ 13 መዘርዘር ይጀምራል። ዋና ነጥቡ አንድ ሰው ብዙ የመንፈስ ቅዱስ ሥጦታዎች ቢኖሩት ነገር ግን በፍቅር ካልተመላለሰ ለእግዚአብሔር መንግሥት ምንም የማይጠቅም እንደሆነ ነው። እዚህ ላይ መገንዘብ የሚገባን የመንፈስ ቅዱስ ሥጦታን መቀበልና በክርስትና ሕይወት በስሎ መገኘት አብረው ላይሄዱ እንደሚችሉ ነው። አንድ ሰው የመንፈስ ቅዱስ ሥጦታን በሥራ የሚያሳይ ሆኖ ሕይወቱ ግን ፍጹም ሥጋዊ ሊሆን እንደሚችል ነው። የቆርንቶስ ሰዎች የመንፈስ ቅዱስ ሥጦታዎች በሙላት ነበሯቸው፤ ነገር ግን በጣም ሥጋውያን እንደነበሩ ሐዋርያው ይመሰክራል፤ ( 1ኛ ቆሮ.1:4-6፤ 3:1-4)።  ጥያቄ 1. የ12:31 ላይ «ደግሞም ከሁሉ የሚበልጥ መንገድ አሳያችኋለሁ» ባላውና በምዕራፍ 13 መካከል ያለውን ግንኙነት አስረዳ።  ጥያቄ 2. ከቁጥር 1-3 የፍቅርን አስፈላጊነት ዘርዝር።  ጥያቁ 3. ከቁጥር 4-7 የፍቅርን ፀባይ ዘርዝር።  ጥያቄ 4. ከቁጥር 8-13 የፍቅርን ጽናት ዘርዝር፡፡  ሐዋርያው ስል ፍቅር በሰፊው ይጽፋል። በቆርንቶስ የነበሩ እማኞች በመንፈስ ቅዱስ ሥጦታዎች በመመካት ምን ያህል ፍቅር የተጎደላቸው ክርስቲያኖች እንደሆኑ ያስንዘባቸዋል። ያለ ፍቅር ሁሉ ከንቱ እንደሆነ ይጽፋል። ሰው ብዙ ነገርን በክርስትና ስም ቢፈጽም ያ ሁሉ ነገር ያለ ፍቅር ከሆነ ዋጋ ቢስ እንደሆነ ያስጠነቅቀናል። በ1ኛ ቆሮ. 12:31 ላይ ጳውሎስ አንደተናገረ ይህንንም የፍቅር መንገድ ከሁሉ የሚበልጥ መንገድ ይለዋል።  ከቁጥር 1-3:- የፍቅር አስፈላጊነት! ያለ ፍቅር አስደናቂ ልሳን ቢሆን፥ እውቀት ቢሆን፥ እምነት ቢሆን፥ ምጽዋት ቢሆን ፈጽሞ ዋጋ ቢስ ነው። የእግዚአብሔርን መንግሥት አይገነባም። የእግዚአብሔርን መልክና ፀባይ ባለማሳየት ለጸጋውና ለፍቅሩ መሣሪያ አይሆኑም። ስለዚህ ፍቅርን ላለመርሳት ታላቅ ጥንቃቄ እናድርግ።  ጥያቄ 5. በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ አንዳንድ ነገሮች ያለ ፍቅር ስለተሠሩ የእግዚአብሔርን ሥራ ከመሥራት ይልቅ ሥራውን ሲያበላሹ አይተሃል? እንዴት?  እዚህን መንፈሳዊ ሥጦታዎች በመጥቀስ፡- (በልሳን መናገርን፥ ትንቢት መናገርንና፥ እውቀትና እምነት) ጳውሎስ ብዙ ሰዎች ሥጦታዎቹን አንደሚመኙአቸው፥ ነገር ግን የእነዚህ ሥጦታዎች በአንድ ሰው ውስጥ መኖር የእርሱን መንፈሳዊነት እንደማያሳዩና በሥጋ ሊደረጉ እንደሚችሉ ያሳየናል። ሰዎች ዛሬም ቢሆን እነዚህንና ሌሎችን መንፈሳዊ ሥጦታዎች ለእግዚአብሔር ክብር ሳይሆን ለራሳቸው ክብር ሲያውሏቸውና ሲጠቀሙባቸው እናያለን።  ከቁጥር 4-7:- የፍቅር ፀባይ! ክርስቲያን በፀባዩ ክርስቶስን ካልመሰለ በአገልግሎቱ ፍሬቢስ ነው። በዚህ ክፍል ውስጥ የክርስቶስ ፀባይ ተዘርዝሮአል። በሮሜ 8፡29 ላይ እዚአብሔር ልጁን እንድንመስል ወስኗልና በፍቅር ፀባይ ፀባያችን ካልተለወጠ ክርስቶስን መምሰል አንችልም።  እነዚህን የፍቅር ፍሬዎች በምናጠናበት ጊዜ፥ አንድ ልናስተውል የምንችለው ነገር ቢኖር፥ ብዙዎቹ ከሌሎች ጋር ያለን ግንኙነት ላይ የሚያተኩሩ መሆናቸው ነው። ፍቅር እንዲሁ በልባችን ውስጥ የሚሰማን ስሜት ብቻ ሳይሆን በተግባርም ሊታይ የሚገባው ነገር ነው። ስለዚህም ጳውሎስ ፍቅርን በአንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ያብራራዋል፡-  1. ሌሎችን መታገሥ፡- እኛ እንደምንፈልገው ባይሆኑልንም፥ እንደምን ፈልገው ባያደርጉልንም፥ …ወዘተ መታገሥ።  2. ለሌሎች ቸርነት ማድረግ (ቸር መሆን):- የሰዎችን ችግር ለመፍታት መጣር።  3. በሌሎች አለመቅናት:- ከእኛ የበለጠ ክብር ወይም ገንዘብ ቢያገኙም አለመቅናት።  3. ፍቅር አይመካም፥ አይታበይም፡- በምንታበይበት ጊዜ ራሳችንን ከሌሎች የተሻልን ነን ብለን ከፍ ከፍ ማድረጋችን ነው። ይህንንም ብዙ ጊዜ የምናደርገው ራሳችንን ከሌሎች ጋር አወዳድረን እነርሱን ዝቅ በማድረግ ነው። 5. ፍቅር የማይገባውን አያደርግም፡- በልጆች ወይም በተናቁት ወይም በድሆች ላይ እንከን የማይገባውን አያዳርገም።  6. ፍቅር የራሱን አይፈልግም:- ከራሱ ችግሮች ይበልጥ ለሌሎች ሰዎች ችግር ያስባል፤ (ፊልጵ.2:4)  7. ፍቅር አይበሳጭም፡- ብስጭታችንን ብዙ ጊዜ የምንገልጸው ሌሎችን የሚያናደድ ንግግር በመናገር ነው።  8. ፍቅር በደልን አይቆጥርም፡- በቀልን ለመበቀል ሳይሆን ለመታረቅ ነው የሚያስበው።  9. ፍቅር ከእውነት ጋር ደስ ይለዋል እንጂ ስለ ዓመፃ ደስ አይለውም፡- ስለ ክፉ ሰዎች የሚነገር ወሪን መስማት አንዳንዴ ያስዳስተናል! በዚህም ምክንያት ደጉን ነገር ከማውራት ሰዎች የሚሠሩትን ክፉ ሥራ ለሌሎች የምናወራ ወሬኞች እንሆናለን። በምትኩ ግን ጥሩ የሆነውን ነገር መውደድ ይገባናል። የአመፃ ወሪ ሲደርሰን ይህንን ወሬ ላለመስማት ወስነን እውነት የሆነውን ለመስማት መወሰን አለብን።  10. ፍቅር ሁሉን ያምናል፥ ሁሉን ይታገሣል፥ ሁሉን ተስፋ ያደርጋል፥ በሁሉ ይጸናል፡- ሌሎች መልካም ነገር እንዲሆንላቸው ይመኛል እንጂ ያጋጥማቸዋል ተብሎ የሚገምተው መጥፎ ነገር እንዲደርስባቸው አይፈልግም።  11. ፍቅር ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም እስከሚመጣበት ጊዜ ድረስ ለዘወትር አይወድቅም።  ጥያቄ 6. ከላይ የተዘረዘሩትን በመመልከት በሕይወትህ ውስጥ ፍቅርን ታሳይ የነበረው በየትኛው ዓይነት መንገድ ነው? ፍቅርስ ሳታሳይ የቀረኸው እንዴት ነው?  ጥያቄ 7. በቤተ ክርስቲያን ውስጥና በመሪዎቹ መካከል ፍቅር የሚታይባቸው ሥፍራዎች የትኛዎቹ ናቸው? የፍቅር ፍሬዎች የሉበትም የምትለውስ ሥፍራ በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ የትኛው ነው?  በመጽሐፍ ቅዱስ ቀዳሚው የመንፈስ ቅዱስ ሥራ ፀባይ እግዚአብሔርን ወደ መምሰል እንዲቀይር እንጂ በአገልግሎት እንዲያሠልፈን አይደለም። አገልገሎት ሁለተኛ ደረጃ ነው። ስለዚህ በመንፈስ ቅዱስ ሥጦታ ላይ ከማተኮራችን በፊት በመንፈስ ቅዱስ ፍሬ ላይ እናተኩር፤ (ገላ.5፡22-26)።  ከቁጥር 8-13:- የፍቅር ጽናት! የመንፈስ ቅዱስ ሥጦታዎች ፈጽመው የማይፈልጉበት ጊዜ ይመጣል፤ ያም ጌታ ሲመለስ ይሆናል። የአሁኑ ሁኔታችን እንደሕፃንነት ጊዜ ይታያል፤ እንደመስታወት መልክ ይቆጠራል። ግን ጌታ ሲመለስ በከፊል የነበረን ሁሉ ሙሉ ይሆናል። እምነት፥ ተስፋ፥ ፍቅር ግን ጸንተው ይኖራሉ። ፍቅር ከእነዚህ ከሁለቱም ይበልጣል። ስለዚህ የቆሮንቶስ አማኞች በፍቅር ማተኮር እንዳለባቸው እንደተነገራቸው እኛም እንዲሁ የፍቅር ሕልውናችንን እናጠናክር፡፡  ጥያቀ 8. ፍቅር ከእምነትና ከተስፋ ይበልጣል የተባለው ለምንድነው?

1ኛ ቆሮ. 13፡1-13 Read More »

1ኛ ቆሮ.12:14-31

ጥያቄ 15. በቁጥር 22 እስከ 26 ባለው ክፍል ውስጥ በአካል መካከል መተሳሰብ እንዲኖር ካለ በቆሮንቶስ ምእመናን መካከል ግን ምን እንደነበር እንረዳለን?  ጥያቁ 16. ከቁጥር 28-31 ያለውንና ከቁጥር 8-11 ያለውን አወዳድረህ መመሳሰልም ሆነ ልዩነት ጻፍ።  ከቁጥር 14 – 26 ባለው ክፍል ውስጥ ሐዋርያው እንዴት የክርስቶስ አካል እንደ ሰውነት በአንድነት መስራት እንዳለበት ያስተምራል። በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እግዚአብሔር የተለያየ ሥጦታን ስለሰጣቸው ይህ በመካከላቸው መለያየትን፥ መናናቅን፥ መቀናናትን ፈጠረ። ምንም እንኳ የመንፈስ ቅዱስ ሥጦታዎች በብዛት የሚታዩበት ቤተ ክርስቲያን ቢሆንም “መለያየት” የተባለው የሥጋ ሥራ ነግሶባቸው እንደነበር እንረዳለን። አሁንም በዘመናችን የመንፈስ ቅዱስን ሥጦታዎች አሉን በሚሉ መካከል እንዲሁ ከባድ መለያየት እንዳለ እንመለከታለን። ስለዚህ የመንፈስ ቅዱስን ሥጦታዎች በመንፈስ ቅዱስ ፍሬ በሆነው በፍቅር መስራትን አንዘንጋ ( 1ኛ ቆሮ.13፤ ገላ.5፡22-26)።  ስለ ቤተ ክርስቲያን ማወቅ የምንችለው ዋነኛ የሆነውን የክርስቶስን አካል ትምህርት በመረዳት ነው። ልክ እንደ ሰው አካል ቤተ ክርስቲያን አንድ ራስ ነው ያላት። ይህም የቤተ ክርስቲያን ራስ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፤ (ኤፌ.1፡22-23)። ራስ የሆነው ከሁሉ የበላይ ሆና ይመራል፤ ከእርሱም ምሪት ሥር ደግሞ በጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ያመኑት የተለያዩ አማኞች በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነትም ከአካሉ ጋር ይገናኛሉ። የመንፈስ ቅዱስ ሥራ በዚህ ብቻ አይወሰንም፤ እያንዳንጹን ሰው ተገቢውን ቦታ አስይዞ ሥሪውን የሚፈጽምበትን ሥጦታ ይሰጠዋል። የሚሰጣቸው አንዳንዶቹ ሥጦታዎች በጣም የከበሩ ይመስላሉ! በዚህም ምክንያት የበለጠ ክብር የሚያስገኙት ለሰውየው እንደሆነ ይገመታል። ሌሎች ሥጦታዎች ደግሞ የተደበቁ ናቸው፤ ነገር ግን አካካሉ ጤንነትና ሥራ ትልቅ አስተዋፅኦ አላቸው። በዚህ ምክንያት የክርስቶስ አካል አባል የሆነ ሰው ሁሉ በጣም አስፈላጊ ነው። አንዱ ከሌላው ጋር አብሮ ስለሚሠራ ኃላፊነት ካለባቸው ከመሪዎች አንሥቶ እስከ ተራ አባል ድረስ ያለው በሙሉ ጥቅም የሚሰጥ ነው። በእግዚአብሔር አይን ሁሉም እኩል ናቸው። እንደ አንድ አካል ጤነኛ ሆነን እንሠራለን የምንለው እያንዳንዱ የአካሉ ክፍል የተሰጠውን መንፈሳዊ ስጦታ በተገቢው መንገድ ሲጠቀምበት ነው። ስለዚህ አንዱ የአካሉ ክፍል ሥጦታውን የማይጠቀምበት ከሆነ ልክ እግሩ እንደተቆረጠና አይነ ስውር እንደሆነ ሰው፥ አካሉ በአጠቃላይ አካል ስንኩል ሆኗል ማለት ነው። በዚህም ምክንያት ሌሎች አባላት እንደ እኛ ሥጦታ የላቸውም ብለን ገለልተኛ ማድረግ የለብንም። እያንዳንዱ አባል ሥጦታውን አውቆ፥ ለቤተ ክርስቲያን ዕድገት እንዲጠቀምበት የማድረግ ኃላፊነት የተሰጠው ለቤተ ክርስቲያን መሪዎች ነው።  ጥያቄ 17. ሀ/ የቤተ ክርስቲያንህ መሪዎች እንዴት አድርገው ነው እያንዳንዱ አባል መንፈሳዊ ሥጦታውን አውቆ እንዲ ያገለገል የሚያደርጉት? ለ/ ከዚህ ከሚያደርጉት ሌላ የተሻለ፥ አባላቱን በአንድነት ለቤተ ክርስቲያን ዕድገት እንዲሠሩ የሚረዳ ምንድነው ብለህ ትገምታለህ?  በዚህ ክፍል ውስጥ ደግሞ ሌላ የምናየው ዋና ትምህርት አለ። ይህም፡- “አንድ ብቸኛ የክርስቶስ አካል” መናሩን ነው። ይህም ማለት እውነተኛው የክርስቶስ አካል የተሠራው በኢየሱስ ክርስቶስ በሚያምኑት ክርስቲያናት ነው ማለት ነው። አጥቢያ ቤተ ክርስቲያኖች ያንን እውነት በከፊል የሚያንፀባርቁ መሆን አለባቸው። ይህም በሰዎች የተለያየ ስም የተሰጣቸው ቤተ ክርስቲያና (ቃለ ሕይወት፥ መካነ ኢየሱስ፥ ወዘተ) የዚህ አካል አባል ናቸው ማለት ነው። በዚህም ምክንያት ለክርስቶስ አካል ዕድገት አብረን መሥራት ይኖርብናል እንጂ በአካሉ ላይ ብዙ ክፍፍልን መፍጠር የለብንም።  ጥያቄ 18. ዓለም አቀፍ ስለሆነው የክርስቶስ አካል ያለን ግንዛቤ እንዴት አድርጎ ነው ከሌሎች ከእኛ ከተለዩ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያኖች ጋር ሊኖረን የሚገባውን ግንኙነት የሚወስነው?  ከቁጥር 27-31 ባለው ክፍል ውስጥ እንደገና ስለ መንፈስ ቅዱስ ሥጦታዎች ይናገራል። በዚህ ላይ አጥብቀን መመልከት ያለብን በመጀመሪያ ሁሉም አንድ ዓይነት ሥራ የላቸውም። ሁለተኛ በሥጦታዎች መካከል እኩል ቤተ ክርስቲያንን የማነጽ ኃይል የለም። አንዳንድ ሥጦታዎች ከሌሎች ሥጦታዎች የበለጠ ቤተ ክርስቲያንን የመገንባት ኃይል አላቸው። ቃሉን የማስተላለፍ ሥጦታዎች ከሌሎች ሥጦታዎች የበለጠ ጥቅም አላቸው።  በኤፌሶን 2:20-22 ላይ ሐዋርያትና ነቢያት የቤተ ክርስቲያን መሠረቶች ናቸው። ቤተ ክርስቲያን በዚያን ጊዜ በነበሩት ሐዋርያትና ነቢያት ትምህርት ላይ ቆማለች እንጂ በየጊዜው በሚነሡ ነቢያት አማካይነት አዲስ ትምህርትን አትቀበልም፡፡  ጥያቄ 19. ሀ/ ጳውሎስ «ነገር ግን የሚበልጠውን የጸጋ ሥጦታ በብርቱ ፈልጉ» ይላል። እነዚህ ሥጦታዎች የትኞቹ ናቸው?

1ኛ ቆሮ.12:14-31 Read More »

1ኛ ቆሮ.12:12-13

ጥያቄ 13. በመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት አማካይነት ምን ሆንን ይላል?  ቁጥር 12:- የአማኞችን አንድነት ለማስረዳት የሰውን አካል ምሳሌ ይሰጣል። የሰውነት ክፍሎች ብዙም ቢሆኑ በአንድ ኅብረት አብረው እርስ በርስ ይገለገላሉ። መንፈስ ቅዱስም የዋላባቸው ምእመናን በአድመኛነት መሰሎቻቸውን ብቻ በመጥቀስ ሌሎችን ከቡድናቸው የማያስገቡ ሳይሆኑ በተሰጣቸው ሥጦታ ሌሎችን ያገለግላሉ።  ቁጥር 13፡- በክርስቶስ አንድ አካል ተደርገናል። ይህም አንድነት የተመሠረተው በመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት አማካይነት ነው። የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 2 ለመጀመሪያ ጊዜ ተሰጠ። በዚያ የነበሩት አይሁዶች ነበሩ። አይሁዳውያን የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ተካፋዮች በመሆን በክርስቶስ አካል በቤተ ክርስቲያን ገቡ። ከዚያ በኋላ ያመኑት (የሐዋ.2:41-42፤ በተጨማሪ ቁጥር 33ን ተመልከት ) በተደጋጋሚ መንፈስ ቅዱስ እንደ መጀመሪያው ጊዜ ሳይሆን ያው በመጀመሪያው የወረደውን መንፈስ ቅዱስ ተካፋዮች ሆኑ፤ ያም በመንፈስ ቅዱስ የተጠመቁት ባመኑ ጊዜ ነበር ማለት ነው።  የሰማርያ ሰዎች በመጀመሪያ ሲያምኑ መንፈስ ቅዱስን እንዲቀበሉ የሐዋርያት እጅ መጫን አስፈላጊ ነበር፤ (የሐዋ.8፡14-18)። ከዚህ በኋላ የሰማርያም ሰዎች የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ተካፋዮች ስለሆኑ ከመጀመሪያዎቹ ተከትለው ያመኑትም ባመኑ ጊዜ ከቤተ ክርስቲያን ጋር በመንፈስ ቅዱስ ይተባበራሉ እንጂ እንደገና የሐዋርያት ወይም የሌላ ሰው እጅ መጫን አላስፈለገም። እንዲሁም አህዛብ (የሐዋ.10፡44-48) በመጀመሪያ ሲያምኑ አሕዛብም የመንፈስ ቅዱስ ሥጦታ ተካፋይ መሆናቸው ተረጋገጠ። ከዚህ በኋላ አህዛብ ሲያምኑ ወዲያውኑ የመንፈስ ቅዱስን ጥምቀት ይቀበሉና የክርስቶስ አካል ማህበረተኞች ይሆናሉ፤ የመንፈስ ቅዱስን ጥምቀት ለመቀበል ልዩ ሥርዓት አይደረገም! (የሐዋ.13:48፤ 14:21-22 ወዘተ )። በሐዋ.16 ላይም የመጥምቁ ዮሐንስ ደቀ መዛሙርት የዚሁ የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ተካፋዮች ሆኑ።  እነዚህ ሁሉ በመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት አማካይነት የአንዱ አካል ክፍሎች ሆኑ። እንግዲህ የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት በመጀመሪያ ስናምን ከክርስቶስ ጋር አንድ የሚያደርገን ሲሆን የመንፈስ ቅዱስ ሙላትም ለመጀመሪያ ጊዜ ባመንንና በመንፈስ ቅዱስ በተጠመቅን ጊዜ ተሰጥቶናል። ይህ ቁጥር 13 ላይ «አንዱን መንፈስ ጠጥተናል» ሲል መንፈስ ቅዱስን በመጠጣት መንፈስ ቅዱስ በውስጣችን ሞልቷል ማለት ነው፤ (ዮሐ.7:37-39፤ ቲቶ 3:5-7)። የመንፈስ ቅዱስ ሙላት ተደጋጋሚ ልምምድ መሆን አለበት፤ ሁልጊዜ ደጋግመን በመንፈስ ቅዱስ ልንሞላ ያስፈልጋል፤ (ኤፌ.5፡18)። የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ባመንን ጊዜ ከክርስቶስ ጋር አንድ ያደረገን መሣሪያ ስለሆነ አይዳጋገምም።  ጥያቄ 14. እንደዚህ የማያምኑ ክርስቲያን ቡድኖች እነማን ናቸው? ምን ያምናሉ? በጥናታችን መሠረት እንዴት ትመልስላቸዋለህ?

1ኛ ቆሮ.12:12-13 Read More »

1ኛ ቆር.12:1-11

በቆርንቶስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በጉባኤያቸው ብዙ ስሕተቶች ነበሩ። እስከአሁን እንኳ ሁለት ስሕተቶችን ሐዋርያው እንዳረመላቸው አይተናል፤ እነርሱም ስለ ሴቶችና ስለቅዱስ ቁርባን ነበሩ። አሁን በዚህ ምዕራፍ ስለመንፈሳዊ ሥጦታዎች ይፈጽሙ የነበሩትን ስሕተቶች ያርምላቸዋል። ይህ የመንፈሳዊ ሥጦታ ጉዳይ በዘመናችንም አከራካሪ ሆና ስለመጣ የሐዋርያውን መምሪያ በጥንቃቄ በመመልከት የእኛንም ስሕተት በቃሉ መሠረት ማረም ይኖርብናል።  ጥያቄ 6. የመንፈሳዊ ሥጦታዎች ዋና ዓላማ ምንድነው?  ጥያቄ 7. ከቁጥር 8-10 ውስጥ ስንት መንፈሳዊ ሥጦታዎች ተዘርዝረዋል?  ጥያቄ 8. እነዚህ ሥጦታዎች ለምን ያህል አማኛች ነው የተሰጡት?  በቁጥር 1 ላይ፡- «ስለመንፈሳዊ ነገርም» ሲል የቆሮንቶስ ሰዎች ከጠየቋቸው ጥያቄዎች አንዱ ይህ አንደነበር ያመላክታል።  ቁጥር 2:- «አህዛብ ሳላችሁ» ከማመናቸው በፊት በተለያዩ የጣዖት አምልኮዎች ያለ አእምሮ ይነዱ ነበር። ጣዖት አእምሮን ያደነዝዛል። አሁን ግን በአእምሮ መጎልመስና በመንፈስ ቅዱስ ብርሃን የሕያው አምላክ ተከታዮች ሆነዋል። በጣዖት ሥር በነበሩ ጊዜ ብዙ ነገሮችን ከቁጥጥራቸው ውጭ በሰይጣን አስገዳጅነት ይፈጽሙ ነበር። አሁን ግን በመንፈስ ቅዱስ ሲመሩ አእምሮአቸውን ሳይለቁ በልባቸው መንፈስ ቅዱስ ያስተማራቸውን ረጋ ባለ መንፈስ ይናገራሉ በፈቃዳቸው ይናገራሉ፡፡  ጥያቄ 9. ከማመንህ በፊትና ካመንህ በኋላ በሕይወትህ ምን ዓይነት ለውጥ ታይቶአል?  ቁጥር 3፡- ይህ እርግማን ወይም እውቀት እንዲሁ በቸልተኝነት የሚሠነዘረውን ሳይሆን ከልብ የመነጨ አጋርን ያመለክታል። ሰው በመንፈስ ቅዱስ ካልተመራ በስተቀር የኢየሱስን ማንነት ማወቅ አይችልም፤ ( 1ኛቆሮ.2፡6-13)። እንዲሁ ሰው በአጋንንት መንፈስ ተወስዶ ኢየሱስን ሊረገም ይችላል።  ስለ ጸጋ ሥጦታዎቶ መወያየት ይጀምራል። ከቁጥር 4 እስከ 7 ድረስ ስለዚህ ነገር ያብራራል። የጸጋ ሥጦታዎች ሥላሴን ያመላክታሉ፡፡ ሥጦታዎችን እንደፈቃዱ ለእያንዳንዱ አማኝ የሚያድል መንፈስ ቅዱስ ነውና ብዙ ሥጦታዎች በአንዱ መንፈስ ይሰጣሉ፡፡ የሥጦታዎችም ዓላማ ጌታ ኢየሱስን ለማክበር ስለሆነ ብዙ ቢሆኑም አንድ ዓላማ አላቸው። የሥጦታዎች አሠራር የተለያየ ቢሆንም በእግዚአብሔር አስተዳዳር ሥር ናቸው። እነዚህ ሥጦታዎች በሙሉ ዓላማቸው ቤተ ክርስቲያንን ለማሳደግና ለማነጽ ነው እንጂ ለግል ጥቅም ወይም ክብር ተብለው የሚሰጡ አይደሉም። ለዚህም ነው አንዳንድ ሥጦታዎች ለጥቂት ሰዎች ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ክርስቲያኖች የሚሰጡት፤ ( 1ኛጴጥ.4:10-11)።  ክቁጥር 8-11 ሥጦታዎችን ይዘረዝራል፡፡  ጥበብ፡- በተፈጥሮ ሊታወቁ የማይቻሉትን ጥልቅና መንፈሳዊ እውቀቶች መንፈስ ቅዱስ ለተለያዩ ሰዎች ይገልጣል፡፡ ሁሉም አማኞች ክርስቶስን የማወቅ ጥበብ ተሰጥቷቸዋል፤ ይህ ጥበብ ግን የተለየ ሥጦታ ሆኖ ለቤተ ክርስቲያን አስተማሪዎች የሚሰጥ ማለት ነው።  እውቀት:- ይህ በመሠረቱ ከጥበብ አይለይም።  እምነት፡- ይህም ለእያንዳንዱ አማኝ የሚሰጠው በኢየሱስ የማመን የደህንነት እምነት ሳይሆን በተለይ በእምነት የመራመድ ሥጦታ የሚታይባቸው አማኞች አሉ ማለት ነው።  የመፈወስ ሥጦታ፡- ይህ ሥጦታ ለምሳሌ ሐዋርያው ጴጥሮስ ነበረው፤ የልብሱን ጫፍ እንኳ የነካ ይፈወስ ነበር።  ተአምራትን ማድረግ፡- ይህ ልዩ ኃይልን የመግለጥ ሥጦታ ነበር። ለምሳሌ፡- ጴጥሮስ በተግሣጽ ሐናንያንና ሰጲራን እንደገደለ፤ ጳውሎስ አስማተኛውን በእውርነት አንደመታው ዓይነት ያለ ኃይል ነው። (የሐዋ.5፡1-11፤ 13:6-12)።  ትንቢት፡- የእግዚአብሔር አንደበት ሆና የእግዚአብሔርን ቃል ማስተላለፍ ማለት ነው። ይህ የወደፊቱን መተንበይ ብቻ ሳይሆን የትምህርት ቃልም መስጠት ትንቢት ይባላል፤ (የሐዋ. 15፡32)። ደግሞም ጌታ ኢየሱስ ነቢይ ነበር፤ ግን ዋና ሥራው ማስተማር ነበር እንጂ የወደፊቱን ነገር መተንበይ ብቻ አልበረም። ነቢያት ሲተነብዩ ከአእምሮአቸው ተለይተው ዛር እንዳለበት በመንቀጥቀጥና በንግግር በመፈንዳት አልነበረም። ነገር ግን ዘና ብለው በጽሞና መንፈስ በማስተማር አቀራረብ ነበር። አንዳንድ ጊዜም በጥያቄና በመልስ በውይይት መልክ ትንቢታቸውን በትምህርት መልክ አቅርበዋል። ይህ አይሆንም ያለ የጌታን ትምህርት አሰጣጥ ከወንጌል አንብቦ ይረዳ!!  መናፍስትን መለየት፡- አማኞች በሙሉ መናፍስትን እንዲመረምሩ ታዘዋል፤ ( 1ኛ ዮሐ.4፡ 1)። ነገር ግን ይህ የተለየ የስሕተትን መንፈስ ቶሎ የመለየትና ቤተ ክርስቲያንን የማስጠንቀቅ ሥጦታ ነው። ያልበሰሉ አማኞች ብዙ ጊዜ «እኔ ለዶክትሪን ገድ የለኝም» እያሉ ሲኩራሩ ይታያሉ። ዶክትሪን በመሠረቱ ትምህርት ማለት ነው። ክርስቲያን ምን ዓይነት ትምህርት መቀበል እንዳለበት መጠንቀቅ አለበት። የቤተ ክርስቲያን አስተማሪዎች ሕዝባቸው ሐሰተኛ ትምህርት እንዳይቀበሉና ከክርስቶስ መንገድ ፈቀቅ እንዳይሉ መንከባከብ አለባቸው። እነዚህ ተንከባካቢዎች እንገዲህ የመለየት ሥጦታ ሊኖራቸው ይገባል ማለት ነው፤ (2ኛቆሮ.11:2-4፤ ገላ.1:6-9፤ 2ኛጴጥ.2:1-3)።  ልሳን፡- ይህ ሥጦታ ለመጀመሪያ ጊዜ በሥራ ላይ የዋለው በሐዋ. ምዕራፍ 2 ላይ መንፈስ ቅዱስ በወረደ እለት ነው። በ1ኛ ቆርንቶስ የተጠቀሰውና በሐዋርያት ሥራ ያለው የተለያየ ነው የሚሉ ማስረጃ የላቸውም። ልዩነት የተባሉትን ስንመረምር ልዩነት እንዳልሆኑ እንገነዘባለን። በመሠረቱ በግሪክ ቋንቋ በሁለቱም ቦታ የተጠቀሰው ያው ልሳን የሚለው ቃል ነው። ስለዚህ ትርጉሙን ሁለት አድርገን ለመስጠት በቂ ምክንያት ሊኖረን ይገባል፤ ምክንያትም የለንም። ስለዚህ ሥጦታ ዝቅ ብለን በተጨማሪ እንወያያለን። (የዚህ ዌብ ሳይት አዘጋጅ ከዚህ የተለየ ሃሳብ አለው) ከዚያ በፊት ግን ጠቅላላ ሥጦታዎቹን በሁለት ወገን እናጠቃልላቸዋለን። ያም የእውቀትና የኃይል ሥጦታዎች በመባል። የእውቀት ሥጦታዎች የተባሉት፡- ጥበብ፥ እውቀት፥ ትንቢት፥ መናፍስትን መለየት፥ ልሳን መተርጉም ሲሆኑ! የኃይል ሥጦታዎች ደግሞ፡- ዕምነት፥ መፈወስ፥ ተአምእራት ማድረግ ናቸው። በሁለቱ መካከል ያለው ዝምድና ይኸ ነው። በቃሉ የተነገረው እውቀት እውነተኛ ለመሆኑ የኃይል ሥጦታዎች ማረጋገጫ ሆነው ቀርበዋል፡፡ ለዚህ ማስረጃ ዕብ.2፡3-4ን ተመልከት። ይህንን ክፍል ከኤፌ.4:11-12፤ ከ1ኛ ጴጥ.4፡10-11፤ ከሮሜ 12፡4-8 እና ከ1ኛ ቆሮ.12:28-30 ጋር ካነፃፀርነው ሌሎች መንፈሳዊ ሥጦታዎች እንዳሉ መገንዘብ እንችላለን።  ጥያቄ 10. 1ኛ ቆሮ.12:8–10፤ 28-30ን ከኤፈ.4፡11-12፤ ከ1ኛ ጴጥ.4:10-11 እና ከሮሜ 12:4-8 ጋር አነፃፅር። በእዚህ ጥቅሶች ውስጥ የተሰጡትን ሥጦታዎች በዝርዝር ጻፍ።  ጥያቄ 11. ሀ/ የትኛው መንፈሳዊ ሥጦታ ይመስልሃል የተሰጠህ? ለ/ ይህንን ሥጦታ ያሰብከው ለምንድነው? ሐ/ አንድ ሰው መንፈሳዊ ሥጦታውን ሊያውቅ የሚችለው እንዴት ነው? መ/ ለቤተ ክርስቲያንህ ዕድገት ይህንን ሥጦታህን በምን ዓይነት መንገድ ነው የምትጠቀምበት?  ጥያቄ 12. ሀ/ አንዳንድ አማኝ ከዚህ የተለየ ሃሳብ አለው። ስለ መንፈስ ቅዱስ ሥጦታዎች ምን ያምናሉ? ለ/ አሁን በተማርከው መሠረት እንዴት ልትመልሳቸው ትችላለህ?

1ኛ ቆር.12:1-11 Read More »

2ኛ ቆሮንቶስ 12፡11-13፡14

ጳውሎስ ደብዳቤውን ለመዝጋት በሚቃረብበት ወቅት፥ ለቆሮንቶስ ሰዎች የነበረው ታላቅ ፍቅር አንድ የመጨረሻ ልመና እንዲያቀርብ ገፋፋው። በቤተ ክርስቲያናቸው የሚያደርገው ሦስተኛው ጉብኝቱ ለእርሱም ሆነ ለእነርሱ የሚያሳዝን ነገር እንዲሆን አልፈለገም ነበር። ለእነርሱ ልቡን ከፍቶላቸዋል፤ ስለ አገልግሉቱ ማብራርያ ሰጥቶአቸዋል፤ ለነቀፋዎቻቸው ምላሽ ሰጥቷል፤ እንዲሁም ለእግዚአብሔር ቃል እንዲገዙና ጌታን እንዲታዘዙም ገፋፍቶአቸዋል። እንግዲህ ከዚህ በላይ ምን ሊያደርግ ወይስ ምን ሊል ይችል ነበር?  በዚህ በደብዳቤው መዝጊያ ክፍል ውስጥ ጳውሎስ የቆሮንቶስ ሰዎችን ወደ መታዘዝና መገዛት ለማምጣት በሚያደርገው ጥረት፥ በሦስት የአቀራረብ ዘዴዎች ተጠቅሟል።  አሳፈራቸው (2ኛ ቆሮ. 12:11-21) ልጆች በነበርን ጊዜ፥ ከወላጅም ይሁን ከጎረቤት«ኀፍረት አይሰማህም!» የሚል ቃል ሲሰነዘርብን፥ ስንት ጊዜ ሰምተን ይሆን? ሰዎች ስለ ክፉ ነገራቸው ወይም አመለካከታቸው ማፈራቸው መልካም ነው። አንድ ጥፋተኛ ሰው የኀፍረት ስሜት የማይሰማው ከሆነ፥ ደንዳና ልብና የደነዘዘ ሕሊና እንዳለው ይታወቃል። «ርኩስን ነገር ስለ ሠሩ አፍረዋልን? ምንም አላፈሩም፤ እፍረትንም አላወቁም» (ኤር. 6፡15)።  በመጀመሪያ፥ ጳውሎስ የቆሮንቶስን ሰዎች ሊያመሰግኑት ባለመፈለጋቸው በመውቀስ ያሳፍራቸዋል (2ኛ ቆሮ. 12፡11-13)። እርሱን ለትምክህት ከመገፋፋት ይልቅ፥ ስለ እርሱ በትምክህት ሊናገሩ ይገባቸው ነበር። ከዚህ ይልቅ ግን፥ የቆሮንቶስ ሰዎች ተወዳጅነትን አትርፈው ቤተ ክርስቲያናቸውን በመቆጣጠር ላይ ስለነበሩት «ምጡቅ-ሐዋርያት»፥ የአይሁድ ሃይማኖት አስፋፊዎች በትምክህት ይናገሩ ነበር።  ጳውሎስ ከእነዚህ ሰዎች ያንስ ነበር? በምንም ዓይነት! የቆሮንቶስ ሰዎች ጳውሎስን በተግባር አይተውታል፤ እንዲያውም፥ ነፍሳቸውን ጭምር ወደ ትክክለኛ አቅጣጫ የመራላቸው ባለውለታቸው ነበር። በመካከላቸውም ሐዋርያነቱን የሚያረጋግጡ ተአምራዊ ነገሮችን አድርጎ ነበር (ዕብ. 2፡1-4)። ውጫዊ ስደትንና ውስጣዊ ችግሮችን ተጋፍጦ፥ በቆሮንቶስ ውስጥ በአገልግሎቱ ጸንቶ ነበር። ከቤተ ክርስቲያኗ ምንም ነገር አልወሰደም ነበር። ጳውሎስ አሁንም «በእናንተ ላይ ሸክም ሳልሆን ከመቅረቴ በቀር፥ ከሌሎች አብያተ-ክርስቲያናት እናንተን ያሳነስሁአችሁ በምንድነው? ይህም ጥፋት ሆኖ ከተቆጠረ ይቅር በሉኝ» (2ኛ ቆሮ. 12፡13 – አዲስ ትርጉም) በማለት በረቀቀ ቅኔአዊ አነጋገር ተጠቅሟል።  ከክርስትና ሕይወት አደጋዎች አንዱ፥ በረከቶቻችንን እንደ ልማዳዊ ነገሮች አድርገን መውሰዳችን ነው። ፈሪሃ-እግዚአብሔር ያደረበት መጋቢ ወይም የሰንበት ትምህርት ቤት አስተማሪ ብዙ ነገር ሊያደርግልን ይችላል፤ እኛ ግን እንደ ተራ ነገር እንቆጥረዋለን። (ላለማዳላት፥ አንዳንድ ጊዜ መጋቢዎች የቤተ ክርስቲያን ምዕመናን በረከቶችን እንደ ተራ ነገር ቆጥረው እንዲቀበሉ በማድረጉ በኩል ጥፋት እንዳለባቸው ለመግለጽ እወዳለሁ።) በዚህ ዝንባሌ በመመራት ካለፃመስገናቸው የተነሣ ጳውሎስ ሲያሳፍራቸው እናያለን (ቁ 14-18)።  ይህን የመሳሰሉ ችግሮች ቢኖሩም ቅሉ፥ ጳውሎስ ግን የቆሮንቶስን ሰዎች በመጎብኘት ታማኝ ነበር፤ እናም አሁን ሦስተኛውን ጉብኝት ሊያደርግ ነበር (13፡1 ተመልከት)። በማመስገን ፈንታ፥ የቆሮንቶስ ሰዎች ጳውሎስስ ዕቅዱን በመቀየሩ ወቀሱት። ጳውሎስ ከቤተ ክርስቲያን ምንም ድጋፍ አላገኘም ነበር፤ ይልቁንም፥ ለቤተ ክርስቲያን በመሥዋዕትነት ሰጥቷል። ይሁን እንጂ እነርሱ ደግሞ ከሌሎች ጋር በመካፈል አመስጋኝነታቸውን ለማሳየት ፈቃደኞች አልነበሩም። ጳውሎስ ይበልጥ ሲወዳቸው፥ እነርሱ ደግሞ ባነሰ ሁኔታ የሚወዱት ይመስል ነበር። ለምን? ምክንያቱም ለክርስቶስ እውነተኛ ፍቅር አልነበራቸውምና ነው (ቁ. 13)። ጳውሎስ ቤተ ክርስቲያንን ለመርዳት ያለውን ነገር ለማካፈል ይፈልግ ነበር።  የአይሁድ ሃይማኖት አስፋፊዎች ቤተ ክርስቲያንን ለመበዝበዝ የማታለያ ዘዴዎችን ይጠቀሙ ነበር (4፡2 ተመልከት)፤ ዳሩ ግን ጳውሎስ ግልጽና ከአታላይነት የራቀ ነበር። ጳውሎስ የፈጸመው ብቸኛው «በደል» ከእነርሱ የገንዘብ ድጋፍ አለመቀበሉ ነበር። በዚህ ትጥቃቸውን ስላስፈታቸው፥ ገንዘብ ብቻ እንደሚፈልግ አድርገው ለሚያቀርቡት ክስ ምንም ምላሽ ሊሰጡ አይችሉም ነበር። ከእርሱ ጋር አብረው ከሚያገለግሉት ጳውሎስ የላካቸው ሰዎችም ቢሆኑ፥ አንዳቸውም በምንም መንገድ አልበዘበዙዋቸውም ወይም መጠቀሚያ አላደረጉዋቸውም ነበር።  ልጆች ወላጆቻቸው ለሚያደርጉላቸው በጎ ነገር ሳያመሰግኑ ሲቀሩ እጅጉን ያሳዝናል። እንዲሁም ደግሞ የእግዚአብሔር ልጆች «መንፈሳዊ ወላጆቻቸው» ለሚያደርጉላቸው ነገሮች ባለውለታነታቸውን ሲዘነጉ አሳዛኝ ይሆናል። ለዚህ ለምስጋና እጦት መነሻው ምንድነው? ጳውሎስ በቀጣዩ አንቀጽ ውስጥ ገልጾታል – የቅድስና መታጣት (ቁ. 19-21)። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የከፉ ኃጢአቶች ነበሩና ጳውሎስ ለጉብኝት ከመምጣቱ በፊት ፍርድ ተሰጥቶባቸው እንዲወገዱ ይፈልጋል። ይህ ካልሆነ ግን የአሁኑም ጉብኝቱ በሌላ አሳዛኝ ልምምድ ይቋጫል።  ምናልባትም አንዳንድ የቤተ ክርስቲያን አባላት፥ «ጳውሎስ ዳግም ሊጎበኘን ከመጣ፥ ተጨማሪ ችግሮችን ይፈጥርብናል» ብለው እየተናገሩ ይሆናል። ጳውሎስ መሻቱ ችግሮችን መቅረፍና አብያተ ክርስቲያናትን ማጠናከር እንደ ሆነ በግልጽ ይናገራል። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚገኙትን ኃጢአቶች ለማስወገድ በታማኝነት መጋፈጥንና ድፍረትን ይሻሉ። «አለባብሶ ማረሱ» ግን፥ የበለጠ ለክፋት ይዳርጋል። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚገኝ ኃጢአት በሰው ሰውነት ውስጥ እንዳለ ካንሰር ነው .ተቆርጦ መውጣት አለበት።  እስኪ ቤተ ክርስቲያኒቱ የወደቀችባቸውን ኃጢአቶች እናስብ – በመናዘዝና ንስሐ በመግባት ሊወገዱ የሚገባቸው ኃጢአቶች። እርስ በርሳቸው ስለሚመቀኛኙ ይጣሉ (ይከራከሩ) ነበር። ገንፍሎ የሚወጣ ቁጣም ነበረባቸው። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሥጋዊ ሤራዎችን፥ አድመኛነትንና ሐሜትን ያስፋፉ ነበር። ይህም ሁሉ ከትዕቢትና የራስን አስፈላጊነት ከፍ አድርጎ ከመመልከት የመነጨ ሲሆን፥ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሁከትን አስከትሏል (2ኛ ቆሮ. 12፡20)። ይህንን የኃጢአቶች ዝርዝር ከ1ኛ ቆሮንቶስ 13 ጋር ብናወዳድር፥ በማኅበረ-ምዕመናኑ መካከል የፍቅር መተሳሰብ እንዳልነበረ እንመለከታለን።  ከእነዚህ «የመንፈስ ኃጢአቶች» ጎን (7፡1)፥ ታላላቅ የሥጋ ኃጢአቶችም ነበሩ- ዝሙትና ፍትወት። ጳውሎስ ስለ እነዚህ ኃጢአቶች በ1ኛ ቆሮንቶስ ምዕራፍ 5-6 ውስጥ ገልጾአል፤ ዳሩ ግን አንዳንድ ጥፋተኞች ባለመታዘዛቸው ጸንተው ነበር። ለአዲሱ ሕይወት ራሳቸውን ከመስጠት ይልቅ፥ አሮጌው ሕይወታቸው ዳግመኛ በላያቸው ላይ ግዛቱን እንዲያስፋፋ ይፈቅዱለት ነበር(1ኛ ቆሮ. 6፡9-10።  ጳውሎስ ለዚህ ለሦስተኛው ጉብኝት ብዙም አልጓጓም ነበር። ቤተ ክርስቲያን እንደሚፈልጋት ሳትሆን ቀርታ ላለማየት ከመሥጋቱም፥ እርሱም እንደሚፈልጉት ሆኖ ሳይገኝ እንዳይቀር ፈርቶ ነበር። ይሁን እንጂ፥ ምንም እንኳ በሁኔታው ማፈሩና ማዘኑ ባይቀርም (የቃሉ ትርጉም «ለሞተ ሰው ዘን»ን ያመለክታል)፥ ዳሩ ግን ነገሮችን የተቃና ለፃድረግ አሁንም በሥልጣኑ እንደሚጠቀም ቃል ይገባላቸዋል። ለእነርሱ የነበረው ፍቅር እጅግ ታላቅ በመሆኑ፥ እነዚህን ችግሮች ችላ በማለት ቤተ ክርስቲያኒቱን ማዳከማቸውን እንዲቀጥሉ ሊፈቅድላቸው አይሻም ነበር።  የቆሮንቶስ ሰዎች ማፈር ሲገባቸው ሳለ፥ እነርሱ ግን አላፈሩም ነበር። ጳውሎስ መልእክቱን በትክክል ማስተላለፉን ለማረጋገጥ ሲል፥ ቀጥሎ በምንመለከተው ሁለተኛው የአቀራረብ ዘዴ ይጠቀማል።  አስጠነቀቃቸው (2ኛ ቆሮ. 13፡1-8)  በዚህ ስፍራ ሁለት ማስጠንቀቂያዎች ቀርበዋል።  «ራሳችሁን አዘጋጁ» (2ኛ ቆሮ. 13፡1-4)። በአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ኃጢአትን ለማስወገድ በምንጣጣርበት ጊዜ፥ የምንመራው በሐሜቶች ሳይሆን በሐቆች መሆን አለበት። ጳውሎስ ዘዳግም 19፡15ን የጠቀሰ ሲሆን፥ ተመሳሳይ አሳብ ያላቸውን ምንባቦች ከዘኁልቁ 35፡30 እና ከማቴዎስ 18፡16፥ እንዲሁም ከ1ኛ ጢሞቴዎስ 5፡19 ላይ እናገኛለን። በተለይ የቤተ ክርስቲያን ምዕመናን እርስ በርሳችው በማይስማሙበት ጊዜ የምስክሮች መኖር የነገሩን እውነትነት ለማረጋገጥ ይረዳል።  የቤተ ክርስቲያን ምዕመናን ኢየሱስ በማቴዎስ 18፡15-20 የሰጣቸውን ትዕዛዛት ቢከተሉ ኖሮ፥ ራሳቸው ብዙዎቹን ችግሮቻቸውን ለመፍታት ይችሉ ነበር። አማኞች የጌታችንን ትዕዛዛት ባለማክበራቸው ምክንያት ብቻ፥ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አናሳ አለመግባባቶች ወደገዘፉና የተወሳሰቡ ችግሮች ሲሸጋገሩ ተመልክቻለሁ። ጉዳዩ የሚመለከታቸው ግለሰቦች በእውነተኛነት መፍትሔ እስካልፈለጉ ድረስ፥ መጋቢውና ማህበረ-ምዕመናኑ ጣልቃ መግባት የለባቸውም።  የአይሁድ መምሕራን ጳውሎስን ደካማ ነው በማለት ከሰውታል (2ኛ ቆሮ. 10፡7-11 ተመልከት)። የጳውሎስ አገልግሉት የውሃትና ገርነት የሚታይበት ሲሆን (1፡24 ተመልከት)፥ የእነርሱ ግን ጠንካራና አምባገነናዊ ነበር። አሁን ግን ጳውሎስ እንዴት ጠንካራ ሊሆን እንደሚችል እንደሚያሳያቸው ያረጋግጥላቸዋል – ችግሮቹን ለመቅረፍ የሚያስፈልገው ይኸው ከሆነ። ማስጠንቀቂያውም፥ «አልራራላችሁም!» የሚል ነበር። የተጠቀመውም «በጦርነት ውስጥ መራራት» ን የሚያመለክት ቃል ነው። ባጭሩ፥ ጳውሎስ የእግዚአብሔርን ቃል ሥልጣን በሚቃወም በማንኛውም ሰው ላይ ጦርነት እያወጀ ነበር።  ባላንጣዎቹ፥ «እስኪ ጳውሎስ እውነተኛ ሐዋርያ መሆኑን ያረጋግጥ» ብለው ነበር። የጳውሎስም ምላሽ፥ «የደከምሁ በምመስልበት ወቅት፥ እኔም እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ ብርቱ ነኝ» የሚል ነበር። በመስቀል ላይ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ደካማነትን አሳይቷል፤ ይሁንና መስቀሉ አሁንም «የእግዚአብሔር ኃይል» ነው (1ኛ ቆሮ. 1፡18)። ጳውሎስ ቀደም ብሎ የመንፈሳዊ ውጊያውን ዘዴ የገለጸ ሲሆን (2ኛ ቆሮ. 10፡1-6)፥ አንባቢዎቹም ነገሮችን ላይ ላዩን በመመልከት ምትክ በጥልቀት እንዲያጤኑ አስጠንቅቋቸዋል።  በዓለም መመዘኛ መሠረት፥ ጳውሎስና ኢየሱስ ሁለቱም ደካሞች ነበሩ፤ ዳሩ ግን በጌታ መመዘኛ መሠረት፥ ሁለቱም ብርቱዎች ነበሩ። ለምሳሌ በአንድ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሥነ-ሥርዓት ጉዳዮችን ፈር በሚያስይዝበት ጊዜ፥ መቼ «መድከም» እና መቼ «መበርታት»

2ኛ ቆሮንቶስ 12፡11-13፡14 Read More »

በአገልግሎት ውስጥ የሚከሰቱ የአሳብ አለመግባባቶች (2ኛ ቆሮንቶስ 10:1-18)

ከአንባብያን ወይም ከሬድዮ አድማጮች ጠጠር ያለ ደብዳቤ ሲደርሰኝ፥ ብዙውን ጊዜ ለመልሱ በብቃት እንደ ተዘጋጀሁበት እስከሚሰማኝ ድረስ በተለየ ፋይል ውስጥ አስቀምጠዋለሁ። በጥቂት አጋጣሚዎች፥ ለደብዳቤዎች እጅግ ፈጣን መልሶችን ሰጥቻለሁ፤ በኋላ ግን ተጸጽቼአለሁ። ቆይታ በማድረግ፥ ለማሰብና ለመጸለይ፥ ብሉም የደብዳቤውን አሳብ በትክክል ለመረዳት ለራሴ በቂ ጊዜ እሰጣለሁ። ይህም ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው ምላሽ ለመስጠት ስለሚያስችለኝ ነው።  ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች በሚጽፍበት ጊዜ፥ ጥበብ ያለበትን እርምጃ እንዲከተል የእግዚአብሔር መንፈስ መርቶታል። የሚጽፈው ለተከፋፈለች (1ኛ ቆሮ. 1 ከቁ 11 ጀምሮ)፥ ሐዋርያዊ ሥልጣኑን እየተገፋች ለነበረችና በሐሰተኛ መምህራን በማመረክ ላይ ለነበረች ቤተ ክርስቲያን ነበር። በመሆኑም፥ እውነተኛነቱን እንዳይጠራጠሩ በመጀመሪያ አገልግሎቱን ይገልጽላቸዋል። ከዚያም፥ የሚያቀርብላቸው የእርዳታ ጥያቄ ለመንፈሳዊ ሕይወታቸው ዕድገት እንደሚረዳቸው ስለሚያውቅ፥ በመዋጮው ውስጥ እንዲካፈሉ ያበረታታቸዋል። በጸጋ መስጠትና በጸጋ መኖር ጎን ለጎን ይሄዳሉ።  አሁን በመጨረሻው የደብዳቤው ክፍል፥ ሐሰተኛ አስተማሪዎችን ጨምሮ፥ ጳውሎስ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሁከት የሚፈጥሩትን ሰዎች ይሞግታል – ሐዋርያዊ አገልግሎቱንም ያጠናክረዋል። ከምዕራፍ 10-13 ያለውን በምታነብበት ጊዜ፥ ጳውሎስ በቀጥታ ከሳሾቹን ሲጠቅስ (ለምሳሌ፥ 10፡7፥ 10-12፤ 11፡4፥ 20-23) እና ለሐሰት ክሶቻቸውም ምላሽ ሲሰጥ ትመለከታለህ። እንደዚሁም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የነበሩ የአይሁድ ሃይማኖት አስፋፊዎች የእግዚአብሔርን ሥራ ለማፍረስ የሚሠሩ የሰይጣን አገልጋዮች መሆናቸውን አልሸሸገም (11፡12-15)።  ጳውሎስ ከምዕራፍ 10-13 ውስጥ አንድን ቃል ሃያ ጊዜ ያህል ጠቅሶአል – መመካት ተብሎ የተተረጎመውን ቃል። እነዚህን ምዕራፎች በመጀመሪያ ስታነብ፥ ጳውሎስ ስለ ራሱ እንደሚመካ አድርገህ ታስብ ይሆናል፤ ዳሩ ግን አይደለም። ጳውሎስ «የተመካው በኢየሱስ ክርስቶስ» ነው እንጂ፥ በራሱ ወይም ባደረጋቸው ነገሮች አልነበረም (ሮሜ 5፡11፤ ገላ. 6:14፤ ፊልጵ. 3፡ 3)። እንዲሁም ስለ ቆሮንቶሶች ያለውን ትምክህት ለሌሎች ተናግሯል፤ ዳሩ ግን ትምክህቱ ከንቱ የሚቀር ይመስል ነበር (2ኛ ቆሮ. 7፡4፥ 14፤ 8፡24)።  ጳውሎስ ለአገልግሎቱና ለሐዋርያዊ ሥልጣኑ እንጂ፥ ለራሱ ሲል በግል እየተከላከለ እንዳልነበረ፥ ልብ በል። ከሌሎች አገልጋዮች ጋር «የዝና ውድድር» እያደረገ አልነበረም። ጠላቶቹ እርሱን በውሸት ለመክሰስ አልቦዘኑም ነበር፤ ራሳቸውንም ከፍ ከፍ ከማድረግ አልተመለሱም ነበር (11፡12)። ጳውሎስ ስለ ራሱና ስለ አገልግሎቱ በመግለጽ በግሉ እንዲከላከል ያስገደደው፥ የቆሮንቶስ ሰዎች ዓለማዊ አመለካከት ነበር። ጳውሎስ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ለመናገር አያቅማማም፤ ዳሩ ግን በቂ ምክንያት እስከሌለው ድረስ፥ ስለ ራሱ አይናገርም ነበር፡፡  በመጨረሻም፥ ጳውሎስ በተመካበት ወቅት፥ እግዚአብሔር በሰጠው አገልግሎት ላይ ተወስኖ ነበር (10፡13)፤ ከዚያም አጽንኦቱን ያደረገው በመከራዎቹ ላይ እንጂ፥ በስኬቶቹ ላይ አልነበረም። ይህ ደብዳቤ በቆሮንቶስ ማህበረ-ምዕመናን ዘንድ በሚነበብበት ወቅት፥ ጳውሎስን በከሰሱት ሰዎች ልብ ውስጥ የኀፍረት ስሜት መጫሩ የማይቀር ነበር – የአይሁድ ሃይማኖት አስፋፊዎችንም ሞኝነት ይፋ ማድረጉ የማይጠረጠር ነበር።  ጳውሎስ አገልግሎቱን የገለጸበት የመጀመሪያው ዓላማ፥ ከሥራው ጋር በተያያዘ መንገድ በሰዎች አእምሮ ውስጥ የሰረፀውን ውዥንብር (አለመግባባቶች) ማስወገድ ነበር። እነርሱም አስፈላጊ የሆኑትን ሦስት የአገልግሎት ክፍሉች አልተረዱም ነበር።  መንፈሳዊ ውጊያን ስለ ማካሄድ (2ኛ ቆሮ. 10፡1-6)  1. የቀረበበትን ክስ (2ኛ ቆሮ. 10፡1-2) ለማግኘት የሚያዳግት አይደለም። (በአይሁድ ሃይማኖት አስፋፊዎች የሚመሩ) የቤተ ክርስቲያን ውስጥ ዓመፀኞች፥ ጳውሎስ ከርቀት ሆኖ ደብዳቤ ሲጽፍ እንደሚደፍርና ዳሩ ግን ከቆሮንቶስ ሰዎች ጋር ፊት ለፊት በሚጋፈጥበት ጊዜ አልፈራም እንዲያውም በጣም ደካማ እንደ ሆነ አድርገው ያስወሩ ነበር (በተጨማሪም ቁ9-11 ተመልከት)። ከበስተጀርባ ሆነው የሚገፋፏቸው የአይሁድ ሃይማኖት አስፋፊዎች በአመለካከታቸው ላይ ያላቋረጠ ተፅዕኖ ቢያሳድሩባቸውም፥ ሕዝቦቹ ግን ወደዋቸው ነበር (11፡20)። «አንድን መሥመር ያልተከተለው» የጳውሎስ የሕይወት ዘይቤ «አዎን እና አይደለም። ከሚለው የተስፋ ቃሉ ጋር ተጓዳኝ ነበር (1፡15-20)።  ጳውሎስ በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ሲመሠርት፥ ዓላማው ክርስቶስን እንጂ ራሱን ማስከበር አልነበረም (1ኛ ቆሮ. 2፡1-5)። ብዙውን ጊዜ ክርስቲያኖች የሚያድጉት በተወለዱበት መንገድ ነው። አምባገነናዊ አገዛዝ በበዛበት ክልል ከተወለዱ፥ በሰው ጥበብና ብርታት ላይ ተደግፈው ያድጋሉ። ትህትናና ፍቅር በሰፈነበት አካባቢ ካደጉ፥ በጌታ ላይ መደገፍን ይማራሉ። ጳውሎስ አዲስ አማኞቹ በጌታ እንጂ በአገልጋዩ ላይ እንዳይተማመኑ ስለሚፈልግ፥ ሆን ብሉ ሥልጣኑንና ችሎታውን ዝቅ ያደርገዋል።  ጳውሎስ ያንን ሁሉ ካስተማራቸው በኋላ እንኳ፥ ክርስቲያኖቹ ግን አሁንም አላዋቂዎች ነበሩ። እውነተኛ መንፈሳዊ ኃይል የሚገኘው፥ በ«የዋህነትና ገርነት» እንጂ (2ኛ ቆሮ. 10፡1)፡ «ሥልጣንን አላግባብ በመጠቀም» እንዳልሆነ ለመረዳት አልቻሉም ነበር። በእነዚህ የመግቢያ ቁጥሮች ላይ የተጠቀሰው የጳውሎስ አመለካከት ባላንጣዎቹን ትጥቅ ያስፈታቸዋል። (እንዲያውም ጳውሎስ ማለት «ትንሽ» ማለት ስለ ሆነ፥ በዚህ ስፍራ ስሙን መጥቀሱም አስፈላጊ ነበር።) ጳውሎስ ደካማ ከነበር፥ ኢየሱስ ክርስቶስም እንዲሁ ነበር፤ ኢየሱስ ትሁትና ገር ነበርና (ማቴ. 11፡29)። ይሁንና አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ፥ ጌታችንም ብርቱና ብሎም ተቆጪ ነበር (ማቴ. 15፡1-2፤ 23፡13-33፤ ማር. 11፡15-17፤ ዮሐ 2፡13-16 ተመልከት።) ጳውሎስ ፍቅር በተመላው መንገድ፥ «እባካችሁ መጥቼ እንዴት ደፋር ልሆን እንደምችል እንዳሳያችሁ አታስገድዱኝ!» በማለት እያስጠነቀቃቸው ነበር።  2. የሰጠው መልስ ደግሞ (2ኛ ቆሮ. 10፡3-6) መንፈሳዊ ውጊያ ምን እንደ ሆነ ይገልጻል። የቆሮንቶስ ሰዎች (በሐሰት መምህራን ተመርተው) በጳውሎስ አገልግሎት ላይ በውዊው ሁኔታው ስለ ፈረዱበት፥ ከውስጡ የነበረውን ኃይል አጥተው ነበር። ነገሮችን «ከሥጋ» አንጻር (ቁ2) እንጂ፥ ከመንፈስ አንጻር አልገመገሙም ነበር። የአይሁድ ሃይማኖት አስፋፊዎች፥ ዛሬ እንደምናያቸው «አንዳንድ ታላላቅ የሃይማኖት ሰዎች»፥ በመግዛት ብቃታቸው፥ በርቱዕ አንደበታቸውና ከቤተ ክርስቲያን መሪዎች በሚያገኛቸው «ሙገሳዎች» ያስደንቁዋቸው ነበር።  ጳውሎስ ምንም እንኳ እንደ ማንኛውም ሰው ሰብዓዊ ፍጡር ቢሆንም የተደገፈው በመለኮታዊና ከጌታ ዘንድ በሚመጡ መንፈሳዊ የጦር ዕቃዎች እንጂ በሰብዓዊ ነገሮች ላይ ባለመሆኑየተለየ ፈለግ ተከትሏል። ከሥጋና ከደም ጋር ስለማይዋጋ፥ ውጊያው እንደ ሥጋ ፈቃድ አልነበረም (ኤፌ. 6 ከቁጥር 10 ጀምሮ ተመልከት)። ማንም ቢሆን መንፈሳዊ ውጊያዎችን በሥጋዊ የጦር ዕቃዎች ሊዋጋ አይችልም።  በቁጥር 4 ላይ የተጠቀሰው ጦር «ጦርነት» ወይም «ዘመቻ» ማለት ነው። ጳውሎስ በቆሮንቶስ አነስተኛ ጦርነት እየተጋፈጠ አልነበረም፤ በዚያ የነበረው የጠላት ጥቃት ከፍተኛ የሆነ ሰይጣናዊ ዘመቻ አካል ነበር። አሁንም ቢሆን የገሃነም ኃይላት የእግዚአብሔርን ሥራ ለማኮላሸት እየተጣጣሩ ስለ ሆነ (ማቴ. 16፡ 18)፥ ለጠላት ምንም ዓይነት ስፍራ አለመስጠታችን አስፈላጊው ነገር ነው፤ አንዲት ቤተ ክርስቲያን እንኳ መልቀቅ የለብንም!  በሰዎች አእምሮ የተቃወሞ ግድግዳዎች የሚገኙ በመሆኑ፥ (እንደ ኢያሪኮ ግንብ) እነዚህ ግድግዳዎች መናድ አለባቸው። ለመሆኑ «የአእምሮ ግድግዳዎች» የተባሉት ምንድን ናቸው? ግድግዳዎቹ፥ ከእግዚአብሔር ቃል እውነት ጋር የሚቃረኑ ፍልስፋናዎችና ራሱን ከፍ ከፍ የሚያደርገው በእውቀት መታበይ ናቸው። ጳውሎስ የሚቃወመው እውቀትን ሳይሆን፥ ዳሩ ግን ሰዎችን ከሚያውቁት በላይ እንደሚያውቁ አድርገው እንዲያስቡ የሚገፋፋቸውን የምሁርነት ወይም የሊቅነት አመለካከት ነው (ሮሜ 12፡16)። ጳውሎስ ቤተ ክርስቲያኒቱን በሚመሠርትበት ጊዜ ይህንን «የሰዎች ጥበብ» የተጋፈጠ ሲሆን (1ኛ ቆሮ. 1፡ ከቁ. 18 ጀምሮ)፥ አሁን ደግሞ በአይሁድ ሃይማኖት አስፋፊዎች መምጣት የተነሣ ትግሉ እንደ ገና ሲጧጧፍ እናያለን።  ትዕቢት በሰይጣን እጅ እንደሚጥል ለተረዳው ጳውሎስ ከከፍተኛ የውጊያ መሣሪያዎቹ ውስጥ አንዱ ትህትና ነበር። ትሁቱ የእግዚአብሔር ልጅ ከጲላጦስ እጅግ የበለጠ ኃይል ነበረው (ዮሐ 19፡11 ተመልከት)፤ ይህንኑም ደግሞ አረጋግጧል። ጳውሎስ ተቃውሞውን ለመጣል መንፈሳዊ የጦር ዕቃዎችን ተጠቅሞአል፡- ጸሎት፥ የእግዚአብሔር ቃል፥ ፍቅርና በሕይወቱ ውስጥ የሚሠራ የመንፈስ ቅዱስ ኃይል ናቸው። ጳውሎስ በራሱ ስብዕና፥ ወይም በችሎታዎቹ፥ ወይም በሐዋርያነቱ ሥልጣን ላይ አልተደገፈም ነበር። ይሁንና ማኅበረ-ምዕመናኑ አንድ ጊዜ ራሱን ለጌታ አስከ ሰጠ፥ ጳውሎስ አስፈላጊ ሆኖ ባገኘው ጊዜ አጥፊዎቹን ለመቅጣ ተዘጋጅቶ ነበር።  ዛሬ በርካታ አማኞች ቤተ ክርስቲያን በጦርነት ፍልሚያ ላይ እንዳለች አይገነዘቡም፤ የክርስትናን ጦርነት አደገኛነት የሚረዱትም ቢሆኑ፥ ብዙውን ጊዜ እንዴት መዋጋት እንዳለባቸው አያውቁም። አጋንንታዊ ኃይላትን ለመርታት ሰብዓዊ ዘዴዎችን ይጠቀማሉ፤ እነዚህም ዘዴዎች ለውድቀት ይዳርጉዋቸዋል። ኢያሱና ሠራዊቱ የኢያሪኮን ግንብ ለሰባት ቀናት በዞሩበት ጊዜ፥ የኢያሪኮ ከተማ ታዛቢዎች አብደዋል የሚል አሳብ ነበራቸው። ይሁንና አይሁዶች በእግዚአብሔር ተማምነው ትዕዛዛቱን በመፈጸማቸው፥ ከፍ ያሉትን ቅጥሮች አፍርሰው፥ ጠላትን ድል ነሥተዋል (ኢያሱ 6፡1-20)።  በሺካጎ ከተማ በመጋቢነት ሳገለግል ሳለሁ፥ በየሳምንቱ ከሦስት መጋቢ ወዳጆቼ ጋር እየተገናኘን «በጸሎት ጦርነት» እንተባበር ነበር። ሰዎችን ለእግዚአብሔር ከመሰጠት የሚከላከላቸውን የተሳሳተ አሳብ ለማስወገድ የሚያስችለውን የተስፋ ቃል

በአገልግሎት ውስጥ የሚከሰቱ የአሳብ አለመግባባቶች (2ኛ ቆሮንቶስ 10:1-18) Read More »

የመስጠት ጸጋ – ክፍል 2፣ (2ኛ ቆሮንቶስ 9፡1-15)

እኛ ክርስቲያኖች እግዚአብሔር አብዝቶ ከሰጠን በኋላ፥ ለሌሎች ለመስጠት የሚገፋፋን ሌላ ሰው መፈለጋችን ግራ የሚያጋባ ነገር ነው። እግዚአብሔር የቆሮንቶስን ሰዎች በድንቅ ሁኔታ ቢያበለጽጋቸውም፥ ዳሩ ግን ያላቸውን ነገር ለሌሎች ለማካፈል ያመነቱ ነበር። በጸጋ መስጠትን አልተለማመዱም ነበርና ጳውሎስ ይህንኑ አሳብ ለእነርሱ ማብራራት ነበረበት። ጳውሎስ በጸጋ መስጠትን ከገለጸላቸው በኋላ፥ በልዩ መዋጮው ውስጥ አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ሊያነሣሣቸው ይሞክራል። ይህንንም ያደረገው በጸጋ ከመስጠት ጋር የተያያዙትን አምስት ማበረታቻዎች (መጽናኛዎች) በማቅረብ ነው።  ያንተ መስጠት ሌሎችንም ያነሣሣቸዋል (2ኛ ቆሮ. 9፡1-5)  ክርስቲያኖች ለክርስቶስ በምናቀርበው አገልግሎት እርስ በርስ መወዳደር ባይኖርብንም፥ ጳውሎስ «ለፍቅርና ለመልካም ሥራ እንድንነቃቃ እርስ በርሳችን እንተያይ» (ዕብ 10፡24) እንዳለው ልንፈጽም ይገባል። እግዚአብሔር በሌሉች አማኞች ውስጥና በእነርሱም በኩል የሚሠራውን ነገር ስንመለከት፥ እኛም በበለጠ ለማገልገል መጣጣር አለብን። በሥጋዊ አድራጎት ኩረጃና በመንፈሳዊ ሕይወት ቅጂ መካከል እስከዚያ ልዩነት እንደሌለ ልንገነዘብና በዚህም በኩል ጥንቃቄ ልናደርግ ይገባል። በመሆኑም ቀናተኛ ክርሲትያን ቤተ ክርስቲያንን ለማነቃቃትና ምዕመኑንም ለጸሉት፥ ለሥራ፥ ለምስክርነትና ለስጦታ ለማነሣሣት መሣሪያ ሆኖ ሊያገለግል ይችላል።  የሚያስገርመው ነገር ግን የሚከተለው ነው፡- ጳውሎስ የመቄዶንያን አብያተ ክርስቲያናት ለማበረታታት በቆሮንቶስ ሰዎች ቅንዓት ተጠቅሞ ነበር፤ ግን አሁን ደግሞ የቆሮንቶስን ሰዎች ለማበ ረታታት በመቄዶንያ ሰዎች ይጠቀማል። ከአንድ ዓመት በፊት፥ የቆሮንቶስ ሰዎች በመዋጮው ውስጥ ተካፋይ እንደሚሆኑ በከፍተኛ ፍላጎት ገልጠውለት ነበር፤ ከዚያ በኋላ ግን ምንም አላደረጉም ነበር። የመቄዶንያ ሰዎች ደግሞ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ አበርክተው ነበርና ጳውሎስ ስለ ቆሮንቶስ ሰዎች የተናገረው ትምክህት ከንቱ እንዳይሆንበት ሠጋ።  ስለ ሆነም የቆሮንቶስ ሰዎች በመዋጮው አሰባሰብ ውስጥ የድርሻቸውን እንዲወጡ ያነቃቋቸው ዘንድ፥ ጳውሎስ ቲቶንና ሌሎች ወንድሞችን ወደ ቆሮንቶስ ላከ። ከገንዘቡ ይልቅ እጅግ የሚልቀው፥ በሕይወታቸው ውስጥ ላለው የእግዚአብሔር ጸጋ ምላሽ በመስጠት ያላቸውን በሚያካፍሉበት ጊዜ ቤተ ክርስቲያኗ የምታገኘው መንፈሳዊ በረከት ነበር። ጳውሎስ አስተዋጽኦውን ስለሚያሰባስቡበት ሁኔታ ለቤተ ክርስቲያኒቱ አስቀድሞ ስለ ጻፈ (1ኛ ቆሮ. 16፡1-4)። ለመዘግየታቸው የሚያመካኙበት ነገር አልነበራቸውም። ጳውሎስ ባለቀ ሰዓት ላይ ተሰብስበው ችግር የሚፈጥሩ መዋጮዎች እንዳይኖሩ ሲል፥ እርሱና «የመዋዕለ-ንዋይ ኮሚቴው» በሚደርሱበት ጊዜ ሁሉም ነገር ተሰናድቶ እንዲጠብቀው ይፈልግ ነበር።  ጳውሎስ ለማስወገድ የፈለገው ነገር ምን ነበር? የፈለገው መዋጮው ካልተሰናዳ በራሱና በቤተ ክርስቲያን ላይ የሚደርሰውን ኀፍረት ለማስወገድ ነበር። በይበልጥም ኀፍረቱ ያሳሰበው ከመቄዶንያ አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ ተውክለው ከልዩ ኮሚቴው ጋር የሚሄዱ በርካታ ሰዎች በመኖራቸውም ጭምር ነበር (የሐዋ.20፡4 ተመልከት)። ጳውሎስ ስለ ቆሮንቶስ ሰዎች ለመቄዶናውያን ተናግሮ ስለ ነበር የነገራቸው ነገር ከንቱ ሆኖ እንዳይቀር በእርግጥም ፍርሐት ገብቶት ነበር።  ጳውሎስ ሰዎች ለመስጠት ቃል እንዲገቡ መጠየቅን፥ ስህተት ወይም መንፈሳዊነት የጎደለው ተግባር አድርጎ ያልተመለከተ ይመስላል። እያንዳንዳቸው ምን ያህል መስጠት እንደሚገባቸው አልተናገራቸውም፤ ዳሩ ግን የተስፋ ቃላቸውን መፈጸማቸውን ይጠብቅ ነበር። አንድ ሰው ለቤቱ ስልክ ሲያስገባ፥ በየወሩ የተወሰነ ገንዘብ ለመክፈል ቃል ይገባል። እንደ ስልክ፥ መኪናና የዱቤ መውሰጃ መዝገብ ለመሳሰሉ ነገሮች ገንዘብ ለመስጠት ቃል መግባቱ ተቀባይነት ካለው፥ ለጌታም ሥራ ቃል የምንገባው ቅሬታ የሚያሳድርበት ምክንያት አይኖርም።  ጳውሎስ ስለ መዋጮው ሲጽፍ ምን እንዳለ ተመልከት። ይህ «ለቅዱሳን የሚሆን አገልግሎት» ነበር፡፡ እንዲሁም ደግሞ ስጦታው «በረከት» (2ኛ ቆሮ. 9፡5) ማለትም «የልግስና ስጦታ» ነበር። ምናልባት ጳውሎስ የቆሮንቶስ ሰዎች ካቀዱት በላይ እንዲሰጡ እየገፋፋቸው ይሆን?  ጳውሎስ ምንም ዓይነት ጫና ላለማሳደር ይጠነቀቅ ነበር። ጳውሎስ ስጦታቸው «እንደ በረከት (ልግስና) ሆኖ ከስስት (ከውጥረት) ነጻ» እንዲሆን ይፈልግ ነበር። ከፍተኛ ጫና የታከለባቸው የስጦታ ልመናዎች በጸጋ ከመስጠት ጎን ሊሰለፉ አይችሉም።  ለመስጠት ከሁሉም በላይ የሚያበረታታን ነገር ስጦታችን ጌታን የሚያስደስት መሆኑ ነው፤ ይሁንና ሌሎችን ለመስጠት የሚያነሣሣ ዓይነት የስጦታ ልምምድ ማድረጉም ስህተት አይደለም። እንዲህም ስለ ተባለ በግል የምንሰጠውን ነገር እንደማስታወቂያ ለሁሉም ማወጅ አለብን ማለት አይደለም . ይኸውም የዚህ ዓይነቱ መስጠት ከመስጠት መሠረታዊ መመሪያዎች አንደኛውን ስለሚያፋልስ ነው (ማቴ. 6፡1-4)። ይሁንና ጳውሎስ የሚጽፈው ለአብያተ ክርስቲያናት ስለ ሆነ፥ ማኅበረ – ምዕመናን የሰጡትን ነገር ቢያሳውቁ ስህተት አይሆንም። ዓላማችን ያደረግነውን ለሌሎች በመግለጽ ለመመካት ከሆነ፥ በጸጋ የመስጠትን ልምምድ እያደረግን አይደለም። ዳሩ ግን መሻታችን ሌሎችም ያላቸውን እንዲያካፍሉ ለማነሣሣት ከሆን፥ የእግዚአብሔር ጸጋ ሌሎችን ለመርዳት በእኛ በኩል ሊሠራ ይችላል።  ያንተ መስጠት ለራስህ በረከት ይሆናል (2ኛ ቆሮ. 9፡6-11)  የጌታችን የተስፋ ቃል «ስጡ፤ ይሰጣችሁማል» የሚል ነበርና ይህ ቃል አሁንም በእውነትነቱ ጸንቶ ያለ ነው (ሉቃ. 6፡38)። መልሶ የሚሰጥበትም «መልካም መስፈሪያ» ሁልጊዜም ገንዘብ ወይም ቁሳዊ ነገር የተመለከተ ባይሆንም፥ ዳሩ ግን ሁልጊዜም እኛ ከሰጠነው አብልጦ የሚልቅ ነው። መስጠት የእኛነታችን ማረጋገጥ እንጂ፥ እኛ የምናደርገው ነገር አይደለም። የእግዚአብሔርን ጸጋ ለሚገነዘብ ክርስቲያን፥ መስጠት የሕይወት ዘይቤ ነው። ዓለም እንደ ምሳሌ 11፡24 የመሳሰለውን አሳብ አትረዳም፡- «ያለውን የሚበትን ሰው አለ፤ ይጨመርለታልም፤ ያለ ቅጥ የሚነፍግ ሰውም አለ፤ ይደኸያልም።» በጸጋ በምንሰጥበት ጊዜ ዓላማችን «አንድን ነገር ማግኘት» አይደለም፤ ዳሩ ግን የእግዚአብሔርን በረከት ማግኘት «እናገኛለን» ብለን የማናስበው ምርቃት ነው።  መስጠታችን እንዲባርከንና እንዲያንጸን ከተፈለገ፥ ጳውሎስ በዚህ ክፍል ውስጥ የገለጻቸውን መመሪያዎች ለመከተል ልንጠነቀቅ ይገባል። 1. የዕድገት መመሪያ – የምንዘራውን ያህል እናጭዳለን (2ኛ ቆሮ. 9፡6)። ይህ መመሪያ በዕለታዊ ሕይወታችን ውስጥ የሚንጸባረቅ ስለ ሆነ፥ በመጠኑ ማብራራት አስፈላጊ ነው። ብዙ ዘር የሚዘራ ገበሬ ብዙምርት ለመሰብሰብ የሰፋ ዕድል ይኖረዋል። በባንክ ውስጥ ከፍተኛ ገንዘብ ያስቀመጠ ባለ ሀብት፥ ብዙ ወለድ ያገኛል። በጌታ ሥራ ውስጥም ብዙ ትርፋማ ተግባር ባከናወንን መጠን፥ በመዝገባችን ውስጥ የበለጠ «ፍሬ» ይገኛል (ፊል. 4፡10-20)  ይህን መመሪያ ለመዘንጋት በምንፈተንበት ጊዜ ሁሉ፥ እግዚአብሔር በስጦታው ቁጥብ እንዳለሆነ ልናስታውስ ይገባል። «ለገዛ ልጁ ያልራራለት፥ ነገር ግን ስለ ሁላችን አሳልፎ የሰጠው፥ ያው ከእርሱ ጋር ደግሞ ሁሉን ነገር እንዲያው እንዴት አይሰጠንም? » (ሮሜ 8፡32)። በተፈጥሮም ይሁን በጸጋ፥ እግዚአብሔር ለጋስ ሰጪ ነው፤ እንዲሁም ፈሪሃ-እግዚአብሔር የነገሠበትን ሕይወት ለመምራት የሚፈልግ ሰው መለኮታዊውን ምሳሌ መከተል አለበት።  2. የመሻት መመሪያ – በትክክለኛ ልብ እንደ ዘራን እንዲሁ እናጭዳለን (2ኛ ቆሮ. 9፡7)። ለአንድ ገበሬ ግብርናውን ለማካሄያድ ልዩ የሆኑ አነሣሽ ምክንያቶች እምብዛም ፋይዳ አይኖራቸውም። ጥሩ የዘር እህል ካለውና በጥሩ ወቅት ላይ ከዘራ፥ ለትርፍም ይሁን ለብልጽግና፥ ወይም ለኩራት ቢሠራ፥ ዞሮ ዞሮ ፍሬ ማግኘቱ አይቀርም። ከምርቱ የሚያገኘውን ገንዘብ ለመጠቀም የሚያቅድበትም ሁኔታ በምርቱ ላይ ልዩነት አይፈጥርም። እንደ ዘመኑ ሁኔታ ምድሪቱ ያፈራችለትን ሰብል ይሰበስባል።  ዳሩ ግን ለክርስቲያን ነገሩ እንዲህ አይደለም – በመስጠት (ወይም በሌላ በማንኛውም እንቅስቃሴ) ውስጥ፥ አነግሱ ምክንያት «ዓላማው፥ መንስኤው) ወሳኝ ነው። የምንሰጠው ከልባችን መሆን አለበት፤ ከልባችን ውስጥ ያለው አነሣሽ ምክንያት ደግሞ እግዚአብሔርን ሊያስደስተው ይገባል። የልብ ፈቃደኛነት ሳይታከል «በኃዘኔታ እንደሚሰጡ» ወይም «በእብደት ያላቸውን እንደሚበትኑ» ሰዎች መሆን የለብንም፤ ዳሩ ግን የእግዚአብሔርን ጸጋ ስለ ተለማመድን፥ ያለንን በደስታ የምናካፍል «ደስተኛ ሰጪዎች» መሆን አለብን። እንዲህ ያለው «ርኅሩኅ የተባረከ ይሆናል» (ምሳ 22፡9)።  በደስታ መስጠት አቀበት ከሆነብን፥ ልባችንን ወደ አምላካችን አንሥተን፥ ጸጋውን እንዲሰጠን መጠየቅ አለብን። በርግጥ እግዚአብሔር በኃላፊነት ስሜት የተሰጠውን ስጦታ ሊባርክ ይችላል፤ ዳሩ ግን ልቡ እስካልተስተካከለ ድረስ፥ ሰጪውን ሊባርክ አይችልም። በጸጋ መስጠት ማለት እግዚአብሔር ስጦታውንም ሰጪውንም ይባርከዋል ማለት ነው – ሰጪውም ለሌሎች በረከት ይሆናል።  3. የፈጣን ውጤታማነት መመሪያ – እየዘራን ሳለ እንኳ ልናጭድ እንችላለን (2ኛ ቆሮ. 9፡8-11)። ገበሬ የመከሩን ጊዜ መጠባበቅ አለበት፤ ዳሩ ግን በጸጋ መስጠትን የሚለማመድ አማኝ ወዲያውኑ መከሩን መሰብሰብ ይጀምራል። ከስጦታችን የሚገኙ የረዥም ጊዜ ጥቅሞች ቢኖሩም፥ ዳሩ ግን ወዲያውኑ የሚከሰቱ በረከቶችም አሉ።  አስቀድሞ እግዚአብሔር ከሚያበዛልን ጸጋው መካፈልን እንጀምራለን (ቁ 8-9)። በዚህ ጥቅስ መሠረቱ «ሁሉም» የቃሉ አጠቃቀም ሁላችንም ከምናስተውለው በላይ ነው፤ በጸጋ ሁሉ፥ ሁልጊዜ፥ ብቃትን ሁሉ፥ ለበጎ ሥራ ሁሉ ይላል። ይህም ማለት እግዚአብሔር ሁሉንም ክርስቲያን በቁሳዊ ነገሮች ያበለጽገዋል ማለት ሳይሆን፥ ዳሩ ግን በጸጋ መስጠትን የሚለማመድ ክርስቲያን ሁልጊዜም በሚያስፈልገው

የመስጠት ጸጋ – ክፍል 2፣ (2ኛ ቆሮንቶስ 9፡1-15) Read More »