የአዲስ ኪዳን መጽሐፍ ቅዱስ ጥናት

2ኛ ቆሮ. 5፡11-15

ጥያቄ 1. በቁጥር 11 «የጌታን ፍርሃት» ሲል ምን ዓይነት ፍርሃት ማለቱ ነው?  ጥያቀ 2. በቁጥር 12 ላይ «በመልክ እንጂ በልብ ለማይመኩ» ሲል ስለነማን ነው የሚናገረው?  በቁጥር 11 ላይ «የጌታ ፍርሃት» ማለት የማያምኑ የኩነኔ ፍርሃት ሳይሆን የእግዚአብሔር ልጆች ለእግዚአብሔር ያላቸው የአክብርት ፍርሃት ነው። «ሰዎችን ሁሉ እናስረዳለን» ማለትም ሕይወታችን በእውነት ለእግዚአብሔር አገልግሎት እንጂ ለግል ጥቅም የዋለ አለመሆኑን ለሰዎች ግልጽ አድርገን ሕይወታችንን እናሳያለን አንደብቅም ማለቱ ነው። ይህ የቅንነት ኑር ለእግዚአብሔር ብቻ ሳይሆን ለቆርንቶስም ቤተ ክርስቲያን የተሰወረ አለምሆኑን “ለእግዚአብሔር ግን የተገለጥን ነን፤ በሕሊናችሁም ደግሞ የተገለጥን እንደሆንን ተስፋ አደርጋለሁ” ማለት ይገልጻል።  ጥያቄ 3. በሕይወታችን ዘመን በሙሉ በእግዚአብሔር ፍርሃት መኖሩ አስፈላጊ የሆነበት ምክንያት ምንድነው?  ጥያቄ 4. መሪዎች ሕይወታቸውን በግልጽ እያሳዩ መምራት የሚገባቸው ለምንድነው?  ቁጥር 12:- «በመልክ እንጂ በልብ ለማይመኩ» የሚላቸው በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ሾልከው የገቡትን ሐሰተኛ አስተማሪዎች ነው፤ (2ኛ ቆሮ.11:13)። ለሰው ለመታየት ብቻ በውጭ አምረው ይታያሉ እንጂ በልባቸው የረከሱ ናቸው። ሐዋርያው ስለራሱ የሕሊና ንጽሕና የተናገረው የቆርንቶስ ክርስቲያኖች በእነዚህ ሐሰተኛች አስተማሪዎች በሐዋርያው ላይ የቀረበውን ክስ መመለስ እንዲችሉ ነው። ለዚህ እንደሆነም «በእኛ ልትመኩ ምክንያት እንሰጣችኋለን» በሚለው ዐረፍተ ነገር እንገነዘባለን፡፡  ቁጥር 13፡- «እብዶች ብንሆን ለእግዚአብሔር ነው» ሲል ይህ ዓይነት ክስ ወይም ሐሜት በጠላቶቹ የተሰነዘረበት መሆኑን ያመለክታል። እብድ የሚለው ከማር. 3፡21-31 ካለው በጌታ ላይ ከተሰነዘረው ክስ ጋር ይመሳሰላል፤ እርሱንም አበደ ብለው ነበርና! እንዲሁም በሐዋ.26፡24 ሐዋርያው ለወንጌል ካለው ፍቅር የተነሳ ዕብድ ተባለ፡፡ ስለ ክርስቶስ መሰደዱ በማያምኑ ዘንድ እውነትም እንደ እብደት ሊታይ ይችል ነበር፤ (2ኛ ቆሮ 11:23)።  ጥያቄ 5. በኢትዮጵያ ውስጥ ክርስቲያኖች እንደ እብድ ሊታዩ የሚችሉት እንዴት እንደሆነ ምሳሌዎች በመስጠት አስረዳ፡  ቁጥር 14 እና 15፡- ይህ ለክርስቶስ በአንድ ልብ መኖሩ የክርስቶስ ፍቅር ግድ ስላለው እንጂ ስላበደ አልነበረም። ይህ ፍቅር ለእርሱ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም አማኞች ስለተሰጠ ሁሉ ለክርስቶስ በአንድ ልብ ራሳቸውን ሊሰጡ ይገባል፡፡ “አንዱ ስለ ሁሉ ሞተ፤ እንገዲያስ ሁሉ ሞቱ”። በአዳም ሁሉም በኃጢአት አንደወደቁ በክርስቶስ ደግሞ ሁሉም አማኞች በሕይወት ይኖራሉ። የክርስቶስ ሞት ለእነርሱ ስለተቆጠረላቸው የክርስቶስ ሞት የእነርሱ ሞት ነው።  እግዚአብሔርን በምናገለግልበት ጊዜ እነዚህን እውነታዎች ማስተዋልና መገንዘቡ አስፈላጊ ነው። አንደኛ፡- ለማገልገል የሚያነሣሣን ነገር ፍቅር መሆን አለበት። ይህም ለክርሰቶስ ያለን ፍቅር ነው። ሌሎችን እንድንወድ በልባችን ውስጥ ኢየሱስ ያስቀመጠውንም ፍቅር ያጠቃልላል።  ክርስቲያኖችንና ያልዳኑትን በፍቅር ዓይን በመመልከት እነርሱን ለማገልገል መነሣሣት ይኖርብናል። ሁለተኛ፡- ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ስለሞትን (ሮሜ 6 ተመልከት )። ከአሁን ወዲያ ራሳችንን ለማስደሰት ሳይሆን ከሙታን በተነሣው በክርስቶስ ኃይል ተደግፈን ያዳነንን እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ሕይወት ለመኖር መጣር ይገባናል።  ጥያቄ 6. ሀ/ እነዚህ ሁለት እውነታዎች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ስላለው መሪነት ያለንን አመለካከት የሚቀይሩት እንዴት ነው? ለ/ ብዙ መሪዎች እነዚህን ሁለት እውነታዎች በአእምሮአቸው ይዘው ይምራሉን? 

2ኛ ቆሮ. 5፡11-15 Read More »

2ኛ ቆሮ. 5፡1-10

ጥያቄ 15. በቁጥር 1 ላይ «ድንኳን» የሚለውን በአንድ ወገን፥ «ሕንጻ» የሚለውን በሌላ ወገን አድርጉ ሁለቱን ያነጻጽራል፤ ድንኳንና ሕንጻ ምንና ምንን ያመለክታሉ?  ጥያቄ 16. ከቁጥር 2-4 ባለው ክፍል ውስጥ የሚከተሉትን ቃላት አብራራ። መልበስ፣ ራቁት መገኘት፣ መገፈፍ፣ መቃተት፡፡  ጥያቄ 17. በስደት መኖርና ማደር እያንዳንዱ ምን ማለት እንደሆን አስረዳ፡፡  ጥያቄ 18. በሥጋ የተሠራውን በብድራት ለመቀበል በክርስቶስ ወንበር ፊት መገለጥ ማለት ምን ማለት ነው?  በቁጥር 1 ላይ ድንኳን የሆነው ምድራዊ መኖሪያችን የሚለው ይህንን በሥጋ በዚህ ዓለም ያለንን ኑሮ ነው። ጠቅላላ የሃሳቡም ትርጉም ከዚህ ዓለም በሞት ብንለይ እግዚአብሔር የዘላለም የትንሣኤ አካል አዘጋጅቶልናል ማለት ነው። ይህ ሥጋችን ፈራሽ ስለሆነ ድንኳን ተብሏል፤ ነገር ግን የትንሣኤ አካላችን ሕንጻ ተብሏል፤ የማይፈርስ ስለሆነ።  በዚህ ውስጥ እንቃትታለን ማለት የዚህ ዓለም ኑሮ ከባድ ነው ማለት ነው። በዚህ ዓለም በሽታ፥ ስደት፥ ሥቃይ፥ ድካም ስላለ የዚህ ዓለም ኑሮ የመቃተት ኑሮ ነው። ይህም መቃተት የመናፈቅ ወይም ለውጥን የመፈለግ መቃተት ነው። “እስከ መቼ ነው?” እንደ ማለት ነው። ይህን ሃሳብ ከሮሜ 8፡22 ጋር አስተያይ።  የምንናፍቀው ወይም በምጥ የምንጠብቀው የትንሣኤን ጊዜ ነው። “በዚህ ውስጥ በእውነት እንቃትታለን።” በዚህ የሚለው ይህንን ሥጋችንን ነው። የምንቃትተውም «ከሰማይ የሚሆነውን መኖሪያችንን እንድንለብስ» በመናፈቅ ነው።  የትንሣኤን አካል ከአጎናጸፈን በኋላ ራቁታችንን አንገኝም። ይህም ማለት አንሞትም ማለት ነው። ነፍስ ከተሰጣት ሥጋ በሞት ስትለይ ሥጋን ወይም ልብሷን ተገፈፈች ይባላል። አሁን የለበስነው አካል ሟች ስለሆነ በሞት ልንገፈፍ እንችላለን። የትንሣኤን ልብስ ከለበስን በኋላ ግን ከምት ባሻገር ስለምንሆን ዳግመኛ አንገፈፍም።  «የሚሞተው በሕይወት ይዋጥ ዘንድ» ይህ አነጋገር የትንሣኤ አነጋገር ነው። 1ኛ ቆሮ.15:51-57ን ተመልከት። በዚህ መሠረት የክርስቲያን ተስፋ ሞት ሳይሆን የክርስቶስ መምጣት ነው። ምክንያቱም በሕይወት እያለን ጌታ ከተመለሰ ሞትን ሳናይ የትንሣኤን አካል በመለወጥ እንለብሰዋለን፡፡ ስለዚህ ሐዋርያው “ልንለብስ እንጂ ልንገፈፍ የማንወድ” በማለት ይናገራል። አሁን ሞትን ቀምሰን ሥጋችን ከበሰበሰ በኋላ በጌታ ዳግም ምጽአት ጊዜ ትንሣኤን ከመጕናጸፍ፥ አሁን በሕይወት እያልን ጌታ መጥቶ የትንሣኤን አካል ብንለብስ እንመርጣላን። «ልንለብስ እንጂ ልንገፈፍ የማንወድ» ማለቱ የትንሣኤን አካል ልንቀበል እንጂ ልንሞት አንወድም ማለቱ ነው። ለዚህ ለትንሣኤ ተስፋ የመንፈስ ቅዱስን መያዣ ሰጠን፤ (ቁጥር 5 )። ከሞት እስከምንነሣ ድረስ የሚጠብቀን መንፈስ ቅዱስ ነው፤ ከሞት ከተነሣን በኋላ የተለየ አካል መልበሱ ደግሞ በእግዚአብሔር በኩል የተሰጠ የተስፋ ቃል ነው።  ከቁጥር 6-8 ባለው ክፍል ውስጥ የሚናገረው በሥጋችን በዚህ ዓለም ከጌታ ተለይተን ከመኖር ይልቅ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቶ ከጌታ ዘንድ ያለሥጋ ትንሣኤን መጠበቅ የተሻለ መሆኑን ነው። የትንሣኤን አካል የምንለብሰው በዳግም ምጽአት ጊዜ ከሆነ ከዳግም ምድጽአት ወዲህ የሚዋቱ ክርስቲያኖች በጌታ ዘንድ ናቸው። ግን ከሥጋቸው ተለይተው ስለሆነ ከሁሉም የሚመርጡት የትንሣኤን አካል በመጕናጸፍ ከጌታ ጋር መሆንን ነው። «ከሥጋ ተለይተን በስደት መኖር» ማለት ከዚህ ከሥጋችን ተለይተን ያለትንሣኤ አካል መኖር ማለት ነው። ሆናም በሥጋ ከማደር በስደት መኖር ይመረጣል፤ ምክንያቱም አሁን ከሥጋ መለየት ከጌታ ዘንድ ማደር ስለሆነ ነው።  የጅሆቫ ምስክሮች ሰው ሲሞት ከትንሣኤ በፊት በሕይወት የለም የሚሉት ትምህርት ይህንን የሐዋርያውን ቃል ይጻረራል። ምክንያቱም ከዚህ ዓለም በሞት ከሥጋችን መለየት ማለት በገነት ከጌታ ጋር ማደር እንደሆነ ሐዋርያው ስለሚናገር ነው! (5:8)።  ጥያቄ 19. ሞትን እንዳይፈሩ ይህ ለክርስቲያኖች ማበረታቻ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው?  ቁጥር 9 «ብናድር ወይም ተለይተን ብንሆን» ሲል በሕይወት ብንኖርም ወይም በሞት ከዚህ ዓለም ተለይተን ብንሆን ማለቱ ነው። የእያንዳንዱ ክርስቲያን ግብ እግዚአብሔርን ሁሌ ማስደሰት መሆን ይገባዋል። በዚህች ምድር ሳለን ነው እግዚአብሔርን ማስደሰት የሚኖርብን፡፡ ይህም ማልት አካላችን፥ መንፈሳችን፥ አእምሮአችንና ፈቃዳችን በሙሉ ለእግዚአብሔር ክብርና ደስታ መስጠት አለባቸው። ይህ በዓለም የምንኖረው ሕይወት ጊዜያዊ በመሆኑ ለዘላለም አብረነው የምንኖረውን እግዚአብሔርን የማስደሰቱን ነገር በቂ ግንዛቤ ልንሰጠው ይገባናል።  ጥያቄ 20. ይህ አመለካከት ለእግዚአብሔር ያለንን አገልግሉትና አኗኗሪችንን በእንዴት ዓይነት ሁኔታ ነው ሊቀይር የሚችለው? ቁጥር 10፡- ክርስቲያን በዳግም ምድዓት ጊዜ በሕይወቱ ስላደረገው አገልግሎት ሊጠየቅ በጌታ የፍርድ ወንበር ፊት ይቀርባል፡፡ ይህ የጥያቄ ጊዜ የፍርድ ወይም የኩነኔ ጥያቄ ሳይሆን የሽልማት ጉዳይ ነው። «መልካም ቢሆን ክፉ» ማለት መልካም የሚለው ወርቅ ብር የከበረ ድንጋይ እንዳለው ዓይነት ነው፤ (1ኛ ቆሮ.3፡13-15)። ክፉ የሚለውም እንደዝሙት፥ እንደመስረቅ፥ እንደመዋሸት የመሳሰሉ ለሰው ዓይን የተገለጡ የኃጢአት ሥራዎች ሳይሆኑ አሁን ሰው ከጌታ ምጽአት በፊት ሊመዝናቸው የማይችል ናቸው። ግን ጌታ በመምጣቱ የሚገልጣቸው እስከዚያ ቀን ግን ለእኛ ጥሩ መስለው የሚታዩ ናቸው። ለእኛ አሁን መጥፎ መሆናቸው ከታየ ቤተ ክርስቲያን በቅጣት ልታስወግዳቸው ይገባል፤ (1ኛ ቆሮ. 5:12 እና 13)። በዚህ ፍርድ ድርጊታችን፥ ሥራችንና ምኞታችን በሙሉ ይገለጻል። ለእግዚአብሔር ክብር የሚያስገኘውና በንጹሕ ሕሊና የተሠራው ነገር ነው የሚቆጠርልንና የሚያሸልመን፡፡ እግዚአብሔርን የማናገልገል ከሆነ አስተሳሰባችንም ጥሩ ካልሆነ እግዚአብሔር ሊሰጠን ያቀደውን ሽልማት አናገኝም።  ብድራት ማለቱ ጽድቅን ወይም ኩነኔን ሳይሆን ሸልማትን ማለቱ ነው። ይህ የጥያቄ ጊዜ ስላለ ሕይወታችንን ለጌታ አገልግሎት በመስጠት ወደኋላ አንበል፡፡ ብድራትን የሚሰጠን ራሱ ጌታ ስለሆነና ደግምም ሳናገለግለው ኖረን በእርሱ ፊት ማፈርን አንፈልግምና። ከሞት በኋላ አንደገና ተመልሰን እግዚአብሔርን የማገልገሉን ዕድል አናገኘውም።  ጥያቄ 21. ይህ እውነት ሕይወታችንን እንዴት አድርገን ለእግዚአብሔር አገልገሎት መጠቀም እንዳለብን የሚያሳስበን በእንዴት ዓይነት መልኩ ነው?

2ኛ ቆሮ. 5፡1-10 Read More »

2ኛ ቆሮ.4:13-18

ጥያቄ 10. ቁጥር 13ን ሐዋርያው የጠቀሰው ከየት ነው?  ጥያቄ 11. በቁጥር 13 ላይ የተነገረው የእምነት መንፈስ ምንድነው?  ጥያቄ 12. በቁጥር 16 ላይ የውጭና የውስጥ ሰውነት ሲል ምንና ምንን ይጠቅሳል?  ጥያቄ 13. ቁጥር 17ንና 18 በራስህ አማርኛ አብራራ።  በቁጥር 13 ላይ «አመንሁ ስለዚህም ተናገርሁ» የሚለውን ቃል ሐዋርያው ከመዝሙረ ዳዊት 118(116):1 ላይ ይጠቅሳል። ይህ መዝሙር የተጻፈው እግዚአብሔር ከመከራ ባዳነው ሰው ነው፡፡ የሀሳቡን ዝርዝር ለማየት መዘሙር 115(16)ን በሙሉ አንብብ። የሐዋርያው እምነትና የመዝሙረኛው እምነት አንድ ነበር፤ «ያው አንዱ የእምነት መንፈስ ስላለን»። መዝሙረኛውም ሐዋርያውም ሙታንን በትንሣኤ በሚያነሣ አምላክ እምነታቸውን ጥለው በር።  ይህ እምነት በትንሣኤ የማመን እምነት መሆኑን ሐዋርያው በቁጥር 14 ላይ ገልጿል። «ጌታን ኢየሱስን ያስነሣው እኛንም እንዲያነሣን» ሲል የእርሱም የመዝሙረኛውም እምነት እግዚአብሔር የሙታንን ትንሣኤ የሚሰጥ መሆኑን ማምን እንደሆነ ያረጋግጣል፡፡ ይህ የሐዋርያው በትንሣኤ ማመን የቆሮንቶስም ምእመናን እንደሚካፈሉ ይመሰክርላቸዋል። ስነዚህ ይህ የትንሣኤ እምነት ከአማኝ ወደ አማኝ በምስክርነት ይተላለፋል ማለት ነው። “አመንሁ ስለዚህም ተናገርሁ” ማለቱ መሰከርሁ ማለቱ ነው። የቆሮንቶስም ሰዎች ምስክርነቱን ሰምተው ሙታንን በሚያነሣው አመኑ፡፡ ስለዚህ እነርሱም የትንሣኤ ተስፋ ተካፋዮች ሆኑ።  ይህ በትንሣኤ ማመን አለመታከትን ወይም ተስፋ አለመቁረጥን ይሰጣል። ቁጥር 16 «ስለዚህም አንታክትም» ይላል። የውጭ ሰውነት ማለቱ በገላ.5፡11-19 እንደተጻፈው «ሥጋ» ማለቱ አይደለም። ሰውነት ሲል ይህን የለበስነውን አካል ማለቱ ነው። እንግዲህ በዚህ ዓለም ስንኖር ሰውነታችን እያረጀና እየወደቀ ይሄዳል። ግን በትንሣኤ ስለምናምን የውስጥ ሰውነታችን እየታደሰ ይሄዳል። የውስጥ ሰውነት ማለትም በመንፈስ ቅዱስ የታደሰችው ነፍሳችን ማለት ነው። በክርስቶስ የሚያምን ሰው የዚህ ዓለም ኑሮው ወደ ማለቁ ባዘነበለ ቁጥር በመንፈሱ እየታደሰ መሄድ አለበት እንጂ በመንፈሱ እየተሸበረ መሄድ የለበትም። ክርስቲያን እውነተኛ ኑሮውን የሚጀምረው ከዚህ ዓለም በኋላ ነው። እንዲያውም ክርስቲያን በዚህ ዓለም መከራ በተቀበለ ቁጥር የሚመጣውን ክብር ማሰብና ይህን የዚህን ዓለም መከራ መናቅ አለበት። ይህን ሃሳብ በቁጥር 17 እና 18 ላይ ዘርዝሮአል።  ጥያቄ 14. ሀ/ አንድ ክርስቲያን ዓይኑን በማይታየው ነገር ላይ ማቅናት ያለበት ለምንድነው? ለ/ እዚህ የማይታዩት ነገሮች ምንድናቸው? ሐ/ ለጊዜው ብቻ የሚቆዩት ነገሮች የትኞቹ ናቸው?

2ኛ ቆሮ.4:13-18 Read More »

2ኛ ቆሮ. 4፡7-12

ጥያቄ 6. «ይህ መዝገብ በሸክላ ዕቃ ውስጥ አለን» ሲል ምን ማለቱ ነው?  ጥያቄ 7. በቁጥር 12 ላይ «ሞቱ በእኛ ሕይወቱም በእናንተ ይሠራል» ሲል ምን ማለቱ ነው?  ቁጥር 7:- «ይህ መዝገብ በሸክላ ዕቃ ውስጥ አለን»። መዝገብ ያለው ክቡር ዕቃ ወይም እንደ ወርቅና እንደ አልማዝ የሆነ የከበረ እንቁ እንደ ማለት ነው። መዝገብ ያለው ሕይወት ሰጭውን ወንጌል ሲሆን ሸክላ ያለው ደግሞ የራሱንና የወንጌላውያንን ሕይወት ነው። የወንጌል ክብር ከተሸካሚዎቹ አለመሆኑን ይገልጻል። ወንጌሉን የሚያስተላልፈውን ሰው እግዚአብሔር ደካማ ያደርገዋል። ይህንንም የሚያደርገው፥ የወንጌል ሕይወትን የመቀየር ኃይል ምንጭ የተገኘው ከእግዚአብሔር እንደሆነና ከወንጌላዊው ችሎታ እንዳልሆነ ለማሳየት ነው። በዚህም እግዚአብሔር ክብር ለእርሱ እንደሚሆንና ለወንጌላዊው እንደማይሆን ያረጋግጣል።  ከቁጥር 8-10፡- ሸክላ ክብር የሌላው ከመሆኑም በላይ ተሰባሪ ነገር ነው። ወንጌላውያንም እንዲሁ ተሰባሪ ናቸው። እንዲያውም በታላቅ አደጋ ተጋልጠው ይገኛሉ። ለአደጋ ይጋለጡ እንጂ እንደሸክላ አይንኮታኮቱም። አንዲያውም ለስብራት አልፈው በተሰጡ ቁጥር የእግዚአብሔር ኃይል በሕይወታቸው ይገለጣል። እርግጥ ቀናቸው ሲደርስ ሩጫቸውን ሲፈድሙ በሞት መወሰደቸው አይቀርም። ሆኖም ወንጌል ከእነርሱ ጋር አይጠፋም እግዚአብሔር ሌሎችን በምትካቸው ያስነሣል።  የወንጌል ጎዳና ቀላል አይደለም። ጠላትና መከራ ተባብረው እግዚአብሔርን ለመከተል የወሰኑትን ሰዎች ለማጥፋት ይጥራሉ። ደካሞች በመሆናችን በችግር፥ በንዴት፥ በስደትና በሞትም ጭምር ተወጥረን እንጨነቃለን። ነገር ግን የሕይወታችን ኃይል በእግዚአብሔር ቁጥጥር ውስጥ ስለሆነ መቼም ቢሆን ክርስቲያኖች አንሸነፉም። መከራን ስንቀበል የኢየሱስ መከራ ተካፋዮች ነው የምንሆነው። ያውም አንደ እግዚአብሔር ፈቃድ መከራን በምንቀበልበት ወቅት የረሳችን ሕይወት ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር እንደ ሞተ ሆኖ የኢየሱስ ክርስቶስን ሕይወት በሙላት አንደምንኖር ዓይነት ነው የሚሆነው።  ጥያቄ 8፣ ይህ ጥቅስ በአንተም ሆነ በቤተ ክርስቲያንህ መሪዎች ሕይወት ውስጥ ተግባራዊ የሚሆነው እንዴት ነው?  ቁጥር 11 እና 12:- ይህ ለሞት መሰጠት፥ ሁልጊዜም ተሰባሪ ሆኖ መገኘት የክርስቶስን መሞት መካፈል ነው። ግን ተሰባብሮ ወድቆ ዓላማ ሳይበላሽ ሁልጊዜ የዓላማ መሳካት ማግኘት የክርስቶስን የትንሣኤ ኃይል መካፈል ነው። ስለዚህ ምንም እንኳን ወንጌላውያን ለስብራት አልፈው ቢሰጡም በተጎሰሙ መጠን ሕይወት ከእነርሱ የመፍለቅና ሰሚዎችን የማደስ የእግዚአብሔርን መንግሥት የማስፋፋት እድል ይኖረዋል።  ጥያቄ 9፤ እግዚአብሔር መከራንና ስደትን በመጠቀም ቤተ ክርስቲያንህ እንድታድግ ያደረገው እንዴት ነው?

2ኛ ቆሮ. 4፡7-12 Read More »

2ኛ ቆሮ.4፡1-6

ምዕራፍ 4 ክርስቲያን በአገልግሎቱ መታከትና ተስፋ መቁረጥ እንደሌለበት የሚያሳይ ነው። የክርስቲያን አገልግሎት ከባድ ቢሆንም ተስፋ የሚያስቆርጥ አይደለም። ተስፋ ባለመቁረጥም አገልግሎታችንን በንድሕና እንፈድማለን። አገልጋይ በአገልግሎቱ ተስፋ በሚቆርጥበት ጊዜ በሕይወቱም እየደከመ ጌታን ማሳዘን ይጀምሪል። ስለዚህ በአገልግሎታችን አንታክትም ሲል ሐዋርያው ይመሰክራል።  5፡1-20 ደግሞ ስለ ክርስቲያን ከሞት በኋላ ስላለው ተስፋው የሚያበስር የተስፋ ቃል ነው። የትንሣኤው ተስፋ የመንፈስ ቅዱስ መያዣ እንደተሰጠን ይናገራል። ስለዚህ ክርስቲያን ፍጻሜውን ስለሚያውቅ በጊዜያዊ ፈተናና ችግር አይፈታም ማለት ነው።  ጥያቄ 1. የእግዚአብሔርን ቃል ስለ አለመቀላቀል ከዚህ በፊት በየትኛው ክፍል ተወያይተን ነበር?  ጥያቄ 2. «ለሰው ሕሊና ሁሉ ራሳችንን እናመሰግናለን» ሲል ምን ማለቱ ነው?  ቁጥር 1 እና 2፡- ሐዋርያው ምንም ፈተናና ትግል ቢገጥመው የአገልግሎቱ ክብር ሁልጊዜ የልብ ጥንካሬ ይሰጠዋል። ግን ሰው በአገልግሎቱ ተስፋ ሊቆርጥና ሊታክት የሚችለው በሕይወቱ ድካምን ሲያጠራቅም ብቻ ነው። ሐዋርያው በአገልግሎቱ ያልታከተው 1ኛ/ የአገልግሎቱ ታላቅነት ሁልጊዜ ልቦናውን ስለሚደግፍ። 2ኛ / አገልግሎቱን በንጹህ ሕሊና ይመራ ስለበር።  ይህም ንጹሕ ሕሊና በሁለት ደረጃ ይከፋፈላል። 1ኛ/ በግል ሕይወቱ «የሚያሳፍረውን ስውር ነገር ጥሏል» ። ይህም ማለት ሐዋርያው በጨለማ ሥራ ሕይወቱን አያጠላልፍም ነበር። ሕይወቱን ለምእመናን አርአያ አድርጎ «እኔ ጌታን እንደምመስል እኔን ምሰሉ” ይል ነበር። በ2ኛ ደረጃ አገልግሎቱን በንጹሕ ሕሊና ይመራ የነበረው የእግዚአብሔርን ቃል በጥቅምና በስሕተት አለመበረዙ ነበር፡፡ «የእግዚአብሔርንም ቃል በውሸት አንቀላቅልም»። (ይህን ሃሳብ በ2፡17 ላይ በሰፊው ስለተወያየንበት ለዚያ ጥቅስ የተሰጠውን ማብራሪያ ተመልክት)፡፡ ስለዚህ ለአገልጋይ ጥንካሪ የሚሰጠውና ታክቶ ተስፋ ከመቁረጥ የሚጠብቀው በቀጥተኛነት የእግዚአብሔርን ቃል ማስተላለፉ ነው።  ጥያቄ 3. ሀ/ መሪዎች አገልግሎታቸውን ሊያጠፋና ሊያበላሸባቸው የሚችል ምስጢር የሆነ ምን አሳፋሪ ነገር ሊያደርጉ ይችላሉ? ለ/ ክርስቲያኖች እንዴት አድርገው የእግዚአብሔርን እውነት ሊያጣምሙ እንደሚችሉ ወይም ደግሞ የሚሰብኩበት ጊዜ እንዴት አድርገው የተሳሳቱ መንገዶችን ሊጠቀሙ እንደሚችሉ አንዳንድ ሁኔታዎችን በመጥቀስ ዘርዝረህ ጻፍ።  «በእግዚአብሔር ፊት ለሰው ሁሉ ሕሊና ራሳችንን እናመሰግናለን» የሚለውን ዐረፍተ ነገር ለመረዳት ከዚህ በፊት በ3፡1 ላይ «የማመስገኛ ደብደቤ» ለሚለው የተሰጠውን ማብራሪያ ተመልከት። በዚህ ክፍል የዐረፍተ ነገሩ ትርጉም «ይህ ሰው ጥሩ አገልጋይ ነውና ተቀበሉት» ብሎ ለአንድ ታማኝ ወንጌላዊ የማስተዋወቂያ ደብደቤ እንደሚልክ፥ እንዲሁም ሐዋርያው ሕይወቱን ንጹሕ ነው ብሎ ለሌሎች ሕሊና ይናገራል። ይህም ንጹሕ ሕሊና እውነትን በግልጽ የሚናገር ለመሆኑ ምስክር ነው። ይህ ግልጥ የሚለው መጋረጃ የሌለበት ማለቱ ነው። የአለማመንና የተንኮል መጋረጃን ቀዶ የጣለ ሰው ነበር። ስውር ነገር የሚለው በማያምኑት ልብ ውስጥ ያለውን መጋረጃ ያመለክታል፤ እውነትን በግልጥ መናገር ማለትም ያለ መጋረጃ የሆነ የአዲስ ኪዳን አገልግሎት መሆኑን ያመለክታል።  ቁጥር 3 እና 4:- ሐዋርያው ይህን ሲል አንዱ «ታዲያ ለምን ሁሉም ሰዎች ስብከትህን አይቀበሉም?» ብሎ ሊጠይቅ አንደሚችል ተገንዝቦ አስቀድዋ መልስ ይሰጣል። ምንም እንኳ ወንጌልን በግልጥነት ቢሰብክም አእምሮአቸው ወንጌልን የማይቀበል አሉ። እነርሱም የዚህ ዓለም አምላክ የሆነው ሰይጣን አእምሮአቸውን ስላጨለመባቸው ነው። ሰይጣንን የዚህ ዓለም አምላክ ያለው ሰዎች አምላካቸው አድርገው በሰይጣን ሀሳብ እየተመሩ እግዚአብሔርን ስለሚክዱ ነው እንጂ እውነትስ ሰይጣን አምላክነት ኖሮት አይደለም።  ቁጥር 5፡- ከላይ ራሳችንን ለሰው ሕሊና እናመሰግናለን ሲል ራሱን የሚሰብክ አድርገው እንዳይነቅፋት አስቀድሞ መልስ ይሰጣል። የሚሰብከው ክርስቶስን እንጂ ራሱን አልነበረም። ይህም ለቤተ ክርስቲያን ራስን ባሪያ አድርጎ በታማኝነት መገኘት ማለት ነው።  ጥያቀ 4. ይህ ጥቅስ ምን መስበክ እንደሚገባንና የቤተ ክርስቲያንን ምሪት በተመለከተ የሚሰጠን ግንዛቤ ወይም ትምህርት ምንድነው?  ቁጥር 6:- የወንጌል አገልጋዮች በብርሃንና በግልጥነት እንዲያገለግሉ ሕይወታቸውን ብርሃን ያደረገ የብርሃን አምላክ ራሱ እግዚአብሔር ነው። ይህም ብርሃን በክርስቶስ ፊት ላይ አንጸባርቋል። በሙሴ ፊት ላይ ያንጸባረቀው ብርሃን ወደ እስራኤላውያን አልተላለፈም። እንዲያውም ከሙሴ ፊት ላይ ጠፋ። በክርስቶስ ፊት ላይ የነበረው ብርሃን ግን ለምእምናን ሁሉ ይተላለፋል። ግን በውጭ ለጊዜው የሚያበራ ሳይሆን ለዘለዓለም በልባቸው ውስጥ ይበራል። ይህም ማለት በክርስቶስ አማላጅነት መንፈስ ቅዱስ በምእመናን ልብ ውስጥ ብርሃንን ይፈጥራል። ይህም ብርሃን ንጹህና ግልጽ የሆነ ሕይወትንና አገልግሎትን ለምእመናን ይሰጣል።  ጥያቄ 6. በእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ፥ መሪነትን በተመለከተ የተሰጡትን ዋና ዋና መመሪያዎች በዝርዝር ደፍ። 

2ኛ ቆሮ.4፡1-6 Read More »

2ኛ ቆሮ.3:12-18

ጥያቄ 14. በቁጥር 12 ላይ ገልጠን እንናገራለን ሲል ምን ማለቱ ነው? መልስህን ካለፈው ጥናት ጋር አገናኝ።  ጥያቄ 15. በቁጥር 14 ላይ “በክርስቶስ ብቻ የተሻረ ነውና” ያለው ምኑን ነው?  በቁጥር 12 ላይ ተስፋ የሚለው ከላይ የተዘረዘረውን የአዲስ ኪዳንን ተስፋ ነው። የአዲስ ኪዳን ተስፋ ሕይወትን መስጠት ነው።  እስራኤላውያን የሙሴን ፊት እስከመጨረሻ ትኩር ብለው እንዳይመለክቱ ሕጉን አንብቦ ከጨረሰ በኋላ መጋረጃ በፊቱ ላይ አደረገ፤ (ዘፀ.34:33-35)። ይህም መጋረጃ የልቦናቸው አለማመንና ድንደኔ ምልክት ሆነ። «ነገር ግን ሃሳባቸው ደነዘዘ»። ይህም ማለት አእምሮአቸው የእግዚአብሔርን ክብር በእምነት ከማየት ደነዘዘ ማለት ነው። ይህ የአለማመን ወይም የመደንዘዝ ምልክት የሆነው መጋረጃ የተሻረው ወይም የተገለጠው በክርስቶስ ብቻ ነው። ሰው በክርስቶስ ሲያምን የእግዚአብሔርን ክብር ያለመጋረጃ ያያል። በማቴ.27:51 ላይ ጌታ በመስቀል ላይ በሞተ ጊዜ ቀስተ የመቅደሱ መጋረጃ ተሰነጠቀ። ይህም በክርስቶስ ሰው ወዶ እግዚአብሔር መቅረብና የእግዚአብሔርን ክብር ማየት ከዚህ ጊዜ በኋላ አይከለከልም ማለት ነው፡፡  ጥያቄ 16. የማያምኑ ሰዎች አስተሳሰብ ዛሬ እንዴት እንደሚገልጽ ምሳሌ በመስጠት አስረዳ።  ከቁጥር 15-16፡- ጌታ ኢየሱስን ሳይቀበል ሰው ብሉይ ኪዳንን ቢያነብ ብሉይ ኪዳን ለእርሱ የተሸፈነ መጽሐፍ ነው። ግን ብሉይ ኪዳን ስለ ክርስቶስ ስለሚናገር በክርስቶስ አምኖ ለሚያነበው ሰው ብሉይ ኪዳን ያለመጋረጃ የሚነበብ መጽሐፍ ነው። የእግዚአብሔርንም ክብር በክርስቶስ በኩል ከብሉይ ኪዳን መጽሐፍት ማየት ይቻላል፤ (ዮሐ.5፡46 እና 47፤ ሉቃ.24:44-47)። ስለዚህ ሐዋርያው እንዲህ አለ፡- «ያ መጋረጃ በልባቸው ይኖራል፤ ወደ ጌታ ግን ዘወር ባለ ጊዜ ሁሉ መጋረጃው ይወሰዳል»። (ቁጥር 16)  ቁጥር 17 እና 18፡- “ጌታ ግን መንፈስ ነው” ማለት ወልድና መንፈስ ቅዱስን ያለመለየት አነጋገር አይደለም፡፡ ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ነው ሲል አስቀድሞ ገልጿል፡፡ ያ መንፈስም የሚሠሪው ሰው በጌታ በኢየሱስ ሲያምን ብቻ ነው። ይህን ሃሳብ በአጭሩ ለማለት የጌታንና የመንፈስ ቅዱስን ሥራ በማቀናበር ጌታ ግን ሕጉ ሳይሆን ሕይወት የሚሰጠው መንፈስ ነው አለ።  ሐዋርያው ይህን ያለመጋረጃ በመገለጥ መሆንን ለአገልገሎቱም አዋለው። የሐዋርያት አገልግሎት ስውርነት የበዛበት በመጋረጃ የተከደነ አገልግሎት አልነበረም። ስለዚህ በስውር ሳይሆን «ገልጠን እንናገራለንና» ሲል በቁጥር 12 ላይም ጽፏል፤ ( 4:2)። የክርስቲያንም ሕይወት እንደዚህ መሽፋፈን የሞላበት ሳይሆን በጌታ ፊት ግልጥ የሆነና የጌታን ክብር በመቀበል በክብር ከደረጃ ወደ ደረጃ ይራመዳል።  ሰዎች በጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ሲያምኑ፥ ልባቸውን የጋረደው ነገር ይገፈፋል። እግዚአብሔር ለእርሱ በእነርሱም በኩል ለሌሎች ይገለጻል። ስለዚህ ክርስቲያኖች የእግዚአብሔርን ቅድስና፥ ፍቅር፥ ድድቅ፥ ወዘተ ማንፀባረቅ አለባቸው። ይህንን ስናንፀባርቅ ሕይወታችን ይለወጣል። ኢየሱስ ክርስቶስን እንመስላለን። ይህ ክርስቶስን የመምሰል ጉዳይ የሕይወታችንን ዘመን ሁሉ የሚፈጅብንና ያልተቋረጠ ዕድገትን የሚጠይቅ ነው። የእግዚአብሔር ቃል ኪዳን በሕይወታችን መጨረሻ ኢየሱስን በምንገናኝበት ጊዜ እርሱን እንደምንመስል ነው፤ (1ኛ ዮሐ.3፡2)።  ጥያቄ 17. ሕይወትህ “ጌታን እየመሰለ ከክብር ወደ ክብር የሚለወጠው” እንዴት ነው?

2ኛ ቆሮ.3:12-18 Read More »

2ኛ ቆሮ.3:7-11

ጥያቄ 10. በቁጥር 7 ላይ በፊደላት በድንጋዮች ላይ የተቀረጸ የሞት አገልግሎት» የሚለው ምኑን ነው?  ጥያቄ 11. ቁጥር 10ን በጥንቃቄ አንብበህ አጭር መግለጫ ጻፍ።  የብሉይ ኪዳን የሕግ ሥነ ሥርዓት በክብር መጣ፡፡ ይህ ክብር በዘፀ.34፡29-32 ባለው ክፍል ተተርኳል። ይህን ክፍል አንብብ። ሙሴ በሲና ተራራ ሕጉን በተቀበለ ጊዜ በተራራው ላይ ካለው ክብር የተነሣ ፊቱ በብርሃን አንፀባርቆ ነበር። ይህ የክብር መንፀባረቅ የብሉይ ኪዳን ክብር ነበር።  “የሙሴን ፊት ትኩር ብለው መመልከት እስኪሳናቸው ድረስን” ማለቱ ሙሴ ፊቱ ያበራ ስለነበር እስራኤላውያን መፍራታቸውን መግለጹ ነው። ይህ እንደዚህ ክብር የተሰጠው የሕይወት ሳይሆን የሞት አገልገሎት ነው። ከላይ እንደተመለከትነው ሕጉ ራሱ የሞት መሣሪያ አይደለም፤ ግን ኃጢአት በሰው ላይ ስላለ ሕጉ በኃጢአተኛው ላይ ሞትን አስከተለ። እንግዲያስ ጉድለቱ ከሕጉ ሳይሆን ከኃጢአተኛው ከሰው ነው።  ጥያቄ 12. ጥሩ ሥራ በመሥራት ወይም የተወሰኑ ሕገጋትን በመጠበቅ እንድናለን ለሚሉ ሰዎች ይህ እውነታ ምን የሚያስተምራቸው ይመስልሃል?  የሞት አገልገሎት የሆነው እንዲህ ክብር ከነበረው ለኃጢአተኛው ሕይወትን የሚሰጠው የመንፈስ አገልግሉት እንዴት የበለጠ ክብር አይኖረውም? የመንፈስም አገልግሎት ክብር አለው። እንዲያውም ከሕጉ ክብር የበለጠ ክብር አለው።  ይህ የአዲስ ኪዳን ክብር ምንድነው? በሥጋ ፊት ላይ የሚያበራ ሥጋዊ ክብር ሳይሆን የቅድስናና የድድቅ ክብር በነፍስ ውስጥ የሚያበራ ውስጣዊ ክብር ነው። ኃጢአተኛን ቀይሮ ክርስቶስን መምሰልን የሚሰጠው የጽድቅ ክብር አለው።  በቁጥር 9 ላይ ኩነኔንና ጽድቅን ያወዳድራል። የብሉይ ኪዳን አገልግሎት ኩነኔን አመጣ። ሕጉን ጠብቅ ሕይወት ታገኛለህ አለ፤ (ሮሜ 10፡5)። ሕጉ ስላልተጠበቀም የተባለው ኩነኔ መጣ። አዲስ ኪዳን ግን «ክርስቶስ ሕጉን በአንተ ምትክ ጠብቀልሃልና ክርስቶስን በመቀበል ጽድቅን ተቀበል» ይላል፤ (ሮሜ 10፡4)። ከዚህም ጨምሮ አዲስ ኪዳን የሕይወት ለውጥን (ቅድስናን) በመንፈስ ቅዱስ ሠሪነት በክርስቲያን ሕይወት ይሰጣል፡፡  ቁጥር 10 የሚለው የአዲስ ኪዳን ክብር ከብሉይ ኪዳን ክብር እጅግ ስለሚበልጥ የብሉይ ክብር ከአዲስ ኪዳን ክብር ጋር ሲወዳደር ፈጽሞ ክብር እንደሌለው ሆኖአል። ቁጥር 11 ብሉይ ኪዳን ጊዜያዊ አዲስ ኪዳን ግን ጽንቶ ይኖራል ይላል። የሙሴ ፊት ክብር አለመቆየት የብሉይ ኪዳንን ጊዜያዊነት አሳየ። ስለዚህ አሁን ብሉይ ኪዳን ተሽሮአል። ይህ ማለት ግን ሕጉ ሕይወታችንን አይቆጣጠርም ማለት አይደለም። ግን እንደ ብሉይ ኪዳን በውጭ ሳይሆን በልባችን ሕጉ ተድፎአል። ሕጉን የመጠበቅ ችሎታ መንፈስ ቅዱስ ይሰጠናል፤ (ሮሜ 8፡2-4)። በዚህም በ2ኛ ቆሮ.3፡11 ተሻረ ያለው ሕጉን ሳይሆን የብሉይ ኪዳንን አሠራር ነው። ሕጉ ዘላለማዊ የሆነውን የእግዚአብሔርን ባሕርይ የሚገልጥ ስለሆነ ለዘለዓለም አይሻርም። አሠራሩ ግን በውጭ በአዋጅ የሆነ የብሉይ አሠራር ተቀይሮ አሁን በኃይል በልብ ለውጥን የሚያመጣ የመንፈስ ቅዱስ ያም የአዲስ ኪዳን አመራር ተተክቷል። በአማርኛው ትርጉም አገልግሎት እያለ የሚተረጉመው አሠራር ተብሎ መተርጉም ይቻላል።  ጥያቄ 13. የአዲሱን ቃል ኪዳን ክብር ከበፊቱ ቃል ኪዳን ክብር ጋር አነፃፅር። እንዴት ነው የሚመሳሰሉት? እንዴት ነው አንደኛው ከሌላኛው የሚበልጠው? 

2ኛ ቆሮ.3:7-11 Read More »

2ኛ ቆሮ. 3:4-6

ጥያቄ 5. «በክርስቶስ በኩል ወደ እግዚአብሔር እንዲህ ያለ እምነት አለን» ሲል «እምነት» ማለቱ ምን ማለቱ ነው? ጥያቄ 6. «ፊደል ይገድላልና መንፈስ ግን ሕይወትን ይሰጣል» ሲል ምን ማለቱ ነው?  «በክርስቶስ በኩል ወደ እግዚአብሔር እንዲህ ያለ እምነት አለን» ማለቱ የአዲስ ኪዳን አገልጋይነት መቀበሉን ማመልከቱ ነው። በቁጥር 3 ላይ «በእኛም የተገለገለ» ያለው ወንጌልን ለቆሮንቶስ ሰዎች ስለሰበከ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ሕይወታቸው ተቀየረ ለማለት ነው። ይህ በሰው ኃይል የሚከናወን ስላልሆነ ሐዋርያውን ይህን ሥራ ለመሥራት እግዚአብሔር አስቻለው። እግዚአብሔር እንዲህ እንደሚያስችለው ወደ እግዚአብሔር በክርስቶስ በኩል እምነት አለው።  ጥያቄ 7. ይህ ዛሬ መሪዎች በሥራቸው ላይ ሊኖራቸው ከሚገባው እምነት ጋር የሚመሳሰለው እንዴት ነው?  ቁጥር 5 በቁጥር 4 ላይ በአጭሩ የተጻፈውን ሃሳብ በሰፊው ያብራራል። የአዲስ ኪዳን አገልጋይ ያዳረጋቸው፥ ለሥራው ብቃትን የሚሰጣቸው እግዚአብሔር እንጂ በእነርሱ ውስጥ ምንም ብቃት የለም። ብቃት ማለቱም ሥራውን ለማከናወን በቂ ኃይል መኖር ማለት ነው።  ጥያቄ 8. መሪዎች የእግዚአብሔርን ሥራ በራሳቸው ኃይል ለመሥራት ሲሞክሩ ምን ያጋጥማቸዋል?  በቁጥር 6 ላይ ይህን አገልግሎት እንደገና ማብራራት ይቀጥላል፤ «በመንፈስ እንጂ በፊደል ለማይሆን ለአዲስ ኪዳን አገልጋዮች እንሆን ዘንድ አበቃን»። እዚህ ላይ ፊደል የሚለው በቁጥር 3 በድንጋይ ላይ የጻፈው ካለው ጋር ይስማማል። እንግጺህ የፊደል አገልገሉት ማለት በልብ ሳይሆን በውጭ በድንጋይ ጽላት ላይ ብቻ የሚጻፍ የብሉይ ኪዳንን ሥርዓት ያመለክታል።  ቀጥሎም «ፊደል ይገድላልና መንፈስ ግን ሕይወትን ይሰጣል» ይላል። ይህም ማለት ሕጉ አድርግ ብሎ ከማዘዝ በስተቀር ልቦናን ቀይሮ ትእዛዝን የመጠበቅ ችሎታን አይሰጥም። ስለዚህ ሕጉን ካልጠበቅህ ትሞታለህ ስለሚልና ሰውም ሕጉን መፈጸም ስለማይችል ሕግ ይገድላል ይላል። ይህን ሃሳብ በሮሜ 7:7-12 ዘርዝሮአልና ያን ክፍል በጥንቃቄ አንብብ።  አዲስ ኪዳን የመንፈስ አገልግሎት እንጂ የሕግ አገልግሎት ስላልሆነ በውስጥ በልብ በመንፈስ ቅዱስ ሠሪነት ሕጉን ይጽፋል። ይህም ማለት ሕይወትን ይቀይራል።  ጥያቄ 9. የአዲሱ ቃል ኪዳን አገልግሎት ከፊተኛው ቃል ኪዳን አገልግሎት የሚሻለው በምን መልኩ ነው? ሁለቱን ቃል ኪዳኖች አነፃፅር።

2ኛ ቆሮ. 3:4-6 Read More »

2ኛ ቆሮ.3:1-3

በዚህ ምዕራፍ ውስጥ አጥብቀን ልናስተውል የሚገባን በቁጥር ሦስት ላይ ያለው “ሰዎች ሁሉ የሚያውቁትና የሚያነቡት በልባችን የተጻፈ መልእክታችን እናንተ ናችሁ” የሚለው ነው። መጽሐፍ ቅዱስን ገልጠው ለማያነቡት ሰዎች፥ ክርስቲያኖች ሕያዋን የሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ መሆን አለባቸው። የክርስቲያን ሕይወት ክርስቶስን የሚያሳይ ግልጽ መድሐፍ መሆን አለበት።  ጥያቄ 1. የማመስገኛ መልእክት ምን ነበር? ጥያቄ 2. የቆርንቶስን ቤተ ክርስቲያን «በልባችን የተጻፈ መልእክታችን እናንተ ናችሁ» ሲል ምን ማለቱ ነው?  የአማርኛው ትርጉም “የማመስገኛ ደብዳቤ” ብሎ የተረጕመው ትክክለኛ ትርጉም አይደለም። ትክክለኛ ትርጉሙ «የመሸኛ ደብዳቤ» ወይም «የማስተዋወቂያ ደብዳቤ» ነው። መሠረታዊ ሃሳቡ አንድ ወንጌላዊ ከአንድ ቤተ ክርስቲያን ለአገልገሎት ወደማያውቀው ቤተ ክርስቲያን ሲሄድ ከነበረበት ቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎች የመታወቂያ ደብደቤ ተሰጥቶት ይሄዳል። በዚያ ደብዳቤ መሠረት የሄደበት ቤተ ክርስቲያን በአክብሮት ተቀብሎ አገልገሎቱን ይቀበላል።  ሐዋርያውም የዚህ ዓይነት የማስተዋወቂያ ደብደቤ ለሚያስፈልጋቸው አገልጋዮች ይሰጥ ነበር፤ (1ኛ ቆሮ.16፡10 እና 11፡ 2ኛ ቆሮ. 8:22-24፤ ሮሜ 16፡1 እና 2)። አሁን ግን የቆርንቶስን ቤተ ክርስቲያን እርሱ ራሱ የመሠረታት ስለሆነች ለቆርንቶስ ቤተ ክርስቲያን የማስተዋወቂያ ደብዳቤ ይዞ ሊቀርብ አይገባውም። እንዲሁም በሁሉም ቦታ ሐዋርያነቱ የታወቀ ስለሆነ የቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያውን የሚያስተዋውቅ ደብደቤ ልትሰጠው አይገባም። «የማመስገኛ መልእክት ወደ እናንተ ወይስ ከእናንተ ያስፈልገን ይሆንን?» ብሎ በአሽሙር ይጠይቃል።  በተጨማሪም «እንደሌሎች» በማለት የሚጠቅሳቸው ከእርሱ በኋላ ሐዋርያ ነን እያሉ የማስተዋወቂያ ደብደቤ ይዘው ወደ ቆርንቶስ ቤተ ክርስቲያን ሾልከው የገቡ ሐሰተኛ ሐዋርያት እንደነበሩ ያመለክታል፤ (2ኛ ቆሮ.11:13-15)።  ሐዋርያው በቀለም የተጻፈ ደብዳቤ ሳይሆን በመንፈስ ቅዱስ የተጻፈ መታወቂያ መልእክት ነበረችው፤ እርሱም የተከላት የሐዋርያነቱ ማህተም የሆነች የቆርንቶስ ቤተ ክርስቲያን ነበረች። የቆርንቶስ ሰዎች ከዓለማዊነት ተለውጠው የክርስቶስ ሰዎች የሆኑት በእርሱ አገልግሎት ስለሆነ በይፋ የቆመ ማንም ሰው የሚመለከተው መልእክት ናቸው፤ (1ኛ ቆሮ. 6፡9-11)። ይህ መልእክት በሐዋርያውም ልብ ደግሞ አለ። ይህም ማለት ሐዋርያው በልቡ በፍቅር ይመለከታቸዋል ማለት ነው።  ጥያቄ 8. ሀ/ ሁላችንም የዓለም መልእክት ልንሆን የምንችለው እንዴት ነው? ለ/ ሕይወታችን ማሳየት ያለበት ምን ዓይነት መልእክት ነው?  በቁጥር 3 ላይ የልብ ጽላትና የድንጋይ ጽላትን ያነጻጽራል (በተቃራኒ ያስተያያቸዋል)። ጽላት የሚለው ቃል አሥርቱ ትእዛዛት የተጻፈበት በእግዚአብሔር ለሙሴ የተሰጠው ድንጋይ ነው፤ (ዘፀ. 31:18)። አዲስ ኪዳንንና ብሉይ ኪዳንን ያነጻጽራል።  ሐሰተኞቹ ሐዋርያት በሙሴ ሕግ የሚመኩ ሳይሆኑ አይቀሩምና ስለዚህ የእርሱ አገልግሎት የብሉይ ኪዳን ሳይሆን የአዲስ ኪዳን መሆኑን ያስረዳል፤ (ኤር.31:33)።  የብሉይና የአዲስ ኪዳን ተቃራኒነት የመጻፊያው እቃ ነው እንጂ የተጻፈው አይደለም፡፡ ብሉይ ኪዳን በድንጋይ ጽላት ሲጻፍ አዲስ ኪዳን ግን በልብ ጽላት ላይ ተጻፈ። ነገር ግን በሁለቱ ጽላት ላይ ያለው ያው የእግዚአብሔር ሕግ ነው እንጂ የተለያየ አይደለም። እግዚአብሔር ለአዲስ ኪዳን ምእመናን ከአሥርቱ ትእዛዛት ሌላ አዲስ ትእዛዝ አልሰጠም፤ አሥርቱ ትእዛዛትንም አልሻረም። ግን በአዲስ ኪዳን መንፈስ ቅዱስን ስለተቀበልን ሕጉን ለመጠበቅ እንችላለን። ስለዚህ ነጥብ የሚከተሉትን ጥቅሶች በጥንቃቄ አጥና፤ (ዘፀ. 20፡3-17፤ ሕዝ.36፡26-27፤ ማቴ. 5:17፤ ሮሜ 13:9-10፤ 1ኛ ዮሐ.1:5-8)።  ጥያቄ 4. የእግዚአብሔር ቃል በልባችን የመጻፉ እውነታ በብሉይ ኪዳን ጊዜ በድንጋይ ላይ ከተጻፈው የእግዚአብሔር ሕግ የሚበልጠው እንዴት ነው? 

2ኛ ቆሮ.3:1-3 Read More »

2ኛቆሮ.2:14-17

ጥያቄ: ድል በመንሣቱ ለሚያዞረን ሲል ምን ማለቱ ነው?  ጥያቄ : የሞት ሸታና የሕይወት መዓዛ መሆን ምን ማለት ነው? ጥያቄ : በቁጥር 17 የእግዚአብሔርን ቃል መሸቃቀጥ ማለት ምንድነው?  ቁጥር 14:- «ድል በመንሣቱ ለሚያዞረን» ይህ አነጋገር ግልጽ አይደለም። መሆን ያለበት «ድል በመንሣት ለሚያዞረን» ነው። ይህም ማለት እግዚአብሔር ሐዋርያትን በድል ከቦታ ወደ ቦታ ያዞራቸዋል ማለት ነው። ይህ አነጋገር በዘመኑ የነበረውን የነገሥታትን ልማድ ይመረኮዛል። አንድ ንጉሥ ድል ሲያደርግ ለድል ያበቁትን ጃግኖች በክብር አሰልፎ በድል ሰልፍ ይመራቸዋል። ሐዋርያው ያን ተመርኩዞ ክርስቶስ በተጕናጸፈው ድል እግዚአብሔር ሐዋርያቱንና የወንጌልን አገልጋዮች በክብር ሰልፍ ይመራቸዋል ማለቱ ነው።  በዚህም ሰልፍ በየሄዱበት ቦታ የእግዚአብሔርን እውቀት ሽታ ያሰራጫሉ። አሁንም ሐዋርያው የጥንትን ባህል ተመርኩዞ ነው ስለዚህ ሽታ የሚናገረው። በዘመኑ በድል ሰልፍ ላይ ጣፋጭ ሽታ ያለው እጣን ይጤስ ነበር። ይህን ምሳሌ ተመርኩዞ ሐዋርያው የወንጌል አገልጋዮች የአሸናፊው የክርስቶስ እጣን ናቸው ይላል። ይህም እጣን “የእግዚአብሔር እውቀት” ነው። በዞሩበት ቦታ ሁሉ ሰዎችን ወደ እግዚአብሔር እውቀት ይመራሉ።  ጥያቄ: የአንተ ሕይወት የእግዚአብሔርን እውቀት ለሌሎች የሚገልጽ ጣፋጭ ሽታ የሆነው እንዴት ነው?  ቁጥር 15 እና 16፡- ይህ ሽታ ሁለት ዓይነት ነው። ወንጌላውያንን የሰሙ ሁሉ ወደ እምነት አይመጡም። አንዳንዶች ሲቀበሉ ሌሎች ይክዳሉ። የሚያምኑት ሕይወትን ሲቀበሉ ወንጌላውያን የሕይወት ሽታ ይሆኑአቸዋል። የማያምኑት ደግሞ ባለመቀበላቸው ለፍርድ ሲቀሩ ወንጌላውያን ለማያምኑት የሞት ሽታ ይሆኑባቸዋል። ከዚህ ጋር የሚከተሉትን ጥቅሶች አስተያይ፤ ሉቃስ 2:34፤ ዮሐ.3፡36።  ለዚህ ሥራ መሰለፍ ከባድ ነገር እንደሆነ ተረድቶ ሐዋርያው «ስለዚህ ነገር የሚበቃ ማነው?» ይላል። ለዚህ ሥራ አገልጋዮቹን የቀባ እግዚአብሔር ስለሆነ ብቃትንም የሚሰጥ እርሱው ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ እንኳን ያለ እግዚአብሔር ረዳትነት ሙሉ በሙሉ ጥሩ ሽታ እንደማይኖረው ተረድቶ ነበር። ታዲያ እኛ ምን ያህል ነው እግዚአብሔር የሰጠንን ሥራ ለመሥራት በእርሱ ላይ መደገፍ ያለብን?  ወንጌላዊ የሥራውን ታላቅነት ተረድቶ በእምነት በእግዚአብሔር ብቻ ተደግፎ አንደመቆም ቃሉን ለማሳመን የተለያዩ ዘዴዎችን እንዲጠቀም ይፈተናል። አንዳንዶች በእኛም ዘመን በሰው ዘንድ መከበርን ፍለጋ የሥጋ ጥበቦችን ሲጠቀሙ ይታያሉ። ሰው በጌታ ቃል ላይ ምንም ዘዴ መቀላቀል አያስፈልገውም፤ ቃሉ ራሱን የቻለ ኃይል ነውና። ስለዚህ ሐዋርያው «የእግዚአብሔርን ቃል እንደሚሸቃቅጡ እንደብዙዎች አይደለንምና» ይላል። የእግዚአብሔርን ቃል መሸቃቀጥ ማለት ሰዎች ወንጌልን እንዲቀበሉ የሰዎችን ዘዴ በወንጌል ላይ መጨመር ማለት ነው። ይህን መሸቃቀጥ የተባለውን ቃል ሐዋርያው በዘመኑ ከነበሩ የወይን ጠጅ ነጋዴዎች ሥራ ተበድሮአል። በዘመኑ የነበሩ ሌቦች የሆኑ የወይን ጠጅ ነጋዴዎች በማታለል ገንዘብ ለማትረፍ በወይኑ ላይ ውኃ ይቀላቅሉ ነበር። ይህም ወይኑን ርካሽ ወይን ያደርገዋል። በእግዚአብሔርም ቃል ላይ የግል ጥቅምን አስምርኩዞ የሰውን ዘዴና ጥበብ መጨምር ትርፉ ንጹሑን ቃል ማራከስ ነው።  ጥያቄ 13. የሰዎችን የአሠራር ዘይቤ በመጠቀም እንዴት አድርገን ወንጌልን ማስተላለፍ እንደምንችል ምሳሌ በመስጠት አስረዳ።  ሐዋርያው ግን «በቅንነት» ወንጌልን ምንም ሐተታ ሳይቀላቅል ይናገር ነበር። ይህም ውጭን አይቶ በሚፈርድ ሰው ፊት የሚደረግ ጥንቃቄ ሳይሆን ልብን በሚመረምር በእግዚአብሔር ፊት የሚደረግ ጥንቃቄ ነው። «በእግዚአብሔር እንደተላክን በእግዚአብሔር ፊት በክርስቶስ ሆነን እንናገራለን»። ወንጌላዊ ሁልጊዜ አስቀድሞ ሰውን ሳይሆን እግዚአብሔርን ደስ ለማሰኘት መሰለፍ አለበት። በእግዚአብሔር እንደተላከ በእግዚአብሔር ፊት የሚቆም ካህን መሆኑን መዘንጋት የለበትም። ወንጌልን በተገቢው መንገድ ለማስተላለፍ ሁለት ነገር ያስፈልገናል።  አንደኛ:- ወንጌል ምን እንደሆነ በደንብ ማወቅ ይገባናል፤ ምክንያቱም የሰዎችን ሃሳብ በውስጡ ላለመጨመር ስንል ነው። ይህ ማለት ወንጌልን በተመለከተ ሰዎች ጥሩ ትምህርት ማግኘት አለባቸው።  ሁለተኛ፡- ወንጌልን በምንሰብክበት ጊዜ ከውስጥ ይህንን እንድናደርግ ያነሳሳን ሃሳብ ንጹሕ መሆኑን ማየት ይገባናል። ገንዘብን ከመውደድ ወይም ታዋቂነትን ለማግኘት ስንል መስበክ አይኖርብንም። በምትኩ ለእግዚአብሔር ካለን ፍቅርና ታዛዥነት የተነሣ መሆን ይገባዋል።  ጥያቄ 14. ህ/ እውነተኛውን ወንጌል ለማስተላለፍ አንድ ሰው ማወቅ ይገባዋል ብለህ የምታምንባቸውን ነገሮች በዝርዝር ጻፍ። ለ/ አንዳንድ ሰዎች ወንጌልን ለመስበክ በሚነሡበት ጊዜ ሊኖራቸው የሚችለውን የተሳሳተ አመለካከት አብራራ። ሐ/ ወንጌልን ለመስበክ የሚያነሣሡን ትክክለኛ የሆኑ አስተሳሰቦች ምን መሆን ይገባቸዋል?

2ኛቆሮ.2:14-17 Read More »