የአዲስ ኪዳን መጽሐፍ ቅዱስ ጥናት

2ኛ ቆሮ. 9፡6-15

ጥያቄ 7. በቁጥር 6 ላይ ሐዋርያው መስጠትን ከምን ጋር ያመሳስላል?  ጥያቄ 8. በቁጥር 10 መሠረት መስጠት የማይችል ክርስቲያን ሊኖር ይገባዋል?  ጥያቄ 9. በቁጥር 12 መሠረት የመስጠት መንፈሳዊ ውጤት ምንድነው?  ጥያቄ 10. የመስጠት አርአያችን ማነው? (ቁጥር 15)  ቁጥር 6፡- መስጠት እንደመዝራት ይመስላል። በግብርና ዓለም በጥቂት የዘራና በብዙ የዘራ እኩል አያጭድም። እንዲሁም በመስጠት ለጋስነት ብዙ በረከትን ያስገኛል፤ (ሉቃ.6፡38)። ይሁን እንጂ ክርስቲያን ብዙ ለመሰብሰብ ብሎ በንግድ መንፈስ መስጠት የለበትም። ይህ አሰጣጥ በደስታ የሚደረግ መሥዋዕት ሳይሆን ንግድ ስለሚሆን እግዚአብሔርን አያስደስተውም፤ (ዕብ.13:16)። ነገር ግን በልግስና ለሚሰጥ ክርስቲያን ይህ የዘሪው ተስፋ መጽናኛ ሊሆነው ይገባል።  ጥያቄ 11. በመስጠትና በመዝራት መካከል ያለውን መመሳሰል ወይም ግንኙነት አብራርተህ ገልጽ።  ቁጥር 7:- የክርስቲያን ስጦታ እንደግብር በገድ ሊሆን አይገባም። ለእግዚአብሔር የሚቀርብ የምስጋና መሥዋዕት ስለሆነ በግድ ከሆነ ትርጉሙን ይቀይራል። ስለዚህ የእግዚአብሔር ሕዝብ ከስስት መንፈስ ነፃ ሆነው በልግስናና በደስታ መስጠት አለባቸው። አለመስጠትም በደል ነው፤ ቅር እየተሰኙ መስጠትም በደል ነው። ስለዚህ ትክክለኛው ነገር የማይነገረውን የእግዚአብሔርን ስጦታ እያሰብን በልግሥናና በደስታ መስጠትን መማር ነው።  ጥያቄ 12. ለምንድነው በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ ያሉ ሰዎች አሥራት የሚሰጡት? ከልማድ የተነሣ ነው? የሚሰጡበትስ ምክንያት እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ነው? ለምን?  ከቁጥር 8-9:- ከመዝሙረ ዳዊት 111 (112) በመጥቀስ የክርስቲያንን መስጠት ይደግፋል። በዚህ መዝሙር ላይ የተጻፈው ስለጻድቅ ሰው ነው። በቁጥር 1 ላይ “እግዚአብሔርን የሚፈራ ትእዛዙንም እጅግ የሚወድ ሰው ምስጉን ነው” ብሎ ይጀምራል። ከዚያም በቁጥር 9 ላይ ይህንን በ2ኛ ቆሮንቶስ 9፡8 እና 9 የተጠቀሰውን እናነባለን። «በተነ ለችግረኞች ሰጠ» በማለት የአሰጣጡን ልግስና ይገልጻል። ለቆሮንቶስም ክርስቲያኖች ይህንን እንዲህ ለመስጠት የሚያስችለውን ጸጋ እግዚአብሔር ስለሆነ የሚሰጠው ለእነርሱም ሊሰጥ ዝግጁ መሆኑን ያስረዳል።  በቁጥር 8 ላይ ጳውሎስ አንድ ትልቅ እውነታን ያስተምረናል። እግዚአብሔር በግላችን የሚሰጠን በረከቶች ከአሰጣጣችን ጋር ግንኙነት እንዳለው ያስተምረናል። በለጋስነት የሚሰጥን ሰው እግዚአብሔር ሁልጊዜ በነገር ሁሉ ብቃትን አግኝቶ ለበጎ ሥራ ይበዛ ዘንድ ጸጋን እንደሚያበዛለት ቃል ይገባል። አንድ ሰው እንዳለው «እግዚአብሔር ከሚሰጠን በላይ ለእርሱ መልሰን የምንሰጠው ከቶ አይኖርም።» እግዚአብሔር በሚሰጠን በትንሽ ነገር ታማኞች መሆናችንን ካሳየን፥ በትልቁ ነገር ሊተማመንብን ይችላል። የሚሰጡትን የተለያዩ ስጦታዎች በአግባቡ የማንጠቀምበት ከሆነ ሌላ የበለጠ ስጦታ ለመስጠት በእኛ ላይ አይተማመንብንም፤ (ሚልክ.3፡ 6-12 ተመልከት )።  ቁጥር 10፡- ማንም ክርስቲያን «የምሰጠው የለኝም፤ ስለዚህ ተቀባይ እንጂ ሰጭ መሆን አልችልም» ማለት አይገባውም። በእግዚአብሔር ፊት የስጦታ ትልቅነት የሚመዘነው በተሰጠው ብዛት ሳይሆን ባስቀረው ብዛት ነው። በብሉይ ኪዳን ከአሥር አንድ መስጠት ተገቢ ነበር። የአሥራቱ ብዛት ሳይሆን በእርግጥ ሰው ካለው አሥራት መስጠቱ ነበር የሚታየው። በስጦታ ብዛት ከሆነ ሀብታም ከአንድ ሺህ ብር ሃምሳ ብር ቢሰጥ ስጦታው ትንሽ ነው፤ አሥራቱ ከሺህ ብር መቶ ብር እንጂ ሃምሳ ብር ስላልሆነ። ጽሃው ግን ሃምሳ ብር ኖሮት ከሃምሳው አሥራት አምስት ብር ብቻ ሳይሆን አሥር ብር ቢሰጥ ሃምሳ ብር ከሰጠው የእርሱ ይበልጣል፤ (ማር.12: 43-44)።  በተለይ እኛ ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች ከውጭ አገር ከሐብታም ክርስቲያኖች የሚላከውን የስጦታ ብዛት በማየት እራሳችን ከመስጠት በመቆጠብ የመስጠትን ጸጋ ልናጣ ስለምንችል መጠንቀቅ አለብን። መፍትሄው ስጦታውን አለመቀበል ሳይሆን «ስጡ» የሚለውን የእግዚአብሔርን ቃል መከተል ነው። «ለዘሪ ዘርን… የሚሰጥ እርሱም የምትዘሩትን ዘር ይሰጣችኋል»! (ቁጥር 10)።  ጥያቄ 13. ሀ/ በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ የሚገኙ ድኃና ሀብታም ምዕመናን ለቤተ ክርስቲያን አሥራት ይሰጣሉን? ለ/ ይህ ከላይ የተጠቀሰው ችግር በቤተ ክርስቲያናችሁ ውስጥ ይታያል? እንዴት?  ቁጥር 11:- «በሁሉ ነገር ባለወጠጎች ትሆናላችሁ» ማለቱ ስለቁሳቁስ ብልጽግና ሳይሆን ስለመንፈሳዊ ቸርነትና መልካም ተግባር ነው የሚናገረው። የእግዚአብሔር ልጆች በመልካም ሥራ ድሆች እንዲሆኑ እግዚአብሔር ፈቃዱ አይደለምና ለበጎ ሥራ የተጋን እንሁን፤ (ኤፌ. 2:10)።  ከቁጥር 12-14:- ክርስቲያን ለተቸገረ ወንድሙ ሲሰጥ ያ ችግረኛው ወንድም ስለተቀበለው ስጦታ እግዚአብሔርን ስለሚያመሰግን የክርስቲያን ስጦታ እግዚአብሔርን ያከብራል። ስለዚህም የክርስቲያን ስጦታ የምስጋና መሥዋዕት ይሆናል። እንዲሁም በተቀባዩ ዘንድ የክርስቲያንን ፍቅር ይመሠርታል። ፍቅርም ስላለ ክርስቲያኖች እርስ በርስ በጸሎት ይደጋገፋሉ፤ (ቁጥር 14)።  ቁጥር 15፡- በክርስቲያን የስጦታ አገልግሎት አለመሰለፍ የማይነገረውን የእግዚአብሔርን ስጦታ አለመገንዘብ እንደሆነ መረዳት አለብን። ይህ በልጁ በኩል የሰጠን ስጦታ ነው፤ (ዮሐ.3፡16)። የእግዚአብሔርን ታላቅ ስጦታ በነፃ ስላገኘን እኛም እንደአባታችን ይህንን ነገር ለሌሎች ለማካፈል ፈቃደኞች መሆን አለብን።  ጥያቄ 14. ከምዕራፍ 8 እና 9 መስጠትንና አሥራትን በተመለከተ ልንከተላቸው የሚገቡንን የተለያዩ መመሪያዎች በዝርዝር  ጻፍ። 

2ኛ ቆሮ. 9፡6-15 Read More »

2ኛ ቆሮ. 9፡1-5

ጥያቄ 5. ቁጥር 4ን አብራራ፤ በተለይ ያልተዘጋጃችሁም ሆናችሁ ቢያገኗችሁ … እኛ እንዳናፍር ይሁን» ያለውን አብራሪ።  ከቁጥር 1-2:- ሐዋርያው ጳውሎስ ከአንድ ዓመት በፊት የቆሮንቶስ ሰዎች ይህን መዋጮ ለመስጠት ተዘጋጅተዋል ብሎ ለመቄዶንያ ሰዎች ተናግሮ ነበር። የቆሮንቶስ ሰዎች በውስጣቸው በተነሣው ጭቅጭቅ ምክንያት የሰጡትን ተስፋ ገና ሥራ ላይ ስላላዋሉት ጳውሎስ ስለእነርሱ ለመቄዶንያ ሰዎች በተናገረው ማፈር አልፈለገም። ሆኖም ይህ ከአንድ ዓመት በፊት የቆሮንቶስ ሰዎች ማዘጋጃት ለመቄዶንያ ሰዎች መነሳሻ ሆኖ እንደነበር ይነግራቸዋል። አሁን በአጸፋው የመቄዶንያ ሰዎች የቆሮንቶስን ሰዎች እንዲያበረታቸው ሐዋርያው ስለመቄዶንያ ክርስቲያኖች ትጋት ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ይናገራል። ይህ የቅንዓት ፉክክር ሳይሆን ቅዱስ የሆነ እርስ በርስ ማበረታታት መሆኑን ተገንዝበን የአንድ ቤተ ክርስቲያን ትጋት ሌሎችን እንደሚያበረታታ ማወቅ አለብን።  ቁጥር 3፡- ይህ የተመካባቸው ትምክህት ወሬ ብቻ ሆኖ እንዳይገኝ ተግተው የገቡትን ቃል ኪዳን ሥራ ላይ እንዲውሉ የሚያበረታቷቸውን ወንድሞች አስቀድሞ ወደ ቆሮንቶስ ይልካል።  ቁጥር 4:- ይህንንም የደረገበት የመቄዶንያ ሰዎች ወደ ቆሮንቶስ ከሐዋርያው ጋር ከመጡ ሐዋርያው እንዳያፍር ነው። ሆኖም እዚህ ላይ የሐዋርያውን ጥበብ መገንዘብ አለብን፡፡ በሐዋርያውና በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን መካከል መቃቃር ስለነበር «እናንተ እንዳታፍሩ» ብሎ መናገር አልፈለገም። የሰጡትን ተስፋ ሥራ ላይ ለማዋላቸው ሐዋርያው ብቻ ሳይሆን እነርሱም ማፈር እንደሚገባቸው ገልጽ ነው። ይህንን ከመናገር ግን ሐዋርያው ይቆጠባል።  ቁጥር 5፡- «ከስስት ሳይሆን» ይላል። ስጦታ በደስታ መደረግ አለበት እንጂ በቅሬታ መሆን የለበትም። የቆሮንቶስ ሰዎች ከመቄዶንያ አስቀድመው ተስፋ እንደሰጡ መጠን አሁንም ከመቄዶንያ አስቀድመው ስጦታውን ማዘጋጃት እንዳለባቸው ይነግራቸዋል። አንዳንድ ጊዜ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ኃይለ ቃልንና ችክ ያለ ልመናን በመጠቀም ምዕመናን ገንዘብ እንዲሰጡ ያደርጋሉ። በዚህ ምክንያት ሰዎች ከደስታ ሳይሆን ከአንገት በላይ በሆነ ስሜት ተገፋፍተው ይሰጣሉ። መሪዎች የአሥራትን አሰጣጥ እውነታ የማስተማር ኃላፊነት አለባቸው፤ ይህም ሲሆን በመስጠት የሚገኘውን ደስታ ከሰዎች ልቦና ውስጥ ማውጣት አይገባቸውም።  ጥያቄ 6. እንዴት አድርገው የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ምዕመናንን ለተሳሳተ ዓላማ ገንዘብ እንዲሰጡ ሊያደርጓቸው እንደሚችሉ ምሳሌ በመስጠት አስረዳ።

2ኛ ቆሮ. 9፡1-5 Read More »

2ኛ ቆሮ. 8:16-24

ጥያቄ 1. በቁጥር 19 ላይ «በምናገለግለው በዚህ ቸር ሥራ ከእኛ ጋር እንዲጓደድ በአብያተ ክርስቲያናት ተመረጠ» ሲል ቸር ሥራ ያለው ምኑን ነው? (መጓደድ ማለት መጓዝ ማለት ነው)።  ጥያቄ 2. ቁጥር 20 እና 21ን በሰፊው አብራራ።  ከቁጥር 16-17:- ለኢየሩሳሌም ምእመናን ከቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን የተሰበሰበውን ገንዘብ ወደ ኢየሩሳሌም ለማድረስ መሪ ሆና እንዲያገላገል ቲቶ ተመረጠ። ቲቶም በሐዋርያው ስለታዘዘ ብቻ ሳይሆን በራሱ ልብ ለቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያንና ለዚህ ለተባለው መዋጮ ታላቅ ትጋትን ያሳየ ሰው ነበር። ከዚህ ላይ የምንማረው አንድ ሰው በቤተ ክርስቲያን ለአንድ ሥራ ሲመረጥ ያ ሰው ለዚያ ሥራ ትጋትና ፍላጉት ያለው ሰው መሆን አለበት።  ከቁጥር 18-19፡- ቲቶ ብቻውን የአብያተ ክርስቲያናትን ገንዘብ ከቆሮንቶስ ወደ ኢየሩሳሌም ይዞ እንዲሄድ የሐዋርያው ፈቃድ አልነበረም። ይህ ከሆነ ሐሜት እንደሚነሣ አውቆ ይህን ጥርጥር በሰው አእምሮ ውስጥ ላለማሳደር ከቲቶ ጋር ሌሎችን ለመላክ ወሰነ። እነዚህም በታማኝነታቸው በአብያተ ክርስቲያናት የተመሰከረላቸው ወንድሞች እንደሆኑ ያስታውቃል።  ከቁጥር 20-21:- «ስለምናገለግለው ስለዚህ ለጋስ ስጦታ ማንም እንዳይነቅፈን እንጠነቀቃለን»። ይህ ማለት ስለሚሰበሰበው ገንዘብ ሐሜት እንዳይነሣ ጥንቃቄ እናደርጋለን ማለት ነው። ይህንም ያዳረገው በአንድ ሰው ብቻ ሳይሆን በርከት ባሉ ሰዎች እጅ ገንዘቡን በመላክና የተላኩት ሰዎች ስለታማኝነታቸው በአብያተ ክርስቲያናት የተመሰከረላቸው እንዲሆኑ በማድረግ ነበር። «በጌታ ፊት ብቻ ያይደለ ነገር ግን የሰው ፊት ደገሞ መልካም የሆነውን እናስባለንና» ። ይህም ማለት ንጽሕናንና ጥሩ ስምን በሰው ዘንድ መጠበቅ በክርስትና ሃይማኖት የሚፈለገብን ነገር ነው ማለት ነው። «ጌታ ልቤን ያውቃል ሰው ስለኔ በሚለው አልጨነቅም» ማለት መልካም እያደረገን በግፍ በምንታማበት ጊዜና ያን ሐሰተኛ ሐሜት ለማስተባበል ማስረጃ አቅርበን ሳይሳካልን ሲቀር እንጂ ሐሜት የሚያስነሣ ነገር እየሠራን መሆን የለበትም፤ 1ኛ ጴጥ.4፡14 እና 15ን ተመልከት።  እንደቤተ ክርስቲያን መሪ፥ ጳውሎስ ገንዘብ ነክ ነገሮችን የተለየ ትኩረት ሰጥቷቸው ነበር። ከዚህ በፊት እንደተመለከትነው ወንጌልን ለመስበክ ያነሣሣውን ሃሳብ እንዳይጠይቁት ሲል ደመወዝ ላለመቀበል ወስኖ ነበር (1ኛ ቆሮ.  9፡7-18)። አሁን ደግሞ ከየአብያተ ክርስቲያናቱ ለኢየሩሳሌም ቤተ ክርስቲያናት ተብሎ የሚሰበሰበውን ገንዘብ ለብቻው በኃላፊነት ለመያዝ ፈቃዳኛ አልሆነም። ፈተና ውስጥ ለመግባት አይፈልግም ነበር። በተጨማሪም ምስክርነቱን የሚያጎድፉ ነቀፋዎች እንዲሰነዘሩበት አይፈልግም፡፡ የቤተ ክርስቲያን መሪዎችን የሚያጠፋበት አንደኛው የሰይጣን መንገድ ገንዘብን በተመለከተ ያላቸውን ምስክርነት የጎደፈና የተጠላ ማድረግ ነው።  ጥያቄ . ሀ/ የቤተ ክርስቲያንን ገንዘብ በቅጡ ባለመያዙ አንድ የቤተ ክርስቲያን መሪ ምስክርነቱ ሲበላሽ አይተህ ታውቃለህ? ለ/ ገንዘብን በተመለከተ ጥሩ የሆነ ምስክርነት ማግኘቱ አስፈላጊ የሚሆነው ለምንድነው?  ከቁጥር 22-23፡- ሐዋርያው ገንዘቡን ይዘው ስለሚሄዱት ሰዎች የራሱን ምስክርነት ይሰጣል። እነዚህ ሰዎች ለዚህ ሥራ ታማኝ ሆነው በመገኘታቸው የሐዋርያው ብቻ ሳይሆን የክርስቶስም ክብር ሆነው ተገኙ። እኛም በተጠራንበት ጥሪ ታማኝ በመሆን እንዲህ ለጌታና ለሚመኩብን ወንድሞች የማናሳፍር ሠራተኞች ሆነን እንድንገኝ ጌታ ይርዳን!  ከቁጥር 24፡- ፍቅር በልብ ቢኖር በሥራ መገለጥ አለበት። ይህንን እንዲያዳርጉ የቆሮንቶስን ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያው ይመክራል።  ጥያቄ 4. ገንዘብ ነክ ነገሮችን በተመለከተ አንድ ቤተ ክርስቲያንና መሪዎችዋ መውሰድ የሚገባቸውን ጥንቃቁ የሚገልጹ መመሪያዎችን በዝርዝር ጻፍ። 

2ኛ ቆሮ. 8:16-24 Read More »

2ኛ ቆሮ. 8:8-15

ጥያቄ 14. “በሌሎች ትጋት በኩል የፍቅራችሁን እውነተኛነት ደግሞ ልመረምር እላለሁ” ሲል ምን ማለቱ እንደሆነ አብራራ።  ጥያቄ 15. የክርስትና ልግሥና መመርያ ምንድነው? (ቁጥር 9)  ጥያቄ 16. ቁጥር 15ን የጠቀሰው ከየት ነው? ከየት እንደተጠቀሰ ካመለክትህ በኋላ ታሪኩን ሰፋ አድርገህ አብራራ ። ቁጥር 8:- ሐዋርያው ማዘዝ ሲችል ግን በፍቅር ይለምናቸዋል። የእግዚአብሔር ሥራ በፍቅር እንጂ በግድ መደረገ የለበትም፡፡ በሌሎች ትጋት ሲል ቀደም ሲል የጠቀሳቸውን የመቄዶንያን አብያተ ክርስቲያናት ማለቱ ነው። «የፍቅራችሁን እውነተኛነት ልምረምር» ማለቱ ያላቸውን የክርስትና ፍቅር ሥራ ላይ በማዋል ማረጋገጥ እንዳለባቸው ማለቱ ነው። ከዚህ ጋር 1ኛ ዮሐ.3:17-18ን ተመልከት።  ቁጥር 9:- የክርስቲያን ስጦታ ምንጩ የክርስቶስ ራሱን ለእኛ መስጠቱ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ምድር ላይ ከመምጣቱ በፊት በምንግሥተ ሰማይ ወስጥ በሺህ በሚቆጠሩ መላእክት በመገልገሉ፥ የሁሉም ነገር ፈጣሪ በመሆኑ፥ የሁሉም ነገር ባለቤት በመሆኑ ሀብታም ነው ማለት እንችላለን። ነገር ግን እኛን የእግዚአብሔር ልጆች ለማድረግ ሲል መንግሥተ ሰማያትን ትቶ ወደ ምድር በመምጣት እንደ ድሃ ሰው ኖረ። ይህ ሁሉ የሆነበት ምክንያት እኛ የእግዚአብሔር ቤተሰብ አባል እንድንሆንና የእግዚአብሔር በረከት ወራሾች እንሆን ዘንድ ነው። ጌታ ራሱን የሰጠው በምድራዊ ነገር ሀብታም እንድንሆን ሳይሆን ከምድራዊ ሀብት በበለጠው በመንፈሳዊ በረከት ሀብታም እንድንሆን ነው።  ጥያቄ 17. ይህ ሁኔታ ለሌሎች መስጠትን በተመለከተ ምን ያስተምረናል?  ከቁጥር 10-12:- መስጠት የምንችለው ካልን ነው። ሰው እንዳለው መጠን እንዲሰጥ ይጠበቅበታል እንጂ ከአቅሙ በላይ እንዲሰጥ አይጠበቅበትም። እንዲሁም ለመስጠት ፍላጎት ካለ ያ ፍላጐት በሥራ ላይ ካልዋለ ወሬ ብቻ ሆኖ ይቀራል። «ማድረጉንም ፈጽሙ» በማለት ይህንኑ ይመክራቸዋል።  ከቁጥር 13-14:- የክርስቲያን መስጠት አንደኛ፡- በግድ ሳይሆን በፈቃዱ ነው። ሁለተኛ፡- ያላቸው ባዶ ሆነው የሌላቸው በእነርሱ እንዲበለጽጉ ሳይሆን ባላቸውና በሌላቸው መካከል እኩልነት እንዲመሠረት ነው። “ትክክል እንዲሆን ነው እንጂ … የእናንተ ትርፍ የእነርሱን ጉድለት ይሙላ”። በትክክል እንዲሆን ማለት እኩልነት እንዲመሠረት ማለቱ ነው። እኩልነት በፈቃድ እንጂ በአዋጅ ወይም በገድ እንዳይሆን የክርስትና ሃይማኖት ያስተምራል። እንዲሁም የክርስትና ሃይማኖት አንድ ሰው ባለው ሀብቱ የፈለገውን እንዲያደርግበት ሳይሆን የራሱን ችግር ካቃለላ በኋላ ለሌላቸው በልግስና እንዲያካፍል ነው! (በተጨማሪ ኤፌ.4፡28፤ 1ኛ ጢሞ. 6፡14-19)።  ጥያቄ 18. በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያሉትን ሀብታምና ድሃ ምእመናንን በተመለከተ ይህ ነገር እንዴት ነው ተግባራዊ ሊሆን የሚችለው?  ቁጥር 15፡- ይህን ክፍል የሚጠቅሰው ከዘፀ.16፡ 17ና 18 ላይ ነው። እስራኤላውያን መና እንዲሰበስቡ ታዘዙ፡፡ ለየቤተሰባቸው የሚበቃቸውን እንጂ ትርፍ እንዲሰበስቡ አልተፈቀደላቸውም ነበር። አንዳንዶች ግን ከስገብገብነት የተነሣ ትርፍ ሰበሰቡ። ግን በኋላ በተሰፈረ ገዜ «አንዱ አብዝቶ አንዱም አሳንሶ ለቀመ። በጎሞርም በሰፈሩት ጊዜ እጅግ ለለቀመ አልተረፈውም ጥቂት ለለቀመም አልጎደለበትም፡፡” አሁንም በክርስትና እምነት ሳለን ሰው የሚበቃው ካለው ትርፋን ከማጃብ ላሌለው ወንድሙ እንዲያካፍል ታዟል። ይህም የፍቅርና የርኅራኄ መግለጫ ብቻ ሳይሆን በእግዚአብሔርም የመታመን መግለጫ ነው። የሚከተሉትን ጥቅሶች አንብብ፤ ማቴ.6፡25-33፤ ኤፌ.4:28 1ኛ ጢሞ.6፡17-19።  ጥያቄ 19. ከምዕራፍ 8 መስጠትንና አሥራትን በተመለከተ የተማርከው ትምህርት ምንድነው?

2ኛ ቆሮ. 8:8-15 Read More »

2ኛ ቆሮ. 8፡1-7

በ2ኛ ቆሮንቶስ ምዕራፍ 8 እና 9 ሐዋርያው ስለመስጠት በሰፊው ያስተምራል። በኢየሩሳሌም የነበሩት ክርስቲያኖች ከአይሁዳውያን በደረሰባቸው ስደት ምክንያት ብዙ ችግር ነበረባቸው። የችግራቸው መንሥኤ ያላቸውን ማካፈላቸው አልበረም፤ (የሐዋ.4:32-37)። ግን ይህ ያላቸውን ማካፈላቸው በስደት ምክንያት የደረሰባቸውን ችግር ለመቋቋም የወሰዱት እርምጃ ነበር እንጂ!  ክርስትናን ላካፈሏቸው አይሁዳውያን የአሕዛብ ዕርዳታ በክርስቶስ ያላቸውን አንድነት የሚያረጋግጥ መሆኑን ሐዋርያው ጳውሎስ ተገንዝቦት ነበር። ስለዚህ ለዚህ አገልግሎት በጣም ይተጋ ነበር። ስለዚህ ነገር በሮማ 15:25-27 ያለውን ክፍል በመመልከት በበለጠ መረዳት ይቻላል።  ጥያቄ 8. በቁጥር 1 ላይ ለመቄዶንያ አብያተ ክርስቲያናት የተሰጠው ጸጋ የምን ጸጋ ነው?  ጥያቄ 9. «የጽህነታቸው ጥልቅነት የልገስናቸውን ባለጠግነት አብዝቶአል» ሲል ምን ማለቱ ነው? (ቁጥር 2)  ጥያቄ 19. የክርስቲያን ስጦታ መነሻው ምንድነው? (ቁጥር 6)  በቁጥር 1 ላይ ለመቄዶንያ ተሰጠ ያለው ጸጋ በልግስና የመስጠት ጸጋ ነበር። የክርስትና ሕይወት ምንጩ ምንጊዜም ቢሆን ጸጋ ነው።  «በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ የራሳችሁን መዳን ፈጽሙ፤ ስለ በጎ ፈቃዱ መፈለግንም ማድረግንም በእናንተ የሚሠሪ እግዚአብሔር ነውና» (ፊልጵ.2:12-13)። የመቄዶንያ አብያተ ክርስቲያናት የተባሉትም የፊልጵስዩስና የተሰሎንቄ አብያተ ክርስቲያናት ናቸው።  ከቁጥር 2–3:- እነዚህ አብያተ ክርስቲያናት ራሳቸው ምንም እንኳ ብዙ የሌላቸው ቢሆኑም ሠውተው ስለሰጡ ድህነታቸው የልግስናቸውን ትልቅነት አሳየ። ከዚህ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ታሪክ በማርቆስ 12:41-44 ተጽፏልና ያን ክፍል አውጥተህ አንብብ።  በቁጥር 4፡- ቅዱሳን የተባሉት በኢየሩሳሌም የነበሩት ምእመናን ነበሩ። በቁጥር 5 እንደተጻፈው እውነተኛ የክርስቲያን መስጠት መንሥኤው አስቀድሞ ራስን ለእግዚአብሔር መስጠት እንደሆነ ይናገራል። የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች እንዳበለጸጉ ሁሉ አሁንም በዚህ በመስጠት ጸጋ መበልጸግ እንዳለባቸው ይነገራቸዋል (ቁጥር 7)።  ጥያቄ 11. ራሳችንን አሳልፎ መስጠቱ አሥራት ከመስጠቱ የሚቀድመው ለምንድነው?  መስጠትን በተመለከተ የመቄዶንያ ክርስቲያኖች በጣም ጠቃሚ የሆነ ትምህርት ተምረዋል። አንደኛ፡- መስጠት መጀመር ያለበት ሁለንተናችንን “ለእግዚአብሔር በመስጠት” መሆን እንዳለበት ተማሩ፡፡ እግዚአብሔር ገንዘባችንን ብቻ ሳይሆን ሕይወታችንንም ጭምር እንዲቆጣጠርልን ለእርሱ አሳልፈን መስጠት ይገባናል። ሁለተኛ፡- እግዚአብሔር በሚሰጡት አሥራት ብቻ ደስተኛ እንደማይሆን ተገንዝበዋል፡፡ ያላቸው ሁሉ የእግዚአብሔር እንደሆነና ለእርሱ መሰጠት እንዳለበትም ተምረዋል።  ጥያቄ 12. ከገንዘብ ሌላ ለእግዚአብሔር ልንሰጣቸው የሚገቡንን ነገሮች ጥቀስ።  በመጨረሻም መስጠት ግዴታ ሳይሆን መታደል እንደሆነ ተረድተዋል። ምንም እንኳ በቦታው ባንገኝ፥ በመስጠታችን እግዚአብሔር በሌሎች ሥራ ውስጥ ተካፋዮች እንድንሆን ያደርገናል። ስለዚህ ጳውሎስ «ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ ነው» (የሐዋ.20፡35) የሚለውን ቃል ደግሞ መጻፋ ሊያስገርመን አይገባም።  ጥያቄ 13. እነዚህን መመሪያዎች በመጠቀም ሌሎች ለምን ለእግዚአብሔር መስጠት እንደሚገባቸው ልናሳውቅና ልናስተምራቸው የምንችለው እንዴት እንደሆነ አብራራ። 

2ኛ ቆሮ. 8፡1-7 Read More »

2ኛ ቆሮ. 7:5-16

ጥያቄ 5. በቁጥር 5 ላይ “በውስጥ ፍርሃት” ሲል ምን ዓይነት ፍርሃት ነበረ?  ጥያቄ 6. ከቁጥር 7-13 ባለው ክፍል ውስጥ የተጠቀሰውን በአጭሩ አብራራ።  በቁጥር 5 ላይ ያለው ሃሳብ 2:13 ላይ የተወውን ሃሳብ እንደገና ይጀምራል። በ2:13 ላይ «ቲቶን ወንድሜን ስላላገኘሁት መንፈሴ እረፍት አልነበረውም። ነገር ግን ከእነርሱ ተሰናብቼ ወደ መቄዶንያ ወጣሁ»። አሁን ደግሞ ያንን ሃሳብ እንደገና አንሥቶ በ7:5 ላይ «ወደ መቄዶንያ በመጣን ጊዜ» ይልና የቲቶን መምጣት ይተርካል። እንግዲህ ከ2፡14 ጀምር እስከ 7:4 ድረስ የነበረው በሃሳቡ የመጣለት ስለነበረ ዋና ታሪኩን አሁን ይቀጥላል። ይህ ዓይነት አጻጻፍ በጳውሎስ መልእክቶች ውስጥ በብዙ ቦታ ይገኛል። ይህንንም በማድረጉ በተለይ በዚህ በ2ኛ ቆሮ. 2:14 እስከ 7፡4 ጥልቅ የሆነ የክርስትና ትምህርት ሰጠን!  እንገዲህ የሃሳቡ አቅጣጫ ይህ ነው። ሐዋርያው ለወንጌል ሥራ ወደ ጢሮአዳ ይሄዳል፤ (2:12)። እዚያ ሳለ ስለቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ጥሩ ያልሆነ ሪፖርት (ወሪ) ይደርሰዋል፤ (1ኛ ቆሮ. 1፡11ና 5፡1-2)። ከዚያ ከባድ ተግሣጽ ያዘለውን 1ኛ ቆሮንቶስን ይጽፍላቸዋል፤ (7፡8-9)። ይህንን ደብዳቤ በቲቶ እጅ ወደ ቆሮንቶስ ልኮ መልሱን በምጥ መጠባበቅ ይጀምራል፡፡ «የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በመልእክቱ ተገሥጸው ንሰሐ ይገቡ ይሆን ወይስ እንደዓለማውያን ተቆጥተው ከክርስትና መንገድ ያፈገፍጉ ይሆን?» በማለት ሐዋርያው የነበረውን ምጥ በ7:5 እና በ2፡13 ይገልጣል። በጢሮአዳ ምንም በር ቢከፈትለት ልቡ ስላላረፈለት የቆሮንቶስን ቤተ ክርስቲያን ወሬ በቅርብ ሆኖ እንዲያዳምጥ ተነሥቶ ወደ መቄዶንያ ይሄዳል፤ (2:13)። መቄዶንያ በነበረበት ጊዜ ጳውሎስ በውጭ ችግር ነበረበት፤ በውስጥም የቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ሰዎች የመጃመሪያውን መልእክቱን አይቀበሉትም ብሎ ፈርቶ ነበር። በዚህ ቦታ ላይ ጳውሎስ ተስፋ ቀርጦ ነበር። በመቄዶንያ ሳለ ቲቶ መልካም ወሬ ይዞለት መጣ፤ (7፡6-7)። በዚያን ጊዜ ነው «ኃዘንተኛን የሚያጽናና አምላክ በቲቶ መምጣት አጽናናንን ብሎ በ7:6 ላይ የተናገረው!  የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በቲቶ በኩል የተላከላቸውን የሐዋርያውን ከባድ ተግሣጽ ያዘለ ደብዳቤ በተቀበሉ ጊዜ በታላቅ ኃዘን ንስሐ ይገባሉ። «ናፍቆታችሁንና ልቅሶአችሁን ስስእኔም ቅንዓታችሁን ሲነገረን …ደስ አለን፤› (ቁጥር 7)።  ከቁጥር 8-12 ባለው ክፍል ውስጥ በደብዳቤው ምክንያት ስላዘኑ ማዘኑንና ግን ደግሞ ይህ ኃዘን ሕይወትን የሚሰጥ የንስሐ ኃዘን በመሆኑ መደሰቱን ይገልጽላቸዋል። በቁጥር 12 ላይ ስለ እኛ ያላችሁ ትጋታችሁ ከእናንተ ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት እንዲገለጥ እንጂ ስለበዳዩ ወይ ስለተበዳዩ አልጻፍሁም» ሲል የአይሁዳውያን የአነጋገር ዘይቤ መሆኑን መገንዘብ አለብን። ሐዋርያው የጻፈው እርግጥ በደልን ስለፈጠረው ሰው መሆኑ አይካድም። ግን ከዚህም በላይ ዋናው ነጥብ የእነርሱ የልቦና መዘጋጀትና መታዘዝ መሆኑን ለማስረዳት ብሎ ነው ስለበዳዩ ወይም ስለተበዳዩ አልጽፍም ያለው። ተመሳሳይ ሃሳብ በሆሴዕ 6፡6 ላይ ተጽፎአል።  «ከመሥዋዕት ይልቅ ምሕረትን እወዳለሁና» ሲል መሥዋዕትን እጠላለሁ ወይም እንዲያቀርቡ ያዘዛቸውን መሥዋዕት አልፈልግም ማለቱ አልበረም። ይህ ዓይነት አነጋገር የሚበልጠውን ሃሳብ ለመምረጥ አነሥተኛውን ሃሳብ ይተዋል።  በዳዩ የአባቱን ሚስት የወሰደው ሲሆን ተበዳዩ ጸግዋ ሚስቱን የተቀማው አባትየው ነበር! (5:1-2)። በዳዩ ሰው ብቻ አልነበረም ስለኃጢአቱ የሚናዘዘው፤ የቆሮንቶስም ክርስቲያኖች ስለትዕቢታቸው፥ ስለመጋጨታቸውና ስለተሳሳተው የሥጦታ አጠቃቀማቸው ሁሉ ንስሐ ይገቡ ነበር። ጳውሎስ «እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ አዝናችኋልና» ይላቸዋል። ይህ ኃዘን ከልብ የሚመነጭ ሲሆን ያለንን አመለካከትና አረማመድ የሚያስቀይረን ነው። ዓለማዊ የሆነ ኃዘን ግን የአመለካከትም ሆነ የአረማመድ ለውጥ ስለማያመጣ መጨረሻው ሞት ነው።  ጥያቄ 7. “እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የሚመጣውን ኃዘን” ከዓለማዊ ኃዘን ጋር አነፃፅር። የእያንዳንዱ የመጨረሻ ውጤት ምንድነው? ልንለያያቸው የምንችለው እንዴት ነው?

2ኛ ቆሮ. 7:5-16 Read More »

2ኛ ቆሮ. 7:2-4

ጥያቄ 1. በቁጥር 2 ላይ “በልባችሁ ስፍራ አስፋልን” ሲል ይህን መሰል ንግግር ከዚህ በፊት የት ተጽፎ እናገኛለን?  ጥያቄ 2. በቁጥር 3 “ለኩነኔ አልልም” ማለቱ ምን ማለቱ ነው? በቁጥር 2 ላይ ከዚህ በፊት በ6፡12 የተናገረውን በመድገም “በልባችሁ ሥፍራ አስፉልን” ይላል። ልባቸውን ለሐዋርያው የማያሰፉበት ምንም ምክንያት የለም፤ ምክንያቱም በሐዋርያው በኩል ምንም በደል አልነበረምና! በተለያዩ ሦስት ቃላት ይህንን ይገልጻል፤ ማንንም አልበደልንም፤ ማንንም አላጠፋንም፤ ማንንም አላታለልንም።  ጥያቄ 3. አንድ የቤተ ክርስቲያን መሪ ምዕመናኑን እንዴት አድርጎ ሊያሳስት፥ ሊጎዳ ወይም ለራሱ ፍላጎት ሊጠቀምባቸው እንደሚችል መንገዶቹን በመጥቀስ አስረዳ።  በቁጥር 3 ላይ «ለኩነኔ አልልም» ማለት ለፍርድ ወይም ለወቀሳ አልልም ማለቱ ነው። ሐዋርያው እንዲህ አድርጎ የእርሱን ልብ መግለጡ እነርሱን ለመውቀስና ለማሳፈር እንዳልሆነ መናገሩ ነው። እንዲያውም ለእነርሱ ጥልቅ ፍቅር እንዳለው ይገልጽላቸዋል። «በአንድነት ለመሞትና በአንድነት ለመኖር በልባችን እንዳላችሁ አስቀድሜ ብዬአለሁና።» ብዙውን ጊዜ እኛ ወንጌላውያን የእግዚአብሔርን ሕዝብ ስናስተምር እንደዚህ በፍቅር ልብ ሳይሆን ቅር ባለውና በቀዘቀዘ ልብ ስለሚሆን ሕዝቡ እንደሚገባ አይባረኩም፤ እግዚአብሔርም በሙላት በረከቱን አይልክም። ስለዚህ በፍቅር ለማገልገል የሐዋርያውን አርአያ እንከተል። ሕዝቡን የምንገስጸው ከራሳችን ቅያሜ አንፃር ሳይሆን ከእግዚአብሔር ፍቅር አንፃር መሆን አለበት።  ጥያቄ 4. አንድ የቤተ ክርስቲያን መሪ አንድን ክርስቲያን በሚገስጽበት ፍቅር ማሳየቱ በጣም አስፈላጊ የሆነበት ምክንያት ምንድነው?  በቁጥር 4 ላይ በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን ላይ ያለውን ትምክሕት ይገልጻል። እኛም በምናገለግለው የአግዚአብሔር ሕዝብ ላይ እንዲህ ያለ ትምክሕት ሊያድርብን ይገባል። 

2ኛ ቆሮ. 7:2-4 Read More »

2ኛ ቆሮ. 6፡14-7:1

ጥያቄ 22. ከማያምኑ ጋር በማይመች አካሄድ አትጠመዱ ማለት ምን ማለት ነው?  ጥያቄ 23. በቁጥር 17 እና 18 ላይ «ከመካከላቸው ውጡና የተለያችሁ ሁኑ» ሲል ምን ማለቱ ነው?  ቁጥር 14:- ከማያምኑ ጋር በማይመች አካሄድ አትጠመዱ የሚለው ስለ ጋብቻ ብቻ ሳይሆን በጠቅላላ ከማያምኑ ጋር ያለንን ግንኙነት ይመለከታል። ለምሳሌ ከዚህ በፊት ሐዋርያው ለቆሮንቶስ ምእመናን ከማያምኑ ጋር በሚከተሉት መንገዶች እንዳይጠመዱ ይከለክላል። ጋብቻ 1ኛ ቆሮ.  7፡12-15፤ ለጣዖት የተሠዋ ሥጋ አለመብላት 1ኛ ቆሮ. 10፡27፤ በማያምኑ አጠገብ በልሳን አለመናር (ስላማይገባቸው ይሰናከላሉና በማያምኑ ፊት በልሳን መናርን ከለከለ።) 1ኛ ቆሮ. 14፡24፤ በማያምኑ ዳኞኛ ፊት ምእመናንን አለመክሰስ 1ኛ ቆሮ. 6፡5።  «አለ መጠመድ» ማለት በክርስቲያንና ክርስቲያን ባልሆነ መካከል ያለውን ልዩነት በሚያጠፉ መንገድ ከማያምን ጋር በአንድ ቀንበር ሥር መገኘት ማለት ነው፡፡ የሚያምንንና የማያንን ሲያነጻጽር ብርሃንና ጨለማ፥ ክርስቶስና ሰይጣን፥ የሚያምንና የማያምን፥ ቤተ መቅደስና ጣዖት ይላል። እንግዲህ እግዚአብሔር እንዲህ የለያያቸውን ሰው ማጋጠም የለበትም።  ሐዋርያው «በማይመች አካሄድ ከማያምኑ ጋር አትጠመዱ» አለ እንጂ በጠቅላላው ከማያምኑ ተለዩ አላለም፤ (1ኛ ቆሮ. 5፡9-10)፡፡ እነዚህም የማይመቹ መንገዶች ከላይ የተዘረዘሩት ዓይነቶች ናቸው። ኢየሱስ «እናንተ በዓለም ውስጥ ናችሁ እንጂ የዓለም አይደላችሁም» ይላል። እኛ የዓለም ብርሃንና ጨው መሆን አለብን። ይህም ማለት የማያምኑ ሰዎችን ማነጋር እነርሱን መርዳትና ለእነርሱ መመስከር ይገባናል። ይህን ስናደርግ እነርሱ የእኛን ሕይወት እንዳይቀይሩ መጠንቀቅ ይኖርብናል። የእነርሱ አስተሳሰብ፥ አኗኗርና ስሜት ከእኛ የተለየ ነው የሚሆነው። ክርስቲያን ከእነርሱ ጋር በሚገናኝበት ጊዜ ራሱን ንጹሕ አድርጎ መጠበቁን መዘንጋት የለበትም።  ጥያቄ 24. አንድ ክርስቲያን ከዓለማውያን ጋር በአኳኋን ወይም በአስተሳሰብ ወይም ደግሞ በስሜት እንዴት አድርጎ ሊቆራኝ ይችላል?  በቁጥር 17 እና 18 ላይ ከማያምኑ ተለዩ ያለው ክክፉ ሥራቸው ተባባሪዎች አትሁኑ ማለቱ ነው፤ (መዝ.1:1 ተመልከት )። እግዚአብሔር አባት ሆና እንደልጆቹ ስለሚቀበለን እርሱን ከማይወዱት ጋር በመተባበር ልናሳዝው አይገባም። በ7፡1 ላይ ሐዋርያው ሀሳቡን በማጠቃለል የዚህ ተስፋ ቃል ካለን ቅድስናን ፍጹም እናድርግ ይላል፡፡ የተስፋ ቃል የሚለው እግዚአብሔር እንደ ልጆች አድርጎ እቀበላችኋለሁ ያለውን ነው።  ጥያቄ 25. ሀ/ ሰውነትን ያረክሳሉ ብለህ የምትገምታቸውን ነገሮች ዘርዝረህ ጻፍ። ለ/ መንፈስንም ሊያረክሱ የሚችሉ ነገሮችን ዘርዝረህ ጻፍ። ሐ / «ቅድስናን ልንጎናጸፍ» የምንችለው እንዴት ነው? ምሳሌዎችን ስጥ።

2ኛ ቆሮ. 6፡14-7:1 Read More »

2ኛ ቆሮ. 6፡1-13

ጥያቄ 13. በቁጥር 1 ላይ «አብረን እየሠራን» ሲል አብረን ያለው ማንን ሲጨምር ነው?  ጥያቄ 14. በቁጥር 1 ላይ እንደተጻፈው የእግዚአብሔርን ጸጋ በከንቱ መቀበል ማለት ምን ማለት ነው?  ጥያቄ 15. ቁጥር 3ን አብራራ።  ጥያቄ 16. በቁጥር 4 ማማጠን ምን ማለት ነው?  ጥያቄ 17. ቁጥር 12ን አብራራ።  በቁጥር 1 ላይ አብረን እየሠራን ያለው ሐዋርያው ከእግዚአብሔር ጋር ይሠራል ማለት ነው። ለዚህ ተመሳሳይ ሀሳብ በ1ኛ ቆሮ. 3፡9 ላይ ተመልከት። ይህም ሐዋርያው ከእግዚአብሔር ጋር አብሮ የሚሠራው የማስታረቅን ሥራ ነው። ከላይ በ5፡19 ላይ እግዚአብሔር ዓለሙን ከራሱ ጋር ለማስታረቅ ይማልዳል ተብሎ እንደተጻፈ ሁሉ ሐዋርያውም የቆሮንቶስን ክርስቲያናት ከእግዚአብሔር ጸጋ ፈቀቅ እንዳይሉ ይለምናል። በሐሰተኛ አስተማሪዎች በመታለል ከእምነታቸው ፈቀቅ ብለው የተቀበሉትን የእግዚአብሔርን ጸጋ ከንቱ እንዳያዳርጉ ይለምናቸዋል። ይህ ብቻ ሳይሆን ከጳውሎስ ጋር ተባብረው የጠፉትን ኃጢአተኞች ከእግዚአብሔር ጋር ማስታረቅ ነበረባቸው። የመዳንን ሥጦታና የማስታረቅን አገልገሎት ስጦታ በተሳሳተ አመለካከት ወይም በራስ ወዳድነት ማሰናከል አይገባንም።  ቁጥር 2፡- ይህን ጥቅስ ከኢሳይያስ 49፡8 ላይ በመጥቀስ በክርስቶስ በኩል አሁን የመዳን ዘመን መሆኑን ያስታውሳቸዋል። ለዚህ ነው እግዚአብሔርም በኃጢአተኞች ላይ እንደመፍረድ ፈንታ እንዲድኑ የሚለምነው። ግን ይህ የመለመኛ ሰዓት የሚያልፍበት ወቅት ስለሚመጣ ሰው አሁን ንስሐ ቢገባ ይሻለዋል። የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ከሐሰተኛ አስተማሪዎች ርቀው ወንጌልን በመጀመሪያ ወደ ሰበከላቸው ወደ ጳውሎስ እንዲመለሱ ያመለክታቸዋል።  በቁጥር 3 ላይ ሐዋርያው ሕይወቱ ለማንም ሰው መሰናክል እንዳልሆነ ይናገራል። ሕይወታችንን ካልጠበቅን የእግዚአብሔርን መንግሥት ወደፊት እንደማራመድ ወደኋላ እንዲጎተት እናደርጋለንና፤ ሕይወታችንን ጌታ ይጠብቅልን! በውድቀታችንም በእግዚአብሔር ጸጋ የምንታደስ መሆናችንን መዘንጋት የለብንም!  ጥያቄ 18. አንዳንድ ክርስቲያኖች የሚያደርጉት ወንጌልን የሚከላከልና ለሌሎች የመሰናከያ ድንጋይ ሊሆን የሚችል ነገር ምንድነው?  በቁጥር 4 ላይ ማማጠን ማለት ከዚህ በላይ በ3፡1 የማመስገኛ ደብዳቤ ካለውና በ4:2 ሕይወቱን ለሰዎች ሕሊና ማመስገን ከሚለው ሃሳብ ጋር ይዛመዳል። በዚህ ቦታ ትርጉሙ ሕይወቱን በጥንቃቄ በመምራቱ ማንንም አላሰናከለም ግን እንደ እግዚአብሔር አገልጋይ በጥንቃቄ የኖረ መሆኑን ያስረዳል።  ከቁጥር 5-10: ባለው ክፍል ውስጥ ሐዋርያው ለወንጌል ሲል ምን ያህል መከራና ችግር ይቀበል እንደነበር ያስረዳል። ግን በችግሩ ሁሉ ጌታ ከእርሱ ጋር ስለነበር አልተረታም!  መሪነትን በተመለከተ ሁለት እውነታዎች አሉ፡-  አንደኛ፡- መሪዎች ከሌሎች የበለጠ ችግር የሚደርስባቸው መሆኑን እናያለን። ለጳውሎስ ይህ ችግር ስደት፥ እንቅልፍ ማጣት፥ ከባድ ሥራ፥ ወዘተ ነበር። ነገር ግን ጳውሎስ የጠፋ ኃጢአተኞች ከእግዚአብሔር ጋር እንዲታረቁ ካለው ጉጉት የተነሣ ይህንን ጉዳት ለመቀበል ፈቃደኛ ነበር። አንዳንድ መሪዎች ከክርስቲያኖችና ካልዳኑት ሰዎች ጋር አለመግባባት ያጋጥማቸዋል፤ ነገር ግን የፈለገው ዓይነት መሰናክል ቢያጋጥማቸውም አገልገሎታቸውን መቀጠል አለባቸው።  ጥያቄ 19. ሀ/ ለወንጌል ሲሉ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ መሪዎች የሚያጋጥሟቸው ችግሮች ምንድናቸው? ለ/ ይህ ክፍል መሪዎች በራሳቸው ፍላጎት ሳይሆን በእግዚአብሔር ጥሪ ላይ ተመሥርተው አገልገሎታቸውን መጀመር እንደሚገባቸው የሚያሳየን እንዴት ነው? ሐ/ ይህ ክፍል አንድ መሪ የጠፋውን ሰው ወደ ኢየሱስ ለማምጣት ሊኖረው የሚገባውን ፍላጎት የሚያሳየን በእንዴት ዓይነት ሁኔታ ነው?  ሁለተኛ፡- ጳውሎስ አነጋገሩና አረማምዱ አንድ ዓይነት መሆኑን ያይ ነበር። ወንጌልን ይሰብክ የነበረው በእንደዚህ ዓይነት ችግር ብቻ አልበረም፤ ከበስተኋላ ያለው አስተሳሰቡ ንጹሕ መሆኑን በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ተደግፎ ማገልገሉንና የመንፈስ ቅዱስ ፍሬዎች በሕይወቱ መታየታቸውንም ጭምር ነበር የሚመለከተው።  ጥያቄ 20. አንድ መሪ ሲመራ የመንፈስ ቅዱስ ፍሬዎች በሕይወቱ ውስጥ መታየታቸው ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ምሳሌ በመስጠት አስረዳ።  ቁጥር 11-13፡- «አፋችን ለእናንተ ተከፍቷል» ማለት ሐዋርያው ምንም ሳያስቀር በንግግሩ ሃሳቡን የገለጻ መሆኑን ያስረዳል፡፡ «ልባችን ሰፍቶላችኋል» ማለት በሙሉ ልቡ ይወዳቸዋል ማለት ነው። «በእኛ አልጠበባችሁም በሆዳችሁ ግን ጠቦባችኋል» ማለት የሐዋርያው ልብ ሰፋ ብሉ በፍቅር ሲቀበላቸው የቆሮንቶስ ምእመናን ግን ለሐዋርያው ልባቸውን አጠበቡ! ይህ መሆን የለበትም! እርሱ እንደ ልጆቹ እያፈቀራቸው ሳለ ልባቸውን ለአባታቸው ከማጥበብ ይልቅ እርሱ እንዳፈቀራቸው ሊያፈቅሩት ይገባል።  ጥያቄ 21. በዚህ ምዕራፍ ውስጥ ስለመሪነት የተሰጡትን መመሪያዎች በዝርዝር ጻፍ። 

2ኛ ቆሮ. 6፡1-13 Read More »

2ኛ ቆሮ. 5:16-21

ጥያቄ 7. ክርስቶስን በሥጋ ማወቅ ማለት ምን ማለት ነው?  ጥያቄ 8. በቁጥር 17 ላይ «ሁሉም አዲስ ሆኖአል» ማለት ምን ማለት ነው?  ጥያቄ 9. በቁጥር 19 ላይ «እግዚአብሔር በክርስቶስ ሆኖ ዓለሙን ከራሱ ጋር ያስታርቅ ነበርና» ሲል ምን ማለቱ ነው?  ቁጥር 16፡- «ማንንም በሥጋ እንደሚሆን አናውቅም» ሲል ሥጋ ማለቱ በተፈጥሮ ሰው አስተሳሰብ መንገድ ማለቱ ነው። ለምሳሌ በዘር ወይም በእውቀት በሀብት መመካት የሥጋ ፀባይ ነው፡፡ ሰው በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነትን የሚያገኘው በእነዚህና በመሳሰሉት ነገሮች አይደለም። በክርስቶስ ያመነ ሁሉ ዳግመኛ ስለተወለደ የእግዚአብሔር ልጅ ነው። ሰውን የምንገምተው «ክርስቶስን ያውቃል ወይስ አያውቅም?» በማለት ብቻ ነው።  ጥያቄ 10. በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ ያሉ ክርስቲያኖች ሌሎች ሰዎችን የሚያዩት በዓለማዊ አመለካከት ነው (ማለትም ዓለማውያን በሚመዝኑበት መመዘኛ ነው የሚመዝኑት) ወይስ መንፈሳዊ በሆነ አመለካከት?  «ክርስቶስንም በሥጋ እንደሆነ ያወቅነው ብንሆን እንኳ አሁን ግን ከእንግዲህ ወዲህ እንደዚህ አናውቀውም።» ክርስቶስን በሥጋ ማወቅ ማለት ጌታን በአዳኝነቱና በእግዚአብሔር ልጅነቱ ሳይሆን እንደተራ ሰው ማወቅ ነው። ለምሳሌ በምድር በነበረበት ጊዜ ብዙዎች «ይህ የጠራቢው የዮሴፍ ልጅ አይደለምን?» እያሉ በሥጋ ብቻ ነበር ያወቁት። ከእነዚያ ውስጥ ሐዋርያው አንዱ ነበር፡፡ አሁን ግን በመንፈስ ቅዱስ ገላጭነት ጌታን በሚገባ አውቆታል።  ቁጥር 17:- በክርስቶስ አዲስ ፍጥረት ተጀምሮአል። በመጀመሪያ ጌታን የተቀበሉ ሁሉ አዲስ ልደትን ተቀብለው የእግዚአብሔር ልጆች በመሆን ታድሰዋል። ሁለተኛው ክርስቶስ ከመቃብር በመነሣቱ አዲስ ዓለም ተጀምሮአል። ይህንን በክርስቶስ ትንሣኤ የተገለጠውን አዲስ ዓለም እኛም በትንሣኤ ጊዜ እንቀበለዋለን፤ ግን አሁን የትንሣኤው ፍሬ የሆነውን መንፈስ ቅዱስንና ዳግመኛ መወለድን ተቀብለናል። የአዲሱን ዓለም ፍሪ አሁኑኑ በቅምሻ ስለተቀበልነው አዲሱ ዓለም አንደተጀመረ ይቆጠራል። “ሁሉም አዲስ ሆኖአል፡፡”  ጥያቄ 11፣ አንድን ሰው እግዚአብሔር አዲስ ፍጥረት አድርጎ ካዳነው በኋላ የሚከሰቱትን ለውጦች በዝርዝር ጻፍ።  ከቁጥር 18-21:- በዚህ ክፍል ውስጥ ሦስት ሃሳቦችን እዘረዝራለን፡፡  1ኛ/ የማስታረቅ አገልገሎት ተሰጠን! እኛ ከክርስቶስ ጋር ስለታረቅን በወንጌል ስብከት በኩል ሌሎችም ከክርስቶስ ጋር እንዲታረቁ ክርስቶስ የማስታረቅ አገልግሉት ሰጠን።  2ኛ/ ይህ የማስታረቅ አገልግሎት የእኛ ልመና ሳይሆን «ታረቁኝ» የሚል የእግዚአብሔር ልመና ነው። «እግዚአብሔር በክርስቶስ ሆኖ ዓለሙን ከራሱ ጋር ያስታርቅ ነበርና» ። እግዚአብሔር ራሱ ተበድሎ እኛን ጥፋተኞችን “ኑ ታረቁኝ” በማለት  አስታራቂ የሆነውን አማላጅ ክርስቶስን ላከ።  3ኛ/ ይህ ኃጢአተኞችን ከእግዚአብሔር ጋር የማስታረቅ ነገር በቀላሉ አልተገኘም። እግዚአብሔር ኃጢአተኞችን ይቅር የሚለው ክርስቶስ የኃጢአተኞችን በደል በራሱ ላይ ስለወሰደ ነው።  (ቁጥር 21) ክርስቶስ በእኛ ምትክ ኃጢአት ሆነ! እኛም በእርሱ የእግዚአብሔር  ጽድቅ ሆንን!  ክርስቲያኖች ዛሬ እንደ እግዚአብሔር አምባሳደሮች ወይም አስታራቂ መልእክተኞች ናቸው። እግዚአብሔርን ወክለው ነው የሚናገሩት። ይህ ታላቅ አገልግሎት ኢየሱስን የሕይወት ዋጋ አስከፍሎታል፤ አስታራቂ መልእክቱንም የሚያቀርቡትን ሰዎች ከዚህ የበለበጠ ያስከፍላቸዋል። ይህ የእርቅ መልእክት የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ነው። ይህን ወንጌል «ክርስቶስ ለኃጢአታችን ሞቶ የእርሱን ጽድቅ ሰጥቶናል» በማለት ልናጠቃልለው እንችላለን።  ጥያቄ 12. ሀ/ እንደ እግዚአብሔር አምባሳደር የምትሠራው እንዴት ነው? ለ/ እግዚአብሔር በአንተ በኩል እንዴት አድርጎ ሰዎችን ወደ እርቁ እንዳመጣ ምሳሌ በመስጠት አስረዳ። 

2ኛ ቆሮ. 5:16-21 Read More »