ወደ ፊልሞና

ፊልሞና 1-25

መግቢያና ሰላምታ (ፊልሞና 1-7) ከቀድሞይቱ ቤተ ክርስቲያን አስገራሚ ባሕርያት አንዱ በአማኞች መካከል የነበረው ፍቅርና መተሳሰብ ነበር። በተራራቁ ስፍራዎች የነበሩት ብዙም የማይታወቁ አማኞች ሳይቀር ከልባቸው ይዋደዱ ነበር። ጳውሎስ የሚኖረው ሮም ውስጥ ሲሆን ፊልሞና ደግሞ በቆላስይስ ውስጥ ይኖር ነበር። ይህም በመካከላቸው ከ1200 ኪሎ ሜትሮች በላይ ርቀት መኖሩን ያመለክታል። ጳውሎስ ቀደም ብሎም ከፊልሞና ጋር አብሮ ያሳለፈ አይመስልም። ይሁንና ለፊልሞና የጻፈው መልእክት ጥልቅ የወዳጅነት መንፈስ የሚታይበት ነበር። በተጨማሪም ጳውሎስ በቀላሉ የሰውን ስሜት ሊነኩ ስለሚችሉ አንዳንድ ጉዳዮች የፊልሞናን እርዳታ ለመጠየቅ ሲደፍር እንመለከታለን። ጳውሎስ አማኞች ሁሉ የእግዚአብሔር ቤተሰብ አካላት ናቸው የሚለውን እውነት ተግባራዊ እያደረገ ነበር። በመሆኑም፥ ጣልቃ እንደገባን ወይም ሌላውን ሰው ለራሳችን ዓላማ እንደተጠቀምንበት ሳናስብ ከክርስቲያን ወገኖች እርዳታ ልንጠይቅና አንዳችን ለሌላችን ልንጸልይ እንደምንችል ከዚህ መልእክት ውስጥ መረዳት ይቻላል። ጳውሎስ ይህንን አጭር መልእክት የጻፈው ለፊልሞና፥ ለአፍብያ (ምናልባትም የፊልሞና ባለቤት) እና አርክጳ ነበር። አንዳንድ ሰዎች አርክጳ የፊልሞና ልጅና በፊልሞና ቤት ውስጥ የምትሰባሰብ ቤተ ክርስቲያን መሪ እንደነበረ ያስባሉ። ጳውሎስ እስረኛ የነበረ ቢሆንም፥ ከእስረኛነቱ ችግሮች ባሻገር ስለ ሌሎች ያስብ ነበር። ጸሎቶቹ ያተኮሩት በግል ራሱ ስለሚባረክበት መንገድ አልነበረም። ይልቁንም ጳውሎስ ለሌሎቹ ሲማልድ እንመለከታለን። ጳውሎስ ስለ ፊልሞናና ስለ ቤተሰቡ ለእግዚአብሔር እንደሚጸልይ ይናገራል። ጳውሎስ ፊልሞና በክርስቶስ ላይ ጠንካራ እምነት እንደነበረውና ቅዱሳንን ሁሉ እንደሚወድ በመስማቱ፥ ጸሎቱ በምስጋና የተሞላ ነበር። ፊልሞና የራሱን ቤተሰብ፥ የራሱን ጎሳ ወይም የራሱን ቤተ ክርስቲያን ብቻ የሚወድ ሰው አልነበረም። ፊልሞና አማኞችን ሁሉ በመውደዱ የታወቀ ሰው ነበር። ጳውሎስ የፊልሞና ፍቅር እንደ ንጹሕ የምንጭ ውኃ እንደነበር ይናገራል። ይህም ፊልሞና የሚያጋጥመውን ሰው ሁሉ በመንፈሳዊ ሕይወቱ የሚያነቃቃ መልካም አገልጋይ እንደነበረ ያመለክታል። የውይይት ጥያቄ፡- ከፍቅራቸው ትኩስነት የተነሣ ሌሎችን አማኞች የሚያነቃቁትን ክርስቲያኖች አይተህ ታውቃለህ? እንዲህ ዓይነቱ ሰው በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚፈለገው ለምንድን ነው? አንድ ሰው ለሌሎች የዚህ ዓይነት ፍቅር እንዲኖረው ምን ማድረግ ይኖርበታል? ጳውሎስ ከምስጋናው በተጨማሪ ፊልሞና በክርስቶስ ላይ ያለውን እምነት ለሌሎች በድፍረት ማካፈል እንዲችል ይጸልይለታል። ጳውሎስ «እኛ ዘንድ ያለውን በጎ ነገር ሁሉ በማወቅ» የሚለውን አሳብ ከምስክርነት ጋር ማያያዙ አስገራሚ ነው። እምነታችንን ለሌሎች በምናካፍልበት ጊዜ መንፈስ ቅዱስ ለእግዚአብሔር ያለን እውቀት እንዲያድግ ይረዳናል። እንዲሁም የእግዚአብሔር ልጆች እንደ መሆናችን ልዩ ዕድሎች እንዳሉን እንድንረዳ ያስችለናል። ጳውሎስ ፊልሞና አናሲሞስን ይቅር እንዲለውና እንዲቀበለው ይጠይቀዋል (ፊልሞና 8-22) ጳውሎስ እዚህ ላይ የመልእክቱን ዓላማ ያብራራል። ጳውሎስ ፊልሞና አናሲሞስ ወደ እርሱ በሚመለስበት ጊዜ በፍቅር እንዲቀበለው ይለምነዋል። የስሙ ትርጉም «ጠቃሚ» የሆነው እናሲሞስ ቀደም ሲል ከፊልሞና በመኮብለሉ ሳይጠቅመው ቀርቶ ነበር። አሁን ግን አናሲሞስ የተለወጠና እንደ ፊልሞና በክርስቶስ የሚያምን ሰው ሆኖ ስለሚመለስ ለፊልሞናም ሆነ ለጳውሎስ «ጠቃሚ» ነበር። ጳውሎስ አናሲሞስን «ልጄ» ይለዋል። ይህም ምናልባትም ጳውሎስ አናሲሞስን ወደ ጌታ እንዳመጣውና አብረው በቆዩባቸው ጊዜያት በጣም ተዋድደው እንደ ነበር ያሳያል። አናሲሞስ በክርስቶስ ካመነ በኋላ እስረኛ የነበረውን ጳውሎስን ሲያገለግለው ቆይቷል። በመሆኑም እዚያ ቆይቶ ቢረዳው ይወድ እንደ ነበር አስረድቷል። ነገር ግን ያለባለቤቱ ፈቃድ አንድን ነገር መውሰዱ ትክክል አለመሆኑን ያውቃል። ስለሆነም ጳውሎስ አናሲሞስን ወደ ፊልሞና መለሰው። ፊልሞና አናሲሞስን መልሶ ለጳውሎስ ለመስጠት ቢፈልግ ውሳኔው የራሱ ነበር። ፊልሞናም ወደ ክርስቶስ የመጣው በጳውሎስ ምስክርነት በመሆኑ የጳውሎስ ውለታ ነበረበት። ጳውሎስ ከአናሲሞስ አሳዛኝ ሕይወት፥ ጳውሎስን በማግኘቱና በክርስቶስ በማመኑ ውስጥ የእግዚአብሔር ታላቅ እጅ እንደ ነበረበት ተገንዝቧል። የአናሲሞስን መኮብለል ጨምሮ እግዚአብሔር ሁኔታዎችን በሙሉ ይቆጣጠር ነበር። አሁን አናሲሞስ ለመታዘዝ የማይፈልግ ባሪያ ሆኖ አልነበረም ወደ ፊልሞና የተመለሰው። ነገር ግን በጌታ የተወደደ ወንድም ሆኖ ነበር የተመለሰው። አናሲሞስ ለጳውሎስም ሆነ ለፊልሞና የተወደደው ወንድም ነበር። ምክንያቱም አሁን ሁሉም የእግዚአብሔር ቤተሰቦች ናቸውና። ጳውሎስ ፊልሞናን የክርስቶስ አካል እናሲሞስ እንዲቀጣ ከሚፈቅደው የአገሪቱ ሕግ በላይ አስፈላጊ መሆኑን ያስገነዝበዋል። አሁን በክርስቶስ ወንድሞች በመሆናቸው፥ ፊልሞና አናሲሞስን በጌታ ወንድሙ አድርጎ እንዲቀበለውና ይቅርታን እንዲያደርግላት ይጠይቀዋል። የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ሀብታሙ ፊልሞናና ባሪያው እናሲሞስ አሁን የእግዚአብሔር ቤተሰብ አካላት ሆነዋል። አናሲሞስ ወደ ቤቱ ከተመለሰ በኋላ ፊልሞና እንዴት ሊያስተናግደው ይገባል ትላለህ? ለ) ይህ ባህላዊውን የጌታና ባሪያ ግንኙነት እንዴት የሚያናጋው ይመስልሃል? ሐ) በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ የሚገኙትን አንዳንድ ማኅበረሰቡ ያገለላቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች ዘርዝር። የአንድ መንፈሳዊ ቤተሰብ አካል መሆናቸው ቀደም ሲል ይንቋቸው ከነበሩት ሰዎች ጋር የሚኖራቸውን ግንኙነት እንዴት እንደሚለውጥ ግለጽ። መ) እነዚህ የተገለሉ ሰዎች በክርስቶስ ወንድሞችና እኅቶች መሆናቸውን ለማሳየት ፍቅርህን እንዴት ትገልጽላቸዋለህ? ለእነዚህ ሰዎች ፍቅርህንና አቀባበልህን ለማሳየት በዚህ ሳምንት ምን ልታደርግ እንደምትችል ግለጽ። አናሲሞስ ምናልባትም ከፊልሞና ንብረት ዘርፎ ይሆናል የሄደው። ይህ በፊልሞና ልብ ውስጥ መራርነት እንዳይፈጥር ሲል ጳውሎስ በአናሲሞስ ላይ ያለውን ዕዳ ራሱ ለመክፈል ዝግጁ መሆኑን ገለጸ። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ፥ እርቅ ይቅርታ መጠየቅን ብቻ ሳይሆን ከተቻለ የተሰረቀውን ንብረት መመለስን ወይም በሌላው ሰው ላይ የፈጸምነውን ጥፋት ማስተካከል ይጨምራል። ጳውሎስ በአናሲሞስ ምትክ ይህንን ለማድረግ ፈቃደኛ ነበር። የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ጳውሎስ አናሲሞስ የሰረቀውን ንብረት ዋጋ ለመከፈል የፈለገው ለምን ይመስልሃል? ለ) ይህ ይቅርታ በምንጠይቅበት ጊዜ በተግባራችን ወይም ያጠፋነውን በማስተካከል ልንፈጽመው ስለሚገባው ተግባር ምን ያስተምረናል? ሐ) ብዙ ክርስቲያኖች ከሰረቁት ገንዘብ ይቅርታ ከጠየቁ ገንዘቡን የመመለስ ግዴታ እንደሌለባቸው የሚያስቡት ለምንድን ነው? ይህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ይመስልሃል? ለምን? ጳውሎስ በቅርቡ ከእስር ቤት እንደሚወጣ ያስባል። በዚህም ጊዜ በቆላስይስና ሎዶቅያ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ እያገለገለ የተወሰነ ጊዜ ለመቆየት ዐቅዷል። ስለሆነም ጳውሎስ ፊልሞና በቤቱ ውስጥ እንዲቆይ ይፈቅድለት ዘንድ ይጠይቀዋል። ጳውሎስ ለብቻው የእንግዳ ክፍል ተዘጋጅቶለት ለመቆየት ይፈልጋል። የመዝጊያ አሳቦች (ፊልሞና 23-25) የውይይት ጥያቄ፡- ቆላ. 4፡12-14 እንብብ። የቆላስይስና የፊልሞና መልእክቶች አጨራረስ ተመሳሳይ የሚሆነው እንዴት ነው? በሁለቱም መልእክቶች ውስጥ የተጠቀሱትን ስሞች ዘርዝር። ጳውሎስ የኤጳፍራን ሰላምታ በማቅረብ ይህንን ደብዳቤ ይደመድማል። ኤጳፍራ የቆላስይስ ክርስቲያኖች በሚገባ የሚያውቁትና በዚህ ጊዜ ከጳውሎስ ጋር ታስሮ የሚገኝ የቤተ ክርስቲያን መሪ ነበር። ጳውሎስ በተጨማሪም የማርቆስን፥ የአርስጥሮኮስን፥ የዴማስና የሉቃስንም ሰላምታ አስተላልፎአል። እነዚህ ሁሉ ስሞች በቆላስይስም መልእክት ውስጥ ይገኛሉ። ይህም ሁለቱም መልእክቶች በተመሳሳይ ጊዜ መጻፋቸውን ያመለክታል። የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ማኅበረሰቡ ላገለላቸው ሰዎች ስለሚኖረን አመለካከት ከፊልሞና መልእክት ምን እንማራለን? ለ) ማኅበረሰቡ ካገለላቸው ሰዎች፥ በተለይም ከክርስቲያኖች ጋር ስለሚኖረን ግንኙነት እግዚአብሔር ከእኛ ምን ይጠብቃል? (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ፊልሞና 1-25 Read More »

የፊልሞና ዓላማ፣ ልዩ ባሕሪያት እና አስተዋጽኦ

የፊልሞና ዓላማ የመጀመሪያ ዓላማ፡- ፊልሞና የኮበለለ ባሪያውን አናሲሞስን እንዲቀበል ለማግባባት። በሆነ ምክንያት ባሪያው አናሲሞስ ከፊልሞና ኮብልሎ ነበር። ምናልባትም የሆነ ነገር ሰርቆ ሊሆን ይችላል የኮበለለው። አናሲሞስ ነጻነቱን ፍለጋ ብዙ ርቀት ተጉዞ ወደ ሮም ሄደ። ሮም ከአንድ ሚሊዮን የሚበዛ ሕዝብ የነበረባት በመሆኗ በቀላሉ ሊደበቅባት ይችል ነበር። በጥንት ዘመን፥ ከጌቶቻቸው የኮበለሉ ባሮች በጭካኔ ይቀጡ ነበር። ድንገት ቢያዙ በጋለ ብረት የማን ንብረት መሆናቸውን የሚያመለክት ምልክት ሰውነታቸው ላይ ይደረግ ነበር። በተጨማሪም በእሳት ይቃጠሉ፥ አንገታቸው ይቀላ ወይም ይገደሉ ነበር። ይህ ጭካኔ የተሞላበት ቅጣት የሚፈጸመው ሌሎች ባሪያዎች እንዳይኮበልሉ ለማስጠንቀቅ ነበር። እግዚአብሔር አናሲሞስን ወደ ጳውሎስ በመምራቱ ወንጌልን ሊሰማ ችሏል። አናሲሞስ በወንጌል አምኖ ከዳነ በኋላ ለአጭር ጊዜ እስረኛውን ጳውሎስን ሲረዳው ቆየ (የሐዋ. 28፡17–31 አንብብ።) አናሲሞስ የተመለሰው በጳውሎስ ገፋፊነት ወይም ራሱ አናሲሞስ ወደ ጌታውና አሁን ደግሞ በክርስቶስ ወንድሙ ወደ ሆነው ፊልሞና ተመልሶ ራሱን ማስገዛት እንዳለበት በመገንዘቡ ይሆን የምናውቀው ነገር የለም። በሮም ሕግ መሠረት፥ ጳውሎስ አናሲሞስን ወደ ጌታው የመመለስ ግዴታ ነበረበት። ጳውሎስ ፊልሞና በዘመኑ ልምድ አናሲሞስን በሞት እንዳያስቀጣውና ዳሩ ግን እንደ ክርስቲያን ወንድም እንዲቆጥረው በመጠየቅ ይህን ደብዳቤ ላከለት። አንዳንድ ምሁራን ጳውሎስ ፊልሞና ለወንጌል መልእክተኝነት አገልግሎቱ ይረዳው ዘንድ አናሲሞስን መልሶ እንዲልክለት እየጠየቀው ነበር ይላሉ (ፊልሞና 14)። ሌሎች ደግሞ ጳውሎስ በፊልሞና 21 ላይ «ከምልህ ይልቅ አብልጠህ እንድታደርግ አውቄ» ሲል፥ ፊልሞና አናሲሞስን ነፃ እንዲያወጣው መጠየቁ ነው ይላሉ። በዚህ ጊዜ ሁለቱም በክርስቶስ አንድ ናቸውና። ይህ እጭር መልእክት በአዲስ ኪዳን ውስጥ መካተቱ፥ ምናልባትም ፊልሞና እግዚአብሔር ሰዎችን ሁሉ በእኩል ደረጃ እንደሚወድና በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ባሪያዎችና ነፃ ሰዎችም እኩል መሆናቸውን እንደተገነዘበ ያመለክታል። ምናልባትም አናሲሞስ ነፃ ወጥቶ ሊሆን ይችላል። ሁለተኛ ዓላማ፡- ጳውሎስ በቅርቡ ተፈትቶ ወደ ቆላስይስ ለመምጣት እንደሚፈልግ ለፊልሞና ለመግለጽ ነው። ጳውሎስ በፊልሞና ቤት ውስጥ ማረፍ ይችል እንደሆነም ጠይቋል። ጳውሎስ በአካባቢው የአገልግሎት ጣቢያ አድርጎ ሊጠቀምበት የሚችለውን ልዩ የእንግዳ ክፍል እንዲያዘጋጅለት ይፈልጋል። ሦስተኛ ዓላማ፡- ሌሎች ክርስቲያን ባሪያ አሳዳሪዎች ባሪያዎቻቸውን፥ በተለይም ክርስቲያን ባሪያዎቻቸውን እንዴት ማስተናገድ እንዳለባቸው ለመምከር፡፡ በዚያን ዘመን በሮም ከተማ ውስጥ ይኖሩ ከነበሩት ሰዎች ግማሾቹ፥ በአቴና ከነበሩት ደግሞ ሦስት አራተኞቹ ባሪያዎች እንደነበሩ ይገመታል። ይህም በመጀመሪያው ምእተ ዓመት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ባሮች እንደነበሩ ያመለክታል። እነዚህ ባሮች ምንም ዓይነት መብት ያልነበራቸውና እንደ ንብረት የሚቆጠሩ ነበሩ። ከእነዚህ ባሪያዎች ብዙዎቹ በክርስቶስ አምነው ነበር። እንዲያውም በብዙ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ የባሪያዎች ቁጥር ከነፃ ሰዎች ይበልጥ ነበር። ወንጌሉ እየተስፋፋ ሲሄድ፥ ቤተ ክርስቲያን ይህንን ክፉ ልምምድ (ባሪያ ፍንገላ) ምን ማድረግ እንዳለባት መወሰን ነበረባት። ክርስቲያን የባሪያ አሳዳሪዎችና ክርስቲያን ባሪያዎች ክርስቶስ ከእነርሱ የሚጠብቀው ምን እንደሆነ ማወቅ ያስፈልጋቸው ነበር። አዲስ ኪዳን ይህንን ክፉ የባሪያ ፍንገላ ልምምድ በግልጽ ሲቃወም እንመለከትም። ባሪያዎች እንዲያምጹ ወይም እንዲኮበልሉ አይመክርም። ባሪያ አሳዳሪዎችም ባሪያዎቻቸውን ነፃ እንዲያወጡ አይጠይቅም። ችሎቶች ወይም የፖለቲካ አስተዳደሮች ለዚህ ችግር መፍትሔ እንዲፈልጉ አላሰቡም። ልክ ውኃ ቀስ ብሎ ልብሳችንን እንደሚያጸዳ ሁሉ፥ አዲስ ኪዳንም የባርነትን መጥፎነት በርጋታ ያሳያል። በዚህም ረገድ አያሌ ነጥቦች ተጠቅሰው እንመለከታለን። በመጀመሪያ፥ አዲስ ኪዳን ባሪያዎች እንስሳት ሳይሆኑ፥ በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠሩ ሰዎች መሆናቸውን ያስረዳል። ሁለተኛ፥ በእግዚአብሔር ዓይን ፊት ሰዎች በምድር ላይ ባሪያዎች ይሁኑም አይሁኑም እኩል መሆናቸውን ያስረዳል። ሦስተኛ፥ እንደ ጳውሎስ ያሉ ጸሐፊዎች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የባሪያዎቹ ጌቶችና ባሪያዎች አንድ መሆናቸውን ይገልጻሉ። ባሪያ ወይም ጨዋ የሚባል ነገር የለም (ገላ. 3፡28)። ይህም አንዱ አስፈላጊ ሌላው የተናቀ ተደርጎ የሚቆጠርበት ሁኔታ እንደሌለ ያመለክታል። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ካለው ከእንዲህ ዓይነቱ አንድነት የተነሣ ጳውሎስ አናሲሞስ ከእንግዲህ ባሪያ ብቻ ሳይሆን በጌታ ወንድም መሆኑን ገልጾአል ( ፊልሞና 16)። ይህ ባሪያዎች ጌቶቻቸው የሚጠቀሙባቸው መሣሪያዎች ናቸው ብሎ የሚያስበውን የባሪያ አሳዳሪነት ሥርዓት ከመሠረቱ አናግቷል። በመሆኑም፥ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በባሪያዎችና በጌቶቻቸው መካከል ፍጹም አዲስ ግንኙነት መመሥረቱ አስፈላጊ ነበር። አራተኛ፥ ጳውሎስ የባሪያ አሳዳሪዎች ባሪያዎቻቸውን በፍትሕ እንዲያስተዳድሩ ይጠይቃል። ምክንያቱም እርስ በርሳችን ፍትሕ የሰፈነበት ግንኙነት እንዲኖረን በሚጠይቀው በእግዚአብሔር ፊት አድልዎ የለምና (ቆላ. 4፡1፥ ኤፌ. 6፡9)። አምስተኛ፥ ጳውሎስ ክርስቲያን ባሪያዎች ነፃ ለመውጣት እንዳይታገሉና ወንጌሉን በሚያስከብር መንገድ አገልግሎታቸውን እንዲያበረክቱ ጠይቋል (ቆላ. 3፡22-25)። ምናልባትም ቀደምት የቤተ ክርስቲያን አባቶች በመንፈስ ቅዱስ ተመርተው የፊልሞና መልእክት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዲያስቀምጡ ያደረጋቸው በባርነት ላይ የተሰጠው ይህ ድነትን (ደኅንነትን) የሚያንጸባርቅ ትምህርት ሳይሆን አይቀርም። አራተኛ ዓላማ፡- ቤተ ክርስቲያን ማኅበረሰቡ ላገለላቸው ሰዎች መራራት እንዳለበት ለማሳየት፡፡ ክርስቶስ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ በአብዛኛው የኃጢአተኞች፥ የቀራጮችና የአመንዝራዎች ወዳጅ በመሆኑ ምክንያት ወቀሳ ይሰነዘርበት ነበር (ማቴ. 11፡19)፡፡ እነዚህ ማኅበረሰቡ ያገለላቸው ሰዎች እግዚአብሔር እንደሚወዳቸው የሚያመለክተውን ወንጌል መስማት ያስፈልጋቸው ነበር። ሁሉም በእኩልና ተወዳጅ ወደሚሆኑበት የቤተ ክርስቲያን ቤተሰብነት መምጣት ያስፈልጋቸው ነበር። የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በኢትዮጵያ ውስጥ ማኅበረሰቡ የሚያገልላቸውን ቡድኖች ዘርዝር። ለ) ክርስቶስ በኢትዮጵያ ውስጥ ቢኖር ኖሮ ከእነዚህ የሕዝብ ቡድኖች ጋር ምን ዓይነት ግንኙነት የሚያደርግ ይመስልሃል? እንዴት የሚያስተናግዳቸው ይመስልሃል? ሐ) ክርስቶስ ሕዝቡ (ቤተ ክርስቲያን) እነዚህን ሰዎች እንዴት እንዲያስተናግዱ የሚፈልግ ይመስልሃል? መ) ቤተ ክርስቲያን እነዚህን ሰዎች ያስተናገደበትን ሁኔታ ክርስቶስ እንድናስተናግዳቸው ከሚፈልገው መንገድ ጋር አነጻጽር። ይበልጥ ክርስቶስ የሚፈልገውን ለማድረግ እንደሚችል ዛሬ በቤተ ክርስቲያን ግንዛቤ ልምምድ ውስጥ ሊከሰቱ የሚገባቸው ለውጦች ምን ምንድን ናቸው? የፊልሞና ልዩ ባሕርያት በዚህ መልእክት ውስጥ ዐቢይ አስተምህሮ ወይም የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ አልተነሣም። ነገር ግን ፊልሞና የግል ጉዳይ የሚመስለውን አጀንዳ ሲያንጸባርቅ እንመለከታለን። ይህም ቀደም ሲል የኮበለለውንና አሁን ወደ ጌታው የሚመለሰውን ባሪያ የሚመለከት ነበር። ፊልሞና ጳውሎስ የኮበለለውን ባሪያ በሚመለከተው አስቸጋሪ ጉዳይ ውስጥ በምን እጁን እንዳስገባ ሊጠይቅ ስለሚችል፥ ጳውሎስ መልእክቱን የጻፈው በጥንቃቄና በዘዴ ነበር። ጳውሎስ ፊልሞናን ሳያስቀይም ጥያቄውን ለማቅረብ ይፈልጋል። ምሁራን ጳውሎስን ጥንታዊ የግሪክና የሮም ጸሐፊዎች የሚከተሉትን የደብዳቤ አጻጻፍ እንደተከተለ ያስባሉ። ከፊልሞና ጋር ግንኙነት ለመመሥረት በመሻት ደብዳቤውን ሲጀምር እንመለከታለን (ፊልሞና 4-10)። ከዚያ በኋላ ፊልሞና ለአናሲሞስ የነበረውን አመለካከት ለመቀየር ይሞክራል (ፊልሞና 11፡19)። ከዚያም የፊልሞናን ልብ ለመንካት ይፈልጋል (ፊልሞና 20-21)። በዚህ ዓይነት ጳውሎስ ፊልሞና እግዚአብሔር ለአናሲሞስ እንዲያደርግ የፈለገውን ለማድረግ ወደሚችልበት ደረጃ ሲመራው እንመለከታለን። ጳውሎስ መልእክቱን ለፊልሞና ለማስተላለፍ የቃላት ጨዋታን ይጠቀማል። የአናሲሞስ የስሙ ትርጉም ጠቃሚ ማለት ነው። ጳውሎስ በመንፈሳዊ አነጋገር ያልዳነና የኮበለለ ባሪያ በመሆኑ አናሲሞስ ቀደም ሲል ለፊልሞና እንዳልጠቀመ ይናገራል። አሁን ግን ወደ ጌታው ስለተመለሰና ከሁሉም በላይ የፊልሞና መንፈሳዊ ወንድም በመሆኑ፥ አናሲሞስ ጠቃሚ ሰው ሆኖ መገኘቱን ያስረዳል (ፊልሞና 11)። የፊልሞና አስተዋጽኦ መግቢያና ሰላምታ (ፊልሞና 1-7) ጳውሎስ ፊልሞና አናሲሞስን ይቅር ብሎ እንዲቀበለው ይጠይቀዋል (ፊልሞና 8–22)። የማጠቃለያ አሳቦች (ፊልሞና 23-25) (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የፊልሞና ዓላማ፣ ልዩ ባሕሪያት እና አስተዋጽኦ Read More »

የፊልሞና መግቢያ

ቤተልሔም ያደገችው ክርስቲያን ባልሆኑ ቤተሰቦች ዘንድ ነበር። አባቷ ሰካራም በመሆናቸውና እናቷም ቅስም ሰባሪ ቃላት ስለሚሰነዝሩባት፥ በ14 ዓመቷ የተሻለ ሕይወት ፍለጋ ወደ አዲስ አበባ ጠፍታ መጣች። አዲስ አበባ ደርሳ ከአውቶቡስ ስትወርድ ዙሪያዋን የከበቡትን ጸጉረ ልውጥ ሰዎች ተመልክታ ፈራች። ለአያሌ ቀናት በጎዳናዎች ላይ ላይ ታች እያለች ሥራ ስትፈልግ ቆየች። የኋላ ኋላ አንዲት አሮጊት ሴትዮ ከሆቴላቸው ውስጥ እንድትሠራ ቀጠሯት። ነገር ግን ክፍያው በጣም አነስተኛ በመሆኑ ልብስ ለመግዛት የሚያስችል ገንዘብ ልታገኝ አልቻለችም። አንድ ቀን የሆቴሉ ባለቤት የሆኑት አሮጊት ወደ ሆቴሉ ከሚመጡት እንግዶች ጋር አብራ ብትተኛ የተሻለ ገንዘብ ልታገኝ እንደምትችል ነገሯት። ይህን አሳብ ካልተቀበለች ደግሞ ከሥራ እንደሚያባርሯት አስጠነቀቋት። በመሆኑም በ14 ዓመት ዕድሜዋ ቤተልሔም ሴተኛ አዳሪ ሆነች። በዚህ ጊዜ ሕይወት መረራት። የሚተኟት ወንዶች አለአግባብ ያንገላቷት ነበር። ብዙውን ጊዜ ከተኟት በኋላ ገንዘብ አይሰጧትም። ከምታገኘውም ገንዘብ አብዛኛውን የሆቴሉ ባለቤት ይወስዱባታል። አንድ ቀን ሁኔታው በጣም ስለመረራት ራሷን ለመግደል ወሰነች። ራሷን ስለምታጠፋበት መንገድ እያሰላሰለች ስትሄድ ከአንዲት ትንሽ ቤት የሙዚቃ ድምጽ ተሰማት። ይህ በሆቴሉ ውስጥ ሁልጊዜ ከምትሰማው ሙዚቃ የተለየ በመሆኑ፥ ቀረብ ብላ ከግቢው ጥግ በመቀመጥ ታዳምጥ ጀመር። የቤቱ ባለቤት ቤተልሔምን ተመልክታ ቀረብ አለችና ስለ ክርስቶስ ወንጌል መሰከረችላት። በዚህ ጊዜ እርሷን ከመውደዱ የተነሣ ሕይወቱን ሊሰጥ የፈቀደ ሰው በመኖሩ እጅግ ተደነቀች። እግዚአብሔር ኃጢአትን ይቅር ለማለትና አዲስ ሕይወት ለመስጠት በመቻሉ ልቧ ራደ። በተሰበረ ልብ እንባዋን እያፈሰሰች ክርስቶስን የግል አዳኝዋ አድርጋ አመነች። የውይይት ጥያቄ፡- ሉቃስ 5፡29-32 አንብብ። ክርስቶስ እንደ ሐኪም ሁሉ መንፈሳዊ በሽተኞች የሆኑትን ሰዎች ለመፈወስ እንደ መጣ ተናግሯል። ሀ) እግዚአብሔር እንደ ቤተልሔም ዓይነቷን ልጅ የመረጠው ለምን ይመስልሃል? ለ) እግዚእብሔር እንደ ቤተልሔም ያሉትን ሰዎች የሚወድና የሚያድን ከሆነ፥ ብዙ ክርስቲያኖች ማኅበረሰቡ ለሚንቃቸው ሰዎች ወንጌሉን ለመመስከር የማይፈልጉት ለምንድን ነው? ሐ) ማኅበረሰቡ ካገለላቸው ሰዎች ጋር ለመተባበር አለመፍቀዳችን ስለ ልባችን፥ ስለ ራሳችን፥ ስለ ኃጢአትና ስለ እግዚአብሔር ምን ዓይነት ግንዛቤ እንዳለን ያሳያል? ይህ በሉቃስ 5፡29-32 ከተገለጸው የክርስቶስ አመለካከት የሚለየው እንዴት ነው? የፊልሞና መጽሐፍ እግዚአብሔር አንድን ባርያ በማዳን ያሳየውን አስደናቂ ጸጋ ይናገራል። አናሲሞስ የተባለ ባርያ ከቆላስይስ ኮብልሎ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮች ተጉዞ ወደ ሮም ሄደ። ኑሮው በፍርሃት የተሞላ መሆኑ አያጠራጥርም። ባለሥልጣናት ቢያገኙት፥ ሊገደል ይችል ነበር። እሚኖርበት ቤትና ስፍራ ስላልነበረው፥ ምናልባትም ለምኖ እየበላ በጎዳናዎች ላይ ሳያድር አልቀረም። እግዚአብሔር ግን ይህን ባርያ አሰበው። በሚያስገርም ሁኔታ እግዚአብሔር አናሲሞስን ወደ ጳውሎስ መራው። አናሲሞስ የክርስቶስን ወንጌል በሰማ ጊዜ በክርስቶስ አዳኝነት አመነ። በሕይወቱ ለመጀመሪያ ጊዜ አናሲሞስ በመንፈሱ ነፃ ሆነ። እንግዲህ አሁን ምን ማድረግ አለበት? ጳውሎስ አናሲሞስን ፊልሞና ወደሚባለው ጌታው እንዲመለስ ግድ አለው። ፊልሞና ነጻነቱን ቢሰጠው መልካም ይሆናል። ነገር ግን ለአናሲሞስ ከጌታው በመኮብለል ነጻነቱን ማግኘቱ ተገቢ አልነበረም። በመሆኑም ጳውሎስ አጭር ደብዳቤ ለፊልሞና ጽፎ አናሲሞስን ወደ ጌታው መለሰው። ጳውሎስ በዚህ ደብዳቤ ውስጥ ፊልሞና አናሲሞስን በክርስቶስ ወንድሙ አድርጎ እንዲቀበለውና በጥሩ ሁኔታ እንዲያስተናግደው ይጠይቀዋል። መንፈስ ቅዱስ ዝቅተኛ ለሆነው ባሪያ እግዚአብሔር ያሳየውን ፍቅር ለማመልከትና ሰዎች ከክርስቶስ ጋር ከመገናኘታቸው በፊት ምንም ዓይነት ጥፋት ቢፈጽሙ የእግዚአብሔር ቤተሰብ በጸጋ፥ በይቅርታና በአቀባበል የተሞላ እንዲሆን ሁላችንንም ለማስተማር ይችን አጭር ደብዳቤ ጠብቋታል። የውይይት ጥያቄ፡- ከመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ስለ ፊልሞና አንብብ። ስለ ጸሐፊው፥ ፊልሞና ማን እንደ ነበረ፥ አናሲሞስ ማን እንደ ነበረና የመልእክቱ ዓላማ ምን እንደሆነ ጠቅለል አድርገህ ግለጽ። የፊልሞና ጸሐፊ የውይይት ጥያቄ፡- ፊልሞና 1ን አንብብ። ሀ) ጸሐፊው ማን ነው? ራሱን እንዴት ገለጸው? ይህ በቲቶ መልእክት ውስጥ ራሱን ከገለጸበት ሁኔታ የሚለየው እንዴት ነው? ለ) መልእክቱ የተጻፈው ለማን ነው? የፊልሞና መልእክት በአዲስ ኪዳን ውስጥ ከምናገኛቸው የጳውሎስ መልእክቶች በጣም አጭሩ ነው (ይህ መልእክት አንድ ምዕራፍ ብቻ ስላለው የፊልሞናን መልእክት በምንጠቅስበት ጊዜ ምዕራፉን ትተን ቁጥሩን ብቻ እንጽፋለን።) የፊልሞና መልእክት አጭርና በባህሪውም ግላዊ መልእክት ያዘለ መሆኑ፥ ቀደምት የቤተ ክርስቲያን አባቶች ከጳውሎስ መልእክቶች የመጨረሻው አድርገው አስቀምጠውታል። በጊዜ ቅደም ተከተል ይህ መልእክት የተጻፈው ሦስቱ የእስር ቤት መልእክቶች፥ ማለትም የኤፌሶን፥ የፊልጵስዩስ፥ የቆላስይስ መእክቶች በተጻፉበት ወቅት ነው። እነዚህ አራቱ መልእክቶች የተጻፉት በተመሳሳይ ጊዜ ጳውሎስ ሮም ውስጥ ታስሮ በነበረበት ወቅት ነው። ጳውሎስ የዘመኑን የደብዳቤ አጻጻፍ ሥርዓት ተከትሎ በቀዳሚነት የደብዳቤው ጸሐፊ ራሱ መሆኑን በማስታወቅ ይጀምራል። ነገር ግን ጳውሎስ ራሱን የክርስቶስ እስረኛ በማለት በተለየ ሁኔታ ይገልጻል። በዚህ ስፍራ ሐዋርያ መሆኑን አልጠቀሰም። ሰሌሎች ስፍራዎች እንዳሰፈረው የእግዚአብሔር ባሪያ ነኝ ሲልም አልተናገረም። ጳውሎስ ራሱን እንደ እስረኛ ያስታወቀው በዚህኛው መልእክት ውስጥ ብቻ ነው። ጳውሎስ በዚህ መልእክት ውስጥ ሐዋርያነቱን ያልጠቀሰው እንደ ሌሎቹ መልእክቶች ለብዙ አንባቢዎች የማይቀርብ በመሆኑ ነው። ይህ መልእክት የሚነበበው በፊልሞና ቤተሰብ ብቻ ይሆናል። በመሆኑም በሐዋርያነት ሥልጣኑ ላይ ብዙም ትኩረት አልሰጠም። ይልቁንም ጳውሎስ ለፊልሞናና ቤተሰቡ የላከው በወዳጅነት መንፈስ የሚነበብ መልእክት ነበር። ጳውሎስ ስለመታሰሩ የገለጸው ስለ ወንጌሉ እየከፈለ ያለውን ዋጋ ለፊልሞና ለመግለጽ ነበር። በዚህም ውስጥ ፊልሞና በኮበለለው ባሪያው በአናሲሞስ በኩል ምን ያህል እንዳጽናናው መግለጽ ይፈልጋል። ጳውሎስ ይህን መልእክት የጻፈው ለማን ነበር? ጳውሎስ ይህን መልእክት፥ «ለተወደደውና አብሮን ለሚሠራ ለፊልሞና፥ ለእኅታችንም ለአፍብያ፥ ከእኛም ጋር አብሮ ወታደር ለሆነ ለአርክጳ፥ በቤትህም ላለች ቤተ ክርስቲያን» እንደላክ ይናገራል። ፊልሞናና አፍብያ ምናልባትም የኮበለለው ባሪያ የአናሲሞስ ጌቶችና ባልና ሚስት ሳይሆኑ አይቀሩም። አርክጳ ፊልሞና የነበራት የቆላስይስ ቤተ ክርስቲያን መሪ ነበር። አንዳንዶቹ አርክጳ የፊልሞናና የአፍብያ ልጅ ነበር ይላሉ። ጳውሎስ ወደ ቆላስይስ ሄዶ እንደማያውቅ ታስታውሳላችሁ። ስለሆነም ከፊልሞናና ከአፍብያ ጋር የነበረው ግንኙነት ምናልባትም ስለዚሁ ቤተሰብ በሰማው መረጃ ላይ የተመሠረተ ሊሆን ይችላል። ወይም ጳውሎስ በኤፌሶን በሚያገለግልበት ወቅት ከፊልሞና ጋር ተገናኝቶ ይሆናል (የሐዋ. 19)። ጳውሎስ ምናልባትም ደግሞ ከእርክጳ ጋር በኤፌሶን ተገናኝቶ የቆላስይስን ቤተ ክርስቲያን እንዲያንጽ ሾሞት ይሆናል። ስለ ፊልሞናና አፍብያ ብዙም የምናውቀው ነገር የለም። እነዚህ ሰዎች በቆላስይስ ከተማ የሚኖሩ አማኞች ነበሩ። ምናልባትም በክርስቶስ ያመኑት ጳውሎስ በሦስተኛው የወንጌል መእልክተኝነት ጉዞው ኤፌሶን ውስጥ በሚያገለግልበት ወቅት ሳይሆን አይቀርም። ጳውሎስ በሆነ መንገድ ለፊልሞና ድነት (ደኅንነት) አስተዋጽኦ እንዳበረከተ ይናገራል (ፊልሞና 19)። ምናልባትም ፊልሞና ሀብታም ነጋዴ ሳይሆን አይቀርም። ይህንንም የምናውቀው በሁለት ምክንያቶች ነው። በመጀመሪያ፥ ባሪያ ነበረው። ይህ ድሆች ሊያደርጉት የማይችሉት ነገር ነው። ሁለተኛ፥ በቆላስይስ አማኞች የሚሰባሰቡበት ትልቅ ቤት ነበረው። ፊልሞና የተጻፈበት ጊዜና ስፍራ ጳውሎስ ይህን መልእክት በጻፈበት ወቅት በሮም ታስሮ እንደነበር ግልጽ ነው። ግን ይሄ የትኛው እስራቱ እንደነበር ጳውሎስ በግልጽ አይናገርም። አንዳንድ የቤተ ክርስቲያን ምሁራን ጳውሎስ በኤፌሶን እንደታሰረ ይናገራሉ። ሌሎች ደግሞ በቂሳሪያ ታስሮ ነበር ይላሉ። ይሁንና ጳውሎስ በእነዚህ ሁለት ስፍራዎች የታሰረ አይመስልም። (የእስር ቤት መልእክቶች ስለተጻፉበት ጊዜ የቀረበውን መግቢያ በኤፌሶንና በፊልጵስዩስ መልእክት አንብብ።) በአመዛኙ ተቀባይነት ያለው አመለካከት ጳውሎስ በሮም ከተማ ታስሮ እንደነበር የሚያስረዳው ነው። ስለሆነም ይህ ፊልሞና መልእክት የተጻፈው የሐዋርያት ሥራ 28 እንደሚገልጸው ሳይሆን አይቀርም። ፊልሞና የቆላስይስ መልእክት በተጻፈበት ጊዜ ነበር የተጻፈው። እንደዚህ ከሆነ ደግሞ፥ መልእክቱ የተጻፈው በ60 ዓ.ም አካባቢ ይሆናል። በቆላስይስ 4፡7-9 ጳውሎስ ቲኪቆስና አናሲሞስ መልእክቱን ወደ ቆላስይስ እንደሚያመጡ ይናገራል። በመሆኑም የቆላስይስና የፊልሞና መልእክቶች የተላኩት በእነዚህ ሁለት ሰዎች አማካኝነት እንደነበር እንገነዘባለን። ይኸው አክርጳ የተባለው ሽማግሌ በቆላስይስ ስሙ ተጠቅሷል (ቆላ. 4፡17)። (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የፊልሞና መግቢያ Read More »