ትንቢተ ኢሳይያስ

የትንቢተ ኢሳይያስ መግቢያ

የውይይት ጥያቄ፥ እግዚአብሔር የነገሮች ሁሉ የበላይ ተቈጣጣሪ ነው፡- እርሱም በሕዝብ መሪዎች ላይ፥ ወደ ክርስቲያን ሕይወት በሚመጣ በረከት ላይ፥ በምድር በሚመጡ ፍርዶች ላይ፥ በምድር በሚፈጸሙ ነገሮች ሁሉ ላይ የበላይ ተቆጣጣሪ ነው። አንድ ክርስቲያን ይህን እውነት ከተረዳ በክርስትና ሕይወቱ የሚያበረታታው እንዴት ነው? በብሉይ ኪዳን ከሚገኙ ታላላቅ የትንቢት መጻሕፍት አንዱ ትንቢተ ኢሳይያስ ነው። ታላቅ የተባለባቸው በርካታ ምክንያቶች አሉ፤ በመጀመሪያ፥ ትንቢተ ኢሳይያስ ስለ እግዚኣብሔር ግርማ፥ ቅድስናና በነገሮች ሁሉ ላይ ስላለው ሉዓላዊ ሥልጣን ግልጽ የሆነ ትምህርት ይሰጣል። ስለ እግዚአብሔር ባሕርይ የማያሻማ ገለጻ ያቀርባል። አንድ ክርስቲያን የእግዚአብሔርን ባሕርይ የበለጠ በተረዳ ቍጥር፥ በሕይወቱ በሚገጥሙት አስቸጋሪና አጠራጣሪ ጉዳዮች ውስጥ በእግዚአብሔር በመተማመን በእርግጠኝነት መጓዙን ይቀጥላል። ሁለተኛ፥ ትንቢተ ኢሳይያስ ከመዝሙረ ዳዊት በቀር ከማንኛቸውም የብሉይ ኪዳን መጽሐፍ ይልቅ በአዲስ ኪዳን ተጠቅሶአል፤ ይህም 80 ጊዜ ያህል ነው። በሦስተኛ ደረጃ፥ ትንቢተ ኢሳይያስን ታላቅ ያሰኘው በርካታ የወንጌል መመሪያዎችን መያዙ ነው። በመሠረቱ አንዳንዶች ትንቢተ ኢሳይያስን «አምስተኛው ወንጌል» በማለት ይጠሩታል። ይህም የሆነው፥ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ክርስቶስን የሚያሳዩ ብዙ ተምሳሌቶች ስላሉና ሰው በእግዚአብሔር ፊት ጻድቅ የሚሆንበት መንገድ በግልጽ ስለቀረበ ነው (ለምሳሌ፡-1፡18፤ 44፡22፥ 55፤ 64፡6)። 2ኛ ጥያቄ፥ በትንቢተ ኢሳይያስ ውስጥ የሚገኙ ከዚህ ቀደም ያበረታቱህ አንዳንድ ክፍሎችን ጥቀስ። ትንቢተ ኢሳይያስ ከታላላቅ የነቢያት መጻሕፍት መካከል የመጀመሪያው ነው። ካለፈው ሳምንት ትምህርት እንደምታስታውሰው ከትንቢተ ኢሳይያስ ጀምሮ እስከ ኤርምያስ ድረስ ያሉት መጻሕፍት ስም ከታላላቅ ነቢያት ክፍል የሚመደቡ ናቸው። የታላላቅ ነቢያት መጻሕፍት ስለ እግዚአብሔር ፈቃድና ወደ ፊት ስለሚፈጸሙ ነገሮች የነበረንን እውቀት የሚያጐለብቱ ናቸው።  ትንቢተ ኢሳይያስ በይሁዳ ምድር ባሉት በአይሁድ ሕዝብ ላይ የሚመጣውን የእግዚአብሔርን ጥፋት አስቀድሞ ተንብዮ ነበር፤ ዳሩ ግን የመጽሐፉ የመጨረሻ ግማሽ ክፍል፥ በምርኮ የተወሰደው ሕዝብ የሚለቀቅበትንና አይሁድ ወደ ምድራቸው የሚመለሱበትን ጊዜ ያመለክታል። ኢሳይያስ እግዚአብሔር በሕዝቦች ሁሉ ላይ ያለውን ሉዓላዊ ሥልጣን በማመልከት በምርኮ ይኖሩ የነበሩት ሕዝብ በእግዚአብሔር ላይ ያላቸውን እምነት እንዳይተው ለማጽናናትና ለመምከር ፈልጎ ነበር።  የትንቢተ ኢሳይያስ ጸሐፊ ትንቢተ ኢሳይያስ ስያሜውን ያገኘው መጽሐፉን ከጻፈው ነቢይ ስም ነው። በኢሳይያስ 1፡1 እንደተገለጸው፥ መጽሐፉ የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ የተቀበለው ራእይ ነው። ሰዎች ከብዙ መቶ ዓመታት ጀምሮ የትንቢተ ኢሳይያስ ጸሐፊ ኢሳይያስ ራሱ እንደሆነ ያምኑ ነበር። የመጽሐፉ የመጀመሪያ ቍጥር የሚናገረው ይህንኑ ስለሆነ የምንጠራጠርበት አንዳችም ምክንያት የለም። ሆኖም ባለፉት መቶ ዓመታት ውስጥ፥ ምሁራን ሙሉ መጽሐፉን የጻፈው ኢሳይያስ ስለ መሆኑ ጥያቄ ማንሣት ጀምረዋል። የመጽሐፉን የመጀመሪያ ግማሽ ክፍል (ከምዕራፍ 1-39) ከመጽሐፉ ሁለተኛ ክፍል (ከምዕራፍ 40-66) ጋር ሲያወዳድሩ በርካታ ልዩነቶችን አዩ። ከዚህ የተነሣ፥ ትንቢተ ኢሳይያስን የጻፈው ማን ነው? ለሚለው ጥያቄ መልስ የሚሰጡ የተለዩ ጽንሰ አሳቦች ተፈጠሩ፡፡  1. የትንቢተ ኢሳያይስ ጸሐፊዎች ሁለት ናቸው፤ የመጀመሪያው፥ ኢሳይያስ በመባል የሚታወቅና የእስራኤል መንግሥት ለሁለት ተከፍሎ በቆየባቸው ዘመናት የኖረ ሲሆን፥ የጻፈውም ከምዕራፍ 1-32 ያለውን ከፍል ነው። ሁለተኛው ጸሐፊ ግን አይሁድ ከባቢሎን ምርኮ ከተመለሱ በኋላ የኖረና ከምዕራፍ 33-66 ያለውን ክፍል የጻፈ ሰው ነው። (አንዳንዶች የመጀመሪያው ጸሐፊ ከምዕራፍ 1-39 ያለውን ሁለተኛው ጸሐፊ ደግሞ ከምዕራፍ 40-66 ያለውን ክፍል ጽፏል ይላሉ)። ዛሬ ብዙ ምሁራን፥ በተለይም ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው የጻፉት መጽሐፍ መሆኑን የማያምኑ ሰዎች የሚቀበሉት ይህን አመለካከት ነው።  2. ትንቢተ ኢሳይያስን የጻፉት ሦስት ሰዎች ናቸው። የመጀመሪያው ጸሐፊ የእስራኤል መንግሥት ለሁለት ተከፍሎ በቆየበት ዘመን የኖረ ሲሆን፥ ከኢሳይያስ 1-39 ያለውን ክፍል ጽፏል። ከ580 ዓ.ዓ. በኋላ ሁለተኛው ጸሐፊ ከኢሳይያስ 40-55 ያለውን ክፍል የጻፈ ሲሆን፥ በ444 ዓ.ዓ. በነህምያ ዘመን አካባቢ ይኖር የነበረ ሌላ ምስተኛ ጸሐፊ ከኢሳይያስ 56-66 ያለውን ጽፏል። 3. ትንቢተ ኢሳይያስን በሙሉ የጻፈው ኢሳይያስ ነው። አይሁድና ክስርቲያኖች በዘመናት ሁሉ ውስጥ የያዙት አቋም ይህ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ጻፉት መጽሐፍ መሆንን በሚያምኑ ክርስቲያኖች ዘንድ አሁንም ከፍተኛ ደረጃ ተቀባይነት ያለው አቋም ይህ ነው።  በምሁራን መካከል ይህ ልዩነት የሚታየው ለምንድን ነው? ቢያንስ ሁለት ጸሐፊዎች ነበሩ የሚል አቋም ያላቸው ጸሐፊዎች የሚያቀርቡት ምክንያት እንደሚከተለው ነው፡- ሀ. በርካታ ምሁራን ትንቢተ ኢሳይያስ ውስጥ የምንመለከተው ዓይነት ዝርዝርና ስሕተት የሌለበት ትንበያ ድርጊቱ ከተፈጸመ በኋላ የተመለከተ አንድ ሰው ካልጻፈው በስተቀር ሌላ ሊሆን አይችልም ብለው ያምናሉ። በትንቢተ ኢሳይያስ ውስጥ የምንመለከታቸው አብዛኛዎቹ ትንቢቶች ግልጽና ጥርት ያሉ ሆነው ያለ አንዳች ስሕተት የተፈጸሙ ስለሆኑ፥ መጽሐፉ የተጻፈው ድርጊቶቹ ከተፈጸሙ በኋላ ነው ይላሉ። ለምሳሌ፡- ከ740-700 ዓ.ዓ. የኖረው ኢሳይያስ እስራኤላውያንን ከባቢሎን ምርኮ ነፃ የሚያወጣው የአሕዛብ ንጉሥ ቂሮስ ተብሎ እንደሚጠራ ተንብዮ ነበር (ኢሳይያስ 44፡28፤ 45፡1)። እንደምታውቀው፥ ይህ ትንቢት የተፈጸመው የፋርስ ንጉሥ የሆነው ቂሮስ ከ200 ዓመታት በኋላ የባቢሎንን መንግሥት በማሸነፉ እስራኤላውያን ወደ ምድራቸው እንዲመለሱ በፈቀደ ጊዜ ነበር። ለ. እነዚህ ምሁራን በትንቢተ ኢሳይያስ ውስጥ የሚገኙ ትንቢቶች በሌሎች መጻሕፍት ከሚገኙ ትንቢቶች ሁሉ የተለዩ ናቸው ይላሉ። ሊመጣ ስላለው ምርኮ ሰፊና ግልጽ ያልሆኑ ጥቅሶች ከመሆን ይልቅ፥ ትንቢቶች እጅግ ዝርዝር ወደሆነ ነገር በመግባት ነፃ የመውጣቱን ጉዳይ የሚያስፈጽመውን ሰው ስም እስከ መጥቀስ ድረስ እንኳ ዘልቅዋል። ሐ. እነዚህ ምሁራን፥ የመጽሐፉን የመጀመሪያ ግማሽ ከሁለተኛው ግማሽ ክፍል ጋር በምናወዳድርበት ጊዜ የቋንቋ አጠቃቀማቸው ፍጹም የተለያየ ስለሆነ የተጻፉት በሁለት የተለያዩ ሰዎች መሆን አለበት ይላሉ። የትንቢተ ኢሳይያስ የመጀመሪያ ግማሽ ክፍል ስለ ፍርድና ጥፋት የሚናገር ሲሆን፥ በሰቆቃ ትንበያዎች የተሞላ ነው። ሁለተኛው ግማሽ ክፍል ግን በይበልጥ ሥነ-ግጥማዊና ሥነመለኮታዊ ትምህርት የያዘ ነው። የሚያተኩረው በማበረታቻ መልእክት ላይ ሲሆን፥ የተጻፈውም ሕዝቡ በምርኮ ውስጥ እንዳለ እንጂ ምርኮው ገና ከ150 ዓመታት በኋላ እንደሚፈጸም ተደርጎ አይደለም። የትንቢተ ኢሳይያስ መጽሐፍ የመጀመሪያ ግማሽ የሚያተኩረው በነገሥታትና እግዚአብሔር በሕዝቡ ላይ ከሚያመጣው ፍርድ በኋላ በሚኖሩ ቅሬታዎች ላይ ሲሆን፥ ሁለተኛው ግማሽ ክፍል ግን ሊመጣ ባለው የእግዚአብሔር አገልጋይና እግዚአብሔር ለሕዝቡ በሚያመጣው ደኅንነት ላይ ነው። መ. ለነቢያትና ለትንቢታቸው ህልውና ዐበይት ከሆኑት ምክንያቶች አንዱ፥ በዘመናቸው ለነበሩ ሰዎች አስፈላጊ የሆነ መልእክት መስጠት እንደነበረ ተመልክተናል። የትንቢተ ኢሳይያስ የመጨረሻ ግማሽ ክፍል ግን በነቢዩ ዘመን በጊዜው የነበሩትን ሰዎች የሚመለከት አይመስልም። ይልቁንም የይሁዳ ሕዝብ በምርኮ እንዳሉ አድርጎ የሚናገር ይመስላል። ስለዚህ ይህ ትንቢት የተሰጠው እስራኤል በምርኮ እንዳለች እንጂ በምርኮ ከመወሰዳቸው ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት እንዳልሆነ የሚያመለክት ይመስላል። የውይይት ጥያቄ፥ አንድ ሰው ስለ ትንቢትና እግዚአብሔር የወደፊቱን ጉዳይ አስቀድሞ ለማመልከት ስላለው ችሎታ የሚኖረው አመለካከት በአቋም ላይ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር፥ እነዚህ አመለካከቶች እንዴት ያሳዩናል? ይህ መጽሐፍ የተጻፈው በአንድ ጸሐፊ ብቻ ነበር የሚል አመለካከት ያላቸው ሰዎች ይህን አመለካከት የሚቀበሉት በሚከተሉት ምክንያቶች ነው፡- 1. የአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎች ትንቢቱ እንዴት እንደተፈጸመ ለማሳየት ከትንቢተ ኢሳይያስ የጠቀሱት ከመጀመሪያውም ከሁለተኛውም ግማሽ ሲሆን፥ ሁለቱንም ክፍል የጻፈው ኢሳይያስ እንደሆነ ተናግረዋል (ለምሳሌ፡- ማቴዎስ 3፡3፤ 12፡17-21፤ ሉቃስ 3፡4-6፤ ዮሐንስ 12፡38-41፤ የሐዋርያት ሥራ 8፡28-33)። አዲስ ኪዳንን በመንፈስ ቅዱስ ምሪት የጻፉት ሰዎች ትንቢተ ኢሳይያስን በሙሉ የጻፈው ኢሳይያስ ነው ብለው እንደነበር ግልጽ ነው።  2. ከትንቢተ ኢሳይያስ ዐበይት መልእክቶች አንዱ፥ እግዚአብሔር የመጪውን ጊዜ ሁኔታ በመተንበይ በዘመናት ውስጥ የተለያዩ ድርጊቶች ይፈጸሙ ዘንድ ታሪክን ሁሉ የሚመራ መሆኑ ነው (ኢሳይያስ 42፡9፤ 46፡8-10)። ስለዚህ ክርስቲያኖች መጪውን ጊዜ በሚመለከት ስለተነገሩትና በትክክል ስለተፈጸሙት ትንቢቶች መደነቅ አይኖርባቸውም።  3. አንድ ሰው፥ በእግዚአብሔር የወደፊት ሁኔታዎችን መቆጣጠር ችሎታ የሚያምን ከሆነ፥ እንዲሁም ምንም ያህል የዓመታት ገደብ ይኑር፥ እግዚአብሔር የሚፈጸመውን ነገር ከመሆኑ አስቀድሞ የሚያውቅና መልእክቱን ለቀድሞዎቹ ነቢያት መስጠቱን የሚቀበል ከሆነ፥ እግዚአብሔር የቂሮስን ስም የመሳሰሉትን ግልጽ ትንቢቶች ለመስጠት እንደሚችል የሚጠራጠርበት ምክንያት የለም። እግዚአብሔር በዚህ መልክ ሊሠራ እንደሚችል እስካመንን ድረስ ሌሎች ጸሐፊዎችን የምንፈልግበት ምክንያት የለም።  4. የመጽሐፉ የመጀመሪያና ሁለተኛ ግማሽ ክፍል ቋንቋው በእጅጉ የተለያየው፥

የትንቢተ ኢሳይያስ መግቢያ Read More »

ስለ ትንቢት የሚቀርቡና በአተረጓጐሙ ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ የተለያዩ አመለካከቶች

ትንቢትን ማጥናት ቀላል አይደለም። ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትና ሌሎች የሰጡትን ትርጕም ለመመርመር ረጃጅም ሰዓታትን የሚጠይቅ ነው። በትንቢት መጻሕፍት ውስጥ የሚገኙትን አብዛኛዎቹን የነቢያት መልእክቶች ለመተርጐም በምሁራን ዘንድ አጠቃላይ ስምምነት ቢኖርም፥ ሆኖም ግን በአይሁድ ታሪክ ወይም በኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወት ተፈጻሚነት ያላገኙትን ትንበያዎች ለመተርጎም ትልቅ ልዩነት ታይቶአል። ምሁራን፡- እነዚህ ትንበያዎች ተምሳሌታዊ በሆነ መንገድ ቀደም ሲል በአይሁዳውያን ተፈጽመዋል ወይስ በቤተ ክርስቲያን ልምድ ውስጥ በመንፈሳዊ ሁኔታ ተፈጽመዋል? ወይንስ ደግሞ በቀጥታ የሚፈጸሙበትን መጪውን ጊዜ እየተጠባበቁ ናቸው? ሲሉ ይጠይቃሉ። ያልተፈጸሙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችን በመረዳት ረገድ ከፍተኛ ልዩነቶችን የሚፈጥሩ ሁለት ዐበይት ጉዳዮች አሉ፡- 1. ትንቢቶቹን መረዳት የሚቻለው እንደተጻፉ በቀጥታ ነው ወይስ በተምሳሌታዊ መንገድ? አንዳንድ ምሁራን ወደፊት ስለሚመጣው ጦርነት፥ ስለተባበረው የእስራኤል መንግሥት ዳግም መመሥረት ወይም ወደፊት ስለሚሠራው ቤተ መቅደስ የሚናገሩ ትንቢቶች ሁሉ በተምሳሌታዊ ሁኔታ ከግንዛቤ ውስጥ መግባት እንዳለባቸው ይገምታሉ። እነዚህ ነገሮች መፈጸም ያለባቸው በቀጥታ ለአይሁድ ሕዝብ ሳይሆን፥ ለቤተ ክርስቲያን ነው ይላሉ። እነዚህ ትንቢቶች እግዚአብሔር አንድ ቀን በቤተ ክርስቲያን ላይ የሚያመጣቸው የአንድነት፥ የሰላም ወይም ዘላለማዊ የሆነ አምልኮ መግለጫዎች ናቸው የሚል እምነት አላቸው።  ሌሎች ምሁራን ግን ይህ መጽሐፍ ቅዱስን ለመተርጐም አጥጋቢ ነው ብለው አያምኑም። ቀጥተኛ የሚመስሉትን ትንቢቶች (ለምሳሌ፡- ስለ ቤተ መቅደሱ መሠራት የተነገረው ሕዝቅኤል 40-48) ተምሳሌታዊ አድርገን መውሰድ ከጀመርን ትንቢትን እንዴት እንደምንተረጕምና እንደምናዛምድ እንዲሁም ልንረዳው የሚገባን በቀጥታ ይሁን በተምሳሌት የምንወስንበት መመዘኛ አይኖረንም ይላሉ። ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የመጀመሪያ አመጣጥ፥ በቤተ ልሔም ስለ መወለዱ፥ ወደ ግብጽ ስለ መሸሹ፥ ስለ ሞቱና ትንሣኤው የተነገሩ ኣብዛኛዎቹ ትንቢቶች በብሉይ ኪዳን በተነገሩበት አኳኋን በቀጥታ መፈጸማቸውን ይጠቁማሉ፤ ስለዚህ አብዛኛዎቹ የብሉይ ኪዳን ትንቢቶች ቀጥተኛ አይደሉም፤ የምንረዳቸውና የሚፈጸሙትም በተምሳሌታዊ ሁኔታ ነው ለማለት የምንችልበት ግልጽ መሠረታዊ ምክንያት የለንም ይላሉ። እነዚህ ምሁራን ትንቢቶችን መጀመሪያ ከተጻፉትና መልእክቱ የተጻፈላቸው አይሁድም ከተረዱበት መንገድ ጋር በእጅጉ ተቀራራቢ በሆነ አኳኋን መተርጐምን ይመርጣሉ። ለምሳሌ፡- ሕዝቅኤል 40-48 በግልጽ የሚያስተምረው ስለ እስራኤል ሕዝብ መመለስ፥ ስለ ምድሪቱ መከፋፈል፥ ስለ ቤተ መቅደሱ መሠራትና ስለ መሥዋዕት አቀራረብ ነው። ስለዚህ ይህ ሁሉ በመጨረሻው ዘመን ልክ እንደተነገረው ይፈጸማል ብለው ያምናሉ። 2. በእግዚአብሔር የወደፊት ዕቅድ ውስጥ እስራኤል ያላት ስፍራ፡- በብሉይ ኪዳን ዘመን አይሁድ ሁሉ የእግዚአብሔር ሕዝብ እንደነበሩ ምሁራን በሙሉ ይስማማሉ። ቤተ ክርስቲያን ደግሞ በዚህ ዘመን ያለች የእግዚአብሔር ሕዝብ ማኅበር እንደሆነች ያምናሉ፤ ነገር ግን እስራኤላውያን በእግዚአብሔር የወደፊት ዕቅድ ውስጥ ስላላቸው ስፍራ ምሁራን ኣይስማሙም። እግዚኣብሔር ለአይሁድ ወደፊት ሊፈጽምላቸው ተስፋ የሰጣቸው ልዩ ዕቅድ አላውን? ወይስ በአይሁድና በአሕዛብ መካከል የነበረው የልዩነት ግድግዳ ሙሉ በሙሉ ፈርሶ፥ በብሉይ ኪዳን ስለ አይሁድ የተነገሩ ትንቢቶች ሁሉ ለቤተ ክርስቲያን መፈጸም ያለባቸው ናቸው? ከእንግዲህ የአብርሃም መንፈሳዊ ልጆች እንጂ በሥጋ የአብርሃም ልጆች የሚባሉ የሉም ማለት ነውን? (ገላትያ 3፡29፤ 4፡28-31፤ ሮሜ 9፡8)። የውይይት ጥያቄ፥ የሚከተሉትን ጥቅሶች ተመልከት፡- ገላትያ 3፡29፤ 4፡28-31፤ ሮሜ 9፡8። ጥቅሶቹ ስለ እውነተኞች አይሁድና ስለ እውነተኞች የአብርሃም ልጆች ምን ይላሉ? አንዳንድ ምሁራን እግዚአብሔር በሥጋ የአብርሃም ልጆች ከሆኑ እስራኤላውያን ጋር የነበረው ዕቅድ ያከተመ ይመስላቸዋል። አሁን የሚሠራው አይሁድና አሕዛብ ከሚገኙበት ቤተ ክርስቲያን ጋር ብቻ ነው ይላሉ። ስለዚህ እስራኤልና ይሁዳ እንደገና እንደሚዋሐዱ፥ ምድራቸውን ወደፊት እንደሚያገኙ ወይም ወደ ምድራቸው እንደሚመለሱ ወዘተ. የተነገሩት ትንቢቶች ቤተ ክርስቲያንን በሚያመለክት መንገድ በተምሳሌት መተርጐም አለባቸው ይላሉ። 15ኛ ጥያቄ. ሮሜ 11፡25-32 አንብብ። እነዚህ ጥቅሶች እግዚአብሔር ለእስራኤል ነገድ የተለየ ዕቅድ እንዳለው የሚያስተምሩ ናቸው ወይስ ከቤተ ክርስቲያን ጋር ኣንድ ናቸው? መልስህን አብራራ። ሌሉች ምሁራን እግዚአብሔር የአብርሃም የሥጋ ዝርያ ለሆኑት አይሁድ አሁንም ቢሆን ዓላማ አለው ይላሉ። በብሉይ ኪዳን ውስጥ ስለ ከነዓን ምድር፥ ከኢየሩሳሌም የዳዊት ልጅ እንደሚገዛቸው፥ ወዘተ. ልዩ በሆነ መንገድ የሰጣቸው የተስፋ ቃል ወደፊት በቀጥታ ይፈጸማል። ስለዚህ እነዚህ ምሁራን ያልተፈጸሙ ትንቢቶች የሚፈጸሙት በተምሳሌት ለቤተ ክርስቲያን ሳይሆን፥ በቀጥታ ለእስራኤል ሕዝብ እንደሆነ ይናገራሉ። ስለ እነዚህ ጉዳዮች ያለን ቅድመ አስተሳሰብ እነዚህን ያልተፈጸሙ ትንቢቶች በምንተረጕምበት ሂደት ላይ ምን ያህል ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ልብ ልንል ያስፈልጋል። የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጓሜዎች በትንቢት መጻሕፍት አተረጓጐም ረገድ በከፍተኛ ደረጃ የሚለያዩት በእነዚህ ሁለት ጉዳዮች ላይ ባላቸው የተለያየ ግንዛቤ ነው። ይህ ነገር ክርስቲያኖች በመሆናችን ወይም ባለመሆናችን ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድር አለመሆኑን መገንዘብ አስፈላጊ ነው። በሁለቱም አመለካከቶች ውስጥ የእግዚአብሔር ቃል የሚያስተምረው ነገር እነርሱ እንደሚያስቡት ብቻ እንደሆነ የሚያምኑ ጠንካራ የክርስቲያን ምሁራን አሉ። ሆኖም ስለ ሁለቱ አመለካከቶች ግልጽ የሆነ ግንዛቤ ማግኘት አስፈላጊ ነው። የትኛው አመለካከት የበለጠ መጽሐፍ ቅዱሳዊ እንደሚመስልና ያንንም ያልነው ለምን እንደሆነ ለራሳችን መወሰን አለብን። ነገር ግን እነዚህን ጉዳዮች በሚመለከት ከእኛ የተለየ ግንዛቤና አተረጓጐም ካላቸው ጋር በመቻቻል ለመኖር መዘጋጀት አለብን። የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) የሚቻል ከሆነ፥ ከተለያዩ የክርስትና እምነት ክፍሎች ከሆኑና በሚገባ ከተማሩ ሰዎች ጋር በመነጋገር ስለ መጪው ጊዜ ምን እንደሚያስቡ ተረዳ። የብሉይ ኪዳን ትንቢቶች እንዴት መተርጐም እንዳለባቸውና እግዚአብሔር ለእስራኤል ስለወጠነው የወደፊት ዕቅድ ያላቸው አስተሳሰብ ምንድን ነው? ለ) ቤተ ክርስቲያንህ ስለ እነዚህ ሁለት ጉዳዮች ያላት እምነት ምንድን ነው? ለምን? የቤተ ክርስቲያንህን መጋቢ ወይም ወንጌላዊን ጠይቅ። ምሁራን አብዛኛዎቹን ያልተፈጸሙ ትንቢቶች በመተርጐም ረገድ ይረዳቸው ዘንድ እያንዳንዱን ትንቢት ለመረዳት የሚጠቅም ሰፋ ያለ መሠረት ጥለዋል። በአጠቃላይ ሰዎች ትንቢቶችን ለመተርጐም የሚጠቀሙባቸው መሠረቶች ሦስት ዓይነት ናቸው። የመጀመሪያዎቹ ሁለት አመለካከቶች ትንቢቶችን በተምሳሌታዊ ሁኔታ የሚተረጕሙበት ሁኔታዎች ናቸው። እንዲሁም ቤተ ክርስቲያንንና እስራኤልን እንደ አንድ የእግዚአብሔር ሕዝብ አድርገው የሚቆጥሩና እግዚአብሔር ለቤተ ክርስቲያንና ለእስራኤል አንድ እንጂ የተለያየ ዕቅድ የለውም የሚሉ ናቸው።  1. ኢየሱስ ክርስቶስ የሚመለሰው ከአንድ ሺህ ዓመት በኋላ ነው የሚለው አመለካከት (ድኅረ ሺህ ዓመት ወይም ፖስት-ሚሌኒያሊዝም)፡- ይህም አመለካከት እግዚአብሔር አንድ ሕዝብ ብቻ እንዳለው ያምናል። ያም ሕዝብ በብሉይ ኪዳን እስራኤል የተባለው ሲሆን፥ በአዲስ ኪዳን ደግሞ ቤተ ክርስቲያን በመባል ይጠራል። እግዚአብሔር በብሉይ ኪዳን ለእስራኤል የገባው ቃል ኪዳን የተፈጸመው በቀጥታ ለእስራኤል ሳይሆን፥ በመንፈሳዊ መንገድ ለቤተ ክርስቲያን ነው። ወንጌል በዓለም ሁሉ ስለሚስፋፋ ዓለም በሙሉ በክርስትና እምነት ትለወጣለች። ክርስቶስ መጀመሪያ ሲመጣ የተጀመረው የእግዚአብሔር መንግሥት ዓለምን ሁሉ እስኪያጠቃልል ድረስ ይስፋፋል። ከዚያም ለረጅም ጊዜ በምድር ላይ ሰላም ከሰፈነ በኋላ ክርስቶስ ይመጣል። ሰው ሁሉ ከተነሣና ፍርድ ከተሰጠ በኋላ ዘላለማዊ ወደሆነው መንግሥተ ሰማያት ወይም ገሃነም ይገባል። ኢየሱስ አንድ ሺህ ዓመት እንደሚነግሥ የተነገረው ቃል ተምሳሌታዊ ሲሆን፥ ክርስቶስ ወደ ሰማይ ካረገበት ጊዜ ጀምሮ ለዘላለም ሊነግሥ እስከሚመለስበት ድረስ ያለው ወቅት ነው። ከአንደኛውና ሁለተኛው የዓለም ጦርነት በፊት ይህ አመለካከት የታወቀ ነበር። ብዙ ክርስቲያኖች ክርስትና በፍጥነት በማደግ ዓለምን ሁሉ ያጠቃልላል ብለው ያስቡ ነበር፤ ከጦርነቶቹ በኋላ ግን ይህ አመለካከት እስከዚህም የታወቀ አልነበረም። ማስታወሻ፡፡ ሚሊኒየም የሚለው ቃል በእንግሊዝኛ የክርስቶስ ሺህ ዓመት መንግሥት ማለት ነው (ራእይ 20፡1-6)። የውይይት ጥያቄ. ሀ) ማቴዎስ 24፡14 ተመልከት። ወንጌል በዓለም ሁሉ ሊዳረስ የሚችልባቸው አንዳንድ መንገዶች አሉን? ለ) አብዛኛው ሕዝብ ክርስቲያን የሚሆንበት ጊዜ የሚመጣ ይመስልሃል? 2. በምድር ላይ የአንድ ሺህ ዓመት መንግሥት የሚባል ነገር የለም የሚለው አመለካከት (አሚሌኒያሊዝም)፡- እነዚህ ክርስቲያኖች እስከ ዘመኑ ፍጻሜ ድረስ መልካምና ክፉ በምድር ላይ ይኖራሉ ይላሉ። ክርስቶስ በአካል በምድር ላይ የሚነግሥበት ጊዜ ከቶ አይኖርም። የክርስቶስ የሺህ ዓመት መንግሥት ጉዳይ ተምሳሌታዊ ነው። ክርስቶስ በአሁኑ ጊዜ በመንፈሱ በሕዝቡ ልብ ውስጥ ነግሦአል፤ ከሞቱና በሰማይ ከእርሱ ጋር ካሉ ቅዱሳን ጋር ነግሦአል። በመጨረሻው ዘመን በምድር ላይ ሁኔታዎች ሁሉ ይከፋሉ። ክሕደት ይጨምራል። ከዚያም ክርስቶስ በክብሩ ይመጣና ጠላቶቹን ሁሉ ያሸንፋቸዋል። የሞቱት ይነሡና ይፈረድባቸዋል። ከዚያም በኋላ ሰው ሁሉ በመንግሥተ ሰማያት ወይም በገሃነም ውስጥ ለዘላለም ይገባል። እስራኤልና ቤተ ክርስቲያን አንድ ስለሆኑ በብሉይ ኪዳን ለእስራኤል

ስለ ትንቢት የሚቀርቡና በአተረጓጐሙ ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ የተለያዩ አመለካከቶች Read More »

ትንቢትን ለመተርጐም የሚጠቅሙ መመሪያዎች

በብሉይ ኪዳን ውስጥ 17 የትንቢት መጻሕፍት እንዳሉ ተመልክተናል። ይህ ማለት ከብሉይ ኪዳን መካከል ብዙዎቹ መጻሕፍት የተጻፉት በነቢያት ነው ማለት ነው። እነዚህ ነቢያት እኛ በምናስተውለው በተለመደው መንገድ አልነበረም ነቢይነታቸው፤ ነገር ግን ለነበሩበት ትውልድ የእግዚአብሔር ቃል አቀባዮች ነበሩ። የትንቢት መጻሕፍት ስለ ወደፊት ሁኔታዎች እንደሚናገሩ ከማሰብ ይልቅ መልእክቶች (ስብከቶች) እንደሆኑ መቊጠሩ ይመረጣል። ብዙውን ጊዜ ነቢያት የእስራኤልን ሕዝብ በሚመለከት ከዚህ ቀደም እግዚአብሔር በታሪካቸው ውስጥ ስላደረገው ነገር ይናገሩ ነበር። አብዛኛው መልእክታቸው በዘመናቸው የነበሩ የእግዚአብሔር ሰዎች ስለነበሩበት ሁኔታ የሚናገር ነበር። ስለ ወደፊት ሁኔታዎች የሚናገረው የመልእክታቸው ክፍል ጥቂቱ ብቻ ነበር። እነዚህ ታሪካዊ ድርጊቶች ለመጀመሪያዎቹ ሰሚዎች ወደፊት የሚፈጸሙ ቢሆኑም፥ ዛሬ ግን ለእኛ ያለፉ ታሪኮች ናቸው፤ ስለዚህ ከነቢያት መጻሕፍት መካከል እስካሁን ድረስ ያልተፈጸሙ ትንቢቶች ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው። ብዙ ሰዎች የነቢያትን መጻሕፍት በተሳሳተ መንገድ የሚተረጕሙት ስለ እነርሱ ያላቸው አስተሳሰብ በዚህ ዓይነት የተሳሳተ ስለሆነ ነው። ለዚህም ጉዳይ ምቹ ሁኔታ የፈጠረው ስለ ወደፊት ሁኔታ ለማወቅ ከፍ ያለ ጒጒት ያላቸው ብዙ ክርስቲያኖች በመኖራቸው ነው። እነዚህ የትንቢት መጻሕፍት ወደፊት ስለሚሆኑ ነገሮች ግልጽ የሆነ አስተዋጽኦ እንደሚሰጡ ይገምታሉ። የትንቢት መጻሕፍት ሕይወታቸውን እንዴት መለወጥ እንዳለባቸውና ለእግዚአብሔር ክብር እንዴት እንደሚኖሩ የሚያሳዩ ከመሆን ይልቅ፥ ወደፊት ስለሚሆኑ ነገሮች ግምታዊ ሙከራ ለማድረግ የሚጠኑ መጻሕፍት ይመስሏቸዋል። ይህ አመለካከት ከመጠን ያለፈ ግምታዊ ነገር ውስጥ እንድንገባና የተሳሳቱ ትርጕሞችን እንድንሰጥ ያደርገናል። አንዳንድ ክርስቲያኖች ክርስቶስ በዚህ ዓመተ ምሕረት፥ በዚህ ቀን ይመጣል በማለት ይናገራሉ። ወይም ከመንግሥታት መሪዎች መካከል አንዱን «እርሱ ሐሰተኛው ክርስቶስ ነው» ይላሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ወደፊት ሁኔታዎች ሲናገር ግልጽ ያልሆነውን ያህል ግልጽ ለማድረግና ራሳቸውን ደስ ለማሰኘት ዝርዝር ጉዳዮች ውስጥ በመግባት ትርጓሜ ለመስጠት ይሞክራሉ። ይህን በማድረጋቸውም ብዙ ጊዜ ይሳሳታሉ። የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) በነቢያት መጻሕፍት ላይ የዚህ ዓይነት አመለካከት ሲንጸባረቅ ያየኸው እንዴት ነው? ለ) የዚህ ዓይነት አመለካከት ያላቸው ክርስቲያኖች ብዙ ጊዜ የሚያደርጉት ትንበያ (ቅድመ ምልከታ) ምን ዓይነት ነው? ሐ) የተሳሳተ ትንበያ ወይም ትርጕም ቤተ ክርስቲያንና ክርስቲያኖች በዓለም ፊት ያላቸውን ገጽታና አመለካከት የሚያበላሸው እንዴት ነው? የቤተ ክርስቲያን መሪዎች እንደ መሆናችን መጠን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለነቢያት መጻሕፍት የሚሰጡ ከእውነት የራቁና የተሳሳቱ አተረጓጐሞች የሚያስከትሏቸውን አደገኛ ሁኔታዎች ተረድተን ጥንቃቄ ማድረግ አለብን። ሰዎች ኢየሱስ የሚመጣው በዚህ ቀን ነው እያሉ ሲናገሩ ይህ ሌሎች ክርስቲያኖችን ይረብሻቸዋል። በክርስትና ሕይወት ውስጥ ከሁሉም በላይ አስፈላጊ የሆኑ እንደ መመስከርና ማስተማር የመሳሰሉ ነገሮችን እንዲዘነጉ በማድረግ በእምነታቸው ሰነፎች ያደርጋቸዋል። እንዲሁም ከእውነት የራቀ አተረጓጐም በዓለም ፊት የቤተ ክርስቲያንን ስም የሚያጎድፍ ነው። የኢየሱስ ወንጌል በኃይል እንዲነገር መንገድ ከመክፈት ይልቅ ወንጌልን መሳለቂያ ያደርገዋል። ኢየሱስ በቅርብ ይመጣልና መዘጋጀት ያስፈልጋል በሚለው አሳብ ላይ የሚሳለቁ ብዙ ሰዎች አሉ። ምክንያቱም ክርስቲያኖች ትንቢትን በተሳሳተ መንገድ ተጠቅመው ኢየሱስ በዚህ ቀን ይመጣል የሚል ቃል በመናገራቸው ነው። ከማንኛውም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ይልቅ በተሳሳተ መንገድ የመተርጐም ዝንባሌ ያላቸው የነቢያት መጻሕፍት ናቸው። ለዚህም የተለያዩ ምክንያቶች አሉ፡- 1. አብዛኛዎቹ የነቢያት መጻሕፍት፥ በተለይም የታላላቅ ነቢያት መጻሕፍት (ለምሳሌ፡- ኢሳይያስ – ዳንኤል) የተከታታይ መልእክቶች ስብስብ ናቸው። መጻሕፍቱ ግልጽ በሆነ አስተዋጽኦ ተቀናብረው የተጻፉ አይደሉም፤ ስለዚህ በመጻሕፍቱ ውስጥ እየጐለበተ የሚሄድ የሃሳብ ሂደት ስለማናገኝ መልእክቱን መረዳት አስቸጋሪ ነው። 2. ብዙውን ጊዜ መጻሕፍቱ በተናጠል ያሉና ተያያዥነት የሌላቸው መልእክቶችን ያካተቱ ስለሆኑ አንድ ስብከት ወይም መልእክት የት ቦታ እንደሚጠቃለልና ሌላው የት እንደሚጀምር ማወቅ አስቸጋሪ ነው። ነቢያቱ መጻሕፍቱን በጻፉበት ጊዜ የምዕራፍና ቍጥር ክፍፍል እንዳልነበረ ማስታወስ አስፈላጊ ነው። የምዕራፍ ክፍፍል ሰዎች ለመጻሕፍቱ አስተዋጽኦ ለማበጀት ያደረጉት ሙከራ ነው። አንዳንድ ጊዜ ግን እንደ አጋጣሚ ሆኖ ጸሐፊው ባቀረበው መልእክት ወይም ስብከት አንጻር ሳይሄዱ ይቀራሉ። በዚህም ምክንያት የመልእክቱን ተዛማጅነትና የአሳብ ሂደት እናጣለን። 3. አብዛኛዎቹ መልእክቶች የሰፈሩት በጊዜ ቅደም ተከተል መሠረት አይደለም። የዚህን እውነትነት በተለይ የምናየው በትንቢተ ኤርምያስ ሲሆን፥ መልእክቶቹ አንድ ንጉሥ ከነበረበት ዘመን ወደ ሌላ ንጉሥ ዘመን ያለምንም የታሪክ ቅደም ተከተል ሲሸጋገሩ እንመለከታለን።  የውይይት ጥያቄ፥ ኤርምያስ 1፡1-3፤ 25፡1፤ 26፡1፤ 27፡1፤ 34፡1፤ 36፡1፤ 40፡1-2፤ 45፡1 ተመልከት። ሀ) ኤርምያስ የተነበየው በእነማን ዘመነ መንግሥት ነበር? ለ) ከዚህ ቀደም ከምታውቀው የነገሥታቱ ዘመነ መንግሥት ቅደም ተከተል አንጻር እነዚህን ምዕራፎች በጊዜ ቅደም ተከተል አስፍራቸው። 4. ብዙውን ጊዜ እነዚህ ትንቢቶች በተሰጡባቸው ጊዜያት የተፈጸሙትን ታሪካዊ ድርጊቶች አናውቅም። ብዙዎቹ ትንቢቶች (መልእክቶች) በዘመኑ ለተፈጸሙ ለተወሰኑ ታሪካዊ ድርጊቶች ምላሽ ይሆኑ ዘንድ የተሰጡ ነበሩ (ለምሳሌ፡- ኢሳይያስ 9)። ነገር ግን ለአብዛኛዎቹ ትንቢተች ያ ድርጊት ምን ግንኙነት እንደነበረው አናውቅም። ስለዚህ ትንቢተቹን በሚመለከት ግልጽ የሆነ ታሪካዊ ሥረ መሠረት የለንም። 5. አብዛኛዎቹ ትንቢተች የተሰጡት በተራ ቋንቋ ሳይሆን በግጥም መልክ ነው። በጥንት ዘመን ጸሐፊዎች በዚህ መንገድ መጻፍ ይመርጡ የነበረው ሰዎች መልእክቱን ለማስታወስ ይቀላቸው ስለነበረ ነው። (ለምሳሌ፡- የመልእከት ወይም የስብከት ቃላትን ከማስታወስ ይልቅ የመዝሙር ቃላትን ማስታወስ ይቀላል።) ስለዚህ ነቢያት ብዙ ጊዜ የጻፉት በርካታ ተምሳሌታዊውን መግለጫዎችን በመጠቀም በግጥም መልክ ነበር። አንዳንድ ጊዜ ተምሳሌታዊውን ቋንቋ ከቀጥተኛ ትንቢታዊ አነጋገር መለየት አስቸጋሪ ነው። 6. መልእክቱ በመጀመሪያ ለደረሳቸው ሰሚዎች ግልጽ ቢሆንም እንኳ መልእክቱ በተሰጠበትና እኛ በምንኖርበት ዘመን መካከል የብዙ መቶ ዓመታት ልዩነት ስላለ በባህላችን ማለትም በሃይማኖታዊ፥ በታሪካዊና በልማዳዊ ዘይቤያችን በጣም የተለያየን ስለሆንን እነዚህን ትንቢቶች የመተርጐም አስቸጋሪነት እየጨመረ ይሄዳል።  የትንቢት መጻሕፍትን ለመተርጐም የሚጠቅሙ መመሪያዎች  አንድን የትንቢት መጽሐፍ ክፍል በትክክል ለመተርጐም በምትሞክርበት ጊዜ የሚከተሉትን መመሪያዎች አስታውስ፡- 1. የትርጕም አካሄዱን ለመረዳት ክፍሉን በጥንቃቄ አጥና። ትንበያ ከሚመስል ቍጥር አትጀምር። ይልቁንም ክፍሉን በሙሉ አንብብ። ያንን የተለየ ክፍል ለመረዳት በዙሪያው ያሉ አሳቦች ይረዱህ እንደሆነ ለመመልከት ከክፍሉ በኋላና በፊት ያሉትን ምዕራፎች አንብብ። ከተቻለ የመጽሐፉን አጠቃላይ ትምህርት ለመረዳት መጽሐፉን በሙሉ አንብብ። ቀጥለህ የሚከተለውን ጥያቄ ጠይቅ፡- «ይህ ክፍል ከመጽሐፉ አጠቃላይ ትምህርት ጋር የሚዛመደው እንዴት ነው?»  2. ግልጽ ያልሆኑልህን አሳቦችና ቃላት ዘርዝር። እነዚህ ቃላት ወይም አሳቦች ምን ማለት እንደሆነ ለመረዳት የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላትን ወይም ማብራሪያን ተመልከት። ተምሳሌታዊ መግለጫዎች በሚኖሩበት ጊዜ መግለጫዎቹ መጀመሪያ ለተጻፈላቸው ሰዎች ምን ማለት እንደሆነ ተረዳ። ቀጥሎ ከባህልህ ወይም በዚህ ዘመን ካሉ ነገሮች ለዚህ ተምሳሌታዊ መግለጫ አቻ የሆነ ነገር ፈልግ (ለምሳሌ፣ ጦሮችና ሰረገላዎች በዚህ ዘመን ባሉ ጠመንጃዎችና ታንኮች ሊመስሉ ይችላሉ)። 3. መልእክቱ የቀረበው በግጥም መሆኑን ልብ በል። ስለሆነም ትንቢቱን ለመተርጐም ለግጥምና ለቅኔ አተረጓጐም የሚረዱ ሕግጋትን ተጠቀም። 4. የክፍሉን ዋና ዋና አሳቦች (ትምህርቶች) በሙሉ ዘርዝር። በክፍሉ ውስጥ የአሳብ መጐልበት መኖሩን ለማሳየት በሚያስችል መንገድ በዝርዝር ግለጻቸው።  5. ክፍሉ የተጻፈበትን ጊዜ ታሪካዊ ሁኔታ ለመወሰን ሞክር። ምን በመፈጸም ላይ ነበር? ድርቅ ነበርን? ጦርነት ነበርን? ባቢሎናውያን አይሁድን ይወጉ ነበርን? ከመጽሐፈ ነገሥትና ዜና መዋዕል ስለ ዘመኑ ለማንበብ ሞክር። እነዚህ ነቢያት በነበሩበት ዘመን በእስራኤል ብዙ ችግሮች እንደነበሩ አስታውስ። የሕዝቡን ሕይወት ያጐሳቆሉ ከፍተኛ ጦርነቶች ነበሩ። በእስራኤልና በይሁዳ መካከል የእርስ በርስ ጦርነቶች ነበሩ። ከሶርያውያን፥ ከአሦራውያንና ከባቢሎናውያን ጋር የተደረጉ ብሔራዊ ጦርነቶች ነበሩ። ከሕዝባቸው አብዛኛው ክፍል በሌሎች ሕዝቦች ተማረኩ። ከግዛታቸው አብዛኛው ክፍልም ተወሰደባቸው። ብዙ ሕዝብ ባህላዊ እምነታቸው የሆንውን አንድ አምላክ እግዚአብሔርን ትተው የተለያዩ ጣዖታትንና የተቀረጹ ምስሎችን ያመልኩ ስለነበር በአይሁድ ሕዝብ መካከል ክሕደት ተስፋፍቶ ነበር። የውይይት ጥያቄ፥ አይሁድ የነበሩበትን ታሪካዊ ሁኔታ ማወቅ ነቢያትንና እነርሱ ያመጡአቸውን ልዩ መልእክቶች አስፈላጊነት ለመረዳት ምን ያህል የሚጠቅም ይመስልሃል? 6. በዚያ ክፍል ውስጥ ነቢዩ ለአይሁድ ሊያስተምር የሞከረውን ዋናውን መልእክት ለማግኘት ሞክር። ትንቢት የሚሰጥበት ዋና ምክንያት ስለ ወደፊቱ ሁኔታ ለሰዎች ለመናገር አይደለም። ይልቁንም ሰዎችን ለማበረታታት፥ ለመገሠጽና ለማስጠንቀቅ ነበር፤ የክፍሉ ዋና መልእክት ይህ ነው። ስለ እግዚአብሔር ምን ያስተምረናል?

ትንቢትን ለመተርጐም የሚጠቅሙ መመሪያዎች Read More »

ነቢያትና ትንቢቶች

የውይይት ጥያቄ፥ «ነቢይ» ማለት ምን ማለት ነው? ይህንን ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ውስጥ በመመልከት ነቢይ ምን እንደሆነና ምን እንደሚሠራ የሚያመለክት አጭር መግለጫ ጻፍ።  የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ዛሬ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ነቢያት አሉን? ለ) ካሉ፥ የሚሠሩት ምንድን ነው? ነቢያት እንዳሉ የምናውቀውስ እንዴት ነው? ሐ) ከብሉይና ከአዲስ ኪዳን ነቢያት የሚለዩት ወይም የሚመሳሰሉት በምንድን ነው? የትንቢት መጻሕፍት ብዙ ጊዜ በተሳሳተ መንገድ ይተረጐማሉ። ለዚህ ዋናው ምክንያት በነቢዩ ማንነትና በሚሠራው ሥራ ረገድ የተምታታ ነገር ስላለ ነው። ስለ ነቢዩና ስለሚናገረው ትንቢት በምናስብበት ጊዜ በሁላችን አእምሮ የሚቀረጹ የተለያዩ ምስሎች አሉ። ብዙውን ጊዜ ነቢይ ወደፊት ስለሚሆነው ነገር የማመልከት ችሎታ ያለው ሰው የሆነ ይመስለናል። የብሉይና የአዲስ ኪዳን ነቢያት ዋና ተግባር ይህ የሆነ ይመስለናል። ይህም ነገር ሰዎችን ዛሬ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ነቢያት አሉን? የሚል ጥያቄ አሳድሮባቸዋል፤ ብዙዎችንም እንዲደነቁ አድርጓቸዋል። በአዲስ ኪዳን ውስጥ መንፈስ ቅዱስ ለሰዎች የትንቢትን ስጦታ እንደሚሰጥ እናነባለን (1ኛ ቆሮ. 12፡28፤ ኤፌሶን 4፡11 ተመልከት)። ይህ ስጦታ ለቤተ ክርስቲያን ከተሰጡ እጅግ አስፈላጊ ስጦታዎች አንዱ ሲሆን፥ ቤተ ክርስቲያን ከተመሠረተችባቸው መሠረቶች አንዱ ክፍል ነው። በአሁኑ ዘመን ነቢይ የሚመስሉ ሰዎች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ቢኖሩም፥ ነቢይ ማን እንደሆነና ምን እንደሚሠራ ስላለን ግንዛቤ ከፍተኛ ጥንቃቄ ልናደርግ ይገባል። በተጨማሪ በዚህ ዘመን ያሉትን ነቢያት ሥልጣን በብሉይ ኪዳን ዘመን የእግዚአብሔርን ቃል ያለ ምንም ስሕተት ይናገሩ ከነበሩ ሰዎች ጋር እንዳናስተካክል ልንጠነቀቅ ይገባል። እንዲያውም አንዳንዶች የአዲስ ኪዳን ዘመን ነቢያት በብሉይ ኪዳን ዘመን እንደነበሩ ነቢያት መለኮታዊ የመንፈስ ቅዱስ ምሪት እንደነበራቸው ተደርገው እንዳልታዩ ይናገራሉ። ብዙ ጊዜ የነቢያት ሥራ ስለ ወደፊቱ ጉዳይ መናገር የሆነ ይመስለናል፤ ስለዚህ የትንቢት መጻሕፍት በምናጠናበት ጊዜ፥ ስለ ወደፊቱ የተነገረ ሰፊና ጥልቅ አሳብ እንፈልጋለን። በአመዛኙ ክርስቲያኖች የትንቢትን መጻሕፍት በሚመለከቱበት ጊዜ፥ የሚያነቡትን ነገር የኢየሱስን ምጽአት ወይም የዘመናት መጨረሻን በሚያመለክት መልኩ የሚተረጉሙባቸውን መንገዶች ይፈልጋሉ። እነዚህን ጉዳዮች የሚያመለክቱ ትንቢቶች ቢኖሩም እንኳ የብሉይ ኪዳን ትንቢቶች በአብዛኛው የሚናገሩት ስለ ኢየሱስ ወይም ስለ እኛ የወደፊት ሁኔታ አይደለም። አንዳንድ ምሁራን እንደሚገምቱት፥ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚናገሩ የብሉይ ኪዳን ትንቢቶች ከ2 በመቶ አይበልጡም። ኢየሱስ ከተወለደ በኋላ ስላሉት ጊዜያት የሚናገሩት ትንቢቶች ከ5 በመቶ በታች ናቸው። ከ1 በመቶ ያነሱት ደግሞ ዛሬ እኛም ብንሆን ገና ወደፊት ይፈጸማሉ የምንላቸው ናቸው። የብሉይ ኪዳን ነቢያት ስለ ወደፊቱ ሁኔታ አስታውቀዋል፤ ነገር ግን ይህ ብዙ ጊዜ ለእስራኤል ልጆችና በአካባቢያቸው ለነበሩት መንግሥታት የቅርብ ጊዜ አመልካች መልእክት ነበር፤ ስለዚህ ከእነዚህ የትንቢት መጻሕፍት የምናገኛቸው አብዛኛዎቹ ትንቢቶች በብሉይ ኪዳን ዘመን ከነበረችው እስራኤል ጋር የሚዛመዱ እንጂ ስለ እኛ ወደፊት ሁኔታ የሚናገሩ አይደሉም። ነቢይ ምንድን ነው? በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ፥ ነቢይ የእግዚአብሔርን መልእክት ለሰዎች የሚያስተላልፍ ሰው ነው። አብዛኛውን ጊዜ መልእክቱ ያተኩረው በሕዝቡ ወቅታዊ ፍላጎት ላይ ነበር። ነቢያት የእግዚአብሔር መልእክተኞች ሆነው እስራኤል ከእግዚአብሔር ጋር የገቡትን ቃል ኪዳን መታዘዝ እንዳለባቸው፥ ካልታዘዙ ግን ያለመታዘዛቸውን ውጤቶች የሚቀበሉ መሆናቸውን የሚያሳስቡ ነበሩ። ነቢያት ሕዝቡ ንስሐ እንዲገቡና ለቃል ኪዳኑ እንዲታዘዙ ለማድረግ የሚጥሩ የእግዚአብሔር አፈ-ቀላጤዎች ነበሩ። በቃል ኪዳኑ የተመለከተው ፍርድ እንደሚመጣባቸው የሚያስጠነቅቁ ነበሩ፤ ወይም ደግሞ የእግዚአብሔር ልጆች ለቃል ኪዳኑ ታዛዥ ሆነው በሚኖሩበት ጊዜ ስለሚቀበሉት በረከት ይናገሩ ነበር። የነቢያት አገልግሎት ከእግዚአብሔር ርቆ የሄደው ሕዝብ ወደ እግዚአብሔር እንዲመለስ ማነቃቃትን አጥብቆ የሚሻ ነበር። ነቢያት ወደዚህ አገልግሎታቸው የመጡት በገዛ ፈቃዳቸው ሳይሆን፥ ጥሪውን ከእግዚአብሔር ተቀብለው ነበር (ለምሳሌ፡- ኢሳይያስ 6፤ ሕዝቅኤል 1-3)። ስለዚህ ነቢያት ብዙ ጊዜ የሚናገሩት እግዚአብሔር እንደሚናገር ሆነው የእግዚአብሔርን ድምፅ በመጠቀም ነበር። (እግዚአብሔር ራሱ እንደተናገራቸው እንጂ ነቢዩ እንዳልተናገራቸው የሚመስሉ ትንቢቶች ምን ያህሉ እንደሆኑ አስተውል።) ነቢያት ስለ ወደፊት ሁኔታዎች የሚናገሩት አልፎ አልፎ ብቻ ነበር። አብዛኛዎቹ ትንቢተቻቸው በእስራኤላውያን ላይ በቅርብ ጊዜ ስለሚሆኑ ነገሮች የሚያመለክቱ ነበሩ፤ ለምሳሌ አብዛኛዎቹ የብሉይ ኪዳን ትንቢቶች እስራኤል በአሦር፥ ይሁዳ ደግሞ በባቢሎን ስለ መደምሰሳቸው ወይም ደግሞ ስለ ሕዝቡ ከምርኮ መመለስ የተነገሩ ነበር። ስለ ኢየሱስ መምጣትና ስለ ዘመኑ ፍጻሜ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የሚናገሩ ጥቂት ትንቢቶች ነበሩ። እነዚህን በረዥም የጊዜ ሂደት ውስጥ የሚፈጸሙ ትንቢቶች በመስጠት ረገድ የእግዚአብሔርና የነቢያቱ መሠረታዊ ፍላጎት የእስራኤልን ሕዝብ ማስተማር ነበር። እግዚአብሔር በታሪክና በእነርሱ ሕይወት ውስጥ ያለውን የበላይ ተቈጣጣሪነት እንዲመለከቱ ይፈልግ ነበር። ስለሚመጣው ፍርድ ተረድተው እንዲጠነቀቁና በመጨረሻም ስለሚያገኙት በረከት በማሰብ እንዲነቃቁ ይፈልግ ነበር። ትንቢቶች ወደፊት ስለሚሆኑ ነገሮች ዝርዝር መግለጫዎችን ይሰጣሉ ማለት አይደለም፤ ነገር ግን አሁን እግዚአብሔርን በሚያስከብር መንገድ ስለ መኖር የሚያስተምሩን ናቸው። ስለ ወደፊት ሁኔታዎች ለማወቅ ያለንን ጕጕት ለማርካት የተሰጡ አይደሉም። አንዳንድ ክርስቲያኖች በትንቢቶች አተረጓጐም ረገድ ግምታዊ አስተያየት በመስጠት፥ ኢየሱስ በዚህ ጊዜ መመለስ አለበት፤ ወይም ሐሰተኛው ክርስቶስ ይህ ወይም ያ ሰው ነው ማለታቸው ፍጹም ስሕተት ነው። ይህ ስለ ትንቢት የተዛባ ትርጕም መስጠት ነው። እግዚአብሔር ለጥንት ነቢያት መልእክቱን ያስተላለፈው እንዴት ነበር? በአንድ የተወሰነ መንገድ ወይም ዘዴ አልተጠቀመም። ለአንዳንዶች መልእክቱን በሕልም ወይም በራእይ ተናግሯል። (ለምሳሌ፣ ለዳንኤል)። ለሌሎች ደግሞ በጥሞና በነበሩበት ጊዜ እግዚአብሔር የተለያዩ ነገሮችን በማሳየት መልእክቱን አስተላልፏል (ለምሳሌ፣ ለሐዋርያው ዮሐንስ በፍጥሞ ደሴት)። ዳሩ ግን እግዚአብሔር በአብዛኛው የተናገረበት መንገድ «እግዚአብሔር እንዲህ ይላል» በማለት መልእክቱን በእርግጠኛነት እንዲያስተላልፉ ለነቢያቱ በቀጥታ በመናገር ነበር ( ለምሳሌ፣ 2ኛ ነገሥት 20፡4-6)። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የምናያቸው ያተኮሩት የወደፊቱን ሁኔታ በሚቈጣጠርና መልእክቱን ለነቢዩ በሚሰጠው በእግዚአብሔር ላይ እንጂ፥ በነቢዩ ላይ አይደለም። መልእክቱን የሚያዘጋጁት ነቢያት አልነበሩም፤ መልእክቱ የእግዚአብሔር ሲሆን፥ ነቢያት እግዚአብሔር መልእክቱን ለሕዝቡ የሚያስተላልፍባቸው መሣሪያዎች ብቻ ነበሩ። እነዚህ ነቢያት የእግዚአብሔርን አመለካከት፥ ለተለያዩ ጉዳዮች የሚሰጣቸውን ምላሾች አሳቡንና ዕቅዱን ለእነርሱ በገለጠላቸው መንገድ ያቀርቡ ነበር፡፡ ስለዚህ የሚኮሩበትና የሚታበዩበት አንዳችም ምክንያት አልነበራቸውም። የውይይት ጥያቄ፥ ይህ ነቢያትን የሚመለከት ትምህርት ብዙ ሰዎች በዘመናችን ስለ ነቢያትና መልእክቶቻቸው ካላቸው አሳብ የሚለየው እንዴት ነው? በብሉይ ኪዳን ውስጥ፥ የነቢያት ሥራ እግዚአብሔር ከእስራኤላውያን ጋር በሲና ተራራ ካደረገው ቃል ኪዳን ጋር በቅርብ የተሳሰረ ነበር። አብዛኛው ትምህርታቸው (መልእክታቸው) በይዘት አዲስ አልነበረም። ይልቁንም እግዚአብሔር በቃል ኪዳኑ የሰጣቸውን የእርግማንና የበረከት አይቀሬነት በተለየ መንገድ አጠናክረው የሚያውጁ ነበሩ። የውይይት ጥያቄ፥ ዘዳግም 28-32 አንብብ። ሀ) በቃል ኪዳኑ ውስጥ የሚገኙት አንዳንድ በረከቶች ምን ነበሩ? ለ) ከእነዚህ አንዳንዶቹ በእስራኤል ሕዝብ ታሪክ ውስጥ የተፈጸሙት እንዴት ነበር? ሐ) በቃል ኪዳኑ ውስጥ ይገኙ ከነበሩት መርገም አንዳንዶቹን ጥቀስ። መ) ከእነዚህ አንዳንዶቹ በእስራኤል ሕዝብ ታሪክ ውስጥ የተፈጸሙት እንዴት ነበር? እነዚህ ነቢያት መልእክታቸውን የተቀበሉት በቀጥታ ከእግዚአብሔር ነበር። ሆኖም ከተናገሯቸው ነገሮች መካከል አብዛኛዎቹ በሙሴ ሕግ፥ በተለይም ባለመታዘዝ ስለሚመጣው መርገምና በመታዘዝ ስለሚገኝ በረከት በሚናገረው በቃል ኪዳኑ ክፍል ውስጥ የሚገኙ ነበሩ። በሕግ መጻሕፍት ውስጥ በሚገኘው ቃል ኪዳኑ እግዚአብሔር ለሚታዘዙት ሁሉ በረከትን እንደሚሰጥ ቃል ገብቷል። እነዚህ ሰረከቶች ሕይወት፥ ጤንነት፥ ብልጽግና፥ በእርሻ ፍሬያማ መሆን፥ የደኅንነት ዋስትናና በአሕዛብ መካከል የክብር ስፍራ ማግኘትን የሚጨምሩ ነበሩ። እስራኤል እግዚአብሔርን በታዘዘች ቍጥር ይህ ነገር ሲፈጸም እንመለከታለን (ለምሳሌ፣ የዳዊትና የሰሎሞን ዘመነ መንግሥት)። በፍርድ መልክ የተደነገጉት መርገሞች በሕዝቡ ሁሉ ላይ የሚደርሱ ነበሩ። ያለመታዘዝ ምትን፥ በሽታን፥ ድርቅን፥ አደጋን፥ ጥፋትን፥ በጠላቶች ድል መመታትን፥ በምርኮ መጋዝንና ውርደትን ያስከትል ነበር። የነቢያትን መልእክት በጥንቃቄ በምንመረምርበት ወቅት ከመልእክታቸው አብዛኛው ክፍል በእነዚህ በረከቶች ወይም መርገሞች ላይ የሚያተኩር እንደነበር ለማየት እንችላለን። የነቢያት መልእክቶች በሕግ ውስጥ የሚገኙት መርገሞች በእስራኤል ሕዝብ ላይ ሊደርሱ እንደተቃረቡ ያመለክቱ ነበር። በቃል ኪዳኑ ውስጥ የተሰጡት በረከቶች በሙላት የሚፈጸሙበትን የወደፊቱንም ጊዜ አመልክተዋል። በ586 ዓ.ዓ. የሆነው ምርኮ እስከተፈጸመበት ጊዜ ድረስ የአብዛኛዎቹ ነቢያት መልእክቶች ስለ ጥፋት የሚናገሩ ነበሩ። ከምርኮ በኋላ የነበሩት አብዛኛው የነቢያት መልእክቶች ደግሞ በወደፊት በረከቶች ላይ ያተኮሩ የማበረታቻ መልእክቶች

ነቢያትና ትንቢቶች Read More »

የትንቢት መጻሕፍት አጠቃላይ ገጽታ

በብሉይ ኪዳን ጥናታችን እስካሁን ሦስት ዋና ክፍሎችን ተመልክተናል። በመጀመሪያ፥ ፔንታቱክ በመባል የሚታወቁትን አምስቱን የመጀመሪያ መጻሕፍት ተመልክተናል። እነዚህ አምስት መጻሕፍት በይበልጥ ስለተመረጠው የእግዚአብሔር ሕዝብ ጅማሬ ማለትም ስለ አይሁድ የሚናገሩ ናቸው። እግዚአብሔር ከእስራኤል ሕዝብ ጋር በሲና ተራራ ስላደረገው ቃል ኪዳን ይናገራሉ። ይህ ቃል ኪዳን የቀሩትን የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ሁሉ ለመረዳት መሠረት የሚጥል ነው። በሁለተኛ ደረጃ፥ የእስራኤል ሕዝብ ወደ ተስፋዪቱ ምድር ከገቡበት ጊዜ ጀምሮ ወደ ባቢሎን በምርኮ ተወስደው ከቆዩ በኋላ እስከተመለሱበት፥ እስከ ነህምያ ዘመን ድረስ ያለውን፥ ታሪካቸውን የሚናገሩትን አሥራ ሁለት መጻሕፍት ተመልክተናል፡፡ እነዚህ የታሪክ መጻሕፍት እግዚአብሔር በሲና ተራራ ከእስራኤላውያን ጋር የገባውን ቃል ኪዳን በታዘዙበትና ባልታዘዙበት ወቅት ስላጋጠሙዋቸው ነገሮች የሚናገሩ ናቸው። ከእነዚህ የታሪክ መጻሕፍት በግልጽ እንደምንመለከተው፥ እስራኤላውያን በሲና ተራራ በተሰጣቸው ቃል ኪዳን ውስጥ የተዘረዘረው ፍርድ የደረሰባቸው በተቀበሉት ቃል ኪዳን መሠረት ለመኖር ባለመቻላቸው ነበር። በሦስተኛ ደረጃ የተመለከትነው፥ አምስቱን የግጥምና የቅኔ ወይም የጥበብ መጻሕፍት ነው። እነዚህ መጻሕፍት አምልኮ እንዴት መከናወን እንዳለበትና እግዚአብሔር ከእስራኤላውያን ጋር ያደረገውን ቃል ኪዳን በማክበር እንዴት መኖር እንደሚቻል ያስተምሩናል። የውይይት ጥያቄ፥ አሥራ ሰባቱን የትንቢት መጻሕፍት ዘርዝር። በብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ክፍፍል ውስጥ፥ የመጨረሻውና እጅግ ሰፊ የሆነው ከኢሳይያስ እስከ ሚልክያስ ያለው አሥራ ሰባቱን የትንቢት መጻሕፍት የያዘው ክፍል ነው። እነዚህን የትንቢት መጻሕፍት ለመከፋፈል ሦስት የተለያዩ መንገዶች አሉ፡- 1. በመጀመሪያ፥ እነዚህን መጻሕፍት በሁለት ዋና ዋና ክፍሎች ልንከፍላቸው እንችላለን። የመጀመሪያው ክፍል ታላላቅ ነቢያት በመባል ይታወቃል። ይህ ክፍል ከኢሳይያስ እስከ ዳንኤል ያሉትን የመጀመሪያዎቹን አምስት የትንቢት መጻሕፍት የያዘ ነው። ሰቆቃወ ኤርምያስ በዚህ ክፍል ውስጥ የተመደበው ከትንቢተ ኤርምያስ ጋር በቅርብ የተያያዘ ስለሆነ ነው። እነዚህ መጻሕፍት የታላላቅ ነቢያት መጻሕፍት የተባሉት ከቀሩት የነቢያት መጻሕፍት ይልቅ የበለጠ ጠቃሚና አስፈላጊ ስለሆኑ ሳይሆን፥ ረጃጅምና መልእክታቸው ከሌሉቹ መጻሕፍት የበለጠ በዝርዝር የቀረበ በመሆኑ ብቻ ነው። ሁለተኛው ክፍል ታናናሽ ወይም የአሥራ ሁለቱ ነቢያት መጻሕፍት በመባል ይታወቃል። እነዚህም ከሆሴዕ እስከ ሚልክያስ የሚገኙትን አሥራ ሁለት የነቢያት መጻሕፍት የሚያጠቃልሉ ናቸው።  2. በሁለተኛ ደረጃ፥ እነዚህን የነቢያት መጻሕፍት ነቢያቱ ባገለገሉባቸው ሦስት ዐበይት የታሪክ ወቅቶች ልንከፋፍላቸው እንችላለን።  ሀ. የእስራኤል መንግሥት ለሁለት ከተከፈለ በኋላና ከምርኮ በፊት ያገለገሉ ነቢያት፡- እነዚህ ነቢያት ቅድመ-ምርኮ ነቢያት በመባል ይታወቃሉ። አብዛኛዎቹ ነቢያት በሚከተለው ክፍል የሚመደቡ ናቸው፡- ኢሳይያስ፣ ኤርምያስ፣ ሰቆቃወ ኤርምያስ፥ ሆሴዕ፥ አሞጽ፥ ሚክያስ፥ ኢዩኤል፥ አብድዩ፥ ዮናስ፥ ናሆም፥ ዕንባቆም፥ ሶፎንያስ። ለ. እስራኤላውያን በምርኮ ምድር በነበሩበት ጊዜ ያገለገሉ ነቢያት፡ እነዚህ ነቢያት የምርኮ ነቢያት በመባል ይታወቃሉ። በዚህ ወቅት ያገለገሉት ሁለት ነቢያት ሕዝቅኤልና ዳንኤል ናቸው።  ሐ. እስራኤላውያን 70 ዓመታት በባቢሎን ምርኮ ቆይተው ከተመለሱ በኋላ ያገለገሉ ነቢያት፡- እነዚህ ነቢያት ድኅረ ምርኮ ነቢያት በመባል ይታወቃሉ። በዚህ ወቅት ያገለገሉት የመጨረሻዎቹ ሦስት ነቢያት ሐጌ፥ ዘካርያስና ሚልክያስ ናቸው።  3. አንዳንድ ጊዜ እነዚህ ነቢያት በተለያዩ ክፍሎች የሚመደቡበት ምስተኛው መንገድ ነቢያቱ ባገለገሉባቸው ወይም ትንቢት በተናገሩባቸው አገሮች ነው።  ሀ. ለሰሜኑ የእስራኤል መንግሥት ያገለገሉ ነቢያት፡- እነዚህ እስራኤልን ያገለገሉ ነቢያት ሆሴዕና አሞጽ ነበሩ።  ለ. ለደቡቡ የይሁዳ መንግሥት ያገለገሉ ነቢያት፡- አብዛኛዎቹ የቅደመ-ምርኮ ነቢያት የሚመደቡት በዚህ ክፍል ነው። እነዚህም ኢሳይያስ፥ ኤርምያስ ከሰቆቃወ ኤርምያስ ጋር፥ ኢዩኤል፥ ሚክያስ ዕንባቆምና ሶፎንያስ ናቸው።  ሐ. ለአሕዛብ መንግሥታት ያገለገሉ ነቢያት፡- ዮናስና ነህምያ በአሦር፥ አብድዩ ደግሞ በኤዶም ላይ ትንቢት ተናግረዋል። እነዚህ ነቢያት አይሁድ ሲሆኑ፥ መልእክታቸው ግን በይበልጥ ያተኮረው በአሕዛብ ላይ ነበር።  መ. በምርኮ ለነበሩ አይሁድ ያገለገሉ ነቢያት:- እነዚህ ሕዝቅኤልና ዳንኤል ነበሩ።  ሠ. ከምርኮ ለተመለሱ አይሁድ ያገለገሉ ነቢያት፡- የመጨረሻዎቹ ሦስቱ ነቢያት ሐጌ፥ ዘካርያስና ሚልክያስ ከባቢሎን ተመልሰው በይሁዳ ምድር ከተቀመጡ አይሁድ ጋር የሠሩ ናቸው።  ሁለተኛ፣ ከነቢያት አብዛኛዎቹ ያገለገሉት በተመሳሳይ ጊዜ መሆኑ፡፡ ዮናስ፣ አሞጽና ሆሴዕ በሰሜን እስራኤል ያገለገሉት ኢሳይያስና ሚኪያስ በይሁዳ ሳልገሉበት ዘመን ነበር። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ደግሞ ኤርምያስ፣ ዕንባቆምና ምናልባትም አብድዩ በይሁዳ ያገለገሉት በተመሳሳይ ጊዜ ነበር። ሦስተኛ፣ እነዚህ ጊዜያት ግምታዊ ስለሆኑ አንዳንድ ማብራሪያዎች የተለዩ ጊዜያት ሊሰጡ ይችላሉ። የአንዳንድ የትንቢት መጻሕፍትን በሚመለከት የተጻፉበትን ጊዜ ለመወሰን የምናገኛቸው ታሪካዊ መረጃዎች በጣም አነስተኛ ናቸው። ምሁራን፣ በተለይ ከነቢያት መካከል ሁለቱ ኢዩኤልና አብድዩ ስላገለገሉባቸው ጊዜያት ይከራከራሉ። ስለዚህ ነው በነዚህ ጊዜያት ላይ የጥያቄ ምልክት የተደረገባቸው።  ዳንኤልና ሕዝቅኤል ያገለገሉት በተመሳሳይ ጊዜ ሲሆን፥ ሐጌና ዘካርያስ ደግሞ በተመሳሳይ ጊዜ አገለገሉ። ዳንኤልና ሕዝቅኤል አገልግሎታቸውን የጀመሩት በይሁዳ ነገሥታት በነበሩበት ጊዜ ቢሆንም፥ እነዚህ ሁለት ነቢያት የኖሩትና ያገለገሉት በባቢሎን ነበር። (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የትንቢት መጻሕፍት አጠቃላይ ገጽታ Read More »