ክርስቶስ በትንሹ እስያ ውስጥ ለነበሩ ሰባት አብያተ ክርስቲያናት ያስተላለፈው መልእክት (ራእይ 1፡9-3፡22)
እምነታችን እየደከመ ከሚሄድባቸው ምክንያቶች አንዱ ስለ ክርስቶስ ያለን ግንዛቤ እየደበዘዘ በመምጣቱ ነው። ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጆች እንሆን ዘንድ ምን ያህል ታላቅ ዋጋ እንደከፋፈለ እንዘነጋለን። የክርስቶስ መስቀል ብዙም የማያስደንቀን ልባችንን የማይሰብር ታሪክ ይሆንብናል። የክርስቶስን ታላቅነት፥ እውነታዎችን ሁሉ መቆጣጠር መቻሉንና በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተገኝቶ ሁሉንም ነገር ለማየት መቻሉን እንዘነጋለን። እርሱ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተገኝቶ ደካማና ጠንካራ ጎኖቻችን ሁሉ እንደሚያይ እንረሳለን። ክርስቶስ ሁለት ወይም ሦስት አማኞች በስሙ በተሰበሰቡት ስፍራ በመካከላቸው እንደሚገኝ ቃል ገብቷል (ማቴ. 18፡20)። በራእይ 1፡3፥ ክርስቶስ ለአማኞች ይህንኑ እውነት ያስገነዝበናል። እርሱ በአብያተ ክርስቲያናት (መቅረዞች) መካከል እየተመላለሰ ባህሪያቸውንና ተግባራቸውን በቅርብ ይከታተላል። በመካከላቸው ያለውን ታላቅ ጌታ እንዳይዘነጉ ለማሳሰብ ክርስቶስ ታላቅነቱን ለዮሐንስና ለ7ቱ አብያተ ክርስቲያናት ያሳያል። ይኸው ክርስቶስ ዛሬም በአብያተ ክርስቲያኖቻችን ውስጥ እየተመላለሰ ነው። እርሱ ከእኛ ርቆ በሰማይ የሚገኝ ብቻ ሳይሆን፥ አብሮን የሚኖር አምላክ ነው። ክርስቶስ በእኛ ውስጥ የሚያየው ምን ይሆን? የውይይት ጥያቄ፡– ሀ) ስለ ክርስቶስ ማንነትና በመካከላችን እየተመላለሰ ስለመሆኑ የጠራ ግንዛቤ ቢኖረን፥ አምልኮአችንና ተግባራችን እንዴት እንደሚለወጥ ግለጽ። ለ) ክርስቶስ በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ የሚመለከተው መልካም ነገር ምን ይመስልሃል? ሐ) ኢየሱስ ባንተ ሕይወት ውስጥ የሚያየው መጥፎና መልካም ነገር ምን ይመስልሃል? እንዲያሳይህ ለመጠየቅ አሁኑኑ ጊዜ ውሰድ። ፩. ለአብያተ ክርስቲያናት መልእክቱን ያስተላለፈው የክርስቶስ ራእይ (ራእይ 1፡9-20) ይህ የክርስቶስ ራእይ ለሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት ለሚተላለፈው መልእክቱ መሠረት ነው። ዮሐንስ የዚህን ራእይ ክፍል ለሰባቱም አብያተ ክርስቲያናት ባስተላለፋቸው መልእክቶች ውስጥ ያካትታል (ራእይ 2-3)። በዚህ የክርስቶስ ራእይ ውስጥ ዮሐንስ በሰባቱ መቅረዞች መካከል የሚጓዘው ክርስቶስ ምን ያህል ታላቅ እንደሆነ ያሳየናል። እነዚህም ሰባት መቅረዞች ሰባቱን አብያተ ክርስቲያናት የሚያመለክቱ ናቸው። ክርስቶስ አማኞች መልእክቱን ቀለል አድርገው እንዲመለከቱ አልፈለገም። ምሁራን እያንዳንዱ የራእዩ ክፍል ምን እንደሚያሳይ በሚሰጡት ትንታኔ ይለያያሉ። ነገር ግን የተላላፈው መልእክት ግልጽ ነው። የምናመልከው ክርስቶስ አፍቃሪ እና የሚመች ብቻ አይደለም። እርሱ በአብያተ ክርስቲያናቱ መካከል የሚመላለስ፥ የሚመለከትና የሚገመግም፥ እንዲሁም አብያተ ክርስቲያናቱን ለማንጻት ፍርድን የሚሰጥ ታላቅና ፈራጅ አምላክ ነው። ከዚህ ራእይ ውስጥ አንዳንድ ቁልፍ ነገሮችን ልንመለከት እንችላለን:- ሀ. ክርስቶስ የሰውን ልጅ እንደሚመስል ተገልጾአል። ዮሐንስ ክርስቶስ የዳንኤል 7፡13ን ራእይ እንደሚፈጽም ለአብያተ ክርስቲያናቱ ለማስገንዘብ ይፈልጋል። በዚህ ራእይ ውስጥ ታላቁ ሰው የእግዚአብሔርን መንግሥት ሥልጣን ከእግዚአብሔር አብ ሲቀበል እንመለከታለን (ዳን. 7፡13-14 አንብብ)። ለ) ኢየሱስ ክርስቶስ ሊቀ ካህናትና ዳኛ ነው። የክርስቶስ ልብሶች በብሉይ ኪዳን ሊቀ ካህናቱ ከሚለብሳቸው ጋር የሚመሳሰሉ ይመስላል። ስለዚህ አማኞች ክርስቶስ ሊቀ ካህናችን መሆኑን ማስታወስ ይኖርብናል። በተጨማሪም ልብሱ የሮማውያን ዳኞች የሚለብሱትን ይመስላል። ይህም አማኞች ክርስቶስ ዳኛ መሆኑንና በፊቱ ቆመው መልስ እንደሚሰጡ ያስገነዝባቸዋል። ሐ) ክርስቶስ ታላቅ አምላክ ነው። ዮሐንስ ከዳንኤልና ከሕዝቅኤል መጽሐፎች የወሰዳቸውን ተምሳሌቶች በመጠቀም ክርስቶስ ታላቅ፥ ኃያልና ቅዱስ አምላክ መሆኑን ያስረዳል። እንደ ፈራጅ፥ ቅዱስ ብርሃን የሚተፉ ዓይኖች አሉት፥ ጠላቶቹን የሚደመስስ ሰይፍም በእጁ ይዟል። መ) ክርስቶስ ታሪክን ሙሉ በሙሉ ይቆጣጠራል። እርሱ የሁሉም ነገር መጀመሪያ በመሆኑ፥ ታሪክ ሁሉ ሲጠናቀቅና ፍጥረት ሁሉ ሲጠፋ የመጨረሻው ሆኖ ይኖራል። በተጨማሪም እርሱ በሞትና በዘላለማዊ ፍርድ ላይ ሙሉ የበላይነት አለው። ስለሆነም አማኞች ሰውነታቸውን ሊገድሉ የሚችሉትን ሰዎች መፍራት አይኖርባቸውም። ነገር ግን እኛን ለመግደል የሚፈልጉትን ሰዎች መቆጣጠር ብቻ ሳይሆን፥ ሰዎችን ወደ ሲዖል የመላክ ሥልጣን ያለውን ክርስቶስን መፍራት ይኖርብናል። ያለ እርሱ ፈቃድ ማንም የእግዚአብሔርን ልጆች ሊገድል አይችልም። ሠ. ክርስቶስ በመቅረዞች (በአብያተ ክርስቲያናቱ) መካከል እየተመላለሰ ነው። እርሱ ከእኛ ርቆ በሰማይ የሚኖር ብቻ ሳይሆን፥ በመካከላችን ያለ አምላክ ነው። ሰባቱን ከዋክብት በእጁ የያዘው እርሱ ነው። እነዚህ ሰባት መላእክት ክርስቶስ በሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት ላይ የሾማቸው መላእክት ይሁኑ ወይም በእያንዳንዱ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በኃላፊነት የሚያገለግሉ ሰባት የቤተ ክርስቲያን መሪዎች በትክክል የምናውቀው ነገር የለም። እነዚህ በክርስቶስ ቁጥጥር ሥር የሚሠሩ በመሆናቸው ለራሳቸው ጥቅም መኖር የለባቸውም። የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ከዚህ ራእይ ውስጥ በመከራ ውስጥ በምትሆንበት ጊዜ የሚያበረታቱ ምን ምን ቁልፍ እውነቶችን ትመለከታለህ? ለ) ከዚህ ራእይ ውስጥ ለአንተም ሆነ ለቤተ ክርስቲያንህ ማስጠንቀቂያ የሚሰጡ ቁልፍ እውነቶች ምን ምንድን ናቸው? ፪. ለሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት የተላኩ መልእክቶች (ራእይ 2-3) ለሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት የተላኩት እያንዳንዳቸው መልእክቶች ተመሳሳይ ቅርጽ አላቸው። ሀ) ደብዳቤው ለቤተ ክርስቲያን መላእክት በሚተላለፈው መልእክት ይጀምራል፡፡ ይህ ምናልባትም ቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ በኃላፊነት የሚያገለግለውን መሪ የሚያመለክት ሊሆን ይችላል። ለ) ከራእይ 1፡13-18 ካለው ራእይ የተወሰደ የክርስቶስ ገለጻ ይከተላል። ይህም ገለጻ ክርስቶስ ለዚያች ቤተ ክርስቲያን ከሚሰጠው መልእክት ጋር የሚዛመድ ነው። ሐ) ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያኒቱን ለመልካም ተግባሯ ያመሰግናታል። አንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት እጅግ በደከመ መንፈሳዊ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ በመሆናቸው፥ ክርስቶስ ስለ ምንም መልካም ነገር ሊያመሰግናቸው አልቻለም። መ) ከዚያም ክርስቶስ፥ በምን እንዳሳዘኑት ይገልጻል። በጣም ድሆችና የተሰደዱ ሁለት አብያተ ክርስቲያናት ክርስቶስን እጅግ ደስ በማሰኘታቸው ከማንኛውም ተግሣጽ ነፃ ለመሆን ችለዋል። ሠ) ክርስቶስ እርሱን ደስ ያሰኙና ከቅጣቱ ያመልጡ ዘንድ ምን ሊያደርጉ እንደሚገባ ይነግራቸዋል። ረ) መልእክቱ ድልን ለሚነሣና ክርስቶስን በሚያስከብር ሕይወት ለሚመላለስ ሰው ክርስቶስ በሚገባው የተስፋ ቃል ይደመደማል። (ማስታወሻ፡ እነዚህ ሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ ያሉትን ምዕራፎች በተምሳሌትነት እንደሚያመለክቱ የሚናገሩ ምሁራን አሉ። ለምሳሌ ያህል፥ ኤፌሶን በዮሐንስ ዘመን የነበረችውን ቤተ ክርስቲያን ታመለክታለች ይላሉ። ሰምርኔስ በሁለተኛ እና በሦስተኛው ክፍለ ዘመን ጠንካራ ስደት የተጋፈጠችውን ቤተ ክርስቲያን የምታመለከት መሆኗን ይናገራሉ። ጴርጋሞን ሐሰተኛ ትምህርትና ኃጢአት በነገሠበት የመካከለኛው ዘመን የነበረችውን ቤተ ክርስቲያን የምታሳይ መሆኗን ያስረዳሉ። ሎዶቅያ ደግሞ ዛሬ በሃብትና በለብታ የምትታወቀውን ቤተ ክርስቲያን ታሳያለች ሲሉ ያስተምራሉ። ነገር ግን፥ እግዚአብሔር ለሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት ባስተላለፈው መልእክት ሊነግራቸው የፈለገው ይህንን አይመስልም። በሁሉም የቤተ ክርስቲያን ታሪኮች የፍቅር ቅዝቃዜ፥ ስደት፥ ሐሰተኛ ትምህርት፥ ኃጢአትና ለብ ማለት የሚፈታተናቸው የተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት አሉ። ስለሆነም በየትኞቹም አገሮች እና ዘመናት የሚኖሩ አብያተ ክርስቲያናት እነዚህን ለሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት የተላኩትን መልእክቶች ሊያነቡና ለራሳቸው የሚጠቅሙ ግላዊ መልእክቶች ሊያገኙ ይችላሉ።) ሀ. ኤፌሶን፡ የመጀመሪያ ፍቅሯን ያጣች ትጉሕ ቤተ ክርስቲያን (ራእይ 2፡1-7)። የኤፌሶን ቤተ ክርስቲያን በእስያ ለነበሩት አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ እናት ወይም ቁልፍ ቤተ ክርስቲያን ነበረች። ጳውሎስ በዚህች ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከሁለት ዓመታት በላይ ያገለገለ ሲሆን፥ ዮሐንስም የጳጳስነት ወይም የሽምግልና አገልግሎቱን ለረጅም ጊዜ በዚህች ቤተ ክርስቲያን ውስጥ አበርክቷል። ዮሐንስ በሮም ግዛት ውስጥ ባለችው የእስያ እውራጃ ለሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ያስተባባሪነት ሥራውን የሚያከናውነው በኤፌሶን ውስጥ ተቀምጦ ነበር። በመሆኑም የኤፌሶን ቤተ ክርስቲያን ለዮሐንስ እንደ ዋና ጽሕፈት ቤት ያገለግል ነበር። እንዲሁም ለሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት መልእክት የሚያስተላልፈው ግለሰብ በፍጥሞ ደሴት ከነበረው ከዮሐንስ የተቀበላቸውን መልእክቶች መጀመሪያ ለኤፌሶን ቤተ ክርስቲያን ያደርስ ነበር። ክርስቶስ ይህችን ቤተ ክርስቲያን ብዙም አልነቀፋትም። ኤፌሶን ወንጌሉን ለማዳረስ የምትተጋ ጠንካራ ቤተ ክርስቲያን ነበረች። አማኞቹ ከደረሰባቸው ስደት ባሻገር በእምነታቸው ጸንተው ቆመዋል። እንዲሁም ኤፌሶን የሐሰተኞችን ትምህርት ለመከተል ያልፈለገች ንጹሕ ቤተ ክርስቲያን ነበረች። እነዚህ ሐሰተኞች ሐዋርያት ነን ይሉ ነበር። ኒቆላውያን እነማን እንደ ነበሩ በትክክል ለማወቅ አንችልም። እነዚህ ሰዎች አማኞች ነን እያሉ የእግዚአብሔርን ጸጋና ይቅርታ በማመሃኘት የተቀደሰ ሕይወት ላለመኖር የሚመርጡ ይመስላል። እነዚህ ሰዎች አማኞች በአካባቢያቸው እንዳሉ ሰዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ያስተምሩ ነበር። እነዚህም ማኅበረሰቦች ከቤተ መቅደስ ካህናት ጋር ወሲብ መፈጸም የሚታከልበትን ባህላዊ የጣዖት አምልኮ ይፈጽሙ ነበር። ነገር ግን ክርስቶስ ከዚህ ጠለቅ ብሎ የሚያሳስበውን ነገር ይመለከታል። ይኸውም ለእርሱ፥ ለእርስ በርሳቸውና ድነትን (ደኅንነትን) ላላገኙት ሰዎች የነበራቸው ፍቅር መቀዝቀዙ ነበር። ክርስቶስ ፍቅራቸው እየቀዘቀዘ በሚሄድበት ጊዜ መልካም ነገሮቻቸው ሁሉ እንደሚከስሙ ያውቅ ነበር። ይህም በጽኑ ስላሳሰበው ክርስቶስ ንስሐ እንዲገቡ፥ ካልሆነ ግን መጥቶ መቅረዛቸውን እንደሚወስድባቸው ያስጠነቅቃል። በሌላ አገላለጽ፥ የክርስቶስ
ክርስቶስ በትንሹ እስያ ውስጥ ለነበሩ ሰባት አብያተ ክርስቲያናት ያስተላለፈው መልእክት (ራእይ 1፡9-3፡22) Read More »
