ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች

ጳውሎስ ለክርስቶስ እንዴት ልንኖር እንደሚገባ ያስተምራል (ፊልጵ. 1፡27-2፡18)

ክርስቶስን የግል አዳኝ አድርጎ ማመኑ አስፈላጊ ነው። ይህ ወደ ሲዖል እንዳንገባና የእግዚአብሔር ልጆች እንድንሆን ያስችለናል። ነገር ግን እግዚአብሔር በሚያድነን ጊዜ ከዚህ የበለጠ ብዙ ይጠብቅብናል። ለእኛ ያለውን ታላቅ ፍቅር በሚያንጸባርቅ መልኩ እንድንኖርለት ይሻል። ምንም እንኳ እግዚአብሔር ከእኛ የሚፈልገው ምስጋናችንን ብቻ ነው ብንልም፥ አዲስ ኪዳን ግን እርሱን በሚያስከብር መንገድ እንድንኖርም ያስተምራል። ጳውሎስም ለተጠራችሁለት የክርስቶስ ወንጌል እንደሚገባ ተመላለሱ ይለናል። ለመሆኑ ከተቀበልነው ወንጌል ጋር በሚስማማ መንገድ መኖራችንን የሚያመለክቱ አንዳንድ ነገሮች ምን ምንድን ናቸው? ፩. ከሌሎች ክርስቲያኖች ጋር በአንድነት መኖር አለብን። በፊልጵስዩስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሆነ ክፍፍል ተፈጥሮ ነበር። ሁለት ሴቶች እየተጣሉ ነበር። ይህም በሌሎች አማኞች መካከል ክፍፍልን ያስከተለ ይመስላል። ስለሆነም፥ ጳውሎስ አማኞች በኅብረት አብረው እንዲኖሩ ሊያስተምራቸው ይፈልጋል። የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) መክ 4፡9-12 እና ምሳሌ 27፡17 አንብብ። እነዚህ ጥቅሶች ሰዎች በኅብረት አብረው በሚኖሩበት ጊዜ ስለሚገኘው ጥንካሬ ምን ያስተምራሉ? ለ) ፊልጵ. 1፡27 እና 2፡1-11ን አንብብ። ጳውሎስ በዚህ ክፍል ውስጥ «አንድነት» «ኅብረት»፥ «አንድ» የሚሉትን ቃላት ምን ያህል ጊዜ በተደጋጋሚ ጠቅሷል? ሐ) አንድነት እንዲኖር ሰዎች ምን ዓይነት ባሕርይ ሊኖራቸው ይገባል? መ) ክርስቲያኖች በአንድነት እንዲኖሩ መሠረት የሚሆኗቸውን ነገሮች ዘርዝር። ያለነው ብዙ አብያተ ክርስቲያናት በተከፋፈሉበት ዘመን ውስጥ ነው። ጳውሎስ ካስተማረው እውነት አንጻር፥ ይህ ለተቀበልነው ወንጌል የሚገባውን አኗኗር እንደማንከተል ያሳያል። ወንጌሉ አማኞች ከቤተ እምነት ውክልናቸው፥ ከቤተሰባዊ ውርሳቸው ወይም ከጎሳዊ አባልነታቸው ባሻገር አንድ መሆናቸውን ያስተምራል። ከሌሎች ክርስቲያኖች ጋር መጣላቱ እናምናለን የምንለውን ሁሉ ይቃረናል። ክርስቲያኖች በአንድነት ሊኖሩ የሚገባቸው ለምንድን ነው? ጳውሎስ ሁለት ዐበይት ምክንያቶችን ሰጥቷል። ሀ. ጳውሎስ በኅብረት ሊኖሩ የሚገባቸው እንዲህ ዓይነቱ ሕይወት ጥንካሬን የሚፈጥር በመሆኑ ነው ይላል። ስለሆነም ክርስቲያኖችን በአንድ ልብ ስለ ወንጌል አብራችሁ እየተጋደላችሁ፥ «በአንድ መንፈስ እንድትቆሙ» ሲል ይመክራል። ሰሎሞን ሁለት ሰዎች እንኳን በኅብረት ቢኖሩ የሕይወትን ማዕበሎች ተቋቁመው እንደሚጸኑ ገልጾአል። እንዲሁም ሰዎች በመንፈሳዊ ሕይወታቸውና በእውቀት ስለታም ሊሆኑ የሚችሉት ብረት ቢላዋን እንደሚስል እርስ በርሳቸው የተሣሣሉ እንደሆነ ብቻ ነው ብሏል። ክፍፍል ይህንኑ ጥንካሬ በማስወገድ ሰዎች ለጠላቶቻቸው ጥቃቶች እንዲጋለጡ ያደርጋል። እነዚህም ጠላቶች ዓለም፥ ሰይጣንና የኃጢአት ተፈጥሮ ናቸው። ማንም ክርስቲያን ብቻውን ወደ ጥንካሬ ወይም መንፈሳዊ ብስለት ሊያድግ አይችልም። ሁላችንም ሌሎች እንዲረዱን እንሻለን። ጳውሎስ የሚጽፈው ስለ ምን ዓይነቱ አንድነት እንደሆነ ማወቁ መልካም ነው። በመጀመሪያ፥ ጳውሎስ እውነትን የሚሠዋ አንድነት መሥርቱ እንዳላለ መረዳት ይኖርብናል። መጽሐፍ ቅዱሳዊ አንድነት በጋራ እምነት ላይ የሚመሠረት ነው። እነዚህም እምነቶች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በግልጽ የቀረቡ ናቸው። ጳውሎስ የእግዚአብሔር ቃል የማይደግፋቸውን ነገሮች ከሚያስተምሩ ሌሎች ሃይማኖቶች ጋር አንድነት መሥርቱም አላለም። ከሌሎች ሃይማኖቶች ጋር ጸብ ሳንፈጥር በሰላም ልንኖር እንጂ አንድነትን ልንመሠርት አንችልም። መጽሐፍ ቅዱሳዊ አንድነት ችግሮችንና ኃጢአቶችን በማስወገድ ላይ የተመሠረተ እንጂ መደባበቅን አያበረታታም። ብዙውን ጊዜ ክፍፍል እንዳይከሠት ወይም ሰዎች እንዳይጎዱ በማሰብ ችግሮችን ወይም ኃጢአትን እንደብቃለን። ይህ ዘዴ ጊዜያዊ ሰላምን ሊያመጣ ቢችልም፥ የችግሩ ሥር ስላልተነካ የኋላ ኋላ ጸብን ማስከተሉ አይቀርም። ይቅርታን ልናገኝና ልንፈወስ የምንችለው ኃጢአት መፈጸማችንንና ችግሮች መኖራቸውን አምነን ስንቀበል ብቻ ነው። አንድነት በእውነትና በቅድስና መሠረት ላይ መታነጽ አለበት። ሁለተኛ፥ ጳውሎስ የሚገልጸው የአንድነት ዓይነት ከፍቅር ጋር በተዋሃደ እውነት ላይ የተመሠረተ ነው። በዚህ ዓይነቱ አንድነት ውስጥ ፍቅር፥ ለሌሎች ማሰብና መራራቱ፥ እንዲሁም እግዚአብሔር እንዲሆኑለት የሚፈልጉትን ሁሉ ሲሆኑ ለማየት የመጓጓት ፍላጎት ይኖራል። ይህም ኃጢአታቸውን ሳይናዘዙ ኖረው ውስጣዊ ሕይወታቸውን እንዲያወድሙ አይቶ እንዳላየ ዝም ከማለት ይልቅ ኃጢአታቸውን ተናዝዘው ከጎጂ መዘዞቹ እንዲላቀቁ ለማገዝ መፍቀድን ይጨምራል። እንዲሁም እውነትን፣ ሁሉም ሰው ስለ ክርስቶስ ባለው እውቀት የሚያድግበትንና የእግዚአብሔርን ቃል በመጠበቅ እውቀቱን የሚያንጸባርቅበትን ቆራጥነትም ያካትታል። ሦስተኛ፣ ጳውሎስ በእሑድ ቀን ብቻ ተሰባስበው ስለሚያመልኩት ሰዎች አንድነት አይደለም የጻፈው። ጳውሎስ የሚጽፈው በክርስቲያኖች ድካምና ተጠያቂነት ላይ ስለተመሠረተ አንድነት ነው። የሌሎችን ጸሎትና እገዛ በመሻት ትግሎቻችንን ለሌሎች ለማካፈል መፍቀድ ይኖርብናል። የተጠያቂነት አንድነትም ሊኖረን ይገባል። ይህም እንደ ቃሉ እንድንኖር የምንጠየቅበትና ሌሎችም ለክርስቶስ ክብር እንዲኖሩ የምናበረታታበት ነው። ምእመናን በዚህ ዓይነት መንገድ አንድነትን እስካልመሠረቱ ድረስ የትኛውም ቤተ ክርስቲያን ወይም ክርስቲያን ሊጠናከሩ አይችሉም። የውይይት ጥያቄ፡– በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ የተፈጠረ አንድ አለመግባባት ምረጥ። ሀ) ያ አለመስማማት እውነትን በመሽፋፈን እንዴት ሊረግብ ይችል ነበር? ለ) አንድ ሰው ከፍቅር ይልቅ በእውነት ላይ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ክፍፍሉን ሊያባብስ የሚችለው እንዴት ነው? ሐ) እውነትንና ፍቅርን በመቀላቀል ችግሩን ለመፍታት ምን ማድረግ ይቻላል? መ) የእውነትና የፍቅር የቅርብ ግንኙነት አብዛኞቹን ክፍፍሎች ሊያስወግድ የሚችለው እንዴት ነው? ለ. ጳውሎስ በአንድነት ስንኖር ጌታችንና ምሳሌያችን የሆነውን ክርስቶስን እንደምንመስል ያስረዳል። በፊልጵስዩስ 2፡6-11 በአዲስ ኪዳን ውስጥ ስለ ክርስቶስ ከተሰጡት እጅግ ጠቃሚ ትምህርቶች አንዱን እናገኛለን። ብዙ ምሁራን ይህ ግጥም የቀድሞይቱ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን የሚዘምሩት መዝሙር እንደነበረ ያምናሉ። ምናልባትም ይህ ጳውሎስ የጻፈው መዝሙር ሳይሆን አይቀርም። ይህ መዝሙር ክርስቶስ ሰው ከመሆኑ በፊት ምን ይመስል እንደነበረ፥ ሰው በሆነ ጊዜ ምን እንደ ተከሠተና የውርደቱም ውጤት ምንን እንዳስከተለ ይናገራል። ነገር ግን ይህ ትልቅ ትምህርት የቀረበው በቀዳሚነት ክርስቶስን ታላቅ ያደረገውን አስተሳሰብ ለእኛ ለማሳየት ነው። ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ክርስቲያኖች ስለያዟቸው መሠረታዊ እምነቶች በማውሳት ይጀምራል። አቀራረቡ፥ «ይህን ታምናላችሁ?» ብሎ የሚጠይቅ ይመስላል። ሁሉም «አዎን» ብለው እንዲመልሱለትም ይጠብቃል። ከዚያም እነዚህ እውነቶች እንዴት ወደ አንድነት እንደሚያመሩ ያሳያቸዋል። «ከክርስቶስ ጋር በመተባበራችሁ (አንድ በመሆናችሁ)» ደስ ይላችኋል? ጳውሎስ ከክርስቶስ ጋር ወይም በክርስቶስ መሆን ሲል፥ «በመዳናችሁና ከክርስቶስ ጋር የቅርብ ግንኙነት በመመሥረታችሁ ደስተኞች ናችሁ?» ማለቱ ነበር። ሁላችንም ለዚህ ጥያቄ አዎንታዊ ምላሽ መስጠታችን የማይቀር ነው። ክርስቶስ ስለሚወዳችሁ ደስ ይላችኋል? በሮሜ 8፡31-39 ጳውሎስ ማንም ከክርስቶስ ፍቅር ሊለየን እንደማይችል ይናገራል። እንድንድን ያደረገን ያ ፍቅሩ ነው። ያ ፍቅር እሁን ዋስትናን ይሰጠናል። እግዚአብሔር እንደሚጠብቀን ቃል ገብቶልናልና። ያ ፍቅር ከእግዚአብሔር ጋር በመንግሥተ ሰማይ ለዘላለም እንደምንኖር ያረጋግጣል። አሁንም ምላሻችን የሚሆነው «አዎን» ነው። በሁላችሁ ውስጥ ካለው መንፈስ ቅዱስ ጋር ኅብረት አላችሁ? መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ልጆች እንደ መሆናችን፥ መንፈስ ቅዱስ በልባችን ውስጥ እንደሚኖር ይናገራል (ሮሜ 8፡9-10)። እርሱ ሊያጽናናን፥ ሊረዳን፥ ሊጠብቀን፥ ኃይልን ሊሰጠንና በውስጣችን ሊሠራ ተዘጋጅቶ ከልባችን ውስጥ ይኖራል። ለዚህም «አዎን» ብለን እንመልሳለን። እግዚአብሔር ለሚጎዱ ሰዎች የምትራሩበትን ኃይል ሰጥቷችኋል? ይህም የሕይወታችን መለያ ባሕርይ ሊሆን ይገባል። እነዚህ አራት ነገሮች እውነት ከሆኑ፥ ከሌሎች ክርስቲያኖች ጋር በአንድነት ለመኖር እንችላለን። በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ የተለያየ አቋም ልንይዝ ብንችልም፥ እምነታችን አንድ በመሆኑ ምክንያት አንድ ዓይነት አስተሳሰብ ይኖራል። እርስ በርሳችን በመዋደድ ክርስቶስን በማስከበሩ አንድ ዓላማ ላይ እንሳተፋለን። መንፈስ ቅዱስም ይህንኑ ተግባር ከዳር እንድናደርስ ያግዘናል። ሁላችንም ይህንን የምንፈልግ ከሆነ፥ ያለመተባበርና መከፋፈል ከየት ይመጣል? መሪዎች ለምን ይጣላሉ? ቤተ እምነቶች ለምን እርስ በርሳቸው ይጣላሉ? ጳውሎስ ለዚህ ችግሩ አመለካከታችን፥ ራስ ወዳድነታችንና በትሕትና ለመቀባበል አለመፈለጋችን እንደሆነ ያስረዳል። የኃጢአት ሥር ራስ ወዳድነት ነው። ይህም ነገሮችን በራስ መንገድ ለማከናወን፥ ለራስ ለመጠቀምና ሌላውን ሳይሆን ራስን የመንከባከብ ፍላጎት ነው። የአንድነት ምሥጢሩ ራስን የሕይወት ማዕከል አለማድረግ ነው። ይህም ስለ ሌሎች ሰዎችና ስለ ፍላጎቶቻቸው ማሰብ ነው። ለመሆኑ ከሌሎች ይልቅ የራስን ፍላጎት ማስቀደም ምን ክፋት አለው? ጳውሎስ ይህ ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌነት ውጭ እንደሆነ ያስረዳል። እርሱ የተወልን ምሳሌነት ምን ነበር? ሀ. እርሱ ማን እንደነበረ፡- ክርስቶስ በባሕርዩ ፍጹም አምላክ ነበረ። ክርስቶስ የእግዚአብሔር አብ ባሕርያት ሁሉ ነበሩት። በምንም መንገድ ከእግዚአብሔር አላነሰም ነበር። መላእክት እያመለኩትና እየታዘዙት ከምናስበው ባለፈ ክብርና ተድላ በመንግሥተ ሰማያት ይኖር ነበር። ለ. አመለካከቱ (እሳቡ) ምን ነበር፡- ከእግዚአብሔር ጋር እኩል የመሆን ደረጃ ውን ይዞ በሰማያዊ በረከቶች ደስ ለመሰኘት አልፈለገም። እነዚህን ነገሮች የሙጥኝ ብሎ ሳይዝ ጥሏቸዋል። አምላክ የነበረው ክርስቶስ ራሱን አዋርዶ

ጳውሎስ ለክርስቶስ እንዴት ልንኖር እንደሚገባ ያስተምራል (ፊልጵ. 1፡27-2፡18) Read More »

በጳውሎስ እስራት ወንጌል መስፋፋቱ (ፊልጵ. 1፡12–26)

መከራ በሚደርስብን ጊዜ ትክክለኛ አቋም መያዝ አስቸጋሪ ነው። በቀላሉ ተስፋ መቁረጥ ይቻላል። ታላቁ የወንጌል አገልጋይ ከአራት ዓመታት በላይ ወኅኒ ቤት ውስጥ ቆይቷል። በዚህ ጊዜ ለጳውሎስ እግዚአብሔር ተሳስቶ ይሆን? ብሎ ማሰብ ቀላል ነበር። የፊልጵስዩስ አማኞችም የቤተ ክርስቲያናቸው መሥራችና ወዳጃቸው የሆነው ሰው በመታሠሩ ተጨንቀው ነበር። ጳውሎስ በወኅኒ ቤት ውስጥ ቢሆንም፥ እግዚአብሔር ታላቅ አምላክ በመሆኑ ክፉውን ነገር ወደ መልካም ሊቀይር እንደሚችል በመግለጽ የፊልጵስዩስን አማኞች ያበረታታል። ጳውሎስ በመታሠሩ ምክንያት እንደሚከናወኑ የተናገራቸው መልካም ነገሮች የሚከተሉት ናቸው። ሀ. ወንጌሉ ወደ ሮም ቤተ መንግሥት (እስከ ቤተ መንግሥት ጠባቂው ድረስ) ደርሷል። ቄሣርን ለመጠበቅ የተሰማሩ ወደ 6,000 ልዩ ወታደሮች ነበሩ። ምናልባትም በቄሣር ፊት ስለሚመረመር ሳይሆን አይቀርም። ከእነዚህ ወታደሮች አንዳንዶቹ ጳውሎስን ይጠብቁት ነበር። ጳውሎስም ለእነዚህ ወታደሮች ክርስቶስን መሰከረላቸው። በዚህም ጊዜ አንዳንዶቹ በክርስቶስ አመኑ። ወታደሮቹ በየተራ ጳውሎስን የሚጠብቁት በመሆናቸውና የዳኑትም ለሌሎች በመመስከራቸው ብዙም ሳይቆይ ወንጌሉ በቁልፍ ወታደሮች መካከል ተስፋፋ። ጳውሎስ ባይታሠር ኖሮ እነዚህ ሰዎች ወንጌሉን የመስማት ዕድል ላያገኙ ይችሉ ነበር። ለ. ጳውሎስ ለክርስቶስ ለመሠቃየት መፍቀዱን ሲመለከቱ ክርስቲያኖች በድፍረት እምነታቸውን ለሌሎች ያካፍሉ ጀመር። ጳውሎስ ለክርስቶስ የሚመሰክሩ ሁለት ዓይነት ክርስቲያኖች እንደነበሩ ገልጾአል። በመልካም ልብ ጳውሎስን የሚያከብሩና ወንጌልን የሚሰብኩ ነበሩ። በጳውሎስ ላይ የሚቀኑም ደግሞ ነበሩ። እነዚህ ሰዎች ወንጌሉን የሚሰብኩት ሮማውያን ባለሥልጣናት በጳውሎስ ላይ የበለጠ ችግር እንዲፈጥሩ በማሰብ ነበር። ጳውሎስ ግን ለራሱ የግል ጉዳይ አልተጨነቀም። የእርሱ ትልቁ አሳብና ፍላጎት የወንጌሉ መሰበክ ነበር። ጳውሎስ የሚጠሉትን ሰዎች ልባዊ ፍላጎት እያጸደቀ አልነበረም። ጳውሎስ በሌላ ስፍራ ልባዊ ፍላጎታችን ትክክል ካልሆነ ላከናወንነው ተግባር ከእግዚአብሔር ዘንድ ሽልማትን እንደማናገኝ ይናገራል (1ኛ ቆሮ 3፡10-15)። ነገር ግን ጳውሎስ ከሰዎች መጥፎ የልብ ፍላጎት ባሻገር የወንጌሉ መልእክት እየተሰበከ መሆኑን ለመግለጽ ይፈልጋል። የእግዚአብሔር ቃል ኃይል ስላለው በእንዲህ ዓይነት ሰዎች በሚሰበክበት ጊዜ ሳይቀር የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል። ሐ. ጳውሎስ በፊልጵስዩስ አማኞች ተግባር ስለተበረታታ እነርሱን መልሶ ያበረታታቸዋል። እንደሚጸልዩለት ስለሚያውቅ በዚሁ የእግዚአብሔር ሕዝብ ጸሎት ይበረታታል። እግዚአብሔር ጳውሎስን ጠንካራ፥ በምስክርነት አገልግሎት የሚተጋና ሞትን የማይፈራ ደፋር ለማድረግ የእነዚህን ወገኖች ጸሎት ተጠቅሟል። ጳውሎስ ቄሣር እንዲገደል ቢያዝ እንኳን እንደማይሸነፍ ስለሚያውቅ በእሥር ቤት ውስጥ በድፍረት ያገለግል ነበር። ሞት ክርስቲያንን ወደ ክርስቶስ ይወስደዋል እንጂ ለሽንፈት አይዳርገውም። ይህም ከእሥር ቤት ወይም ኃጢአትና ሥቃይ ካለበት ከየትኛውም ምድራዊ ሕይወት የበለጠ ነው። ነገር ግን ጳውሎስ እግዚአብሔር በሕይወቱ የሚፈጽመው ተግባር ስላለ ከወኅኒ እንደሚወጣ ተስፋ ያደርጋል። የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ከክፉው የኮሚኒዝም ዘመን ቤተ ክርስቲያን ያገኘቻቸው አንዳንድ መልካም ነገሮች ምን ምንድን ናቸው? ለ) በትልቅ ችግር ሳቢያ በሕይወትህ ውስጥ የተከሠቱትን አንዳንድ መልካም ነገሮች ዘርዝር። ሐ) ይህ በሕይወታችንና በቤተ ከርስቲያናችን አስቸጋሪ ጊዜያት በሚመጡበት ጊዜ ምን ማድረግ እንዳለብን ያሳያል? (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

በጳውሎስ እስራት ወንጌል መስፋፋቱ (ፊልጵ. 1፡12–26) Read More »

ምስጋናና ጸሎት (ፊል. 1፡1-10)

ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ሰዎች በጻፈው መልእክቱ፥ ሁለት ዐበይት እውነቶችን ለማስተላለፍ ይፈልጋል። በመጀመሪያ፥ የፊልጵስዩስ አማኞች በማንኛውም ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ቢሆኑ በክርስቶስ ደስ መሰኘትን እንዲማሩ ይፈልጋል። እሥራት፥ ስደት፥ ድህነት፥ ሞትም እንኳን ቢያጋጥማቸው ደስታቸውን ማጣት አይኖርባቸውም። በሚጎዱን ነገሮች አንደሰትም። አፍቃሪው አምላካችን ሁኔታዎችን በመቆጣጠር ላይ በመሆኑ ደስ ልንሰኝ እንችላለን። ሁለተኛ፥ ጳውሎስ የፊልጵስዩስ አማኞች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አንድነትን ለመፍጠር እንዲጥሩ ይፈልጋል። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ክፍፍል የተስፋፋ ይመስላል። ከፍተኛ ግምት የሚሰጣቸው ሁለት ሴቶች ግብግብ የገጠሙ ሲሆን፥ የቤተ ክርስቲያኒቱ አባላትም በቲፎዞነት የተከተሏቸው ይመስላል። ጳውሎስ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሰላም፥ አንድነትና ፍቅር እንዲኖር ይለምናቸዋል። ሰዎች የተለያዩ አቋሞችን ይዘው ሳለ እንዴት ሰላምና አንድነት ሊኖር ይችላል? ይህ ሊሆን የሚችለው የክርስቶስን ምሳሌነት በመከተል የግል አመለካከታችንን ስንተውና ሌሎችን ስናከብርን ነው። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ክፍፍል በሚኖርበት ጊዜ ሁሉ የችግሩ ሥር ትዕቢትና ራስ ወዳድነት ሆኖ ይገኛል። ይህ የራሳችንን መሳሳት ወይም የሌሎችን አስተሳሰብ ተገቢነት ለመቀበል ካለመፈለግ የሚመነጭ ነው። ይህ ይቅር ለማለት አለመፈለግ፥ ሰዎች እኛን የሚጎዱበትን መንገድ መመርመርና ሳይቃወሙን ተቃውመውናል ብሎ ማሰብ ነው። የሐሰት ትምህርትን ከመቃወም ውጭ የሚመጣ ማንኛውም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚከሠት ክፍፍል ክርስቶስ አንድ እንሆን ዘንድ ባቀረበው ጸሎት ላይ የሚሰነዘር ስድብ ነው። በተጨማሪም፥ ይህ ጳውሎስ ለእኛ ለመሞት ሲል ሰማይን ትቶ ወደ ምድር የመጣውን የክርስቶስን ምሳሌነት እንድንከተል ያቀረበውን ልመና አለመቀበል ነው። አንድ የቤተ ክርስቲያን መሪ ከሚያገለግልበት ቤተ ክርስቲያን ጸሎትና እገዛ በሚያገኝበት ጊዜ፥ ሥራው አስደሳች ይሆንለታል። ይህም በቤተ ክርስቲያኒቱና በመሪው መካከል ጠንካራ ትሥሥርን በመፍጠር እግዚአብሔርን ደስ ያሰኘዋል። በጳውሎስና በፊልጵስዩስ ቤተ ክርስቲያን መካከል የተከሠተው ይኸው ነበር። እንደ ቆሮንቶስና ገላትያ ያሉት አብያተ ክርስቲያናት የጳውሎስን ሥልጣን ሲጠራጠሩ፥ የፊልጵስዩስ ቤተ ክርስቲያን ግን አጥብቃ ደግፋዋለች። ጳውሎስን ከማክበራቸውና ለአገልግሎቱ ከመጸለያቸው በተጨማሪ፥ ጳውሎስ በሌሎች አካባቢዎች የሚያካሂደውን አገልግሎት ለመደገፍ ገንዘባቸውን ሰጥተውታል። ይህ የፊልጵስዩስ መልእክት መግቢያ ይህንኑ በጳውሎስና በፊልጵስዩስ ቤተ ክርስቲያን መካከል የነበረውን በፍቅር ያንቆጠቆጠ ግንኙነት ያሳያል። ጳውሎስ ራሱንና ጢሞቴዎስን ካስተዋወቀና ሰላምታ ካቀረበ በኋላ፥ ቤተ ክርስቲያኒቱንና የወንጌል ተካፋይነቷን በሚያስታውስበት ጊዜ ምን ዓይነት ደስታ እንደሚሰማው ይገልጻል። የወንጌል ሸሪኮች ለመሆን መፍቀዳቸው እያደገ የመጣው የመንፈሳዊ ብስለታቸው ምልክት ነበር። ጳውሎስ ወደ ክርስቶስ አምሳል ሊለውጣቸው የጀመረው እግዚአብሔር እስከ ክርስቶስ ምጽአት ድረስ ይህንኑ ተግባር እንደሚያጠናቅቅ ይናገራል። ከእነርሱ ርቆ በወኅኒ ቤት ውስጥ መቀመጡ ጳውሎስ ከእነርሱ ጋር ካለው ግንኙነት የተነሣ የተሰማውን ደስታና ፍቅር ሊቀንስበት አልቻለም። እግዚአብሔር ለአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን የወጠነው እማኞች በብስለት እንዲያድጉ ነው። ብስለት ከሚገለጽባቸው መንገዶች አንዱ የቤተ ክርስቲያን ከጥገኝነት ራስን ወደ መቻል መለወጥ ነው። ይህም ቤተ ክርስቲያን መርሐ ግብሮቿን ለማካሄድና ለገንዘብ ፍጆታዋ በውጭ ወንጌላውያን፥ ሚሲዮናውያን ወይም ለጋሾች ላይ ከመደገፍ ወጥታ በራሷ ገንዘብ የወንጌል ስርጭትና ድሆችን የመርዳት ተግባር የምታከናውንበት ነው። ከዚህ በኋላ ቤተ ክርስቲያን ከሌሎች ጋር በመተባበር ወንጌልን ወደ ሌሎች አካባቢዎች ልታደርስ ትችላለች። የሚያሳዝነው ብዙ አብያተ ክርስቲያናት በውጭ እገዛ ላይ ይደገፋሉ። እንዲሁም ብዙ አብያተ ክርስቲያናት በራስ ወዳድነት የራሳቸውን ፍላጎት ብቻ በማሟላት ላይ ይገኛሉ። እግዚአብሔር የሚፈልገው ግን ቤተ ክርስቲያን በፍጥነት ተጠናክራ ወንጌልን በማስፋፋቱ ሥራ ላይ እንድትሳተፍ ነው። የሚያስገርመው የፊልጵስዩስ ቤተ ክርስቲያን ሰዎች ወንጌሉን ከሰሙ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ወንጌሉን ለሌሎች ለማካፈል ተግተው ይሳተፉ ጀመር። የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) የቤተ ክርስቲያንህን ዕድገት ገምግም። ቤተ ክርስቲያንህ ከሦስቱ የዕድገት ደረጃዎች በየትኛው ላይ ነች? (ጥገኛ፥ ራሷን የቻለች፥ ወይስ ከሌሎች ጋር ተባብራ ወንጌልን የምታሰራጭ?) ለ) ቤተ ክርስቲያንህ ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ጋር ተባብራ ወንጌሉን ለማስፋፋት ትችል ዘንድ ምን ማድረግ ያስፈልጋታል? ሐ) ለቤተ ክርስቲያን በጥገኝነት ወይም ራሷን ችላ የራሷን ፍላጎቶች በማሟላቱ ተግባር ላይ ብቻ ማተኮር ቀላል የሚሆነው እንዴት ነው? ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ቤተ ክርስቲያን እንደሚጸልይ ገልጾአል። ይህ ጸሎት በመንፈሳዊ ብስለት ማደጋቸው ላይ እንደሚያተኩር አስተውል። ሀ. ጳውሎስ ፍቅራቸው፥ እውቀታቸውና የማስተዋላቸው ጥልቀት ይበልጥ እንዲጎለብት ጸልዮአል። አሁንም ጳውሎስ በመንፈሳዊ ዕድገትና ጤንነት ትክክለኛነት ላይ እንዳተኮረ እንመለከታለን። በስሜት የተጋጋለ አምልኮ ማካሄዱ ብቻ በቂ አይደለም። የመንፈሳዊ ብስለት መሠረቱ ስለ እግዚአብሔር፥ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ፥ በክርስቶስ ስላለን በረከት፥ ወዘተ… እያደገ የሚሄድ ግንዛቤ መጨበጥ ነው። ማንም ክርስቲያን እግዚአብሔርን ካላወቀና ቃሉን ካልተከተለ በቀር ስሜታዊ አምልኮ በማካሄዱ ብቻ እግዚአብሔርን ደስ ሊያሰኝ አይችልም። የቤተ ክርስቲያን መሪዎች የምእመኖቻቸውን እውቀት ለማሳደግ መትጋት ያለባቸው ለዚህ ነው። ለ ጳውሎስ የፊልጵስዩስ አማኞች ለክርስቶስ ቀን ተዘጋጅተው ቅኖችና አለነውር እንዲሆኑ ይጸልያል። ክርስቲያኖች ወይም ቤተ ክርስቲያን ልታደርጋቸው የሚገቡ መልካም ነገሮች አሉ። ጳውሎስ ግን እነዚህ ክርስቲያኖች ከመልካም ነገሮች ሁሉ ምርጥ የሆኑትን እንዲመረምሩና እነዚሁኑ ከሁሉም የበለጠ መንፈሳዊ ለውጥ የሚያስከትሉትን ተግባራት እንዲያከናውኑ ይጸልያል። ቤተ ክርስቲያን ሕንጻ ትገንባ ወይስ ለወንጌላውያን ገንዘብ ትስጥ? የቤተ ክርስቲያን ገንዘብ ለኳዬር ልብስ መግዣ ይዋል ወይስ ሰዎች በመንፈሳዊ ሕይወታቸው እንዲያድጉ የሚያግዙትን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መሣሪያዎችን ለመግዛት? በእንዲህ ዓይነት ሁኔታዎች ውስጥ ከሁሉም የሚበልጠውን ለማወቅ መንፈሳዊ ጥበብን መጠቀም አስፈላጊ ነው። ጳውሎስ የፊልጵስዩስ አማኞች ከሁሉም የሚሻለውን እንዲያውቁና እንዲመርጡ የፈለገበት ምክንያት እግዚአብሔር ምን እንዲያደርጉ እንደሚፈልግ እንዲያውቁና ክርስቶስ ሲመጣም፥ ንጹሐንና እንከን የሌላቸው ሆነው እንዲገኙ ነው። ሐ. ጳውሎስ በጽድቅ ፍሬ እንዲሞሉ ይጸልያል። ጳውሎስ የሚሻው ሰዎች እግዚአብሔር እንደሚፈልገው በመኖር የእምነታቸውን እውነትነት እንዲያሳዩ ነው። ጽድቅ ኃጢአትን አለመፈጸም ብቻ አይደለም። ይህ በእግዚአብሔር ዓይኖች ፊት ትክክል የሆነውን መፈጸም ጭምር ነው። ይህም ድሆችን መርዳት፥ ሌሎችን መታዘዝ፥ በፍቅርና በአንድነት መኖር፥ በአጠቃላይም ማንኛውም እግዚአብሔርን ለማስደሰት ሲባል በጥሩ የመነሻ እሳብ የሚወሰድ እርምጃ ነው። የውይይት ጥያቄ፡– እነዚህ ሦስት ጥያቄዎች የመንፈሳዊ ብስለት አመልካቾች ናቸው። እስኪ የራስህን ሕይወት ገምግም። ሀ) ፍቅርህ በይበልጥ በእግዚአብሔር ቃል እውቀት ላይ ተመሥርቶ እያደገ የሄደበትን ሁኔታ ግለጽ። ለ) እግዚአብሔር ሁልጊዜም እንድታከናውን ከሚፈልጋቸው ነገሮች ሁለቱን በምሳሌነት ጥቀስ። ከሁለቱ የሚሻለው የትኛው ነው? መሻሉን እንዴት አወቅህ? ሐ) ባለፈው ሳምንት በሕይወትህ ውስጥ የተገለጡትን አንዳንድ የጽድቅ ፍሬዎች ዘርዝር። እነዚህ ፍሬዎች እያደጉና እየተደጋገሙ የመጡት እንዴት ነው? (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ምስጋናና ጸሎት (ፊል. 1፡1-10) Read More »

የፊልጵስዩስ መልእክት ዓላማ፣ ልዩ ባሕሪያት፣ መዋቅርና አስተዋጽኦ

የፊልጵስዩስ መልእክት ዓላማ የፊልጵስዩስ ቤተ ክርስቲያን በአፍሮዲጡ መታመም ላይ የነበራትን ስጋት አስመልክቶ መረጃ መስጠት። የጳውሎስ ደብዳቤ የመጣው በሮምና ፊልጵስዩስ መካከል ተከታታይ መልእክቶች ከተላለፉ በኋላ ነበር። በፊልጵስዩስ የነበሩ ክርስቲያኖች ስለ ጳውሎስ መታሠር በሰሙ ጊዜ፥ ሁኔታውን ይከታተል ዘንድ አፍሮዲጡን ወደ እርሱ ላኩት። መጠነኛ ገንዘብም ሰደዱለት (ፊልጵ. 4፡10-18)። አፍሮዲጡ የጳውሎስን የተጎሳቆለ አኗኗር ከተመለከተ በኋላ ተጨማሪ ገንዘብ ይልኩለት ዘንድ መልእክተኛ ላከ (ፊልጵ. 2፡25፡30)። ከዚያም አፍሮዲጡ ለሞት እስከሚያሰጋ ድረስ በጣም ታመመ። የፊልጵስዩስም ቤተ ክርስቲያን የመታመሙን ዜና በሰማች ጊዜ በጣም ሰጋች (ፊልጵ. 2፡26-27፥ 30)። አፍሮዲጡም የፊልጵስዩስ ሰዎች በእርሱ መታመም መስጋታቸውን ሰምቶ ተጨነቀ (ፊልጵ. 2፡26)። እግዚአብሔር አፍሮዲጡን ፈወሰው። ጳውሎስም የፊልጵስዩስን ሰዎች ጭንቀት ለማርገብ ሲል ደብዳቤ አስይዞ ወደ ፊልጵስዩስ ሊመልሰው ወሰነ። ጳውሎስ አጋጣሚውን በመጠቀም ላበረከቱለት የገንዘብ ድጋፍ ምስጋናውን ለማቅረብና ስለ መታሰሩ እንዳይጨነቁ ሊያሳስባቸው ፈለገ። ከዚህም በላይ፥ ጳውሎስ ይጎበኛቸው ዘንድ ጢሞቴዎስን እንደሚልክና ፈጥኖ ከተፈታም መጥቶ እንደሚጎበኛቸው ገልጾአል። ጳውሎስን የሚቃወሙ፥ የሐሰት ወንጌል የሚያስተምሩ ወይም በአንድነት የማይኖሩ ሰዎች የሚያስከትሉትን ክፍፍል በተመለከተ የፊልጵስዩስን ሰዎች ለማስጠንቀቅ። ጳውሎስን ያሳሰቡ ሦስት ቡድኖች የነበሩ ይመስላል። በመጀመሪያ፥ በሮም ምናልባትም በመቄዶንያ ጳውሎስን የማትወድ ቤተ ክርስቲያን አካል የሆኑ ቡድኖች የነበሩ ይመስላል። እነዚህ ቡድኖች የጳውሎስን መታሠር በተመለከቱ ጊዜ በሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ላይ ተጽዕኖአቸውን ለማጠናከር ተስፋ አደረጉ። በጳውሎስ ላይ ተጨማሪ ስደት ለማምጣት የሚያስችል ስብከትም ያቀርቡ ነበር። ጳውሎስ ግን ከእነርሱ ጋር ግብግብ ሊገጥም አልፈለገም። ወንጌል በመስበካቸው ግን ደስ ተሰኘ (ፊልጵ. 1፡16-18)። ለጳውሎስ ዋናው ነገር የእርሱ መታሠር ወይም የዝናው መጉደፍ ሳይሆን የወንጌሉ መሰበክ ነበር። ሁለተኛ፥ አንዳንድ ሐሰተኛ አስተማሪዎች የሐሰት ወንጌል እያስተማሯቸው ነበር። ይህም ለገላትያ ሰዎች ከቀረበው ትምህርት ጋር የሚመሳሰል ነበር። እነዚህ ሰዎች አሕዛብ በክርስቶስ ከማመናቸው በተጨማሪ መገረዝ እንዳለባቸው የሚያስገድዱ አይሁዶች ሳይሆኑ እይቀሩም። ጳውሎስ እነዚህን አስተማሪዎች «ክፉ ሠራተኞች» (ፊልጵ. 3፡2) እና «የመስቀሉ ጠላቶች» (ፊልጵ 3፡18) ይላቸዋል። ጳውሎስ የፊልጵስዩስ ክርስቲያኖች ይህንን የሐሰት ትምህርት እንዳይቀበሉ ያስጠነቅቃቸዋል። ሦስተኛ፥ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ክፍፍል ተፈጥሮ ነበር። ይህም ክፍፍል የተከሠተው በሁለት ሴቶች ምክንያት ሳይሆን አይቀርም (ፊልጵ. 4፡2)። ክፍፍሉ የተከሠተው beሃይማኖታዊ አስተምህሮ ምክንያት ሳይሆን በራስ ወዳድነት ሳቢያ ነበር (ፊልጵ. 1፡27፤ 2፡2-4፥ 14)። እናም ጳውሎስ አንድነትን እንዲመሠርቱ ይለምናቸዋል። ወንጌሉ የምናምንበት ብቻ ሳይሆን እውነትነቱን በሚያሳይ መልኩ የምንኖርበትም ነው። ፍቅርና እውነት የወንጌሉ ቁልፍ መረጃዎች ናቸው። ጳውሎስ ይህንን የራስ ወዳድነት አመለካከት ለመመከት በአዲስ ኪዳን ውስጥ ከታወቁት መዝሙሮች አንዱን ይጠቅሳል። በፊልጵስዩስ 2፡6-11 ጳውሎስ ክርስቶስ ራስን የማዋረድና የራስን መብቶች በመሥዋዕትነት ለሌሎች ከመስጠት የሚመጣ ክብር ምሳሌ መሆኑን ያብራራል። ጳውሎስ በዚህ መዝሙር ውስጥ ስለ ክርስቶስ አምላክነትና ሰብአዊነት እጅግ ግልጽ የሆኑትን አሳቦች አቅርቧል። የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) እነዚህ ሦስት ዓይነት ክፍፍሎች በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ ስለሚገኙበት ሁኔታ ግለጽ። ለ) አብያተ ክርስቲያናት እነዚህን ሦስት ዓይነት ክፍፍሎች የሚያስተናግዱባቸውን መንገዶች የሚያሳዩትን ምሳሌዎች ጥቀስ። ሐ) እያንዳንዱ የክፍፍል ዓይነት መጽሐፍ ቅዱሳዊ በሆነ መንገድ እንዴት ሊስተናገድ ይገባል? ለአገልግሎቱ ስላበረከቱት የገንዘብ ድጋፍ የፊልጵስዩስ ክርስቲያኖችን ለማመስገን። እርሱ ቢታሠርም፥ ወንጌሉ አልታሠረም ነበር። እናም በስፋት እየተሰራጨ ነበር። በጳውሎስ አማካኝነት ምርጥ የሮም ወታደሮች ሳይቀር በክርስቶስ እያመኑ ነበሩ። ስለሆነም፥ በእሥራቱ ከማዘን ይልቅ አብረውት ደስ እንዲሰኙ አበረታቷቸዋል። ለክርስቶስ ሲሉ ስደትን ለመጋፈጥ በመፍቀድ ምሳሌነቱን እንዲከተሉ መክሯቸዋል። የፊልጵስዩስ መልእክት ልዩ ባሕርያት በፊልጵስዩስ መልእክት ውስጥ ከብሉይ ኪዳን የተወሰደ ጥቅስ አልሰፈረበትም። ጳውሎስ ብዙውን ጊዜ ትምህርቱን በብሉይ ኪዳን ምሳሌዎች ስለሚያጠናክር፥ ይኼ ያልተለመደ ነገር ነው። ጳውሎስ ይህን ያደረገው ምናልባትም ከአንባቢዎቹ አብዛኞቹ አይሁዶች ባለመሆናቸውና ብሉይ ኪዳንን ባለመረዳታቸው ይሆናል። ይህ የጳውሎስ እጅግ ግላዊ መልእክት ነው። መልእክቱ «እኔ» በሚሉና በመሳሰሉ ግላዊ ቃላት የተሞላ ነው። ይህም ከፊልጵስዩስ ቤተ ክርስቲያን ጋር የነበረውን ጥብቅ ግንኙነት የሚያሳይ ነው። ጳውሎስ በግለሰብ ደረጃ ለሚያውቁትና ለሚወዱት፥ እርሱም ለሚወዳቸው ሰዎች ነበር የሚጽፈው። ይህ መልእክት የጳውሎስን ውስጣዊ ፍላጎት ያንጸባርቃል። ምንም እንኳ ታላቅ ሐዋርያና እግዚአብሔርም ብዙ አብያተ ክርስቲያናትን ለመመሥረት የተጠቀመበት ቢሆንም፥ ጳውሎስ ገና ብዙ ለማደግ እንደሚፈልግ ያስረዳል። ስለሆነም፥ ስለ ክርስቶስ ገና ብዙ ለማወቅና ኃይሉን ለመለማመድ ወደ ፊት እንደሚዘረጋ ይገልጻል። ጳውሎስ በመንፈሳዊ ሕይወቱ ለማደግ የቆረጠ ሰው በመሆኑ፥ ከመጨረሻው የብስለትና የመንፈሳዊነት ደረጃ ላይ እንደ ደረሰ አያስብም ነበር። ብዙውን ጊዜ ክርስቲያኖች ባለን የዕድገት ደረጃ እንረካለን። በመሆኑም፥ ለመማር አንጥርም። ስለ ክርስቶስ የበለጠ ለማወቅ አንሞክርም። በሕይወታችን የክርስቶስ ኃይል በበለጠ ኃይል እንዲገለጥ አንሻም። ይኼ አሳዛኝና አደገኛ ነገር ነው። ምክንያቱም ወደፊት ካላደግን ወደኋላ እየሄድን ነው። የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ብዙ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች በመንፈሳዊ ሕይወታቸው ማደግ ያቆሙበትን ሁኔታ ግለጽ። ይኼ አደገኛ የሚሆነው ለምንድን ነው? ለ) ባለፈው ዓመት በእምነትህ ያደግህበትን ሁኔታ ግለጽ። ክርስቶስ ሰው በሆነ ጊዜ የተፈጸመውን ሁኔታ ጥርት አድርገው ከሚያብራሩት ክፍሎች አንዱ ፊልጵስዩስ 2፡5-11 ነው። ክርስቶስ ከድንግል ማርያም ከመወለዱ በፊት ከእግዚአብሔር ጋር እኩል ነበር። በባሕርይ በመብት፥ በኃይል ከእግዚአብሔር ጋር እኩል ነበር። ጳውሎስ እንደሚለው ግን ከርስቶስ ሰው በሆነ ጊዜ “ራሱን ባዶ አደረገ”፡፡ ይህ ክርስቶስ መለኮታዊ ባሕርዩን እንዳጣ አያሳይም። መለኮትነቱን ይዞ በሰብአዊነት ኖሯል። እንደኛው ቢፈተንም ኃጢአትን አልፈጸመም። በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ነበር። እኛም እንዲሁ ልንመላለስ ይገባል። በተራራው ላይ ክርስቶስ ከመለኮታዊ ክብሩ የተወሰነውን በማንጸባረቅ ልብሶቹና ፊቱ እንዲለወጥ አድርጓል (ማቴ. 17፡1-13)። የዕብራውያን መልእክት ጸሐፊ እንደሚለው፥ ይህ ራሱን ባዶ የማድረጉ ተግባር ክርስቶስ ሊቀ ካህናችን እንዲሆን አብቅቶታል (ዕብ. 2፡17-18)። የፊልጵስዩስ መልእክት መዋቅር ብዙውን ጊዜ የጳውሎስ መልእክቶች በሁለት ዐበይት ክፍሎች ይከፈላሉ። የመጀመሪያው ክፍል ጠቃሚ አስተምህሮዎችን፥ ሁለተኛው ክፍል ደግሞ ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ግንኙነት በሚያንጸባርቅ መንገድ እንዴት መመላለስ እንዳለብን ያስተምራል። የፊልጵስዩስ መልእክት ግን ይህን ስልት አይከተልም። መልእክቱ የግል ደብዳቤን ይመስላል። በውስጡ የምንመለከተው የጳውሎስን ግላዊ መረጃና ወዳጆቹ እንዲያውቁ የሚፈልጋቸውን አንዳንድ ትምህርቶች ነው። በመሠረታዊነት ደረጃ ጳውሎስ ስለ እሥራቱ በመናገር ይጀምርና (ፊልጵ. 1፡1-26) ክርስቲያኖች የእግዚአብሔር ልጆች መሆናቸውን በሚያሳይ መልኩ መኖር እንዳለባቸው ያስተምራል (ፊልጵ. 1፡27-2፡18)። ከዚያም ጳውሎስ ጢሞቴዎስንና አፍሮዲጡን ስለመለኩ ይናገራል (ፊልጵ. 2፡19-30)። በመጨረሻም፥ ስለ ሐሰተኛ አስተማሪዎችና እግዚአብሔርን ስለሚያስከብር አኗኗር ያስተምራል : (ፊልጵ. 3፡1-4፡23)። የፊልጵስዩስ መልእክት አስተዋጽኦ መግቢያ (ፊልጵ. 1፡1-11) የግል መረጃ፡- ጳውሎስ ስለ እሥራቱ ያብራራል (ፊልጵ. 1፡12-26) የመጀመሪያው ትምህርት፡- ጳውሎስ ለክርስቶስ እንዴት ልንኖር እንደሚገባን ያስተምራል (ፊልጵ. 1፡27-2፡18) የግል መረጃ ፡- ጳውሎስ ስለ አፍሮዲጡ መመለስና የጢሞቴዎስ መምጣት ይናገራል (ፊልጵ. 2፡19-30) ሁለተኛው ትምህርት፡- ጳውሎስ ስለ ክርስቲያናዊ አኗኗር ተጨማሪ ትምህርቶችን ይሰጣል (ፊልጵ. 3፡1-4፡19) ሀ. ጳውሎስ ስለ ሐሰተኛ አስተማሪዎች ያስጠነቅቃል (ፊልጵ. 3፡1-21) ለ. ጳውሎስ በአንድነት ለክርስቶስ እንዲኖሩ ያበረታታል (ፊልጵ. 4፡1-9) ጳውሎስ የፊልጵስዩስን ክርስቲያኖች ለስጦታቸው አመሰገነ (ፊልጵ. 4፡10-20) ማጠቃለያ (ፊልጵ. 4፡21-23) (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የፊልጵስዩስ መልእክት ዓላማ፣ ልዩ ባሕሪያት፣ መዋቅርና አስተዋጽኦ Read More »

የፊልጵስዩስን መልእክት ማን ጸፈው፣ ለማን ተጻፈ፣ መቼና የት ተጻፈ

የፊልጵስዩስ መልእክት ጸሐፊ ጳውሎስ ይህንን መልእክት ለፊልጵስዩስ ሰዎች ያቀረበው ራሱንና የአገልግሎት ተባባሪው የነበረውን ጢምቴዎስን በማስተዋወቅ ነው። መልእክቱን የጻፈው ጢሞቴዎስ ነበር። ነገር ግን ጢሞቴዎስ ከጳውሎስ ጋር አብሮ ስለነበረና መጀመሪያ ወንጌሉን ለፊልጵስዩስ ሰዎች ከጳውሎስ ጋር አብሮ ስላደረሳ፥ ጳውሎስ ሰላምታውን ሊያካትትለት ፈለገ። ጳውሎስ በሌሎች መልእክቶቹ ውስጥ ከሚያሳየው ሁኔታ በተለየ መልኩ ሐዋርያነቱን አለመግለጹ አስገራሚ ነው። ጳውሎስ በዚህ መልእክት ውስጥ ራሱን “ባሪያ” ሲል ያስተዋውቃል። ይህ የግሪኩ ቃል ትክክለኛ ትርጉም ነው። አንድ አገልጋይ ለማን እንደሚያገለግል የመምረጥ መብት አለው። ባሪያ ግን ይኼ መብት የለውም። በእስራኤል ሁለት ዓይነት ባሪያዎች ነበሩ። ለአንድ ሰው ተሽጠው ሕጋዊ ንብረት የሆኑ ባሮች ነበሩ። በገዛ ፈቃዳቸው ባሮች የሚሆኑም ነበሩ። ለምሳሌ ያህል አንድ ሰው የተበደረውን ገንዘብ ለመክፈል ባለመቻሉ ለ10 ዓመታት ባርነት ቢሸጥ፥ እንዲህ ዓይነቱ ሰው ጌታው የሚያዘውን ሁሉ የመፈጸም ግዴታ ይወድቅበታል። ከ10 ዓመታት አገልግሎት በኋላ ግን ነፃ ይወጣል። ከ10 ዓመታት በኋላ ግን ሰውዬው ጌታውን በመውደዱ ምክንያት በባርነቱ ለመቀጠል ቢፈልግ፥ ምርጫው የራሱ ይሆናል። በዚህም ጊዜ ጆሮውን ይበሳና ከፍቅሩ የተነሣ ለቀረው ዘመኑ ሁሉ ጌታውን ሲያገለግል ይኖራል (ዘጸ. 21፡4-6)። በጳውሎስ አእምሮ ውስጥ የነበረው ይኸው ሁለተኛው ዓይነት ባርነት ሳይሆን አይቀርም። ጳውሎስ ክርስቶስን እጅግ በመውደዱ ምክንያት በገዛ ፈቃዱ ባሪያው ለመሆንና ለተቀረው ዘመኑ ሁሉ እርሱን ለማገልገል ፈቀደ (1ኛ ቆሮ. 6፡20 አንብብ)። ጳውሎስ እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያ፥ ሕይወቱን ሙሉ በሙሉ ለክርስቶስ ፈቃድ አስገዝቷል። ስለሆነም፥ ለሚሄድበት፥ ለሚያደርገውና በአጠቃላይም በሕይወቱ ውስጥ ለሚያከናውነው ተግባር የራሱ ፈቃድ አልነበረውም። ምንም እንኳን ይኼ ሥቃይንና እስራትን የሚጨምር ቢሆንም፥ ጳውሎስ ጌታው ኢየሱስ ክርስቶስ የፈለገውን ብቻ ነበር የሚቀበለው። የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በአገልጋይና ባሪያ መካከል ያለው የአመለካከት ልዩነት ምንድን ነው? ለ) ለክርስቲያኖች በክርስቶስ መዋጀታችንን ማስታወሱ ለምን ይጠቅማል? ሐ) ክርስቲያኖች የክርስቶስ ባሪያዎች መሆናችንን ብናስታውስ፥ አመለካከታችንና ተግባራችን እንዴት ይለወጣል? መ) እየተመላለስህ ያለኸው እንደ ክርስቶስ ባሪያ ነውን? ክርስቶስ በሕይወትህ ውስጥ ሙሉ ተቆጣጣሪነት እንዳይኖረው የምትከለከልባቸውን ክፍሎች መንፈስ ቅዱስ እንዲያሳይህ በጸሎት ጠይቅ፡፡ ኃጢአትህን ተናዘዝና ይህንኑ የሕይወትህን ክፍል ዛሬውኑ ለክርስቶስ አሳልፈህ ስጥ። ጳውሎስ የጻፈው ለማን ነበር? የውይይት ጥያቄ፡– ሀ) ጳውሎስ ይህንን መልእክት የጻፈው ለማን ነበር? ለ) የሐዋ. 16፡6–40 አንብብ። የፊልጵስዩስ ቤተ ክርስቲያን እንዴት እንደተ መሠረተችና በዚያ ስፍራ በጳውሎስ ላይ ስለደረሰው ሁኔታ ጠቅለል ያለ አሳብ ጻፍ። ጳውሎስ በመግቢያው ውስጥ፥ «በፊልጵስዩስ ለሚኖሩ ከኤጲስ ቆጶሳትና ከዲያቆናት ጋር በክርስቶስ ኢየሱስ ላሉት ቅዱሳት ሁሉ» ሲል የመልእክቱን ተቀባዮች ይጠቅላል። ጳውሎስ መልእክቱን የጻፈው በፊልጵስዩስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለነበሩት ሁለት ቡድኖች ነበር። ከእነዚህም የመጀመሪያዎቹ የቤተ ክርስቲያን ምእመናን ነበሩ። ጳውሎስ እነዚህን ወገኖች «ቅዱሳን»፥ ማለትም በክርስቶስ ከማያምኑ ሰዎች በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት የተለዩ ብሎ ይጠራቸዋል። ሁለተኞቹ ቡድኖች የፊልጵስዩስ ቤተ ክርስቲያን መሪዎች ናቸው። ጳውሎስ መልእክቱን ለመሪዎች መላኩን የጠቀሰበት ብቸኛው ስፍራ ይኼ ነው። ጳውሎስ ስለ መሪዎች ያነሣው አሳብ በጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የነበሩትን ሁለት ዓይነት ዐበይት መሪዎች ያመለክታል። በመጀመሪያ፥ ኤጲስ ቆጶሳት ነበሩ። አዲስ ኪዳንን በጥንቃቄ ስናጠና ዐበይት የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ሽማግሌዎችና ኤጲስ ቆጶሳት ይባሉ እንደነበረ እንረዳለን። በግሪክ ባሕል፥ ኤጲስ ቆጶስ የሃይማኖታዊ ወይም የፖለቲካዊ ድርጅት መሪ ነበር። ጳውሎስ በዚህ ስፍራ ቃሉን የጠቀሰው የቤተ ክርስቲያንን መሪዎች ለማመልከት ነው። በሌሎች ስፍራዎች፥ ይህ ቃል «ሽማግሌዎች» የሚል ፍች ተሰጥቶታል (የሐዋ. 14፡23፣ 1ኛ ጢሞ. 5፡17)። ሁለቱም ተመሳሳይ ዓይነት መሪዎች ናቸው። በአዲስ ኪዳን ቤተ ክርስቲያን ውስጥ፥ ከአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎች ያለፈ የአመራር ደረጃ አልነበረም (ከሐዋርያት በስተቀር)። ክልላዊ ወይም ብሔራዊ የቤተ እምነት መሪዎች አልነበሩም። እነዚህ የአመራር ደረጃ ዎች የተመሠረቱት በኋላ ነው። አዲስ ኪዳን ቤተ ክርስቲያንን በሥልጣን ማስተዳደሩ የተዋረዳዊ መሪዎች ሳይሆን የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን መሪዎች ኃላፊነት እንደሆነ ያስረዳል። አጥቢያዊ መሪዎች የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ምእመናንን የመምራት፥ የመጠበቅና የማስተማር ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል። ሁለተኛ፥ «ዲያቆናት» ነበሩ። በኮሚኒዝም ዘመን የወጣት ቡድኖችን አባላት ዲያቆናት እያሉ መጥራት የተለመደ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ ግን ይህንን ቃል የሚጠቀመው የተወሰነ የመሪነት ዓይነትን ለማመልከት ነው። በግሪክ ቋንቋ፥ ቃሉ «የሚያገለግል» የሚል ፍች አለው። እንዲህ ዓይነት መሪዎች የተመሠረቱት በሐዋርያት ሥራ 6፡1-6 ነው። እነዚህ ወገኖች ኤጲስ ቆጶሳት በጸሎት፥ በማስተማርና ቤተ ክርስቲያንን በመምራቱ አገልግሎት ላይ ያተኩሩ ዘንድ በማገዝ ድሆችን እንደ መንከባከብ ያሉትን ተግባራት ያከናውኑ ነበር። በአዲስ ኪዳን ቤተ ክርስቲያን፥ ዲያቆናት መባ መሰብሰብ ብቻ ሳይሆን ጠቃሚ አገልግሎቶችን ያካሂዱ ነበር። የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) እነዚህ ሁለት የአመራር ደረጃዎች በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ አሉ? ለ) ከሆነ፥ በእያንዳንዱ የመሪነት ኃላፊነት ላይ የሚገኙ ሰዎች የሚያከናውኗቸው ተግባራት ምን ምንድን ናቸው? ሐ) እነዚህ መሪዎች የአገልግሎት ደረጃዎቹ በአዲስ ኪዳን ውስጥ ካገለገሉበት ሁኔታ ጋር የሚነጻጸሩት እንዴት ነው? ጳውሎስ መጀመሪያ ወንጌሉን ወደ ፊልጵስዩስ ያደረሰው በ49 ወይም በ50 ዓ.ም በሁለተኛው የወንጌል መልእክተኝነት ጉዞው ነበር። በአውሮፓ ወንጌልን ለመጀመሪያ ጊዜ የሰበከው በዚህች ከተማ ነበር። የፊልጵስዩስ ከተማ ጳውሎስ ከመርከብ ከወረደበት ስፍራ 15 ኪሎ ሜትሮች ያህል ርቃ ትገኝ ነበር። ፊልጵስዩስ በሮም የመቄዶንያ ግዛት ውስጥ ከሚገኙት አውራጃ ዎች ትልቋ ነበረች። ጥድፍያ በበዛበት የንግድ መንገድ ላይ ከመገኘቷ የተነሣ የፊልጵስዩስ ከተማ ለአካባቢዋ አገሮች ዐቢይ የገበያ ማዕከል ነበረች። የዚህች ከተማ ነዋሪዎች በአብዛኛው የሮም ዜግነት ያላቸው፥ የሮማውያንን የአለባበስ ስልት የሚከተሉና የሮም ቋንቋ የሆነውን ላቲን የሚናገሩ ነበሩ። ከተማይቱ ከሮም ሹመት ውጭ ራሷን የማስተዳደር መብት ነበራት። በከተማይቱ ውስጥ ጥቂት አይሁዶች ብቻ ስለነበሩ፥ ጳውሎስ የስብከት ተግባሩን የሚያከናውንበትን ምኩራብ ሊያገኝ አልቻለም። ይህ ሕዝቡ ለአይሁዶች የነበረውን ጥላቻ የሚያመለክት ሊሆን ይችላል። ወንጌሉ ወደ መቄዶንያና ወደ ፊልጵስዩስ የመጣው በጳውሎስ ዕቅድ ሳይሆን በእግዚአብሔር ጣልቃ ገብነት ነበር። ጳውሎስ በሁለተኛው የወንጌል መልእክተኝነት ጉዞው ወንጌል ያልደረሰባቸውን የትንሹ እስያ አካባቢዎች ለማካለል ሞክሮ ነበር። ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ ከመንገድ ላይ አስቆመው። በመጨረሻም፥ ጳውሎስ በትንሹ እስያ ምዕራባዊ ጫፍ ወደምትገኘው ጢሮአዳ (የዛሬዋ ቱርክ) ደረሰ። ጳውሎስ ወዴት እንደሚሄድ አያውቅም ነበር። ከዚያ በኋላ ግን እግዚአብሔር ለፊልጵስዩስ ራእይ አሳየው። በራእዩ ውስጥ ጳውሎስን አንድ ሰው ወደ መቄዶንያ አልፎ እንዲረዳው ይጠይቀዋል። በ50 ዓ.ም አካባቢ ጳውሎስ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አውሮፓ አደረሰው። ወዲያውም ክርስትና በአውሮፓ ታላቅ ሃይማኖት ሆነ። ጳውሎስ በዋና ዋና ከተሞች ውስጥ በመስበኩ ላይ ስለሚያተኩር ነበር ወደ ፊልጵስዩስ ከተማ የተጓዘው። በዚያ ስፍራ ምኩራብ ስላልነበረ፥ ጳውሎስ ከወንዙ አካባቢ ለተሰበሰቡት አይሁዶች ወንጌሉን በመስበክ አገልግሎቱን ጀመረ። በዚያም ሊድያ የተባለች ሴት የመጀመሪያዋ አማኝ ሆነች። ከአፍታ በኋላ አነስተኛ ቤተ ክርስቲያን ተመሠረተች። በሰይጣን ኃይል ወደፊት ምን እንደሚከሠት እየጠነቆለች ለጌቶቿ ገንዘብ ከምትሰበስብ ባሪያ ላይ አጋንንትን ባስወጡ ጊዜ ግን ጳውሎስና ሲላስ ወደ ወኅኒ ቤት ተወረወሩ። በወኅኒ ቤቱ ውስጥ ድብደባ ተፈጸመባቸው። ይሁንና ጳውሎስና ሲላስ ለእግዚአብሔር የምስጋና መዝሙር እየዘመሩ በደስታ ያመልኩ ነበር። ምስክርነታቸውም የወኅኒ ቤቱን ጠባቂ ቤተሰቦች ወደ ክርስቶስ አፈለሱ። የፊልጵስዩስ ቤተ ክርስቲያን ምን ያህል ሰፊ እንደነበረች አናውቅም። ምእመኖቿ ሙሉ በሙሉ ማለት ይቻላል አሕዛብ ነበሩ። ጳውሎስ በፊልጵስዩስ ብዙ ሊቆይ ባለመቻሉ ወደ ተሰሎንቄ ተጓዘ። ነገር ግን ጳውሎስ ከፊልጵስዩስ ቤተ ክርስቲያን ጋር የጠበቀ ግንኙነት ስለነበረው ፊልጵስዩስ ለእርሱ ተወዳጅ ቤተ ክርስቲያን ነበረች። ይህች ቤተ ክርስቲያን የጳውሎስን አገልግሎት ትደግፍ ነበር (2ኛ ቆሮ. 11፡9፤ ፊልጵ. 4፡15)። እንዲያውም ጳውሎስ ይህን መልእክት ከጻፈባቸው ምክንያቶች አንዱ ለስጦታቸው ማመስገን ነበር። ጳውሎስ በሦስተኛው የወንጌል መልእክተኝነት ጉዞው የፊልጵስዩስን ቤተ ክርስቲያን ሁለት ጊዜ ጎብኝቷታል። ጳውሎስ የፊልጵስዩስን መልእክት የጻፈበት ዘመንና ስፍራ ጳውሎስ «የእሥር ቤት መልእክቶችን (ፊልጵስዩስን ጨምሮ) ከእሥር ቤት ውስጥ ሆኖ እንደ ጻፋቸው ከኤፌሶን ጥናት ተመልክተናል።» ምሁራን ጳውሎስ ፊልጵስዩስን በጻፈበት ወቅት የት ቦታ ታሥሮ እንደነበረ የሚያስረዱ ሦስት አሳቦችን ያቀርባሉ። ጥቂት ምሁራን ቂሣሪያ ሊሆን እንደሚችል ይናገራሉ። ይኼ አሳብ ግን ብዙ ድጋፍ የለውም።

የፊልጵስዩስን መልእክት ማን ጸፈው፣ ለማን ተጻፈ፣ መቼና የት ተጻፈ Read More »

የፊልጵስዩስ መልእክት መግቢያ

ወንጌላዊ ተገኘወርቅ ከነበረበት ስፍራ ወደ ሌላ አካባቢ ሄዶ ወንጌልን እንዲሰብክ ተልኮ ነበር። በዚሁ ስፍራ ለ10 ዓመታት ሲያገለግል እግዚአብሔር በሚገባ ባረከው። ከ20 የሚበዙ አብያተ ክርስቲያናት ተመሠረቱ። ይሁንና፥ ብዙም ጎልቶ ሳይታይ የቆየው ተቃውሞ ይበልጥ እየተጠናከረ መጣ። አንድ ቀን ተገኘወርቅ በነበረባት ከተማ ውስጥ የሚገኝ አንድ ሱቅ ተዘረፈ። በዚህም ጊዜ ጠላቶቹ ተገኘወርቅ ዝርፊያውን ሲፈጽም መመልከታቸውን ተናገሩ። በመሆኑም፥ ተገኘወርቅ በፖሊስ ተይዞ ፍርድ ቤት ከቀረበ በኋላ የ5 ዓመታት እስራት ተፈረደበት። ተገኘወርቅ ራሱን በወኅኒ ቤት ውስጥ ሲያገኘው ደነገጠ። ንጹሕ ሆኖ ሳለ እግዚአብሔር እንዴት እንዲህ ዓይነት ሁኔታ እንዲደርስበት ፈቀደ? አገልግሎቱስ እንዴት ይሆናል? «እግዚአብሔርን ለማገልገሌ የማገኘው ወሮታ ይኼ ከሆነ፥ ማገልገሉ ተገቢ አይደለም» ሲል አሰበ። በምሬት ተሞልቶ በእግዚአብሔር ላይ ተቆጣ። ብዙነሽ በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ በዋናነት ከሚታወቁ ሴቶች አንዷ ነበረች። ይህች እኅት የጸሎት ቡድኖችንና የሴቶች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን በታማኝነት ትመራ ነበር። አንድ ቀን ባሏና ልጆቿ ዘመድ ለመጠየቅ በአውቶቡስ ተሳፍረው ይጓዙ ነበር። በዚህ ጊዜ አውቶቡሱ ተገልብጦ ገደል ውስጥ በመግባቱ ባሏና ልጆቿ ሞቱ። ብዙነሽ ጥልቅ ኃዘን ደረሰባት። ባለቤቷ የሚያመጣው ገቢ ከቆመ በኋላ እንዴት ልትኖር እንደምትችል ሊገባት አልቻለም። ምንም እንኳን ጥያቄዎች አእምሮዋን ቢያጨናንቁና እግዚአብሔር እንዲህ ዓይነቱ አሳዛኝ ሁኔታ እንዲከሰት እንዴት ሊፈቅድ እንደቻለ ባትረዳም፣ እግዚአብሔር ሁኔታዎችን በመቆጣጠር ላይ እንደሆነና ምንም ዓይነት ክፉ ነገር እንዲከሰት እንደማይፈቅድ ታውቅ ነበር። ስለሆነም፥ ምንም እንኳን ልቧ በኃዘን ቢቆስልም፥ እግዚአብሔርን በደስታ ከማገልገል አልተቆጠበችም። የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) የብዙነሽ አመለካከት ከተገኘወርቅ የሚለየው እንዴት ነው? ለገጠሟቸው ሁኔታዎች የተለያዩ ምላሾችን የሰጡት ለምንድን ነው? ከሁለቱ እግዚአብሔርን ይበልጥ ደስ የሚያሰኘው የትኛው ምላሽ ነው? ለ) ፊልጵስዩስ 1፡12-19፤ 4፡4 አንብብ። ጳውሎስ ለደረሰበት እሥራት ምን ዓይነት አመለካከት ነበረው? ጳውሎስ ክርስቲያኖች በሁሉም ሁኔታዎች ውስጥ ምን እንዲያደርጉ አዘዘ? ሐ) በሕይወታችን ውስጥ ነገሮች እንደምንጠብቃቸው በማይሆኑበት ጊዜ የብዙነሽን ዓይነት ምላሽ ለመስጠት እንችል ዘንድ ስለ እግዚአብሔር ልናስታውሳቸው የሚገቡ አንዳንድ ነገሮች ምን ምንድን ናቸው? ጳውሎስ በኢየሩሳሌም ለሚገኙ መሪዎች ለመታዘዝ ሲል ወደ ቤተ መቅደስ ተጉዞ መሥዋዕት አቀረበ። አይሁዶች ተግባሩን በተሳሳተ መንገድ በመረዳታቸው ሊገድሉት ሞከሩ። ይሁንና፥ የሮም ወታደሮች ጳውሎስን አሠሩት። ጳውሎስ ወንጌሉን ይዞ ወደ ሮምና ከዚያም ወደ ስፔይን የመሄድ ዕቅድ ነበረው። ጳውሎስ ይህ እግዚአብሔር የፈቀደለት ተግባር እንደሆነ ያስብ ነበር። እግዚአብሔር ግን የተለየ ዕቅድ ነበረው። እግዚአብሔር እጅግ የላቀ የወንጌል ሰባኪነት ስጦታ ያለው አገልጋዩ ከቦታ ቦታ ተዘዋውሮ እንዳይሠራ እስር ቤት ውስጥ የሚያጉረው ለምን ይሆን? ከኢየሩሳሌም እግዚአብሔር ለከተማይቱ ትመሰክርልኛለህ እንዳለው ሁሉ ወደ ሮም ሄደ። ነገር ግን ጳውሎስ ጉዳዩን ከፍርድ ችሎት ፊት ለማቅረብ ለሁለት ዓመታት ያህል መጠበቅ ነበረበት። ይህም ወንጌሉን ወደ ስፔይን የማድረስ ዕቅዱን አጓተተበት። እግዚአብሔር ከብዙ ዓመታት በፊት ጴጥሮስን እንዳዳነው ለምን ጳውሎስን ከእስራት ነፃ አላወጣውም? (የሐዋ. 12) ለጳውሎስ እንደ ተገኘወርቅ በመራርነት መሞላቱ ቀላል ነበር። ጳውሎስ ግን እግዚአብሔር በሚያስቀምጠው ስፍራ ሁሉ ደስ ሊሰኝ እንደሚችል ተናግሯል። በነጻነትም ሆነ በእሥራት ጊዜ በጌታ ደስ ይለዋል። ይህንን ሊያደርግ የቻለው እንዴት ነበር? ቀዳሚው ምክንያት ጳውሎስ እግዚአብሔርን ማወቁ ነው። እግዚአብሔር ሁኔታዎችን እንደሚቆጣጠርና በእሥር ቤት ውስጥ መገኘቱ በአጋጣሚ የተከሠተ ጉዳይ እንዳልሆነ ተገንዝቦ ነበር። እግዚአብሔር ልጆቹን ስለሚወድ የዕቅዱ አካል ያልሆነና ለልጆቹ መልካም ያልሆነ ነገር እንዲፈጸም የሚያደርግ አለመሆኑን ያውቅ ነበር። ስለሆነም፥ ጳውሎስ በመከራ፥ በሥቃይ፥ በስደትና ግራ በመጋባት መካከል ሆኖ ደስ ሊሰኝ ችሏል። ጳውሎስ የፊልጵስዩስ፥ የኤፌሶን፥ የቆላስይስና የፊልሞና መልእክቶችን የጻፈው በእስር ቤት (ምናልባትም ሮም) ውስጥ ሆኖ ነበር። ጳውሎስ ለመራርነት ራሱን አሳልፎ ባለመስጠቱ እግዚአብሔር በእሥር ቤት ውስጥ በነበረበት ጊዜ እጅግ አስፈላጊዎቹን መልእክቶች እንዲጽፍ አድርጎ ሊጠቀምበት ችሏል። ስለሆነም፥ ይህ የእሥራት ጊዜ በጳውሎስ ሕይወት ውስጥ የባከነ ጊዜ አልነበረም። ጳውሎስ ወንጌሉን በይፋ ለመስበክ ያልቻለባቸው ሁለቱ ዓመታት በመልእክቶቹ አማካኝነት ለሁለት ሺህ ዓመታት እንዲሰብክ ያሚያስችሉት መሆናቸውን አልተገነዘበም ነበር። የፊልጵስዩስ መልእክት በጳውሎስ ደስተኛነት ላይ ያተኩራል። «ደስታ» የሚለው ቃል በዚህ መልእክት ውስጥ ለ16 ጊዜያት ያህል የተጠቀሰ ሲሆን፥ ጳውሎስ ለአማኞች ለማስተማር ከፈለጋቸው ወሳኝ እውነቶች አንዱ ነበር። የውይይት ጥያቄ፡- ፊልጵስዩስ 1፡1ን አንብብ። የመጽሐፉ ጸሐፊ ማን ነው? መጽሐፉ የተጻፈው ለማን ነው? የውይይት ጥያቄ፡– ስለ ፊልጵስዩስ በመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ውስጥ የተጻፈውን አንብብ። ስለ ጸሐፊው፥ ስለ ከተማይቱ፥ ስለ ቤተ ክርስቲያኒቱና ስለ መልእክቱ ዓላማ የተገለጸውን አሳብ ጠቅለል አድርገህ ጻፍ። (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የፊልጵስዩስ መልእክት መግቢያ Read More »