የመንፈስ ቅዱስ የጥናት መምሪያና ማብራሪያ

ስለ ተአምራትና ፈውሶች የሚሰጡ የተሳሳቱ አሳቦች

ተአምራትና ፈውሶች በዚህ ዘመን ስላላቸው ሚና ሁልጊዜ አከራካሪ አሳቦች ይነሣሉ። የሚያሳዝነው ነገር ብዙ ጊዜ ክርስቲያኖች በአንድ እቅጣጫ ማክረራቸውና ሰዎች የእነርሱን አመለካከት እንዲቀበሉ ለማስገደድ መሞከራቸው ነው። አቋማችንን በትሕትና መያዝ አለብን። ሆኖም ግን እንደማምነው ምንም መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት የሌላቸውና ልንርቃቸው የሚገቡን አንዳንድ ትምህርቶች አሉ።  1. ስለ መንፈስ ቅዱስ በምናደርገው ጥናት በተደጋጋሚ እንደተመለከትነው ተአምራትንና ፈውሶችን በተመለከተ ያሉት ክፍተኛ ችግርች ወደ ከረሩ አቅጣሚዎች መሄድ ነው። አንደኛው የከረረ አቋም እግዚአብሔር ፈውስን ለማምጣት ሰዎችን ዛሬ አይጠቀምም የሚል ነው። ከሐዋርያት ሞት በኋላ እግዚአብሔር ፈውስን መስጠት አቁሟል ማለት ወይም ዛሬ የምንመላከታቸው ፈውሶች ሁሉ ከዲያብሎስ ናቸው ወይም እውነተኛ ያልሆኑ ማስመሰያዎች ናቸው ማለት አደገኛ ነው። ከሐዋርያት ሞት ወይም አዲስ ኪዳን ተጽፎ ካለቀ በኋላ ተአምራት ቆመዋል የምንልበት ምንም መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት የለንም። እንደዚህ ይነት ዐረፍተ ነገር በራስ አመለካከት የመንፈስ ቅዱስን ሥራ ለመቆጣጠር መፈለግን የሚያመለክት ነው። የመንፈስ ቅዱስን አገልግሎት በመገደብ በአንድ መንገድ ብቻ ይሠራል ከማለት መጠንቀቅ አለብን።  2. ወደ ሌላኛው የከረረ አቋም ስንሄድ ሁልጊዜ ፈውሶችንና ተአምራትን መፈለግ ደሞ አደገኛ ነው። ብዙ ክርስቲያኖች በፈውሶች እጅግ ይደነቃሉ። ወደ ስብሰባዎች የሚሄዱት የእግዚአብሔርን ቃል ለመማር መሆኑ ብዙ ሳይቆይ ይቀርና በመንፈስ ቅዱስ ለመዝናናት ይሆናል። መንፈስ ቅዱስ ፈውስን እንዲያደርግ ይፈልጋሉ። አንዳንድ ጊዜም ፍላጐታቸው የማስገደድ ያህል ነው። ከእንደዚህ ዓይነት ክርስቲያኖች አብዛኛዎቹ እነርሱ በፈለጉት መንገድ እግዚአብሔር ተአምራትን ሳያደርግ ሲቀር እምነታቸውን ይተዋሉ።  3. ሌላው አደጋ እምነታችንን በእግዚአብሔር ላይ ከማድረግ ይልቅ በተአምራት ላይ ማድረጋችን ነው። ተአምራትን ያለማቋረጥ መፈለግ የሰውን እምነት ለማሻሻሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያለው ማረጋገጫ አነስተኛ ነው። ታላላቅ ተአምራት በተፈጸሙባቸው ጊዜያት (እስራኤላውያን በምድረበዳ በነበሩበት ጊዜ፥ በኤልያስ፥ በኤልሳዕ ወይም በኢየሱስ ዘመን ብዙ ሰዎች እጅግ በርካታ ተአምራት እየተመላክቱ እንኳ ለማመን ፈቃደኞች አልነበሩም። ወይም ለጊዜው እጅግ ይደነና ወዲያውኑ እግዚአብሔርን ከመከተል ይልቅ በራሳቸው አሳብ ይጓዙ ነበር። በሕይወት ከምንማራቸው እጅግ ጠቃሚ ከሆኑ ትምህርቶች እንዱ ለማመናችን የሚታይ ውጫዊ ችሮታ ሳንፈል. እግዚአብሔርን መከተል መማር ነው። የተስፋይቱን ምድር እንዳልወረሰው እንደ አብርሃም የእግዚአብሔር የተስፋ ቃሎች በሙሉ ወደሚፈጸሙበት ወደ ዘላላም ዓይኖቻችንን በማተኮር መማር አለብን (ዕብ. 11፡8-10፥16)።  4. «እግዚአብሔር በሽታዎችን ሁሉ ይፈውስ ዘንድ ቃል ገብቶልናል።» ይህ አሳብ በክርስቲያኖች መካከል በከፍተኛ ደረጃ የተሳሳተ መረዳትን ያስከተለ ጉዳይ ነው። በአዲስ ኪዳን የጳውሎስ ወዳጆች ታመው ጳውሎስ ፈውስን ሊያመጣላቸው ያልቻለበት ጊዜያት ነበሩ። (ለምሳሌ አፍሮዲጡ (ፊልጵ. 2፡27)። ጢሞቲዎስ (1ኛ ጢሞ. 5፡23)፥ ጥሮፊሞስ (2ኛ ጢሞ. 4፡20)። ጳውሎስ እራሱም (ገላ. 4፡13-14)። ስለዚህ እግዚአብሔር ፈውስን ሁልጊዜ እንደማያከናውን ግልጽ ነው። እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ እንድትናገር በልብህ ሳያስቀምጥ አንድ ሰው እንደሚፈወስ መናገር የአጉል መተማመን ኃጢአት ነው። የእግዚአብሔር መንገዶች ዓላማዎች ከእኛ የራቁ ናቸው። እግዚአብሔር ሊፈውስ እንደሚችል እናውቃለን ደግሞ ይፈውስ ይሆናል። ነገር ግን አንድ ሰው እንደሚፈወስ እግዚአብሔር ካልነገረን ይፈወሳል ብሎ መናገር ስሕተት ነው። እግዚአብሔር ልጆቹ በሕመም እንዲሰቃዩ ደግሞም እንዲሞቱ ብዙ ጊዜ ይፈቅዳል። ነገር ግን የትንሣኤ ዋስትና ላለን በሽታና ሞት ለክርስቲያን ቋሚ ችግርች እንዳልሆኑ እናውቃለን።  5. ክርስቲያኖች ለታመመ ሰው ሊናገሩት የሚችሉት እጅግ ዘግናኝና ጐጂ አባባል አንዱ «ያልተፈወስከው እምነት ስለሌለህ ወይም በሕይወትህ ኃጢአት ስላለ ነው» የሚል ነው። ይህ አባባል ከፊል እውነት አለው። የእምነት ማነስ ወይም የኃጢአት በሕይወታችን መኖር ፈውስ እንዳንቀበል ሊያግደን ይችላል። እነዚህ ፈውስ ላለመኖሩ አንደኛዎቹ ምክንያቶች ናቸው። ነገር ግን ብቸኛዎቹ ምክንያቶች አይደሉም። ብዙ ሰዎች ለመፈወስ እምነት እያላቸው አይፈወሱም። ብዙ ሰዎች ንስሐ ያልገቡበት ኃጢአት በሕይወታቸው ባይኖርም ፈውስን ግን አይቀበሉም። ስለዚህ አንድ ሰው ፈውስን ያልተቀበለው በኃጢአት ወይም ባለማመን ምክንያት መሆኑን እግዚአብሔር በልዩ ሁኔታ ካልተናገረህ በስተቀር በጭራሽ በጭራሽ በጭራሽ ያልተፈወስኸው በኃጢአት ባለማመን ምክንያት ነው አትበል። የሰውን ልብ የሚያውቅ እግዚአብሔር ብቻ ስለሆነ የፍርድን ቃል መናገር ተገቢ አይደለም። እግዚአብሔር እንደ እምነታችን ለመሥራት የተወሰነ አይደለም። ኢየሱስ እምነት እንደነበራቸው ምንም ምልክት የማይታይባቸውን ሰዎች ፈውሷል።  6. ሌላው አባባል «መንፈስ ቅዱስን ተአምራት እንዲያደርግ ላዝዘው እችላላሁ፤ እምነት ካለኝ ይህን ለማድረግ አያቅተኝም» የሚል ነው። ማንም ሰው መንፈስ ቅዱስን ተአምራት ያደርግ ዘንድ ለማዘዝ አይችልም። መንፈስ ቅዱስ እግዚአብሔር ነው። አንድን ነገር እንዲያደርግልን ለማስገደድ ፈጽሞ መሞከር የለብንም። እርሱ ጌታ ነውና ለእርሱ ተገዝተን መኖር አለብን። በማንኛውም ወቅት መንፈስ ቅዱስ ቢሠራ የተደረገው ነገር በእርሱ ምሕረት እንጂ የሚገባን ስለሆንን አይደለም። የሚፈጸመው የተአምራት መጠን በእምነት መጠን አይደለም። ማንኛውም ተአምራት በእግዚአብሔር ማንነት መጠን ላይ የሚወሰን ነው። እንደ ክርስቲያን የምናገለግለው ታላቅ አምላክ ስለሆነ ወደ እርሱ ከተመለከትን ሁልጊዜ ከግምታችን በላይ በሆኑ መንገዶች ይሠራል።  7. «እግዚአብሔር አንድ ሰው እንደሚፈወስ እናገር ዘንድ መብት ከሰጠኝ ሁሉም ሰው ይፈወስ ዘንድ የመናገር ኃይል አለኝ ማለት ነው። ስለዚህ ትላልቅ የአደባባይ ስብሰባዎችን በማዘጋጀት ሁሉንም ሰው መፈወስ አለብኝ» የሚል አመለካከትም አለ። እግዚአብሔር ለአንድ ሰው ብዙ ሰዎችን የመፈወስ ኃይል እንደ ሰጠ መጽሐፍ ቅዱስ የትም ቦታ አያመለክትም። ኢየሱስም እንኳ የተሰበሰቡትን ሰዎች በሙሉ የፈወሰበት ጊዜ አንዴም አልነበረም።  8. «እግዚአብሔር ደረጃ በደረጃ ይፈውሳል። አሁን በከፊል ይፈውሰኛል። ጸሎቴን በቀጠልኩ ቁጥር የበለጠ እየተፈወስኩ እሄዳለሁ።» በአንድ በኩል እግዚአብሔር ይህን ያደርግ ዘንድ የሚያግደው የለም። ነገር ግን እንዲህ ዓይነት ሰውን ደረጃ በደረጃ የመፈወስ አሠራር መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የለም። እግዚአብሔር አንድን ሰው እንደ ፈወሰ ተናግሮ ፍጹም ያልዳነበት ወቅት የለም። እንደዚህ ዓይነት ልምድ ፈጽሞ ስላልነበረ እንደዚህ ይሆናል ብለን ከመናገር መቆጠብ አለብን።  ጥያቄ፡- ሀ) በአሁኑ ጊዜ ባሉ ቤተ ክርስቲያኖች ከላይ ከጠቀስናቸው የተሳሳቱ አመለካከቶች የትኞቹ ዘወትር ይንጸባረቃሉ? ለ) በከፊል እውነት የሚሆኑት በምን ዓይነት መንገድ ነው?  ጥያቄ፡- ሀ) የቤተ ክርስቲያን መጋቢ ነህ። ከአባላትህ አንዱ ታምሟል እንበል። በዚህ ትምህርት የተጠቀሱትን መርሆዎች በመጠቀም ምን እንደምታደርግ አስረዳ። ምንጭ፡- “የመንፈስ ቅዱስ የጥናት መምሪያና ማብራሪያ”፣ በቲም ፌሎስ ተጽፎ፣ በጌቱ ግዛው የተተረጎመ እና በኤስ አይ ኤም ጽሑፍ ክፍል የተዘጋጀ ነው፡፡ ለዚህ ድንቅ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡ ይህን ጽሁፍ ኮፒ እና ፕሪንት አድርጎ መጠቀም ይቻላል፤ ሆኖም ጽሁፉን መለወጥና ለሽያጭ ማዋል በሕግ የተከለከለ ነው፡፡

ስለ ተአምራትና ፈውሶች የሚሰጡ የተሳሳቱ አሳቦች Read More »

እግዚአብሔር ፈውስን የሚሰጥባቸው የተለያዩ አሠራሮች

ጥያቄ፡- ያዕ. 5፡14–15 አንብብ። ሀ) በዚህ ክፍል በምታገኘው መሠረት የፈውስን ቅደም ተከተሎች አስፍር። ለ) ይህ የፈውስ አሠራር ለመፈወስ ኃይል እንዳላቸው ከሚናገሩት ሰዎች አሠራር ጋር እንዴት ይሄዳል?  እግዚአብሔር አሁንም ይፈውሳልን? አዎን። እግዚአብሔር በቀደሙት ዘመናት ተአምራትን እንዳደረገ ዛሬም ፈውስን የሚያካትቱ ተአምራትን ያደርጋል። እግዚአብሔር የፈውስ ሥራውን አቁሟል ማለት ስሕተት ነው። ነገር ግን እግዚአብሔር ሁልጊዜ ይፈውሳል ማለትም ስሕተት ነው። ኢየሱስ በከነዓን የነበሩትን በሙሉ እንዳልፈወሰና ደቀ መዛሙርትም በአገልግሎታቸው የፈወሱት ያገኙትን ሰው ሁሉ እንዳልሆነ ዛሬም እግዚአብሔር ሰውን ሁሉ እንደሚፈውስ ማስረጃ ማቅረብ እንችልም።  ታዲያ እግዚአብሔር ዛሬ ፈውስን የሚያደርግበት ተለምዶአዊ መንገድ ምንድን ነው? ስንታመም ወይም የምንወደው ሰው ሲታመም ወይም በቤተ ክርስቲያን ያለ አንድ ሰው ሲታመም ምን ማድረግ አለብን? አዲስ ኪዳን የሚከተሉትን ነገሮች ያስተምራል።  1. በመጀመሪያ ስትታመም እግዚአብሔር ይፈውስህ ዘንድ ጸልይ። እግዚአብሔር እየቀጣህ ያለው ያልተናዘዝኸው ኃጢአት እንዳለ እራስህን መርምር። ፈውስን እስኪሰጥህ ድረስ በትዕግሥት በመጠበቅ እግዚአብሔር በዚህ በሽታ ውስጥ ሊያስተምርህ የሚፈልገው ነገር ምን እንደሆነ ጠይቀው። በሽታ ብዙ ጊዜ እግዚአብሔር ልጆቹን ለማስተማር የሚጠቀምበት መሣሪያ ነው።  2. ወደ ሐኪም ወይም በሕክምና ሙያ ወደ ሠለጠነ ሰው በመሄድ ምርመራ አድርግ። እግዚአብሔር ያለ ምንም መድኃኒት ሊፈውሰን ቢችልም እንኳ አእምሮአችንን በመጠቀም ውሳኔ ልናደርግና ተገቢውን የሕክምና እርዳታ ሊሰጠን ወደሚችል ሰው ልንሄድ ይገባናል። ለሕክምና ባለሙያዎች ችሎታንና ሥልጣናን የሰጠ እግዚአብሔር መሆኑን አስታውስ። እግዚአብሔር ፈውስን ለማምጣት መሣሪያው አድርጐ ሊጠቀምባቸው ይችላል። ነገር ግን እምነታችን በመድኃኒት ወይም በሰዎች ሳይሆን ፈውስን ለማምጣት በሰዎች በሚሠራ በእግዚአብሔር እንደሆነ መረዳት እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡  3. የሕክምና እርዳታ ፈውስን ሊያመጣ ካልቻላ ስያዕ. 5 ላይ ያለውን መመሪያ ተከተል። የመፈወስ ስጦታ አለን ወደሚሉ ሰዎች አትሂድ። በምንታመምበት ወቅት እግዚእብሔር በቀጥታ ያላመለከተውን መንገድ ከመከተል መጽሐፍ ቅዱስ የሚለውን መከተል ይሻላል።  ሀ. የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎችን ጥራ።  ለ. ከሽማግሌዎች ጋር በመሆን በእግዚአብሔር ፊት ንጹሕ ትሆን ዘንድ ራስህን መርምር። ብዙ በሽታዎች በቀጥታ የኃጢአት ውጤት ባይሆኑም እግዚአብሔር ያለመታዘዛችንን ለመቅጣት በሽታዎችን አንዳንድ ጊዜ ወደ ሕይወታችን ያመጣል። ኃጢአትን ካደረግን እግዚአብሔር ይፈውሰን ዘንድ ከመጠየቃችን በፊት ተናዝዘን ንስሐ መግባት አለብን።  (ማስታወሻ፡–በሽታ ሁሉ የኃጢአት ውጤት ነው ከማለት እጅግ ተጠንቀቅ። ብዙ ጊዜ አይደለም። እግዚአብሔር ክፉዎችን የሚቀጣበት ጊዜ ቢኖርም እንኳ ብዙ ጊዜ እስከ መጨረሻው የፍርድ ቀን ድረስ ሳይቀጡ ይቆያሉ። ደግሞም እግዚአብሔር ኃጢአትን የሚያደርጉ ክርስቲያኖች አንዳንድ ጊዜ ቢቀጣም እንኳ ሁልጊዜ አይቀጣም (መዝ. [73]፡1-17)። እግዚአብሔር ልዩ በሆነ መገለጥ ችግሩን ካልጠቆመ በስተቀር በሰው ሕይወት ውስጥ ንስሐ ያልተገባበት ኃጢአት እንዳለ የሚያውቁት ግለሰቡና እግዚአብሔር ብቻ ናቸው።  ሐ. ኃጢአትህን ከተናዘዝክ ወይም ሽማግሌዎች ነፃ መሆንህን ካረጋገጡልህ በኋላ ሽማግሌዎች ዘይት ቀብተው ይጸልዩልህ። ለምን ዘይት መቀባት አስፈለገ? ብዙ ክርስቲያኖች በዘይት ውስጥ የተለየ ነገር እንዳለ ስለሚያስቡ ዘይት መኖር አለበት፤ በዘይቱና እርሱ በሚወክለው ነገር አማካኝነት ፈውስ ያመጣል ያላሉ። ይህ ግን ሊሆን የሚችል ነገር አይደለም። በጥንት ጊዜያት ከሁሉ የተሻለና የታወቀ መድኃኒት ዘይት ነበር። በመዝ 23 ላይ እግዚአብሔር ራሳችንን በዘይት የሚቀባ እረኛ መሆኑ የተነገረው ለዚህ ነው። መቀባቱ ፈውስን ለማምጣት የታለመ ነበር። ዘይት መጠቀም ስሕተት ባይሆንም እንኳ ያዕቆብ የሚናገረው ጸሎትን ለበሽታው ተስማሚ ከሆነ መድኃኒት ጋር የማቀናጀት ጉዳይ እንደሆነ አምናለሁ።  መ. ሽማግሌዎች ዘይት ከመቀባት ጋር ሊጸልዩልህ ይገባል። ጸሎት ከመድኃኒት ወይም ከዘይት ጋር ሲቀናጅ እግዚአብሔር ይፈውሳል። ነገር ግን የሚፈውሰው ምንድን ነው? ፈውስን የሚያመጣው ዘይቱ ወይም መድኃኒቱ ብቻ ሳይሆን ጸሎቱም ጭምር ነው። ፈውስን የሚሰጥ እግዚአብሔር ነው።  ሠ. እግዚአብሔር እንደሚያደርግልህ ማመን አለብህ። የእምነት ጉድለት እግዚአብሔር እንዳይነካህና ፈውስን እንዳታገኝ ሊያደርግ ይችላል።  እግዚአብሔር ልዕለ-ተፈጥሮአዊ ፈውስ የሚሰጥበት መንገድ በቤተ ክርስቲያን ጸሎትና ለታመመው ሰው በሚሰጠው መድኃኒት ነው።  4. አንዳንድ ጊዜ እግዚአብሔር ለአንዳንድ ሰዎች የታመመ ሰው መፈወሱን የሚያውጁበት ወይም የሚያሳውቁበት ችሎታ ይሰጣቸዋል። ይህ የፈውስ መንፈሳዊ ስጦታ በመባል ተገልጿል።  በ1ኛ ቆሮ. 12፡9-10 ጳውሎስ ሁለት ተአምራዊ የሆኑ መንፈሳዊ ስጦታዎችን ጠቅሷል። የመጀመሪያው ተአምራት የማድረግ ሌላው ደግሞ የፈውስ ስጦታ ነበር። ከሌሎች መንፈሳዊ ስጦታዎች በተለየ ሁኔታ ለእነዚህ ሁለት ስጦታዎች ጳውሎስ የተጠቀመው የብዙ ቁጥር ማለትዎ የፈውሶችና ተአምራትን የማድረግ ስጦታዎች እያለ ነው። እንዲህ ያደረገው ለምን ነበር? እነዚህ መንፈሳዊ ስጦታዎች በሚሰጠው ሰው ላይ በተደጋጋሚ የመስጠቱንና እንደገና ተመልሶ የመወሰዱን ጉዳይ የሚያመለክት ይመስላል። አትኩሮቱ ሰው ላይ አይደለም። ይህ ስጦታዎች ተብሎ በብዙ የመጠቀሱ ጉዳይ የሚያመለክተው እግዚአብሔር አንድን ሰው ለመፈወስ ሲፈልግ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ላለ ሰው ያንን የታመመ ሰው ለመፈወስ ፈቃዱ እንደሆነ በመግለጥ የታመመው ሰው እንደሚፈወስ እንዲናገር ማድረጉን ነው። ይህ ስጦታ የተሰጠው ሰው ከተናገረ በኋላ ሰውዬው ይፈወሳል። ይህ የፈውስ ስጦታ ግን ከሰውዬው ሊወሰድ ይችላል። በሌላ ሰው ላይ ፈውስ እንዲያውጅ እግዚአብሔር እንደሚናገረው እስኪሰማው ድረስ ጊዜ ሊወስድ ይችላል።  በቤተ ክርስቲያን ያሉ የታመሙ ሰዎች ሁሉ እንደሚፈወሱ ለመናገር ችሎታ የለውም። ይልቁኑ ይህ ሰው የፈውስን ጉዳይ በተናጠል ሊመለከት ይገባዋል። በእያንዳንዱ ወቅት እግዚአብሔር አንድን ሰው እንደሚፈውስ እንዲናገር መንፈሱን ሊያነሣሣለት ይገባል። እግዚአብሔር ፈውስን ያመጣ ዘንድ በሚፈልግበት ጊዜ ሁሉ በአንድ ሰው እንደሚጠቀም ምንም ዋስትና የለም። ይህን ሊያደርግ ይችላል። ነገር ግን የፈውስ መልእክት ለማምጣት በሌላ ሰውም በቀላሉ መጠቀም ይችላል። ስጦታው የሚሰጠው ለቤተ ክርስቲያን እንጂ ለግለሰቦች አይደለም። (ማስታወሻ፡- የፈውስ መልእክት በአንድ ሰው በኩል መምጣቱ ከሰውየው ማንነት ወይም መንፈሳዊ ታላቅነት አድርገን መመልከት እንደሌለብን ማስታወስ እጅግ አስፈላጊ ግዴታ ነው። የሚፈውሰው እግዚአብሔር ብቻ ነው። ሰውዬው እግዚአብሔር የሚያደርገውን ለሕዝቡ ለማሳወቅ የሚጠቀምበት መሣሪያ ብቻ ነው። የመፈወስ ስጦታ ያለው ሰውዩው ነው ብለን ካሰብን እግዚአብሔርን ሳይሆን ሰውዬውን ማክበር ጀምረናል ማለት ነው።  እግዚአብሔር ፈውስን ካልሰጠስ? እራሳችንን መርምረን የመንፈስ ቅዱስን ሥራ የሚያግድ ኃጢአት እንደሌለ ካረጋገጥን በኋላ እንኳ ፈውስ ባይመጣልንስ? እግዚአብሔር እንደሚፈውስ በልባችን ፈጽሞ እያመንን እንኳ እግዚአብሔር ካልሠራና ፈውስን ካላመጣስ? መጽሐፍ ቅዱስ እንደምንፈወስ የሚሰጠን ዋስትና የለም። አንዳንድ ጊዜ እግዚአብሔር በተሰወረ ፈቃዱ በሽታና ሞት እንዲሆኑ ይፈቅዳል። የእግዚአብሔር ዓላማዎች ሁልጊዜ የምንረዳቸው አይደሉም። ነገር ግን ሁለት እውነቶችን እናውቃለን። በመጀመሪያ እግዚአብሔር ነገሮችን ሁሉ ይቆጣጣራል። ስለዚህ በሽታዎች እግዚአብሔር ሳያውቅ ድንገት የሚሆኑ አይደሉም። ሁለተኛ በሽታና ሐዘን እግዚአብሔር ሰዎችን የሚያስተምርባቸው ሁለት ትላልቅ መሣሪያዎች ናቸው። እግዚአብሔር ጳውሎስን የእግዚአብሔር ጸጋ በድካም ጊዜ በቂ እንደሆነ እስተምሮታል (2ኛ ቆሮ. 12፡7-10)። ስለሆነም በሽታ እግዚአብሔር እጅግ አስፈላጊ የሆኑ መንፈሳዊ ትምህርቶችን ለእኛ የሚያስተምርበት መሣሪያ ነው።  ደግሞ በጸሎት መትጋት አለብን። እግዚአብሔር ጸሎታችንን እስኪመልስ ወይም ጥያቄያችንን እንደማይመልስ ነገር ግን በዚያ ሁኔታ ውስጥ እንኖር ዘንድ ችሎታን እንደሚሰጠንና ለክብሩ እንደሚጠቀምበት ዋስትና እስክናገኝ ድረስ ጸሎታችንን መቀጠል አለብን። ምንጭ፡- “የመንፈስ ቅዱስ የጥናት መምሪያና ማብራሪያ”፣ በቲም ፌሎስ ተጽፎ፣ በጌቱ ግዛው የተተረጎመ እና በኤስ አይ ኤም ጽሑፍ ክፍል የተዘጋጀ ነው፡፡ ለዚህ ድንቅ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡ ይህን ጽሁፍ ኮፒ እና ፕሪንት አድርጎ መጠቀም ይቻላል፤ ሆኖም ጽሁፉን መለወጥና ለሽያጭ ማዋል በሕግ የተከለከለ ነው፡፡

እግዚአብሔር ፈውስን የሚሰጥባቸው የተለያዩ አሠራሮች Read More »

ተአምራትና ፈውሶች በአዲስ ኪዳን

አዲስ ኪዳን በተአምራትና ፈውሶች ታሪክ የተሞላ ነው። በተለይ ደግሞ በወንጌላትና በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ የዚህን እውነትነት እንመለከታለን። ዛሬ በቤተ ክርስቲያን ተአምራት ማየት አለብን በሚሉ ሰዎች እነዚህ ተአምራት በምሳሌነት ሲጠቀሱ እንመለከታለን። ሰዎች የመፈወስ መንፈሳዊ ስጦታ እንዳላቸው እንዲናገሩ የገፋፋቸውም ይህ ነው። ፈውስ የአገልግሎታቸው ማዕከል ይሆናል። እጅግ ብዙ ሕዝብ በተሰበሰበት ማንኛውም ሰው ከማንኛውም ዓይነት በሽታ እንዲፈወስ ያውጃሉ። ከእነዚህ ወንጌላውያን እንዳንዶቹ በቴሌቪዥንና በቪዲዮ ይህ አለን የሚሉትን የፈውስ ኃይላቸውን ሀብትና ክብር ለማግኘት ይጠቀሙበታል። የፈውስ መንፈሳዊ ስጦታ የተሰጠበት ዓላማ በእርግጥ ይህ ነውን?  በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተአምራትንና የፈውስን ስፍራ ወደየት ሄደን መመልከት አለብን? ወደ መጽሐፍ ቅዱስ መመለስ አለብን። መጽሐፍ ቅዱስ የፈውስ ስጦታ እንዴት በሥራ ላይ መዋል እንዳለበት በልሳናት የመናገርና የትንቢትን ያህል ዝርዝር መመሪያ አይሰጥም። በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ስጦታው የነበረ ቢሆንም ከፍተኛ ትኩረት ግን አልተሰጠበትም ነበር። የእነርሱ ትኩረት የነበረው በልሳን በመናገር ስጦታ ላይ ነበር።  ተአምራት በአዲስ ኪዳን ውስጥ በኢየሱስ ሕይወትና በሐዋርያት አገልግሎት ያላቸውን ስፍራ ብንመለከት ዛሬ ለዚህ ስጦታ ሊኖረን ስለሚገባ አካሄድ ፍንጭ እናገኛለን። እግዚአብሔር ለመፈወስና ተአምራትን ለማድረግ ሲመርጥ አንድ መመሪያ ይከተላል ወይም ከዚህ ቀደም በሠራበት ተመሳሳይ መንገድ ይሠራል። መንፈስ ቅዱስ ከዚህ በፊት ከሠራበት መንገድ በከፍተኛ ደረጃ የሚለይ ማንኛውም አሠራር በጥንቃቄ ሊመረመር ይገባል። «የፈውስ አገልግሎት ሰዎች ከእግዚአብሔር ይልቅ አገልግሎቱን በሚያካሂደው ሰው ላይ እንዲያተኩሩ የሚያደርግ ከሆነ ይህ የዚያን ሰው አገልግሎት እንድንጠራጠር ሊያደርገን ይገባል።  ጥያቄ፡- «ተእምራትን» ማድረግ የሚችል እግዚአብሔር ብቻ ነው። ስለዚህ ማንኛውንም ዓይነት ተአምራት ካየን ከእግዚአብሔር መሆን አለበት። ይህ አባባል እውነት ይመስልሃል ወይስ ውሸት? መልስህን አብራራ።  በኢትዮጵያ የሚገኝ አንድ የቤተ ክርስቲያን መሪ እንዲህ አለ። «ተአምራትን ማድረግ የሚችል እግዚአብሔር ብቻ ነው። ስለዚህ ማንኛውም ተአምራት ከእግዚአብሔር መሆን አለበት።» ይህ እውነት ነውን? ተአምራትን ማድረግ የሚችል እግዚአብሔር ብቻ ነውን? ሰይጣን ተአምራትን ማድረግ ይችላልን? ለዚህ በአዲስ ኪዳን ግልጽ የሆነ መረጃ እናገኛለን። እግዚአብሔር የተአምራት አምላክ ቢሆንም እንኳ ሰይጣንም ደግሞ ተአምራት የማድረግ ኃይል ያላውና ሰዎችም ተአምራት እንዲያደርጉ የሚያስችል ነው። የተአምራትና የፈውስ መኖር ከእግዚአብሔር ለመሆናቸው ማስረጃ አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያስተምረን በመጨረሻው ዘመን በምድር ላይ ሐሰተኛ አስተማሪዎችና ነቢያት ይነሣሉ። ከእነዚህ አንዱ ሰዎችን ከሙታን እስኪያስነሣ ድረስ ኃይል ይሰጠዋል (ራእይ 16፡14፤ 2ኛ ተሰ. 2፡9 ተመልከት)። የጠንቋዮችን ሥራ የሚያውቁ ሁሉ ጠንቋዮች ተአምራትን እንደሚያደርጉ ይገነዘባሉ። ሰይጣን ሰዎች እርሱንና ተከታዮቹን እንዲከተሉአቸው የሚያደርገው እንዴት ነው? ብዙ ጊዜ ሰዎች እንዲከተሉት ኃይሉን በማሳየት ነው።  እንደ ብዙዎቹ መንፈሳዊ ስጦታዎች የተአምራትና የፈውስ ስጦታዎች መመዘን አለባቸው። ተአምራቱ ከእግዚአብሔር ዘንድ ለመሆናቸው እርግጠኞች መሆን አለብን። ስለዚህ ተአምራት በኢየሱስና በመጀመሪያዎቹ ሐዋርያት የነበራቸውን ስፍራ በመመርመር ጥናታችንን እንጀምር። ብዙ ሰዎች ዛሬ ተአምራትንና ፈውስን የሚለማመዱባቸው መንገዶች ከአዲስ ኪዳን መንገድ የሚለዩት በዓይነት ሳይሆን በዝንባሌ ነው። ልንጠይቃቸው ከሚገቡ እጅግ አስፈላጊ ጥያቄዎች አንዱ ኢየሱስ ተአምራትን ለምን አደረገ? የሚለው ነው። ይህ ጥያቄ እጅግ አስፈላጊ የሚሆንበት ምክንያት እግዚአብሔር ዛሬ ተአምራት የሚያደርግበት ምክንያት ከዚህ ቀደም ለኢየሱስና ለመጀመሪያይቱ ቤተ ከርስቲያን ካደረገበት ጋር ተመሳሳይ በመሆኑ ነው። ልንከተላቸው የሚገቡ ምሳሌዎች ናቸው። ተመሳሳይ የልምምድ ዓላማዎች፥ ዝንባሌዎችና አቀራረቦች የሌላቸው ነገሮች ከእግዚአብሔር እንጂ ከሰይጣን አለመሆናቸው በጥንቃቄ መመርመር አለበት።  ተአምራትና ፈውሶች በክርስቶስ ዘመን  ጥያቄ፡- የሚከተሉትን ጥቅሶች በማንበብ ኢየሱስ የፈጸማቸውን የተለያዩ ተአምራት ዘርዝር። ሉቃ. 4፡38-41፤ 5፡12-14፤ 17-26፤ 6፡6-11፤ 7፡1-7፤ 8፡26-58፤ 9፡10-17።  በወንጌል ውስጥ ስለ ኢየሱስ ታሪክ በምናነብበት ጊዜ በእያንዳንዱ ገጽ ኢየሱስ ስለፈጸማቸው ተአምራት የተጻፈ ነገር አለ ለማለት ያስደፍራል። ተአምራቱ ብዙ ዓይነት ነበሩ። የፈውስ፥ እውርን የማብራት፥ደንቆሮን የመክፈት፥ ሙታንን የማስነሣት፥ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን የመመገብ፥ ወዘተ… ተአምራት ነበሩ።  ኢየሱስ ተአምራትን ያደረገባቸው ምክንያቶች ምን ምን ነበሩ? ምከንያቶቹን በሙሉ ባናውቅም እንኳ አዲስ ኪዳን የሚከተሉትን አሳቦች ይጠቁማል።  1. ኢየሱስ ተአምራትን ያደረገው በብሉይ ኪዳን ዘመን እንደሚመጣ የተነገረለት መሢሕ እርሱ እንደሆነ ለሕዝቡ ለማሳየት ነበር (ዮሐ 10፡25-26፤ 14፡11)።  2. ተአምራትና ፈውሶች ብዙ ጊዜ የተደረጉት ኢየሱስ እግዚአብሔር መሆኑን ለማሳየት ነበር። በተፈጥሮ፥ በበሽታ፥ በሰይጣን፥ በቦታ ርቀት፥ ወዘተ… ላይ ሥልጣን እንዳለው የሚያሳዩ ነበሩ።  3. ኢየሱስ ለሕዝቡ ይራራ ስለነበር አንዳንድ ጊዜ በዚህ ምክንያት ተአምራትን አድርጓል። ለምሳሌ አምስት ሺህ ሰዎችን የመገበው ምግብ እንዳልነበራቸው በማየት ነበር (ዮሐ 6፡1-13)። ከኢየሱስ ተአምራት አብዛኛዎቹ ድሆችን፥ ያልታደሉትን፥ የተናቁትንና የተጣሉትን፥ ወዘተ… ለመርዳት ከነበረው ፍላጐት አንጻር የተደረጉ ነበሩ።  4. ኢየሱስ በሰይጣን ላይ ያለውን ኃይል ለማሳየት ብዙ ጊዜ አጋንንትን ያወጣ ነበር። አጋንንት ከሰዎች በማስወጣት ኃይሉ ጥያቄ ለነበራቸው ፈሪሳውያንን ያደረጋቸው ተአምራት ሰይጣንን ለማሸነፍና ድል ለመንሳት የመጣ መሆኑን እንደሚያሳዩ ነግሮአቸዋል (ሉቃ 11፡14-26)።  5. የኢየሱስ ተአምራት ንጉሥ በመካከላቸው የመኖሩ ማረጋገጥ ነበር። የእግዚአብሔር መንግሥት እንደ ቀረበች የሚያስረዳ ነበር (ሉቃስ 11፡20)።  ጥያቄ፡– በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ዛሬም ተአምራት ይፈጸም ዘንድ ከላይ ከተጠቀሱት ዓላማዎች የትኞቹ ምክንያቶች ትክክለኞች ሊሆኑ ይችላሉ?  ኢየሱስ ያደረጋቸውን ፈውሶችና ተአምራት ስንመለከት የሚከተለውን እንነዘባለን።  1. ኢየሱስ ሰዎችን ለማስደነቅ ብሎ ተአምራትን አድርጐ አያውቅም። ሰዎች ምልክት ወይም ተአምራት ያደርግ ዘንድ በጠየቁት ጊዜ ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል (ማቴ. 12፡38-39)። ኢየሱስ አምስት ሺህ ሰዎችን ከመገበ በኋላ እንደመጡት ዓይነት ሰዎች ለግል የስግብግብነት ዓላማቸው ተአምራት ያደርግላቸው ዘንድ በፈለጉ ጊዜ ተአምራትን ለማድረግ ፈቃደኛ አልነበረም። ተአምራቱ ሕዝቡን ለማስገረምና ግርግር ለመፍጠር ሳይሆን ግልጽ የሆነ ዓላማ ነበራቸው።  2. ኢየሱስ በርካታ ሰዎችን በአንድ ጊዜ በተሰበሰቡበት ፈውሶ ከሆነም “ሁላችሁም ተፈውሳችኋል” ሲል ከስንት አንዴ ነው የምንመለከተው። ፈውስ ባከናወነባቸው ጊዜያት ሁሉ አንድ በአንድ እንዳደረገ ነው። ይህ እንግዲህ ዛሬ በዘመናችን በርካታ ሰዎች በአንድ ጊዜ እንደ ተፈወሱ ከሚናገሩት ሰዎች አሳብ ተቃራኒ ነው።  3. ኢየሱስ ለፈውስ የገንዘብ ክፍያ የተቀበለበት ጊዜ ፈጽሞ አልነበረም። ፈውስን ለግል ጥቅሙ የተጠቀመበት ወቅትም ፈጽሞ አልነበረም።  4. ኢየሱስ ያደረጋቸው ተአምራቶች ፈውሶች በሙሉ ስኬታማ ነበሩ። እንድን ሰው ለመፈወስ ሞክሮ ያልተሳካበት ወይም ከፊል ፈውስ የሰጠበት ወቅት ፈጽሞ አልነበረም።  5. ተፈዋሾቹ ምንም እምነት እንደነበራቸው ሳይጠቅስ ኢየሱስ ሰዎችን የፈወሰበት ወቅት ነበረ። በእርግጥ ግልጽ የሆነ ተቃውሞና ያለማመን በነበረበት ስፍራ ፈውስን ከመፈጸም ተቆጥቧል። ነገር ግን ኢየሱስ ፈውስን አውጆ ያልተሳካበትና ለዚህም እምነት ጉድለት እንደ ምክንያት ያቀረበበት የለም። ስለዚህ ኢየሱስ ፈውስን ለመፈጸም ወይም ላለመፈጸሙ የእምነት ቅድመ–ሁኔታ አልነበረም። ነገር ግን እንዳንድ ጊዜ ላመፈወስ ፈቃደኝነቱ ቅድመ-ሁኔታ ይሆን ነበረ።  6. የኢየሱስ አገልግሎት ትኩረት የእግዚአብሔርን ቃል ማወጅ ነበር። ያደረጋቸው ተአምራት አብዛኛዎቹ ከነበረው የማስተማር አገልግሎት ጋር የተያያዙ ነበር። ተአምራቱ ትምህርቱን ያጠናክሩለት ነበር። ከትምህርቱ ውጭ የሚደረጉ አልነበሩም። ተአምራት በተለይ ደግሞ ፈውስ ኢየሱስ ለሕዝቡ የነበረው ፍቅር ተፈጥሮአዊ መግለጫዎች ነበሩ። ኢየሱስ ግን በማስተማር ላይ በማተኮር ሰዎች ከእግዚአብሔር ጋር ያላቸው ግንኙነት ትክክለኛ እንዲሆን ሞክሯል። ተአምራት አድራጊ በመባል እንዲታወቅ አይፈልግም ነበር። ደግሞ የእውነት አስተማሪ ከመባል ይልቅ ተአምራት አድራጊ የመባል ዝናው እየናረ ከመጣ ያንን አካባቢ ለቅቆ ይሄድ ነበር (ማር. 1፡32-38)። እንዲያውም ለአንዳንዶች ያደረገላቸውን ተአምራት ለሌሎች እንዳይነግሩ አስጠንቅቆአቸው ነበር (ማር. 1፡44)።  7. ኢየሱስ ያደረጋቸው ተአምራት መሢሕ መሆኑን የሚያረጋግጡ ቢሆኑም ሊያሳምኑ የቻሉት ጥቂት ሰዎችን ብቻ ነበር። ተአምራት በራሳቸው ሰዎች በእርሱ ላይ እምነት እንዲኖራቸው ፈቃደኞች አላደረጉአቸውም። ይልቁኑ ሰዎች በራስ ወዳድነት መንፈስ እንዲከተሉት የሚያደርጉ ነበሩ ( ዮሐ 6፡30-48)። ስለዚህ ሰዎች አስቸጋሪ ምርጫ ያደርጉ ዘንድ የሚያስገድድ ነገር ማድረግ ወይም አንድ ነገር ማስተማር ነበረበት። ለእነርሱ ከሚያደርግላቸው ነገር ይልቅ በማንነቱ ላይ በመመርኮዝ በልባዊ ውሳኔ መከተልን እንዲመርጡ ለማስገደድ የተአምራት አድናቆትን ከእነርሱ ማስወገድ ነበረበት። ተአምራትን አይተው ኢየሱስን የተከተሉ በስደት ጊዜ ለመፈርጠጥ የመጀመሪያዎቹ ነበሩ።  8. ኢየሱስ ካደረጋቸውና የሰዎችን ሥጋዊ ሕይወት ከለወጡት ተአምራት የድነት (ደኅንነት) ተአምር ከሁሉ የላቀ አስፈላጊ ነው። ባደረጋቸው ተአምራት ሰዎች ሲደነቁ ከማየት ይልቅ የእምነት እርምጃ ሲወስዱና በእርሱ

ተአምራትና ፈውሶች በአዲስ ኪዳን Read More »

የብሉይ ኪዳን ተአምራትና አዲሱን ዘመን በተስፋ መመልከት

2ኛ ጥያቄ፡- የሚከተሉትን ጥቅሶች ተመልከት። ዘጸአ 14፡5-22፤ ኢያሱ 10፡11-14 1ኛ ሳሙ. 12፡18፤ 1ኛ ነገ 18፡30-38፤ 2ኛ ነገ. 4፡32-35። የእግዚአብሔር በብሉይ ኪዳን ሰዎች አማካኝነት የሠራቸውን ተአምራት ዘርዝር።  በብሉይ ኪዳን የተዘረዘሩ ተአምራት በርካታ ናቸው። ከብሉይ ኪዳን የምንማረው ነገር ቢኖር እግዚአብሔር ታላቅና ኃያል፥ ተአምራትን ማድረግ የሚችል ለሕዝቡም ይህንን በተደጋጋሚ ያደረገ መሆኑን ነው። ቀይ ባሕርን መክፈል፥ የኢያሪኮን ግንብ መጣል በሽተኞችን መፈወስ፥ ሙታንን ማስነሣት እነዚህ ሁሉ እግዚአብሔር በብሉይ ኪዳን የፈጸማቸው ተአምራት ናቸው።   ነገር ግን የብሉይ ኪዳን ተአምራት አስገራሚ የሆነ የአፈጻጸም ሂደት አላቸው። ተአምራቱ ደረጃ በደረጃ የሚፈጸሙ ይመስላሉ። እግዚአብሔር በርካታ ተአምራት ያደረገባቸው ጊዜያት ነበሩ። እጅግ በጣም ጥቂት ተአምራት የፈፀመባቸው ረጅም ጊዜያትም ነበሩ። እግዚአብሔር ምንም ተአምራት ያላደረገበት ወቅት የሕዝቡን መንፈሳዊ ሕይወት እጅግ ዝቅተኛ የነበረበት ወቅት እንደሆነ ልናስብ እንችላለን። ነገር ግን እንደዚያ አልነበረም። የእስራኤል ሕዝብ መንፈሳዊ ሕይወት ከፍተኛ የነበረበት የዳዊት አመራር ዘመን አንዳችም ተአምራት አልተደረገም ለማለት የሚያስችል ነበር።  የብሉይ ኪዳን ታሪክ እንደሚያመላክተን ተአምራት እጅግ ቶሎ ይፈጸሙ የነበሩበት ዘመን የነበረ ቢሆንም የእስራኤል ሕዝብ አብዛኛው ታሪከ ግን በቁጥር እጅግ አነስተኛ ተአምራት የተፈጸመበት ጊዜ ነበር። ተአምራት የተዘወተረባቸው ሦስት ዘመናት ነበሩ።  1. እግዚአብሔር ነገሮችን ሁሉ በሠራበት የፍጥረት ዘመን።  2. እግዚአብሔር እስራኤላውያን ከባርነት ነፃ በማውጣት በምድረ በዳ ውስጥ መርቶ በተስፋይቱ ምድር ያሳረፋቸው ዘመን።  3. ኤልያስና ኤልሳዕ ነቢያት የነበሩበት ዘመን።  ይህ ማለት እግዚአብሔር በሌሎች ዘመናት ተአምራትን አላደረገም ማለት አይደለም። ወይም ደግሞ እግዚአብሔር በሁሉም ዘመናት ተአምራትን ሊያደርግ አይችልም ማለት አይደለም። ይልቁኑ ይህ የሚያሳየው በእግዚአብሔር አሠራር ውስጥ እግዚአብሔር ለአንድ በግልጽ ተለይቶ ለታወቀ ዓላማ ተአምራትን ለመሥራት የሚፈልግበትና ብዙ ተአምራትን ለመሥራት የማይመርጥበት ጊዜ መኖሩን ነው።  ከብሉይ ኪዳን የምንመለከተው ሌላው አስገራሚ ነገር ተአምራት በሚፈጸሙበት ወቅት ተአምራቱ ለእግዚአብሔር ስም ክብርን የሚያመጡ በሰዎች ዘንድ ፈሪሃ እግዚአብሔርን የሚያሳድሩ ቢሆንም እንኳ ብዙ ጊዜ ሰዎች በእግዚአብሔር ላይ ያላቸው እምነት እንዲጨምር አያደርጉም ነበር። በሙሴና በኢያሱ ዘመን እግዚአብሔር በርካታ ተአምራት ቢያደርግም እንኳ የእስራኤል ሕዝብ እምነት አልነበራቸውም፥ ያጉረመርሙ ነበር፡ ስለሆነም እግዚአብሔር አብዛኛዎቹን አጠፋቸው። በተመሳሳይ መንገድ በኤልያስና በኤልሳዕ ዘመን በርካታ ተአምራት የነበሩ ቢሆንም፥ እግዚአብሔር የበዓልን ነቢያት ለማሸነፍ በርካታ ተአምራት ቢያሳይም (1ኛ ነገ. 18፡30-38)፥ እስራኤላውያን ሕይወታቸውን ለውጠው በእውነተኛ ልብ እግዚአብሔርን አልተከተሉም ነበር። በተቃራኒው እጅግ ጥቂት ተአምራት ብቻ በተደረገባቸው በዳዊትና በሰለሞን ዘመናት ሕዝቡ ጤነኛ መንፈሳዊ ሕይወት ነበራቸው።  ስለዚህ ከብሉይ ኪዳን ታሪኮች ልንገነዘባቸው የሚገቡ ሦስት ዋና ትምህርቶች  ሀ) እግዚአብሔር ለሕዝቡ ተአምራትን የሚያደርግ ኃይል የተሞላ አምላክ መሆኑን  ለ) እግዚአብሔር በዘመናት ሁሉ ተአምራት የሚያደርግበት ድግግሞሽ በየጊዜያቱ እኩል ያለመሆኑንና  ሐ) ተአምራት በራሳቸው የእግዚአብሔርን ኃይል የሚገልጡ ቢሆንም ብዙ ጊዜ ግን የእግዚአብሔርን ሕዝብ መንፈሳዊ ብስለት ሲጨምሩ አለመታየታቸው ናቸው።  ጥያቄ፡- ሀ) እግዚአብሔር ልዩ የሆነ ተአምር አድርጐልህ ለማየት ተመኝተህ ታውቃለህ? ምን ዓይነት ተአምራት እንዲያደርግልህ ነበር የፈለግኸው? ለ) እግዚአብሔር ይህን ተአምር እንዲያደርግልህ የፈለግኸው ለምን ነበር? ሐ) ይህ ነገር ስለ እምነት ምን ያሳያል? እምነትህ ደካማ ወይስ ብርቱ ነበር? መ) እግዚአብሔር ተአምራት እንዲያደርግ ሁልጊዜ የሚጠብቁ ሰዎች እምነት ምን ዓይነት ነው ብለህ ታምናለህ? ብርቱ ወይስ ደካማ? ይህን ለምን አልክ?  ብሉይ ኪዳን ወደ መጠቃለል በቀረበበት ወቅት እግዚአብሔር ከሕዝቡ ጋር ልዩ የሆነ ግንኙነት የሚያደርግበት አስደናቂ አዲስ ዘመን እንደሚመጣ በነቢያቱ በኩል መናገር ጀመረ። በአዲሱ ዘመን መሢሑና መንፈስ ቅዱስ ልዩ ስፍራ ይኖራቸዋል። ከዚህ ቀደም ትንቢትን የመናገር ስጦታ ለብዙዎች እንደሚሰጥ በኢዩኤል መጽሐፍ ተመልክተናል። ነገር ግን እግዚአብሔር ለሕዝቡ እንደገና ተአምራትን የሚያደርግበትን ዘመን እንደሚያመጣና መሢሑን እንደሚያስነሣ የሚያመላክት ነገር አለ። መሢሑ ለታሠሩ መፈታትን፥ ለታወሩት ብርሃንን ያወጣል (ኢሳ.6፡1-2)። እንዲሁም ሕዝቡን ከበሽታቸው ይፈውሳቸዋል (ኢሳ. 3፡5)።  ኢሳ 53፡5 በክርስቲያኖች መካከል ከፍተኛ ውዝግብን የፈጠረ ክፍል ነው። እግዚአብሔር፥ ኢየሱስ በሽታዎቻችንን «ሁሉ» እንደሚፈውስ ቃል መግባቱ ነበርን? እንደዚያ ከሆነ ብዙ ክርስቲያኖች ለምን ይታመማሉ? ኃጢአት በሕይወታቸው ስላለ ወይም በቂ እምነት ስለሌላቸው ነው? ብዙ ሰዎች ለክርስቲያኖች ሕመም የሚሰጡት ምክንያት ይህ ነው። ለነገሩ እግዚአብሔር ኃያል አምላክ ነውና ሁሉንም መፈወስ ይችላል። አፍቃሪ ስለሆነ ልጆቹ ሲሰቃዩ ማየት አይፈቅድም፤ እግዚአብሔር ከማንኛውም በሽታ እንደሚፈውሰን ቃል ገብቶልናል። ስለዚህ ካልተፈወስን በኃጢአት ወይም በቂ እምነት በማጣት ምክንያት ነው ይላሉ።  ጥያቄ፡- በክርስቲያኖች መካከል እንደዚህ ዓይነት አስተሳሰብ ሲንጸባረቅ ሰምተህ ታውቃለህን? ከሰማህ ምን ምላሽ ትሰጣቸዋለህ?  የሚያሳዝነው ነገር ይህ ዓይነት መረዳት ኢሳ. 53፡5 በተሳሳተ መንገድ በመተርጐሙ የመጣ መሆኑ ነው። ይህ ጥቅስ የሚናገረው በእርግጥ ስላ ሥጋዊ ፈውስ ነውን? በአይሁዳውያን አስተሳሰብ “ፈውስ” የሚለው ቃል ምሉዕነትን ያመለክታል። ብዙ ጊዜ የሥጋዊ አካል ምሉዕነትን ቢያመለክትም ቅሉ መንፈሳዊ ምሉዕነትንም ያመለክታል። አንድ ሰው ከኃጢአቱ በሚድንበት ጊዜ ይፈወሳል። ኢየሱስ የሚለውንና «እዳኝ» የሚል ትርጓሜ ያለውን ስም ያገኘነው ከዚህ ነው። ምሉዕ የሚያደርገን እርሱ ነው። ስለዚህ በኢሳ. 53፡5 የምናገኘው «ተፈወሳችሁ» የሚለው ቃል የግድ ሥጋዊ ሕመምን የሚያመለክት አይደለም። በዙሪያው ያሉትን አሳቦች ስንመላክት እግዚአብሔር በዚህ ቦታ የሚያመለክተው በተቀዳሚ ሥጋዊ ምሉዕነትን ሳይሆን መንፈሳዊ ምሉዕነትን ነው። ሌሎች ጥቅሶች የሚናገሩት ለለ መተላለፍ፥ ስለ በደልና፥ ስለ ሰላም ወዘተ… ነው። ስለዚህ በዚህ ጥቅስ አሳብ ላይ መሢሑ ፈውስን እንደሚያመጣ (በማቴ. 8፡16-17 የተተረጐመው በዚህ መንገድ ነው) የሚያመላክት አሳብ ሊገኝ ቢችልም ተቀዳሚ መረዳታችን ሊሆን የሚገባው ኢየሱስ ከኃጢአታችን እንደሚያድነን የሚናገር ስለመሆኑ ነው። የአዲስ ኪዳንን አጠቃላይ አሳብ በቅርብ በምንመረምርበት ወቅት እግዚአብሔር ለክርስቲያኖች ሁሉ ሙሉ የሆነ አካላዊ ፈውስን አልሰጠም። ጳውሎስ ይሰቃይ ነበር፥ ከእርሱ ጋር ይሠራ የነበረው አፍሮዲጡ አብሮት ሳለ እስከ ሞት ድረስ ታሞ ነበር (ገላ. 4፡13-14፤ ፊልጵ. 2፡27)። በሺህ የሚቆጠሩ መንፈሳዊ ክርስቲያኖች እግዚአብሔር ሌሎችን ለመፈወስ የሚጠቀምባቸው እንኳ ይታመማሉ። ስለዚህ እነዚህን ጥቅሶች ሰው ከሥጋዊ በሽታዎቹ ሁል ጊዜ ይፈወሳል ለማለት ልንጠቀምባቸው አንችልም። ምንጭ፡- “የመንፈስ ቅዱስ የጥናት መምሪያና ማብራሪያ”፣ በቲም ፌሎስ ተጽፎ፣ በጌቱ ግዛው የተተረጎመ እና በኤስ አይ ኤም ጽሑፍ ክፍል የተዘጋጀ ነው፡፡ ለዚህ ድንቅ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡ ይህን ጽሁፍ ኮፒ እና ፕሪንት አድርጎ መጠቀም ይቻላል፤ ሆኖም ጽሁፉን መለወጥና ለሽያጭ ማዋል በሕግ የተከለከለ ነው፡፡

የብሉይ ኪዳን ተአምራትና አዲሱን ዘመን በተስፋ መመልከት Read More »

የመፈወስና ተአምራትን የማድረግ ስጦታዎች

ጉባኤው እጅግ ታላቅ ነበር። እርሱን ለመስማት በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ተሰብስበው ነበር። ያን ያህል ቁጥር ያለው ሰው የተሰበሰበት ዋና ምክንያት ግን ተአምራት ለማየት ነው። ይህ ሰው የፈውስ ስጦታ እንዳለው ይነገር ነበር። በስብከቱ መጨረሻ ላይ የታመሙ ሰዎች ሁሉ እንዲቆሙ ጠየቀ። ከአንድ በላይ በሽታ ያለባቸው ቢሆንም ፈውስን እንደሚያገኙ ነገራቸው። በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ይፈወሱ ዘንድ ቆሙ። ከዚህ በኋላ እንደ ተፈወሱ አወጀ። በጉባኤው መካክል ከአዲስ አበባ የመጣች በጠና የታመመች ሌት ነበረች። እንደ ተፈወሰች አምና ወደ ቤቷ ተመለሰች። ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ሞተች።  እግዚአብሔር፥ ፈዋሽ እምላክ ነው። ነገር ቀን እግዚአብሔር የሚፈውሰው ከላይ በተጠቀሰው መንገድ ነውን? ሰዎች መፈወሳቸው ከተነገራቸው በኋላ ባይፈወሱ ምንድን ነው የሚሆነው? ጥፋቱ የማን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ምን ያስተምረናል።  ጥያቄ፡- ማቴ. 12፡ 25-28፤ ሉቃስ 1፡21 ጀምሮ፤ ዮሐ 12፡31፤ ራእይ 21፡4። እነዚህ ጥቅሶች በኢየሱስ ዘመን የተአምራት ሚና ምን እንደነበር ያሳያሉ?  እግዚአብሔር ተአምራትን የሚሠራ አምላክ ነው። ተአምራትን ሲሠራ ነበር። ወደፊትም ተአምራትን መሥራት ይቀጥላል። እግዚአብሔር ተአምራትን ማድረጉን አቁሟል የሚሉ አንዳንድ ክርስቲያኖች ቢኖሩም እንኳ ለዚህ አባባላቸው ምንም ዓይነት መጽሐፍ ቅዱሳዊ መረጃ የላቸውም። ከቤተ ክርስቲያን ታሪክ የምንመለከታቸው መረጃዎች የሚያሳዩን እግዚአብሔር ተአምራት ማድረጉን እንደቀጠለ ነው። ስለዚህ ዛሬም ቢሆን እግዚአብሔር ተአምራትን ያደርግ ዘንድ፥ ይፈውስ ዘንድ፥ ሰዎችን ከአጋንንት ነፃ ያወጣ ዘንድ፥ ወዘተ… ልንጠብቅ እንችላለን።  ነገር ግን እግዚአብሔር ተአምራትን በብሉይ ኪዳንና በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ባደረገው ዓይነት በተዘወተረ ሁኔታ እንደሚያደርግ ማመንና መጠበቅ ትክክል አይደለም። በተጨማሪ ተአምራት ማንኛውም ክርስቲያን በፈለገው ጊዜ ሊያደርገው የሚችለው ነገር እንደሆነ ማሰብም ስሕተት ነው። ተአምራትን የማድረግ ኃይል ፈጽሞ በሰው ላይ የሚመሠረት አይደለም። የተአምራት መሠረት እግዚአብሔር ነው። ተአምራትን ያደርግ ዘንድ እግዚአብሔርን ሊያዝዘው የሚችል ማንም የለም። አንድ ሰው ሊያደርግ የሚችለው ነገር የእግዚአብሔር ተአምራት ይፈጸም ዘንድ መጠቀሚያ መሣሪያ ለመሆን እራሱን አዘጋጅተ መቅረብ ነው። ይህ ነገር ደግሞ ደረጃ በደረጃ ሊፈጸም ይገባል። ሰዎች ዛሬ በተአምራት ላይ ያላቸው በጥልቅ የመወሰድ ሁኔታ አደገኛ ነው። ለማመን ምልክትን እንደሚጠይቁ አይሁዶች ሆነናል። ኢየሱስ ከሞት የመነሣቱ እውነት ምልክት የሆነውን የዮናስን ምልክት ለማመን እምቢ እንላለን (ማቴ. 12፡39-4)።  እግዚአብሔር በዚህ ዘመን ምንም ተአምራትን አያደርግም የሚሉትና እግዚአብሔር በእኛ ትእዛዝ ሁልጊዜ ተአምራትን ያደርጋል የሚሉ ሁለቱም አቋሞች ስሕተት ናቸው። እውነቱ ያለው በሁለቱ መካከል ነው። በልሳናት እንደ መናገርና እንደ ትንቢት ስጦታዎች የፈውስና ተአምራትን የማድረግ ስጦታዎችም ዛሬ በቤተ ክርስቲያን የጋላ ክርክር የሚካሄድባቸው ናቸው። በሌሎች ስጦታዎች እንደሆነው ሁሉ የከረሩ አቋሞችና ከአግባብ ውጭ የሆኑ አጠቃቀሞች ሰዎች ከሚገባ በላይ እንዲሄዱ አድርገዋቸዋል።  ጥያቄ፡- ሀ) ተአምራትን እንዴት ትተረጉመዋለህ? ለ) መለኮታዊ ፈውስን እንዴት ትተረጉመዋለህ?  አንድ አስደናቂ ነገር ሲፈጸምልን «ተአምር ነው» እንላለን። ሕመም ሲሰማንና መድኃኒት በመውሰድ ሊሻለን እግዚአብሔር ፈወሰን እንላለን። በአንድ አንጻር ስናየው በሕይወታችን የሚፈጸሙ ነገሮች በሙሉ ተአምራት ናቸው። አካላዊ ሕይወታችን ራሱ ተአምር ነው። ሰውነታችን ከበሽታ ባገገመ ጊዜ ሁሉ ከእግዚአብሔር ዘንድ የሚገኝ ፈውስ ተቀበልን ማለት ነው።  እግዚአብሔር ተአምራትን አደረገ ወይም በተአምር ፈውስን ሰጠ ስንል በእርግጥ ምን ማለታችን ነው? ተአምር የምንለው እግዚአብሔር ዓለም ትተዳደርባቸው ዘንድ የደነገጋቸውን ተፈጥሮአዊ ሕግጋት ያለፈ ነገር ሲፈጽም ነው። ይህም ማለት እግዚአብሔር በተፈጥሮአዊ መንገድ ፈጽሞ የማይቻለውን ነገር ሲያደርግ ነው። መለኮታዊ ፈውስ ማለት እግዚአብሔር በሰው ሰውነት የሚካሄደውን ተፈጥሮአዊ የእርጅናና የበሽታ ሂደት ያለፈ ነገር ሲያደርግ ነው። እግዚአብሔር በተፈጥሮአዊ መንገድ በሰውነት ውስጥ ፈውስ ሲያካሂድ በሽታውን በቅጽበት በማንሣት ሙሉ ጤንነትን ይመልሳል። ይህ የሚሆነው በሽታን ለማስወገድ እግዚአብሔር በተፈጥሮ ከሰጠው የመድኃኒት ውጤት የተለየ ነው።  ለማያምኑም ሆነ ለሚያምኑ ሰዎች ያልተለመዱ ነገሮች ይደረጋሉ። ነገር ግን ሁልጊዜ እንደ ልዕለ-ተፈጥሮአዊ ተአምራት መታየት የለባቸውም። እግዚአብሔር የሥጋ ፈውስን የሚሰጥበት የተለመደ መንገድ በተፈጥሮአዊ ሕግጋትና ለሰው ልጆች በሰጠው ተፈጥሮአዊ ፈዋሽ መድኃኒቶች አማካኝነት ነው። ነገር ግን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስላለው ተአምራትና ፈውስ ስንነጋገር እግዚአብሔር ፍጥረታትን ለማስተዳደርና ለመምራት ከደነገጋቸው ተፈጥሮአዊ ሕግጋት ባሻገር (እግዚአብሔር) ጣልቃ ገብቶ ካላደረገው በስተቀር ፈጽሞ ሊሆን የማይችለውን ነገር ነው። ምንጭ፡- “የመንፈስ ቅዱስ የጥናት መምሪያና ማብራሪያ”፣ በቲም ፌሎስ ተጽፎ፣ በጌቱ ግዛው የተተረጎመ እና በኤስ አይ ኤም ጽሑፍ ክፍል የተዘጋጀ ነው፡፡ ለዚህ ድንቅ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡ ይህን ጽሁፍ ኮፒ እና ፕሪንት አድርጎ መጠቀም ይቻላል፤ ሆኖም ጽሁፉን መለወጥና ለሽያጭ ማዋል በሕግ የተከለከለ ነው፡፡

የመፈወስና ተአምራትን የማድረግ ስጦታዎች Read More »

የትንቢት ስጦታን ለመጠቀም መመሪያዎቹ ምን ምን ናቸው?

በ1ኛ ቆሮ. 12-14 ከተመለከትነው አንጻር የአዲስ ኪዳን አብያተ ክርስቲያናት አገልግሎት በአሁኑ ጊዜ ካሉን የቤተ ክርስቲያን ፕርግራሞቻችን በጣም የተለዩ ናቸው። በዚያ ዘመን በአምልኮ ፕሮግራሞች ሰዎች ሁሉ ይሳተፉ ነበር። የተለያዩ ጸሎቶችና መዝሙሮች፥ በድንገት እግዚአብሔር ለሕዝቡ የሚሰጣቸው መልእክቶችና የሚለውጠውን የእግዚአብሔር ቃል ትምህርት የመስሚያ ጊዜያት ነበሩ። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከነበሩ መንፈሳዊ ስጦታዎች አንዱ የትንቢት ስጦታ ነበር። ነገር ቀን እንደማንኛውም ስጦታ ይህ ስጦታም ያለ አግባብ በተግባር ላይ ሊውል ይችል ነበር። ስለዚህ ጳውሎስ ስልሳናት ለመናገር ስጦታ እንዳደረገው ትንቢት ስለመናገር ስጦታም መመሪያን ሰጠ። የሚከተሉትን በእዚህ ቁጥሮች ስለቀረበው ትንቢት ከተሰጡት እውነቶች ጥቂቶቹ ናቸው።  1. ትንቢት የሚመጣው በመገለጥ ነው። መገለጡ እንደ ሕልምና ድምፅ ባሱ ልዩ ተአምራዊ መንገዶች ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ብዙ ጊዜ የሚገለጸው የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያንን ፍላጐቶች በሚያሟላ መልኩ ልዩ እውነተችን ከመጽሐፍ ቅዱስ በአዲስ መንገድ በመረዳት ነው። እነዚህ ትንቢቶች ሁልጊዜ የሚመጡት ትንቢት ተናጋሪው እራሱን በሚቆጣጠርበት ሁኔታ እንጂ ፈጽሞ እራሱን ስቶ በሰመመን ውስጥ ባለበት ሁኔታ አይደለም። ትንቢት ተናጋሪው እራሱን ሙሉ በሙሉ በሚቆጣጠርበት ሁኔታ ሳይሆን ከቁጥጥር ውጭ ሆኖ የሚናገር ከሆነ የትንቢቱን እውነተኛነት በጥርጣሬ ልንመለከተው ይገባል።  2. የቤተ ክርስቲያን ፕሮግራም በሚካሄድበት ወቅት መንፈስ ቅዱስ ለብዙ ሰዎች መልእክት ከሰጠ ሁሉም በአንድ ጊዜ ለመናገር መሞከር የላባቸውም። ነገር ግን ተራ በተራ በሥርዓት ሊናገሩ ይገባል።  3. የትንቢት መልእክት , በሚመጣበት በማንኛውም ጊዜ መልእክቱ መመዘን እላበት። ጳውሎስ እነዚህን መልእክቶች መመዘን ያለበት ጉባኤው ይሁን ወይም የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ለይቶ አይናገርም። ለማንኛውም የመጨረሻው ኃላፊነት የሚወድቀው በቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎች ላይ ነው። አንዳንዶቹ ትንቢቶች እውነት ሌሎች ደግሞ ሐሰት ሊሆኑ ይችላሉ።  ወይም አንዳንዶቹ ዋጋ ያላቸው ሌሎቹ ደግሞ የሌላቸው ይሆናሉ። ክርስቲያኖችን ለማነጽ ምንም ዋጋ የሌላቸው ትንቢቶች ተቀባይነት ማግኘት የለባቸውም። ስለዚህ የትኛው የመልእክቱ ክፍል እግዚአብሔር ለእነርሱ የሰጠው እንደሆነና የትኛው ደሞ እንዳልሆነ ሕዝቡ እንዲያውቅ ማድረግና መልእክትን መመዘን የቤተ ክርስቲያን በተለይም ደግሞ የመሪዎች ኃላፊነት ነው።  4. ትንቢቶች መመዘናቸውና እውነት የሆኑት ካልሆኑት የመለየታቸው እውነታ ትንቢቶች የመጽሐፍ ቅዱስን ያህል «ሥልጣን» እንደሌላቸው ያሳየናል። በእርግጥ በመንፈስ ቅዱስ ሥልጣን አማካኝነት ልዩ የሆኑ ነቢያትና ሐዋርያት የጻፉት መጽሐፍ ቅዱስ እውነት የሚለይበት መመዘኛ መሆን ይገባዋል።  5. በአንድ ስብሰባ ትንቢት እንዲናገሩ የተፈቀደላቸው ሰዎች ቁጥር የተወሰነ ነበር። ይህ የሚያመለክተው ነቢያት ስብሰባውን በሚያቀነባብሩና በሚመሩ ሰዎች ቁጥጥር ሥር መሆናቸውን ነው። ሥርዓት አልበኝነትና ግራ የሚያጋቡት ሁኔታዎች ከእግዚአብሔር ባሕርይ በተቃራኒ የሚሄዱ ስለሆኑ እርሱን ለማምለክ ትክክለኛና ተገቢም አዝማሚያ አይደለም።  6. እማኞች ሁሉ ከእግዚአብሔር መገለጥን ሲያገኙ ትንቢት የመናገር መብት ቢኖራቸውም ይህ መንፈሳዊ ስጦታ ግን ሁሉም ሰው አይኖረውም።  7. በመጽሐፍ ቅዱስና በዚህ ስፍራ በተገላጣው የትንቢት ስጦታ መካከል የብቃት ልዩነት መኖሩን ብንረዳም ቅሉ ይህ ስጦታ እዲስ ኪዳን ተጽፎ ካለቀበት ጊዜ ጀምሮ አይሠራም ለማለት ምንም አመልካች ማስረጃ አናገኝም። ይህ ስጦታ ዛሬ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ላላመኖሩ ምንም አመልካች ማስረጃ የለም። የቤተ ክርስቲያን መሪዎች እንደዚህ ዓይነቱን ስጦታ እንዳያግዱ መጠንቀቅ አለባቸው። ሆኖም ግን የተነገረውን ትንቢት የመመዘንና ከመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ጋር አብረው የማይሄዱ ስሕተቶች ያሉበትን አካባቢ ለሕዝቡ የማሳወቅ ኃላፊነት አለባቸው።  8. ያልተፈተነ ትንቢት ለቤተ ክርስቲያን አደገኛ ነው። የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ይህ እንዲደረግ ከፈቀዱ ከእግዚአብሔር ቃል ጋር በቀጥታ ይቃረናሉ። ይህ የማይተረጐም ልሳን የመናገርን ያህል ለሕተት ነው።  ጥያቄ፡- በዚህ ቀን ትምህርቶች መጀመሪያ ላይ የተመለከትናቸውን ሁኔታዎች ከልስ። ከላይ ከተጠቀሱት መመሪያዎች አንጻር በጸሎት ስብሰባ ላይ የምትገኝ የቤተ ክርስቲያን መሪ ብትሆን ኖሮ በዚያ ሁኔታ ውስጥ እግዚእብሔር ምን እንድታደርግ የሚፈልግ ይመስልሃል?  ባደረግሁት ጥናት በትንቢት ስጦታ ከሚያምንና በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ይህን ስጦታ ከሚለማመድ አንድ ሰው የሚከተሉትን አሳቦች አግኝቻለሁ።  1 እግዚአብሔር የትንቢት ቃል ስለሌላ ሰው ከሰጠህ፥ በተለይ ደግሞ ያን ሰው የመጉዳት ኃይል ካለው እግዚአብሔር መልእክቱን እንድትነግረው በግልጽ እስኪያሳውቅህና እስኪፈቅድልህ ድረስ ፈጽሞ አትንገረው። እግዚአብሔር ያንን መልእክት የሰጠህ ያንን ከርስቲያን እንድትጐጻው ሳይሆን እንድትጸልይለት ሊሆን ይችላል። አንዳንድ መገለጦች የሚሰጡህ ለሌሎች እንድታካፍል ሳይሆን በአንተና በእግዚአብሔር መካክል ብቻ እንዲቀሩ ነው (ለምሳሌ 2ኛ ቆሮ. 12፡4፤ መዝ. (25)፡1-4)  2. እንድ መገለጥ በመቀበልና ያላ ስሕተት ተርጉሞ በሥራ ላይ በማዋል መካከል ልዩነት አለ። ትርጉምህና አጠቃቀምህ ያለ ስሕተት ለመሆኑ እርግጠኛ ሁን። የትንቢት ቃልህን ይህ እግዚአብሔር የሰጠኝ መልእክት እንደ ሆነ አምናለሁ በማለት በፍጹም ትሕትና ተናገር። «እግዚአብሔር እንደዚህ ይላል» በማለት ኃይለ ቃል ከመጠቀም ተጠንቀቅ። ይልቅ እግዚአብሔር እንደዚህ እንደሚል አስባለሁ… በሚል የአነጋገር ዘይቤ ተጠቀም።  3. የትንቢትን ቃል አንድን ሰው በግልጽ ለመኮነን አትጠቀምበት። አንድን ሰው መገጽ እንዳለብህ እግዚአብሔር ካመለከተህ በማቴ. 18፡6 17 የተሰጠውን በመጠቀም በግሉ ቀርበህ ለመገሠጽ እርግጠኛ ሁን።  4. የተቀበልከውን መልእክት ካካፈልህ በኋላ ስለ ውጤቱ ኃላፊነቱን በእግዚአብሔር ላይ ጣል። አንተ እግዚአብሔር ፈቃዱን ለመግለጥ የሚጠቀምብህ መሣሪያ ብቻ ነህ። ያቀረብከውን መልእክት መመዘንና እግዚአብሔር እንደተናገራቸው ያመኑበትን ክፍል መታዘዝ መልእክቱ የመጣለት ግለሰብ ወይም ቡድን ኃላፊነት ነው። አንተ እግዚአብሔር እንዳሳየህ የምታምነውን ነገር ሰዎች ባያምኑ ወይም ባይከተሉ አትመረር። በዚህ ምክንያት መራራ ከሆንክ፥ መጥፎ አመለካከት ካደረብህ ወይም እራስህን የመጥላት ስሜት የተሞላህ የትንቢቱን መልእክት ያመጣኽው ሰዎችን እንጂ እግዚአብሔርን ደስ ለማሰኘት እይደለም ማለት ነው። በዚህ ፈንታ ትንቢቱን የተቀበሉት ሰዎች እነርሱም የእግዚአብሔርን ቃል ይሰሙ ዘንድ ጸልይላቸው። በመጨረሻ መንፈስ ቅዱስን በልባቸው አድምጠው ለመታዘዝ እግዚአብሔር ፊት ኃላፊነት አለባቸው። እግዚአብሔር በኃላፊነት የሚጠይቃቸው ለሚያደርጉአቸው ውሳኔዎች እንጂ አንተ ትክክል ነው ብለህ ላመንክበት ነገር አይደለም።  5. በሰው ሕይወት ውስጥ ያለን ኃጢአት የመግለጥ ትንቢት እግዚአብሔር ቢያሳይህ ትንቢቱን እንዴት እንደምትጠቀምበት ከፍተኛ ጥንቃቄ አድርግ።  ሀ) ስለዚያ ትንቢት ከማንም ጋር አትነጋገር። ይህ የሐሜት ኃጢአት ነው። ከተሳሳትክ እንድ ሰው ስለ ኃጢአት በሐሰት ከሰለህ ማለት ነው። ይህ ደግሞ በእግዚአብሔር ፊት ኃጢአትን ማድረግ ነው።  ለ) መልእክቱን ከመናገርህ በፊት እግዚአብሔር ፊት ለፊት ሄደህ በመናገር ትገሥጸው ዘንድ ይፈልግ እንደሆነ እርግጠኛ ሁን። እግዚአብሔር ስለዚያ ኃጢአት እንድታውቅ ያደረገህ እንድትጸልይ ብቻ ሊሆን እንደሚችልም አስታውስ። ሰውዩውን ከነኃጢእቱ በግልጽ የሚገናኝበት ሌላ ዕቅድ ሊኖረው ይችላልና።  ሐ) ለሰውዬው ኃጢአቱን ፊት ለፊት ትነግረው ዘንድ እግዚአብሔር ካሳሰበህ ለባለጉዳዩ ብቻ በጥበብና በትሕትና ንገረው።  መ) በተቀበልከው መገለጥ ላይ ብቻ ተመሥርተህ አንድን ሰው ስለ ኃጢአቱ በኃይል ልትገልጸው አትቅረብ። አስቀድመህ በእርግጠኛነት ማጣራት አለብህ። በተለይ ደግሞ መሪ የሆነን ሰው ስለ ኃጢአት ለመገሰጽ ልዩ ጥንቃቄ አድርጎ (1ኛ ጢሞ. 5፡19 ተመልከት)።  6. ስለተጣላኽው ወይም ስለምትቀርበው ሰው የምታገኘውን መገለጥ አትመን። እነዚህ መገለጦች ብዙ ጊዜ የሰይጣን እንጂ የእግዚአብሔር አይደሉም።  7. ታዋቂ «ነቢይ” የመሆን ፍላጐት እንዳይኖርህ እራስህን በመመርመር ጥንቃቄ አድርግ። መልእክት የምታመጣው ለግለሰቦች ወይም ጥቂት ሰዎች ላሉበት ቡድን፡ ወይም ለበርካታ ሰዎች መሆኑን የሚወስን እዚአብሔር ነው። እግዚአብሔር እንድታደርገው ለነገረህ ነገር ብቻ ታማኝ ለመሆን ጥረት በማድረግ ውጤቱን ለእርሱ ተው። በተጨማሪ ስለ ችሎታህ፥ ስላየኸውና ስላደረግኸው ነገር በትምክህት አትናገር።  8. ትንቢትን ለግል ጥቅምህ ፈጽሞ አታውል። እንደ ነቢይ በመታወቅ ምክንያት ደመወዝህ ክሌመረ ተጠንቀቅ። ይህ ወጥመድ ነው። ነቢዩ እግዚአብሔርን ለማገልገል ሳይሆን ለግል ጥቅሙና ለስግብግብ ዓላማዎቹ መኖር ይጀምራል። እንክብካቤ ለሚያደርጉላቸው መልካም መልእክትን፥ ለማያደርጉላቸው ደግሞ መጥፎ (ክፉ) መልእክትን የሚያመጡ ነቢያት ሰውን ደለ በማሰኘት ወጥመድ የተያዙ ስለሆነ እግዚአብሔርን አያከብሩም።  9. የትንቢት ስጦታህን «እግዚአብሔር ይህን እንድነግርህ ነግሮኛል በሚል ሥልጣን በሞላበት መንገድ ፈጽሞ አትጠቀም። ይህ ዓይነቱ አጠቃቀም በሰውዬው ላይ ፈራጅና የበላይ ተቆጣጣሪ ወደ መሆን እንድታዘነብል ስለሚያደርግ በቀላሉ ከአግባብ ውጭ ወደ መጠቀም ያደርስሃል። እግዚአብሔር ትንቢትን የሚሰጣው ሰዎችን ለማነጽ+ ላመገሠጽ፥ ለማበረታታት፥ ለመምከርና ለማጠንከር እንጂ ሕይወታቸውን በበላይነት ለመቆጣጠር አይደለም። ነቢያት ሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል እንዲያረጋግጡ የሚያግዙ ቢሆንም እንድን ሰው ወይም ቡድን ለመቆጣጠር ከእግዚአብሔር የተቀበሉትን ቃል ሊጠቀሙበት አይገባም።

የትንቢት ስጦታን ለመጠቀም መመሪያዎቹ ምን ምን ናቸው? Read More »

የእውነተኛና ሐሰተኛ ነቢያት ንጽጽር

ጥያቄ፡- ሀ) ኤር. 14፡13-16፤ 23፡9-40 አንብብ። ኤርምያስ ከሐሰተ ነቢያት ጋር ያሳለፈውን ችግር ግለጽ። ለ) ዘዳ 13፡3-5፤ 18፡17-22 አንብብ። ) አንድ ሐሰተኛ ነቢይ ከእውነተኛ ነቢይ የሚለይባቸው መንገዶች ምንድን ናቸው? 2) ሐሰተኛ ነቢይ የሚቀጣው በምን ነበር?  በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የእግዚአብሔርን ቃል ለሕዝብ የሚናገሩ እውነተኛ ነቢያት እንደነበሩ ሁሉ እውነተኛ ነቢያትን በመቃወም የሚሠሩ ሐሰተኛ ነቢያትም ነበሩ። የመጀመሪያዎቹ የእግዚአብሔርን ቃል ይናገሩ የነበሩ ሲሆን ሌሎች ደግሞ በእግዚአብሔር ስም ቢናገሩም እንኳ የሚናገሩት የእግዚአብሔርን ቃል አልነበረም። እውነተኞች ከእግዚአብሔር ስለነበሩ የእግዚአብሔር ሰዎች ሊሰሟቸው ይገባ ነበር። ሐሰተኞቹ ግን በሰይጣን ኃይል ቁጥጥር ሥር ሆነው የሚናገሩ ወይም እራሳቸው የፈጠሩትን ነገር የሚናገሩ ነበሩ። እነዚህን ማንም ሊቀበላቸው አይገባም ነበር። እግዚአብሔር ሐሰተኛ ነቢያትን እጅግ ከመጥላቱ የተነሣ ማንኛውም ነቢይ ሐሰተኛነቱ በሚረጋገጥበት ጊዜ መገደል ነበረበት።  እስራኤላውያን አንድ ነቢይ፥ እውነተኛ ወይም ሐሰተኛ መሆኑን የሚያውቁት እንዴት ነበር? መጽሐፍ ቅዱስ ሐሰተኛ ነቢያት የሚለዩባቸውን የሚከተሉትን ባሕርያት ይሰጣል።  1) ሐሰተኛ ነቢያት የእግዚአብሔርን ቃል በቀጥታ የሚቃወም መልእክቶችን ያመጣሉ። እግዚአብሔር ለእስራኤላውያን በሚናገርበት ወቅት አንድ ነቢይ ወደ እናንተ ቢመጣና ከሙሴ ሕግጋት ጋር በቀጥታ የሚቃረን መልእክት ቢያመጣላችሁ ሐሰተኛ ነቢይ መሆኑን አውቃችሁ ልትገድሉት ይገባል ያላቸው ለዚህ ነበር። ነቢያት ያመጡትን መልእክት የምንመዝንበት የመጨረሻው ሥልጣን ያለው መጽሐፍ ቅዱስ የመሆኑን እውነታ ይህ እንደገና ያስረግጣል። መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ከሚያስተምራቸው ትምህርቶች ከእኛ አተረጓጐም ሳይሆን) አብሮ የማይሄድ ማንኛውም መላእክት ሐሰተኛ ነውና ሊኮነን ይገባዋል።  2) ሐሰተኛ ነቢያት የተናገሩት መልእክት ልክ እንደተናገሩት አይፈጸምም። እግዚአብሔር የወደፊቱንም የሚያውቅ አምላክ ነው። ስለዚህ ወደፊት የሚፈጸመውን ነገር ለሕዝቡ ማሳወቅ እያስቸግረውም። ስለዚህ እንድ ሰው የወደፊቱን ጉዳይ በዝርዝር ቢያመለክትና ባመለከተው መንገድ ነገሮች ባይከናወኑ ሰውዬው ያመጣው መልእክት የእግዚአብሔር ቃል (ፈቃድ) አልነበረም ማለት ነው። ይህንንም ያለማቋረጥ ካደረገ እርሱ ሐሰተኛ ነቢይ ነው። ከዚህ ቀደም «ጌታ ኢየሱስ በዚህና በዚህ ቀን በዚህና በዚህ ስፍራ ይመጣል» ብለው የተናገሩ ብዙ ሰዎች ነበሩ። ብዙዎች ስላመኗቸው ሥራቸውን ሁሉ ትተው የኢየሱስን መመለስ ተጠባበቁ። ነገር ግን ቀኑ ቢደርስም እንኳ ኢየሱስ እልተመለሰም። ስለዚህ ሰው የምንረዳው ነገር ምንድን ነው? እግዚአብሔር ስለማይሳሳት ከእግዚአብሔር አለመሆኑን ነው። እውነተኛ ነቢያት የሚናገሩት መልእክት በሙሉ በትክክል ይፈጸማል። (ማስታወሻ፡— አንዳንዶች እግዚአብሔር ስለ ወደፊት የሚናገረው ነገር በሙሉ ትክክል ቢሆንም መልእክቱን የሚቀበላው ነቢይ ያለአግባብ ሊረጻውና ያለ አግባብ ሊተገብረው ይችላል የሚሉ አሉ፡፡)  የአንድን ነቢይ መልእክት ለመመዘን መፈጸሙን ብቻ ማየት በቂ አይደለም። ሰይጣን እንደ ጠንቋዮች ያሉ ተከታዮቹን ስለ ወደፊቱ ጉዳይ እንዲናገሩ ሊረዳቸው ይችላል። የሚናገሩትም መልእክት ብዙ ጊዜ ትክክል ሊሆን ይችላል። ነገር ግን የሚናገሩአቸውን መልእክት ትክክለኛነት ላማረጋገጥ ለረጅም ጊዜ ብንከታተል ከትንቢቶቻቸው ብዙዎቹ አይፈጸሙም። እነዚህ የሐሰተኛ ነቢያት ባሕርያት አብዛኛው እርስ በርስ የተያያዙ ስለሆኑ አንድ ትንቢት መፈጸሙን ለማረጋገጥ አንዱን ዘርፍ ብቻ መመልክት የለብንም በቂ አይደለም።  3) የሐሰተኛ ነቢያት ባሕርይ ብዙ ጊዜ መልካም አይደለም። አንድ ሰው ነቢይ ነኝ እያላ የእግዚአብሔርን ቅድስና በማያንፀባርቅ መንገድ የሚኖር ከሆነ እውነተኛ ነቢይ መሆኑን ወይም መሆኗን መጠራጠር ተገቢ ነው። አውነተኛ ነቢያት በትሕትና ይመላለሳሉ። አገልግሎታቸውም በሌሎች ሕይወት ውስጥ ትሕትናን ይፈጥራል።  4) የሐሰተኛ ነቢያት አገልግሎት ለእግዚአብሔር ክብርን አያመጣም። እንድ ሰው ነቢይ ነኝ እያለ ለራሱ ጥቅም፥ ሀብት፥ ክብር ወይም ኃይል ለማግኘት ከሠራ ወይም የአገልግሎቱ ክብር ወደ እግዚአብሔር ሳይሆን ወደ ራሱ የሚሄድ ከሆነ ሰውዩውን መጠራጠር ተገቢ ነው። እግዚአብሔር «ክብሬን ለሌላ አልሰጥም» (ኢሳ. 42፡8) ብሏል። ስለዚህ ከእግዚአብሔር ያልሆነ ማንኛውም ትንቢት ክብርን ለሰው እንጂ ለእግዚአብሔር አያመጣም። እውነተኛ ነቢይ ለኢየሱስ ክብርን ያመጣል፤ ሌሎችም ኢየሱስ ክርስቶስን እንዲያከብሩ ያደርጋል።  5) የእውነተኛ ነቢይ ትንቢት የመንፈስ ቅዱስ ፍሬን ያፈራል። በክርስቶስ አካል ውስጥ መክፋፈልን አያመጣም።  ጥያቄ፡- እነዚህ መመሪያዎች አንድ ሰባኪን ወይም ነቢይን ለመመዘን የሚጠቅሙት እንዴት ነው?  ጥያቄ፡- 1ኛ ቆሮ. 14፡26-40 አንብብ። ትንቢት ለመናገር የሚጠቅሙ የተላያዩ መመሪያዎችን ዘርዝር። ምንጭ፡- “የመንፈስ ቅዱስ የጥናት መምሪያና ማብራሪያ”፣ በቲም ፌሎስ ተጽፎ፣ በጌቱ ግዛው የተተረጎመ እና በኤስ አይ ኤም ጽሑፍ ክፍል የተዘጋጀ ነው፡፡ ለዚህ ድንቅ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡ ይህን ጽሁፍ ኮፒ እና ፕሪንት አድርጎ መጠቀም ይቻላል፤ ሆኖም ጽሁፉን መለወጥና ለሽያጭ ማዋል በሕግ የተከለከለ ነው፡፡

የእውነተኛና ሐሰተኛ ነቢያት ንጽጽር Read More »

የትንቢት ስጦታ ምንድን ነው?

ዛሬ የትንቢት ስጦታ በሚያካትታቸው ነገሮች ላይ በርካታ የተለያዩ እመለካከቶች አሉ። አንዳንዶች ትንቢት የእግዚአብሔርን ቃል ወስዶ በግልጽ ለማስተማርና ለሚሰሙት ሰዎች ሕይወት ተግባራዊ የሚሆንበትን መንገድ ሰማዛመድ ለማመልከት መቻል ነው ይላሉ። እግዚአብሔር በቃሉ ይናገራል እንጂ ቀጥተኛ መገለጥ መስጠቱን አቁሟል ይላሉ። በእነርሱ አመለካከት ምን መስማት እንዳለባቸው በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት በአጠቃላይ መልኩ ለሰዎች መናገር የመንፈስ ቅዱስ ሚና ነው። ይሁንና፥ ስለ ትንቢት ይህን ጠባብ አመለካከት የምንቀበልበት ምንም ዓይነት መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት የለንም።  ሌሎች ደግሞ እግዚአብሔር ዛሬም ቢሆን ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጭ በሆኑ መንገዶች ቀን መልእክቱ ከመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ጋር በማይቃረንበት ሁኔታ ይናገራል ይላሉ። የአዲስ ኪዳን የትንቢት ስጦታ ዛሬም ለክርስቲያኖች የሚሠራ እንደሆነ ይቀበላሉ። በትንቢት መንፈሳዊ ስጦታና በነቢያት እግዚአብሔር ለክርስቲያኖች ያለውን ፈቃድ ለየት ባሉ ቃሎች አማካኝነት ይናገራል ይላሉ።  ጥያቄ፡- የሚከተሉትን ጥቅሶች ተመልከት። ማቴ. 16፡17፤ ማቴ. 11፡27 1ኛ ቆሮ. 2፡10፤ ኤፌ. 1፡17። ሀ) በእነዚህ ጥቅሶች መሠረትነት «መግለጥ። ወይም «መገለጥ» ለሚለው ቃል ስላሉት የተለያዩ ዓይነት ትርጉሞች ምን መረዳት እንችላለን? ለ) በእነዚህ ጥቅሶች «መገለጥ» የሚለው ቃል የትንቢት አካል መሆኑን ብዙ ጊዜ በማንረዳበት ሁኔታ አገልግሎት ላይ የዋለው እንዴት ነው? ሐ) እነዚህ ጥቅሶች የትንቢት ስጦታ ሊያካትታቸው ስለሚችላቸው ነገሮች መረዳትን እንዴት ሊሰጡን ይችላሉ?  ትንቢት እንዲኖር መገለጥ የግድ ያስፈልጋል። ነቢይ የሚለው ቃል ፍቺ እግዚአብሔር የገለጠለትን ለሰዎች የሚያስተላልፍ ማለት ነው። ነገር ግን መገለጥ በተለያየ መንገድ ሊመጣ ይችላል የግድ በድንቃ ድንቅ መንገዶች ብቻ አይደለም የሚመጣው።  1. መገለጥ እግዚአብሔር በአንድ ሰው ልብ ውስጥ ሰውዬው በማይረዳበት ሁኔታ እንኳ የሚያስቀምጠው ነገር ነው። በማቴ. 16፡17 ጴጥሮስ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን ከተናገረ በኋላ ኢየሱስ “ለጴጥሮስ ሲናገር «ይህን የገለጠልህ በሰማያት ያለው አባቴ ነው» አለው። ጴጥሮስ ራእይ አላየም ወይም ድምፅ አልሰማም። ይልቁኑ በቅጽበት አእምሮአዊ መረዳቱ ተቀይሮ ኢየሱስ ማን መሆኑን በክፊልም ቢሆን እንኳ ተረዳ። በከፊል ልንል የተገደድንበት ምክንያት ጴጥሮስ ከዚያ በኋላ ወዲያውኑ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም እንዳይሔድ ለመከላክል በሞከረ ጊዜ ኢየሱስ ይህንን ከሰይጣን ከራሱ የመጣ ፈተና ነው በማለቱ ነው። ደቀ መዛሙርቱ ከኢየሱስ ትንሣኤ በፊት ኢየሱስ ማን መሆኑንና በመሢሕነቱ የነበረውን ሚና አልተረዱም ነበር።  2. ኢየሱስ መሆኑን ተረድቶ በእርሱ የሚያምን ሰው ይህን የሚያደርገው እግዚአብሔር እውነትን ስለሚገልጥለት ነው። ኢየሱስ ሰው በእርሱ የሚያምነው አብ ወልድን ብቻ ሊገልጥለት እንደሆነ መናገሩ ተጠቅሷል (ማቴ. 11፡27)። እምነት እውን ይሆን ዘንድ እግዚአብሔር መለኮታዊ ጥበቡን ለሰው መግላጥ አለበት (1ኛ ቆሮ. 2፡10)።  3. በመንፈሳዊ መረዳት የማደግ ችሎታ እውን የሚሆነው መንፈስ ቅዱስ ያለማቋረጥ እውነትን ስለሚገልጥ ብቻ ነው (ኤፌ. 1፡17)።  4 እግዚአብሔር ፈቃዱን በተፈጥሮአዊ ነገሮች ይገልጻል። ለምሳሌ የምትጠልቅ ፀሐይን በሚመለከትበት ጊዜ እግዚአብሔር ኃያልነቱንና ብርታቱን ለሰው ሊጎልጽ ይችላል።  5. አንዳንድ ጊዜ እግዚአብሔር እራሱን ፈጽሞ በተለየ ልዕለ-ተፈጥሮአዊ በሆነ መንገድ ይገልጣል። ራእዮችን፥ ድምፁን፥ ወዘተ… በመጠቀም በቀጥታ ለአንድ ሰው ሊናገርና ፈቃዱን ሊገልጽ ይችላል። ጳውሎስ ከቲቶ ጋር ወደ ኢየሩሳሌም እንዲሄድ የተናገረው እግዚአብሔር በሰጠው ልዩ መገለጥ ምክንያት ነበር (ገላ. 2፡1-2)።  ጳውሎስ ትንቢት በመገለጥ ይመጣል ሲል ልዩ የሆኑ ሕልሞች፤ የሚሰሙ ድምፆች ወይም ልዩ ድንቀኛ መልእክት ለቤተ ክርስቲያን የግድ ይሰጥ ማለቱ እንዳልነበረ እነዚህ ምሳሌዎች ያሳዩናል። ጸጥ ባለ መንገድ በመንፈስ ቅዱስ የክርስትና ሕይወትን ጥልቅ ነገርና ይኸው ጉዳይም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንዴት ተግባራዊ እንደሚሆን ሰው እንዲረዳው ማድረጉን ጳውሎስ ማካተት ይችል ነበር። እንደዚህ ዓይነት መገለጦች ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር እኩል አልነበሩም። ምክንያቱም መገለጡን የሚቀበሉት ሰዎች በትክክል ላይረዱት ስለሚችሉ ነበር። የአንድ ሰው ትንቢት መመዘንና አስፈላጊ ከሆነም መታረም የነበረበት ለዚህ ነው። የቤርያ ሰዎች የጳውሎስን መልእክት እንኳ በጊዜው በእጃቸው ከነበሩት ቅዱሳት መጻሕፍት ጋር ለማወዳደር አመዛዝነውታል (የሐዋ. 17፡1)።  ስለዚህ በአዲስ ኪዳን የትንቢት ስጦታ ምን ነበር? ትንቢት አንድ ሰው በማንኛውም ጊዜ በመንፈስ ቅዱስ ምሪት አማካይነት የሚያመጣው የእግዚአብሔርን ሕዝቦች የሚያንጽና የሚያበረታታ መልእክት ነበር። ብዙ ጊዜ እነዚህ መልእክቶች በድንገት ወደ አንድ ሰው የሚመጡና መልእክቶቹን የተቀበለው ሰው ለሌሎች የሚያካፍላቸው ነበሩ። የብሉይ ኪዳን ትንቢትና የአዲስ ኪዳን ትንቢት የሚለያዩት እንዴት ነው?  ጥያቄ፡- የሚከተሉትን ትንቢቶች ማለትም ኤር. 44፡1፤ 29፤ 48፡1፤ ከሐዋ. 11፡28፤ 21፡4 ና 21፡10-14 ጋር አወዳድር። ሀ) እነዚህ ትንቢቶች ተመሳሳይ የሆኑት በምን መንገድ ነው? ለ) የሚለያዩትስ በምን መንገድ ነው?  በብሉይ ኪዳን ሁለት ዓይነት ነቢያት ነበሩ። የመጀመሪያዎቹ የሚጽፉ ነቢያት ናቸው። እነዚህ እግዚአብሔር መገለጡን የሰጣቸው ብቻ ሳይሆን በኋላ ትንቢታቸውን በሚጽፉበት ጊዜ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት እንዲወጣው እግዚአብሔር የተቆጣጠራቸው ናቸው። መልእክታቸውን በጽሑፍ ያልተው ወይም የማይጽፉ ነቢያትም ነበሩ። ኤልሳዕ፥ ኤልያስ፥ ናታንና ሌሎች በስም ያልተጠቀሱ የነቢያት ልጆች (2ኛ ነገ 2፡3) የእንደዚህ ዓይነት ነቢያት ምሳሌዎች ናቸው። እነዚህ የሁላተኛዎቹ ዓይነት ነቢያት የእግዚአብሔርን ቃል እንደሚናገሩ የታወቀ ቢሆንም ትንቢታቸው ስላልተጻፈ በጽሑፍ መልእክታቸውን የተው ነቢያትን ያህል ለመላእክታቸው ዘላቂነት ያለው ዋጋ አልተሰጠም።  በአዲስ ኪዳንም እዚህ ሁለት ዓይነት ነቢያት ይታያሉ። የመጀመሪያዎቹ በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው የእግዚአብሔርን ፈቃድ እንዲያውቁና የተረዱትን ፈቃዱን በጽሑፍ እንዲያሰፍሩ እግዚአብሔር ያደረጋቸው ሲሆን ጽሑፋቸውም አዲስ ኪዳን ሆኗል። ይህ ተግባር በተቀዳሚነት የተከናወነው ከሐዋርያት በአንዳንዶቹ (ጴጥሮስና ዮሐንስ) እና በተመረጡ ሌሎች ጥቂት ደቀ መዛሙርት (ይሁዳ፣ ማርቆስ) ነው። ሐዋርያት የጻፉት በሙሉ የመጽሐፍ ቅዱስን ያህል ሥልጣን ያለው አልነበረም። ብዙ ሊቃውንት እንደሚያምኑት ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች ሌላ መልእክት የጻፈ ቢሆንም እንደ እግዚአብሔር ቃል ተጠብቆ ይቆይ ዘንድ መንፈስ ቅዱስ አላደረገም (2ኛ ቆሮ.2፡1-10)። በሁለተኛ ደረጃ፥ የትንቢት ስጦታ ያላቸውና መገለጥን ከእግዚአብሔር ዘንድ የተቀበሉ ነገር ግን በጽሑፍ ያላስቀሩ ነቢያት አሉ። እነዚህኞቹ የተናገሩትን ቃል እግዚአብሔር እንደ ጸሐፊ ነቢያት መልእክቶች አልጠበቀውም።  አንዳንድ ሊቃውንት የአዲስ ኪዳን ነቢያት ሚናና የብሉይ ኪዳን ነቢያት ሚና የተለያየ እንደሆነ ያምናሉ። የእግዚአብሔርን ፈቃድ ያለአንዳች ስሕተት ያወጁት የብሉይ ኪዳን ነቢያት አገልግሎት በሐዋርያትም እንደተከናወነ ያምናሉ። የአዲስ ኪዳን ነቢያት ከእግዚአብሔር መገለጥን የተቀበሉበት መንገድ (ራእይና ውስጣዊ ድምፅ) ከብሉይ ኪዳን ነቢያት ጋር ተመሳሳይ ነው። ነገር ግን በብሉይ ኪዳን ለነበሩ ነቢያት እንደተደረገው ቃል በቃል የእግዚአብሔር ቃል አይደለም። መጻሕፍቱን የጻፉት ሰዎች በራሳቸው ቃል በመጠቀም እግዚአብሔር በልባቸው ያደረገውን መልእክት በራሳቸው አሳብ ተናገሩት። ስለዚህ የአዲስ ኪዳን ነቢያት ቃል የብሉይ ኪዳን ነቢያትን ያህል ሥልጣን የለውም።  ወደ አዲስ ኪዳን ስንመለከትና ትንቢቶች እንዴት እንደተሰጡ ስናስብ ከብሉይ ኪዳን ትንቢቶች በርካታ ልዩነቶች እንዳሉአቸው እናያለን።  በመጀመሪያ፥ ትንቢተቹ በብሉይ ኪዳን የተሰጡበትን ሁኔታ በአዲስ ኪዳን ከተሰጡበት ጋር ስናወዳድር አንዳንድ ልዩነቶች እናያለን። በዘዲ 18፡18-22 ነቢዩ በጌታ ስም እንደተናገረ እናነባለን። ይህን ዓይነቱን ልምምድ በትንቢት መጻሕፍቶች በግልጽ እንመለከታለን። እያንዳንዱ ነቢይ «የእግዚአብሔር ቃል መጣልኝ» ብሎ ለመናገር እጅግ ይጠነቀቅ ነበር። ከዚያም ትንቢት በሚናገርበት ጊዜ ነቢዩ ራሱ መናገሩን ያቆምና እግዚአብሔር እራሱ እንደሚናገር የሚያመለክተውን እኔ የሚለው ተውላጠ ስም ሊጠቀም እግዚአብሔር መናገሩን ይጀምራል። ነቢዩ እግዚአብሔር መልእክቱን የሚያስተላልፍበት መሣሪያ ብቻ ይሆናል። እግዚአብሔር የነቢዩን ድምፅ ብቻ በመጠቀም ለሕዝቡ የመናገሩ ያህል ነው። በአዲስ ኪዳን ነቢያት «እግዚአብሔር እንዲህ ይላል» የሚል የአነጋገር ዘይቤ ሲጠቀሙ ፈጽሞ እንመለከትም። ይህን ሲያደርጉ ኖሮ የብሉይ ኪዳን ነቢያት የእግዚአብሔርን ቃል ለመናገር በነበራቸው ዓይነት ሥልጣን እንደተናገሩ ራሳቸውን መቁጠራቸውን የሚያመላክት ይሆን ነበር። ይልቁኑ ትንቢተቻቸው በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት የሆነ ግላትም ትክክለኛነቱ በጣም ዝቅተኛ እሳብ ነው። ስለሆነም ሰማይጽፉ ወይም መልእክታቸውን በጽሑፍ በማያልቀሩ ነቢያት መልእክታቸውን በሚያስተላልፉበት ወቅት እግዚአብሔር እንደሚናገር «እኔ» የሚለውን ተውላጠ ስም የተጠቀሙበት ጊዜ የለም። በብሉይ ኪዳን ነቢያትና የትንቢት ስጦታዎች ባላቸው ሰዎች መካከል የብቃት ልዩነት ስላለ በዚህ ዘመን ያሉ ነቢያት «እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ወይም እግዚአብሔርን ወክላው «እኔ ፡ ወይም «ሕዝቤ ሆይ» እያሉ የብሉይ ኪዳን ቀመርን ተጠቅሞ መናገር ለሕተት ነው። እነዚህን አባባሎች መጠቀም ቃሎቹ የመጽሐፍ ቅዱስን ያህል ትክክል ናቸው ማለት ሊሆን ይህ ደግሞ እጅግ

የትንቢት ስጦታ ምንድን ነው? Read More »

ትንቢት ምንድን ነው? ነቢይስ?

ብዙ ጊዜ ስለ ነቢይ በምናስብበት ጊዜ ለለ ወደፊቱ ጉዳይ ለመናገር የሚችል እንደሆነ እናስባለን። የመጽሐፍ ቅዱስ ነቢያት እግዚአብሔር የወደፊቱን ነገር ለመናገር የተጠቀመባቸው ቢሆኑም ይህ የአገልግሎታቸው አነስተኛው አካል ብቻ ነበር። ትንቢት ሰው ከእግዚአብሔር የሚቀበለው መልእክት ነበር። እግዚአብሔር ፈቃዱን በተለያዩ መንገዶች የሚገልጥበት ነበር። (ይህም በሕልም፥ በራእይ፥ በድምፅ፥ ሊሆን ይችላል።) የተገለጠውንም መልእክት ለሌሎች እንዲያካፍል ለሰው በእግዚአብሔር የሚነገር ነበር። ትንቢተች ወይም መገለጦች መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት የሚመጡ አይደሉም። ከመንፈስ ቅዱስ ዘንድ መልእክቱን ለሚቀበለው ሰው በቀጥታ የሚመጡ ናቸው። በአዲስ ኪዳን እያንዳንዱ ክርስቲያን የትንቢት ቃል ከእግዚአብሔር ዘንድ የመቀበል መብትና ችሎታ ያለው ይመስላል (የሐዋ. 2፡16-18)። ይህ ክርስቲያኖች ሁሉ ወንጌልን በመስበክና በማስተማር ሥራ መሳተፍ አለባቸው ከሚለው እውነት ጋር ተመሳሳይ ነው። ሆኖም ቀን ክርስቲያኖች ሁሉ ነቢያት አይሆኑም። የእግዚአብሔርን እውነት ያለማቋረጥ በቤተ ክርስቲያን ለማስተላለፍ ስጦታና ችሎታ ላላቸው ሰዎች የተሰጠ ነው።  ነቢይ ከእግዚአብሔር ቃልን በቀጥታ ተቀብሎ ብዙ ጊዜ ለእግዚአብሔር ሰዎች የሚናገር ነው። ይህ መገለጥ ላለ ወደፊቱ ጉዳይ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ስለሌላ ሰው ምስጢር የሆነ መልእክት ወይም እግዚአብሔር ሕዝቡ በተቀጻሚ እንዲያደረገው የሚፈልገውን ነገር መግለጥ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ነቢዩ የአንድ ጊዜ መገለጥን የሚያመጣ ሳይሆን እግዚአብሔር ለሕዝቡ የሚሆነውን መልእክት ያላማቋረጥ የሚሰጠውና ለሌሎች የሚያስተላለፍ ሰው ነው። ብዙ ሰዎች ከእግዚአብሔር ዘንድ እንዳንድ መልእክቶች የሚቀበሉ ቢሆኑም ነቢይ ግን የእግዚአብሔርን ፈቃድ ያላማቋረጥ የመግለጥ አገልግሎት አለው።  ከእግዚአብሔር ዘንድ ስለሆነ ስለ ትንቢት ወይም መገለጥ ስናስብ ለለ ሁላት ዋና ዓይነት ትንቢቶች ለይተን መናገር አለብን። አንደኛ ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ ሕዝቡ በነቢይ አማካይነት የሚመጡ አንዳንድ ትንቢተች ነበሩ። እግዚአብሔር እነዚህን ትንቢቶች የመጽሐፍ ቅዱሳችን አካል ለመሆን በሚጻፉበት ወቅት ጥንቃቄ አድርጐባቸዋል። እነዚህ ትንቢተች ነቢዩ የእግዚአብሔርን መልእክት በተቀበለበት ግልጽነት ብቻ ሳይሆን መገለጦች በተጻፉባቸው ቃላትም ጭምር መለኮታዊነትን የተላበሱና በእግዚአብሔር ቁጥጥር የተከናወኑ ነበሩ። በሙሉ መተማመን መጽሐፍ ቅዱስ ሰዎች በእግዚአብሔር መንፈስ ተነድተው የጻፉት ነው የምንለው ለዚህ ነው። ቃሎቹ እንኳ በእግዚአብሔር የተጠበቁ እስከሚሆኑ ድረስ በመንፈስ ቅዱስ የተጠነቀቀለትና አንዳችም ስሕተት የሌለበት ነው (ማቴ. 5፡7-18)። እግዚአብሔር እንደዚህ ዓይነቱን ትንቢት መስጠት አቁሟል (ራእይ 22፡18-19)። ሰዎች በእግዚአብሔር መንፈስ ተነድተው የጻፉት ሥልጣን ያለው መጽሐፍ ተጠናቋል። የእግዚአብሔር ፈቃድ ምን እንደሆነ ማወቅ እንድንችል፥ እግዚአብሔር መመዘኛ እንድናደርገው የሚፈልገውን እውነት በሙሉ በስድሳ ስድስቱ የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ውስጥ በተጻፈው መገለጥ አማካኝነት እናገኛለን። የትኛውም የወንጌል አማኝ የሆነ . ክርስቲያን ከእግዚአብሔር የተቀበላው ትንቢት የመጽሐፍ ቅዱስ ያህል ጥራትና ሥልጣን እንዳለው መናገር አይችልም። የኑፋቄ ትምህርቶች አንዱ ምልክት ሌሎች ጽሑፎችን ሥልጣን ባለው መጽሐፍ ቅዱስ ላይ መጣመራቸው ነው። ሰዎች በእግዚአብሔር መንፈስ ተነድተው የጻፉት መጽሐፍ ቅዱስ እውነት ናቸው የሚባሉት ሌሎች ትምህርቶች ሁሉ የሚዳኙበት ብቸኛው መንፈስ ቅዱስ ያረፈበት የእግዚአብሔር ቃል ነው።  ሁለተኛ፥ እግዚአብሔር በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት ለሕዝቡ የሚሰጣቸው ሌሎች መገለጦች አሉ። እነዚህ መገለጦች በተለያዩ መልኮች ሊመጡ የሚችሉ ናቸው። ሕልሞችና ራእዮች ሊኖሩ ይችላሉ። በሌላ ጊዜ ደሞ አንድን ነገር የማድረግ ወይም የመናገር ጠንካራ ውስጣዊ ስሜት ይኖራል። ወዲያውኑ ባንረዳውም እንኳ ከጊዜ በኋላ የተናገረን እግዚአብሔር እንደነበር እናውቃለን። ለአንዳንዶች እግዚአብሔር ግልጽ የሆነ ቃል በድምጽ ወይም በውስጣዊ ስሜትን ሰጥቶአቸዋል። ለምሳሌ እግዚአብሔር ምስጢራዊ በሆነ መንገድ የምታገባት ሴት ይህች ናት በማለት እንደተናገራቸው ያውቃሉ። ሌሎችን ደግሞ ኢየሱስ ክርስቶስን ለመቀበል ወደተዘጋጀ ሰው «ሂድና ላዚያ ሰው ስለ እኔ ተናገር» ብሎ እግዚአብሔር ወርቶአቸዋል። እነዚህ መገለጦች በሙሉ ከእግዚአብሔር ናቸው። እግዚአብሔር ምን እንድናደርግ እንደሚፈልግ በትክክል የሚናገሩ ናቸው። ነገር ግን እነዚህ መገለጦች እግዚአብሔር በመጽሐፍ ቅዱስ ከሰጣቸው መገለጦች የተለዩ ናቸው። የሚለዩት በሁለት መንገዶች ነው።  1. በእንደዚህ ዓይነት መገለጦችና በመጽሐፍ ቅዱስ መገለጥ መካከል ያለው ትልቁ ልዩነት በብሉይና በአዲስ ኪዳን መጻሕፍት እግዚአብሔር መልእክቱን መስጠቱ ብቻ ሳይሆን መልእክቱ ወደ ሰዎች የሚደርስበትን ሁኔታ እንኳ በመጠበቅ አንዳች ስሕተት እንዳይኖር እደረገ። ዛሬ እግዚአብሔር የትንቢት ቃሎችን ወይም መገለጦችን ሊሰጥ የሚነገረውን ቃል እይጠብቅም። በሌላ አባባል የመጨረሻው ውጤት ወይም የሚሰጠው መልእክት የመጽሐፍ ቅዱስን ያህል መላኮታዊነትን የተላበሰ አይደለም።  2. በመጽሐፍ ቅዱስ የተሰጡ መገለጦች ለዓለም አቀፍዋ ቤተ ክርስቲያን የተሰጡ ናቸው። በመጽሐፍ ቅዱስ ተጽፈው ያሉ በሙሉ በየትኛውም ዘመን በየትኛውም አገር ለሚኖሩ ለየትኛውም የብሔር አባላት የተሰጡ ናቸው። ዛሬ በዚህ ዘመን ላለ አንድ ቀለሰብ ወይም ለአንድ የአማኞች ኅብረት ብቻ የተወሰኑ አይደለም። ምንጭ፡- “የመንፈስ ቅዱስ የጥናት መምሪያና ማብራሪያ”፣ በቲም ፌሎስ ተጽፎ፣ በጌቱ ግዛው የተተረጎመ እና በኤስ አይ ኤም ጽሑፍ ክፍል የተዘጋጀ ነው፡፡ ለዚህ ድንቅ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡ ይህን ጽሁፍ ኮፒ እና ፕሪንት አድርጎ መጠቀም ይቻላል፤ ሆኖም ጽሁፉን መለወጥና ለሽያጭ ማዋል በሕግ የተከለከለ ነው፡፡

ትንቢት ምንድን ነው? ነቢይስ? Read More »

በቤተ ክርስቱያን ውስጥ ስለሚመጣው ትንቢት ተጨማሪ አሳቦች

ዮሐንስ ጐላ ያላ ድምፅ ማውጣት የሚችል ወጣት ሰው ነበር። አንድ ቀን የጸሎት ስብሰባ ተካፈለ። መሪው ሰዎችን ለበለጠ ጸሎት ያነሣሣል ብሎ በማሰብ የመሰብሰቢያ ክፍሉን መብራት አጠፋው። ወዲያውኑ ሰዎች በከፍተኛ ድምፅ መጸለይ ጀመሩ። አንዳንዶቹ በልሳናት ይጸልዩ ነበር። በድንገት በቡድኑ ውስጥ ከነበሩት ሰዎች አንዱ ወደ ዮሐንስ «መጣና እግዚአብሔር ለአንቺ የሚሆን መልእክት ሰጥቶኛል» አለው። «ማሕፀንሽ አሁን ተስፍቶአልና ልጅ ይኖርሻል» አለው። ዮሐንስ ቀን መለሰና እኔ እኮ ወንድ ነኝ አለው። ሰውዬውም መልሶ «እግዚአብሔር በውስጥህ ያለውን ከፉ መንፈስ ይገስጸው» አለው።  ትንቢት መናገርና የጌታን ቃል እንደተናገሩ መቁጠር። ከላይ የተመለከትነው ታሪክ መንፈሳዊ ስጦታ ያለአግባብ ሥራ ላይ የዋለበትን አንድ ሁኔታ ብቻ የሚያሳየን ነው። ያ ቃል የማን ነበር! የእግዚአብሔር ቃል እንዳልነበረ ግልጽ ነው። ስለዚህ የሌላ አካል ማለትም የሰው ወይም የክፉ መንፈስ ነው። ይህ የጌታ ቃል አለኝ በማለት የሚናገርን ሰው ሳንመዝነው እንዲናገር የመፍቀድን አደገኛነት የሚያሳየንና የሚያስጠነቅቀን ይሆናል። በዚህ ዘመን በአብያተ ክርስቲያናት አካባቢ የሐሰት ትምህርቶችና ልምምዶች በታላቅ ፍጥነት እያደጉ የመጡበት አንድ ምክንያት የሰማናቸውን መልእክቶች ለመመዘን ባለመቻላችን ነው። ቢሆንም እግዚአብሔር አሁንም መናገሩን አይተውም። ከተዘረዘሩት መንፈሳዊ ስጦታዎች አንዱ የትንቢት ስጦታ ነው። ዛሬ ይህን ስጦታ በመመልከት መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ስጦታ የሚያስተምረውን እንመለከታለን።  ጥያቄ፡- ሀ) አንድ ሰው ከእግዚአብሔር የተሰጠ መልእክት አለኝ ያለበትን ሁኔታ ግለጽ። ከእግዚአብሔር ዘንድ የተሰጠ ቃል ይመስልሃልን? ከእግዚአብሔር መሆኑንና ያለመሆኑን እንዴት ታውቃለህ? ለ) አንድ ሌላ ሰው ደግሞ ከእግዚአብሔር መልእክት አለኝ ብሉ የመጣበትንና አንተ ደግሞ መልእክቱ ከእግዚአብሔር መሆኑን የተጠራጠርክበትን ሌላ ሁኔታ ግላጽ፡ ከእግዚአብሔር እንዳልሆነ ለምን አሰብክ?  ጥያቄ፡- የሚከተሉትን ጥቅሶች አንብብ። 1ኛ ተሰ. 5፡20፤ 1ኛ ቆሮ. 145 12፡8-14፤ ሮማ 12፡6፤ ኤፌ. 2፡20፤ 4፡11፣ 1ኛ ጢሞ. 18፤ 4፡14። በእነዚህ ጥቅሶች ስለ ትንቢት የተነገሩ የተለያዩ እውነቶችን ዘርዝር።  በጳውሎስ መልእክቶች ከተዘረዘሩት መንፈሳዊ ስጦታዎች በሙሉ በተደጋጋሚ የተጠቀሰው የትንቢት ስጦታ ነው። ነቢያት በቀደምቷ ቤተ ክርስቲያን እጅግ አስፈላጊዎች ስላነበሩ እንደ ዋና የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ሆነው ተመዝግበዋል። ቀደምታ ቤተ ክርስቲያን የተገነባችበት መሠረት አካል ነበሩ (ኤፌ. 2፡20)። ስለዚህ ነቢያትም ሆኑ የትንቢት ስጦቃዎች በቀደምቷ ቤተ ክርስቲያን ዋና ክፍል ነበሩ።  በልሳናት መናገር መንፈሳዊ ስጦታ እንደሆነው ሁሉ የትንቢት ስጦታም ዛሬ በክርስቲያኖች መካከል አከራካሪ ጉዳይ ነው። ይህ መንፈሳዊ ስጦታና (እግዚአብሔር ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጥ ከልጆቹ ጋር የሚያደርገው ቀጥተኛ ግንኙነት በሙሉ) ከአዲስ ኪዳን መጻፍ በኋላ ቆሟልን? ብዙ ክርስቲያኖች በተለይ ደግሞ በልሳናት የመናገር ስጦታ በዚህም ዘመን መሥራቱን የማይቀበሉ ሁሉ የሚሉት ይህንን ነው። ወይስ የትንቢት ስጦታ ዛሬም ቢሆን የሚሠራ ነው? እግዚአብሔር ዛሬም ቢሆን በሕልም፥ በራእይ፡ በድምፅ፥ ወዘተ… ይናገረናልን? ይህ ከሆነ ይህ ስጦታ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ያለው ግንኙነት ምንድን ነው? የትንቢት ቃሎች በአዲስና በብሉይ ኪዳን ካሉ ቃሎች ጋር እኩል ሥልጣን አላቸው?  ጥያቄ፡– ሀ) ስለትንቢት ምንነት የምታምነውን ጻፍ። ላ) ነቢይ ምንድን ነው? ሐ) የእግዚአብሔርን ቃል በጻፈ የብሉይ ኪዳን ነቢይና በዚህ ዘመን የትንቢት መንፈሳዊ ስጦታ አለኝ በሚል ሰው መካከል ልዩነት ያላ ይመስልሃልን? ካለስ ልዩነቱ ምንድን ነው?  በትንቢት ምንነትና በነቢይ ማንነት ርእሰ ጉዳይ ላይ በዚህ ዘመን ባለች ቤተ ክርስቲያን ብዙ ውዥንብር አላ። በአንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት ሰዎች ይቆሙና ከእግዚአብሔር ዘንድ የተቀበሉት የትንቢት ቃል እንዳላቸው ይናገራሉ። የሚያመጡት መልእክት ግን ለእግዚአብሔር ሕዝብ ምንም ወይም አነስተኛ ዋጋ ብቻ ያለው ይሆናል። አንዳንድ ጊዜ የእግዚአብሔር ቃል ከሚያስተምረው ጋር እንኳ የሚቃረን ይሆናል። አንዳንድ ሰዎችን የትንቢት ቃል ያመጡ ዘንድ እነርሱን የመጠባበቅ ዝንባሌ እየጨመረ መጥቷል። እግዚአብሔር ተናገረኝ ስንል ምን ማለታችን እንደሆነና የትንቢትን ምንነት በሚገባ ካላወቅን እንስታለን። ምንጭ፡- “የመንፈስ ቅዱስ የጥናት መምሪያና ማብራሪያ”፣ በቲም ፌሎስ ተጽፎ፣ በጌቱ ግዛው የተተረጎመ እና በኤስ አይ ኤም ጽሑፍ ክፍል የተዘጋጀ ነው፡፡ ለዚህ ድንቅ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡ ይህን ጽሁፍ ኮፒ እና ፕሪንት አድርጎ መጠቀም ይቻላል፤ ሆኖም ጽሁፉን መለወጥና ለሽያጭ ማዋል በሕግ የተከለከለ ነው፡፡

በቤተ ክርስቱያን ውስጥ ስለሚመጣው ትንቢት ተጨማሪ አሳቦች Read More »