ሌሎች ትምሕርቶች

በውኑ፣ ክርስቶስ ያማልዳልን?

1. መግቢያ፡- የሰው ልጅ ውድቀት የዚህ ጽሁፍ አቢይ አላማ በየዕለቱ በሚገጥሙን ጉዳዮች ማለትም፣ ስለታመሙ ሰዎች፣ በእስር ስላሉ ሰዎች፣ ስለ መሪዎች፣ ስለ ቤተ ክርስቲያን፣ ስለ አገር፣ ስለ አገልግሎት፣ ወዘተ አንዱ ለሌላው ወደ ፈጣሪው የሚያደርሰው የምልጃ ጸሎት፣ ክርስቶስ ለእኛ ባደረገው የማማለድ ሥራ ላይ ጥላውን እንዳያጠላበት ጥንቃቄ እንድናደርግ ለማሳሰብ ነው፡፡ እነደነዚህ አይነቶቹ – አንዱ ስለ ሌላው የሚጸልየው ጸሎት – ክርስቶስ ለእኛ ከፈጸመው የምልጃ አገልግሎት ጋር ምንም ዝምድና እንደሌለው ማሳሰብና እነዚህ ሁለት ነገሮች ሊነጻጸሩም ጭምር እንደማይገባ ማሳየት፣ የማንም ሰው የጸሎት ምልጃ የክርስቶስን የመስቀል ላይ ምልጃ ሊተካው እንደማይችል መግለጽ፣ እንዳውም አንዳችን ለአንዳችን የመጸለይ (የመማለድ) ፈቃድን ያገኘነው በክርስቶስ የምልጃ ሥራ ከእግዚአብሔር ጋር ስለታረቅንና ከተቆጣን ፈጣሪ ጋር ሰላም ስለፈጠርን መሆኑን ማስገንዘብ የዚህ ጽሁፍ ዋነኛ ጉዳዮች ናቸው፡፡ ይህንን አሳብ ለመገንዘብ ይረዳን ዘንድ ከችግሩ መነሻ ማለትም ከሰው ልጅ የውድቀት ታሪክ እንነሳና ጉዳዩን በጥልቀት እንመልከት፡፡ የሰው ልጅ፣ አጽናፈ አለሙ፣ የምድር አራዊት፣ የሰማይ ወፎች፣ የባሕር ዓሶች ከተፈጠሩ በኋላ በፈጣሪው አምሳል በስድስተኛው ቀን የተፈጠረ ልዩ ፍጥረት ነው፡፡ ከእርሱ ቀድሞ የተፈጠሩትን ይገዛና ያስተዳድር ዘንድ ሃላፊነት ጭምር የተሰጠው ይህ ሰው፣ ይኖርበት ከነበረው ዔደን ገነት የአንዲቷን ዛፍ ፍሬ እንዳይበላ ከፈጣሪው ትእዛዝ ተሰጠው፡፡ በፈጣሪው ላይ መታመን ያልፈለገው የሰው ልጅ በትዕቢት ከፍሬዋ ቀጥፎ በላ፡፡ ከፍሬዋ በበላህ ጊዜ ሞትን ትሞታለህ ያለው አምላክም ጻድቅ ፈራጅ እንደ መሆኑ፣ የጽድቅ ብያኔውን በራሱ ላይ ተደግፎ ለመኖር በወሰነው በዚህ የሰው ልጅ ላይ አስተላለፈ፡፡ ከብያኔዎቹ መካከል አንዱ እንዲህ ይነበባል ፡- “… የሚስትህን ቃል ሰምተሃልና፣ ከእርሱ እንዳትበላ ካዘዝሁህ ዛፍም በልተሃልና፣ ምድር ካንተ የተነሳ የተረገመች ትሁን፤…” (ዘፍ. 3፡17)፡፡ የሰውና የፈጣሪ ጠብ እንግዲህ ከዚህ መጥፎ ጊዜ ይጀምራል፡፡ ከዚህች ቀንና ሰዓት ጀምሮ ሰውና ፈጣሪው ጥለኞች ሆኑ፡፡ እግዚአብሔር ለሰው ልጅ ያዘጋጀውም መልካም ሃሳብ በሰይጣን ፈታኝነት፣ በሰው ልጅ ተባባሪነት እንቅፋት ገጠመው፡፡ አግዚአብሔር ሕግ ሰጠ፣ የሰው ልጅ ተላለፈው፣ ፈጣሪም የጽድቅ ፍርድ አስተላለፈ፡፡ ይህም ፍርድ ሞት ይባላል፡፡ የሰው ልጅ በሞት ፍርሃት ውስጥ እየማቀቀ ለበርካታ አመታት በምድር ላይ የስቃይ ኑሮ መግፋት ጀመረ፡፡ ይህን ፍርድ ያስተላለፈው አምላክ ጻድቅ ብቻ ሳይሆን የፍቅር አምላክ በመሆኑ፣ ከእስትንፋሱ የተካፈለው ሰው በምድር ላይ ሲሰቃይ ማየት አላስቻለውም፡፡ በዚህም ምክኒያት ጻድቅ ፈራጅነቱንና የፍቅር አምላክነቱን አዋህዶ የሚያሳይ የድነት (የደኅንነት) መንገድ ለሰው ልጅ አዘጋጀ፡፡ ይህ የድነት መንገድ፣ ጽንፍ የሚመስሉትን የአምላክ ሁለት ባሕሪያት (ፍርድና ምሕረት) በአንድ መስመር ያገናኘ አስገራሚ ክስተት ነበር፡፡ እግዚአብሔር በሰው ዘር ሁሉ ላይ ያሳለፈው ሊታጠፍ የማይችል የሞት ፍርድ ሳይቀለበስ፣ የሰው ልጅ ከተቆጣው አምላኩ ጋር ታረቀ፡፡ የአገራችን የእምነት ሊቃውንት ይህንን ሁኔታ ግሩም በሆነ መንገድ እንዲህ በማለት ይገልጹታል፡፡ «እግዚአብሔር ሰውን ከፈጠረበት ጥበቡ ይልቅ ያዳነበት ጥበቡ ተጠበበች”፡፡ የዚህ አስገራሚ ትዓይንት ጀማሪ፣ ማእከሉ እና ፈጻሚው ደግሞ ምንም በደል ያልተገኘበት ኢየሱስ ነበር፡፡ እግዚአብሔር በሰው ልጅ ላይ የተቆጣውን ቁጣ በኢየሱስ ላይ አሳረፈው፤ ፍርዱን አሳየ፡፡ ኢየሱስ ስለ ኃጢአተኞቹ ስለ እኛ ሞተ፡፡ በእርሱም ምክኒያት የሰው ልጅ ምኅረትን ተቀበለ፡፡ ከፈጣሪውም የፍርድ ቁጣ ተረፈ (ሮሜ. 5፡9)፡፡ የብሉይና የሐዲስ ኪዳናት ቅዱሳት መጻሕፍት አስኳልና መሰረታዊ ጭብጥም ይኸው ታላቅ ሥራ ነው፡፡ ብሉይ ኪዳን የሐዲሱ ኪዳን ጥላ/ምሳሌ (ዕብ. 10፡1) እንደ መሆኑ፣ በዚህ ዘመን ውስጥ የሰው ልጅ የድነት መሰረት የሆነው (1ቆሮ. 3፡10-11) ክርስቶስ ዘመኑ ደርሶ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ እስኪመጣ ድረስ፣ በታላቅ ምጥ ውስጥ ነበር፡፡ በብሉይ ኪዳን የሰው ልጅ ጥላ የነበረውንና ፍጹም ሊያደርገው የማይችለውን የእርቅ ሥርዓት (ዕብ. 9፡9፣10) እየፈጸመ ከአምላኩ ጋር ሊያስታርቀው የሚችለውን ፍጹሙን የድንነት ተስፋ መጠበቅ ጀመረ፡፡ አንዳንዶች ይህን ተስፋ በሩቅ ተሳለሙት (ዕብ. 11፡13፣ 11፡49፣40)፤ ሊሎች ደግሞ ይህን ተስፋ በአይናቸው አዩት (ሉቃስ 2፡29-32)፡፡ የዚህ ጽሑፍ አንባቢ እርሶ እና እኔ ደግሞ በዚህ የምሕረት ዘመን ውስጥ ለመገኘት የእግዚአብሔር መልካፍ ፈቃድ ሆነ፡፡ የሰው ልጆች ሁሉ ተስፋ የነበረው፣ የዓለሙን ሁሉ ኃጢአት የሚቤዠው፣ ሰውንና እግዚአብሔርን የሚያስታርቀው፣ የተዋረደውንና በውድቀት ከእግዚአብሔር ቁጣ ስር ለሞት የሚጠበቀውን የሰውን ዘር የሚታደገው ብቸኛ አዳኝ እስኪመጣ ድረስ፣ የሰው ልጅ የዚህን ፍጹም ተስፋ ጥላ እየተከተለ አካሉን ናፈቀ፡፡ ጥላው የነበረውን የብሉይ ሥርዓት እየፈጸመ የአካሉን መገለጥ ለግማሽ ምዕተ ዓመት በናፍቁት መጠበቅ ግድ ሆነበት፡፡ ከዚህ በታች ባሉት ጥቂት አንቀጾች ከሰው ውድቀት አንስቶ እስከ መሲሁ መምጣት ድረስ ባለው ግማሽ ምዕተ አመት፣ የሰው ልጅ ከእግዚአብሔር ጋር ተቀባይነት ያለውን ሕብረት ለማድረግ፣ የኃጢአት ሥርየትን ለማግኘትና የምስጋና መሥዋዕት ለማቅረብ ምን ነገሮችን ይፈጽም እንደነበረ አለፍ አለፍ እያልን እናያለን፡፡ ይህ የብሉይ ሥርዓት ሊመጣ ያለው እውነተኛ አካል ጥላ/ምሳሌ እንደሆነ አንባቢ ልብ ይበል (ቆላ. 2፡17)፡፡ በዚህ ስር የምናያቸው ቁም ነገሮች ግልጽ ከሆኑ፣ ኋላ ላይ የምናየው የሐዲስ ኪዳኑ አካል ፍሬ አሳብ ፍንትው ብሎ ይታየናል፡፡ 2. የብሉይ ኪዳን ክህነት የክህነት አገልግሎት የእስራኤል ሕዝብ በሙሴ መሪነት ከግብጽ ባርነት ከወጣ በኋላ የተጀመረና ለአንድ ሺህ አመታት የዘለቀ ታላቅ አገልግሎት ነው፡፡ እነዚህ የክህነት ሕግጋቶች ለእስራኤል የተሰጡት በሲና ተራራ ላይ ሲሆን (ዘሌ. 7፡38፣ 25፡1፣ 26፡46፣ 27፡34) የአገልግሎቱም አስፈላጊነት እስራኤል የኃጢአት ስርየትን በመቀበል ከርኩሰት ነጻ እንዲሆን ነበር (ዘሌ. 11፡45)፡፡ ይህ የአምልኮ ሥርዓት አንዳንዶች የብሉይ ኪዳን ወንጌል በሚሉት የዘሌዋዊያን መጽሐፍ ላይ በስፋት ሰፍሮ እናገኘዋለን፡፡ ካህን፣ የሰው እንደራሴ በመሆን መባና መሥዋዕት በማቅረብ ሰውን ከእግዚአብሔር ጋር የሚያስታርቅ አገልጋይ ነው፡፡ በሰውና በእግዚአብሔር መካከል በመቆም የሚማልድ ነው፡፡ «ከሰው ተመርጦ ለእግዚአብሔር በሆነው ነገር ሁሉ ስለ ሰው ይሾማል” (ዘጸ. 28፡1፣ ዕብ. 5፡1-4) የሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ የካህናትን አጠራርና ተግባር በግልጽ ያሳያል፡፡ የዘሌዋዊያን መጽሐፍ ጭብጥ ወደ እግዚአብሔር መቅረብ የሚቻለው በመሥዋዕት አማካኝነት ብቻ መሆኑን ያስገነዝባል፡፡ ይህም ምሥዋዕት በእስራኤል የአምልኮ አገልግሎት ውስጥ ትልቅ ስፍራ እንዳለው ጨምሮ ያስገነዝባል፡፡ እስቲ አሁን በአጭሩ የአሮን ክህነት ባሕሪን እንመልከት፡፡ 2.1 የአሮን ክህነት የሰው ልጅ በኃጢአት ከወደቀ በኋላ በእግዚአብሔር ፊት ዳግም ተቀባይነት ያለውን ኑሮ ለመግፋትና እግዚአብሔርን ለማምለክ የክህነትን ሥራ ተጠቅሞበታል፡፡ እግዚአብሔር የነገድ ምርጫ ሳያደርግ የእስራኤልን ሕዝብ ባጠቃላይ የእርሱ ካህን የማድረግ ውጥን ቢኖረውም (ዘጸ. 19፡6) ሙሴ በሲና ተራራ ላይ ሕግና ትዕዛዛት የድንጋይም ጽላት ለመቀበል አርባ ቀንና ለሊት ከእግዚአብሔር ጋር የቆየበትን አጋጣሚ በመጠቀም የወርቅ ጥጃ ሰርተው በማምለካቸው ምክንያት ለዚህ ክህነት አገልግሎት የሌዊን ነገድ ብቻ ለመምረጥ ተገደደ፡፡ ከዚህ ነገድ ደግሞ የመቅደሱን ውስጠኛ አገልግሎት ለመፈጸም የተፈቀደለት የአሮን ቤተሰብ ብቻ ነበር (ዘኁ. 3፡10)፡፡ ስለ መሥዋዕቶቹ ስንመልከት ደግሞ፣ በመጀመሪያዎቹ ሰባት የዘሌዋዊያን መጽሐፍ ሃሳብ መሰረት አራት ዋና ዋና መሥዋዕቶች እናያለን፡፡ እነዚህም የሚቃጠል መሥዋዕት፣ የኃጢአት መሥዋዕት፣ የበደል መሥዋዕትና የደኅንነት መሥዋዕት በመባል ይታወቃሉ፡፡ ሊቀ ካህናት 4 ዋና ዋና ተግባራት ሲኖሩት እነዚህም በእግዚአብሔር ፊት የእስራኤል እንደራሴ መሆን (ዘጸ. 28፡17-29)፣ የነቢይነትን አገልግሎት በአግባቡ መወጣት (ዘጸ. 28፡30)፣ ለሕዝቡ ቡራኬ መስጠት (ዘኁ. 6፡22-27)፣ በማስተረያ ቀን ሥርዓቱን መፈጸም እና ለሕዝቡ መጸለይ (1ሳሙ. 12፡23) ናቸው፡፡ የመሥዋዕት አቀራረቡን በተመለከተ ደግሞ ካህናት በየዕለቱ የሚቀርቡ መሥዋዕቶችን የሚያሳርጉ ሲሆኑ፣ በዓመት አንድ ጊዜ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን በመግባት መሥዋዕት ማቅረብ የሚፈቀድላቸው ግን ሊቀ ካህናት ብቻ ነበሩ፡፡ ሊቀ ካህኑ በአመት አንድ ጊዜ፣ የማስተስረያ ቀን በመባል በሚታወቀው ልዩ ዕለት፣ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ገብቶ የሚፈጽመው ስርዓት የሚከተለውን ይመስላል፡- አሮን ሊቀ ካህናት ሆኖ ለመሥዋዕትነት ከሚቀርቡት ከሁለቱ ፍየሎች አንዱን «ስለ ሕዝቡ ኃጢአት የሚሰዋውን … ፍየል ያርዳል፤ ደሙንም ወደ መጋረጃው ውስጥ ያመጣዋል በወይፈንም ደም እንዳደረገ በፍየሉ ደም ያደርጋል፤ በመክደኛውም ላይና በመክደኛውም ፊት ይረጨዋል´፡፡ ይህንም ሥርዓት ከፈጸመ በኋላ «ሕያውን ፍየል ያቀርባል፤ አሮንም ሁለቱን እጆቹን በሕያው ፍየል ራስ ላይ የጭናል፤ በላዩም የእስራኤልን ልጆች በደል ሁሉ፣ መተላለፋቸውንም ሁሉ ኃጢአታቸውንም ሁሉ ይናዘዛል፤ በፍየሉም ራስ ላይ

በውኑ፣ ክርስቶስ ያማልዳልን? Read More »

ለምን እግዚአብሔር ክፉ ነገር በመልካም ሰዎች ላይ እንዲደርስ ይፈቅዳል?

በስነ-መለኮቱ አለም ከሚነሱ ዋነኛ ጥያቄዎች መካከል አንዱ ለምን እግዚአብሔር ክፉ ነገር በመልካም ሰዎች ላይ እንዲደርስ ይፈቅዳል? የሚለው ነው። እግዚአብሔር መጀመሪያ እና መጨረሻ የለውም፣ ሁሉን ቻይ፣ በሁሉ ስፍራ በአንዴ የሚገኝ እንዲሁም ሁሉን አዋቂ ነው። በተቃራኒው ሰው ደግሞ ፍጡር፣ ውሱን እና በስባሽ ነው። ይህ ፍጡር ትልቁን ፈጣሪ ሙሉ በሙሉ ለመረዳት ሲሞክር ነው እንግዲህ እነኚህን የመሳሰሉ ጥያቄዎች መነሳት የሚጀምሩት። ሰው፣ ፈጣሪውን ሙሉ በሙሉ ሊረዳው እንደሚችል ሊያስብ አይገባውም የሚለውን አጠቃላይ እውቀት ከግንዛቤ ከተን ወደተነሳንበት ርዕሰ ጉዳይ እንመለስ። ለምን እግዚአብሔር ክፉ ነገር በመልካም ሰዎች ላይ እንዲደርስ ይፈቅዳል? ስለዚህ ጉዳይ የኢዮብ መጽሐፍ መጠነኛ ግንዛቤ ይሰጠናል። ሰይጣን ኢዮብን እና የኢዮብ የሆነውን ሁሉ (ከነፍሱ በስተቀር) እንዲያጠፋ ከእግዚአብሔር ፈቃድ አገኘ። ለዚህ የእግዚአብሔር ውሳኔ የኢዮብ ውሳኔ ምን ነበር? ‘‘እነሆ፥ ቢገድለኝ ስንኳ እርሱን በትዕግሥት እጠባበቃለሁ ነገር ግን መንገዴን በፊቱ አጸናለሁ’’ (ኢዮብ 13፡15)። ‘‘ራቁቴን ከእናቴ ማኅፀን ወጥቻለሁ፥ ራቁቴንም ወደዚያ እመለሳለሁ እግዚአብሔር ሰጠ፥ እግዚአብሔርም ነሣ የእግዚአብሔር ስም የተባረከ ይሁን’’ (ኢዮብ 1፡21)። በሕይወቱ ላይ ይህ ክፉ ነገር እንዲደርስ እግዚአብሔር ለምን እንደፈቀደ ኢዮብ ምንም ግንዛቤ አልነበረውም። ነገር ግን እግዚአብሔር መልካም እንደሆነ ስለሚያውቅ እምነቱን በእግዚአብሔር ላይ ጣለ። የነገሩም ዋነኛ ጉዳይ ይኸው ነው – በእንደዚህ አይነት ወቅቶች የእኛም ምላሽ እንዲሁ ሊሆን ይገባል። ለምን ክፉ ነገር በመልካም ሰዎች ላይ ይደርሳል? ለዚህ ጥያቄ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምላሹ – በዚህ ምድር ላይ ምንም አይነት ‘መልካም’ ሰው የለም የሚል ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ሁላችን ከሃጢአት በታች እንደወደቅን፣ በሃጢአት እንደተበከልን በተደጋጋሚ ይነግረናል (መክብብ 7፡20፤ 1ዮሐንስ 1፡8)። በምድር ላይ መልካም ነገር ገንዘቡ የሆነች፣ ኃጢአትንም የማያደርግ ሰው አለመኖሩን ሮሜ 3፡10-18 በግልጽ ያሳየናል፣ ‘‘ጻድቅ የለም አንድ ስንኳ፤ አስተዋይም የለም፤ እግዚአብሔርንም የሚፈልግ የለም፤ ሁሉ ተሳስተዋል፥ በአንድነትም የማይጠቅሙ ሆነዋል፤ ቸርነት የሚያደርግ የለም፥ አንድ ስንኳ የለም። ጕሮሮአቸው እንደ ተከፈተ መቃብር ነው፥ በመላሳቸውም ሸንግለዋል፤ የእባብ መርዝ ከከንፈሮቻቸው በታች አለ፤ አፋቸውም እርግማንና መራርነት ሞልቶበታል፤ እግሮቻቸው ደምን ለማፍሰስ ፈጣኖች ናቸው፤ ጥፋትና ጉስቁልና በመንገዳቸው ይገኛል፥ የሰላምንም መንገድ አያውቁም። በዓይኖቻቸው ፊት እግዚአብሔርን መፍራት የለም።’’ በዚህ ምክንያት በዚህ ምድር ላይ የሚኖር እያንዳንዱ ሰው በአሁኑ ሰአት ሊያገኝ የሚገባው አንድ እና ትክክለኛ ነገር ቢኖር ወደ እቶን እሳት መጣል ብቻ ነው። ከዚህ በተቃራኒው በሆነ መንገድ በዚህ ምድር ላይ የምናሳልፋት እያንዳንዷ መልካም ሰከንድ የእግዚአብሔር ምህረት እና ፀጋ ውጤት ናት እንጂ የተገባን ሆና አይደለም። በዚህች ምድር ላይ የምንቀበለው ትልቁ ክፉ ነገር በሲኦል ልንቀበለው ከነበረው ታላቅ መከራ ጋር ሲተያይ የአግዚአብሔርን ምህረት አሳንሰን እንድናይ ሊያደርገን አይገባም። እናም፣ ጥያቄው ሊሆን ይገባ የነበረው – ‘‘ለክፉዎች ለምን እግዚአብሔር መልካም ነገር እንዲሆንላቸው ፈቀደ?’’ የሚል ነበር። ሮሜ 5፡8 እንዲህ ይላል፣ ‘‘ነገር ግን ገና ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ስለ እኛ ሞቶአልና እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር ያስረዳል’’። እርሱ የእኛ  ክፋት፣ ሃጢአትና ጠማማነት ሳያግደው ልጁን ስለእኛ ሲል ለሞት አሳልፎ እስከመስጠት ድረስ ይወደናል (ሮሜ 6፡23)። ኢየሱስ ክርስቶስን እንደ አዳኝ የምንቀበለው (ዮሐንስ 3፡16፤ ሮሜ 10፡9) ከሆነ፣  ሃጢአታችን ይቅር ይባልልናል፣ በመንግስተ ሰማይም የዘላለም ቤት ይኖረናል (ሮሜ 8፡1)። ይህ የሚገባን ስጦታ አልነበረም። ይገባን የነበረው ገሃነመ እሳት ነበር። ነገር ግን እኛን ስለመውደዱ ምክንያት እምነታቸውን በኢየሱስ ላይ ባደረጉ ሁሉ ላይ ዘላለማዊ ሕይወትን አዟል። የም ሆኖ፣ አንዳንድ ጊዜ ክፉ ነገሮች ሊያገኛው አይገባቸውም በምንላቸው ሰዎች ላይ ሲደርሱ ይታያል። እነዚህ ነገሮች ባንረዳቸውም እንኳ በእግዚአብሔር ዘላለማዊ እቅድ ውስጥ ፋይዳ እንዳላቸው  ልናምን ይገባል። በሕይወታችን ላይ የመጣው ነገር ምንም ሆነ ምን፣ እግዚአብሔር መልካም፣ ፍቅር እና መሃሪ እንደሆነ ልንዘነጋ አይገባም። ልንገነዘባቸው የማንችላቸው ጉዳዮች ሲገጥሙን የእግዚአብሔርን መልካምነት ከመጠራጠር ይልቅ ልንታመንበት ይገባል። ‘‘በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፥ በራስህም ማስተዋል አትደገፍ በመንገድህ ሁሉ እርሱን እወቅ፥ እርሱም ጎዳናህን ያቀናልሃል’’ (ምሳሌ 3፡5-6)።

ለምን እግዚአብሔር ክፉ ነገር በመልካም ሰዎች ላይ እንዲደርስ ይፈቅዳል? Read More »

በውኑ አምላክ ከባድ ኃጢአቶችን ይቅር ይል ይሆን? ነፍሰ ገዳዩንስ ይቅር ይል ይሆን?

ብዙ ሰዎች፣ እግዚአብሔር እንደ ውሸት፣ ቁጣና ከፉ ሀሳብ የመሳሰሉ “ትንንሽ” ኃጢአቶችን ይቅር እንደሚል ያምኑና  ነገር ግን እንደ ግድያ እና ምንዝርና ያሉትን “ትላልቅ” ኃጢአቶች ይቅር እንደሚል ለማመን ይቸገራሉ። ይህ እውነት አይደለም። እግዚአብሔር ይቅር የማይለው “ትልቅ” ኃጢያት የለም። ኢየሱስ በመስቀል ላይ ሲሞት የመላው ዓለምን የኃጢአት ዋጋ ለመክፈል ሞቷል (1ኛ ዮሐንስ 2፡2)። አንድ ሰው ድነትን ለማግኘት በኢየሱስ ክርስቶስ ሲያምን፣ ለሁሉም ኃጥያቶቹ ይቅርታን ያገኛል። ይህም ይቅርታ ያለፈ፣ የአሁን፣ እና የወደፊት “ትልቅም ሆነ ትንሽ” ኃጥያቶቹን ያካትታል። ኢየሱስ የሞተው ለኃጢአቶቻችን ሁሉ ቅጣት ለመቀበል ነው። እናም ኃጢአተኛው ሰው ይቅር ከተባለ ዘንዳ ከሁሉም ኃጢአቶች ይቅርታን ያገኛል ማለት ነው (ቆላስያስ 1፡14; ሐዋርያት ሥራ 10:43)። ሁላችንም በኃጢያታችን ምክንያት በደለኞች ነን (ሮሜ 3፡23)። በበደላችን ምክንያት ደግሞ ዘላለማዊ ቅጣት መቀበል ይገባናል (ሮሜ 6 23)። ነገር ግን፣ መድሃኒታችን ኢየሱስ ቅጣታችንን ተቀብሎ ስለ እኛ ሞቷል (ሮሜ 5፡8)። ማንም ሰው ምንም ዓይነት ኃጢአት ቢሠራም እነኩዋን ለመዳን በኢየሱስ ክርስቶስ ካመነ፣ የኃጥያት የቅርታን ያገኛል (ሮሜ 6 23; ዮሐንስ 3:16)። ነፍሰ ገዳይ ወይም አመንዝራ ከውሸታሙ ሰው ይልቅ ለክፉ ተግባሩ (ህጋዊ፣ ማሀበራዊ፣ ወዘተ) ከባድ ችግሮች ሊደርስበት ይችላል። ነገር ግን ለድነቱ በክርስቶስ እስከታመነ ድረስ ለኃጥያቶቹ ሁሉ እንደማንኛውም ኃጢአተኛ ፍጹምና ዘላለማዊ ይቅርታን ያገኛል። የኃጢያት ይቅርታን ለማግኘት  ወሳኙ ነገር የኃጢአቱ አይነትና መጠን ሳይሆን ለኃጢያት ስርየት በክርስቶስ የተከፈለው የመስዋዕት መጠን ነው። ኃጢያት የሌለበት የእግዚአብሔር በግ (አኢየሱስ ክርስቶስ) የአለሙን ሁሉ ኃጢያት ሊያስወግድ የሚችል ከሆነ፣ ይህ መስዋዕት ሊከድነው የማይችለው የኃጢአት አይነትም ሆነ መጠን ሊኖር አይችልም። መጽሐፍ ቅዱስ “ተፈጸመ” ብሎ ሲናገር፣ የተሟላ ስርየት ተደረገ፤ እግዚአብሔር በመስዋዕቱ ረካ፤ ፍጹም ምህረት ተገኘ፤ ሰላም ተፈጠረ፤ ከኃጢአት ሁሉ መቤዠት ተገኘ ማለቱ ነው። የክርስቶስ መስዋዕት እውን እና የተሟላ ነው። ይህ መስዋዕት የጎደለው ነገር ስለሌለ በላዩ ላይ ማንም ምንም ነገር ሊጨመርበት አይችልም፤ ሊቀለበስውም እንዲሁ። መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የሕይወትዎ ጌታ በማድረግ ቀሪው ዘመንዎን ለመኖር ወስነው ከሆነ፣ ይህንን ሊንክ በመጫን ስምዎንና የኢ-ሜይል አድናሻዎን ይላኩልንና፣ ለመንፈሳዊ ሕይወት እድገትዎ የሚቻለንን ሁሉ እገዛ እናደርግሎታለን።

በውኑ አምላክ ከባድ ኃጢአቶችን ይቅር ይል ይሆን? ነፍሰ ገዳዩንስ ይቅር ይል ይሆን? Read More »