ሌሎች ትምሕርቶች

ዳግም ልደት ማለት ምን ማለት ነው?

ዳግም ልደት ከክርስትና ዋነኛ ትምህርቶች መካከል አንዱ ነው። የሰው ልጅ ሁለት ልደቶች አሉት። አንደኛው ከስጋ ፈቃድ በሩካቤ ከአባት እና ከእናት የሚያገኘው ስጋዊ ልደት ሲሆን ሁለተኛ ደግሞ ኢየሱስን በማመን እና በመቀበል የሚያገኘው መንፈሳዊ ልደት ነው፣ ‘‘ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤ እነርሱም ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ ከደም ወይም ከሥጋ ፈቃድ ወይም ከወንድ ፈቃድ አልተወለዱም’’ (ዮሐንስ ወንጌል 1፡12-13)። ያለዚህ ልደት ሰው የእግዚአብሔርን መንግስት ሊወርስ አይችልም። ሰው በስጋ ልደቱ የሰው ልጅ እንደሚባል፣ በመንፈስ ልደቱ ደግሞ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል። ስጋ እና ደም የእግዚአብሔርን መንግስት ሊወርሱ አይችሉም፣ የእግዚአብሔር ልጆች ግን የእግዚአብሔርን መንግስት ሊወርሱ ይችላሉ። የመጀመሪያውን ልደት ብቻ ያገኙ፣ የእግዚአብሔር መንፈስ በውስጣቸው የለምና ስጋ እና ደም ብቻ ተብለው ይጠራሉ። እነዚህ ሰዎች የእግዚአብሔርን መንግስት ሊወርሱ አይችሉም፣ ‘‘ሥጋና ደም የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊወርሱ አይችሉም፥ የሚበሰብሰውም የማይበሰብሰውን አይወርስም’’ (1ቆሮንቶስ 15፥50)። የመጀመሪያውን ልደት ብቻ ያገኙ ፍጥረታዊ ሰዎች ይባላሉ። አካላቸው ደግሞ ፍጥረታዊ አካል ይባላል (1ቆሮንቶስ15፡46)። እነዚህ ሰዎች መንፈሳዊ የሆነውን የእግዚአብሔርን ነገር ሊያስተውሉ አይችሉም ‘‘ለፍጥረታዊ ሰው የእግዚአብሔር መንፈስ ነገር ሞኝነት ነውና አይቀበለውም፤ በመንፈስም የሚመረመር ስለ ሆነ ሊያውቀው አይችልም’’ (1ቆሮንቶስ 2፡14)። የመጀመሪያውን ልደት በመወለድ እንዳገኘነው፣ ሁለተኛውንም ልደት በመወለድ እናገኘዋለን። የመጀመሪያውን ስጋዊ ልደት ስጋዊ ከሆኑ ቤተሰቦቻችን እናዳገኘነው ሁለተኛውን ልደት ደግሞ መንፈሳዊ ከሆነው አባታችን በመወለድ የምናገኘው ይሆናል። የመጀመሪያውን ልደት መልካም ሰው በመሆን፣ ምጽዋት በመስጠት፣ በመፀለይ እና በመጾም እናዳላገኘነው፣ ሁለተኛውንም ልደት በእነዚህ መንገዶች አናገኘውም። የቤተሰቦቻችን ልጅ ለመሆን የከፈልነው ክፍያም ሆነ አስተዋጽዎ እንደሌለ ሁሉ፣ የእግዚአብሔር ልጅ ለመሆንም የምናዋጣው መዋጮ የለም። የእግዚአብሔር ልጅ ለመሆን ከእኛ የሚጠበቀው አንድ ነገር ብቻ ነው። ይኸውም፣ በኢየሱስ ማመን እና እርሱን መቀበል፣ ‘‘ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤ እነርሱም ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ ከደም ወይም ከሥጋ ፈቃድ ወይም ከወንድ ፈቃድ አልተወለዱም’’ (ዮሐንስ ወንጌል 1፡12-13)። ‘‘በእምነት በኩል ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጆች ናችሁና’’ (ገላቲያ 3፡26)። የሰው ልጅ ሁለተኛውን ልደት ካላገኘ ወይም ዳግም ካልተወለደ የእግዚአብሔርን መንግስት ሊወርስ አይችልም፣ ‘‘ኢየሱስም መለሰ፥ እንዲህ ሲል፦ እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም። ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው፥ ከመንፈስም የተወለደ መንፈስ ነው’’ (የዮሐንስ ወንጌል 3፡5-6)። ምንም ይስራ ምን፣ ከስጋ የተወለደ ስጋ ነው። ስጋ እና ደም ደግሞ የእግዚአብሔርን መንግስት ሊወርሱ አይችሉም። የተፈጥሯዊ ሰው መልካምነት እስከ አለም ዳርቻ ቢሰማም እንኳ፣ ከስጋ ከተወለደ ስጋ ብቻ ነው። ድርጊቱ ምንም ያህል የተከበረ፣ አንቱ የተባለ እና የተመሰከረለት ቢሆን፣ ተፈጥሮውን አይቀይርለትም። ሃይማኖተኛ ቢሆን፣ አዘውትሮ ረዥም ፀሎት ቢያደርግ (ማቴዎስ 23፡14) በሳምንት ሁለት ጊዜ ቢጾም ሳያጓድል ለእግዚአብሔር አስራት ቢያወጣ (ሉቃስ 18፡12)፣ ቀማኛ፣ ዓመፀኛ አመንዝራ ባይሆን (ሉቃስ 18፡11)፣ በሌላ አባባል በሰፈሩ የተመሰከረለት የሞራል ሰው ቢሆን፣ ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር ያው ስጋዊ፣ ያው ፍጥረታዊ ብቻ ነው። በእግዚአብሔር መንግስትም እድል ፈንታ የለውም። ዳግም ልደት የእግዚአብሔር ምህረት ውጤት እንጂ የእኛ መልካም ስራ ውጤት አይደለም። ‘‘እንደ ምሕረቱ መጠን ለአዲስ ልደት በሚሆነው መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ በመታደስ አዳነን እንጂ፥ እኛ ስላደረግነው በጽድቅ ስለ ነበረው ሥራ አይደለም’’ (ቲቶ 3፡5)። በመልካም ስራ ተፈጥሯችን አይቀየርም። መልካም ስራችን በእግዚአብሔር ፊት ተቀባይነት የሚኖረው ከአዲሱ ተፈጥሯችን ሲመነጭ ብቻ ነው። ዳግም ልደት ሰው በእግዚአብሔር መንፈስ ዳግም ሲፈጠር ወይም ሲለወጥ የሚከናወን መንፈሳዊ ድርጊት ሲሆን ይህም ድርጊት ሰው ከእግዚአብሔር መለኮታዊ ባሕሪይ ተካፋይ እንዲሆን ያስችለዋል፣ ‘‘ስለ ክፉ ምኞት በዓለም ካለው ጥፋት አምልጣችሁ ከመለኮት ባሕርይ ተካፋዮች በተስፋ ቃል እንድትሆኑ፥ በእነዚያ ክብርና በጎነት የተከበረና እጅግ ታላቅ የሆነ ተስፋን ሰጠን’’ (2ጴጥሮስ 1፡4)። ኢየሱስን በማመን እና በመቀበል የተገኘው ልጅነት (ዮሐንስ 1፡12)፣ እግዚአብሔርን አባት ብለን እንድንጠራው እና የእግዚአብሔር ወራሾች እንድንሆን መብትን አስገኝቶልናል፣ ‘‘በእግዚአብሔር መንፈስ የሚመሩ ሁሉ እነዚህ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸውና። አባ አባት ብለን የምንጮኽበትን የልጅነት መንፈስ ተቀበላችሁ እንጂ እንደገና ለፍርሃት የባርነትን መንፈስ አልተቀበላችሁምና። የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን ያ መንፈስ ራሱ ከመንፈሳችን ጋር ይመሰክራል። ልጆች ከሆንን ወራሾች ደግሞ ነን፤ ማለት የእግዚአብሔር ወራሾች ነን፥ አብረንም ደግሞ እንድንከበር አብረን መከራ ብንቀበል ከክርስቶስ ጋር አብረን ወራሾች ነን’’ (ሮሜ 8፡14-17)። በመጀመሪያው ልደት ከቤተሰቦቻችን (ከፊተኛው አዳም)  የወረስነው ተፈጠሮ፣ አዳማዊ ተፈጥሮ ወይም አሮጌው ሰው ይባላል። በዳግም ልደት ኢየሱስን በማመን ከእግዚአብሔር ያገኘነው አዲሱ ተፈጥሮ ደግሞ አዲሱ ሰው ይባላል፣ ‘‘እርስ በርሳችሁ ውሸት አትነጋገሩ፥ አሮጌውን ሰው ከሥራው ጋር ገፋችሁታልና፥ የፈጠረውንም ምሳሌ እንዲመስል እውቀትን ለማግኘት የሚታደሰውን አዲሱን ሰው ለብሳችሁታል’’ (ቆላሲያስ 3፡9-10)። ‘‘ስለዚህ ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፤ አሮጌው ነገር አልፎአል፤ እነሆ፥ ሁሉም አዲስ ሆኖአል’’ (2ቆሮንቶስ 5፡17)። ኢየሱስን አምኖ የተቀበለ ሰው፣ በዳግም ልደት ሌላ አዲስ ተፈጥሮ ስለሚኖረው የሁለት ተፈጥሮዎች ባለቤት ይሆናል ማለት ነው። በዳግም ልደት አዲስ ተፈጥሮን እናገኛለን እንጂ የቀድሞውን አሮጌ ተፈጥሮ አናጣም። አሮጌው ተፈጥሮ እስከሞታችን ከእኛ ጋር ይኖራል። እነዚህ ሁለት ተፈጥሮዎች በባህሪይ ተቃራኒ በመሆናቸው እርስ በእርሳቸው ይቀዋወማሉ፣ ‘‘5፥17 ሥጋ በመንፈስ ላይ መንፈስም በሥጋ ላይ ይመኛልና፥ እነዚህም እርስ በርሳቸው ይቀዋወማሉ …’’ (ገላቲያ 5፡17)። ዳግም የተወለደ ሰው በፊተኛው እና እግዚአብሔርን በማያከብረው ስጋዊ ወይም አሮጌ ተፈጥሮ ቁጥጥር ስር እንዳይሆን በእግዚአብሔር ቃል እውቀት እለት እለት መታደስ ይኖርበታል። የአዲሱ ተፈጥሮ ምግብ የእግዚአብሔር ቃል ነው (ማቴዎስ 4፡4)። የአሮጌውን ተፈጥሮ ፍላጎት እንቢ እያልን የአዲሱን ተፈጥሮ ፈቃድ እየተቀበልን የምንጓዘው ጉዞ የቅድስና ጉዞ ይባላል፣ ‘‘ፊተኛ ኑሮአችሁን እያሰባችሁ እንደሚያታልል ምኞት የሚጠፋውን አሮጌውን ሰው አስወግዱ፥ በአእምሮአችሁም መንፈስ ታደሱ፥ ለእውነትም በሚሆኑ ጽድቅና ቅድስና እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠረውን አዲሱን ሰው ልበሱ። ሰው በአሮጌው ተፈጥሮ እግዚአብሔርን ደስ ማሰኝት ስለማይችል ዳግም ልደት ያስፈልገዋል፣ ‘‘እነሆ፥ በዓመፃ ተፀነስሁ፥ እናቴም በኃጢአት ወለደችኝ (መዝሙር 51፡5)። ‘‘የሰው ልብ ከሁሉ ይልቅ ተንኰለኛ እጅግም ክፉ ነው ማንስ ያውቀዋል? (ኤርሚያስ 17፡9።) ‘‘ስለ ሥጋ ማሰብ በእግዚአብሔር ዘንድ ጥል ነውና፤ ለእግዚአብሔር ሕግ አይገዛምና፥ መገዛትም ተስኖታል፤ በሥጋ ያሉትም እግዚአብሔርን ደስ ሊያሰኙት አይችሉም’’ (ሮሜ 8፡16-17)። ‘‘በእነዚህም ልጆች መካከል እኛ ሁላችን ደግሞ፥ የሥጋችንንና የልቡናችንን ፈቃድ እያደረግን፥ በሥጋችን ምኞት በፊት እንኖር ነበርን እንደ ሌሎቹም ደግሞ ከፍጥረታችን የቁጣ ልጆች ነበርን’’ (ኤፌሶን 2፡3)። ዳግመኛ ልደት ያገኘ ሰው ምልክቶች ምንድን ናቸው? ዳግም የተወለደ ሰው ከሃጢአት ልምምድ ነፃ የወጣ ነው (ሮሜ 6፡14-23)። ዳግም የተወለደ ሰው የእግዚአብሔርን መንፈስ ምሪት ለመቀበል እና ለመታዘዝ መሻት ይኖረዋል (ሮሜ 8፡13-14)። ዳግም የተወለደ ሰው የጽድቅ ሕይወት ይኖረዋል (1ዮሐንስ 2፡29)። ዳግም የተወለደ ሰው ሌሎችን ይወዳል (1ዮሐንስ 4፡7)። ዳግም የተወለደ ሰው ከሃጢአት ሕይወት ይርቃል (1ዮሐንስ 3፡9፤ 5፡18)። ዳግም የተወለደ ሰው አለምን መውደድ ይተዋል (1ዮሐንስ 2፡15-16)። ኢየሱስን በማመን እና በመቀበል ይህን ዳግም ልደት ለማግኘት የሚሹ ከሆነ ይህን ሊንክ በመጫን፣ ኢየሱሰን መቀበል መጽሐፍ ቅዱሳዊ ወይስ መናፍቃዊ የሚለውን ትምህርት እንዲያነቡ በትህትና እንጠይቆታለን። የመዳን ቀን አሁን ነው (2ቆሮንቶስ 6፡2)፣ ለነገ ቀጠሮ አይስጡ። ነገ የእርሶ አይደለምና። መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የሕይወትዎ ጌታ በማድረግ ቀሪው ዘመንዎን ለመኖር ወስነው ከሆነ፣ ይህንን ሊንክ በመጫን ስምዎንና የኢ-ሜይል አድናሻዎን ይላኩልንና፣ ለመንፈሳዊ ሕይወት እድገትዎ የሚቻለንን ሁሉ እገዛ እናደርግሎታለን።

ዳግም ልደት ማለት ምን ማለት ነው? Read More »

የግል ፀሎት ምንድን ነው?

አንተ ግን ስትጸልይ፣ ወደ እልፍኝህ ግባ፣ መዝጊያህንም ዘግተህ በስውር ላለው አባትህ ጸልይ፣ በስውር የሚያይ አባትህም በግልጥ ይከፍልሀል፡፡ ማቴዎስ 6፡6 ኢየሱስ ‹‹በስውር ላለው አባታችሁ ፀልዩ›› እንጂ ‹‹በስውር ስፍራ ወዳለው አባታችሁ ህልምን አልሙ፡፡›› አላለም፡፡ ፀሎት ፈቃድን ማስገዛት ይጠይቃል፡፡ ወደ እልፍኛችን ከገባንና በራችንን ከዘጋን በኋላ ልናደርግ የሚቸግረን ትልቁ ነገር ቢኖር መፀለይ ነው፡፡ አእምሮአችንን ለፀሎታችን ልንጠቀምበት በምንችለው ሁኔታ ማዘጋጀት አስቸጋሪው ሥራችን ይሆናል፡፡ የመጀመሪያ ውጊያችን የሚሆነው ሀሳባችንን ማሰባሰብና ለፀሎት ራሳችንን መግዛት ነው፡፡ በግል የፀሎት ጊዜ ያለው ታላቁ ጦርነት ሀሳባችንን ማሰባሰብና ለፀሎት ያልተዘጋጀውን አዕምሮአችንን ለዚሁ መንፈሳዊ ስራ እንዲነሳሳ ማድረግ ነው፡፡ በፈቃዳችን ላይ ለተመሠረተ እና ለታሰበበት ፀሎት አዕምሮአችንን በዲሲፕሊን መግዛት መማር ይኖርብናል፡፡ ለፀሎት የተለየ ስፍራ ሊኖረን ይገባል፡፡ ያም ሆኖ ግን ወደዚህ ስፍራችን ስንገባ ሀሳባችን መባከን ይጀምራል፣ ‹‹ይህ መሰራት አለበት››፤ ‹‹ያኛውን ደግሞ ዛሬ መጨረስ ይኖርብኛል፡፡›› የሚሉ ሀሳቦች በአዕምሮአችን መመላለስ ይጀምራሉ፡፡ ኢየሱስ ‹‹በራችሁን ዝጉ፡፡›› ነው ያለው፡፡ በፀሎት ወቅት የተረጋጋ የአዕምሮ ሁኔታን ለመፍጠር፣ የአዕምሮአችንን ደጆች ለሚያንኳኩ ስሜቶቻችን ሆን ብለን ደጃችንን በመዝጋት፣ እርሱን ብቻ ማሰብ ይኖርብናል፡፡ እግዚአብሔር በስውር አለ፡፡ ከ ‹‹ስውር ስፍራውም›› ይመለከተናል፡፡ እርሱ የሚመለከተን፣ ሰዎች እኛን ወይም ራሳችን ራሳችንን እንደ ምንመለከተው አይደለም፡፡ እግዚአብሔር እኛን በሚያየን በዚህ ‹‹ስውር ስፍራ›› መኖር መለማመድ ስንጀምር እግዚአብሔርን መጠራጠር አይሆንልንም፡፡ ከማንም እና ከምንም ነገር በላይ ስለ እርሱ እርግጠኞች እንሆናለን፡፡ ወደዚህ ‹‹ስውር ስፍራ›› ስትገባ በእለት ተዕለት ሕይወትህ እግዚአብሔር በእርግጥ ትክክል እንደሆነ ታረጋግጣለህ፡፡ በሁሉም ጉዳዮች ላይ ከእግዚአብሔር ጋር የማውጋት ልማድ ይኑርህ፡፡ የማለዳው ጎህ ሲቀድ የሕይወትህን ደጆች ወለል አድርገህ ከፍተህ እግዚአብሔርን ማስቀደም መማር ካልጀመርክ፣ የቀን ውሎህ ሁሉ በተሳሳተ መስመር ላይ መሆኑን እንዳትዘነጋ፡፡ ነገር ግን የሕይወትህን ደጆች ከፍተህ ‹‹በስውር ላለው አባትህ ፀሎት ካደረስክ››፣ በሕይወትህ የሚያለፉ ማህበራዊ ነገሮችህ ሁሉ የእግዚአብሔር የይሁንታ ማህተም ያረፈባቸው ይሆናሉ፡፡ በግለህ ወደ ፀሎት በገባህ ጊዜ የሚደርስብህን የትኩረት መበታተን ችግር ለመቀነስ፣ ወደ አይምሮህ እየመጡ የሚያስቸግሩህ እና ኋላ ላይ ልትሰራቸው የሚገቡህን ነገሮች የምታሰፍርበት ማስታወሻ ደብተር አዘጋጅ፡፡  

የግል ፀሎት ምንድን ነው? Read More »

የዘላለም ሕይወት፣ የእግዚአብሔር ታላቁ ስጦታ

የዘላለም ሕይወትን የማገኘው እንዴት ነው? የዘላለም ሕይወትን እንዳገኝ የየትኛው ቤተ ክርስቲያን አባል መሆን አለብኝ የሚል ጥያቄ ያስጨንቆታል? የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ከእኔ የሚጠበቀውስ ምን ይሆን በሚል ሃሳብ ተወዛግበው ያውቃሉ? እርሶ ሃጢአተኛ በመሆኖ እና እግዚአብሔር ደግሞ ፍጹም ፃድቅ ስለሆነ የዘላለም ሕይወት ሊደረስበት የማይቻል እና የተወሰኑ ሰዎች ብቻ የሚያገኙት እንደሆነስ አስበው ያውቃሉ? ከእነዚህ ጥያቄዎች አንዱ የሚመለከትዎ ከሆነ ምላሹን እነሆ። የዘላለም ሕይወት የሚለው ሃሳብ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከ38 ጊዜ በላይ ተጠቅሷል። በእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ ባለው አገባብ (አውድ) መሰረት የዘላለም ሕይወት ማለት የሰው ልጅ በሰማያዊ ስፍራ በእግዚአብሔር መንግስት ውስጥ በተድላና በደስታ የሚኖረውን ቁጥር አልባ የሕይወት ዘመን ያመለክታል። የሰው ልጅ በእግዚአብሔር ላይ ካመፀበት ወቅት (ዘፍጥረት 3፡6) ጀምሮ፣ በሰራው ሃጢአት ምክንያት የተፈረደበትን ሞት (ሮሜ 6፡23) እየጠበቀ፣ ሕይወቱ ከስጋው የምትለይበትን ቅንጭብጫቢ እድሜዎች እየቆጠረ፣ በተስፋቢስነት የሚኖር ምስኪን ፍጥረት ነው። ከዚህ ውድቀት በኋላ የሰው ልጅ የሃጢአት ባሪያ ሆነ። ይህንን እውነት ቅዱስ ዮሐንስ እንዲህ በማለት ይገልፀዋል ‘‘ኢየሱስ መለሰ፥ እንዲህ ሲል፦ እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ኃጢአት የሚያደርግ ሁሉ የኃጢአት ባርያ ነው።’’ (ዮሐንስ 8፡34፤ ሮሜ 6፡17-18፤ ሮሜ 6፡20)። የእግዚአብሔር ልጅ በመሆን ከዚህ እስራት የተፈታ ካልሆነ በቀር የሃጢአት ባሪያ የሆነ ሁሉ በእግዚአብሔር ቤት ደርሻ እንደማይኖረው  የእግዚአብሔር ቃል በሚከተለው መንገድ ማስረጃ ይሰጠናል፣ ‘‘ባርያም ለዘላለም በቤት አይኖርም፤ ልጁ ለዘላለም ይኖራል’’ (ዮሐንስ 8፡35)። መጽሐፍ ቅዱስ የሰው ልጅ የሃጢአት ባርያ መሆኑን ብቻ ሳይሆን፣ ለምን የሃጢአት ባሪያ እንደሆነም ይነግረናል። የሃጢአት ደራሲ ዲያብሎስ ነው (1ዮሐንስ 3፡8)። ሃጢአትን ያደረግነው በዚህ እርኩስ ፍጥረት ስር ስለተገዛን እነደሆነ ዮሐንስ በቁጥር 8 ላይ ይነግረናል። በዚህ መሰረት የሰው ልጅ የሃጢአት ባሪያ የሆነው በቅዱስ አምላኩ ትዕዛዝ ላይ አምጾ የዲያብሎስን ውሸት ለማድመጥ በመረጠ ወቅት (ዘፍጥረት 3፡1-8) እንደሆነ እንረዳለን። የዘላለም ሕይወት ማለት ከዚህ ባርነት ነፃ መውጣት ማለት ነው። የዘላለም ሕይወት የሚያገኙት እነማን ናቸው ብሎ መጠየቅ በሌላ አነጋገር ከዚህ እስር እና ባርነት ነፃ የሆኑት እነማን ናቸው ማለት ነው። በዚህ ባርነት ውስጥ ያለ ሰው የሚያፈራው መልካም ነገር ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት አፀያፊ ነው (ሮሜ 8፡8)። የሚያፈሩት ፍሬ፣ የልጅ ሳይሆን የባሪያ ፍሬ ነውና በእግዚአብሔር ፊት ሞገስ ሊኖረው አይችልም። ከባርነት ሳይወጡ፣ በሃይማኖተኝነት በመነሳሳት፣ መልካም ስራ በመስራት፣ እግዚአብሔርን ደስ ለማሰኘት መሞከር ይቻላል። ሙከራው ግን ፍሬ ቢስ ነው። እግዚአብሔር በዚህ ደስ አይሰኝምና። የዘላለም ሕይወት የስራ ጉዳይ ሳይሆን የተፈጥሮ ጉዳይ ነው። የፍሬ ጉዳይ ሳይሆን የዛፍ ጉዳይ ነው። ከእሾህ ዛፍ የበለስ ፍሬ እንደማይቆረጥ ሁሉ ከአጣጥ ቍጥቋጦም የወይን ፍሬ አይለቀምም። ሁለቱንም አንድ የሚያደርጋቸው ነገር ቢኖር፣ ፍሬ ማፍራቸው ነው። የሚያለያያቸው ደግሞ የፍሬው አይነት ነው። በዲያብሎስ እና በሃጢአት ባርነት ስር ያለ ሰውም ሆነ ነፃ የወጣ፣ ሁለቱም ፍሬ ያፈራሉ። ስራ ይሰራሉ። ጥያቄው እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኘው ፍሬ የቱ ነው የሚለው ነው።  በባርነት ስር ሆነው እግዚአብሔር በፍሬያችን ደስ በማሰኘት የዘላለም ሕይወት እናገኛል ስለሚሉ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ግልጽ መልዕክት አለው፣ ‘‘በሥጋ ያሉትም እግዚአብሔርን ደስ ሊያሰኙት አይችሉም’’ (ሮሜ 8፡8)። መጀመሪያ ፍሬው ሳይሆን ግንዱ መቀየር አለበት። ግንዱ ከተቀየረ ፍሬው መልካም ይሆናል። ስለዚህ የዘላልም ሕይወት ከተፈጥሯችን እንጂ ከመልካም ምግባሮቻችን ጋር ምንም ግንኙነት የለውም። የግንድ ለውጥ ያደረገ፣ (የተፈጥሮ ለውጥ ያደረገ) የግንዱ ሕይወት ውጤት የሆነውን ፍሬ ማፍራቱ አይቀርምና። በዚህ ምድር ላይ አፋቸውን ሞልተው ‘‘እግዚአብሔር የለም’’ የሚሉ ነገር ግን በሕይወታቸው በሚያደርጉት ሰናይ ምግባር አለምን ያስደመሙ በርካታ ሰዎች መኖራቸውን ታሪክ ለሚያገላብጥ እና አካባቢውን በትኩረት ለሚቃኝ ሰው እንግዳ ነገር አይደለም። እነዚህ ሰዎች በሚያደርጉት ልግስና፣ ታማኝነት፣ ታታሪነት በርካታ ተከታዮችን ለማፍራት የቻሉ መሆናቸውንም መዘንጋት የለብንም። አንዳንዶቹ ስለያዙት መልካም አላማ መሳካት ሲሉ ራሳቸውን ለሞት አደጋ እንኳ አሳልፈው ሰጥተዋል፣ እየሰጡም ነው። የዘላልም ሕይወት ጉዳይ የተፈጥሮ ጉዳይ ሳይሆን የመልካም ምግባር ጉዳይ ቢሆን ኖሮ እነዚህን ሰዎች በመንግስተ ሰማይ ባገኘናቸው ነበር። በዚህ ምድር ላይ ላበረከቱት መልካም ተጽዕኖ አክብሮት ቢኖረኝም፣ የዘላለም ሕይወት ተካፋዮች ስለመሆናቸው ግን ተስፋ ልንሰጣቸው አልችልም። ስለዚህ ስለዘላለማዊ ሕይወት ተገቢው ጥያቄ – ‘‘ምን ሰርቻለው?’’ ሳይሆን፣ ‘‘ከዚህ የዲያብሎስ እስራት ተፈትቻለው ወይ?’’፣ ‘‘ከሃጢአት ባርነት ነፃ ወጥቻለው ወይ’’፣ ‘‘ባሪያ ሳይሆን ልጅ ሆኛለው ወይ?’’ የሚለው ይሆናል። ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጅ የሚያስፈልገውን አርነት የሚያውቅ አምላክ ነውና በምድር ላይ በነበረ ጊዜ ይህንን የአርነት ስብከት መስበክ ጀመረ። ለዚህ የኢየሱስ ስብከት፣ ትምህርቱን የተቃወሙ አንዳንድ አይሁድ የሰጡትን ምላሽ እንመልከት። ኢየሱስም፣ ‘‘እውነትንም ታውቃላችሁ እውነትም አርነት ያወጣችኋል አላቸው። እነርሱም መልሰው። የአብርሃም ዘር ነን ለአንድም ስንኳ ከቶ ባሪያዎች አልሆንም፤ አንተ፣ አርነት ትወጣላችሁ እንዴት ትላለህ? አሉት። ኢየሱስ መለሰ፥ እንዲህ ሲል፦ እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ኃጢአት የሚያደርግ ሁሉ የኃጢአት ባርያ ነው። ባርያም ለዘላለም በቤት አይኖርም፤ ልጁ ለዘላለም ይኖራል። እንግዲህ ልጁ አርነት ቢያወጣችሁ በእውነት አርነት ትወጣላችሁ። …እናንተ ከአባታችሁ ከዲያብሎስ ናችሁ የአባታችሁንም ምኞት ልታደርጉ ትወዳላችሁ’’ (ዮሐንስ 8፡32-44፣)። የዘላለም ሕይወትን የሚሰጥ ማን ነው? የዘላለም ሕይወት ከእግዚአብሔር የሚሰጠን እና እኛ የምንቀበለው ውድ ስጦታ ነው። የሰው ልጅ በራሱ ማንነት እና ጥረት ሊያገኛት ስላልቻለ፣ እግዚአብሔር እንዲሁ በነፃ፣ ለሚቀበላት ሁሉ ሊሰጣት ወዷል። በዘላለም ሕይወት ውስጥ የእግዚአብሔር ድርሻ መስጠት ሲሆን የእኔ እና የእርሶ ድርሻ ደግሞ በእምነት መቀበል ነው። የዮሐንስ ወንጌል 10፥28 ‘‘እኔም የዘላለም ሕይወትን እሰጣቸዋለሁ፥ ለዘላለምም አይጠፉም፥ ከእጄም ማንም አይነጥቃቸውም።’’ የዮሐንስ ወንጌል 17፥1-2 ‘‘ኢየሱስም ይህን ተናግሮ ወደ ሰማይ ዓይኖቹን አነሣና እንዲህ አለ፦ አባት ሆይ፥ ሰዓቱ ደርሶአል፤ ልጅህ ያከብርህ ዘንድ፥ በሥጋም ሁሉ ላይ ሥልጣን እንደ ሰጠኸው፥ ለሰጠኸው ሁሉ የዘላለምን ሕይወት ይሰጣቸው ዘንድ ልጅህን አክብረው።’’ 1ኛ የዮሐንስ መልእክት 2፥25 ‘‘እርሱም የሰጠን ተስፋ ይህ የዘላለም ሕይወት ነው።’’ 1ኛ የዮሐንስ መልእክት 5፥11 ‘‘እግዚአብሔርም የዘላለምን ሕይወት እንደ ሰጠን ይህም ሕይወት በልጁ እንዳለ ምስክሩ ይህ ነው።’’ ወደ ሮሜ ሰዎች 6፥23 ‘‘የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነውና፤ የእግዚአብሔር የጸጋ ስጦታ ግን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን የዘላለም ሕይወት ነው።’’ የዮሐንስ ወንጌል 5፥39 ‘‘እናንተ በመጻሕፍት የዘላለም ሕይወት እንዳላችሁ ይመስላችኋልና እነርሱን ትመረምራላችሁ፤ እነርሱም ስለ እኔ የሚመሰክሩ ናቸው፤’’ የዘላለም ሕይወት ያላቸው እነማን ናቸው? ከዚህ የሃጢአት ባርነት ነፃ የሚያወጣኝ ማን ነው? ከዲያብሎስ አገዛዝ የሚታደገኝ ማነው? ማነው ይህን አጋንንታዊ አሮጌ ተፈጥሮ ሽሮ የእግዚአብሔር ልጅ የሚያደርገኝ? ማነው የዘላልም ሕይወት የሚሰጠኝ? መልሱ አጭር ነው፣ ኢየሱስ ብቻ። ይህ የኔ አስተያየት አይደለም። የዘላለም ሕይወት የሚለው ቃል ተጠቅሶ በምናገኘው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ሁሉ የዚያ ስጦታ ምክንያት ኢየሱስ እንደሆነ ይናገራል። የዘላለም ሕይወት ያላቸው ከሃጢአት ባርነት ነፃ የወጡ ናቸው። ‘‘አሁን ግን ከኃጢአት አርነት ወጥታችሁ ለእግዚአብሔርም ተገዝታችሁ፥ ልትቀደሱ ፍሬ አላችሁ፤ መጨረሻውም የዘላለም ሕይወት ነው’’ (ወደ ሮሜ ሰዎች 6፥22)። ከዚህ ሞት እና ሃጢአት ባርነት ነፃ ለመውጣት  ነፃ አውጪ ያስፈልጋል (ሮሜ 8፡2)። ያ ነፃ አውጪ ኢየሱስ ነው (ዮሐንስ ወንጌል 8፡36፤ 1ዮሐንስ መልዕክት 3፡8፤ ሉቃስ 4፡17-20)። ከዚህ ባርነት በመልካም ምግባሮቻችን ማምለጥ የምንችል ቢሆን ኖሮ የኢየሱስ ነፃ አውጪነት ባላስፈለገም ነበር። ከዚህ ባርነት ነፃ የሚያወጣን ክርስቶስ እንደሆነ ካመንን የዘላለም ሕይወት የእኛ ናት። የዘላለም ሕይወት ራሱ ኢየሱስ ነው። ‘‘የእግዚአብሔርም ልጅ እንደ መጣ፥ እውነተኛም የሆነውን እናውቅ ዘንድ ልቡናን እንደ ሰጠን እናውቃለን፤ እውነተኛም በሆነው በእርሱ አለን፥ እርሱም ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እርሱ እውነተኛ አምላክና የዘላለም ሕይወት ነው’’ (1ኛ የዮሐንስ መልእክት 5፥20)። የዘላለም ሕይወት የሚገኘው በኢየሱስ ውስጥ ነው፣ ‘‘እግዚአብሔርም የዘላለምን ሕይወት እንደ ሰጠን ይህም ሕይወት በልጁ እንዳለ ምስክሩ ይህ ነው’’ (1ኛ የዮሐንስ መልእክት 5፥11)። ይህን ዘላለማዊ ሕይወት፣ ኢየሱስን ስንቀበል ገንዘባችን (የራሳችን) እናደርጋለን። የዘላለም ሕይወት ያላቸውም ኢየሱስ ያላቸው ብቻ ናቸው። የዘላለም ሕይወት፣ ኢየሱስ በሌለበት የለችምና

የዘላለም ሕይወት፣ የእግዚአብሔር ታላቁ ስጦታ Read More »

የእግዚአብሔር ቃል ፋይዳ ምንድን ነው?

የእውነት ምንጭ እኔ ወይም ሌላ ሰው አይደለም፡፡ የእውነት ምንጭ የመንግስትና የግል ዜና ማሰራጫዎች ወይም ሚዲያዎችም አይደሉም። የእውነት ምንጭ የታዋቂ ሰዎች አስተያየቶች አልያም የሳይንቲስቶች ላብራቶርም አይደለም። የእውነት ምንጭ ስሜት ሕዋሶቻችንም አይደሉም። እውነት ከራሱ ከእግዚአብሔር ብቻ ትፈልቃለች፡፡ እናም እውነት ብዬ የያዝኳቸውን እውቀቶች ሁሉ ወይም ደርሼባቸዋለው የምላቸውን ‘‘እውነቶች’’ ሁሉ በእግዚአብሔር ቃል ፈትሼ በእርግጥም እውነት ስለመሆናቸው ማረጋገጥ ይኖርብኛል። ሀ. የእግዚአብሔር ቃል የታመነ ነው፡፡ መዝ. 119፡89 አቤቱ ቃልህ በሰማይ ለዘላለም ይኖራል፡፡ (1ጴጥ. 1፡25 በተጨማሪ ይመልከቱ) ማቴ. 24፡35 ሰማይና ምድር ያልፋሉ ቃሌ ግን አያልፍም፡፡ ዮሐ. 14፡6 እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ …፡፡ ዮሐ. 17፡17 በእውነትህ ቀድሳቸው ቃልህ እውነት ነው፡፡ ኤፌ. 4፡21   …እውነትም በኢየሱስ እንዳለ በእርሱ ተምራችኋል፤… 1ዮሐ. 5፡6 (አ.መ.ት.) የሚመሰክረው መንፈስ ነው፤ መንፈስም እውነት ነውና ፡፡ ለ. የእግዚአብሔር ቃል፣ በየዕለቱ እንደ ምመገበው ምግብ አስፈላጊዬ ሊሆን ይገባል፡፡ ዘዳ. 6፡5-9 …እኔም ዛሬ አንተን የማዘውን ይህን ቃል በልብህ ያዝ፡፡ ለልጆችህም አስተምረው፣ በቤትም ስትቀመጥ፣ በመንገድም ስትሄድ፣ ስትተኛም፣ ስትነሳም ተጫወተው፡፡ በእጅህም ምልክት አድርገህ እሰረው፤ በአይኖችህም መካከል እንደ ክታብ ይሁንልህ፡፡ በቤትህም መቃኖች በደጃፍህም በሮች ላይ ጻፈው፡፡ ኢዮብ 23፡12 ከአፉ ከወጣው ትእዛዝ አልራቅሁም፣ የአንደበቱን ቃል ከእለት እንጀራዬ አብልጬ ይዣለሁ፡፡ (አ.መ.ት.) መዝ. 119፡16 በትዕዛዝህ ደስ ይለኛል፤ ቃልህንም አልረሳም፡፡ መዝ. 119፡103 ቃልህ ለጉሮሮዬ ጣፋጭ ነው ከማርና ከወለላ ይልቅ ለአፌ ጣፈጠኝ፡፡ ማቴ. 4፡4 እርሱም መልሶ ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም ተብሎ ተጽፏል አለው፡፡ ሐ. ለማደግ የእግዚአብሔርን ቃል ማስታወስና ማሰላሰል ያስፈልገኛል፡፡ መዝ. 1፤1-3 ምስጉን ነው በክፉዎች ምክር ያልሄደ በኃጢአተኞችም መንገድ ያልቆመ፣ በዋዘኞችም ወንበር ያልተቀመጠ፡፡ ነገር ግን በእግዚአብሔር ሕግ ደስ ይለዋል፣ ሕጉንም በቀንና በሌሊት ያስባል፡፡ መዝ. 119፡11 አንተን እንዳልበድል ቃልህን በልቤ ሰወረኩ፡፡ መዝ. 119፡97 አቤቱ ሕግህን እንደ ምን እጅግ ወደድሁት፤ ቀኑን ሁሉ እርሱ ትዝታዬ ነው፡፡ መዝ. 145፡5 (አ.መ.ት.) ስለ ግርማህ ውበትና ስለ ክብርህ ይናገራሉ፤ እኔም ስለ ድንቅ ሥራህ አሰላስላለሁ፡፡ ቆላ. 3፡16 የእግዚአብሔር ቃል በሙላት ይኑርባችሁ . . . የእግዚአብሔርን ቃል ለማስታወስ የሚረዱ ሁኔታዎች፡ ወደመስሪያ ቤትዎ ሲሄዱ አንድ ጥቅስ ለማስታወስ እየሞከሩ ይሂዱ፤ ካርድ ላይ ጥቅስ በመፃፍ በግልፅ የሚታይ ቦታ ላይ ይለጥፉ፣ ያንን ጥቅስ ቀኑን በሙሉ ያሰላስሉ፡፡ መ. የእግዚአብሔር ቃል በሕይወቴ ውስጥ እንደሚያበራ መብራት ነው፡፡ የእግዚአብሔር ቃል የልቤን ምስጢሮች ይገልጣል፤ የእግዚአብሔር ቃል እግዚአብሔር እኔን እንደ ሚያየኝ ራሴን እንዳይ ይረዳኛል፡፡ መዝ. 119፡105 ሕግህ ለእግሬ መብራት ለመንገዴም ብርኃን ነው፡፡ መዝ. 119፡130 የቃልህ ፍቺ ያበራል፣ ህፃናትንም አስተዋዮች ያደርጋል ሮሜ. 10፡17 እንግዲያስ እምነት ከመስማት ነው መስማትም በእግዚአብሔር ቃል ነው፡፡ ዕብ. 4፡12-13 የእግዚአብሔር ቃል ሕያው ነውና፣ የሚሰራም ሁለትም አፍ ካለው ሰይፍ ሁሉ ይልቅ የተሳለ ነው፣ ነፍስንና መንፈስንም ጅማትንና ቅልጥምንም እስኪለይ ድረስ ይወጋል፤ የልብንም ስሜትና አሳብ ይመረምራል፤ ሠ. እግዚአብሔር ራሱ የቃሉን መገለጥ ይሰጣል፡፡ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃሎችን ፍቼ ለመረዳት ቢያቅተኝም እንኳ፣ ለእርሱ ታማኝና ግልፅ በሆንኩ መጠን በሚያስፈልገኝ ደረጃ ቃሉን እንደሚገልፅልኝ ልታመነው እችላለው፡፡ ዘዳ. 29፡29 ምስጢሩ ለአምላካችን ለእግዚአብሔር ነው የተገለጠው ግን የዚህን ሕግ ቃሎች ሁሉ እናደርግ ዘንድ ለእኛ ለዘላለምም ለልጆቻችን ነው፡፡ ሉቃስ 24፡45 በዚያም ጊዜም መጽሕፍትን ያስተውሉ ዘንድ አእምሮአቸውን ከፈተላቸው፡፡ 1ቆሮ. 2፡12-14 እኛ ግን ከእግዚአብሔር እንዲያው የተሰጠንን እናውቅ ዘንድ ከእግዚአብሔር የሆነውን መንፈስ እንጂ የአለምን መንፈስ አልተቀበልንም መንፈሳዊውን ነገር ከመንፈሳዊው ነገር ጋር አስተያይተን መንፈስ በሚያስተምረን ቃል ይህን ደግሞ እንናገራለን እንጂ የሰው ጥበብ በሚያስተምረን ቃል አይደለም፡፡ ለፍጥረታዊ ሰው የእግዚአብሔር መንፈስ ነገር ሞኝነት ነውና አይቀበለውም፤ በመንፈስም የሚመረመር ስለሆነ ሊያውቀው አይችልም፡፡ 2ጴጥ. 3፡15-16 እንዲህም የተወደደው ወንድማችን ጳውሎስ ደግሞ እንደ ተሰጠው ጥበብ መጠን ጻፈላችሁ፣ በመልዕክቱም ሁሉ ደግሞ እንደ ነገረ ስለዚህ ነገር ተናገረ፡፡ በእነዚያ ዘንድ ለማስተዋል የሚያስቸግር ነገር አለ፣ …  

የእግዚአብሔር ቃል ፋይዳ ምንድን ነው? Read More »

የሰይጣን ዋነኛ የጦር ስልት ምንድን ነው?

የሰይጣን ዋነኛ የጦር ስልት የእግዚአብሔር ባህሪ አጣሞ፣ ቀይሮ እና አወናብዶ በማስቀመጥ ለሚሰሙት ሁሉ መስበክ ነው። ያለው ትልቁ የውጊያ መሳሪያ ማታለል፣ የተዘራውን እውነተኛ የእግዚአብሔር ቃል መንጠቅ፣ መዋሸት እና የመሳሰሉትን የማወናበድ ስራዎች መስራት ነው። ውሸትን እውነት አስመስሎ ማቅረብ የተዋጣለት ብልሃቱ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ስለሰይጣን የጦር ስልቶች የሚለውን የተወሰኑ አብነቶች እንመልከት፡- የማቴዎስ ወንጌል 4፥15 በሰሙት ጊዜም ሰይጣን ወዲያው መጥቶ በልባቸው የተዘራውን ቃል ይወስዳል። 2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 2፥11 በሰይጣን እንዳንታለል፤ የእርሱን አሳብ አንስተውምና። 2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 11፥14 ይህም ድንቅ አይደለም፤ ሰይጣን ራሱ የብርሃንን መልአክ እንዲመስል ራሱን ይለውጣልና። 2ኛ ወደ ተሰሎንቄ ሰዎች 2፥9-10 ይድኑ ዘንድ የእውነትን ፍቅር ስላልተቀበሉ ለሚጠፉ፥ የእርሱ መምጣት በተአምራት ሁሉና በምልክቶች በሐሰተኞች ድንቆችም በዓመፅም መታለል ሁሉ እንደ ሰይጣን አሠራር ነው። የዮሐንስ ራዕይ 3፥9 እነሆ፥ አይሁድ ሳይሆኑ። አይሁድ ነን ከሚሉ ነገር ግን ከሚዋሹ ከሰይጣን ማኅበር አንዳንዶችን እሰጥሃለሁ እነሆ፥ መጥተው በእግሮችህ ፊት ይሰግዱ ዘንድ እኔም እንደ ወደድሁህ ያውቁ ዘንድ አደርጋቸዋለሁ። የዮሐንስ ራእይ 12፥9 ዓለሙንም ሁሉ የሚያስተው፥ ዲያብሎስና ሰይጣን የሚባለው ታላቁ ዘንዶ እርሱም የቀደመው እባብ ተጣለ፤ ወደ ምድር ተጣለ መላእክቱም ከእርሱ ጋር ተጣሉ። የሰይጣንን ውሸት ለመቃወም አቅም የምናገኘው የእግዚአብሔርን ባሕሪ በአግባቡ ያወቅን እንደሆነ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እግዚአብሔር ባሕሪ የገለጠውን እውነታ ማወቅ በጣም ጠቃሚ ነገር ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ በኩል የገለጠውን የእግዚአብሔርን ባሕሪ በውል መገንዘብ በእርሱ ላይ መታመናችን ምን ያህል ምክንያታዊና ተገቢ እንደሆነ ለማወቅ ይረዳናል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ የተገለጠውን የእግዚአብሔርን ባሕሪ በአመክኗዊ ሚዛን ላይ ስናስቀምጥ፣ እርሱን አለማመን ኢ-ምክንያታዊ፣ በእርሱ ላይ መታመን ደግሞ ምክንያታዊ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ እርሱን ለመቃወም ወይም ታቅበን ለመኖር ምንም አይነት አሳማኝ ምክንያት የለንም፡፡ የወደቀው/የተበላሸው/አሮጌው የሰው ተፈጥሮ ሁል ጊዜ በእግዚአብሔር ላይ ያምፃል፡፡ እግዚአብሔርን የማናምንበት ዋና ምክንያት እርሱ እንደኛ አይነት ባሕሪ ያለው ስለሚመስለን ነው፡፡ እርሱ እንደ እኛ አይነት ባሕሪ ቢኖረው እርሱን አለማመናችን ምክንያታዊ ይሆን ነበር፡፡ ሆኑም ግን ያ እውነት አይደለም። ዘዳግም 32፡3-4 የእግዚአብሔርን ስም እጠራለሁና፤ ለአምላካችን ታላቅነትን ስጡ። እርሱ አምላክ ነው፤ ሥራውም ፍጹም ነው፤ መንገዱም ሁሉ የቀና ነው፤ የታመነ አምላክ፣ ክፋትም የሌለበት፣ እርሱ እውነተኛና ቅን ነው። ኢዮብ 34፡10 ስለዚህ አእምሮ ያላችሁ ሰዎች ስሙኝ ክፋትን ያደርግ ዘንድ ከእግዚያብሔር በደልንም ይሰራ ዘንድ ሁሉን ከሚችል አምላክ ይራቅ፡፡ ዕብራዊያን 6፡18 (አ.መ.ት.) እግዚአብሔር ከቶ ሊዋሽ አይችልም፤… 1ዮሐንስ መልዕክት 4፡16 … እግዚያብሔር ፍቅር ነው፤… ሚኪያስ 3፡6 እኔ እግዚአብሔር አልለወጥም፤ … የሰይጣን የጦር ታክቲክ የሰይጣን ዋና የጦር ታክቲክ፣ ሰዎች በእግዚአብሔር ባሕሪ ላይ ያላቸውን እምነት በመሸርሸር እግዚአብሔር ሊታመን የማይችል አምላክ እንደሆነ ማሳመን ነው፡፡ ለአብነት- በዘፍጥረት 3፡1-5 ሰይጣን፣ እግዚአብሔር ከአዳምና ሔዋን አንዳች የሚጠቅም ነገር እንደ ደበቀባቸው፣ የእነርሱንም መልካም ነገር የማይሻ እንደሆነ በእጅ አዙር በመንገር፣ በውስጣቸው ጥርጥርን በመዝራት እግዚአብሔርን ውሸታም ለማድረግ ያደረገውን ሴራ ያስተዉሉዋል፡፡ ዘፍጥረት 3፡1-5 እባብም እግዚአብሔር አምላክ ከፈጠረው ከምድር አውሬ ሁሉ ይልቅ ተንኮለኛ ነበረ፡፡ ሴቲቱንም፡- በውኑ እግዚአብሔር ከገነት ዛፍ ሁሉ እንዳትበሉ አዟልን? አላት፡፡ ሴቲቱም ለእባቡ አለችው፡- በገነት ካለው ከዛፍ ፍሬ እንበላለን ነገር ግን በገነት መካከል ካለው ከዛፉ ፍሬ እግዚአብሔር አለ እንዳትሞቱ ከእርሱ አትብሉ አትንኩትም፡፡ እባብም ለሴቲቱ አላት ሞትን አትሞቱም ከእርስዋ በበላችሁ ቀን ዓይኖቻችሁ እንዲከፈቱ እንደ እግዚአብሔርም መልካሙን እና ክፉውን የምታውቁ እንድትሆኑ እግዚአብሔር ስለሚያውቅ ነው እንጂ፡፡ አዳምና ሔዋን በተፈጠሩ ጊዜ እንደሌሎቹ የእግዚአብሔር ፍጥረታት ሁሉ፣ እንከን የለሽ (perfect) ነበሩ፡፡ ሙሉ እና ምንም ሳይጎድላቸው ፍፁም የረኩ (complete and totally satisfied) ነበሩ፡፡ ያደርጉት የነበረው ነገር ሁሉ ከእግዚአብሔር ባሕሪ አንፃር የተጣጣመና የተዋሀደም ነበር፡፡ በዚህ ወቅት ሞት አልነበረም፡፡ ሮሜ 5፡12 ስለዚህ ምክንያት ኃጢአት በአንድ ሰው ወደ አለም ገባ፣ በኃጢአትም ሞት፣ እንደዚሁም ሁሉ ኃጢአትን ስላደረጉ ሞት ለሰው ሁሉ ደረሰ … 1ቆሮንቶስ 15፡21-22 ሞት በሰው በኩል ስለ መጣ … ሁሉ በአዳም እንደ ሚሞቱ … አዳምና ሔዋን በእግዚአብሔር ላይ ያላቸውን መደገፍ ወደጎን በመተው፣ በራሳቸው ላይ በመተማመን፣ ሰይጣን በእግዚብሔር ባሕሪ ላይ የተናገረውን የውሸት ቃል አደመጡ፡፡ ከእግዚአብሔር ውጪም በራሳቸው አይን እርካታን ለማግኘት ተራመዱ፡፡ በእግዚአብሔር ላይ ካላቸው መታመን ለመውጣት መወሰናቸውን የሚያመላክቱ ሦስት ማሳያዎች አሉ፡፡ (1) የሰው ማስተዋል/human understanding (ለጥበብ መልካም እንደሆነ አዩ)፣ (2) የሰውነት ፍላጎት/appetites of the body (ለመብላት ያማረ እንደሆነ አዩ)፣ እና (3) ሐብት/possessions (ለዓይን እንደ ሚያስጎመጅ አዩ)፡፡ ዛሬም የዘወትር ፈተናዎቻችን ከነዚህ በአንዱ ውስጥ ይወድቃሉ፡፡ ‹‹በራስ የመተማመን ዝንባሌ›› የሰው ልጆች ችግር ‹‹ሥር›› እንዲሁም እኛና አለሙ ሁሉ በእግዚአብሔር ላይ ለምናደርገው አመፅ ዋነኛ አነሳሽ ምክንያት መሆኑን መገንዘብ በጣም አስፈላጊ ነገር ነው፡፡ ዘፍጥረት 3፡6 ሴቲቱም ዛፉ ለመብላት ያማረ እንደሆነ ለዓይንም እንደሚያስጎመጅ ለጥበብም መልካም እንደሆነ አየች ከፍሬውም ወሰደችና በላች ለባልዋም ደግሞ ሰጠችው እርሱም ከእርስዋ ጋር በላ፡፡ ልክ አዳም እንደ ተፈተነ ኢየሱስም በተመሳሳይ ሦስት አቅጣጫዎች ላይ ተፈተነ፡፡ ነገር ግን ኢየሱስ ሰይጣን ያቀረበለትን በራስ የመታመን ግብዣ ወደጎን በመተው ራሱን በእግዚአብሔር ጥበቃ ስር አሳልፎ በመስጠት ለመኖር ወሰነ፡፡ የማቴዎስ ወንጌል 4፡1-10 ከዚያ ወዲያ ኢየሱስ ከዲያብሎስ ይፈተን ዘንድ መንፈስ ወደ ምድረ በዳ ወሰደው፥ አርባ ቀንና አርባ ሌሊትም ከጦመ በኋላ ተራበ። ፈታኝም ቀርቦ። የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ፥ እነዚህ ድንጋዮች እንጀራ እንዲሆኑ በል አለው። እርሱም መልሶ፦ ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም ተብሎ ተጽፎአል አለው። ከዚህ በኋላ ዲያብሎስ ወደ ቅድስት ከተማ ወሰደውና እርሱን በመቅደስ ጫፍ ላይ አቁሞ። መላእክቱን ስለ አንተ ያዝልሃል እግርህንም በድንጋይ ከቶ እንዳትሰናከል በእጃቸው ያነሡሃል ተብሎ ተጽፎአልና የእግዚአብሔር ልጅስ ከሆንህ፥ ወደ ታች ራስህን ወርውር አለው። ኢየሱስም፦ ጌታን አምላክህን አትፈታተነው ተብሎ ደግሞ ተጽፎአል አለው። ደግሞ ዲያብሎስ እጅግ ረጅም ወደ ሆነ ተራራ ወሰደው፥ የዓለምንም መንግሥታት ሁሉ ክብራቸውንም አሳይቶ። ወድቀህ ብትሰግድልኝ ይህን ሁሉ እሰጥሃለሁ አለው። ያን ጊዜ ኢየሱስ፦ ሂድ፥ አንተ ሰይጣን ለጌታህ ለአምላክህ ስገድ እርሱንም ብቻ አምልክ ተብሎ ተጽፎአልና አለው። ኢየሱስ በአባቱ ቃል ላይ በመደገፍ የሰይጣንን የፈተና ጥበብ እንዳዋረደ፣ እኛም መንፈስ ቅዱስ በገለጠው እግዚአብሔር ቃል እውነትነት ላይ እና በማይለወጠው የእግዚአብሔር ባሕሪይ ላይ በመደገፍ የሰይጣንን የውሸት ታክቲክ እንቃወም።  

የሰይጣን ዋነኛ የጦር ስልት ምንድን ነው? Read More »

እግዚአብሔር የማያምኑ ሰዎችን/የኢ-አማኒያንን ፀሎት ሰምቶ ይመልስ ይሆን?

ዮሐንስ 9፡31 ‘‘እግዚአብሔርን የሚፈራ ፈቃዱንም የሚያደርግ ቢኖር ያንን እግዚአብሔር ይሰማዋል እንጂ ኃጢአተኞችን እንዳይሰማ እናውቃለን’’ ይላል። ከዚህ በተጨማሪ፣ ‘‘እግዚአብሔር፣ ኢ-አማኒው ኢየሱስን ለመቀበል ሲል የሚያደርገውን የንስሃ ፀሎት ብቻ ነው ሰምቶ የሚመልሰው’’ የሚል የተለመድ አባባል አለ። በእነዚህ ምክንያቶች አንዳንዶች እግዚአብሔር፣ የማያምኑ ሰዎችን ፀሎት ሰምቶ እንደማይመልስ ያምናሉ። የዮሐንስ 9፡31 የአውድ ትርጉም ግን እግዚአብሔር በማያምን ሰው እጅ ተአምራትን አያደርግም የሚል ነው። በ 1ዮሐንስ 5፡14-15 መሰረት፣ እግዚአብሔር ፀሎትን የሚመልሰው በፈቃዱ ላይ በመንተራስ እንደሆነ እናነባለን። በሌላ አነጋገር፣ ፈቃዱ ከሆነ ይመልሳል፤ ካልሆነ አይመልስም ማለት ነው። ይህ መርህ በማያምኑት ላይ ሳይቀር የሚሰራ ነው። የማያምን ሰው እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ መሰረት ቢፀልይ እግዚአብሔር በፈቃዱ መሰረት ይመልስለታል ማለት ነው። አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች፣ እግዚአብሔር የማያምኑ ሰዎችን ፀሎት ሰምቶ ሲመልስ ያስነብቡናል። በዛ በሚሉት በእነዚህ ታሪኮች ውስጥ ኢ-አማኒያኑ ሲፀልዩ እናነባለን። በአንድ ወይም በሁለቱ ታሪኮች ውስጥ ደግሞ እግዚአብሔር የኢ-አማኒያኑን የልብ ጩኸት  ሲመልስ እናያለን። በእርግጥ በታሪኮቹ ውስጥ ጩኸቶቹ ወደ እግዚአብሔር ስለመቅረባቸው እርግጠኛ የሚያደርገን ነገር አናገኝም። በሌሎቹ ታሪኮች ውስጥ ደግሞ የኢ-አማኒያኑ ፀሎት ከንስሃ ጋር የተቀላቀለ መሆኑን እናነባለን። በተቀሩት ታሪኮች ውስጥ ደግሞ ኢ-አማኒያኑ ለምድራዊ በረከት ፀልየው ሲቀበሉ እናነባል። በእነዚህ ታሪኮች ውስጥ ሁሉ እግዚአብሔር ከርህራሄው ወይም ከኢ-አማኒያኑ ጥልቅ ፍላጎት የተነሳ ወይም ከአስደናቂ መታመናቸው በመነሳት ፀሎታቸውን ሲመልስ እናነባለን።  ከዚህ በታች በኢ-አማኒያኑ ዙሪያ የሚያጠነጥኑ የተወሰኑ ታሪኮች ቀርበዋል፡- የነነዌ ሰዎች እግዚአብሔር ሊያመጣባቸው ካለው ቅጣት ለመዳን ፀለዩ (ዮናስ 3፡5-10)። እግዚአብሔር ፀሎታቸውን ሰማ፤ ሊያመጣባቸው ከነበረው ቅጣትም እጁን ከለከለ። አጋር ስል ልጇ እስማኤል፣ ወደ እግዚአብሔርን ፀለየች (ዘፍጥረት 21፡14-19)። እግዚአብሔርም የአጋርን ፀሎት ሰማ፤ እስማኤልን በብዙ ባረከው። አክዓብ፣ ነቢዩ ኤሊያስ ባመጣለት ትንቢት ምክንያት ጾመ፣ አዘነ። እግዚአብሔርም ሊመጣበት ያለውን ጥፋት በእርሱ ዘመን አላመጣበትም (1ነገስት 21፡17-29 በተለይ ከቁጥር 27-29 ይመልከቱ)። ከጢሮስ እና ሲዶና አገር የሆነች አንዲት ሴት ኢየሱስ ልጇን ከርኩስ መንፈስ ቁራኛ እንዲፈውስላት ጠየቀች (ማርቆስ 7፡24-30)። ኢየሱስም ርኩስ መንፈሱን ከልጅቷ እንዲወጣ አዘዘው። ፈወሳትም። በሐዋሪያት ስራ 10 ላይ ታሪኩን የምናነበው የሮም መቶ አለቃ ቆርኔሌዎስ ደግመሞ መልካም ሰው እንደነበረ እና ፀሎቱ በእግዚአብሔር እንደተሰማለት እናያለን። ይህ ሰው አዘውትሮ ወደ እግዚአብሔር ይፀልይ ነበር (ሐዋሪያት ስራ 10፡2)። እግዚአብሔርም ለዚህ ሰው ሐዋሪያው ጴጥሮስን ላከለት። እግዚአብሔር ላመኑም ይሁን ላላመኑ ሁሉ የሚሰራ በኤርሚያስ 29፡13 ላይ እንደተዘገበው አይነት ተስፋ ሰጥቷል፣ ‘‘እናንተ ትሹኛላችሁ፥ በፍጹም ልባችሁም ከሻችሁኝ ታገኙኛላችሁ’’። እንደ ቆርኔሌዎስ (ሐዋሪያት ስራ 10፡1-6) ያሉ ሰዎች የዚህ ተስፋ ተጠቃሚ ናቸው። ያም ሆኖ፣ የፀሎቱ ሃሳቦቹ በሚገኙባቸው አውዶች መሰረት፣ ክርስቲያኖችን (አማኞችን) ብቻ የሚመለከቱ በርካታ ተስፋዎች እንዳሉ ልንዘነጋ አይገባም። ለአብነት፣ ኢየሱስን እንደ ቤዛቸው በመቀበል የዳኑ ክርስቲያኖች፣ በሚያስፈልጋቸው ጊዜ ሁሉ ከእግዚአብሔር እርዳታን ለማግኘት ወደ ፀጋው ዙፋን በድፍረት የመቅረብ መብት ተሰጥቷቸዋል (ዕብራውያን 4፡14-16)። አንደ ፈቃዱ አንዳች ብንለምንም ፀሎታችን እንደሚሰማና የጠየቅነውን እንደምናገኝ ቃል ተገብቶልናል (1ዮሐንስ 5፡14-15)። ከእነዚህ በተጨማሪ፣ ክርስቲያኖችን በሚመለከት ስለፀሎታቸው የተሰጣቸው በርካታ ተስፋዎች አሉ (ማቴዎስ 21፡22፤ ዮሐንስ 14፡13፣ 15፡7)። እግዚአብሔር የኢ-አማኒያንን ፀሎት የማይሰማበት ሁኔታ እንዳለ ሁሉ፣ ከቸርነቱና ከምሕረቱ የተነሳ በሕይወታቸው ጣልቃ በመግባት ለፀሎታቸው ምላሽ የሚሰጥበ ወቅቶችም እንዳሉ ሊዘነጋ አይገባም።  

እግዚአብሔር የማያምኑ ሰዎችን/የኢ-አማኒያንን ፀሎት ሰምቶ ይመልስ ይሆን? Read More »

እግዚአብሔር ሁሉን አዋቂ መሆኑ ፀሎትን አላስፈላጊ አያደርገውም ወይ?

እግዚአብሔር የማያውቀውን ነገር ልንነግረው አንችልም፡፡ ስንፀልይ የምንናደርገው ነገር ቢኖር እርሱ አስቀድሞ የሚያውቀውን ነገር በቃላችን መደርደር ነው፡፡ ይህ ጉዳይ እንድንፀልይ የሚያበረታታን እንጂ ፀሎትን አላስፈላጊ የሚያደርገው አይደለም፡፡ ስለ እኛ እና ስላለንበት ሁኔታ በሚገባ ከሚያውቅ ሰው ጋር ያው የሚያውቀውን ጉዳይ ስናወራ እረፍት ይሰማናል፡፡ የእግዚአብሔር ምላሽ በሰጠነው መረጃ ላይ ሳይሆን እርሱ ስለእኛ ሁኔታ በሚያውቀው ፍፁም እውቀት ላይ የተመሰረተ መሆኑ ተደላድለን እንድንኖር ያደርገናል፡፡ በእኛ ላይ ተፅዕኖ ሊያሳድሩ የሚችሉ ያለፉ፣ የአሁን እና የወደፊት ሁኔታዎቻችንን ጠንቅቆ ያውቃልና፡፡ ኢየሱስ በማቴ. 6፡8 ላይ እንዳለው አባታችን ሁሉን ያውቃል፡፡ እርሱ ሃሳቦቻችንንና ፍላጎቶቻችንን ያውቃል፡፡ መንገዶቻችንን ጠንቅቆ ይረዳቸዋል (መዝ. 139፡3)፡፡ የልባችንን ጭንቀትና ስቃይ ይረዳል፤ የማያቋርጥ ተስፋ መቁረጥ የሚያደርስብንን የስሜት ጉዳትም ያውቃል፤ በውስጣችን ያሉ ሁለቱ ተቃራኒ ተፈጥሮዎች (አዳማዊው እና አዲሱ ሰው) በነፍሳችን ላይ የሚያደርጉት ጦርነትም ከእርሱ የተሸሸገ አይደለም፡፡ እንዲህ ከሆነ፣ ካሉብን ችግሮችና ተቃውሞዎች እንዴት እና በየትኛው ሰዓት መውጣት እንዳለብን ለማወቅ እግዚአብሔር ላይ የመታመን አስፈላጊነት አይታያችሁም?  ሕይወታችን ሊታነፅ የሚችልበትን የተሻለ መንገድ እኛ ለእግዚአብሔር ልንጠቁም የምንችል ይመስላችኋል? በፍፁም፣ እግዚአብሔርን ምንም ነገር ልናስተምረው አንችልም፡፡ እርሱ ብቻውን እኛን ወደ ክብር የሚያደርሰውን ጎዳና ያውቃል፡፡ ካሉት መንገዶች ሁሉ፣ ለማንነታችንና በእኛ ውስጥ እርሱ ላስቀመጠው ነገር የሚስማማውን ልዩ መንገድ መርጦልናል፡፡   እግዚአብሔርን እውቀት ልናስገበየው አንችልም፡፡ ልናፈቅረውና ልንደላደልበት ግን እንችላለን፡፡ እርሱ ከኛ የሚጠይቀው ይህንን አንድ ነገር ነው፡፡ እግዚአብሔር ከመነሻው የመጨረሻውን ያውቃል፤ ስለዚህ በመካከል በሚፈጠሩ ነገሮች ላይ ሁሉ በእርሱ ልንታመን እንችላለን፡፡ በእግዚአብሔር ላይ ያለኝን መታመን በጨመርኩ መጠን እርሱ ለእኔ ባለው ፍቅር እርግጠኛ እየሆንኩ እሄዳለሁ፡፡ አንዳንዴ ነገሮች ከዚህ አስተሳሰብ ተቃራኒ ቢመስሉም፣ እግዚአብሔር ለእኔ ያለው ሃሳብ በጎና የሚጠቅመኝ ነው፡፡ መዝ. 34፡15 የእግዚአብሔር አይኖች ወደ ፃድቃን፣ ጆሮቹም ወደ ጩኸታቸው ናቸውና፡፡ መዝ. 37፡4-5 በእግዚአብሔር ደስ ይበልህ፤ የልብህንም መሻት ይሰጥሀል፡፡ መንገድህን ለእግዚአብሔር አደራ ስጥ፤ በእርሱም ታመን እርሱም ያደርግልሀል፡፡ መዝ. 86፡5 አቤቱ አንተ መሓሪና ይቅር ባይ ነህና፣ ምህረትህም ለሚጠሩህ ሁሉ ብዙ ነውና፡፡ መዝ. 145፡18-19 እግዚአብሔር ለሚጠሩት ሁሉ፣ በእውነት ለሚጠሩት ሁሉ ቅርብ ነው፡፡ ለሚፈሩት ምኞቶቻቸውን ያደርጋል፣ ልመናቸውንም ይሰማል፣ ያድናቸዋልም፡፡ ኤር. 10፡23 አቤቱ የሰው መንገድ ከራሱ እንዳይደለ አውቃለሁ አካሄዱንም ለማቅናት ከሚራመድ ሰው አይደለም፡፡ 1ዮሐ. 5፡14-15 በእርሱ ዘንድ ያለን ድፍረት ይህ ነው፤ እንደ ፈቃዱ አንዳች ብንለምን ይሰማናል፡፡ የምንለምነውንም ሁሉ እንዲሰማልን ብናውቅ፣ ከእርሱ የለመነውን ልመና እንደተቀበልን እናውቃለን፡፡ እኔ ግን ዘወትር ከአንተ ጋር ነኝ፥ ቀኝ እጄንም ያዝኸኝ። እኔ ግን ዘወትር ከአንተ ጋር ነኝ፥ ቀኝ እጄንም ያዝኸኝ። በሰማይ ያለኝ ምንድር ነው? በምድርስ ውስጥ ከአንተ ዘንድ ምን እሻለሁ? የልቤ አምላክ ሆይ፥ ልቤና ሥጋዬ አለቀ እግዚአብሔር ግን ለዘላለም እድል ፈንታዬ ነው። (መዝሙር 73፡23-26)  

እግዚአብሔር ሁሉን አዋቂ መሆኑ ፀሎትን አላስፈላጊ አያደርገውም ወይ? Read More »

እውን እግዚአብሔር አለ?

በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች እግዚአብሔር እንዳለ ያምናሉ፡፡ ጥቂቶች ማስረጃ አለን ሲሉ ይደመጣሉ፡፡ እግዚአብሔር እንዳለ በማስረጃ አረጋግጠህ ታውቃለህ? በውኑ የእርሱ መኖር በሳይንስ ሊረጋገጥ ይችላልን? አንተን ራስህንና አለማትን አንድ ድንቅ አዕምሮ እንዲፈጠራቸው በእርግጠኝነት ታውቃልህ? ወይስ ይህ ጉዳይ በእምነት ብቻ ሊቀበሉት የተገባ ነው ብለህ ትደመድማለህ? እስቲ ይህን ጥያቄ እንዳስ፡፡ ሰዎች በእግዚአብሔር መኖር ጥያቄ ላይ መከራከር ከጀመሩ ብዙ ሺ አመታት ነጉደዋል፡፡ ብዙዎቹ ታዲያ የእግዚአብሔርን መኖር በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ማረጋገጥ ይቻላል ሲሉ ይደመጣሉ፡፡ ይህ የሰው ልጆች ትልቅ ጥያቄ፣ በረቂቅ ፍልስፍና (abstract philosophy) እና በ ሜታፊዚካል (metaphysical) አስተምህሮቶች ውስጥ ምላሽ ያገኛል የሚል ሰፊ ግምት ይሰጣሉ፡፡ ከፊሎቹ ደግሞ፣ ማለትም የአግኖስቲክስ /agnostics/ ትምህርት አራማጆች፣ እግዚአብሔር መኖሩን እርግጠኛ የሚያደርገን ነገር ፈፅሞ የለም ይላሉ፡፡ የተቀሩት ደግሞ “የእግዚአብሔር አለ” መለኮተ ትምህርተ ከልጅነታቸው እንደ ተረት የሰሙ ናቸው፤ አልያም ጥያቄው የማይሞቃቸውና የማይበርዳቸው ለዘብተኞች ናቸው፡፡ መጽሐፍ ቅዱሳችን በእግዚአብሔር መኖር ላይ የሚጠራጠሩትንና በድፍረት ‹የለም› ለሚሉትን አንድ ስም ይሰጣቸዋል – ሞኞች፡፡ “ሰነፍ በልቡ፡- አምላክ የለም ይላል” መዝ. 14፡1፡፡ ይህ ጥቅስ በ መዝ. 53፡1 ላይም ተደግሞ እናገኘዋለን፡፡ ይህ ፅሁፍ እግዚአብሔር ለምን እነዚህን ሰዎች “ሞኞች” እንደሚላቸው ይመረምራል፡፡ በጽሑፉ አቅራቢ እምነት ከዚህ በታች ስለ እግዚአብሔር መኖር በሳይንስ አንፃር በአስረጂነት የተቀመጡ ታሪኮች፣ አንዳንዶችን ይህንን ጥያቄውን ዳግመኛ እንዳያነሱት ያደርጋቸዋል፤ እየወላወሉ ያሉ ሌሎችን ደግሞ ያፀናል፡፡ በመጀመሪያ አንዳንድ ባህላዊ ማስራጃዎችን እንዳስሳለን፡፡ በመቀጠልም ከሳይንስ ማህደር የሥነ ሕይወት (biology)፣ የጠፈር ሳይንስ (astronomy)፣ ኬሚስትሪንና ሒሳብ ማህደሮችን እናገላብጣለን፡፡ ስነፍጥረት ወይስ የዝግመታዊ ለውጥ ፍልስፍና (evolution) የእግዚአብሔር መኖርና አለመኖር ጥያቄ ሲነሳ አብሮ ሊነሳ የሚገባ አንድ ተዛማጅ ሀሳብ አለ፡፡ ይህም ሀሳብ -ሕይወት በምድር ላይ የተገኘው ድንገት፣ በእድል ነገር ግን በዝግመታዊ የለውጥ ስርዐት ነው ወይስ በአንድ ልዩና ታላቅ አካል ፈጣሪነት? በሌላ አነጋገር በምድራችን ላይ የሚገኙ ፍጥረታት፣ የዝግመታዊ ለውጥ አርበኞች (evolutionist) እንደሚሉት የሚሊዮን አመታት የዝግመታዊ ለውጥ ገፀ በረከቶች ወይስ “ይሁን” የሚለው የእግዚአብሔር ስልጣናዊ ቃል ፍሬዎች? አንድ በዚህ በዝግመታዊ የለውጥ ሳይንስ ላይ ለ ሁለት አመት ተኩል ጠለቅ ያለ ጥናት ያደረገ ሰው ዴቪድ ሲ. ፓክ (David C. pack) በጥናቱ መባቻ ላይ እንዲህ አለ፡፡ “የዝግመታዊ ለውጥ ሳይንስን መቀበል እግዚአብሔር አለ በሎ ከማመን የበለጠ እምነት ይጠይቃል” ሲል በዝግመታዊ ሳይንስ ንድፈ ሃሳቦች ውስጥ ያሉትን ሕፀፆች ወይም ግጭቶች (fallacies) ለማስቀመጥ ሞክሯል፡፡ ምናልባት ብዙዎች ይህ ሳይንስ እንደ 1 + 1 = 2 ስሌት ከህፀፅ የፀዳ፣ የተረጋገጠና የፀና የመላምት መሰረት ያለው አድርገው ያስቡት ይሆናል፡፡ ሆኖም የዝግመታዊ ለውጥ ሳይንስ እንደሌሎች ንድፈ ሃሳቦች ሁሉ ከራሱና ከሌሎች የሳይንስ ሕጎች ጋር የሚጣረስበት ነጥቦች ጥቂቶች አይደሉም፡፡ ይህንን ‘ሳይንስ’ ነው እንግዲህ ብዙዎች ስለ ፍጥረት ለሚነሱ ጥያቄዎች እንደ ማጣቀሻ ዶሲያቸው የሚቆጥሩት፡፡ በነገራችን ላይ፣ በኔ እምነት በሳይንስ አንፃር፣ ሊረጋገጡ (proof) የማይቹሉ እሳቤዎች ሁሉ ከእምነት የተለየ ጎራ ሊሰጣቸው አይችልም፡፡ የዝግመታዊ ለውጥ ሳይንስ የፍጥረት መጀመሪያን እሳቤ በሳይንስ ላቦራቶር ውስጥ ቀምሮ ሊያስጨብጠን፣ ሊያስዳስሰን ወይም ሊያስነካን አይችልም፡፡ ሳይንሱ እሳቤዎቹን ከመላምት ይጀምርና ከዛ በመቀጠል ለሆኑት የዝግመታዊ ለውጥ ክስተቶች ማስረጃ ሊያስቀምጥ ይሞክራል፡፡ ያም ሆነ ይህ መነሻው መላምት ነውና የአንድ እምነት ክፍል ከመሆን ዘሎ ሙሉ በሙሉ የሳይንስ አካል ነው ለማለት አልደፍርም፡፡ ስለ ዝግመታዊ ሳይንስ ተጣርሶዎች በሌላ ጊዜ እንደምመለስበት በመግለፅ ወደተነሳው ሃሳብ እመለሳለሁ፡፡ እምነትና ማስረጃ በአንድ ክርስቲያን ሕይወት ውስጥ እምነት ትልቅ ትርጉም ያለው መለኮታዊ ስጦታ ነው፡፡ እግዚአብሔርን ደስ ሊያሰኝ እርሱንም ሊያውቅ የሚወድ ቢኖር የእግዚአብሔር መንፈስ አንድ ምክር ይለግሰዋል፡- “ያለ እምነት (እግዚአብሔርን) ደስ ማሰኘት አይቻልም፤ ወደ እግዚአብሔር የሚደርስ እግዚአብሔር እንዳለ ለሚፈልጉትም ዋጋ እንዲሰጥ ያምን ዘንድ ያስፈልገዋልና” ዕብ. 11፡6፡፡ እምነት ለክርስቲያን ትልቅ ጉዳይ ነው፡፡ እንደውም ያለ እምነት እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት ከቶ አይሞከርም፡፡ የትኛው አምላክ ሐዋርያው ጳዉሎስ በ 1ቆሮ. 8፡5-7 እንዲህ ሲል ጽፏል፡- “መቼም ብዙ አማልክትና ብዙ ጌቶች አሉ፤ ነገር ግን በሰማይ ሆነ በምድርም ሆነ አማልክት የተባሉ ምንም ቢኖሩ ለእኛስ ነገር ሁሉ ከእርሱ የሆነ እኛም ለእርሱ የሆንን አንድ አምላክ አብ አለን… ነገር ግን ይህ እውቀት በሁሉ ዘንድ አይገኝም”፡፡ ሃይማኖቶች ፍጥረታዊ ከሆኑቱ – ከድንጋይ፣ ከእንጨትና ከሌሎች ግዑዛን የሆነ ብዙ አማልክት ለራሳቸው አበጅተዋል፡፡ ስርዐትና ወግ ቀርጸውላቸውም ያመልኳቸዋል፡፡ ያስገርምዎ ከሆነ፣ ጥንታዊያን ግሪኮች 30,000 የሚያህሉ የፈጠሯቸውን ‹ፈጣሪዎች› ያገልግሉ እንደነበረና በዚህ ዘመን የሚኖሩ ሂንዱዎች ደግሞ ከ 5 ሚሉዮን በላይ ለሚሆኑ አማልክት እንደሚያጥኑ ልንገርዎ፡፡ ሆኖም የመጽሐፍ ቅዱሱ እግዚአብሔር እነዚህ ሰዎች አማልክቶቻቸውን የሰሩበትን ቁስ (malerial) የፈጠረ መሆኑ የሚገልጥ እውቀት፣ ጳዉሎስ እንዳለው “በሁሉ ዘንድ አይገኝም”፡፡ የመጽሐፍ ቅዱሱ እግዚአብሔር በዚ የምሪት መጽሐፍ ለመተዳደር ፈቃዳቸውን ላሳዩ ሁሉ የሰላም፣ የደስታ እና የተትረፈረፈ ሕይወት መንገድን ጠቁሞበታል፡፡ ይህን በመጠቀም የሰው ልጅ ከተጋረጠበት የግርግር፣ የወከባና የጥርጥር ክፋቶች መዳን ይችላል፡፡ ሆኖም ብዙ ባወቀ ቁጥር ብዙ መጠየቅ ባሕሪው የሆነ አዕምሮ ይህንን ጥያቄ ሊያነሳ ይችላል፡- ‹መፅሐፍ ቅዱስ ሊረጋገጥ የሚችል የስልጣን መፅሐፍ ነውን?› መልሴ ‹መጠርጠሩስ› ነው፡፡ ሆኖም የዚህን ምላሽ ለማግኘት የሚረዳዎትን ውይይት ሌላ ጊዜ እንደምመለስበት ቃል ገብተቼ አሁን ወደተነሳሁበት ሃሳብ ልመለስ፡፡ ሳይንስ ምን ይለናል? አንተ አማኝ ሆይ ሳይንስ እግዚአብሔር አለ ብዬ ያመንኩበትን እምነቴን በማስረጃ ውድቅ disprove ያደርጋል ብለህ አትስጋ፡፡ በእርግጥ ብዙ የዘርፉ ጠበብት ሳይንስ የእግዚአብሔር መኖርን ማረጋገጥም ሆነ መካድ የሚችልበት መሠረት የለውም ይላሉ፡፡ ይህንን ሊያደርግ እንኳ ቢሞክር የዘመናችን ታዋቂ የእግር ኳስ ተጨዋች ተጠቅሞበት ስለማያውቀው አንድ መገልገያ ተአምራዊ ጠቀሜታ በማስታወቂያ አማካኝነት ሞግቶና አሳምኖ የምርቱ ተጠቃሚዎች ሊያደርገን ከሚያደርገው ደካማ የማስታወቂያ ጥበብ ተለያይቶ ሊታይ አይችልም፡፡ ሆኖም በዚሁ የሳይንስ መለኪያም ቢሆን እንኳ እግዚአብሔር የራሱን መኖር ከማሳወቅ አልከለከለም፡፡ እንደውም መማር ላልለገመ አዕምሮ ከዚሁ ጎራ የእዚአብሔርን መኖር ጮኸው የሚናገሩ ብዙ ማስረጃዎችን መቁጠር ይቻላል፡፡ አስቀድሜ ከላይ እንደገለጥኩት እግዚአብሔር በእምነታችን ደስ ይሰኛል፡፡ ስላልታየውና ስላልተዳሰሰው፣ ስላልተሰማውና ስላልተሸተተው ነገር ሁሉ ማስረጃ ስንፈልግ መኖር አለብን የሚል አስተምህሮ የለኝም፡፡ ይህን የማድረግ ጊዜና አቅሙም የለምና፡፡ ከዚህ በተጨማሪ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚል “ከእውቀት ከፍለን እናውቃለን” 1ቆሮ. 13፡9፣ ስለዚህ ተፈጥሯዊ ለሆኑት የስሜት ሕዋሶቻችን ማስረጃን ስንመግብ መዋልና ማደር የለብንም፡፡ ይህን ብናደርግ ነገም ከነገም ወዲያ ይህ ጥያቄ ማብቂያ ሳይኖረው ይቀጥላል፡፡ ይህ ማለት ግን ማስረጃ መፈለግን መጽሐፍ ቅዱሳችን ፈፅሞ ይቃወመዋል ማለት እንዳልሆነ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ እምነታችን ጭፍን እንደሆነ ለሚመስላቸው ሁሉ ሊረዳቸው ቢችል፣ ራሳቸው ከሚጠቅሱት ማህደራቸው እግዚአብሔር መኖሩን ለመግለፅ ከበቂ በላይ ማስረጃዎችን እነሆ ብንል ክፋቱ አልታይህ ቢለኝ እንጂ፡፡ ምን ያህል ከምለው ጉዳይ ጋር እንደሚዛመድ ባላውቅም በአንድ የታሪክ አጋጣሚ ኢየሱስ ክርስቶስ ከመረጣቸው ሐዋሪያት መካከል ትንሳኤውን ለመቀበል የከበደው ሰው ተገኘ፤ ስሙም ቶማስ ይባላል፡፡ ባጭሩ ይህ ሰው ማስረጃ ፈለገ፡፡ “የችንካሩን ምልክት በእጆቹ ካላየሁ፤ ጣቴንም በችንከሩ ምልክት ካላገባሁ፣ እጁንም በጎኑ ካላገባሁ አላምንም” አለ (ዮሐ. 20፡25)፡፡ ኢየሱስ ደግሞ ከስምንት ቀን በኃላ ቶማስ በነበረበት ወቅት ራሱን ገለጠ፡፡ ቶማስንም እንዲህ አለው፡- “ጣትህን ወደዚህ አምጣና እጆቼን እይ፤ እጅህንም አምጣና በጎኔ አግባው፤ ያመንህ እንጂ ያላመንህ አትሁን አለው” ዮሐ. 20፡27፡፡ እዚህ ላይ ኢየሱስ የቶማስን የማስረጃ ጥያቄ ሲመልስ እንመለከታለን፡፡ ሆኖም ይህን ማስረጃ ሳይጠይቁ የሚያምኑ ብፁዓን መሆናቸውንም ሳይነግረው አላለፈም (ዮሐ. 20፡29)፡፡ ኢየሱስ ማስረጃ መስጠቱን አልከለከለም፣ ቢሆንም አላሞገሰም፡፡ ምክንያት ቢሉ እርሱን ደስ የሚያሰኘው እምነት ነውና (ዕብ. 11፡6)፡፡ ጳዉሎስ በ (1ተሰ. 5፡21) ላይ ሁሉን ስለመፈተን ክርስቲያኖችን ሲመክር እናያለን፡፡ የመጀመሪያው የቴርሞዳይናሚክስ ሕግ (The First Law of Thermodynamics) የመጀመሪያው የቴርሞዳይናሚክስ ሕግ እንዲህ ይላል “ማተርና ሐይል አይፈጠሩም አይጠፉም (Matter & energy can be neither created nor destroyed)፡፡ በዚህ መርህ መሠረት በማተር ወይንም ሀይል ላይ ለውጥን ለማምጣት የሚችል አንዳች ተፈጥሯዊ ሂደት የለም፣ ሊኖርም አይችልም፡፡ ይህ

እውን እግዚአብሔር አለ? Read More »

ኢየሱስን መቀበል – መጽሐፍ ቅዱሳዊ ወይስ መናፍቃዊ?

እስቲ ለአፍታ በቡድ ማሰብ ትተን በግላችን፣ ለግላችን እናስብ። ሰከን ባለ ስሜት መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረንን ቃል እንመርምር። ለማሸነፍ ወይም ለመሸነፍ ሳይሆን ለማወቅ ቃሉን እንመርምር። ‘‘የትኛው ቡድን እንዲህ ያምናል?፣ የትኛውስ እንዲህ አያምንም?’’ የሚለውን ውጤት አልባ ክርክር ወደጎን ትተን ‘‘መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃ ያለው እውነት፣ የትኛው ነው?’’ በሚል መንፈስ ርዕሰ ጉዳዩን እንመርምር። ለመሆኑ ኢየሱስን መቀበል መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነው ወይ? መቀበል የሚለው ቃል – ይሁንልኝ፣ አሜን፣ እስማማለው፣ ይህንኑ አረጋግጣለው፣ የራሴ አድርጌዋለሁ፣ እወስዳለሁ፣ ወዘተ የሚሉ ትርጉሞች አሉት። እነዚህን ትርጉሞች ከሚከተሉት የእግዚአብሔር ቃል ላይ እንፈልግ፡- ማቴዎስ 10፡14 ከማይቀበላችሁም ቃላችሁንም ከማይሰሙ ሁሉ፥ ከዚያ ቤት ወይም ከዚያች ከተማ ስትወጡ የእግራችሁን ትቢያ አራግፉ። ማቴዎስ 10፡41 ነቢይን በነቢይ ስም የሚቀበል የነቢይን ዋጋ ይወስዳል፥ ጻድቅንም በጻድቅ ስም የሚቀበል የጻድቁን ዋጋ ይወስዳል። ማርቆስ 6፡11 ከማይቀበሉአችሁና ከማይሰሙአችሁ ስፍራ ሁሉ፥ ከዚያ ወጥታችሁ ምስክር ይሆንባቸው ዘንድ ከእግራችሁ በታች ያለውን ትቢያ አራግፉ። እውነት እላችኋለሁ፥ ከዚያች ከተማ ይልቅ ለሰዶምና ለገሞራ በፍርድ ቀን ይቀልላቸዋል አላቸው። ሉቃስ 9፡5 ማናቸውም የማይቀበሉአችሁ ቢሆኑ፥ ከዚያ ከተማ ወጥታችሁ ምስክር እንዲሆንባቸው ከእግራችሁ ትቢያ አራግፉ። ዮሐንስ 3፡11 እውነት እውነት እልሃለሁ፥ የምናውቀውን እንናገራለን ያየነውንም እንመሰክራለን፥ ምስክራችንንም አትቀበሉትም። ዮሐንስ 3፡32 ያየውንና የሰማውንም ይህን ይመሰክራል፥ ምስክሩንም የሚቀበለው የለም። ዮሐንስ 3፡33 ምስክሩን የተቀበለ እግዚአብሔር እውነተኛ እንደ ሆነ አተመ። ከላይ በቀረቡት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ውስጥ፣ ‘መቀበል’ ማለት ምን ማለት እንደሆነ መጠነኛ ግንዛቤ ከማግኘታችን በተጨማሪ ቃሉ ለመጽሐፍ ቅዱስ እንግዳ እንዳልሆነ የተረዳን ይመስለኛል። በመቀጠል ኢየሱስን መቀበል መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሆን አለመሆኑን ከመመርመራችን አስቀድሞ፣ መጽሐፍ ቅዱስ – የእግዚአብሔርን ቃል (መልዕክት) ስለ መቀበል እና መንፈስ ቅዱስን ስለ መቀበል የሚናገረውን በቅደም ተከተል እንመልከት፡- የእግዚአብሔርን ቃል መቀበል የሐዋርያት ሥራ 2፡41 ቃሉንም የተቀበሉ ተጠመቁ፥ በዚያም ቀን ሦስት ሺህ የሚያህል ነፍስ ተጨመሩ፤ የሐዋርያት ሥራ 8፡14 በኢየሩሳሌምም የነበሩት ሐዋርያት የሰማርያ ሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል እንደተቀበሉ ሰምተው ጴጥሮስንና ዮሐንስን ሰደዱላቸው። ዮሐንስ 17፡8 የሰጠኸኝን ቃል ሰጥቻቸዋለሁና፤ እነርሱም ተቀበሉት፥ ከአንተም ዘንድ እንደ ወጣሁ በእውነት አወቁ፥ አንተም እንደ ላክኸኝ አመኑ። ዮሐንስ 12፡48 የሚጥለኝ ቃሌንም የማይቀበለው እርሱ የሚፈርድበት አለው፤ እኔ የተናገርሁት ቃል እርሱ በመጨረሻው ቀን ይፈርድበታል። የሐዋርያት ሥራ 11፡1 ሐዋርያትና በይሁዳም የነበሩት ወንድሞች አሕዛብ ደግሞ የእግዚአብሔርን ቃል እንደ ተቀበሉ ሰሙ። የሐዋርያት ሥራ 17፡11 እነዚህም በተሰሎንቄ ከሚኖሩት ይልቅ ልበ ሰፊዎች ነበሩና። ነገሩ እንደዚሁ ይሆንን? ብለው ዕለት ዕለት መጻሕፍትን እየመረመሩ ቃሉን በሙሉ ፈቃድ ተቀበሉ። 1ቆሮንቶስ 15፡1 ወንድሞች ሆይ፥ የሰበክሁላችሁን ደግሞም የተቀበላችሁትን በእርሱም ደግሞ የቆማችሁበትን በእርሱም ደግሞ የምትድኑበትን ወንጌል አሳስባችኋለሁ፤ 2ቆሮንቶስ 11፡4 የሚመጣውም ያልሰበክነውን ሌላ ኢየሱስ ቢሰብክ፥ ወይም ያላገኛችሁትን ልዩ መንፈስ ወይም ያልተቀበላችሁትን ልዩ ወንጌል ብታገኙ፥ በመልካም ትታገሡታላችሁ። ገላቲያ 1፡9 አስቀድመን እንዳልን እንዲሁ አሁን ሁለተኛ እላለሁ፥ ከተቀበላችሁት የተለየውን ማንም ቢሰብክላችሁ የተረገመ ይሁን። 1ተሰሎንቄ 1፡6 ደግሞ እናንተ ቃሉን በብዙ መከራ ከመንፈስ ቅዱስ ደስታ ጋር ተቀብላችሁ፥ እኛንና ጌታን የምትመስሉ ሆናችሁ፤ 1ተሰሎንቄ 2፡13 ስለዚህም የመልእክትን ቃል እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ከእኛ በተቀበላችሁ ጊዜ፥ በእውነት እንዳለ በእናንተ በምታምኑ ደግሞ እንደሚሠራ እንደ እግዚአብሔር ቃል እንጂ እንደ ሰው ቃል አድርጋችሁ ስላልተቀበላችሁት፥ እኛ ደግሞ እግዚአብሔርን ሳናቋርጥ እናመሰግናለን። ያዕቆብ 1፡21 ስለዚህ ርኵሰትን ሁሉ የክፋትንም ትርፍ አስወግዳችሁ፥ ነፍሳችሁን ማዳን የሚችለውን በውስጣችሁም የተተከለውን ቃል በየዋህነት ተቀበሉ። የሐዋርያት ሥራ 22፡18 እርሱም፦ ፍጠን ከኢየሩሳሌምም ቶሎ ውጣ፥ ስለ እኔ የምትመሰክረውን አይቀበሉህምና ሲለኝ አየሁት። 2ዮሐንስ 1፡10 ማንም ወደ እናንተ ቢመጣ ይህንም ትምህርት ባያመጣ በቤታችሁ አትቀበሉት ሰላምም አትበሉት፤ መንፈስ ቅዱስን መቀበል ዮሐንስ 7፡39 ይህን ግን በእርሱ የሚያምኑ ሊቀበሉት ስላላቸው ስለ መንፈስ ተናገረ፤ ኢየሱስ ገና ስላልከበረ መንፈስ ገና አልወረደም ነበርና። ዮሐንስ 14፡17 እርሱም ዓለም የማያየውና የማያውቀው ስለ ሆነ ሊቀበለው የማይቻለው የእውነት መንፈስ ነው፤ ነገር ግን ከእናንተ ዘንድ ስለሚኖር በውሥጣችሁም ስለሚሆን እናንተ ታውቃላችሁ። የሐዋርያት ሥራ 8፡15 እነርሱም በወረዱ ጊዜ መንፈስ ቅዱስን ይቀበሉ ዘንድ ጸለዩላቸው፤ የሐዋርያት ሥራ 8፡17 በዚያን ጊዜ እጃቸውን ጫኑባቸው መንፈስ ቅዱስንም ተቀበሉ። የሐዋርያት ሥራ 8፡19 እጄን የምጭንበት ሁሉ መንፈስ ቅዱስን ይቀበል ዘንድ ለእኔ ደግሞ ይህን ሥልጣን ስጡኝ አለ። የሐዋርያት ሥራ 10፡47 በዚያን ጊዜ ጴጥሮስ መልሶ፦ እነዚህ እንደ እኛ ደግሞ መንፈስ ቅዱስን የተቀበሉ እንዳይጠመቁ ውኃን ይከለክላቸው ዘንድ የሚችል ማን ነው? አለ። የሐዋርያት ሥራ 19፡2 አንዳንድ ደቀ መዛሙርትንም አገኘ። ባመናችሁ ጊዜ መንፈስ ቅዱስን ተቀበላችሁን? አላቸው። እርሱም፦ አልተቀበልንም መንፈስ ቅዱስ እንዳለ ስንኳ አልሰማንም አሉት። ሮሜ 8፡15 አባ አባት ብለን የምንጮኽበትን የልጅነት መንፈስ ተቀበላችሁ እንጂ እንደገና ለፍርሃት የባርነትን መንፈስ አልተቀበላችሁምና። 1ቆሮንቶስ 2፡12 እኛ ግን ከእግዚአብሔር እንዲያው የተሰጠንን እናውቅ ዘንድ ከእግዚአብሔር የሆነውን መንፈስ እንጂ የዓለምን መንፈስ አልተቀበልንም። 1ቆሮንቶስ 2፡14 ለፍጥረታዊ ሰው የእግዚአብሔር መንፈስ ነገር ሞኝነት ነውና አይቀበለውም፤ በመንፈስም የሚመረመር ስለ ሆነ ሊያውቀው አይችልም። ገላቲያ 3፡14 የመንፈስን ተስፋ በእምነት እንድንቀበል፥ የአብርሃም በረከት ወደ አሕዛብ በኢየሱስ ክርስቶስ ይደርስላቸው ዘንድ። 1ዮሐንስ 2፡27 እናንተስ ከእርሱ የተቀበላችሁት ቅባት በእናንተ ይኖራል፥ ማንም ሊያስተምራችሁ አያስፈልጋችሁም፤ ነገር ግን የእርሱ ቅባት ስለ ሁሉ እንደሚያስተምራችሁ፥ እውነተኛም እንደ ሆነ ውሸትም እንዳልሆነ፥ እናንተንም እንዳስተማራችሁ፥ በእርሱ ኑሩ። የሐዋርያት ሥራ 2፡38 ጴጥሮስም፦ ንስሐ ግቡ፥ ኃጢአታችሁም ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፤ የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ። የእግዚአብሔርን ቃል ወይም መልዕክት መቀበል እንዲሁም መንፈስ ቅዱስን መቀበል መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነታ እንደሆነ በበርካታ ማጣቀሻዎች ለማረጋገጥ የቻልን ይመስለኛል። መንፈስ ቅዱስ፣ ከስላሴ አንዱ መሆኑን እና አምላክነት የባሕሪዩ እንደሆነ በስላሴ ትምህረት ለሚያምኑ ሁሉ እንግዳ ሃሳብ አይደለም። ይህን አምላክ እያንዳንዳችን መቀበል እንዳለብን በማያወላዳ መልኩ ከጥቅሶቹ መገንዘብ ከቻልን፣ እግዚአብሔር ወልድን፣ ማለትም ኢየሱስን መቀበል እንዲሁ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሊሆን እንደሚችል ከወዲሁ ልንገምት እንችል ይሆናል። ሆኖም ግን ግምታችንን ለጊዜው ወደጎን እናድርግና፣ እውነታውን ከቅዱሱ መጽሐፍ እንመርምር፡- ኢየሱስን መቀበል ቆላስያስ 2፡6 እንግዲህ ጌታን ክርስቶስ ኢየሱስን እንደ ተቀበላችሁት በእርሱ ተመላለሱ። ዮሐንስ 1፡11-12 የእርሱ ወደ ሆነው መጣ፥ የገዛ ወገኖቹም አልተቀበሉትም። ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤ ማቴዎስ 10፡40 እናንተን የሚቀበል እኔን ይቀበላል፥ እኔንም የሚቀበል የላከኝን ይቀበላል። ማርቆስ 9፡37 እንደዚህ ካሉ ሕፃናት አንዱን በስሜ የሚቀበል ሁሉ እኔን ይቀበላል፤ የሚቀበለኝም ሁሉ የላከኝን እንጂ እኔን አይቀበልም አላቸው። ዮሐንስ 5፡43 እኔ በአባቴ ስም መጥቻለሁ አልተቀበላችሁኝምም፤ ሌላው በራሱ ስም ቢመጣ እርሱን ትቀበሉታላችሁ። ዮሐንስ 13፡20 እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ማናቸውን የምልከውን የሚቀበል እኔን ይቀበላል፥ እኔንም የሚቀበል የላከኝን ይቀበላል። ከላይ በቀረቡት ማስረጃዎች መሰረት ኢየሱስን መቀበል፣ መናፍቃዊ ሃሳብ ሳይሆን መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሆኑን የተገነዘብን ይመስለኛል። ‘‘እናም ኢየሱስን ተቀብያለሁ ወይ?’’ ‘‘መንፈስ ቅዱስንስ ተቀብያለሁ ወይ?’’ ‘‘እውነተኛ ወንጌል ተቀብያለሁ ወይ?’’ ብሎ ራስን መጠየቅ ተገቢ ከመሆኑ በላይ ራሳችንን ልንጠይቅ ከሚገቡን ጥያቄዎች መካከል ዋነኛዎቹ ናቸው። ክቡሩን አምላክ፣ መድሃኔዓለም ክርስቶስን ያልተቀበልን ማንን ልንቀበል ነው? ይህን የእግዚአብሔር ልጅ ያልተቀበሉት አይሁድ (ዮሐንስ 1፡11-12) ከእግዚአብሔር ፍርድ ስር ከሆኑ፣ ልጁን ያልተቀበልን እኛ ከዚህ ፍርድ እንዴት ልናመልጥ እንችላለን? የተቀበሉቱ ግን፣ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚል የእግዚአብሔር ልጆች እንዲሆኑ ስልጣን ተሰጧቸዋል። የእግዚአብሔር ልጆች ከሆንን ደግሞ የመንግስቱ ወራሾች ነን (ሮሜ 8፡17)። እናም፣ ፍርድን ከመቀበል ኢየሱስን ተቀብለን በእርሱ እንመላለስ (ቆላሲያስ 2፡6)። የአውሬውን ቁጥር ከመቀበል (ራዕይ 14፡9-10፤ ራዕይ 14፡ 11፤ ራዕይ 20፡4) ኢየሱስን ተቀብለን የእግዚአብሔር ልጆች እንሁን (ዮሐንስ 1፡11-12)። መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የሕይወትዎ ጌታ በማድረግ ቀሪው ዘመንዎን ለመኖር ወስነው ከሆነ፣ ይህንን ሊንክ በመጫን ስምዎንና የኢ-ሜይል አድናሻዎን ይላኩልንና፣ ለመንፈሳዊ ሕይወት እድገትዎ የሚቻለንን ሁሉ እገዛ እናደርግሎታለን።  

ኢየሱስን መቀበል – መጽሐፍ ቅዱሳዊ ወይስ መናፍቃዊ? Read More »

አስቀድሞ መወሰን ማለት ምን ማለት ነው? አስቀድሞ የመወሰን ሃሳብ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነው?

ሮሜ 8፡29-31 የሚከተለውን ይላል፣ ‘‘ልጁ በብዙ ወንድሞች መካከል በኵር ይሆን ዘንድ፥ አስቀድሞ ያወቃቸው የልጁን መልክ እንዲመስሉ አስቀድሞ ደግሞ ወስኖአልና፤ አስቀድሞም የወሰናቸውን እነዚህን ደግሞ ጠራቸው፤ የጠራቸውንም እነዚህን ደግሞ አጸደቃቸው፤ ያጸደቃቸውንም እነዚህን ደግሞ አከበራቸው። እንግዲህ ስለዚህ ነገር ምን እንላለን? እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ ማን ይቃወመናል?’’ ኤፌሶን 1፡5 እና 11 ደግሞ የሚከተለውን ያስነብበናል፣ ‘‘በበጎ ፈቃዱ እንደ ወደደ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ሥራ ለእርሱ ልጆች ልንሆን አስቀድሞ ወሰነን። … እንደ ፈቃዱ ምክር ሁሉን የሚሠራ እንደ እርሱ አሳብ፥ አስቀድመን የተወሰንን በክርስቶስ ደግሞ ርስትን ተቀበልን።’’ በርካታ ሰዎች ስለአስቀድሞ መወሰን አሉታዊ አስተያየት አላቸው። መጽሐፍ ቅዱሳዊ ፍቺው ካልሆነ በቀር አስቀድሞ መወሰን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሃሳብ መሆኑ ብዙ አከራካሪ አይደለም። አስቀድሞ መወሰን የሚለው ቃል proorizo ከሚለው የግሪክ ቃል የተወሰደ ሲሆን የቁም ትርጉሙም ‘ቀደም ብሎ መወሰን’ ማለት ነው። ይህ ቃል፣ እግዚአብሔር አስቀድሞ የተወሰኑ ነገሮች ባሉበት ሁኔታ እንዲሆኑ እንደወሰነ ያሳያል። ከላይ በቀረቡት ጥቅሶች መሰረት፣ እግዚአብሔር አስቀድሞ እንዲሆኑ የወሰናቸው ነገሮች ምንድን ናቸው? በ ሮሜ 8፡29-30 መሰረት፣ የተወሰኑ ሰዎች የልጁን መልክ እንዲመስሉ፣ እንዲጠሩ፣ እንዲፀድቁ፣ እና እንዲከብሩ እግዚአብሔር አስቀድሞ ወስኗል። እግዚአብሔር የተወሰኑ ሰዎች እንዲድኑ አስቀድሞ ወስኗል። በበርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ውስጥ አማኞች በክርስቶስ እንደተመረጡ እናነባለን (ማቴዎስ 24፡22፣31፤ ማርቆስ 13፡20፣ 27፤ ሮሜ 8፡33፣ 9፡11፣ 11፡5-7፣ 28፤ ኤፌሶን 1፡11፤ ቆላሲያስ 3፡12፤ 1ተሰሎንቄ 1፡4፣ 1ጢሞቴዎስ 5፡21፤ 2ጢሞቴዎስ 2፡10፣ ቲቶ 1፡1፤ 1ጴጥሮስ 1፡1-2፣ 2፡9፤ 2ጴጥሮስ 1፡10)። አስቀድሞ መወሰን፣ እግዚአብሔር በሉአላዊነቱ የተወሰኑ ሰዎች እንዲድኑ መምረጡን የሚናገር መጽሐፍ ቅዱሳዊ ዶክትሪን ነው። በዚህ ዶክትሪን ላይ አስቀድሞ የሚነሳው መከራከሪያ፣ ‘ፍትሃዊ አይደለም’ የሚለው ነው። እግዚአብሔር የተወሰኑትን መርጦ ሌሎቹን እንዴት ይተዋል? እዚህ ላይ መዘንጋት የሌለብን ትልቅ ቁም ነገር ቢኖር ማናችንም ብንሆን የመዳን መብት የሌለን መሆኑን ነው። ማናችንም መዳንን እንደመብት ልንጠይቅ ሕጋዊ መሰረት የለንም። ምክንያቱም ሁላችን ሃጢአትን አድርገናል (ሮሜ 3፡23)፣ በዚህም ምክንያት የሚጠብቀን ዘላለማዊ ቅጣት ብቻ ነው (ሮሜ 6፡23)። እናም፣ ከፊላችንን አይደለም ሁላችንንም ወደ ገሃነም እሳት ቢሰደን እግዚአብሔር ፍጹም ፍታዊ ያደርገዋል። ፍትህ ተገቢውን ውሳኔ ማግኘት ማለት ነውና። ሆኖም ግን እግዚአብሔር የተወሰኑትን ለማዳን መረጠ። እግዚአብሔር በዚህ ምርጫ ውስጥ ባልተካተቱት ሰዎች ምክንያት ኢፍታዊ አይሆንም። ምክንያቱም ያሉበት ቦታ የሚገባቸው ነውና። እግዚአብሔር የተወሰኑትን ለማዳና ያደረገው ሉአላዊ ምርጫ በተቀሩት ላይ ያለውን ኢፍታዊነት አያሳይም። ማንም ሰው ከእግዚአብሔር አንዳች መልካም ነገር የማግኘት መብት የለውም። አንዳች ባለማግኘቱም በእግዚአብሔር ላይ ቅሬታ ማሰማት አይችልም። አንድ ሰው ከ20 ሰዎች መካከል መርጦ ለ5ቱ ብቻ ገንዘብ ቢሰጥ፣ የተቀሩት 15ቱ ይበሳጩ ይሆን? ሊበሳጩ ይችሉ ይሆናል። ለመበሳጨት ሕጋዊ መብት ይኖራቸው ይሆን? ፈጽሞ። ለምን? ለጋሹ የማናቸውም እዳ የለበትምና። ሰውየው ያደረገው አንድ ነገር ቢኖር ለተወሰኑቱ ሰዎች ለጋስ ለመሆን መወሰኑ ነው። እግዚአብሔር የሚድኑትን የሚመርጥ ከሆነ፣ በገዛ ፈቃዳችን መርጠን በክርስቶስ ለማመን የምንወስነውን ውሳኔ ከንቱ አያደርገውምን? መጽሐፍ ቅዱስ ምርጫ እንዳለን ይናገራል – በክርስቶስ የሚያምን ሁሉ ይድናል (ዮሐንስ 3፡16፤ ሮሜ 10፡9-10)። መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር በእርሱ የሚያምኑትን እና ፈቃዱን የሚሹትን ሰዎች እንደሚጥላቸው አይናገርም (ዘዳግም 4፡29)። በእነዚህ ሁለት ሃሳቦች መካከል አንድ የምናስተውለው መለኮታዊ አሰራር አለ። ይህም የእግዚአብሔር አስቀድሞ አማኙን የመሳብ ስራ (ዮሐንስ 6፡44) ግለሰቡ አምኖ ለመዳን ከሚያደርገው የግል ውሳኔ ጋር (ሮሜ 1፡16) መለኮታዊ አብሮነት እንዳላቸው። እግዚአብሔር የሚድኑትን አስቀድሞ ወስኗል የሚለውና ለመዳን ክርስቶስን መምረጥ ይኖርብናል የሚሉት ሁለቱም ሃሳቦች ውሁድ እውነታዎች ናቸው። ‘‘የእግዚአብሔር ባለ ጠግነትና ጥበብ እውቀቱም እንዴት ጥልቅ ነው፤ ፍርዱ እንዴት የማይመረመር ነው፥ ለመንገዱም ፍለጋ የለውም’’ (ሮሜ 11፡33)። አስቀድሞ መወሰንና መመረጥ፣ አስቀድሞ ከመታወቅ ጋር ያላቸው ዝምድና ምነድን ነው? እግዚአብሔር ሁሉን አስቀድሞ በማወቁ፣ አስቀድሞ የወሰናቸውን እና የመረጣቸውን ሰዎች በዚህ እውቀቱ ላይ ተመስርቶ መምረጥ ይችል ነበር። ነገር ግን የአስቀድሞ ውሳኔውም ሆነ ምርጫው ስለእነዚህ ሰዎች ባለው የአስቀድሞ እውቀቱ ላይ የተመሰረተ አይደለም። በቀላል ቁጥር የማይገመቱ ክርስቲያኖች በዚህ መንገድ ያምናሉ፤ አመለካከቱም የአርሜናውያን አስቀድሞ ውሳኔ አመለካከት በመባል ይታወቃል። የዚህ አመለካከት ችግር መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አስቀድሞ መወሰን፣ መመረጥ እና አስቀድሞ መታወቅ ከሚናገረው ጋር አብሮ የማይሄድ መሆኑ ነው። እግዚአብሔር ይህን ምርጫ ያደረገው ስለ መረጣቸው ሰዎች መጪ ዘመን አስቀድሞ በማወቁ ላይ ተመስርቶ አለመሆኑን ለመገንዘብ፣ እግዚአብሔር የተወሰኑ ሰዎችን ለድነት የመረጠበትን ወይም የወሰነበትን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምክንያት መገንዘብ ይኖርብናል። ኤፌሶን 1፡5 እንዲህ ይላል፣ ‘‘በበጎ ፈቃዱ እንደ ወደደ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ሥራ ለእርሱ ልጆች ልንሆን አስቀድሞ ወሰነን።’’ በዚህ ጥቅስ መሰረት፣ እግዚአብሔር እኛን አስቀድሞ የወሰነበት ምክንያት እኛ የሰራነው ወይም የምንሰራው ስራ ሳይሆን በጎ ፈቃዱና የገዛ ደስታው ነው። ሮሜ 9፡15-16 ደግሞ እንዲህ ይላል፣ ‘‘ለሙሴ፡- የምምረውን ሁሉ እምረዋለሁ ለምራራለትም ሁሉ እራራለታለሁ ይላልና። እንግዲህ ምሕረት ለወደደ ወይም ለሮጠ አይደለም፥ ከሚምር ከእግዚአብሔር ነው እንጂ።’’ አዲሱ መደበኛ ትርጉም እንዲህ ይላል፣ ‘‘ለሙሴ፣ የምምረውን እምረዋለው፣ ለምራራለትም እራራለታለው ይላልና። እንግዲህ ይህ ከሰው ፍላጎት ወይም ጥረት ሳይሆን፣ ከእግዚአብሔር ምህረት የተነሳ ነው።’’ ስለያዕቆብና ኤሳው በሮሜ 9፡11 ‘‘ልጆቹ ገና ሳይወለዱ፥ በጎ ወይም ክፉ ምንም ሳያደርጉ፥ ከጠሪው እንጂ ከሥራ ሳይሆን በምርጫ የሚሆን የእግዚአብሔር አሳብ ይጸና ዘንድ፥ …’’ የሚል ተጽፎ እናነባለን። በኤፌሶን 1፡11 ላይ ደግሞ፣ ‘‘እንደ ፈቃዱ ምክር ሁሉን የሚሠራ እንደ እርሱ አሳብ፥ አስቀድመን የተወሰንን በክርስቶስ ደግሞ ርስትን ተቀበልን።’’ በእነዚህና በሌሎች በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ላይ የምናነበው ነገር፣ አስቀድሞ መወሰን ወይም መመረጥ እኛ ባደረግነው ወይም ወደፊት በምናደርገው ተግባር ላይ የተመሰረተ አለመሆኑን ነው። እግዚአብሔር ሕዝቦችን ከነገድ እና ከቋንቋ ለመንግስቱ የመረጠው በገዛ ሉአላዊ ፈቃድ ላይ ተመስርቶ ነው። እግዚአብሔር እነዚህን ሕዝቦች ከነገድ እና ከቋንቋ ለመንግስቱ የመረጠው ገና አለም ሳይፈጠር በፊት (ኤፌሶን 1፡4)፣ በገዛ ሉአላዊ ፈቃዱ ላይ ተመስርቶ እንጂ የወደፊቱን ስለሚያውቅ፣ ወደፊት በሚያደርጉት ተግባር ላይ ተመስርቶ አይደለም። ሮሜ 8፡29 ‘‘አስቀድሞ ያወቃቸውን … አስቀድሞ ደግሞ ወስኖአልና፤’’ ይል የለምን? ይህ ማለት አስቀድሞ መወሰን በእግዚአብሔር አስቀድሞ ማወቅ ላይ የተመሰረተ እንደሆነ አያሳይምን? መልሱ፣ አዎ አስቀድሞ መወሰን በእግዚአብሔር አስቀድሞ ማወቅ ላይ የተመሰረተ ነው። ችግሩ አስቀድሞ ስለማወቅ የምነሰጠው ትርጉም የተዛባ መሆኑ ነው። የእግዚአብሔር አስቀድሞ መወሰን፣ እግዚአብሔር አስቀድሞ በማወቅ ችሎታው ላይ የተመሰረተ ነው የሚለው ሃሳብ፣ እግዚአብሔር ሊያድናቸው የወሰናቸውን ሰዎች የመረጠው መፃኢ ጊዜያቸውን ካየ በሁዋላ እና ማን ወንጌልን እንደሚቀበል እና እንደማይቀበል ጋረጋገጠ በሁዋላ ነው ወደሚል ትርጉም የሚወስደን ከሆነ ከላይ ካየናቸው የእግዚአብሔር የምራጭ ምክንያቶች ጋር እንቃረናለን። ስለሚድኑ ሰዎች የዮሐንስ ወንጌል 10፡26 የሚለውን እንይ። ኢየሱስ ስለ ሚቃወሙት ሰዎች ሲናገር እንዲህ አለ፣ ‘‘ከበጎቼ ስላልሆናችሁ አታምኑም’’። በዚህ ጥቅስ መሰረት ሰዎች የሚያምኑት የእግዚአብሔር በግ ስለሆኑ ነው። እግዚአብሔር እነዚህን ሰዎች ለድነት የመረጣቸው አንድ ቀን በሚያደርጉት የማመን ውሳኔ ምክንያት ሳይሆን ገና ሳይፈጠሩ በክርስቶስ የራሱ ልጆች እንዲሆኑ አስቀድሞ ስለመረጣቸው ነው። አንዱ አምኖ ሌላው የማያምንበት ምክንያት አንደኛው በእግዚአብሔር አስቀድሞ ልጁ እንዲሆን ስለተመረጠ እና ሌላው ደግሞ ስላልተመረጠ ነው።

አስቀድሞ መወሰን ማለት ምን ማለት ነው? አስቀድሞ የመወሰን ሃሳብ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነው? Read More »