ትንቢተ ሚልክያስ

የብሉይ ኪዳን ጥናት ክለሳ

የብሉይ ኪዳንን የተለያዩ መጻሕፍት ስናጠና ቆይተናል። የእያንዳንዱ መጽሐፍ ጸሐፊ ማን እንደሆነ፥ የመጽሐፉን ታሪካዊ ሥረ-መሠረት፥ ዓላማና ዐበይት ትምህርቶች ተመልክተናል። እያንዳንዱን መጽሐፍ ያጠናነው በግል ስለሆነ በመጨረሻ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት በሙሉ በአንድነት እንዴት እንደተዋሀዱ ለመረዳት ጠቃሚ የሆነውን የመጻሕፍቱን ክለሳ መመልከት አስፈላጊ ነው። የውይይት ጥያቄ፦ ሀ) በብሉይ ኪዳን የሚገኙ መጻሕፍት ስንት ናቸው? ለ) የብሉይ ኪዳንን መጻሕፍት ዋና ዋና ክፍሎች ጥቀስና በእነዚህ ክፍሎች ውስጥ የሚገኙትን መጻሕፍት ዘርዝር። 1. ፔንታቱክ (አምስቱ የሙሴ መጻሕፍት) ብሉይ ኪዳን በአራት ዐበይት ክፍሎች ይከፈላል። የመጀመሪያው ዋና ክፍል ፔንታቱክ ወይም አምስቱ የሙሴ መጻሕፍት የሚባለው ሲሆን፥ የብሉይ ኪዳንን የመጀመሪያ አምስት መጻሕፍት የያዘ ነው። እግዚአብሔር ከእስራኤል ሕዝብ ጋር ያደረጋቸውን ቃል ኪዳኖች ስለሚገልጹ በብዙ አንጻር በብሉይ ኪዳን ውስጥ ከሚገኙ መጻሕፍት ሁሉ እጅግ አስፈላጊ መጻሕፍት ናቸው። እነዚህ ቃል ኪዳኖች ብሉይና አዲስ ኪዳን የተመሠረቱባቸው መሠረች ናቸው። ከፔንታቱክ መጻሕፍት ግማሽ ያህሉ ታሪካዊ መጻሕፍትን የያዘ ነው፡- (ዘፍጥረት፥ ዘጸአት፥ ዘኁልቁ)። ቀሪው ግማሽ ያህል ደግሞ ይኖሩበት ዘንድ እግዚአብሔር ለአይሁድ የሰጣቸውን ቃል ኪዳንና ሕግጋት የያዘ ነው (ዘጸአት፥ ዘሌዋውያን፥ ዘዳግም)። ታሪክ የሚጀምረው ስለ ፍጥረታት አጀማመር የሚናገሩ ታሪኮችን በያዘው በኦሪት ዘፍጥረት ነው። ይህ መጽሐፍ ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ የእግዚአብሔር ሕዝብ ከአንድ ሰው፥ ማለትም ከአብርሃም በመጀመር፥ በግብፅ ታላቅ ሕዝብ እስኪሆኑ ድረስ እንዴት እንደበዙ ያሳየናል። የኦሪት ዘጸአት የመጀመሪያ ግማሽ ክፍል፥ እግዚአብሔር ሕዝቡ በግብፅ የነበሩበትን ቀንበር ለመስበርና ነፃ ለማውጣት በኃይልና በሥልጣን እንዴት እንደሠራ ያሳየናል። እግዚአብሔር ሕዝቡን ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳን ወዳደረገበት ወደ ሲና ተራራ መራቸው። የመጽሐፉ ሁለተኛ ክፍል ይህን ቃል ኪዳን በዝርዝር ያሳየናል። ቃል ኪዳኑ በቅድመ-ሁኔታ ላይ የተመሠረተ ስለነበር ለሕጉ በመታዘዝ ሲኖሩ እግዚአብሔር እንደሚባርካቸው፥ ካልታዘዙት ደግሞ እንደሚቀጣቸው ተናግሮ ነበር። የቃል ኪዳኑ ማዕከል በመካከላቸው የእግዚአብሔርን ዙፋን መገኘት የሚያመለክተው የቃል ኪዳኑ ታቦት የነበረበት የመገናኛው ድንኳን ነበር። እስራኤላውያን የሲናን ተራራ ከመልቀቃቸው በፊት ዕቅዱ በእግዚአብሔር የተነደፈውን የመገናኛ ድንኳን ሠሩ። ኦሪት ዘሌዋውያን፥ እስራኤላውያን በእግዚአብሔር የተመረጡ ቅዱስ ሕዝብ እንደመሆናቸው መጠን እንዴት መኖር እንዳለባቸው የሚያሳዩ ሕግጋትን ይዟል። እስራኤላውያን እግዚአብሔርን ለማምለክ ሊያቀርቧቸው ስለሚገቡ የተለያዩ መሥዋዕቶች ይገልጻል። ሕዝቡ እግዚአብሔር ያደረገላቸውን ነገሮች የሚያስታውሱባቸው የተለያዩ የሃይማኖት በዓላትን ይደነግጋል። ካህናት ደግሞ ሕዝቡን በተቀደሰ አምልኮ መምራት ይችሉ ዘንድ እንዴት መኖር እንዳለባቸው ይዘረዝራል። አይሁድ ሁሉ በየዕለቱ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ሁኔታ እንዴት እንደሚኖሩና የእግዚአብሔርን በረከቶች ለማግኘት እንዴት እርግጠኛች መሆን እንደሚችሉ ግልጽ መመሪያዎችን ይሰጣል። ኦሪት ዘኍልቍ የሚያተኩረው የእግዚአብሔር ሕዝብ በተስፋዪቱ ምድር ያሉ ጠላቶቻቸውን ለማሸነፍ በእግዚአብሔር መታመን ስላቃታቸው በምድረ በዳ ለ40 ዓመታት መንከራተታቸውን በሚናገረው አሳዛኝ ታሪክ ላይ ነው፡፡ አንድ ትውልድ ባለመታዘዙ ምክንያት ሙሉ በሙሉ መጥፋቱን የሚናገር ታሪክ ነው። ኦሪት ዘኁልቁ የሚጠናቀቀው አይሁድ ከዮርዳኖስ በስተምሥራቅ የሚገኘውን ምድር ወርረው በማሸነፍ እግዚአብሔር ወደሰጣቸው ወደ ተስፋይቱ ምድር ለመግባት እንደተዘጋጁ በመናገር ነው። በኦሪት ዘዳግም ውስጥ ሙሴ በሲና ተራራ የተሰጡትን ሕግጋት ለአዲሱ ትውልድ በድጋሚ ሲናገር እንመለከታለን። ሙሴ የተስፋይቱን ምድር ከሩቅ አሻግሮ ቢመለከትም እንኳ ወደ ከነዓን ሳይገባ ሞተ። የፔንታቱክ ታሪክ የሚጀምረው እግዚአብሔር ምድርን ከፈጠረበት ካልታወቀ ጊዜ ሲሆን፥ የሚደመደመው ደግሞ በ1400 ዓ.ዓ. ገደማ ነው።  2. የታሪክ መጻሕፍት ከመጽሐፈ ኢያሱ እስከ አስቴር ድረስ ያሉት የሚቀጥሉት አሥራ ሁለት መጻሕፍት በብሉይ ኪዳን ዘመን የተፈጸመውን የእስራኤል ሕዝብ ታሪክ የሚናገሩ ናቸው። ይህም ከነዓን ድል ከሆነችበት ከ1400 ዓ.ዓ. ጀምሮ፥ ከምርኮ መልስ የኢየሩሳሌም ቅጥር እስከተሠራበት እስከ 400 ዓ.ዓ. ድረስ የነበረውን ታሪክ ያጠቃልላል።  ኢያሱ ስለ ከነዓን ድል መሆን ይናገራል። የእስራኤል ሕዝብ በእግዚአብሔር ላይ በነበራቸው እምነት ምክንያት አብዛኞቹን የከነዓንን ምድር ከተሞች ለማሸነፍና በዚያ የሚኖሩትን ከነዓናውያንን ማንበርከክ ችለው ነበር። መጽሐፈ መሳፍንት የሚናገረው ግን እስራኤላውያን ለእግዚአብሔር ፍጹም ታዝዘው ከነዓናውያንን ባለማጥፋታቸው ምን እንደ ተፈጸመ ነው። አይሁድ ከከነዓናውያን ጋር ጎን ለጎን በመኖራቸው፥ ወዲያውኑ በባዕድ አምልኮ ኃጢአት ወደቁ። እግዚአብሔር በባርነት ይገዟቸው ዘንድ ለተለያዩ ከነዓናውያን መንግሥታት አሳልፎ በመስጠት ቀጣቸው። እስራኤላውያን ንስሐ በሚገቡበትና ወደ እግዚአብሔር በሚጮሁበት ጊዜ ከጠላቶቻቸው የሚታደጉአቸው የተለያዩ ተዋጊዎችን (መሳፍንትን) ያስነሣላቸው ነበር። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ደግሞ ወደ ቀድሞው የኃጢአት መንገዳቸው ይመለሱና እግዚአብሔር ይቀጣቸው ነበር። በዘመነ መሳፍንት ለእግዚአብሔር በታማኝነት የቆሙ አንዳንድ ሰዎች ነበሩ። ለዚህ ምሳሌ ከሚሆኑት መካከል ሩትና ቦዔዝ ይገኛሉ። ለእግዚአብሔር ተስፋ ታማኞች ሆነው በመቆየታቸው በእስራኤል ላይ ከነገሡ ነገሥታት ሁሉ በላይ የሆነው የንጉሥ ዳዊት አያቶች እንዲሆኑ እግዚአብሔር ፈቀደ። 1ኛ ሳሙኤል የሚያስተዋውቀን ከመሳፍንት ወደ ነገሥታት ዘመን የተደረገውን የሽግግር ወቅት ነው። የመጨረሻዎቹ ሁለት መሳፍንት ዔሊና ሳሙኤል ነበሩ። ይህ ማለት የግል ነፃነትን ማጣትና ከፍተኛ ግብር መገበር ማለት ቢሆንም እንኳ ሕዝቡ እንደቀሩት አሕዛብ ንጉሥ እንዲኖራቸው ፈለጉ። ሳኦል የእስራኤል ሕዝብ የመጀመሪያ ንጉሥ ነበር። ሳኦል አጀማመሩ መልካም ቢሆንም፥ የእግዚአብሔርን ሕግጋት ባለመጠበቁ፥ መንግሥቱ ከእርሱ ተወስዳ ለዳዊት ተሰጠች። የ1ኛ ሳሙኤል አብዛኛው ታሪክ የያዘው ሳኦል፥ ዳዊት ንጉሥ እንዳይሆን ባደረበት ቅንዓት እርሱን ለመግደል ያደረጋቸውን የተለያዩ ሙከራዎች ነው። 2ኛ ሳሙኤል በእስራኤል ላይ ከነገሡት ነገሥታት ሁሉ በላይ የሆነውን የንጉሥ ዳዊትን ታሪክ ይናገራል። ዳዊት እግዚአብሔርን ይወድ ነበር። ምንም እንኳ በኃጢአት ቢወድቅም፥ ዝርያዎቹ የእስራኤልን ዙፋን እንደሚቆጣጠሩ የተስፋ ቃል በመስጠት እግዚአብሔር አከበረው። ይህም የዳዊት ልጅ በሆነው በመሢሑ በኢየሱስ ሙሉ ለሙሉ ይፈጸማል። 1ኛ መጽሐፈ ነገሥት የነገሥታትን ታሪክ መናገሩን ይቀጥላል። የሚጀምረው በምድር ላይ ከኖሩት ሁሉ የላቀ ጥበበኛ በነበረው በዳዊት ልጅ በሰሎሞን ነው። ዳሩ ግን ሰሎሞን ለሴቶች የነበረው ፍቅር ወደ ጣዖት አምልኮ መርቶት፥ የእግዚአብሔርን ፍርድ እንዲቀበል አደረገው። ከሰሎሞን ሞት በኋላ እግዚአብሔር የእስራኤልን መንግሥት የሰሜኑን ክፍል የእስራኤል መንግሥትና የደቡቡን የይሁዳ መንግሥት ተብሎ እንዲከፈል አደረገ፡፡ የቀረው 1ኛ እና 2ኛ መጽሐፈ ነገሥት እግዚአብሔር ሰሜኑ የእስራኤልን መንግሥት ወደ አሦር፣ ደቡቡ የይሁዳን መንግሥት ወደ ባቢሎን በምርኮ እንዲወሰድ ከማድረጉ በፊት የነበሩትን ነገሥታት ታሪክ በአጭሩ ያብራራል። 1ኛ- 2ኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል ከዳዊት እስከ ምርኮ ድረስ ያለውን የደቡቡ የዳዊትን ዝርያ የሆኑ ነገሥታት ታሪክ በድጋሚ ይተርካል። እነዚህን ጊዜያት ከታሪክ አቅጣጫ ከመመልከት ይልቅ አንድ ንጉሥ እግዚአብሔርን በሚያከብርበት ጊዜ መንግሥቱና ሕዝቡ እንደሚባረክ። ንጉሡ ለእግዚአብሔርና ለሕግጋቱ በማይታዘዝበት ጊዜ መንግሥቱና ሕዝቡ እንደሚፈረድበት እነዚህ መጻሕፍት ይናገራሉ። መጽሐፈ ዕዝራ፥ ነህምያና አስቴር የይሁዳ ሕዝብ ከምርኮ ከተመለሱ በኋላ ስለተፈጸሙ ድርጊቶች የሚናገሩ ናቸው። መጽሐፈ ዕዝራ የሚገልጸው ከባቢሎን ወደ ምድራቸው ስለተመለሱት ሁለት የመጀመሪያ የአይሁድ ቡድኖች ጉዳይና ስለ ቤተ መቅደሱ መሠራት ነው። ነህምያ ደግሞ ወደ ምድሪቱ ስለተመለሰ ሌላ ቡድን ስለ ኢየሩሳሌም ቅጥር መሠራት ይናገራል። መጽሐፈ አስቴር በንጉሥ አርጤክስስ ዘመን እግዚአብሔር አይሁድን በአሕዛብ ፈጽመው ከመደምሰስ እንዴት እንደጠበቃቸው ይናገራል። ከእዚህ አሥራ ሁለት መጻሕፍት በኋላ የእስራኤል ሕዝብ ታሪክ ትረካ ያበቃል። ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ ለመኖር እስከመጣበት ጊዜ ድረስ 400 የጸጥታ ዘመናት ነበሩ። የእነዚህን የጸጥታ ዘመናት ታሪክ ሌሎች መጻሕፍት የዘገቡት ቢሆንም፥ መጽሐፍ ቅዱስ ግን ስለ እርሱ ምንም አይናገርም።  3. የግጥምና የጥበብ መጻሕፍት በብሉይ ኪዳን ውስጥ እጅግ ተወዳጅ ከሆኑ መጻሕፍት መካከል አምስቱ የግጥምና የጥበብ መጻሕፍት ይገኛሉ። እነርሱም መጽሐፈ ኢዮብ መዝሙረ ዳዊት መጽሐፈ ምሳሌ፥ መጽሐፈ መክብብና መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን ናቸው። መዝሙረ ዳዊት የአይሁድ የአምልኮ መዝሙራት መጽሐፍ ተብሎ ሊጠራ ይችላል። በመዝሙረ ዳዊት ውስጥ የሚገኙት አብዛኛዎቹ መዝሙራት የተጻፉት ለእግዚአብሔር ምስጋናን በሚገልጡና እግዚአብሔር ክፉዎችን በመቅጣት ጻድቃንን እንደሚባርክ በሚያስረዱ መንገዶች ነው። ሌሎቹ መጻሕፍት የጥበብ መጻሕፍት በመባል ይታወቃሉ፤ ምክንያቱም አይሁድ እርሱን በሚያስከብር መንገድ እንዲኖሩ እግዚአብሔር ስለሰጣቸው ጥበብና በጊዜው ይቸገሩባቸው ስለነበሩ አንዳንድ የፍልስፍና ጥያቄዎች የሰጣቸውን መልስ ስለሚያስረዱ ነው። መጽሐፈ ኢዮብ የሚያስተምረን ጻድቅ ሰው ከቶ ባልታወቀ ምክንያት መከራን ቢቀበል እንኳ በእግዚአብሔር ታምኖ መከራውን በትዕግሥት ሊቀበለው እንደሚገባ ነው። መጽሐፈ ምሳሌ ደግሞ ማንኛውም የሕይወት ሁኔታ ውስጥ በጥበብ መኖር እንዴት

የብሉይ ኪዳን ጥናት ክለሳ Read More »

አራት መቶ የጸጥታ ዓመታት

የብሉይ ኪዳን ታሪክ የሚደመደመው በመጽሐፈ ነህምያ ሲሆን፥ ትንቢታዊ መልእክቶች የሚጠቃለሉት ደግሞ በትንቢተ ሚልክያስ ነው። እግዚአብሔር ለሕዝቡ ለእስራኤላውያን የሚሰጠው መልእክት ተፈጸመ። እግዚአብሔር ኤልያስንና መሢሑን እንዲጠባበቁ ለእስራኤላውያን መልእክት ከሰጣቸው በኋላ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚያክሉት ሌላ ተጨማሪ መልእክት አልሰጣቸውም። የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን ከሚልክያስ ዘመን ጀምሮ (400 ዓ.ዓ.) ኢየሱስ እስከ መጣበት (5 ዓ.ዓ.) ድረስ የነበረውን ጊዜ «400 የጸጥታ ዓመታት» ብለው የሚጠሩት ስለዚህ ነበር። አይሁድ የአዋልድ መጻሕፍት (አፖክሪፋ) በመባል የሚታወቁ ሌሎች ተጨማሪ መጻሕፍት የጻፉ ቢሆንም፥ እነዚህ መጻሕፍት ከብሉይ ኪዳን 39 መጻሕፍት ጋር እኩል እንዳይደሉ ተገንዝበው ነበር።  እነዚህ አራት መቶ ዓመታት ለአይሁድ እጅግ ወሳኝ ስለነበሩ በእነዚህ ዓመታት ምን እንደተደረገ ማወቅ አስፈላጊ ነው። እነዚህን አራት መቶ ዓመታት የበለጠ በተረዳን ቁጥር፥ በአዲስ ኪዳን ውስጥ የተፈጸሙትን አንዳንድ ነገሮች በይበልጥ እንረዳለን። ከጊዜና ከቦታ እጥረት የተነሣ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ጥቂት አሳቦች ብቻ ተጠቃልለው ቀርበዋል። 1. የፋርስ ንጉሠ ነገሥት ግዛቶች (539-331 ዓ.ዓ.)፡- የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት በተደመደመበት ጊዜ፥ የፋርስ መንግሥት ነገሥታት አይሁድን ራቅ ብሎ እንደሚገኝ የግዛታቸው ክፍለ ሀገር ይዙዋቸው ነበር። በፖለቲካ ረገድ ከታላቁ የፋርስ የሥልጣን ማዕከል እጅግ ርቀው ይገኙ ስለነበር የፋርስ መንግሥት አይሁዳውያንን የራሳቸውን ጉዳይ እንዲያከናውኑ ትተዋቸው ነበር። ኢየሩሳሌም ከፍተኛ የንግድ ዕከልና የጳለስጢን ዋናዋ የፖለቲካ ሥልጣን ቁንጮ ነበረች። በፋርስ የንጉሠ ነገሥት ግዛት የሥልጣን ዘመን ውስጥ፥ የኋላ ኋላ በአዲስ ኪዳን ዘመን ላይ ተጽዕኖ ያሳደሩ ብዙ ነገሮች ተፈጽመዋል።  ሀ. አይሁድ በዓለም ዙሪያ ሁሉ መሠራጨታቸውን ቀጠሉ። አብዛኛዎቹ አይሁድ የሚኖሩት ከኢየሩሳሌምና ከይሁዳ ውጭ ነበር። እንደ ሀገራችን የጉራጌ ብሔር አባሉች የተዋጣላቸው ነጋዴዎች በመሆን፥ በጥንቱ ዓለም በነበሩ በአብዛኛዎቹ ከተሞች ይገኙ ነበር። ይህ በየስፍራው ተበትኖ የመኖር ነገር በሚቀጥለው የግሪክ ንጉሠ ነገሥት ግዛትም እየጨመረ ሄዶ ነበር። በአዲስ ኪዳን ዘመን በግልጽ እንደሚታየው ጳውሎስ ወንጌልን ይዞ በተዘዋወረባቸው ስፍራዎች ሁሉ፥ በቅድሚያ ይሰብክ የነበረው የተበተኑት አይሁድ ወደሚሰበሰቡበት ምኩራብ በመሄድ ነበር። ለ. የአይሁድ ዋና ቋንቋ ተለወጠ። አብዛኛዎቹ አይሁድ በእስራኤል ውስጥ ይኖሩ የነበሩት ሳይቀሩ አራማይክ የተባለውን የንግድ ቋንቋ ይናገሩ ነበር። የብሉይ ኪዳን ቋንቋ የሆነውን ዕብራይስጥ ይጠቀሙ የነበሩት በአምልኮ ፕሮግራም ብቻ ነበር። ለምሳሌ የእግዚአብሔር ቃል በሚነበብበት ጊዜ ዕዝራ የተረጐመበት አንዱ ምክንያት ይህ ነበር (ነህምያ 8፡7-8)። ኢየሱስ አገልግሎቱን የሰጠው በአራማይክ ቋንቋ ነው።  ሐ. የምኩራቦች አጀማመር፡- የአይሁድ ማኅበረሰብ ባሉበት ስፍራ ሁሉ፥ የማኅብረሰብ ማዕከልና ምኩራብ የተባለ የአምልኮ ስፍራ ይሠሩ ጀመር። በእነዚህ ምኩራቦች ውስጥ መሥዋዕት ባያቀርቡም እንኳ የእግዚአብሔርን ቃል ለመስማት ይሰበሰቡ ነበር። እነዚህ ምኩራቦች በኋላ የጣዖት አምልኮ የሰለቻቸው አሕዛብ ስለ እውነተኛው አምላክ ለመስማት የሚሰበሰቡባቸው ስፍራዎች ሆኑ። ጳውሎስና ሌሎች አገልጋዮች ወንጌልን ለመስበክ ወደ እነዚህ ስፍራዎች እንደሄዱ እነዚህ አሕዛብ ፈጥነው በክርስቶስ በማመን ተለወጡ፡፡  መ. የካህናት ሥልጣን እየጨመረ መምጣት፡- ገና ከመጀመሪያው በኢየሩሳሌም የነበረው የአይሁድ ማኅበረሰብ አንድ የፖለቲካ (ለምሳሌ ዘሩባቤል)፥ ሌላ የሃይኖት (ለምሳሌ ታላቁ ካህን ኢያሱ) መሪ የነበረው ቢሆንም፥ ካህናቱ የፖለቲካና የሃይማኖት መሪነቱን ጠቅልለው ለመያዝ ብዙ ጊዜ አልፈጀባቸውም ነበር። ይህም ካህናቱ ሕዝቡን በመንፈሳዊ ረገድ ከመምራት ይልቅ በፖለቲ ጉዳይ ላይ በማተኮር በሥልጣን እንዲባልጉ አደረጋቸው። ሠ. “ጸሐፍት” የተባሉ አይሁድ ያሉብት መደብ ፈጠር፡- ጸሐፍት በሕግ እውቀትና ትርጓሜ ሥራ የተካኑ ነበሩ፡፡ እነርሱም የእስራኤል ቁልፍ የሕግ መምህራን ሆኑ፡፡ ሕዝቡ የብሉይ ኪዳንን ተዛዛት እንዳይጥሱ ለማረጋገጥ በመፈለጋቸው፣ ሕዝቡ ለተጻፉት ሕግጋት አንታዘዝም እንዳይሉ ለመጠበቅ ሲሉ እንደ “አጥር” የሚሆኑ ሌሎች ሕግጋትን ጨመሩ፡፡ በኋላ ለእነዚህ ሕግጋት ወግ ከመጀመሪያው የእግዚአብሔር ሕግ የበለጠ ስፍራ ይሰጣቸው ጀመር፡፡ ይህም ወዲያውኑ ይሑዲነትን ልባዊ ሳይሆን ሕጋዊነት ወደሚንጸባረቅበት “አድረግ፣ አታድርግ” የአይሁድ የሃይማኖት ሥርአት ለወጠው፡፡ ጸሕፍትም በተራቸው የፖለቲካ መሪዎች እስኪሆኑ ድረስ በስልጣን መጥቀው ሄዱ፡፡ በመጨረሻም ጸሐፍት፣ ካህናትና የአይሁድ ሽማግሌዎች “ሸንጎ” የተባል ጉባኤ በማቋቋም የአይሁድን የአስተዳደር አካል መሠረቱ፡፡  ረ. የሳምራውያንና የአይሁድ ጥላቻ አጀማመር፡- እስራኤላውያን በአሦር እጅ በወደቁና በተማረኩ ጊዜ ከሌላ ስፍራ አሕዛብን ወደ እስራኤል በማምጣት ከቀሩት አይሁድ ጋር ለመቀላቀል እንደሞከሩ ታስታውሳለህ፡፡ አይሁድና አሕዛብ በመጋባታቸው ምክንያት የተወለዱት ልጆች ሳምራውያን ተባሉ፡፡ ከአይሁድ ወደባቢሎን ተወስደው የነበሩት አይሁድ ወደ እስራኤል በተመለሱ ጊዜ የእስራኤል ሃይማኖት ከይሁዲነትና ከአሕዛብ የጣዖት አምልኮ ጋር ተደባልቆ ነበር። እነዚህ ሳምራውያን ከአይሁድ ጋር ተባብረው ቤተ መቅደሱን ለመሥራት በመጡ ጊዜ አይሁድ ተቃወሙ። አምልኮአቸው ንጹሕ ሆኖ እንዲቆይ ይፈልጉ ነበር። ይህም ሳምራውያንን አስቆጣቸውና የአይሁድ ጠላቶች እንዲሆኑ አደረጋቸው። ቆየት ብለው ሳምራውያን ከአይሁድ ተለዩ። ገረዚም በተባለ ተራራ ላይ የራሳቸውን ቤተ መቅደስ ሠሩ። ከአይሁድ የአምልኮ ሥርዓት ጋር የሚመሳሰል የራሳቸው የአምልኮ መዋቅር አበጁ። በተቀዳሚ አምስቱን የሙሴ መጻሕፍት የያዙ የራሳቸው የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ነበሯቸው። ይህም አይሁድን እጅግ አስቆጥቷቸው ስለነበር በነጻነታቸው ጊዜ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሳምራውያንን ገደሉ። በአይሁድና በሳምራውያን መካከል የነበረው ይህ ጠላትነት፥ በአዲስ ኪዳን ዘመን ኢየሱስ በሰማርያ ሲያልፍና በተለይ ከሳምራዊቷ ሴት ጋር ሲነጋገር ደቀ መዛሙርቱ አይተው በመደነቃቸው ይስተዋላል (ዮሐንስ 4)።  ሰ. ምሁራን የአይሁድ መሠረታዊ ትምህርቶች በአንዳንድ መንገዶች የፋርስ ሃይማኖት ተጽዕኖ አድሮባቸዋል ብለው ያስባሉ። በፋርስ ዘመን የፋርስ ሰዎች ያደርጉት እንደነበረው አይሁዶች በመለኮታዊ ፍርድ፥ በሙታን ትንሣኤ፥ በአጋንንትና በመላእክት ሕልውና፥ ወዘተ. ላይ ያተኩሩ ነበር።  2. የግሪክ ንጉሠ ነገሥት ግዛት (331-142 ዓ.ዓ.) የግሪክ ንጉሠ ነገሥት ግዛት በታላቁ እስክንድር መሪነት፥ በዓለም ላይ እስከዚያ ዘመን ድረስ ተነሥተው ከነበሩ መንግሥታት ሁሉ በላቀ ሁኔታ ተስፋፍቶ ነበር። የፋርስን የንጉሠ ነገሥት ግዛት በሙሉ ከመጠቅለል አልፎ፥ ወደ ታች ወደ ግብፅና ሕንድ ድረስ ተስፋፋ። በጥንት ታሪክ ለመጀመሪያው ጊዜ አንድ የአውሮፓ አገር ግዛቱን እስከ ትንሹ እስያ ድረስ በማስፋፋት፥ በአንዳንድ ረገድ ከነበረው ተመሳሳይነት በስተቀር በወረራቸው ሕዝቦች ላይ በእጅጉ የተለየ ባህል አመጣ። ሆኖም ታላቁ እስክንድር የፋርስን መንግሥት መዋቅርንም ሆነ የክልል መንግሥታት አደረጃጀትን ለመደምሰስ አልሞከረም። ታላቁ እስክንድር በዘመኑ የታወቁ የዓለም ክፍሎችን በሙሉ ወርሮ ከያዘ በኋላ አንዳንዶች እንደሚያስቡት ገና በወጣትነት ዘመኑ በ323 ዓ.ዓ. ሞተ። በ301 ዓ.ዓ. የታላቁ እስክንድር ጦር ሜጀር ጄኔራሎች እያንዳንዳቸው አንዳንድ ከፍል በመያዛቸው መንግሥቱ ለአራት ተከፈለ። በይሁዳ ላይ ተጽዕኖ አሳድረው የነበሩት ሁለቱ መንግሥታት ግብፅንና ሊቢያን ይዞ የነበረው የፕቶሎሜካዊ ንጉሠ ነገሥት ግዛትና ሶርያና ፋርስን ተቆጣጥሮ የነበረው የሲሉሲድ ንጉሠ ነገሥት ግዛት ነበሩ። በእነዚህ ሁለት የግሪክ ንጉሠ ነገሥት ግዛቶች መካከል ወዳጅነት አልነበረም። እነዚህ ሁለት መንግሥታት ጳለስጢናን ለመቆጣጠር በመምከር ያለማቋረጥ ይዋጉ ነበር። ይህ ማለት አይሁድ ያለማቋረጥ እርስ በርሳቸው በሚጋጩና አብረዋቸው እንዲምቱ በሚጠይቋቸው ባዕዳን ሠራዊት ይጠቁ ነበር ማለት ነው። ከ320-200 ዓ.ዓ. ፕቶሎሚዎች ጳለስጢናን ተቆጣጠሩ። በይሁዳ ይኖሩ የነበሩትን አይሁድ እንደፈለጋቸው እንዲኖሩ ለቀቋቸው። በዚህ ጊዜ የአይሁድ ገዢዎች ካህናት ነበሩ። ከ200-142 ዓ.ዓ. ሲሉሲዶች ጳለስጢናን ተቆጣጠሩ። ከፍተኛው ትኩረታቸው አይሁድ የግሪክን ባህል እንዲለምዱ ማድረግ ነበር። ቀረጥ እንዲከፍሉ አይሁድን አስገደዷቸው። በጭካኔ ከሁሉ የከፋው መሪ፥ ከ175-164 ዓ.ዓ. የገዛው አንቲዩከስ 4ኛ ኤፒፋነስ የተባለው ነው። አይሁድ የጣዖት አምልኮ ያካትት የነበረውን የግሪኮችን ባህል እንዲለማመዱ ለማስገደድ ሞከረ። በኃላፊነት ላይ የነበረውን የአይሁድ ሊቀ ካህን አባርሮ የግሪክን ባህል ለመቀበል ይፈልግ የነበረውን የራሱን አይሁዳዊ ሊቀ ካህን በሕዝቡ ላይ ሾመ። ከግብፅ ጋር ይዋጋ ለነበረው ጦሩ ለመክፈል በቤተ መቅደስ የነበረውን ገንዘብ ሁሉ ወሰደ። ሮማውያን ግብጽን ወርሮ እንዳይዝ በከለከሉት ጊዜ እጅግ ተቆጥቶ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ። በቤተ መቅደስ ውስጥ ይቀርብ የነበረው መሥዋዕት ሁሉ እንዲቆም በማድረግና በመሠዊያው ላይ አሳማ በመሠዋት መሠዊያውን አረከሰው። ዚዩስ ለተባለው የግሪክ ጣዖት መሥዋዕት ማቅረቢያ የሚሆን መሠዊያ በማሠራት ለዚዩስ መሥዋዕትን እንዲያቀርቡ አዘዘ። (በዳንኤል 11፡31-36 ስለዚህ ዘመን የተነገረውን ትንቢት ተመልከት)። ከ167-164 ዓ.ዓ. ለሦስት ዓመታት በቤተ ለእግዚአብሔር የሚቀርብ ማንኛውም መሥዋዕት ቆመ፡፡  ይህ የአንቲዩከስ ተግባር አይሁድን ለዓመፅ አነሣማቸው፡፡ መቃብያን ተብለው ይጠሩ በነበሩ በአንድ ካህንና በሁለት ልጆቹ መሪነት አይሁድ በመካከላቸው የነበረውን የግሪክ ባህል መስፋፋት

አራት መቶ የጸጥታ ዓመታት Read More »

የትንቢተ ሚልክያስ ዐበይት ትምህርቶች

1. ለቃል ኪዳኑ ሕግ መታዘዝ በማይኖርበት ጊዜ ከእግዚአብሔር ጋር የገባነውን ቃል ኪዳን አንፈጽምም። ዳሩ ግን የገባነውን ቃል ኪዳን የምንፈጽመው መታዘዛችን ከንጹሕ ልብና ከትክክለኛ ዝንባሌ ሲሆን ነው። ለእግዚአብሔር የሚቀርብ እውነተኛ አምልኮ ትክክለኛ ድርጊቶችን (ተገቢ የሆኑ ሥርዓቶች) የሚያካትት ብቻ መሆን የለበትም። ነገር ግን ለእግዚአብሔር ከሚገዛ ልብ የሚመነጭ፥ ለእግዚአብሔር ሕግ የሚታዘዝ፥ ከኃጢአት የነጻ፥ ከቤተሰብና ከጎረቤቶች ጋር ትክክለኛ በሆነ ግንኙነት መኖርን ጭምር የሚያጠቃልል ነው።  የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ሰዎች እግዚአብሔርን በሚያስከብር መንገድ ሳይሆን፥ ከአምልኮ ሥርዓት አንጻር ብቻ አምልኮአቸውን ሊያቀርቡ የሚችሉባቸውን ሁኔታዎች ግለጽ። ለ) ይህን ዝንባሌ ለማረም ምን ማድረግ ትችላለህ? 2. ጋብቻና ፍቺ (ሚልክያስ 2፡10-16)፡- ከሚስቶቻችን ወይም ከባሎቻችን ጋር በትክክለኛ ግንኙነት ውስጥ ካልሆንን ከእግዚአብሔር ጋር ትክክለኛ በሆነ ግንኙነት ልንኖር አንችልም። ሚልክያስ ስለ ጋብቻ ሁለት ዐበይት እውነቶችን ያስተምረናል፡-  ሀ) አንድ ሰው ማንን እንደሚያገባ ወይም ሴት ከሆነች ማንን እንደምታገባ ጠንቅቆ መወሰን አለበት ወይም አለባት። ኢየሱስ ክርስቶስን ለመከተል ካደረግነው ውሳኔ ቀጥሎ ያለን ከፍተኛ ውሳኔ ማንን እንደምናገባ መወሰን ነው። አንድን ሰው የማያምን ወይም ሥጋዊ ክርስቲያን ብቻ መሆኑን እያወቅን ለቤተሰብ ውርስ፥ ለመልክ፥ ለሀብት ስንል ብናገባ እጅግ አስቸጋሪና ከባድ በሆነ ሕይወት ውስጥ እናልፋለን። ዘይትና ውኃ ሊቀላቀሉ እንደማይችሉ ወይም ብርሃን ከጨለማ ጋር ሊስማማ እንደማይችል ሁሉ በዚህ ዓይነቱ ጋብቻ ውስጥ በፍጹም ስምምነት ሊኖር አይችልም (2ኛ ቆሮንቶስ 6፡14-16 ተመልከት)። በመጨረሻም ከእግዚአብሔር ጋር የነበረን ግንኙነት ይለወጥና እግዚአብሔርን በምንፈልገው መንገድ ሳናገለግለው እንቀራለን። እግዚአብሔርን ሙሉ በሙሉ ሊያከብር በማይችል ቤተሰብ ውስጥ ስለሚያድጉ ጉዳቱ ለልጆቻችንም ይተርፋል። የእግዚአብሔር ቃል ግልጽ ነው፡- የማያምን ሰው ልናገባ አይገባም። ሚስትን ወይም ባልን ለመምረጥ ዋናው መመዘኛ መንፈሳዊ ሕይወታቸው ነው። ሥጋዊ የሆነ ክርስቲያን ብናገባ የሚያጋጥመን ችግር የማያምን ሰው በማግባት ከሚገጥመን ችግር የተለየ አይደለም። ዳሩ ግን እንደ እኛው እግዚአብሔርን ለማገልገልና ለመታዘዝ ጥማት ያለውን ሰው ካገባን፥ የቤተሰቡ ውርስ ወይም ውበት ወይም ሀብት ምንም ዓይነት ቢሆን በትዳራችን ውስጥ ስምምነት፥ ሰላምና ፍቅር ይኖራል። ለ. አንድ ሰው ያገባውን ሰው መፍታት የለበትም። የሚያሳዝነው ነገር አይሁዶች ፍቺ ምንም ችግር የሚያስከትል አይመስላቸውም ነበር። እንዲያውም ኢየሱስ በኖረበት ዘመን አንዲት ሴት እንጀራ ወይም ወጥ ብታሳርር ወይም ጥሩ ምግብ ለማዘጋጀት ባትችል፥ ባሏ ሊፈታት ይችል ነበር። ፍቺ በሚፈልጉበት ጊዜ ሁሉ በዘዳግም 24፡1-4 የሚገኘውን ጥቅስ እንደ ይለፍ ፈቃድ አድርገው ይጠቀሙበት ነበር። ለእስራኤላውያን ፍቺ የሚፈቀደው በሕይወታቸው ውስጥ ባለ ኃጢአት ምክንያት ብቻ ነበር (ማቴዎስ 19፡8)። እግዚአብሔር የደገፈው አማራጭ አልነበረም። ጋብቻ ሴትና ወንድ በእግዚአብሔር ፊት የሚገቡት የተቀደሰ ቃል ኪዳን ነው። ይህም እግዚአብሔር የሚያከብረውና የሚባርከው ነው። ጋብቻ ማለት ፍጹም መጣመርና እግዚአብሔርን የሚፈሩ ልጆችን ማፍራት ማለት ነው። ሚልክያስ ሚስትን «ባልንጀራ» ብሎ ይጠራታል (ሚልክያስ 2፡14)። ይህንን አሳብ የሚገልጠው የዕብራይስጡ ቃል ሁለት እንጨቶች ሊለያዩ በማይችሉበት መንገድ በምስማር ማጣበቅን የሚያመለክት ነው። የእግዚአብሔር ፍላጎት ጋብቻን በምንመሠርትበት ጊዜ ከትዳር ጓደኛችን ጋር በአካል፥ በስሜትና በመንፈስ አንድ እንድንሆን ነው። ፍላጎቶቻችን አንድ ይሆናሉ። ዕቅዶቻችን አንድ ይሆናሉ። ኑሮአችን ፍጹም በሆነ መግባባት፥ በስምምነትና በፍቅር የተመሠረተ ይሆናል። ባል ለሚስቱ ምን ማድረግ፥ ምን ማመን ወይም ምን ማቀድ እንዳለባት ያዛታል ማለት አይደለም። በአንድነትና በኅብረት ይሠራሉ። የእስራኤልና የቤተ ክርስቲያን ባል በሆነው በእግዚአብሔርና ሚስት በሆነችው በእስራኤል ወይም በቤተ ክርስቲያን መካከል ያለው ግንኙነት ተምሳሌታዊ በሆነ መንገድ በሙላት ሊፈጸም የሚችለው የዚህ ዓይነቱ ኅብረትና ግንኙነት በተገቢው ሁኔታ ሲኖር ብቻ ነው (ኤርምያስ 2፡1-3፤ 31፡32፤ ሕዝቅኤል 16፤ ሆሴዕ 2፡1-9። እስራኤልና እግዚአብሔር የሚስትና የባል ግንኙነት እንዳላቸው የሚያሳዩ ጥቅሶች ስለሆኑ ተመልከታቸው)። አዲስ ኪዳን ፍቺ የእግዚአብሔር ፈቃድ እንዳልሆነ ያስተምረናል (ማቴዎስ 5፡31-32፤ 19፡1-10፤ ማርቆስ 10፡1-10፤ ሮሜ 7፡13፤ 1ኛ ቆሮንቶስ 7፡10-16፥ 39)። የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ብዙ ክርስቲያኖች ሚስት ወይም ባል በሚመርጡበት ጊዜ የተሳሳተ መመዘኛ የሚጠቀሙት እንዴት ነው? ለ) ወንድ ወይም ሴት የትዳር ጓደኛ በሚመርጡበት ጊዜ ሊጠቀሙበት የሚገባ አንዳንድ መመዘኛዎችን ዘርዝር። ሐ) ከላይ የጠቀስነው እግዚአብሔር ለጋብቻ ያለው ዓላማ የሚፈጸመው በጥቂት ክርስቲያናዊ ጋብቻዎች ብቻ የሚሆነው ለምን ይመስልሃል? 3. ነቢዩ ኤልያስ (ሚልክያስ 4፡5-6)፡- ትንቢተ ሚልክያስ የሚጠቃለለው የነቢዩ ኤልያስን መምጣት እንዲጠባበቁ ለእስራኤል ሕዝብ በመንገር ነው። የዚህ ነቢይ መምጣት «የጌታን ቀን» የሚቀድም ሲሆን፥ የልጆችን ልብ ወደ አባቶች ይመልሳል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ኤልያስ የእግዚአብሔር ነቢይ ማለት ምን ማለት እንደሆነ የሚገልጽና ከሌሉች ነቢያት መካከል አብዛኛዎቹ የተከተሉት ዐቢይ ምሳሌ ነበር። ምክንያቱም፡- ሀ) ኤልያስ የሃይማኖትና የፖለቲካ መሪዎችን በድፍረት በመቃወም፥ ከአባቶቻቸው እምነት ዞር በማለታቸው፥ በሥነ ምግባር ጉድለታቸውና ማኅበራዊ ፍትሕን በማዛባት ኃጢአታቸው ወቅሶአቸዋል።  ለ) ኤልያስ ንስሐ የመግባትን አስፈላጊነት፥ ይህ ካልሆነ ግን ሰው የእግዚአብሔር ፍርድ እንደሚጠብቀው በግልጽ አስተምሯል።  ሐ) የኤልያስ መልእክቶች እውነትነት በተአምራት የተረጋገጠ ነበር። መ) ኤልያስ ከሃይማኖት መሪዎች አንዱ አልነበረም፤ ዳሩ ግን ከተመሠረተው ሃይማኖታዊ መዋቅር ውጭ ሆኖ ሕዝቡ ወደ እውነተኛ ሃይማኖት እንዲመለሱ ለማድረግ ሠራ። ኢየሱስ በተራራ ላይ በተለወጠ ጊዜ ከሙሴና ከኤልያስ ጋር ተገናኝቶ ነበር (ማቴዎስ 17፡1-8)። ሙሴ ሕግን፥ ኤልያስ ደግሞ ነቢያትን የሚወክሉ ሲሆን፥ ሁለቱም የመሢሑን መምጣት የሚያመለክቱ ነበሩ። የእነርሱ መገለጥ ኢየሱስ ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት የነበሩት የሕግና የነቢያት ፍጻሜ መሆኑን ማሳየት ነበር። ሚልክያስ በዚህ ስፍራ የተናገረው፥ አንድ ቀን ኤልያስን የሚመስል ሰው እንደሚመጣ ነው። የእርሱ መምጣት ከመጨረሻዎቹ ቀናትና ከመሢሑ መምጣት በፊት ይሆናል። ሚልክያስ ይኖር በነበረበትና መጥምቁ ዮሐንስ በተነሣበት ዘመን መካከል በነበሩት 400 ዓመታት ውስጥ አይሁድ ስለዚህ ኤልያስ የነበራቸው ወግ ዕድገት እያሳየ መጥቶ ነበር። ይህ የኤልያስ ተምሳሌት ይሁን ወይም የኤልያስ ከሞት ተነሥቶ መምጣት የሚያውቁት ነገር አልነበረም። መጥምቁ ዮሐንስ በመጣ ጊዜ በአለባበስና በመልእክቱ እነርሱ የሚጠብቁትን ኤልያስ ይመስል ነበር። ብዙ ሕዝብ ወደ መጥምቁ ዮሐንስ የመጡበትና በእርሱ ያመኑበት አንዱ ምክንያት ይህ ነበር። በኋላ ጌታ ኢየሱስ መጥምቁ ዮሐንስ ይህን ትንቢት እንደፈጸመ ተናገረ (ማቴዎስ 11፡7-15)። ብዙ ምሁራን ከዘመናት መጨረሻ ጥቂት ቀደም ብሎ የሚመጣ ሌላ “ኤልያስ” አለ ብለው ያስባሉ። ይህ ሰው ከዘመኑ ፍጻሜ በፊት ሕዝቡን ለንስሐ የሚጋብዝ የመጨረሻ መልእክተኛ ይሆናል። በራእይ 11፡1-12 ከምናያቸው ሁለት ነቢያት አንዱ ኤልያስን የሚመስል ነቢይ ነው ብለው ያስባሉ። የውይይት ጥያቄ፥ ክርስቲያኖች እነዚህን እውነቶች ሊያውቋቸውና ሊታዘዟቸው አስፈላጊ የሚሆነው ለምንድን ነው? የውይይት ጥያቄ፥ ሚልክያስ 1-4 አንብብ። ሀ) አይሁድ ለእግዚአብሔር ያቀረቧቸውን የተለያዩ ጥያቄዎች ዘርዝር። ለ) እግዚአብሔር እነዚህን ጥያቄዎች የመለሰላቸው እንዴት ነበር? ሐ) ከእነዚህ ጥያቄዎችና ትምህርቶች አብዛኛዎቹ በዚህ ዘመን ላሉ ክርስቲያኖች ጠቃሚ የሚሆኑት እንዴት ነው? እግዚአብሔር ለቤተ ክርስቲያን መሪዎች ከሰጣቸው ኃላፊነቶች አንዱ፥ ለእግዚአብሔር ሕዝብ «ነቢይ» የመሆን ኃላፊነት ነው። ይህን ስል የእግዚአብሔር ሕዝብ ኃጢአታቸውን እንዲያዩ ማድረግና የተሳሳተ ዝንባሌያቸውን ሁሉ በግልጽ መቃወም አለባቸው ማለቴ ነው። እግዚአብሔር በረከቱን ያለማቋረጥ እንዲሰጥ የእግዚአብሔር ሕዝብ ንጹሕ አምልኮና ኑሮ እንዲኖሩ የማስተማርና የማበረታታት ኃላፊነት አለባቸው። እግዚአብሔር የሕዝቡን ንጽሕና ጠብቆ ለማቆየት በቤተ ክርስቲያን መሪዎች እንዴት እንደሚጠቀም የሚያሳይ ጥሩ ምሳሌ ሚልክያስ ነው። ሚልክያስ በሕዝቡ ሕይወት ውስጥ ያሉትን ችግሮች የሚጠቁሙ አጫጭር መልእክቶችን በመጽሐፉ ውስጥ አቅርቧል። ብዙ ጊዜ የሚጀምረው እውነታን ወይም ጭብጥን የያዙ አጫጭር ዐረፍተ ነገሮችን በማቅረብ ሲሆን፥ ሕዝቡ ከእነዚህ ዐረፍተ ነገሮች በመነሣት እግዚአብሔርን ይጠይቃሉ።  1.1ኛ ጥያቄ፥ እግዚአብሔር እኛን የወደደን እንዴት ነው? (ሚልክያስ 1፡1-5)  ሰዎች ሁሉ የኢኮኖሚ ችግር ወይም በሥጋቸው ላይ ጉዳት የሚያደርስ ነገር ሲገጥማቸው የሚሰጡት ምላሽ ከሚከተሉት ሁለት ነገሮች አንዱን ነው:- አንዳንዶች ትከሻቸውን በመስበቅ ይህንን ችግር በሕይወቴ ላይ ያመጣ እግዚአብሔር ስለሆነ ምንም ማድረግ አልችልም ይላሉ። ሌሎች ደግሞ ወደ አለማመንና የተጣመመ ትርጉም ወደ መስጠቱ በመቻኰል የእግዚአብሔርን ፍቅር በጥያቄ ምልክት ያስቀምጡታል። አይሁድ ተጠራጣሪና ጠማማ በሆን ልባቸው ወደ እግዚአብሔር በመመልከት፥ እርሱ በእርግጥ ይወዳቸው እንደሆነ መጠየቅ ጀምረው ነበር። እግዚአብሔር ለእነርሱ ያለውን ፍቅር ለማረጋገጥ

የትንቢተ ሚልክያስ ዐበይት ትምህርቶች Read More »

የትንቢተ ሚልክያስ አስተዋጽኦ እና ዓላማ

የትንቢተ ሚልክያስ አስተዋጽኦ የውይይት ጥያቄ፥ ) ስለሚልክያስ ከመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት አንብብ። ለ) በዚህ ስፍራ ስለ ሚልክያስ የተጠቀሱትን ዐበይት እውነቶችን ዘርዝር። ሚልክያስ የተጻፈው እጅግ ልዩ በሆነ መንገድ ነበር። በመጀመሪያ አብዛኛው የመጽሐፉ ክፍል የተጻፈው ሚልክያስ እግዚአብሔርን ወክሎ እንደሚናገር ሳይሆን፥ እግዚአብሔር ራሱ ለእስራኤላውያን በቀጥታ እንደሚናገር ሆኖ ነው። በመጽሐፉ አብዛኛ ክፍል ውስጥ እግዚአብሔር ለአይሁድ የሚናገረው «እኔ» የሚለውን ተውላጠ ስም በመጠቀም ነው። በሁለተኛ ደረጃ፣ ሚልክያስ በጽሑፉ የተጠቀመው ልዩ የሆነ የአጻጻፍ ሥልትን ነው። አብዛኛዎቹ መልእክቶቹ የሚከተለውን አደረጃጀት የተከተሉ ናቸው፡- ሀ. እግዚአብሔር ስለ ራሱ ወይም ስለ እስራኤላውያን መንፈሳዊ እውነትን ይናገራል። ለ. ቀጥሉ እስራኤላውያን በዚህ የእግዚአብሔር ንግግር ላይ ተመሥርተው የሚያነሡት ጥያቄ በመላ ምት ይቀርባል።  ሐ. እግዚአብሔር፥ ጥያቄአቸው ትክክል አለመሆኑን በሚያስረዳ መንገድ ለእስራኤላውያን ጥያቄ መልስ ይሰጣል። መ. እግዚአብሔር ለተናገረው ቃል ማረጋገጫ ያቀርባል። የውይይት ጥያቄ፥ ሚልክያስ 1፡2-5 አንብብ። በዚህ ክፍል ውስጥ እነዚህ አራት ደረጃዎች የሚታዩት እንዴት ነው? ትንቢተ ሚልክያስ መልእክቱን የመሠረተባቸውን ስድስት ስብከቶች ይዟል። እነዚህ ስድስት መልእክቶች መልሶችን የያዙ ጥያቄዎች ሆነው ሊቀርቡ ይችላሉ።  እግዚአብሔር በሕዝቡ ላይ ያቀረበው ክስ 1ኛ ጥያቄ፡- እግዚአብሔር እኛን የወደደን እንዴት ነው? (ሚልክያስ 1፡1-5)። መልስ፡- ሀ) እግዚአብሔርን እስራኤልን የራሱ አድርጎ መርጧታል፤ ለ) እግዚአብሔር እስራኤልን ይጠብቃታል።  2ኛ ጥያቄ፡- እኛ ካህናት የእግዚአብሔርን ስም የናቅነው እንዴት ነው? (ሚልክያስ 1፡6-2፡9)። መልስ፡- ሀ) ካህናቱ እግዚአብሔርን አያከብሩም፤ ለ) ካህናቱ ለእግዚአብሔር ተገቢ ያልሆነ መሥዋዕት ያቀርባሉ፤ ሐ) ካህናቱ ለእግዚአብሔር ስም ክብር አይሰጡም፤ መ) ካህናቱ ለሕዝቡ የእግዚአብሔርን ሕግ አያስተምሩም።  3ኛ ጥያቄ፡- እኛ እስራኤላውያን ለቃል ኪዳኑ ታማኞች ያልሆንነው እንዴት ነው? (ሚልክያስ 2፡10-16)።  መልስ፡- ሀ) ሕዝቡ ሌሎች አማልክትን ከሚያመልኩ አሕዛብ መካከል ሚስቶችን አግብተዋል፤ ለ) ሕዝቡ በእግዚአብሔር ፊት በቃል ኪዳን ያገቧቸውን ሚስቶቻቸውን ፈትተዋል።  እግዚአብሔር በፍርድና በመቤዥት ወደ ሕዝቡ እንደሚመጣ ተስፋ ይሰጣል  4ኛ ጥያቄ፡- እግዚአብሔርን ያሰለቸነው እንዴት ነው? (ሚልክያስ 2፡17-3፡6)። መልስ፡- ሀ) ሕዝቡ እግዚአብሔር ጻድቅ አይደለህም ብለው ይከሱት ነበር፤ ለ) እግዚአብሔር በቃላቸውና በተግባራቸው ታማኝ ባልሆኑት ሕዝቡ ላይ ፍርድን ያመጣና ይቀጣቸዋል፤ ያነጻቸዋልም።  5ኛ ጥያቄ፡- ወደ እግዚአብሔር መመለስ የምንችለው እንዴት ነው? (ሚልክያስ 3፡7-12)። መልስ፡- ሀ) ከእግዚአብሔር መስረቅን በማቆምና ለእግዚአብሔር መክፈል የሚገባውን አሥራትና መባ በመስጠት። ለ) ለእግዚአብሔር በሚሰጡበት ጊዜ እርሱ በረከቱን ያፈስላቸዋል።  6ኛ ጥያቄ፡- በእግዚአብሔር ላይ በድፍረት የተናገርነው እንዴት ነው? (ሚልክያስ 3፡13-4፡3)። መልስ፡– ሀ) እግዚአብሔርን ማገልገል ምንም ጥቅም የለውም ብላችኋል፤ ለ) የሚያከብሩኝንና የሚታዘዙኝን አስባቸዋለሁ፤ ደግሞም እሸልማቸዋለሁ፤ ሐ) እኔን ባለመታዘዝ የማያከብሩኝን እቀጣቸዋለሁ፤ መ) «የጽድቅ ፀሐይ» በምትወጣበት ጊዜ፥ እግዚአብሔር በረከትና ፍርድን ያመጣል።  7. ለሕዝቡ የተሰጠ የመጨረሻ ግሣጹ (ሚልክያስ 4፡4-6) ሀ) የእግዚአብሔርን ሕግጋት መጠበቅን አስታውሱ፤ ለ) ሕዝቡን ለመሢሑ ለማዘጋጀት ከመሢሑ በፊት የሚመጣውን ኤልያስን ጠብቁ።  የትንቢተ ሚልክያስ ዓላማ የብሉይ ኪዳን ትምህርቶች እምብርት ቃል ኪዳንን የሚመለከት አሳብ ያዘለ ነው። እግዚአብሔር በጸጋውና በፍቅሩ የቃል ኪዳኑ ሕዝብ እንዲሆኑ እስራኤላውያንን መረጣቸው። ይህም የተጀመረው እግዚአብሔር ከአብርሃም ጋር ባደረገው ቃል ኪዳን ነበር። ይህ ቃል ኪዳን እግዚአብሔር ለአይሁድ በሲና ተራራ ቃል ኪዳን በሰጣቸው ጊዜ ሊስፋፋ ችሏል። ይህም ከካህናት፥ በኋላም ከዳዊት ጋር የተደረገውን ቃል ኪዳን ይጨምር ነበር። ቃል ኪዳኖቹ የእግዚአብሔርን ፍቅርና ጸጋ የሚያስረዱ ናቸው። የቃል ኪዳኑ ጀማሪ እርሱ ሲሆን፥ ሕዝቡ በቃል ኪዳኑ ውስጥ የሚጠበቅባቸውን ነገር ባላደረጉ ጊዜ እንኳ ሊለውጠው አልፈለገም። ይሁን እንጂ ብሉይ ኪዳን የሚያስተምረን በቃል ኪዳኑ ውስጥ የተጠቀሱትን በረከቶች ለመቀበል ለቃል ኪዳኑ ታዛዥ መሆናቸው አስፈላጊ እንደ ነበር ነው። ይህ መታዘዝ በውጫዊ ሥርዓት ብቻ የሚሆን ሳይሆን፥ ከሕዝቡ ልብ የሚመነጭ መሆን ነበረበት። እግዚአብሔር ሚልክያስን በጠራው ጊዜ ሕዝቡ በቃል ኪዳኑ ውስጥ የታዘዙትን አብዛኛዎቹን ሥርዓቶች እየተከተሉ ነበር። ዳሩ ግን እግዚአብሔርን ከልባቸው አያመልኩትም ነበር። መሥዋዕቶችንም ያቀርቡ ነበር፤ ነገር ግን ለእነርሱ የማይጠቅሙትን ሽባ ወይም ዕውር እንስሳት በመስጠት እግዚአብሔርን ያቃልሉት ነበር። እንደ ቀደምት አባቶቻቸው ጣዖትን አያመልኩም ነበር፤ ነገር ግን የእግዚአብሔር ሕዝብ የመሆናቸውን እውነታ ለመቀበልና ልባቸውን ለመለወጥ አይፈቅዱም ነበር። ስለዚህ እግዚአብሔር ነቢዩን ሚልክያስን ማስጠንቀቂያ የሚሰጣቸው የመጨረሻ መልእክተኛ አድርጎ ላከው። ሚልክያስ እግዚአብሔር ከእስራኤል ጋር በገባው ቃል ኪዳን ላይ ያተኵር ነበር። ይህ ለእስራኤላውያን የእግዚአብሔር ፍቅር ማረጋገጫ ነበር። ካህናቱ በእግዚአብሔር ፊት አገልግሎታቸውን የሚፈጽሙበት መሠረት ነበር። ሚልክያስ የቃል ኪዳኑ ውጤት በእስራኤላውያን ሕይወት ምን መሆን እንዳለበት ተመለከተ። የቃል ኪዳኑ እምብርት ወደ እግዚአብሔር የሚመለከት ትክክለኛ ዝንባሌ ነበር። ቃል ኪዳኑ እግዚአብሔርን እንደ ቅዱስነቱ በክበርና በሙሉ ሕይወታቸው እርሱን ለማክበር ባላቸው ፍላጎት ላይ መመሥረት ነበረበት። ያ አክብሮት ለእግዚአብሔር ወደሚቀርብ እውነተኛ አምልኮ ሊመራቸውና ለእግዚአብሔር የማይረባውን ሳይሆን ከሁሉም የተሻለውን መሥዋዕት እንዲያቀርቡ ሊያደርጋቸው ይገባ ነበር። መሪዎችና ሕዝቡ እርስ በርስ በመከባበር እንዲነጋገሩና በተለይም ለሚስቶቻቸው የገቡትን ቃል ኪዳን በመጠበቅ ከመፋታት እንዲታቀቡ ሊያደርጋቸው ይገባ ነበር። በእግዚአብሔር የማያምኑትን እንዳያገቡ እምነታቸውን በንጽሕና የመጠበቅ ፍላጎት ሊያሳድርባቸው ይገባ ነበር። ይህንንም እግዚአብሔር ከሰጣቸው ነገር አሥራታቸውን በታማኝነት በመስጠት ማረጋገጥ ነበረባቸው። የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) በአዲስ ኪዳን ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ቃል ኪዳን ከዚህ ጋር የሚመሳሰለው እንዴት ነው? ለ) የእግዚአብሔር የቃል ኪዳን ሕዝብ በመሆናችን ምክንያት በሕይወታችን ሊለወጡ የሚገባቸው አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው? ሐ) ክርስቲያኖች የእግዚአብሔር የቃል ኪዳን ሕዝብ እንደሆኑ የሚናገሩባቸው፥ ዳሩ ግን ለዚህ ቃል ኪዳን ባለመታዘዝ እግዚአብሔርን የማያስከብሩባቸው አንዳንድ መንገዶች የትኞቹ ናቸው? ነቢዩ ሚልክያስ በእግዚአብሔር የተጠራው አይሁድ ለቃል ኪዳኑ ታዛዦች ይሆኑ ዘንድ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ለመስጠት ነበር። እግዚአብሔር በሚልክያስ በኩል አይሁድን ስለ ኃጢአታቸው ሊወቅሳቸውና ወደ እርሱ እንዲመለሱ ሊጠራቸው ፈልጎ ነበር። ሚልክያስ ሕዝቡን፥ በተለይም የሃይማኖት መሪዎችን መሢሑ በሚመጣበት ጊዜ ስለ ኃጢአታቸው እንደሚፈርድባቸውና ለእግዚአብሔር ታማኞች የሆኑትን ደግሞ እንደሚሸልማቸው ያስታውሳቸዋል። ልዑል አባት፥ የፍጥረታት ሁሉ ጌታና የቃል ኪዳኑ መሥራች የሆነው እግዚአብሔር ሊከበር፥ ከእርሱ ጋር ግንኙነት የሚያደርጉ ሰዎች ደግሞ በቃል ኪዳኑ ውስጥ በተመለከተው መንገድ በተገቢ ሁኔታ ግንኙነት ሊያደርጉ ይገባል (ዘጸአት 20፡12፤ ዘዳግም 31፡1-10)። እግዚአብሔር ሕዝቡ ንስሐ እንዲገባና ከእርሱ ጋር የገቡትን ቃል ኪዳን እንዲያድሱ ጥሪ ያደርጋል። በዚህ መሠረት፡- ሀ) የተበላሽውን የክህነት አገልግሎት ማንጻት ነበረባቸው፤  ለ) ሥርዓታዊውን አምልኮ ሐሤትና ደስታ ወደሞላበት አምልኮ መለወጥ ነበረባቸው፤  ሐ) አሥራት በመክፈልና መሥዋዕት በማቅረብ በኩል የሚታዩትን ድክመቶች ማስተካከል ነበረባቸው፤  መ) ከሚስቶቻቸውና ከልጆቻቸው ጋር ተገቢ የሆነ ግንኙነት ሊያደርጉ ይገባቸው ነበር፤  ሠ) ከጎረቤቶቻቸው ጋር በማኅበራዊ ፍትሕ መኖር ነበረባቸው። የትንቢተ ሚልክያስ መልእክት ውጤት ምን እንደነበር አልተነገረንም። በቅድሚያ ሕዝቡ መጠነኛ የሆነ ምላሽ ሳይሰጡና ንስሐ ሳይገቡ አልቀሩም። ዳሩ ግን አይሁድ ብዙም ሳይቆዩ ወደ ቀድምው ዝንባሌያቸው ተመለሱ። ኢየሱስ በምድር ላይ ይመላለስ በነበረ ጊዜ ሕዝቡ በተለይም ፈሪሳውያን የዚህ ዓይነት ዝንባሌ ነበራቸው። የልባቸው ዝንባሌ ትክክል ባይሆንም እንኳ ይከተሉት የነበረው ሥርዓታዊ አምልኮ እግዚአብሔርን ደስ እንደሚያሰኝ አስበው ነበር። ኢየሱስ ስለነበራቸው ዝንባሌ በግልጽ እየወቀሳቸው፥ በልባቸው ተለውጠው እግዚአብሔርን በተገቢው ሁኔታ እንዲያመልኩ በነገራቸው ጊዜ ተቃወሙት፤ በመጨረሻም ሰቅለው ገደሉት። ይህ ብዙ ጊዜ በግልጽ የሚታይ እውነታ ነው። ለትምህርቶቻቸውና ለሥርዓተቸው ጥብቅና ለመቆም የሚፈልጉ የሃይማኖት መሪዎች ሁልጊዜ እውነትን ይቃወማሉ። የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) በሚልክያስ ዘመን የነበሩት ካህናትና በኢየሱስ ዘመን የነበሩት ፈሪሳውያን ያደርጉት እንደነበረው በዚህ ዘመን ያለን ክርስቲያኖች ተመሳሳይ ዝንባሌ ሊኖረን የሚችለው እንዴት ነው? ለ) የቤተ ክርስቲያን መሪዎች የሚወቀሱበትን ማንኛውንም ስሕተት ላለመቀበል የሚቃወሙትና ከዚህ ቀደም የለመዷቸውን ሥርዓቶች ለመጠበቅ የሚጥሩት ለምን ይመስልሃል? (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡) የመመዘኛ ጥያቄዎችን ለማግኘት ከታች ያለውን ሊንክ (መስፈንጠሪያ) ይጫኑ፡፡

የትንቢተ ሚልክያስ አስተዋጽኦ እና ዓላማ Read More »

የትንቢተ ሚልክያስ ታሪካዊ ሥረ-መሠረት

ትንቢተ ሚልክያስ በዕዝራና በነህምያ ታሪክ ዘመን አካባቢ የተጻፈ ነው። ከትንቢተ ሐጌና ዘካርያስ ጥናታችን እንደሚታወሰው እነዚህ ሁለቱ፥ ነቢያት አይሁዶች ቤተ መቅደሱን እንዲሠሩ ያበረታቱ ነቢያት ነበሩ። በመጨረሻ በ516 ዓ.ዓ. የቤተ መቅደሱ ሥራ ተጠናቀቀ። አይሁድ የተሰጧቸውን የተስፋ ቃላት ፍጻሜ ይጠባበቁ ነበር። መሢሑ እንደሚመጣ ቢጠባበቁም፥ መምጣቱን በሚመለከት አንዳችም ምልክት አልታየም ነበር። ከእግዚአብሔር በረከትን በመቀበል በቁሳዊ ነገሮች እንደሚበለጽጉ አስበው ነበር፤ ዳሩ ግን እስካሁን ድረስ ድሆች ነበሩ። ከአሕዛብ መንግሥታት ነፃ ለመሆንና ራሳቸውን ለመቻል ፈልገው ይጠባበቁ ነበር፤ ነገር ግን እስካሁን ድረስ በፋርስ መንግሥት ውስጥ እጅግ አነስተኛና ከቁጥር የማይገባ አንድ ክፍለ ሀገር ነበሩ፡፡ ታላቅ ሕዝብ እንደሚሆን አስበው ነበር፤ ነገር ግን ብዙ አይሁድ ወደ አገራቸው ለመመለስ ፈቃደኞች ሳይሆኑ ቀሩ። የቤተ መቅደሱን ሥራ ለመጨረስ ከነበራቸው የስሜት ምጥቀት በፍጥነት በመውረድ፣ ተስፋቸው ተሟጥጦ ቅንነት በራቀው የአሳብ ማዕበል ውስጥ ተዘፈቁ። ለእግዚአብሔር የነበራቸውን መንፈሳዊ ግለት አጡ። እግዚአብሔር እንደሚወዳቸው ማሳብ ተሳናቸው። በ458 ዓ.ዓ. በፋርስ ንጉሥ በአርጤክስስ ችሮታ ካህኑ ዕዝራ ከብዙ ሺህ አይሁድ ጋር ወደ አገሩ ተመለሰ። በእርሱ መንፈሳዊ አመራር የእግዚአብሔር ሕዝብ ንስሐ ለመግባትና ለሕጉ በመታዘዝ ለመኖር ተነቃቁ። ከአሥራ ሦስት ዓመታት በኋላ፥ ማለትም በ445 ዓ.ዓ. ነህምያ ከብዙ አይሁዶች ጋር ተመለሰና የኢየሩሳሌምን ቅጥሮች ሠራ። ሕዝቡ ቤተ መቅደሱን ይሠሩ ዘንድ እንዳስቻሉት እንደ ሐና ዘካርያስ፥ ነህምያ ሕዝቡን ሁሉ ለማሳመንና የኢየሩሳሌምን ቅጥሮች እንዲሠሩ ለማድረግ ችሎ ነበር። ከዚህም በላይ ነህምያ በይሁዳ አንዳንድ ተሐድሶዎችን ለማምጣት ችሎ ነበር። ከእነዚህም መካከል ድሆችን መርዳት (ነህምያ 5፡2-13)፥ ድብልቅ ጋብቻዎችን ማስቆም፥ ሰንበትን መጠበቅ (ነህምያ 10፡30-31) መባቸውንና አሥራታቸውን ወደ ቤተ መቅደስ ማምጣት (ነህምያ 10፡37-39) ይገኙባቸዋል። በዚህ ጊዜ ሚልክያስ ከነህምያ ጋር እየሠራ ነበር ለማለት ይቻላል። በ433 ዓ.ዓ. ነህምያ ከንጉሥ አርጤክስስ ጋር ለመሥራት ወደ ፋርስ ተመለሰ። እርሱ በሌለበት ሕዝቡ እንደገና በኃጢአት ወደቁ። ነህምያ ከብዙ ዓመታት በኋላ በተመለሰ ጊዜ ሕዝቡ አሥራታቸውን እንደማይከፍሉ፥ ሰንበትን እንደማያከብሩ፥ ከአሕዛብ ጋር እንደሚጋቡና ካህናቱም ምግባረ ብልሹዎች እንደሆኑ ደረሰበት (ነህምያ 13፡7-31)። በትንቢተ ሚልክያስ ከተጠቀሱት አንዳንድ ተመሳሳይ ኃጢአቶች መካከል እነዚህ ይገኙባቸዋል (ሚልክያስ 1፡6-14፤ 2፡14-16፤ 3፡8-11)። ስለዚህ ሚልክያስ ያገለገለው ነህምያ ወደ ፋርስ ሄዶ ሳለ ወይም በዚሁ ጊዜ ከነህምያ ጋር ሳይሆን አይቀርም። ኃጢአት እንደ ማግኔት በመሆኑ የእግዚአብሔርን ሕዝብ ያለማቋረጥ ይስባል፡፡ የእግዚአብሔር ሕዝቦች መንፈሳዊ ግዴለሽነትንና በኃጢአት የመውደቅ ዝንባሌን ያለማቋረጥ ካልተዋጉ በስተቀር፥ አያሌ ጊዜ ሳይፈጅ መንፈሳዊ ግለታቸውንና ቅድስናቸውን ይጥላሉ። በቤተ ክርስቲያን መሪዎች ራስ ላይ ከተጣሉት ብዙ ዐበይት ኃላፊነቶች አንዱ የእዚአብሔር ሕዝብ ለኢየሱስ የነበራቸውን የመጀመሪያ ፍቅር እንዲጠብቁና ዓለምን ከመምሰል ይልቅ በእግዚአብሔር ፊት የንጽሕና ሕይወት እንዲኖሩ ማበረታታት ነው። ነህምያና በሚልክያስ ጊዜ በእስራኤላውያን የተፈጸመው ነገር ዛሬም በቤተ ክርስቲያን ደግሞ ሊፈጸም ይችላል። የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) በኃጢአት የመውደቅ ዝንባሌ በምታውቃቸው ክርስቲያኖች ሕይወት ውስጥ ሲፈጸም ያየኸው እንዴት ነው? ለ) ይህን ዝንባሌ በራስህ ሕይወት ውስጥ ያየኸው እንዴት ነው? ሐ) ይህን ነገር ለማሸነፍ ምን እያደረግህ ነው? መ) የቤተ ክርስቲያን መሪ እንደ መሆንህ ሰዎች ለእግዚአብሔር ያላቸው መንፈሳዊ ግለት ከፍተኛ እንዲሆንና የቤተ ክርስቲያን አባሎች በኃጢአት እንዳይወድቁ ምን ማድረግ ትችላለህ? (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡) የመመዘኛ ጥያቄዎችን ለማግኘት ከታች ያለውን ሊንክ (መስፈንጠሪያ) ይጫኑ፡፡

የትንቢተ ሚልክያስ ታሪካዊ ሥረ-መሠረት Read More »

ትንቢተ ሚልክያስ መግቢያ

የብሉይ ኪዳንን የትንቢት መጻሕፍት በምናጠናበት ጊዜ ሁሉ ሕዝቡ የወደፊቱን ነገር በተስፋና በጉጉት ይጠብቁ እንደነበር ተመልክተናል። ምንም እንኳ የእግዚአብሔር ሕዝብ በስደትና በመከራ ውስጥ ቢሆኑ ወይም አይሁድ በምድር ዙሪያ ሁሉ ተበትነው የሚኖሩ ቢሆኑም የእግዚአብሔር ቃል የወደፊቱን ነገር እንዲመለከቱ ያበረታታቸው ነበር፡፡ በብሉይ ኪዳን ውስጥ ከሚገኙ የወደፊት ተስፋዎች መካከል አይሁድ ይጠብቁት የነበረው ዋና ተስፋ የመሢሑን መምጣት ነበር። የእስራኤል ንጉሥና የምድር ሁሉ ገዥ እንደመሆኑ ለእግዚአብሔር ሕዝብ ሁሉንም ነገር ያስተካክላል። ይህ ቃል ኪዳን በጨለማ ውስጥ እንደሚበራ ብርሃንና በትልቅ ችግር ውስጥ እንደሚሰማ አበረታች የተስፋ ቃል ነበር። የመጨረሻው የብሉይ ኪዳን መጽሐፍ ትንቢተ ሚልክያስ ስለ መሢሑ መምጣትና ከእርሱ በፊት ስለሚመጣው ኤልያስ የተስፋ ቃል በማስተላለፍ ይጠቃለላል። እግዚአብሔር ከሚልክያስ በኋላ አዳዲስ ትንቢቶቹን የሚናገሩ ነቢያት አልላከም። እነዚህም ዓመታት 400 የጸጥታ ዓመታት በመባል ይታወቃሉ። በእነዚህ 400 ዓመታት አይሁዶች የተሰጣቸውን ተስፋ ፍጻሜ ሲጠባበቁ ኖረዋል። ከ400 ዓመታት በኋላ ግን በሚልክያስ እንደተተነበየው በድንገት በምድረ በዳ የሚጮህ ሰው ድምፅ የተባለለት መጥምቁ ዮሐንስ የነቢያት መልእክት ይፈጸም ዘንድ የጊዜውን መድረስ በሚመለከት አዋጅ መናገር ጀመረ። መሢሑ መጣ። በብሉይ ኪዳን ሲጠበቁ የነበሩ ነገሮች በሙሉ መፈጸም ነበረባቸው። የሚያሳዝነው ነገር፥ መሢሑ፥ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በመጣ ጊዜ ሕዝቡ ሊቀበሉት አልተዘጋጁም ነበር፤ ስለዚህ ሳይቀበሉት ቀሩ። አዲስ ኪዳን ይህንን የተስፋ ላይ ሐረግ ከብሉይ ኪዳን ቀጥሎአል። ዳሩ ግን የመጀመሪያ አመጣጡን ከልብ በማመን ምትክ ኢየሱስ ዳግም በሚመለስበት ጊዜ ያተኩራሉ። በዚያን ጊዜ በፍጥረታት ሁሉ ላይ በመግዛት፥ በብሉይ ኪዳን ውስጥ የተጻፉትን የበረከት ተስፋዎች በሙሉ ይፈጽማል። የኢየሱስ ክርስቶስን መመለስ የሚመለከተው ተስፋ ለእኛ ለክርስቲያኖች በስደት ጨለማ ውስጥ በምንሆንበት ጊዜ ብርሃን የሚሆነን «ተስፋ» ነው። ክርስቲያኖች በኢየሱስ ዳግመኛ መምጣት ቃል እርስ በእርስ እንድንጽናና ታዘናል (1ኛ ተሰሎንቄ 4፡13-18)። ክርስቲያኖች በዚህ በሚያልፍ የዓለም ነገር ላይ እምነታቸውንና ተስፋቸውን መጣል ጨርሶ የለባቸውም። ዜግነታቸው ሰማያዊ መሆኑን፥ ወደ መንግሥተ ሰማያት በመጓዝ ላይ ያሉ መናንያን መሆናቸውን፥ የእግዚአብሔር በረከት በሙላት የሚፈጸመው በሰማይ እንደሆነ ዘወትር ሊያስታውሱ ይገባል። የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ክርስቲያኖች በከባድ ችግርና መከራ ውስጥ በሚሆኑበት ጊዜ ኢየሱስ ሲመለስ የሚያገኙትን ብሩህ ፍጻሜ፥ ተስፋ ማድረግ የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው? ለ) ኢየሱስ ሲመለስ የሚፈጸሙልንን አንዳንድ የተስፋ ቃሎች ዘርዝር? ሐ) ክርስቲያኖች ወደ ሰማይ አገራቸው በሚደርሱበት ጊዜ ሊፈጸምላቸው ከተገባላቸው ተስፋ ይልቅ በዚህ ምድር ሊቀበሏቸው ባሉት በረከተች ላይ ብዙ ጊዜ የሚያተኩሩባቸውን አንዳንድ መንገዶች ዘርዝር።  የትንቢተ ሚልክያስ ጸሐፊ ምንም እንኳ መጽሐፈ ዜና መዋዕል፥ ዕዝራና ነህምያ ከሚልክያስ በኋላ ሊጻፉ ቢችሉም፥ በብሉይ ኪዳን ውስጥ የእግዚአብሔርን ቃል የጻፈ የመጨረሻ ነቢይ ሚልክያስ ነበር። በመጽሐፉ ጸሐፊ ማንነት ላይ ምሁራን የተለያዩ አሳቦች አሏቸው። ስለዚህ ጉዳይ ሁለት ዐበይት አመለካከቶች አሉ፡- 1. በዕብራይስጥ «ሚልክያስ» የሚለው ስም ትርጉም «መልእክተኛዬ» ማለት ነው። ይህ ቃል አንዳንድ ጊዜ ነቢያትን፥ ካህናትንና መላእክትንም እንኳ ለመግለጥ የሚጠቅም ነበር። ስለዚህ ብዙ ምሁራን ሚልክያስ 1፡1 «የእግዚአብሔር ቃል ለእስራኤል በመልእክተኛው በኩል መጣ» ተብሎ መተርጐም አለበት ይላሉ። ይህ መልእክተኛ (ነቢይ) ማን እንደሆነ አይታወቅም። በአብዛኛዎቹ የነቢያት መጻሕፍት በተለየ ሁኔታ፥ ነቢዩ መቼ እንደኖረና የእግዚአብሔርን ቃል እንደተናገረ ወይም የማን ልጅ እንደሆነ የሚገልጹ የተለመዱ እውነቶች አልተሰጡም። ይህም ትንቢተ ሚልክያስ የተጻፈው በአንድ ባልታወቀ የእግዚአብሔር መልእክተኛ ነው የሚለውን አሳብ ይደግፋል። የሴፕቱዋጀንት ትርጉም የሚልክያስን ስም ሳይጠቅስ የእግዚአብሔር ቃል በመልእክተኛው በኩል እንደተላለፈ አድርጎ ይህን ጥቅስ ይተረጉማል። 2. ሌሎች ምሁራን ደግሞ ጸሐፊው “ሚልክያስ” ተብሎ ከመጠራቱም፥ መልእክቶቹን ያሰፈረው ራሱ ሚልክያስ ወይም ሌላ አንድ ጸሐፊ ነው ይላሉ። ከዚህ ሌላ ስለሚልክያስ የምናውቀው ምንም ነገር የለም። የአይሁድ ትውፊት ሚልክያስ የኖረው በሐጌና በዘካርያስ ዘመን እንደነበር ይናገራል። ሚልክያስ የታላቁ ምኩራብ የጸሐፍት ጉባኤ አባላትና ከባቢሎን ምርኮ በኋላ ለአይሁድ የሃይማኖት ሕይወት እውቅና ለመስጠት እገዛ ካደረጉት የአይሁድ መሪዎች አንዱ ነበር ይላሉ።  ትንቢተ ሚልክያስ የተጻፈበት ጊዜ ሚልክያስ ይህን መጽሐፍ መቼ እንደጻፈው ስለማይናገር በይሁዳ ያገለገለው መቼ እንደሆነ መጽሐፉን በመመርመር መረጃ ማግኘት አለብን። አሁንም ምሁራን በዚህ ጉዳይ ላይ ያላቸው አሳብ የተለያየ ነው። አንዳንዶች ሚልክያስ የኖረውና ያገለገለው ዕዝራና ነህምያ በኖሩበት ዘመን ነው ይላሉ (450-430 ዓ.ዓ.)። በሚልክያስና በነህምያ ዘመን የነበረውን የአይሁዶች መንፈሳዊ ሁኔታ ብንመረምር ተመሳሳይ ነበረ። ለምሳሌ በሦስቱም መጻሕፍት ማለት በዕዝራ፥ በነህምያና በሚልክያስ ከአሕዛብ ጋር የተደረጉ ጋብቻዎች ችግር፥ ድሆችን ያለ አግባብ መበደል፥ ሰንበትን ባለማክበር ለሕግ ተገዥ አለመሆንና የቤተ መቅደሱ አገልግሎት ችላ መባል በጋራ ከተጠቀሱ ነገሮች ጥቂቶቹ ነበሩ። ሌሎች ምሁራን ግን የዕብራይስጡን የአጻጻፍ ስልትና ሌሎች የቋንቋ ጉዳዮችን በመመልከት ሚልክያስ የተጻፈው ቀደም ሲል ዕዝራ ወደ ይሁዳ ከመምጣቱ በፊት ነው ይላሉ፤ የተጻፈውም ከ500-475 ዓ.ዓ. ነው ብለው ያስባሉ።  ትንቢተ ሚልክያስ የተጻፈው ከ475-425 ዓ.ዓ. ባለው ጊዜ ነው ማለት ከሁሉም የተሻለ አሳብ ነው። (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡) የመመዘኛ ጥያቄዎችን ለማግኘት ከታች ያለውን ሊንክ (መስፈንጠሪያ) ይጫኑ፡፡

ትንቢተ ሚልክያስ መግቢያ Read More »