መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን

የመኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን መጽሐፍ ዓላማ

ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው፥ መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞንን ልንረዳባቸው የምንችልባቸው በርካታ መንገዶች አሉ። የመጽሐፉ ዓላማ የሚወሰነው መጽሐፉ በሚተረጐምበት መንገድ ነው። ይህን መጽሐፍ በምንተረጕምበት ጊዜ ልንጠነቀቅባቸው የሚገቡ ሁለት ከፍተኛ ደረጃዎች ይኖራሉ። የመጀመሪያው መጽሐፉ ሙሉ በሙሉ ዓለማዊ የሆነና ስለ ፍቅር አሳፋሪ በሆነ መንገድ የሚናገር ነው በለሚል ብዙ ክርስቲያኖች ሐፍረት ስለሚሰማቸው ይህንን መጽሐፍ ከማጥናት ይቈጠባሉ። እንዴት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደተካተተ በማሰብም ይገረማሉ። ሁለተኛው ከፍተኛ ደረጃ ደግሞ፥ መጽሐፉን ከመጠን በላይ መንፈሳዊ ማድረግና የሚሰጠው ትርጕም ግጥሙ ከያዛቸው ነገሮች ጋር አንዳችም ግንኙነት የሌለው አድርጎ ማቅረብ ነው። አንዳንድ ክርስቲያኖች፥ እያዳንዱን የአነጋገር ዘይቤ ስለ እግዚአብሔርና እርሱ ለእኛ ስላለው ፍቅር የሚገልጽ ነው ብለው እስከ መገመት ይደርሳሉ። ይህም በተርጓሚው አመለካከት ብቻ የሚታይና በእውነታ ላይ ያልተመሠረተ ግምታዊ አተረጓጐምን ወደ መከተል ይመራል። ለመጽሐፉ የምንሰጠው ማንኛውም ትርጒም በእነዚህ ሁለት አመለካከቶች መካከል ሚዛናዊ ሆኖ መቅረብ አለበት። ይህን የጥናት መጽሐፍ በጻፈው ሰው አመለካከት፥ የመኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞንን ትርጕም በሁለት ደረጃ ማየት ከሁሉ የተሻለ ነው። 1. ለማንኛውም ዓይነት አተረጓጐም ልዩ ክብደት ከመስጠታችን በፊት፥ በቅድሚያ ለመጽሐፉ ታሪክ ልዩ ትኵረት መስጠት አለብን። ታሪኩ የፍቅር መዝሙር ሲሆን፥ በባልና ሚስት መካከል ሊኖር ስለሚችልና መኖርም ስላለበት የግንኙነትና የፍቅር ውበት ምሳሌ ነው። ይህ ፍቅር በመጨረሻ በፍትወተ ሥጋ ግንኙነት ይገለጣል። በባልና ሚስት መካከል የሚደረግ የግብረ ሥጋ ግንኙነት ንጹሕና መንፈሳዊ እንዳልሆነ የሚመስላቸው ብዙ ሰዎች አሉ። በእግዚአብሔር ፊት መልካም ያልሆነና ልጆችን ለማፍራት ብቻ የሚደረግ ነገር አድርገው ይገምቱታል። ይህ አመለካከት በካቶሊክና በኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት የሚገኙ አንዳንድ ሃይማኖታዊ መሪዎች ስለ ጋብቻ ያላቸው አመለካከት ዝቅተኛ እንዲሆንና ሳያገቡ መኖርን እንደ ከፍተኛ ብቃት እንዲቈጥሩ አድርጓቸዋል፤ ዳሩ ግን ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት አይደለም። እግዚአብሔር የመጀመሪያዎቹን ሰዎች ወንድና ሴት አድርጎ በአምሳሉ ፈጥሯቸዋል (ዘፍጥ. 1፡27)። የጾታ ባሕርያቸውን በመወሰን፥ በጋብቻ ውስጥ በሚፈጸም የግብረ ሥጋ ግንኙነት ደስ እንዲላቸው አስቀድሞ አቀደ። እርቃናቸውን ባያቸው ጊዜ እንኳ «መልካም» እንደነበሩ ተናግሯል። በመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት፥ የግብረ ሥጋ ግንኙነት በጋብቻ መጣመር ውስጥ እስከሆነ ድረስ መልካም ነው። ጋብቻ ክቡር ነው (ምሳሌ 18፡22፤ ዕብ. 13፡4። መጽሐፍ ቅዱስ የሚከለክለው የግብረ ሥጋ ግንኙነትን ከጋብቻ ውጭ በመፈጸም፥ ክቡር የሆነውን ግንኙነት ማበላሸትን ነው (ዘጸ. 20፡14፤ ዘሌ. 18፡22፤ ማቴ. 5፡27-28፤ 1ኛ ቆሮ. 6፡13፥ 18)። ሁለት ሰዎች ከመጋባታቸው በፊት የሚያደርጉት ማንኛውም የግብረ ሥጋ ግንኙነትና ከጋብቻ ውጭ የሚደረግ የግብረ ሥጋ ግንኙነት አጥብቆ የተከለከለ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ፥ የተሳሳተ የግብረ ሥጋ ግንኙነት የሰው ልጅ በኃጢአት የመውደቅ ምልክትና በጋብቻ ውስጥ ብቻ የተቀደሰውን ነገር እንደማጥፋት ተደርጎ ተወስዷል (ለምሳሌ፡- ሮሜ 1፡24-32)። መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን በዚህ የግብረ ሥጋ ግንኙነት ባልና ሚስት ደስ ሊሰኙበት እንደሚገባ ይናገራል (መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን 6፡2-3፤ 7፡10-13፤ 8፡1-3)። የግብረ ሥጋ ግንኙነት የሚፈቀደው ለተጋቡ ሰዎች ብቻ ነው (መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን 4፡12 ተመልከት)። የግብረ ሥጋ ግንኙነት የሥጋዊ ፍላጎት ውጤት ከመሆን ይልቅ በባልና ሚስት መካከል ሊኖር የሚገባው የፍቅር ግንኙነት ውጤት መሆን አለበት (መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን 6፡2-3፣ 7፡10-13)። በባልና ሚስት መካከል የጠለቀ የፍቅር ግንኙነት ከሌለ፥ እግዚአብሔር አስቀድሞ በባልና ሚስት መካከል እንዲኖር ያቀደው የአእምሮ፥ የመንፈስና የአካል ውሕደት ጭምር ግቡን ሳይመታ ይቀራል። በዚህ ሁኔታ የግብረ ሥጋ ግንኙነት እንስሶች ከሚያደረጉት ነገር ያልተለየ አካላዊ እንቅስቃሴ ይሆናል። የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ብዙ ሰዎች የግብረ ሥጋ ግንኙነት በጋብቻ ውስጥ ስላለው ስፍራ ካላቸው አስተሳሰብ ይህ ትምህርት የሚለየው እንዴት ነው? ለ) ይህ ነገር ይሟላ ዘንድ ባሎች ስለሚስቶቻቸው ካላቸው አስተሳሰብ ውስጥ ሊለውጡት የሚገባው ምንድን ነው? በጋብቻ የተጣመሩ ሰዎች መኃልየ መኃልይን በማንበብ አንዳቸው ለሌላቸው ያላቸው ፍቅር ጥልቅ መሆን እንደሚገባው ቢመለከቱ ብዙውን ጊዜ ጠቃሚ ነው።  2. በአንድ በኩል መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን ሀ) በእግዚአብሔርና በእስራኤል፥ ደግሞም ለ) በክርስቶስና በቤተ ክርስቲያን መካከል ያለውን ግንኙነት የሚገልጽ ሥዕላዊ ሁኔታ ነው። ለዚህ ነው አይሁዳውያን እንዲረዱት እግዚአብሔር መኃልየ መኃልይን በቡሉይ ኪዳን ውስጥ እንዲጠቃለል ያደረገው። በብሉይ ኪዳን፥ እስራኤል ብዙ ጊዜ ከሙሽራ ጋር ትነጻጸር ነበር (ለምሳሌ፡- ኢሳይያስ 50፡1፤ 54፡4-5፤ ሕዝቅኤል 16፡23፤ ሆሴዕ 1-3)። ማንኛውም የጣዖት አምልኮ እንደ ማመንዘር ይታይ ነበር። ለእስራኤላውያን መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን በእግዚአብሔርና በሕዝቡ መካከል ሊኖር የሚገባው የፍቅር ጥልቀት ምሳሌ ነው። አንድ ሰው ይህ ግጥም ሦስት ባሕርያት አሉት የሚለውን አመለካከት ከያዘ፥ ሴቲቱ እስራኤልን፥ እረኛው እግዚአብሔርን የሚወክሉ ሲሆን፥ ሰሎሞን ደግሞ በእግዚአብሔርና በእስራኤል መካከል የሚኖረውን የፍቅር ግንኙነት ለማበላሸት የሚጥረውን ዓለምን ይወክላል። ሴቲቱ ከሰሎሞን ጋር ለመዋሐድ እሺ ብትል ኖሮ በኤኮኖሚ በኩል የሚበጃት ቢሆንም ቅሉ አሻፈረኝ በማለቷ እስራኤል ለእግዚአብሔር ሊኖራት የሚገባውን ታማኝነት የሚያመለክት ነበር። ሌሉች አማልክት ወይም ሕዝቦች የእርሷን ታማኝነት የቱንም ያህል ቢሹም እንኳ ለእግዚአብሔር ታማኝ መሆን ነበረባት። በታሪኩ ውስጥ ሰሎሞንና ሴቲቱ ብቻ አሉ በሚለው አመለካከት ግን ሰሎሞን የእግዚአብሔር፥ ሴቲቱ የእስራኤል ምሳሌ ናቸው። አዲስ ኪዳን ይህንን የጋብቻ ተምሳሌት በመጠቀም፥ ክርስቶስ ሙሽራው፥ ቤተ ክርስቲያን ደግሞ ሙሽራይቱ እንደሆነች ይናገራል። የውይይት ጥያቄ፥ ኤፌ. 5፡23-33፤ ራእይ 19፡7፤ 21፡2፥ 9-10፤ 22፡17 ተመልከት። ሀ) በእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ የክርስቶስ ሙሽራ ተብለው የተጠሩት ነገሮች ምንድን ናቸው? ለ) ምድራዊ የሆነው ጋብቻ ከክርስቶስ ጋር ካለን ግንኙነት ጋር የተነጻጸረው እንዴት ነው? ብዙ ሰዎች በክርስቶስና በቤተ ክርስቲያን መካከል ያለው ግንኙነት የመጣው በአንድ ወንድና በአንዲት ሴት መካከል ከሚኖር የጋብቻ ግንኙነት ተምሳሌት የሆነ ይመስላቸዋል፤ ነገር ግን ምድራዊው ጋብቻ በእግዚአብሔር በራሱ መካከል ከነበረው ግንኙነት ተምሳሌት እንደተከሠተ ማሰቡ የተሻለ ይመስላል።  (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የመኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን መጽሐፍ ዓላማ Read More »

የመኃልየ መኃልይ ትርጕም እና አስተዋጽኦ

የመኃልየ መኃልይ ትርጕም ምሁራን ይህ መኃልየ መኃልይ እንዴት መተርጐም እንዳለበት ለመወሰን ሞክረዋል። ይሁን እንጂ መጽሐፉን መረዳት ስለሚችሉበት መንገድ ለመስማማት አልቻሉም። በዚህም ምክንያት መጽሐፉ ሲተረጐም የቆየባቸው አያሌ የተለያዩ መንገዶች አሉ። እንዲሁም ይህን መጽሐፍ መተርጐም እጅግ አስቸጋሪ የሆነበት ሦስት ምክንያቶች አሉ፡- 1. የመጽሐፉ ርእሰ-ጉዳይ የሆነው የሁለት ግለ ሰቦች ፍቅርና በመጽሐፉ ውስጥ የምናየው የቋንቋ አጠቃቀም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መኖር ያለበት ዓይነት አይመስልም። ስለ ፍትወተ-ሥጋ የሚናገር እንጂ የሥነ-መለኮት ትምህርት እውነቶችን የሚያስተምር አይመስልም።  2. መጽሐፉን ራሱ ለመረዳት ቀላል አይደለም። በመጽሐፉ ውስጥ ያሉት አብዛኛዎቹ ቃላት ግልጽ ያልሆኑና ያልታወቁ ትርጒሞች ያሏቸው ናቸው። እንደ እውነቱ መጽሐፉ የሚናገረው ስለ ሁለት ይሁን ወይም ስለ ሦስት ሰዎች ግልጽ አይደለም። አንዳንዶች መጽሐፉ የሚናገረው ስለ ሰሎሞንና ስለ ሱላማጢሲቱ ሴት ፍቅር ነው ሲሉ፥ ሌሎች ደግሞ በታሪኩ ውስጥ የሚገኙት ሰዎች ሦስት ናቸው፤ እነርሱም:- በአንድ በኩል ሴትየዋን ወደ እልፍኙ ሊያስገባት የቃጣው ንጉሥ ሰሎሞን ሲሆን፥ በሌላው በኩል ደግሞ የሴትየዋ የመጀመሪያ ወዳጅ የሆነውና በፍቅሩም ሊማርካት የቻለው ፍቅረኛዋ እረኛ አለ በሦስተኛ በኩል ደግሞ ሰሎሞንን ለማግባት ተቃርባ የነበረችው ነገር ግን መጨረሻ ላይ እረኛውን ያገባችው ሱላማጢሲቱ ሴት ነበረች። የታሪኩም ትርጕም እንደስሜታችን ሊለያይ ይችላል። እዚህ ላይ ሰሎሞን የቀረበው በመልካም ነው ወይስ በክፉ አስተሳሰብ በሚለው ስሜት ላይ የተመረኮዘ ይሆናል ማለት ነው። 3. ታሪኩ የተፈጸመበትን ጊዜና ቦታ አናውቅም። መዝሙሩ የቀረበው ሰሎሞን አንዲትን ሴት በፍቅሩ ለማሸነፍ በመቻሉ እንደ ሠርግ መዝሙር ሆኖ ነውን? ወይስ ሰሎሞን ባሉት ሚስቶቹ ላይ ሌላ ሴት ለመጨመር ባደረገው መከራ የታየበትን ሞኝነት ለመግለጥ ነው? ይህ መዝሙር የተተረጐመባቸው ስድስት መንገዶች አሉ። የመጀመሪያዎቹን ሦስት የአተረጓጐም መንገዶች የማይቀበሉት የመጽሐፍ ቅዱስን እውነተኛነት የማያምኑ ሰዎች ናቸው። እነዚህም ሦስት መንገዶች መጽሐፉን ለመተርጐም ተቀባይነት የሌላቸው ናቸው። እነርሱም፡- 1. ታሪኩ ልብ ወለድ ሲሆን፥ የተጻፈውም ለእስራኤል ነገሥታት መዝናኛ ይሆን ዘንድ በተውኔት (ድራማ) መልክ እንዲቀርብ ነው።  2. ታሪኩ የተወሰደው ከከነዓናውያን እምነት ሲሆን፥ በሁለት አማልክት መካከል ስላለ ፍትወተ-ሥጋ ግንኙነት የሚናገር አፈ ታሪክ ነው።  3. መዝሙሩ የሠርግ መዝሙር ሲሆን፥ የሚዘመረው ለሙሽራዪቱና ለሙሽራው ፍቅር አክብሮት ለመስጠት ነበር። የሚዘመረውም በሠርግ በዓል ላይ ነበር።  የመጨረሻዎቹ ሦስት የአተረጓጐም መንገዶች ግን በክርስቲያኖችና በአይሁድ ዘንድ የተለመዱ መንገዶች ናቸው፡- 4. አንዳንዶች ይህ ታሪክ ተምሳሌታዊ ብቻ እንደሆነ ይናገራሉ። ከሰሎሞንና ከሴቲቱ ፍቅር ጋር ምንም ግንኙነት የሌለው ተምሳሌታዊ ትርጕም አዘል ነው። እግዚአብሔር ሙሽራው ለሆነችው እስራኤል ያለውን ፍቅር ለአይሁድ የሚያሳይ ሲሆን፥ ለክርስቲያኖች ደግሞ፥ ከርስቶስ ሙሽራው ለሆነችው ቤተ ክርስቲያን ያለውን ፍቅር የሚያሳይ ነው። በታሪክ ውስጥ በጣም የታወቀውና ከፍተኛ ተቀባይነት ያለው አተረጓጐም ይህ ነው። ሆኖም ግን ይህ አተረጓጐም በርካታ ችግሮች አሉት። ሰዎች በይሆናል ታሪኩን በሚተረጕሙበት ጊዜ ከእውነት የራቀ ትርጕም ወደ መስጠት ይመራቸዋል። 5. ይህ አመለካከት ከአንድ ልዩነት በቀር፥ በተራ ቊጥር 4 ከሚገኘው አመለካከት ጋር ይስማማል። መዝሙሩ የሚያንጸባርቀው የሰሎሞንና የሴቲቱ ገጠመኞችን ነው። ታሪኩ በእርግጥ የተፈጸመ ነው። ሆኖም ይህ ታሪክ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገኘበት ዋና ምክንያት ከዚህ ለጠለቀ እውነት ተምሳሌት እንዲሆን ነው። የመጀመሪያው ሰው አዳም የመጨረሻው ሰው የክርስቶስ ተምሳሌት እንደሆነ ሁሉ (ሮሜ 5)፣ መልከ ጸዴቅም የኢየሱስ ተምሳሌት ነው (ዕብ. 7)፤ ይህም ታሪክ የሚከተለውን ተምሳሌት ይዞአል፡- ለአይሁድ ሰሎሞን የእግዚአብሔር፥ ሴቲቱ ደግሞ የእስራኤል ተምሳሌት በመሆን በመካከላቸው ያለውን ግንኙነት ያሳያሉ። ለክርስቲያኖች ደግሞ፥ ሰሎሞን የክርስቶስ፥ ሴቲቱ የክርስቶስ ሙሽራ የሆነችውን የቤተ ክርስቲያን ምሳሌ ናት። 6. የመጨረሻው አመለካከት ታሪኩን እንዳለ በቀጥታ የሚቀበል ነው። በሰሎሞንና በሴቲቱ ወይም በሰሎሞን፥ በሴቲቱና በእረኛው መካከል ያለ የፍቅር ታሪክ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተካተተበት ምክንያት፥ እግዚአብሔር በጋብቻ ውስጥ በፍትወተ ሥጋ ለሚገለጥ ፍቅር አክብሮት እንዳለው ለማሳየት ነው። እግዚአብሔር ወንድና ሴት እርስ በርሳቸው በጥልቅ ፍቅር እንዲዋደዱና አንዱ ለሌላው ደስታ ሙሉ በሙሉ ራሱን ይሰጥ ዘንድ እንደሚፈልግ ያሳያል። የጋብቻን ክቡርነትና በጋብቻ ውስጥ የፍትወተ ሥጋ መልካምነትን ያሳያል።  የመኃልየ መኃልይ አስተዋጽኦ  ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጓሜዎች ለመኃልየ መኃልይ የተለያየ አስተዋጽኦ አላቸው። እነዚህ አስተዋጽኦዎች የጥቅሶቹ አከፋፈልና የተናጋሪዎቹ ማንነት ከአንዱ ትርጓሜ ወደ ሌላው ይለያያል። ይህ የሚያሳየው ይህን ግጥም መተርጐም ምን ያህል አስቸጋሪ እንደሆነ ነው። ከዚህ በታች ሁለት አስተዋጽኦዎች ቀርበዋል። አንዱ አስተዋጽኦ መጽሐፉ ሁለት ዋና ገጸ-ባሕርያት እንዳሉት አድርጎ የሚያቀርብ ሲሆን፥ ሌላው ደግሞ መጽሐፉ ሦስት ዋና ገጸ-ባሕርያት እንዳሉት አድርጎ የሚያቀርብ ነው። 1ኛ. መጽሐፉ ሁለት ዋና ገጸ ባሕርያት ማለትም ሰሎሞንና ሴቲቱ ብቻ እንዳሉት አድርጎ የሚያቀርበው አመለካከት፡- 1. ሴቲቱ ስለ ወደደችው ንጉሥ የፍቅር መዝሙሯን ትዘምራለች (1፡2-7)፤  2. ንጉሡ ከሴቲቱ ጋር ይነጋገራል (1፡8-2፡7)፤  3. የፀደይ ወቅት መዝሙር ነው (2፡8-13)፤  4. ሴቲቱ ፍቅረኛዋን ትፈልጋለች (2፡14-3፡5)፤  5. የንጉሡ የሠርግን ሂደት ያሳያል (3፡6-11)፤  6. የሴቲቱ ውበት እንደ አትክልት ስፍራ ነበር (4፡1-5፡ 1)፤  7. ሴቲቱ ስለ ፍቅረኛዋ ያደረገችውን ንግግር ያመለክታል፤ (5፡2-6፡3)፤  8. ሰውዬው ስለ ፍቅረኛው ውበት ያደረገውን ንግግር ያመለክታል (6፡4-7፡9)፤  9. ሴቲቱና ሰውዩው ስለ ፍቅር ያንጸባረቁት ነገር ነበር (7፡10-8፡14)።  2ኛ. በታሪኩ ውስጥ ሦስት ዋና ገጸ ባሕርያትን ማለትም ሰሎሞን፥ እረኛውንና ሴቲቱን የሚያሳየው አመለካከት፡- 1. ሱላማጢሲቱ ሴት በቤተ መንግሥት አደባባይ  ሀ. ንጉሡና ሴቲቱ ሲነጋገሩ (1፡2-2፡2)፥ 2) ሴቲቱ ስለጠፋባት ፍቅረኛዋ ስትናገር (1፡2-4)፥ 3) የቤተ መንግሥቱ ሴቶች ቁንጆይቱን ሲያሞግሷት (1፡4)፥  4) ቁንጆይቱ ለቤተ መንግሥቱ ሴቶች ምላሽ ስትሰጥ (1፡5-7)።  5) የቤተ መንግሥቱ ሴቶች ቆንጆይቱን ሲመክሯት (1፡8)።  6) ሰሎሞን ቆንጆይቱን ሲናገራት (1፡9-10፥  7) ቆንጆዪቱ ለሰሎሞን ስትመልስለት (1፡12-14)።  8) ሰሎሞን እንደገና ቆንጆይቱን ሲናገራት (1፡15)።  9) ቆንጆይቱ ለሰሎሞን ምላሽ ስትሰጥ (1፡16-2፡1)፥ 10) ሰሎሞን ቆንጆይቱን ሲናገራት (2፡2)።  ለ. ቆንጆዪቱ አፍቃሪዋን እረኛ ስትፈልገው (2፡3-3፡5)  2. ሰሎሞን ቆንጆይቱን በፍቅር ለመማረክ ይናገራል  ሀ. ሰሎሞን ቆንጆይቱን ለመማረክ ያደረገው የመጀመሪያ ሙከራ (3፡6-5፡8)  ለ. ሰሎሞን ቆንጆይቱን ለመማረክ ያደረገው ሁለተኛ ሙከራ (5፡9-7፡9)  3. ሱላማጢስቱ ሴት ንጉሥ ሰሎሞንን ሳትቀበል እንደቀረች (7፡10-8፡4)  4. ሱላማጢሲቱ ቆንጆና እረኛው እንደገና በፍቅር እንደተዋሐዱ (8፡5-14)። (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የመኃልየ መኃልይ ትርጕም እና አስተዋጽኦ Read More »

መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን መግቢያ

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) እግዚአብሔር መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዲካተት ያደረገው ለምን ይመስልሃል? ለ) የመጽሐፉን አተረጓጐም በሚመለከት ምን ሰምተሃል? መጽሐፈ መክብብ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለመረዳት እጅግ አስቸጋሪ ከሆኑት መጻሕፍት አንዱ ነው። አስቸጋሪ ከሆኑት ውስጥ ሌላው ደግም መኃልየ መኃልይ ነው፤ ታዲያ ለምንድን ነው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተካተቱት? መኃልየ መኃልይ ላይ ላዩን ቢያዩት አስቸጋሪ አይመስለኝም። በአንድ ወንድና በአንዲት ሴት መካከል ስላለ ግንኙነት የቀረበ የፍቅር ግጥም ነው፤ ዳሩ ግን ለምን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተካተተ? በመጽሐፉ ውስጥ ስለ እግዚአብሔር የተጠቀሰ ነገር የለም ማለት ይቻላል። መጽሐፉ ሊያስተምረን የሚሞክረው ነገር ምንድን ነው? እነዚህ ጥያቄዎች በምሁራን መካከል ብዙ ክርክር አስነሥተዋል። ሰዎች ይህን መጽሐፍ በአጠቃላይ በታሪክ ውስጥ በተለያዩ መንገዶች ተረድተውታል። መጽሐፉ የተተረጐመባቸው በርካታ የተለያዩ መንገዶች ቢኖሩም፥ በዘመናት ሁሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የላቀ ስፍራ ከተሰጣቸው መጻሕፍት አንዱ ሆኖ ቆይቷል። አብዛኛዎቹ የጥንት የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጓሜ አዘጋጆች ስለዚህ መጽሐፍ ታላላቅ ትርጓሜዎችን ጽፈዋል። ባለንበት ዘመን ግን ይህን መጽሐፍ የምንረዳበትን ሁኔታ በሚመለከት ጥያቄዎች ተነሥተዋል። በመሆኑም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተረሱትና ጥቂት ክርስቲያኖች ከሚያነቡት ወይም ከሚሰብኩት መጻሕፍት አንዱ ሆኗል።  የመኃልየ መኃልይ መጽሐፍ ስያሜ  የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) በግዕዝ መኃልየ መኃልይ ማለት ምን ማለት እንደሆነ አንድን የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ቄስ ጠይቅ። ለ) ለዚህ ስያሜ አቻ የሚሆን የአማርኛ ቃል ምንድን ነው? በታሪክ ውስጥ ሁሉ ይህ መጽሐፍ የተለያዩ ስሞች ነበሩት። አንዳንድ ጊዜ «የሰሎሞን መዝሙራት» እየተባለ ይጠራል። ይህ የሚያንጸባርቀው መዝሙሩን የጻፈው ሰሎሞን እንደሆነ ሰዎች ያምኑ እንደነበር ወይም ስለ ሰሎሞን የተጻፈ መጽሐፍ እንደነበር ነው። አይሁድ ይህን መጽሐፍ «ከመዝሙራት ሁሉ የሚበልጥ የሰሎሞን መዝሙር» ብለው ይጠሩታል። ይህ ርእስ የተገኘው ከመኃልየ መኃልይ 1 ቁጥር 1 «ከመዝሙር ሁሉ የሚበልጥ የሰሎሞን መዝሙር» ከሚለው ቃል ነው። በዕብራይስጥ «የመዝሙሮች መዝሙር» ማለት «ከሁሉ የላቀ ታላቅ መዝሙር» ማለት ሲሆን፥ ይህ የሚያሳየው በጥንት ጊዜ መዝሙሩ ምን ያህል ተወዳጅ እንደነበረ ነው። ይህ የዕብራይስጡ ርእስ፣ ጸሐፊው ሰሎሞን መሆኑን ወይም መዝሙሩ ለሰሎሞን የተበረከተ ይሁን ወይም መዝሙሩ የተጻፈው ስለ ሰሎሞን መሆኑን ግልጽ አያደርግም።  የመኃልየ መኃልይ ጸሐፊ  የዚህ መጽሐፍ ዋና ገጸ-ባሕርይ ሰሎሞን እንደሆነ የሚያጠራጥር አይደለም፤ ነገር ግን ይህ ማለት ሰሎሞን የዚህ ግጥም ጸሐፊ ነው ማለት አይደለም። ይህ መዝሙር ስለተጻፈበት ሁኔታ ሦስት ዐበይት አመለካከቶች አሉ፡-  1. ሰሎሞን ያፈቀራትን ሴት አግኝቶ ስላገባበት ሁኔታ የጻፈው ግጥም ነው። 2. ሰሎሞን ከሚስቶቹ አንዷን ስላገባበት ሁኔታ አንድ ሌላ እስራኤላዊ የጻፈው ግጥም ነው። 3. ከሰሜን እስራኤል የሆነ አንድ ያልታወቀ እስራኤላዊ፥ በተከፋፈለው መንግሥት ዘመን መጀመሪያ ገደማ፥ ሰሎሞን ወደ ውድቀት የመሩትን ሴቶች እንዴት ባለማስተዋል እንደተከተላቸው ለማሳየት የጻፈው ግጥም ነው።  ታሪካዊ ሥረ-መሠረት  የውይይት ጥያቄ፥ 1ኛ ነገሥት 4፡20-28፤ 10፡14-11፡4 አንብብ። ሀ) ሰሎሞን ከሴቶች ጋር የነበረው ግንኙነት ምን ይመስል ነበር? ለ) ሰሉሞንን በኃጢአት እንዲወድቅ ያደረገው ምን ነበር? በመኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን ውስጥ በርካታ ታሪካዊ መረጃ ባይኖርም፥ ታሪኩ የሚያንጸባርቀው ከ971-931 ዓ.ዓ. በእስራኤል ላይ ነግሦ ስለነበረው ስለ ሰሎሞን እንደሆነ በቂ ማብራሪያ ይሰጣል። ሰሎሞን በዓለም ላይ ከኖሩ ሰዎች ሁሉ የላቀ ጥበበኛ ሰው የነበረ ቢሆንም የራሱ የሆነ ትልቅ ድክመት ነበረው። ልቡ በቀላሉ በሴቶች ይነሆልል ነበር። 700 ሚስቶችና 300 ቁባቶች እንደነበሩት መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። አብዛኛዎቹ ሴቶች ባዕዳን አማልክትን ያመልኩ የነበሩ የአሕዛብ ወገን የነበሩ ናቸው። እነዚህ ሴቶች የሰሎሞንን ልብ ወደ ጣዖት አምልኮ አሸፈቱት። እንዲሁም በርሱ ላይ የእግዚአብሔርን ፍርድ አመጡበት፤ የእስራኤል መንግሥትም እንዲከፈል አደረጉ። (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን መግቢያ Read More »