የማቴዎስ ወንጌል

የብሉይና አዲስ ኪዳናት ዐበይት ጭብጦች

አንድ የልቦለድ መጽሐፍ ለማንበብ ትፈልጋለህ እንበል። በዚህን ጊዜ የመጽሐፉን የመጀመሪያ ምዕራፍ ብቻ እንዳነበብህ የታሪኩን አጀማመር ልታውቅ ትችላለህ፤ ታሪኩ እንዴት እንደተጠናቀቀ ግን ልታውቅ አትችልም። ከእያንዳንዱ ምዕራፍ አንዳንድ ገጽ ብታነብ ደግሞ ስለ ታሪኩ አጠቃላይ አሳብ ይኖርሃል፤ ነገር ግን በመጽሐፉ ውስጥ የሚገኙትን ክንዋኔዎች በትክክል ልትረዳ አትችልም። ወይም ደግሞ የመጽሐፉን ሁለተኛ ክፍል ብቻ ብታነብ ደግሞ፥ አንዳንድ ነገሮች ለምን በዚያ መንገድ እንደተጻፉ ለማወቅ የተለያዩ ጥያቄዎችን ማንሣት ትጀምራለህ። የውይይት ጥያቄ፦ መጽሐፍ ቅዱስ «የእግዚአብሔር ታሪክ ነው»። ይህ ታሪክ እግዚአብሔር ስለ ራሱ፥ ስለ ሰው ልጆችና በሁለቱ መካከል ስላለው ግንኙነት የተናገረበት እውነተኛ ታሪክ ነው። የሚያሳዝነው ታዲያ የእግዚአብሔርን ታሪክ በአግባቡ የሚያነቡ ብዙ ክርስቲያኖች አለመኖራቸው ነው። መንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል እንዲነበብ በሚፈልገው መንገድ በማንበብ ፈንታ፥ እነርሱ የሚወዷቸውን ክፍሎች ብቻ ያነባሉ። ከዚህም የተነሳ ብዙ ክርስቲያኖች እጅግ ጠቃሚ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን ገለል አድርገው ይተዋሉ። ይህም ስለ እግዚአብሔርና ከሰዎችም ጋር ስላለው ግንኙነት ግራ የተጋባ ግንዛቤ ውስጥ እንዲገቡ ያደርጋቸዋል። አዲስ ኪዳን እግዚአብሔር ከሰዎች ጋር ስለሚያደርገው ግንኙነት መንፈስ ቅዱስ የሚሰጠን የመጨረሻው መለኮታዊ ትምህርት ነው። መደምደሚያ እንደ መሆኑ መጠን፥ እጅግ አስፈላጊ የሆነ የታሪኩ ክፍል ነው። እግዚአብሔር ከልጆቹ ጋር የሚያደርገውን ግንኙነት ለማወቅ ከፈለግን በአዲስ ኪዳን ውስጥ የሚገኙትን 27 መጻሕፍት በሚገባ መረዳት አለብን። በዚህ ጥናታችን በአዲስ ኪዳን ውስጥ የሚገኙትን ዐበይት ትምህርቶች በሙሉ ለመረዳት እንሞክራለን። በተጨማሪም፥ መንፈስ ቅዱስ ለአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎች ሊያስተላልፍ የፈለገውን መልእክት እንዲገልጥልን እየተማጠንን እያንዳንዱን መጽሐፍ አጠር አጠር አድርገን እንመለከታለን። የእግዚአብሔርን ቃል ማጥናት ብቻ ሳይሆን ዛሬ በሕይወታችን ተግባራዊ ማድረግ ስላለብን፥ የአዲስ ኪዳንን እውነቶች ወስደን ከሕይወታችን ጋር ለማዛመድ እንጥራለን። እግዚአብሔር በሚፈልገው መንገድ ልባችን ከእርሱ ጋር እንዲዛመድ ሳናደርግ ዝም ብለን ስለ እግዚአብሔር ማጥናቱ ምንም ፋይዳ የለውም። ስለሆነም፥ ቃሉን በምናነብበት ጊዜ ሳሙኤል እንዳለው፥ «ባሪያህ ይሰማልና ተናገር» ልንል ይገባል (1ኛ ሳሙ. 3፡9-10)። ለጥናቱ የሚረዱ መመሪያዎች ቀጥለህ የጥያቄዎቹን መልስ በደብተር ላይ ጻፍ። የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ-ቃላት ከሌለህ ለጥናትህ ስለሚረዳህ መግዛት ይኖርብሃል። አዲሱ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉምና የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ቅዱስ ካሉህ ለጥናትህ ተጠቀምባቸው። የእያንዳንዱን ዕለት ትምህርት በአንድ ቀን ለማጠናቀቅ ሞክር። አንዳንዱ ትምህርት ከሌሎቹ ስለሚረዝም፥ ከሳምንታዊ ስብሰባው በፊት ጥናትህን ለማጠናቀቅ በቂ ጊዜ መመደብ ይኖርብሃል። በትምህርቶቹ ውስጥ አያሌ የማጣቀሻ ምንባቦች አሉ። «አንብብ» ተብሎ የተጻፈባቸውን ጥቅሶች የግድ ማንበብ ይኖርብሃል። እንደዚህ የሚል ማሳሰቢያ የሌለባቸውን ግን ጊዜ ካለህ ብቻ ልታነባቸው ትችላለህ። የመግቢያ ትምህርቶቹ ስለ አዲስ ኪዳን አንዳንድ ጠቃሚ አሳቦችን ያስጨብጡሃል። ምንም እንኳ እነዚህ አሳቦች አዲስና አስቸጋሪ ቢሆኑብህም፥ ለመረዳት ግን የተቻለህን ጥረት አድርግ። ከዚህ ጥናት ዓላማዎች አንዱ ተማሪው አዲስ ኪዳንን ሙሉ በሙሉ እንዲያነብ መርዳት ነው። ስለሆነም፥ ተማሪው እንዲያነብ የተጠየቀውን ክፍል በሙሉ ማንበብ አለበት። ከእያንዳንዱ ጥናቶች ጋር ተያይዘው የቀረቡት ጥያቄዎች ምን ያህል ግንዛቤህን ለመመዘን የቀረቡ በመሆናቸው ጊዜ ሰጥተህ ሥሪያቸው። (ማስታወሻ፦ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የቀረቡት ታሪኮች ሁሉ መንፈሳዊ እውነቶችን ለማብራራት የተዘጋጁ እንጂ፥ እውነተኛ ገጠመኞች አይደሉም።) የብሉይና የአዲስ ኪዳናት ዐበይት ጭብጦች መጽሐፍ ቅዱስ በዓለም ውስጥ ከሚገኙ መጻሕፍት ሁሉ እጅግ ልዩ መጽሐፍ ነው። መጽሐፍ ቅዱስን ጽፎ ለመጨረስ 1500 ዓመታት ፈጅቷል። ከኦሪት ዘዘፍጥረት እስከ ኦሪት ዘዳግም ያሉት የመጀመሪያዎቹ መጻሕፍት የተጻፉት በ1400 ዓ.ዓ አካባቢ ነበር። የመጨረሻው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የዮሐንስ ራእይ የተጻፈው በ100 ዓ.ም አካባቢ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ የ66 ልዩ ልዩ መጻሕፍት ስብስብ ሲሆን፥ የደራስያኑም ቁጥር ቢያንስ 45 ይሆናል። ከእነዚህ መጻሕፍት መካከል አንዳንዶቹ የታሪክ መጻሕፍት ሲሆኑ፥ ሌሎቹ ደግሞ ግጥሞችን ያካተቱ ናቸው። ለግለሰቦችና ለአብያተ ክርስቲያናት የተጻፉ ደብዳቤዎችም ይገኙባቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ በረጅም ጊዜ ውስጥና በብዙ ደራስያን አማካይነት የተጻፈ በመሆኑ ብዙ የሚጋጩ አሳቦችና ስሕተቶች ይኖሩታል ብለን ልናስብ እንችላለን። ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስን በጥንቃቄ በምናጠናበት ጊዜ በውስጡ የሚገኙ መጻሕፍት ሁሉ የሚያስደንቅ የሃሳብ ስምምነት እንዳላቸው እንገነዘባለን። ምንም እንኳ እግዚአብሔር በሰዎች ተጠቅሞ መጽሐፍ ቅዱስን ቢጽፍም፥ ዋናው የመጽሐፍ ቅዱስ ደራሲ መንፈስ ቅዱስ እንደሆነ ግልጽ ነው (2ኛ ጴጥ. 1፡20-21)። በ1500 ዓመታት ውስጥ በተጻፉት 66 መጻሕፍት መካከል ያለውን ፍጹም ስምምነት ሊያብራራ የሚችለው ይህ መለኮታዊ እውነት ብቻ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ በጥሩ ሁኔታ እንደተሠራ የጋቢ ጥለት፥ በውስጡ ከዳር እስከ ዳር እየተጠላለፉ የእግዚአብሔርን ታሪክ የሚያስተሳስሩ ታላላቅ ጭብጦች አሉት። መጽሐፍ ቅዱስን በአግባቡ ለመረዳት እነዚህን ጭብጦች ማወቅ አለብን። የውይይት ጥያቄ፦ ስለ ብሉይና ስለ አዲስ ኪዳን ባለህ ዕውቀት መሠረት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት እነዚህ ጭብጦች ምን ምን እንደሆኑ ግለጽ። ፩. እግዚአብሔር ሁሉን ነገር የሚቆጣጠር ልዑል ፈጣሪ ነው መጽሐፍ ቅዱስ የሚጀመረው፥ «በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ» በማለት ነው (ዘፍጥ. 1፡1)። የመጽሐፍ ቅዱስ ዐቢይ ጭብጥ፥ የእግዚአብሔር ባሕርይና የዓላማው መገለጥ ነው። እግዚአብሔር የአጽናፈ ዓለሙ (ዩኒቨርስ) ማዕከል፥ ሁሉንም ነገር ወደ ሉዓላዊ ዕቅዱ የሚመራ፥ ሁሉን አዋቂና ሁሉን ቻይ አምላክ ነው። ምንም እንኳ በአጽናፈ ዓለሙ አማካይነት ስለ እግዚአብሔር አንዳንድ ነገሮችን ማወቅ ብንችልም፥ እግዚአብሔር ማን እንደሆነ ትክክለኛውን ማረጋገጫ የምናገኘው ከዘፍጥረት እስከ ራእይ በሚገኙት ቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ ነው። እግዚአብሔር ልጁን ወደዚህ ምድር በላከው ጊዜ ራሱን ፍጹም አድርጎ እንደገለጠ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል። ሰዎች ክርስቶስን በሚመለከቱበት ጊዜ እግዚአብሔር አብን በማየት፥ የእግዚአብሔርን ባሕርይ ይበልጥ ፍጹም በሆነ መንገድ ይረዱታል (ዮሐ. 14፡8-11፤ ዕብ. 1፡1-3)። ይህም ሆኖ፥ ብዙዎች ነገሩ አልገባቸውም ነበር። አንዳንድ ጊዜ ሰይጣን እግዚአብሔር እኛን ማገልገል ይገባዋል ብለን እንድናስብ ያደርገናል። ሰው ከምንም ነገር በላይ ትልቅ ትኩረት ሊሰጠው ስለሚገባ፥ እግዚአብሔር ፍላጎታችንን ማሟላት አለበት ብለን እናስባለን። መጽሐፍ ቅዱስ ግን እግዚአብሔር የእውነት ሁሉ ማዕከል እንደሆነና ሰዎች እግዚአብሔርን ማገልገል እንደሚገባቸው በግልጽ ያስተምረናል። እርሱ ፈጣሪ፥ እኛ ደግሞ ፍጥረቱ ነን። ጳውሎስ እንዳለው፥ እኛ የተፈጠርነው እርሱን ለማክበር ነው (1ኛ ቆሮ. 10፡31፤ ኤፌ. 1፡11-12፤ 3፡20-21)። መጽሐፍ ቅዱስ አሁን ያለውን ነገር ሁሉ እግዚአብሔር እንደ ፈጠረና እርሱ ብቻ ያልተፈጠረ አምላክ እንደሆነ ያስረዳል። በዘፍጥረት 1-2 ላይ ስለ መጀመሪያው ፍጥረት እናነባለን። ዘፍጥረት 3 ስለ ሰው ልጅ ዓመፅ ቢገልጽም፥ እግዚአብሔር ግን የፈጠረውን ዓለም ለመቆጣጠር አልተሳነውም። ነገሮችን ከፍና ዝቅ እያደረገ ታሪክን በመቆጣጠር ላይ ይገኛል (ኢሳ. 5፡26፤ 40፡15-17)። እግዚአብሔር የነገሥታትን ልብ ያንቀሳቅሳል (ምሳሌ 21፡1)። እርሱ የታሪክን ፍጻሜ ወስኗል። እግዚአብሔር በእርሱ ላይ የሚያምፁትን ሁሉ እንዴት እንደሚያንበረክካቸው ከራእይ መጽሐፍ እንመለከታለን። ይህንን ዓለም ከፍጻሜ ካደረሰ በኋላ፥ ፈቃዱ ብቻ የሚከናወንበትን አዲስ ዓለም ፈጥሯል። እግዚአብሔር የሁሉም ተቆጣጣሪና የነገሮችንም ፍጻሜ የወሰነ አምላክ በመሆኑ፥ ወደፊት የሚከሰተውን መለኮታዊ ዕቅድ ልንለውጥ አንችልም። ነገር ግን የዘላለማዊ መንግሥቱ አካል እንሆን ዘንድ ፈቃዳችንን ከፈቃዱ ጋር እንድናስማማ ያሳስበናል። አሁን የምናደርገው ውሳኔ የዘላለም ዕጣ ፈንታችንን ይወስነዋል። የውይይት ጥያቄ፦ ምንም ያህል ሁኔታዎች ክፉ ቢመስሉም እንኳ፥ እግዚአብሔር ሁልጊዜ ነገሮችን እንደሚቆጣጠር ማስታወስ አስፈላጊ የሚሆነው ለምንድን ነው? ፪. እግዚአብሔር ከሰው ጋር ያለው ግንኙነትና የዓለም በኃጢአት መበከል የትም ብንሄድ ዓለም በኃጢአት ተበክላ እናገኛታለን። በየዓመቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን የሚገድሉ በሽታዎች አሉ። እንደ ድርቅና ጎርፍ የመሳሰሉ የተፈጥሮ አደጋዎችም የእግዚአብሔርን ፍጥረት ሰላም በመንሳት ላይ ናቸው። በአገሮች፥ በሕዝቦችና በጎሳዎች መካከል መከፋፈልና ጦርነት በመቀስቀሱ ምክንያት በሺህ የሚቆጠሩ ወገኖች ሕይወት እየተቀጠፈ ነው። እነዚህ ሁሉ ከየት መጡ? መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሁለተኛው የኃጢአት ጭብጥም ይነግረናል። በዘፍጥረት 3 ላይ እንደተናገረው፥ እነዚህ ሁሉ ችግሮች የተከሰቱት በአዳምና በሔዋን ኃጢአት ምክንያት ነው። ጳውሎስ በሮሜ 5፡12-13 ላይ እንደተናገረው፥ ከአንዱ ሰው ከአዳም የተነሳ ኃጢአትና ሞት በሰዎች ሁሉ ላይ ደረሰ። ይህ በአዳምና በሔዋን የተጀመረው የዓመፀኛነት መንፈስ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሁሉ ተንጸባርቋል። የአዳምና የሔዋን ልጆችም የኃጢአትን መንገድ ተከተሉ፤ ከዚያም ቃየን አቤልን ገደለ። ከጥፋት ውኃ በፊት ዓለም ሁሉ በዓመፅ ስለተበላሸች የጥፋት ውኃ ጠርጎ ወሰዳቸው። የተመረጡት

የብሉይና አዲስ ኪዳናት ዐበይት ጭብጦች Read More »

የኢየሱስ ትንሣኤ (ማቴ. 28:1-20)

ማቴዎስ ስለ ኢየሱስ ትንሣኤ የሰጠው ገለጻ በጣም አጭር ነው። ብዙ ያተኮረው መቃብሩን ይጠብቁ በነበሩት ወታደሮች ላይ ነው። የመሬት መንቀጥቀጥ ሲነሣና መልአኩን ሲመለከቱ ምን ያህል እንደ ፈሩ ገልጾአል። ሊቀ ካህናቱ ለወታደሮቹ ገንዘብ በመክፈል የኢየሱስ ኣስከሬን ስለ ጠፋበት ሁኔታ ማመኻኛ ማቅረባቸውን አመልክቷል። በሮም ሕግ እስረኞች ካመለጡ ጠባቂ ወታደሮች ይገደሉ ነበር። የሃይማኖት መሪዎቹ የፈጠራ ታሪካቸውን ለማስፋፋት ሲሉ ወታደሮቹን ከጲላጦስ ቅጣት ለማዳን ቃል ገቡ። ማቴዎስ ስለ ትንሣኤው እሑድ ሁለት አጋጣሚዎችን ብቻ አመልክቷል። በመጀመሪያ፥ ሴቶች ባዶውን መቃብር እንዳዩና መልአኩ የኢየሱስን ትንሣኤ እንዳበሰረላቸው ገልጾአል። ሁለተኛ፥ ኢየሱስ ለሴቶቹ እንደ ተገለጠ ጠቅሷል። እነርሱም አካሉን በመዳሰስ መንፈስ አለመሆኑን አረጋግጠዋል። አምላክነቱን በማወቅም ሰግደውለታል። የውይይት ጥያቄ:- ማቴ. 29፡19-20 አንብብ። በዚህ ክፍል ውስጥ የሚገኙትን ትእዛዛትና የተስፋ ቃሎች ዘርዝር። የማቴዎስ ታሪክ፥ ኢየሱስ ከጥቂት ቀናት በኋላ በገሊላ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደተገናኘበት ሁኔታ ያመራል። ከዚያም ኢየሱስ ለዐሥራ አንዱ ደቀ መዛሙርትና ለጠቅላላው ተከታዮቹ በሰጠው ተልዕኮ ላይ ያተኩራል። በዚህም ሦስት ጠቃሚ እውነቶችን ይጠቅሳል። ሀ. ኢየሱስ ሙሉ መለኮታዊ ሥልጣን አለው። በዚህ ጊዜ የዳንኤል 7፡13-14 ትንቢት ተፈጽሟል። እግዚአብሔር አብ በሰማይና በምድር ላይ ሥልጣን ሰጥቶታል። ሁሉንም የሚቆጣጠረው እርሱ እንጂ የአይሁድ ወይም የአሕዛብ መሪዎች ወይም ሰይጣን አልነበሩም። ክርስቲያኖች በሚገደሉባቸው ጊዜያት ኢየሱስ ነገሮችን በመቆጣጠር ላይ ያለ ላይመስል ቢችልም፥ አማኞች ክርስቶስ በደቀ መዛሙርቱና በዓለም ላይ የሚፈጸሙትን ድርጊቶች በሙሉ እንደሚቆጣጠር ማወቅ አለባቸው። ለ. የኢየሱስ ተከታዮች የሚፈጽሙት ሥራ ነበራቸው። ይህም ወደ ሁሉም የጎሳ ቡድን ወንጌሉን ይዘው መሄድ ነው። በግሪኩ በዚህ ስፍራ “አሕዛብ” የሚለው የጎሳ ቡድን ማለት ነው፡፡) ሥራችን ግልጽ ነው። ኢየሱስ 12 ደቀ መዛሙርትን እንዳስተማረ ሁሉ፥ እኛም ሌሎችን ደቀ መዛሙርት ማድረግ አለብን። ኣዳዲሶቹ ደቀ መዛሙርት የእኛ ሳይሆኑ፥ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት መሆን አለባቸው። ይሁንና ሰዎችን ደቀ መዛሙርት የምናደርገው እንዴት ነው? በመጀመሪያ፣ ክርስቶስ በእነርሱ ምትክ ባቀረበው መሥዋዕት እንዲያምኑ እንመሰክርላቸዋለን። አለበለዚያ እንዴት የእርሱ ደቀ መዛሙርት ሊሆኑ ይችላሉ? ሁለተኛ፥ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት የሆኑ አዳዲስ ክርስቲያኖች በሥላሴ ስም መጠመቅ አለባቸው። የኢየሱስ ይህ ድርጊትም ተከታዮች ብቻ ከሚያስተምሩት ማለትም አንዱ አምላክ (አብ፥ ወልድና መንፈስ ቅዱስ) ሦስት አካል መኖሩን የሚያመለክት መልካም ማረጋገጫ ነው። (ማስታወሻ፡- በቀድሞይቱ ቤተ ክርስቲያን፥ አንድ ሰው የሚጠመቀው ባመነበት ቅጽበት ነበር። ዛሬ እንደሚታየው ሰው አምኖ ለመጠመቅ ብዙ ጊዜ አይቆይም ነበር (የሐዋ. 22፡16)፡፡ ሦስተኛ፣ ክርስቶስ ያዘዘንን ሁሉ ለአዳዲስ ክርስቲያኖች ማስተማር አለብን፡፡ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ክርስቲያኖች ነን እያሉ በታዛዥነት በማይመላለሱ ብዙ ሰዎች፥ መርካት የለባቸውም። የታዘዝነውም ሰዎችን እንድናሳምን ሳይሆን፥ ደቀ መዛሙርት እንድናደርግ ነው። ደቀ መዝሙር ደግሞ በአንዳንድ እውነት ላይ የስምምነት ምልክት የሚያሳይ ሳይሆን፥ ሙሉ በሙሉ የሚከተል ነው። ይህ ብዙ አብያተ ክርስቲያናት በትጋት የማይወጡት ተግባር ነው። ሰዎች በክርስቶስ እንዲያምኑ ጥሩ አድርገው እየመሰከሩ፥ ነገር ግን አዳዲስ አማኞች እንደ እውነተኞች ደቀ መዛሙርት ክርስቶስን የሚከተሉበትን ትምህርት፥ ጊዜ ወስደው አይሰጡም። ይህም ቤተ ክርስቲያን፥ ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ ያቀደውን ያህል ባልተለወጡ ዓለማዊና ደካማ ክርስቲያኖች እንድትሞላ አድርጓታል። ሐ. የክርስቶስ ተከታዮች፥ ክርስቶስ ሁልጊዜም አብሮን የሚኖር አማኑኤል እንደሆነ ማስታወስ አለብን።በግርግም የተወለደው ሕፃን አማኑኤል ተብሎ ተጠርቷል። አሁንም ከሞት የተነሣው ጌታ አማኑኤል ነው። በምድር ላይ ለሠላሣ ዓመታት በቆየባቸው ጊዜያት እንደ ነበረው፣ ለደቀ መዛሙርቱ በአካል ባይታይም፥ በሚሄዱበት ስፍራ ሁሉ አብሯቸው ይሄዳል። ከዚህ በበለጠ አደጋ፥ በአዳዲስ ጎሳዎች፥ መካከል ለክርስቶስ ተከታዮች ድፍረትን የሚሰጣቸው ምንድን ነው? አምስት ሺዎችን የመገበው፥ በውኃ ላይ የተራመደው፥ በሽተኞችን የፈወሰውና አጋንንትን ያስወጣው እርሱ ከእኛ ጋር ነው። የምንፈራበት ምክንያት የለንም። የክርስቶስ ተከታዮች እርሱ ያስተማረውን የደቀ መዝሙርነት ትምህርት ተግባራዊ ከማድረግ ውጭ የሚፈለግባቸው ነገር አይኖርም። የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ከዚህ «ታላቁ ተልዕኮ» ከተባለው ክፍል ለራስህና ለቤተ ክርስቲያንህ የተማርሃቸው ዐበይት ትምህርቶች ምንድን ናቸው? ለ) ቤተ ክርስቲያንህ መልካሙን የምሥራች ለሰዎች ሁሉና ለጎሳ ቡድኖች ሁሉ በተጠናከረ ሁኔታ የምታደርሰው እንዴት ነው? ሐ) ወንጌሉን ላልደረሳቸው ለማድረስና ላመኑት የደቀ መዝሙርነት ትምህርት ለመስጠት በግልህ ምን ልታደርግ ትችላለህ? መ) በተማርኸው መሠረት፥ አዳዲስ ክርስቲያኖች ክርስቶስን፥ እንደ ደቀ መዛሙርት በሚከተሉበት ጊዜ ሊማሯቸው ይገባል የምትላቸውን እውነቶች ዘርዝር፡ (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ ስለዚህ አስደናቂ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡)

የኢየሱስ ትንሣኤ (ማቴ. 28:1-20) Read More »

ማቴዎስ 26፡47- 27፡66

ወደ ኢየሱስ ስቅለት የሚመሩ ክስተቶች (ማቴ. 26፡47-27፡8) ከኢየሱስ ጸሎት በኋላ ነገሮች በፍጥነት ተከናወኑ። ይሁዳ ወታደሮችን አስከትሉ በመምጣት ኢየሱስን በመሳም አሳልፎ ሰጠ። ክርስቶስ በሚያስደንቅ ሁኔታ መንግሥቱ በውጊያና በዐመጽ እንደማትሸነፍ አሳይቷል፡፡ አልፎ በመሰጠቱ፥ በመያዙና በሞቱ ሳይቀር፥ ኢየሱስ ይህ ሁሉ በብሉይ ኪዳን የተተነበየ የእግዚአብሔር ዕቅድ አካል መሆኑን ያውቅ ነበር (ማቴ 28፡54፣ 56)። ክርስቶስ ከተያዘ በኋላ፥ ደቀ መዛሙርቱ ፈርተው ሸሹ፡፡ ማቴዎስ ለአይሁዶች በጻፈው ወንጌሉ፥ እያንዳንዱ በኢየሱስ ላይ የተካሄደው ምርመራ ሕገወጥ እንደ ነበረ አመልክቷል። ኢየሱስ የተሰቀለው ሰዎች በደለኛና ሞት የሚገባው እንደሆነ በማመናቸው አልነበረም። ንጹሕ እንደሆነ ያውቁ ነበር። ግን ኣይሁዶች በፍትሕ አልባነት ነበር የመረመሩት። ማቴዎስ የጠቀሰው የመጀመሪያው ምርመራ የተካሄደው 70 አባላት በሚገኙበት የአይሁድ ሸንጎ ፊት ነበር። የዚህ ሸንጎ ሕገ መንግሥት የሞት ፍርድ ለመበየን በምሽት ሊሰባሰቡ እንደማይችሉ ያስረዳል። እንዲሁም፥ መረጃውን ከቀረበላቸው በኋላ የፍርድ ውሳኔ ከመስጠታቸው በፊት፥ አዳዲስ መረጃዎችን በመጠባበቅ ብዙ ጊዜ መቆየት እንደሚገባቸው ይደነግጋል። ማቴዎስ እንዳመለከተው ግን እነዚህ ሰዎች ስለ ፍትሕ ሳይጨነቁ ኢየሱስን ለመግደል አሰፍስፈው ተነሡ። ምርመራው የተካሄደው በሌሊት ሲሆን፥ ምስክሮቹ ስምምነት አልነበራቸውም። ሊቀ ካህናቱ ኢየሱስ፥ «ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ» መሆን አለመሆኑን እንዲነግረው አዘዘው። ኢየሱስ ዳንኤል 7፡13-14ን በማመልከት የሰው ልጅ መሆኑን ከገለጸ በኋላ ነበር፥ እርሱን ለመግደል የሚያስችል መረጃ እንዳላቸው ያመኑት። የአይሁድ መሪዎች ይህ ስድብ ነው ብለው ያምኑ ነበርና። ተፈላጊውን የሕግ ሂደት ጊዜ ሳይጠብቁ መሪዎቹ ወዲያውኑ በኢየሱስ ላይ የሞት ፍርድ ወሰኑ። ምንም እንኳ ይህን ለማድረግ የሚያስችል ፖለቲካዊ ሥልጣን ባይኖራቸውም፥ እነዚህ የአይሁድ መሪዎች በኢየሱስ ላይ በመሳለቃቸውና ድብደባ በመፈጸማቸው ሌሎች ሕግጋትን ጥለዋል። ማቴዎስ በዚህን ጊዜ የተከናወኑ ሁለት ክስተቶችን ይገልጻል። መጀመሪያ፥ ጴጥሮስ የኢየሱስን መገረፍ አይቷል። የተለያዩ ሰዎች ጴጥሮስን የኢየሱስ ተከታይ እንደሆነ አውቀውታል። ጴጥሮስ ግን ኢየሱስን አላውቀውም ሲል ሦስት ጊዜ ማለ። የዶሮ ጩኸት የኢየሱስን ትንቢት አስታወሰው፥ እርሱም በኃጢአተኝነቱ ተጸጽቶ አለቀለ። ሁለተኛ፥ በዚህን ጊዜ ይሁዳ ወደ ካህናት አለቆች ዘንድ በመሄድ ኢየሱስ ንጹሕ መሆኑን ገልጾ እንዲለቅቁት ለመናቸው። ፈቃደኞች ሳይሆኑ ሲቀሩ፥ ራሱን በስቅላት ገደለ። ጸጸቱ በንስሐ ወደ እግዚአብሔር እንዲመለስ አላደረገውም። በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሳይቀር ማቴዎስ የእግዚአብሔርን እጅ አይቷል። አሳልፎ የሰጠው የይሁዳ ሞትና ለወንጀለኞች የመቃብር መሬት መገዛቱ፥ የብሉይ ኪዳንን ትንቢት ፈጽሟል። (ኤር. 32፡6-9፣ ዘካ. 11፡12-13 አንብብ።) ማቴዎስ የገለጸው ሁለተኛው ምርመራ የተካሄደው የሮም ገዥ በነበረው በጲላጦስ ፊት ነበር። ጲላጦስ ለአይሁድ ሃይማኖት ግድ ስላልነበረውና ኢየሱስ አምላክ ነኝ በማለቱ ምክንያት በሞት ስለማይቀጣው፥ አይሁዶች ነገሩን ፖለቲካዊ አድርገው በማቅረብ፥ ክርስቶስ የአይሁድ ንጉሥ ነኝ ብሏል አሉ። ይህ ደግሞ በሮም ላይ የሚካሄድ የዓመፅ ተግባር ነበር። ጲላጦስ ክርስቶስ ሮምን ያሚያሰጋ ኣማፂ እንዳልሆነ ያውቅ ነበር። የጲላጦስም ሚስት ስለ ክርስቶስ ንጽሕና የሚያስረዳ ሕልም አይታ ነበር። ነገር ግን ጲላጦስ አይሁዶን ፈራ። (ማቴዎስ ለክርስቶስ ሞት አብዛኛው ጥፋት የጲላጦስ ሳይሆን፥ የአይሁዶች እንደሆነ አመልክቷል።) ጲላጦስ አንድ እስረኛ በመፍታት ኢየሱስን ነፃ ለማውጣት ሲሞክር፥ አይሁዶች ከኢየሱስ ይልቅ ነፍሰ ገዳዩን በርባንን መረጡ። ጲላጦስ ሌላ ቅጣት በመረጠ ጊዜም ኢየሱስን እንዲሰቅል አስገደዱት። አይሁዶች እነርሱንና ልጆቻቸው ለኢየሱስ ደም ኃላፊነት እንደሚወስዱ በመግለጽ ለተግባራቸው ተጠያቂነታቸውን አመልክተዋል። ጲላጦስም ከኀላፊነት አያመልጥም። በሥነ ምግባራዊ ድክመቱና በፍርሃቱ ምክንያት ንጹሕ ሰው እንዲደበደብ፥ በወታደሮቹ መሳለቂያ እንዲሆንና በመጨረሻም እንዲገደል ፈቅዷል። ስለሆነም አይሁዶችም ሆኑ አሕዛብ ኢየሱስን በመስቀላቸው በድለዋል። የኢየሱስ ስቅለት፥ ሞትና ቀብር (ማቴ. 27፡2-66) ሮማውያን ወንጀለኛው ክሱ የተጻፈበትን ምልክት ተሸክሞ እንዲሄድና በመስቀል ላይ እንዲሰቀል የማድረግ ልማድ ነበራቸው። በክርስቶስም ላይ «የአይሁድ ንጉሥ» የሚል የክስ ቃል ተጻፈ። የክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅነት ጉዳይ ሦስት ጊዜ ተነሥቷል። መጀመሪያ ሕዝቡ (ቁ 40)፥ ከዚያም ካህናቱ ቁ 43) ለስቅላት ተጠቅመውበታል። ነገር ግን ከስቅለቱ ባሻገር ተመልክቶ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልዩ ልጅ እንደሆነ የተገነዘበው አንድ የአሕዛብ ወታደር ነበር ቁ 54)። አይሁዶች ሊያዩ ያልቻሉትን ኢየሱስን ለመስቀል የቆመው የአሕዛብ ወታደር እየ። ሕዝቡ «እስኪ ከመስቀል ውረድ» እያሉ ሲፈታተኑት ኢየሱስ ይህንኑ ሊያደርግ ይችል ነበር። መላእክት እንዲረዱት በመጥራት የመሢሕነት ኃይሉንና ሥልጣኑን ሊያሳይ ይችል ነበር። እንዲሁም ኢየሱስን በመስቀል ላይ ያቆየው በእጆቹና እግሮቹ ላይ የተቸነከሩት ምስማሮች፣ ወይም የአይሁድ እና የሮም ባለሥልጣናት አልነበሩም። ክርስቶስን በመስቀል ላይ ያኖረው ታላቅ ፍቅሩና እኔና አንተ የዘላለምን ሕይወት እንድናገኝ መቁረጡ ነው። የውይይት ጥያቄ፡- ስለ ክርስቶስ ፍቅርና ለአንተ ለመሞት ስለ መፍቀዱ እያሰብህ ጸልይ። ለፍቅሩ እመስግነው። በአኗኗርህ ለእርሱ ያለህን ፍቅር ለመግለጽ ቃል ኪዳንህን እድስ። ኢየሱስ ለስድስት ሰዓታት በመስቀል ላይ ቆየ። በዚህ ጊዜ የሰው ልጆች ኃጢአት በላዩ ላይ ስለነበር አብ ፊቱን አዞረበት። ኢየሱስ በመስቀል ላይ ከተናገራቸው ነገሮች ማቴዎስ የጠቀሰው በአባቱ የመተውን ሥቃይ ብቻ ነበር። ከዚያም ኢየሱስ ነፍሱን እንደ ተወ ገልጾአል። ክርስቶስ የእግዚአብሐርን ዕቅድ ከፈጸመ በኋላ፥ መንፈሱን ተወ እንጂ በአይሁዶች ወይም በሮማውያን አልተገደለም። ኢየሱስ በሞተባት ቅጽበት፥ አንድ አስደናቂ ነገር ተከሰተ። ከሙሴ ዘመን ጀምሮ በቤተ መቅደስ ውስጥ እግዚአብሔር ከሚኖርበት ቅድስተ ቅዱሳን የሚለይ መጋረጃ ነበር፡ ያ የመለያ መጋረጃ በቅዱሱ አምላክና በኃጢአተኞች ሰዎች መካከል ያለውን ልዩነት በዘላቂነት የሚያስታውስ ነበር። ይህ መጋረጃ «ወደዚህ ብትጠጋ ትሞታለህ» አንተ ኃጢአተኛ ስትሆን፥ እኔ ቅዱስ ነኝ» ለሚለው መለኮታዊ ቃል ዘላቂ ማስታወሻ ነበር። ከኢየሱስ ሞት በኋላ ግን ያ ክፍፍል ተፈጸመ። ለዓለም ኃጢአት ተገቢው ዋጋ ስለ ተከፈለ፥ በኢየሱስ የሚያምኑ ሰዎች ወደ ቅዱስ አምላክ ያለ ፍርሃት ሊቀርቡ ቻሉ። የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ዕብ 4፡5-16፤ 8፡1-2፤ 9፡11-15፥ 24-28፤ 10፡19–22 ኣንብብ። የክርስቶስ ሞት ያለ ፍርሃት ወደ እግዚአብሔር እንድንቀርብ ያስቻለን እንዴት ነው? ለ) አንዳንድ ክርስቲያኖች (ለምሳሌ፥ ኦርቶዶክሶች) የብሉይ ኪዳንን ዓይነት መጋረጃ የሚጋርዱት እንዴት ነው? ይህን ማድረግ ኢየሱስ በተሰቀለ ጊዜ የተከሰተውን ሁኔታ ያለመረዳት የሚሆነው እንዴት ነው? በዘጠኝ ሰዓት ኢየሱስን ከመስቀል ላይ አውርደው ቀበሩት። ቅዳሜ ዕለት የአይሁድ መሪዎች ጲላጦስ በልዩ የሮም ወታደሮች መቃብሩን እንዲያስጠብቅላቸው ጠየቁት። የዚህ ምክንያት ኢየሱስ ከሦስት ቀናት በኋላ ከሞት መነሣቱን እንደተናገረ ያውቁ ነበር። ኢየሱስ በእርግጥ ከሞት ይነሣል ብለው ባያምኑም፥ ደቀ መዛሙርቱ አስከሬኑን ከሰረቁ በኋላ ሕያው ነው ብለው እንዳያስወሩ ፈርተው ነበር። ኢየሱስ ከሞት ከተነሣ የእግዚአብሔር ልጅነቱ እንደሚረጋገጥ ያውቁ ነበር። ማቴዎስ ይህንን የመቃብር ጥበቃ ታሪክ ጨምሮ የጻፈው ያለ ምክንያት አይደለም። ኢየሱስ ከሞት ከተነሣ በኋላ፥ የአይሁድ መሪዎች ደቀ መዛሙርቱ አስክሬኑን እንደ ሰረቁ የሚገልጽ ልብ ወለድ ታሪክ ለማስወራት ተገደው ነበር። ይህ የአይሁድ መሪዎች ከትንሣኤው በኋላ ያሰራጩት ውሸት ነበር። የአንዳንድ ጻድቃን መቃብሮች ተከፍተው ሙታኑ ለተወሰነ ጊዜ ሕያዋን ሆነው መቆየታቸውን የገለጸው ማቴዎስ ብቻ ነው። ማቴዎስ የትንሣኤው ጊዜ እስካለፈበት ቀን ድረስ በኢየሩሳሌም ከተማ አለመታየታቸውን ስለገለጸ፥ ምሑራን ይህ ክስተት ኢየሱስ ከሞት በተነሣበት እሑድ ጠዋት እንደ ተፈጸመ አምነዋል። ይህም በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ምክንያት ሞት በሰዎች ላይ የነበረውን ኀይል እንዳጣ ያሳያል። (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ ስለዚህ አስደናቂ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡)

ማቴዎስ 26፡47- 27፡66 Read More »

ማቴዎስ 26:1–46

የውይይት ጥያቄ፡- ኢየሱስ በምድር ላይ ከኖሩት ሰዎች ሁሉ በላይ ታላቅ እንደሆነ ሲነገር እንሰማለን። ኢየሱስ ያደረገውና ታሪክን ሁሉ የለወጠው አንድ ዐቢይ ነገር ምን ይመስልሃል? መልስህን አብራራ። ስለ ክርስቶስ ሕይወት አጽንኦት ልንሰጥባቸው የምንችላቸው ብዙ ነገሮች አሉ። ብዙዎቻችን በፈውስ አገልግሎቱ ላይ ለማተኮር እንፈልጋለን። እርግጥ በምድር ላይ ከጤና በላይ ምን አለ? ወይም በማስተማር አገልግሎቱ ላይ ለማተኮር እንፈልጋለን። ነገር ግን የወንጌላት ጸሓፊዎች ሁሉ ያተኮሩት በክርስቶስ ሞት ላይ ነው። ሁሉም የወንጌላት ጸሓፊዎች ከክርስቶስ ሕይወት እጅግ ጠቃሚውና ታሪክን ሁሉ የተገዳደረው ተኣምራት ሠሪነቱ ወይም ማስተማሩ ሳይሆን፥ (እነዚህ ነገሮች አስፈላጊዎች ቢሆኑም)፥ የክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ እንደሆነ ተገንዝበው ነበር። ክርስቶስ በሞቱ ኃጢአተኞች የእግዚአብሔር ቤተሰብ የሚሆኑበትን መንገድ ከፍቷል። በትንሣኤው ክርስቶስ መለኮታዊ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን ብቻ ሳይሆን፥ እግዚአብሔር የኃጢአት መሥዋዕቱን እንደ ተቀበለ አረጋግጧል። ማቴዎስ ክርስቶስን በመጀመሪያዎቹ ሦስት ዓመታት ያካሄደውን አገልግሎት፥ (ፈውስና ማስተማሩን ጨምሮ) በአጭሩ ጠቅለል አድርጎ ካቀረበ በኋላ፥ በዘመናት ከሁሉም በላቀው እውነት ላይ አጽንኦት እድርጓል። ይህም የክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ነው። እኛ ክርስቶስ ለሰው ልጆች በተቀበለው ሰብአዊ ሥቃይ ላይ ብናተኩርም፥ የወንጌላት ጸሓፊዎች በዚህ ጕዳይ ላይ አላተኮሩም። ብዙ ስቅለቶችን ያዩ በመሆናቸው ጸሓፊዎቹ ክርስቶስ ለእኔና ለእናንተ ምን ያህል እንደ ተሠቃየ ሊያብራሩ ይችሉ ነበር። ነገር ግን በሐቆች ላይ ለማተኮር መረጡ። በተለይም ማቴዎስ አይሁዶችን በሚያስገርም መልኩ የክርስቶስ ሞት የእግዚአብሔር ዕቅድ አካል እንደሆነ በሚገባ ለማብራራት ፈልጓል። የኢየሱስ ጠላቶች ሊገድሉት ተዘጋጁ (ማቴ. 26፡1-16) ቀደም ሲል ማቴዎስ በኢየሱስ የአገልግሎት ጊዜ ሁሉ ከሃይማኖት መሪዎች ጋር ሲጋጭ መቆየቱን አስረድቷል። አሁን ያ ግጭት ወደ ባሰ ደረጃ እየደረሰ ነው። የሃይማኖት መሪዎቹ በሕዝብ ፊት ብዙ ጊዜ ስላሸነፋቸውና ስላዋረዳቸው ከክርስቶስ ጋር ከመከራከር ይልቅ ገድለውት ሊገላገሉ ወሰኑ። ነገር ግን በዚህ ግጭትና ኢየሱስ ወደሚያዝበት ደረጃ ባደረሱት ድርጊቶች መካከል፥ ማቴዎስ ጠቃሚ የፍቅር ታሪክ አውግቷል። ይህም ኢየሱስ በለምጻሙ ስምዖን ቤት ማዕድ ሊበላ ተቀምጦ ነበር። እርሱም ኢየሱስ የፈወሰው ግለሰብ ሳይሆን አይቀርም። ምግቡ እየተበላ ሳለ፥ አንዲት ሴት መጥታ ኢየሱስን ሽቱ ትቀባው ጀመር። ዮሐንስ ይህች ሴት ኢየሱስ ከሚቀርባቸው ልዩ ወዳጆች አንዷ ማርያም እንደ ነበረች ገልጾአል (ዮሐ 12፡1-8)። ሴትዮዋ ውድ ሽቶ አምጥታ ጌታን ስትቀባ ያዩ ደቀ መዛሙርት ሀብት ማባከን መሰላቸው። ምናልባትም ለድሆች ማሰብ እንደሚያስፈልግ ከኢየሱስ መማራቸውን ለማሳየት ሲሉ፥ ደቀ መዛሙርቱ ሴቲቱ ሽቱውን ሸጣ ገንዘቡን ለድሆች ባለመስጠቷ ገሠጹኣት። ነገር ግን ለኢየሱስ ልባዊ ፍቅርን በስጦታ መግለጥ ምን ጊዜም የሞኝነት ተግባር አልነበረም። ማርያም ለእርሱ ክብር ለሞቱ መታሰቢያ ሽቶውን እንደ ቀባችው ክርስቶስ ተናግሯል። ኢየሱስ በጥቂት ቀናት ውስጥ ተይዞ እንደሚገረፍ፥ ከዚያም እንደሚሰቀል፥ በተጨማሪም ከሃይማኖት መሪዎችና ከሕዝቡ የሚደርስበትን ጥላቻ እያሰበ ይህን የመታሰቢያ ሽቶ ስትቀባው አክብሮ ተቀበለ። የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) አንድ የተጋነነና ያልተለመደ ነገር በማድረግ ለኢየሱስ ያለህን ፍቅር ገልጸህ ታውቃለህ? ምን ነበር ያደረግኸው? ፍቅርህ ለኢየሱስ እንዲበዛ ያደረገው ምንድን ነው? ለ) አንዳንድ ጊዜ ባልተለመዱ መንገዶች፥ ለኢየሱስ ያለንን ፍቅር የማናሳይ ከሆነ፣ ይህ ስለ ልባችንና ስለ ፍቅራችን ምን ያሳየናል? ከማርያም በተቃራኒ፥ ይሁዳም የኢየሱስ የቅርብ ወዳጅ ነበር። እርሱ ግን ኢየሱስን በ30 ብር ሸጦታል። በዚህ ሁኔታ ኢየሱስ የመጀመሪያውን በደል የተቀበለው ከይሁዳ ነበር። ይህ ኢየሱስን ምን ያህል እንደ ጎዳው የሚያውቁት የቅርብ ወዳጃቸው የከዳቸው ሰዎች ብቻ ናቸው። ይሁዳ ለሦስት ዓመታት ኢየሱስ ጋር አብሮ እየኖረ ትምህርቱን አድምጧል። እርሱም የቡድኑን ገንዘብ እስከ መያዝ ድረስ የተከበረ ደቀ መዝሙር ነበር። ይሁዳ ኢየሱስን ለምን አሳልፎ ሰጠ? ለገንዘብ ብሎ ነው? አይመስልም። ምናልባትም ይሁዳ ኢየሱስ ሲናገር የነበረውን ምድራዊ መንግሥት እንዲጀምር ለማስገደድ አስቦ ይሆናል። ክፉዎቹ የአይሁድ መሪዎችና እስራኤልን የሚቆጣጠሩት ሮማውያን ሲገረሰሱ ለማየት ፈልጎ ይሆናል። ኢየሱስ ጴጥሮስ እንደሚክደው መተንበዩና የጌታን እራት ማክበሩ (ማቴ. 26፡7-35) በአይሁዶች ሃይማኖታዊ የጊዜ ሰሌዳ፥ በአንድነት የሚከበሩ ሁለት ሃይማኖታዊ በዓላት አሉ። የመጀመሪያው አይሁዶች ከግብጽ ለመውጣት መዘጋጀታቸውን የሚገልጽ የአንድ ቀን የቂጣ በዓል ነበር። ሌላው የፋሲካ በዓል ሊሆን፥ ይህም የእግዚአብሔር መልአክ በበራቸው ላይ ደም የረጨትን ሰዎች እያለፈ የግብኦችን የበኩር ልጆች የገደለበትን ሁኔታ የሚያስታውሱበት ነበር። እነዚህ ሁለቱም በዓላት ወደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያመለክቱ ነበር። ኢየሱስ ለዓለም ኃጢኣት በመሞት የእግዚአብሔርን ልጆች፥ (አይሁዶችንም አሕዛብንም) ከመንፈሳዊ እስራት ነፃ አወጣ። ማቴዎስ ስለዚህ የፋሲካ በዓል ምግብ ባቀረበው ገለጻ፥ በክርስቶስ አልፎ መሰጠት ላይ ያተኩራል። ኢየሱስ ይሁዳ አሳልፎ እንደሚሰጠው አስቀድሞ ተናግሯል። ክርስቶስ የሚሆነውን ሁሉ ቀደም ብሎ እያወቀ በፈቃደኛነት ወደ መስቀል ሞት አመራ። ምናልባትም ኢየሱስ በእራት ላይ ለይሁዳ ምግብ ያጎረሰው ከኃጢአቱ ንስሐ እንዲገባ ዕድል ሊሰጠው ይሆናል። በተጨማሪም፥ ጴጥሮስና ሌሎችም ደቀ መዛሙርቱ የብሉይ ኪዳንን ትንቢት በመፈጸም እንደሚክዱት ኢየሱስ ተናግሯል። ማቴዎስ ሁለቱን ክህደቶች የጠቀሰው ለምንድን ነው? ክርስቲያኖች በስደት ጊዜ እንዴት ክርስቶስን ሊክዱ እንደሚችሉ ለማስተማር ፈልጎ ይሆን? ምናልባትም ይሆናል። በማቴዎስ ዘመን፥ አይሁድና አሕዛብ ክርስቲያኖች በስደት ምክንያት ለክርስቶስ መከራ መቀበል ወይም መሞት ይገባቸው እንደሆነ በማሰብ ይጨነቁ ነበር። አንዳንዶች ከፍርሃት የተነሣ ይክዱት ነበር። እነዚህ ሰዎች ከዚያ በኋላ ተስፋ ይኖራቸዋል? ቤተ ክርስቲያን ምን ዓይነት ምላሽ ልትሰጣቸው ይገባል? ማቴዎስ በይሁዳና ጴጥሮስ ታሪክ አማካኝነት ሁለት ዓይነት ክህደት እንዳለ ይናገራል። በመጀመሪያ፥ አንድ ሰው ክርስቶስን ከካደ በኋላ ንስሐ ሳይገባ የሚሞትበት የይሁዳ ዓይነት ክህደት አለ። የዚህ ዓይነቱ ክህደት ተስፋ የለውም። ክርስቲያኖች በፍርሃት ሳቢያ ከክርስቶስ ሲለዩና ንስሓ ገብተው ወደ ክርስቶስ ከመመለሳቸው በፊት ቢሞቱ፥ የይሁዳን ዓይነት ፍርድ ይቀበላሉ። ነገር ግን አንድ ሰው ለሕይወቱ ፈርቶ ከክርስቶስ ወደ ኋላ ካፈገፈገ በኋላ፥ ንስሐ ቢገባ፥ እንደ ጴጥሮስ ሙሉ በሙሉ ይቅርታ ተደርጎለት ወደ ቤተ ክርስቲያን ፍሬያማ አገልግሎት ይመለሳል። ክርስቶስ መሓሪና ይቅር ባይ አምላክ ነው። የቤተ ክርስቲያን መሪዎችም የክርስቶስን ምሳሌነት በመከተል፥ በስደት ምክንያት ክርስቶስን የካዱትን ወገኖች ይቅር ሊሏቸው ይገባል። የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) እነዚህን ሁለት ዓይነት ክህደቶች ያየህባቸው ምሳሌዎች ካሉ ግለጽ። ለ) ኤር. 31፡31-34 እና ሕዝ. 36፡25-27 አንብብ። ስለ አዲስ ኪዳን የተሰጡት የተስፋ ቃሎች ምንድን ናቸው? እነዚህ የተስፋ ቃሎች ለክርስቶስና በቤተ ክርስቲያን የተፈጸሙት እንዴት ነው? ሐ) ክርስቶስ ዘመናችንን «አዲስ ኪዳን» ሲል ምን ማለቱ ይመስልሃል? ክርስቶስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር የበላው የመጨረሻው ምግብ በሌላ ምክንያት ልዩ ነበር። ክርስቶስ «የጌታ እራት» የምንለውን ሥርዓት መሥርቷል። ይህ የመታሰቢያ ምግብ ነው። ክርስቶስ በመስቀል ላይ ሲሞት ደሙ በመፍሰሱ፥ የብሉይ ኪዳን የአምልኮ ሥርዓት እንዳበቃ ገልጾአል። በኤርምያስ የተተነበየው አዲስ ኪዳን ተጀመረ። ክርስቲያኖች ሁሉ ከእግዚአብሔር ጋር ያላቸው ግንኙነት በሞቱ ላይ የተመሠረተ መሆኑን በተደጋጋሚ እንዲያስታውሱ ለማድረግ፥ ደቀ መዛሙርቱ ወይን በመጠጣትና እንጀራ በመቁረስ ሞቱን የሚያከብሩበትን ቀን እንዲያስቡ ነገራቸው። ይህ በዓል ለክርስቶስ ተከታዮች በሙሉ የተሰጠ ሲሆን፥ በአዲስ ኪዳን ዘመን ሁሉም ክርስቲያኖች የጌታ እራት ሥነ ሥርዓት ተሳታፊዎች ነበሩ። ኢየሱስ በጌቴሴማኒ ጸለየ (ማቴ. 26፡36-46) ኢየሱስ ፍጹም አምላክና ፍጹም ሰው ነው። አንድ ሰው እንዴት በአንድ ጊዜ ሰውና አምላክ ሊሆን እንደሚችል ምሥጢር ቢሆንም፥ ይህ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረው እውነት ነው። ኢየሱስ ከሞት እንደሚነሳ ቢያውቅም፥ ጭንቀት ስለ ጸናበት ከተቻለ እግዚአብሔር ሌላ አማራጭ እንዲሰጠው ሦስት ጊዜ በጸሎት ጠይቋል። ነገር ግን በእያንዳንዱ ጊዜ ክርስቶስ «ፈቃድህ ይፈጸም» በማለት ለእግዚኣብሔር መታዘዙን አሳይቷል። አንዳንድ ሰዎች ለፈውስ በምንጸልይበት ጊዜ ፈቃድህ ከሆነ» ማለቱ ያለማመን ምልክት ነው ይላሉ። ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ይህ የትሕትናና ራስን የማስገዛት ምልክትም ሊሆን ይችላል። እግዚአብሔር አንድን ነገር እንዲፈጽምልን ልናስገድደው አንችልም። እርሱ ዓለምንና ድርጊቶችን ሁሉ የሚቆጣጠር ፈጣሪና ሁሉን ቻይ አምላክ ነው፡፡ እግዚአብሔር አንድ ነገር ፈቃዱ እንደሆነ በግልጽ ካልነገረን፥ “ፈቃድህ ይፈጸም” ማለታችን በፈውስም እንኳ ትልቁ ፍላጎታችን የእግዚአብሔር መክበር መሆኑን ያሳያል። ይህም፥ ፈቃዱና ዓላማው ምንም ይሁን ምን እንደምንገዛለት ያመለክታል። የውይይት ጥያቄ:- ሀ) “ፈቃድህ ይፈጸም” የሚለው ሐረግ እንደ ማመኻኛ ወይም የአለማመን

ማቴዎስ 26:1–46 Read More »

ክርስቶስ ላልተጠበቀው ምጽአቱ ስለ መዘጋጀት የሚያስረዳ ምሳሌ ተናገረ (ማቴ 25:1-46)

ለክርስቲያኖች የመጨረሻው ዘመን ምን ዓይነት እንደሚሆን ማሰቡ ቀላል ነው። ብዙውን ጊዜ በተለያዩ አተረጓገሞች ክርክሮች ሲካሄዱ ቆይተዋል። ይህ ብዙውን ጊዜ ጥቅም የሌለው የሞኝነት ተግባር ነው። ክርስቶስ ስለ መጨረሻው ዘመን ባስተማረበት ወቅት፥ መዘጋጀት እንዳለብን ተናግሯል። ዋናው ነገር ይኸው ነው። ክርስቶስ በየትኛውም ጊዜ እንደሚመለስ ተገንዝበን ከተዘጋጀንና በየዕለቱ በታማኝነት ከተመላለስን፥ የሚያሳስበን ነገር አይኖርም። በዚህ ዓይነት ከኖርን፥ እርሱ ሲመጣ አናፍርም። ክርስቶስ እርሱ በሚመለስበት ጊዜ የማያሳፍር ሕይወት መምራት እንደምንችል ሦስት የተለያዩ እውነቶችን የሚያስተምሩ ሦስት ምሳሌዎችን ሰጥቷል:- ሀ. ለክርስቶስ ምጽአት የተዘጋጁ ክርስቲያኖች ብቻ፥ ወደ ዘላለማዊ የበረከት መንግሥት ይገባሉ (ማቴ. 25፡1-13)። የመሢሑን መንግሥት ለማመልከት አይሁዶች ከሚጠቀሙባቸው ዐበይት ምሳሌዎች አንዱ፥ ጋብቻ ነበር (ራእይ 19፡7-9)። ክርስቶስ የአይሁድን ጋብቻ ሁኔታ ምሳሌ በማቅረብ፥ ደቀ መዛሙርቱ ለምጽአቱ እንዲዘጋጁና ካልተዘጋጁ ደግሞ ምን እንደሚገጥማቸው አብራርቷል። (ማስታወሻ፡- እንደ ገጠሪቱ ኢትዮጵያ ሁሉ፥ በአይሁዶች የጋብቻ ሥነ ሥርዓት አፈጻጸም ሰዓት አይወሰንም ነበር። በተለይም ሙሽራው ከርቀት የሚመጣ ከሆነ፥ እስኪመጣ ድረስ የሙሽራይቱ እድምተኞች ሲጠብቁት ይቆያሉ።) በዚህ ታሪክ ውስጥ አሥሩ ቆነጃጅት የክርስቶስን ተከታዮች ይወክላሉ። ወደ ሰርጉ በዓል የሄዱት አምስቱ ቆነጃጅት የክርስቶስን ዳግም ምጽአት በትጋት ለመጠበቅ የተዘጋጁትን አማኞች ያመለክታሉ። አምስቱ ሞኞች ክርስቶስ በፍጥነት ይመለሳል ብለው ያላሰቡና ብዙ ለመጠበቅ ያልተዘጋጁ አማኞችን ይመስላሉ። (እስካሁን 2000 ዓመታት አልፈዋል።) እውነተኛ የክርስቶስ ተከታይ የመሆኑ ምልክት፥ ሁልጊዜም ለክርስቶስ ምጽአት ተዘጋጅቶ መኖር ስለሆነ፥ ያልተዘጋጁ ሰዎች የሰርጉን በዓል (የክርስቶስን መንግሥት) በረከቶች የመቋደስን ዕድል ተነፍገዋል። ለ. የክርቶስን ምጽአት በምንጠባበቅበት ጊዜ፥ ታማኝ መጋቢዎች ልንሆን ይገባል (ማቴ. 25፡14-30)። በሁለተኛ ምሳሌው፥ ክርስቶስ ራሱን ሩቅ አገር ከሄደ ሀብታም ጌታ ጋር ያነጻጽራል። ባሪያዎቹን ጠርቶ ለእርሱ ጥቅም እንዲያውሉ የተለያዩ ሀብቶችን ሰጣቸው። ከሩቅ አገር ጉዞው ሲመለስ፥ እያንዳንዱ ባሪያ ሀብቱን እንዴት እንደ ተጠቀመበት በመገምገም የሽልማት ወይም የፍርድ ውሳኔ ሰጠ። በተመሳሳይ መንገድ፥ ክርስቶስ ለእያንዳንዱ የእርሱ ተከታይ ልዩ ስጦታዎችን ሰጥቶ ወደ ሰማይ ሄዷል። እነዚህ ስጦታዎች የተሰጡን ለራሳችን ጥቅም ሳይሆን ጌታችንን እንድናገለግልባቸው ነው። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሚመለስበት ጊዜ፥ በሕይወታችን ውስጥ ለእርሱ ምን እንዳተረፍን ይገመግመናል። አንዳንዶች ታላላቅ ሽልማቶችን ያገኛሉ። የክርስቶስ እውነተኛ ተከታዮች ያልነበሩና ሕይወታቸውን ለእርሱ ጥቅም ያላዋሉ ግን በዘላለማዊ ሞት ይቀጣሉ። እዚህ ላይ ልንገነዘባቸው የሚገቡን ሦስት ዐበይት እውነቶች አሉ። በመጀመሪያ፥ እያንዳንዱ የክርስቶስ ተከታይ የሚጠቀምባቸው ሀብቶች ተሰጥተውታል። እነዚህ ሀብቶች ገንዘብ፣ ጊዜ፥ ወይም ለቤተ ክርስቲያን ኣገልግሎት የሚውሉ መንፈሳዊ ስጦታዎች ሊሆኑ ይችላሉ። ሁለተኛ፥ ለእያንዳንዱ አማኝ የተለያዩ ሀብቶች ተሰጥተውታል። ለእያንዳንዱ ባሪያው ምን መስጠት እንዳለበት የሚወስነው ክርስቶስ ነው። ይህም አንዱ ባሪያ ባገኘው ሀብት ሊኩራራ፥ ሌላው ደግሞ ሊቀና እንደማይገባ ያሳያል። ሦስተኛ፥ እግዚአብሔርን የሚያሳስበው ማን የበለጠ ወይም ያነሰ ሀብት አለው? የሚለው ሳይሆን፥ እርሱ የሰጠንን በታማኝነት መጠቀማችን ነው። የውይይት ጥያቄ፡- እግዚአብሔር ለእንተ ብቻ የሰጣቸውን ሀብቶች ዘርዝር። እነዚህን ሀብቶች ለክርስቶስ ክብርና ለመንግሥቱ መስፋፋት እየተጠቀምክ ያለኸው እንዴት ነው? ሐ. ክርስቶስ በሚመለስበት ጊዜ አንዳንዶች ወደ ዘላለማዊ በረከት፥ ሌሎች ወደ ዘላለማዊ ፍርድ ይሄዳሉ (ማቴ. 25፡31-46)። በአይሁዶች ባሕል፥ በጎች (የበለጠ ጠቀሜታ አላቸው)፥ ስለዚህ ጌታ በፍየሎች ምሳሌ የተናገረው እርሱ በሚመለስበት ጊዜ የሚሆነውን ሁኔታ ለማሳየት ነበር። እርሱ በበጎች የተመሰሉትን እውነተኞች የእግዚአብሔርን ሕዝብ፥ ከፍየሎች ከተመሰሉት የማያምኑ ሰዎች ይለያል። ለመሆኑ ክርስቶስ ጥሩዎችን ከመጥፎዎቹ ለመለየት የሚጠቀምበት መመዘኛ ምን ነበር? መመዘኛው ተግባራቸው ይሆናል። ለተራቡት፥ ለታመሙትና ለታሰሩት ርኅራኄን ያሳዩት ሰዎች የዘላለምን ሕይወት ያገኛሉ። ርኅራኄን ያላሳዩት ግን በዘላለማዊ ሞት ይቀጣሉ። ይህ ማለት በሰናይ ምግባራችን ወደ መንግሥተ ሰማይ ልንገባ እንችላለን ማለት ነው? አይደለም። በሥራ ሳይሆን በእምነት እንደዳንን ግልጽ ነው (ኤፌ. 2፡8-9)። በዚህ ስፍራ ኢየሱስ ሦስት ዐበይት እውነቶችን አስተምሯል። በመጀመሪያ፥ በእግዚአብሔር ቤተሰብ እርስ በርሳችን ልንዋደድና ልንረዳዳ እንደሚገባን ያሳያል። ሁልጊዜም የተቸገሩትን እንድንረዳ የተጠየቅን ብንሆንም፥ «ታናናሾች» [ማቴ. 25፡45] የሚለው ክርስቲያኖችን እንጂ ሁሉንም ሰው አያመለክትም።) ክርስቲያኖች ከሚደርስባቸው ስደት የተነሣ፥ ብዙዎች ሥራቸውን አጥተው ይራቡና መጠለያ አጥተው ይቸገሩ፥ ሌሎች ደግሞ ይታሰሩ ነበር። ኢየሱስ ስደትን በመፍራት እነዚህን ሰዎች ቸል ከማለት ይልቅ፥ ተከታዮቹ ቀርበው ሊረዷቸው እንደሚገባ አስተምሯል። ሁለተኛ፥ ኢየሱስ የክርስቶስን አካል ኣንድነት እያሳየ ነው። ክርስቲያኖችን መርዳት ኢየሱስን መርዳት ነው። ሌላው ክርስቲያን በችግር ላይ እያለ አለመርዳት ማለት ደግሞ ኢየሱስን አለመርዳት ነው። ኢየሱስ በሌላው ክርስቲያን ውስጥም ነውና። ሦስተኛ፥ እውነተኛ የክርስቶስ ተከታዮች መሆናችንን ከሚያሳዩ ዐበይት ማስረጃዎች ኣንዱ፥ እርስ በርሳችን የምንቀራረብበት መንገድ ነው። ለራሳችን ፍላጎት ብቻ የምናስብ ብልጦች ከሆንን፥ ክርስቶስና የእርሱ ፍቅር በልባችን ውስጥ እንደሌለ ግልጽ ነው። ስለሆነም፥ በመልካም ሥራችን የዘላለምን ሕይወት ከማግኘት ይልቅ፥ መዳናችንን በአኗኗራችን እናሳያለን። የክርስቶስ ተከታዮች መሆናችንን የምንመሰክረው በቀዳሚነት በምንናገራቸው ቃላት ወይም በምንዘምራቸው መዝሙሮች ሳይሆን፥ ሌሎችን ክርስቲያኖችና ተጎጂዎችን በምናስተናግድበት መንገድ ነው። የክርስቶስ ዓይነት የርኅራኄ ልብ ከሌለን፥ የእርሱ ተከታዮች አለመሆናችንና እርሱን አለማወቃችን ግልጽ ነው። የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ይህ ዛሬ ፍቅራችንን እንዴት ማሳየት እንደሚገባን ጠንካራ ማስጠንቀቂያ የሚሆነን እንዴት ነው? ለ) ሌሎች ክርስቲያኖችንና ድሆችን ለመርዳታ እጅህን የምትዘረጋባቸውን መንገዶች ዘርዝር። ሐ) ወንጌላውያን ክርስቲያኖች ብዙውን ጊዜ ድሆችን ለመርዳት ባለመፈለጋቸው ይታወቃሉ። ይህ የሆነው ለምንድን ነው? ይህንን ዝና ለውጠን እርስ በርሳችን በመዋደዳችንና ድሆችን በመውደዳችን ልንታወቅ የምንችለው እንዴት ነው? (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ ስለዚህ አስደናቂ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡)

ክርስቶስ ላልተጠበቀው ምጽአቱ ስለ መዘጋጀት የሚያስረዳ ምሳሌ ተናገረ (ማቴ 25:1-46) Read More »

ክርስቶስ ስለ መጨረሻው ዘመን ተናገረ ማቴ. 24:1-51

ክርስቶስ ስለ ቤተ መቅደሱ ሙሉ በሙሉ መፈራረስ በተነበየበት ወቅት፥ ደቀ መዛሙርቱ በድንጋጤ መራዳቸው አይጠራጠርም። ቤተ መቅደሱ በጥንቱ ዘመን ከነበሩት ታላላቅ ሕንጻዎች አንዱ ነበር። እግዚአብሔርም የሚመለክበት ስፍራ ነበር። እግዚአብሔር እንዴት ይህ ቤተ መቅደስ እንዲፈርስ ይፈቅዳል? ይህ የሚሆነውስ መቼ ነው? ደቀ መዛሙርቱ ክርስቶስ ወደፊት ስለሚፈጸሙት ክስተቶች እንዲያብራራላቸው ጠየቁት። ክርስቶስ ጥያቄያቸውን የመለሰው በቅርቡ የሚፈጸመውን የቤተ መቅደስ መውደም ገና ከሚሆነው የእርሱ ምጽአት ጋር በማጣመር ነበር። (ስለ ምጽአቱ ከተነበየ አሁን 2000 ዓመታት አልፎታል።) ትንቢትን መተርጎም በጣም አስቸጋሪ ከሚሆንባቸው ምክንያቶች አንዱ፥ በአነስተኛ የጊዜ ማእቀፍ ውስጥ (with little time frame) አንዳንድ ትንቢት በፍጥነት ሊፈጽሙ ሲችሉ፥ ሌሎች ብዙ ጊዜ የሚወስዱ መሆናቸው ነው። በተጨማሪም አንዳንድ ጊዜ አንድ ትንቢት ሁለት ወይም ከዚያ የበለጡ ፍጻሜዎች ያሉት መሆኑ ትንቢትን የበለጠ ያወሳስበዋል። ምሑራን በእነዚህ ትንቢቶች አተረጓጎም ላይ የሚከራከሩ ሲሆን፥ አንዳንዶች ይህ ሁሉ በ 70 ዓ.ም. ሮማውያን ቤተ መቅደሱን ባፈራረሱበት ጊዜ እንደ ተፈጸመ ይናገራሉ። ሌሎች ደግሞ ኢየሩሳሌም በተደመሰሰችበት ጊዜ ከትንቢቶቹ ብዙዎቹ በከፊል ቢፈጸሙም፥ አብዛኛዎቹ ግን በመጨረሻው ዘመን የሚፈጸሙ መሆናቸውን ያስረዳሉ። እነዚህ ትንቢቶች መቼና እንዴት ይፈጸማሉ? በሚሉ ዝርዝር አሳቦች ላይ ብዙ ውዝግቦች ታይተዋል። እነዚህን ትንቢቶች የምንረዳበት መንገድ በቀደሚነት እስራኤል ወደፊት በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ ስለሚኖራት ድርሻ ባለን ግንዛቤ ላይ የተመሠረተ ይሆናል። ትንቢቱ እስኪፈጸም ድረስ መረዳቱ አዳጋች ስለሆነ፥ በዚህ ጉዳይ ላይ ከእኛ የተለየ አቋም ለሚይዙት የጥላቻ ስሜት ሊኖረን አይገባም። ከክርስቶስ ጋር የነበሩት ደቀ መዛሙርት፥ እስከ ሞቱና ትንሣኤው ድረስ ትንቢትን እንዴት እንደ ፈጸመ ለመገንዘብ ከተቸገሩ፥ እኛም ትንቢቶቹ ከመፈጸማቸው በፊት መቼና እንዴት እንደሚፈጸሙ ለማወቅ መቸገራችን የማይቀር ነው። ክርስቶስ ትንቢቶቹ የሚፈጸሙበትን ትክክለኛ የጊዜ ማእቀፍ ወሰን ሳይሰጥ፥ ለደቀ መዛሙርቱ አመልካች «ምልክቶችን» ብቻ ሰጥቷቸዋል። ከምልክቶቹ መካከል የሚከተሉት ይገኙባቸዋል፡- ሀ. ብዙ የሐሰት መሢሖች ይነሣሉ። በ70 ዓ.ም. ኢየሩሳሌም ከመደምሰሷ በፊት ብዙ ሰዎች የተስፋ ቃል የተሰጣቸው መሢሖች መሆናቸውን እየገለጹ ለሥልጣን ቢሯሯጡም፥ ከሮማውያን እጅ አላመለጡም። ክርስቶስ ከመመለሱ በፊትም ብዙዎች ይህን ሥልጣን ለራሳቸው ለማድረግ ይሽቀዳደማሉ። ዓለም መጽሐፍ ቅዱስ «ሐሳዊ – መሢሕ» ወይም «የዐመፅ ሰው» እያለ የሚጠራውን ሐሰተኛ የራሷ መሢሕ አድርጋ ትቀበላለች ራእይ 12፤ 2ኛ ተሰ. 2፡3-12)። ለ. ጦርነት፥ የጦርነት ወሬ፥ አብዮትና የቤተሰብ ጠብ ይበዛል። ሐ. በክርስቶስ ተከታዮች ላይ የሚደርሰው ስደት ይጨምራል። ዓለም ክርስቲያኖችን መታገሥ ተስኖት ያሳድዳቸዋል፥ ይገድላቸዋል። መ. የክርስቶስ ተከታዮች ነን የሚሉ ብዙ ሰዎች እምነታቸውን ይክዳሉ። ሠ. ብዙ ሰዎችን የሚያታልሉ በርካታ የሐሰት አስተማሪዎችና ነቢያት ይነሣሉ። እነዚህ ሐሰተኞች ተአምራትን ሳይቀር ሊሠሩ ይችላሉ (ማቴ. 24፡24)። ረ. የዓለማውያን ክፋት የሚጨምር ሲሆን፥ ብዙ ክርስቲያኖች ለክርስቶስና ለወንጌሉ የነበራቸው ፍቅር ይቀዘቅዛል። ሰ. ወንጌሉ በሁሉም አገር ለሚገኙ ጎሳዎች ይሰበካል። ክርስቶስ ይህ ከመጨረሻው ዘመን ዐበይት መረጃዎች አንዱ እንደሆነ ገልጾአል። በአሁኑ ዘመን በዓለም ለሁሉም ጎሳዎች ማለት ይቻላል ወንጌል ተሰብኮ የተወሰኑ ክርስቲያኖች አምነዋል። ስለሆነም፥ ይህ ትንቢት በዘመናችን ሊፈጸም እንደ ቀረበ ልንመለከት እንችላለን።) ሸ. «ች» የተባለ፥ ሃይማኖታዊ ርኩሰት ይከሰታል። አብዛኞቹ ምሑራን ኢየሩሳሌም በተደመሰሰችና የሮም ወታደሮች ወደ ቤተ መቅደሱ ውስጥ ገብተው ባወደሙት ጊዜ፥ ይህ ትንቢት መጀመሪያ እንደ ተፈጸመ ያምናሉ። (እንዲሁም ዳንኤል ስለዚህ ጉዳይ የሰጠው ትንቢት በ168 ዓ.ዓ አንቲዮስስ ኤጲፋነስ በኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ውስጥ በመሠዊያው ላይ አሳማ በሠዋ ጊዜ፥ በቀዳሚነት እንደ ተፈጸመ ይናገራሉ።) አንዳንድ ምሑራን፥ ደግሞ ይህ ክርስቶስ ከመመለሱ በፊት ኣይሁዶች ሌላ ቤተ መቅደስ እንደሚገነቡና ሐሳዊ መሢሕ እንደሚያረክሰው የሚያመለክት ነው ይላሉ። ቀ. ክርስቶስ ሕዝቡ ከአደጋው እንዲሸሽ አዝዟል። ማቴዎስ ይህን መጽሐፍ ከጻፈ በኋላ፥ ብዙም ሳይቆይ በኢየሩሳሌም ጦርነት ተቀሰቀሰ። በዚህን ጊዜ ክርስቲያን የሆኑ አይሁዶች ምን ማድረግ ነበረባቸው? በኢየሩሳሌም ተቀምጠው ከሌሎች ኣይሁዶች ጋር ይሙቱ ወይስ ይሽሹ? አንዳንድ ምሑራን ክርስቶስ ሸሽተው ሕይወታቸውን እንዲያተርፉ እንዳዘዛቸው ያምናሉ። ይህ የመጨረሻዎቹን ትግሎች ፍጥነት ያሳያል።   በ. የመጨረሻው ዘመን አስፈሪ በመሆኑ፥ እግዚአብሔር ጊዜውን ባይገድብ ኖሮ፥ በምድር ላይ አንድም ሰው አይድንም ነበር። «ምርጦቹ» በእነዚህ ቀውጢ ቀናት ውስጥ ስለሚኖሩ እግዚአብሔር ጊዜውን ይገድበዋል። ተ. የክርስቶስ ተመልሶ መምጣት ድንገተኛና ያልተጠበቀ (እንደ መብረቅ) ይሆናል። ይህም ሆኖ፥ የምጽአቱን መቃረብ የሚያሳዩ በቂ ምልክቶች ይኖራሉ። (በሰማይ የአሞራዎች ማንዣበብ የሞተ ነገር መኖሩን ያመለክታል።) እንዲሁም በበለስ ዛፍ ላይ የሚገኙ ቅጠሎች አንድን ወቅት እንደሚያሳዩ ሁሉ፥ ክርስቶስ የሰጣቸው እነዚህ ምልክቶችም በቅርብ እንደሚመለስ ያሳያሉ። ቸ. ፀሐይን፥ ጨረቃንና ከዋክብትን የሚያናጋ ታላቅ የዓለም (cosmic) ውድመት ይሆናል። ኀ. ክርስቶስ በሙሉ ኃይሉና ሥልጣኑ በደመናት ይገለጻል። በዚያን ጊዜ መጀመሪያ ሲመጣ እንደሆነው ሁሉ ሰብአዊነቱ ሳይሆን አምላክነቱ ይገለጣል። በመላእክትና በመለከት ድምፅ ታጅቦ ይመጣል። የሁሉም አገር ሰዎች ክርስቶስን በሚያዩበት ጊዜ ያለቅሳሉ። የሚያለቅሱት በንስሐ ይሁን ስለሚፈረድባቸው የምናውቀው ነገር የለም። ነ. የተመረጡት ከዓለም ተለይተው ወደ ሰማይ ይነጠቃሉ። ክርስቶስ «ይህ ሁሉ እስኪሆን ይህ ትውልድ አያልፍም» (ማቴ. 24፡34) ሲል ምን ማለቱ ነው? የሚለው ጥያቄ ብዙ አነጋግሯል። በኣጠቃላይ አራት ዐበይት አመለካከቶች ይንጸባረቃሉ። በመጀመሪያ፥ ክርስቶስ በኣንድ ትውልድ ጊዜ ውስጥ ኢየሩሳሌም በሮማውያን እንደምትወድም የሚናገሩ ትንቢቶች እንደሚፈጸሙ መግለጹ ነው የሚሉ አሉ። ሁለተኛ፥ ሌሎች ደግሞ የተጠቀሰው ትውልድ የክርስቶስን ዳግም ምጽኣት የሚያሳዩ ምልክቶች በሚጀምሩበት ጊዜ የሚኖረው እንደሆነ ያስባሉ። ስለሆነም፥ ምልክቶቹ በተጀመሩ 40 ዓመታት ውስጥ ክርስቶስ ይመለሳል ብለው ያስባሉ። ሦስተኛ፥ «ትውልድ» የሚለው ቃል «ዘር» ተብሎ ሊተረጎም ስለሚችል፥ ክርስቶስ እርሱ ከመመለሱ በፊት የአይሁድ ዘር እንደማይጠፋ መግለጹ ነው ይላሉ። አራተኛ፥ አንዳንዶች የሌሎችን አመለካከቶች ውህድ አድርገው ያዩታል። የክርስቶስ ትንቢቶች የ70 ዓመተ ምሕረቱን የኢየሩሳሌምን መደምሰስና እርሱ የሚመለስበትን የመጨረሻ ዘመን የሚያጠቃልሉ ስለሆኑ፥ ብዙ ደቀ መዛሙርት የኢየሩሳሌምን ውድመት እንደሚመለከቱ ያስተምራሉ። ስለሆነም፥ የክርስቶስን ዳግም ምጽአት ይመለከቱ ዘንድ እግዚአብሔር የአይሁድን ዘር ከጥፋት ይጠብቃል። ኘ. ክርስቶስ መቼ እንደሚመለስ በርግጠኝነት የሚያውቅ ማንም የለም። ይህ ክርስቶስ በዚህ ጊዜ ይመጣል ብለን እንዳንናገር ሊያስጠነቅቀን ይገባል። (በታሪክ ሁሉ ብዙ ሰዎች እንዲህ ዓይነት ሙከራዎችን አካሂደው መሳሳታቸው ታውቋል። ይህ በክርስቲያኖች መካከል ብዙ ውዝግብ ከማስከተሉም በላይ፥ የክርስቲያኖችና የክርስቶስን ስም ያሰድባል።) ምሑራን ክርስቶስ ስለሚመለስበት ጊዜ እንደማያውቅ በተናገረው አሳብም ላይ ይከራከራሉ። «ክርስቶስ አምላክ ከሆነ፥ እንዴት አያውቅም?» ብለው ይጠይቃሉ። ለዚህ ጥያቄ ቀላል ማብራሪያ ማቅረብ አይቻልም። ምናልባትም ከሁሉም የሚሻለው ማብራሪያ፥ ክርስቶስ በምድር ላይ በሰብአዊ ማንነቱ በነበረበት ጊዜ፥ መለኮታዊ እውቀቱን እንደ ወሰነ የሚያመለክተው አሳብ ይሆናል። ስለሆነም፥ እንደ ሰው አለማወቁን ሊናገር ይችላል። አሁን ግን በምልዐተ መለኮቱ በሚኖርበት ሰማይ የሚመለስበትን ጊዜ ያውቃል። አ. ክርስቲያኖች ሊያስተውሉት የሚገባው ከሁሉም የላቀው እውነት፥ ምን ጊዜም መዘጋጀት እንዳለባቸው ነው። ለጉዞ ወጥቶ ባልተጠበቀ ሰዓት እንደሚመጣ ባለሀብት፥ ክርስቶስ በየትኛውም ሰዓት ሊመጣ ይችላል። ክርስቶስ በሚመለስበት ጊዜ እንዳናፍርና ድንገተኛ ሆኖብን እንዳንደናገር፥ በየቀኑ ክርስቶስ ሊመጣ እንደሚችል እያሰብን ልንኖር ይገባል። እርሱ በሚመለስበት ጊዜ በታማኝነት እያገለገልነው ከተገኘን ሽልማቱን እንቀበላለን። ይህ ካልሆነ ግን የከፋ ቅጣት ይጠብቀናል። የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ክርስቶስ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ እንደሚመጣ ብናውቅ ኖር፥ እንዴት ኣድርገን የኣስተሳሰባችንና የተግባራችንን ሁኔታ እንለውጥ ነበር? ለ) ይህ ክፍል ክርስቶስ ዛሬ እንደሚመጣ እያሰብን እንድንኖር የሚያስጠነቅቀን እንዴት ነው? ሐ) አብያተ ክርስቲያኖቻችን ክርስቶስ በእውነት እንደሚመጣ እያሰቡ ቢኖሩ፥ ትኵረታቸውንና ተግባራቸውን እንዴት ይለውጣሉ? (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ ስለዚህ አስደናቂ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡)

ክርስቶስ ስለ መጨረሻው ዘመን ተናገረ ማቴ. 24:1-51 Read More »

ኢየሱስ ፈሪሳውያንንና የኦሪት ሕግ መምህራንን ነቀፈ (ማቴ. 23:1-39)

የክርስቶስን ሕይወት የመጨረሻ ሳምንት ሁኔታ ባጠናንበት ወቅት ማቴዎስ የሃይማኖት መሪዎች ከክርስቶስ ጋር ያካሄዷቸውን አያሌ ግጭቶች እንዴት እንደገለጸ ተመልክተናል። አይሁዶች፥ «ክርስቶስ መሢሕ ከሆነ፥ ለምን ተሰቀለ? እርሱ የብሉይ ኪዳን ትንቢቶች ፍጻሜ ከሆነ፥ የሃይማኖት መሪዎች ለምን አልተከተሉትም?» እያሉ ይጠይቁ ነበር። ማቴዎስ የሃይማኖት መሪዎቹ ክርስቶስ ምን ዓይነት መሢሕ እንደነበረ እንዳልተገነዘቡና፥ ከሁሉም በላይ በክርስቶስ ላይ የነበራቸውን ቅናት በመግለጽ ለእነዚህ ጥያቄዎች የመሰላቸውን መስጠታቸውን ጽፎአል። የሃይማኖት መሪዎቹ ክርስቶስን የተቃወሙት አንዳች ስሕተት ስላገኙበት ሳይሆን፥ እግዚአብሔርን ለመከተልና ሰዎችን ለመርዳት ባልነበራቸው ፍላጎት ተመርተው ነበር። ማቴዎስ 23-25 የክርስቶስን ትምህርት የሚያቀርብ የመጨረሻው ዐቢይ ክፍል ነው። ይህ ክፍል የፈሪሳውያንን ሃይማኖትና ስለመጨረሻው ዘመን የሚያስተምሩትን ትምህርት መከተል እንደማይገባን ያስጠነቅቃል። ክርስቶስ በሃይማኖት መሪዎች ላይ ስምንት የ«ዋይታ» ፍርዶችን አስተላልፎአል (ማቴ. 23) ክርስቶስ በሥልጣን ላይ የተቀመጡት ማለትም (የሃይማኖትም ሆነ የፖለቲካ) ሰዎች በሚያጠፉበት ጊዜ ተከታዮቹ ዓመፅ እንዲያካሂዱ አላስተማረም! ነገር ግን ደቀ መዛሙርቱ በመታዘዝና ተቀባይነትን በማግኘት መካከል ያለውን ልዩነት እንዲማሩ ነግሯቸዋል። ለሃይማኖት መሪዎች የሃይማኖት ሥልጣን የሰጣቸው እግዚአብሔር ነው። ስለሆነም፥ በዚያን የታሪክ ወቅት እግዚኣብሔር ፈሪሳውያን «በሙሴ ወንበር ላይ ተቀምጠው»፥ በሕዝቡ ላይ ሃይማኖታዊ ሥልጣን እንዲያካሂዱ ፈቅዶላቸዋል። ነገር ግን ለፈሪሳውያንና ሌሎች የሃይማኖት መሪዎች መታዘዝ ማለት በሚያደርጓቸውን እኩይ ተግባራት መሳተፍን አይጨምርም፡፡ እንደ ብዙ ሰባኪዎች፥ ፈሪሳውያን የሚመላለሱት በሁለት ደረጃዎች ነበሩ። ሲያስተምሩ ወይም ሲሰብኩ፥ በሰዎች ላይ ብዙ ትእዛዛትን ያሸክሙ ነበር። እነርሱ ግን በግል ሕይወታቸው አይፈጽሙትም ነበር። እነዚህ ሰዎች ሕዝብ እንዲጾም እያዘዙ እንደማይጾሙ፥ ወይም ወንጌሉን ለጎረቤቶቻቸው እንዲመሰክሩ እየተናገሩ ራሳቸው እንደማይመሰክሩ ሰባኪዎች ናቸው። የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ዛሬ ሰባኪዎችና አስተማሪዎች ብዙውን ጊዜ ተግባራዊ የማያደርጓቸውን ነገሮች እንዴት እንደሚሰብኩ ምሳሌዎችን ስጥ። ለ) እንደሚገባቸው በመንፈሳዊነት ለማይመላለሱ መሪዎች ክርስቶስ ምላሻችን (በተለይም ወጣቶች) ምን መሆን እንዳለበት ኣስተማረ? ክርስቶስ ተከታዮቹ የሃይማኖት መሪዎችን በመምሰል ለሰው ምስጋናና ክብር እንዳይኖሩ ተናግሯል። በገላትያ 1፡10 ጳውሎስ፥ «ሰውን ወይስ እግዚአብሔርን አሁን እሺ አሰኛለሁን? ወይም ሰውን ደስ ላሰኝ እፈልጋለሁን? አሁን ሰውን ደስ ባሰኝ የክርስቶስ ባሪያ ባልሆንሁም» ብሏል። መሪዎች ሁለት ምርጫዎች አሏቸው። እግዚአብሔርን ወይም ሰዎችን ደስ ለማሰኘት ወስነው መሥራት፡፡ ፈሪሳውያን በአብዛኛው ለአገልግሎት የሚነሣሡት የሰዎችን ምስጋና ለማግኘት ነበር። ስለሆነም የሰዎችን ትኩረት ለመሳብ ሲሉ በግንባራቸው ላይ ሰፋፊ አሸንክታቦችን ያደርጉ ነበር (ዘዳግ. 6፡4-9 አንብብ።) እንዲሁም በብዙ ጥለት ያጌጡ ማራኪ ሃይማኖታዊ ልብሶችን ይለብሳሉ። በምኩራብ ውስጥ በሚሰበሰቡበት ጊዜ፥ «እዩን፥ እኛ የሃይማኖት መሪዎች ነን» በሚል አመለካከት የፊት ወንበር ይዘው ይቀመጣሉ። በዚህም ከአመራር የሚገኘውን ክብር ይፈልጉ ነበር። ሰዎች «ረቢ» (መምህር) እያሉ በአንቱታ ይጠሯቸዋል። ዛሬም ቢሆን በትምህርታቸው የገፉ ሰዎች «ዶክተር» ተብለው ለመጠራት እንደሚፈልጉት ማለት ነው። ክርስቶስ ሰዎች እንዲህ ዓይነት አመለካከት እንዳይኖራቸው አስጠንቅቋቸዋል። ስለዚህ ደቀ መዛሙርቱ በሁለት መንገዶች ይህን አመለካከት መዋጋት ነበረባቸው። በመጀመሪያ፥ በሥራዎቻቸው ሁሉ የእግዚአብሔርን ታላቅነት ማጉላት ያስፈልጋቸው ነበር። እግዚአብሔር ሰብአዊ መምህራንን ቢጠቀምም፥ መንፈሳዊ ስኬት ሊገኝ የሚችለው እግዚአብሔር በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ያስተማረ እንደሆነ ነው (ዮሐ 14፡26)። እግዚአብሔር በሕዝቡ ላይ ሰብአዊ መሪዎችን ቢሾምም፥ የሁሉም መሪ የሆነው እርሱ ብቻ ነው። ሁለተኛ፣ የክርስቶስ ተከታዮች ኃይል፥ ከብርና ሀብት ከመፈለግ ይልቅ፥ ትሕትናንና ዝቅ ብሎ ማገልገልን ሊያከብሩ ይገባል። ብዙውን ጊዜ ቢናቁና በሰዎች ዘንድ ባይከበሩም፥ ራሳቸውን የሚያዋርዱ ሰዎች በእግዚአብሔር መንግሥት ከሁሉም ይልቃሉ። የመሪነትን ክብርና ጥቅሞች የሚፈልጉ ሰዎች፥ በእግዚአብሔር ዓይን ምንም ካልተማሩት ምእመናን አንሰው ይታያሉ። የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በዚህ የሰይጣን ወጥመድ ውስጥ የወደቀን አንድ መሪ በምሳሌነት ጥቀስ። ለ) ሁሉም የቤተ ክርስቲያን መሪዎች በትሕትና እግዚአብሔርን ቢያከብሩ የቤተ ክርስቲያን አመራር እንዴት ሊለወጥ ይችላል? ክርስቶስ በፈሪሳውያን ላይ ሰባት የዋይታ ፍርዶችን ሰንዝሯል። (የተጠቀሱት ስምንት ዋይታዎች ሲሆኑ፥ ቀጥለን እንደምንመለከተው፥ አንደኛው ዋይታ በመጀመሪያው መጽሐፍ ውስጥ ያልተካተተ ይመስላል።) «ዋይታዎች» ከፍተኛ ቅጣት ያስከተሉ የፍርድ መግለጫ ቃላት ናቸው። በእነዚህ በሰባቱ ዋይታዎች ክርስቶስ ፈሪሳውያንን «ግብዞች» ብሏቸዋል። በግሪክ ቋንቋ “ግብዝ” የሚለው ቃል ከድራማ የመጣ ቃል ነው። በድራማ ውስጥ ሰዎች ያልሆኑትን ባሕርያት ወክለው ይጫወታሉ። መንፈሳዊ ግብዝ በርግጥ መንፈሳዊ ሳይሆን፥ ነኝ እያለ የሚኖር ሰው ነው። ሀ. ዋይታ 1፡ ፈሪሳውያን፣ ሰዎች ወደ እግዚአብሔር መንግሥት እንዳይገቡ ስለ ከለከሉ፥ እግዚአብሔር ይፈርድባቸዋል (ቁ. 13)። ክርስቶስን ለመከተል ባለመፈለጋቸው፥ ፈሪሳውያን ወደ ክርስቶስ መንግሥት አይገቡም። እንዲሁም በሥልጣናቸው ተጠቅመው ሌሎችም በክርስቶስ አምነው እንዳይድኑ ስለሚያደርጉ፥ እግዚአብሔር ከፍተኛ ፍርድ ያደርስባቸዋል። ለ. ዋይታ 2፡ የደካሞችን መብት በመጣሳቸው፥ እግዚአብሔር በፈሪሳውያን ላይ ይፈርዳል (ቁ. 14)። ፈሪሳውያን ረዥም ጸሎት በመጸለይ፥ ምናልባትም እግዚኣብሔር ድሆችን እንዲረዳ በመጠየቅና መንፈሳዊ ለመምሰል በመሞከራቸው ክርስቶስ አውግዞአቸዋል። መሪዎቹ ለድሆች ምሕረትን ስላላሳዩና ሀብታቸውን ለመበዝበዝ ስለጣሩ፥ እግዚአብሔር ፈርዶባቸዋል። ሒ ዋይታ 3፡ ሰዎችን ሃይማኖታዊ ባሪያዎች ስላደረጉ፥ እግዚአብሔር በፈሪሳውያን ላይ ይፈርዳል (ቁ. 15)። ፈሪሳውያን ሰዎችን ወደ አይሁድ እምነትና ወደ ራሳቸው አመለካከት ለመመለስ ከፍተኛ ተግባር ያከናውኑ ነበር። እነርሱም ሰዎች ሕጋቸውን እንዲያከብሩ፥ የፖለቲካ ቡድናቸው አባላት እንዲሆኑ በማስገደድና የሌላ ቡድን አባል ከሆኑ ደግሞ የበደለኝነት ስሜት እንዲሰማቸው በማድረግ በባርነት ይገዟቸው ነበር። በምድር ላይ ሕይወታቸው በሸክሞች የተሞላ ነበር። በተጨማሪም፥ ፈሪሳውያን ተከታዮቻቸው እውነትን እንዳያውቁ በመከልከል ወደ ዘላለማዊ ፍርድ የሚጓዙ የሲዖል ልጆች አድርገዋቸው ነበር። መ. ዋይታ 4፡ የእግዚአብሔርን ሕግጋት ላለመጠበቅ ሊሉ ሕግጋቱን በማጣመማቸው፥ እግዚአብሔር በፈሪሳውያን ላይ ይፈርዳል (ቁ. 16-22)። ጥሩና መጥፎ ስለሆኑት ነገሮች ፈሪሳውያን ሕግጋትን በሚያወጡበት ጊዜ፥ በራሳቸው ሕይወት ላይ ችግርን አስከተሉ። ስለሆነም፥ ሕጉ የተሰጠበትን ምክንያት ዘንግተው፥ ዙሪያ ጥምጥም ተግባር ለማካሄድ የሚችሉበትን ጥረት ሁሉ አደረጉ። ይህን ከሚያደርጉባቸው መንገዶች አንዱ፥ ለእግዚአብሔር ስጦታ ለመስጠት ቃል በሚገቡበት ጊዜ ነበር። ለምሳሌ ያህል አንድ ሰው ለእግዚአብሔር የአንድ ወር ደመወዙን ለመስጠት ቃል ገብቷል እንበል። በኋላ ግን ገንዘቡን ለራሱ ለማስቀረት ይፈልጋል። ፈሪሳውያን ይህን ለማድረግ የሚቻልበት መንገድ እንዳለ ያስተምሩ ነበር። ሁለት ዓይነት ስለቶች እንዳሉ ያስረዳሉ። አንድ ሰው በቤተ መቅደሱ ወይም በእግዚአብሔር ፊት ከተሳለ ስዕለቱን ማፍረስ አይችልም። ነገር ግን አንድ ሰው በቤተ መቅደሱ ውስጥ ባለው መሠዊያ ፊት ከተሳለ፥ ለመጠበቅ አይገድድም ነበር። ስለሆነም ሕጋቸውን እንዳሻቸው እየጠመዘዙ ለእግዚአብሔርና ለሌሎች ሰዎች የገቧቸውን የተስፋ ቃሎች ስለሚጥሱ፥ እግዚአብሔር ፈርዶባቸዋል። ፈሪሳውያን ከራሳቸው አልፈው ሌሎችም ቃላቸውን እንዲያፈርሱ ያስተምሩ ነበር። ሠ. ዋይታ 5፡ በማይጠቅሙ ሕግጋት ላይ እያተኮሩ፥ እግዚአብሔር የሚፈልጋቸውን ዐበይት ጉዳዮች ስለዘነጉ፥ እግዚአብሔር በእነርሱ ላይ ይፈርዳል (ማቴ. 23፡23-24)። ብሉይ ኪዳን አይሁዶች ከምርታቸው የተወሰነውን ድርሻ ለእግዚኣብሔር ኣስራት መክፈል እንዳለባቸው አዝዛል። ፈሪሳውያኑም ይህን ትእዛዝ ለመፈጸም ከእህልና ከቅመም ሁሉ አንድ አሥረኛውን እጅ በጥንቃቄ ይሰጣሉ። ክርስቶስ ይህ መጥፎ ስላልሆነ ሊቀጥሉበት እንደሚገባ ነግሯቸዋል። ነገር ግን ከእግዚአብሔርና ከሰዎች ጋር ተገቢውን ግንኙነት የማድረጉን ዋንኛ ተግባር ባለማከናወናቸው፥ እግዚአብሔር እንደሚፈርድባቸው ገልጾላቸዋል። ፈሪሳውያን ትናንሽ ዝርዝር ጉዳዮችን ለመፈጸም ደፋ ቀና ሲሉ እንደ ምሕረት፣ ፍትሕ፥ ፍቅርና ታማኝነት የመሳሰሉ ዐበይት ተግባራትን ዘንግተው ነበር። ረ. ዋይታ 6፡ ፈሪሳውያን ልባቸውን ሳይለውጡ በውጫዊ ነገሮች ላይ ያተኩሩ ስለነበር፥ እግዚአብሔር ይፈርድባቸዋል (ማቴ. 23፡25-26)። በእግዚአብሔር ዓይኖች ፊት ከሁሉም የሚልቀው የግለሰቡ ልብ፥ አነሣሽ ምክንያት እና ብሎም ከእግዚአብሔርና ከሰዎች ጋር ያለው ግንኙነት ነው። ፈሪሳውያን ግን በውጫዊ ነገሮች ላይ ያተኩሩ ነበር። ብዙውን ጊዜ ሰዎች ልባቸውን ሳይለውጡ፥ መንፈሳውያን መስለው ለመታየት አድርጉ! አታድርጉ የሚሉትን የትእዛዛት ዝርዝር ይጠብቃሉ። እግዚአብሔር ቅድሚያ የሚሰጠው ግን በልብ ለውጥ ላይ ነው። ይህ ተግባራትን እንደሚለውጥ ግልጽ ነው። በሕግጋት ላይ ማተኮሩ የወጪቱን የውስጥ እድፍ ሳያጸዱ፥ ውጭውን የማጥራት ያህል የሞኝነት ተግባር ነው። ሰ. ዋይታ 7፡ ፈሪሳውያን የሰውን ኃጢአተኛ ልብ ሳይነካ ለሃይማኖታዊ ሥርዓት አጽንኦት ስለሚሰጡ፥ እግዚአብሔር ይፈርድባቸዋል (ማቴ. 23፡27-28)። ይህ ከዋይታ 6 ጋር ተመሳሳይ ነው። ፈሪሳውያን ከእጅ መታጠብ አንሥቶ ለሃይማኖታዊ የመንጻት ሥርዓቶች ከፍተኛ ትኩረት ይሰጣሉ። ነገር ግን ለሰው የልብ መንጻት አያስቡም ነበር። አንድ ሰው ለሥርዓታዊ ርኩሰት ከሚጋለጥባቸው መንገዶች አንዱ፥ በመቃብር ላይ በመሄድ እንደሆነ ይታመን

ኢየሱስ ፈሪሳውያንንና የኦሪት ሕግ መምህራንን ነቀፈ (ማቴ. 23:1-39) Read More »

ማቴዎስ 22፡15-46

የሄሮድስ ደጋፊዎች ኢየሱስን ለማጥመድ ያነሡት ሁለተኛው ጥያቄ (ማቴ 22፡15-22) መሪዎቹ ኢየሱስን በሃይማኖታዊ ጥያቄዎች ሊያታልሉት ስላልቻሉ፣ ፊታቸውን ወደ ፖለቲካ መለሱ፡፡ የሄሮድስ ደጋፊዎች በይሁዳ ላይ ለመንገሥ የቻሉት በተለያዩ የሄሮድስ ዝርያዎች ድጋፍ ነበር። የእነዚህ ሰዎች ፍላጎት ሃይማኖት ሳይሆን ፖለቲካ ነበር፡፡ ኢየሱስ በእስራኤል ከነገሠ ኃይላቸው ስለሚከስም፥ ኢየሱስ ለእነርሱ የስጋት ምንጭ ነበር፡፡ ስለሆነም፥ ፖለቲካዊ የቀረጥ ጥያቄ አንሥተው ኢየሱስን ለማጥመድ ሞከሩ። ኢየሱስ የቀረጥን መከፈል ባይደግፍ በሮማውያን ፊት ሊከሱትና ሊያሳስሩት ይችሉ ነበር። የቀረጥን መክፈል ቢደግፍ ደግሞ የሕዝቡን ድጋፍ ያጣ ነበር። ሕዝቡ ይህ የሮማውያንን አገዛዝ እንደሚያሳይ በመገንዘብ ቀረጥ መክፈልን ይጠሉ ነበር፡፡ ቀረጥ በመክፈል የሚታየውንና ምድራዊውን መንግሥት መታዘዝ ያስፈልጋቸው ነበር። ይህም የቄሣር ምስል ባለበት የሮማውያን ሣንቲም ምልክትነት ተገልጾአል። ለመንፈሳዊ መንግሥት ደግሞ ቀዳሚ ታማኝነታቸውን በመስጠት መታዘዝ ያስፈልጋቸው ነበር። የውይይት ጥያቄ:- ሀ) ብዙ ክርስቲያኖች ቀረጦችን ወይም መንግሥት የሚፈልጋቸውን ክፍያዎች ላለመክፈል ይሞክራሉ፡፡ ክርስቶስ ስለዚህ ጉዳይ ምን የሚል ይመስልሃል? ለ) ክርስቲያኖች የሆንን ከምድራዊ መንግሥታችን በላይ መንፈሳዊ መንግሥታችንን እንዴት ልናከብር እንደምንችል ምሳሌ ጥቀስ። ሰዱቃውያን ኢየሱስን ለማጥመድ የሞከሩበት ሦስተኛው ጥያቄ (ማቴ 22፡23-33) ሰዱቃውያን በአብዛኛው የሊቀ ካህንነቱንና የሃይማኖታዊ አመራሩን ሥልጣን የተቆጣጠሩ ካህናት ነበሩ፡፡ ብዙውን ጊዜ ፖለቲካውም በእነርሱ ቁጥጥር ሥር ነበር፡፡ በሥነ መለኮታዊ ክርክር ኢየሱስን ለማጥመድ ሞከሩ። ሰዱቃውያን በትንሣኤ ስለማያምኑ ይህ ጥያቄ የቀረበው እውነትን ለመሻት ሳይሆን ለክርክር ነበር፡፡ በብሉይ ኪዳን ዘመን አንድ ሰው ልጅ ሳይወልድ ቢሞት፣ ወንድምየው ሚስቱን እንዲያገባ ይደረግ ነበር፡፡ በዚህ ጋብቻ የተወለደው የመጀመሪያው ልጅ የሟች ልጅ እንደሆነ ተቆጥር የቤተሰቡን የዘር ሐረግ ይቀጥላል፡፡ ሰዱቃውያን ይህን ሕግ ለመፈጸምና ልጅ ለመውለድ በመሞከር ሰባት ወንድማማቾች አንዷን ሴት ስላገቡበት ሁኔታ የሚተርክ የፈጠራ ታሪክ ነገሩት፡፡ ሁሉም ከሞቱ በኋላ በዳግም ትንሣኤ ይህች ሴት የማን ሚስት ትሆናለች? ሊሉ ጠየቁት። ኢየሱስ ትርጉም የማይሰጥ ሥነ መለኮታዊ ክርክር ለማካሄድ ስላልፈለገ፥ ወደ ጉዳዩ ሥር ዘልቆ የተሳሳተ ሥነ መለኮታዊ ግንዛቤ እንደነበራቸው አመለከተ። በመጀመሪያ የትንሣኤ አካለ ሥጋዊ ጋብቻን እንደማይቀበል አለመገንዘባቸውን አወዝ፡፡ ከሙታን የተነሡ ሰዎች ሚስት አግብተው ልጅ እንደማይወልዱና እንደ መላእክት እንደሚሆኑ ገለጸላቸው። ሁለተኛ፥ በትንሣኤ ባለማመናቸው ሙሉ በሙሉ መሳሳታቸውን በማመልከት ወቀሳቸው። ኢየሱስ ሰዱቃውያን እንደ ቅዱሳት መጻሕፍት የሚቀበሉትን የዘፍጥረት 1 መጽሐፍ በመጠቀም (ከሙሴ ሕግ ውጭ ያሉትን መጻሕፍት ሁሉ አይቀበሉም)፣ አብርሃም፥ ይስሐቅና ያዕቆብ ከሞቱ በኋላ እንደ ሕያዋን እንደተጠቀሱ አሳያቸው። እግዚአብሔር “እኔ የአብርሃም፥ የይስሐቅና የያዕቆብ አምላክ ነበርኩ” ሳይል፥ “እኔ የአብርሃም፥ የይስሐቅና የያዕቆብ አምላክ ነኝ” ብሏል። እነዚህ ሰዎች በሥጋ ቢሞቱም በመንፈሳቸው ሕያዋን ሆነው የትንሣኤን እውነተኛነት ያረጋግጣሉ። ፈሪሳውያን ኢየሱስን ለማጥመድ ያነሡት አራተኛው ጥያቄ (ማቴ 22፡34-40) ከብሉይ ኪዳን ሕግጋት እጅግ አስፈላጊው የትኛው ነው? በሚለው ጥያቄ ላይ የሃይማኖት መሪዎች በተደጋጋሚ ይከራከሩ ነበር። እነዚህ ሰዎች የእግዚአብሔርን ሕግጋት የሚያስፈልጉና የማያስፈልጉ ብለው ለሁለት ለመክፈል በመቻላቸው አንዳንዶቹን ሊጠብቁና ሌሎቹን ሊተዉ እንደሚችሉ ያስቡ ነበር፡፡ በተጨማሪም፣ አርቀው ከሚመለከቱት አምላካቸው ጋር የሚኖራቸው ግንኙነት ብዙም አያሳስባቸውም ነበር። ምክንያቱም ለእነርሱ ዋናው ነገር ሕግጋትን መጠበቅ ነበር፡፡ ኢየሱስ ግን የእግዚአብሔርን ሕጋት ሁሉ የሚያካትቱ ሁለት ትእዛዛት ነበሩት። እነዚህም አድርጉ አታድርጉ በሚባሉ ዝርዝሮች ብቻ የሚፈጸሙ ሳይሆኑ፥ በግንኙነት ላይ የተመሠረቱ መሆናቸውን በመግለጽ የሥነ መለኮት አስተምህሯቸውን አናግቷል። በፍጹም ማንነትህ እግዚአብሔርን አክብር የሚለው ትእዛዝ፥ ሁሉንም አምልኮና ከእግዚአብሔር ጋር የመዛመድን ሕግጋት ያካትታል። ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ የሚለው ደግሞ ከሰዎች ጋር የሚኖረንን ግንኙነት ያጠቃልላል። ፍቅር ልባችንን እስከገዛው ድረስ፥ ተግባራችን ትክክል ስለሚሆን፥ ሌሎች ሕግጋት በሙሉ ተግባራዊ ይሆናሉ። የውይይት ጥያቄ:- ሀ) ከእግዚአብሔር ጋር ካለን ግንኙነት ጋር የሚዛመዱ ትእዛዞችን ዘርዝር። በሙሉ ልብ መውደድ የሚለው ትእዛዝ እነዚህን ትእዛዞች የሚፈጽመው እንዴት ነው? ለ) ከሌሎች ሰዎች ጋር ካለን ግንኙነት ጋር የሚዛመዱ ትእዛዞችን ዘርዝር። ራሳችንን የምንወደውን ያህል ሌሎችንም መውደድ አለብን የሚለው ትእዛዝ እነዚህን ትእዛዞች የሚፈጽመው እንዴት ነው? ኢየሱስ የኃይማኖት መሪዎቹን አንድ ጥያቄ ጠየቃቸው (ማቴ. 22፡41-46) ኢየሱስ የኃይማኖት መሪዎቹን በጥያቄዎቻቸው በሙሉ ከረታ በኋላ፥ ጥያቄ የመጠየቁ ተራው የእርሱ ሆነ። መሲሑ የማን ልጅ እንደሆነ ጠየቃቸው። መሲሑ የዳዊት ልጅ ነው የሚለውን የተለመደውን መልሳቸውን ሰጡት። ነገር ግን ኢየሱስ ስለ መሲሑ በመዝ. (110)፡1 የተተነበየውን በመጥቀስ፥ እግዚኣብሔር መለኮትነቱን ለማመልከት «ጌታ» ብሎ እንደጠራው ነገራቸው። ኢየሱስ ከአይሁዶች ጋር መከራከሩን አልፈለገውም። ይልቁንም፥ እርሱ የሚፈልገው ዓይኖቻቸውን ከፍቶ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉ ሌሎች እውነቶችን እንዲመለከቱና እርሱን እንደ ዳዊት ልጅ ሳይሆን፥ እንደ መለኮታዊ የእግዚአብሔር ልጅ እንዲያውቁት ነበር። (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ ስለዚህ አስደናቂ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡)

ማቴዎስ 22፡15-46 Read More »

ያለማመንን የሚገልጹ ሦስት ምሳሌዎች (ማቴ. 21፡28-22፡14)

ኢየሱስ የሃይማኖት መሪዎች በጥያቄ ጥቃታቸው እንዲገፉበት ከመፍቀድ ይልቅ በምሳሌዎች ተጠቅሞ በእርሱ ያለማመን ስለሚያስከትለው ውጤት መግለጽ ጀመረ። ሀ. የሁለት ልጆች ምሳሉ (ማቴ 21፡28-32)። ክርስቶስ በምሳሌው እንደ ገለጸው፥ እንደኛው ልጅ መጀመሪያ አባቱ የሰጠውን ትእዛዝ ላለመፈጸም ይወስናል። በኋላ ግን በልቡ ተጸጽቶ የታዘዘውን ይፈጽማል። ሁለተኛው ልጅ ግን የተሰጠውን ተግባር እንደሚያከናውን ቢናገርም፥ ቃሉን በሥራ ሳይተረጉም ይቀራል። የመጀመሪያው ልጅ ፈሪሳውያን እንደሚንቋቸው የታወቁ ኃጢአተኞች፥ ቀራጮችና ሴተኛ አዳሪዎች ነበር። እነዚህ ሰዎች በግልጽ በእግዚአብሔር ላይ ቢያምፁም፥ በዮሐንስና በኢየሱስ ትምህርት አማካኝነት ንስሐ ገብተው ሕይወታቸውን ለውጠዋል። ስለሆነም፥ እግዚአብሔር ተቀብሏቸዋል። ፈሪሳውያን እንደ ሁለተኛው ልጅ ብዙ ሕጋትን ለመጠበቅ ታዘዋል። ነገር ግን ፈሪሳውያን በወሳኝ ጉዳዮች ላይ እግዚአብሔርን ስላልታዘዙት፥ የእግዚአብሔርን ፍርድ ይቀበላሉ። ለ. የገባሮች ምሳሌ (ማቴ. 21፡33-46)። ሁለተኛው ምላሌ ርስቱን ለገባሮች ስላከራየው የመሬት ባለቤት ይናገራል። ብዙውን ጊዜ የመሬቱ ባለቤት እንደ ዘር ያሉትን ነገርች ለመስጠት፥ ገባሮቹ ደግሞ ሥራውን አከናውነው የተወሰነውን እጅ ለባለቤቱ ለመስጠት ይስማማሉ። ባለቤቱ የድርሻውን የሚቀበልበት የመከር ጊዜ ሲደርስ፥ ባሮቹንና የኋላ ኋላ ልጁን ቢልክም፣ ገባሮቹ ለመተባበር አልፈቀዱም፣ ኣንዳንድ ባሮችንና በመጨረሻም የወይኑ እርሻ ወራሽ የሆነውን ልጁን ገደሉ። እስራኤል የእግዚአብሔር ወይን መሆኗን ከብሉይ ኪዳን እንረዳለን። (ኢሳ 5ን አንብብ።) እግዚአብሔር መሪዎቹ እስራኤልን እንዲመሩ መብት ሰጥቷቸው ነበር። እነርሱ ግን ራስ ወዳዶች በመሆናቸው፥ መብታቸውን አላግባብ ተጠቀሙ። እግዚአብሔር የላካቸው ባሪያዎች የብሉይ ኪዳን ነቢያትና መጥምቁ ዮሐንስ ነበሩ። ነገር ግን አብዛኞቹ መሪዎችና ሕዝብ ሊሰሟቸው አልፈለጉም። በመጨረሻም እግዚአብሔር ልጁን ላከ። ኢየሱስ እርሱንም ብዙም ሳይቆይ እንደሚገድሉት ተነበየ፡፡ ኢየሱስ ትክክለኛው ፍርድ ምን ሊሆን እንደሚገባ ሕዝቡን ጠየቀ። የፈሪሳውያንና የሰዱቃውያን የራስ ወዳድነት አገዛዝ ያሰለቻቸው ተራ ሰዎች ኢየሱስ የሚያስተላልፈውን መልእክት ሳይረዱ አልቀሩም፡፡ ስለሆነም፥ እግዚአብሔር መሪዎቹን ሙሉ በሙሉ አጥፍቶ በሌሎች እንደሚተካቸው ተናገረ፡፡ በ70 ዓ.ም. ጠቅላሳዎቹ ሰዱቃውያን ሲገደሉና ፈሪሳውያንም በአይሁዶች ላይ የነበራቸውን ሥልጣን ሲነጠቁ የተከሰተው ይኸው ነበር። ይህ ቀን ከመሪዎች ቅጣት ያለፈ ነበር። ጠቅላላው የአይሁድ ሕዝብ ኢየሱስን እንደ መሢሓቸው ባለመቀበላቸው ተፈርዶባቸዋል። የእግዚአብሔር ወይን የመሆኑ በረከትም ለአሕዛብ ተሰጠ። ኢየሱስ ይህ ሁሉ ቅዱሳት መጻሕፍትን እንደሚፈጽም ገልጾአል። እርሱ አይሁዶች ለእግዚአብሔር ሕንጻ አይጠቅምም ብለው የጣሉትና እግዚአብሔር ግን የማዕዘን ራስ ያደርገው መሢሕ ነበር። እንደማይጠቅም አድርገው የጣሉት ድንጋይ በናቡክደነፆር ሕልም ውስጥ ታላቅ ሆኖ የታየው ነበር (ዳን. 2፡44-45)። እርሱ ሙሉ በሙሉ ያጠፋቸዋል፡፡ ሐ. በሰርግ ድግስ ላይ የተጠሩ ሰዎች ምሳሌ (ማቴ. 22፡1-14)። ብዙውን ጊዜ አይሁዶች የመሢሑ መንግሥት እንደ የሰርግ ግብዣ ታላቅ እንደሚሆን ያስቡ ነበር። ስለሆነም፥ ኢየሱስ የንጉሥ ልጅ ስለሚያገባበት ሰርግ ምሳሌ ተናገረ። ታላላቅ ሰዎች የተባሉት ሁሉ ቢጠሩም፥ ማመኻኛዎችን ሰጥተው ለሰርጉ ከመታደም ታቅበዋል። ይጠሯቸው ዘንድ ባሪያዎቹን ሲልካቸው፥ ባሪያዎቹን አጉላሏቸው፤ አንዳንዶቹንም ገደሏቸው። ንጉሡ እጅግ ተቆጥቶ ሠራዊቱ ሄዶ እንዲያጠፋቸው አዘዘ። ከዚያም ንጉሡ አድራሻ ያልነበራቸውን ድሆች ከመጋበዙም በላይ፥ ለሰርጉ የሚስማማ ነፃ ልብስ አደላቸው። ኣንድ ሰውዬ በነፃ የተሰጠውን ልብስ ለመልበስ ባለመፈለጉ የእድምተኝነት ዕድሉን አጣ። ንጉሡ እግዚኣብሔርን ሲወክል፥ ሙሽራው ክርስቶስን ያሳያል። ሰርጉ እግዚአብሔር ለሰዎች የሚሰጠው ደኅንነትና በረከት ያመለክታል፡፡ የሃይማኖት መሪዎችና ሌሎች አይሁዶች ግን በክርስቶስ በኩል የቀረበውን የደኅንነት ስጦታ ለመቀበል ባለመፈለጋቸው፥ ለእግዚአብሔር የነበራቸውን ንቀት አሳይተዋል። ከዚህም የተነሣ፥ እግዚአብሔር በእነዚህ ወገኖች ላይ በመፍረድ ያጠፋቸዋል። እግዚአብሔር የተናቁትን ኃጢአተኞችንና አሕዛብን ጨምሮ ለሁሉም የደኅንነትን ስጦታ ይሰጣል። የጽድቅ ልብሱንም እንዲሁ ይሰጣቸዋል። ነገር ግን በራሳቸው የጽድቅ ልብሶች በመተማመን፥ እግዚአብሔር በክርስቶስ በማመን የሚሰጠውን የጽድቅ ልብስ ላለመቀበል ከወሰኑ፥ ወደ እግዚአብሔር መንሥት የመግባቱን በረከት ተነፍገው ወደ ዘላለማዊ ሲዖል ይወርዳሉ። የውይይት ጥያቄ፡- ከእነዚህ ምሳሌዎች እግዚአብሔር ስለሚሠራበት መንገድ፣ ስለ ሰዎች ማንነትና ስለ ራሳችን ኃላፊነት ምን እንማራለን? (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ ስለዚህ አስደናቂ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡)

ያለማመንን የሚገልጹ ሦስት ምሳሌዎች (ማቴ. 21፡28-22፡14) Read More »

ማቴዎስ 21፡1-27

ኢየሱስ እንደ ሰላም ንጉሥ ወደ ኢየሩሳሌም ገባ (ማቴ. 21፡1-11) በዚህን ጊዜ ከዳዊት የዘር ሐረግ የወጣ ንጉሥ ኢየሩሳሌምን ከገዛ ከ600 ዓመታት በላይ አልፎ ነበር። እነዚህ ዓመታት አይሁዶች መሢሑን ሲናፍቁና ሲጠብቁ የቆዩባቸው ጊዜያት ነበሩ። ኢየሱስ ይፋዊ አገልግሎቱን በጀመረ ጊዜ፥ ሰዎች ደጋግመው የሚያነሡት ጥያቄ፥ «ይህ የዳዊት ንጉሥ ነውን?» የሚል ነበር። አንድ ቀን ንጉሣቸው በአህያ ላይ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም መጣ። ለምን በሰጋር በቅሎ ላይ ሳይሆን በአህያ ላይ ተቀመጠ? ክርስቶስ ሌላ የመጓጓዣ እንስሳ ለማግኘት የሚያስችል ገንዘብ አልነበረውም? በጥንት ዘመን አንድ ንጉሥ የሚቀመጥበት የመጓጓዣ እንስሳ ማንነቱን ያሳይ ነበር። በፈረስ ላይ ከተቀመጠ ይህ ኃይልና ሥልጣን ያለው ድል ነሺ ንጉሥ እንደሆነ ያሳይ ነበር። ነገር ግን በአህያ ላይ ተቀምጦ ከመጣ በትሕትና ሕዝቡን የሚያገለግል ሰላማዊ ንጉሥ መሆኑን ያሳይ ነበር። (ከመሳ. 10፡4፤ 2ኛ ሳሙ. 16፡1-2 ሉሎች የአይሁድ መሪዎች በአህያ ላይ ተቀምጠው መጓዛቸውን የሚያመለክቱ ምሳሌዎችን ተመልከት። ይህ ትንቢት ስለመፈጸሙ ዘካ 9፡9ን አንብብ።) ኢየሱስ በአህያ ላይ ተቀምጦ ሲመጣ አይሁዶች ከዳዊት የዘር ሐረግ የወጣ መሢሕ መሆኑን እየገለጸ እንደሆነ ተረድተዋል። በዚህ ጊዜ እጅግ ደስ ተሰኝተው እግዚአብሔርን ያመሰግኑ ጀመር። ኢየሱስ ሰዎች መሢሕነቱን እንዳይናገሩ ሲያስጠነቅቅ የቆየ ሲሆን (ማቴ. 1፡9)፥ በዚህ ጊዜ ግን የተሰጠውን ክብር ተቀብሏል። የክርስቶስ የሕይወት ፍጻሜ እየተቃረበ ሲመጣ፥ ማቴዎስ አሁንም ክርስቶስ ባደረጋቸውና ጥንታዊ ትንቢቶችን በመፈጸሙ ላይ ትኩረት አድርጓል። ስለ መሢሑ መምጣት የሚናገር የብሉይ ኪዳን የተስፋ ቃል ሁሉ፥ በክርስቶስ እንደ ተፈጸመ፥ ለአይሁዶች በድጋሚ አሳይቷል። ክርስቶስን ካልተቀበሉ ሌላ መሢሕ ሊኖራቸው አይችልም ነበር። ኢየሱስ ቤተ መቅደሱን አፅዳው (ማቴ. 21፡12-17) ኢየሱስ ይናደዳል ብለን አንገምትም። ስለዚህ እርሱ የዋህ፥ ታጋሽና ደግ እንደሆነ እናስባለን። በእርግጥም ኢየሱስ በተለይ ለኃጢአተኞች እንዲህ ዓይነት ባሕርይ ያሳይ ነበር። ነገር ግን ክርስቶስ ሰዎች የእግዚአብሔርን አምልኮ ሲያበላሹ በመመልከቱ በጣም ተቆጣ። ፈሪሳውያን ሰዎች ከእግዚአብሔር ጋር እንዳይቀራረቡ የተሳሳተ መንገድ በማሳየታችው ተቆጣቸው። በቤተ መቅደሱ ሕዝቡ እግዚአብሔርን እንዳያማልክ ባደረጉትም ወገኖች ላይ ተቆጣ። [ማስታወሻ:- ክርስቲያኖች ሊቆጡ ይችላሉ? መልሱ፥ አዎን የሚል ነው፡፡ (ኤፌ 4፡26 አንብብ፡፡) መቆጣት ያለብን ግን ኃጢአተኛችን ሳይሆን፥ በሰዎችና በማኀበረሰቡ ኃጢአት ላይ እንዲሁም የእግዚአብሔርን ክብር በሚያጎድፉ ነገሮች ላይ ሊሆን ይገባል። ብዙውን ጊዜ ግን ኃጢአትን እታገሥ በሆነ መንገድ የሚጎዱንን ሰዎች እንቆጣለን፡ ይህ ኃጢአት ስለሆነ መናዘዙ ተገቢ ነው።] የውይይት ጥያቄ:- ሀ) ብዙ ሰዎች በተሳሳተ መንገድ የሚቆጡባቸውን ጉዳዮች ዘርዝር። ለ) እግዚአብሔር ክርስቲያኖች እንዲቆጡ የሚፈልባቸውን ነገሮች ዘርዝር፡፡ ሐ) የተቆጣህነትን የመጨረሻ ጊዜ አስታውስና ይህ የጽድቅ ቁጣ ነበር ወይስ የኃጢአት? በእነዙህ በሁለቱ መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው? ሄሮድስ የሠራው ቤተ መቅደስ አራት የተለያዩ ክፍሎች ነበሩት፡፡ በውስጠኛው ክፍል የካህናት አደባባይ ይገኛል። በዚህ አደባባይ ውስጥ ቆመው ሊያመልኩ የሚችሉት ካህናት ብቻ ነበሩ፡፡ ከዚያ ቀጥሉ አይሁዳውያን ወንዶች የሚያመልኩበት የወንዶች አደባባይ ይገኛል። ሦስተኛው አይሁዳውያን ሌቶች የሚያመልኩበት የሴቶች አደባባይ ነበር፡፡ በመጨረሻም፥ ለአሕዛብ አምልኮ የተፈቀደ የአሕዛብ አደባባይ ተዘጋጅቷል። ለኣሕዛብ ከዚህ ውጫዊ አደባባይ በቀር ወደሌሎቹ አደባባዮች ለመቅረብ መሞከር ራስን ለሞት መጋበዝ ነበር፡ በዚሁ የአሕዛብ አደባባይ ነበር ነጋዴዎች ንግዳቸውን የሚያጧጡፉት። ሰዎች የአሕዛብ ገንዘቦቻቸውን ወደ ተቢው የቤተ መቅደስ ገንዘብ እንዲለውጡ የሚያስችል ገንዘብ ለዋጮች ነበሩ። እንዲሁም፥ ለመሥዋዕት እንስሳትን የሚሸጡ ሰዎች ነበሩ፡፡ የሚያሳዝነው እነዚህ ነጋዴዎች ብዙውን ጊዜ ከካህናት ጋር በመተባበርና ሕዝቡ የተፈለጉትን እንስሳት በውድ ዋጋ እንዲገዙ በማስገደድ ከፍተኛ ገንዘብ ለማትረፍ ይሞክሩ ነበር፡፡ (ይህ በፋሲካ ሰሞን ዶሮ እንደሚወደድ ማለት ነው፡፡) ኢየሱስ ነጋዴዎችን ያስወጣው ከዚህ የአሕዛብ አደባባይ ነበር፡፡ ማርቆስ ነጋዴዎቹ የአሕዛብን አምልኮ በማደናቀፋቸው ኢየሱስ በመቆጣቱ ላይ ሲያተኩር፥ ማቴዎስ የአምልኮው አካል በነበረው ሙስናና ስግብግብነት ላይ አጽንኦት ሰጥቷል፡፡ በቤተ መቅደሱ ውስጥ ቢቆጣም፥ ኢየሱስ ሕዝቡን በመፈወስ ርኅራኄውን አሳይቷል። ልጆች ቀደም ሲል ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም በአህያ ላይ ተቀምጦ ሲገባ ከተደረለት አቀባበል የሰሟቸውን ቃላት በመደጋገም፣ “ሆሳዕና ለዳዊት ልጅ” ይሉ ጀመር፡፡ ኢየሱስ ይህ የትንቢት ፍጻሜ መሆኑ ገብቶታል። ምንም እኳ የሃይማኖት መሪዎች ባያመሰኙትም፣ ልጆች ሳያውቁ ለይተው ሊያመሰኙት ቻሉ፡፡ ኢየሱስ የበለስ ዛፍን ረገመ (ማቴ. 21:18-22)። አንድ ቀን ኢየሱስ፣ የፍሪ ምልክት በምታሳይ ዛፍ አጠገብ አለ፡፡ ነገር ግን ፍሪ ስላልነበራት ረግሞ እንድትደርቅ አደረጋት፡፡ ኢየሱስ ለምን ይህን አደረገ? ኢየሱስ በለሲቱ የእስራኤል ሕዝብ ተምሳሌት እንደሆነች ገልጾአል፡፡ እግዚአብሔር እስራኤል ለስሙ ክብርን እንድታመጣ በማሰብ ነበር የመረጣትና የፈጠራት። እንደ በለሲቱ ሁሉ፥ እስራኤልም ከርቀት ስትታይ ፍሪያማ ትመስል ነበር። በቅርብ ሲታዩ ግን አይሁዶች ፍሬ (ጽድቅ፥ ፍቅር፥ ፍትሕ) እንደሌላቸው ይታወቅ ነበር። በለሲቱ እንደ ተረገመች ሁሉ፥ አይሁዶችም ለእግዚአብሔር ፍርድ ራሳቸውን አመቻችተው ነበር። ከዚያን ጊዜ በኋላ ኢየሩሳሌም ለአርባ ዓመታት ቆይታ በሮማውያን እጅ ትደምስሳለች። ለቀጣይ 1900 ዓመታት አይሁዶች አገር አልነበራቸውም። የሃይማኖት መሪዎች የኢየሱስን ሥልጣን ተጠራጠሩ (ማቴ. 21፡23-27) ፈሪሳውያንና የሃይማኖት መሪዎች በኢየሱስ ላይ የሚሰነዝሩት የቃላት ጦርነት ቀጥሏል። መሪዎቹ ኢየሱስን በሕዝብ ፊት ለማሳጣት የሚችሉትን ጥረት ሁሉ ያደርጉ ነበር፡፡ ኢየሱስን ለማሳጣት የታሰበው የመጀመሪያው ጥያቄ የተነሣው ከሰዱቃውያን ነበር፡፡ ዋንኞቹ ካህናትና ሽማግሌዎች ለአብዛኞቹ የአገሪቱ ሃይማኖታዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ኃላፊነቶች ነበረባቸው። ዋንኛው አጀንዳቸው ሥልጣን ነበር። የእነርሱ ሥልጣን የመነጨው በአይሁዶች ላይ እንዲገዙ ከሾሟቸው ሮማውያን ነበር፡፡ ኢየሱስን ሰዎችን ከቤተ መቅደሱ ለማስወጣትና ለመፈወስ የሚያስችል ሥልጣን ከየት አገኘ? እነዚህ ነገሮች ስለ ኢየሱስ ምን እንደሚያሳዩ የመገንዘብ ፍላጎት አልነበራቸውም። የሚያሳስባቸው ጉዳይ ቢኖር፥ የእርሱ ሥልጣን የእነርሱን ሥልጣን እያደበዘዘ መሄዱ ወይም ሰዎች በሮም ላይ ቢያምፁ የሚደርስባቸው ችግር ብቻ ነበር። የክርስቶስ ሥልጣን ከሰማይ መምጣቱን ለማረጋገጥ የፈጸማቸው ተአምራትና ያስተማራቸው እውነቶች ይበቁ ነበር፡፡ እነርሱ ግን የዚህ ዓይነቱን ሥልጣን ለመቀበል አልፈለጉም። ኢየሱስ ግን የጥያቄያቸውን አፈሙዝ ወደ ራሳቸው አዞረ። በዚህ ጊዜ መጥምቁ ዮሐንስ እንደ ነቢይና ለእምነቱ እንደ ተሠዋ ጻድቅ ይታሰብ ነበር። ነገር ገን እነዚህ የሃይማኖት መሪዎች ዮሐንስ በሚያገለግልበት ጊዜ ሊቀበሉት አልፈለጉም ነበር። የሃይማኖት መሪዎቹ የዮሐንስ ሥልጣን ከሰማይ ወይ ከምድር መሆኑን ለመናገር አልፈለጉም ነበር። ሕዝቡ ዮሐንስ የእግዚአብሔር ነቢይ እንደሆነ ያምኑ ስለነበር፥ ችግር እንዳይፈጠርባቸው በመስጋት አገልግሎቱ ሰብአዊ ሥልጣን ብቻ ነበር ለማለት አልደፈሩም። ከእግዚአብሔር ነበር ካሉ ደግሞ ለምን አልሰማችሁትም? የሚል ጥያቄ ስለሚከተል፥ እንደዚያ ለማለት አልፈለጉም። ኢየሱስም ጥያቄያቸውን ለመመለስ ባለመፈለጉ ትተውት ሄዱ። (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ ስለዚህ አስደናቂ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡)

ማቴዎስ 21፡1-27 Read More »