የማቴዎስ ወንጌል

ማቴዎስ 11፡1-30

የውይይት ጥያቄ፡– ስለ እምነትህ የተጠራጠርህበትን ጊዜ ግለጽ። የተጠራጠርኸው ምን ነበር? በክርስቶስ ላይ ያለህን እምነት መልሰህ እንድትቀዳጅ የረዳህ ምን ነበር? በአንድ ወይም በሌላ ጊዜ ሁሉም ክርስቲያኖች ጥርጣሬዎች ይኖሯቸዋል። ለጸሎትህ መልስ ስትጠብቅ አይመጣም፤ ደግሞም እግዚአብሔር በዚህ መንገድ ይሠራል ብለህ የማታስበው አንድ ነገር ይከሰታል። የመኪና አደጋ ደርሶ ለአገልግሎት የወጣ ጠንካራ ክርስቲያን ወንድም ሽባ ይሆናል። በእንዲህ ዓይነት ጊዜያት እግዚአብሔርን ልንጠራጠር እንችላለን። መጥምቁ ዮሐንስ ለተወሰነ ጊዜ ታስሮ ቆይቶ ነበር። ደቀ መዛሙርቱ ክርስቶስ ስለሚያከናውናቸው ተግባራት ቢገልጹለትም፥ ለዮሐንስ ስሜት አልሰጠውም። የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀትና የእሳት ፍርድ የታሉ? ክርስቶስ ክፉዎችን አጥፍቶ የጽድቅ መንግሥቱን የሚጀምረው መቼ ነው? ክርስቶስ የመጣው እርሱ ከጠበቀው መንገድ ሙሉ በሙሉ በተለየ ሁኔታ በመሆኑ፥ ዮሐንስ ግራ ተጋባ። እግዚአብሔር የክርስቶስን መሢሕነት ለእርሱ መግለጹ ስሕተት ይሆን? ስለሆነም፥ ዮሐንስ «የክርስቶስን መሢሕነት ወይም ሌላ መጠበቅ እንዳለባቸው» ለማረጋገጥ ደቀ መዛሙርቱን ወደ ክርስቶስ ላከ። ክርስቶስ ወደ ተአምራቱ በማመልከት፥ «እግዚአብሔር በእኔ በኩል ያደረገውን ሄዳችሁ ንገሩት። እነዚህ ለመሢሕነቴ በቂ ማረጋገጫዎች ናቸው፤ አትጠራጠር በሉት» አላቸው። ማቴዎስ ተመሳሳይ ጥርጣሬ ለነበራቸው አይሁዶችም ይህንኑ ምላሽ ሰጥቷቸዋል። አይሁዶች መሢሕ ድል ነሺ ንጉሥ እንደሚሆን ጠብቀው ነበር። ማቴዎስ በመጽሐፉ «ክርስቶስ ያደረጋቸውን ተአምራት ተመልከቱ። እነዚህን ተአምራት እንዳደረገ ታውቃላችሁ፤ እነርሱም የመሢሕነቱ ማረጋገጫዎች ናቸው። ሌላ ሰው አትፈልጉ» ሲል አስረድቷል። ለጥርጣሬዎች ምላሽ ለመስጠት የእግዚአብሔርን ቃል እውነት እንጠቀማለን። ክርስቶስም የመጥምቁ ዮሐንስን ዓይኖች ለእግዚአብሔር እውነቶች አብርቷል። ክርስቶስ በዚህ ጊዜ ለሕዝቡ ስለ ዮሐንስና ከመጪው እግዚአብሔር መንግሥት ጋር ስላለው ግንኙነት አስተምሯል። ባማረ ልብስ ባያጌጥና ተአምራት ባይሠራም፥ ዮሐንስ ለመሢሑ መንገድ እንዲጠርግ የተላከ ክቡር ነቢይ ነበር። ስለሆነም፥ ዮሐንስ ታላቅ አገልጋይ ነበር። ከዚያ በኋላ ክርስቶስ ለመረዳት የሚያስቸግር አሳብ ሰንዝሯል። ዮሐንስ ታላቅ ቢሆንም፥ በመንግሥተ ሰማይ እጅግ አነስተኛ የሆነው ሰው ይበልጠዋል። ክርስቶስ ይህን ሲል ምን ማለቱ ነው? በክርስቶስ መምጣት አዲስ የዘመን ምዕራፍ ተከፍቷል። የብሉይ ኪዳን ዘመን አብቅቶ የአዲስ ኪዳን ዘመን እየተጀመረ ነበር። ዮሐንስ ታላቅ ነቢይ ቢሆንም፥ የብሉይ ኪዳን ዘመን አካል ነበር። መሢሑን ለዓለም የማስተዋወቅን ልዩ ዕድል ስላገኘ፥ የአሮጌው ዘመን ታላቅ ነቢይ ነበር። ነገር ግን የክርስቶስን ሞትና ትንሣኤ ለማየት አልታደለም ነበር፤ የቤተ ክርስቲያን አባል አልሆነም ነበር። አዲሱ ዘመን ከብሉይ ኪዳን ዘመን ስለሚልቅ፥ የአዲሱ ዘመን ተራ አባል ከአሮጌው ዘመን ታላቅ ሰው ይበልጣል። ክርስቶስ በተጨማሪም፥ «ከመጥምቁም ከዮሐንስ ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ መንግሥተ ሰማይ ትገፋለች፤ ግፈኞችም ይናጠቋታል» ብሏል። ይህም ለመረዳት የሚያስቸግር አሳብ ነው። አንዳንድ ምሑራን ከማቴዎስ 10 ዐውድ በመረዳት፥ ስደትን እንደሚያመለክት ይገልጻሉ። በአንድ በኩል፥ የእግዚአብሔር መንግሥት መስፋፋት ጠላትን እያሸነፈ ነበር። ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያኑን እንደሚመሠርትና የገሃነም ደጆች እንደማይቋቋሟት ገልጾታል። ከመጥምቁ ዮሐንስ ዘመን ጀምሮ፥ ይህ ሁኔታ በመካሄድ ላይ ቆይቷል። በተመሳሳይ ጊዜ፥ የእግዚአብሔርን መንግሥት መስፋፋት የሚቃወሙ ሰዎች ነበሩ። ስደት የቤተ ክርስቲያን የማይቋረጥ ሂደት ነው። መጥምቁ ዮሐንስ የታሰረ ሲሆን፥ ክርስቶስ ደግሞ ተሰቅሏል። በታሪክ ሁሉ፥ ቤተ ክርስቲያን ስደትን ስትጋፈጥ ቆይታለች። መጥምቁ ዮሐንስና አይሁዶች የመሢሑ መንግሥት ከመቅጽበት መጥቶ አሕዛብን ወይም የክፋት ኃይሎችን ሁሉ እንደማያስወግድ መገንዘብ ነበረባቸው። የእግዚአብሔር መንግሥት ቀስ በቀስ እያደገ ሲሄድ፥ የክፉ ሰዎች ተቃውሞ አይለየውም። ምሑራን የክርስቶስን አሳብ የሚረዱበት ሌላው መንገድ የእግዚአብሔር መንግሥት አካል ለመሆን ጥረትን እንደሚጠይቅ ነው። አንድ ሰው የክርስቶስ ተከታይ ሆኖ ካለመወለዱም በላይ፥ ምርጫውም ቀላል አይደለም። የመንግሥቱ አካል መሆንን፥ አንድ ሰው ከምንም ነገር በላይ ሊሻው ይገባል። ሁልጊዜም ስደት ስለሚኖር፥ ብርታት፥ ኃይልና ቁርጥ ውሳኔ አስፈላጊዎች ይሆናሉ። ከዚያም ክርስቶስ አይሁዶች የእግዚአብሔርን አሠራር ለመገንዘብ ባለመቻላቸውና በሌሎች ላይ በመፍረዳቸው ገሥጿቸዋል። መጥምቁ ዮሐንስ ቆዳ ለብሶ ጠንካራ የፍርድ መልእክት እየሰበከ ሲመጣ፥ «ወግ አጥባቂ ነው» አሉት። ይህም በጋኔን ቁጥጥር እንደሚሠራ የመግለጽ ያህል ነበር። ክርስቶስ ደግሞ ከሰዎች ጋር በመብላትና በመጠጣት የቅርብ ወዳጃቸው ሆነ። ከኃጢአተኞች ጋር ወዳጅነትን በመመሥረቱ፥ ብዙውን ጊዜ ይጋብዙት ነበር። አይሁዶች ግን ይህን ባሕርዩን በመጥላት ቀለል ያለ በላተኛና ጠጪ እንደሆነ ተናገሩ። በቂ መንፈሳዊነት እንደሌለውና የቀራጮችና ኃጢአተኞች ወዳጅ በመሆን የተሳሳተ ዝምድና እንዳፈራ ገለጹ። የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ክርስቶስ ከሴተኛ አዳሪዎች፥ ከጎዳና ተዳዳሪዎችና ዱርዬዎች ጋር ወዳጅነትን እየጠበቀ በቤተ ክርስቲያንህ ቢያገለግል፥ ምን ዓይነት ስም የሚሰጠው ይመስልሃል? በሽማግሌዎች የሚወደድ ይመስልሃል? ለምን? ለ) ክርስቶስ በዚህ ተግባሩ የማይወደድ ከሆነ፥ ይህ ክርስቶስን መምሰልን አስመልክቶ የተሳሳተ አመለካከት መያዛችንን የሚያሳየው እንዴት ነው? ክርስቶስ ሰዎች ንስሐ ባልገቡባቸው ከተሞች ላይ ፍርድን ማወጁ እና ለሚያምኑበት ዕረፍትን እንደሚሰጣቸው መግለጡ (ማቴ. 11፡20-30) ብዙ ከተሰጠው ብዙ እንደሚጠበቅ የሚያመለክት መጽሐፍ ቅዱሳዊ መርሕ አለ (ሉቃስ 12፡48)። ይህም ገንዘብ፥ ትምህርት፥ የክርስቶስ እውቀትና መንፈሳዊ ስጦታ ላላቸው የሚሠራ ነው። እግዚአብሔር ለእያንዳንዳችን ይህን ስጦታ የሰጠን ለክብሩ እንደምንጠቀምበት በመገንዘብ ሲሆን፥ እንዴት እንደተጠቀምንበት ይጠይቀናል። የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) እግዚአብሔር እንደ በረከት የሰጠህን አንዳንድ ነገሮች ዘርዝር። ለ) እነዚህን ነገሮች እግዚአብሔርን በሚያስከብር መንገድ የምትጠቀምባቸው እንዴት ነው? የኮራዚንና የቤተሳይዳ ከተሞች፥ ክርስቶስ አብዛኞቹን ተአምራት ባደረገበት በገሊላ ውስጥ የሚገኙ ስፍራዎች ነበሩ። በዚያ ዘመን እነዚህ ከተሞች ከሌሎች ከተሞች ሁሉ በላይ ተባርከው እንደነበር ታሪካቸው ይመሰክራል። ክርስቶስን በሥጋ ማየታቸውና ተአምራቱን መመልከታቸው ኃላፊነትን የሚያስከትል በረከት ነው። ክርስቶስ ተአምራቱን እየተመለከቱ ያላመኑበት ሰዎች በመሢሕነቱ ሊያምኑ እንደሚገባቸው አስጠንቅቋቸዋል፤ ክርስቶስ ሊዶናና ጢሮስ የተባሉት የአሕዛብ ከተሞች እነዚህን ተአምራት ቢመለከቱ ኖሮ፥ በእርሱ ያምኑ እንደነበር ተናግሯልና። ነገር ግን አይሁዶች እርሱን ባለመቀበላቸው የእግዚአብሔርን ልጅ ካላዩት ሰዎች ይልቅ ጥፋተኞች መሆናቸውን አሳይተዋል። ሰዶምና ገሞራ የአይሁዶችን ያህል ግልጽ ምስክርነት አላገኙም ነበር። ስለሆነም በአይሁዶች ላይ ፍርድ ይሰጣል። በ70 ዓ.ም. ብዙ ከተሞቿ በመደምሰሳቸው ገሊላ ፍርዱን የተቀበለች ስትሆን፥ ሌሎች አይሁዶች በመጨረሻው ዘመን ፍርድን ያገኛሉ። ማቴዎስ በዚህ መልእክቱ በዘመኑ የነበሩትን አይሁዶችና በየትኛውም ዘመን የሚኖሩትን ሰዎች እያስጠነቀቀ ነበር። ወንጌሉ ተጨማሪ ተጠያቂነትን ያስከትላል። ወንጌሉን ከሰሙና የመንፈስ ቅዱስን ሥራ ከተመለከቱ በኋላ፥ በክርስቶስ ለማመን የማይፈልጉ ሰዎች ስለ ክርስቶስ ሰምቶ ከማያውቅ ሰው የከፋ ቅጣት ይጠብቃቸዋል። ክርስቶስ ለሚያምኑበት ዕረፍትን እንደሚሰጣቸው ቃል ገባ (ማቴ. 11፡25-30) ወንጌሉ ሁልጊዜም የሚያምኑትን ሰዎች ከማያምኑት ይለያል። ክርስቶስ አብዛኛው ሰው በእርሱ ባለማመኑ ተስፋ ሳይቆርጥ፥ በዘመናት ሁሉ እውነት የሆነውን ምሥጢር ለመመልከት ችሏል። በአጠቃላይ፥ እንደ ፈሪሳውያንና የዩኒቨርሲቲ መምህራን ምድራዊ ዕውቀት የነበራቸው ሰዎች ወንጌሉን ከሞኝነት ስለቆጠሩት ወንጌሉን አልተቀበሉም ነበር። እንደ ሊቀ ካህናትና የሮም ገዥዎች ያሉት ሀብታሞችና ባለሥልጣናትም ልባቸውን በሌሎች ነገሮች ስላጣበቡ፥ ወንጌሉን ለመቀበል አልፈለጉም። ዓለም የናቃቸው ድሆች ግን በክርስቶስ አመኑ። አብዛኞቹ የቀድሞይቱ ቤተ ክርስቲያን አባላት፥ ባሮችና ድሆች የነበሩ ሲሆን፥ ይኸው ሁኔታ በታሪክ ሂደት ውስጥ ሁሉ ቀጥሏል። የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) 1ኛ ቆሮ. 1፡18–31ን አንብብ። ጳውሎስ ይህን የወንጌል ምሥጢር ያብራራው እንዴት ነው? ለ) አንዳንድ ጊዜ ጠቢባንን፥ ሀብታሞችንና ኃይለኞችን ለመማረክ እየሞከርንና ድሆችንና የተናቁትን እየተውን ይህንን ምሥጢር ችላ የምንለው እንዴት ነው? ክርስቶስ ሊከተሉት የሚፈልጉት ተራ ሰዎች መሆናቸውን በመገንዘቡ፥ እግዚአብሔርን ለሚሠራበት መንገድ አመሰገነው። ክርስቶስ፥ ደኅንነት የሰው ሥራ ሳይሆን የእግዚአብሔር ሥራ መሆኑን ገልጾታል። እግዚአብሔር የመንግሥቱን ምሥጢራት ለልጁ ለኢየሱስ ክርስቶስ ሰጥቷል። ክርስቶስም የወንጌሉን ምሥጢራት ገልጾ ለመረጣቸው ሰዎች ሰጥቷል። ይህ በሲኖፕቲክ ወንጌላት ውስጥ ከቀረቡት የክርስቶስን አምላክነት ከሚያስረዱትና ከእግዚአብሔር አብ ጋር ያለውን ልዩ ግንኙነት ከሚያሳዩት ግልጽ መግለጫዎች አንዱ ነው። ክርስቶስ አንድ ሰው እርሱን ለመከተልና ለመዳን የሚያጋጥመውን ስደት ከገለጸ በኋላ፥ አሁን ደግሞ ሌላኛውን የወንጌሉን ምሥጢር ገጽታ ያሳያል። ክርስቶስ፥ የሕይወት ውጥረትና ሸክም ያደከማቸው ሰዎች ወደ እርሱ እንዲመጡ ጋብዟል። ፈሪሳውያንና ሌሎች የሃይማኖት መሪዎች ብዙ ሕጎቻቸውን በሰዎች ላይ ሲጭኑ፥ ክርስቶስ ከባድ ነገር እንደማይጠይቃቸው ተናግሯል። የምንፈልገውን አግኝተን ውስጣዊ ሰላም የምናገኘው በክርስቶስ ብቻ ነው። ነገር ግን ሌሎች ሰዎች የደቀ መዝሙርነትን መንገድ ይከተሉ ዘንድ፥ ሕይወታችን ከክርስቶስ ጋር እንዲጣመር (ልክ ሁለት በሬዎች በአንድ ቀንበር እንደሚጣመሩ) ልናደርግ ይገባል። ልባችንንና ሕይወታችንን

ማቴዎስ 11፡1-30 Read More »

የዐሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት መላክ (ማቴዎስ 10:1-42)

ክርስቶስ ታላቁ መምህርና ፈዋሽ ብቻ ሳይሆን፥ ዋና አሠልጣኝም ነበር። ብዙውን ጊዜ ስለ ትምህርት ስናስብ፥ በትምህርት ቤት የተወሰኑ እውነቶችን ተምሮ ቤተ ክርስቲያንን ስለ መምራት እናስባለን። ይህን ዓይነቱን ሥልጠና ካገኘን በኋላ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለማገልገል ብቁዎች ነን ብለን እናስባለን። የዚህ ዓይነቱ የአመራር ሥልጠና ዓይነት የቤተ ክርስቲያንን ፍላጎቶች ለማሟላት አልቻለም። በትምህርት ቤት ውስጥ መማር የክርስቶስ ሥልጠና ተቃራኒ ነው። ክርስቶስ መጽሐፍ ቅዱስ ያልነበረው ከመሆኑም በላይ ቁጭ ብሎ ንድፈ አሳቦችን (ቲዎሪ) አላስተማረም። በአንድም ጊዜ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን አላስተማረም። ለክርስቶስ አገልግሎት ውጤታማነት ከሚጠቀሱት ዐበይት ነገሮች አንዱ፥ ደቀ መዛሙርቱን ያማከለበት ሁኔታ ነው። ደቀ መዛሙርቱን ደህና አድርጎ ባያሠለጥናቸው ኖሮ፥ ክርስቶስ ወደ ሰማይ እንደ አረገ ቤተ ክርስቲያን ትሞት ነበር። ነገር ግን ደቀ መዛሙርቱ እንደ ክርስቶስ ለመሆን በመብቃታቸው፥ ቤተ ክርስቲያን ጠቅላላውን የሮም ግዛት በአንድ ትውልድ እስክታጥለቀልቅ ድረስ አደገች። እንግዲህ፥ ከክርስቶስ ሥልጠና ውስጥ ልንመለከታቸውና ዓለምን የሚለውጡ መሪዎችን ለማፍራት የምንጠቀምባቸው ቁልፍ አሳቦች ምንድን ናቸው? ክርስቶስ የሕያው እምነትና ከእርሱ ጋር የተጋጋለ ግንኙነት የማድረግን ሁኔታ አሳይቷል። ደቀ መዛሙርቱ ሁሉ ከክርስቶስ ጋር ኖረው ለሦስት ዓመታት ያህል ሲመለከቱት ቆይተዋል። በዚህም ከቃላቱ ይልቅ ከምሳሌው የበለጠ ተምረዋል። ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱ እንዴት እንደሚያስተዳድሩ፥ እንደሚሰብኩና እንዴት ተአምራትን እንደሚፈጽሙ ሳይሆን፥ እንዴት የተለወጠ ባሕርይ ሊኖራቸው እንደሚችል አስተምሯቸዋል። ብዙውን ጊዜ አንድ ሰው አንድን ተግባር እንዴት እንደሚያከናውን ማሳየቱ ቀላል ነው። ነገር ግን ባሕርዩን ወደ መንፈሳዊ መሪነት መለወጡ የበለጠ አስቸጋሪ ነው። ብዙ እውቀት ኖሮት የመንፈሳዊ አመራር ባሕርይ የሌለው ሰው፥ ሰይጣን ቤተ ክርስቲያንን ለማውደም የሚጠቀምበት መሣሪያ ነው። ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱ ትክክል ነው ብለው ያሰቡትን የዓለምን የአመራር ሁኔታ በጥብቅ ተቃውሟል። ደቀ መዛሙርቱ ኃይልን፥ ሥልጣንንና የመሪነትን ጥቅሞች ለማግኘት ሲፈልጉ፥ ክርስቶስ ግን መሪነት አገልግሎት እንደሆነ ገልጾላቸዋል። ይህንንም እግራቸውን በማጠብ አርአያነቱን ያሳያቸው ሲሆን፥ የዚህ ዓይነቱ አመራር አገልግሎት መሆኑን አስተምሯቸዋል። ክርስቶስ በመንግሥቱ ውስጥ ታላቁ የተባለ ሰው የሌሎችን ፍላጎቶች ከራሱ የሚያስቀድምና ዝቅ የሚልና የሚያገለግል እንደሆነ በመግለጽ አስተማራቸው። ዛሬ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚታየው ትልቁ ችግር ብዙ መሪዎች አሁንም የዓለምን የአመራር አመለካከት የሚያንጸባርቁ መሆናቸው ነው። ክርስቶስ እንዴት በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ማገልገል እንደሚቻል አሳይቷል። እንዴት ማስተማር፥ መስበክ፥ መፈወስ፥ መጸለይ እንደሚቻል በራሱ ምሳሌነት አስተምሯቸዋል። ከክርስቶስ ዕርገት በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ያደረጉት ሁሉ እርሱ ሲያደርግ የተመለከቱት ነበር። የክርስቶስ ትምህርት እውነትን ከሕይወት ጋር የማዛመድ ተግባር ነበር። ክርስቶስ ያስተማረው ስለ እግዚአብሔር እውነትን ወይም በንድፈ አሳባዊ መንገድ መመስከርን አልነበረም። ክርስቶስ የተመላለሰውና ያስተማረው ምሳሌዎችንና የዕለት ተዕለት ሁኔታዎችን ተጠቅሞ ለደቀ መዛሙርቱ መንፈሳዊ እውነቶችን በመግለጽ ነበር። ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱ እርሱ እየተመለከታቸው እንዲያገለግሉ በማድረግ ሲያጠፉ አርሟቸዋል (ይህንን በዛሬው ትምህርታችን እንመለከተዋለን)። ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱ አገልግሎታቸውን በሚያካሂዱበት ጊዜ፥ መንፈስ ቅዱስ እንዲያድጉ እንደሚረዳቸው ተማምኗል (ዮሐ. 14፡26)። እርሱ ያስተማረበት ጊዜ፥ የትምህርት መጨረሻ ሳይሆን መጀመሪያ ነበር። ለራሳቸው እንዴት እንደሚማሩ በማሳየት፥ መማራቸውን እንዲቀጥሉ አበረታቷቸዋል። የውይይት ጥያቄ፡- የአመራር የሥልጠና ፕሮግራሞቻችንን የክርስቶስን ምሳሌነት ተከትለን ብናዋቅር፥ ምን ምን ነገሮችን መለወጥ ይኖርብናል? የውይይት ጥያቄ፡- ማቴዎስ 10–11ን አንብብ። ሀ) ከዚህ ክፍል ስለ ክርስቶስ ምን እንማራለን? ለ) ስለ ደቀ መዝሙርነትና አመራር የምንማራቸው ነገሮች ምንድን ናቸው? ደቀ መዛሙርቱ እግዚአብሔር ብዙ ትክክለኛ መሪዎችን ያስነሣ ዘንድ እንዲጸልዩ ከነገራቸው በኋላ፥ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱ የሰዎችን ፍላጎቶች እንዲያሟሉና ስለ መጪው የእግዚአብሔር መንግሥት እንዲያስተምሩ ላካቸው። እነዚህ ደቀ መዛሙርት ሌላ ሰው ለችግሩ የእግዚአብሔር መፍትሔ እንዲሆን ከመጸለይ አልፈው ራሳቸው በትጋት በአገልግሎቱ ውስጥ ይሳተፉ ነበር። ክርስቶስ አሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርት መርጦ ለአገልግሎት አሰማራቸው (ማቴ. 10) ክርስቶስን በደቀ መዝሙርነት የሚከተሉት ብዙ ሰዎች ነበሩ። ክርስቶስ እነዚህን ሁሉ ደቀ መዛሙርት በእኩል ደረጃ ካለመመልከቱም በላይ፥ በተለያየ ብቃት ደረጃ አሠልጥኗቸዋል። የመጀመሪያ ደረጃ ደቀ መዛሙርት በብዛት የሚከተሉት ነበሩ። በክርስቶስ ዕርገት ጊዜ፥ ቢያንስ 120 ደቀ መዛሙርት እንደነበሩ ሲታወቅ፥ ቁጥራቸው ከዚህ እንደሚበልጥ የሚያጠራጥር አይሆንም (1ኛ ቆሮ. 15፡6)። ሁለተኛ፥ የሰባ ደቀ መዛሙርት ቡድን ነበር፤ ክርስቶስ እነዚህንም ለአገልግሎት አሰማርቷቸዋል (ሉቃስ 10፡1)። ሦስተኛ፥ 12ቱ ደቀ መዛሙርት ነበሩ። ማቴዎስ ክርስቶስ እነዚህን ደቀ መዛሙርት እንዴት እንደመረጣቸው በመግለጽ፥ ስማቸውን ዘርዝሯል። እነዚህ ሰዎች በጥልቀት የሠለጠኑ ሲሆን፥ የሐዋርያነት ኃላፊነት ተሰጥቷቸው ነበር። እነዚህ ሰዎች በቀድሞይቱ ቤተ ክርስቲያን፥ የክርስቶስን ሥልጣን ይዘው በእንደራሴነት አገልግለዋል። በመጨረሻም፥ ከክักษቶስ ጋር እጅግ ቀርበው የሚሠሩ ሦስት ደቀ መዛሙርት ነበሩ። በልዩ አጋጣሚዎች ክርስቶስ ጴጥሮስን፥ ዮሐንስንና ያዕቆብን በመውሰድ አንዳንድ እውነቶችን ገልጦላቸው ነበር (ለምሳሌ፥ ማቴ. 17፡1)። ክርስቶስ አንድ ከሁሉም በላይ የቀረበ ወዳጅ እንደነበረው የሚያሳዩ ፍንጮች አሉ። ዮሐንስ ራሱን የገለጸው «ክርስቶስ ይወደው የነበረው ደቀ መዝሙር» በማለት ነበር (ዮሐ. 20፡2)። ክርስቶስ ከሁሉም ደቀ መዛሙርት ጋር እኩል ዝምድና አልነበረውም። ክርስቶስ ዓለምን ለመለወጥ ጥቂት ሰዎችን በብቃት አሠልጥኗል። ዛሬ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች የክርስቶስን አብነት ተከትለው ብዙ ሰዎች ከማሠልጠን ሊቆጠቡና ጥቂቶችን ደህና አድርጎ በማሠልጠኑ ላይ ሊያተኩሩ ይገባል ትላለህ? ማቴዎስ 10 ክርስቶስ 12ቱ ደቀ መዛሙርት በአንድ የአገልግሎት ጉዞ እንዲያከናውኑ የሚፈልገውን መስፈርት የቀድሞይቱ ቤተ ክርስቲያን መሪዎች የ12ቱን ደቀ መዛሙርት ምሳሌነት ተከትለው ወንጌልን በዓለም ሁሉ በሚመሰክሩበት ጊዜ ሊጠብቁ ከሚገባቸው ገጠመኞች ጋር የሚያዋህድ በመሆኑ፥ አስገራሚ የወንጌል ክፍል ነው። ማቴዎስ የ12ቱን ደቀ መዛሙርት ለአገልግሎት መላክ ተጠቅሞ፥ ከሁሉም የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ምን እንደሚጠበቅ አስተምሯል። በምኵራብ መደብደብን የመሳሰሉት ብዙዎቹ ነገሮች ክርስቶስ በምድር ላይ በነበረ ጊዜ ባይከሰቱም፥ ክርስቶስ ካረገ በኋላ በአይሁድ ክርስቲያኖች ላይ ደርሰዋል። ከዚህ ክፍል የሚከተሉትን ነገሮች እንመለከታለን፦ ሀ. መጀመሪያ ክርስቶስ 12ቱ ደቀ መዛሙርቱ አሕዛብን ወይም ሰማርያውያንን ሳይሆን አይሁዶችን እንዲያገለግሉ አዝዟቸዋል። በኋላ ግን ክርስቶስ ይህንን አመለካከት ለውጧል። በማቴዎስ 28፡19-20 እና በየሐዋ. 1፡8 ክርስቶስ እነዚህ አገልጋዮች ወደ ሰዎች ሁሉ እንዲሄዱ አዟቸዋል። ምናልባትም ማቴዎስ የቀድሞይቱ ቤተ ክርስቲያን የአገልግሎት አሠራር እያሳየ ይሆናል። እንደ ጳውሎስ ከአይሁዶች ይጀምሩና ወንጌሉን በፍጥነት ወደ አሕዛብ ይወስዱ ነበር (የሐዋ. 13፡44-48ን አንብብ)። ለ. ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ የጠራ መልእክት ሰጥቷቸዋል። ይኸውም ስለ መንግሥተ ሰማይ እንዲያስተምሩ ነበር። ያስተላለፉት መጥምቁ ዮሐንስና ክርስቶስ ያስተማሩትን ተመሳሳይ መልእክት ነበር። የክርስቶስ ተከታዮች አዳዲስ እውነቶችን ከመሻት ይልቅ መልእክታቸውን ቀለል አድርገው ማቅረብ ነበረባቸው። ሐ. ደቀ መዛሙርቱ የክርስቶስን ዓይነት አገልግሎት በማካሄድ፥ ሊፈውሱ፥ ሙታንን ሊያስነሡና አጋንንትን ሊያስወጡ ይገባቸው ነበር። በኋላም እነዚህ 12ቱ ደቀ መዛሙርት፥ «ሐዋርያት» ተብለው ተጠርተዋል። ለዚህም ምክንያቱ መልእክቱን ለማወጅና ተግባራቱን ለማከናወን በክርስቶስ ሥልጣን የተላኩ መሆናቸው ነው። መ. ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱ ገንዘብና ተጨማሪ ልብስ በመውሰድ ራሳቸውን ከሚንከባከቡ ይልቅ በሰዎች እንግዳ ተቀባይነት ላይ እንዲደገፉ ነግሯቸዋል። ብዙውን ጊዜ አንድ ሰው ወደ አዲስ አካባቢ በሚሄድበት ጊዜ፥ ለምግብና መኝታ የሚከፍለውን ገንዘብ፥ ተጨማሪ ልብስ ይይዛል። ክርስቶስ ለዚህ የደቀ መዛሙርት የጉዞ አገልግሎት የሰጠው መመሪያ ጊዜያዊ ነበር። የክርስቶስ ትእዛዝ ሌሎችን ለእግዚአብሔር መንግሥት የማዘጋጀቱ ተግባር አጣዳፊ እንደሆነ ያሳያል። እርሱም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ለመቆየት ብዙ ጊዜ አልቀረውም። ይህ ትእዛዝ ጊዜያዊ በመሆኑ፥ ክርስቶስ በኋላ ለውጦታል (ሉቃስ 22፡35-37)። ክርስቶስ ካረገ በኋላ፥ ሐዋርያት ለረዥም ጊዜ አገልግሎት የሚስማማ ሌላ አሠራር ተከተለዋል። ደቀ መዛሙርቱ ወደ አንዲት ከተማ በሚደርሱበት ጊዜ፥ እግዚአብሔር ወደ ቤቱ ወስዶ የሚንከባክባቸውን ሰው ያዘጋጅላቸው ነበር። ባለቤቱና የከተማይቱ ነዋሪዎች የክርስቶስ መልእክተኞች አድርገው ሲቀበሏቸው፥ በእነርሱ ላይ የእግዚአብሔርን ሰላም የማወጅ ሥልጣን ተሰጥቷቸው ነበር። ነገር ግን ሕዝቡ የክርስቶስን ደቀ መዛሙርት ለመቀበል ካልፈለጉ፥ ደቀ መዛሙርቱ የእግራቸውን ትቢያ ማራገፍ ነበረባቸው። ይህም አይሁዶች ከከተማይቱ ምንም ነገር እንዳልወሰዱና እግዚአብሔር በከተማይቱ እንደሚፈርድ ለማመልከት የሚጠቀሙበት ተምሳሌት ነበር። ሕዝቡ ወንጌሉን ሰምተው ሊቀበሉ የሚችሉበት ዕድል ነበራቸው፤ ይህን ለማድረግ ባለመፈለጋቸው፥ እግዚአብሔር በአብርሃም ዘመን ካጠፋቸው የሰዶምና ገሞራ ከተሞች በላይ፥ ኃጢአተኞች ይሆናሉ (ዘፍጥ. 19)። ስለሆነም፥ በፍርድ ቀን በእግዚአብሔር ይኮነናሉ። ማቴዎስ፥ ለክርስቶስ የሚሰጠው አገልግሎት

የዐሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት መላክ (ማቴዎስ 10:1-42) Read More »

ክርስቶስ የፈጸማቸውን የተለያዩ ተአምራት ማቴዎስ 8:1-9:38

የውይይት ጥያቄ፡- ማቴ. 8-9ን አንብብ። ሀ) ክርስቶስ የፈጸማቸውን የተለያዩ ተአምራት ዘርዝርና እያንዳንዳቸው ስለ ክርስቶስ ምን እንደሚያስተምሩ ግለጽ። ለ) ከእነዚህ ምዕራፎች ስለ ደቀ መዝሙርነት ምን እንማራለን? ሐ) የክርስቶስ ፈውስ ዛሬ ብዙ አገልጋዮች ከሚያካሂዱት ፈውስ ጋር በምን እንደሚመሳሰልና እንደሚለያይ ግለጽ። ማቴዎስ የክርስቶስን የሕይወት ታሪክ የጻፈው፥ እውነተኛ መሢሕ መሆኑን ለአይሁዶች ለማሳመንና ለክርስቲያኖች ደግሞ የክርስቶስ ተከታይ መሆን ማለት ምን ማለት እንደሆነ ለማመልከት መሆኑን ተመልክተናል። ማቴዎስ ክርስቶስ ስለፈጸማቸው አሥር ተአምራት የገለጸበት ሁኔታም እነዚህኑ ጭብጦች ያሳየናል። ማቴዎስን ከሌሎች ሁለት የወንጌል መመሳሰል (ማመሳከሪያዎች) ጋር በምናነጻጽርበት ጊዜ፥ 1) ማቴዎስ እነዚህን ታሪኮች በጊዜ ቅደም ተከተል እንደማይተርክ እንመለከታለን። ከእነዚህ ተአምራት ውስጥ አንዳንዶቹ ከተራራው ስብከት በፊት የተፈጸሙ ሲሆኑ፥ የተቀሩት ግን ከዚያ በኋላ የተፈጸሙ ሳይሆኑ አይቀሩም። ማቴዎስ ግን ክርስቶስ የፈጸማቸውን የተአምራት ዓይነቶች ለማብራራት ተጠቅሞባቸዋል። 2) ማቴዎስ በክርስቶስ ትምህርት ላይ በማተኮሩ ምክንያት፥ ስለ እነዚህ ተአምራት ከማርቆስና ከሉቃስ ያነሰ ማብራሪያ ይሰጣል። የለምጻሙ ሰው መፈወስ ተአምር (ማቴ. 8፡1-4) በአይሁዶች አመለካከት እንደ ለምጽ ያለ አስከፊ በሽታ አልነበረም። አይሁዶች በአያሌ ምክንያቶች ለምጽን ይጠሉ ነበር። በመጀመሪያ፥ በሽታው ሊፈወስ የማይችልና የግለሰቡን መልክ የሚያበላሽ ነው ብለው ስለሚገምቱ ነበር። ሁለተኛ፥ በአይሁድ እምነት ለምጻም ሰው ርኩስ በመሆኑ፥ ከቤተሰቡና ከኅብረተሰቡ ተለይቶ ሌሎች የማይፈለጉ ሰዎች ከሚኖሩበት ወጣ ያለ አካባቢ ለመኖር ይገደድ ስለነበረ ነው። ለምጻሙ ሰው ክርስቶስ እንዲፈውሰው በጠየቀው ጊዜ፥ ክርስቶስ አንድ ቃል በመናገርና በመዳሰስ ፈወሰው። ክርስቶስ ለምጻሙን በመንካቱ በሽታውን አለመፍራቱንና ለበሽተኛው ርኅራኄ እንዳለው አሳይቷል። የክርስቶስ ዳሰሳ ከማርከስ ይልቅ በሽተኛውን ከለምጹ አነጻው። ክርስቶስ ግለሰቡ እንደገና ከማኅበረሰቡ ለመቀላቀል የብሉይ ኪዳንን መስፈርቶች እንዲያሟላ በማዘዙ፥ ለሕጉ የነበረውን አክብሮት አሳይቷል (ዘሌዋ. 13-14)። ከዚያም ለምጻሙ ስለ ተአምሩ ለማንም እንዳይናገር አስጠነቀቀው። ለምን? ለዚህ በምክንያትነት የሚጠቀሱ አያሌ አሳቦች አሉ። በመጀመሪያ፥ ክርስቶስ በተአምር አድራጊነት ለመታወቅ አልፈለገም ነበር። ስለሆነም የተአምራት ሠሪነቱ ዜና እንዲሰራጭ አልፈቀደም። ሁለተኛ፥ ክርስቶስ አገልግሎቱ ሚዛናዊነትን እንዲያጣ አልፈለገም። ፍላጎቱ በሰዎች ሕይወት ውስጥ ዘላቂ ፍሬና ለውጥ ሊያስከትል በሚችለው የማስተማር አገልግሎቱ ላይ ለማተኮር ነበር። በፈውስ አገልግሎቱ ላይ ማተኮር፥ የሰዎችን አሳብ ይበልጥ በመሳብ፥ አስፈላጊ ከሆነው ጉዳይ ለማስተማሪያ የሚፈልገውን ጊዜ ይሻማበት ነበር። ሦስተኛ፥ ሕዝቡ ለመንፈሳዊ ለውጦች ትኩረትን ሳይሰጥ ሥጋዊ ፍላጎታቸውን የሚያሟላ ዓይነት መሢሕ አድርገው እንዲረዱት አልፈለገም ነበር። ማቴዎስ ይህን የመጀመሪያ ተአምር የጠቀሰው፥ ለአያሌ ምክንያቶች ነበር። በመጀመሪያ፥ አይሁዶች በመሢሑ የአገዛዝ ዘመን ለምጽ እንደማይኖር ያምኑ ነበር። ስለሆነም ክርስቶስ እንደ መሢሕ ለምጽን የማስወገድ ኃይል እንዳለው ለማሳየት ፈለገ። ሁለተኛው፥ ማቴዎስም ኢየሱስ በየትኛውም ዓይነት በሽታ ላይ ኃይል እንዳለው አሳየ። በዚህ ረገድ ኢየሱስ ለምጽን መፈወስ ከቻለ የትኛውንም ዓይነት በሽታ ሊፈውስ ይችላል ማለት ነው። የክርስቶስ ተከታዮች የሆንን ሁላችን ክርስቶስ ከበሽታ ሊፈውስ እንደሚችል ማመን አለብን። ነገር ግን ክርስቶስ በሽታዎችን ሁሉ የመፈወስ ኃይል ቢኖረውም፥ የሚሠራው እንደ ፈቃዱ ስለሆነ፥ የተገዥነት መንፈስ ሊኖረን ይገባል። ዛሬ ብዙ ሰዎች የፈውስ አገልግሎት ይዘው ወደ ተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት ይሄዳሉ። የፈውስ አገልጋይ ሁሉ ከእግዚአብሔር እንዳልሆነ ግልጽ ነው (2ኛ ተሰ. 2፡9፤ ራእይ 13፡13-14፤ 19፡20ን አንብብ።) አንድ የፈውስ አገልጋይ እግዚአብሔርን መወከል አለመወከሉን እንዴት እናውቃለን? ባለፈው ሳምንት እንደተመለክተነው፥ ቀዳሚው መንገድ የግለሰቡን ባሕርይ መፈተን ነው። ግለሰቡ በማቴዎስ 5፡3-12 ላይ የተጠቀሱት ባሕርያት አሉት? ከዛሬው ታሪክ የምንመለከታቸው ሌሎች ፍንጮች አሉ። ግለሰቡ የክርስቶስን የፈውስ አገልግሎት ምሳሌ ይከተላል? የክርስቶስን የፈውስ አገልግሎት በምንመለከትበት ጊዜ፥ ሰዎች ሁሉ ብድግ ብለው በመቆም ፈውሳቸውን እንዲቀበሉ እንዳላዘዘና «አጠቃላይ» ፈውስ እንዳልሰጠ እንመለከታለን። ከሕዝቡ መካከል ሳይሆን፥ ከሚፈውሰው ግለሰብ ጋር በግል ይገናኝ ነበር። በተጨማሪም፥ ሰዎች እንደ ተአምራት ሠሪ እንዲረዱትና ወደ እርሱ እንዲሳቡ የማድረግ ፍላጎት አልነበረውም። ስለዚህ ሕዝቡ ስለ ተአምራቱ እንዳያወሩ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት ያደርግ ነበር። ክርስቶስ ሰዎች ከእርሱ ጋር ግንኙነት እንዲመሠርቱና እግዚአብሔርን በሚያስከብር መንገድ እንዲኖሩ ማስተማር ከፈውስ እንደሚበልጥ ያውቅ ነበር። በዚህም እንዲሁም የክርስቶስ ፈውስ ቅጽበታዊና የተሟላ እንደሆነ እንመለከታለን። ከፊል ፈውስ (ለምሳሌ፥ የሽባው ወደ ማነከስ ደረጃ መሻሻል) ወይም በሽታው ዳግም ያገረሸበት ሁኔታ አልነበረም። የውይይት ጥያቄ፡- ዛሬ የምንመለከታቸው አብዛኞቹ የፈውስ አገልግሎቶች ከነዚህ መመዘኛዎች አንጻር እንዴት ይታያሉ? المቶ አለቃው ባሪያ ፈውስ (ማቴ. 8፡5-13) ምንም እንኳ ማቴዎስ ወንጌሉን የጻፈው ለአይሁዶች ቢሆንም፥ ክርስቶስ ለአሕዛብም ትኩረትን እንደሰጠ አመልክቷል። ስለሆነም፥ ማቴዎስ የመቶ አለቃውን ባሪያ የፈውስ ታሪክ አካትቷል። የመቶ አለቃው የ100 ሰዎች (ወታደሮች) ሹም የሮም ጦር መኮንን ነበር። ይህ የመቶ አለቃ ዋነኛ የንግድ መተላለፊያ በሆነችው በቅፍርናሆም ይኖር ነበር። ምንም እንኳ የሮም ወታደሮች በአይሁዶች የተጠሉ ቢሆኑም፥ ይህ የመቶ አለቃ በጣም የተከበረ መሆኑን ሉቃስ (7፡1-5) ይናገራል። ይህን ሰው ራሳቸው አይሁዶች ነበሩ ወደ ክርስቶስ አምጥተው እንዲፈውሰው የለመኑት። ማቴዎስ የዚህን መቶ አለቃ አስደናቂ እምነትና ስለ ክርስቶስ ኃይል የነበረውን ግንዛቤ ገልጾታል። ሰውየው አሕዛብ ቢሆንም፥ እምነቱና ለክርስቶስ የሰጠው እውቅና ከአብዛኞቹ አይሁዶች የላቀ ነበር። አይሁዶች እንረክሳለን ብለው ስለሚፈሩ፥ ወደ አሕዛብ ቤት አይሄዱም ነበር። ነገር ግን ክርስቶስ ለዚህ ዓይነት ግርጃ ስለማይገዛ ወደ ግለሰቡ ቤት ለመሄድ ፈለገ። የመቶ አለቃው ግን ከለከለው። ይህን ያደረገው ክርስቶስ እንዳይረክስ ስለፈለገ ነበር ወይስ፥ ኃጢአተኛ በመሆኑ ክርስቶስን በቤቱ የማስተናገድ ብቃት እንዳልነበረው በመገንዘብ? መልሱን አናውቅም። ከግለሰቡ ምላሽ የምንረዳው ነገር ቢኖር፥ በክርስቶስ ኃይል ላይ ሙሉ እምነት እንደነበረው ነው። የመቶ አለቃው የክርስቶስን ኃይል ከራሱ ሥልጣን ጋር አነጻጸረ። ሮማውያን ሁሉም ሥልጣን ከንጉሡ እንደሚመነጭ ያምኑ ነበር። ያ ሥልጣን በተዋረድ እስከ ተራው ወታደር ይደርሳል። በየትኛውም የተዋረደ ደረጃ ላይ «አልታዘዝም» ማለት ንጉሡን ካለመታዘዝ እኩል ይቆጠር ነበር። ተግባራቱም የሚፈጸሙት በቃል ትእዛዝ ነበር። እንደ መቶ አለቃ፥ ሥራውን ራሱ የማከናወን ግዴታ አልነበረበትም፤ ሥልጣን ማለት ሌሎችን እያዘዙ ማሠራት ማለት ነበር። የመቶ አለቃው ይህንኑ ግንዛቤውን ከክርስቶስ ጋር አዛምዷል። ሁሉም አጠቃላይ ሥልጣን ከእግዚአብሔር እንደሚመነጭና እንደ እግዚአብሔር ወኪል የክርስቶስ ቃላት የእግዚአብሔርን ሥልጣን እንደሚያንጸባርቁ ተገነዘበ። የመቶ አለቃው ክርስቶስ ታላቅ ኃይል እንዳለውና ራሱ ወደ ቤቱ መምጣት እንደማያስፈልገው አመነ። የአፉ ቃል ብቻ ፈውስን ያመጣል ብሎ አሰበ። የክርስቶስ ንግግር እግዚአብሔርን ስለሚወክል፥ የአፉ ቃል እንደሚፈውስ አመነ። የዚህን ግለሰብ እምነት ታላቅነት የምንገነዘበው ስለ ክርስቶስ ኃይልና ከእግዚአብሔር ጋር ስላለው ግንኙነት ከማወቁ ላይ ብቻ ሳይሆን፥ ክርስቶስ ከበሽተኛው አጠገብ ርቆ ቢገኝም እንኳ ሊፈውስ እንደሚችል በማመኑ ነው። እስከዚህ ጊዜ ድረስ፥ ክርስቶስ ይህንን አላደረገም ነበር። ክርስቶስ በመቶ አለቃው እምነትና ግንዛቤ ተደነቀ። ኢየሱስ ለአይሁዶችና ለደቀ መዛሙርት ብዙ አሕዛብ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት እንደሚጨመሩ በመግለጽ አስጠነቀቀ። ሥጋዊ ዝርያቸው የእግዚአብሔር ቤተሰብ አካል ያደርገናል ብለው የሚያስቡ ብዙ አይሁዶች ደግሞ ከመንግሥቱ ውጭ ቀርተው የዘላለምን ፍርድ ይቀበላሉ። ኢየሱስ የጴጥሮስን አማትና ሌሎች ሰዎችን ፈወሰ (ማቴ. 8፡14-17) ማቴዎስ የክርስቶስን የፈውስ አገልግሎት ማብራራቱን ቀጥሏል። የጴጥሮስ አማትና ሌሎችም የከተማይቱ ነዋሪዎች ተፈወሱ። በተጨማሪም፥ ክርስቶስ አጋንንትን ከሰዎች አስወጣ። ነገር ግን ማቴዎስ በዚህ ታሪክ ውስጥ አጽንኦት የሰጠው ለተአምሩ ሳይሆን፥ ለብሉይ ኪዳን ትንቢት ፍጻሜ ነበር። ክርስቶስ በሁሉም ዓይነት በሽታዎች ላይ ኃይል እንዳለው በማሳየቱ፥ በኢሳይያስ 53፡4 እንደተተነበየው፥ መሢሑ የእግዚአብሔር ባሪያ መሆኑን አረጋግጧል። እነዚህ ሦስት ተአምራት ሁሉ፥ ማቴዎስ በዓለም የማይጠቅሙ ተደርገው የሚታሰቡትን ሰዎች መምረጡ አስገራሚ ነው። የመጀመሪያው ከበሽታው የተነሣ ከኅብረተሰቡ የተገለለ ለምጻም ሲሆን፥ ሁለተኛው በብዙ ምክንያት የተናቀ አሕዛብ ነበር። ሦስተኛዋ በጾታዋ ምክንያት ዝቅተኛ ግምት የሚሰጣት ሴት ነበረች። ምናልባትም ማቴዎስ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዓለም ለናቃቸው ሰዎች የሚያስብ መሆኑን ለማሳየት የፈለገ ይመስላል። ማንም ለእርሱ አላስፈላጊ አይደለም፤ እርሱ ሰዎችን በእኩል ደረጃ ያያል። ክርስቶስ ደቀ መዝሙርነት ስለሚያስከፍለው ዋጋ አብራራ (ማቴ. 8፡18-22) ማቴዎስ የክርስቶስ ደቀ መዝሙር ለመሆን ስለፈለገ አንድ ሰው በመግለጽ፥ የተአምራት ትረካውን ገትቷል። በዚህም ማቴዎስ ዋናኛው ጉዳይ ደቀ መዝሙርነት እንጂ ተአምር እንዳልሆነ አሳይቷል። ክርስቶስን መከተል ማለት ምን

ክርስቶስ የፈጸማቸውን የተለያዩ ተአምራት ማቴዎስ 8:1-9:38 Read More »

የኢየሱስ ተከታዮች ሊከተሏቸው የሚገቡ መሠረታዊ መርሖዎች (ማቴ. 6፡19-7፡29)

አንዳንድ ጊዜ ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ግንኙነት እናወሳስበዋለን። የተለያዩ ክርስቲያን መሪዎች እንደ ክርስቲያን ፍሬያማ መሆን ማለት ምን ማለት እንደሆነ ብዙ አሳቦችንና ደንቦችን ያስተምራሉ። ይህ ደግሞ ክርስቲያኖች ተስፋ እንዲቆርጡና የበደለኛነት ስሜት እንዲሰማቸው ከማድረጉም በላይ በኋላ ሰዎችን ለማስደሰት ከመጣር በቀር ከእግዚአብሔር ጋር መልካም ግንኙነት እንዲኖረን አያደርግም። ኢየሱስ በቀጣዩ የተራራው ላይ ስብከቱ የመንፈሳዊ ሕይወትን መሠረታዊ መርሖዎች ቀለል አድርጎ አቅርቧል። እነዚህን መርሖዎች ከግል ሕይወታችን ጋር ብናዛምድ፥ በመንፈሳዊ ሕይወታችን አድገን የክርስቶስ በሳል ደቀ መዛሙርት ለመሆን እንችላለን። የውይይት ጥያቄ፡- ማቴ. 6፡19-7፡29ን አንብብ። ሀ) ክርስቶስ የሰጣቸውን መሠረታዊ ትምህርቶች ዘርዝር። ለ) የክርስቶስ ተከታይ መሆን ማለት ምን ማለት እንደሆነ ለመረዳት እነዚህን መርሖዎች መገንዘብ የሚያስፈልገን እንዴት ነው? መርሕ አንድ፦ በግል ሕይወትህ ላይ ሳይሆን፥ በዘላለሙ መንግሥት ላይ ትኩረት አድርግ። ክርስቲያኖችን ከሚያጋጥሙ ዐበይት ፈተናዎች አንዱ፥ የገንዘብ ጉዳይ ነው። ሁላችንም ለመተዳደሪያ የምንፈልገው ነገር በመሆኑ ገንዘብ በራሱ መጥፎ አይደለም። በዛሬው ዓለም ውስጥ ገንዘብ ከሌለን፥ ምግብ ለመመገብ፥ ልብስ ለመግዛት፥ የመኖሪያ ቤት ለመከራየት አንችልም። ነገር ግን ከዚህ አልፈን ገንዘብን በልባችን ውስጥ ከዐበይት ፍላጎቶቻችን አንዱ እንዲሆን በቀላሉ እናደርጋለን። ብዙ ገንዘብ ካገኘን ደስታችን የሚጨምር ይመስለናል። አዳዲስ ልብሶችን ልንገዛ፥ የተሻለ ምግብ ልንመገብ፥ በምርጥ ቤት ውስጥ ልንኖር እንችላለን። ይህም ብዙዎቻችን ተጨማሪ ገንዘብን እንድናገኝና ገንዘቡ የሚያስገኘውን ተጽዕኖና ደኅንነት እንድናሳድድ ያደርገናል። ገንዘብ ሕይወታችንን እንዲቆጣጠር የምንፈቅድበት ዋንኛው ምክንያት፥ የተሳሳቱ ነገሮችን መመልከታችን እንደሆነ ኢየሱስ ራሱ ገልጾታል። ሥጋዊና መንፈሳዊ ዓይኖቻችን ለራሳችን የተመቻቸ ሕይወትን በማዘጋጀት ላይ ካተኮሩ፥ ልባችን በመንፈሳዊ ጽልመት ይሞላል። ነገር ግን መንፈሳዊ ዓይኖቻችን በመንፈሳዊ ነገሮችና በዘላለማዊ ጉዳዮች ላይ ካተኮሩ፥ ከሁሉም የሚልቀው ምን እንደሆነ በመገንዘብ ለዘላለም ሕይወታችን የሚጠቅም አኗኗርን እንከተላለን። ሥጋዊ ዓይኖቻችን መንገድ አይተን እንድንሄድ እንደሚረዱን ሁሉ፥ መንፈሳዊ ዓይኖቻችንም መንፈሳዊ እውነቶችን ተረድተን በመንፈሳዊ አኳኋን እንድንመላለስ ይረዱናል። የዓለም ነገሮች መንፈሳዊ ዓይኖቻችንን እንዲያሳውሩ ከፈቀድናቸው መንገዳችን በጨለማ ተደናቅፎ ከእግዚአብሔር እውነት እንርቃለን። ከዚያ በኋላ ክርስቶስን ልንከተል አንችልም። (ይህ የምንመለከታቸውን ቪዲዮዎችና የምናነባቸውን መጻሕፍት በጥንቃቄ መምረጥ እንዳለብን ያስጠነቅቀናል። የምንመለከታቸው ቪዲዮዎች፥ የምናነባቸው መጻሕፍትና መጽሔቶች በአስተሳሰባችንና በተግባራችን ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖን ያስከትላሉ።) ኢየሱስ አንድ ልብ ከአንድ ጌታ የበለጠ ሊያስተናግድ እንደማይችል ገልጾታል። ይህም ክርስቶስ ወይም እንደ ገንዘብ ያለ ሌላ ነገር ሊሆን ይችላል። አንድ ሰው ገንዘብን ወይም ሌላ ማንኛውንም ሥጋዊ ነገር የሕይወቱ ቀዳሚ ትኩረት እያደረገ «የክርስቶስ ተከታይ ነኝ» ሊል አይችልም። ብዙም ሳይቆይ የገንዘብ ፍቅሩ ከምድርና ከሰማይ መርሖዎች አንዱን እንዲመርጥ ስለሚያስገድደው፥ ምድርንና ጊዜያዊ በረከቶቿን መምረጡ አይቀርም። የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ዛሬ ሰዎች እጅግ የሚፈልጓቸውና እነርሱን ለማግኘት ሲሉ በክርስቶስ ላይ ያላቸውን እምነት የሚያመቻምቹላቸው ነገሮች ምንድን ናቸው? ለ) እነዚህ ሰዎች ዓይኖቻቸውን ከዘላለማዊ ነገሮች ላይ ያነሡት እንዴት ነው? መርሕ ሁለት፦ ስለ ማንኛውም ነገር አትጨነቅ፥ ለሁሉም በእግዚአብሔር ተማመን (ማቴ. 6፡25-34)። በዕብ. 11፡6 ላይ፥ ያለ እምነት እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት እንደማይቻል ይናገራል። በአንድ ደቀ መዝሙር ሕይወት ውስጥ እጅግ መሠረታዊ የሆነው መርሕ በነገር ሁሉ በእግዚአብሔር የመታመን መርሕ ነው። በምንጨነቅበት ጊዜ ሁሉ፥ እግዚአብሔር ፍላጎታችንን ስለ ማሟላቱ መጠራጠራችን ነው። ሰዎች የሚጨነቁባቸው መሠረታዊ ነገሮች ምንድን ናቸው? ምግብና ልብስ ናቸው። ክርስቶስ ግን ለእነዚህም መጨነቅ እንደማያስፈልግ አስተምሯል። ገንዘብ የሚያስቀምጡባቸው ባንኮች ወይም ምግብ የሚገዙባቸው የገበያ አዳራሾች ባይኖሯቸውም፥ እግዚአብሔር የምድር ፍጥረታትን ሁሉ ይመግባል። እነዚህ ፍጥረታት ምግብ አጥተው አይራቡም። እግዚአብሔር ሰዎች ከአዕዋፋትና ከእንስሳት እንደሚበልጡ ገልጾታል። ስለሆነም እግዚአብሔር አነስተኛ አስፈላጊነት ያላቸውን እንስሳት ከመገበ፥ የሰዎችን ብቻ ሳይሆን የመንፈሳዊ ልጆቹን ፍላጎቶች እንደሚያሟላ እንገነዘባለን። ክርስቶስ የንጉሥ ሰሎሞንን ውብ ልብሶች ከአበቦች ጋር አነጻጽሯል። እግዚአብሔር ትናንሽ ተክሎችን እንደ ሰሎሞን ካሉት እጅግ ሀብታሞች የበለጠ አድምቆ ያላብሳቸዋል። እነዚህ አበቦች ከጥቂት ቀናት ወይም ሳምንታት የበለጠ ዕድሜ የላቸውም፤ ወዲያው ጠውልገው በእሳት ይቃጠላሉ። ሰዎች፥ በተለይም የእግዚአብሔር መንፈሳዊ ልጆች፥ ለእግዚአብሔር ከአበቦችና ከተክሎች በላይ አስፈላጊዎች ናቸው። ስለሆነም ያለጥርጥር የምንፈልገውን ልብስ ያለብሰናል። የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) የምትጨነቀው ምን ለማግኘት ነው? ለ) ጭንቀት በእግዚአብሔር አለመታመንህን የሚያሳየው እንዴት ነው? የጭንቀት ተቃራኒ ምንድን ነው? ከጭንቀት ለመገላገል የሚረዳን ምንድን ነው? በሕይወት የተሳሳቱ እሴቶችን ከመያዝ የሚጠብቀን ምንድን ነው? ክርስቶስ ተከታዮቹ በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ከፍተኛ ትኩረት እንዲያደርጉ አሳስቧቸዋል። ዓይኖቻቸውን በእግዚአብሔር ዘላለማዊ ነገሮች ላይ ልንጥል ይገባል። ክርስቶስ ሀ) በእርሱ አገዛዝና ለእርሱ አስፈላጊ በሆኑት ነገሮችና ለ) ከእርሱ ጋር ካለን ግንኙነት በሚመጣው ጽድቅ ላይ ብናተኩር፥ ጭንቀታችን እንደሚወገድ ገልጾታል። ይህም ጽድቅ በታዛዥነትና በትክክለኛ መንገድ በመመላለስ ራሱን ይገልጻል። ጠቃሚዎቻችን ናቸው የምንላቸው ነገሮች ከእግዚአብሔር መንገዶች ጋር የሚስማሙ ሲሆኑ፥ እንደ ገንዘብና ትምህርት ያሉ ሌሎች ጌቶች እንዲቆጣጠሩን አንፈቅድም። ይህም ሲሆን እግዚአብሔር ብዙውን ጊዜ የሚያስጨንቁንን መሠረታዊ ፍላጎቶቻችንን ያሟላል። የውይይት ጥያቄ፡- ማቴ. 6፡33ን በቃልህ አጥና። ሀ) የክርስቶስን መንግሥትና ጽድቅ በትጋት የምትሻባቸውን መንገዶች ዘርዝር። ለ) ጭንቀት በዘላለማዊ ነገሮች ላይ አለማተኮራችንን የሚያመለክተው እንዴት ነው? በመጨረሻም ክርስቶስ ስለ ወደፊቱ ዘመን መጨነቁ ሞኝነት እንደሆነ አብራርቷል። ምንም ያህል ብንጨነቅ የነገን ክስተቶች መለወጥ አን can’t። ጭንቀት የሚያስከትለው ነገር ቢኖር ኀዘን፥ ሽበትና የጨጓራ ሕመም ብቻ ነው። አባታችን የወደፊቱን ዘመን እንደሚቆጣጠርና እርሱ ያልወሰነው ነገር እንደማይደርስብን እርግጠኞች ልንሆን ይገባል። በእርሱ ላይ ዓይኖቻችንን ተክለን በታዛዥነት የምንመላለስ ከሆን፥ እግዚአብሔር ወደፊት የሚመጣውን የትኛውንም ችግር ለመቋቋም የሚያስችል ብርታት ይሰጠናል። ችግሩ የሚመጣው መፍትሔውን ከራሳችን ለማመንጨት በምንታገልበት ጊዜ ነው። መርሕ ሦስት፦ ከሰዎች ጋር ባለህ ግንኙነት የፈራጅነትን አመለካከት አታንጸባርቅ (ማቴ. 7:1-6)። «የሆነ ምሥጢራዊ ነገር ስላለ ተጠንቀቅ። ልታታልልህ እየሞከረች ነው። አፏ የሚናገረው ቃል ከልቧ የፈለቀ አይደለም።» «ይህንን ለምን እንዳደረገች አውቃለሁ፤ ስለማትወደኝ ልትጎዳኝ ትፈልጋለች።» «ከእኔ ለመቅደም ስለሚፈልግ፥ ከእኔ ጋር አይስማማም። ይህን ያደረገው እርሱ የሌላ ጎሳ አባል ስለሆነና የእኛን ጎሳ ስለማይወድ ነው።» «ሊፕስቲክ መቀባቷ መንፈሳዊት ሴት አለመሆኗን ያሳየናል።» የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት ምሳሌዎች ክርስቶስ በማቴ. 7፡1-6 ላይ ካስተማረው አሳብ ጋር የማይስማሙት እንዴት ነው? ለ) የሌሎች ሰዎችን አነሣሽ ምክንያቶች ለመፍረድ የምንሞክርባቸው ሌሎች መንገዶች ምንድን ናቸው? የክርስቶስ ተከታዮችን ከሚያጋጥማቸው ታላላቅ ችግሮች አንዱ፥ ከሌሎች ክርስቲያኖች ጋር መልካም ግንኙነት አለማድረግ ነው። የችግሩም መንሥዔ በጎሳዎች፣ በመሪዎችና በግለሰቦች መካከል ጥርጣሬ የሚከሰትባቸውን ዐበይት ምክንያቶች አለመገንዘባችን ነው። ከግለሰቡ ተግባር ባሻገር ዘልቀን፥ ልቡን የምንመረምርበት የተለየ ዓይን ያለን ይመስለናል። ይህ ግን ስሕተት ነው። የሰውን ልብ የሚያውቀው እግዚአብሔር ብቻ ነው። ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱ ከዚህ የሰዎች ዝንባሌ እንዲታቀቡ «አትፍረዱ» ሲል አጥብቆ አስጠንቅቋቸዋል። «መፍረድ» የሚለው ቃል ሁለት ፍካሬያዊ ትርጉሞች አሏቸው። በመጀመሪያ፥ ክርስቲያኖች ሊያደርጉ የሚገቧቸውን ነገሮች መገምገምን ሊያመለክት ይችላል። ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱ የሰዎችን፥ በተለይም የሐሰተኛ አስተማሪዎችን ሕይወት በመገምገም እውነተኛ ደቀ መዛሙርት መሆን አለመሆናቸውን እንዲለዩ ነግሯቸዋል (ማቴ. 7፡15-20)። ግምገማው የሚካሄደው ግን በግልጽ መረጃዎች እንጂ በስውር አነሣሽ ምክንያቶች አይደለም። ሁለተኛው፥ መፍረድ የሌሎችን አነሣሽ ምክንያቶች በንቀት መመልከትን ሊያመለክት ይችላል። ይህንን በምናደርግበት ጊዜ አመለካከታችን፥ «እኛ ከእነርሱ እንሻላለን» የሚል ነው። ከተግባራቸው አልፈን ልባቸውን ለማየት የምንችል ይመስለናል። ክርስቶስ በዚህ መንገድ መፍረድ እንደሌለብን ተናግሯል። ብዙውን ጊዜ ሌሎችን ስንተች የራሳችንን ልብ በኃጢአት መቆሸሽ ከምንም አንቆጥርም። ኢየሱስ በዓይኑ የእንጨት ግንድ (ምሰሶ) ስላለበት ሰው በሚናገር አስገራሚ ምሳሌ ተጠቅሟል። ይህ ሰው በዓይኑ ጉድፍ ያለበት ሰው ሲያጋጥመው ለመርዳት ይሽቀዳደማል። በራሱ ዓይን ውስጥ ያለው ግንድ ግን ይህን ከማድረግ ይከለክለዋል። በተመሳሳይ መንገድ፥ የሌላውን ሰው የባሕርይ ችግር ወይም ድብቅ ኃጢአት ማየቱ ቀላል ነው። ነገር ግን ብዙዎቻችን ራሳችንን አጥርተን አንመለከትም። ለዚህ መፍትሔው የሌላውን ሰው ችግር ለማቃለል አለመሞከር አይደለም፤ ችግር ያለበትን ሰው መርዳቱ ተገቢ ነው። በመጀመሪያ ግን የራሳችንን ሕይወት አይተን ሌሎች ሕይወታችንን ለመመርመር እንዲረዱን ልንጠይቃቸው ይገባል። መጀመሪያ ሕይወታችን ከእግዚአብሔር ጋር እንዲስተካከል ካደረግን በኋላ፥ ሌላው ሰው በእግዚአብሔር ቃል ብርሃን ሕይወቱን እንዲመረምር በትሕትና ልንረዳው

የኢየሱስ ተከታዮች ሊከተሏቸው የሚገቡ መሠረታዊ መርሖዎች (ማቴ. 6፡19-7፡29) Read More »

የአምልኮ መርሖዎች (ማቴ. 6፡1-18)

ዮሐንስ የአንዲት አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን መጋቢ ነበር። እርሱም በጸሎቱ የታወቀ አገልጋይ ነበር። በየእሑዱ «ሃሌሉያ» እያለ ረዥም ጸሎት ያቀርባል። ዮሐንስ በረዥም ጸሎቱ መንፈሳዊነቱን ለሰዎች እንደሚያሳይ ያስብ ነበር። ብዙነሽ ክርስቲያን ነጋዴ ነበረች። አንድ ቀን ቤተ ክርስቲያኗ ለአዲስ የሕንጻ ግንባታ ገንዘብ ታሰባስብ ነበር። ብዙነሽ መሪው በምእመናኑ ፊት እያንዳንዱ ሰው የሰጠውን የገንዘብ ልክ እንደሚናገር ታውቅ ነበር። ስለሆነም ትክክለኛውን ጊዜ ጠብቃ ብዙ ስጦታ ይዛ ገባች። ለእግዚአብሔር ብዙ ገንዘብ ለመስጠት ሰዎችን ማስደነቅ መቻሏ ያስደስታታል። የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) መንፈሳዊ ነገሮችን በራስ ወዳድነት አመለካከት ማድረግ የሚቀልለው እንዴት ነው? ለ) መንፈሳዊ የሚመስሉ ነገሮችን የሰዎችን ትኩረት ለመሳብ ባለን ፍላጎት ልናደርግ የምንችልባቸውን መንገዶች ዘርዝር። ኤርምያስ በ17፡9 ላይ የሰው ልብ ክፉና ተንኮለኛ ማንም የማያውቀው እንደሆነ ይናገራል። በልባችን ራሳችንን ከምናታልልባቸው እጅግ አደገኛ መንገዶች አንዱ አምልኮ ነው። የሐሰት አምልኮ ሊመጣ የሚችለው የውሸት ጣዖት በማምለክ ወይም በኢየሱስ ክርስቶስ ባለማመን ብቻ አይደለም። ለእግዚአብሔር ሕዝብ፥ በምናከናውናቸው የአምልኮ ተግባራት ሁሉ የሐሰት አምልኮ መፈጸሙ ቀላል ነው። ስለሆነም ክርስቶስ የተሳሳተ አመለካከት በሚኖረን ጊዜ፥ ሊከሰቱ የሚችሉትን የተለመዱ የአምልኮ ተግባራት ገልጾታል። እነዚህ ምሳሌዎች ብቻ ናቸው። ለሌሎች መንፈሳዊ መስለን ለመታየት በምንፈልግበት ጊዜ ሁሉ፥ እግዚአብሔርን ማምለክ አቁመናል ማለት ነው። በኳየር (በሕብረ ዝማሬ) ውስጥ የምንዘምረው የኳየር ልብሳችንን ለማሳየት፥ ዓይኖቻችንን በመጨፈን ወደ ሰማይ በማየትና በመወዛወዝ መንፈሳዊነታችንን ለማሳወቅ፥ ወይም «ሃሌሉያ» እያልን በመጮኽ የሕዝቡን ስሜት ለማነሣሣት ከሆነ፥ እነዚህ ሁሉ ነገሮች የማይጠቅሙ ይሆናሉ። እውነተኛ አምልኮ ለእግዚአብሔር የሚቀርብ የልባችን መግለጫ ነው። ከዚህ ውጭ የምናደርገው ሁሉ የሐሰት አምልኮ ነው። በክርስቶስ ዘመን ሌሎችን ለማስገረም የሚካሄዱ የአምልኮ ተግባራት በፈሪሳውያን ሕይወት ውስጥ ይታዩ ነበር። አለባበሳቸው፥ በሕዝቡ ፊት የነበራቸው አክብሮትና ሰዎች ልብ ብለው እንዲያዩዋቸው መፈለጋቸው ሁሉ አምልኳቸው እንዲበላሽ አድርገዋል። ክርስቶስ እነዚህን አደጋዎች በመረዳት፥ ደቀ መዛሙርቱ አምልኳቸው ተቀባይነትን እንዲያገኝና ትክክለኛ አመለካከት እንዲኖራቸው «ምጽዋታችሁን በሰው ፊት እንዳታደርጉ ተጠንቀቁ፤ ያለዚያ በሰማያት ባለው አባታችሁ ፊት ዋጋ የላችሁም» ሲል አስጠነቀቃቸው። ክርስቶስ «ምጽዋታችሁን» ሲል በእግዚአብሔር ፊት «ትክክለኛ ነገሮችን» እንድንሠራ ማሳሰቡ ነው። ለድሆች በመመጽወት ማምለክ (ማቴ. 6፡1-4)። ለድሆች መስጠት እግዚአብሔር ከልጆቹ ሁሉ የሚጠብቀው ተግባር ነው። የወንጌል አማኝ ክርስቲያኖች፥ ሌሎች ወገኖች የሚሰጡበትን ምክንያት በመንቀፍ የሕይወት ማዕበል ለሚያንገላታቸው ወገኖች ርኅራኄን ማሳየት አቁመዋል። ነገር ግን ከመስጠት የሚበልጠው በምንሰጥበት ጊዜ በልባችን ውስጥ ያለው አመለካከት ነው። በመስጠት ዙሪያ አራት አመለካከቶች ይንጸባረቃሉ። በመጀመሪያ፥ «ለድሃ ብሰጥ እግዚአብሔር እኔን ወደ መንግሥተ ሰማይ ያስገባኛል፤ ኃጢአቴንም ይሰርዝልኛል» የሚል አመለካከት አለ። አንድ መልካም ነገር በማድረግ ኃጢአታችንን ልናስወግድ ወይም ወደ መንግሥተ ሰማይ ልንገባ አንችልም። አንድ ሰው የኃጢአትን ይቅርታ አግኝቶ በእግዚአብሔር ፊት ተቀባይነትን ሊያገኝ የሚችለው፥ የእግዚአብሔርን ይቅርታ በመጠየቅና በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን ብቻ ነው። ሁለተኛው፥ በመስጠት እግዚአብሔር ሀብታም እንዲያደርገን ለማስገደድ እንችላለን ብለው የሚያስቡ ሰዎች አሉ። «ለእግዚአብሔር ብዙ ገንዘብ ስጠው፤ ይህም እግዚአብሔር ከሰጠኸው የበለጠ እንዲመልስልህ ያደርገዋል። ለእግዚአብሔር 100 ብር ብትሰጠው፥ እርሱ 1000 ብር ይሰጥሃል። ብዙ ከሰጠኸው ሀብታም ትሆናለህ።» እግዚአብሔር በትክክለኛ አመለካከት ከሰጠነው ይባርከናል። ነገር ግን ብዙውን ጊዜ እግዚአብሔር የሚሰጠን የበረከት ተስፋ የግድ በምድር ላይ ብዙ ገንዘብ የምናገኝበት ሳይሆን፥ በመንግሥተ ሰማይ የምንቀበለው ነው። ከእግዚአብሔር ዘንድ አንድ ነገር ለማግኘት ተብሎ የሚደረግ ስጦታ የራስ ወዳድነት ተግባር ነው። ይህ በርኅራኄ ሳይሆን አንድን ነገር በአጸፋው ለማግኘት የሚደረግ ጥረት በመሆኑ፥ እግዚአብሔር የሚያከብረው ዓይነት ስጦታ አይደለም። ሦስተኛው፥ «ሌሎች አይተው በችሮታዬ ሊያመሰግኑኝ በሚችሉበት መንገድ ለድሃ መስጠት አለብኝ» የሚሉ ሰዎች አሉ። ይህ የርኅራኄ መግለጫ ሳይሆን፥ በሌሎች ፊት ታዋቂ ለመሆን የሚደረግ ስጦታ ነው። ክርስቶስ የዚህ ዓይነቱ መስጠት የሰዎችን ምስጋና ከማስከተል ያለፈ፥ ሌላ ማዕረግ እንደማያስገኝ ተናግሯል። ይህ እግዚአብሔርን የማያስደስት በመሆኑ፥ ከእርሱ ዘንድ ምንም ምስጋና አያስገኝም። ፈሪሳውያን የሚያደርጉት ይህንኑ ነበር። በቤተ መቅደስ ገንዘብ በሚሰጡበት ጊዜ ሕዝቡ ምን ያህል እንደሰጡ እንዲያውቁላቸው ይፈልጉ ነበር። እንዲያውም አንዳንዶች ሰዎች እንዲያዩላቸው መለከት እየነፉ ይሰበስቧቸው ነበር። አራተኛው፥ ከርኅራኄና እግዚአብሔርን ከመታዘዝ የተነሣ ለተጎዱ ሰዎች የሚበረከት ስጦታም አለ። ይህ ስጦታ በሚለገስበት ጊዜ ተመልካች ስለመኖር አለመኖሩ ሳንጨነቅ የምናደርገው ነው። መንፈሳዊ ልብ ለእውቅና አይጣደፍም። ስሙ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ስለ መጠራት አለመጠራቱም አይጨነቅም። ክርስቶስ በመስጠት ጊዜ የሚከሰተውን አደጋ በማጤኑ፥ ቀኝ እጃችን የሚሰጠውን ግራው እንደማያውቅ ያህል በምሥጢር እንድናደርገው አዟል። እግዚአብሔርን የሚያስደስተው የዚህ ዓይነቱ ልግስና ብቻ ነው። እግዚአብሔር ትልቅ ግምት የሚሰጠው የዚህ ዓይነቱን ልግስና ብቻ ነው። አንዳንድ ጊዜ እርሱን እንድናገለግለው በምድር ብዙ ሀብት በመስጠት ቢባርከንም፥ ከሁሉም የሚበልጠው በሰማይ የሚገኘው በረከት ነው። (አሁንም ቢሆን በሰማይ ትልቅ ስጦታ ለማግኘት ስንል፥ በራስ ወዳድነት ዓላማ አለመስጠታችንን ማረጋገጥ አለብን። እግዚአብሔር ከሰው ምንም ነገር ለማግኘት ሳይሆን፥ ከፍቅሩና ከርኅራኄው የተነሣ እንደሚሰጥ፥ የእኛም ስጦታ ከርኅራኄ ልብ ሊመነጭ ይገባል።) የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ክርስቲያኖች በእነዚህ አራት መንገዶች ሊሰጡ ስለሚችሉባቸው መንገዶች ግለጽ። ለ) በቤተ ክርስቲያንህ ሰዎችን ወደ ተሳሳቱ አቅጣጫዎች ሊመሩ የሚችሉ አንዳንድ ልምምዶች ምንድን ናቸው? ሐ) ምእመናን እግዚአብሔርንና ሰዎችን በመውደዳቸው ምክንያት፥ ከራስ ወዳድነት በጠራ መንፈስ በልግስና እንዲሰጡ ለማገዝ፥ ሊለወጥ የሚገባው ነገር ምንድን ነው? አምልኮ በጸሎት (ማቴ. 6:5-15)። ጸሎት ከተሳሳቱ አነሣሽ ምክንያቶች ሊመነጭ ይችላል? ክርስቶስ፥ «አዎን» ብሏል። ክርስቲያኖች የአምልኮ ግብዝነታቸውን ከሚያሳዩባቸው ዐበይት መንገዶች አንዱ ጸሎት ነው። ክርስቶስ ካስተማራቸው ዐበይት የአምልኮ ተግባራት አንዱ ጸሎት ነው። ብዙ ሰባኪዎች ሰዎችን ለማስደሰት ሲሉ ረዥም በሆኑ ወይም በስሜት ጸሎቶች ይጠቀማሉ። እንዲሁም ለስብከት የጸሎት ጊዜን ይጠቀማሉ። ጸሎት ከሰዎች ጋር ሳይሆን፥ ከእግዚአብሔር ጋር የምንነጋገርበት መሣሪያ ነው። ሌሎች መሪዎች የተወሰኑ ቃላትን በመደጋገም መንፈሳዊነታቸውን ለማሳየት ይፈልጋሉ። አንዳንዶች የእግዚአብሔርን ወይም የክርስቶስን ስሞች ይደጋግማሉ። ሌሎች ደግሞ «ሃሌሉያ» የሚለውን ቃል ይደጋግማሉ። በኢየሱስ ዘመን ፈሪሳውያን መንፈሳዊነታቸውን በጸሎት ለማሳየት ይፈልጉ ነበር። ስለሆነም በአምልኮ ዕለት ወደ ምኩራብ ገብተው ከፊት በመቀመጥ ረዥም ጸሎቶችን ያቀርባሉ። ያም ባይሆን ሕዝብ ወደሚሰበሰብባቸው አካባቢዎች ሄደው ሁሉም ሰው እስኪሰማቸው ድረስ፥ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ይጸልያሉ። ክርስቶስ፥ «ይኼ ምን እርባና አለው?» ሲል ነቅፏቸዋል። ብድራታቸው የእግዚአብሔር ሳይሆን፥ የሰዎች አድናቆት ነበር። የኢየሱስ ተከታዮች የጸሎት አመለካከት ፍጹም የተለየ ሊሆን ይገባል። ጸሎት ከእግዚአብሔር ጋር የምናደርገው ንግግር ስለሆነ፥ የሰዎች መኖር አለመኖር ሊያሳስበን አይገባም። ክርስቶስ በሕብረት መጸለይ የለብንም አላለም። ክርስቶስም ሆነ ሐዋርያት ብዙ ሕዝብ በተሰበሰበባቸው ስፍራዎች ጸልየዋል። ነገር ግን ክርስቶስ በሕዝብ ፊት በምንጸልይበት ጊዜ አመለካከታችን ትክክለኛ መሆን እንዳለበት አስገንዝቧል። ኢየሱስ ተከታዮቹ በትክክለኛ መንገድ እንዲጸልዩ የተወሰኑ መመሪያዎችን ሰጥቷቸዋል። ሀ. ክርስቶስ ጸሎትን ከተሳሳቱ አነሣሽ ምክንያቶች ለመጠበቅ፥ አብዛኛውን ጸሎታችንን እግዚአብሔር ብቻ በሚሰማባቸው ስውር ስፍራዎች እንድናደርግ አስተምሮናል። እግዚአብሔር ከመናገራችን በፊት ጸሎታችንን ስለሚያውቅ፥ ስለ ጸሎታችን መጮኹ የግድ አስፈላጊ አይደለም። ጮክ ብሎ መጸለዩ ተጨማሪ በረከት አያስገኝም። ጮክ ብለን መጸለያችን እግዚአብሔር በተሻለ ሁኔታ እንዲያደምጠን አያደርገውም። እግዚአብሔር ደንቆሮ ስላልሆነ መጮኽ አያስፈልገንም። ጮክ ብለን የምንጸልይ ከሆነ፥ አነሣሽ ምክንያታችንን መመርመር ይኖርብናል። ክርስቶስ ከእርሱ ጋር ከተነጋገርን፥ ለጸሎታችን መልስ እንደሚሰጠን ተናግሯል። ለ. ጸሎት በቃላት አማካኝነት ከእግዚአብሔር ጋር መነጋገር ነው። ስለሆነም ቀጥተኛ የሆነ አነጋገር ለጸሎት ተስማሚ ነው። ክርስቶስ ቀጥተኛ ከሆነ የጸሎት ቃላት ውጪ ሳይታሰቡ የሚወረወሩ ቃላት ለጸሎት ሊያገለግሉ እንደማይገባ አስጠንቅቋል። ስሙን በመደጋገማችን ወይም «ሃሌሉያ» እያልን በመጮኻችን ብቻ እግዚአብሔር ጸሎታችንን በተሻለ ሁኔታ አያደምጥም። ይህንን የምናደርግ ከሆነ፥ «ለምንድን ነው የማደርገው?» ብለን ራሳችንን መጠየቅ አለብን። ያለልማድ የምንጠቀምባቸው ቃላት ብዙውን ጊዜ ለሌሎች እንደምንጸልይ ወይም ሳናስብ በልማድ እንደምንጸልይ ያሳያሉ። ሐ. ረዥም ጸሎት የግድ አስፈላጊ አይደለም። ክርስቶስ ብዙ ቃላት መደጋገም እንደማያስፈልግ ገልጾታል። ብዙ በጸለይን ቁጥር ትክክለኛ ጸሎት እናደርጋለንን? አናደርግም። ጥርት ባለ ሁኔታ እግዚአብሔርን የሚያመሰግንና ለእግዚአብሔር ለመናገር የምንፈልጋቸውን ነገሮች የሚገልጽልን የሁለት ደቂቃ ጸሎት በቂ ነው። በተለይ በሌሎች ሰዎች ፊት ረጅም ጸሎት የምንጸልይ ከሆነ፥

የአምልኮ መርሖዎች (ማቴ. 6፡1-18) Read More »

ክርስቶስ የመጣው የብሉይ ኪዳንን ሕግ ለመሻር ሳይሆን ለመፈጻም ነው (ማቴ. 5፡16-48)

የውይይት ጥያቄ፡- ማቴ. 5፡16-48ን አንብብና ክርስቶስ ከብሉይ ኪዳን ሕግ ጋር ምን ዓይነት ግንኙነት እንደ ነበረው ግለጽ። የክርስቶስ ቀንደኛ ጠላቶች ፈሪሳውያን ነበሩ flip። እነዚህ ሰዎች ከክርስቶስ ጋር የሚጋጩት እርሱ የብሉይ ኪዳን ሕግን ባለመፈጸሙ ምክንያት ሳይሆን፥ እነርሱ የጨመሯቸውንና ከብሉይ ኪዳን ሕግ እኩል እንደሆኑ የሚያስተምሯቸውን ሕግጋት ለመፈጸም ባለመፈለጉ ነበር። ይህም ክርስቶስ ሕግን አያከብርም የሚል ወሬ እንዲዛመት አደረገ። ማቴዎስ ግን ክርስቶስ የብሉይ ኪዳንን ሕግ እንደማይቃወም አመልክቷል። ክርስቶስ ከእግዚአብሔር ሕግ አንዲት ነቁጥ እንኳ እንደማትወድቅ አስተምሯል። ሰዎች የእርሱ ተከታዮችና የመንግሥቱ አካል ለመሆን ከፈለጉ፥ የእግዚአብሔርን ሕግ በሙሉ መጠበቅ እንዳለባቸውም አስተምሯል። ምሑራን ክርስቶስ «ልፈጽም» ሲል ምን ማለቱ እንደሆነ ይከራከራሉ። ክርስቶስ የብሉይ ኪዳን የሕግ ዓይነቶች በሙሉ በሁሉም ዘመን ለሚኖሩ ክርስቲያኖች አሁንም ይሠራሉ ማለቱ ይሆን? ቤተ ክርስቲያን ዛሬ የሥነ ምግባር ሕግን (ለምሳሌ፥ «አታመንዝር»)፣ ሥርዓታዊ ሕግን (ለምሳሌ፥ ለእግዚአብሔር በመሠዊያ ላይ መሥዋዕቶችን ማቅረብ)፥ እና ማኅበራዊ ሕግን (ለምሳሌ፥ የአንድ ሰው በሬ ወደ ሌላው ግለሰብ እርሻ ዛሬ በሚገባበት ጊዜ ምን እንደሚደረግ) መጠበቅ አለበት? ይህ የዕብራውያን መጽሐፍ ከክርስቶስ መሥዋዕት የተነሣ የብሉይ ኪዳን መሥዋዕቶች እንደተሻሩ ከሚናገረው ወይም የምግብ ሥርዓቶች ከእንግዲህ እንደማይጠቅሙ ከሚያስረዳው ከሐዋርያት ሥራ 10 ጋር እንዴት ይዛመዳል? ስለሆነም ኢየሱስ ሕግን ስለመፈጸሙ ሲናገር ምን ማለቱ እንደሆነ የሚያስረዱ የተለያዩ አሳቦች አሉ። ኢየሱስ የብሉይ ኪዳን ሕግን ሙሉ በሙሉ ፈጽሟል፤ ለሕጉ ታዟል። ብሉይ ኪዳን በሙሉ ወደ ክርስቶስ ያመለክታል። ዘጸአት ክርስቶስ ከባርነት እንደሚያወጣን ያሳያል። መሥዋዕቶችና ሃይማኖታዊ በዓላት ሁሉ ወደ ክርስቶስና አገልግሎቶቹ ያመለክታሉ። ነቢያት ሁሉ በክርስቶስና በተግባሩ ላይ ያተኩራሉ። ስለሆነም የብሉይ ኪዳን የተስፋ ቃሎች በሙሉ በኢየሱስ ተፈጻሚነትን አግኝተዋል። እርሱ እውነተኛ የአምልኮ መንገድ ነው። እርሱ ሰዎች ከእግዚአብሔር ጋርና እርስ በርሳቸው የሚዛመዱበትን መንገድ ያስተምራል። ሰዎች እንዴት በፍቅር አብረው እንደሚኖሩ ያሳያል። ክርስቶስ የኢሳይያስን ትንቢቶች እንደፈጸመ ሁሉ፥ በብሉይ ኪዳንም የእግዚአብሔርን ተምሳሌቶች ሁሉ ፈጽሟል። የብሉይ ኪዳን ሥርዓታዊ ሕግና ማኅበራዊ ሕግ መሢሑ ከመጣ በኋላ አስፈላጊዎች አልነበሩም። በኢየሱስ መምጣት፥ የብሉይ ኪዳን ሕግና የተስፋ ቃሎች፥ እግዚአብሔር ለእነርሱ የነበረው ዓላማ ከፍጻሜ ደረሰ። ኢየሱስ ብሉይ ኪዳን ከእንግዲህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል እንዳልሆነ አልተናገረም። ይህ ከእግዚአብሔር የመነጭ በመሆኑ፥ ሁልጊዜም የመጽሐፍ ቅዱስ አካል ነው። ነገር ግን በክርስቶስ መምጣት ብሉይ ኪዳንን የምንረዳበት መንገድ የተለወጠበት ሁኔታ አለ። አሁን እግዚአብሔር ብሉይ ኪዳንን የሰጠባቸውን ዓላማዎች ከአዲስ ኪዳንና ከክርስቶስ ትምህርቶች እንረዳለን። ከዚያ በኋላ ግን ክርስቶስ የዘላለምን ሕይወት የሚቀበሉት፥ ከፈሪሳውያንና ከሕግ መምህራን የበለጠ ጽድቅ ያላቸው ብቻ እንደሚሆኑ ገልጾታል። ይህ አባባሉ አይሁዶችን አስደነገጠ። የፈሪሳውያንን ያህል መንፈሳዊ የሚመስል ሰው አልነበረም። የሕይወታቸውን ክፍሎች የሚገዙ በሺዎች የሚቆጠሩ ሕግጋትን ይከተሉ ነበር። አይሁዶች «እንዴት ከፈሪሳውያን በላይ መንፈሳዊ መሆን ይቻላል?» ብለው ማሰባቸው አልቀረም። ክርስቶስ ምክንያቱ የፈሪሳውያን በውጫዊ ነገሮች ላይ ማተኮር እንደሆነ ገለጸ። የእግዚአብሔርን ሕግጋት ከመጠበቅ ጀርባ ስለነበሩት መርሖዎች አይጨነቁም ነበር። እግዚአብሔርን የሚያሳስበው ከውጫዊ ሥርዓት ይልቅ የልባችን ነገር ነው። እግዚአብሔር ልባችን ትክክል ከሆነ ትክክለኛ ተግባር እንደምናከናውን ያውቃል። ፈሪሳውያን የተለወጠ ልብና ትክክለኛ ምኞት ስላልነበራቸው በእግዚአብሔር ፊት ከንቱዎች ነበሩ። የውይይት ጥያቄ፡- ብዙውን ጊዜ ክርስቲያኖች ከተግባሩ ባሻገር ያሉትን አነሣሽ ምክንያቶችና አመለካከቶች ሲያጤኑ በውጫዊ ተግባራት ላይ እንዴት እንደሚያተኩሩ አብራራ። ኢየሱስ ሕግን እግዚአብሔር በሚፈልገው መንገድ ከልብ መታዘዝ ከውጫዊ ተግባራት እንዴት እንደሚለይ ለማሳየት ስድስት ምሳሌዎችን ሰጥቷል። እነዚህም እግዚአብሔር ሕግን ስለመጠበቅ ያለው አመለካከት ከፈሪሳውያን የላቀ መሆኑን የሚያሳዩ ናቸው። (ማቴዎስ በዚህ ክፍል ውስጥ ከሚያሳያቸው ነገሮች መካከል አንዱ ኢየሱስ የእግዚአብሔርን ልብ ለመተርጎም እንደሚችል ነው። የእግዚአብሔር ልጅ እንደመሆኑ መጠን፥ ክርስቶስ የተጻፉትን የብሉይ ኪዳን ሕግጋት ብቻ ሳይሆን ከ1400 ዓመታት በፊት የሙሴን ሕግ ሲሰጥ ከሕዝቡ ምን እንደፈለገም ያውቅ ነበር። ክርስቶስ «ሙሴ ተብሏል እኔ ግን እላለሁ» ሲል ሕግን ከሰጠው እግዚአብሔር ጋር ራሱን እኩል እያደረገ ነበር።) ሀ. ስለ መግደል የተነገረ ምሳሌ (ማቴ. 5፡21-26)። ብሉይ ኪዳን ሰው መግደል የተከለከለ መሆኑን በግልጽ አስተምሯል። ፈሪሳዊ ሰው ገድሎ ስለማያውቅ፥ ከእግዚአብሔር ጋር ትክክለኛ ግንኙነት እንዳለው ያስብ ነበር። ይህ ሕግ ትዕቢቱንና ቁጣውን እንዲያስወግድ፣ ወይም የተበላሸውን ግንኙነት እንዲያስተካክል አላስገደደውም ነበር። ክርስቶስ ግን የግድያ ሁሉ ሥር በሆነው ጥላቻ ላይ አተኮረ። በእግዚአብሔር ዐይን፥ አንድን ሰው መጥላት ኃጢአት ነው። የቁጣ ውጤት በመጀመሪያ ደረጃ የግድያን ያህል አስከፊ ላይሆን ቢችልም፥ የግድያ ሁሉ ሥር ቁጣ ነው። ስለሆነም ከሕይወታችን ውስጥ ቁጣን እስካላስወገድን ድረስ እግዚአብሔር የሚፈልገውን የፍቅር ግንኙነት፥ ከሌሎች ጋር የማድረግ ሕይወት ልንመራ አንችልም። («ደንቆሮ» የሚለው አንድ ሰው በሌላው ላይ የሚሰነዝረው የንቀት ስድብ ነው። የአይሁድ ሸንጎ የግድያ ጉዳዮችን የሚመረምር የአይሁዶች የሕግ ምክር ቤት ነበራቸው።) ትዕቢተኛ፥ ሌሎችን የሚንቅ፥ በጥላቻና በክፋት የተሞላ ልብ ለእግዚአብሔር የነፍሰ ገዳይን ያህል የከፋ ነው። ሁለቱም ግለሰቡ ከእግዚአብሔር ጋር ግንኙነት እንደማያደርግና የተለወጠ ሕይወት እንደሌለው ያሳያሉ። ክርስቶስ የሕግ ዋንኛ መልእክት ከሌሎች ጋር መልካም ግንኙነት ማድረግ መሆኑን ለማሳየት ሁለት ምሳሌዎችን ተጠቅሟል። የመጀመሪያው ምሳሌ በመሠዊያው ላይ እንስሳትን በመሠዋት እግዚአብሔርን የሚያመልከውን ሰው ይመለከታል። እየሰገደ ሳለ አንድ የተጣላው ሰው እንዳለ ትዝ አለው። ምንም እንኳ ሰጋጁ ከራሱ ልብ ጉዳዩን ያወጣው ቢሆንም፥ ግለሰቡ ግን አሁንም እንደተናደደ ያውቅ ነበር። በሰዎች መካከል ጥል እያለ እግዚአብሔርን ማምለክ አይቻልም። ስለሆነም ኢየሱስ፥ መሥዋዕትን የሚሠዋው አማኝ፥ አስቀድሞ የተቀየመውን ግለሰብ መታረቅ እንዳለበት ገልጾታል። ከዚያ በኋላ ተመልሶ መሥዋዕት በማቅረብ እግዚአብሔርን ሊያመልክ እንደሚቻል አስረድቷል። ዛሬ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ብዙ መከፋፈል ይታያል። ብዙ ጊዜ እግዚአብሔር እንደሚደሰትብን እያሰብን በመዘመር፥ ስብከቶችን በመስማት፥ በመጸለይና በመጾም እናመልከዋለን። ክርስቶስ ግን ግንኙነቶች ከተበላሹ ማንም ይበድል ማን ሁለቱም ወገኖች ግንኙነቱን ለማስተካከል መጣር እንዳለባቸው ገልጾታል። እግዚአብሔር በአምልኳችን ደስ የሚሰኘው በዚህ ጊዜ ብቻ ነው። የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በብዙ የተበላሹ ግንኙነቶች ውስጥ እግዚአብሔርን ለማምለክ ብንሞክር፥ ዛሬ ለእኛ የሚሰጠው ማስጠንቀቂያ ምንድን ነው? ለ) የተቀያየምኸው ሰው አለ? እግዚአብሔር ብርታትና ምሪት እንዲሰጥህ ጠይቅና ግንኙነቱን ለማስተካከል ትችል ዘንድ ወደ ግለሰቡ ሄደህ ተነጋገር። በክርስቶስ ዘመን ሰዎች ገንዘብ የመበደር ልማድ ነበራቸው። የተበደሩትን ገንዘብ ለመክፈል ካልቻሉ፥ እነርሱ ወይም ቤተሰቦቻቸው ለባርነት ይሸጡ ነበር። ወይም ደግሞ ገንዘቡን እስኪከፍሉ ድረስ ወኅኒ ቤት ይወርዳሉ። ክርስቶስ ጉዳዩ ወደ ፍርድ ችሎት ከመድረሱ በፊት ተበዳሪው ከአበዳሪው ጋር ሆኖ መፍትሔ መፈለግ እንዳለበት ተናግሯል። ክርስቶስ ይህንን በመጠቀም አለመስማማትና ክርክሮችን እንዴት ማስተናገድ እንደሚገባ አስተምሯል። በክርክር ውስጥ አቋምህን በልበ ደንዳናነት ይዘህ በቀጠልህ ቁጥር፥ ክርክሩ እየከፋ ሄዶ በአንተና በተሟጋችህ ላይ ጉዳት ማድረሱ የማይቀር ነው። ስለሆነም ቁጣና ትዕቢት የፍትሕን በር ከመዝጋታቸው በፊት፥ ችግሩን ለመፍታት መሞከሩ መልካም ነው (ምሳሌ 25፡8-10ን አንብብ።) አለመስማማትን በጊዜ ውስጥ ለመፍታት መሞከራችን ክብደቱን ከማቃለሉም በላይ በእኛና በቤተሰባችን፥ በቤተ ክርስቲያናችንና ከሁሉም በላይ በጌታ ስም ላይ የሚያስከትለውን ጉዳት በእጅጉ ይቀንሳል። ለ. ስለ ዝሙት የተነገረ ምሳሌ (ማቴ. 5፡27-30)። የሙሴ ሕግ ሰዎች ዝሙትን መፈጸም እንደሌለባቸው በግልጽ አመልክቷል። ያገባ ሰው ከሚስቱ ውጭ ወሲባዊ ግንኙነት እንዳያደርግ ተከልክሏል። ያላገባ ሰው ደግሞ ከማግባቱ በፊት ምንም ዓይነት ወሲባዊ ግንኙነት ማድረግ አይችልም ነበር። አሁንም ለክርስቲያኖች «ዝሙት አልፈጸምሁም» ብሎ መኩራራቱ ቀላል ነው። ነገር ግን ክርስቶስ ዋናው ጉዳይ ውጫዊው የወሲብ ተግባር እንዳልሆነ ገልጾታል። ዋናው ጉዳይ ከልብ ጋር ሲሆን፥ አንድ ሰው በተግባር ዝሙት ባይፈጽምም ይህንኑ ለማድረግ ሊመኝ ይችላል። የዝሙት ሥር ምኞት ስለሆነ፥ እግዚአብሔርንና ሌላውን ሰው የሚያስከብር ውስጣዊ ሕይወት ለመምራት ከምኞት መራቅ እንዳለበት ኢየሱስ አስተምሯል። ብዙ ጊዜ ኃጢአትን ቀላል አድርገን እንመለከታለን። ኃጢአት ከፈጸምን በኋላ ይቅርታ ለመጠየቅ እንደምንችል እናስባለን። «ሌላውን ሰው እስካልጎዳሁ ድረስ ምን ችግር አለው?» ብለን ራሳችንን እንጠይቃለን። ክርስቶስ የሰዎችን ትኩረት ለመሳብና እግዚአብሔር ኃጢአትን እንዴት አጥብቆ እንደሚጠላ ለማሳየት ፈለገ። ሰዎችን ለማስደንገጥ የሚያስችል የንግግር ዓይነት በመጠቀም፥ ክርስቶስ ወደ አንድ ኃጢአት የሚመራ ዝንባሌ ያለው

ክርስቶስ የመጣው የብሉይ ኪዳንን ሕግ ለመሻር ሳይሆን ለመፈጻም ነው (ማቴ. 5፡16-48) Read More »

የክርስቶስ ተከታዮች ለዓለም ብርሃንና ጨው መሆን አለባቸው (ማቴ. 5፡13-16)

ብዙ ክርስቲያኖች፥ «ዓለም ለእኛ በጣም መጥፎ ስለሆነች የመንግሥት ሥራ ትተን ወደ ክርስቲያናዊ ድርጅቶች ብንሄድ ይሻላል። ወይም ከማኅበረሰባችን ወጥተን ከሚመስሉን ሰዎች ጋር የምንሠራበትንና የምንኖርበትን ክርስቲያናዊ ማኅበረሰብ እንመሥርት» ይላሉ። ነገር ግን ይህ ክርስቶስ ያስተማረው የደቀ መዝሙርነት ዐይነት ነው ወይ? ከማኅበረሰቡ ወጥተው የራሳቸውን የቅዱሳን ማኅበረሰብ ከመሠረቱት ኢሴናውያን በተቃራኒ፥ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱ በዓለም ውስጥ እንደ ጨውና ብርሃን እንዲያገለግሉ የሚፈልግ መሆኑን ገልጾአል። ኢየሱስ በዓለም ውስጥ ደቀ መዛሙርቱ ያደረጉትን አስተዋጽኦ ከሦስት ነገሮች ጋር በማነጻጸር አብራርቷል። በመጀመሪያ፥ ከጨው ጋር አነጻጽሯቸዋል። በጥንት ዘመን ጨው በጣም ጠቃሚ ነገር ነበር። እንደ ጥንታዊት ኢትዮጵያ በመሳሰሉት አገሮች፥ የመገበያያ ገንዘብ ሆኖ አገልግሏል። ጨው ለሁለት ነገሮች ያገለግል ነበር። ሀ ለጣዕም፥ ወጥ እንዲጣፍጥ፥ በገጠር በቡና ጭምር ጨው እንደሚጨመር ሁሉ፥ በክርስቶስ ዘመን ጨው ለጣዕም መስጫ ያገለግል ነበር። 2) ለማቆያ። ሥጋ እንዳይበላሽ በጨው ቀምመው ቋንጣ ያደረጉት ነበር። በተመሳሳይ ሁኔታ በቁጥር ቢያንሱም እንኳ እግዚአብሔር በሚፈልገው መንገድ ቢኖሩ ክርስቲያኖች በማኅበረሰቡ ውስጥ እነዚህን ሁለት ተግባራት መፈጸም ይችላሉ። መንፈሳዊ ምሳሌነት ያለው ሕይወት በመምራት በክፋት ለተሞላው ማኅበረሰብ መልካም መዓዛ ይጨምራሉ። በተጨማሪም እግዚኣብሔር ክፋት እንዳይጨምርና ማኅበረሰቡ የበለጠ ክፉ እንዳይሆን ለመከላከል፥ በውስጡ ያሉትን ክርስቲያኖች ይጠቀማል። እስራኤላውያን ጨው የሚያገኙት ከኢየሩሳሌም በስተ ደቡብ ምሥራቅ ከሚገኘው ሙት ባሕር ነበር። ከመሬትም ቆፍረው ያወጡታል። ነገር ግን ይህ ንጹሕ ጨው ስላልሆነ፥ በፍጥነት ካልተጠቀሙበት ጨውነቱን እያጣ ይሄድ ነበር። ከዚያ በኋላ ሊያገለግል የሚችለው ወደ መሬት በመጣል፥ ወይም ጣሪያቸው እንዳያፈስ ከዚያው ላይ በማስቀመጥ ብቻ ይሆናል። ዛሬም እንኳ ብዙ የአይሁድ ቤቶች ውኃ የሚያስገቡ ጣሪያዎች አሏቸው። ዛሬም ድረስ ያረጀና የማይጠቅም ጨው በጣሪያቸው ላይ በማድረግ ዝናብ ይከላከላሉ።) በተመሳሳይ ሁኔታ የአንድ ክርስቲያን ባሕርይ የዓለምን ሲመስል፥ ለማኅበረሰቡ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ሊኖር አይችልም። ሁለተኛው ማብራሪያ ብርሃን ነበር። በጥንት ዘመን ኤሌክትሪክ ስላልነበረ፥ ሰዎች በወይራ ዘይት የተሞሉ ኩራዞችን ይጠቀሙ ነበር። ብርሃን አስደናቂ ነገር ነው። ትንሽ ብርሃን ብዙ ጨለማ ትገፋለች። የክርስቶስ ተከታዮች በቁጥር ቢያንሱም እንኳ፥ የክርስቶስን ባሕርያት በዓለም ውስጥ ማብራት አለባቸው። የሰዎችን ክፋት አብርተን በማሳየት፥ ሕይወታቸውንና ማኅበረሰባቸውን በሚለውጥ መንገድ እንዴት ሊኖሩ እንደሚችሉ እናሳያቸዋለን፡ ነገር ግን ሕይወታችን ዓለምን በመምሰል በኃጢአት ከጨለመ፥ ይህ በማሰሮ ውስጥ እንዳለ መብራት ይሆናል። ወይም ደግሞ ስደትን ፈርተን ብርሃናችንን ብንደብቅ፥ እግዚአብሔር ጽድቁን ለማብራት እኛን የተጠቀመበት ዓላማ ከግቡ ሳይደርስ ይቀራል፡፡ ሦስተኛው ምሳሌ በተራራ ላይ ያለች ከተማ ናት። እንደተለኮሰ መብራት፥ በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትሰወር አትችልም። በተመሳሳይ ሁኔታ እነዚህን ክርስቶስ የጠቀሳቸውን ባሕርያት የያዙ ክርስቲያኖች ለሁሉም በግልጽ የሚለዩ ይሆናሉ። ምስክርነታችን የሚመጣው ከአፋችን ሳይሆን ከተግባራችን ነው። የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ለእግዚአብሔር የሚኖሩ ጥቂት ክርስቲያኖች እንደ ብርሃንና ጨው ኅብረተሰቡን ሲለውጡ ያየህበትን ሁኔታ ግለጽ። ለ) እንደ ዓለማውያን በመኖራቸው ምክንያት የብርሃንነትና የጨውነት አገልግሎታቸው የጠፋበትን ሁኔታ ግለጽ። ሐ) ሕይወትህ እንደ ብርሃንና ጨው የሆነው እንዴት ነው? ብርሃንህና ጨውህ የበለጠ እያደገ በማኅበረሰቡ ላይ የበለጠ ለውጥ ለማስከተል ትችል ዘንድ ምን ታደርጋለህ? (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ ስለዚህ አስደናቂ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡)

የክርስቶስ ተከታዮች ለዓለም ብርሃንና ጨው መሆን አለባቸው (ማቴ. 5፡13-16) Read More »

የተራራው ስብከት [እግዚአብሔር የባረከው ሰው ባሕርይ] (ማቴ. 5፡1-12)

የውይይት ጥያቄ፡- አራት ዓምዶች ያሉት ሠንጠረዥ በወረቀት ላይ ሣል። የመጀመሪያውን ዓምድ «ባሕርይ»፥ ሁለተኛውን «ያ ባሕርይ ምን ማለት እንደሆነ»፤ ሦስተኛውን ዓምድ «ክርስቶስ ተስፋ የሰጠው በረከት»፥ እንዲሁም አራተኛውን ዓምድ «ዓለም ሰዎች እንዴት እንዲኖሩ እንደምትፈልግ» በሚሉ ርእሶች ለይ። በማቴ. 5፡3-12 የሚገኙትን የብፅዕና ዓይነቶች በሠንጠረዥ ውስጥ ሙላ። ይህ የመጀመሪያው ክፍል በክርስቶስ ተከታዮች ባሕርይ ላይ ያተኩራል። እኛ ብዙውን ጊዜ ክርስቲያን ሊያደርገው ይገባል ወይም አይገባም በምንለው ውጫዊ ተግባር ላይ ስናተኩር፥ ክርስቶስ ግን የተገቢው ተግባር መሠረቱ፥ ባሕርይ መሆኑን ያመለክታል። ክርስቶስ የባሕርያችን መለወጥ የተግባራችንን መለወጥ እንደሚያስከትል ያውቃል። ከእነዚህ ባሕርያት ውስጥ አንዱን መርጠን ሌሎችን መተው አንችልም። እነዚህ ሁሉ የክርስቶስ ተከታዮችን መለያ ባሕርያት ለመመሥረት በአንድነት የሚታዩ ናቸው። አንድ ሰው እንደተናገረው፥ እነዚህ ባሕርያት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ወደር የሌላቸው የክርስቶስ መገለጫዎች ናቸው። እነዚህ ባሕርያት ዓለም አስፈላጊዎች ናቸው ብላ ከምታስተምረው ትምህርት ጋር የሚቃረኑ ናቸው። ሀ. በመንፈስ ድሆች የሆኑ ብፁዓን ናቸው፥ መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና። ለአይሁዶች «ብፁዕ» የሚለው ቃል ደስተኛ ከመሆን የላቀ ፍች ነበረው። ይህ ቃል በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት ማግኘትንና የበረከቱ ተቋዳሽ መሆንን ያሳያል። የመጀመሪያው በረከት የተሰጠው፥ በመንፈስ ድሆች ለሆኑት ሰዎች ነው። እዚህ ላይ ክርስቶስ የሚናገረው ስለ ሥጋዊ ድህነት ሳይሆን፥ ስለ መንፈሳዊ ድህነት ነው። ሥጋዊ ድህነት ያጠቃቸው ሰዎች ሙሉ በሙሉ በሰዎች ላይ ጥገኞች ሆነው የሚኖሩ ናቸው። የራሳቸው ሀብት ስለሌላቸው ለኑሮአቸው የሚደገፉት በሰዎችና በእግዚአብሔር ላይ ነው። በመንፈስ ድሀ መሆን ማለት፥ እግዚአብሔርን የሚያስደስትና ለእግዚአብሔር ለመኖር የሚያስችል መንፈሳዊ ሀብት እንደሌለን መገንዘብ ነው። ስለሆነም እርሱ ይረዳን ዘንድ ወደ እግዚአብሔር እንመለከታለን። በመንፈስ ድሆች የሆኑ ሰዎች ሊያደርጉት የሚችሉት ነገር ቢኖር፥ ወደ እግዚአብሔር ጸጋና ምሕረት ፊታቸውን መመለስ እንደሆነ ያውቃሉ። ወደ እርሱ ስለሚመለከቱ እግዚአብሔር ምሕረትን፥ ጸጋንና መዳንን ይሰጣቸዋል። በመንፈስ ድሆች የሆኑ ሰዎች በራሳቸው ችሎታ ሳይመኩ ማንኛውም መፍትሔ ከእግዚአብሔር እንደሚመጣ ያምናሉ። ዓለም የምታስተምረው የዚህን እውነታ ተቃራኒ ነው። የኋላ ኋላ ዓለም በሌሎች ላይ በሚደገፍ ሰው ትቀልድበታለች። ዓለም በማንነታችንና በተግባራችን እንድንኮራ ታስተምረናለች። ስለዚህ በሃይማኖታዊ ውርሳችንና በመንፈሳዊነታችን እንኩራራለን። እንዲሁም ተነሣሽነት ያላቸውን፥ ብልሆችን፥ ሀብታሞችንና ኃይለኞችን እናደንቃለን። በራሳቸው ብርታት ሊሠሩ የሚችሉ ሰዎች የሥልጣን ስፍራ ይሰጣቸዋል። የሃይማኖት ሰዎች ሳይቀሩ መንፈሳውያን ለመሆንና ደኅንነትን ለማግኘት በመቻላቸው ይኩራራሉ። ነገር ግን እነዚህ ሁሉ በመንፈሳዊ ባለጸግነታቸው በመመካታቸው ክርስቶስ ሊሰጣቸው የሚፈልገውን በረከት ያጣሉ። በመንፈስ የሚታበዩ ሰዎች የክርስቶስ መንግሥት አካል አለመሆናቸውን ያሳያሉ። በመንፈስ ድሆች የሆኑ መንግሥተ ሰማይን ከእግዚአብሔር ዘንድ በስጦታ ይቀበላሉ። ክርስቶስ እንደ አማኑኤል ከእነርሱ ጋር ይኖራል። እርሱ በሕይወታቸው ላይ ይነግሣል። ስለሆነም በመንፈስ ድሆች የሆኑ ሰዎች በምድር ላይ የእርሱ መንግሥት አካል ሲሆኑ፥ መንፈሳዊ በረከቶቹን ይቀበላሉ። ከዚህም በላይ የክርስቶስ ዘላለማዊ መንግሥት አካል ለመሆናቸው እርግጠኞች ናቸው። የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) አንድ ክርስቲያን በመንፈስ ድሀ ከመሆን ይልቅ፥ በመንፈስ ሀብታም ሊሆን የሚችልባቸውን መንገዶች ዘርዝር። ለ) በመንፈስ ድሀ የሆነው ክርስቲያን፥ በመንፈስ ትዕቢተኛ ከሆነው ክርስቲያን በአኗኗሩ እንዴት እንደሚለይ ግለጽ። ለ. የሚያዝኑ ብፁዓን ናቸው፥ መጽናናትን ያገኛሉና። ክርስቶስ በምን ምክንያት እንደሚያለቅሱ አልገለጸም። ዐውደ ምንባቡ ግን መንፈሳዊ ባሕርይ ያለው ነው። በኃጢአተኛነታቸውና በልባቸው ድንዳኔ የሚያዝኑ፥ እንዲሁም በቤተ ክርስቲያንና በአገራቸው ኃጢአት ምክንያት የሚያለቅሱ ወገኖች ይጽናናሉ [መዝ. (119)፡136 አንብብ]። የሚያለቅሱት የራስ ወዳድነት ፍላጎቶቻቸው ስላልተሟሉላቸው ሳይሆን፥ ዓለምና ሰዎች እግዚአብሔር በሚፈልገው መንገድ ባለመጓዛቸው ምክንያት ነው። ይህም ዓለም ከምታስተምረው አሳብ ተቃራኒ ነው። ዓለም በሕይወታችን እንድንደሰት ታስተምረናለች። ስለዚህም «ሰው እስከሆንህ ድረስ ለኃጢአት መጨነቅ የለብህም፥ የቤተ ክርስቲያንም ሆነ የአገር ኃጢአት ሊያስጨንቅህ አይገባም ልትለውጠው አትችልምና» ትለናለች። ክርስቶስ ስለ ኃጢአት የሚያለቅሱ ሰዎች እንደሚጽናኑ ተናግሯል። እነርሱም እግዚአብሔር የሚሰጣቸውን ይቅርታ ስለሚያውቁ ይጽናናሉ። እግዚአብሔር በእነርሱና በጸሎታቸው አማካይነት የራሳቸውንና የሌሎችንም ሕይወት እንደሚለውጥ ስለሚያውቁ ይጽናናሉ። በኀዘናቸው ጊዜ ራሱ ክርስቶስ አብሯቸው እንደሚሆን ስለሚያውቁ፥ ይጽናናሉ። አንድ ቀን ኀዘንም ሆነ ለቅሶ የሌለበት መንግሥት ቤተሰቦች ስለሚሆኑ ይጽናናሉ (ራእይ 7፡17፤ 21፡4)። የውይይት ጥያቄ፡- ለመጨረሻ ጊዜ በሕይወትህ ውስጥ ወይም በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ ስለተከሰተው ኃጢአት ያለቀስኸው መቼ ነበር? አልቅሰህ ከሆንህ ይህ ስለ ልብህ ሁኔታ ምንን ያሳያል? ሐ. የዋሆች ብፁዓን ናቸው፥ ምድርን ይወርሳሉና። የዋህ የሚለውን ቃል ለመተርጎም አስቸጋሪ ነው። ብዙውን ጊዜ የዋህነት ሰዎች ያሻቸውን ነገር ሲያደርጉ መልስ አለመስጠት ወይም ሞኝነት እንደሆነ እናስባለን። ይህ ግን ክርስቶስ ያስተማረው የዋህነት አይደለም። ክርስቶስ የዋህ የነበረ ቢሆንም፥ ይፋዊ ተቃውሞ ሳያሳይ ኢ-ፍትሐዊ የሆነ ነገር እንዳይደረግ ተከላክሏል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የዋህነት የተለያዩ ጽንሰ አሳቦች አሉት። በሕይወታችን ውስጥ ችግሮች በሚከሰቱበት ጊዜ ቁጡና መራር ሳይሆኑ፥ በትዕግሥት መገዛት የዋህነት ነው። ወይም የዋህነት ነገሮችን በራሳችን መንገድ ከማከናወንና የምንፈልገውን የማያደርጉትን ከመቃወም ይልቅ፥ በገር መንፈስ መመላለስ ሊሆን ይችላል። የዋህ ሰው እግዚአብሔር ሁሉንም ነገር እንደሚሠራና የኋላ ኋላም ለጥቅማችን እንደሚያውለው ይገነዘባል። ስለሆነም እግዚአብሔር በሁኔታዎች ሁሉ ውስጥ ፍጹም ፈቃዱን ተግባራዊ እንደሚያደርግ ይተማመናል። የዋህነት በራስ ጥረት ሳይመኩ ሕይወትን ከእግዚአብሔር እጅ እንደተቀበሉ አድርጎ ማስተናገድ ነው። የዋህነት ራሳችንን ወይም አሳባችንን ለመከላከል አለመሞከርና ስሕተታችንን መቀበል ነው። ከዚህ በተቃራኒው ዓለም ዐመፅን፥ ተቃውሞንና የግል ፍላጎትን ታከብራለች። አንድን ነገር ከፈለግህ ተጠቀምበት። አንድ ሰው ካበሳጨህ እርሱን የሚያበግን አንድ እርምጃ ውሰድ። በሕይወት ቀዳሚ ሆነህ ለመገኘት፥ ከሌሎች ተማሪዎች የተሻለ ውጤት ለማግኘት፥ የተሻለ ሥራ ለመያዝ፥ የቤተ ክርስቲያን መሪ ለመሆን፥ ጠልፈህ መጣል፥ ካስፈለገም ሰዎችን መገፍተርና ማጭበርበር ይኖርብሃል ትላለች። የዓለም ሥርዐት በሰዎች ላይ ኃይልን እንድንቀዳጅ ያበረታታል። በዚህ ሁኔታ ዓለም ሰዎች በማታለልና በማጭበርበር የቀዳሚነትን ስፍራ እንደሚይዙ ስታስተምር፥ ክርስቶስ ግን የዋሆች ምድርን እንደሚወርሱ አስተምሯል [መዝ. (37)፡9-11 አንብብ።] ይህ እንዴት ይሆናል? በመጀመሪያ፥ ብዙ ጊዜ እግዚአብሔር ዓለም ከምትጠብቀው ተገላቢጦሽ የሆነውን ይሠራል። የቀዳሚነትን ስፍራ ለመያዝ የሚፍጨረጨሩ ሰዎች ምንም እንኳ ለጊዜው መጠቀም ቢችሉም፥ የኋላ ኋላ ፍሬያማ አይሆኑም። እግዚአብሔር በራሱ ጊዜና በራሱ መንገድ እንደሚባርካቸው የሚተማመኑ ግን፥ ባልተጠበቀ መንገድ የእግዚአብሔርን በረከት ይቀበላሉ። ይህም ሆኖ በረከቶቹ ይገቡናል፥ በበጎ ሥራችን አገኘናቸው የሚል ስሜት የላቸውም። ማቴዎስ ያተኮረው ግን በወደፊቱ ጉዳይ ላይ ነው። ክርስቲያኖች ምድራዊ በረከት ልንቀበል ወይም ላንቀበል ብንችልም፥ ከክርስቶስ ጋር እንደምንነግሥ ግን ጥርጥር የለውም። ይህ አጭር ምድራዊ ቆይታ፥ በዘላለማዊ መንግሥት የሚተካ ሲሆን፥ ምድራዊ የዋህነታችን መንፈሳዊ በረከትን ያስገኝልናል (ሉቃስ 22፡29-30፤ ራእይ 20፡4)። የውይይት ጥያቄ፡- በቤተ ክርስቲያንህ የየዋህነት ጉድለት ችግር ያስከተለበትን አጋጣሚ ግለጽ። መ. ጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙ ብፁዓን ናቸው፥ ይጠግባሉና። በዓለም ውስጥ ከሚገኙ እጅግ ጠንካራ ስሜቶች ሁለቱ ረሃብና ጥማት ናቸው። ምግብና ውኃ ሳናገኝ ብንቀር፥ አሳባችን ሁሉ እነዚህን ሁለት ነገሮች በማግኘቱ ላይ ያተኩራል። ያለእነዚህ ነገሮች ለመኖር አንችልም። ብዙውን ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ ጥልቅ መንፈሳዊ ፍላጎትን ከረሃብና ከጥማት ጋር ያነጻጽራል [መዝ. (42)፡1-2 አንብብ።] ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን በጊዜያዊ ነገሮች ከመወሰድ ይልቅ፥ ጽድቅን ሊራቡ እንደሚገባ አስተምሯቸዋል። ጽድቅ ከእግዚአብሔር ጋር ትክክለኛ ግንኙነት ማድረግ ወይም ሙሉ በሙሉ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ መመላለስ ነው። በአሉታዊ ጎኑ፥ ከኃጢአትና እግዚአብሔርን ከማያስደስቱ ነገሮች መራቅ ነው። በአዎንታዊ ጎኑ፥ እግዚአብሔርን የሚያስደስቱትን ነገሮች ማድረግ ነው። እግዚአብሔርን በበለጠ ለማወቅና እርሱን ለማስከበር መፈለግ ነው። በተጨማሪም በቤተ ክርስቲያንም ሆነ በዓለም ሰዎች ትክክለኛና የእግዚአብሔር ፈቃድ ያለበትን ሕይወት ሲመሩ ለማየት መፈለግ ነው። ዓለም ግን የምትራበው ሌሎች ነገሮችን ነው። ትምህርትን፥ ገንዘብን፥ ኃይልና ሥልጣንን፥ ሌሎችንም ነገሮች ትራባለች። ዓለማውያን እግዚአብሔርን በሚያስደስት መንገድ የሚኖር ሰው ሞኝ እንደሆነ ያስባሉ። ኢየሱስ ጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙ እንደሚጠግቡ ተናግሯል። ከእግዚአብሔር ጋር ያላቸው ግንኙነት እያደገ ሲሄድ ይመለከታሉ። ጽድቅን የሚሹ ሰዎች ባሕርያቸው ተለውጦ፥ ከእግዚአብሔር ፈቃድ ጋር ሲስማማ ያያሉ። በእነርሱ አማካይነት በቤተ ክርስቲያናቸውና በማኅበረሰቡም መካከል ለውጦች ይከሰታሉ። ከሁሉም በላይ ጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙ ሰዎች፥ ጽድቅ የሚገዛበት ዘላለማዊ መንግሥት ዜጎች በመሆናቸው ይጠግባሉ። 9ኛ ጥያቄ፡- ሕይወትህን መርምር። የምትራበውና የምትጠማው ለምንድን ነው? ጽድቅን የምትራብና የምትጠማ

የተራራው ስብከት [እግዚአብሔር የባረከው ሰው ባሕርይ] (ማቴ. 5፡1-12) Read More »

ክርስቶስ ለተከታዮቹ ያቀረበው ግብረገባዊ ትምህርት ማጠቃለያ (ማቴ. 5-7)

ክርስቶስ በማቴ. 5-7 ላይ ያስተማራቸው ትምህርቶች፥ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኙ ዐበይት እውነቶች መካከል የሚመደቡ ናቸው። የውይይት ጥያቄ፡- ማቴ. 5፡1-2ን አንብብ። ሀ) ክርስቶስን ስለ መከተል የምንማራቸው ዐበይት ትምህርቶች ምንድን ናቸው? ለ) ከእነዚህ ባሕርያት መካከል ብዙውን ጊዜ ሰዎችን የሚታገሏቸው የትኞቹ ናቸው? አንዳንድ ምሳሌዎችን ጥቀስ። ተመስገን በወንጌላዊነት የሚያገለግል ወንድም ሲሆን፥ ለሌላ ጎሳ ስለ ክርስቶስ እንዲመሰክር ቤተ ክርስቲያኑ ላከችው። እርሱ የተላከባቸው ሰዎች አርብቶ አደሮች ነበሩ። ምንም እንኳ ተመስገን ለእነዚህ ሰዎች ስለ ክርስቶስ ቢመሰክርም፥ የወንጌል ትምህርቱን ያቀረበበት መንገድ ከእነርሱ አኗኗርና ባሕል የተለየ ነበር። በክርስቶስ በሚያምኑበት ጊዜ ሰውነታቸውን እንዲታጠቡ፥ ልብስ እንዲለብሱ፥ መጠጥ እንዲያቆሙ፥ ሁለተኛ ሚስቶቻቸውን እንዲፈቱ አሳሰባቸው። ጌታሁን ለቤተ ክርስቲያን ቅድስና የሚያስብ መጋቢ ነበር። ስለሆነም በሚሰብክበት ጊዜ ሰዎች ከመጠጥ፥ ከዝሙትና ከጫት እንዲታቀቡ አስጠነቀቀ። የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) አንድ ሰባኪ ወይም ወንጌላዊ፥ ሰዎች ሊያደርጓቸው የሚገባቸውን ወይም የማይገባቸውን ነገሮች በመዘርዘር ወንጌልን ሲሰብክ የሰማኸው መቼ ነው? ለ) ከማቴ. 5፡1-12 ክርስቶስ ስለ መንግሥት ያቀረበው ስብከት፥ ብዙውን ጊዜ እኛ ወንጌሉን ከምንገልጽበትና ክርስቶስን ስለ መከተል ከምናስተምርበት መንገድ የሚለየው እንዴት ነው? ሐ) ሰዎች መንፈሳዊነትን እንዲማሩ ከመምከር ይልቅ፥ ውጫዊ ተግባራት ላይ በማተኮር ይህን አድርጉ፥ ያን አታድርጉ የሚሉ ዝርዝሮችን ሰጥቶ፥ አፈጻጸማቸውን መለካት የሚቀልለው እንዴት ነው? ማቴዎስ 5-7 ድረስ የተጻፈው ትምህርት ከየትኞቹም ወንጌላት በላይ ሰፋ ብሎ የቀረበ ሲሆን፥ ክርስቶስ ምን ትምህርት እንዳስተማረ ያብራራል። ምሑራን ይህ ትምህርት በአንድ ስብከት ስለ መጠናቀቁ ይከራከራሉ። ምናልባትም ክርስቶስ ይህን ትምህርት በሁለትና ሦስት ቀናት ውስጥ ለሕዝቡ ያስተማረው ትምህርት አጠቃላይ አሳብ ሊሆን ይችላል። ክርስቶስ ከስፍራ ወደ ስፍራ እየተዘዋወረ ስለሚያስተምር፥ ከእነዚህ እውነቶች ብዙዎቹ በሌሎችም ስፍራዎች ላይደገሙ አልቀሩም። አንዳንድ ምሑራን ማቴዎስ መጽሐፉን በሚጽፍበት ወቅት፥ ክርስቶስ፥ ደቀ መዛሙርቱ ሊኖሩት የሚገባቸውን ሕይወት በአንድ ላይ እንዳሰባሰበ ይናገራሉ። ስለሆነም ምንም እንኳ ማቴዎስ ኢየሱስ ለረዥም ጊዜ በተራራ ላይ ሆኖ ማስተማሩን ቢገልጽም፥ ክርስቶስ በሦስት ዓመት ይፋዊ አገልግሎቱ ጊዜያት ያስተማራቸውን ሌሎች እውነቶችም ጨምሯል። ኢየሱስ በገሊላ በአገለገለባቸው ጊዜያት ለደቀ መዛሙርቱ፥ የእርሱ ተከታይ መሆን፥ ፈሪሳውያን ብቁ አይሁዳዊ ስለ መሆን ከሚያስተምሩት ትምህርት የተለየ መሆኑን አሳይቷል። ምንም እንኳ ብዙ ሰዎች ትምህርቱን ቢከታተሉም፥ ማቴዎስ እንደሚነግረን፥ ክርስቶስ በተለይ ትምህርቱን ያተኮረው በደቀ መዛሙርቱ ላይ ነበር። ከማቴዎስ 5-7 ድረስ የተጠቀሱትን እውነቶች ክርስቶስ በደቀ መዛሙርቱ ሕይወት ውስጥ ሲተገበሩ ለመመልከት ፍላጎት ነበረው። በየዘመኑ ውስጥ የኖሩ ክርስቲያኖች እነዚህን እውነቶች ተግባራዊ ለማድረግ ታግለዋል። ይሁን እንጂ ሙሉ በሙሉ መፈጸም አልተቻላቸውም። አንዳንድ ክርስቲያኖች የእነዚህ ምዕራፎች ትምህርት በተራ ክርስቲያኖች የማይሞከሩ ስለሆነ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ብቻ ሊፈጽሟቸው የሚገቡ እንደሆነ አስተምረዋል። ሌሎች ደግሞ ክርስቶስ እነዚህን ትምህርቶች መፈጸም የማይቻል መሆኑን እያወቀ፥ ሰዎች ወደ ጸጋው እንዲመለሱ ለማበረታታት እንዳስተማረ አድርገው ገልጸዋል። የተቀሩት ደግሞ ክርስቶስ እነዚህን ትምህርቶች ለክርስቲያኖች እንዳልሰጠና፥ ክርስቶስ በዚህ ምድር ላይ ለሺህ ዓመታት በሚነግሥበት ጊዜ ለሚኖሩት አይሁዶች የታቀዱ እንደሆነ አስረድተዋል። እነዚህ ሁሉ ክርስቶስ ከአስተማረው አስቸጋሪ ትምህርቶችና ደቀ መዛሙርቱ እንዲኖሩት ይፈልግ ከነበረው ሕይወት ለመሸሽ የተደረጉ ጥረቶች ነበሩ። ክርስቶስ እርሱን ለመከተል የሚፈልጉ ሁሉ ራሳቸውን ለእርሱ ሊያስገዙና በተለወጠ ሕይወት የመንግሥቱ አካል እንዲሆኑ ይሻል። ባሕርያቸው፥ ከሌሎች ጋር የሚዛመድበት መንገድና ለእግዚአብሔር የሚያቀርቡት አምልኮ ሁሉ መለወጥ አለበት። የክርስቶስ ተከታይ በሁሉም የሕይወት ዘርፍ ዐቢይ ለውጥ ማሳየት ይኖርበታል። ማቴዎስ 5-7 የተሰጠው ትምህርት ምናልባትም እንደ ክርስቶስ ተከታዮች እንዴት መኖር እንደሚገባን ከአዲስ ኪዳን ምንባቦች ሁሉ ጥርት ባለ ሁኔታ የሚያስተምረን ክፍል ነው። ምንም እንኳ ይህ በራሳችን ኃይል የማይቻል ቢሆንምና ማናችንም ከመቅጽበት ለመለወጥ ባንችልም፥ ክርስቶስ እንድንኖር የሚፈልገው በዚህ መንገድ ነው። (ማብራሪያው የተወሰደው በኤስ አይ ኤም ከታተመውና «የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ» ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ ስለዚህ አስደናቂ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው።)

ክርስቶስ ለተከታዮቹ ያቀረበው ግብረገባዊ ትምህርት ማጠቃለያ (ማቴ. 5-7) Read More »

የክርስቶስ የመጀመሪያ ዓመት አገልግሎት ማጠቃለያ (ማቴ. 4፡12-25)

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ማቴ. 4፡12-25ን አንብብ። የክርስቶስ የመጀመሪያው አገልግሎት ዐበይት ባሕርያት ምንድን ናቸው? ለ) የክርስቶስ ትምህርት ከመጥምቁ ዮሐንስ ጋር የሚመሳሰለው እንዴት ነው? ከማቴ. 3፡2 ጋር አነጻጽር። የክርስቶስ የመጀመሪያ ዓመት አገልግሎት እንደ ቀጣዩ ሁለት ዓመት ጥድፊያ የበዛበት አልነበረም። ማቴዎስ የመጀመሪያውን ቀዳሚ ዓመት አገልግሎቱን አልጠቀሰም። ክርስቶስ ውኃውን ወደ ወይን ጠጅ እንደለወጠ ወይም በኢየሩሳሌም ከኒቆዲሞስ ጋር እንደተገናኘ ማቴዎስ አልገለጸም። ማቴዎስ ከመጀመሪያው ዓመት ብዙ ሥራዎችን አልፎ፥ ይፋዊ አገልግሎቱን ብቻ በማጠቃለያ መልክ ይጀምራል። ይህንንም የሚያደርገው መጥምቁ ዮሐንስ ከታሰረበት ዓመት በመጀመር ነው። ምናልባትም ማቴዎስ ታሪኩን በዚህ መልክ የጻፈው፥ ክርስቶስ ከተጠመቀ በኋላ የመጥምቁ ዮሐንስ «የመንገድ ጠራጊነት» ተግባር እንደተጠናቀቀ ለማሳየት ይሆናል፡፡ በዚህ ጊዜ መሢሑ መጥቷል። ማቴዎስ ስለ ክርስቶስ የመጀመሪያ አገልግሎት ሲያጠቃልል በቀረው ማጠቃለያ ላይ በአራት ነገሮች ላይ ትኩረትን አድርጓል፡ ሀ. ክርስቶስ በቀዳሚነት በገሊላ ስለ ማገልገሉ በተከታዩ የአንድ ዓመት ተኩል ጊዜ፥ ክርስቶስ በአብዛኛው ከናዝሬት 25 ኪሎ ሜትር ያህል ርቃ በምትገኝ በገሊላ ባሕር ጫፍ ላይ በነበረችው በቅፍርናሆም ከተማ አገልግሏል። ከተማይቱ ጠቃሚ በሆነ የንግድ መስመር ላይ ትገኝ ስለነበር፥ በቅፍርናሆም የሚያልፉ ብዙ ሰዎች ስለ ክርስቶስ ሰምተው ሊያምኑበት ችለዋል። በተጨማሪም ቅፍርናሆም ጴጥሮስንና ማቴዎስን ጨምሮ የብዙ ደቀ መዛሙርት መኖሪያ ነበረች። ማቴዎስን ያስደነቀው ነገር ቢኖር፥ ክርስቶስ በገሊላ የሰጠው አገልግሎት የትንቢት ፍጻሜ መሆኑ ነበር (ኢሳ. 9፡1-2)። ገሊላ በብሉይ ኪዳን ዘመን በዛብሎንና በንፍታሌም ነገዶች ግዛት ውስጥ ትገኝ ነበር። እነዚህ ሁለቱም አካባቢዎች በኢየሩሳሌም በሚኖሩ አይሁዶች ዘንድ የተናቁ ነበሩ። ለዚህም ምክንያት የነበረው፥ በእነዚህ አካባቢዎች ይኖሩ የነበሩ አይሁዶች ከአሕዛብ ጋር ተጋብተው ጣዖታቸውንም ያመልኩ ስለነበር ነው። በ722 ዓ.ዓ. እስራኤል በአሦር ከተማረከችበት ጊዜ አንሥቶ፥ ይህ የፍልስጤም ክፍል በአሕዛብ ቅኝ ግዛት ሥር ውሎ ነበር። ከዚህ በኋላ አይሁዶች በመቃባውያን ዘመን በገሊላ ሰፈሩ። እነዚህ አነስተኛ የአይሁድ ቅኝ ግዛቶች እያደጉ የሄዱ ሲሆን፥ ብዙውን ጊዜ በይሁዳ ከሚኖሩ አይሁዶች በላይ ብሔራዊ ስሜት ይሰማቸው ነበር። ይህም ሆኖ፥ በይሁዳ የሚኖሩ አይሁዶች የገሊላ አይሁዶችን ይንቋቸው ነበር። እንኳን መሢሑ አብዛኛውን ጊዜውን በምድር ላይ ማሳለፉ ቀርቶ፥ ምንም መልካም የሆነ ነገር ከገሊላ ይመጣል ብሎ የጠበቀ ሰው አልነበረም (ዮሐ. 1፡45-46፤ 1፡41፥ 52 አንብብ)። ምንም እንኳን ገሊላ በብዙ ሰዎች ብትናቅም፥ እንደ ሰው የአገርና የጎሣ ኩራት በማያጠቃው አምላክ ተከበረች። ለ. ኢየሱስ፥ «መንግሥተ ሰማይ ቀርባለችና ንስሐ ግቡ» እያለ አስተማረ። ማቴዎስ፥ የክርስቶስ መሠረታዊ ትምህርት የመጥምቁ ዮሐንስ ዓይነት መሆኑን አሳይቷል። ይህም ለሰዎች መንግሥተ ሰማይ እንደቀረበችና ንስሐ መግባት እንዳለባቸው የሚያሳስብ ትእዛዝ ነበር። መሢሑ በመካከላቸው ስለነበረ፥ ሕዝቡ ሕይወታቸውን መለወጥ ነበረባቸው። ከአሮጌው ሕይወታቸው ተመልሰው ለመሢሑ መንግሥት መዘጋጀት ያስፈልጋቸው ነበር። ሐ. ኢየሱስ ሰዎች ደቀ መዝሙሩ ሆነው እንዲከተሉት ጠርቷል። በአፈ ታሪክ እንደሚነገረው፥ የአይሁድ ሃይማኖት መሪዎች ስለ እግዚአብሔር ዐበይት እውነቶችን የሚያስተምሯቸው ደቀ መዛሙርት ነበሯቸው። እነዚህ ደቀ መዛሙርት መምህሮቻቸው ወደሚሄዱበት ሁሉ እየሄዱ ይረዷቸውና ትምህርት ይቀስሙ ነበር። ክርስቶስ ይህንን ትውፊት በመከተል ከመጀመሪያው ራሱን እንደ ሃይማኖት መሪ አስተዋውቋል። ክርስቶስ ሰዎች እስኪከተሉት ከመጠበቅ ይልቅ፥ ደቀ መዛሙርቱን ለመምረጥ የአስተዋይነት ምርጫ አድርጓል (ማቴ. 4:18-22)። ማቴዎስ ክርስቶስ ከመረጣቸው ደቀ መዛሙርት የመጀመሪያ አራቱን ጠቅሷል። የመጀመሪያዎቹ ሁለቱ፥ ስምዖን ጴጥሮስና እንድርያስ የሚባሉ ወንድማማቾች ሲሆኑ፥ ሌሎቹ ሁለቱ ያዕቆብና ዮሐንስ የሚባሉ ወንድማማቾች ነበሩ። ክርስቶስ ከዚህ በፊት የነበራቸውን ሥራ ትተው እንዲከተሉት ጠራቸው። ዓሣ ማጥመዳቸውን እንዲተዉና የእርሱን ትምህርት ተቀብለው ሰዎችን እንዲያጠምዱ አሳሰባቸው። (ይህንን በዮሐንስ 1 ከሚገኘው ታሪክ ጋር በምናነጻጽርበት ጊዜ፥ አራቱም ደቀ መዛሙርት ለተወሰነ ጊዜ ክርስቶስን ከተከተሉ በኋላ ወደ ቀድሞ ሥራዎቻቸው በመመለሳቸው፥ ክርስቶስን ለመከተል እንደገና የተጠሩ ይመስላል።) በወንጌላት ውስጥ ብዙውን ጊዜ የክርስቶስ ደቀ መዝሙር ስለመሆን ያገለገለው ቃል፥ «መከተል» የሚል ነው። ክርስቶስ ይህን ቃል በመጠቀም በእርሱ የሚያምኑ ሰዎች በሕይወታቸው ላይ ላለው ሥልጣን እንዲገዙ እየጠየቃቸው ነበር። ዕቅዶቻቸውን ትተው የክርስቶስን ፈቃድ መፈጸም ያስፈልጋቸው ነበር። አኗኗሩን፥ ከእግዚአብሔር ጋር የነበረውን ቅርበት፥ ከሰዎች ጋር የነበረውን ቅርበትና ያገለገለበትን መንገድ መከተል ነበረባቸው። ተከታዮቹ እርስ በርሳቸው ኅብረት ነበራቸው። ይህም ኅብረት ቤተ ክርስቲያን ይባላል። አካሉ በሆነችው ቤተ ክርስቲያን አማካይነት ለጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ይሠራሉ። የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ለጴጥሮስ፥ እንድርያስ፥ ያዕቆብና ዮሐንስ ክርስቶስን የመከተሉ ምርጫ አስቸጋሪ ሊሆን የቻለው እንዴት ነበር? ለ) ከዚህ፣ የክርስቶስ ደቀ መዝሙር ስለ መሆን ምን እንማራለን? ሐ) የክርስቶስ «ተከታይ» መሆንህን እንዴት እያሳየህ እንደሆነ አብራራ። በማቴ. 28፡19-20 ላይ፥ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱ የራሱን አርአያ በመከተል ሌሎች ደቀ መዛሙርትን እንዲያፈሩ ነግሯቸዋል። በምድር ላይ ከሚገኙ ነገዶች ሁሉ ሰዎችን ደቀ መዛሙርት ማድረግ ይኖርባቸዋል። እያንዳንዱ ክርስቲያን የክርስቶስ ደቀ መዝሙር ለመሆን ተጠርቷል። ይህ ምን ማለት ነው? ማቴዎስ ደቀ መዝሙር የክርስቶስን አዲስ የሕይወት ልምምድ ለመቀበል ሲል፥ አሮጌ ሕይወቱን የሚተው ሰው እንደሆነ ይነግረናል። ይህ በቀዳሚነት ስለ ኢየሱስ በመመስከር፥ ደቀ መዛሙርት ይሆኑ ዘንድ «ሰዎችን ማጥመድ»ን ጭምር የሚያካትት ነው። ክርስቶስ እርሱን ለመከተል ሥራችንን እንድንተው አይጠይቀን ይሆናል፤ ይሁንና ሕይወታችንን ሙሉ በሙሉ ለእርሱ እንድናስገዛ ይፈልጋል። ማቴዎስ ክርስቶስን መከተል ማለት እርሱን ለመከተል ሁሉንም ነገር መተው እንደሆነ አመልክቷል። ይህ ከፍተኛ ዋጋን የሚያስከፍለን እንጂ ቀላል ውሳኔ አይደለም። መ. ኢየሱስ ሲያስተምር፥ ሲሰብክና ሲፈውስ ዝናው እየገነነ መጣ። ማቴዎስ፥ ክርስቶስ ያደረጋቸውን ነገሮች ሁሉ ከመዘርዘር ይልቅ በማቴዎስ 5-7 ላይ በቀረበው የትምህርት አገልግሎቱ ላይ ያተኩራል። ነገር ግን የክርስቶስ ትምህርት የታላቁ አገልግሎት አካል እንደሆነ ለማሳየት ሲል፥ ማቴዎስ የክርስቶስን ተግባራትና የሕዝቡን ምላሽ ጠቅለል አድርጎ ገልጾታል። እንደተጻፈው ሁሉ ክርስቶስ በገሊላ ከተማ ውስጥ ከስፍራ ወደ ስፍራ እየተዘዋወረ ያስተምር ነበር። በምኩራብና በሜዳ ላይ ባለማቋረጥ ያስተምር፥ ይሰብክና ይፈውስ ነበር። አንድ ምሑር እንደገለጹት፥ «ማስተማር» ኢየሱስ ሰዎች እንዲያውቁ የፈለጋቸውን እውነቶች ማሳወቁን ያመለክታል። ስብከት ደግሞ ክርስቶስ ሰዎች እውነትን ተግባራዊ ለማድረግ ሕይወታቸውን እንዲለውጡ መፈለጉን ያሳያል። ፈውስ ደግሞ ክርስቶስ ለሕዝቡ የነበረውን ርኅራኄ ብቻ ሳይሆን፥ መሢሕ መሆኑንም በይፋ ያሳየበት አገልግሎት ነበር። ከፈውሱ ዓይነት አንዱ ከአጋንንት ነፃ መውጣት ሲሆን፥ ይህም የክርስቶስ መንግሥት የሰይጣንን መንግሥት እያሸነፈ መሆኑን አሳይቷል። ክርስቶስ በዚህ ባሕሪው በሰዎች ዘንድ ተወዳጅነትን እያተረፈ ሊመጣ ችሏል። ከገሊላ በስተ ሰሜን ከምትገኘው ከሶሪያ እስከ ደቡባዊቷ ኢየሩሳሌምና በስተምሥራቅ እስከሚገኙት ዐሥሩ ከተሞች ድረስ ስለ እርሱ ሥራ በሰፊው ይወራ ነበር። ማቴዎስ ክርስቶስ የፈጸመውን ተግባር ጠቅለል ባለ ይዘት ካቀረበ በኋላ፥ በተቀረው የመጽሐፉ ክፍል ሁሉ በክርስቶስ ተአምራትና ዐበይት ትምህርቶች ላይ ያተኩራል። (ማብራሪያው የተወሰደው በኤስ አይ ኤም ከታተመውና «የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ» ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ ስለዚህ አስደናቂ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው።)

የክርስቶስ የመጀመሪያ ዓመት አገልግሎት ማጠቃለያ (ማቴ. 4፡12-25) Read More »