በተደጋጋሚ የሚነሱ ጥያቄዎች (FAQs)

የቤተ ክርስቲያን ንጥቀት ገለጣ (ዮሐ. 14፡1-3፤ 1ኛ ቆሮ. 15፡51-57፣ 1ኛ ተሰ. 4፡13-18)

This entry is part 21 of 23 in the series በተደጋጋሚ የሚነሱ ጥያቄዎች (FAQs)

“መነጠቅ” [Rapture/ራፕቸር] የሚለው ቃል በ1ኛ ተሰሎንቄ 4፡17 ላይ ተጠቅሶ ይገኛል። እንዲሁም ፊልጶስ በሐዋርያት ሥራ 8፡39 እና ጳውሎስ በ2ኛ ቆሮንቶስ 12፡2 4 ስለመነጠቃቸው ተገልጧል። በመሆኑም የቤተ ከርስቲያን መነጠቅ፥ ወደ ላይ መውጣት ማለት ነው። በዮሐንስ 14፡1-3 ላይ በተሰጠው ተስፋ መሠረት ወደ መኖሪያ ስፍራ መምጠቅ ነው። ጳውሎስ በቆሮንቶስ መልዕክቱ ይህ ምስጢር ነው ይላል። “ምስጢር” የሚለው ቃል ትርጉም፣ ከዚህ በፊት ያልታወቀ፥ አሁን የተገለጠ ማለት መሆኑን ልብ ማለት ያሻል። ትንሣኤ ምስጢር አልነበረም፤ ምክንያቱም ብሉይ ኪዳን ሰዎች ከሞቱ በኋላ እንደሚነሱ በግልጥ አስተምሯል (ኢዮብ 19፡25፤ ኢሳ. 26፡19 ዳን. 12፡2)። የተወሰኑ ሰዎች ሞትን ሳይቀምሱ ወደ እግዚአብሔር እንደሚሄዱ ግን በምንባቦቹ ውስጥ አልተገለጠም። ለዚህ ነው ሁላችን “አናንቀላፋም” የሚለው ቃል ምስጢር የሆነው (1ኛ ቆሮ. 15፡51)። በመነጠቅ ጊዜ በሕይወት ያሉ ሰዎች የማይሞት አካል ይለብሳሉ። በሞት የበሰበሱትም በትንሣኤ የማይብስብስ አካል ይሰጣቸዋል። በሁለቱም መንገድ ወደ ሰማይ የሚደረግ ጉዞ ለውጥ ይሻል፤ ሕያዋን መለወጥ፥ ሙታንም መነሳት አለባቸው፤ የመጨረሻው የክርስቲያን ትውልድ ሞትን አይቀምስም፡፡ ይህ ለውጥና መነጠቅ የዓይን ሽፋን መርገብገብን ያህል ቅጽበታዊ” እንጂ አዝጋሚ ክንውን አይደለም። እንዲሁም መነጠቅ ሳይከፋፈል በአንድ ጊዜ ይሆናል። ጳውሎስም ሁላችን እንለወጣለን አለ እንጂ ስለተወሰኑ አማኞች አልተናገረም። 1ኛ ቆሮንቶስ 15፡51-58 ሦስት ነገሮች ያስተምራል።  1. መነጠቅ የሞቱ አማኞችን ብቻ ሳይሆን፥ በጊዚው ሕያው የሆኑ አማኞችንም የአካል ለውጥ ያመለክታል። 2. በቅፅበት ይፈጸማል። 3. አማኞችን ሁሉ ያካትታል እንጂ፥ ለተወሰኑ ብቻ አይደለም።  ከሌሎቹ ይልቅ በ1ኛ ተሰሎንቄ 4፡13-18 ያለው ጥቅስ ነው ጌታ ሲመጣ ምን እንደሚሆን የተብራራ አሳብ የሚሰጠን። በዚህ ክፍል አራት ነገሮች ተጠቅሰዋል።  1. ክርስቶስ ራሱ ይመለሳል (ቁ. 16)፣ በአካል መገለጡ የሚያስከትላቸው በኃይል የተሞሉ ክስተቶችም ይኖራሉ፤ ታላቅ የትእዛዝ ድምጽ፥ የሊቀ መላእከት ድምጽ፥ የእግዚአብሔር መለከት ድምጽ ይሰማሉ።  2. ትንሣኤ ይሆናል (ቁ. 16)። የሞቱት ይነሳሉ፥ ሕያዋንም ይለወጣሉ፥ ይህ ሁሉ በቅስበት የሚከናወን ይሆናል። የሰው ዘር በሙሉ ሳይሆን፥ የሞቱና ሕያዋን ክርስቲያኖች ብቻ ናቸው ይህን መነጠቅ የሚቀምሱት። ይህ አማኛችን ብቻ የሚመለከት ይሆናል፤ ምክንያቱም አንድ አጠቃላይ ትንሣኤ ሳይሆን የተለያዩ ትንሣኤዎች ናቸው ያሉት።  3. መነጠቅ ይሆናል (ቁ. 17)። የቃሉ ትርጉም፣ አንድን ሰው ከአንድ ስፍራ ወደ ሌላ መውሰድ ማለት ሲሆን ይህም ሕያዋን ሰዎችን ወደ መንግሥተ ሰማያት መውሰድ ማለትን በትክክል ያመለክታል (2ኛ ቆሮ. 12፡4)።  4. ከዚያም እንደገና መገናኘት ይኖራል (ቁ. 17)፤ በጌታ ከሞቱና ከምንወዳቸው ሰዎች፥ እንዲሁም ከጌታም ጋር እንገናኛለን። ግንኙነቱም ዘላለማዊ ይሆናል።  የመነጠቅ ጊዜ  መነጠቅ ከጌታ ዳግም ምጽአት የተለየ ስለመሆኑ ብዙ ሰዎች ይስማማሉ። የመጀመሪያው መነጠቅ፥ ከርስቶስ የራሱ የሆኑትን ለመውሰድ የሚመጣበት ጊዜ ሲሆን ሁለተኛው ግን ከነርሱ ጋር በድል አድራጊነትና በክብር የሚመለስበት ወቅት ነው። አከራካሪው ጉዳይ በነዚህ ሁለት ክንውኖች መካከል ምን ያህል የጊዜ ልዩነት አለ? የሚለው ጥያቄ ነው። አልቦ-ሺህ ዓመታውያን፥ ሁለቱም በፍዳው ዘመን መጨረሻ ላይ የሚከናወኑ ሲሆን፥ ንጥቀት ይቀድምና ወዲያውኑ ዳግም ምጽአት ይከተላል (ወዲያውኑ፥ ያለ ሺህ ዓመት አገዛዝ) ይላሉ። በቅድመ-ሺህ ዓመታውያን ዘንድ ስለመነጠቅ ጊዜያት አራት አመለካከቶች እንዳሉ ይታወቃል።  የድህረ–ፍዳ ዘመን አመለካከት። ይህ አመለካከት የመነጠቅንና የዳግም ምጽአትን የጊዜ ቅደም ተከተል አስመልክቶ የሚያሰራጨው ትምህርት ከአልቦ-ሺህ ዓመታውያን የተለየ አይደለም (የሺህ ዓመቱ አገዛዝ ከዳግም ምጽአት በኋላ ይከተላል በሚለው አመለካከቱ ግን ይለያል)። በዚህ አመለካከት መሠረት ቤተ ክርስቲያን በፍዳው ዘመን ሁሉ በምድር ላይ ትኖራለች። የክርስቶስ ለቅዱሳኑና ከነሱ ጋር መምጣት፥ በዚህ ዘመን ማብቂያ ላይ ወዲያውኑ የሚከሰቱ ድርጊቶች ናቸው።  ዋና ዋናዎቹ የመከራከሪያ ነጥቦቻቸው፡-  1. መነጠቅና ዳግም ምጽአት በመጽሐፍ ቅዱስ በተመሳሳይ ቃላት ነው የተገለጡት። ይህ ሁለቱም በአንድ ጊዜ የሚከናወኑ መሆናቸውን ያመለክታል (1ኛ ተሰ. 4፡15፤ ማቴ. 24፡27)።  2. በፍዳው ዘመን ቅዱሳን እንደሚኖሩ ስለተገለጠ፥ ቤተ ክርስቲያንም በዚያን ጊዜ በምድር ትኖራለች (ማቴ. 24፡22)።  3. ትንሣኤ በሺሁ ዓመት አገዛዝ መጀመሪያ ላይ የሚከሰት ነው ተብሎ ይታመናል። ይኽው ትንሣኤም በመነጠቅ ጊዜ የሚከናወነው ትንሣኤ መሆኑ ስለሚገመት፥ መነጠቅ ልክ ከሺሁ ዓመት አገዛዝ በፊት የሚፈጸም ይሆናል (ራእይ 20፡4)።  4. ቤተ ክርስቲያን ከፍዳው ዘመን ቁጣ በመለኮታዊ ኃይል ትጠበቃለች። ጥበቃው የሚከናወንላት በዚያው ዘመን እየኖረች እንጂ፥ ከዚያ ወጥታ ወይም ተነጥቃ አይደለም እስራኤላውያን በግብፅ እየኖሩ ከመቅሰፍት እንደተጠበቁ)።  5. መጽሐፍ ቅዱስ ከክርስቶስ ዳግም ምጽአት በፊት መፈጸም ያለባቸው ትንቢቶች እንዳሉ የሚያስተምር በመሆኑ፥ መነጠቅ ከታወቀው የፍዳ ዘመን ክንዋኔ በኋላ ይሆናል።  6. ይህ ድህረ-ፍዳ ዘመን አመላካከት የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ትምህርት ነበር።  ማዕከላዊ የፍዳ ዘመን። የዚህ አመለካከት አቀንቃኞች ክርስቶስ ለሕዝቡ የሚመጣው በፍዳው ዘመን አጋማሽ ላይ ነው፤ ማለትም የፍዳ ዘመን ከጀመረ ከሦስት ዓመት ተኩል በኋላና ሊያልቅም ሦስት ዓመት ተኩል ሲቀረው ነው፤ ያኔ ነው ክርስቶስ የሺህ ዓመቱን መንግሥት ለመመሥረት ከቅዱሳኑ ጋር የሚመጣው ይላሉ።  የዚህ አመለካከት መከራከሪያ ነጥቦች፡-  1. 1ኛ ቆሮንቶስ 15፡52 ላይ የተጠቀሰው የመጨረሻ መለከት” በዮሐንስ ራእይ 11፡15 ላይ ከተጠቀሰው “ሰባተኛ መለከት” ጋር አንድ ነው፤ ይህም የተሰማው በፍጻሜው ዘመን መካከል ላይ ነው።  2. እርግጥ ታላቁ የፍዳ ዘመን ከዳንኤል ሰባኛ ሳምንት ሱባኤ መጨረሻ የሳምንት አጋማሽ ሰለሆነ፥ ቤተ ክርስቲያን ከዚያ መከራ ነው የምትጠበቀው (ራእይ 11፡2፤ 12፡6)።  3. የሁለቱ ምስክሮች ትንሣኤም የቤተ ክርስቲያን መነጠቅ ያመለክታል፤ የነሱም ትንሣኤ የሚከናወነው በመከራው ዘመን አጋማሽ ላይ ነው (ራእይ 11፡11)።  ከፈል መነጠቅ። ይህ አመለካከት ያላቸው ወገኖች የሚያስተምሩት ደግሞ፥ ተገቢ የሆኑ አማኞች ብቻ የፍዳው ዘመን ከመጀመሩ በፊት ይነጠቃሉ፤ ሌሎች ግን ቁጣውን በትዕግሥት እንዲያልፉ ይተዋሉ ማለት ነው። በምድርም ለሚቀሩት ይህ ጊዜ የመጥራት ጊዜ ይሆንላቸዋል። አሳቡ የተወሰደው እንደ ዕብራውያን 9፡28 ካለው ጥቅስ ሲሆን፥ በዚህ ጥቅስ መሠረት ጌታን ለመገናኘት ቅድመ ዝግጅት ማስፈለጉ ግዴታ ይሆናል። ምንም እንኳን በዚህ አመለካከት መሠረት መልካም ሥራ አንድን ሰው ለመነጠቅ ያበቃዋል ሲባልም፥ ምን ያህል ጥሩ ሥራ ነው የሚያስፈልገው? ለሚለው ጥያቄ ግን የአሳቡ ደጋፊዎች መልስ አይሰጡም። እነዚህ ሰዎች በዚህ ሳይወሰኑ በ1ኛ ቆሮንቶስ 15፡51 ላይ “ሁላችንም እንለወጣለን” የሚለውን ግልጥ ቃል ወደ ጎን ይሉታል።  ቅድመ-ፍዳ ዘመን። ይህ አመለካከት ያላቸው ወገኖች ቤተ ክርስቲያን ሰባቱ የፍዳ ዘመን ከመጀመሩ በፊት ትነጠቃለች በማለት ያስተምራሉ። ከሰባቱ ዓመት በኋላ ማለት፥ የፍዳው ዘመን እንዳለቀ፣ የሺህ ዓመቱን መንግሥት ለመመሥረት ጌታ ከሕዝቡ ጋር ይመጣል ብለው ሲያምኑ፥ አሳባቸውን ለማጠናከር የሚከተሉትን ነጥቦች ይጠቅሳሉ።  1. የፍዳው ዘመን “ታላቁ የቁጣ ቀን” (ራእይ 6፡17) ተብሎ ተጠርቷ፡፡ ከሚመጣው ቁጣ የሚታደጋቸው አዳኝ እንዳላቸው ያወቁ አማኞች (1ኛ ተሰ. 1፡10) እግዚአብሔር ለቁጣ እንዳልመረጣቸው እርግጠኞች ይሆናሉ (1ኛ ተሰ. 5፡9)። በዚህ ጥቅስ ምንባብ ጳውሎስ በጌታ ቀን ወይም በፍዳው ዘመን መጀመሪያ ስለሚኖረው ነገር ነው የሚናገረው (1ኛ ተሰ. 5፡2)፤ ከርስቲያኖች በዚያን ጊዜ እንደማይገኙና የቁጣው ዘመን ከመጀመሩ በፊት እንደሚወሰዱ ግልጥ አድርጓል። ይህ እውን የሚሆነው ግን መነጠቅ ከፍዳው በፊት የተፈጸመ እንደሆነ ብቻ መሆኑን በማስታወስ ነው።  2. ከሞት የተነሣው ጌታ በፊላደልፊያ ላለችው ቤተ ክርስቲያን “በዓለም ሁሉ ላይ ሊመጣ ካለው የፈተና ሰዓት እጠብቅሃለሁ” (ራእይ 3፡10) በማለት ቃል ገብቷል። የቅድመ-ፍዳ ዘመን አመለካከት ተከታዮች ይሆን የተስፋ ቃል ለሌሎች አጥቢያ ቤተ ክርስቲያናት ከተጻፉት የተስፋ ደብዳቤዎች ጋር ያዛምዱታል (እርግጥ ይህን እውነት የሚያዩት ክርስቶስ ሲመጣ የሚኖሩት አማኞች ብቻ ቢሆኑም)። በመቀጠልም “የፈተና ሰዓት” የተባለው ጊዚ ዓለምን በሙሉ የሚያዳርስ ስለሆነ የፍዳን ዘመን ያመለክታል ይላሉ። የድህረ-ፍዳ ዘመን አመለካከት ያላቸው ወገኖች ይህ ተስፋ (ከዳቶ ዘመን ጋርም ያዛምዱታል) ክርስቲያኖች ምንም እንኳን በፈተናው ዘመን ውስጥ መኖር ቢኖርባቸውም ከፍዳው ዘምን ፍርድ የሚጠበቁበት ነው ይላሉ። ይሁን እንጂ ተስፋው ከችግሩ ሳይሆን ከችግር ጊዚው እንደሚጠበቁ ነው የሚያረጋግጠው። ይህ ክርስቲያኖች በዚያን ጊዜ ፍጹም ይወገዳሉ ማለት ይመስላል። “ከ..እጠብቅሃለሁ” የሚል ቃል በአዲሰ ኪዳን ሁለት ጊዜ ብቻ የተጠቀሰ ሲሆን፥ እዚህ ቦታና ዮሐንስ 17፡15 ላይ ይገኛል። በሁለተኛው

የቤተ ክርስቲያን ንጥቀት ገለጣ (ዮሐ. 14፡1-3፤ 1ኛ ቆሮ. 15፡51-57፣ 1ኛ ተሰ. 4፡13-18) Read More »

ጥምቀት

This entry is part 22 of 23 in the series በተደጋጋሚ የሚነሱ ጥያቄዎች (FAQs)

የውኃ ጥምቀት ጉዳይ ሁለት ጥያቄዎች ያስነሳል። እነርሱም እንዴት ነው ጥምቀት መከናወን ያለበት? (አሠራሩ) እና በማን ላይ ነው መከናወን ያለበት? (አማኞች ብቻ ወይስ ሕፃናትም ጭምር) የሚሉ ናቸው። እነዚህን ጥያቄዎች ከመመለሳችን በፊት ግን የጥምቀትን ትርጉምና ጥቅም መግለጥ አስፈላጊ ይሆናል።  ማንኛውም የጥምቀት ትርጉም፥ ከክርስቲያን ጥምቀት ጋር ተያይዞ ብቻ ሳይሆን፥ ወደ ይሁዲነት የሚለወጡ ሰዎች የሚወስዱትን ጥምቀት፥ የመንፈስ ቅዱስን ጥምቀትና በ1ኛ ቆሮንቶስ 10፡2 ላይ የተጠቀሰውን እንግዳ አሳብ ሳይቀር ማካተት አለበት። ብዙ ትርጉሞች የተመሠረቱት በውኃ ማጥለቅ በሚለው ቃል ላይ ነው። የጥምቀት ሥነ-መለኮታዊ ትርጉም ግን ከአንድ ማኅበር፥ ወይም መልእክት ወይም ልምድ ጋር አንድ መሆንና ኅብረት መመሥረትን ነው የሚያስገነዝበው።  የጥምቀት አፈጻጸም እስካሁን ያከራከረና ወደፊትም የሚያከራክር ጉዳይ ነው። በማጥለቅ ማጥመቅ አስፈላጊ አይደለም የሚሉ ክፍሎች የሚከተሉትን መከራከሪያ ሃሳቦች ያቀርባሉ፡፡ 1. “ባፕቲዞ” የሚለው የግሪክ ቃል ሁለተኛ ትርጉም አለው። ይኸውም “በአንድ ነገር፥ ወይም ተጽዕኖ ሥር መሆን” ማለት ነው። ስለዚህ ውኃውን በተጠማቂው ላይ ማፍሰስ፥ ወይም መርጨት፥ የሚሉት ቃላት ማጥለቅ ከሚለው በተሻለ ጥምቀት የሚለውን አሳብ ይገልጡታል።  2. ጥምቀት የመንፈስ ቅዱስን በአንድ ሰው ላይ መውረድ የሚያስረዳ ከሆነ፥ የውኃ ጥምቀትን አስመልክቶም ማፍሰስ ወይም መርጨት የሚሉት ቃላት ይበልጥ ይገልጡታል።  3. ለምሳሌ በሐዋርያት ሥራ 2፡41 እንደተጠቀሰው በውኃ ውስጥ ማጥለቅ የማይቻልበት ሁኔታ ያጋጥም ይሆናል (በጣም ብዙ ሰዎችን በማጥለቅ ማጥመቅ ያዳግታል)። በሐዋርያት ሥራ 8፡38 (በረሃ ውስጥ ያለው ውኃ ትንሽ ስለሆነ) እና ሐዋ. 10፡47 እና 16፡33 (በየቤቱ ለማጥለቅ በቂ ውኃ አለመገኘቱ፣ በማጥለቅ የማጥመቁን ተግባር የማይችል ባያደርገውም፥ ተግባራዊነቱ ያጠራጥራል)።  4. በዕብራውያን 9፡10 ጥምቀት የሚለው ቃል በብሉይ ኪዳን ያሉትን ብዙ ወጎች ስለሚጠቅስና ከነዚህም አንዱ መርጨት ስለሆነ፥ ቃሉ ማጥለቅ ማለት ብቻ አይሆንም።  5. ማጥለቅ ለሚለው ቃል ሌላ የማያጠራጥርና ግልጥ የሆነ የግሪክ ቃል አለ። ታዲያ ትክክለኛው የማጥመቅ አሠራር ማጥለቅ ከሆነ፥ ለምን ትክክለኛው የግሪክ ቃል አልተጠቀሰም?  በውኃ በመጥለቅ መጠመቅን የሚደግፉ ወገኖች ከሚያቀርቡዋቸው ማስረጃዎች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፡-  1. “ባፕቲዞ የሚለው የግሪክ ቃል የመጀመሪያ ትርጉም ማጥለቅ ነው።  2. “ወደ ውስጥ” እና “ወደ ውጭ” (ውኃ) የሚሉትን መስተዋድዶች በሚገባ ከተረዳን፥ ቃላቱ የሚያመለክቱት መጥለቅን ነው።  3. ወደ ይሁዲነት የገባ ሰው የሚጠመቀው በማጥለቅ ነበር (ጥምቀቱን የሚፈጽመው ግን ሌሎች ሳይሆኑ ሰውየው ራሱ ነበር)። ክርስቲያናዊው አሠራርም ያን የተከተለ መሆኑን ከዚህ እንረዳለን (በሌላ ሰው የሚከናወን ቢሆንም።  4. የማጥለቅ ጥምቀት፥ የጥምቀትን ጥቅም ማለትም የአሮጌውን ሕይወት ሞትና የአዲሱኝ ሕይወት ትንሣኤ በሚገባ የሚገልጥ አሠራር ነው (ሮሜ 6፡1-4)።  5. የማጥለቅ ጥምቀት በጥንት ቤተ ክርስቲያናት ይፈጸም የነበረ አሠራር ሲሆን፥ አያሌ የአዲስ ኪዳን ምሳሌዎችም ይህን ያዛሉ፥ ወይም ይፈቅዳሉ (በኢየሩሳሌም አካባቢ ባሉ የውኃ ጉድጓዶች ውስጥ ሊጠመቁ ይችላሉ)። ሦስት ሺህ ሰዎች በበዓለ አምሳ ዕለት በመጥለቅ ሊጠመቁ ይችሉ እንደነበር መገመት አያዳግትም።  6. የግሪኩ ቋንቋ ለማፍሰስና ለመርጨት የተለያዩ ቃላት አሉት፤ ይሁን እንጂ ጥምቀትን በማመልከት አገልግሎት ላይ አልዋሉም።  አንድ ሰው ይህን ሲመለከት ማጥለቅ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አሠራር ነው ለማለት ይገደድ ይሆናል። ማጥለቅ የየትኛዋም ጥንታዊት ቤተ ክርስቲያን አሠራር የነበረ ይመስላል። የቃሉ ተገቢ ትርጉምና በሥርዓቱ የሚተላለፈው መልእክት ማጥለቅን ያመለክታሉ። ከማጥለቅ ቀጥሉ በሥራ ላይ የሚውለው ማፍሰስ እንጂ መርጨት አልነበረም። ይህም በተግባር ይውል የነበረው፣ የታመሙና በመጥለቅ መጠመቅ የማይችሉ ሰዎችን ለማጥመቅ ነበር። ከዚህ በመነሳት ማፍስስ “የሕሙማን ጥምቀት” ይባላል። ሲፕርያን [Cyprian] የተባለ ሰው (200-257 ዓ.ም.) በመርጨት መጠመቅን በመደገፍ የመጀመሪያው ነበር። ይሁን እንጂ እሰከ አሥራ ሁለተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ድረስ ይህ ዓይነቱ አሠራር በስፋት አልተለመደም።  ሌላው ጥያቄ መጠመቅ ያለበት ማንነው? አማኞች ወይስ ሕጻናትም መጠመቅ ይችላሉ? የሚል ነው። የሕፃናትን ጥምቀት የሚደግፉ ወገኖች በእምነታቸው መሠረት የሚደረድሯቸው ነጥቦች፡-  1. የግርዘት ሥርዓት (በሕፃናት ላይ የሚደረግ መሆኑ ይታወቃል) እና የጥምቀት ሥርዓት ተመሳሳይ ናቸው። ግርዘት የአሮጌው ኪዳን የመጀመሪያ ሥርዓት ሲሆን፣ ጥምቀት ደግሞ የአዲሱ መጀመሪያ ነው፡፡ 2. የቤተሰቡ መጠመቅ ሕፃናትንም እንደሚጨምር አያጠራጥርም (ሐዋ. 16፡33)።  3. በአዲስ ኪዳን ከቤተሰቡ አንድ ሰው አማኝ ከሆነ፥ ለቤተሰቡ ሁሉ የተስፋ ቃል የሚሰጥ ይመስላል። እንደዚህ ያለው ቤተሰብ ሕፃናትን ማጥመቁ አግባብ ይሆናል ይላሉ (1ኛ ቆሮ. 7፡14)።  የሕጻናትን ጥምቀት የሚቃወሙና የአማኞችን ጥምቀት የሚደግፉ ደግሞ፥ የሚከተሉትን ማሳመኛ ነጥቦች ያቀርባሉ።  1. ጥምቀት የመጀመሪያ ሥርዓት ከሆነ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ያመኑና የእግዚአብሔር ቤተሰብ አባላት የሆኑ ሰዎች የሚፈጽሙት ተግባር መሆን አለበት። የእስራኤል ወገን ለመሆን ከዚያ ዘር መወለድን ይጠይቃል። ዛሬ ደግሞ የእግዚአብሔር ቤተሰብ ለመሆን አዲስ ልደት ያሻል። ይህን የተረዱና ያመኑ ናቸው ሊጠመቁ የሚገባቸው።  2. ስለ ቤተሰብ መጠመቅ በአዲስ ኪዳን በተጠቀሰው ክፍል፥ በቤተሰሱ ውስጥ ሕፃናት ስለመኖራቸው የተብራራ ነገር የለም።  3. በሐዋርያት ዘመን፥ በአይሁዳውያንም ሆነ በክርስቲያኖች ዘንድ የሕፃናት ጥምቀት መኖሩን የሚያመለከት አንዳች ማረጋገጫ አይገኝም። ጥምቀት ከክርስቶስና ከክርስትና ጋር አንድ የመሆን ምልከት ከሆነ፣ ይህን ምልክት የሚጠቀሙበት አንድነት ያላቸው ብቻ ናቸው። ከከርስቶስና ከክርስትና ጋር ለመተባበር ደግሞ አንድ መንገድ ብቻ ነው ያለው፡- ክርስቶስን በግል ማምን። ይህ እምነት ያላቸው ሰዎች ብቻ ናቸው መጠመቅ ያለባቸው። ለምሳሌ የፊልጵስዩስ ወህኒ ጠባቂ ቤተሰቦች፥ ጳውሎስ የሰበከውን የጌታ ቃል ለመስማትና ለመረዳት በሚችሉበት የዕድሜ ክልል መሆናቸው ግልጥ ነው (ሐዋ. 16፡32)። ሰለዚህ አምነው የተጠመቁት፥ የተነገራቸውን ተረድተው ሊቀበሉ በሚችሉበት የዕድሜ ክልል ውስጥ የነበሩ ይሆናሉ። ይህ ልጆችን ይጨምራል ቢባል እንኳን፥ ሕፃናትን አይመለከትም።  እንደገና መጠመቅስ (ዳግም ጥምቀት)? በአዲስ ኪዳን ለዚህ ማስረጃ የሚሆን አንድ ግልጥ ምሳሌ አለ። ይኸውም በዮሐንስ የተጠመቁ ሰዎች፥ ጳውሎስ ክርስትናን ከሰበከላቸው በኋላ የሰሙትን በማመን በክርስቲያን ጥምቀት መጠመቃቸው ነው (ሐዋ. 19፡1-7። ይህ ሁኔታ የዮሐንስ ጥምቀትና የክርስትና ጥምቀት የተለያዩ መሆናቸውን ሲያሳይ፣ አንድ ሰው ከዚህ በፊት ቢጠቅም፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ሲያምን ከአዲሱ መልእክትና ውገን ጋር ያለውን አንድነት ለመግለጥ እንደገና ሊጠመቅ እንደሚገባው ያመለክታል። ምንጭ፡- “የመጽሐፍ ቅዱስ ሥርዓተ ትምህርት ጥናት”፣ በዶክተር ቻርልስ ሲ. ራይሪ ተጽፎ፣ በሲሳይ ደሳለኝ የተተረጎመ እና በየላፕስሊ/ብሩክስ ፋውንዴሽን የታተመ ነው፡፡ ለዚህ ድንቅ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡ ይህን ጽሁፍ ኮፒ እና ፕሪንት አድርጎ መጠቀም ይቻላል፤ ሆኖም ጽሁፉን መለወጥና ለሽያጭ ማዋል በሕግ የተከለከለ ነው፡፡

ጥምቀት Read More »

የጌታ እራት

This entry is part 23 of 23 in the series በተደጋጋሚ የሚነሱ ጥያቄዎች (FAQs)

የተለያዩ ሰዎች ስለ ጌታ እራት የተለያየ ትርጉም አላቸው። የሮም ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ተከታዮች፥ ህብስቱና ወይኑ መልካቸውን ባይለውጡም፣ በትክክል የክርስቶስ አካልና ደም ይሆናሉ ብለው ያምናሉ። ይህ አመለካከት [“ትራንስብስታንሺዬሽን” /Transubstantiation] የሚባል ሲሆን፥ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆነም ነው። ምክንያቱም የክርስቶስ ደምና ሥጋ ይህ ሥርዓት በተፈጸመ ቁጥር መሥዋዕት ሆኖ በመቅረቡ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ በተቃራኒው የሚገልጠው የክርስቶስ ሞት ሙሉና በቂ፥ እንዲሁም ላንዴና ለሁልጊዜ የተፈጸመ መሆኑን ነው (ዕብ. 10፡101 9፡12)። ሉተራውያን ደግሞ ወይኑና ህብስቱ ለውጥ ባይኖራቸውም፥ ሰው ከቅዱስ ቁርባኑ በሚቋደስበት ጊዜ እውነተኛ የክርስቶስ ሥጋና ደም ይሆናሉ ይላሉ። ይህም “ካንሰብስታንቪዬሽን” [Consubstantiationa] ይባላል። ሌሎች ደግሞ ይበልጥ ትክክል የሚመስል አመላካከት ያቀርባሉ፡- የጌታ እራት ሥርዓት የሚዘከረው ለመታሰቢያነት ብቻ ነው (1ኛ ቆር. 11፡24-25 “ለመታሰቢያዬ”) ህብስቱም ሆነ ወይኑ አይለወጡም፤ ክርስቶስ ግን በአገልግሉቱ ወቅት በመካከላችን ይገኛል፤ ያም ቢሆን ከህብስቱና ከወይኑ ውስጥ አይደለም ይላሉ።  የጌታ እራት የተለያዩ ዓላማዎች አሉት፡- 1. የጌታችን ሕይወትና ሞት መታሰቢያ ነው። ህብስቱ ፍጹምና ቅዱስ ሕይወቱን ያመለክታል፤ ይህ ቅዱስ ሕይወት ለኃጢአት መሥዋዕትነት የበቃና ተቀባይነት ያለው ነው። ስለሆነም ህብስቱ ኃጢአታችንን በመስቀል ላይ የተሸከመውን የክርስቶስ አካል ያመለክታል (1ኛ ጴጥ. 2፡24)። ወይኑም ለኃጢአታችን ስርየት የፈሰሰውን ደም ይወክላል። ያ አካል ዳግመኛ ሲሰቀል ለማየትም ሆነ ደሙ ሲፈስ ለመመስከር ስለማንችል፥ የቅዱስ ቁርባን ሥርዓት ለመታሰቢያነት ሲባል ብቻ የሚደረግ መሆኑን ማወቅ አለብን።  2. የጌታ እራት የወንጌልን እውነት የምናውጅበት ነው (1ኛ ቆሮ. 11፡26)።  3. የጌታን ዳግም ምጽአት በናፍቆት እንድንጠባበቅ ያሳስበናል፡፡ ይህን ሥርዓት የምናከብረው እስከዚያ ዕለት (ጌታ እስኪመጣ ድረስ ብቻ ይሆናል (1ኛ ቆሮ. 12፡26)።  4. እራቱ በክርስቶስ አካል ውስጥ ያለንን አንድነትና በዚህ አካል ውስጥ ካሉት አባላት ጋር ያለንን ኅብረት ያስታውሰናል(1ኛ ቆሮ. 10፡17)።  መቼ መቼ ነው የጌታ እራት መከበር ያለበት? አንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት በየሦስት ወሩ ሲያደርጉ፥ በተለምዶ ሥርዓቱን ለመፈጸም ካሰቡበት እሁድ በፊት ዮዝግጅት አገልግሎቶችን ያከናውናሉ። አንዳንዶች በየወሩ ሲያደርጉ፥ በየእሁዱም መደረግ አለበት የሚሉ አሉ። እርግጥ መጽሐፍ ቅዱስ የጌታን እራት መከበሪያ ጊዜ ለይቶ አይነግረንም። ከበዓለ አምሳ ሰኋላ የነበሩት የመጀመሪያ አማኞች በየቀኑ ያደርጉት የነበረ ይመስላል። ይህ ግን በየቀኑ በእያንዳንዱ ሰው ቤት ይከበር ነበር ማለት ሳይሆን፥ በኢየሩሳሌም ከተማ በአንድ ማዕከል መፈጸሙን ለማመልከት ነው (ሐዋ. 2፡46)። በጢሮአዳ (ሐዋ. 20፡6) እሁድ ዕለት ተደርጎ ነበር። ታዲያ አንዳንዶች ከጥቅሱ በመነሳት በየእሁዱ ተደርጓል ቢሉም፥ በዚህ ሁኔታ ስለመዘከሩ በግልጥ የተጻፈ መረጃ አናገኝም። የቱንም ያህል ቢደጋገም፥ አንዳንድ ጊዜ በምሽት ቢከናወን ተመራጭ ሊሆን ይችላል። እራት ስለሆነ ብቻ ሳይሆን፥ ጠዋት ጠዋት መምጣት የማይችሉ ምእመናንም እንዲካፈሉ ለማድረግም ነው። ይህ ሥርዓት ቤተ ክርስቲያን ከምታደርጋቸው ሌሎች ሥርዓቶች ይበልጥ ጠቃሚ ስለሆነ ሰፊ ጊዜ የሚሰጠው እንጂ፥ በችኮላ የሚከናወን ጕዳይ አይደለም። ምንጭ፡- “የመጽሐፍ ቅዱስ ሥርዓተ ትምህርት ጥናት”፣ በዶክተር ቻርልስ ሲ. ራይሪ ተጽፎ፣ በሲሳይ ደሳለኝ የተተረጎመ እና በየላፕስሊ/ብሩክስ ፋውንዴሽን የታተመ ነው፡፡ ለዚህ ድንቅ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡ ይህን ጽሁፍ ኮፒ እና ፕሪንት አድርጎ መጠቀም ይቻላል፤ ሆኖም ጽሁፉን መለወጥና ለሽያጭ ማዋል በሕግ የተከለከለ ነው፡፡

የጌታ እራት Read More »