የማርቆስ ወንጌል

ማርቆስ 6፡1-56

1. ኢየሱስ ባደገባት የናዝሬት ከተማ ተቀባይነትን አጣ (ማር. 6፡1-6) ለብዙ ሰዎች፥ በተለይም እርሱን በቅርብ ለሚያውቁት ከስብእናው አልፎ የኢየሱስን መለኮታዊነት መመልከቱ ከባድ ነበር። በሥጋዊ ሁኔታው ኢየሱስን ከሌሎች ሰዎች የሚለይ ምንም ነገር አልነበረም። በአሁኑ ዘመን የክርስቶስን ሥዕል በብርሃን አሸብርቆ መሥራት የተለመደ ቢሆንም፥ ትክክለኛ መልኩ እንደዚህ ዓይነት አልነበረም። የናዝሬት ሰዎች ለምን ሊቀበሉት አልፈቀዱም? ምክንያቱም ከተአምራቱ ሁሉ ባሻገር፥ መለኮታዊነቱን ሊመለከቱ አልቻሉም ነበር። ኢየሱስ እንደ ሰው ተራ የአናጺነት ተግባር የሚያከናውን ሰው ነበር። ቤተሰቦቹ ድሆችና በማኅበረሰቡ ውስጥ የማይታወቁ ነበሩ። በሥጋዊ ሁኔታው መሢሕ የሚያስመስል ምንም ዓይነት ነገር አልነበረውም። ማርቆስ የኢየሱስን መለኮታዊነትና ሰብአዊነት ሚዛናዊ አድርገን ማነጻጸር እንዳለብን ገልጿል። ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ ቢሆንም፥ ሰው ነው። ግልጽ ተቃውሞ በነበረበት ናዝሬት ኢየሱስ ተአምራትን የማድረግ ኃይል ቢኖረውም፥ ይህንኑ ከማድረግ ተቆጥቧል። 2. ኢየሱስ 12ቱን ደቀ መዛሙርቱን ላከ (ማር. 6፡6-13)። አንድ ሰው ከተወሰነ ሥራ በላይ ሊያከናውን አይችልም። ስለሆነም፥ አገልግሎቱ እንዲያድግና ወደ ሁሉም ሰው እንዲደርስ ከተፈለገ፥ ክርስቶስ ሥራውን ለማከናወን ሌሎችን ማሠልጠን ያስፈልገው ነበር። ክርስቶስ ለተወሰነ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን ሲያሠለጥን ነበር። እነዚህ ደቀ መዛሙርት ስለ ንስሐ ሲሰብክ፥ አጋንንትን ሲያወጣና ሰዎችን ሲፈውስ ተመልክተዋል። አሁን የተመለከቱትን ተግባራዊ የሚያደርጉበት ጊዜ ደረሰ። ክርስቶስ ብዙ ሰዎች ወንጌል የሚሰሙበትን አጋጣሚ ለማመቻቸትና ደቀ መዛሙርቱን በመፈተን ለአመራር ለማዘጋጀት ሲል፥ ሁለት ሁለት አድርጎ ላካቸው። ለዚህም ሁለት ምክንያቶች ነበሩ። በመጀመሪያ፥ እርስ በርሳቸው መደጋገፍ ነበረባቸው። አንድ ሰው (ወንጌላዊ) በቀላሉ ብቸኝነትና ተስፋ የመቁረጥ ስሜት ሊሰማው ስለሚችል፥ ሁለት ሆነው ኅብረት ሊያደርጉና ሊበረታቱ ችለው ነበር፡፡ ሁለተኛ፥ በአይሁዶች ልማድ አንድን እውነት ለማጠናከር ቢያንስ የሁለት ሰዎች ምስክርነት ወሳኝ ነበር (ዘዳግ 19:5)። ከዚህ የተነሣ፥ ስለ ክርስቶስ በቂ ምስክሮች ነበሩ። ክርስቶስ ያደረገውን ሁሉ (መስበክ፥ አጋንንትን ማውጣትና መፈወስን) 12ቱ ደቀ መዛሙርት የማከናወን ብቃት ተሰጥቷቸዋል። ማርቆስ ክርስቶስ ይህንን ሥልጣንና ኀይል እንደ ሰጣቸው ያሳያል። በተመሳሳይ መንገድ የእኛም ኃይልና ሥልጣን የሚመነጨው ከራሳችን ሳይሆን ከክርስቶስ ነው። የውይይት ጥያቄ፡- መሪዎች ብዙውን ጊዜ እንደ ልባቸው የሚረዳቸው ሰው እንደሌለ በመግለጽ ያማርራሉ። ሀ) ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን ማሠልጠኑ እያንዳንዱ የቤተ ክርስቲያን መሪ አገልግሎቱን ለማስፋትና የቤተ ክርስቲያንን የአመራር ፍላጎቶች ለማሟላት፥ ሊያከናውን ስለሚገባው ተግባር ምን ዓይነት አርአያነትን ይሰጣል? ለ) ይህ ብዙም የማይታየው ለምን ይመስልሃል? ሐ) አንተ የቤተ ክርስቲያን መሪ ከሆንህ፥ እግዚአብሔር አሠልጥነህ በሥራህ ውስጥ የምታሳትፋቸውን አምስት ወጣቶች እንዲሰጥህ በጸሎት ጠይቅ። 3. የመጥምቁ ዮሐንስ አንገት መቀላት (ማር. 6፡14-29) ማርቆስ የዮሐንስን መሞት የገለጸው አንዳንድ ዝርዝር ጉዳዮችን በመጨመር ነበር። ለምን? ምናልባትም የመጥምቁ ዮሐንስ ሞት በሌሎች ላይ ለሚደርሰው ስደት አርአያነት ያለው ተግባር ሳይሆን አይቀርም። መጥምቁ ዮሐንስ ክፋትን ስለ ተቃወመ ታስሮ ነበር። ሰዎች በኃጢአታቸው ሲቀጥሉ ዝም ብሎ ሊመለከታቸው ይችል የነበረ ቢሆንም፥ ይህን አላደረገም። እኛም በተመሳሳይ መንገድ የሰዎችንና የአገራችንን ኃጢአት ማጋለጥ አለብን። ይህንን በምናደርግበት ጊዜ ግን ስደት ሊገጥመን እንደሚችል ማወቅ አለብን። 4. ኢየሱስ አምስት ሺህ ሰዎችን መገበ (ማር 6፡30-44)። ማርቆስ ኢየሱስ አምስት ሺህ ሰዎችን እንደ መገበ በገለጸበት ታሪክ ውስጥ፥ ስለ ጠቅላላዎቹ ደቀ መዛሙርት የስብከት ጉዞ ዘግቧል። «ሐዋርያ» የሚለው ቃል በግሪክ ቋንቋ ሌላውን ሰው ወክሎ አንድን ተግባር የማከናወን ሥልጣን የተሰጠውን ሰው ያመለክታል። በአዲስ ኪዳን ውስጥ፥ ይህ ቃል በሁለት የተለያዩ መንገዶች አገልግሏል። በመጀመሪያ፥ ይህ ለ12ቱ ደቀ መዛሙርት የተሰጠ ስያሜ ነው። አዲስ ኪዳን ሁልጊዜም እነዚህ 12 ደቀ መዛሙርት ቤተ ክርስቲያንን ለመምራትና ከእግዚአብሔር የሆነውንና ያልሆነውን ለመበየን ሥልጣን እንደ ተሰጣቸው አድርጎ ያቀርባል። በተጨማሪም፥ አዲስ ኪዳን ጳውሎስም የ12ቱን ያህል ሥልጣን እንዳለው ያስተምራል (ሮሜ 1፡1)። ከጳውሎስና ከ12ቱ ሐዋርያት ሞት በኋላ በቤተ ክርስቲያን እንዲህ ዓይነት ልዩ ስፍራ የነበረው ሰው እንደ ነበር የሚያመለክት መረጃ የለም። ከእነዚህ መሪዎች ሞት በኋላ የዚህ ዓይነቱ ሥልጣን እንዳበቃ የቀድሞይቱ ቤተ ክርስቲያን ጸሐፊዎች ጠቅሰዋል። ስለዚህ፥ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለሰዎች ምን ሊያደርጉ እንደሚገባ ለመናገር የሚያስችል ፍጹም ሥልጣን ያላቸው ሐዋርያት ይኖራሉ ብለን መጠበቅ የለብንም። በአንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት በቤተ ክርስቲያን ላይ ሙሉ ሥልጣን ያለን ሐዋርያት ነን የሚሉ ሰዎች ተግባር፥ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት የሌለው አደገኛ ትምህርት ነው። ሁለተኛ፥ ሌሎችም ሐዋርያት ተብለው ተጠርተዋል። ምንም እንኳ የተለየ ሥልጣን ቢኖራቸውም፥ የ12ቱንና የጳውሎስን የሚያህል ሥልጣን አልነበራቸውም። እነዚህ አገልጋዮች (እና የአዲስ ኪዳን የትንቢት ስጦታ የነበራቸው ሰዎች) ዐበይት የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ተደርገው የሚቆጠሩ ሲሆን፥ ምናልባትም እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያንን የመትከልና በመጀመሪያዎቹ ጊዜያት የመምራት ስጦታ ከሰጣቸው ሰዎች ጋር ተመሳሳይ ሳይሆኑ አይቀሩም። በርናባስ (የሐዋ. 14፡14፥ የጌታ ወንድም የሆነው ያዕቆብ (ገላ. 1፡19)፥ አንዲራኒቆንና ዩልያን (ሮሜ 16፡7) ሐዋርያት መሆናቸው ተጠቅሷል። ኢየሱስ አምስት ሺህ ሰዎችን ከመገበበት ታሪክ፥ ስለ ኢየሱስ አያሌ እውነቶችን እንመለከታለን። በመጀመሪያ፥ ኢየሱስ የሰዎችን ፍላጎት ለማሟላት፥ ነገሮችን የመለወጥና የማብዛት ሥልጣን ያለው የእግዚአብሔር ልጅ ነው። ሁለተኛ፣ ኢየሱስ መልካም እረኛ መሆኑን እንመለከታለን። በመዝሙር 23፡1 እንደ ተመለከተው፥ ክርስቶስ የበጎቹን ፍላጎት ያሟላል። ይህ ታሪክ የክርስቶስ ተከታዮች ለሥጋዊ ፍላጎቶቻቸው፥ በተለይም ለሚበሉት ምግብ መጨነቅ እንደሌለባቸው ያስተምራል። ክርስቶስ ሁልጊዜም ለተከታዮቹ በመራራት ፍላጎታቸውን ያሟላላቸዋል። በመጨረሻም፥ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርት (በተለይም ለቤተ ክርስቲያን መሪዎች) ያላቸውን ትንሽ ነገር ወስዶ በማብዛት የእግዚአብሔርን መንጋ ፍላጎቶች እንደሚያሟላ የሚያስገነዝብ ነው። እንዲሁም፥ የሰዎችን ፍላጎቶች እንዴት እናሟላለን ብለን ሳንጨነቅ፥ ለእግዚአብሔር ያለንን በልግስና ልንሰጥና እግዚአብሔር እንደሚያባዛው ልንተማመንበት ይገባል። ምክንያቱም ሕዝቡ የእግዚአብሔር ሀብት በመሆናቸው፥ እግዚአብሔር ይራራላቸዋል፤ ስለሆነም፥ መሪዎቹ የሕዝቡን ፍላጎቶች እንዲያሟሉም ይጠቀምባቸዋል። 5. የኢየሱስ በውኃ ላይ መራመድ (ማር. 6፡45-56) አንዳንድ ጊዜ ፍርሃት ተፈጥሯዊና ጠቃሚ ምላሽ ነው። በመኪና መንገድ ላይ ተጠንቅቀን እየሄድን ሳለ፥ ጥሩምባው ሲነፋና ፍሬኑ በሚያዝበት ወቅት ሰቅጣጭ ድምፅ ሲሰማ፥ በፍርሃት ከመንገዱ ፈቀቅ እንላለን። በሌሎች ጊዜያት ደግሞ ፍርሃት ያለማመን ምልክት ይሆናል። የክርስቶስ ተከታዮች እግዚአብሔር በሚፈልገው መንገድ በእምነት ለመመላለስ ከፈለጉ፥ የስደትንና የችግሮችን ፍርሃት ማስወገድ አለባቸው። ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስ በውኃ ላይ ሲራመድ በማየታቸው፥ (አይሁዶች) መናፍስት ከውኃ ውስጥ ወደ ላይ እንደሚወጡ የሚያስረዳ ባሕል ነበራቸው) እና በነፋሳት ላይ ባሳየው ኀይል በመደነቃቸው፥ «ያለ መጠን እጅግ ተገረሙ ስለ እንጀራው አላስተዋሉምና ነገር ግን ልባቸው ደንዝዞ ነበር።” (ማር. 6፡51-52)። ክርስቶስን በበለጠ ስናውቅ፥ እርሱ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር እንዳለ ሁልጊዜም ማስታወስ አለብን። እርሱ ከእኛ ጋር ካለ የሚያስፈራን ነገር አይኖርም። ክርስቶስ ፍላጎታችንን ሁሉ ከማሟላቱም በላይ፥ የተፈጥሮንም ኃይል ይቆጣጠራል። ነፋስን መቆጣጠር ከቻለ፥ ማዕበልንም ሊቆጣጠር ይችላል። ማዕበሉን እንደተቆጣጠረ ሁሉ፥ ደቀ መዛሙርቱ የሚጋፈጧቸውን ችግሮችና ስደትም ሊቆጣጠር ይችላል። የሕይወት ማዕበል በሚያጋጥመን ጊዜ የምንፈራ ከሆነ ክርስቶስ ነገሮችን ሁሉ የሚቆጣጠር የእግዚአብሔር ልጅ ለመሆኑ እምነት የለንም ማለት ነው። እምነት በቃል ወይም በዝማሬ ብቻ የሚገለጽ አይደለምና። ሕይወታችንን በምናምነው እውነት ላይ ተመሥርተን ልንመራ ይገባል። ክርስቶስ ሁሉን ቻይ አምላክ እንደሆነ ካመንን፥ እርሱ ነገሮችን እንደሚቆጣጠር በማወቅ ወደ ሕይወታችን ለሚመጡ ጉዳዮች ሁሉ በእርሱ ልንተማመን ይገባል። የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በፍርሃት ስለተያዝክበት ጊዜ ግለጽ። ይህ በክርስቶስ ላይ ስላለህ የእምነት ጥልቀት ምን ያሳያል? ለ) ፍርሃት፥ አንድ ክርስቲያን እግዚአብሔር በሚፈልገው መንገድ እንዳይኖር የሚያደርገው እንዴት ነው? ሐ) የፍርሃት መድኃኒቱ ምንድን ነው? (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ማርቆስ 6፡1-56 Read More »

ኢየሱስ የሞተች ልጅ አስነሣ፥ የታመመች ሴት ፈወሰ (ማር. 5፡21–43)

በሰዎች ላይ ከፍተኛ ፍርሃትና የተስፋ መቁረጥ ስሜት የሚያስከትሉ ሁለት ነገሮች አሉ። በመጀመሪያ፥ ከሁሉም የከፋው የሰው ልጅ ጠላት ሞት ነው። ኢየሱስ በሞት ላይ ምን ሥልጣን አለው? የሚለው ምላሽን የሚሻ ጥያቄ ነበር። ሁለተኛ፥ የረዥም ጊዜ ሕመም አለ። ኢየሱስ ለረዥም ጊዜያት ሐኪሞችን ሁሉ አሸንፎ የቆየን በሽታ ሊፈውስ ይችላል? ማርቆስ እነዚህን ሁለት ታሪኮች በመጠቀም የእግዚአብሔር ልጅ የሆነው ኢየሱስ፥ እነዚህን ሁለት ጠላቶች ሊያሸንፍ እንደሚችል አሳይቷል። የመጀመሪያው ታሪክ ለ 12 ዓመታት ደም ስለሚፈሳት ሴት የሚናገር ነበር። ከዚህ በሽታ የተነሣ ሴትዮዋ ከማኅበረሰቡ ተገልላ ትኖር ነበር። የዚህ ዓይነት ችግር ያለባቸው ብዙ ሴቶች ከትዳራቸው ለመፈናቀል ተገድደዋል። ይህች ሴት መፍትሔ ለማግኘት ወደ ብዙ ሐኪሞች ዘንድ ብትሄድም አልተሳካለትም ነበር። የመጨረሻ ተስፋዋ ኢየሱስ ስለነበር፥ በሕዝብ መካከል እየተጋፋች ሄዳ ልብሱን ነካችው። ወዲያውም ተፈወሰች። ኢየሱስ በነበረበት ስፍራ እንዲቆምና ይህች ሴት እንደነካችው እንድታምን ያስገደዳት ለምን ነበር? ኢየሱስ ሁሉንም ነገር ስለሚያውቅ፥ እንደ ነካችው ቀድሞውኑ ተረድቶ ነበር። ክርስቶስ ይህንን ያደረገው የመፈወስ ችሎታውን ለማሳየት አልነበረም። ምክንያቱም ብዙውን ጊዜ ስለ ተአምራቱ ለሌሎች እንዳይናገሩ ሰዎችን ያስጠነቅቅ ነበርና። ነገር ግን ኢየሱስ ለዚህች ሴት ስለ ራሱ አንድ ነገር ለማስተማርና ወደ መንፈሳዊ ፈውስም ለመምራት ፈልጎ ነበር። ኢየሱስ ምንጊዜም በሥጋዊ ፈውስ ብቻ ስለማይረካ፥ ለእያንዳንዱ ሰው የመንፈሳዊ ፈውስ ዕድል ለመስጠት ይፈልጋል። ለዚህም ነው ሕዝቡን ሁሉ ከመፈወስ ይልቅ በግለሰብ ደረጃ መፈወስን የመረጠው። ስለሆነም ኢየሱስ ሴቲቱ የተከሰተውን ሁኔታ እንድታምን በማድረግ፥ እምነቷ ሥር እንዲሰድ እያደረገ ነበር። ሴትዮዋ ሥጋዊ ፈውስ ብታገኝም፥ መንፈሳዊ ፈውስና እውነተኛ ሰላምን ማግኘት ያስፈልጋት ነበር። በማርቆስ ወንጌል ኢየሱስ ለፈውስ የተጠቀመው ቃል «መዳን» ከሚለው ጋር ተመሳሳይ ነው። ስለሆነም ሥጋዊ ፈውስ አግኝታ ከመከራዋ የዳነችው ይህች ሴት፥ አሁን ደግሞ መንፈሳዊ ፈውስን አግኝታ ሰላምን ተጎናጽፋለች። በሁለተኛው ታሪክ፥ ኢየሱስ በቀላል የትእዛዝ ቃል የኢያኢሮስን ልጅ ከሞት አስነሥቷል። ከኢየሱስ ጋር ሲነጻጸር ሞት ኀይል ያለው ጠላት አይደለም። በቀላል የትእዛዝ ቃል ሁላችንም ከሞት እንነሣለን። ለዚህም ነው ጳውሎስ ለክርስቲያኖች የሞት መውጊያ እንደ ተሰበረ የጻፈው (1ኛ ቆሮ. 15፡53-56)። በዚህ ታሪክ ውስጥ ሌላም አስገራሚ ነገር ተከስቷል። ኢየሱስ ተአምሩን ለማሳየት ደቀ መዛሙርቱን ሁሉ ከመውሰድ ይልቅ፥ ዮሐንስን፥ ያዕቆብንና ጴጥሮስን ብቻ ወሰደ። ይህ የቀድሞይቱ ቤተ ክርስቲያን ቁልፍ መሪዎች ለሚሆኑት ለእነዚህ ሦስት ደቀ መዛሙርት፥ የሥልጠና ዓይነት ተግባር ነበር። ኢየሱስ ከ12ቱ በላይ በጥልቀት አስተምሯቸዋል። (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ኢየሱስ የሞተች ልጅ አስነሣ፥ የታመመች ሴት ፈወሰ (ማር. 5፡21–43) Read More »

ማርቆስ 5:1-20

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) የሰይጣን ኀይል አይሎ ያየህበትን ጊዜ ግለጽ። ለ) የኢየሱስ ኀይል ሰይጣንን ሲያሸንፍ ያየህበትን ሁኔታ ዓለጽ፡፡ ይህ ስለ ኢየሱስ ምን ያስተምረናል? ሐ) ብዙ ክርስቲያኖች ሰይጣንን፡ ቡዳን፥ እርግማንን የመሳሰሉትን የሚፈሩት ለምንድን ነው? መ) መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ፍርሃት ምን ያስተምራል? የግርማ አባት ጠንቋይ ነበሩ። እርሱ ከልጅነቱ ጀምሮ ለሰይጣን የተሰጠ በመሆኑ ብዙ ክፉ መናፍስት ሰፍረውበት ነበር። እያደገ ሲመጣ የሰይጣን ጭቆና በዛበት። አንድ ቀን ጭንቀቱን መቋቋም ተስኖት ራሱን ለማጥፋት ሞከረ። በዚህ ጊዜ አንድ ክርስቲያን ሕይወቱን አተረፈለት። ክርስቲያኑ በኢየሱስ ክርስቶስ ቢያምን ከሰይጣን ነፃ እንደሚወጣ ገለጸለት፡ ግርማም ምስክርነቱን ሰምቶ አመነ። ወዲያውኑ ክፉ መናፍስት ወደ መሬት ጣሉት። እዚያ ወድቆ ይንፈራፈርና ያጓራ ጀመር። ክርስቲያኑ ወዳጆቹን ሰብስቦ ብዙ ጸሎት ካደረገ በኋላ፥ መናፍስቱ ለቅቀውት ወጡ። በቀጣዩ እሑድ ግርማ በአቅራቢያው ወደምትገኝ ቤተ ክርስቲያን ሄደ። በአምልኮው ጊዜ አንድ ሰው፥ ሰይጣን ታስሮ ወደ ጥልቁ እንዲወርድ እያዘዘ ሲጸልይ ሰማ። ሰዎች፥ «በኢየሱሱሱሱሱሱስ ስም?» እያሉ ይጮኹ ጀመር፡ «ሰዎች የኢየሱስን ስም እንዲህ የሚጠሩት ለምንድን ነው?» ሲል አሰበ። ክርስቲያኖቹ የግርማ አባት ኃይል አላቸው ብሎ የሚያምንባቸውን ቃላት በሚደጋግምበት መንገድ የኢየሱስ ስም ምትሐታዊ ኃይል አለው ብለው ስለሚያምኑ ይሆን? በሌላ ስፍራ ከአንድ ጠንቋይ አጠገብ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት ተከፍቶ ነበር። አንዳንድ ጊዜ ጠንቋዩ ሌሊት ሌሊት ከበሮውን እየመታ በማጓራት ክርስቲያኖችን ይረግም ነበር። በዚህ ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ ት/ቤት ተማሪዎች ይፈራሉ። ከመኝታ ክፍላቸው ተሯሩጠው በመውጣት፥ «በኢየሱሱሱሱስም ስም!» እያሉ ድምፃቸውን አጉልተው ይጮኻሉ፡፡ ኢየሱስ ከሰይጣን ጋር ምን ዓይነት ግንኙነት አለው? እኛ በሰይጣን ላይ ምን ሥልጣን አለን? የኢየሱስ «ስም» ከሥልጣናችን ጋር ምን ግንኙነት አለው? የኢየሱስን ስም እየደጋገሙ መጥራቱ ተጨማሪ ኃይል ይሰጠዋል? ይሄ የሚያጠራጥር አይደለም። የምንፋጠጠው ከሰይጣን፥ ከትልቅ ጠላት ጋር ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ሊውጠን ፈልጎ ከሚያገሳ አንበሳ ጋር ያነጻጽረዋል (1ኛ ጴጥ. 5፡8)። ጎይሉ ከፍተኛ ነው። ተአምራትን መሥራት ይችላል፥ ተፈጻሚነት የሚኖራቸውን እርግማኖችና ሌላም ሊያደርግ ይችላል። ነገር ግን ኢየሱስን በመታዘዝ ከሚመላለሱ ክርስቲያኖች ጋር ሲነጻጸር፥ ጎይሉ ምንድን ነው? ከዚህ በበለጠ ደግሞ ከኢየሱስ ጋር ሊነጻጸር፥ ኀይሉ ምንድን ነው? ለክርስቲያኖች መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረውን እውነት በግልጽ መረዳቱ አስፈላጊ ነው። ልናስወግዳቸው የሚገቡን ሁለት አክራሪ አቋሞች አሉ። ብዙ የተማሩ በተለይም በምዕራቡ ዓለም የሚገኙ ክርስቲያኖች ሰይጣንን ችላ ይላሉ። ሰይጣን መኖሩን ሊያምኑ ቢችሉም፥ ስለ እርሱ አያሳስባቸውም። ዛሬ እንደምንመለከተው ሰይጣን ብርቱ ጠላት ስለሆነ፥ እነዚህ ክርስቲያኖች በእርሱ ተሸንፈዋል። ሰይጣን ክርስቲያኖችን ለማሸነፍ የሚሠራባቸውን መንገዶች የማያውቁትን ክርስቲያኖች በቀላሉ ያጠቃቸዋል። ሌሎች ደግሞ ስለ ሰይጣን ሁልጊዜም ያስባሉ። በሚጸልዩበት ጊዜ ሁሉ ሰይጣን ወደ ጥልቁ እንዲጣል ያዝዛሉ። የሚደርሰው ጉዳት ሁሉ የሰይጣን ጥቃት እንደሆነ ያምናሉ። ብዙውን ጊዜ የሰይጣንን ኀይል ይፈራሉ። እርሱን እየፈሩ ስለሚኖሩ ሰይጣን እነርሱንም አሸንፎአቸዋል። ይህም መንፈሳዊ ሕይወታቸው ጠንካራና በድፍረት የተሞላ እንዳይሆን ያደርገዋል። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሰይጣን ብዙ ያስተምራል። አራት ዐበይት እውነቶችን ማስታወስ አለብን፡ ሀ. ሰይጣን ህልውናው የተረጋገጠ ኀይለኛ ጠላታችን ነው። የእግዚአብሔር መራራ ጠላት ሲሆን፥ ሰዎችን በራሱ የጨለማ መንግሥት ለማቆየት ወይም የእግዚአብሔር መንግሥት አካል የሆኑትን ወገኖች ውጤታማነት ለመቀነስ ተግቶ ይሠራል። ለ. ኢየሱስ በሰይጣን ላይ ሙሉ ሥልጣንና ኀይል አለው። ሰይጣንና አጋንንት ኢየሱስ ማን እንደሆነ ስለሚያውቁ ይፈሩታል (ያዕ. 2፡19)። ይታዘዙታል። በአዲስ ኪዳን ውስጥ እንደተጻፈው ኢየሱስ ከሰይጣን ወይም ከአጋንንት ጋር ሲገናኝ፥ በአንዲት የትእዛዝ ቃል ያሸንፋቸው ነበር። ሐ. ሰይጣን ተሸንፎአል። ኢየሱስ በመስቀል ላይ የኀጢአታችንን ዕዳ በመክፈል ሰይጣን የእግዚአብሔርን ልጆች ለመክሰስ የሚጠቀምበትን ሥልጣን አስወግዷል። በዚያም የፍጻሜያቸውን እርግጠኛነት በማሳየት ምርኮ ወስዷል (ቆላ. 2፡13-15)። በሰይጣን ላይ ዐቢዩን ድል ከተጎናጸፍን በኋላ፥ ሰይጣን የሽንፈት ጦርነት በሚያካሂድበት ዘመን ውስጥ እንኖራለን። ኢየሱስ በዳግም ምጽአቱ ሰይጣንና አጋንንቱን ወደ ሲኦል በመስደድ ሙሉ በሙሉ ያሸንፋቸዋል (ራእይ 20፡7-10)። መ. ክርስቲያኖች “በክርስቶስ” ስለሆንን፥ ጥበቃውና ሥልጣኑ አይለየንም። መንፈሳዊ የጦር ዕቃዎቻችንን እስከ ለበስን ድረስ (አፌ. 6፡10-18 አንብብ)፥ የሰይጣንን ጥቃት መፍራት የለብንም። ሰይጣን አምልኳችንን እንዳይረብሽ ወይም በሕይወታችን ውስጥ ጣልቃ እንዳይገባ፥ እያሰርነው እንድንጸልይ የተሰጠ ትእዛዝ በአዲስ ኪዳን ውስጥ አይገኝም። ትኩረት የተሰጠው መንፈሳዊ የጦር ዕቃዎችን በመልበስ፥ ከሰይጣን ጥቃት የተጠበቅን መሆናችንን በማረጋገጡ ላይ ነው። በብቁ ሁኔታ የታጠቀ ሠራዊት የተሸነፈን ዓማፂ መፍራት የለበትም። እናም ሰይጣንን መፍራት የለብንም። በክርስቶስ ሥልጣን ሥር እስከ ተጠለልን ድረስ ሰይጣንን እናሸንፋለን። በራሳችን ኀይል ብንዋጋ ግን ምንጊዜም አናሸንፍም። “በኢየሱስ ስም” ከታገልነው በራሳችን ላይሆን፥ በክርስቶስ ኃይል እናሸንፋለን። ይሁንና ብዙ ክርስቲያኖች በኢየሱስ ስም እየጸለዩ ሰይጣንን መዋጋት ማለት ምን ማለት እንደሆነ በትክክል አያውቁም። «በኢየሱሱሱሱስ. . . ስም» የሚሉት፥ ስሙን እየጠሩ የሚጮኹት፥ ወይም የኢየሱስን ስም ሦስት ጊዜ የሚጠሩት ለምንድን ነው? ይህ ሁሉ የመጣው መጽሐፍ ቅዱስ በኢየሱስ ስም ስላለን ሥልጣን የሚያስተምረውን ጠንቅቆ ካለማወቅ ነው። «በኢየሱስ ለም» መጸለይ ማለት ምን ማለት ነው? በመጀመሪያ፥ ኀይልን የምናገኘው በኢየሱስ ስም ብለን በመጮኻችን አይደለም። ስለሆነም «በኢየሱሱሉሱስ ስም» ማለቱም ሆነ መጮኹ ወይም ሦስት ጊዜ መደጋገሙ የሚጨምረው ነገር አይኖርም። ስለዚህ የኢየሱስን ስም እንደ ምትሐታዊ ቃል ከመጠቀም መጠንቀቅ አለብን። ይህን በማድረግ ክፉ መናፍስትን ለመቋቋም ክታቦችን ከሚያንጠለጥሉ ሰዎች ጋር እንዳንመሳሰል ልንጠነቀቅ ይገባል። ሁለተኛ፥ በራሳችን ኀይልና ሥልጣን እንደሌለን ለሰይጣን መናገራችን ነው። የጸሎታችንና የትእዛዛችን ሥልጣን ሁሉ የሚመጣው ከክርስቶስ ኀይል ነው። እኛ ያለን በውክልና የተሰጠን ኀይልና ሥልጣን ብቻ ነው። ስለዚህም፥ በኢየሱስ ክርስቶስ የምናምንና ሰይጣንን ለማሸነፍ፥ ከክርስቶስ ሥልጣን የተሰጠን ሰዎች በመሆናችን፥ ሰይጣንን እናዝዘዋለን። (ማስታወሻ፡- ይህ ጸሎታችንን “በኢየሱስ ስም” ብለን ከምንፈጽምበት ሁኔታ ጋር አንድ ዓይነት ፍች አለው። ይህን ስንል ወደ ሁሉን ቻይ አምላክ ለመምጣትና ከእርሱ ዘንድ መልስ ለመጠበቅ የቻልነው፥ ከክርስቶስ ጋር ባለን ግንኙነትና ወደ እግዚአብሔር እንድንመጣ በሰጠን ሥልጣን ምክንያት መሆኑን መግለጻችን ነው። ይህም በእግዚአብሔር ፊት የቀረብነው በራሳችን ጽድቅና የብቃት ስሜት እንዳልሆነ የምንገልጽበት ነው።) የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ሰዎች የኢየሱስን ስም ጮክ ብለው የሚጠሩት ወይም የሚደጋግሙት ለምንድን ነው? ለ) ከላይ ከቀረበው ትምህርት አንጻር፥ ጸሎታችን እንዴት ሊለወጥ ይገባል? ኢየሱስ በሰይጣን ላይ ሙሉ ሥልጣን እንዳለው በግልጽ ከሚያሳዩት ነገሮች አንዱ፥ በጌርጌሴኖን አካባቢ በብዙ ክፉ መናፍስት የተያዘውን ግለሰብ ባዳነበት ሁኔታ ተገልጾአል። ቀደም ብለን እንደተመለከትነው፥ እነዚህ ክፉ መናፍስት ክርስቶስን ለይተው አውቀውታል። ስለዚህም፥ ኢየሱስ “የልዑል እግዚአብሔር ልጅ” እንደሆነ በግልጽ አውጀዋል። ይህም ኢየሱስ ራሱ አምላክ እንደሆነ የሚያመለክት ነበር። ኢየሱስ በእነርሱ ላይ ሙሉ ሥልጣን እንዳለውና እግዚአብሔር ለዘመናት የወጠነው ዕቅድ በሚፈጸምበት ጊዜ፥ ኢየሱስ ወደ ሥቃይ ስፍራ (ሲዖል) እንደሚልካቸው ያውቁ ነበር። ይሁንና፥ የኢየሱስ ጎይል ከሰይጣን ጋር የሚነጻጸረው እንዴት ነው? ኢየሱስ ከሰይጣን የሚበልጠው ትንሽ ብቻ ነው? ማርቆስ የኢየሱስ ኀይል ፍጹማዊ እንደሆነና መጨረሻ በሌለው ሁኔታ ከሰይጣን ኀይል እንደሚለቅ አሳይቷል። በሮም ሠራዊት፥ አንድ ሌጌዎን (ጭፍራ) 6,000 ወታደሮችን ይይዛል። አጋንንት መንፈሳዊ ፍጥረታት ስለሆኑና አካላዊ ስፍራ ስለማይይዙ፥ በዚህ አንድ ግለሰብ ሰውነት ውስጥ 6,000 ክፉ መናፍስት ነበሩ። ነገር ግን ኢየሱስ ይህን የአጋንንት ሠራዊት ምን አደረገው? ፈራቸው? በፍጹም። አጋንንቱ እርሱን እንዳዩ በፍርሃት ተሸበሩ። ወደ ሥቃይ ስፍራ እንዳይልዳቸው ኢየሱስን ለመኑት። ቀላል ትእዛዙን ሰምተው ለመታዘዝ ተገደዱ። ክፋት በባሕርዩ ራሱ ያጠፋል። ይህንኑ ለማሳየት፥ ክፉ መናፍስት ወደ እሪያዎች ገብተው ገደሏቸው። ክፉ መናፍስቱ አልሞቱም ነበር። ነገር ግን የመኖሪያ ስፍራቸው ተወሰደባቸው። በተጨማሪም፥ ማርቆስ ለዚህ የኢየሱስ ታላቅ ተግባር ሁለት የተለያዩ ምላሾችን ያነጻጽራል። አብዛኞቹ ሰዎች ለኢየሱስ ለመገዛትና እርሱን ለማክበር ስላልፈለጉ፥ ከአካባቢያቸው ለቅቆ እንዲሄድ ጠየቁት። በአጋንንት ተይዞ የነበረው ሰውዩ ግን ኢየሱስን ለመከተል ፈለገ። ኢየሱስ ግን ለዚህ ሰው የተሻለ አገልግሎት ሰጠው። ክርስቶስ ግለሰቡ ወደ ቤተሰቡ ተመልሶ እግዚአብሔር ስላደረገለት ምሕረት እንዲመሰክር ነገረው። ከደቀ መዛሙርት የሚጠበቀው ምንድን ነው? ማርቆስ ደቀ መዛሙርት ለሌሎች ስለ ክርስቶስ መመስከር እንዳለባቸው አመልክቷል። ነገር ግን የምስክርነታችን ዋና ነገር ምን መሆን

ማርቆስ 5:1-20 Read More »

ማርቆስ 4፡1-41

ሀ. ክርስቶስ ስለ መንግሥቱ አስተማረ (ማር. 4፡1-34)። እንደ ማቴዎስ ሁሉ፥ ማርቆስም የክርስቶስን ምሳሌዎች በአንድ ክፍል ውስጥ አስቀምጧል። ይህ ማርቆስ ስለ ክርስቶስ ትምህርት ከገለጸባቸው ጥቂት አጋጣሚዎች አንዱ ነው። ክርስቶስ በእርሱ ላለማመን ልባቸውን ያደነደኑት አይሁዶች ፍርድን እንደሚቀበሉ ለማሳየት፥ በምሳሌ እንደሚናገር ለደቀ መዛሙርቱ ተናግሯል። ነገር ግን ለጥሪው ምላሽ ሰጥተው የተከተሉት የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት፥ እውነትን የበለጠ እንዲረዱ በምሳሌ ያስተምራቸዋል። እነዚህ ምሳሌዎች እያንዳንዳቸው በክርስቶስ መንግሥት፣ ሕይወት ምን እንደሚመስል ያስተምራሉ። 1. የአራት ዓይነት መሬት ምሳሌ (ማር. 4፡1-20)። ደቀ መዛሙርቱ የክርስቶስን መልካም የምሥራች ካካፈሉ በኋላ ምን ሊጠብቁ ይገባል? ክርስቶስ ሰዎች በሦስት መንገዶች ምላሽ እንደሚሰጧቸው አስተምሯል። በመንገድ ላይ እንደወደቀው ዘር፥ ከመጀመሪያው ለመቀበል የማይፈልጉ ሰዎች ይኖራሉ። የሚያምኑ መስለው ከቀረቡ በኋላ ችግር ወይም ስደት በደረሰባቸው ጊዜ በጭንጫ መሬት ላይ እንደተዘራው ዘር የሚክዱም ይኖራሉ። አማኞች መስለው ከቀረቡ በኋላ ከደቀ መዝሙርነት ጎዳና ይልቅ የዓለምን መንገድ በመውደዳቸው ምክንያት፥ በእሾህ መካከል እንደተዘራው ዘር ወደ ኋላ የሚመለሱ ሰዎች ይኖራሉ። በአንጻሩ በመልካም መሬት ላይ እንደወደቀው ዘር እምነታቸውን በተለያዩ መንገዶች ሊገልጹ የሚችሉት ጥቂቶች ብቻ ናቸው። የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ሰዎች እነዚህን አራት ምላሾች ሲሰጡ ያየህባቸውን ሁኔታዎች በምሳሌዎች አብራራ። ለ) ለደቀ መዛሙርት እነዚህን አራት መንገዶች ማወቁ ለምን ያስፈልጋል? 2. የመቅረዝ ምሳሌ (ማር. 4፡21-25)። ክርስቶስን ለመከተል የሚፈልጉ ሰዎች የሮም ክርስቲያኖች የሚጋፈጡት ዓይነት ስደት ቢኖርም እንኳ፥ እምነታቸውን ከመደበቅ ይልቅ የእምነታቸው ብርሃን ለሁሉም እንዲያበራ ማድረግ እንዳለባቸው ሊያውቁ ይገባ ነበር። ከሰዎች የተሸሸጉ ምሥጢራዊ ማኅበረሰብ ከመሆን ይልቅ፥ በቃላቸው ብቻ ሳይሆን በሕይወታቸው ጭምር የክርስቶስ መንግሥት ተከታዮች መሆናቸውን ማሳየት ያስፈልጋቸው ነበር። የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት መሆናቸውን ማሳየት ያስፈልጋቸው ነበር። ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱ እርሱን ለመስማትና በሕይወታቸው ውስጥ እውነቱን ተግባራዊ ለማድረግ ባይፈልጉ፥ ፍርድ እንደሚደርስባቸው አስጠንቅቋቸዋል። የክርስቶስን ትምህርት ይበልጥ ተግባራዊ ባደረጉ ቁጥር፥ ተጨማሪ መንፈሳዊ እውነቶችና ግንዛቤዎችን ይሰጧቸዋል። እኛም መንፈሳዊ እውነቶችን ተግባራዊ የማናደርግ ከሆነ፥ መንፈሳዊ እውነቶችን የመገንዘብ ችሎታችን ይቀንሳል። የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ይህ መንፈስ ቅዱስ የሚያስተምረንን ተግባራዊ ማድረግ እንዳለብን የሚያስጠነቅቀን እንዴት ነው? ለ) በቅርቡ መንፈስ ቅዱስ ያስተማረህን ሁለት እውነቶች ግለጽ። እንዴት ተግባራዊ እያደረግህ እንደሆነ አብራራ። 3. የአዳጊ ዘር ምሳሌ (ማር. 4፡26-29)። ይህ ምሳሌ የሚገኘው በማርቆስ ወንጌል ውስጥ ብቻ ነው። ክርስቶስ በዚህ ምሳሌ፥ መንግሥቱና ቤተ ክርስቲያኑ፥ እንደ ዘር በምሥጢራዊ መንገድ በራሷ የማደግ ኀይል እንዳላት አስተምሯል። ሰዎች ዕድገቱ እንዴት እንደሚካሄድ ለመገንዘብ ቢሞክሩም፥ ሁልጊዜም ምሥጢር ይሆናል። 4 የሰናፍጭ ቅንጣት ምሳሌ (ማር. 4፡30-34)። የኢየሱስ መንግሥት፥ ጅማሬዋ ልክ እንደ ኢየሱስና 12ቱ ሐዋርያት፥ አነስተኛ ይመስላል። ኃያል መንግሥት ባላቸው በሮማውያን ዓይን ፊት፥ በጣም አነስተኛና ምንም ያማያሳስብ ሆኖ ታያቸው። ነገር ግን ያቺ አነስተኛ መንግሥት በአስደናቂ መንገድ አድጋ፥ ታላቁ የሮም መንግሥት እንዲለወጥ ታደርጋለች። ቤተ ክርስቲያንም አድጋ፥ ከሮም መንግሥት በበለጠ መልኩ ዓለምን ታዳርሳለች። ለ. ኢየሱስ በተፈጥሮ ላይ ኃይሉን አሳየ (ማር. 4፡35-41)። ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ ከሆነ፥ በፍጥረቱ ላይ ምን ኃይል አለው? ማርቆስ ይህን ታሪክ በመናገር፥ ክርስቶስ በፈጠራት ዓለም ላይ ሙሉ ሥልጣን እንዳለው አመልክቷል። ማዕበሎችና ነፋሳት ሁሉ ለክርስቶስ ቃል ታዝዘዋል። የክርስቶስ ጎይል በደቀ መዛሙርቱ ላይ ከፍተኛ ስሜት በማሳደሩ «ፈሩ»። በተጨማሪም እርሱ ከተራ ሰው የላቀ መሆኑን ስለ ተገነዘቡ፥ ትክክለኛ ማንነቱን ለመረዳት ተገድደው ነበር። ነገር ግን ይህ ታሪክ እካላዊም ሆነ የስደት ማዕበል፥ በክርስቶስ ተከታዮች ላይ እንደሚደርስ ያሳያል። ከዚህ ማዕበል ማምለጥ አይቻልም። በዚህም ጊዜ በፍርሃት ልንኖር ወይም ክርስቶስ ከእኛ ጋር እንዳለ በመገንዘብ በእርሱና ማዕበሉን በመቆጣጠር ችሎታው ልንታመን እንችላለን። የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ስላጋጠመህ አንድ ማዕበል ግላጽ። በዚህ ጊዜ ከምን ዓይነት ልማቶች ጋር ታግለሃል። እምነት ነበረህ ወይስ አልነበረህም? ለ) ለማዕበሉች የምንሰጠው ምላሽ በክርስቶስ ላይ ያለንን የእምነት መጠን የሚያመለክተው እንዴት ነው? (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ማርቆስ 4፡1-41 Read More »

ማርቆስ 3፡7-35

1. የሕዝቡ ክርስቶስን መከተልና የክርስቶስ 12 ተከታዮችን መምረጥ (ማር. 3፡7-19)። ማርቆስ የሕዝቡን አመለካከት ከሃይማኖታዊና የአይሁድ የፖለቲካ መሪዎች አመለካከት ጋር ያነጻጽራል። ይህንንም ያደረገው መሪዎች ክርስቶስን ጠልተው ሊገድሉት ሲፈልጉ፥ ሕዝቡ ግን ከፍልስጥኤም ምድር ሁሉ ሊጎበኘው እንደሚመጣ በማሳየት ነው። ክርስቶስም ወደ እርሱ የሚመጡትን ሰዎች ይረዳ ነበር። ማርቆስ አጋንንት ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ ማወቃቸውን በድጋሚ ገልጾአል። የክርስቶስ ዓላማ ግን ብዙ ሕዝብ እንዲያጅበው ማድረግ አልነበረም። ስለሆነም፥ ከዚያ ሁሉ ሕዝብ 12ቱን መረጠ። «ሐዋርያት» ብሎ ሰየማቸው። ማርቆስ እነዚህ 12ቱ ሐዋርያት በቤተ ክርስቲያን ላይ ሥልጣን እንዳላቸው እያመለከተ ሳይሆን አይቀርም። ሁሉም ክርስቲያኖች የክርስቶስ ተከታዮች ወይም ደቀ መዛሙርት ናቸው። ነገር ግን «ሐዋርያት» ተብለው የተጠሩ ወይም ክርስቶስን ለመወከልና በእርሱ ፋንታ ለማገልገል ሙሉ ሥልጣን የተሰጣቸው ጥቂቶች ብቻ ነበሩ። እንደ ሐዋርያት፥ ክርስቶስ ሲያካሂድ የነበረውን ተግባር የማከናወን፥ ወንጌልን የመስበክና አጋንንትን የማስወጣት ኀይል ተሰጥቷቸው ነበር። ማርቆስ፥ ክርስቶስ ሐዋርያትን የመረጠባቸውን ሁለት ምክንያቶች ጠቅሷል። ከእርሱ ይማሩና ይሠለጥኑ ዘንድ አብረውት ሊሆኑ ይገባ ነበር። በክርስቶስ ፋንታ ለመጠራት ይላኩ ነበር። 2. ኢየሱስ በአጋንንት ላይ የነበረው ኀይል፥ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ መሆኑ መጠን፥ በበለጠ ኃያል መንግሥት እየመሠረተ መሆኑን ያሳያል (ማር. 3፡20-30)። ለሮማውያን ኀይልና ሥልጣን በጣም አስፈላጊ ነገሮች ነበሩ። ሮማውያን ኀይልና ሥልጣን ሁሉ፥ ከንጉሡ እንደሚመነጩና ከእርሱ ጋር በመዛመድ እነዚህን ነገሮች ማግኘት እንደሚቻል ያምኑ ነበር። የክርስቶስ ኃይል የመጣው ከየት ነበር? ማርቆስ የክርስቶስ ኀይል ከሰይጣን እንዳልመጣ ገልጾአል። ምክንያቱም አጋንንትን በሰይጣን ኃይል ማስወጣት እንደ እርስ በርስ ጦርነት የሰይጣንን መንግሥት የሚያፈራርስ ነበር። ነገር ግን የክርስቶስ ኀይል የመነጨው ከመለኮታዊ ንግሥናው ሲሆን፥ የሰይጣንን (የብርቱውን ሰው) መንግሥት በማጥቃትና በማሸነፍ ላይ ይገኛል። 3. ኢየሱስ መንፈሳዊ ቤተሰባችን፥ ከሥጋዊ ቤተሰባችን በላይ አስፈላጊ መሆኑን አስተማረ (ማር. 3፡31-35)። ደቀ መዛሙርቱ ከሚወስኗቸው ነገሮች አንዱ፣ ታማኝነታቸው ለማን እንደሚሆን መወሰን ነው። ማርቆስ፥ ከደቀ መዛሙርቱ በተቃራኒ፥ የክርስቶስ የሥጋ ዘመዶች የአእምሮ በሽተኛ እንደሆነ ማሰባቸውን አሳይቷል (ማር. 3፡20-21)። በክርስቶስና በአገልግሎቱ አልተደሰቱም ነበር። ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን ከቤተሰቡ በላይ የቅርብ መንፈሳዊ ዘመዶቹ አድርጎ ተመለከተ። ብዙውን ጊዜ ሰዎች ሥጋዊ ቤተሰባቸውን ዐቢይ የዋስትናቸው ምንጭ አድርገው በመመልከት፥ የተፈለገውን ዋጋ ከፍለው ቤተሰባዊ ግንኙነቶች በሰላማዊ መንገድ እንዲቀጥሉ ያደርጋሉ። ክርስቶስ ግን ደቀ መዛሙርቱ በእርሱ በማመንና ትእዛዛቱን በመጠበቅ የእግዚአብሔርን ፈቃድ እየፈጸሙ ላሉት ተከታዮቹ፥ ስለ መንፈሳዊ ቤተሰቦቻቸውን የበለጠ ግድ እንዲላቸው አስተምሯቸዋል። የውይይት ጥያቄ፡- ሥጋዊ ቤተሰቦቻችንን ከመንፈሳዊ ቤተሰቦቻችን በምናስበልጥበት ጊዜ፥ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚከሰቱትን ችግሮች ግለጽ። (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ማርቆስ 3፡7-35 Read More »

ማርቆስ 1፡40-3:6

ማርቆስ የክርስቶስን የመጀመሪያ ክፍል አገልግሎት ጠቅለል ባለ ይዘት ያቀረበ ሲሆን፥ አሁን ግን በዝርዝር ማብራራት ይጀምራል። እነዚህ ታሪኮች እያንዳንዳቸው ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነና እንደ ደቀ መዝሙር ከእርሱ ጋር መዛመድ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ለማስተማር የተመረጡ ናቸው። ሀ. ኢየሱስ ለምጻሙን ሰውዩ ፈወሰ (ማር. 1፡40-45)። በጥንት ዘመን ለምጽ በጣም የተፈራ በሽታ ስለነበረ፥ ማርቆስ ክርስቶስ ይህንኑ አደገኛ በሽታ እንዴት በቀላል የትእዛዝ ቃል ሊፈወስ እንደ ቻለ ያሳያል። ክርስቶስ ለምጻሙን በፈወሰ ጊዜ፥ ለማንም እንዳይናገር እንዳዘዘው ማርቆስ አመልክቷል። አሁንም ክርስቶስ በመፈወስ ኃይሉ ዝነኛ ሆኖ ለመታወቅ እየፈለገ አልነበረም፡፡ የተፈወሰው ግለሰብ የተሰጠውን ትእዛዝ ባለመጠበቅ ለሰዎች ሁሉ ስለ ክርስቶስ ኃይል በመናገሩ ብዙ ሰዎች ወደ እርሱ ተሰበሰቡ። ይህም በከተሞች ውስጥ መኖሩን ትቶ ከከተሞች ውጥ እንዲያገለግል አደረገው። ሊ ኢየሱስ ሽባውን ፈወሰው (ማር. 2፡1-12)። ማርቆስ፥ ክርስቶስ አስቸጋሪ በሆነ ሰብአዊ ሁኔታ ላይ ኃይል እንዳለው ለማሳየት ብቻ ሳይሆን፥ ለሌላ ዓላማ ጭምር ሽባውን እንደ ፈወሰ ገልጾአል። (አንድ ሰው ለረዥም ጊዜ ሽባ ሆኖ የቆየ፥ በሕክምና ነርቮቹን ለማዳንና ግለሰቡ እንደገና እንዲራመድ ለማድረግ አይቻልም።) በዚህ ጊዜ ክርስቶስ እንደ እግዚአብሔር ልጅ (ክርስቶስ ራሱን መለኮታዊ «የእግዚአብሔር ልጅ» እያለ መጥራቱን ይመርጥ ነበር [ዳን. 7፡13-14]፥ ኃጢአትን የማስተሰረይ ኀይል እንዳለው ለማሳየት ፈለገ። የበሽታው ምንጩ የግል ኃጢአት ነበር። ስለዚህ ክርስቶስ ኃጢአቱን ይቅር አለው። ኃጢአትን ሊያስተሰርይ የሚችለው እግዚአብሔር ብቻ ነው። ግን ከሰዎች ዓይን የተሰወረ ክስተት በመሆኑ፥ ኀጢአትን ይቅር ለማለት መቻሉን እንዴት ሊያውቁ ይችላሉ? ይህን ሊያውቁ የሚችሉት ክርስቶስ በሽተኛውን ሲፈውስ በማየት ነበር። እግዚአብሔር ኃጢአትን ይቅር የማለት መለኮታዊ ኃይል አለኝ ብሎ በድፍረት የተናገረን ሰው፥ ተአምር እንዲሠራ በማገዝ ሊያከብረው አይችልም። ሒ ኢየሱስ ማቴዎስን (ሌዊን) ደቀ መዝሙሩ እንዲሆን ጠራው (ማር. 2፡13-17)። ወንጌላት ሁሉ የማቴዎስን ለደቀ መዝሙርነት መጠራት ይዘግባሉ። ለዚህ ምክንያቱ ይህ ታሪክ ስለ ክርስቶስና አገልግሎቱ ሁለት ዓበይት ትምህርቶችን የሚያስተምር መሆኑ ነው። በመጀመሪያ፥ ይህ ታሪክ ክርስቶስ እንደ እግዚአብሔር ልጅ ሰዎች ሁሉ ከእግዚአብሔር ጋር ግንኙነት እንዲመሠርቱ ሊጠራ መምጣቱን ያሳያል። አንድ ሰው ሀብታም ወይም ድሀ፥ የተማረ ወይም መሐይም፥ ምርጥ የማኅበረሰቡ አባል ወይም ተራ ማኅበረሰቡ የማያከብረው ወይም ያራቀው ቢሆን ሁሉም ኀጢአትን ሠርተዋል። እውነቱ ይህ ሲሆን፥ ጻድቃን ነን ብለው ያሰቡት ሰዎች ግን የክርስቶስን ጥሪ ተቀብለው ወደ ክርስቶስ አልተመለሱም። የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ብዙውን ጊዜ በኢትዮጵያ «ኃጢአተኞች» ወይም ማኅበረሰቡ የማይቀበላቸው ተብለው የተመደቡትን የኅብረተሰብ ክፍሎች ዘርዝር። ለ) ክርስቶስ ለእነዚህ ለዎች ምን ዓይነት አመለካከት የሚኖረው ይመስልሃል? ሐ ቤተ ክርስቲያንህ ለእነዚህ ሰዎች ምን ዓይነት አመለካከት አላት? አንተና ቤተ ክርስቲያንህ ሁሉንም ዓይነት ሰዎች ወደ ንስሐ ለመጥራት የምትተጉት እንዴት ነው? ሁለተኛ፡ ይህ ታሪክ የክርስቶስ ደቀ መዝሙር መሆን የሚያስከፍለውንም ዋጋ ያሳያል። ማቴዎስ ክርስቶስን ለመከተል ሁሉንም ነገር መተው እንደ ነበረበት ሁሉ፥ በዘመን ሁሉ የሚኖሩ ደቀ መዛሙርት ክርስቶስን ለመከተል የቀድሞ ክፉ ልማዳቸውን፥ ለገንዘብና ለቤተሰብ የነበራቸውን የተዛባ አመለካከት፥ ክርስቶስን የማያስከብር ባሕላቸውን ሁሉ መተውና መለወጥ ነበረባቸው። የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) የክርስቶስ ተከታይ ከሆንህበት ጊዜ አንሥቶ በሕይወትህ ውስጥ የተለወጡት ነገሮች ምንድን ናቸው? ለ) አንዳንድ ክርስቲያኖች አሁንም ያልተላቀቋቸውና ክርስቶስን ከመከተል የሚያደናቅፉአቸው አንዳንድ ነገሮች ምን ምንድን ናቸው? መ. ኢየሱስ ከእግዚአብሔር ጋር ግንኙነት መፍጠር የሚቻልበትን ፍጹም አዲስ መንገድ ለመጀመር እንደ መጣ ገለጸ (ማር. 2፡18-22)። ክርስቶስ ለምን እንደማይጾም የቀረበለትን ጥያቄ ካደመጠ በኋላ ነገሮች አሁን የተለወጡበትን ሁኔታ አብራራ። ጾም እርሱ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር አብሮ በሚኖርበት ጊዜ ሊያከናውነው የሚገባው ተቀዳሚ መንፈሳዊ ተግባር እንዳልሆነ አስተምሯል። ምክንያቱም እርሱ ፍላጎታቸውን እያሟላላቸው በመሆኑ፥ መጾም አያስፈልጋቸውም ነበር። ይህ ለእነርሱ ሙሽራውና ሙሽራይቱ እንደሚደሰቱበት የሰርግ ጊዜ ነበር። ክርስቶስ ዋንኛው አስፈላጊ ነገር መጾም እንዳልሆነና እርሱ ከመጣ በኋላ ነገሮች እንደ ተለወጡ አመልክቷል። ክርስቶስ ከመጣ በኋላ፥ አንድ ሰው ስለ ብሉይ ኪዳን ሕግጋትና ሰው ሠራሽ የፈሪሳውያን ሕግጋት የሚኖረው ግንዛቤ መለወጥ ነበረበት። የክርስቶስ ተከታዮች የብሉይ ኪዳንን የአምልኮ ሥርዓት ማለትም (አርጌ የወይን አቁማዳዎች) እንዲከተሉ ማስገደድ፥ የአዲስ ቃል ኪዳን መንገድ ማለትም (አዳዲስ አቁማዳዎች) የሆነውን የክርስቶስን አምልኮ ከማጥፋት አልፎ፥ የክርስቶስን ትምህርት (አዲስ ወይን) ያበላሽ ነበር። ማርቆስ ይህንን አሳብ ያካተተው በሮም የሚገኙ ክርስቲያኖች አንዳንድ የአይሁድ ክርስቲያኖች የብሉይ ኪዳንን የአምልኮ ሥርዓት ለማስፈጸም የሚያቀርቡትን ውትወታ እንዳይሰሙ ለማስጠንቀቅ ይሆናል። ሠ. የእግዚአብሔር ልጅ የሆነው ኢየሱስ በሰንበት ላይ ሥልጣን አለው (ማር. 2፡23-3፡6)። የአይሁድ የሃይማኖት መሪዎች ክርስቶስን ለማስገደል መፈለጋቸው ሮማውያንን ሳያስገርም አልቀረም። ጥላቻቸው ከምን የመነጨ ነበር? ማርቆስ የችግሩ ምንጩ በቁልፍ ሃይማኖታዊ ጉዳዮች ላይ የነበረው የግንዛቤ ልዩነት መሆኑን ያሳያል። ከእነዚህ ልዩነቶች አንዱ የሰንበት ጉዳይ ነበር። ማርቆስ ይህንኑ የሰንበት ግጭት ለመግለጽ ሁለት ታሪኮችን ተናግሯል። በመጀመሪያው አጋጣሚ፥ ክርክሩ የተነሣው ደቀ መዛሙርቱ እሸት በመቅጠፋቸው ነበር። ይህም አይሁዶች በሰንበት ቀን ምንም ዓይነት ሥራ እንዳይሠራ የሚከለክለውን የብሉይ ኪዳን ሕግ እንደ መተላለፍ አድርገው የሚቆጥሩት ተግባር ነበር። ክርስቶስ ለዚህ ጥያቄ ምላሽ የሰጠው በሁለት መንገዶች ነበር፡፡ በመጀመሪያ፥ በብሉይ ኪዳን ዘመን እግዚአብሔር ለካህናት ብቻ የተፈቀደውን የመገናኛ ድንኳን የመሥዋዕት እንጀራ ዳዊት ሲበላ እንዳልቀጣው ገለጸላቸው። እግዚአብሔር ይህ መንፈሳዊ ሰው በሰንበት ቀን የበለጠ መልካም ተግባር ለመፈጸም ሲል የሕጉን ዝርዝር ጉዳዮች እንዲጥስ ፈቅዶለታል። የክርስቶስ ደቀ መዛሙርትም መንፈሳዊ ስለነበሩ፥ እግዚአብሔር ሕጉን በትንሹ በመተላለፋቸው ሊቀጣቸው አልፈለገም። ለዚህም ምክንያቱ ከእርሱ ጋር የነበራቸው ግንኙነትና ሰንበትን የጣሱት ለመጥፎ ዓላማ አለመሆኑ ነው። ሁለተኛ፣ ክርስቶስ እንደ መለኮታዊ የእግዚአብሔር ልጅ፥ መጥፎውንና ጥሩውን፥ እንዲሁም በሰንበት ቀን ሊሠራ የሚገባውንና የማይገባውን የመወሰን ሥልጣን እንዳለው አስረዳ። የሰንበት ሕግጋት የተሰጡት በሰዎች ላይ ሸክም ለመሆን ሳይሆን፥ ሰዎች እግዚአብሔርን እንዲያመልኩ፥ እርስ በርሳቸው መልካም ግንኙነት እንዲኖራቸውና ከአጣዳፊ የሳምንቱ ሥራ እንዲያርፉ ለማገዝ ነበር። ሁለተኛው ታሪክ ክርስቶስ እጁ የሰለለችውን ሰው በሰንበት ቀን እንደ ፈወሰ ያስረዳል። ሰንበትን ተላልፈሃል ብለው በከሰሱት ጊዜ፥ ክርስቶስ መልካምን ማድረግ መቼም ቢሆን በእግዚአብሔር ፊት ስሕተት ሊሆን እንደማይችል አብራርቷል። ይህ ከልብ ሁኔታና ሰዎችን ከመረዳት ይልቅ በሕግጋት ላይ የማተኮሩ ተግባር ክርስቶስን በጣም አስከፋው። የውይይት ጥያቄ፡ እኛም ከሰዎች ልብ ይልቅ በሕግጋትና ደንቦች ላይ ልናተኩር የምንችልባቸው አንዳንድ መንገዶች ምንድን ናቸው? (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ማርቆስ 1፡40-3:6 Read More »

የኢየሱስ የመጀመሪያ አገልግሎት ማጠቃለያ (ማር. 1:14-39)

እንደ ማቴዎስ ሁሉ፥ ማርቆስ ስለ ኢየሱስ የመጀመሪያ ክፍል ይፋዊ አገልግሎት አልዘገበም። ይህም ኢየሱስ መጥምቁ ዮሐንስ እስከታሰረበት ጊዜ ድረስ በግልጽ አለመሥራቱን የሚያመለክት ይመስላል። ከመጥምቁ ዮሐንስ ጋር እየተፎካከረ አልነበረም። ሀ. የመጀመሪያዎቹ ደቀ መዛሙርት መጠራት (ማር. 1፡14-20)። ኢየሱስ ይፋዊ አገልግሎቱን በጀመረ ጊዜ፥ መልእክቱ ከዮሐንስ ጋር ተመሳሳይና የተለየም ነበር። ዮሐንስ ወደፊት እያመለከተ ሰዎችን ሲያዘጋጅ፡ ኢየሱስ ግን፥ «ጊዜው ደርሷል፤ የእግዚአብሔር መንግሥት ቀርባለች» ብሏል። ኢየሱስ አሁን ስለ ነገሠ፥ በሰዎች ሕይወት ውስጥ ሊገባ ተቃርቦ ነበር፡፡ አንድ ሰው ወደ እግዚአብሔር መንግሥት የሚገባው እንዴት ነው? እንደ ዮሐንስ ሁሉ፥ ክርስቶስም ንስሐ በመግባትና የምሥራቹን ቃል በማመን መሆኑን ተናግሯል። ክርስቶስን መከተል ማለት ምን ማለት እንደሆነ ማርቆስ ለመጀመሪያ ጊዜ ይነግረናል። ስምዖን፥ እንድርያስና ዮሐንስ በእግዚአብሔር እንደ ተጠሩ ሁሉ ክርስቶስ እያንዳንዳችንን እየጠራ ነው፡፡ ደቀ መዛሙርቱ የዓሣ ማጥመጃ መረቦቻቸውንና የቤተሰቦቻቸውን የአኗኗር ዘይቤ ትተው፥ ክርስቶስን እንደ ተከተሉ ሁሉ፥ እኛም ክርስቶስን ለመከተል አሮጌውን አኗኗራችንን መተው አለብን። የውይይት ጥያቄ፡- የክርስቶስ ተከታይ ለመሆን ስትወስን ሕይወትህ እንዴት እንደ ተለወጠ ግለጽ። ለ. ኢየሱስ በአጋንንት ላይ የነበረው ኀይል የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን ያሳያል (ማር. 1፡21-28)። ለማርቆስ፥ የክርስቶስን መለኮታዊ ባሕርይ ጥርት አድርገው የሚያሳዩት ነገሮች አንዱ፥ በአጋንንት ላይ የነበረው ኃይል ነበር። በአጋንንት የተያዘ ሰው ክርስቶስን እንዳየ ወዲያውኑ “ቅዱስ-የእግዚአብሔር ልጅ” እንደሆነ ይናገር ነበር። ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ፥ አጋንንት የክርስቶስን አምላክነት ያውቁ ነበር፡ ስለዚህ የትእዛዝ ቃል ታዝዘውት ከያዟቸው ሰዎች ስለሚወጡ፥ ክርስቶስ በእነርሱ ላይ ሙሉ ሥልጣን ነበረው። ነገር ግን ሰዎችን ያስደነቀው ክርስቶስ በአጋንንት ላይ የነበረው ኀይል ብቻ አልነበረም። የክርስቶስ ትምህርት በጣም የተለየ መሆኑንም ተገንዝበው ነበር። ማርቆስ በዚህ የክርስቶስ የመጀመሪያው ክፍል አገልግሎት ሰዎች መደነቃቸውን በአጽንኦት ጠቅሷል። ክርስቶስ በሙሉ ሥልጣን አዲስ ትምህርት ያስተምር ነበር (ማር. 1፡27)። ክርስቶስ ፈሪሳውያን እንደሚያደርጉት ሁሉ፥ ትምህርቱን ከታወቁ የሃይማኖት መሪዎች እንዳገኘ ሰው፥ በእግዚአብሔር ሥልጣን አስተምሯል። ሐ. ኢየሱስ በበሽታ ላይ የነበረው ሥልጣን የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን መስክሯል (ማር. 1፡29-39)። ማርቆስ ከጴጥሮስ አማት ጀምሮ፥ የትኛውንም በሽታ የመፈወስ ኃይል እንደነበረው አመልክቷል። ማርቆስ ክርስቶስ በአጋንንት ላይ የነበረውን ኀይል እንደገና ገልጾአል። በዚህ ጊዜ ግን ክርስቶስ ከአጋንንት ጋር ስለነበረው ግንኙነት አንድ ነገር ጨምር ጠቅሷል። ይህም ክርስቶስ አጋንንትን በሚያስወጣበት ጊዜ፥ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን በይፋ እንዳይናገሩ ከልክሏቸዋል። ይህ ማርቆስ ካተኮረባቸውና ለየት ካሉ የክርስቶስ ባሕርያት አንዱ ነበር። ክርስቶስ ስለ ማንነቱ ለሰዎች እንዳይናገሩ አጋንንትን የከለከላቸው ለምንድን ነው? ምናልባትም ሁለት ምክንያቶች ነበሩት። በመጀመሪያ፥ ክርስቶስ ዝናንና ክብርን አልፈለገም። እርሱ የፈለገው ሰዎች ትምህርቱን ሰምተው ሕይወታቸውን ከእግዚአብሔር ጋር እንዲያስተካክሉ ነበር። እርሱ ዛሬ ብዙ ሰው ለመሳብ ተአምራትን እንደሚያደርጉና አጋንንትን እንደሚያስወጡ አገልጋዮች አልነበረም። ሁለተኛ፣ ክርስቶስ ከትክክለኛ ምንጭ የመጣ ምስክርነት ነበር የፈለገው፡፡ አጋንንት ስለ ማንነቱ እንዲመሰክሩለት አልፈለገም ነበር። ደቀ መዛሙርቱ የክርስቶስን ታዋቂነት በመደገፍ ተአምራቱንና ፈውሱን ሲያደንቁ ሳሉ፥ ክርስቶስ አጽንኦት የሚሰጠው ለስብከት መሆኑን ገልጾላቸዋል። በአንድ ስፍራ ተወስኖ የሰዎችን ፍላጎት ከማሟላት ይልቅ፥ ብዙ ሰዎች ቃሉን ሰምተው የሚያምኑበትን ዕድል ለመስጠትና ለመንግሥቱ እንዲዘጋጁ ለማድረግ ፈለገ፡፡ ክርስቶስ «እኔ የመጣሁት ለዚሁ ነው» ሲል ተናገረ። ምንም እንኳ ለማኅበረ ምእመኖቻችን እንክብካቤ ማድረግ ቢኖርብንም፥ በማኅበረ ምእመናኑ ላይ ብቻ ማተኮሩ በቂ አይደለም። የቤተ ክርስቲያን ጥሪ ወደ ጠፉት መድረስ ስለሆነ፥ እያንዳንዷ ቤተ ክርስቲያን፥ «ወንጌሉን ላልሰሙት ለማዳረስ ምን እያደረግን ነው?» እያለች ራሷን መጠየቅ አለባት። የውይይት ጥያቄ፡– ሀ) የክርስቶስ የፈውስ አገልግሎትና፥ ስለ ታዋቂነት የነበረው አመለካከት ዛሬ ከሚታየው የብዙ ሰዎች ሁኔታ የሚለየው እንዴት ነው? ለ) ክርስቶስ ይህንን አመለካከት ያሳየው ለምን ይመስልሃል? ሐ) ተደናቂ ስም ለማግኘትና በተአምራት አማካኝነት የሰዎችን ልብ ወደ ራሳችን ወይም ወደ ቤተ ክርስቲያናችን ከመሳብ እንድንቆጠብ ሊያስጠነቅቀን የሚገባው እንዴት ነው? መ) ቤተ ክርስቲያንህ የምእመኖቿን ፍላጎቶች በማሟላት ብቻ ሳትወሰን ወንጌሉን ለሌሎች ለማዳረስ ምን እያደረገች ነው? ክርስቶስ ፍጹም አምላክና ፍጹም ሰው ነበረ። እንደ ሰው፥ ከእግዚአብሔር ጋር የነበረውን ግንኙነት መጠበቅ ያስፈልገው ነበር። ብቻውን የሚሆነው ጠዋት በማለዳ ብቻ በመሆኑ፥ ከሌሎች ሰዎች ተለይቶ ከእግዚአብሔር ጋር ይገናኝ ነበር። ማርቆስ፥ ክርስቶስ ይህንን ማድረግ ካስፈለገው፥ እኛም በበለጠ ማድረግ እንዳለብን ያስተምረናል። ይህንኑ አሳብ የገለጸው ከእግዚአብሔር ጋር ብቻ ጊዜ ማሳለፍ የመንፈሳዊ ሕይወትና አገልግሎት ኃይል ምንጭ ነው ለማለት ነው። (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የኢየሱስ የመጀመሪያ አገልግሎት ማጠቃለያ (ማር. 1:14-39) Read More »

የኢየሱስ ለይፋዊ አገልግሎት መዘጋጀት (ማር. 1፡1-13)

ብዙ ሰዎች በተቻለ ፍጥነት የአመራር ሥልጣን ለመያዝ ይሽቀዳደማሉ። ከዩኒቨርስቲ የሚመረቁ ወጣቶች ሥልጣን ላይ ለመውጣት ይፈልጋሉ። ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤቶች የሚመረቁ ወጣቶች ወዲያውኑ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የኃላፊነትና የሥልጣን ስፍራዎችን እንደሚይዙ ይገምታሉ። ሽማግሌዎች የሚከበሩበት ታሪካዊ የአፍሪካ ባሕል እየሞተ፥ በስፍራው ለትምህርት የሚሰጥ ትኵረት እየተተካ ነው። የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ይህ ለውጥ ሊካሄድ የተመለከትኸው እንዴት ነው? ለ) የተማሩ ወጣቶች አመራር ጠቃሚ ጎኖች ምንድን ናቸው? ሐ) ከችግሮቹ አንዳንዶቹ ምን ምንድን ናቸው? ጥሩ ትምህርት ለሕይወትና አገልግሎት ጠቃሚ መሣሪያ ቢሆንም፥ ለአመራር ከዚያ የበለጠ ዝግጅትን ይጠይቃል። መልካም እመራር ብስለትን ይፈልጋል። ስለ ሕይወት ሁኔታዎች፥ ከሰዎች ጋር ስለሚደረጉ ግንኙነቶች፥ ችግሮችንና አለመስማማቶችን ለማስወገድ በልምድ ማደግ ያስፈልጋል። መንፈሳዊ ብስለት፥ ከክርስቶስ ጋር የቅርብ ግንኙነት ማድረግ፥ የመንፈስ ፍሬ መጨመርና የመንፈሳዊነት ባሕርያት መታየት ይኖርባቸዋል። ዓለም በትምህርትና አመራር ላይ ያለውን አመለካከት፥ እኛ በትሕትናና በአገልጋይነት አመለካከት መተካት አለብን። ክርስቶስ ምድራዊ አገልግሎቱን ቀደም ብሎ ለመጀመር ይችል ነበር። ነገር ግን እግዚአብሔር በብሉይ ኪዳን ብስለትና የአመራር ኀላፊነት ወደ 30 ዓመት አካባቢ እንደሚመጣ አመልክቷል። (ዘኁል. 4፡3 አንብብ።) ስለሆነም፥ ክርስቶስ አገልግሎቱን ለመጀመር 30 ዓመት አካባቢ እስኪሆነው ድረስ ቆየ (ሉቃስ 3፡23)። እኛም ወደ አመራር ሥልጣን ለመውጣት ከመጣር ይልቅ፥ ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ግንኙነት በማሳደግ መንፈሳዊ ባሕርያትን ማጎልበት ይኖርብናል። ከዚያም ዝግጁዎች በምንሆንበት ጊዜ፥ እግዚአብሔር ወደ አመራር ያመጣናል። ሰዎች የእግዚአብሔርን እጅ በሕይወታችን ውስጥ ያያሉ። በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የአመራር ኃላፊነቶችን ይሰጠናል። ከዚህ ውጭ የሆነው ሁሉ የዓለም መንገድ ነው። ይህም ከትዕቢት የመነጨ አመራር የምንሰጥበት በመሆኑ፥ ለእግዚአብሔር ሕዝብ አይስማማም። የውይይት ጥያቄ፡- ማር 1-4 አንብብ። ሀ) ከዚህ ክፍል ስለ ክርስቶስ የምንማራቸው ነገሮች ምን ምንድን ናቸው? ለ) ስለ ደቀ መዝሙርነት ምን እንማራለን? ማርቆስ ኢየሱስ በእግዚአብሔር ከመጠራቱ በፊት በገሊላ እውቅና አግኝቶ እንዳልቆየ አድርጎ በመተረክ፥ ረዥም የዝግጅት ጊዜ እንዳሳለፈ አልጠቀሰም። ስለ ኢየሱስ ልደትም ሆነ የልጅነት ታሪክ ምንም ዓይነት ገለጻ አላቀረበም። ማርቆስ ታሪኩን የጀመረው ኢየሱስ ይፋዊ አገልግሎቱን ሊጀምር አቅራቢያ በተከሰቱት ነገሮች ነው። ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን ለማሳየት ሲል፥ በመጥምቁ ዮሐንስ ታሪክ ጀመረ (ማር. 1፡1)። ማርቆስ ስለ መጥምቁ ዮሐንስ ብዙ ነገር አልነገረንም። ስለ ዮሐንስ የሚያቀርበውን ገለጻ የጀመረው ከብሉይ ኪዳን ነው። ዮሐንስ ሰዎችን ለመሲሑ ለማዘጋጀት ስለሚላከው ስለ «ጌታ መልእክተኛ» በብሉይ ኪዳን የተነገረውን ትንቢት ፈጸመ። ልክ የአውራ ጎዳና ሠራተኞች መንገዱን ጠግነው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት ምቹ እንደሚያደርጉት ሁሉ፥ መጥምቁ ዮሐንስም ሰዎችን «ለጌታ» ለማዘጋጀት ነበር የተላከው። ይህ ትንቢት ክርስቶስን «ጌታ» ብሎ በመጥራት ለክርስቶስ መለኮታዊ ባሕርይ ፍንጭ ይሰጣል። እንደ ብሉይ ኪዳን ነቢይ ለብሶ በመምጣት፥ ዮሐንስ «ለኃጢአት ይቅርታ የንስሐ ጥምቀት» ሰብኳል። ማርቆስ ሰዎች በመጠመቅ የኃጢአት ይቅርታ እንደሚያገኙ አልገለጸም። የዚህ ክፍል ትክክለኛ አተረጓጎም ዮሐንስ ሰዎች ከኃጢአታቸው ንስሐ ስለገቡ ወይም ንስሐ መግባታቸውን ለማሳየት አጠመቃቸው የሚለው ነው። ይህ በልባችን ውስጥ ለተካሄደው ለውጥ ውጫዊ ምልክት ነበር። ምክንያቱም ለመሢሑ መምጣት በመዘጋጀት ከአሮጌው አኗኗራቸው ተመልሰው (ንስሐ ገብተው)፥ እግዚአብሔር ይቅር እንዲላቸው በመጠየቅ ላይ ነበሩ። በአዲስ ኪዳን ዘመን፥ አንድ ሰው የሚጠመቀው ወዲያውኑ ንስሐ እንደገባ ነበር። እነዚህ ሁለቱ እንደ አንድ ተግባር የተያያዙ ነበሩ። ነገር ግን ጥምቀት ብቻውን ሊያድን እንደሚችል የሚገልጽ አሳብ ከአዲስ ኪዳን ውስጥ ልታገኙ አትችሉም። የውይይት ጥያቄ፡- አንዳንድ ወንጌላውያን ጥምቀት እንደሚያድንና ያልተጠመቁ ሰዎች እውነተኛ ደኅንነትን እንዳላገኙ ያስተምራሉ። ከማርቆስ 1፡4 ምን መልስ ትሰጣቸዋለህ? ስለዚህ ለሰዎች እውነቱን ለማስተማር የምትጠቀምባቸው ሌሎች ጥቅሶች የትኞቹ ናቸው? የዮሐንስ ሌላኛው ዐቢይ መልእክት፥ «ለመሢሑ ተዘጋጁ» የሚል ነበር። ዮሐንስ ዝነኛ ነቢይ በመሆኑ፥ ሰዎች ከዓለም ሁሉ እየመጡ ይጎበኙት ነበር። ነገር ቀን ከመሢሑ ጋር ሲነጻጸር፥ ባሪያው ሊሆን እንኳ እንደማይገባው ተናግሯል። በአዲስ ኪዳን ዘመን፥ ከባሪያ ተግባራት አንዱ ጌታው ወደ ቤቱ በሚመለስበት ጊዜ ጫማውን መፍታት ነበር። ዮሐንስ ለሌላ ሰው እንዲህ ዐይነት አገልግሎት ሊሰጥ ስለማይችል ይህም ለኢየሱስ መለኮታዊነት ሌላው ፍንጭ ነው። ዮሐንስ የመሢሑን ታላቅነት ለማጉላት በመንፈስ ቅዱስ እንደሚያጠምቅ ገልጾአል። ማርቆስ እሳትን አለመጥቀሱ አስገራሚ ነው። ምናልባትም በቤቱ ውስጥ በተካሄደው የበዓለ ኀምሳ ሥነ ሥርዓት ላይ የነበረውን ሁኔታ ላያስታውስ አይቀርም። የእግዚአብሔር ልጅነቱን በማረጋገጥ መንፈስ ቅዱስን ለክርስቲያኖች የላከው ክርስቶስ ነበር። የክርስቶስ የእሳት ፍርድ የሚመጣው ገና ወደፊት ስለሆነ አልተጠቀሰም። ኢየሱስ ለይፋዊ አገልግሉቱ ያካሄደው ሁለተኛው ዝግጅት በዮሐንስ መጥመቁ ነበር። ማርቆስ በኢየሱስ ላይ አጽንኦት በመስጠት ታሪኩን ጠቅለል አድርጎ አቅርቧል። በዚህ ጊዜ መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል በኢየሱስ ላይ ከመውረዱም በላይ፥ እግዚአብሔር አብ ኢየሱስ የእርሱ ልጅ መሆኑን በግልጽ አስታውቋል። እግዚአብሔር አብ ኢየሱስን እንደሚወድና በእርሱ ደስ እንደ ተሰኘ ተናግሯል። ኢየሱስ ለይፋዊ አገልግሎቱ ያደረገው ሦስተኛው ዝግጅት መፈተን ነበር። ማርቆስ ይህን ታሪክ ጠቅለል አድርጎ አቅርቧል። መንፈስ ቅዱስ ኢየሱስን ወደ ምድረ በዳ እንደ ወሰደውና በሰይጣን እንደ ተፈተነ አመልክቷል። እዚህ ላይ ማርቆስ አንድ አስገራሚ አሳብ አክሏል። ይኸውም ኢየሱስ በምድረ በዳ ከዱር አራዊት ጋር እንደነበረ የሚያመለክት ነው። ብዙ ምሑራን ይህ ማርቆስ ከጥቂት ጊዜ በኋላ በዱር አራዊት ፊት የሚጣሉትን ክርስቲያኖች ለማበረታታት የጠቀሰው እንደሆነ ይገምታሉ። እግዚአብሔር ኢየሱስን ከዱር አራዊት ጠብቆታል። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ይህ ክርስቲያኖች ሊቋቋሙት የሚገባ ችግር እንደሆን ያውቅ ነበር። (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የኢየሱስ ለይፋዊ አገልግሎት መዘጋጀት (ማር. 1፡1-13) Read More »

የማርቆስ ወንጌል መዋቅርና አስተዋጽኦ

I. የማርቆስ ወንጌል መዋቅር የማርቆስ መጽሐፍ ጴጥሮስ ስለ ክርስቶስ መሢሕነት በሰጠው ምስክርነት ላይ ያማከለ ይመስላል (ማር. 8፡29)። የቀረቡት ተአምራት ሁሉ፥ ሰዎች ክርስቶስ መሢሑ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን እንዲገነዘቡ የታሰቡ ናቸው። ከጴጥሮስ ምስክርነት በኋላ፥ የማርቆስ ወንጌል በመጭው የክርስቶስ ስቅለት ላይ ያተኩራል። ከመጽሐፉ ግማሽ ያህሉ ስለ ክርስቶስ የመጨረሻ ሳምንትና የመስቀል ላይ ሞት ይዘግባል። ሌላው የመጽሐፉ መዋቅር መልክዐ ምድራዊ አቅጣጫ የተከለ ይመስላል። የመጽሐፉ የመጨረሻ አጋማሽ ክርስቶስ በሰሜን ፍልስጥኤም፥ ማለትም በገሊላና አካባቢዋ ባካሄደው አገልግሎት ላይ ሲያተኩር (ማር. 1-8፡30)። ሁለተኛው አጋማሽ ክርስቶስ በኢየሩሳሌም ባካሄደው አገልግሎትና በሞቱ ላይ ያተኩራል (ማር 8፡31-16፡20)። II. የማርቆስ ወንጌል አስተዋጽኦ የማርቆስ ወንጌልን አስተዋጽኦ በብዙ መንገዶች መመልከት ይቻላል። የሚከተለው አንድ መንገድ ነው። 1. የእግዚአብሔር ልጅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ለይፋዊ አገልግሎት መዘጋጀት (ማር. 1፡1-5) 2. ኢየሱስ በገሊላና በሰሜን የእግዚአብሔር ልጅነቱን ማሳየቱ (ማር. 1፡16-8፡26) ሀ. ኢየሱስ አገልግሎቱን በገሊላ መጀመሩ (ማር. 1፡16-3፡6) ለ ኢየሱስ በገሊላ ያካሄደው የኋለኛው አገልግሎት (ማር. 3፡7-6፡29) ሐ ኢየሱስ አገልግሎቱን ከገሊላ ውጭ ማስፋፋቱ (ማር. 6፡30-8፡26) 3. የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ክርስቶስ መሢሑ፥ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን ተገነዘቡ (ማር. 8፡27-30) 4. ኢየሱስ ለመሞት ወደ ኢየሩሳሌም ተጓዘ (ማር. 8፡31-10፡52) 5. የእግዚአብሔር ልጅ የሆነው ኢየሱስ በኢየሩሳሌም ማገልገሉ (ማር. 11፡1-13፡37) 6. ኢየሱስ በስቅላት መሞትና መነሣቱ (ማር. 14-16) (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የማርቆስ ወንጌል መዋቅርና አስተዋጽኦ Read More »

የማርቆስ አንዳንድ ልዩ ገጽታዎች

1. ማርቆስ ሰዎች ለኢየሱስ በሚሰጧቸው ምላሾች ላይ ያተኩራል። ሀ. መጥምቁ ዮሐንስ የኢየሱስን የጫማ ክር መፍታት እንደማይገባው ባሪያ አድርጎ ራሱን ተመለከተ (ማር. 1፡7)። ለ. የኢየሱስን ቃል የሰሙ ሰዎች በሥልጣን በማስተማሩ ተደንቀዋል (ማር. 1፡27፤ 6፡2፤ 10፡24)። ሐ. ሰዎች ኢየሱስ በፈጸማቸው ተአምራት ተደንቀዋል (ማር. 2፡12፤ 6፡5) መ. ምንም እንኳ መጥምቁ ዮሐንስ፥ አጋንንት፥ አሕዛብና አንዳንድ አይሁዶች የኢየሱስን ልዩ መሆን ቢገንዘቡም፥ የሃይማኖት መሪዎች ሊያምኑበት አልፈለጉም። 2. የማርቆስ ታሪክ በኢየሱስ ሞት ላይ ያተኩራል። ማርቆስ የኢየሱስን ጠቅላላ አገልግሎት የሚሸፍን 10 ምዕራፎች የጻፈ ሲሆን፥ 6 ምዕራፎች ስለ መጨረሻው ሳምንትና የኢየሱስ ሞት ይነግሩናል። 3. ማርቆስ ተግባራዊ ወንጌል በመባል ይታወቃል። በብዛት ከሚጠቀምባቸው ቃላት አንዱ «ወዲያው» የሚለው ሲሆን፥ ከ40 ጊዜ በላይ ተጠቅሷል (ለምሳሌ፥ 1፡12፥ 18፥ 20፥ 23፤ 6፡45፥ 50፤ 9፡20)። ይህም ታሪኩ ወደፊት እንደሚንቀሳቀስና የክርስቶስ ሕይወት እንዴት በፍጥነት ወደ ሞቱ እንዳመራ ያመለክታል። የክርስቶስ ሞት በአጋጣሚ የተከሰተ ሳይሆን፥ በእግዚአብሔር የታቀደ ነበር። ሌሎች ወንጌላት የክርስቶስ አገልግሎት ከሦስት ዓመታት በላይ እንደተካሄደ ሲያመለክቱ፥ ማርቆስ ግን ግልጽ የሆነ የጊዜ ገደብ አልጠቀሰም። በመጽሐፉ ውስጥ የሚገኙ ታሪኮች ሁሉ በአንድ ዓመት ውስጥ ሊከናወኑ ይችላሉ። ይህም የሆነው ለማርቆስ ታሪኩን ፈጠን ፈጠን አድርጎ ማቅረቡ ከሕይወት ታሪካዊና ቅደም ተከተላዊ አተራረክ የበለጠ ተመራጭ ሆኖ በመገኘቱ ነው፡፡ ማርቆስ፥ ታሪኮቹ አጫጭርና ፈጣን እንዲሆኑለት በማሰብ እንደ ሉቃስና ማቴዎስ ዝርዝር ገለጻዎችን አስወግዶ፥ ጠቅለል ባለ መልኩ ያቀርባቸዋል። ማርቆስ የክርስቶስን መምህርነት ቢጠቅስም ከክርስቶስ ምሳሌዎች ብዙዎቹን አላሰፈረም። ከአንድ የበለጠ ዐቢይ የማስተማሪያ ክፍልም በመጽሐፉ ውስጥ አልተጠቀሰም። 4. ማርቆስ፥ ኢየሱስ “የእግዚአብሔር ባሪያ” በመሆኑ ጉዳይ ላይ አጽንኦት ሰጥቷል (ማር. 10፡45)። (ማቴዎስ ግን የክርስቶስን ንጉሥነት አመልክቷል፡፡) የእግዚአብሔር ባሪያ እንደ መሆኑ መጠን፥ ለሰዎች የእግዚአብሔርን መንገድ አስተምሯል (ማር 1፡4-5፡ 21-27፥ 38)። ኢየሱስ፥ እንደ እግዚአብሔር ባሪያ፥ ለሕዝቡ ራርቶ ተአምራትን አድርጓል (ማር. 1፡32-34)። 5. ማርቆስ፥ ክርስቶስ በተደጋጋሚ ሕዝቡ ያደረገላቸውን ወይም የነገራቸውን ነገር ለሌሎች እንዳያወሩ ማዘዙን ገልጾአል (ማር. 1፡34፥ 44፤ 3፡12፣ 5፡43፤ 7፡36-37)። ይህንን ያደረገው በሦስት መንገዶች ነው። መጀመሪያ፣ አጋንንት ማንነቱን እንዳይናገሩ አዝዟቸዋል። የተናገሩት እውነት ቢሆንም እንኳ የጠላቱን ምስክርነት አልፈለገም ነበር። ሁለተኛ፥ ብዙውን ጊዜ የፈወሳቸው ሰዎች ያደረገላቸውን ነገር ለሌሎች እንዳይናገሩ አዞል። ሰዎች ለተሳሳተ ዐላማ እንዲከተሉት አልፈለገም ነበር። በተጨማሪም፥ የፈውስ አገልግሎቱ ሰዎችን ወደ ንስሐ ከመጥራቱና ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ከማስተማሩ ቀዳሚ አገልግሎት እንዲያስተጓጉለው አልፈለገም ነበር። ሦስተኛ፣ አንዳንድ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ መሢሕነቱን ለሰዎች እንዳይናገሩ ያዝዛል። ምናልባትም ሞቶ ከመነሣቱ በፊት ደቀ መዛሙርቱ ምን ዓይነት መሢሕ እንደሆነ በትክክል አያውቁም ነበር (ማር. 8፡20-30፣ 9፡9-10)። 6. ከማርቆስ ታሪኮች ከ90 በመቶ የሚበልጡት በማቴዎስ ወይም በሉቃስ ውስጥ ይገኛሉ። ስለዚህ በሌሎቹ ወንጌላት የማይገኙት ምንባቦች እጅግ ጥቂቶች ናቸው። 7. ምሑራን የማርቆስ ወንጌል የት ላይ ያበቃል በሚለው ጥያቄ ላይ ይከራከራሉ። የተለያዩ ጥንታዊ ቅጂዎች መጽሐፉ በማርቆስ 16፡8 ላይ እንደሚያበቃ ይስማማሉ። ነገር ግን ከ16፡8 በኋላ መጽሐፉ የሚያበቃባቸው የተለያዩ መንገዶች አሉ። አንዳንድ መዛግብት 9 ቁጥርን ሲጨምሩ፥ ሌሎች ደግሞ ከ9-20 ያሉትን ቁጥሮች ይጨምራሉ። አብዛኛቹ ምሑራን ማርቆስ 16፡9-20 በመጀመሪያው መጽሐፍ ላይ ያለ አይመስላቸውም። የመጀመሪያው መጽሓፍ ቁጥር 8 ላይ እንዳበቃ ያስባሉ። አንዳንድ ምሑራን የማርቆስ ወንጌል የመጀመሪያው ማጠቃለያ ስለ ጠፋ፥ የኋለኞቹ ጸሐፊዎች ጥሩ አጨራረስ እንዲኖረው ለማድረግ፥ ከ9-20 ያሉትን ቁጥሮች እንደ ጨመሩ ያስባሉ። የዚህ ክፍል እስትንፋሰ እግዚአብሔር መሆኑ አጠራጣሪ ስለሆነ፥ ሥነ መለኮታችንን ከዚህ ላይ ከመመሥረት መቆጠብ ይኖርብናል። በማርቆስ 16፡18 መሠረት፥ አንዳንድ የተሳሳቱ ምዕራባውያን ክርስቲያኖች ቢነድፉኝም አልሞትም በማለት እባቦችን ይዘው ወደ ቤተ ክርስቲያን ይመጣሉ። (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የማርቆስ አንዳንድ ልዩ ገጽታዎች Read More »