የሐዋርያት ሥራ

የኢየሩሳሌሙ ጉባኤ ስለ ብሉይ ኪዳን ሕግ ሚናና ስለ አሕዛብ ተወያየ (የሐዋ. 15፡1-35)

በአስተምህሮ ጉዳዮች ላይ ከፍተኛ የአሳብ ልዩነት በሚከሰትበት ጊዜ፥ ቤተ ክርስቲያን ምን ልታደርግ ይገባል? መሪዎች ችግሩ በራሱ ጊዜ ይፈታል ብለው ዝም በማለት መጠባበቅ አለባቸው ወይስ ጥቂት መሪዎች ብቻቸውን በጉዳዩ ላይ ውሳኔ መስጠት አለባቸው? የውሳኔው መሠረት ምን መሆን አለበት? የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን በዚህ ጉዳይ ላይ ያደረገችው ምንድን ነው? በአሁኑ ጊዜ ተሰሚነት ያላቸው ሰዎች የሚሰጡት አስተያየት ምንድን ነው? የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን የአሳብ ልዩነቶችን የፈታችው እንዴት ነው? የጥንቷን ቤተ ክርስቲያን ያሳሰባት የመጀመሪያው ዐቢይ ችግር ሰው ለመዳን ምን ማድረግ አለበት? የሚለው ጥያቄ ነበር፡፡ አንድ ሰው ለመዳን የብሉይ ኪዳንን ሕግጋት ሙሉ በሙሉ መከተል አለበት? እግዚአብሔር ይቀበላቸው ዘንድ አሕዛብ መገረዝና የአይሁድን እምነት መቀበል አለባቸው? በብሉይና በአዲስ ኪዳን መካከል በነበረው ዘመን መገረዝ ለአይሁዶች የእግዚአብሔር ሕዝብ ለመሆናቸው እንደ ትልቅ ምልክት ይወሰድ ነበር። ስለሆነም፥ አይሁዶች መገረዝ ለድነት (ለደኅንነት) አስፈላጊ ነው ብለው ያምኑ ነበር። ቤተ ክርስቲያን እያደገች ስትመጣ ብዙ ካህናት በክርስቶስ እንዳመኑ ቀደም ሲል ተመልክተናል (የሐዋ. 6፡7)። ከእነዚህም መካከል የብሉይ ኪዳንን ሕግጋትና በየዘመኑ በአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች የተሰጡትን ደንቦች አጥብቀው የሚከተሉ ፈሪሳውያን ይገኙበት ነበር (የሐዋ.15፡5)። እነዚህ የአይሁድ ክርስቲያኖች አንድ ሰው የሚድንበት ብቸኛው መንገድ ልክ እንደ አይሁዶች በመገረዝና የብሉይ ኪዳን ሕግጋትን በመጠበቅ ነው ብለው ያስቡ ነበር። አሕዛብ በክርስቶስ ከማመናቸው በተጨማሪ ድነትን (ደኅንነትን) ለማግኘት ሕግጋትንም መጠበቅ እንደሚገባቸው ገለጹ። በእነርሱ አስተሳሰብ ከእግዚአብሔር ጋር ግንኙነት ማድረግ የሚቻለው በክርስቶስ ከማመን በተጨማሪ የብሉይ ኪዳንን ሕግጋት በመጠበቅ ነበር። ከእነዚህ አጥባቂ ክርስቲያኖች አንዳንዶቹ ከኢየሩሳሌሟ ቤተ ክርስቲያን 150 ኪሎ ሜትር ርቃ ወደምትገኘው ወደ አንጾኪያ ሄደው ነበር። የአሕዛብ ቁጥር ብዙ በሆነበት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ አሕዛብ ሙሉ ክርስቲያኖችና እግዚአብሔር የሚቀበላቸው አማኞች ለመሆን ከፈለጉ፣ የአይሁድን እምነት ተቀብለው መገረዝና የብሉይ ኪዳንን ሕግጋት መጠበቅ አለባቸው በማለት ማስተማር ጀመሩ። ለአሕዛብ ሐዋርያ የነበረው ጳውሎስ እንዲሁም በርናባስ፥ ድነት (ደኅንነት) በክርስቶስ ብቻ እንደሚገኝ በመግለጽ ይህንን ትምህርት አጥብቀው ተቃወሙ። ከእግዚአብሔር ጋር ኅብረት ለማድረግ፥ አሕዛብ የአይሁድን እምነት መቀበል አያስፈልጋቸውም ነበር። ይህም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ መከፋፈልን ፈጠረ። አንዳንዶች ከአይሁድ ክርስቲያኖች ጎን ሲሰለፉ፣ ሌሎች ከጳውሎስና ከበርናባስ ጎን ተሰለፉ። የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎች ይህ ነገረ መለኮታዊ ጉዳይ ትልቅ ችግር እንደሆነ ተገነዘቡ። ስለሆነም፥ ጳውሎስና በርናባስ በኢየሩሳሌም ወደምትገኝ እናት ቤተ ክርስቲያን ተመልሰው እግዚአብሔር ኃይልን ከሰጣቸው ሐዋርያት ጋር በመሆን የእግዚአብሔርን ፈቃድና የቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ እንዲወስኑ አደረጉ። ይህ የኢየሩሳሌም ጉባኤ፥ ቤተ ክርስቲያን በመጀመሪያዎቹ ሦስት ምእተ ዓመታት ውስጥ ካካሄደቻቸው በርካታ ነገረ መለኮታዊ ሙግቶች የመጀመሪያው ነበር። ይህ ሙግት የድነትን (የደኅንነትን) መንገድ የሚመለከት ነበር። ጥያቄ:- ሀ) ቤተ ክርስቲያን አንድ ሰው ከእግዚአብሔር ጋር ኅብረት ለማድረቅ የሚችልበትን መንገድ በተመለከተ፥ ግልጽ አቋም መያዝ ያለባት ለምንድን ነው? ለ) አንዳንድ ጊዜ በሰዎች ሕሊና ውስጥ ስለ ድነት (ደኅንነት) መንገድ፣ ስለ ተወሰኑ ሕጎችና ደንቦች ውዥንብር ይፈጠራልን? እንዲህ ዓይነቱን ውዥንብር ስለተመለከትህበት ሁኔታ አብራራ። ሐ) የአንጾኪያ ቤተ ክርስቲያን ሽማግሌ ብትሆን ኖሮ፥ ድነት (ደኅንነት) የሚገኘው በክርስቶስ በማመን እንጂ ባሕልን በመለወጥ ወይም የብሉይ ኪዳንን ደንቦች በመጠበቅ እንዳልሆነ የሚያመለክተውን እውነት እንዴት ታሳይ ነበር? ዛሬ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ነገረ መለኮታዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ አያሌ የአሳብ ልዩነቶች ይከሰታሉ። በሥላሌ፥ በመንፈስ ቅዱስ፣ በልሳን፣ በተአምራት፥ በብዝሃ ጋብቻ፥ በአምልኮ ስልቶችና በመሳሰሉት ጉዳዮች ላይ ያሉት ግንዛቤዎች የተለያዩ ናቸው። እነዚህን ልዩነቶች ቸል ከማለት ይልቅ ቤተ ክርስቲያን ጉዳዩን በማንሣት በግልጽ መወያየት ይኖርባታል። የጥንቷን ቤተ ክርስቲያን አርአያ በመከተል ነገረ መለኮታዊ ልዩነቶቻችንን ስለምናስተናግድበት መንገድ ጠቃሚ ነጥቦችን ልንመለከት እንችላለን። ሀ. ክርስቲያኖች ሁሉ እግዚአብሔር ስለሚሠራበት መንገድ እንዲሰሙ የተደረገበት ጠቅላላ ስብሰባ ተካሄደ። ጳውሎስና በርናባስ በሄዱባቸው ስፍራዎች ሁሉ እግዚአብሔር በአሕዛብ መካከል ቤተ ክርስቲያኑን ስለሚመሠርትበት ሁኔታ ሪፖርት አቅርበዋል። በዚህ ጠቅላላ ስብሰባ ላይ አንዳንዶች፣ አሕዛብ መገረዝ አለባቸው የሚል አመለካከት ሲያንጸባርቁ ነገረ መለኮታዊ ጉዳዩ በግልጽ ተብራርቷል። ጳውሎስና በርናባስ የእነዚህን ወገኖች አሳብ በመቃወም፥ አሕዛብ ለመዳን በክርስቶስ ማመን ብቻ እንደሚበቃቸው ሳይገልጹ አላለፉም። ለ. የቤተ ክርስቲያን መሪዎች (ሐዋርያትና ሽማግሌዎች) ለብቻቸው ተሰበሰቡ፡፡ ሰፋ ያለ ነገረ መለኮታዊ እውቀት የሌላቸው ምእመናን አንዳንድ ውስብስብ ነገረ መለኮታዊ ልዩነቶችን ላይረዱ ይችላሉ። ስለሆነም፥ መጽሐፍ ቅዱስን በሚገባ የሚያውቁና የእግዚአብሔርን መንጋ የመምራት ኃላፊነት ያላቸው ወገኖች፥ ጊዜ ወስደው ጉዳዩን በጥልቀት መመርመር ይኖርባቸዋል። ሐ. መሪዎቹ የእግዚአብሔርን አሠራር ታሪክ መረመሩ፡፡ የቀድሞውን ተሞክር ዘወር ብለው ተመለከቱ። ጴጥሮስ እግዚአብሔርን ላመኑት አሕዛብ ሳይገረዙ መንፈስ ቅዱስን ስለተቀበሉበት ሁኔታ አብራራ። እግዚአብሔር ለአሕዛብ በክርስቶስ ማመናቸው ከእነርሱ ጋር ግንኙነት ለማድረግ በቂ እንደሆነ አሳይቶ ነበር። አይሁዶችም ቢሆኑ ብሉይ ኪዳንና የአይሁድ ሥርዓት ለአንድ ሰው ሸክሙ እንጂ ወደ እግዚአብሔር እንደማያቀርቡት ያውቃሉ፡፡ ሥርዓቶቹን ሙሉ በሙሉ ለመፈጸም እንደማይቻል ያውቃሉ። ስለሆነም፥ ጴጥሮስ፥ «በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ እንደ እነርሱ ደግሞ እንድን ዘንድ እናምናለን» (የሐዋ. 5፡11) ሲል በሕይወቱ ያየውን እውነት ጠቅሷል፡፡ መ. ሁለቱም የወንጌል መልእክተኞች የወቅቱን ሁኔታና የእግዚአብሔርን እጅ መገለጥ ተናገሩ። ጳውሎስና በርናባስ እግዚአብሔር በአሕዛብ መካከል ተአምራት በመሥራት እምነታቸውን እንደ ተቀበለው አስረዱ። (በእናት ቤተ ክርስቲያናቸው በኢየሩሳሌም፥ ሉቃስ የበርናባስን ስም ከጳውሎስ ማስቀደሙን ልብ በል። የኢየሩሳሌም ቤተ ክርስቲያን በርናባስን ታውቀውና ታከብረው ስለነበርም በርናባስ ዋነኛው ቃል አቀባይ ሆነ።) ሠ. መጽሐፍ ቅዱስን መረመሩ። የኢየሱስ ወንድም የነበረውና በዚህ ጊዜ የኢየሩሳሌሟ ቤተ ክርስቲያን ዋነኛ መሪ የነበረው ያዕቆብ፥ ጴጥሮስ፥ በርናባስና ጳውሎስ የተናገሩት አሳብ እግዚአብሔር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተናገረው ጋር እንደሚስማማ አረጋገጠ። መጽሐፍ ቅዱስ አሕዛብ ወደ እግዚአብሔር ስለሚመጡበትና ከአይሁድ ጋር እኩል ስፍራ ስለሚያገኙበት ዘመን ተንብዮ ነበር። ብሉይ ኪዳን አሕዛብ በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት በመጀመሪያ የአይሁድን እምነት መቀበል እንዳለባቸው አልተናገረም። ረ. ውሳኔው። የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ውሳኔ የመጣው በሁለት ደረጃ ነበር፡፡ አንደኛው፥ መሪዎቹ የቤተ ክርስቲያንን እምነት በግልጽ በመዘርዘር፣ ድነት (ደኅንነት) የሚገኘው በክርስቶስ በማመን እንጂ በውጫዊ የግዝረት ሥርዓት ወይም የአይሁድን እምነት በመቀበል እንዳልሆነ አስረዱ። በክርስቶስ ከማመን በተጨማሪ ሌላ ሥርዓት መደንገግ ወንጌሉን እንደሚለውጥና ይህም በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት ያለው መዳን ሊሆን አይችልም። ማንም ሰው በራሱ ጥረት ከእግዚአብሔር ጋር ግንኙነት ለማድረግ አልቻለም፡፡ ይህ ክርስቶስ በመስቀል ላይ በፈጸመው ሥራ ብቻ በመደገፍ የሚገኝ ነው። ዛሬ ብዙ ክርስቲያኖች በዚህ እምነት ላይ ይታገላሉ። አንዳንድ ጊዜ ክርስቲያኖች ወንጌሉን እያብራሩ ሳለ «በክርስቶስ ስታምንና መጠጥ ስታቆም ትድናለህ» ይላሉ። በወንጌሉ ላይ ሰው ሠራሽ ሥርዓት በመጨመር ወደ እግዚአብሔር የሚያስኬደውን መንገድ የሰው ሥራ ያደርጉታል። አንዳንድ ወንጌላውያን ለዘላኖች በሚመሰክሩበት ጊዜ፥ «በክርስቶስ በማመን፥ ልብስ በመልበስ እንደ ሌሎች ደገኛ ኢትዮጵያውያን በመኖር፥ እርሻ በማረስና ተጨማሪ ሚስቶችህን በመፍታት በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት ታገኛለህ» ይላሉ። በወንጌሉ ላይ የራሳቸውን ትምህርት በመጨመር ወንጌሉን ይለውጡታል። በዚህም ሰው ከእግዚአብሔር ጋር የሚገናኘው በሥራ እንጂ በእምነት እንዳልሆነ ያስተምራሉ። የውይይት ጥያቄ፡- ብዙ ክርስቲያኖች ድነት (ደኅንነት) በክርስቶስ በማመን ሳይሆን፥ እነርሱ በሚፈጽሙት ተግባር እንደሚገኝ በማሰብ ግራ ሲጋቡ የተመለከትኸው እንዴት ነው? ሁለተኛው፥ ሐዋርያቱ አይሁድና አሕዛብ በሚገኙበት ቤተ ክርስቲያን አንድነትን ለማምጣት አንዳንድ ደንቦችን አወጡ። እነዚህም ሁለት ዓይነት ደንቦች ነበሩ። እግዚአብሔር በየትኛውም ዘመን ከሚኖር ሕዝቡ የሚጠብቃቸው ሁሉን አቀፍ ትእዛዛት አሉ። ዝሙት የአሕዛብ ሕይወትና አምልኮ አካል ስለነበር፣ ያዕቆብ አሕዛብ የእግዚአብሔርን ሕግ በመታዘዝ ከዝሙት መራቅ እንዳለባቸው ገለጸ። ይህ ክርስቲያኖች ሁሉ ከዝሙት መራቅ አለባቸው የሚለው ጉዳይ በብሉይም ሆነ በአዲስ ኪዳን የተጠቀሰ በመሆኑ፥ በየትኛውም ዘመን ያሉ ክርስቲያኖችን የሚመለከት ትእዛዝ ነው፡፡ የሚያሳዝነው ታዲያ ዛሬ፥ ለዚህ የማይለወጥ የእግዚአብሔር ትእዛዝ የይገዙ ብዙ ክርስቲያኖች አሉ። አሕዛብ ከፍቅር የተነሣ አይሁዳውያን ወንድሞቻቸውንና እኅቶቻቸውን ላለማስቀየም ብለው የሚጠብቋቸው ደንቦች ነበሩ። እነዚህም የሚከተሉት ናቸው። ሀ. ለጣዖት የተሠዋ ሥጋ አለመብላት። አሕዛብ በግ ወይም በሬ ወደ ቤተ ጣዖት መውሰድ፥ ለቤተ ጣዖቱ አምላክ አሳልፎ መስጠትና ማረድ ልማዱ ነበራቸው። ከሥጋው የተወሰነው ለጣዖቱ

የኢየሩሳሌሙ ጉባኤ ስለ ብሉይ ኪዳን ሕግ ሚናና ስለ አሕዛብ ተወያየ (የሐዋ. 15፡1-35) Read More »

የጳውሎስ አገልግሎት በኢቆንዮን፥ በልስጥራንና በደርቤን እና የጳውሎስና በርናባስ ወደ አንጾኪያ መመለስ (ሐዋ. 14፡1-28)

የጳውሎስ አገልግሎት በኢቆንዮን፥ በልስጥራንና በደርቤን (ሐዋ. 14፡1-20) ሉቃስ ለሦስት ዓመት ያህል የዘለቀውን የጳውሎስንና የበርናባስን አገልግሎት ያቀረበው አጠር ባለ ዘገባ ነው። ኢቆንዮን ከአንጾኪያ 100 ኪሎ ሜትር ርቃ የምትገኝ ከተማ ናት። ጳውሎስ በምኩራብ ለአሕዛብ ወንጌልን ከሰበከ በኋላ፥ ብዙ ሰዎች በክርስቶስ አመኑ ተቃውሞ ቢገጥማቸውም ጳውሎስና በርናባስ በዚያ ለተወሰነ ጊዜ ተቀመጡ። ሉቃስ በዚህ ስፍራ ተአምራት ከተፈጸሙበት ምክንያቶች ውስጥ አንዱን ገልጾአል። “ምልክትና ድንቅ በእጃቸው ይደረግ ዘንድ እየሰጠ ለጸጋው ቃል ስለመሰከረው ስለጌታ ገልጠው እየተናገሩ ረጅም ወራት ተቀመጡ” ብሏል (የሐዋ. 14፡3)። ነገር ግን አይሁዶች አሁንም ከባለሥልጣናት ጋር ያላቸውን ዝምድና ተጠቅመው አሕዛብን በጳውሎስና በርናባስ ላይ አስነሡ። ስደቱ እየጠነከረ ሲመጣ ወንጌላውያኑ ከኢቆንዮን 30 ኪሎ ሜትር ያህል ርቃ ወደምትገኘው ወደ ልስጥራን ሄዱ። አንዳንድ ጊዜ ጳውሎስና በርናባስ ስደት ከመነሣቱ በፊት ከአካባቢው ሲርቁ፥ ሌላ ጊዜ ግን (ለምሳሌ በደርቤ) እዚያው ቆይተው ስደቱን ሲቋቋሙ መመልከት አስገራሚ ነበር። ክርስቲያኖች ስደትን የሚመለከቱት በአንድ መንገድ ብቻ አይደለም። አንዳንድ ጊዜ ከስደቱ መሰወር፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ስደቱን በጽናት መጋፈጥ ሊያስፈልግ ይችላል። መንፈስ ቅዱስ ለእያንዳንዱ አማኝ የትኛውን እርምጃ መውሰድ እንዳለበት ይመራዋል። ስለዚህ በስደት ውስጥ በሚያልፉ ሰዎች ላይ ተገቢ ያልሆነ ነገር ከመናገር መጠንቀቅ አለብን፡፡ ቁም ነገሩ እግዚአብሔርን መታዘዙ እንጂ፥ በሕይወት መኖሩ አይደለም፡፡ በልስጥራን ጳውሎስና በርናባስ እንደ ልማዳቸው ወደ ምኩራብ እንደ ሄዱ ያልተጠቀሰው በአካባቢው ጥቂት አይሁዶች ብቻ ይኖሩ ስለነበር ነው። ነገር ግን አንዲት አይሁዳዊት ሴትና ጢሞቴዎስ የተባለ ሰው በልስጥራን ከተማ ውስጥ ይኖሩ ነበር። እነዚህን ሰዎች ወደ ክርስቶስ ያመጣቸው ጳውሎስ ሳይሆን አይቀርም። ጳውሎስ በሁለተኛው የወንጌል ጉዞው ተመልሶ ሲመጣ፥ ጢሞቴዎስን በአገልግሎቱ ረዳት እንዲሆነው ወስዶታል። ጳውሎስ በልስጥራን ለአሕዛብ በሚሰብክበት ጊዜ አንድ ሽባ ሰውዬ በወንጌሉ እጅግ ተደንቆ ነበር። ጳውሎስ ይህን ግለሰብ ሲፈውስ ያዩ የከተማዋ ሰዎች በሙሉ ተደነቁ፡፡ በልስጥራን ከተማ “ዚዎስ” (ድያ) የሚባል የታወቀ ጣዖት ነበር፡፡ በግሪክ ሃይማኖት፥ ዚዎስ ሄርሜን የሚባል ቃል አቀባይ ነበረው። በአንድ ወቅት ዚዎስና ሄርሜን ልስጥራንን እንደ ጎበኙ የሚያወሳ አፈ ታሪክ አለ። ሕዝቡ ተአምሩን በተመለከቱ ጊዜ ዚዎስና ሄርሜን እንደገና አካባቢውን ለመጎብኘት የመጡ መሰላቸው። በርናባስ ዝምተኛና በሳል ሰው በመሆኑ እርሱን ዚዎስ አሉት። ተናጋሪው ጳውሎስ በመሆኑ እርሱን ደግሞ ሄርሜን ብለው ጠሩት። መሥዋዕት ለመሠዋት ወደ ዚዎስ ቤተ መቅደስ የመጡ ሰዎች ለበርናባስና ለጳውሎስ ለመሠዋት ተነሡ። ይናገሩ የነበሩት በገዛ ቋንቋቸው በመሆኑ፥ መጀመሪያ ጳውሎስና በርናባስ ምን ለማድረግ እንዳሰቡ አላወቁም ነበር። ነገር ቀን ሰዎቹ እንደ አማልክት እያዩአቸው መሆኑን ሲገነዘቡ፥ ወንጌላውያኑ በታላቅ ኀዘን ልብሳቸውን ቀደዱ። ለሕዝቡም እንደ እነርሱ ሰዎች እንጂ አማልክት እንዳልሆኑ ገለጹላቸው። እነዚህ ሰዎች ስለ ብሉይ ኪዳንና ስለ እግዚአብሔር ማንነት የሚያውቁት ነገር ስላልነበራቸው ጳውሎስ ምስክርነቱን ከፍጥረት ታሪክ ጀመረ። ጳውሎስ ፈጣሪው እግዚአብሔር እንጂ፥ እነዚህ ግዑዛን የሆኑ ጣዖታት ኃጢአታቸውን ይቅር እንዳላሏቸው ገለጸላቸው፡፡ እርሱም ለሰብሎቻቸው ዝናብ፥ ለእነርሱም ምግብና የልብ ደስታ የሚሰጥ ቸር አምላክ እንደሆነ አብራራላቸው። አሁን ግን ለእርሱ ምላሽ መስጠት እንደሚገባቸው አሳሰባቸው። በዚህ ጊዜ ስለ ክርስቶስና ስለ ድነት (ደኅንነት) የተናገረው ነገር የለም። ሰዎች ወንጌልን ከመረዳታቸው በፊት ስለ እግዚአብሔርና ስለ ኃጢአት፥ መዳንም እንደሚያስፈልጋቸው መገንዘብ አለባቸው። ይህ ደግሞ ጊዜ ይፈልጋል። የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ጳውሎስ ለልስጥራን ሰዎች ያቀረበውን ስብከት ለኢቆንዮን ሰዎች ካቀረበው ጋር አነጻጽር። ምን ልዩነቶች ይታዩሃል? ለ) ይህ ወንጌልን በሰሚዎቻችን ዳራ ላይ ተመሥርቶ ለለማቅረብ አስፈላጊነት ምን ያስተምረናል? ሐ) ለሙስሊምና ለሃይማኖተኛ ለመመስከር ከፈለግህ፥ ለሁለቱ ሰዎች የምታቀርበው ምስክርነት እንዴት ይለያያል? ጳውሎስና በርናባስ በልስጥራን ብዙ ጊዜ ለመቆየት አልቻሉም። የኢቆንዮንና የአንጾኪያ አይሁዶች በየሄዱበት እየሄዱ ብጥብጥ አስነሡባቸው። በዚህ ጊዜ ጳውሎስ ከስደት አላመለጠም፤ እንዲያውም እስከ ሞት ድረስ በድንጋይ ተወገረ፡፡ እግዚአብሔር ግን ጳውሎስን ከሞት ታደገው። በዚያ በሚገኙ ጥቂት አማኞች እርዳታ በተከታዩ ዕለት ጳውሎስና በርናባስ ከልስጥራን 30 ኪሎ ሜትር ያህል ርቃ ወደምትገኘው ወደ ደርቤን ሄዱ። ጳውሎስና በርናባስ ወደ አንጾኪያ ተመለሱ (የሐዋ. 14፡21-28) በደርቤን ብዙ አማኞች ከመኖራቸው በስተቀር በዚያ ስለነበራቸው አገልሎት ምንም የተነገረን ነገር አልነበረም። በሶርያ ወደምትገኘው አንጾኪያ መመለስ አለብን ብለው ስላሰቡ ጳውሎስና በርናባስ በመልስ ጉዟቸው ወቅት ልስጥራን፥ ኢቆንዮንና ጲስድያን ጎበኙ። (ማስታወሻ፡- አንጾኪያ የሚባሉ ሁለት ከተሞች ስላሉ በጥንቃቄ ልንለያቸው ይገባል። አንደኛዋ በትንሹ እስያ ስትገኝ፥ ሁለተኛይቱ በእስያ ውስጥ ናት)። በዚህ ጊዜ ትኩረት ያደረጉት በአማኞች ላይ ነበር። እንደ ክርስቶስ ሁሉ፥ ጳውሎስና በርናባስም ጌታን መከተል ስለሚያስከፍለው ዋጋ ከመናገር አልተቆጠቡም ነበር። ክርስቶስን ስንከተል መንገዱ የመስቀልና የመከራ መንገድ ነው። ስለሆነም፥ «ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በብዙ መከራ እንገባ ዘንድ ያስፈልገናል» ብለው አስተማሯቸው (የሐዋ. 14፡22)። የኢየሱስ ተከታዮች የሆንን ሰዎች እምነታችንን ከመደበቅ ይልቅ በእምነታችን ጸንተን መከራውንም ሆነ በረከቱን ልንካፈል ይገባል። የውይይት ጥያቄ- ሀ) ክርስቲያኖች፥ በተለይም ወጣቶች መንግሥተ ሰማይ ከመግባታችን በፊት እኛ ክርስቲያኖች ልንቀበለው ስለሚገባ መከራ ብዙም የማይናገሩት ለምንድን ነው? ለ) ስለ መስቀሉ በረከት ብቻ መናገር ሳይሆን፥ ስለሚቀበሉትም መከራ አስቀድሞ መግለጹ አስፈላጊ የሚሆነው ለምንድን ነው? የአንጾኪያ ቤተ ክርስቲያን ጳውሎስና በርናባስ የወንጌል መልእክተኞች ሆነው ወንጌልን ወደ አዳዲስ አካባቢዎች እንዲያደርሱ ልከዋቸው ነበር። ምእመናንም የወንጌል መልእክተኞቹን በጸሎት ይደግፉ ነበር። ስለሆነም፥ ጳውሎስና በርናባስ እግዚአብሔር በገላትያ ቤተ ክርስቲያንን ለመመሥረት እንዴት እንደ ተጠቀመባቸው ለመግለጽ ወደ ቤተ ክርስቲያኒቱ ተመለሱ። (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የጳውሎስ አገልግሎት በኢቆንዮን፥ በልስጥራንና በደርቤን እና የጳውሎስና በርናባስ ወደ አንጾኪያ መመለስ (ሐዋ. 14፡1-28) Read More »

የጳውሎስና በርናባስ አገልግሎት በቆጵሮስ፣ ጲስዲያ እና አንጾኪያ (ሐዋ. 13፡1-52)

ተመስገን ወጣት ክርስቲያን ነው። አባቱ የቤተ ክርስቲያን መሪ ነበሩ። ተመስገን በትምህርቱ ጎበዝ ስላልነበረ የማትሪክ ውጤቱ ሳይሰምርለት ቀረ። ይህም ቀጣይ የትምህርት ዕድሉን አበላሸበት። ሥራ የማግኘት ዕድሉም የመነመነ ሆነ። «የማደርገውን አውቃለሁ። ወደ መጽሐፍ ቅዱስ ኮሌጅ ገብቼ ወንጌላዊ እሆናለሁ። በዚህ ዓይነት እግዚአብሔርን እያገለገልሁ፥ ክፍያም አገኛለሁ። ከዚህም በላይ በቤተ ክርስቲያኔ ውስጥ በሌሎች የተከበርሁ እሆናለሁ» ሲል አሰበ። ይህንንም አሳብ ለአባቱ አቅርቦ አባቱ ሌሎች የቤተ ክርስቲያኒቱን ሽማግሌዎችn አግባብተው ልጃቸውን ወደ መጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት እንዲሰድዱላቸውና ሲመለስም በወንጌላዊነት እንዲቀጥሩት አደረጉ። የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ብዙ ሰዎች የቤተ ክርስቲያን ወንጌላዊ የሚሆኑት ለምን ይመስልሃል? ለ) አንድ ሰው ወንጌላዊ እንዲሆን ወይም እንዳይሆን ከእግዚአብሔር የሚመጣ ግልጽ ጥሪ አስፈላጊ የሚሆነው እንዴት ነው? ሐ) ለሥራ ወይም ለክብር ብሎ ወንጌላዊ በሆነ ሰውና፥ እግዚአብሔር ጠርቶኛል ብሎ ወንጌላዊ በሆነ አገልጋይ መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው? ዛሬ ጳውሎስ ወንጌላዊ ለመሆን እንዴት እንደ ተጠራ እናጠናለን። ጳውሎስ አገሩንና አጥቢያ ቤተ ክርስቲያኑን ጥሎ በወንጌላዊነት ስም ዓለምን ለመዞር አሳብ አልነበረውም። ቤተ ክርስቲያንም ጳውሎስን በወንጌላዊነት ለመቅጠር አሳብ አልነበራትም። ነገር ግን እግዚአብሔር ለሥራው በግልጽ ጠራው። መንፈስ ቅዱስ በጳውሎስና በቤተ ክርስቲያኒቱ መሪዎች ልብ ውስጥ በመሥራት፥ በርናባስና ጳውሎስ የእነርሱ ተጠሪዎች በመሆን ወንጌልን በዓለም ሁሉ እንዲያደርሱ በግልጽ ነገራቸው። በእግዚአብሔር ያልተጠሩ በጣም ብዙ ወንጌላውያን አሉ። እነዚህ ሰዎች ወደ ወንጌላዊነት አገልግሎት የመጡት በራሳቸው ወይም በሌላ ሰው ፍላጎት ነው። ነገር ግን ከእግዚአብሔር ግልጽ የሆነ ጥሪ ካልተቀበሉ፥ ሰዎችም ሆኑ ቤተ ክርስቲያን በአገልግሎቱ እምብዛም ደስ አይሰኙም። ከሐዋርያት ሥራ 13-28 ጀምሮ፣ የመጽሐፉ ትረካ ትኩረቱን ይቀይራል። ሉቃስ በሐዋርያት ሥራ ምዕ. 9 ላይ ጳውሎስን ካስተዋወቀን በኋላ፥ ከ9-11 ስለ ጳውሎስ ብዙ ነገር አይነግረንም። የነገረን ነገር ቢኖር ጳውሎስ በአንጾኪያ ቤተ ክርስቲያን ለማገልገል መምጣቱን ብቻ ነው። ሉቃስ ስለ ጴጥሮስ፥ እስጢፋኖስና ፊልጶስ ሲነግረን ከቆየ በኋላ፥ አሁን ደግሞ ስለ ጳውሎስ ይናገራል። ሉቃስ ከወዳጁ ጋር ብዙ ጊዜ ስለሚያሳልፍና አብሮትም ስለሚጓዝ፥ እነዚህን ታሪኮች በሚገባ ያውቃቸዋል። ወንጌሉ ወደ አሕዛብ አገሮች እንዲደርስ እግዚአብሔር በጳውሎስ ስለ ተገለገለ፥ ሉቃስ እግዚአብሔር በጳውሎስ አማካይነት ባከናወናቸው ተግባራት ላይ ያተኩራል። በርናባስና ጳውሎስ ወንጌልን ወደ ቆጵሮስ አደረሱ (የሐዋ.13፡1-12) እግዚአብሔር የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ወንጌልን ወደ ምድር ዳርቻ እንድታደርስ አዝዟት ነበር። ይህ ትእዛዝ ከተሰጠ 14 ዓመት ቢሆነውም፥ ወንጌሉ መድረስ የቻለው እስከ አንጾኪያ ድረስ ብቻ ነበር። በመሆኑም እግዚአብሔር የቀረውን የዓለም ክፍል ለመድረስ፥ ቤተ ክርስቲያንን የሚቀሰቅስበት ጊዜ ደረሰ። እግዚአብሔር ይህንን ታላቅ ተግባር ለማከናወን የኢየሩሳሌሟን እናት ቤተ ክርስቲያንን ሳይሆን፥ የአንጾኪያዋን ቤተ ክርስቲያን መምረጡ አስገራሚ ነበር። ሥራውን ለማከናወን ከ12ቱ ሐዋርያት አንደኛውን ስመ ጥር ሐዋርያ አልጠራም። ነገር ግን እግዚአብሔር የአሕዛቡን ዓለም በወንጌል ለመድረስ የሚያስችል ብቃት ያለውን ግለሰብ ነበር የጠራው። እግዚአብሔር ልዑል አምላክ በመሆኑ ሥራውን ለማከናወን ማንኛውንም ግለሰብ ወይም ቤተ እምነት መጠቀም ይችላል። ስለሆነም፥ ማንኛውም ግለሰብ ወይም ቤተ እምነት፥ ለእግዚአብሔር በሚያከናውነው ተግባር መመካት የለበትም። ነገር ግን ለእግዚአብሔር ታማኞች በመሆን፥ በመንፈሳዊ ሕይወታችን ሕያዋን መሆናችንን ማረጋገጥ አለብን። ይህ ሲሆን፥ እግዚአብሔር ለአገልግሎቱ በመረጠን ጊዜ ዝግጁ መሣሪያዎቹ መሆን እንችላለን። የአንጾኪያ ቤተ ክርስቲያን በርካታ የሆኑ ብርቱ መሪዎች ነበሯት። እነዚህም መሪዎች «ነቢያት» እና «አስተማሪዎች» ይባሉ ነበር። በአዲስ ኪዳን ውስጥ ነቢያት ሁልጊዜ ከሐዋርያት ቀጥለው ይጠቀሱ ነበር። አዲስ ኪዳን ከመጻፉ በፊት እግዚአብሔር ፈቃዱንና አሳቡን ለሕዝቡ የሚያስታውቀው በነቢያቱ በኩል ነበር (1ኛ ቆሮ. 12፡28-29፤ ኤፌ. 2፡20)። ነቢያቱ የሚናገሯቸው ቃሎች መጻኢውን ወይም የወደፊቱን ዘመን የሚያመለክቱ ነበሩ። ይሁንና በአብዛኛው እንደምንገነዘበው ነቢያቱ ይናገሩ የነበረው ለዚያው ዘመን ሕዝብ ነበር። ይህ አገልግሎት በተለይ አዲስ ኪዳን ከመጻፉ በፊት በጣም ይሠራበት ነበር። አስተማሪ በጽሑፍ የሰፈረውን የእግዚአብሔርን ቃል ሰዎች መረዳትና መታዘዝ እንዲችሉ የማብራራት ስጦታ ያለው ሰው ነበር። አስተማሪዎችም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እጅግ አስፈላጊ መሪዎች ነበሩ (ኤፌ. 4፡11-13)። ሉቃስ የአንኪያን ቤተ ክርስቲያን ዋና መሪዎች ስም የጠቀሰው፥ ቤተ ክርስቲያኒቱ ምን ያህል ትልቅ እንደ ነበረች ለማመልከት ነው። በርናባስ የቤተ ክርስቲያኒቱ ዋነኛ መሪ በመሆኑ በቀዳሚነት የተጠቀሰው በዚህ ምክንያት ሳይሆን አይቀርም። «ኒገር» (ጥቁር) ተብሎ የአይሁድ ስም የተሰጠው ስምዖን አፍሪካዊ ሳይሆን አይቀርም። አንዳንድ ምሑራን ይህ ክርስቲያን የክርስቶስን መስቀል የተሸከመው የቀሬናው ስምዖን ይሆናል ይላሉ። ሉክዮስ (የላቲን ስም ሲሆን፥ ምናልባት ሮማዊ ስምም ሊሆን ይችላል) በሰሜን አፍሪካ ውስጥ የሚገኘው የቀሬና ሰው ነበር። መናሔ ምናልባትም አይሁዳዊ ሲሆን፥ የሄሮድስ አግሪጳ ጉዲፈቻ (ማደጎ) የነበረ ወንድም ሳይሆን አይቀርም። አይሁዳዊው ጳውሎስ የአሕዛብ ከተማ በሆነችው በተርሴስ ነበር ያደገው። የተለያዩ ዘሮች ወይም ጎሣዎች በአንድ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በሚኖሩበት ጊዜ፥ ሁሉም የጎሣ ቡድኖች በአመራሩ ውስጥ በሚገባ መወከላቸው አስፈላጊ ነው። የአንጾኪያ ቤተ ክርስቲያን መሪዎች በጊዜው ለምን ለጸሎትና ለጾም እንደ ተሰበሰቡ አናውቅም። ሆኖም እግዚአብሔር በርናባስና ጳውሎስን ለተለየ ሥራ የመረጠው እየጸለዩ ሳለ ነበር። ከዚህ አራት ዐበይት ነገሮችን ልንመለከት እንችላለን። ሀ. በርናባስና ጳውሎስ ራሳቸውን አልመረጡም። እግዚአብሔር እነዚህን ሰዎች በመምረጥ ወንጌላውያን ሆነው መሄድ እንዳለባቸው ለመሪዎቹ ገልጾላቸዋል። ለ. እግዚአብሔር ወንጌል ወዳልደረሰበት ስፍራ፥ ወንጌልን እንዲያደርሱ ተራ ሰዎችን አልመረጠም፤ የመረጠው ግን እንደ በርናባስና ጳውሎስ ያሉ ታዋቂ መሪዎችን ነው። አብያተ ክርስቲያናት ብዙውን ጊዜ ሰዎችን በወንጌላዊነት ለመላክ ፈቃደኞች ናቸው። ነገር ግን በስጦታቸው የተመሰከረላቸውን ለራሳቸው አስቀርተው፥ ስጦታ የሌላቸውን ወንጌላውያን አድርገው ለመላክ ይፈልጋሉ። ይህ ግን ከእግዚአብሔር ፈቃድ ጋር ተቃራኒ ነው። እግዚአብሔር የአንጾኪያ ቤተ ክርስቲያን ምርጥ መሪዎቿን እንድትልክ ፈልጎ ነበር። በጳውሎስና በበርናባስ ፊት የተደቀነው ሥራ እጅግ ታላቅና ከባድ ስለነበር፥ እግዚአብሔርም የፈለገው ከፍተኛ ስጦታ ያላቸውን መሪዎች እንዲልኩ ነበር። ሐ. በርናባስ እንደ ሽማግሌ መሪ፥ ጳውሎስ ደግሞ እርሱ እንደሚመራው ሰው ይታዩ ስለነበር በርናባስ ከጳውሎስ በፊት ተጠቅሷል። በመጀመሪያው የወንጌል አገልግሎት አጋማሽ ላይ ግን ይህ ቅደም ተከተል ተለውጦ፥ ጳውሎስ የቡድኑ መሪ ሆኗል። መ. ከዚህ በኋላ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሽማግሌዎች በረከቶቻቸውን በመስጠትና እጆቻቸውን ጭነው በመጸለይ ለእግዚአብሔር ሥራ ላኳቸው። የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ወንጌላውያንን ስለ መምረጥ፥ ማሠልጠንና መላክ ከዚህ ምን እንማራለን? ለ) ይህ አሁን እኛ ከምናከናውነው ተግባር የሚለየውና የሚመሳሰለው እንዴት ነው? ቤተ ክርስቲያንህ ወንጌላውያንን የምትመርጥበትና የምትልበትን መንገድ በተመለከተ ምን ልትለውጥ ይገባል? በርናባስና ጳውሎስ ለመጀመሪያው የወንጌል አገልግሎት ሲሄዱ ዮሐንስ ማርቆስ የተባለ ወጣትን ይዘው ሄደዋል። ዮሐንስ ማርቆስ ከበርናባስ ጋር የመጣው፥ በርናባስና ጳውሎስ የእርዳታውን ገንዘብ አድረስው ከኢየሩሳሌም ሲመለሱ ነበር። ምናልባትም እንደ ረዳት እንዲያገለላቸው በማሰብ፥ ዮሐንስ ማርቆስ አብሯቸው እንዲሄድ የወሰነው በርናባስ ሳይሆን አይቀርም። እግዚአብሔር እንዲህ እንዲያደርጉ ያዘዛቸው ነገር ስለመኖሩ ምንም አናገኝም፡፡ ይህ ረዳት ይሆነናል ብለው የወሰዱት ሰው፥ የኋላ ኋላ በበርናባስና በጳውሎስ መካከል መቃቃርንና መከፋፈልን እንደሚያስከትል ሁለቱም ያጤኑት አይመስልም፡፡ በርናባስና ጳውሎስ መጀመሪያ የሄዱት ወደ ቆጵሮስ ደሴት ነበር። በርናባስ ያደገው በቆጵሮስ ስለነበር፥ መንፈስ ቅዱስ የወንጌል አገልግሎታቸውን በዚያ እንዲጀምሩ መራቸው። ወንጌሉን እየሰበኩ በደሴቲቱ መሀል በሚጓዙበት ወቅት፥ ሰርግዮስ ጳውሎስ የተባለ የሮም ባለሥልጣን ወንጌልን እንዲሰብኩለት ጠየቃቸው። ሰርግዮስ ጳውሎስ ጠንቋይ የነበረ አይሁዳዊ አማካሪ ነበረው። ይህ ሰው የበርናባስንና የጳውሎስን አገልግሎት ተቃወመ። በዚህ ጊዜ ጳውሎስ በጠንቋዩ ኤልማስ ላይ የእግዚአብሔርን ፍርድ በማወጅ ዓይኑ እንዲታወር አደረገ። ሰርግዮስ ጳውሎስም በክርስቶስ አመነ ሉቃስ ይህን አስመልክቶ ሁለት ለውጦችን ዘግቦአል። ሀ. እዚህ ላይ ሉቃስ ሳውልን በሮማዊ ስሙ ጳውሎስ እያለ መጥራት ይጀምራል። በዚህ ጊዜ የነበሩት በአሕዛብ ክልል ውስጥ በመሆኑ፣ ሉቃስ ከአይሁዳዊ ስሙ (ሳውል) ይልቅ የአሕዛብ ስሙን ለመጠቀም መርጧል። ለ. የቡድኑን መሪነት ስፍራ ጳውሎስ ወሰደ። ከዚህ በኋላ በመጀመሪያ የወንጌል መልእክተኛነት አገልግሎት ወቅት በሙሉ ጳውሎስ መጀመሪያ ይጠቀሳል። እንዲያውም፥ በሐዋርያት ሥራ 13፡13 የበርናባስ ስም ሳይጠቀስ፥ ቡድኑ «ጳውሎስና ተባባሪዎቹ ተብሎ ተጠቅሷል። ምናልባትም በርናባስ ከአሕዛብ መሪዎች ጋር ለመሥራት ልምዱ አልነበረውም ይሆናል። የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በዚህ ሁኔታ አንዱ ከሌላው በላይ

የጳውሎስና በርናባስ አገልግሎት በቆጵሮስ፣ ጲስዲያ እና አንጾኪያ (ሐዋ. 13፡1-52) Read More »

አይሁዶች ለሁለተኛ ጊዜ ክርስቲያኖችን አሳደዱ (የሐዋ. 12፡1-25)

ክርስቶስ ከተሰቀለ፥ ከሞት ከተነሣ፥ ወደ ሰማይ ካረገና ቤተ ክርስቲያንም ከተመሠረተች አሥራ አራት ዓመት ሆኖታል። ቤተ ክርስቲያን በአንድ ወቅት የተነሣባትን ስደት ተቋቁማለች። አሁን ደግሞ ስደት ለሁለተኛ ጊዜ ተነሳባት፡፡ ስደት በጥንታዊቷ ቤተ ክርስቲያን ላይ በተደጋጋሚ የሚደርስና በየጊዜው እየጨመረ የሚሄድ ነገር በመሆኑ፥ ሉቃስ ስለ ስደት እንዲያውቁ ፈለገ፡፡ የሁለተኛው ስደት ዋናው ቀስቃሽ ሄሮድስ አግሪጳ ነበር። ሄሮድስ አግሪጳ ይሁዳን፥ ሰማርያንና ገሊላን እንዲያስተዳድር በሮማውያን ተሹሞ ስለነበር፥ በይሁዳ ከነበሩ አይሁዶች ጋር ለመወዳጀት ፈለገ፡፡ በዚያን ጊዜ ብዙ አይሁዶች ክርስቲያኖችን ይጠሉ ስለነበር ሊያሳድዳቸው ወሰነ። ስደቱ ከመሪዎች እንዲጀምር ፈልጎ ሐዋርያው ያዕቆብን አስገደለው። ይህ ድርጊቱ አይሁድን ምን ያህል እንዳስደሰተ ሲመለከት ጴጥሮስንም ለማስገደል ሊል አሳሰረው። እግዚአብሔር ግን ለጴጥሮስ የተለየ ዕቅድ ስለነበረው፥ መልአኩን ልኮ አስፈታው። ደቀ መዛሙርቱ ጴጥሮስ እንዲለቀቅ እየጸለዩ ስለ ነበር፥ እግዚአብሒር ጸሎታቸውን በመመለሱ ተደነቁ። ታሪኩ በክርስቲያኖች ላይ ስደት እንደሚመጣ ያስተምራል። የስደቱ ውጤት ግን በእግዚአብሔር ፈቃድ ውስጥ የተሰወረ ነው። ክርስቲያኖች እግዚአብሔር እንዲጠብቃቸው መጸለይ አለባቸው። እግዚአብሔር ሕዝቡን ለማዳን እንደሚሠራና እንዲያውም ተአምር እንደሚያደርግ መጠበቅ አለብን። እግዚአብሔር አንዳንድ ጊዜ ጸሎታችንን በመመለስ ከስደትና ከሞት ይጠብቀናል። ሌላ ጊዜ ደግሞ ከጸሎታችን ባሻገር ልጆቹ እንዲሞቱ ወይም ስደት እንዲደርስባቸው ያደርጋል። ክርስቲያኖች እግዚአብሔር ስደትን ለማስቆምም ሆነ ስደቱ በርትቶ በሞት ውስጥ እንዲያልፉ ሊፈቅድ እንደሚችል ማወቅ አለባቸው። ቁም ነገሩ ለጸሎት ያለን አመለካከት መለወጡ ላይ ነው። ጴጥሮስ እግዚአብሔር እንደሚያድነው ባያውቅም እንኳ፣ በእግዚአብሔር ፈቃድ ውስጥ መኖሩን በማሰብ በፍጹም ሰላምና ዋስትና ውስጥ እንደነበረ ሁሉ፥ እኛም የስደቱን ውጤት በእግዚአብሔር እጅ ውስጥ ትተን በእግዚአብሔር ፍጹም ፈቃድ ውስጥ ልናርፍ እንችላለን። ነገር ግን ሞት እያንዣበበብን ሳለ እንዴት በሰላም መኖር እንችላለን? ምክንያቱም ለእግዚአብሔር ልጆች እርሱ ወደሚገኝበት ስፍራ መሸጋገሪያ መንገድ ነው። ሞት የሕይወት ፍጻሜ ሳይሆን፥ የታላቁ ሕይወት መጀመሪያ ነው። ይህንን አምነን የምንቀበለው በእምነት ነው። የውይይት ጥያቄ:- – ሀ) ከዚህ ታሪክ ስለ ጸሎት መልስ ምን እንማራለን? ለ) ምንም ቢሆን ምን ለእግዚአብሔር ፈቃድ ራስን ስለ ማስገዛት ምን እንማራለን? እግዚአብሔር ያዕቆብን ለማዳን ይችል ነበር፥ ነገር ግን እንዲሞት ፈቀደ። ጴጥሮስም ሊሞት ይችል ነበር፥ እግዚአብሔር ግን ተአምር ሠርቶ አዳነው። ይህ እኛ ልንረዳው የማንችለው የእግዚአብሔር ሉዓላዊ ፈቃድ አካል ነው። ነገር ገን እግዚአብሔር በሁሉ ላይ ጌታ ስለሆነ የያዕቆብን ገዳዮች ሳይቀጣ እያልፍም። ሄርድስ አግሪጳ የእግዚአብሔርን ልጅ ስለ ገደለና በትዕቢት ለአምላክ ብቻ የሚገባውን ስግደት ስለ ተቀበለ፥ እግዚአብሔር በሕመም ቀስፎታል። ሰውነቱም በትል ተበልቶ እንዲሞት አድርጓል። የክርስቲያኖች ጠላት የሆነ ሰው የእግዚአብሔርን ልጆች ለመግደል ይችል ይሆናል። ግን እግዚአብሔር ሁልጊዜ ጌታ ነው። እግዚአብሔር በራሱ ጊዜ ሄሮድስን ቀጥቶታል። በአንጻሩም የቤተ ክርስቲያን እድገትና የእግዚአብሔርን ቃል መስፋት ሊገታ የሚችል ነገር አልነበረም። ንጉሥ ሄሮድስም ሆነ የሲኦል ልጆች ይህንን ማሸነፍ አይችሉም። (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

አይሁዶች ለሁለተኛ ጊዜ ክርስቲያኖችን አሳደዱ (የሐዋ. 12፡1-25) Read More »

ጴጥሮስ የገጠመው ተቃውሞ እና የአንጾኪያ ቤተ ክርስቲያን (የሐዋ. 11፡1-30)

የኢየሩሳሌም አይሁዶች ጴጥሮስ ከአሕዛብ ጋር ሲተባበር አይተው ተቃወሙት (የሐዋ. 11፡1-18) ጴጥሮስ፥ እግዚአብሔር አድልዎን እንደማይፈቅድ ያቀረበለትን ፈተና አልፎአል። ሌሎች የአይሁድ ክርስቲያኖችስ? በሐዋርያት ሥራ 6 ላይ እንደተገለጸው የአይሁድ ክርስቲያኖች፥ በእግዚአብሔር ቤተሰብ ውስጥ በአሕዛብ ላይ የነበራቸውን ጥላቻ ማስወገድ ነበረባቸው። ይህ ግን ለረጅም ጊዜ በመጥፎ ገጽታው ቀጥሎ ነበር። የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ለእግዚአብሔር አልታዘዝም፥ ባሕሉንም አልተውም ብትል ኖሮ፥ አሕዛብ ወደ ኅብረትዋ መቀላቀል ከፈለጉ፥ በቅድሚያ አይሁድ ሁኑ በማለት ባስገደደቻቸው ነበር። አለበለዚያም ቤተ ክርስቲያን ለሁለት ተከፍላ አንዱ ወገን የአይሁድ፥ ሌላው ወገን የአሕዛብ ቤተ ክርስቲያን እየተባለ ይጠራ ነበር። አንድነት ካልኖራቸው ደግሞ ምስክርነታቸው እምብዛም ዓለምን የመለወጥ ኃይል ባልኖረውም ነበር። የጥላቻን አመለካከት ማሸነፍ ቀላል አይደለም። ጴጥሮስ በኢየሩሳሌም ወደነበረችው እናት ቤተ ክርስቲያኑ ሲመለስ፥ ከአሕዛብ ጋር እንዳይተባበሩ የሚያስጠነቅቀውን የአይሁድ ደንብ በመጣሱ ተከስሷል። ጴጥሮስ ስላየው ራእይና እግዚአብሔር ለአይሁድ እንዳደረገው ሁሉ ለአሕዛብም መንፈስ ቅዱስን እንደ ሰጠ፥ በዝርዝር ተናግሯል። አሕዛብ ወደ ይሁዲነት ሳይመጡ፥ በእግዚአብሔር ቤተሰብ ውስጥ ሁሉም እኩል ናቸው፥ የሚለው አሳብ እጅግ ወሳኝ ነበር። በመሆኑም ሉቃስ፥ ጴጥሮስ ያየውን ራእይና መንፈስ ቅዱስ በአሕዛብ ላይ እንዴት እንደ ወረደ ያስተዋለውን ነገር በድጋሚ ጽፎታል። ጴጥሮስ እንዳለው «እንግዲህ እግዚአብሔር በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ላመንነው ለእኛ ደግሞ እንደ ሰጠን ያን ስጦታ ለእነርሱ ከሰጠ፥ እግዚአብሔርን ለመከላከል እችል ዘንድ እኔ ማን ነበርሁ?» ብሏል (ሐዋ.11፡17)፡፡ የሚያሳዝነው ዛሬም ብዙ ክርስቲያኖች ሌሎች ሰዎችን በእኩል ደረጃ ባለመቀበል እግዚአብሔርን ይቃወማሉ። በእኛና በሌሎች ሰዎች መካከል (በሸክላ ሠሪዎች፥ በቀጥቃጮች፥ ወዘተ) ወይም በጎሣዎች መካከል መከፋፈል እንዲከሰት ስናደርግ በድርጊታችን ለእግዚአብሔር እንዲህ እያልነው ነው። «አንተ ነገሮች እንዲሆኑ ከምትፈልግበት መንገድ ጋር አንስማማም» እኛ ከእነርሱ እንሻላለን ብለን ስለምናስብ፥ ባሕላችንን፥ ቋንቋችንን፥ የአምልኮ ስልታችንን፥ ዝማሬአችንን ካልተከተላችሁ እንቀበላችሁም እንላቸዋለን። እንዲህ ስንል ደግሞ ሁሉም ሰው እኛን ይምሰል ማለታችን ነው። ለዓለም ደግሞ፥ ወንጌሉ የጥላቻ አመለካከትን ሊያስወግድ አይችልም። በዓለም ውስጥ ያለው መከፋፈል እኛም ዘንድ አለ። ባሕላችንን መታዘዙ ክርስቶስን ከመታዘዝ የበለጠ ነው። አንድነት ለእኛ ብዙም አስፈላጊ አይደለም እያልን ነው። ሰዎች ወደ ክርስቶስ ከማይሳቡባቸው ምክንያቶች አንዱ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ብዙ ፍቅርና አንድነት አለመታየቱ ነው። እኛ ጎሣዊ ጥላቻን ለማስወገድ ካልቻልን፥ የአገራችንና የዓለም ጎሣዎች ተስማምተው ስለሚኖሩበት ሁኔታ እንዴት ልናስብ እንችላለን? የአንጾኪያ ቤተ ክርስቲያን – የመጀመሪያይቱ የአይሁድና የአሕዛብ ጥምረት የታየባት ቤተ ክርስቲያን ሆነች (የሐዋ. 11፡19-30) ምንም እንኳ በፍልስጥኤም ይኖር የነበረው ቆርኔሌዎስ በጌታ በማመን የመጀመሪያው ሰው ቢሆንም፥ ይህ ግን በቤተ ክርስቲያን ላይ ተጽዕኖ አላደረገም ነበር። በፍልስጥኤም ቁጥራቸው ጥቂት የሆኑ የአሕዛብ አማኞች ነበሩ። ስለሆነም፥ እግዚአብሔር አሕዛብን ወደ ቤተ ክርስቲያን ያመጣበት እውነት በአይሁድ ክርስቲያኖች ዘንድ ተፈትኖ ተቀባይነት ያገኘ ነገር አልነበረም። ነገር ግን ቀስ በቀስ ቤተ ክርስቲያን መስፋፋት ጀመረች። በኋላም በአሕዛብ አገሮች በቆጵሮስና በቀሬና ባደጉ አይሁዳውያን አገልግሎት ወደ ሰሜን እስከ ፊንቄ ሊባኖስ)፥ ከፊንቄ እስከ ቆጵሮስ፥ በመቀጠልም እስከ እንጾኪያ ከተማ ድረስ ተስፋፋች። አንጾኪያ በሮም ግዛት ውስጥ ከሚገኙት ከተሞች ሁሉ በትልቅነቷ የሦስተኛ ደረጃ ነበራት። ሁለቱ ታላላቅ ከተሞች ሮምና እስክንድርያ ነበሩ።) አንጾኪያ ለብዙ ዘመን የሶሉሲድ ግሪክ ግዛት መዲና ነበረች። በሮማውያን እጅ በነበረችበት ጊዜ፥ በመካከለኛው ምሥራቅ ዋነኛ የፖለቲካ ኃይል ማዕከል ሆና ቆይታለች። ቤተ ክርስቲያን ወደ አንጾኪያ መስፋፋቷ ጠቃሚ ነበር። በእግዚአብሔር ዕቅድ ውስጥ አሕዛብን በወንጌል ለመድረስ ያገለገለችው የኢየሩሳሌሟ ሳትሆን፥ የአንጾኪያዋ ቤተ ክርስቲያን ነበረች። የኢየሩሳሌም ቤተ ክርስቲያን በራሷ አሳብና በአይሁድ ባሕል ላይ ስላተኮረች፥ ለእግዚአብሔር ጠቃሚ መሣሪያ ለመሆን አልቻለችም። ነገር ግን የአሕዛብና የአይሁዶች ጥምር የሆነችው የአንጾኪያ ቤተ ክርስቲያን፥ እግዚአብሔር ለሰዎች ሁሉ ያለውን ዕቅድ በተሻለ ሁኔታ ስለ ተገነዘበች፥ እግዚአብሔር አሕዛብን እንድትማርክ ተጠቅሞባታል። የአንጾኪያ አይሁድ ክርስቲያኖች ተወልደው ያደጉት በአሕዛብ አገሮች በመሆኑ፥ በፍልስጥኤም ተወልደው ካደጉት አይሁዶች ይልቅ ከአሕዛብ ጋር በቀላሉ ለመግባባት ይችሉ ነበር። ብዙ አሕዛብ አመኑ። ለመጀመሪያ ጊዜ ከአባላት መካከል ብዙ የአሕዛብ አማኞችን ይዛ የተገኘችው ቤተ ክርስቲያን አንጾኪያ ናት። በኢየሩሳሌም የምትገኘው እናት ቤተ ክርስቲያን ከኢየሩሳሌም 500 ኪሎ ሜትር ያህል ርቃ በምትገኘው አንጾኪያ፥ እግዚአብሔር እየሠራ ያለውን ትልቅ ሥራ ስትሰማ፥ በዚያ የሚደረገው ነገር እውነተኛና ከወንጌሉም ጋር የሚስማማ መሆኑን ለማረጋገጥ በርናባስን ላከችው። በአንጾኪያ የሚሠራው ሥራ በርናባስን እጅግ ደስ ስላሰኘው፥ ወደ ኢየሩሳሌም መመለሱን ትቶ በዚያ ለማገልገል ወሰነ። በርናባስ በአሕዛብ መካከል ተወልዶ ያደገ አይሁዳዊ በመሆኑ፥ እግዚአብሔር እያከናወነ ያለውን ልዩ ተግባር በአንክሮ ሊመለከት ችሏል። ከእርሱ በተጨማሪ በአገልግሎቱ እንዲያግዘው በአሕዛብ መካከል ተወልዶ ያደገ አይሁዳዊ መፈለግ ጀመረ። ስለዚህ 150 ኪሎ ሜትር ተጉዞ ወደ ተርሴስ በመሄድ ጳውሎስ አብሮት እንዲያገለግል አግባባው። ሉቃስ በአንጾኪያ ሁለት ዐበይት ነገሮች እንደተደረጉ ገልጾአል። አንደኛው፥ «ክርስቲያኖች» የሚለው ስም ለክርስቶስ ተከታዮች መስጠቱን ሲሆን፥ ይህ ስም እስከ ዛሬ ድረስ ለክርስቶስ ተከታዮች ሁሉ በማገልገል ላይ ይገኛል። ይህ ሌሎች ክርስቲያኖችን ለመስደብ (በደርግ ዘመን «ጴንጤ» ይባል እንደነበረው) ያወጡት ስም ይሁን ወይም ክርስቲያኖች ራሳቸው ያወጡት ስያሜ የሚታወቅ ነገር የለም። ነገር ግን የቃሉ ትርጉም «የክርስቶስ የሆነ» ስለሚል፥ ክርስቶስን ለሚከተሉ ሰዎች ተስማሚ መጠሪያ ሆኖ ቆይቷል። ሁለተኛው የመጀመሪያው «የእርዳታ» ፕሮግራም በቤተ ክርስቲያን ተጀመረ። በኢየሩሳሌም ረሃብ መነሣቱን ቤተ ክርስቲያኒቱ ስትሰማ ብዙ ሀብት የነበራቸው የአንጾኪያ ክርስቲያን አባላት ለመርዳት ወሰኑ። ገንዘብ አሰባስበው በመሪዎቻቸው ማለትም በበርናባስና በጳውሎስ በኩል ወደ ኢየሩሳሌም ላኩ። ቀደም ሲል ክርስቲያኖች ተለይተው የሚታወቁት እርስ በርሳቸው በመዋደዳቸው እንደሆነ ክርስቶስ እንደ አስተማረ ተመልክተናል። ምንም እንኳ የአንጾኪያ ክርስቲያኖች ከእነርሱ 500 ኪሎ ሜትር በላይ ርቀው የነበሩትን የኢየሩሳሌም ክርስቲያኖች በአካል ባያውቋቸውም፥ ለእግዚአብሔር ቤተሰብ ከነበራቸው ፍቅር የተነሣ የማያውቋቸውን ወገኖች ለመርዳት ፈቀዱ። ከራሷ ምእመናንና ግዛት አልፋ በሩቅ ስፍራ ያሉ ወንድሞችንና እኅቶችን ለመርዳት የተነሣች ቤተ ክርስቲያን፥ መንፈሳዊ መሆኗን አስመሰከረች። የውይይት ጥያቄ:- ቤተ ክርስቲያንህ ለማታውቃቸው ሌሎች ክርስቲያኖች ፍቅሯን የምትገልጸው እንዴት ነው? ቤተ ክርስቲያንህ ይህንን የምታደርግ ከሆነ ምክንያቱ ምንድን ነው? (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ጴጥሮስ የገጠመው ተቃውሞ እና የአንጾኪያ ቤተ ክርስቲያን (የሐዋ. 11፡1-30) Read More »

ጴጥሮስ በይሁዳና ቂሣርያ ያካሄደው አገልግሎት (የሐዋ. 9፡32-10፡48)

እስካሁን ወንጌል በሦስት ዐበይት የዓለም ክፍሎች ሊዳረስ ችሎአል። እነርሱም በኢየሩሳሌም የነበሩ አይሁዶች፥ በይሁዳ የነበሩ አይሁዶችና በሰማርያ የነበሩ ከፊል አይሁዶች ናቸው። አንድ የዓለም ክፍል ግን አሁንም ይቀራል፤ ይህም «እስከ ምድር ዳርቻ» ያለው የአሕዛቡ ዓለም ነው። ስለዚህ ሉቃስ በዚህ ክፍለ ዓለም ወንጌል እንዴት እንደ ተዳረሰ ይነግረናል። ምንም እንኳ አይሁዶች የሰማርያ ሰዎችን ቢጠሏቸውም፥ ቢያንስ ግማሽ አይሁዶች ነበሩ። የብሉይ ኪዳን ቅዱሳት መጻሕፍትን የሚያምኑ ከመሆናቸውም በላይ፥ በአንዱ አምላክ ብቻ ያምኑ ነበር። ነገር ግን አይሁድ አሕዛብ ወደ እምነት ይመጣሉ የሚል ተስፋ የላቸውም። ይህ ሊሆን የሚችለው ደግሞ አሕዛብ በመጀመሪያ የአይሁድን እምነት ሲቀበሉ ነው። ከአይሁድ ሲሆኑ እግዚአብሔር ይቀበላቸዋል። ነገር ግን ወንጌል እስከ ምድር ዳርቻ ሁሉ እንዲዳረሰ ከተፈለገ፥ አሕዛብ ባሕላቸውን ትተው ወደ ይሁዲነት መለወጥ አያስፈልጋቸውም ነበር። ስለሆነም፥ መንፈስ ቅዱስ ይህ ክፍለ ዓለም ወንጌልን እንዲያዳምጥና በቤተ ክርስቲያን ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝ፥ በጴጥሮስ አማካይነት ይሠራ ጀመር። በሐዋርያት ሥራ 9፡31-11፡30 የምናገኘው ክፍል፥ ይህ አዲስ የወንጌል በር እንዴት እንደ ተከፈተ ያስረዳል። ይህ ለመጀመሪያው ምእተ ዓመት ክርስቲያኖች አስፈላጊ እውነት በመሆኑ፥ ሉቃስ ሂደቱን በዝርዝር ገልጾአል። መጀመሪያ እግዚአብሔር በጴጥሮስ ልብ ውስጥ በመሥራት እግዚአብሔር ለአሕዛብ ያለውን ፍቅር እንዲገነዘብ ማድረግ ነበረበት። አይሁዶችም አሕዛብን በእኩልነት ወደ ቤተ ክርስቲያን እንዲቀበሉ ልባቸውን መክፈት ነበረበት። ይህ የአይሁድ ክርስቲያኖች በአሕዛብ ላይ የነበራቸው ጥላቻ እስኪወገድ ብዙ ዓመታትን ወስዷል። ጴጥሮስ ወደ ቆርኔሌዎስ ቤት ሄዶ ወንጌልን ይመሰክር ዘንድ፥ መንፈስ ቅዱስ በጴጥሮስ ልብ ውስጥ የነበረውን የአድልዎ መንፈስ መስበር አለበት። ሀ. የጴጥሮስ አገልግሎት በይሁዳ፡- እስካሁን ድረስ የጴጥሮስ አገልግሎት ያተኮረው በኢየሩሳሌም ከተማ ውስጥ ነበር። አንድ ጊዜ ወደ ሰማርያ ተጉዞ ከሰበከ በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሶ እዚያው ሲያገለግል ቆይቷል። አሁን ግን እግዚአብሔር ከኢየሩሳሌም ውጭ መራው። ጴጥሮስ በምዕራብ ይሁዳ የሚገኙትን አንዳንድ ክርስቲያኖች ለመጎብኘት ስለፈለገ፥ በባሕር ዳርቻ ወደሚገኙት የሊዲያና የኢዮጴ ከተሞች ሄደ። በዚያም መንፈስ ቅዱስ ጣቢታን ከሞት እንዲያስነሣና ሌሎችንም በርካታ ተአምራት እንዲሠራ አደረገው። ለ. ጴጥሮስ በአንድ ክርስቲያን ቆዳ ፋቂ ቤት ተቀመጠ፡- እንደ ኢትዮጵያውያን ሁሉ አይሁዶችም ቆዳ (ቁርበት) ፋቂዎችን ይንቋቸው ነበር። በብሉይ ኪዳን የሞተ እንስሳ የነካ ሰው እንደ ርኩስ ይቆጠር ነበር። ቆዳ ፋቂ ደግሞ የታረዱ ወይም የሞቱ እንስሳትን ቆዳ አልፍቶ ስለሚተዳደር በኅብረተሰቡ ዘንድ ሁልጊዜ እንደ ርኩስ ይቆጠር ነበር። ከእንዲህ ዓይነት ሰው ጋር የሚኖርና ወደ ቤቱም የሚገባ፥ እንደ ርኩስ ተደርጎ ይቆጠራል። ስለሆነም አይሁዶች ከቆዳ ፋቂዎች ይርቁ ነበር። ጴጥሮስ የይሁዲነት ባህላዊ አመለካከቱን ለመተው የመጀመሪያውን እርምጃ የወሰደው፥ መንፈስ ቅዱስ በሥርዓቱ መሠረት ንጹሕ ካልሆነ ሰው ጋር እንዲኖር በመራው ጊዜ ነበር። (ይህ በብዙ ኢትዮጵያውያንም ዘንድ በሚናቁ እንደ ሸክላ ሠሪ፥ ቀጥቃጭ፥ ቆዳ ፋቂ ባሉት ቤት እንደ መኖር ይቆጠር ነበር።) ሐ. እግዚአብሔር፥ ጴጥሮስ ንጹሕ ያልሆነ እንስሳ ሥጋ በራእይ እንዲያይ አደረገ። በእግዚአብሔር ዕቅድ መሠረት ወንጌል የዘር ልዩነት ጋሬጣዎችን ጠራርጎ በቀጥታ ወደ አሕዛብ የሚደርስበት ጊዜ ደረሰ። ይህ ሁሉ ሂደት የተፈጸመው ቆርኔሎዎስ በተባለ አንድ ሰው ቤት ነበር። ቆርኔሌዎስ በቂሣርያ የሚኖር የሮም ወታደር ነበር። ቂሣርያ በፍልስጥኤም ምድር በሮማውያን ቁጥጥር ሥር የምትገኝ ግዛት ነበረች። መንፈስ ቅዱስ ብዙ አማልእክትን ያመልክ በነበረው ቆርኔሌዎስ ልብ ውስጥ መሥራት ጀመር። ቆርኔሌዎስ ብዙ አማልእክት ማምለኩን ትቶ የብሉይ ኪዳኑን ብቸኛ እውነተኛ አምላክ ማምለክ ጀመረ። እግዚአብሔር በመልአኩ አማካይነት ቆርኔሌዎስ 50 ኪሎ ማትር ርቆ በኢዮጴ ወደሚገኘው ወደ ጴጥሮስ መልእክተኛ እንዲልክ ነገረው። በዚያኑ ጊዜ፥ እግዚአብሔር፥ ጴጥሮስ ከአይሁድ የወረሳቸውን ሁለት ዐበይት ጥላቻዎች እንዲያስወግድ አድርጎት ነበር። በመጀመሪያ፥ እግዚአብሔር ጴጥርስ አሕዛብን እንዲቀበል ፈቅዶ ነበር። ሁለተኛ፥ እግዚአብሔር፥ ጴጥሮስን ሰዎች ስለሚመገቧቸውና መመገብ ስለሌለባቸው ነገሮች የነበረውን የአይሁድ ልምድ እንዲተው አግዞት ነበር። እግዚአብሔር የውሻ ሥጋና ትላትሎችን እንድትበላ ቢያዝህ፥ ምን ትሆናለህ? በተመሳሳይ ሁኔታ፥ ጴጥሮስ የደነገጠው፥ እግዚአብሔር ውሻዎችን፥ ጦጣዎችን፥ ትላትሎችን፥ እባቦችንና ብዙ ዓይነት ርኩስ እንስሳትን እንዲመገብ ሦስት ጊዜ (እውነቱ በጣም አስፈላጊ ስለሆነና ለጴጥሮስም መቀበሉ በጣም ከባድ ስለሆነበት ነበር፥ እግዚአብሔር ሦስት ጊዜ ያሳየው) ስለነገረው ነው። ጴጥሮስ «እግዚአብሔር የቀደሰውን አታርክስ» የሚለውን ትምህርት የግድ መቀበል ነበረበት። በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠሩ አሕዛብ ርኩሳን አልነበሩም። እግዚአብሔር የፈጠረው ምግብም ለእግዚአብሔር ሕዝብ ርኩስ አልነበረም፡፡ (ማቴ. 15፡11 እና 1ኛ ጢሞ. 4፡3-5 በመመልከት፥ ክርስቶስና ጳውሎስ ክርስቲያኖች የትኛውንም ምግብ ሊመገቡ እንደሚችሉ መግለጻቸውን አስተውል። ዛሬ ውሾችንና አሣማዎችን የማንበላው በመንፈሳዊ ሕይወታችን ላይ ችግር ስለሚያስከትሉ ሳይሆን፥ ከባሕላችን የተነሣ ስለማንፈቅዳቸው ነው። መ. ጴጥሮስ አሕዛብ ከእርሱ ጋር እንዲኖሩ ፈቀደ፡- በግልጽ ባይነገረንም፥ ቆርኔሌዎስ የላካቸው ሦስት ሰዎች አሕዛብ ሳይሆኑ አይቀሩም። ከቤት ውጭ እንዲቀመጡ በማድረግ ፈንታ፥ ጴጥሮስ ከራሱ ጋር እንዲቆዩ አድርጓል። በዚህ ጊዜ ከአሕዛብ ጋር በመኖሩ ምክንያት እረክሳለሁ የሚለው ፍርሃቱ ተወግዶአል። ሠ. ጴጥሮስ አሕዛብ ወደ ይሁዲ እምነት ሳይለወጡ ከእግዚአብሔር ጋር ግንኙነት ሊያደርጉ እንደሚችሉ ተገነዘበ፤ መልአኩ ከቆርኔሌዎስ ጋር እንዴት እንደ ተገናኘ ሲሰማ፥ «እግዚአብሔር ለሰው ፊት እንዳያደላ ነገር ግን በአሕዛብ ሁሉ እርሱን የሚፈራና ጽድቅን የሚያደርግ በእርሱ የተወደደ እንደሆነ» አስተዋለ (የሐዋ. 10፡34-35)። ከዚያም ጴጥሮስ ለቆርኔሌዎስና በቤቱ ለተሰበሰቡት ስለ ኢየሱስ ሞትና ትንሣኤ እንዲሁም እግዚአብሔር የብሉይ ኪዳን ትንቢቶችን እንዴት እንደ ፈጸመ በመግለጽ አስተማረ። ጴጥሮስ ንስሐ ገብተው እንዲያምኑ ከመጠየቁ በፊት፥ መንፈስ ቅዱስ በአሕዛብ አማኞች ላይ ወረደ። እነዚህ አሕዛብ ጴጥሮስ ካሰማው ስብከት ወንጌሉን ተረድተው በክርስቶስ ስላመኑ፥ መንፈስ ቅዱስ በፍጥነት ወረደባቸው። በቆርኔሌዎስ ቤት ከተፈጸሙት ነገሮች መካከል በርካታ አስፈላጊ ነገሮችን መማር እንችላለን፡- ጴጥሮስ የመጨረሻውን የወንጌል በር እንዲከፍት እግዚአብሔር ተጠቅሞበታል። እግዚአብሔር የወንጌልን በር ለአይሁዶች ለመክፈትና የሳምራውያኑን እምነት ለማረጋገጥ እንደ ተጠቀመበት ሁሉ፥ አሁንም የወንጌሉን በር ለአሕዛብ ለመክፈት በዚሁ ሐዋርያ ተገልግሏል። እግዚአብሔር አሕዛብ በእኔ ዘንድ ተቀባይነት የምታገኙት የአይሁድ እምነትን ስትቀበሉ፥ ስትገረዙ የብሉይ ኪዳንን የአመጋገብ ሕጎችና ሌሎች ሥርዓቶችን ስትከተሉ ነው አላላቸውም። የጠየቃቸው ነገር ቢኖር በክርስቶስ አምነው እምነታቸውን በተለወጠ ሕይወት አማካይነት እንዲያሳዩ ብቻ ነበር። አንዳንድ ክርስቲያኖች እንደሚያስተምሩት፥ መንፈስ ቅዱስ የመጣው ከደኅንነት በኋላ ዘግይቶ አልነበረም። በታሪኩ ላይ እንደምናነበው ባመኑበት ቅጽበት መንፈስ ቅዱስ መጣ። መንፈስ ቅዱስ የወረደው ጴጥሮስ እጁን በጫነባቸው ጊዜ እልነበረም። ገና ጴጥሮስ ሲናገር ሳለ መንፈስ ቅዱስ ወረደባቸው። መንፈስ ቅዱስ የመጣላቸው በእግዚአብሔር ሉዓላዊ ፈቃድ እንጂ፥ በጸሎት አልነበረም። ይህ ሁኔታ መንፈስ ቅዱስ በአንድ መንገድ ብቻ እንደማይመጣ ያሳያል። መንፈስ ቅዱስ እንደ መጣ የተረጋገጠው በልሳን በመናገራቸው ነበር። ይህ ምልክት መንፈስ ቅዱስ መጀመሪያ በኢየሩሳሌም አይሁዶች ላይ በወረደ ጊዜ ታይቷል። ቀደም ብለን እንደተመለከትነው፥ መንፈስ ቅዱስ በሳምራውያኑ ላይ በወረደ ጊዜ በልሳን ሲናገሩ አላየንም። በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር ክርስቲያኖች በደረጃ እንደማይበላለጡ ለአይሁዶች ሊያሳይ ፈለገ። ቤተ ክርስቲያን የታነጸችው በአይሁዶች ወይም በልሳን በሚናገሩ ወይም መንፈሳውያን በሚመስሉ ወይም በአሕዛብ ወይም ልሳን በማይናገሩ ወይም መንፈሳዊያን በማይመስሉ ሰዎች አይደለም። በክርስቶስ አካል ውስጥ ሊኖር የሚገባውን አንድነት ለማሳየት፥ እግዚአብሔር ለአይሁድና ለአሕዛብ እማኞች ያንኑ አንዱን መንፈስ ቅዱስ ሰጣቸው። ራሱ ጴጥሮስ ሲናገር፥ «እነዚህ እንደ እኛ ደግሞ መንፈስ ቅዱስን የተቀበሉ» (የሐዋ. 10፡47) ይላል። ይህ መንፈስ ቅዱስ በልሳን የተገለጸበት ሁኔታ፥ የአይሁድ ክርስቲያኖችን አስደነቃቸው። ከዚህ ነገር በኋላ መንፈስ ቅዱስ በአይሁድና በሰማርያ ሰዎች ላይ በወረደው ዓይነት በእጅ መጫን ሥርዓት፥ በአሕዛብ ክርስቲያኖች ላይ ሲወርድ የሚያሳይ መረጃ በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ አናገኝም። በልሳን መናገር ለመጀመሪያዎቹ የአሕዛብ ክርስቲያኖች መንፈስ ቅዱስን ለመቀበላቸው መረጃ ነበር። በኋላ ጳውሎስ ለሌሎች የአሕዛብ ክርስቲያኖች እንደ ገለጻው፥ ይህ ከመንፈሳዊ ስጦታዎች አንዱ ስለሆነ ብዙዎቹ በልሳን አልተናገሩም (1ኛ ቆሮ. 12፡29-30)። የአሕዛብ ክርስቲያኖች ካመኑና መንፈስ ቅዱስን ከተቀበሉ በኋላ ወዲያው ተጠመቁ። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እገሌ ከዚህ ጎሣ ነው፥ እገሌ ከዚያ ጎሣ ነው የሚለው አስተሳሰብ ስፍራ ሊሰጠው አይገባም። ምክንያቱም እግዚአብሔር ለጴጥሮስ እንዳመለከተው፣ በዘርና በጎሣ መካከል እርሱ አያደላም። ሰዎች ሁሉ በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠሩ በመሆናቸው፥ ሁሉም እኩል

ጴጥሮስ በይሁዳና ቂሣርያ ያካሄደው አገልግሎት (የሐዋ. 9፡32-10፡48) Read More »

የጳውሎስ መለወጥ (የሐዋ. 9፡1-31)

በአንድ ወቅት አንድ ጫማ የሚሸጥ ሰው ነበረ። አንድ ቀን አንድ ሰው ስለ ክርስቶስ መሰከረለት። መንፈስ ቅዱስ ልቡን ለውጦ በክርስቶስ እንዲያምን ረዳው። ወዲያውኑ ሥራውን ትቶ ተነሣና መጀመሪያ ለአነስተኛ ቡድኖች፥ ከዚያም በሺህ ለሚቆጠሩ ሰዎች ስለ ክርስቶስ መመስከር ጀመረ። በምዕራቡ ዓለም ይህ ሰው በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት ለውጧል። ለክርስቲያን ሠራተኞች ያቋቋመው ትምህርት ቤት ዛሬም ዓለምን በመለወጥ ላይ ይገኛል። በእኛ ዘመን ብዙ አገልግሎት እንደ ሰጠው እንደ ቢሊ ግርሃም ሁሉ፥ ድዋይት ኤል. ሙዲም በ18ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ አካባቢ አሜሪካንና አውሮፓን በከፍተኛ ደረጃ ለውጧል። በአንድ የማይታወቅ ሰው ምስክርነት ዓለም ተለወጠች። እግዚአብሔር ለሰዎች ምን ዕቅድ እንዳለው አናውቅም። እግዚአብሔር የጎዳና ተዳዳሪዎችን፥ ሴተኛ አዳሪዎችን፥ ድሆችን፥ ወይም በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ አንዱን ትንሽ ልጅ ወስዶ ዓለምን ለመለወጥ ሊጠቀምባቸው ይችላል። እኛ ብዙ ጊዜ የምናተኩረው በጀማ ስብከት ላይ ነው። በእግዚአብሔር ዓይን ግን ለአንድ ሰውም (እንደ ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ) ሆነ ለብዙ ሰው መስበክ ለውጥ የለውም። እርሱ አንድን ሰው ተጠቅሞ ዓለምን መለወጥ ይችላል። በጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ዘንድ ከሌሎች ሰዎች ሁሉ ይልቅ ክርስትናን ለዓለም ሕዝብ ለማስተዋወቅ ትልቅ ተግባር ያከናወነ አንድ ሰው አለ። ስሙ መጀመሪያ ሳውል ሲሆን፥ በኋላ ጳውሎስ ተብሏል። አነስተኛ የአይሁድ ስብስብ የነበረችው ቤተ ክርስቲያን፥ በጳውሎስ አገልግሎት በመላው ዓለም ታላቅ እምነት ለመሆን በቅታለች። ዛሬም የጳውሎስ አገልግሎትና የጻፋቸው መጻሕፍት ዓለምን በመለወጥ ላይ ናቸው። ሉቃስ ስለ ጥንቷ ቤተ ክርስቲያን በጻፈው ታሪክ ውስጥ፥ ለጳውሎስ አገልግሎት ትኩረት ሰጥቷል። ሉቃስ መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን ከይሁዲነት ወጥታ በአሕዛብ ሁሉ ዘንድ እንድትሰፋ ለማድረግ ጳውሎስን እንዴት እንደ ተጠቀመበት አብራርቷል። በጳውሎስ አማካይነት ወንጌል ወደ ቱርክና ወደ ምሥራቅ አውሮፓ ተስፋፍቷል። ከጊዜ በኋላ በፍልስጥኤምና በአፍሪካ ምድር እስልምና እየሰፋ ሲሄድ፥ እግዚአብሔር ወንጌልን በዓለም ሁሉ ለማዳረስ በአውሮፓ የነበረችውን ቤተ ክርስቲያን ተጠቅሟል። ሉቃስ ስለ ጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ሲተርክ፥ ትኩረቱን ከጴጥሮስ ወደ ጳውሎስ ያደርጋል። ጴጥሮስ ወደ አይሁድ የተላከ ሐዋርያና እግዚአብሔርም ቤተ ክርስቲያንን እንዲመሠረት የተጠቀመበት ሰው ነው። ጳውሎስ ደግሞ ወንጌልን ለአሕዛብ ለመስበክ የተላከ ሐዋርያ ነው። ትላንት ሉቃስ በቀድሞ ስሙ ሳውል (የአይሁድ ስም)፥ በኋላም ጳውሎላ (የሮም ስም) የተባለውን ሰው እንዳስተዋውቀን ታስታውሳላችሁ። ቀድሞ የቤተ የክርስቲያኖች አሳዳጅ የነበረው ሳውል በኋላ ጳውሎስ፥ እንዴት የአሕዛብ ሐዋርያ ሊሆን እንደ ቻለ እንመለከታለን። ሉቃስ በጳውሎስ ምስክርነት ስለ ተደነቀ በመጽሐፉ ውስጥ በተለያዩ ሦስት ስፍራዎች ጠቅሶታል (የሐዋ. 9፡1-31፤ 22፡1-21፤ 26፡1-3)። የውይይት ጥያቄ፦ ሀ) እግዚአብሔር በሰዎች ሕይወት ውስጥ እንደሚሠራ ከዚህ ክፍል ምን እንማራለን? ለ) ስለ ቤተ ክርስቲያን መስፋፋት ምን እንማራለን? ሐ) ሉቃስ ስለ ቤተክርስቲያን እንድናውቅና እንድንከትል የሚፈልጋቸው እውነቶች ምንድን ናቸው? የጳውሎስ መለወጥ (የሐዋ. 9፡1-3) ከእስጢፋኖስ መገደል በኋላ፥ አይሁዶች በክርስቲያኖች ላይ የነበራቸው ጥላቻ እየበረታ በመምጣቱ የመጀመሪያው ስደት በቤተ ክርስቲያኖች ላይ ተነሣ። ይህ ስደት የመጣው ከሮም የፖለቲካ መሪዎች ሳይሆን፥ ከአይሁድ የሃይማኖት መሪዎች ዘንድ ነበር። ከታሪክ እንደምንረዳው ክርስቶስን ለመከተል በወሰኑ ሰዎች ላይ ስደትን የሚያስነሡት የፖለቲካ መሪዎች ሳይሆኑ፥ የሃይማኖት መሪዎች ናቸው። ከክርስቶስ ሞት በኋላ – በኢየሩሳሌም የነበረው የፖለቲካ ሁኔታ ተለውጧል። የአይሁድ ሃይማኖት መሪዎችም ሰዎችን ለማሳደድና ለመግደል ሥልጣን አገኙ። እነርሱም፥ ሳውል የተባለው ዝነኛ ወጣት ክርስቲያኖችን አስሮ ለምርመራ ወደ ኢየሩሳሌም እንዲያመጣ ሥልጣን ሰጡት። ጳውሎስ በኋላ እንደ ገለጸው፥ እርሱ አስሮ ካመጣቸው ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ ተገድለዋል (የሐዋ. 22፡4፤ 26፡10)። በዚህ ስደት ምክንያት ክርስቲያኖች በፍልስጥኤም ምድር ሁሉ ተበተኑ። ሳውልም እየተከታተለ ያሳድዳቸው ጀመር። ለቤተ ክርስቲያን የተሰጠው የመጀመሪያ ስም «መንገድ» የሚል ነበር። ይህ ስም ለመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች የተሰጠበትን ምክንያት ባናውቅም፥ የጥንት ክርስቲያኖች ራሳቸው ያወጡት ስም ሳይሆን አይቀርም። ምናልባትም ይህ የክርስቶስ ተከታዮች እግዚአብሔር ያዘጋጀውን የጽድቅ መንገድ እንደሚከተሉ የሚያመላክት ይሆናል። አማኞቹ እግዚአብሔር በጥንት ዘመን ለነቢያቱ የሰጣቸው ትንቢት ፍጻሜ የሆነውን መሢሕ እየተከተሉ ነበር። ምናልባትም እርሱ «እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ» (ዮሐ 14፡8) በማለት የተናገረውን ሊያንጸባርቅ ይችላል። ደማስቆ በሶርያ አውራጃ የምትገኝ የሮም መዲና ስትሆን፥ ብዙ አይሁዶች ይኖሩባት ነበር። ምናልባትም የአይሁድ ሃይማኖት መሪዎች፥ ሃይማኖታዊ ጉዳዮቻቸውን ለመከታተል ከኢየሩሳሌም 180 ኪሎ ሜትር ርቃ ወደምትገኘው ደማስቆ ድረስ ተጉዘው፥ አይሁዶችን ለመቆጣጠር ከሮም ባለሥልጣናት ጋር ተስማምተው ሊሆን ይችላል። ጳውሎስ አይሁድ ክርስቲያኖችን በኢየሩሳሌም ለፍርድ ለማቅረብ ወደ ደማስቆ በመጓዝ ላይ ሳለ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ተገለጠለት። ምንም እንኳ ሰዓቱ እኩለ ቀንና ጠራራ ፀሐይ ቢሆንም፥ ከዚያ የላቀ የክርስቶስ የክብር ብርሃን በሳውሉ ላይ ወርዶ ለዓይነ ስውርነት አበቃው። በዚህ ጊዜ ጳውሎስ ክርስቶስን ባረገበት ክብሩ ተመለከተው (1ኛ ቆር. 9፡1፤ 15፡7-8)። ጳውሎስን እጅግ ያስደነቀው የተሰቀለው ክርስቶስ ሕያው ብቻ ሳይሆን፥ በታላቅ ኃይል የሚዝ መሆኑም ነበር። ክርስቶስ ጳውሎስ ያምን ዘንድ የሚያስፈልገውን ነገር ሁሉ አልነገረውም። ሐናንያ የተባለ ደቀ መዝሙር ስለ ክርስቶስና ስለ አዳኝነቱ ነግሮ ጳውሎስን ከክርስቶስ ጋር እንዲያስተዋውቀው ተጠቀመበት። ጳውሎስ ዓይነ ስውር እንደ ሆነ ወደ ደማስቆ ሄደ። እዚያ በቆየባቸው ሦስት ቀናት ውስጥ ስለ ብሉይ ኪዳኑ አምላክ የነበረውን ግንዝቤ በደማስቆ መንገድ ላይ ካጋጠመው ሁኔታ ጋር እንደሚያስማማው ምንም ጥርጥር የለውም። ሐናንያ በኢየሱስ የሚያምን ፈሪሃ እግዚአብሔር ያደረበት አይሁዳዊ ነበር። በደርግ ዘመን እግዚአብሔር ወደ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ሄዳችሁ ወንጌልን ስበኩለት ቢለን ኖሮ በጥያቄ ግራ እንደምንጋባ ሁሉ፥ ሐናንያም ክርስቲያኖችን በማሳደድ መጥፎ ስም ወደ ነበረው ወደ ጳውሎስ እንዲሄድ ክርስቶስ ሲያዝዘው ግራ ተጋባ። እግዚአብሔር ለሐናንያ ጳውሎስ መንግሥቱን ለማስፋፋት የተመረጠ መሣሪያ እንደ ሆነ ገልጾለት ነበር። ለአሕዛብ፥ ለነገሥታትና ለአይሁዶች ወንጌልን እንደሚሰብክ አብራራለት። ለጳውሎስም ገና ድነትን (ደኅንነትን) በተቀበለ ጊዜ ስለ ወንጌል መከራን እንደሚቀበል ነገረው። የውይይት ጥያቄ፡- እግዚአብሔር ጳውሎስ ክርስቶስን በመከተሉና ወንጌልን በመስበኩ ከፍተኛ ሥቃይ እንደሚደርስበት የገለጸው ለምን ይመስልሃል? ጳውሎስ አምኖ የዳነው መቼ ነበር? ጳውሎስ በኢየሱስ ማመን የጀመረው በደማስቆ መንገድ ላይ ከኢየሱስ ጋር ከተገናኘና በጸሎትና በጾም በቆየባቸው ሦስት ቀናት ውስጥ ነው። እምነቱ ሙሉ የሆነው ግን ሐናንያ ከመሰከረለት በኋላ ነው። በዚያን ጊዜ ዓይኖቹ ተከፈቱ፥ መንፈስ ቅዱስን ተቀበለ፥ ተጠመቀም። ሉቃስ በዚህ ጊዜ በጳውሎስ ሕይወት ስለተፈጸሙት ጉዳዮች ዝርዝር ነገር አልጻፈም። በገላትያ 1፡17-18 ላይ የተጠቀሱትን ሃሳቦች ከጳውሎስ ታሪክ ጋር ስናነጻጽር፥ ከዚህ የሚከተሉት ነገሮች የተከሰቱ ይመስላል። አንደኛው፥ ጳውሎስ በደማስቆ በሚገኙ ምኩራቦች ኢየሱስ መሢሕ እንደሆነ መስበክ ጀመረ። የኢየሱስ ጠላት የነበረው ሰው፥ አሁን ኢየሱስ ራሱ መሢሕ መሆኑን ይመሰክር ጀመር። የክርስቶስ ተከታዮች የነበሩትን ያሳድድ የነበረው ሰው፥ አሁን ያን ሁሉ ተወ። ጳውሎስ ስለ ክርስቶስ መሢሕነት በሚናገርበት ጊዜ ከብሉይ ኪዳን እየጠቀሰ የሚያቀርበው መረጃ እጅግ ብርቱ በመሆኑ፥ ማንም ሊቋቋመው አልቻለም። ሁለተኛው፥ ከዚያም ጳውሎስ ወደ ዐረቢያ በረሃ ተጓዘ። በዚያም ለሦስት ዓመት ያህል ተቀመጠ። ይህንንም ያደረገው አሁን ባገኘው አዲስ ብርሃን አማካይነት ቅዱሳት መጻሕፍትን በማንበብ የእግዚአብሔርን ዕቅድ ለማስተዋል ነበር። ቀደም ሲል ፈሪሳዊ ላለ የተማረውን ነገር አሁን ኢየሱስ መሢሕ ነው ከሚለው አንጻር መመርመር ነበረበት። ሉቃስ ይህን የጳውሎስን አገልግሎት በተመለከተ ምንም አልነገረንም። ሦስተኛው ለአገልግሎት ወደ ደማስቆ ተመለሰ። ሉቃስ ይህንን «ከብዙ ቀናት በኋላ» ሲል ይገልጸዋል። በዚህ ጊዜ የጳውሎስ ትምህርት እጅግ ፍሬያማ በመሆኑ አይሁዶች ሊይዙት ፈለጉ። ነገር ግን በደማስቆ በነበሩት ክርስቲያኖች እርዳታ ከደማስቆ አመለጠ። ጳውሎስ በኢየሩሳሌም ወደነበሩት ክርስቲያኖች ዘንድ ሲመጣ፥ በእርግጥ እውነተኛ አማኝ ስለመሆኑ አንዳንድ ሰዎች ጥርጣሬ ገባቸው። ነገር ግን የመጽናናት ልጅ የሆነው በርናባስ ምንም ጥርጣሬ ሳይገባው ከጳውሎስ ጋር ተገናኘ። በርናባስ ክርስቶስ ከጳውሎስ ጋር ተገናኝቷል ብሎ ስላመነ፥ ከጴጥሮስና የክርስቶስ ወንድም ከነበረው ከያዕቆብ ጋር አስተዋወቀው። እነርሱም የጳውሎስ መለወጥ እውነት እንደሆነ ተገነዘቡ (ገላ. 1፡19)። ነገር ግን በኢየሩሳሌም የነበሩት አይሁዶች ሊይዙት ይፈልጉ ስለነበር፥ ጳውሎስ ከሌሎች ሐዋርያት ጋር ከመገናኘቱ በፊት ወደ ትውልድ አገሩ ወደ ተርሴስ እንዲሄድ ተደረገ። በቀጣዮቹ ዓመታት ውስጥ በጳውሎስ ሕይወት ውስጥ ስለተፈጸመው ምንም የምናውቀው ነገር የለም። ይህ «የጸጥታ

የጳውሎስ መለወጥ (የሐዋ. 9፡1-31) Read More »

የመጀመሪያው የክርስቲያኖች ስደት እና የፊሊጶስ ምስክርነት (የሐዋ. 8፡1-40)

የመጀመሪያው የክርስቲያኖች ስደት (የሐዋ. 8፡1-3) ክርስቶስ ስደት በደቀ መዛሙርቱ ላይ እንደሚመጣ በተደጋጋሚ አሳስቦአቸው ነበር። ለብዙ ዓመት፥ ክርስቲያኖች በአይሁዶች ዘንድ ተቀባይነት አግኝተው በሰላም ይኖሩ ነበር። ምንም እንኳ አልፎ አልፎ ሐዋርያት ቢታሰሩና ቢሰደቡም፥ ጠቅለል ባለ መልኩ ሲታይ፥ ክርስቲያኖች በሰላም ይኖሩ ነበር። ከእስጢፋኖስ መገደል በኋላ ግን የአይሁድ መሪዎች ስደትን አስነሡ። በሳውል አስተባባሪነት ክርስቲያኖች እየተያዙ እስር ቤት ይጣሉ ጀመር። ምንም እንኳ ሉቃስ ስለዚህ ጉዳይ ባይገልጽም፥ ጳውሎስ ለብዙ ክርስቲያኖች ሞት ምክንያት መሆኑን አልሸሸገም። ይህም በሕይወት ዘመኑ ሁሉ ሲጸጽተው ኖሯል (የሐዋ. 22፡4)። ስደት ሰይጣን ቤተ ክርስቲያንን ለማጥፋት የሚጠቀምበት መሣሪያ ነው። የሚገርመው ታዲያ፥ ስደት እግዚአብሔርም ዓላማውን ለመፈጸም የሚጠቀምበት ታላቅ መሣሪያ መሆኑ ነው። አንደኛው፥ ስደት እምነትን ያጠራል፥ እውነተኛነትን ያመጣል። እምነቱ ሞት እንደሚያመጣበት የሚያውቅ ሰው፥ ኢየሱስን ያለ እውነተኛ ምክንያት አይከተልም። ሁለተኛው፥ ስደት ክርስቲያኖች የወንጌሉን ብርሃን ይዘው በተለያዩ አገሮች እንዲሰራጩ ያደርጋል። በአንድ አውላላ ሜዳ መሀል ላይ ትልቅ እሳት ተቀምጧል፤ አንድ ሰው መጥቶ እሳቱን ቢበትነው፥ እሳቱ በሜዳው ሁሉ ላይ ይሰራጫል። አሁን እሳቱ አንድ መሆኑ ቀርቶ ብዙ ይሆናል። ልክ እንደ ብዙዎቻችን ሐዋርያቱም በኢየሩሳሌም ተደላድለው ተቀምጠው ነበር። ክርስቲያኖች ወንጌልን ከኢየሩሳሌም ውጭ ለማድረስ አልቻሉም። ሐዋርያቱ ወንጌልን ወደ ይሁዳ፥ ሰማርያና አሕዛብ አድርሱ ያላቸውን ጌታ አልታዘዙም፡፡ ስለሆነም፥ እግዚአብሔር በስደት አማካይነት ደቀ መዛሙርቱን በመበተን በየሄዱበት ሁሉ የወንጌል እሳት እንዲቀጣጠል አድርጓል። የውይይት ጥያቄ፡- ስደት እነዚህን ሁለት ነገሮች ሲያከናውን የተመለከትኸው እንዴት ነው? ፊልጶስ በሰማርያ መሰከረ (የሐዋ. 8፡4-25) ምንም እንኳ 12ቱ ሐዋርያት በእናት ቤተ ክርስቲያናቸው በኢየሩሳሌም ቢቀመጡም፥ ሌሎች ብዙ ክርስቲያኖች ግን በየስፍራው ተበትነው ነበር። ሉቃስ የሌሎች ክርስቲያኖችን ተግባር እንደ ምሳሌ ለመጥቀስ ሲል፥ ፊልጶስ ወንጌልን በሰማርያ መስበኩን ገልጾአል። ፊልጶስ ከሰባቱ ዲያቆናት አንዱ ነበር። እንደ ሐዋርያትና እስጢፋኖስ ሁሉ፥ የፊልጶስም መልእክት በተአምራት የታጀበ ነበር። ርኩሳን መናፍስት ከሰዎች ይወጡ ነበር። በመንፈስ ቅዱስ ኃይል በፊልጶስ አማካይነት የክርስቶስ አገልግሎት ከኢየሩሳሌም ውጭ ተስፋፋ። ሉቃስ ስለ ፊልጶስ አገልግሎትና ስሰማርያ ወንጌል እንዴት እንደ ተስፋፋ ሁለት ለየት ያሉ ነገሮችን ይነግረናል። አንደኛው፥ ስለ «አስማተኛው ሲሞን» የገለጸውን አሳብ ነው። ሉቃስ ሲሞንን የጠቀሰው ለሐሰተኞች ክርስቲያኖች ምሳሌ አድርጎ ሳይሆን አይቀርም። ሲሞን ያመነው ለግል ጥቅም ሲል ነው፤ ከጊዜ በኋላ የቤተ ክርስቲያን ጠላት ሆኗል። ሲሞን በሰማርያ አካባቢ በአስማተኛነቱ የታወቀ ሰው ሲሆን፥ በፊልጶስ በኩል የሚሠራውን የመንፈስ ቅዱስ ኃይል ሲመለከት ተደነቀ። እንደ ሌሎች ሳምራውያን በክርስቶስ አምኖ ተጠመቀ። ነገር ግን እምነቱ እውነተኛ ነበር ወይስ በራስ ወዳድነት ላይ የተመሠረተ? እምነቱ እውነተኛ አይመስልም ነበር። ጴጥሮስ የሰማርያ ክርስቲያኖች መንፈስ ቅዱስን እንዲቀበሉ እጁን ጭኖ በጸለየላቸው ጊዜ፥ ሲሞን አሁንም ስግብግብነት ልቡን ሞልቶት ነበር። ሲሞን መንፈስ ቅዱስን ለሌሎች ለማደል እርሱም ሥልጣን እንዲኖረው በማሰብ፥ ለጴጥሮስ ገንዘብ ሊሰጠው ሞከረ። በአስማቱ ገንዘብ ይሰበስብ እንደነበር ሁሉ፥ ይህንንም ጥሩ የንግድ አጋጣሚ አድርጎ ተመለከተ። ጴጥሮስ የሲሞንን ክፉ ምኞች ተመልክቶ፥ ከእግዚአብሔር ፍርድ አስጠነቀቀው። ሲሞን እግዚአብሔር እንዳይፈርድበት ፈርቶ ጴጥሮስ እንዲጸልይለት ከመጠየቁ ውጭ ያደረገው ነገር ስለሌለ፥ ከልቡ ንስሐ የገባ አይመስልም። ሲሞን በኋላ የሐሰት ትምህርት መሪ ሆኖ በክርስትና ላይ እንደተነሣና ብዙ ሳምራውያንን ከወንጌሉ መስመር እንደ መለሰ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ይነግረናል። የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) እንደ ሲሞን ለግል ጥቅም ሲሉ ያመኑ ሰዎች እንዴት እንዳጋጠሙህ ግለጽ። ለ) እንደዚህ ዓይነት ሰዎች እንዴት ከእምነት ወደ ኋላ እንደሚመለሱና አንዳንድ ጊዜም የክርስቶስ ጠላቶች እንደሚሆኑ አብራራ። ሐ) ይህ ሁኔታ ወንጌልን ስንሰብክ የሰዎች እምነት በሚታዩ ነገሮች ማለትም በጤንነት፥ በተአምራት፥ በሀብትና በመሳሰሉት ላይ እንዳይመሠረት ጥንቃቄ እንድናደርግ ምን ያስተምረናል? ሁለተኛው፥ ሉቃስ መንፈስ ቅዱስ በሰማርያ ክርስቲያኖች ላይ በተለየ ሁኔታ መውረዱን ገልጾአል። ሉቃስ ይህን ታሪክ የጠቀሰበት ምክንያት፥ መንፈስ ቅዱስ በሁለት ደረጃዎች መምጣቱ ያልተለመደ በመሆኑ፥ ክርስቲያኖች ልክ በዚሁ ዓይነት መንገድ ይመጣል ብለው እንዳይጠባበቁ ለማሳሰብ ሊሆን ይችላል። ይህ ባይሆን ኖሮ ሉቃስ ስለ ኢየሩሳሌም ክርስቲያኖች ሕይወት ሲናገር ከጠቀሳቸው አሳቦች ጋር ሊያዳብለው ይችል ነበር (የሐዋ. 2፡42-47፣ 4፡32-35)። ሳምራውያን ድነትን (ደኅንነትን) መቀበላቸውንና በእግዚአብሔርም ቤተሰብ ውስጥ እኩል መብት መጎናጸፋቸውን የአይሁድ ክርስቲያኖች ተረድተው የነበረባቸውን የእምነት ማጣት ዐቢይ መሰናክል ማሸነፍ ነበረባቸው። አይሁዶች ሳምራውያንን ይጠሏቸው ነበር። ቀደም ሲል እንደ ተመለከትነው፥ ከገሊላ ወደ ኢየሩሳሌም ለማለፍ ከሁሉም የሚቀርበው አቋራጭ መንገድ በሰማርያ በኩል አድርጎ ማለፍ ቢሆንም፥ በዚህ መንገድ ግን አይጠቀሙም ነበር። ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ፥ ክርስቶስ የሚጠብቁት መሢሕ እንደሆነ እንዲያሳውቃቸው ፊልጶስን ላከ። የኢየሩሳሌም ቤተ ክርስቲያን ስለ ሰማርያ ክርስቲያኖች የሚነገረውን ዜና ስትሰማ ለማመን ተቸገረች። ስለሆነም፥ ስለ ሁኔታው እንዲያጣሩ ሁለት ታላላቅ ሐዋርያትን (ዮሐንስንና ጴጥሮስን) ላኩ። ጴጥሮስና ዮሐንስ የሳምራውያኑ ክርስቲያኖች እምነት ትክክል መሆኑን ካረጋገጡ በኋላ፥ እጃቸውን በላያቸው ጭነው በመጸለይ መንፈስ ቅዱስን እንዲቀበሉ አደረጉ። በዚህ ክፍል መንፈስ ቅዱስ በሳምራውያኑ ላይ ሲወርድ የተገለጠበት ምልክት አልተጠቀሰም። መንፈስ ቅዱስ በተቀበሉ ጊዜ ግልጽ ምልክት እንደ ተከሰተ የሚያጠራጥር ባይሆንም፥ በልሳን መናገራቸው አልተጠቀሰም። ሳምራውያኑ መንፈስ ቅዱስን ከተቀበሉበት ሁኔታ በመነሣት ከዚህ የሚከተሉትን ነጥቦች ልንገዘብ እንችላለን። ሀ. ሁሉም ሳምራውያን መንፈስ ቅዱስን የተቀበሉት በአንድ ጊዜ ነበር። አንዳንዶች ሲቀበሉ፥ ሌሎች ግን ያልተቀበሉበት ሁኔታ አልተገለጸም። ለ. ይህ የመንፈስ ቅዱስ መገኘት እንጂ፥ የመንፈስ ቅዱስ ሙላት አይደለም። ሐ. የሰማርያ ክርስቲያኖች ካመኑ በኋላ፥ መንፈስ ቅዱስን ሳይቀበሉ እንደ ቆዩ የሚያመለክት አሳብ በሐዋርያት ሥራ ታሪክ ውስጥ አናገኝም። በአይሁድ ክርስቲያኖች ላይ ከተፈጸመው ጋር ተመሳሳይ ነው። ከሐዋርያት ሥራ 2 በኋላ የአይሁድ ክርስቲያኖች አምነው ሲድኑ፥ መንፈስ ቅዱስን ለመቀበል ሲጠባበቁ ግን አንመለከትም። መ. እግዚአብሔር ቀደም ሲል ለአይሁድ ክርስቲያኖች አሁን በክርስቶስ አማካይነት የእርሱ ሕዝብ እንዲሆኑ በይፋ ለማሳወቅ ጴጥሮስን እንደ ላከ ሁሉ፥ የሰማርያ ክርስቲያኖችም እንደ አይሁዳውያኑ ሁሉ የእግዚአብሔር ቤተሰብ አባላት መሆናቸውን በይፋ ለማወጅ ጴጥሮስን ተጠቅሞበታል። ይህም ጴጥሮስ የመንግሥተ ሰማይ መክፈቻ ቁልፍ ከመያዙ ልዩ ኃላፊነት ጋር የተያያዘ ነበር (ማቴ. 16፡19)። እያንዳንዱ አዲስ ቡድን ወደ እግዚአብሔር ቤተሰብ ተቀላቅሎ እንዲያገለግል እግዚአብሔር የመረጠው እርሱን ነበር። ሠ. እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስን በሳምራውያን ክርስቲያኖች ላይ ሳያወርድ ከቆየባቸው ምክንያቶች አንዱ፥ በእግዚአብሔር ቤተሰብ ውስጥ የጎሣ ልዩነት እንደሌለ ለአይሁዶች ለማስተማር ነው። ከእንግዲህ በኋላ አይሁድ፥ ሳምራዊ፥ አሕዛብ ብሎ ነገር አይኖርም። ይልቁንም ሁሉም አንድ ቤተሰብ ይሆናሉ። በእግዚአብሔር ቤተሰብ መካከል መበላለጥ እንደሌለ ለማሳየት፥ መንፈስ ቅዱስ በሳምራውያኑ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲወርድ በልዩ ሁኔታና ኃይል ወረደ። ረ. መንፈስ ቅዱስን ለመቀበል የተደረገ ጸሎትም ሆነ አዲስ አማኞች በልሳን እንዴት እንደሚናገሩ የተሰጠ ትምህርት አልነበረም፡፡ (መንፈስ ቅዱስ በእነርሱ ላይ እንደ ወረደ ምልክቱ በልሳን መናገር ነው የምንል ከሆነ)። ጴጥሮስ እጁን ጭኖ እስኪጸልይላችው ድረስ መንፈስ ቅዱስ በሰማርያ ሰዎች ላይ ሳይወርድ ቆይቶ፥ ከዚያ በኋላ ግን በሁሉም ላይ ወረደ። ይህ ክፍል፥ መንፈስ ቅዱስ በተለመደው ሁኔታ ማለትም ሰዎች ድነትን (ደኅንነትን) ካገኙ በኋላ ወደ እነርሱ ይመጣል የሚለውን አሳብ የሚያንጸባርቅ አይመስልም። ጳውሎስ መንፈስ ቅዱስ የሌለው ሰው ክርስቲያን ሊሆን እንደማይችል ገልጾአል (ሮሜ 8፡9)። የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) የዚህ መጽሐፍ ጸሐፊ ይህን ክፍል የሚረዳበትን መንገድ ሌሎች ካሪዝማቲክ ክርስቲያኖች ከሚረዱበት መንገድ ጋር አነጻጽር፡፡ ልዩነቱና ተመሳሳይነቱ ምንድን ነው? ለ) አንተ የትኛውን አመለካከት ትደግፋለህ? ለምን? ስለ መንፈስ ቅዱስ መገኘትና ሙላት ያለህን አመለካከት ለመግለጽ፥ ከመልእክቶች ውስጥ በጥቅሶች ተጠቀም። በማቴዎስ 28፡19-20 ላይ ክርስቶስ በአብ፥ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እንድናጠምቅ አዝዞን ሳለ፥ ሉቃስ ስለ ጥምቀት ሲናገር «በኢየሱስ ስም» የሚለውን ብቻ የጠቀሰው ለምንድን ነው? የ «ኢየሱስ ብቻ» ተከታዮች፥ ይህ ሥላሴ የሚባል ትምህርት ትክክል እንዳልሆነና ክርስቶስ እግዚአብሔር አብ እንደሆነ የሚናገር ነው ይላሉ። የዚህን ምክንያት ሙሉ በሙሉ ባናውቅም፥ የአይሁዶችን አስተሳሰብ መመልከቱ ጠቃሚ ነው። አይሁዶችና የሰማርያ ሰዎች እግዚአብሔር አብን ያውቁታል። መንፈስ ቅዱስ የሚለውም እሳቤ ለእነርሱ እንግዳ አይደለም። ነገር ግን በዓይናቸው ያዩትን፥ ሲናገር የሰሙትን፥ የዳሰሱትን፥

የመጀመሪያው የክርስቲያኖች ስደት እና የፊሊጶስ ምስክርነት (የሐዋ. 8፡1-40) Read More »

እስጢፋኖስ የመጀመሪያው የቤተ ክርስቲያን ሰማዕት (የሐዋ.6፡8-7፡60)

ሉቃስ ስለ ጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ በሚናገርበት ጊዜ፥ ትኩረቱን ከጴጥሮስ ወደ ጳውሎስ ላይ ያደርጋል። ነገር ግን ሉቃስ መንፈስ ቅዱስ ወንጌልን እስከ ምድር ዳርቻ ለማድረስ ጳውሎስን እንዴት እንደ ተጠቀመበት ከመግለጹ በፊት፥ ቤተ ክርስቲያን በኢየሩሳሌም ተወስና ከተቀመጠችበት ሁኔታ በመነሣት በሮም ማዕከል ስለሆነችበት ሁኔታ ያብራራል። እግዚአብሔር ወንጌልን መጀመሪያ ወደ ሰማርያ፥ ቀጥሎም ብዙ አሕዛብ በክርስቶስ ወዳመኑባት እንጾኪያ ለማድረስ የተጠቀመባቸው ግለሰቦች፥ አሁን ወንጌሉን እስከ ምድር ዳርቻ ለማድረስ ተልእኮ የተሰጣቸው የመጀመሪያዎቹ አለመሆናቸው የሚያስደንቅ ነው። እግዚአብሔር በሌሎች ሰዎች ነበር የተጠቀመው። ሉቃስ ስለ እነዚህ የለውጥ ጊዜያት በሚያብራራበት ወቅት፥ እስጢፋኖስና ፊልጶስ በተባሉ ሁለት ዲያቆናት ላይ አጽንኦት ሰጥቷል። እስጢፋኖስ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ መበለቶችን እንዲያገለግል የተመረጠ የግሪክ አይሁዳዊ ነበር። ይህ ማለት ግን መንፈስ ቅዱስ የሰጠውን አስደናቂ ስጦታ በሌሎች መንገዶች ከጥቅም ላይ ሊያውል አይችልም ማለት አይደለም። ሐዋርያትም፥ «መስበክ፥ ማስተማርና መፈወስ» የእኛ አገልግሎት ነው። ብለው በቅናት መንፈስ ተይዘው የእስጢፋኖስን አገልግሎት አላገዱም። ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስ በወደደው ሰው ሁሉ አማካይነት ሊሠራ እንደሚችል ተገንዝበው ነበር። ስለሆነም መንፈስ ቅዱስ ለአንድ ሰው ስጦታዎችን በሚያድልበት ጊዜ፥ ሐዋርያት የአገልግሎት በር አይዘጉበትም ነበር። ዛሬም ብዙ ሽማግሌዎች ይህን ምሥጢር ማወቅ ይኖርባቸዋል። አንዳንድ አገልግሎቶችን መፈጸም ያለባቸውና ክብርንም መውሰድ ያለባቸው እነርሱ ብቻ እንደሆኑ በማሰብ ሰዎችን አጥብቀው የሚቆጣጠሩ ከሆነ፥ ደስ ያሰኘውን ሰው የመምረጥና የመገልገል መብት ያለውን መንፈስ ቅዱስን መቃወማቸው ነው። አንድ ሽማግሌ በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ የአንድን ሰው አገልግሎት በሚወስንበት ጊዜ፥ መንፈስ ቅዱስን መቃወሙ ነው፡፡ ይህ ችግር ዘወትር ስለሚከሰት፥ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ያላቸው ሰዎች ለብዙ ዓመታት ያገለገሉበትን ቤተ ክርስቲያን ጥለው በመሄድ፥ በነጻነት ለማገልገል ወደሚችሉባቸው አብያተ ክርስቲያናት ይፈልሳሉ። እስከዚህ ጊዜ ድረስ፥ የማስተማርና የመፈወስ አገልግሎት ሲያከናውኑ የነበሩት ሐዋርያቱ ብቻ ነበሩ። አሁን ግን እስጢፋኖስ እንደ እነርሱ ከፍልስጥኤም ውጭ የኖሩ አይሁዶችን ለማስተማር ነጻነት አገኘ። በኢየሩሳሌም ብዙ ምኩራቦች ነበሩ። ከእነዚህም መካከል አንዳንዶቹ የፍልስጥኤም አይሁድ ያልሆኑ ሰዎች የሚሰበሰቡበት ነበር። ከምኩራቦቹ አንዱ «ነፃ የወጡ ሰዎች ምኩራብ» ይባል ነበር። በዚህ ምኩራብ ውስጥ ሲሰበሰቡ ከነበሩት ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ ከቀሬና፥ ከእስክንድሪያ፥ ኪልቂያና እስያ የመጡ አይሁዶች ነበሩ። እነዚህ አይሁዶች ባርያ ሆነው የኖሩና በኋላ ነጻነታቸውን ያገኙ ነበሩ። እነዚህ ሰዎች ቀደም ሲል ባሪያዎች የነበሩ ከመሆናቸው በተጨማሪ፥ ከፍልስጥኤም ውጭ የመጡ በመሆናቸው፥ አንድ ላይ ተሰባስበው የራሳቸውን ምኩራብ አቋቋሙ። 12ቱ ሐዋርያት በሙሉ ከፍልስጥኤም አካባቢ የመጡ በመሆናቸው ተቀባይነትን ለማግኘት ወደማይችሉባቸው ምኩራቦች እስጢፋኖስ ሄደ። ስለ ክርስቶስ ወንጌል በሚናገርበት ጊዜ እነዚህ አይሁዶች እጅግ ተቆጡ። ስለ እስጢፋኖስ የሐሰት ወሬ ካሰራጩ በኋላ፥ ለምርመራ ወደ አይሁድ ሸንጎ አቀረቡት። ሉቃስ የእስጢፋኖስን ረዥም ስብከት የዘገበበት በርካታ ምክንያቶች አሉት። አንደኛው፥ የእስጢፋኖስ ስብከት ሐዋርያትና ሌሎች የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ክርስቶስ የአይሁድ መሢሕ መሆኑን በመግለጽ ላቀረቡት ስብከት ምሳሌ ነበር። ሁለተኛው፥ ስብከቱ ቢያንስ እስጢፋኖስ ከኢየሩሳሌምና ከአይሁዶች በተጨማሪ በርከት ላሉ አካባቢዎች መመስከር መጀመሩን ያሳያል። እስጢፋኖስ እግዚአብሔር ታላላቅ ሥራዎችን ከፍልስጥኤም ውጭ ላሉ አይሁዶች ማድረጉን ገልጾአል። እግዚአብሔር በኢየሩሳሌምና ይሁዳ የተወሰነ ሳይሆን፥ ለዓለም ሁሉ ዕቅድ ያለው አምላክ ነው። ሦስተኛው፥ ስብከቱ በተጨማሪም በቤተ ክርስቲያንና በይሁዲነት መካከል ትልቅ ልዩነት መፈጠሩን የሚያሳይ ይመስላል። እስጢፋኖስ የእግዚአብሔር ሕዝብ የአምልኮ ማዕከል ከእንግዲህ በኋላ ኢየሩሳሌምና ቤተ መቅደሱ እንዳልሆኑ አሳይቷል፤ ደግሞም ከእንግዲህ በኋላ የሙሴን የብሉይ ኪዳን ሕጎች መከተል አስፈላጊ አለመሆኑን ገልጾአል። አይሁድ እስጢፋኖስ የቤተ መቅደስና የሙሴ ሕግጋት ተቃዋሚ እንደሆነ አድርገው የከሰሱት ለዚህ ሳይሆን አይቀርም። ከእስጢፋኖስ ስብከት ከዚህ የሚከተሉትን ፍሬ ነገሮች ማስተዋል እንችላለን። ሀ. የአይሁዶች ታሪክ የተጀመረው በፍልስጥኤም ላይሆን፥ በአሕዛብ መካከል ነበር። እግዚአብሔር አብርሃምን የጠራው የባቢሎናውያን ምድር ከሆነችው ዑር ነበር። ከነዓንን እንደሚወርስ የተስፋ ቃል ቢሰጠውም፥ አብርሃም ምንም መሬት አልነበረውም ማለት ይቻላል። ለ. ቀጣዩ የአይሁድ ዐቢይ ታሪክም የተፈጸመው በከነዓን ላይሆን በግብጽ ነበር። በእስጢፋኖስ ዘመን የነበሩት አይሁዶች በክርስቶስና በሐዋርያት ላይ ቅናት እንዳደረባቸው ሁሉ፥ የአይሁድ ቅድመ አያት የሆኑት አሥሩ የያዕቆብ ታላላቅ ልጆችም በዮሴፍ ላይ ቀንተው በባርነት ወደ ግብጽ ሸጡት። እግዚአብሔር ግን የግብጽ አሕዛብ አይሁዶችን እንዲያድኑ አደረገ። አሁንም እግዚአብሔር ፈቃዱን የፈጸመው ከኢየሩሳሌም ውጭ ነበር። ሐ. በአይሁድ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ስፍራ ያለው ሙሴ፥ በእግዚአብሔር የተመረጠው ግብጽ አገር እያለ ነበር። 120 ዓመት የሚሆነውን የሕይወት ዘመኑን ያሳለፈው ከከነዓን ውጭ በመጀመሪያ በግብፅ ቀጥሎም በምድያም፥ በመጨረሻም በምድረ በዳ ነበር። እግዚአብሔር ከሙሴ ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኘው ከፍልስጥኤም ውጭ በሲና ተራራ ላይ ነበር። እግዚአብሔር ለሕዝቡ የሠራቸው ታላላቅ ተአምራት፥ ከፍልስጥኤም ውጭ በምድረ በዳ የተከናወኑ ነበር። ሙሴ ከእርሱ የሚልቅ ነቢይ እንደሚመጣ የተነበየው በዚያ ነበር። እግዚአብሔር ቅዱስ ሕጉን የሰጠው ከፓ ለስቲና ውጭ በሲና ተራራ ላይ ነበር። መ. በሙሴ ዘመን እንደ ነበሩት እንደ ያዕቆብ ልጆች ሁሉ አይሁዶች እግዚአብሔርን ባለመታዘዝ በዐመፀኛነት ኖሩ። እግዚአብሔር በታላቅ ኃይሉ ነፃ ካወጣቸውም በኋላ እንኳ ልባቸው ግብፅ ስለነበር ወደዚያው ለመመለስ ይፈልጉ ነበር። ጣዖት ሠርተው ለማምለክ ሞክረዋል። በክርስቶስ ዘመን የታየው የአይሁዶች ዐመፀኛነት በምድረ በዳም በነበሩት አይሁዶች ላይ የታየ ነበር። ሠ. እግዚአብሔር የመረጠው የመገናኛው ድንኳን ንድፉ የተሠራው በአሕዛብ አገር ሳሉ ነበር። ንጉሥ ዳዊት እግዚአብሔር የሚኖርበትን ዘላቂ ቤተ መቅደስ ለመገንባት ፈለገ። አሳቡን ያመነጨው እግዚአብሔር አልነበረም። በእስጢፋኖስ ዘመን የነበሩት አይሁዶች የእግዚአብሔር ትኩረት፥ ፍቅርና ዓላማ በቤተ መቅደሱ እንደ ተጠቃለለ ያስቡ ነበር። ከ60 ዓመት ቀደም ብሎ የተገነባው ታላቁ የሄሮድስ ቤተ መቅደስ እጅግ ውብ በመሆኑ፥ እግዚአብሔር ምንም ነገር እንዲደርስበት አይፈልግም የሚል አሳብ ነበራቸው። ይህን ሲያስቡ ግን ማንኛውም ሰው ሠራሽ ሕንጻ እግዚአብሔርን ለማስተናገድ ብቃት እንደሌለው ዘንግተው ነበር። ፍጥረት በሙሉ እንኳ እግዚአብሔርን ሊይዝ አይችልም። ከቤተ መቅደስ እጅግ የምትበልጠው ምድር ራሷ በምሳሌያዊ አገላለጽ የእግሩ መረገጫ ብቻ ናት። የውይይት ጥያቄ፡- ዛሬ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ከሚደረግ ግንኙነትና አምልኮ በላይ በተለየ ሁኔታ እዚያ እንደሚገኝ በማሰብ፥ በቤተ ክርስቲያን ሕንጻ ላይ ከፍተኛ ትኩረት የምናደርገው እንዴት ነው? ዛሬ አንዳንድ ክርስቲያኖችም እግዚአብሔር በቤተ ክርስቲያናቸው ላይ ምንም ክፉ ነገር እንደማያደርስ አድርገው ያስባሉ። ቀደም ሲል የኮሚኒስት መንግሥት አብያተ ክርስቲያናትን በመዝጋት አምልኮ እንዲቆም ያደርጋል ብለው አላሰቡም ነበር። እግዚአብሔር ግን በቤተ ክርስቲያን ሕንጻ የተወሰነ አምላክ አይደለም። እግዚአብሔር ውብ የቤተ ክርስቲያን ሕንጻ ሠርተን እርሱ እንደሚኖርበት ልዩ ስፍራ እንድንመለከት አላዘዘንም። ከአንድ መቶ ዓመት በላይ የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን በግለሰብ ቤቶች እንጂ፥ በቤተ ክርስቲያን ሕንጻዎች ውስጥ አያመልኩም ነበር። በኮሚኒስት ዘመን አምልኮ ይደረግ የነበረው በአማኞች ቤት ውስጥ ነበር። በዚህ ጊዜ ቤተ ክርስቲያን አድጋለች። በዚህ ረገድ በእስጢፋኖስ ዘመን እንደ ነበሩት አይሁዶች የተሳሳተ አሳብ ይዘናል ማለት ነው። ረ. እስጢፋኖስ አይሁዶች እግዚአብሔር ስለ ፍልስጥኤም ምድርና ስለ አይሁድ ሕዝብ ብቻ እንደሚጨነቅ በማሰባቸውና በቤተ መቅደስ ላይ ከፍተኛ ትኩረት በማድረጋቸው፥ አድማጮቹ እንደ ብሉይ ኪዳን አይሁዶች ሆነው መገኘታቸውን ገልጾአል። አለማመን አሁንም በሕዝቡ ላይ ይታይ ነበር። በብሉይ ኪዳን አባቶቻቸው የእግዚአብሔርን መንገድና እርሱም የሰጣቸውን መሪዎች ተቃውመው ነበር። ሙሴ፥ ዳዊት፥ ኢሳይያስና ኤርምያስ ሁሉም አይሁዶች እግዚአብሔር የላካቸውን መሪዎች እንደ ተቃወሙ የሚያሳዩ ምሳሌዎች ናቸው። በእስጢፋኖስ ዘመን ደግሞ አይሁዶች መሢሑን ኢየሱስን ተቃውመዋል። የእስጢፋኖስ አድማጮችም እግዚአብሔር የላካቸውን ሐዋርያትና ክርስቲያኖችን በመቃወም ላይ ነበሩ። እንደ ብሉይ ኪዳኖቹ ሁሉ፥ በእስጢፋኖስም ዘመን የነበሩት አይሁዶች በእጃቸው የእግዚአብሔርን ሕግ ይዘው ነበር። የሚያስፈልገው ግን የእግዚአብሔርን ሕግ መታዘዝ እንጂ መያዝ አይደለም። አይሁዶች ክርስቶስን ባለመቀበላቸው የእግዚአብሔርን ሕግ ተላልፈዋል። በሥጋ የተገረዙ አይሁዶች ያልተገረዘ ልብ ነበራቸው። ይህም እነርሱ እንደሚንቋቸው አሕዛብ ያልተገረዙ አድርጓቸዋል። እስጢፋኖስ ለቤተ መቅደሱ ከፍተኛ ትኩረት አልሰጠም፤ እንዲያውም አድማጮቹን የመደባቸው ከዐመፀኞች ጎራ ነው፤ በዚህም ይሰሙት የነበሩት ሁሉ እጅግ ተቆጡ። ነገር ግን እግዚአብሔር የሰማይ በሩን ከፍቶ እስጢፋኖስ ዙፋኑንና በአብ ቀኝ በሥልጣን የተቀመጠውን ክርስቶስን እንዲመለከት ሲያደርግ፥ የአይሁዳውያኑ ቁጣ ቅጥ አጣ፡፡

እስጢፋኖስ የመጀመሪያው የቤተ ክርስቲያን ሰማዕት (የሐዋ.6፡8-7፡60) Read More »

መከፋፈል በአይሁዶች መካከል (የሐዋ 6፡1-7)

በኢትዮጵያ በአንዲት ትልቅ ከተማ ውስጥ ከአንድ ትልቅ ነገድ የተገኙ ሰዎች ይኖሩ ነበር። ለሥራ ወደ አካባቢው የሄዱ የደቡብ ኢትዮጵያ ተወላጆች በአባልነት የሚሳተፉበት ቤተ ክርስቲያን በአካባቢው ነበረች። ሁሉም እንዲሰማው ሲባል አምልኮው በአማርኛ ቋንቋ ተደረገ ምንም እንኳ ትልቅ ጎሣ ከሚባለው ወገን ጥቂት ሰዎች በቤተ ክርስቲያኒቱ አምልኮ ፕሮግራም ላይ ቢገኙም፥ አገልግሎቱ በራሳቸው ቋንቋ ስለማይሰጥ ብዙዎች ቤተ ክርስቲያኒቱን እንደ ውጭ ተቋም አድርገው ይመለከቷት ነበር። ፕሮግራሙ ከሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች ለመጡ ሰዎች የተዘጋጀ መሰላቸው። የቤተ ክርስቲያኒቱ ሽማግሌዎች በሙሉ የሌላ አካባቢ ሰዎች በመሆናቸው ጥቂት የአካባቢው ሰዎች ቤተ ክርስቲያኒቱ ለአካባቢው ነዋሪዎች ተስማሚ እንድትሆን ለማድረግ የሚቻልበት መንገድ እንደሌለ ተገነዘቡ። በመጨረሻም፥ የአካባቢው ምእመናን ከቤተ ክርስቲያኒቱ ተገንጥለው የራሳቸውን ቤተ ክርስቲያን መሠረቱ። የመጀመሪያዪቱ ቤተ ክርስቲያን ከሌላ አካባቢ የመጡትን ሰዎች ብቻ ይዛ ቀጠለች። በሌላ የኢትዮጵያ ከተማ፥ አብዛኞቹ የቤተ ክርስቲያን አባላት የአካባቢው ነዋሪዎች ነበሩ። ለአምልኮ የሚያገለግለው የአካባቢው ቋንቋ ሲሆን፥ ሽማግሌዎቹም በሙሉ የአካባቢው ሰዎች ነበሩ። በዚያች ከተማና ቤተ ክርስቲያን ከሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች የመጡ ሰዎችም ነበሩ። የአካባቢው ሰዎች ሁሉንም ነገር ስለ ያዙ፥ ከሌሎች አካባቢዎች የመጡት ሰዎች የእንግድነት ስሜት ይሰማቸው ነበር። «አመለካከታችንን የምንገልጽበት መድረክ እንኳ የለንም። የሥራ መስኮች፥ የአመራር ቦታዎችና የመዝሙር አገልገሎቶች በሙሉ የተያዙት በአካባቢው ሕዝብ ብቻ ነው። እኛ ምንም ድርሻ የለንም። ይህ ፍትሐዊ አይደለም።» ሲሉ ያማርራሉ። የውይይት ጥያቄ:- ሀ) በኢትዮጵያ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ እንዲህ ዓይነት ችግሮችን እንዴት እንደ ተመለከትህ አብራራ። ለ) ሰይጣን በእነዚህ ሁኔታዎች ተጠቅሞ፣ በእግዚአብሔር ቤተሰብ ውስጥ መከፋፈልን ሊያስከትል የሚችለው እንዴት ነው? ሐ) የመጀመሪይቱ ቤተ ክርስቲያን ሽማግሌ ብትሆን ኖሮ፥ የአካባቢው ሰዎች የቤተ ክርስቲያኒቱ አካል መሆናቸው እንዲሰማቸው ለማድረግ ምን የተለየ ነገር ታደርግ ነበር? መ) የሁለተኛይቱ ቤተ ክርስቲያን ሽማግሌ ብትሆን፥ የአናሳው ጎሣ አባላት የቤተ ክርስቲያን አካል መሆናቸው እንዲሰማቸው ምን የተለየ ነገር ታደርግ ነበር? ሠ) የሐዋ 6፡4-7 አንብብ። የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ባሕላዊ ችግሮችዋን የፈታችው እንዴት ነበር? ከላይ የተጠቀሱትን ሁለት የአብያተ ክርስቲያናት ችግሮች ለመፍታት ከሐዋርያት ሥራ 6፡1-7 ልንጠቀምባቸው የምንችላችው መርሖዎች ምንድን ናቸው? መከፋፈል በአይሁዶች መካከል (የሐዋ 6፡1-7) በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ውጥረቶች መከሰታቸው የማይቀር ነው። በእኩል አልታየንም የሚሉ ቤተሰቦች፥ ጎሣዎችና ነገዶች ሁልጊዜ ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ እዚህን ውጥረች እንዴት መፍታት እንዳለብን ማወቅ ይኖርብናል፤ ምክንያቱም ሰይጣን መከፋፈልን ለመፍጠር ይጠቀምባቸዋል። ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ አስቀድሞ የጸለየው አንድነት እንዲኖራቸው ነበር (ዮሐ 17፡21)። ግን ሰይጣን የክርስቶስን ተከታዮች ለማሸነፍ ከሚጠቀምባቸው ታላላቅ መሣሪያዎቹ አንዱ መከፋፈል ነው። በጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሁለት ዓይነት የአይሁድ ሰዎች ነበሩ፡፡ በመጀመሪያ በፍልስጥኤም አገር የተወለዱ የአካባቢው አይሁዶች ነበሩ። እነዚህ ሰዎች የግሪክ ቋንቋ ቢናገሩም፣ በየዕለቱ የሚጠቀሙት ግን በአረማይስጥ ቋንቋ ነው፡፡ ራሳቸውን እንደ ንጹሕ አይሁድም ይቆጥሩ ነበር፡፡ እግዚአብሔር ለሕዝቡ ያቀደውን ሕይወት ያረክሳል ብለው ስለሚያስቡ፥ ከግሪኩ ባሕላ ጋር መቀላቀል አይፈልጉም ነበር፡፡ ሁለተኛው፥ የግሪክ አይሁዶች ነበሩ እነዚህ ከፍልስጥኤም ውጭ የተወለዱ አይሁዶች ነበሩ። አፍ መፍቻ ቋንቋቸው ግሪክኛ ሊሆን፥ ፍልስጥኤም አገር ከተወለዱ አይሁዶች የተለየ የአለባበስና የአኗኗር ሁኔታ ይታይባቸው ነበር፡፡ እነዚህ እሁዶች ብሉይ ኪዳንን እስካልተቃረነባቸው ድረስ፥ ከአሕዛብ ዓለምና ባሕል ጋር ተስማምተው ለመኖር ፈቃደኞች ነበሩ፡፡ ቀደም ሲል ከዓለም ሁሉ አይሁዶች ወደ ቤተ ክርስቲያን ይመጡ እንደነበር ተመልክተናል፡፡ ለምሳሌ፥ ከቆጵሮስ የመጣው በርናባስ፥ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ጠቃሚ ሰው ለመሆን በቅቷል። ከየትም ይምጡ ከየት፥ አይሁዶች ሁሉ ንብረቶቻቸውን እየሸጡ ለሐዋርያት ይሰጡ ነበር፡፡ ገንዘቡን እንደ አስፈላጊነቱ ማካፋፈል የሐዋርያቱ ተግባር ነበር። ነገር ግን ከውጭ የመጡት የግሪክ አይሁዶች ምንም መተዳደሪያ የሌላቸውን መበለቶች በማስተናበሩ ረገድ አድልዖ እንደ ተፈጸመ በማሰብ ቅሪታዎችን ያሰሙ ጀመር፡፡ የፍልስጥኤም አይሁዳውያን መበለቶች፣ ከሌላ ባሕልና ቋንቋ ከመጡት አይሁዳውያን የበለጠ እንክብካቤ እንደሚደረግላቸው አሰቡ። ይህም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ውጥረትን አስከተለ፡፡ ሰይጣን ቤተ ክርስቲያንን ለመከፋፈልና ለማፍረስ ተግቶ እየሠራ ነበር፡፡ እንዲህ ዓይነት ውጥረቶች በጸሎት ወይም ስለ አንድነት በመስበክ ብቻ የሚወገዱ አይደሉም፡፡ የውጥረቶቹ ምንጭ ተፈልጎ መፍትሔ መሰጠት አለበት፡፡ የተገለጸውን ሁኔታ በተመለከት በትክክል እድልዎ ይፈጸም ወይም ይህ የአንድ ቡድን ችግር ይሁን የተገለጸ ነገር የለም፡፡ ነገሩ እውነትም ይሁን ውሸት ሰዎች የሚያምኑት ነገር ለእነርሱ እውነት ከሆነ፣ መፍትሔ መስጠቱ አስፈላጊ ነበር፡፡ ዛሬ በኢትዮጵያ አብያተ ክርስቲያናት መካከል የሚታየው መከፋፈል በጎሣዎች መካከል የሚቀሰቀሱ ቅራኔዎች በመሆናቸው በዚህ ክፍል ውስጥ የተወሰኑትን መርሖች መከተሉ አስፈላጊ ነው። ስለዚህ ከዚህ ክፍል የሚከተሉትን እውነቶች መመልከት እንችላለን። ሀ. ምንም እንኳ ጸሎትና ትምህርት የመፍትሔው አካላት ቢሆኑም፣ በችግሩ ላይ ግልጽ ውይይት እስካልተካሄደበት ድረስ ወደ ጥላቻና ቂም የሚመራ የአድልዎ ድርጊት ሊወገድ አይችልም። ሐዋርያት የግሪክ አይሁዶችን ለመገሠጽም ሆነ ራሳቸውን ለመከላከል አልሞከሩም፡፡ ሐዋርያት የግሪክ አይሁዶች ችግራቸውን በጸሎት ለጌታ እንዲያቀርቡ ወይም ነገሮች በራሳቸው ጊዜ እንዲፈቱ አልጣሩም፡፡ ነገር ግን ጉዳዩን በሕዝቡ ሁሉ ፊት አንሥተው ግልጽ ውይይት እንዲካሄድ አደረጉ። ለ. ሐዋርያት ችግሩ በራሱ መንገድ እንዲቃለል ከመጠበቅ ይልቅ ወዲያው ሐሜቱን እንደ ሰሙ መፍትሔ መፈለግ ጀመሩ። እንዲህ ዓይነት ችግሮች እንዲሁ ስለማይወግዱ በፍጥነት ትኩረት ካልተሰጠባቸው እየተስፋፉ ይሄዳሉ። መከፋፈል ከሆነ በኋላ ደግሞ፣ ክፍተቱን ለማጥበብ ቀላል አይሆንም። ሐ. ችግሩ በምእመናን ሁሉ ፊት ለግልጽ ውይይት ቀረበ። ሉቃስ ደቀ መዛሙርቱ ሁሉ ሁኔታውን ለማጥናት እንደ ተሰበሰቡ ገልጿል። ሐዋርያቱ የራሳቸውን መፍትሔ መስጠታቸው መልስ አይሆንም ነበር። እነርሱም ከፍልስጥኤም አካባቢ ስለሆኑ፥ ሁልጊዜ ለአንድ ወገን ያደላሉ የሚል ግምት ነበራቸው። ጉዳዩ ከምእመናን ተሰውሮ በሐዋርያት (ሽማግሌዎች) ብቻ ቢቃለል ኖሮ አንደኛው ወይም ሌላኛው ወገን ሽማግሌዎቹ አድልዎአዊ ብያኔ እንዲሰጡ ገፋፍቷል የሚል ሐሜት ይሰራጭ ነበር፡ መ. ሐዋርያቱ (ሽማግሌዎቹ) ለችግሩ መፍትሔ ለመፈለግ ሳይሹ መመሪያዎችን ብቻ ሰጡ። (መንፈስ ቅዱስ የሞላባቸውን ሰባት ሰዎች መረጡ።) ከዚያም ምእመናኑ መበለቶቹን የሚረዱ ሰባት ሰዎች እንዲመረጡ አደረጉ። ሰይጣን ቤተ ክርስቲያንን ከሚዋጋባቸው መንገዶች አንዱ መሪዎች ለችግሮች መፍትሔ በመስጠትና ትናንሽ ጉዳዮችን በማከናወኑ ተግባር ላይ እንዲጠመዱና እንደ ጸሎት፥ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት፥ ምስክርነት፥ የቤተ ክርስቲያን ዕቅድ የመሳሰሉትን ዐቢይ ጉዳዮች ቸል እንዲሉ በማድረግ ነው። ሠ. መፍትሔው በጎሣዊ ስሜት ወይም በዓለማዊ ሁኔታ ሳይሆን በመጽሐፍ ቅዱሳዊ ወመርሖዎች ላይ የተመሠረተ ነው። አራት የፍልስጥኤም አይሁዶችንና ሦስት የግሪክ አይሁዶችን ምረጡ አላሏቸውም። ይህ መከፋፈልን እንጂ የእግዚአብሔርን ቤተሰብ አንድነት አያመጣም ነበር። ወሳኙ ነገር ትምህርት፥ የገንዘብ ብዛት ወይም የአስተዳደር ችሎታ ሳይሆን፥ የመንፈስ ቅዱስ ሙላትና መንፈሳዊ ጥበብ ነበር። ተወካዮቹ በመንፈስ ቅዱስ ኃይልና ምሪት የሚሠሩ ከሆነ፥ ለሁሉም ሰው ፍትሐዊ የሆነ መፍትሄ መስጠት ይችላሉ። ረ. አብዛኞቹ የፍልስጥኤማውያን አይሁዶች የአናሳውን ባሕል ለማክበር ከተለመደው መስመር መጡ። በፍልስጥኤማውያን አይሁዶች የተሞላችው ቤተ ክርስቲያን ምእመናን፥ ሰባቱንም ሰዎች ከግሪክ አይሁዶች መካከል መምረጣቸው አስደናቂ ነገር ነበር። ሰባቱ ዲያቆናት የግሪክ ስሞች የነበሯቸው ሲሆኑ፥ አንደኛው በትውልዱ አሕዛብ ሆኖ ሳለ ወደ ይሁዲነት የተለወጠ ሰው ነበር። ወቀሳው የተሰነዘረው ከዚሁ ክፍል አባላት በመሆኑ፥ ብዙ ቁጥር ያላቸው ክርስቲያኖች ከአናሳው ጎሣ ወገን በሆኑት ላይ መቅናት ጀመሩ፡፡ የአናሳ ወገን አካል መሆን ሁልጊዜ አስቸጋሪ ነው። ቋንቋና ባሕል አስፈላጊ ነገሮች ቢሆኑም ብዙ ጎሣ ላለበት ባሕል፣ ቋንቋና ፍላጎት መገዛት ፍትሐዊ አይደለም፡፡ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ዲሞክራሲ አለ ማለት ሁልጊዜ የብዙኃኑ ፍላጎት ያሸንፋል ማለት ነው። ነገር ግን ቤተ ክርስቲያን የተመሠረተችው በዲሞክራሲ ላይ ሳይሆን በፍቅር ላይ ነው። ፍቅር ደግሞ፥ እየተጎዳ ያለው ማን ነው? እንዴት ልርዳ?” ይላል። ፍቅር ሁልጊዜ የግል ወይም የባሕል መብቶችን በመናቅ፥ የሌሎችን ጥቅም ለማስቀደም ይፈልጋል፡፡ ጳውሎስ ስለ «ብርቱ» ክርስቲያኖችና «ደካማ» ክርስቲያኖች ከተናገረ በኋላ «ብርቱዎቹ ክርስቲያኖች «ደካማዎቹ» የሚጎዱበትን ነገር ማድረግ እንደሌለባቸው አስረድቷል (1ኛ ቆሮ. 10፡23-32)። በተመሳሳይ ሁኔታ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ዘላቂ ሰላም እንዲኖር ከተፈለገ፥ የብዙ ምእመናን ባሕል ከሆነው ከዲሞክራሲው አስተሳሰብ በማለፍ የአናሳውን ባሕል ለማክበር መሻት አለበት። ይህ በሚሆንበት ጊዜ፥ ክርስቲያኖች ሰይጣን ቤተ ክርስቲያንን ለመከፋፈል የሚሸርበውን ሴራ በቀላሉ

መከፋፈል በአይሁዶች መካከል (የሐዋ 6፡1-7) Read More »