ወደ ኤፌሶን ሰዎች

የኤፌሶን መልእክት ጸሐፊ እና ተቀባይ

የኤፌሶን መልእክት ጸሐፊ የውይይት ጥያቄ፡– ኤፌሶን 1፡1 አንብብ። ሀ) የኤፌሶን መልእክት ጸሐፊ ማን ነው? ለ) ራሱን እንዴት ገለጸ? ኤፌ. 1፡1ን ከገላ. 1፡1 ጋር አወዳድርና ጸሐፊው ራሱን እንዴት እንደሚገልጽ አብራራ። እንደ ሌሎች ደብዳቤዎች ሁሉ፥ ጳውሎስ የኤፌሶንን መልእክት የጀመረው ጸሐፊነቱን በመግለጽ ነበር። እንደ ሌሎች ጊዜያት ሁሉ «ሐዋርያ» የሚለውን ማዕረጉንም ጨምሮ ጠቅሷል። ጳውሎስ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ መመረጡንና የኢየሱስ ክርስቶስ ሹም ሆኖ መላኩን አመልክቷል። ጳውሎስ መልእክቱን በዚህ መንገድ የጀመረው በታላቅ ሥልጣኑ ለመመካት ሳይሆን፥ ደብዳቤው ለኤፌሶን ቤተ ክርስቲያን የተላከ የክርስቶስ መልእክት መሆኑን ለማስረዳት ነው። ይህም አማኞቹ ሰምተው እንዲታዘዙት ነው። ጳውሎስን መልእክቱን ለማን ጻፈ? የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ጳውሎስ ይህን መልእክት የጻፈው ለማን ነው? ለ) ጳውሎስ የመልእክቱን ተቀባዮች የገለጸው እንዴት ነው? ሐ) የሐዋ. 18፡18-20፡1 አንብብ። ወንጌሉ መጀመሪያ ወደ ኤፌሶን የደረሰው እንዴት ነው? ጳውሎስ በዚያ ለምን ያህል ጊዜ አገለገለ? ጳውሎስ መልእክቱን የጻፈው «ለኤፌሶን ቅዱሳን» ነበር። «ቅዱስ» የተለየ የሚል ፍች ሲኖረው፥ እነዚህ ክርስቲያኖች ፍጹም ወይም ኃጢአት እልባ መሆናቸውን አያመለክትም። ነገር ግን ክርስቲያኖች በእግዚአብሔር እንደ ተመረጡና ለእግዚአብሔር ቅዱሳን ይሆኑ ዘንድ እንደ ተለዩ ያሳያል። ብዙውን ጊዜ ይህ መልእክት ለኤፌሶን እማኞች እንደተጻፈ እናስባለን። ኤፌሶን፥ ጳውሎስ በሦስተኛው የወንጌል መልእክተኝነት ጉዞው ውስጥ ለሦስት ዓመታት ያገለገለባት ቦታ ናት። ስለሆነም፥ ይህ መልእክት ጳውሎስ ወደ መሠረታት ቤተ ክርስቲያን የተጻፈ ይመስላል። ነገር ግን አንዳንድ ምሁራን ይህ መልእክት በቀጥታ ለኤፌሶን ቤተ ክርስቲያን እንዳልተላከ በመግለጽ አያሌ ምክንያቶችን ይሰነዝራሉ። በመጀመሪያ፥ አንዳንድ ጥንታዊ የኤፌሶን መልእክት ቅጂዎች «ኤፌሶን» የሚል ቃል የለባቸውም። ነገር ግን «በኢየሱስ ክርስቶስ ለታመኑት ቅዱሳን» የሚል ሐረግ ተጽፎባቸዋል። ሁለተኛ፥ ጳውሎስ የሚጽፍላቸውን ሰዎች በአካል የሚያውቅ አይመስልም። በአካል ተገኝቶ እንደ ተመለከተ ሳይሆን፥ ስለ እምነታቸውና ፍቅራቸው እንደ ሰማ ይናገራል (ኤፌ. 1፡15)። በተጨማሪም፥ ጳውሎስ ስለ ክርስቶስ አዳኝነት የሚናገሩትን እውነቶች (ኤፌ. 4፡21፥ ብሎም ስለ አገልግሎቱ መረዳታቸውን እንደሰማ ይናገራል (ኤፌ. 3፡2)። ጳውሎስ መልእክቱን የጻፈው ለሦስት ዓመታት ላገላገላት ለኤፌሶን ቤተ ክርስቲያን ቢሆን ኖሮ፥ ስለ ኤፌሶን ክርስቲያኖች እምነትና ፍቅር ራሱ ይመሰክር ነበር። ሦስተኛ፥ በተጨማሪም በመልእክቱ ውስጥ የግል ሰላምታም ሆነ ሁነኛ ችግሮች አልተጠቀሱም። ከእነዚህ ምክንያቶች የተነሣ ብዙ ምሁራን ይህ መልእክት ወደ ተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት የሚዟዟር እንደ ነበር ይናገራሉ። ጳውሎስ መልእክቱን መጀመሪያ ዐቢይ ቤተ ክርስቲያን ወደምትገኝባት ኤፌሶን ላከ። እዚያ ከተነበበ በኋላ ደብዳቤው በእስያ ውስጥ ወደሚገኙ ሌሎች አብያተ ክርስቲያናት (ምናልባትም በራእይ ውስጥ የተጠቀሱትን ሰባት አብያተ ክርስቲያናት ጨምሮ) ተላከ (ራእይ 1፡1)። በቆላስይስ 4፡16፣ ጳውሎስ ለሎዶቂያ ክርስቲያኖች ስለተጻፈ ሌላ መልእክት ጠቅሷል። አንዳንድ ምሁራን ይህ ኤፌሶን ብለን የምንጠራው ተዘዋዋሪ መልእክት እንደሆነ ያስባሉ። ጳውሎስ እነዚህን ክርስቲያኖች «በክርስቶስ የታመኑ» ይላቸዋል። በክርስቶስ ማመን ብቻ ሳይሆን፥ ከእርሱ ጋር ያላቸውን ግንኙነት በማጥበቅ በታማኝነት ይከተሉት ነበር። የሚያሳዝነው የኤፌሶን ሰዎች ለኢየሱስ የነበራቸው ታማኝነት ዘለቄታ አልነበረውም። ከ40 ዓመታት ያህል በኋላ ክርስቶስ ለኤፌሶን ቤተ ክርስቲያን ልዩ መልእክት ልኳል። ለእርሱ የነበራቸውን የመጀመሪያ ፍቅር በማጣታቸው ወቅሷቸዋል። ንስሐ ገብተው ፍቅራቸውን ካላደሱ በፍርድ እንደሚመጣባቸው አስጠንቅቋቸዋል (ራእይ 2፡1-7 አንብብ)። ቤተ ክርስቲያን ዛሬ ታማኝ መሆኗ ብቻ በቂ አይደለም። ለክርስቶስ ያለን ፍቅር በቀጣይነት ሊያድግና ሊጠናከር ይገባል። ብዙ አብያተ ክርስቲያናት በጠንካራ አቋም ጀምረው ከጥቂት ጊዜ በኋላ እየተዳከሙ ሄደዋል። የውይይት ጥያቄ፡- ስለ ቤተ ክርስቲያንህ አስብ። ሀ) ክርስቶስ ከእርሱ ጋር ያለህን ግንኙነት እንዴት ይገልጻል? ለ) ቤተ ክርስቲያንህ ከዚህ በፊትና አሁን ከእግዚአብሔር ጋር የምታደርገውን ግንኙነቷን አነጻጽር። እየተዳከመች ነው ወይስ እየበረታች? እየተዳከመች ከሆነ፥ የእግዚአብሔር ፍርድ እንዳይደርስባት ግንኙነት ለማደስ ስለ ምን ነገሮች ንስሐ ልትገባ ይገባል? ጳውሎስ በወንጌል መልእክተኝነት ጉዞው ከየትኛውም ስፍራ በላይ በኤፌሶን ብዙ ጊዜ ቆይቷል። ጳውሎስ በአሁኗ ቱርክ ውስጥ የነበረችውን ኤፌሶንን እንደ ቁልፍ የአገልግሎት ስፍራ ነበረ የተመለከተው። ኤፌሶንን መናኸሪያ አድርጎ በመጠቀሙ ወንጌል በእስያ አውራጃ ውስጥ በፍጥነት ሊሰራጭ ችሏል (የሐዋ. 19፡10)። የኤፌሶን ከተማ ዋነኛ የወደብ ከተማና የእስያ አውራጃ መዲና ነበረች። አብዛኛው የንግድ እንቅስቃሴ ከምዕራብ ቱርክ ወደ ኤፌሶን ከመጣ በኋላ ከዚያ ወደ ጥንቱ ዓለም ሁሉ ይሰራጭ ነበር። ጳውሎስ በዚያ በሚሠራበት ጊዜ ቢያንስ የ1100 ዓመታት ዕድሜ የነበራት ጥንታዊ የታሪክ ከተማ ነበረች። ብዙ አይሁዶችና ሌሎችም ከ500,000 የሚበልጡ ሰዎች በከተማይቱ ውስጥ ይኖሩ እንደነበር ይገመታል። በዚያ ከነበሩት አይሁዶች አንዳንዶቹ ወደ ክርስትና እምነት ሲመጡ፥ አብዛኞቹ ግን የወንጌሉ ጠላቶች ሆነው ክርስቲያኖችን ያሳድዱ ነበር። ኤፌሶን ዳያና በተባለች ጣዖት አምልኮም ትታወቅ ነበር። ዳያና የምትመለክበት ቤተ መቅደስና ሐውልቷ እጅግ አስደናቂ በመሆናቸው ከሰባቱ የጥንቱ ዓለም አስደናቂ ነገሮች እንደ አንዱ እንደሆኑ ተደርገው ይቆጠሩ ነበር። ዳያና የሚለው ሮማዊ ስምም ሆነ አርጤምስ የሚለው የግሪክ መጠሪያ የፍሬያማነትን አምላክ የሚያመለክት ነበር። ሴቶች ዳያናን በማምለካቸው ልጅ መውለድ እንደሚችሉ ይታመን ነበር። ከዳያናና ከሌሎች ጣዖታት በተጨማሪ ኤፌሶን ዋነኛ የጥንቆላና የምትሐት ማዕከል ነበረች። የኤፌሶን ሰዎች በክርስቶስ ካመኑ በኋላ ቢያንስ 50,000 ብር የሚገመቱ የምትሐት መጻሕፍት እንዳቃጠሉ ተነግሮናል። በኋላም የሮም ንጉሥ አምልኮ ከተጧጧፈባቸው ከተሞች አንዱ ኤፌሶን ነበረች። በዚህ ሃይማኖት ንጉሡን ለማምለክ ባለመፍቀዳቸው እንደ ዓመፀኞች በታዩት ክርስቲያኖች ላይ ከፍተኛ ስደት ተከስቷል። ጳውሎስ መጀመሪያ በኤፈሶን ወንጌልን የሰበከው በሁለተኛው የወንጌል መልእክተኝነት ጉዞው መጨረሻ አካባቢ ነበር። ጳውሎስ ወደ ኢየሩሳሌም ሲሄድ እግረ መንገዱን ከጵርስቅላና አቂላ ጋር ወደ ኤፌሶን ጎራ አለ (የሐዋ. 18፡18-19)። አንድ ጊዜ ለአይሁዶች ከሰበከ በኋላ ሰዎች እንዲቆይ ቢፈልጉም ወደ ኢየሩሳሌም አመራ። ጵርስቅላና አቂላ ግን እዚያው ቆዩ። በዚህ ጊዜ ከመጥምቁ ዮሐንስ ደቀ መዛሙርት አንዱ የነበረው አጵሎስ የሚባለው ወደ ኤፌሶን መጥቶ ማስተማር ጀመረ። ጵርስቅላና አቂላ ስለ ክርስቶስ የበለጠ ካስተማሩት በኋላ አጵሎስ በኤፌሶን ወንጌሉን እንዲያስፋፋ እግዚአብሔር በሚገባ ተጠቀመበት። ነገር ግን ብዙም ሳይቆይ ወደ ቆሮንቶስ ለአገልግሎት ሄደ። ጳውሎስ በኤፌሶን ዐቢይ የአገልግሎት መሠረት የጣለው በሦስተኛው የወንጌል መልእክተኝነት ጉዞው ነበር። በኤፌሶን ሲሰብክና ሲያስተምር ለሦስት ዓመታት ቆየ። ይህም በየትኛውም የአገልግሎት ጉዞው ካደረጋቸው ቆይታዎች ሁሉ የበለጠ ነበር። ብዙ ሰዎች የንግድ ማዕከል ወደነበረችው ኤፌሶን የንግድ ተግባራቸውን ለማከናወን ሲመጡ ወንጌሉን ይሰብክላቸው ነበር። እነርሱም ወንጌሉን ይዘው ወደመጡበት አገር ይመለሳሉ። ከዚህም የተነሣ ወንጌሉ በእስያ አገሮች ሁሉ ተስፋፋ (የሐዋ. 19፡10)። ምናልባትም በራእይ ውስጥ የተጠቀሱት ሰባቱ አብያተ ክርስቲያናትና የቆላስይስ ቤተ ክርስቲያን የተመሠረቱት በዚህ ጊዜ ሳይሆን አይቀርም። በኤፌሶን አገልግሎቱ መጨረሻ አካባቢ ተቃውሞ እየተጠናከረ በመሄዱ በከተማይቱ ውስጥ ብጥብጥ ተነሣ። ከዚያ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ጳውሎስ የግሪክን አብያተ ክርስቲያናት ጎብኝቶ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ። ጳውሎስ የኤፌሶንን መልእክት የጻፈበት ዘመንና ስፍራ የውይይት ጥያቄ፡– ኤፌ 3፡1 እና 4፡1 አንብብ። ጳውሎስ መልእክቱን የጻፈው የት ሆኖ ነበር? ጳውሎስ ይህን መልእክት በጻፈ ጊዜ የሆነ ስፍራ ታስሮ ነበር። ግን የት እንደ ታሰረ? አያሌ ግምቶች አሉ። ቂሣሪያ ወይም ሮም ታስሮ ሊሆን ይችላል። ጳውሎስ ወደ ኢየሩሳሌም ሲደርስ መታሰሩን አስታውሰ። ለጥቂት ጊዜ በኢየሩሳሌም ታስሮ ከቆየ በኋላ ቂሣሪያ ወደተባለችው የሮም የአውራጃ ከተማ ተወስዶ ለሁለት ዓመታት ያህል ታስሯል (የሐዋ. 24፡27)። የእስር ቤት መልእክቶቹን የጻፈው በዚህ ጊዜ ሳይሆን አይቀርም። ከሁለት ዓመታት በኋላ፥ ጳውሎስ በንጉሥ ችሎት ይዳኝ ዘንድ ወደ ሮም ተላከ። እዚያም ለሁለት ተጨማሪ ዓመታት ራሱ በተከራየው ቤት ታስሮ ቆየ (የሐዋ. 28፡30-31)። አብዛኞቹ ምሁራን ጳውሎስ አራቱን የወኅኒ ቤት መልእክቶች ሮም ሆኖ በ60 ወይም 61 ዓ.ም እንደ ጻፈ ያምናሉ። (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የኤፌሶን መልእክት ጸሐፊ እና ተቀባይ Read More »

የኤፌሶን መልእክት መግቢያ

ተስፋጽዮን በጀማ የወንጌል ስብከት ላይ ስለ ክርስቶስ ሰምቶ በክርስቶስ አመነ። ከዚያ በኋላ ከተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት ተወካዮች ጋር ተገናኘ። በስብሰባው ላይ የቃለ ሕይወት፥ የመካነ ኢየሱስ፥ የሙሉ ወንጌል፥ የመሠረተ ክርስቶስ፥ የሕይወት ብርሃንና የሌሎች ብዙ አብያተ ክርስቲያናት መሪዎች ነበሩ። ሁሉም ተስፋጽዮን ወደ ቤተ ክርስቲያናቸው እንዲመጣ ገፋፉት። ሁሉም ወደ ቤተ ክርስቲያናቸው እንዲመጣ ለማግባባት፥ «ከሁሉም የሚበልጡ ብዙ ምእመናን አሉን። ቃሉን እናስተምራለን። የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች አሉን» ሲሉ አዋከቡት። ተስፋጽዮን በዚህ ሁኔታ ግራ ተጋባ። «ቤተ ክርስቲያን ምንድን ናት? እንዲህ ቤተ እምነቶች የበዙት ለምንድን ነው? ትክክለኛው ቤተ እምነት የትኛው ነው?» ሲል ራሱን ጠየቀ። ጥያቄ፡- ሀ) የተለያዩ ቤተ እምነቶች አዳዲስ ክርስቲያኖችንና አማኞች ያልሆኑትን ሰዎች ግራ የሚያጋቡት እንዴት ነው? ለ) ቤተ እምነቶች የበዙት ለምንድን ነው? ሐ) ጤናማ ይመስልሃል? ለምን? መ) በአማርኛ ቋንቋ «ቤተ ክርስቲያን» የሚለው ቃል ምን ትርጉም ይሰጣል? በአሁኑ ዘመን ብዙ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት የሚገኙ ሲሆን፥ ሌሎች ብዙዎችም እዚሁ ቅርንጫፎችን ለመመሥረት ከምዕራባውያን አገሮች እየጎረፉ ናቸው። እነዚህ ብዙ ቤተ እምነቶች የሚመጡት ከየት ነው? ቤተ እምነቶች የበዙትስ ለምንድን ነው? በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙት አብዛኛዎቹ ቤተ እምነቶች ከሚከተሉት ምንጮች የመጡ ናቸው። በመጀመሪያ፥ ከምዕራቡ ዓለም የመነጩ ቤተ እምነቶች አሉ። የተለያዩ ሚስዮናውያን ወደ ኢትዮጵያ መጥተው በአገራቸው ያሉትን ዓይነት ቤተ እምነቶች መሥርተዋል። እነዚህ ቤተ እምነቶች ከየት የመጡ ናቸው? አብዛኞቹ የምዕራቡ ዓለም ቤተ እምነቶች በትናንሽ የአስተምህሯዊ ልዩነቶች ምክንያት የተፈጠሩ ናቸው። ከእነዚህ አስተምህሯዊ ልዩነቶች መካከል አንዳንዶቹ የሕፃናት ወይም የአዋቂዎች ጥምቀት፥ የቅዱስ ቁርባን ፍችና የመንፈስ ቅዱስ ቀዳሚ አገልግሎት ምንነትን የሚመለከቱ ናቸው። ሁለተኛ፥ ሌሎች ቤተ እምነቶች የራሳቸውን ቤተ እምነቶች የጀመሩትን ታላላቅ መሪዎች፥ ሰባኪዎች ወይም የፈውስ አገልጋዮች በመከተል የተመሠረቱ ናቸው። ይህ በኢትዮጵያ ብዙም ያልተለመደ ቢሆንም፥ በሌሎች የአፍሪካ አገሮች ግን በመቶዎች የሚቆጠሩ ቤተ እምነቶች በመሪዎች ስም ተመሥርተዋል። ሦስተኛ፥ የአንዲት ቤተ ክርስቲያን መእመናን በሰላም ለመኖር ባለመቻላቸው ምክንያት የተጀመሩ ቤተ እምነቶችም አሉ። ባለመስማማታቸው ምክንያት ተከፋፍለው የየራሳቸውን ቤተ እምነቶች ይመሠርታሉ። ብዙውን ጊዜ የእነዚህ ክፍፍሎች ምክንያቶች፥ ጎሰኝነት በተወሰኑ ልምምዶች ላይ በሚከሰቱ የአመለካከት ልዩነቶች ወይም ሰብአዊ ኩራት ናቸው። የሚያሳዝነው ከእነዚህ ምክንያቶች አንዳቸውም አዲስ ቤተ እምነት ለመመሥረት የሚያበቁ አለመሆናቸው ነው። ሁልጊዜም በትናንሽ የመጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮዎች ላይ የአሳብ ልዩነት የሚያሳዩ ክርስቲያኖች ይኖራሉ። ዓይን ለዓይን እንኳን መተያየት የማይፈልጉ መሪዎችም ይኖራሉ። ሁልጊዜም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በተወሰኑ ጉዳዮች ወይም ልምምዶች ላይ ውጥረቶች ይኖራሉ። እግዚአብሔር ግን ከእነዚህ ምክንያቶች አንዱም አዲስ ቤተ እምነት ለመጀመር ብቁ መሆናቸውን አያረጋግጥም። ክርስቲያኖች ባለመስማማታቸው ምክንያት መከፋፈል መከሰቱ እጅግ አሳዛኝ ነገር ነው። በዮሐንስ 17 ክርስቶስ ተከታዮቹ አንድነትን እንዲመሠርቱ ጸልዮአል። ጳውሎስ ክርስቲያኖች አንድ አሳብ እንዲኖራቸው ተማጽኗል (ፊልጵ. 2፡1-2)። ነገር ግን ከኃጢአተኝነታችንና ከኩራታችን የተነሣ ክፍፍሎች ይከሰታሉ። የቤተ እምነቶች መፈጠር ስሕተት ነውን? የተመሠረቱበት ዓላማ ስሕተት ከሆነ፥ እንዲሁም የውድድርና የኩራት መንፈስ የሚታይባቸው ከሆነ፥ የቤተ እምነቶች መፈጠር ትክክል ሊሆን አይችልም። አንዱ ቤተ እምነት ከሌሎች እንደሚበልጥ ሲያስተምርና የተለያዩ ቤተ እምነቶች ተከታዮች እርስ በርሳቸው ቢጣሉ፥ ወይም አንዱ የሌላውን አባላት ለመውሰድ ቢሞክር፥ ይህ የአንድ ቤተሰብ አባላት የሆኑ ወንድማማቾችን ማጣላት ያህል አስከፊ ነው። በሌላ በኩል፥ የተለያዩ ቤተ እምነቶች መፈጠር እግዚአብሔርን ሊያስከብር ይችላል። የተለያዩ ብዙ ዓይነት ዛፎች ለአንድ አካባቢ ውበትን እንደሚጨምሩ ሁሉ፥ የተለያዩ የአምልኮ ስልቶችና ልምምዶች ያሏቸው ብዙ ቤተ እምነቶች የውበት መገለጫዎች ሊሆኑ ይችላሉ። ነገር ግን ይህ የቤተ እምነቶች ልዩነት የታላቁ የክርስቶስ አካል ክፍሎች የመሆናችንን አንድነት ያገናዘበ ሊሆን ይገባል። በፍጥረት ውስጥ የምንመለከተው በአንድነት ውስጥ ያለ ልዩነት በቤተ ክርስቲያንም ውስጥ ሊንጸባረቅ ይገባል። የኤፌሶን መልእክት በክርስቶስ አካል ወይም በቤተ ክርስቲያን ላይ ያተኩራል። ቤተ ክርስቲያን ምንድን ናት? በአማርኛ ቋንቋ፥ ቃሉ ሕንፃ ወይም የክርስቲያኖችን መሰብሰቢያ ያመለክታል። አዲስ ኪዳን ግን ሕንፃን ለማመልከት «ቤተ ክርስቲያን» የሚለውን ቃል የተጠቀመበት ስፍራ የለም። እንዲያውም፥ ከሐዋርያት ዘመን ጀምሮ ለብዙ መቶ ዓመታት ክርስቲያኖች ሁነኛ የመሰባሰቢያ ስፍራ አልነበራቸውም። በአዲስ ኪዳን ቤተ ክርስቲያንን የሚለው ቃል በሰዎች ላይ ያተኩራል። በግሪክ ቋንቋ፥ ቃሉ «ጉባኤ»ን ወይም የተወሰኑ ሰዎችን «አብሮ መሰባሰብ» ያመለክታል። የአንዲት ከተማ ነዋሪዎች ለስብሰባ ተጠርተው የሚያካሂዱት ስብሰባ ቤተ ክርስቲያን ይባል ነበር። ስለሆነም ከዓለም ወደ ክርስቶስ አካል የተጠሩት ክርስቲያኖች የሚያካሂዱትም ስብሰባ ቤተ ክርስቲያን ይባላል። በአዲስ ኪዳን፥ ቤተ ክርስቲያን የሚለው ቃል ሦስት የክርስቲያን ቡድኖችን ሊያመለክት ይችላል። በመጀመሪያ፥ ብዙውን ጊዜ የአጥቢያ ክርስቲያኖችን በአንድ አካባቢ መሰባሰብ ሊያመለክት ይችላል (ሮሜ 16፡5)። አብዛኞቹ የቀድሞዎቹ አብያተ ክርስቲያናት በግለሰቦች ቤቶች ውስጥ ይሰባሰቡ ነበር። ወደ 50 የሚሆኑ ሰዎች በመደበኛነት በግለሰቦች ቤቶች ውስጥ እየተሰባሰቡ ያመልኩና መጽሐፍ ቅዱስ ያጠኑ ነበር። ሁለተኛ ቤተ ክርስቲያን የሚለው ቃል በአንድ መልክዓ ምድራዊ ክልል ውስጥ የሚገኙትን ክርስቲያኖች ሊያመለክት ይችላል። ለምሳሌ ያህል፥ ጳውሎስ ለሮሜ ወይም ለቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ጽፎአል። እነዚህ አብያተ ክርስቲያናት ከአንድ ሕንፃ ሥር የሚሰባሰቡ ሳይሆኑ፥ በተለያዩ ቤቶች ውስጥ የሚሰባሰቡ የአንድ አካባቢ ክርስቲያኖች ነበሩ። ዛሬ በተመሳሳይ ሁኔታ «የአፍሪካ ቤተ ክርስቲያን» ወይም «የብሪታኒያ ቤተ ክርስቲያን» ልንል እንችላለን። ሦስተኛ፥ ዓለም አቀፋዊት (ዩኒቨርሳል) ቤተ ክርስቲያን አለች። ይህ የሞቱትንና በሕይወት ያሉትን፥ በሰማይና በምድር ያሉትን ጨምሮ የክርስቶስ አካል የሆኑትን ሁሉ ያጠቃልላል (ዕብ. 12፡23)። ጳውሎስ በኤፌሶን መልእክት ውስጥ ስለ አጽናፈ አቀፉዋ ቤተ ክርስቲያን ደጋግሞ ጠቅሷል። ሐዋርያው ጳውሎስ፥ እግዚአብሔር በዓለም ውስጥ የሚያከናውነው ታላቁ ሥራ የክርስቶስን አካል መገንባት እንደሆነ ተገንዝቧል። ኢየሱስ ክርስቶስ በእርሱ ያመኑና የሚከተሉት ሰዎች ሁሉ የሚገኙባት ዓለም አቀፋዊት ቤተ ክርስቲያን ራስ ነው። እግዚአብሔር በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለእያንዳንዱ አማኝ የተለየ ስጦታ ይሰጣል። አማኙ በዚህ ስጦታው ሌሎችን በማገልገል ክርስቶስን ያገለግላል። ይህ የአማኞች አካል በምድር ላይ ክርስቶስን ይወክላል። ወንጌሉን ስንመሰክር አፉ፥ እርስ በርሳችንና ሌሎችን ስንረዳ እጆቹ፥ እንዲሁም ወንጌሉን ወደ ዓለም ሁሉ ስናዳርስ እግሮቹ ሆነን እንሠራለን። ጳውሎስ ይህንን የአማኞች መሰባሰብ የእግዚአብሔር «ቤተ መቅደስ» ወይም የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ ይለዋል (ኤፌ. 2፡21)። ምንም እንኳ ክርስቶስ በእያንዳንዱ ክርስቲያን ልብ ውስጥ ቢኖርም፥ ከዚያ በላቀ ሁኔታ በአማኞች ኅብረት ውስጥ ይኖራል። ዛሬ ትኩረት የሚደረገው በግለሰቦች ድነት (ደኅንነት) ላይ ነው። የሰዎችን መዳን አለመዳን እንጠይቃለን። ብዙ ሰዎች ለማምለክ ለራሳቸው ብቻ ቃሉን ለመማር ወደ ቤተ ክርስቲያን ይመጣሉ። ነገር ግን የአማኞች ኅብረት ንቁ ተሳታፊዎች አይሆኑም። በአዲስ ኪዳን ውስጥ እግዚአብሔር ለራሱ ክብር ለማምጣት በሚሠራበት የአማኞች ኅብረት ላይ ትኩረት ተደርጓል። እግዚአብሔር እያንዳንዱ ክርስቲያን በአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በንቃት በመሳተፍ የድርሻውን እንዲያበረክት ይፈልጋል። የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) አዲስ ኪዳን «ቤተ ክርስቲያን» ሲል የሚገልጸውን ሃሳብ ዛሬ ብዙ ሰዎች ስለ ቤተ ክርስቲያን ከሚገነዘቡት ጋር አነጻጽር። ለ) «ቤተ ክርስቲያን» የሚለው ቃል በቀዳሚነት ሰዎችን ሳይሆን የቤተ ክርስቲያንን ሕንፃ እንደሚያመለክት ስናስብ፥ ምን ምን ችግሮች ይከሰታሉ? ሐ) በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ የሚያመልኩት አብዛኞቹ ሰዎች መንፈሳዊ ስጦታዎቻቸውን በትጋት ይጠቀማሉ? ለምን? መ) አብዛኛዎቹ ሰዎች በትጋት ሳይሳተፉ እንደ ተመልካች በየጉባኤዎች ላይ ተገኝተው መመለሳቸው ምን ዓይነት አሉታዊ ውጤቶችን ያስከትላል? የውይይት ጥያቄ፡- ስለ ኤፌሶን ከመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት አንብብና ስለ ጸሐፊው፥ ስለ ቤተ ክርስቲያኒቱ፥ ስለ ደብዳቤው ዓላማና ስለ ከተማው፥ ወዘተ… ጠቅለል ያለ አሳብ ጻፍ። የወኅኒ ቤት መልእክቶች የውይይት ጥያቄ፡– ኤፌ. 3፡1፤ ፊልጵ. 1፡12-13፤ ቆላ. 1፡24፤ ፊል. 1 አንብብ። ጳውሎስ እነዚህን መልእክቶች በጻፈበት ወቅት የት ነበር? ምሁራን የኤፌሶንን፥ የፊልጵስዩስን፥ የቆላስይስንና የፊልሞናን መልእክቶች «የወኅኒ ቤት መልእክቶች» ብለው ይጠሯቸዋል። ለዚህም ምክንያቱ ጳውሎስ እስር ቤት (ምናልባትም ሮም) ውስጥ ሆኖ ስለ ጳፋቸው ነው። የጥንት የቤተ ክርስቲያን መሪዎች የጳውሎስን የተለያዩ መልእክቶች ባደራጁ ጊዜ ሦስቱን ረዣዥም የእስር ቤት መልእክቶች (ኤፌሶን፥ ፊልጵስዩስ፥ ቆላስይስ) አንድ ላይ አስቀምጠዋል። ከሁሉም አጭር የሆነው ፊልሞና ከጳውሎስ መልእክቶች የመጨረሻውን

የኤፌሶን መልእክት መግቢያ Read More »