ወደ ሮሜ ሰዎች

ሮሜ 5፡1-21

ኃጢአተኛው በእግዚአብሔር ከጸደቀ በኋላ የሚቀበላቸው በረከቶች (ሮሜ 5፡1-11) የውይይት ጥያቄ፡– ሮሜ 5፡1-11 አንብብ። እግዚአብሔር በክርስቶስ ለሚያምኑ ሰዎች የሚሰጣቸውን የተለያዩ በረከቶች ዘርዝር። አብርሃም በእምነቱ ምክንያት ተስፋ የተገባለትን ልጅ አግኝቷል። እኛስ ክርስቶስን ብቸኛ የድነት (የደኅንነት) መንገድ እንደሆነ ስናምን ምን እናገኛለን? ጳውሎስ ብዙ ልንደርስባቸው የምንችልባቸውን በረከቶችን ዘርዝሯል። ሀ. ከእግዚአብሔር ጋር ሰላም ይኖረናል። ከእንግዲህ ከእግዚአብሔር ጋር እየተዋጋን ከፍርዱ ሥር የምንኖር ጠላቶቹ አንሆንም። የበረከትና የሰላም ግንኙነት እንመሠርታለን። ለ. የእግዚአብሔር የክብር ተስፋ አለን። በአዲስ ኪዳን፥ ብዙውን ጊዜ «ተስፋ» የሚለው ቃል በመንግሥተ ሰማይ የኋላ ኋላ የድነት (ደኅንነት) ማረጋገጫ እንደሚጠብቀን ያሳያል። ጳውሎስ በእምነታችን መንግሥተ ሰማይ በምንደርስበት ጊዜ ከእግዚአብሔር ዘንድ ክብርን እንደምናገኝ ያሳያል። ሐ. ስደትና መከራ ቢያጋጥሙን እንኳን ድፍረት ይኖረናል። በሕይወታችን ውስጥ የሚከሰተው መከራ የእግዚአብሔርን ቅጣት ሳይሆን በሕይወታችን ውስጥ ሊያከናውን የሚፈልገውን መልካም ነገር እንደሚያሳየን በእምነት እንረዳለን። መከራ እግዚአብሔር ለመንፈሳዊ ዕድገታችን ከሚጠቀምባቸው ዐበይት መሣሪያዎች አንዱ ነው። መ. የእግዚአብሔርን ፍቅር ወደ ልባችን የሚያፈስ መንፈስ ቅዱስ ይሰጠናል። በእያንዳንዱ ክርስቲያን ልብ ውስጥ የሚኖረው መንፈስ ቅዱስ እግዚአብሔር እንደሚወደን የሚያሳይ ምልክት ብቻ ሳይሆን ሌሎችን እንድንወድ የሚያስችለን ነው። ሠ. ጸድቀናል። በክርስቶስ ሞትና በመስቀል ላይ በፈሰሰው ደሙ ምክንያት «ጥፋተኞች አይደላችሁም» ተብለናል። ረ በኃጢአተኞችና ከእግዚአብሔር ጋር ትክክለኛ ግንኙነት በሌላቸው ሰዎች ሁሉ ላይ ከሚደርሰው የእግዚአብሔር የፍርድ ቁጣ ድነናል። ሰ. በክርስቶስ ሕይወት ድነናል። ክርስቶስ ከሞት በተነሣ ጊዜ እግዚአብሔር አብ ለኃጢአታችን ያቀረበውን መሥዋዕት ተቀብሎ አዲስ የድነት (የደኅንነት) መንገድ እንደከፈተ ያሳያል። ሸ. ከፈጣሪ አምላካችን ጋር ታርቀናል። የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) እነዚህ በረከቶች ሁሉ ለአንተ ጠቃሚዎች የሆኑባቸውን ምክንያቶች ዘርዝር። ለ) እግዚአብሔር አብን፥ ወልድንና መንፈስ ቅዱስን ለአንተ ስላላቸው በረከትና ፍቅር አሁኑኑ አመስግናቸው። ኃጢአትንና ሞትን ወደ ዓለም ያመጣው የመጀመሪያው አዳም ሕይወትንና ጽድቅን ወደ ዓለም ካመጣው ሁለተኛው አዳም ጋር ሲነጻጸር (ሮሜ 5፡12-21) የውይይት ጥያቄ፡- ሮሜ 5፡12-21 አንብብ። ሀ) በአዳምና በክርስቶስ መካከል የሚገኙት ልዩነቶችና ተመሳሳይነቶች ምን ምንድን ናቸው? ለ) ክርስቶስ ከአዳም የሚበልጠው እንዴት ነው? ጳውሎስ ክርስቶስ በእምነት የተቀበልነውን ድነት (ደኅንነት) በመስጠቱ ያከናወነውን ታላቅ ተግባር ለማሳየት ሲል ከአዳም ጋር አነጻጽሮታል። በጳውሎስ አእምሮ፥ በአዳምና በክርስቶስ መካከል አንድ ዐቢይ መመሳሰል አለ። ይኸውም ሁለቱም የሕዝብ ሐረግ ጅማሬዎች መሆናቸው ነው። አዳም የሰው ዘር ጅማሬ ነበር። ክርስቶስ የእግዚአብሔር መንፈሳዊ ሕዝብ ጅማሬ ነው። የሕይወታቸው ውጤት ግን በጣም ይለያያል። አዳም እግዚአብሔርን ባለመታዘዙ ምክንያት ኃጢአትን ፈጸመ። ይህም ዘሮቹ የሰው ልጅ በሙሉ) ከእርሱ የኃጢአትን ተፈጥሮ እንዲያገኙና ይህም ኃጢአተኛ ተፈጥሮአቸው ወደ ሞት እንዲነዳቸው አድርጓቸዋል። እያንዳንዱ ልጅ የሚወለደው እግዚአብሔርን የሚያሳዝን የኃጢአት ተፈጥሮ ይዞ ነው። ከኃጢአት ዐበይት ውጤቶች አንዱ ሞት በመሆኑ፥ ሥጋዊና መንፈሳዊ ሞት ከአዳም ወደ ዘሮቹ ተላልፎአል። የአንድ ሰው ኃጢአት በታሪክ ሁሉ በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ኃጢአትን እንዲፈጽሙ አድርጓል። «ስጦታው» ተብሎ የሚጠራው ወይም «ሁለተኛው አዳም» የተባለው ክርስቶስ ከመጀመሪያው አዳም ይበልጣል። የእግዚአብሔር መለኮታዊና ሰብአዊ ልጅ የሆነው ክርስቶስ በመስቀል ላይ በመሞት በታሪክ ሁሉ ለኖሩ በቢሊዮኖች ለሚቆጠሩ ሰዎች የኃጢአትን ዋጋ ከፍሏል። አንድ ጊዜ በመስቀል ላይ በመሞቱ፥ ከአዳም ዘመን ጀምሮ እስከ ታሪክ ፍጻሜ ድረስ በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ኃጢአቶች የሠሩ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች በክርስቶስ በማመን በእግዚአብሔር ዓይኖች ፊት «ጥፋተኞች አይደላችሁም» ሊባሉና ከእግዚአብሔር ጋር ትክክለኛ ግንኙነት ሊጀምሩ ይችላሉ። ጳውሎስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ በመሞቱ ሰዎች ሁሉ ወዲያውኑ ድነትን (ደኅንነትን) ያገኛሉ ማለቱ እንዳልሆነ መገንዘቡ ጠቃሚ ነው። ነገር ግን ሁለት አስፈላጊ ነገሮች ይከሰታሉ። በመጀመሪያ፥ ክርስቶስ ለዓለም ሁሉ በመሞት በታሪክ ለኖሩ ሰዎች ሁሉ የሚሆን እምቅ ይቅርታ አስገኝቷል። ድነት (ደኅንነት) ሰው ሁሉ ሊያገኘው የሚችል ነገር ቢሆንም፥ ድነቱን የሚቀበሉት ግን በግላቸው ኢየሱስን በማመን ብቻ ነው። ሁለተኛ፥ አንድ ሰው ምንም ያህል ኃጢአት ቢሠራም በክርስቶስ የመስቀል ላይ ሞት በማመን ጻድቅ ነህ ሊባልለት ይችላል። አሁን ሕይወት አለን። ይህም ሕይወት፥ ባመንን ጊዜ ከመቅጽበት የምናገኘውን መንፈሳዊ ሕይወትና አዳም ወደ ዓለም ያመጣውን ሞት የሚያሸንፍ ዘላለማዊ ሕይወት ማግኘትንም የሚያካትት ነው። እንግዲህ የሕግ ዓላማ ምንድን ነው? አንደኛው ዓላማ ኃጢአት የመስራት አቅማችንን ግልጽ በማድረግ የሰውን ልጅ ኃጢአተኛ ልብ ማሳየት ነው። «በደል» የእግዚአብሔርን ሕግ መተላለፍን ያሳያል። ጳውሎስ ቀደም ሲል ሕግ በሌለበት የበደል ሕግ እንደሌለ ገልጾአል (ሮሜ 4፡15)። ሰዎች ኃጢአትን መሥራታቸው ባይቀርም ኃጢአተኝነታቸው እንደ አለመታዘዝ በግልጽ አይታይም። ነገር ግን የእግዚአብሔር ሕግ በተገለጠ ጊዜ፥ የድነት (ደኅንነት) መንገድ ባይሰጥም በእምነት የሚገኘውን የድነትን (ደኅንነትን) መንገድ ይሹ ዘንድ ኃጢአተኝነታቸውን አሳይቷቸዋል። የጳውሎስ የኃጢአት ተፈጥሮ የተረጋገጠው ስላለመመኘት የሚናገረውን ሕግ በሰማ ጊዜ ነበር። ሰዎች እያወቁ የእግዚአብሔርን ሕግ ከተላለፉ በኋላ አስከፊ ኃጢአተኝነታቸውን፥ በፈቃዳቸው እግዚአብሔርን ላለመታዘዝ መፈለጋቸውን ይገነዘቡና ምሕረትን ለመቀበል ወደ እግዚአብሔር ዘወር ይላሉ። እግዚአብሔር አሁንም ስለሚወዳቸው በአስደናቂ ጸጋው ጽድቅን በማጎናጸፍ የዘላለምን ሕይወት ይሰጣቸዋል። ይህንንም የሚያደርገው ግን ክርስቶስ በመስቀል ላይ ያከናወነላቸውን ተግባር በእምነት ከተቀበሉ ብቻ ነው። ጥረትን የማይጠይቀውና እግዚአብሔር ለኃጢአተኛ ሰዎች በነፃ የሚሰጠው ጸጋ ሞትን ካመጣው ከሰዎች ኃጢአት በላያቸው ላይ ከነገሠው የበለጠ ነው። ምክንያቱም ከእግዚአብሔር ጋር ትክክለኛ ግንኙነት እንድናደርግና የዘላለምን ሕይወት እንድናገኝ ያስችለናል። የውይይት ጥያቄ፡- ለአንድ ሃይማኖተኛ “ክርስቲያን” እየመሰከርህለት ሳለ የድነትን መንገድ በግልጽ ለማብራራት ትፈልጋለህ እንበል። ስለ እግዚአብሔር የድነት (ደኅንነት) መንገድ በሮሜ መልእክት ውስጥ ከተማርከው አሳብ በመነሣት የድነትን መንገድ እንዴት አድርገህ እንደምትገልጽ ጠቅለል አድርገህ አስረዳ። (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ሮሜ 5፡1-21 Read More »

እምነት እንጂ ሥራችን እንደማያድነን የሚያሳዩ የብሉይ ኪዳን ምሳሌዎች (4:1-25)

የውይይት ጥያቄ፡- እግዚአብሔር ሰዎችን የሚያጸድቀው በእምነት እንጂ በሥራ እንዳልሆነ ጳውሎስ ያረጋገጠበትን ሁኔታ በአጭሩ አብራራ። የጳውሎስን መልእክት የሚያነቡ አይሁዶች አዲስ የድነት (የደኅንነት) መንገድ እያቀረበልን ነው የሚል ስጋት አድሮባቸው ነበር። በተለይም እግዚአብሔር ሕግጋቱን የሚታዘዙትን እንደሚቀበል ያስተምራል ብለው ከሚያስቡት የብሉይ ኪዳን ትምህርት ተቃራኒ ስለመሰላቸው ተጨንቀው ነበር። «በእምነት መዳን በብሉይ ኪዳን የተገለጠውን እውነት አይሽረውም ወይ?» ሲሉ ጠየቁ። ጳውሎስ ግን ብሉይ ኪዳን በግልጽ እንደሚያስቀምጠው ከእግዚአብሔር ጋር መልካም ግንኙነት የሚፈጠረው በእምነት እንጂ ትክክለኛ የሆነ ነገር በማድረግ አለመሆኑን በማስገንዘብ መልስ ሰጥቷቸዋል። የውይይት ጥያቄ፡– ዘፍጥረት 15፡1-6 አንብብ። ሀ) እግዚእብሔር ለአብርሃም የሰጠው የተስፋ ቃል ምን ነበር? ለ) አብርሃም ለእግዚአብሔር የተስፋ ቃል የሰጠው ምላሽ ምን ነበር? ሐ) እግዚአብሔር ለዚህ ምላሹ ለአብርሃም የሰጠው ስጦታ ምን ነበር? ሀ. የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎች (ሮሜ 4፡1-8) ብሉይ ኪዳን ስለ አብርሃም ምን ይላል? (ሮሜ 4፡1-5) አብርሃም ታላቅ ተግባር በመፈጸሙ ነው እግዚአብሔር ጻድቅ የሚለውን ስያሜ እንደ ሽልማት የሰጠው? አልነበረም። ዘፍጥረት 15፡6 እንደሚያሳየው፥ የአይሁዶች አባት በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት ያገኘው የብዙ ሕዝብ አባት እንደሚሆን የተሰጠውን የተስፋ ቃል በማመኑ ምክንያት ነበር። የአብርሃም ጽድቅ እንደ ስጦታ «የተቆጠረ» እንጂ አብርሃም ላከናወነው ተግባር በደመወዝነት የተከፈለው አልነበረም። ሌላው የአይሁዶች ጀግና የነበረው ዳዊት፥ እግዚአብሔር ሰውን የሚባርከው ሕግን በመጠበቁና አንድን ታላቅ ተግባር በማከናወኑ ምክንያት እንዳልሆነ መስክሯል (ሮሜ 4፡6-8)። አንድ ሰው የሚባረከው እግዚአብሔር በነፃ ኃጢአቱን ይቅር ሲል ነው (መዝ. 32፡1-2)። ዳዊት ከእግዚአብሔር ጋር የነበረው ግንኙነት «በትክክለኛ» ነገር ላይ የተመሠረተ ቢሆን ኖሮ ይሞት እንደነበረ ገልጾአል። እርሱ ነፍሰ ገዳይና አመንዝራ ነበር። ነገር ግን ከእግዚአብሔር ጋር የነበረው ግንኙነት በአምላኩ ፍቅር፥ ጸጋና የኃጢአት ይቅርታ ላይ እንጂ የሚገባውን ዋጋ በመቀበሉ ላይ የተመሠረተ አልነበረም። ለ. አይሁዶችም ሆኑ አሕዛብ በእግዚአብሔር ዘንድ በእምነታቸው ምክንያት ተቀባይነት እንደሚያገኙ የሚያሳይ የአብርሃም ምሳሌነት (ሮሜ 4፡9-25)። ጳውሎስ እግዚአብሔር ሁልጊዜም ሰዎችን በእምነታቸው ላይ ተመሥርቶ እንደሚያጸድቅ ከአብርሃም ሕይወት ጠቅሶ አስረድቷል። አይሁዶች አብርሃም አባታችን ነው ይሉ ነበር። እርሱ የአይሁድ ሕዝብ ጅማሬ ነበር። እግዚአብሔር አይሁዶች መሆናቸውንና ከዚህም የተነሣ የተስፋ ሕዝብና የእግዚአብሔር ልዩ ሕዝብ መሆናቸውን ለማመልከት ለአብርሃም ውጫዊ ምልክት የሆነውን የግርዛት ሥርዓት ሰጥቶት ነበር። እዚህ ላይ የጳውሎስን ትምህርት ለመረዳት በአብርሃም ሕይወት ውስጥ የተከናወኑትን ተግባራት ቅደም ተከተል ማወቅ ይኖርብናል። በዘፍጥረት 12 እግዚአብሔር አብርሃምን ጠርቶ ከዑር ወደ ከነዓን እንዲሄድ አዘዘው። አሕዛብ የነበረው አብርሃም ሕይወቱን ከአደጋ ላይ በመጣል ቤተሰቡን ትቶ ወደ ከነዓን እንዲሄድ ያደረገው በእግዚአብሔር ላይ የነበረው እምነት ነበር። በዘፍጥረት 15፥ እግዚአብሔር ለአብርሃም እንደ ሰማይ ከዋክብት የበረከተ ዘር እንደሚሰጥ ተስፋ ገባ። አብርሃም የማይቻል የሚመስለውን የእግዚአብሔርን የተስፋ ቃል በማመኑ እግዚአብሔርም እምነቱን እንደ ጽድቅ ቆጠረለት። በዘፍጥረት 17፥ እግዚአብሔር ለአብርሃምና ለዘሩ የግርዛትን ሥርዓት ሰጠ። ይህም አብርሃም አይሁዳዊና ከእግዚአብሔር ጋር ትክክለኛ ግንኙነት የሚያደርግ ሰው መሆኑን የሚያሳየው ምልክት ነበር። በዚህ ጊዜ ነበር አብራም ይባል የነበረው አሕዛብ አብርሃም የተባለ አይሁዳዊ የሆነው። በዘፍጥረት 21፥ እግዚአብሔር ለአይሁዳዊው አብርሃም ተስፋ የገባለት ይስሕቅ የተባለ ልጅ ተወለደ። ጳውሎስ ከእነዚህ በአብርሃም ሕይወት ውስጥ ከተከሰቱት ነገሮች ቅድም ተከተል በመነሣት የሚከተለውን ገለጻ አድርጓል። እግዚአብሔር አብርሃምን ጻድቅ ያደረገው በግርዛት ሥርዓት አይሁዳዊ ከመሆኑ በፊት አሕዛብ ሳለ ነበር (ሮሜ 4፡9-15)። ይህም አንድ ሰው ከእግዚአብሔር ዘንድ ጽድቅን ለማግኘት አይሁዳዊ መሆንና መገረዝ አስፈላጊው አለመሆኑን ያሳያል። አብርሃም የብሉይ ኪዳንን ሕግ ሳይከተሉ፥ ሳይገረዙና አይሁዳዊ ሳይሆኑ በእግዚአብሔር የሚያምኑ አሕዛብ (ከሕግ ውጭ ያሉት) መንፈሳዊ አባት ነበር። አብርሃም፥ ከሕግ የነበሩት፥ በእግዚአብሔር ላይ እምነት የነበራቸው፥ የብሉይን ሕግ በመጠበቅና በመገረዝም በአካል አይሁዳዊ የነበሩት ሰዎችም አባት ነው። እግዚአብሔር ሰውን “ጥፋተኛ አይደለም” የሚልበት ዋነኛው መስፈርት በእግዚአብሔር ላይ የሆነ እምነት እንጂ አይሁዳዊ መሆን ወይም የብሉይ ኪዳን ሕግጋትን መከተል አይደለም። ሰውን እውነተኛ የአብርሃም ልጅ የሚያደርገውና ጽድቅን የሚያሰጠው እምነት ነው። ሕግን ለመጠበቅ የሚሞክሩና በራሳቸው ጥረት ድነት (ደኅንነት)ን ሊያገኙ እንደሚችሉ የሚያስቡ ሰዎች የእምነት ፈለጉን ስለማይከተሉ የአብርሃም ልጆች ሊሆኑ አይችሉም። ስለሆነም፥ የእግዚአብሔርን ሕግ ሙሉ ለሙሉ ሊጠብቁ ስለማይችሉ ከእግዚአብሔር ቁጣ ሥር ናቸው። ሐ. አብርሃም በእግዚአብሔር እውነተኛ እምነት ምን እንደሆነና የእግዚአብሔርን የተስፋ ቃል ማግኘት የሚቻለው አንድን ተግባር በማከናወን ሳይሆን በእምነት እንደሆነ በሕይወቱ አሳይቷል (ሮሜ 4፡16-23)። (ማስታወሻ፡- ለአብርሃም የተሰጠው የተስፋ ቃል ልጅ ነበር። ለእኛ የተሰጠን የተስፋ ቃል ድነት (ደኅንነት)ን ማግኘት ነው።) በዘፍጥረት 18፥ እግዚአብሔር ለአብርሃም በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ እርሱና ሣራ ልጅ እንደሚወልዱ ተስፋ ሰጥቶት ነበር። በሰው ግንዛቤ ይህ የተስፋ ቃል ሊፈጸም የማይችል ነበር። በዕድሜያቸው መግፋት የተነሣ አብርሃም (የ100 ዓመት አረጋዊ) እና ሣራ የ90 ዓመት አረጋዊት) በሥጋ ልጅ ሊወልዱ አይችሉም ነበር። ሣራ በትዳር ዘመናቸው ሁሉ መካን ነበረች። ስለሆነም፥ ልጅ የመውለድ ችሎታቸው ሙት ነበር። አብርሃም ግን እግዚአብሔር የሰጠውን የተስፋ ቃል አመነ። ሁልጊዜም እምነት የሚነሣው ከእግዚአብሔር የተስፋ ቃል እንጂ ከሰው ተስፋ አይደለም። አብርሃም ልጅ ለመውለድ አለመቻላቸውን ጨምሮ እግዚአብሔር ለሞተው ሕይወትን ሊሰጥ እንደሚችል ያውቅ ነበር። ስለሆነም፥ እግዚአብሔር የተስፋ ቃሉን እንደሚፈጽም አመነ። እግዚአብሔር የአብርሃምን እምነት ያከበረውና «ጥፋተኛ ያልሆነና» ከእርሱ ጋር ትክክለኛ ግንኙነት እያደረገ መሆኑን ያወጀው ለዚህ ነበር። ይህ ሁሉ የሆነው አብርሃም ከመገረዙና አይሁዳዊ ከመሆኑ በፊት ነበር። ስለሆነም፥ አብርሃም ከእግዚአብሔር ጋር ትክክለኛ ግንኙነት ለማድረግ የሚፈልጉ ሰዎች ሁሉ ሊከተሉት የሚገባ ምሳሌ ነው። በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ አማካኝነት ለድነታችን (ለደኅንነታችን) የሚያስፈልገውን ሁሉ እንዳሟላ የሚገልጸውን የእግዚአብሔርን ቃል አምነን እንቀበላለን እንጂ በራሳችን ጥረት ለመዳን አንሞክርም። (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

እምነት እንጂ ሥራችን እንደማያድነን የሚያሳዩ የብሉይ ኪዳን ምሳሌዎች (4:1-25) Read More »

የድነት (ደኅንነት) መሠረቱ የክርስቶስ ስለ ኃጢአተኞች መሞት ነው (ሮሜ 3፡21-31)

ጳውሎስ የወንጌል ገለጻውን ከክርስቶስ ሳይሆን ከሰዎች ኃጢአተኝነት እንደሚጀምር ከዚህ በፊት በነበረው ትምሕርታችን ተመልክተናል። ጳውሎስ መንፈሳዊና መልካም ሥነ ምግባራዊ ሕይወት ያላቸው የሚመስሉትን ጨምሮ ሰዎች ሁሉ ምን ያህል ልባቸው በክፋት እንደተሞላ እንዲያውቁ ይፈልጋል። ይህንንም ያደረገው ተስፋ እንዲቆርጡ ለማድረግ ሳይሆን፥ «እድን ዘንድ ምን ላድርግ?» የሚል ጥያቄ እንዲያነሡና ለድነት (ለደኅንነት) ወደ እግዚአብሔር እንዲመለሱ ነው። ጳውሎስ ስለ ድነት (ደኅንነት) ባቀረበው ትምህርት ሁለተኛው ዐቢይ ደረጃ ቅዱሱ አምላክ ኃጢአተኛ ሰዎችን እንዴት «ጻድቅ ነህ» ብሎ እንደሚያውጅላቸው የሚያሳይ ነው። የእግዚአብሔር ቃል የሌላቸው አሕዛብ ከእግዚአብሔር ፍርድ በታች ከሆኑና የእግዚአብሔርን ሕግ ለመፈጸም የሚጥሩ አይሁዶች በአግባቡ ለመፈጸም ስለተሳናቸው ኃጢአተኞች ከሆኑ፥ የሰው ዘር ምን ተስፋ አለው? ሰው ሊድን የሚችለው እንዴት ነው? ጳውሎስ ወንጌሉንና ሰው ሁሉ የሚድንበትን መንገድ ጠቅለል አድርጎ አቅርቧል። ሀ. «ከእግዚአብሔር የሆነ ጽድቅ» ተብሎ የተጠራው ድነት (ደኅንነት) የሚመነጨው ሰዎች ለእግዚአብሔር ከሚያከናውኑት ተግባር ሳይሆን እግዚአብሔር ለሰዎች ከሚሠራው ሥራ ነው። መሠረታዊ የጽድቅ ግንዛቤ እግዚአብሔር ከመሠረተው መመዘኛ ጋር መስማማቱ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚነግረን፥ እግዚአብሔር ሁልጊዜም ትክክለኛውን ተግባር የሚያከናውን ጻድቅ ሲሆን፥ የሰጠውን የተስፋ ቃል በሙሉ የሚፈጽምና የመሠረተውን ሥነ ምግባራዊ መመዘኛ የሚያሟላ ፍትሐዊ አምላክ ነው። የጻድቅነትን መመዘኛ የመሠረተው እግዚአብሔር ነው። ጻድቅ ፈራጅ እንደመሆኑ መጠን፥ ሰዎች እርሱ ከሰጣቸው ሕግጋትና መመዘኛዎች ጋር ተስማምተው ለመኖራቸው ወይም ላለመኖራቸው በኃላፊነት ይጠይቃቸዋል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ «ጻድቅ» የሚለው ቃል አያሌ የተለያዩ ትርጉሞችን ይሰጣል። ጻድቅ የሚለው ቃል ሰዎችን በሚያመለክትበት ጊዜ የሚከተሉትን አሳቦች ያሳያል። ከእግዚአብሔር ፈቃድና ትእዛዛት ጋር የሚስማማ ሕይወት የሚመራ ሰው። በማኅበረሰቡ መካከል ሰዎች እርስ በርሳቸው ሰላማዊና ትክክለኛ ግንኙነት እንዲኖራቸው የሚያግዝ ሕይወት የሚኖር ሰው። ከእግዚአብሔር ጋር ትክክለኛ ግንኙነት እንደሌለው የታወጀለት ሰው። ይህ ጽድቅ የእግዚአብሔር ስጦታ ሲሆን፥ እግዚአብሔር ስጦታውን በእምነት ወደ እርሱ ለሚመለሰው ይሰጠዋል። ጳውሎስ ከሮሜ 3፡21-26 ውስጥ የጠቀሰው የዚህን ጽድቅ ትርጉም ነው። ጳውሎስ «የእግዚአብሔር ጻድቅ» የሚለው ግለሰቡ ከእግዚአብሔር ጋር ትክክለኛ ግንኙነት እንዳለው የሚያመለክተውን ሕጋዊ አዋጅ ነው። በሌላ አነጋገር ሰውዬው ድኖአል። ነገሩ ገንዘብ ሰርቆ በፖሊስ እንደመያዝ ዓይነት ነው። ፖሊሱ ሌባውን ወደ ዳኛው ያቀርበዋል። ዳኛው መረጃውን ተመልክቶ የጥፋተኝነት ውሳኔ በማስተላለፍ ብዙ ገንዘብ ይበይናል። ከዚያም ዳኛው ከራሱ ኪስ ገንዘቡን አውጥቶ በመክፈል ጥፋተኞች አለመሆናችንን በአደባባይ ለሕዝብ ይገልጻል። ጥፋተኞች አይደሉም ብሎ በመግለጹ ጥፋት እልፈጸማችሁም ማለቱ አይደለም። ነገር ግን የጥፋተኝነቱ ዋጋ እንደተከፈለና ከሕግ የሚፈለግ ቅጣት እንደማይኖር መግለጹ ነው። በመሆኑም፥ ሌባው ስርቆቱን እንዳልፈጸመ ያህል ይስተናገዳል። ለ. ጥፋተኛ ያለመሆንና ከእግዚአብሔር ጋር ግንኙነት የማድረግ ተግባር የሚመጣው «ከሕግ ውጭ» ነው። ይህ ሰዎች የእግዚአብሔርን ሕግጋት በመጠበቅ ከእርሱ ጋር ትክክለኛ ግንኙነት ለማድረግ በመሞክር የሚያመጡት አይደለም። ለምን? ምክንያቱም ሕጉን ያፈረስን ኃጢአተኞች ስለሆንን ነው። ሐ. ይህ ከእግዚአብሔር ጋር ትክክለኛ ግንኙነት የማድረግ እወጃ አይሁዶችም ሆኑ አሕዛብ ሊያገኙ የሚችሉት ነው። የሚፈለገው ነገር ቢኖር የግለሰቡ በኢየሱስ ክርስቶስ ማመን ነው። እይሁዶችም ሆኑ አሕዛብ ኃጢአተኞች እንደሆኑ ሁሉ፥ «ጻድቅ» ተብሎ የመጠራቱ የእግዚአብሔር ግሩም ስጦታም ለሰዎች ሁሉ ክፍት ነው። ይህም በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነትን እንዲያገኙና ከኃጢአት እንዲድኑ ያስችላቸዋል። መ. የእግዚአብሔር ነፃ ስጦታ ጳውሎስ በምናቡ የፈጠረው ሳይሆን፥ «ሕግና ነቢያት» የተባለውን ብሉይ ኪዳንን ከመገንዘብ የመነጨ ነው። ጳውሎስ «እምነት» የሚለውን ቃል እንዴት እንደሚጠቀም መገንዘቡ ጠቃሚ ነው። የሚያድን እምነት ክርስቶስ ስለ እኛ በመስቀል ላይ እንደሞተ ማወቅ ብቻ ሳይሆን፥ ጠቅላላ ሕይወትን በሚለውጠው እውነት ላይ ሙሉ ለሙሉ መደገፍ ነው። በክርስቶስ ማመን ክርስቶስ በመስቀል ላይ ለኃጢአተኞች ሞቷል የሚለውን አእምሯዊ እምነትና አንድን ነገር በማድረግ የእግዚአብሔርን ሞገስ ለማግኘት አለመጣርን ያመለክታል። ሌሎች ሰብአዊ የድነት (ደኅንነት) መንገዶችን ትተን በእግዚአብሔር የድነት (ደኅንነት) መንገድ ላይ እንደገፋለን ማለት ነው። ሠ. ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ካከናወነው ተግባር የተነሣ የእግዚአብሔርን ጽድቅ ማግኘት ይቻላል። እግዚአብሔር አብ ክርስቶስን ወደ መስቀሉ ልኮታል። ክርስቶስ የስርየት መሥዋዕት ሆኖ ደሙን በማፍሰሱ እግዚአብሔር ለሰዎች ድነት (ደኅንነት) በር ከፍቷል። (የእግዚአብሔር የይቅርታ መርህ ሁልጊዜም አንዱን ሕይወት ለሌላው መሥዋዕት የማድረግ ነበር። የእንስሳት መሥዋዕት ስለ ሰው ሕይወት ሲባል የእንስሳት መሰጠት ነበር። የክርስቶስ መሥዋዕት ክርስቶስ ሕይወቱን ለሕይወታችን እንደሰጠ በመገንዘብ ላይ የተመሠረተ ነው።) አማኞች አሁን «ቤዛነትን» አግኝተዋል። ይህም ከኃጢአተኛነት በደል ወጥተው እግዚአብሔርን ለማገልገል ነፃ መሆናቸውን የሚያሳይ ሌላው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ቃል ነው። ዳኛው የኃጢአት ደመወዝ ሞት እንደሆነ አውጇል። ሁላችንም ኃጢአተኞች ስለሆንን መሞት እንዳለብን ያውጃል፡፡ ከዚያም እግዚአብሔር ፍጹም የሆነውን ልጁን በምትካችን እንዲሞት ይጠይቀዋል። ይህም ሞት ለኃጢአት የመሞትን ሕጋዊ መስፈርት ያሟላል። ይህ ክርስቶስ ስለ እኛ መሞቱን መቀበላችን እግዚአብሔርን ለማገልገል ነፃ ያወጣናል። (ስርየት የሚለው ቃል «የእግዚአብሔርን የፍርድ ቁጣ የሚመልስ» ማለት ሲሆን። ቤዛነት የሚለው ቃል ደግሞ ጥንት ባሪያዎችን ከመግዛት ተግባር የመጣ ነው። ብዙውን ጊዜ ባሪያ የነበረ ሰው ለሽያጭ ወደ ገበያ ይወሰድ ነበር። ሰዎች ይገዟቸውና እንደባሪያ ይገለገሉባቸዋል። አንዳንድ ጊዜ ግን ከርኅራኄ የተነሣ አንዳንድ ሰዎች ባሪያዎችን ገዝተው ነፃ ያደርጓቸዋል። ከዚያ በኋላ ቀደም ሲል ባሪያዎች የነበሩት ሰዎች ለሌሎች መገዛታቸው ቀርቶ የራሳቸውን ምርጫ የማድረግና በፈለጉት መንገድ የመኖር ነጻነት ይኖራቸዋል። «ተቤዥተዋል» ማለት ነው። በብሉይና አዲስ ኪዳን እግዚአብሔር ሰዎችን ከባርነት ሕይወታቸው «የሚገዛ» (ከግብጽ፥ ከኃጢአት፥ ከመከራ) እና የተፈጠሩለትን ዓላማ እንዲፈጽሙ የሚያደርግ ቤዛ እንደሆነ ተመልክቷል። የተፈጠሩትም ፈጣሪ አምላካቸውን እንዲያከብሩ ነው። ረ. እግዚአብሔር አብ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የሚገኘውን የድነት (ደኅንነት) መንገድ ሲያዘጋጅ ጻድቅና አጽዳቂም ነበር። እንደ ቅዱስ ፈራጅ እግዚአብሔር የሰውን ልጅ ኃጢአተኝነት አሳንሶ ለመለካትና «ይቅር ብያችኋለሁ» ሊል አይችልም ነበር። እግዚአብሔር ቅዱስ ነው ሲባል የኃጢአተኝነት ዓመፅ መቀጣት አለበት ማለት ነው። ከአዳም ዘመን ጀምሮ የእግዚአብሔር ፍርድ «ኃጢአትን የሚሠራ እርሱ ይሙት» የሚል ነበር። በሌላ በኩል፥ እግዚአብሔር አብ አፍቃሪ፥ መሐሪና ቸር አምላክ ነው። ስለሆነም ከእርሱ ጋር ሊዛመዱ የሚፈልጉትን ሰዎች ለማዳን ይፈልጋል። ስለሆነም እግዚአብሔር ራሱ የድነትን (ደኅንነትን) መንገድ አዘጋጅቷል። በቅድስናውና በፍቅሩ፥ ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ በመሞት የኃጢአታችንን ቅጣት እንዲከፍል አድርጓል። እግዚአብሔር ኃጢአትን በመቅጣቱ ጻድቅ ነበር። ይሁን እንጂ ሰዎችን ጻድቅ የሚያደርገውም እርሱ ራሱ ነበር። የኃጢአታችን ዋጋ ስለተከፈለ እግዚአብሔር «ከበደል ነፃ ናችሁ» ሊለን ይችላል። ሰ. የእግዚአብሔርን የድነት (ደኅንነት) ስጦታ የምንቀበለው በሥራ ሳይሆን ክርስቶስ ለእኛ በመሞቱ ነው (ሮሜ 3፡27-31)። የእግዚአብሔርን የድነት (ደኅንነት) ስጦታ ለማግኘት በፍጹም መደገፍ ላይ የተመሠረተ እምነት ያስፈልጋል። እንደ ድነት (ደኅንነት) ተስፋችን ሆኖ ኢየሱስ በምትካችን መሞቱን ስናምን «አላጠፋህም» የሚለውን የእግዚአብሔር አዋጅ መቀበል እንችላለን። ይህም ሕግ ላላቸው አይሁዶችም ሆነ ሕግ ለሌላቸው አሕዛብ ሁሉ የሚሠራ ነው። የድነትን (ደኅንነትን) መንገድ ያዘጋጀው እግዚአብሔር በመሆኑ፥ ማንም ከእግዚአብሔር ጋር ትክክለኛ ግንኙነት ለመመሥረት ባከናወነው ተግባር በእግዚአብሔር ፊትም ሆነ በሌሎች ዘንድ ሊመካ አይችልም። የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ሮሜ 3፡22-24 በቃልህ አጥና። ለ) ይህን ክፍል በመጠቀም ወንጌሉን በራስህ አገላለጽ ጠቅለል አድርገህ ግለጽ። (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የድነት (ደኅንነት) መሠረቱ የክርስቶስ ስለ ኃጢአተኞች መሞት ነው (ሮሜ 3፡21-31) Read More »

ሁሉም ሰው ኃጢአተኛ ስለሆነ ደኅንነትን ማግኘት ይኖርበታል (ሮሜ 3፡9-20)

የውይይት ጥያቄ፡– ሮሜ 3፡9-20 አንብብ። ሀ) ጳውሎስ ሰዎች ሁሉ ኃጢአተኞች ስለመሆናቸው የሚሰጠው መደምደሚያ ምንድን ነው? ለ) ሰዎች ሁሉ በክርስቶስ ከማመናቸው በፊት ይህን እውነት ማወቅ ያለባቸው ለምን ይመስልሃል? ጳውሎስ ስለ ሰዎች ኃጢአተኝነት ያቀረበውን የመጀመሪያውን ክፍል ትምህርት በግልጽ አሳብ አጠቃሎታል። ይህም ሰዎች ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ኃጢአተኞች ናቸው የሚል ነው። የተጻፈ የእግዚአብሔር ሕግ ባይኖራቸውም እንኳን፥ አሕዛብ ሁሉ ኃጢአተኞች ናቸው። አይሁድም ኃጢአተኛች ናቸው። በምድር ላይ በመጽሐፍ ቅዱስም ሆነ በሰው ሕሊና ውስጥ የተጻፈውን የእግዚአብሔርን ሕግ ሙሉ በሙሉ የጠበቀ ሰው ስለሌለ፥ በእግዚአብሔር ፊት በጥረቱ ጻድቅ ተብሎ ሊጠራ የሚችል ሰው የለም። የእግዚአብሔር ሕግ አይሁዶችም ሆኑ አሕዛብ ኃጢአተኞች መሆናቸውን ለማስገንዘብ ይረዳል። (ጳውሎስ ሕጉ የተሰጠው ሰዎች በእግዚአብሔር ፊት ጻድቅ የሚሆኑበትን መንገድ ለማስገኘት ሳይሆን፥ ሰዎች የእግዚአብሔርን ጸጋና ምሕረት ይቀበሉ ዘንድ ኃጢአተኝነታቸውን ለማሳየት መሆኑን አመልክቷል) መልካም ሥነ ምግባር ያላቸው ሰዎችም ከኃጢአት የጸዱ አይደሉም። ስለሆነም፥ ሰዎች ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት «ኃጢአተኛ» የሚል የፍርድ ውሳኔ ይሰጣቸዋል። ዛሬ ሰዎች ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ዘላለማዊ ፍርድ ሊቀበሉ የሚገባቸው ኃጢአተኞች የመሆናቸውን እውነት እየዘነጋን በመልካምነታቸው ላይ እናተኩራለን። ሰዎች ወደ ቤተ ክርስቲያናችን ሲመጡና ስለ ክርስቶስ ስንመሰክርላቸው፥ ክርስቶስ በሚሰጣቸው በረከት ላይ አጽንኦት እናደርጋለን። «በክርስቶስ ስታምን የዘላለምን ሕይወት ታገኛለህ፥ ትፈወሳለህ፥ ትባረካለህ» እንላለን። ይህም ሰዎች ከእግዚአብሔር አንድ ነገር ለማግኘት ብለው የሚከተሉትን የራስወዳድነት ክርስትና ያበረታታል። እንዲህ ዓይነት ክርስቲያኖች ለኃጢአታቸው ካለማፈራቸውም በላይ፥ ክርስቶስ እነርሱን ከዘላለማዊ ሞት ለመታደግ በመስቀል ላይ ስለመሞቱ አክብሮት የላቸውም። ጳውሎስ በእግዚአብሔር ፊት ምን ያህል ኃጢአተኞች እንደሆንን በመግለጽ ወንጌሉን ያብራራል፡፡ የእግዚአብሔርን ምሕረትና ጸጋ ልንፈልግ የምንችለው በጻድቅ አምላክ ፊት ዘላለማዊ ፍርድ ሊቀበሉ የሚገባቸው ኃጢአተኞች መሆናችንን ስንገነዘብ ብቻ ነው። እግዚአብሔር ከኃጢአተኝነታችን እንዳዳነንና ልጆቹ እንዳደረገን በመገንዘብ ለዘላለም ልናመሰግን የምንችለው በዚህ ጊዜ ብቻ ነው። ከዚህ በኋላ በራሳችን ብቃት ላይ የነበረን ሰብአዊ ኩራት ስፍራውን ይለቅቃል። በምትኩም ልጁን ስለሰጠን እግዚአብሔርን እያመሰገንን እርሱን የሚያስከብርና ምስጋናችንን የሚገልጽ ሕይወት ለመኖር ከልባችን እንነሣሣለን። የውይይት ጥያቄ፡- ጳውሎስ በሮሜ ያደረገውን ምሳሌነት በመከተል ወንጌሉን ብንሰብክ፥ የእሑድ ቀን የነፍሳት ጥሪያችን እንዴት ይለወጥ ይሆን? ለ) በሰዎች ጥሩነት ወይም ክርስቲያን በመሆን በሚያገኙት ነገር ላይ ሳይሆን በክፋታቸው ላይ ብናተኩር፥ ሰዎች በክርስቶስና በእግዚአብሔር ላይ ያላቸው አመለካከት እንዴት የሚለወጥ ይመስልሃል? (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ሁሉም ሰው ኃጢአተኛ ስለሆነ ደኅንነትን ማግኘት ይኖርበታል (ሮሜ 3፡9-20) Read More »

ሃይማኖተኛ የሆኑ አይሁዶችም ኃጢአተኞች ናቸው (ሮሜ 2፡1-3፡8)

የውይይት ጥያቄ፡- ሮሜ 2፡1-3፡8 አንብብ። አይሁዶች (እና የትኛውም ሃይማኖተኛ ጥሩ ሰው) በቅዱስ አምላክ ፊት ኃጢአተኞች መሆናቸውን በራስህ ቃል በአጭሩ አስረዳ። አይሁዶችና ሌሎች ጥሩ ሃይማኖተኛ ሰዎች ስለ አሕዛብ ኃጢአተኝነት በሚያነቡበት ጊዜ ኩራት ሳይሰማቸው አይቀርም። ጥቂት ሰዎች፥ «እኛ እንደ እነርሱ ክፉዎች አይደለንም። የእግዚአብሔርን ሕግጋት እናከብራለን። የወሲብ ኃጢአት አንፈጽምም። ማንንም አልገደልንም። ጣዖታትን እናመልክም። ስለዚህ እግዚአብሔር ሊቀበልን ይገባል» ብለው ያስቡ ነበር። በቀጣዩ ክፍል ጳውሎስ የብሉይ ኪዳን ሕግጋትን በመጠበቃቸው የሚኩራሩትን ሃይማኖተኛ አይሁዶች ያናግራል። ሀ. እግዚአብሔር ያለአድልዎና በእውነት የሚፈርድ ስለሆነ የሃይማኖት ሰዎች ከኩራት እንዲጠበቁ ጳውሎስ ያስጠነቅቃል (ሮሜ 2፡1-16)። የሃይማኖት ሰዎች ከክፉ ጣዖት አምላኪ አሕዛብ የሚሻሉ ሊመስል ይችላል። ጳውሎስ ግን የሃይማኖት ሰዎች እንኳ ኃጢአተኞች በመሆናቸው ለእግዚአብሔር ፍርድ እንደተጋለጡ በመግለጽ ያስጠነቅቃል። የሃይማኖት ሰዎች አምላክ እንደሌላቸው አሕዛብ ግልጽ ኃጢአት ላይፈጽሙ ቢችሉም፥ በልባቸው ተመሳሳይ ኃጢአት ይሠራሉ። ጳውሎስ የእግዚአብሔር ፍርድ በሦስት መርሆዎች ላይ የተመሠረተ እንደሆነ ያስረዳል። በመጀመሪያ፥ የእግዚአብሔር ፍርድ በእውነት ላይ የተመሠረተ ነው። እርሱ በሰው ሕይወት ውስጥ የሚፈጸመውን ነገር በትክክል ያውቃል (ሮሜ 2፡1-4)፡፡ የሃይማኖት ሰዎች ጥሩ ሰዎች መስለው ሰዎችን ሊያሞኙ ሲሞክሩም እንኳን፥ እግዚአብሔር የልባቸውን ኃጢአተኝነት ያውቃል። የሃይማኖት ሰዎች በግልጽ ኃጢአት ላይሠሩ፥ ጣዖት ላያመልኩ፥ ላይገድሉ፥ ወሲባዊ እርኩሰት ላይፈጽሙ ቢችሉም፥ ትዕቢትና የኃጢአት አሳብ ይኖርባቸዋል። ስለሆነም፥ ከእግዚአብሔር የቅድስና መመዘኛ አንጻር ሲታይ በተቀደሰው አምላክ ፊት ኃጢአተኞች ናቸው። እግዚአብሔር በፍጥነት አልፈረደባቸውም ማለት ስለ ስውር ኃጢአታቸው ግድ የለውም ማለት አይደለም። ነገር ግን እግዚአብሔር በፍጥነት የማይፈርደው በደግነቱ ሰዎች ንስሐ እንዲገቡ ጊዜ ለመስጠት እንደሆነ ያመለክታል። ሁለተኛ፥ የእግዚአብሔር ፍርድ በአድልዎ ላይ ያልተመሠረተ ነው (ሮሜ 2፡5-16)። ጳውሎስ የእግዚአብሔር ፍርድ በክፉ ተግባራቸው ላይ የተመሠረተ መሆኑን ተናግሯል። አይሁዶች የእግዚአብሔር የብሉይ ኪዳን ቤተሰብ አካል በመሆናቸው እግዚአብሔር ለእነርሱ የተለየ የፍርድ መመዘኛ እንዲጠቀም አያደርገውም። አይሁድም ቢሆኑ አሕዛብ እግዚአብሔር በእያንዳንዱ ሰው ላይ ፍርድን የሚሰጠው አድልዎ በሌለበት ሁኔታ በሥራቸው ላይ ተመሥርቶ ነው። ጳውሎስ በዚህ ክፍል ሊያስተላልፍ የሚፈልገውን መልእክት መረዳቱ ጠቃሚ ነው። ከአዲስ ኪዳን ገለጻ ለመረዳት እንደሚቻለው፥ ሁሉም ሰው ኃጢአተኛ ስለሆነ ማንም ራሱን ሊያድን የሚችል የለም። ሁላችንም ኃጢአተኞች ነን። ስለሆነም፥ ሁሉም መዳንን ያገኝ ዘንድ የእግዚአብሔር ጸጋ ያስፈልገዋል (ኤፌ. 2፡8-9)። በሌላ በኩል፥ ተግባራችን መዳን አለመዳናችንን ያሳያል። ድነትን (ደኅንነትን) አግኝተን አዲስ ፍጥረት ከሆንን (2ኛ ቆሮ. 5፡17)፥ ልባችንና ተግባራችን ይለወጣል። በሮሜ 2፡12-16፥ ጳውሎስ አይሁዶችም ሆኑ አሕዛብ የእግዚአብሔርን ሕግ ሊታዘዙና በራሳቸው ጽድቅ ሊድኑ እንደሚችሉ እያስተማረ አይደለም። ጳውሎስ ወረድ ብሎ ሥነ ምግባራዊ ሕይወት የሚመሩ አይሁዶች ኃጢአተኞች መሆናቸውን መግለጹ ይህንን አሳብ እንድንረዳ ያደርጋል። ጳውሎስ ሁለት ዓይነት የእግዚአብሔር ሕግጋት እንዳሉ አመልክቷል። እነዚህም ለአይሁዶች የተሰጠው የተጻፈ ሕግና በሰዎች ሁሉ ሕሊናና ልብ ውስጥ የተቀመጠው ያልተጻፈ ሕግ ናቸው። እግዚአብሔር የብሉይ ኪዳን ሕግጋት ባላቸው አይሁዶች ላይ የሚፈርደው እነዚያን የተጻፉ ሕግጋት በጠበቁበት ሁኔታ ላይ በመመሥረት ነው። ከሕሊና በስተቀር የተጻፈ ሕግ በሌላቸው አሕዛብ ላይ የሚፈርደው ግን በልባቸው ውስጥ የተጻፈውን ሕግ በጠበቁበት ሁኔታ ላይ በመመሥረት ነው። እግዚአብሔር አሕዛብ ሰምተው ለማያውቋቸው የተጻፉ ሕግጋት ተጠያቂ አያደርጋቸውም። ነገር ግን አይሁዶችም ሆኑ አሕዛብ የተጻፉ ወይም ያልተጻፉ ሕግጋትን ሙሉ ለሙሉ ጠብቀው ከፍርድ ሊያመልጡ ይችላሉ? ጳውሎስ ወደ በኋላ እንደገለጸው፥ አሕዛብም ሆኑ አይሁድ የእግዚአብሔርን ሕግጋት ሙሉ ለሙሉ ሊጠብቁ አይችሉም። ስለሆነም፥ ሰዎች ሁሉ ከእግዚአብሔር ፍርድ በታች ስለሆኑ፥ ለመዳን ሌላ መፍትሔ ማግኘት ይኖርባቸዋል። ሦስተኛ፥ ጳውሎስ በኋላ እንዳመለከተው፥ እግዚአብሔር ሰዎችን የሚያድነው ከክርስቶስ ጋር ባላቸው ግንኙነት ላይ በመመሥረት ነው (ሮሜ 3፡21-30)፡፡ ለ. አይሁዳዊ መሆን በእግዚአብሔር ዘንድ የተቀባይነትን ዋስትና አያስገኝም (ሮሜ 2፡17–3፡8)። ለብዙ ዓመታት ጳውሎስ ሃይማኖተኛ አይሁዳዊና ኵሩ ፈሪሳዊ ነበር። አይሁዶች የሚያስቡበትን መንገድ ያውቅ ነበር። 1) የእግዚአብሔር ምርጥ ሕዝብ በመሆናቸው፥ 2) የእግዚአብሔር የተጻፈ ቃል ያላቸውና 3) የተገረዙ በመሆናቸው ይኩራሩ ነበር። ይህ ኩራት ብዙውን ጊዜ አይሁዶች ኃጢአተኝነታቸውን እንዳያዩ ስላደረጋቸው፥ ወደ መንፈሳዊ ኩራትና በራስ ወደ መርካት መርቷቸዋል። ጳውሎስ የአይሁዶችን ኃጢአተኝነት ለማሳየት ሲል አይሁዶች በሚማረኩባቸው ሁለት ነገሮች ላይ ያተኩራል። የተጻፈ ዘላለማዊ የእግዚአብሔር ቃል ማግኘት፡ ጳውሎስ ዋናው የእግዚአብሔርን ቃል መቀበል ሳይሆን ቃሉን መታዘዝ እንደሆነ ለአይሁዶች አስገንዝቧቸዋል። አይሁዶች የእግዚአብሔር ቃል ስላለን «ለዓይነ ሥውራን፥ በጨለማ ላሉት፥ ለሞኞችና፥ ሕፃን ለሆኑት» አሕዛብ «መሪዎች ነን» በሚል ተመክተው ይሆናል። ነገር ግን ሕይወታቸውን በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ ከተጻፈው ጋር ሲያነጻጽሩት፥ የልባቸውን ክፋት ሊመለከቱ ይችሉ ነበር። አሥርቱ ትእዛዛት አይሁዶች እንዳይሰርቁና እንዳያመነዝሩ ያዛሉ። ነገር ግን አይሁዶች ከሌሎች ሰዎች ጋር ባላቸው ግንኙነት (በተለይም በንግድ) ብዙውን ጊዜ ከማጭበርበርና ዝሙትን ከመፈጸም ወደኋላ አይሉም ነበር። አምልኮተ ጣዖትን እየተቃወሙ ቢሰብኩም፥ ዕድሉ በሚገጥማቸው ጊዜ ገንዘብ ከቤተ መቅደስ ወስደው ለራሳቸው ይጠቀማሉ። ዘላለማዊ የእግዚአብሔር ቃል ቢኖራቸውም፥ አይሁዶች እግዚአብሔርን አያስከብሩም ነበር። በዚህ አኗኗራቸውም ዘላለማዊ ቃል ያልነበራቸው አሕዛብ በአምላካቸው ላይ እንዲሳለቁ አድርገዋል። የውይይት ጥያቄ፡– የዘላለም ቃል አለን ብለን እየተመካን በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ የተጻፈውን እውነት ባለመታዘዝ የክርስቶስን ስም የምናሰድብባቸውን መንገዶች ዘርዝር። መገረዝ፡ እግዚአብሔር አብርሃምና ልጆቹ፥ የእርሱ ሕዝብ እንደሆኑና ከእርሱ ጋር ልዩ ግንኙነት ያላቸው መሆናቸውን ለማሳየት ውጫዊ ምልክት የሆነውን የግርዛትን ሥርዓት ሰጥቷቸዋል። አይሁዶች አንድ ሰው ሥጋዊ ግርዛትን እስከፈጸመ ድረስ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሚሆን ያምኑ ነበር። ዋናው የልብ ዝንባሌ እንደሆነና አንድ ሰው ከእግዚአብሔር ጋር ያለው ግንኙነት በእምነትና በታዛዥነት እንደሚረጋገጥ ዘንግተው ነበር። ይህ ውስጣዊ ግርዛት ነው። አንድ አሕዛብ በሥጋ ባይገረዝም፥ እንደ አብርሃም በእምነትና በታዛዥነት ከእግዚአብሔር ጋር በመገናኘቱ የልብ ግርዛት ሊሆንለት ይችላል። ለእግዚአብሔር ዋናው ነገር ይሄ ነው እንጂ ውጫዊ የሆነ የሥጋ መገፈፍ አይደለም። እውነተኛ አይሁዳዊነትም የአንድ ነገድ አባልነት ሳይሆን ከእግዚአብሔር ጋር በእምነት የመገናኘት ጉዳይ ነው። የውይይት ጥያቄ፡- በሰው የልብ ሁኔታ ላይ ሳናተኩር በውጫዊ ሥርዓቶች (ለምሳሌ፥ ጥምቀት፥ አለመጠጣት) ላይ ልንመካ የምንችልባቸው መንገዶች የትኞቹ ናቸው? ጳውሎስ በኢየሩሳሌም የነበሩት ብዙ አይሁዶች እንዳልተረዱት ሁሉ የሮም አይሁዶችም በተሳሳተ መልኩ እንዳይረዱት ሰግቶ ነበር። ጳውሎስ አይሁዳዊነታቸውን በመቃወም መገረዝና የእግዚአብሔርን ቃል መቀበል ምንም ጥቅም እንደሌለው የሚያስተምር መስሏቸው ነበር። ጳውሎስ ግን ሕግን እየተቃወመ አልነበረም። ፀረ-አይሁዳዊ ሆኖ አይሁዶች ቅርሳቸውን እንዲትዉ እያስተማረ አልነበረም። ጳውሎስ አይሁዶች ሁለት ነገሮችን እንዲገነዘቡለት ይፈልግ ነበር። እነዚህን አሳቦች ወደ በኋላ በሰፊው ያብራራቸዋል። በመጀመሪያ፥ አንዳንድ አይሁዶች እምነትን አጥተው እግዚአብሔርን ባለመታዘዛቸው እግዚአብሔር ለአይሁዶች የሰጠውን አስደናቂ በረከት ለሌሎች ሊያስተላልፉ አልቻሉም። የተጻፈው የእግዚአብሔር ቃል አሁንም ቢሆን አይሁዶችን ጨምሮ ዓለምን ሁሉ የሚፈርድበት ፍጹማዊ መመዘኛው ነበር። ሁለተኛ፥ አይሁዶች እንደ አሕዛብ የእግዚአብሔርን ሕግጋት ሙሉ በሙሉ ለመታዘዝ አለመቻላቸው ሰዎች ሁሉ እግዚአብሔር በክርስቶስ በኩል ወዳዘጋጀው የጽድቅ መስመር ሊመለሱ እንደሚገባ ያሳያል። (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ሃይማኖተኛ የሆኑ አይሁዶችም ኃጢአተኞች ናቸው (ሮሜ 2፡1-3፡8) Read More »

አሕዛብ ኃጢአትን ሠርተዋል (ሮሜ 1፡18-32)

ወንጌል የሚለው ቃል መልካም የምሥራች ማለት ነው። ይህ እግዚአብሔር ኃጢአታችንን ሁሉ ይቅር ብሎ በነፃ እንደሚያሰናብተን የሚያረጋግጥ አዋጅ ነው። በቤተሰቡ ውስጥ ተቀባይነትን አግኝተን ለዘላለም ልንድን እንችላለን። ሌላኛው የወንጌሉ ገጽታ «የእግዚአብሔር ቁጣ» ነው። ይህ ቁጣ ባልዳኑት ሰዎች ላይ እግዚአብሔር የሚያሳየው የጥላቻ ስሜት እይደለም። እግዚአብሔር ሰዎችን ሁሉ እንደሚወድ እናውቃለን (ዮሐ. 3፡16)። ነገር ግን ይህ ቁጣ እግዚአብሔር ዐመፃን በሚያደርጉት ላይ የሚያመጣው ቅዱስ ፍርድና ቅጣት ነው። እግዚአብሔር ቅዱስና ኃጢአትን የሚቀጣ አምላክ በመሆኑ፥ ኃጢአትን ዝም ብሎ አያልፍም። ጳውሎስ ወንጌሉን በጥድፊያ የሰበከው ይህ ቅጣት ባላመኑት ሰዎች ላይ ዘላለማዊ መዘዝ ስለሚያስከትል ነው። የእግዚአብሔር ቁጣ የማያምኑትን ሰዎች የሚያጋጥም የሲኦል ፍርድ ብቻ ሳይሆን፥ አሁንም መንፈሳዊ ሕይወት በማይኖሩ ሰዎችም ላይ የሚደርስ እንደሆነ ጳውሎስ ገልጾአል። ጳውሎስ የአሕዛብ ክርስቲያኖች እግዚአብሔር በዙሪያቸው ያሉትን አሕዛብ ሁኔታ የሚያመለክትበትን መንገድ እንዲገነዘቡ አድርጓቸዋል። ሰዎች ወንጌልን ባለመስማታቸው ምክንያት ከእግዚአብሔር ፍርድ ያመልጣሉ ብሎ መገመት እንደማያስፈልግ ክርስቲያኖች ቢገነዘቡ መልካም ነው። ሰዎች ወንጌልን አለመስማታቸው ድነትን (ደኅንነትን) ለማግኘት ምክንያት ሊሆን አይችልም። ሮማውያን በከተማዪቱ ውስጥ ለተለያዩ ጣዖታት ቤተ መቅደሶችን ሠርተው የሚያመልኩ ሃይማኖታዊ ሰዎች ነበሩ። ነገር ግን ጳውሎስ ሃይማኖተኛነታቸውንና ኃጢአተኝነታቸውን ከእግዚአብሔር እይታ አንጻር ሲመለከት ከዓመፀኝነትና ከኃጢአት በስተቀር ምንም መልካም ነገር እንዳልነበራቸው ተገንዝቧል። ይህም የሮማውያን ብቻ ሳይሆን የሁሉም ነገዶችና ሕዝቦች ባሕርይ ነው። የውይይት ጥያቄ፡– ዛሬ የእግዚአብሔር ቁጣ እንዲሁም የሕዝቡ ዓመፀኝነትና ኃጢአተኝነት በኢትዮጵያ ውስጥ የሚታየው እንዴት ነው? በብዙ ትምህርት ቤቶቻችን ውስጥ የአዝጋሚ ለውጥ (ኢቮሉሽን) ንድፈ አሳብን ያስተምራሉ። ይህም ሰዎችና እንስሳት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻሉ እንደሚሄዱ የሚያስረዳ ሳይንሳዊ ትምህርት ነው። ጳውሎስ ግን ዓለምን የተመለከተው ለየት ባለ መንገድ ነበር። ጳውሎስ እግዚአብሔርን የማያመልክና ሕግጋቱን የማይታዘዝ የትኛውም ሰው ወይም አገር በጥፋት ጎዳና ላይ እንደሚገኝ ገልጾአል። በዚህ ክፍል፥ ጳውሎስ የእግዚአብሔርን የተጻፉ ሕግጋት ላያውቁ ቢችሉም በኃጢአተኛ ልባቸው በፈጣሪያቸው ላይ ማመፁን እንደሚመርጡ በመግለጽ የሰው ልጆችን በተለይም የአሕዛብን ውድቀት አስረድቷል። ጳውሎስ የሰው ልጆችን ውድቀት በሚከተሉት ደረጃ ዎች ይዘረዝራል። ሀ. ሰዎች ሁሉ ስለ እግዚአብሔር የተወሰነ እውቀት አላቸው (ሮሜ 1፡19-20)። ንጉሥ ሰሎሞን ይህን መንፈሳዊ እውቀት «በሰው ልብ ውስጥ ያለ ዘላለማዊነት» ሲል ገልጾታል (መክ 3፡11 አንብብ)። ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ላያውቁ ቢችሉም፥ ከእግዚአብሔር ፍጥረት አንዳንድ ባሕርያቱንና የመፍጠር ኃይሉን ሊገነዘቡ ይችላሉ (መዝ. 19፡ አንብብ።) ለድነት (ለደኅንነት) የሚያበቃ እውቀት ላይኖራቸው ቢችልም፥ ፈጣሪ አምላክ እንዳለ፥ እነርሱም የእርሱ ፍጡራን ስለሆኑ ሊያመልኩትና ሊታዘዙት እንደሚገባ ያውቃሉ። ለ. ሰዎች ለእግዚአብሔር ለመታዘዝና እርሱን ለማስከበር አይፈልጉም (ሮሜ 1፡21)። በታሪክ ሁሉ በየትኛውም ነገድ ውስጥ የሚገኙ ሰዎች የፍጥረትን ምስክርነት ላለመቀበል ይመርጣሉ። ፈጣሪያቸውን ለማክበርና ደስ የሚሰኙበት መልካም ስጦታ ሁሉ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደሚመጣ ተገንዝበው ምስጋና ሊያቀርቡለት ባለመፈለጋቸው በእግዚአብሔር ላይ ያምፃሉ። (ጳውሎስ እግዚአብሔር ለሰጠን ነገር ሁሉ አመስጋኞች እንድንሆን ምን ያህል በአጽንኦት እንደሚገፋፋን አጢን።) ሐ. ማንነቱን ቢገልጥላቸውም ሰዎች እውነተኛውን አምላክ ለማምለክ አይፈልጉም። ይህም ወደ መንፈሳዊ ዕውርነትና የተሳሳተ አስተሳሰብ ይመራል (ሮሜ 1፡22-23፥ 25)። ይህ ዓመፅ እግዚአብሔርን ለማምለክ ጉልበት እንዳይኖራቸው ያደርጋል። ሰዎች እውነተኛውን አምላክ ለመቀበልና ለማምለክ ስለማይፈልጉ፥ አእምሯቸው ጨልሞ የሞኝነት ውሳኔዎችን ያደርጋሉ። ከሁሉም በላይ ሞኝነት የነገሠበት ውሳኔያቸው ደግሞ የራሳቸውን ሃይማኖት ለመፍጠር መፈለጋቸው ነው። በጳውሎስ ዘመን፥ ይህ ውሳኔ ሰዎችን ወደ ጣዖት አምልኮ መርቷቸዋል። ከእንጨት ወይም ከብረት የቀረጹአቸው ምስሎች አማልክት ሆነው እንደሚያድኗቸው በሞኝነት ያምኑ ነበር። በእኛ ዘመን ደግሞ ይህ የሞኝነት ውሳኔ የሚገለጸው የሐሰት ሃይማኖቶችን በመከተል ነው። ሰዎች ሁሉ በተፈጥሯቸው ሃይማኖተኞች ናቸው። አብዛኞቹ በግልጽ የተብራራ የአምልኮ ሥርዓት ሲኖራቸው፥ ይህም በጥሩ ሁኔታ ላይ እንገኛለን ብለው እንዲያስቡ አድርጓቸዋል። የእግዚአብሔርን ሕልውና የሚክዱ (athiests) ወይም የአዲሱ ትውልድ (New Age) ተከታዮች እንኳ የሕይወታቸው አምላክ እንደሆኑ በማሰብ ራሳቸውን በማምለክ ላይ ይገኛሉ። ነገር ግን እነዚህ ሃይማኖቶች ድነት (ደኅንነት)ን ስለማያስገኙ እግዚአብሔር ይህን ሁሉ ሞኝነት ብሎ ይጠራዋል። መ. ትክክለኛ ያልሆነ አምልኮ ወደ ተሳሳተ አኗኗር ይመራል። ይህም ሰዎች በእግዚአብሔር አምሳል እንደተፈጠሩ ሰብአዊ ፍጡራን ሳይሆን እንደ እንስሳት የሚኖሩበት ዓይነት ሕይወት ይሆናል። ሰዎች ለእውነተኛው አምላክ ለመገዛት በማይፈልጉበት ጊዜ፥ እግዚአብሔር የልባቸውን ፍላጎት እንዲከተሉ በማድረግ ይፈርድባቸዋል። ይህም ተጨማሪ ፍርድን ያስከትልባቸዋል። ጳውሎስ እግዚአብሔር «አሳልፎ ሰጣቸው» እያለ ሦስት ጊዜ ደጋግሞ የጠቀሰውን አስተውል (ሮሜ 1፡24፥ 26፥ 28)። የመጀመሪያው የእግዚአብሔር ፍርድ የሰዎች ሥነ ምግባር እንዲላሽቅና እግዚአብሔር የሰጣቸውን ስጦታ ከአግባብ ውጭ እንዲጠቀሙ አድርጓቸዋል። ይህም አንድ ወንድ ከሚስቱ ጋር፥ አንዲት ሴት ደግሞ ከባሏ ጋር ልታደርግ የሚገባትን ወሲባዊ ግንኙነት በመቃወሙ ነው። በጥንት ዘመን የጣዖት አምልኮ፥ አምላኪዎች በቤተ መቅደስ ከሚገኙ ሴተኛ አዳሪዎች ጋር ከሚፈጽሙት ግብረ ሥጋ ግንኙነት ጋር የተያያዘ ነበር። ነገር ግን ይህ ወሲባዊ ምግባረ ብልሹነት በምድር ላይ በሁሉ ማኅበረሰብ ውስጥ የሚገኝ ሲሆን፥ ይህም የእግዚአብሔር ፍርድ ምን ያህል እንደ ተስፋፋ ያሳያል። ሠ. ባለማቋረጥ የእግዚአብሔርን ሕግጋት አለመታዘዝ ከተፈጥሯዊ ውጭ ወደሆኑት ተግባራት ይመራል። እንስሳት እግዚአብሔር በወንድና ሴት መካከል እንዲፈጸም የወሰነውን ተፈጥሯዊ የግብረ ሥጋ ግንኙነት ሕግጋት ሲያውቁ፥ ሰዎች ግን ከተፈጥሯዊ ደንብ ውጭ ወጥተው የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት ያደርጋሉ። በዓለም ዙሪያ ተቀባይነቱ እያደገ የመጣው ግብረሰዶማዊነት የሰዎችን የማስተዋል ዕድገት የሚያመለክት ሳይሆን ፈጽሞ ከእግዚአብሔር የመለየታቸው ምልክት ነው። ጳውሎስ ከእግዚአብሔር መለየት ቅጣትን እንደሚያስከትል አስረድቷል (ሮሜ 1፡27)። ዛሬ እግዚአብሔር ስለ ወሲባዊ ንጽሕና የሰጠውን ሕግ በማይከተሉ ሰዎች ላይ ፍርድ ማምጣቱን ከምንመለከትባቸው መንገዶች አንዱ የኤድስ ወረርሽኝ ነው። በምዕራቡ ዓለም በኤድስ ወረርሽኝ ከተጠቁት ሰዎች አብዛኛዎቹ ግብረሰዶማውያን ናቸው። በአፍሪካና እስያ ኤድስ እየተስፋፋ ያለው ሰዎች ብዙ ወሲባዊ ግንኙነቶችን ስለሚያደርጉ ነው። ሰዎች የእግዚአብሔርን ሕግ ጠብቀው ከትዳራቸው ውጭ ወሲብ ባይፈጽሙ የኤድስ በሽታ ይጠፋ ነበር። በኢትዮጵያ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች የኤድስን በሽታ የሚያስከትለው ቫይረስ አለባቸው። እግዚአብሔርን ለመታዘዝ ባለመፈለጋቸው ምክንያት በቤተ ክርስቲያንም ሆነ ከቤተ ክርስቲያን ውጭ በሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት ብዙ ሰዎች ይሞታሉ። ይህ በጳውሎስ የተነገረው የእግዚአብሔር ቃል በዘመናችን ከሚፈጸምባቸው መንገዶች አንዱ ነው። ሌሎች ብዙ በሽታዎችም ተገቢ ባልሆኑ ወሲባዊ ግንኙነቶች አማካኝነት ይተላለፋሉ። የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ጳውሎስ ከእግዚአብሔር ጋር የሚደረግ ትክክለኛ ያልሆነ ግንኙነት ወደ ተሳሳተ ወሲባዊ ባሕርይ እንደሚመራ አመልክቷል። ይህን በኢትዮጵያ ውስጥ በማያምኑ ሰዎች መካከል ያየህበትን ሁኔታ ግለጽ። ለ) ብዙ ሰዎች ከሌሎች ሰዎች ጋር ወሲብ መፈጸም ተገቢ ነው ብለው የሚያስቡት ለምንድን ነው? ሐ) እግዚአብሔር ሰዎች ንጹሕ ወሲባዊ ሕይወት እንዲከተሉ የሰጠውን ሕግ በሚመለከትና ከብዙ ሰዎች ጋር ዝሙት ማድረግ ስለሚያስከትለው ውጤት ጥቂት ሰባኪያን ብቻ ግልጽ ትምህርት የሚሰጡት ለምንድን ነው? መ) ስለ ኤድስ አመጣጥና እንዴት ሊወገድ እንደሚችል ለወጣቶችና ለማኅበረሰቡ ለማስተማር ቤተ ክርስቲያንህ ምን ዓይነት አስተዋጽኦ ልታበረክት ትችላለች? ረ. ለእግዚአብሔር በቀጣይነት አለመታዘዝ በሰብአዊ ግንኙነቶች ሁሉ ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል (ሮሜ 1፡28-32)። እግዚአብሔር የሚያምፁ ሰዎችን ሲቀጣ ለበለጠ ውርደት አሳልፎ የሚሰጣቸው እንደሆነ ለሦስተኛ ጊዜ ማንበባችን ነው። ሰዎች የተበላሹት በወሲባዊ ገጽታዎች ብቻ ሳይሆን በሁሉም የሕይወት ክፍሎቻቸው ነው። ጳውሎስ በዚህ ስፍራ ሁለት ዓይነት ኃጢአቶችን ዘርዝሯል። እነዚህም «ትልቅ» ናቸው ብለን የምናስባቸውና «ትንሽ» ናቸው የምንላቸው ኃጢአቶች ናቸው። ጳውሎስ የሰዎች አእምሮ በኃጢአት ስለተበላሸ፥ የክፋት ተግባራቸው ገደብ እንዳጣ አመልክቷል። በሂትለር የተፈጸመው ዓይነት የሕዝብ ጭፍጨፋዎች ተካሂደዋል። በሩዋንዳ ክርስቲያኖች ነን የሚሉ ሰዎች የሌላውን ነገድ አባላት ፈጅተዋል። በዓለም ሁሉ ላይ የሚካሄዱት ጦርነቶች በሰዎች ልብ ውስጥ ስግብግብነት፥ አድመኝነት፥ ውድቀት፥ ኃጢአትና ክፋት እንዳለ ያሳያሉ። በተጨማሪም፥ ጳውሎስ በጣም አሳሳቢ አይደሉም የምንላቸውን አንዳንድ ኃጢአቶችም ይዘረዝራል። በዝርዝሩም ውስጥ እንደ ማታለል፥ መዋሸት፡ ማጭበርበር ሲኖሩ፥ ሐሜት፥ ስድብ፥ ትዕቢትና ለወላጆች አለመታዘዝ እንደ ሌላ ኃጢአቶች ተዘርዝረዋል። ጳውሎስ በእያንዳንዱ ሰው ልብ ውስጥ ያለውን ጥልቅ ጨለማና ኃጢአት ለመግለጥ ይፈልጋል። ከመካከላችን ያልዋሸ፥ ያላማ፥ በትምህርቱ ወይም በቤተሰቡ ወይም በጎሳው፥ ወዘተ… ያልተኩራራ ማን ነው? አንድን ሰው ስላልገደልን ወይም የወሲብ ኃጢአት ስላልፈጸምን

አሕዛብ ኃጢአትን ሠርተዋል (ሮሜ 1፡18-32) Read More »

ጳውሎስ ለሮሜ ክርስቲያኖች ያቀረበው ሰላምታና የመልእክቱ ዓላማ (ሮሜ 1፡1-17)

፩. ጳውሎስ ለሮሜ ክርስቲያኖች ያቀረበው ሰላምታ (ሮሜ 1፡1-7) ምንም እንኳ የሮሜ መልእክት ከደብዳቤነቱ ይልቅ ወደ ትምህርታዊ ሐተታነቱ የሚያደላ በመሆኑ ለየት ያለ ቢሆንም፥ ጳውሎስ በመግቢያው ጥንታዊ የደብዳቤ አጻጻፍን ይከተላል። ሁሉም የጳውሎስ መልእክቶች መግቢያ ቢኖራቸውም፥ የሮሜ መልእክት መግቢያ ረዘም ያለና ከሌሎቹ ሁሉ ያነሰ ግላዊ ጉዳዮች ያሉበት ነው። የጥንት ሰዎች መጀመሪያ የሚያነሡት ጥያቄ፥ «የዚህ መልእክት ጸሐፊ ማን ነው?» የሚል ነበር። በተለይም ጸሐፊውን ወይም መልእክቱን ያመጣውን ሰው ካላወቁት ይህንኑ ጥያቄ አጥብቀው ያነሣሉ። ስለሆነም ጳውሎስ ራሱን በማስተዋወቅና ወንጌሉን ለመጻፍ ሥልጣን ያገኘበትን መሠረት በመግለጽ የሮሜን መልእክት ይጀምራል። ራሱን በአሕዛብ ስሙ ጳውሎስ ብሎ ካስተዋወቀ በኋላ ማንነቱን ለመግለጽ ሦስት ዐበይት ሃሳቦችን ያስቀምጣል። የክርስቶስ አገልጋይ ነበር። ጳውሎስ አብዛኞቹ ባሪያዎች ከሆኑት የሮሜ ክርስቲያኖች ጋር ራሱን እያመሳሰለ ነበር። እርሱም ለጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በመታዘዝ የኖረ ባሪያ ነበር። የሕይወት ዓላማው ኢየሱስ ክርስቶስን ማገልገል ነበር። ሐዋርያው ለመሆን ተጠርቷል። እግዚአብሔር ጳውሎስ ከ12ቱ ሐዋርያት እኩል ሥልጣን እንዲኖረው አድርጎ ጠርቶታል። ስለሆነም፥ መልእክቱ ሥልጣን ያለውና ሊደመጥ የሚገባው ነበር። የጳውሎስን መልእክት አለማመን ማለት የክርስቶስን መልእክት እንደ አለማመን ማለት ነበር። የጳውሎስ ልዩ ዓላማና በእግዚአብሔር የተጠራበት ምክንያት የእግዚአብሔርን ወንጌል እንዲሰብክ ነበር። በሚቀጥሉት ዝርዝሮች ውስጥ ጳውሎስ በቀሪዎቹ የመጽሐፍ ገጾች ስለሚጽፈው ወንጌል ያብራራል። ሀ) ወንጌሉ ከእግዚአብሔር የመጣ እንጂ ሰዎች የፈጠሩት አይደለም። ስለሆነም፥ የጳውሎስ ትምህርት እግዚአብሔርን ለማስደሰት የሚደረግ ሌላው ጥረት ወይም ሃይማኖት አልነበረም። ይህ እግዚአብሔር ለሰዎች ሁሉ የገለጠው መልካም የምሥራች ነበር። ለ) ወንጌሉ በብሉይ ኪዳን የተተነበየ እንጂ አዲስ ክስተት አይደለም። ሐ) የወንጌሉ እውነት በክርስቶስ ላይ ያማክላል። የብሉይ ኪዳን ትንቢቶች ፍጻሜ የሆነው ክርስቶስ መሢሑ የዳዊት ልጅ ነው። ነገር ግን በትንሣኤው እንደተረጋገጠው፥ እርሱ ቅዱሱ የእግዚአብሔር ልጅም ነው። ክርስቶስ ለሰዎች ሁሉ እግዚአብሔር ድነትን (ደኅንነትን) ያመጣበት መንገድ ነው። ስለሆነም፥ ክርስቶስ “ስለ ስሙ” ክብርን ይቀበላል። ጳውሎስ በክርስቶስ በማመን የሚገኘውን ድነት (ደኅንነት) ለአሕዛብ የመስበክ ሥልጣን ተሰጥቶታል። ይህም ድነት (ደኅንነት) ለእርሱ በመታዘዝ ይረጋገጣል። ጳውሎስ የጥንቱን ዘመን የደብዳቤ አጻጻፍ ስልት በመከተል መልእክቱን ለማን እንደጻፈ ይገልጻል። መልእክቱን የጻፈው በሮሜ ላሉት ሁሉ ነበር። ጳውሎስ መልእክቱን የጻፈው በሮሜ ለሚኖሩ ሰዎች ሁሉ ሳይሆን በአነስተኛ የቤት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለሚሰባሰቡ ክርስቲያኖች መሆኑ ግልጽ ነው። ሁሉም የድነት ምንጭ የሆነው እግዚአብሔር ወደ ክርስቶስ ኅብረት የጠራቸው ሰዎች ነበሩ። ሁሉም በእግዚአብሔር የተወደዱና ድነትን አግኝተው ወደ ቤተሰቡ የተቀላቀሉ ነበሩ። የተጠሩትም «ቅዱሳን ለመሆን» እና ለእግዚአብሔር የተቀደሰ የታዛዥነት ሕይወት ለመኖር ነበር። የውይይት ጥያቄ፡– በዚህ የሮሜ መልእክት መግቢያ ውስጥ ስለ ወንጌሉ የተገለጹ ምን ዐበይት እውነቶችን ታያለህ? ጳውሎስ ከመጀመሪያው ጀምሮ ስለ ድነታችን አያሌ ነገሮችን በአጽንኦት ይጠቅሳል። ጳውሎስ ድነት ከእግዚአብሔር ፍቅርና ጥሪ እንደሚመነጭ ያስተምራል። የወንጌሉ እምብርት መልካም ተግባር ለማከናወን መጣር ወይም ሕይወታችንን መለወጥ አይደለም። ነገር ግን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚናገር ነው። ድነት ከእግዚአብሔር ፍርድ ማምለጥ ብቻ አይደለም። ነገር ግን የዳንበት ዓላማ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ሕይወት ለመኖር ነው። ፪. ጳውሎስ ይህን መልእክት የጻፈበት ዓላማ (ሮሜ 1፡8-17)፡- ጳውሎስ ብዙዎቹ የሮሜ ክርስቲያኖች ከእርሱ ጋር ባይተዋወቁም ለረዥም ጊዜ በአእምሮው ውስጥ እንደኖሩ ገልጾአል። ጳውሎስ ስለ እምነታቸው በሰማ ጊዜ በክርስቶስ ላይ ባላቸው እምነት የሚታወቁ ሰዎች በመሆናቸው ደስ ተሰኝቷል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ባለማቋረጥ ለእነዚህ ሰዎች በመጸለይ በግሉ እንደ ወደዳቸው አረጋግጧል። ነገር ግን ለእነርሱ የነበረው በጎ ስሜት ከመጸለይ ያለፈ ነበር። ከረዥም ጊዜ በፊት ሄዶ ሊጎበኛቸው ፈልጎ ነበር። ነገር ግን ሊሄድ ባቀደ ጊዜ ሁሉ መሰናክሎች ይገጥሙት ጀመር። በዚህ ጊዜ ግን ጳውሎስ ወደ ሮም ሄዶ እንደሚያያቸው እርግጠኛ ሆኗል። ወደ ሮም የሚሄደው ለምን ነበር? በመጀመሪያ፥ ጳውሎስ ለሮሜ ክርስቲያኖች መንፈሳዊ አገልግሎት በመስጠት በእምነታቸው እንዲያድጉ ለማገዝ በመፈለግ ነበር። ጳውሎስ «መንፈሳዊ ስጦታዎች» ሲል በ1ኛ ቆሮንቶስ 12 የጠቀሳቸውን ዓይነት የጸጋ ስጦታዎች ማለቱ አይመስልም። ነገር ግን ይህ መንፈሳዊ እውነቶችን ለምእመናን ማስተላለፍን የሚያመለክት ይመስላል። ጳውሎስ በዚህ ክፍል ስለ ማስተማር፥ ማበረታታትና በእምነታቸው እንዲያድጉ ማገዝን ያሳያል። ሁለተኛ፥ ጳውሎስ በሮም ከእነርሱ ጋር «መከር» ለመሰብሰብ ይፈልግ ነበር። ይህም በአብዛኛው አሕዛብ ከሆኑት የሮም ክርስቲያኖች ጋር በመሥራት ወንጌሉን በሮም ለማካፈልና ሰዎች ሲያምኑ ለማየት እንደሚፈልግ ያሳያል። በኋላ ጳውሎስ ወደ ሮም ለመሄድ የፈለገበትን ሌላ ምክንያት ይገልጻል። ይህም ወደ ስፔይን ወንጌሉን ይዞ እንዲሄድ የሮሜ ክርስቲያኖች እንዲረዱት ነበር (ሮሜ 15፡23-33)። ጳውሎስ በሮም ወንጌሉን ለማካፈል አጥብቆ የፈለገው ለምን ነበር? «ግዴታ» ነበረበት። እግዚአብሔር ለሰዎች ሁሉ ወንጌል እንዲሰብክ አዞታል። ጳውሎስ ለአሕዛብ ወንጌልን ካልሰበከ እግዚአብሔር በኃላፊነት እንደሚጠይቀው ያውቅ ነበር። ወንጌሉን ያልመሰከረላቸው ሰዎች የደም ዕዳ ይኖርበታል። የሮሜን መልእክት ከጻፈ ከአያሌ ወራት በኋላ ለኤፌሶን ሽማግሌዎች ከሰዎች ሁሉ ደም ንጹሕ መሆኑን የተናገረው ለዚህ ነበር (የሐዋ. 20፡26)። በብዙ አገሮች መድኃኒት እያለው ለመርዳት የማይፈልግ ሐኪም ለበሽተኛው ሕይወት ተጠያቂ ይሆናል። ጳውሎስም ለሰው ልጆች ችግር መፍትሔ የሚሰጥ መድኃኒት (ወንጌል) እንዳለውና ይህንኑ መድኃኒት ካላሰራጨ እግዚአብሔር እንደሚፈርድበት ያውቅ ነበር። ወንጌሉ የሚያስፈልገው ለማን ነው? ጳውሎስ ወንጌሉ ለሰዎች ሁሉ እንደሚያስፈልግ ገልጾአል። «ግሪኮች» የሚባሉት በግሪክ ቋንቋ አፋቸውን የፈቱ ሰዎች ነበሩ። «ግሪክ ያልሆኑት» ደግሞ በግሪክ ቋንቋ አፋቸውን ያልፈቱ የተቀሩት የዓለም ሕዝቦች ሁሉ ነበሩ። «ጠቢባን» የሚባሉት የተማሩ ሰዎች ሲሆኑ፥ «ሞኞች» የሚባሉት ደግሞ ያልተማሩት ነበሩ። እግዚአብሔር ስብከቱን እንደሚያከብርለት ጳውሎስ እንዴት እርግጠኛ ሆነ? ሌሎች ሰዎች እያፌዙበት ምስክርነቱን ይፋ እንዲያደርግ ያገዘው ነገር ምን ነበር? ምክንያቱም የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል የእግዚአብሔር ኃይል ስላለው ነው። ወንጌል ለሰው ልጅ ችግር ብቸኛው መፍትሔ ነው። ትምህርት፥ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፥ ገንዘብ፥ ልማት የሰውን ልጅ ጥልቅ ፍላጎቶች ሊያሟሉ አይችሉም። የሰው ልጅ ለሚጋፈጣቸው ችግሮች ሁሉ መልስና ቁልፍ መፍትሔ ያለው ወንጌል ነው። ታሪካዊ የእግዚአብሔር ሕዝብ የሆኑት አይሁዶችና አይሁዳውያን ያልሆኑት አሕዛብ ሁሉ ይህ ወንጌል ያስፈልጋቸዋል። በአጭሩ፥ ወንጌል ምንድን ነው? ጳውሎስ በሮሜ 1፡7 «ከእግዚአብሔር የሆነ ጽድቅ» በማለት ጠቅለል ባለ መልኩ ይገልጸዋል። ሁለት ዓይነት ጽድቆች አሉ። እነዚህም በሰው ሥራዎችና ሃይማኖቶች የሚገኝ የሰው ጽድቅና በኢየሱስ ክርስቶስ የሚገኝ የእግዚአብሔር ጽድቅ ናቸው። የሰው ጽድቅ ድነትን (ደኅንነትን) አያመጣም። በእግዚአብሔር ፊት ኃጢአተኛውን ወንጀለኛ የማያደርገውና ተቀባይነትን እንዲያገኝ የሚያደርገው የእግዚአብሔር ጽድቅ ብቻ ነው። ሰው የእግዚአብሔርን ጽድቅ ወይም ደኅንነት ሊያገኝ የሚችለው እንዴት ነው? በእምነት ብቻ ነው። ይህም መንፈሳዊ እጁን ወደ እግዚአብሔር ዘርግቶ ነፃ የጽድቅ ስጦታ ሲቀበል ነው። የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) እያንዳንዳችን በአካባቢያችን ለሚገኙ ከድነት (ከደኅንነት) ለራቁ ሰዎች እንድንመሰክር ተጠርተናል። (የሐዋ. 1፡8 አንብብ።) ጳውሎስ ስለ ወንጌል ምስክርነት ካሳየው ሁኔታ አንጻር ስናይ እያንዳንዳችን ስላለብን ግዴታ ምን እንማራለን? ለ) በቤተ ክርስቲያንህ የሚገኙት አብዛኞቹ ክርስቲያኖች ይህንን ግዴታ የሚፈጽሙ ይመስልሃል? መልስህን አብራራ። ሐ) እግዚአብሔር ይህንን ግዴታ እየፈጸምህ መሆንህን ወይም አለመሆንህን እንዲያሳይህና በዚህ ሳምንት የምትመሰክርለት ሰው እንዲጠቁምህ በጸሎት ጠይቅ። ስማቸውን በወረቀት ላይ ጽፈህ እየጸለይህ በዚህ ሳምንት ውስጥ እንዴት እንደምትመሰክርላቸው ዕቅድ አውጣ። (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ጳውሎስ ለሮሜ ክርስቲያኖች ያቀረበው ሰላምታና የመልእክቱ ዓላማ (ሮሜ 1፡1-17) Read More »

የሮሜ መልእክት መዋቅርና እና አስተዋጽኦ

፩. የሮሜ መልእክት መዋቅር የውይይት ጥያቄ፡– ይህን የሮሜ መልእክት እቀራረፅ በጥንቃቄ ካጠናህ፥ በሮሜ ውስጥ የጳውሎስን ትምህርት ፍሰት በሚገባ ልትገነዘብ ትችላለህ። ከዚህ በታች የቀረቡት ሰባት ነጥቦች ወንጌል ለሚያካትታቸው ነገሮች መልካም ማጠቃለያ የሚሆኑት እንዴት ነው? ጳውሎስ ስለ ወንጌልና እግዚአብሔር ሰዎችን ስለሚያጸድቅበት ሁኔታ የጻፈውን አሳብ ጠቅለል ባለ መልክ (ርዕሰ-ጉዳይ) ማስቀመጡ የሮሜን መልእክት ለመረዳት ይረዳናል። ከሮሜ ውስጥ አንድ ክፍል ሳይገባህ ቢቀር በዚያ ክፍል የተጠቀሰው ዋና ርእሰ ጉዳይ ምን እንደሆነ መለስ ብለህ ብትከልስ መልካም ነው። ብዙውን ጊዜ ጳውሎስ ለማስተላለፍ የሚፈልገውን አሳብ በዚህ ዓይነት መረዳት ይቻላል። ከዚህ በታች የቀረበው ጳውሎስ ስለ እግዚአብሔር የድነት (ደኅንነት) መንገድ ያቀረበው መልእክት ማጠቃለያ ነው። የመጀመሪያው ነጥብ፡– ጳውሎስ በመግቢያው ውስጥ እግዚአብሔር እንዲሰብክ ያዘዘው ወንጌል ለአሕዛብም ሆነ ለአይሁድ ብቸኛው የድነት (ደኅንነት) መንገድ እንደሆነ ገልጾአል (ሮሜ 1፡1-17)። ኃጢአተኞች እንዴት ሊድኑና የእግዚአብሔርን ጽድቅ ሊያገኙ እንደሚችሉ የሚያስረዳው የሮሜ መልእክት ጭብጥ በ1፡16-17 ውስጥ ተጠቅሷል። ሁለተኛ ነጥብ፡– ብሉይ ኪዳንን የሚከተሉ አይሁዶችም ሆኑ ይህንኑ ዕድል ያላገኙ አሕዛብ በእግዚአብሔር ፊት ኃጢአተኞች ናቸው። ስለሆነም፥ ሁለቱም እግዚአብሔር የሚሰጣቸውን ድነት (ደኅንነት) በእኩል ደረጃ መቀበል ይኖርባቸዋል (ሮሜ 1፡18–3፡20)። ሦስተኛ ነጥብ፡– ሰዎች ለኃጢአተኝነታቸው ከሚቀበሉት ቅጣት ሊያመልጡ የሚችሉበት ብቸኛው መንገድ ድነት (ደኅንነት) ወይም በጳውሎስ አገላለጽ «ጽድቅ» (በእግዚአብሔር ጥፋተኛ አይደለህም መባል) ነው። ስዎች የተወሰኑ ሕግጋትን በመጠበቅ ሳይሆን እግዚአብሔር በሰጠው የክርስቶስ አዳኝነት ላይ እምነታቸውን በሚያሳርፉበት ጊዜ ድነት (ደኅንነት) ያገኛሉ። በዚህም ጊዜ ከእግዚአብሔር ጋር ይታረቃሉ። ከዚህ በኋላ የወደፊት ተስፋ፥ ሰላም፥ ደስታና መንፈስ ቅዱስ ሕይወታቸውን ይሞላዋል (ሮሜ 3፡21-5፡21)። አራተኛው ነጥብ፡– ከድነት (ደኅንነት) ዐበይት ፍሬዎች አንዱ የተቀደሰ ሕይወት ነው። በክርስቶስ በምናምንበት ጊዜ የኃጢአት ተፈጥሯችን ተወግዶ እግዚአብሔርን ለመታዘዝና ለእርሱ ለመኖር ነፃ እንሆናለን። የተቀደሰ ሕይወት የምንኖረው ድነትን (ደኅንነትን) ለማግኘት ሳይሆን፥ ስለዳንንና ከኃጢአት እስራት ስለተፈታን እግዚአብሔርን ለማስደሰት ስለምንፈልግ ነው (ሮሜ 6-8)። አምስተኛ ነጥብ፡– አይሁዶችንም ሆነ አሕዛብን የሚያድነው የክርስቶስ ወንጌል እግዚአብሔር በብሉይ ኪዳን ለአይሁዶች የሰጠውን የተስፋ ቃል አያጥፍም። ምንም እንኳ አሕዛብ በክርስቶስ በማመን በብሉይ ኪዳን ለአይሁዶች የተሰጠውን የተስፋ ቃል ቢቀበሉም፥ አይሁዶች እንደ ሕዝብ ወንጌሉን ተቀብለው በእግዚአብሔር በረከቶች ደስ የሚሰኙበት ዘመን ይመጣል (ሮሜ 9-11)። ስድስተኛ ነጥብ፡– ከዳንን ሕይወታችን ይለወጣል። ድነት (ደኅንነት) የሕይወታችንን ገጽታዎች ሁሉ ይዳስሳል። ከመንግሥት፥ ከእኛ የተለየ እምነትና ልምምድ ካላቸው ሌሎች ክርስቲያኖች፥ ወዘተ… ጋር የምናደርገውን ግንኙነት በሙሉ ያካትታል (ሮሜ 12፡14)። ሰባተኛ ነጥብ፡– ጳውሎስ በማጠቃለያው የእርሱ ጥሪ ወንጌሉን ላልሰሙ ሰዎች ይህንኑ መልካም ዜና ማብሰር እንደሆነ ይገልጻል። ጳውሎስ ወደ ኢየሩሳሌም ሄዶ ሲመለስ ወደ ሮም፥ ከዚያም ወደ ስፔይን የመሄድ ዕቅድ እንዳለው ተናግሯል። የሮም ክርስቲያኖች ወንጌሉን ወዳልደረሰበት ስፍራ ለመውሰድ በሚያደርገው ጥረት እንዲተባበሩት ይጠይቃል። ጳውሎስ ለሚያውቃቸው የቤተ ክርስቲያን ሰዎች ሰላምታ በማቅረብ መልእክቱን ይደመድማል (ሮሜ 15-16)። ፪. የሮሜ መልእክት አስተዋጽኦ መግቢያ (ሮሜ 1፡1-17) ሰዎች ሁሉ በቅዱሱ አምላክ ፊት ኃጢአትን ስላደረጉ ወንጌል የግድ ያስፈልጋቸዋል (ሮሜ 1፡18፤ 3፡20)። ሀ. አሕዛብ ኃጢአትን ሠርተዋል (ሮሜ 1፡18-32)። ለ. አይሁዶች ኃጢአትን ሠርተዋል (ሮሜ 2፡1-3፡8)። ሐ. ማጠቃለያ፡- ሁሉም ሰው በእግዚአብሔር ፊት ኃጢአትን ስላደረገ ድነት (ደኅንነት) የግድ ያስፈልገዋል (ሮሜ 3፡9-20)። ወንጌሉ በክርስቶስ የሚያምኑ ሰዎች በእግዚአብሔር እንደ ጸደቁ ያስተምራል (ሮሜ 3፡21-5፡21)። ሀ. የድነት (ደኅንነት) መሠረት፡- የክርስቶስ ስለ እኛ መሞት ነው (ሮሜ 3፡21-26)። ለ. የእግዚአብሔርን የድነት (ደኅንነት) ስጦታ የምንቀበለው በሥራ ሳይሆን ክርስቶስ በእኛ ምትክ እንደሞተ በማመን ነው (ሮሜ 3፡27-31)። ሐ. የእኛ ሥራ ሳይሆን እምነት እንዴት እንደሚያድነን የሚያሳዩ የብሉይ ኪዳን ማስረጃ ዎች (ሮሜ 4)። መ. ኃጢአተኛው በእግዚአብሔር ከጸደቀ በኋላ የሚያገኛቸው በረከቶች (ሮሜ 5፡1-11)። ሠ. ኃጢአትንና ሞትን ወደ ዓለም ያመጣው የመጀመሪያው አዳም ሕይወትንና ጽድቅን ካመጣው ከሁለተኛው አዳም ጋር ሲነጻጸር (ሮሜ 5፡12-21)። ወንጌሉ የተቀደሰ ሕይወት እንድንኖር ይረዳናል (ሮሜ 6፡1-8፡39)። ሀ. ከኃጢአት ባሕርያችን ጋር ያለን ሕብረትና እግዚአብሔር በሕይወታችን ኃጢአትን እንድናሸንፍ እንዴት እንደሚረዳን መገንዘብ (ሮሜ 6፡1-7፡6)። ለ. ሰዎች የእግዚአብሔርን ሕግጋት ለመታዘዝ የሚያደርጉት ጥረት ወደ ውድቀት ሲመራቸው፥ እኛ ግን በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት እግዚአብሔርን መታዘዝና የተቀደሰ ሕይወት መምራት ችለናል (ሮሜ 7፡7-8፡39)። ወንጌሉ፥ አሕዛብና አይሁዶች (ሮሜ 9፡11)። ሀ. አይሁዶች ላለማመን የተጋለጡት የእግዚአብሔርን ጽድቅ ከመቀበል ይልቅ በራሳቸው ጥረት ለመጽደቅ ስለሞከሩ ነው (ሮሜ 9-10)። ለ. ምንም እንኳ ሁልጊዜም ለድነት (ደኅንነት) በክርስቶስ የሚያምኑ ቅሬታዎች የሚኖሩ ቢሆንም፥ አይሁዶች ሁሉ የሚድኑበት ቀን ይመጣል (ሮሜ 11)። ወንጌሉ አማኞች ለእግዚአብሔር የሚኖሩትን ኑሮ ይወስናል (ሮሜ 12፡1-15፡13)። ሀ. አማኞች ሕይወታቸውን ሙሉ ለሙሉ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አድርገው ያቀርባሉ (ሮሜ 12፡1-2)። ለ. አማኞች እግዚአብሔር በሰጣቸው ጸጋዎች አማካኝነት ቤተ ክርስቲያንን ያገለግላሉ (ሮሜ 12፡3-8)። ሐ. አማኞች ከሌሎች የቤተ ክርስቲያናቱ አባላት ጋር በፍቅር ይዛመዳሉ (ሮሜ 12፡14-21)። መ. አማኞች ከክርስቲያኖችም ሆነ ክርስቲያኖች ካልሆኑት ሰዎች ጋር ሰላማዊ ግንኙነት ያደርጋሉ (ሮሜ 12፡14-22)። ሠ. አማኞች ለሰብዓዊ መንግሥታቸው ይጸልያሉ፥ ይታዘዛሉም (ሮሜ 13፡1-7)። ረ. የአማኞች ሕይወት ቶሎ በሚሆነው የክርስቶስ መመለስ ብርሃን ሲታይ (ሮሜ 13፡8–13)። ሰ. ክርስቲያኖች የተለየ አመለካከት ያላቸውን ክርስቲያኖች የሚያሳዝኑ ተግባራት ባለመፈጸም ፍቅራቸውን ያሳያሉ (ሮሜ 13፡14-15፡13)። መደምደሚያ (ሮሜ 15፡14-16፡27)። (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የሮሜ መልእክት መዋቅርና እና አስተዋጽኦ Read More »

የሮሜ መልእክት ልዩ ገጽታዎች

ከቆላስይስ በስተቀር አብዛኞቹ የጳውሎስ ደብዳቤዎች በተወሰኑ ጉዳዮችና የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን አገልግሎቶች ላይ ሲያተኩሩ፥ የሮሜ መልእክት በአብዛኛው አጠቃላይ የሆኑና ነገረ መለኮታዊ ጉዳዮችንም ያነሣል። አንዳንድ ምሁራን ጳውሎስ የሮምን ቤተ ክርስቲያን ስላልጎበኘ፥ ስለ ሮም ቤተ ክርስቲያን ዝርዝር ጉዳዮች የሚያውቀው እንዳልነበረው ይገምታሉ። ስለሆነም፥ በሁሉም አብያተ ክርስቲያናት የሚገኙ ክርስቲያኖች በሚጋፈጧቸው አጠቃላይ ጉዳዮች ላይ አተኮረ። በተጨማሪም፥ አማኞች ሊያውቋቸው ስለሚገቧቸው መሠረታዊ አስተምህሮዎች አስተምሮአል። የሮሜ መልእክት ከጳውሎስ መልእክቶች ሁሉ ረዥሙ ነው። ከሌሎች ሁሉ በበለጠ ሁኔታም የተቀነባበረም ነው። ምሁራን መልእክቱ ከግል ደብዳቤነቱ ይልቅ ነገረ መለኮታዊ ሐተታው እንደሚያመዝን ይናገራሉ። ጳውሎስ ከሌሎች መልእክቶቹ በተለየ ሁኔታ የክርስትና መሠረት በሆኑት ነገረ መለኮታዊ ጉዳዮች ላይ ያተኩራል። በዚህ መልእክት ውስጥ እንደ ኃጢአት፥ ድነት (ደኅንነት)፥ ጸጋ፥ እምነት፥ ጽድቅ፥ ቅድስና፥ ቤዛነት፥ ሞትና ትንሣኤ ያሉ ዐበይት ሥነ መለኮታዊ ትምህርቶች ተብራርተዋል። ምንም እንኳን ጳውሎስ በመልእክቶቹ ውስጥ ብሉይ ኪዳንን በመጥቀስ የጻፈ ቢሆንም፥ በሮሜ መልእክት ውስጥ የተጠቀመባቸው የብሉይ ኪዳን ጥቅሶች ከሌሎች መልእክቶቹ ሁሉ በቁጥር የበረከቱ ናቸው። ትምህርቱን ለማብራራት መሠረት የጣሉለት እነዚህ የብሉይ ኪዳን ጥቅሶች ናቸው። ጳውሎስ አንድ ሰው ብሉይ ኪዳንንና እግዚአብሔር በታሪክ ውስጥ ያከናወነውን ተግባር ሊረዳ የሚችለው ስለ ክርስቶስና በእግዚአብሔር ዕቅድ ውስጥ ስላለው ድርሻ ተገቢውን ግንዛቤ ሲጨብጥ እንደሆነ ያስረዳል። ጳውሎስ በሮሜ ውስጥ ከሌሎች ደብዳቤዎቹ በበለጠ ሁኔታ ስለ እስራኤልና እግዚአብሔር ለእስራኤላውያን ስለወጠናቸው ዕቅዶች ይገልጻል። አብዛኞቹ ሌሎች ደብዳቤዎቹ በአይሁድና በአሕዛብ መካከል የነበረው ግድግዳ እንደፈረሰና የአሕዛብ ክርስቲያኖች የአብርሃምና የእግዚአብሔር ልጆች መሆናቸው ላይ ያተኩራሉ። ጳውሎስ በአሁኑ የእግዚአብሔር ዕቅድ የአሕዛብ ክርስቲያኖች የእግዚአብሔር ልጆች መሆናቸውን አጽንቶ ቢገልጽም፥ እግዚአብሔር አንድ ቀን አይሁዶችን ወደ ራሱ እንደሚመልስና እንደሚያድን ያስተምራል። (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የሮሜ መልእክት ልዩ ገጽታዎች Read More »

የሮሜ መልእክት ዓላማ

የውይይት ጥያቄ፡- ሮሜ 1፡1-17 አንብብ። «ወንጌል» የሚለው ቃል ስንት ጊዜ እንደተጠቀሰ ቁጠር። ይህ ጳውሎስን ስላሳሰበው ዋንኛ ጉዳይ ምን ይነግረናል? የሮሜን መልእክት በጥንቃቄ በምናጠናበት ጊዜ ጳውሎስ ይህን መልእክት ለመጻፍ ያነሣውት አያሌ ዓላማዎች እንደነበሩት እንረዳለን። በታሪክ ሁሉ ክርስቲያኖች፥ የሮሜ መልእክት የእግዚአብሔርን የድነት (የድኅንነት) መንገድ የሚያሳይና እግዚአብሔር ለሰው ልጅ ድነትን (ደኅንነትን) ለመስጠት በወጠነው ዕቅድ ውስጥ ክርስቶስ ምን ዓይነት ስፍራ እንዳለው የሚያመለክት የጳውሎስ ዐቢይ ነገረ መለኮታዊ መጽሐፍ እንደሆነ ሲገነዘቡ ኖረዋል። በመጽሐፉ ውስጥ ተደጋግመው ከተጠቀሱት ቃላት አንዱ «ወንጌል» ሲሆን፥ 12 ጊዜያት ያህል ተጠቅሷል። እንደ ጽድቅ፥ የእግዚአብሔር ጽድቅ፥ ድነት (ደኅንነት) ወዘተ…. ያሉ ቁልፍ ቃላት፥ ጳውሎስ ወንጌሉ በክርስቶስ ላይ እንደሚማከልና ድነት (ደኅንነት) እያንዳንዱ ሰው ከእርሱ ጋር በሚያደርገው ግንኙነት ላይ እንደሚወሰን ለማሳየት መሻቱን ያሳያሉ። ሰው ለመዳን ምን ማድረግ አለበት? በእግዚአብሔር ዓይኖች ፊት እንዴት ጻድቅ ሊሆን ይችላል? የዳኑ ሰዎች እንዴት ሊመላለሱ ይገባል? እነዚህ ጳውሎስ በመጽሐፉ ውስጥ ለማብራራት ከሚፈልጋቸው ዐበይት ሥነ መለኮታዊ ጥያቄዎች ውስጥ ጥቂቶቹ ናቸው። ጳውሎስ በጉብኝቱ ወቅት የሮሜ ቤተ ክርስቲያን ወንጌልን ወደ ስፔይን ለመውሰድ በወጠነው ዕቅድ እንድትተባበረው እያዘጋጃት ነበር። ብዙ ምሁራን ጳውሎስ የሮሜ ክርስቲያኖች በአይሁዶችና በአሕዛብ መካከል ስላለው ግንኙነት፥ ብሎም ከሮም መንግሥት ጋር ስለሚኖራቸው ግንኙነትና ስለ ሌሎችም ጉዳዮች ያነሡዋቸውን ጥያቄዎች ለመመለስ እንደ ሞከረ ያስባሉ። ጳውሎስ አይሁዶችም ሆኑ አሕዛብ በክርስቶስ በማመን ብቻ የሚድኑ መሆናቸውን በመግለጽ ጥያቄዎቻቸውን መልሷል። የክርስቶስ ወንጌል የመጣው አረማውያን ለነበሩት አሕዛብ ብቻ አልነበረም። ረዥም የብሉይ ኪዳን ትውፊት የነበራቸው አይሁዶችም በክርስቶስ ማመን ያስፈልጋቸው ነበር (ሮሜ 1-3)። ምንም እንኳ እግዚአብሔር አሕዛብ ክርስቲያኖችን ወደ ቤተሰቡ ቢያመጣም፥ ይህ እግዚአብሔር ለአይሁዶች የነበረውን ልዩ ዕቅድ አይሰርዘውም። እነዚህ በሥጋ የአብርሃም ልጆች የሆኑት አንድ ቀን ታላቅ መንፈሳዊ መነቃቃትን የሚያገኙ ናቸው (ሮሜ 9-11)። በተጨማሪም፥ ጳውሎስ ለጣዖት የተሠዋን ሥጋ እንደ መብላት ባሉት ባሕላዊ ልምምዶች የሚለያዩ አይሁዶችና አሕዛብ እንዴት ተስማምተው ሊኖሩ እንደሚችሉም አስረድቷል። በሚሲዮናዊነት አገልግሎቱ ሁሉ፥ የአይሁድ ክርስቲያኖች የጳውሎስን ትምህርት ሲቃወሙ ቆይተዋል። እነዚህ አይሁዶች፥ የአሕዛብ ክርስቲያኖች የሕግን ትምህርት በመከተል እንደ ግርዛት ያሉትን ሥርዓቶች ካልፈጸሙ በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት እንደማይኖራቸው በመግለጽ ተቃውመውታል። የገላትያ መልእክት፤ 2ኛ ቆሮንቶስ 3 እና 10-13 ይህንን ትግል ያንጸባርቃሉ። በተጨማሪም ጳውሎስ በእምነት ስለ መዳን የሚሰጠው ትምህርት ክርስቲያኖች ኃጢአት እንዲሠሩ ስለሚያበረታታ አደገኛ ነው የሚል አሳብ ለነበራቸው ሰዎች ምላሽ እየሰጠ ነበር። ስለሆነም፥ ጳውሎስ የሮሜን መልእክት ከጻፈባቸው ምክንያቶች አንዱ ስለ ድነት (ደኅንነት) የነበረውን መረዳት ግልጽ ማድረግ ነበር። ድነት (ደኅንነት) ማለት ምን ማለት እንደሆነ፥ ሰው እንዴት ሊድን እንደሚችልና ከብሉይ ኪዳን ሕግጋት ጋር ምን ዓይነት ግንኙነት እንዳለው አስረድቷል። ጳውሎስ በቅርቡ ወደ ሮም ለመሄድ ተስፋ ስላደረገ፥ እርሱ ወይም ሌላ የአይሁድ ክርስቲያን ደርሶ ክርክር ከመነሣቱ በፊት የሮም ክርስቲያኖች ስለ ድነት (ደኅንነት) በግልጽ እንዲገነዘቡ ፈለገ። አንዳንድ ምሁራን ጳውሎስ ገንዘብ ሰብስቦ ወደ ኢየሩሳሌም ሲደርስ የሚናገረውን አሳብ በሮሜ መልእክት ውስጥ እንዳሰፈረ ይናገራሉ። እነዚህ ምሁራን በአይሁድና በአሕዛብ ክርስቲያኖች መካከል የተጠናከረ ክፍፍል ሲደረግ እንደነበረ ያስባሉ። የአይሁድ ክርስቲያኖች፥ አሕዛብ የብሉይ ኪዳን ሕግጋትን መከተል አለባቸው በሚለው አቋማቸው ሲጸኑ፥ የአሕዛብ ክርስቲያኖች በቁጥር ከአይሁድ ክርስቲያኖች በመላቃቸው ይኩራሩ ነበር። ጳውሎስ ከዚህ ክፍፍል የተነሣ የአይሁድ ክርስቲያኖች ከአሕዛብ የሚመጣውን ስጦታ ላለመቀበል እንዳይወስኑ ፈርቶ ነበር (ሮሜ 15፡31)። ጳውሎስ ይህ ክፍፍል እንዳይባባስ ይፈልግ ነበር። ስለሆነም፥ አይሁዶችም ሆኑ አሕዛብ ኃጢአትን በመሥራታቸው በእኩል ደረጃ በደለኞች እንደሆኑ በማሳየት በእምነት ድነትን (ደኅንነትን) እንዲቀበሉ ያስገነዝባቸዋል። ሁለቱም የኃጢአት አመለካከቶቻቸውን አሸንፈው በፍቅርና በመቻቻል የሚከፋፍሏቸውን ጉዳዮች (ለጣዖት የተሠዋ ሥጋ መብላት፥ ወዘተ…) መቆጣጠር ያስፈልጋቸው ነበር። ጳውሎስ አንዳንዶች እንደሚሉት አይሁዶችንና የብሉይ ኪዳንን እንደማይቃወም ለማሳየት ፈልጎ ነበር (የሐዋ. 21፡20-21)። ምንም እንኳ ጳውሎስ ድነት (ደኅንነት) አይሁዳዊ በመሆን ሳይሆን በእምነት እንደሚገኝ ቢያስተምርም፥ እግዚአብሔር በታሪክም ሆነ ገና ወደፊት ለአይሁዶች የተለየ ዓላማ እንዳለው አመልክቷል። አይሁዶች የእግዚአብሔር የፍሬ ዛፍ ሲሆኑ፥ አሕዛብም እዚያው ላይ ተተክለዋል። አንድ ቀን ግን የጥንቱ ሕዝቡ የሆኑት አይሁዶች ስፍራቸውን ይይዛሉ። የውይይት ጥያቄ፡- በእነዚህ ዓላማዎች ውስጥ የታዩት እውነቶች ዛሬ ለአብያተ ክርስቲያኖቻችን የሚያስፈልጉት ለምንድን ነው? (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የሮሜ መልእክት ዓላማ Read More »