አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን
አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ምንድን ናት? ዛሬ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ምን ምን ማሟላት አለባት? በሚለው ጥያቄ ላይ ሰፊ ውይይት አለ። ቤተ ክርስቲያን ሁለት ወይም ሦስት አማኞች በኢየሱስ ስም የሚያደርጉት ስብሰባ ነው? ምን ያህል ድርጅት ያስፈልጋታል? ለቤተ ክርስቲያን አባልነት ጥምቀት አስፈላጊ ነው? የሚሉና ሌሎችም ጥያቄዎች ይነሱ ይሆናል። አዲስ ኪዳን ስለ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን የሚያስረዳው ግልጥ ማብራሪያ የሌለ መሆኑ ያሳዝናል። የጉባኤው እንቅስቃሴ እንዴት መካሄድ አለበት? ለሚለው ጥያቄ ነው መጽሐፉ መልስ የሚሰጠው። እኛም ከዚህ መንደርደሪያ አሳብ በመነሳት ስለ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ምንነት የሚከተለውን ማብራሪያ ለመስጠት ሞክረናል። በአዲስ ኪዳን እንደምናየው አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ክርስቶስን የተቀበሉ አማኞች ጉባኤ ሲሆን አባላቱም የተጠመቁና የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለማድረግ የተደራጁ መሆን አለባቸው። ማለት፡- 1. የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን አባል የሚሆነው ማመኑን የገለጠ ሰው ብቻ ነው፤ 2. አዲስ ኪዳን ያልተጠመቀ ሰው የቤተ ክርስቲያን አባል ስለመሆኑ የሚገልጠው ነገር የለም፤ 3. ቤተ ክርስቲያናት በተቻለ መጠን በፍጥነት ነበር የሚደራጁት (ሐዋ. 14፡23)። ሰለዚህ በአሁኑ ጊዜም ቢሆን ያልተደራጀ የአማኞች ኅብረት፥ ቤተ ክርስቲያን ተብሎ ሊጠራ አይችልም፤ 4. ቤተ ክርስቲያን ዓላማ አላት። ይህም በተለያየ መንገድ የሚገለጠውን የእግዚአብሔር ፈቃድ መፈጸም ይሆናል (የተለያዩ ትእዛዞችንና ሥርዓቶችን መፈጸም፥ በየትኛውም የዕድሜ ክልል፥ በየትኛውም የዓለም ክፍል ላሉ ሰዎች አገልግሎት መስጠት ወዘተ.)። ይህ የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ትርጉም በወጉ ቢገለጥም የሁለትና ሦስት ሰዎች ለኅብረት መሰብሰብ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን አያሰኘውም። ምክንያቱም ይህ ዓይነቱ ጉባኤ፥ ቢያንስ በአካባቢው ላሉና በየዕድሜው ክልል የሚገኙ ሰዎችን ለማገልገል የተዘጋጀ አይሆንም። እንዲሁም የክርስቲያን ትምህርት ቤት፥ ወይም ከቤተ ክርስቲያን ውጭ የሆነ ክርስቲያናዊ ድርጅት ቤተ ክርስቲያን ሊሆን አይችልም። እርግጥ ይህ መግለጫ የሚለዋውጥበት ሁኔታ ይኖራል። አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን የግድ ለሷ ተብሎ በተሠራ ሕንፃ ውስጥ ትሰብሰብ አይልም። ምን ዓይነት ወይም ስንት ስብስሳዎች መካሄድ እንዳለባቸው አያመለክትም። እንዲሁም ስለ ጥምቀት ዓይነትና ስለ መሪዎች አመራረጥ (ወደፊት በስፋት እናየዋለን) አይወሰንም። የመግለጫው ዋና ጥረት አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ከሌሎች ቡድኖች፥ ከዚያም አልፎ ከቤተ ክርስቲያናት ጋር ከተዛመዱ ድርጅቶች የምትለይበትን ሁኔታ ለማመልከት ነው። እነማን ናቸው የቤተክርስቲያን መሪዎች? ቤተ ክርስቲያን አመራር ይኖራት ዘንድ መለኮታዊ ትእዛዝ ነው (ዕብ. 13፡7፥ 17)። መደራጀት ሥጋዊ ድርጊት፥ ወይም ስሕተት አይደለም። ሰዎች ግን ለዚህ ጉዳይ ከመጠን ያለፈ ትኩረት ይሰጡታል። አንዳንዶች ድርጅቱ እጅግ ሳይሰፋ አነስተኛ ቢሆን ይመረጣል ይላሉ፥ በተግባር ሲታይ ግን የበቂ ድርጅት አለመኖር የታሰበውን ሥራ ያደናቅፋል። በሌላ አቅጣጫ ስናየው ደግሞ አንዳንድ ቤተ ክርስቲያናት እጅግ ከመጠናከራቸው የተነሳ የቤተ ክርስቲያኑ መሪ (እግዚአብሔር) የሚሰጠው ምክርም ሆን ውሳኔ ተቀባይነት የሚያጣበት ጊዜ ይኖራል። ያም ሆነ ይህ ቤተ ክርስቲያን መሪዎች የሚያስፈልጓት ስለመሆኑ በአዲስ ኪዳን በየደረጃው ተገልጧል። 1.ሽማግሌዎች። ያለጥርጥር ሽማግሌዎች የአዲስ ኪዳን ቤተ ክርስቲያን ዋና መሪዎች ነበሩ። ብዙዎች ባይስማሙበት እንኳን፥ ሽማግሌዎችና ጳጳሳት በቤተ ክርስቲያን እኩል ሥልጣን እንዳላቸው ይገመታል። ሽማግሌ የሚለው ቃል ሥልጣንን ሲያመለክት፥ ጳጳስ የሚለው ደግሞ ሥራ አስፈጻሚነትን፥ አጠቃላይ ተቆጣጣሪነትንና ከበላይ ሆኖ መመልከትን ይገልጣል። ቢያንስ ቢያንስ በኤፈሶን ቤተ ክርስቲያን የሽማግሌና የጳጳስ ሥራ ተመሳሳይ ነበር (ሐዋ. 20፡17፥ 28)። በመሆኑም ሽማግሌዎች ከአጠቃላይ ሥራቸው በተጨማሪ በመሪነትም አገልግለዋል (1ኛ ጢሞ. 5፡17)፤ እውነትን ጠብቀዋል፥ አስተምረዋል (ቲቶ 1፡9)፣ የገንዘብ ገቢና ወጪም ተቆጣጥረዋል (ሐዋ. 11፡30)። በእያንዳንዱ ቤተ ክርስቲያን ምን ያህል ሽማግሌዎች ነበሩ የሚለው ጥያቄ አከራካሪ ሆኗል። ምንም እንኳን በግልጥ እንደሚታየው ቤተ ክርስቲያናት በነበሩባቸው ከተሞች ብዙ ሽማግሌዎች ነበሩ (ሐዋ. 14፡23፤ ፊልጵ. 1፡1)። ነገር ግን በየመኖሪያ ቤቱ በሚካሄዱት ስብሰባዎች ላይ ብዙ ሽግሌዎች፥ ወይም አንድ ሽማግሌ ብቻ እንደነበር የታወቀ ነገር የለም። በ1ኛ ጢሞቴዎስ 3 ጳጳስ የሚለው ቃል (በነጠላ) ከቁ. 1-7 ተጠቅሷል፤ ሰለ ዲያቆናት ግን (በብዙ) ከቁ. 8-13 ተገልጧል። ሽማግሌዎች ለተለየ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት በተለየ መንገድ ይመረጡ እንደነበር ደግሞ ከሚከተለው ጥቅስ ለመረዳት እንችላለን (1ኛ ጢሞ. 4፡14፤ ቲቶ 1፡5)። የሽማግሌዎች መምረጫ ስለነበሩት መመዘኛ ነጥቦች በ1ኛ ጢሞቴዎስ 3፡1-7 እና ቲቶ 1፡5-9 ተብራርቷል። የመጀመሪያውን ጥቅስ እንደሚከተለው ዘርዝሮታል፡- የማይነቀፍ (ለወቀሳ ያልተጋለጠ) የአንዲት ሚስት ባል፥ (ይህ ማለት አንዲት ሚስት ብቻ ያገባ ማለት ሲሆን ቃሉም በግሪክ 1ኛ ጢሞቴዎስ 5፡9 ከተጠቀሰው ጋር አንድ ነው፤ ብዙ ሚስት ማግባት በግሪኮችና በሮማውያኑ ዘንድ የሚታወቅ አልነበረም፤ ወይም ከተፋቱ በኋላ የሚያገቡትንም የሚከለክል ሊሆን ይችላል)፥ ልከኛ፥ ራሱን የሚገዛ፥ እንደሚገባው የሚሠራ፥ እንግዳ ተቀባይ፥ ለማስተማር የሚበቃ፥ የማይሰክር፥ የማይጨቃጨቅ፥ የማይከራከር፥ ገንዘብ የማይወድ፥ ቤቱን በመልካም የሚያስተዳድር (የቤቱን ጥቂት ሰዎች በመልካም ሁኔታ ማስተዳደሩ፥ ቤተ ክርስቲያንን ለማስተዳደር የሚችል መሆኑን ያመለክታል)፥ አዲስ ክርስቲያን ያልሆነ (የበሰለ)፣ በኅብረተሰቡ ዘንድ መልካም ምስክርነት ያለው። በቲቶ መልእክት ውስጥ ያለው ክፍል ደግሞ በዚህ ላይ በመጨመር፥ የማይኮራ፥ የማይቆጣ በጎ የሆነውን ነገር የሚወድ (ሰዎችንም ሁኔታዎችንም)፥ ጻድቅና ቅዱስ (ንጹሕ) የሆነ የሚሉትን ያጠቃልላል። የዚህ ሁሉ ዝርዝር ገለጣ አስፈላጊነት ቤተ ክርስቲያን መመራት የሚኖርባት ብቃት ባላቸው ሰዎች መሆኑን ለማስገንዘብና መመዘኛውን ከማያሟሉ ብዙ ሰዎች ይልቅ፥ ብቃት ባላቸው ጥቂቶች መመራት እንደሚሻላት ለመጠቆም ነው። 2. ከሽማግሌዎች በታች ያሉት ደግም ዲያቆናት ነበሩ። ዲያቆን የሚለው ቃል አገልጋይ ማለት ነው። ምንም እንኳን ክርስቲያኖች በሙሉ የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ መሆን ቢችሉም፥ ዲያቆናት የታወቀ ልዩ አገልግሎት አላቸው። የሽማግሌዎች ረዳት ሲሆኑ (ሐዋ. 6፡1-6) በግልጥ የታወቀ የሥራ ድርሻም ነበራቸው (ፊልጵ. 1፡1)። የዲያቆናት ምርጫ መመዘኛ እንደ ሽማግሌዎች በጣም ዝርዝር ባይሆንም፥ አንዳንድ ተመሳሳይ መመዘኛዎችን ይጨምራል። በተለይ “በቃላቸው የሚታመኑ” (1ኛ ጢሞ. 3፡8) የሚል ቃል ታክሎበታል። ይህ የሚያስገነዝበን፣ ምናልባት ዲያቆናት ከምእመናን ጋር በየዕለቱ ፊት ለፊት የሚገናኙና ቤት ለቤት እየዞሩ እርዳታ የሚያደርጉ፥ የታመሙትን የሚጠይቁ በመሆናቸው፥ በዚህ አጋጣሚ ለአንድ ሰው አንድ ነገር፥ ለሌላው ሌላ እንዳይናገሩ ለማስጠንቀቅ ሲባል የተደረገ ይሆናል። በቲቶ መልእክት ዲያቆናት አለመጠቀሳቸው አሰፈላጊነታቸው ውሱን ነው ማለት አይደለም። ምናልባት የቀርጤስ ቤተ ክርስቲያን ትንሽ ከመሆኗ የተነሳ ዲያቆናት ሳያስፈልጓት፥ ወይም ዲያቆናት ኖረዋት ሽማግሌዎች ሳያስፈልጓት ቀርቶ ይሆናል። 3. ሴቶች ዲያቆናት ሊሆኑ ይችላሉን? በአዲስ ኪዳን ውስጥ ሁለት ጥቅሶች ብቻ ናቸው ሴት ዲያቆናት እንደነበሩ የሚያስረዱ (በሮሜ 16፡2)። ፌበን “አገልጋይ” ተብላ ተጠርታለች (ቃሉ “ዲያቆን” ማለት ነው)። ጥያቄው፣ የቃሉ አጠቃቀም የሚያስረዳው ይህች ሴት በድቁና የታወቀች (የሴት ዲያቆን) እንደነበረች ወይስ ተራ አገልጋይ? የሚል ይሆናል። ምናልባት (እንደ 1ኛ ቆሮንቶስ 16፡15 ገለጣ ከሆነ) አገልጋይ ብሎ መቀበሉ ይሻል ይሆናል። ሌላው ጥቅስ 1ኛ ጢሞ. 3፡11 ሲሆን እዚያም የተወሰኑ ሴቶች ስም ተጠቅሷል። እዚህም ላይ የሚነሳው ጥያቄ፥ እነዚህ ሴቶች የዲያቆናት ሚስቶች ናቸው? ወይስ ሴት ዲያቆናት? የሚል ይሆናል (ቃሉ በግሪክ “ሴቶች” ማለት ነው)። ሴት ዲያቆናት ቢሆኑ ኖሮ ስለ ዲያቆናት በሚገልጠው አንቀጽ መካከል ከሚሆን ይልቅ፥ ከቁጥር 13 በኋላ ሰለ ዲያቆናት የተሰጠው ማብራሪያ እንዳለቀ መጠቀስ ይኖርባቸው ነበር። ስለዚህ ምናልባት የዲያቆናት ሚስቶች ይሆናሉ የሚለውን አሳብ ያጠናክረዋል። በጥንቷ ቤተ ክርስቲያን፥ በግልጥ የታወቁ የሴት ዲያቆናት መኖራቸው በጣም አጠራጣሪ ነው። 4. በአዲስ ኪዳን ንብረት ጠባቂ የሚል የሥራ ድርሻ አልነበረም። ዛሬ ግን በማኅበሩ ስም የቤተ ክርስቲያንን ንብረት የሚጠብቁ ሰዎች አስፈላጊ ሆነዋል። የአዲስ ኪዳን ቤተ ክርስቲያናት ስብሰባ የሚያደርጉት በየቤቱ ስለነበር ንብረት ጠባቂ አላሻቸውም። ዛሬ ግን ቤተ ክርስቲያናት የራሳቸው ሕንፃ ያላቸው ስለሆነ ንብረታቸው በግለሰቦች ሊያዝ አይገባም። በነገራችን ላይ በ2ኛ ቆሮንቶስ 8፡17-24 ገንዘብ ያዦችና የንብረት ባለ አደራዎች መኖራቸው ተገልጧል። እርግጥ ቤተ ክርስቲያን ሕጋዊ አቋም ባልነበራት በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን የነዚህ ሰዎች አስፈላጊነት በአሁኑ ዘመን ካለው ሁኔታ እጅግ ይለያል፡፡ እስካሁን ስለ ቤተ ክርስቲያን አመራርና መሪዎቿ ተነጋግረናል። ነገር ግን የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የተከናወነው በእነርሱ ብቻ እንዳልሆነ ማስታወስ ጠቃሚ ነው። እነርሱ ይመራሉ፥ ያስተዳድራሉ፥ ይጠብቃሉ፥ ያገለግላሉ። ነገር ግን ስጦታ ያላቸው ሌሎች ሰዎችም በአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ሊካፈሉ ይችሉ ነበር። ሽማግሌ ወይም
