የኖህ የጥፋት ውሃ መላውን ዓለም ያካተተ ነበር ወይስ የአንድን አካባቢ ክልል ብቻ?

ይህ ጥያቄ በሥነ-መለኮት ምሁራን፣ በጂኦሎጂስቶች (የምድር ጥናት አዋቂዎች) እና በመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ዘንድ ሰፊ ውይይት ሲደረግበት የኖረ አንገብጋቢ ጉዳይ ነው። የእግዚአብሔርን ቃል በጥንቃቄ ስንመረምር የኖኅ የጥፋት ውኃ የአንድን አካባቢ ክልል ብቻ ያጠፋ (Local Flood) ሳይሆን፣ መላውን ዓለም ያካተተ ዓለም አቀፋዊ የጥፋት ውኃ (Global Flood) እንደነበረ እናያለን።

ይህንን እውነት መጽሐፍ ቅዱስ በሚከተሉት ዐበይት ማስረጃዎች ያረጋግጥልናል፡-

1. መጽሐፍ ቅዱስ የሚጠቀምበት ሁሉን አቀፍ ቋንቋ

በዘፍጥረት መጽሐፍ ላይ ስለ ጥፋት ውኃ የተጻፈው ቃል፣ ክስተቱ በዓለም ሁሉ ላይ መድረሱን በግልጽ የሚያሳይ ነው። ውኃውም በምድር ላይ እጅግ በጣም አሸነፈ፥ ከሰማይም በታች ያሉ ረዣዥም ተራሮች ሁሉ ተሸፈኑ (ዘፍ 7:19)። የጥፋት ውኃው የአንድን አካባቢ ክልል ብቻ ያካተተ ቢሆን ኖሮ፣ “ከሰማይ በታች ያሉ ረዣዥም ተራሮች ሁሉ” መሸፈን አያስፈልጋቸውም ነበር። ውኃ ተራራን ሸፍኖ በአንድ አካባቢ ብቻ ሊቆም የሚችልበት የተፈጥሮ ሕግ የለም፤ ተራራዎችን ከሸፈነ መላውን ምድር አጥለቅልቋል ማለት ነው።

2. የመርከቢቱ አስፈላጊነት

የጥፋት ውኃው በአካባቢ ደረጃ (ለምሳሌ በመካከለኛው ምሥራቅ ብቻ) የተከሰተ ቢሆን ኖሮ፣ እግዚአብሔር ኖኅን 120 ዓመታት ሙሉ ግዙፍ መርከብ እንዲሠራ ከማድረግ ይልቅ፣ ልክ ሎጥን ከሰዶም እንዳወጣው ኖኅንም ወደ ሌላ አካባቢ እንዲሰደድ ያደርገው ነበር። እንዲሁም አዕዋፋትና እንስሳት መርከብ ውስጥ ከመግባት ይልቅ ወደ ሌላ አህጉር መሸሽ ይችሉ ነበር። ነገር ግን ሥጋ ያለው ሁሉ፣ ወፎችም፣ እንስሶችም፣ አራዊትም፣ በምድር ላይ የሚርመሰመሱትም ሁሉ፣ ሰውም ሁሉ ሞቱ (ዘፍ 7:21)። መርከቢቱ ያስፈለገችው መላው ምድር በውኃ ስለተጥለቀለቀ ነው።

3. የእግዚአብሔር ቃል ኪዳንና ቀስተ ደመና

ከጥፋት ውኃ በኋላ እግዚአብሔር ለኖኅና ለፍጥረት ሁሉ ቃል ኪዳን ገብቷል። ሥጋ ያለው ሁሉ ዳግመኛ በጥፋት ውኃ አይጠፋም፥ ምድርንም ለማጥፋት ዳግመኛ የጥፋት ውኃ አይሆንም (ዘፍ 9:11)። የኖኅ የጥፋት ውኃ የአንድን አካባቢ ብቻ ያጠፋ (Local Flood) ቢሆን ኖሮ፣ እግዚአብሔር ቃል ኪዳኑን አፍርሷል ማለት ነው፤ ምክንያቱም ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በየዘመናቱ በብዙ አካባቢዎች ከባድ የጎርፍ አደጋዎችና ጥፋቶች ይከሰታሉ። እግዚአብሔር ቃል ኪዳኑን ያደረገው ግን ዓለምን ሙሉ በሙሉ ስለሚያጠፋው ዓይነት የጥፋት ውኃ ነው።

4. የሐዲስ ኪዳን ምስክርነት

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ሆነ ሐዋርያት የኖኅን የጥፋት ውኃ ያዩት እንደ ዓለም አቀፍ ፍርድ ነው። ሐዋርያው ጴጥሮስ ስለ ኖኅ ዘመን ሲናገር፣ በዚያን ጊዜ የነበረው ዓለም በውኃ ተጥለቅልቆ ጠፋ በማለት ክስተቱ መላውን “ዓለም” ያካተተ መሆኑን ይመሰክራል (2ኛ ጴጥ 3:6)። ጌታ ኢየሱስም የጥፋት ውኃ መጥቶ ሁሉን እስኪያጠፋ ድረስ እንዳላወቁ፥ የሰው ልጅ መምጣት ደግሞ እንዲሁ ይሆናል ብሎ አስተምሯል (ማቴ 24:39)። ጌታ ሲመጣ ፍርዱ በዓለም ሁሉ ላይ እንደሚሆን፣ የኖኅም የጥፋት ውኃ በዓለም ሁሉ ላይ ነበር።

ማጠቃለያ

የኖኅ የጥፋት ውኃ እግዚአብሔር በኃጢአት በረከሰችው መላዋ ዓለም ላይ ያመጣው ፍርድ ነው። ይህ ታሪክ የእግዚአብሔርን የቅድስና ቁጣ የሚያሳይ ቢሆንም፣ በሌላ በኩል ደግሞ ታላቅ የምሕረትና የጸጋ መልእክት አለው። ኖኅና ቤተሰቡ በመርከቢቱ ውስጥ ገብተው ከሞት እንደዳኑ፣ ዛሬም የሰው ልጅ ሁሉ መዳኛ በሆነው በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ የሚያምኑ ሁሉ ከሚመጣው የዘላለም ፍርድ ይድናሉ! መርከቢቱ የክርስቶስ ጥላ ነች፤ በእርሱ ውስጥ ያለ ከጥፋት የተጠበቀ ነው።

የጌታ ጸጋ ከእርስዎ ጋር ይሁን፤ ሀሳብዎን ለመስማት ዝግጁ ነን።

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading