እግዚአብሔር ሁልጊዜ ሰዎች ከእርሱ ጋር ኅብረት የሚያደርጉበትን መንገድ ያዘጋጃል። ብዙውን ጊዜ ኃጢአትን ከሚንቁ (ቀልለው ከሚመለከቱ) ሰዎች በተቃራኒ፥ እግዚአብሔር ቅዱስና ጻድቅ ነው። ስለሆነም በሰዎች ኃጢአትና ዓመፃ ላይ በጽድቅ ይፈርዳል። እግዚአብሔር አዳምና ሔዋን ኃጢአት በሚሠሩበት ጊዜ እንደሚሞቱ ቀድሞ ነግሯቸው ነበር (ዘፍጥ. 2፡16-17)። ይህ ሞት ሁለት ታላላቅ ገጽታዎች ነበሩት፦
- የመጀመሪያው ገጽታ፦ የሰዎችን መንፈስ ከእግዚአብሔር የሚለይ ቅጽበታዊ የመንፈስ ሞት ነው። አዳምና ሔዋን ኃጢአት በሠሩ ቅጽበት ከእግዚአብሔር በተደበቁ ጊዜ፥ መንፈሳቸው ከእግዚአብሔር ጋር ያለውን ቅዱስ ኅብረት ማጣቱን (መሞቱን) አሳይተዋል።
- ሁለተኛው ገጽታ፦ ይኸው መንፈሳዊ ሞት የኋላ ኋላ ሥጋዊ ሞትን አስከትሏል። ይህም የሰው መንፈስ ከሥጋው የሚለይበት ፍጻሜ ነው።
ደኅንነት (ድነት) ሙሉ በሙሉ ከእግዚአብሔር እንጂ ከሰው አይደለም። እኛ እግዚአብሔርን እንደመረጥነው ወይም የደኅንነትን መብት የሚያስጨብጥ አንድ ትክክለኛ የጽድቅ ሥራ እንዳደረግን በምናስብበት ጊዜ፥ በልባችን ውስጥ የመንፈሳዊ ኩራት ምልክት እናሳያለን። ለምሳሌ ለድሆች መመጽወት፥ በራስ ጥረት ጥሩ ክርስቲያን ለመሆን መሞከርና የመሳሰሉት በራሳቸው ሰውን ሊያድኑ አይችሉም። ስለሆነም ብዙውን ጊዜ «የዳንሁት በክርስቶስ ስላመንሁ ነው» እንላለን፤ ይህ ፍጹም እውነት የሆነ አባባል ነው። ነገር ግን እኛ ከማመናችንም በፊት የደኅንነትን መንገድ ቀድሞ ያዘጋጀልን እግዚአብሔር ነው። የደኅንነት ብቸኛ ምንጩ እግዚአብሔር እንጂ ሰው አይደለም።
አዳምና ሔዋን ኃጢአትን ከፈጸሙ በኋላ ከእግዚአብሔር ጋር የነበራቸውን ግንኙነት በራሳቸው ጥረት ለማደስ የሚያስችል ምንም ዓይነት ሌላ መላ አልነበራቸውም። ስለዚህም ነው እግዚአብሔር ራሱ የግድ ለእነርሱ አንድን የማዳን ሥራ ማድረግ የነበረበት።
በሰው ልጆች ታሪክ ሁሉ ውስጥ ሰዎች የራሳቸውን የደኅንነት መንገድ በተለያየ ሃይማኖት ለማግኘት ሲሞክሩ ኖረዋል። ነገር ግን ሰዎች ከእርሱ ጋር የሚታረቁበትን እውነተኛ መንገድ ሊያሳይ የሚችለው ፈጣሪ እግዚአብሔር ብቻ ነው። ቡድሂስቶች፥ ሂንዱዎች፥ ሙስሊሞችና ሌሎችም የሃይማኖት ወገኖች ሕግን በመጠበቅና ጥሩ ሰዎች በመሆን የእግዚአብሔርን ይቅርታ ለማግኘት በሥጋዊ ኃይል ይጥራሉ። ብዙ ክርስቲያኖችም ሳያውቁ ይህንኑ የተሳሳተ የይቅርታ መንገድ ይከተላሉ። አንዳንድ ሰዎች ብዙ ስለጸለዩ፥ ሳያቋርጡ ወደ ቤተ ክርስቲያን ስለሄዱ ወይም አሥራታቸውን ስለሰጡ ብቻ እግዚአብሔር ኃጢአታቸውን እንዲሁ ይቅር የሚል ይመስላቸዋል። ይህ ግን የተሳሳተ ድርጊትና አመለካከት ነው።
እኛ ሰዎች በፈጣሪያችን ላይ ስላመፅን፥ በእርሱ ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት ምን ማድረግ እንዳለብን ሊነግረን የሚገባው ፈጣሪያችን ራሱ ነው። እግዚአብሔር እኛን እንዴት ይቅር ብሎ እንደሚያድነን የመወሰን ሥልጣን ለሰው ልጅ አልተሰጠም። ብሉይ ኪዳንም ሆነ አዲስ ኪዳን፥ እግዚአብሔር ራሱ የይቅርታንና የዕርቅን በር በክርስቶስ በኩል ስለሚከፍትበት መለኮታዊ መንገድ ብቻ ይናገራሉ።
የውይይት ጥያቄ፦ ክርስቲያኖችን ጨምሮ ብዙ ሰዎች ለእግዚአብሔር አንድ መልካም ነገር በማድረግ ብቻ ይቅርታን ሊያገኙ እንደሚችሉ የሚያስቡበትን ሁኔታ ግለጽ። ይህ አመለካከት በክርስቶስ መስቀል ፊት የተሳሳተ የሚሆነው ለምንድን ነው?
መለኮታዊው የመሥዋዕት ሥርዓት (ሕይወት ለሕይወት)
እግዚአብሔር በሕዝቡ መካከል ቅዱስ ኅብረትን ለመመሥረት የተጠቀመበት ብቸኛው መንገድ በመሥዋዕት ነው። በዕብራውያን 9፡22 ላይ፥ «ደም ሳይፈስ ስርየት የለም» የሚል ቃል እናነባለን። እግዚአብሔር ፍጹም ቅዱስና ጻድቅ አምላክ በመሆኑ፥ በኃጢአተኞች ላይ በጽድቅ ሳይፈርድ እንዲሁ በደፈናው (ያለ ደም) ይቅር አይላቸውም። ነገር ግን እግዚአብሔር በፍቅርና በምሕረት የተሞላ አምላክ በመሆኑ፥ ለይቅርታ የሚሆን መለኮታዊ ምትክ መንገድ ያዘጋጅላቸዋል። እግዚአብሔር እንስሳት ለኃጢአት መሥዋዕት ይሆኑ ዘንድ በብሉይ ኪዳን በመደንገግ፥ «ሕይወት ለሕይወት» የሚል ታላቅ መንፈሳዊ መርሕ መሥርቷል።
፩. የብሉይ ኪዳን ጊዜያዊ መሥዋዕቶች
በመጀመሪያ እግዚአብሔር በብሉይ ኪዳን ዘመን በኃጢአተኞች ምትክ የሚሰዉ ጊዜያዊ እንስሳትን ሥርዓት አዘጋጅቷል (ዕብ. 10፡1-14)። እግዚአብሔር ለአዳምና ለሔዋን የቆዳን ልብስ በማልበስ፥ ለኃጢአት መሸፈኛ የእንስሳት መሥዋዕት ማቅረብ እንዳለባቸው መጀመሪያ አስተምሯቸዋል። የአዳምና የሔዋን ልጆች የሆኑት ቃየንና አቤል ይህንን የአምልኮ ሥርዓት ያውቁ ነበር (አቤልም በመንፈስ የታዘዘው ለዚህ ነው)። በተቀረው የብሉይ ኪዳን ታሪክ ሁሉ ቅዱሳን ሰዎች እግዚአብሔርን ያመልኩ የነበረው የእንስሳትን መሥዋዕት በማቅረብ ነበር። ሰዎች በሕይወት ይኖሩ ዘንድ በነርሱ ምትክ የእንስሳቱ መሞት የግድ ነበር።
ምንም እንኳን እንስሳት በራሳቸው ኃጢአት ባይሠሩም፥ በሰዎች ምትክ በመሞት የኃጢአትን ዋጋ በምሳሌነት ለመሸከም ተገደው ነበር። ይህንን የምትክ ሞት (Substitutionary death) ለማሳየት፥ መሥዋዕቱን የሚያቀርበው ሰው እጆቹን በሚሠዋው እንስሳ ራስ ላይ በመጫን ኃጢአቱን በግልጽ ይናዘዝ ነበር (ዘፀ. 29፡10፤ ዘሌዋ. 16፡21)። እግዚአብሔር በመገናኛው ድንኳንና በሰለሞን ቤተ መቅደስ የአምልኮን ሥርዓት በሙሴ በኩል ሲመሠረት፥ ሥርዓቱ ሁሉ እነዚህን ደማዊ መሥዋዕቶች እንዲያካትት አድርጓል (ዘሌዋ. ምዕ. 1-5)።
፪. የክርስቶስ ፍጹምና ዘላለማዊ መሥዋዕት
ነገር ግን የእንስሳት ደም ለኃጢአት ችግርና ለዘላለም ይቅርታ ጊዜያዊ ጥላና መፍትሔዎች ብቻ ነበሩ። እግዚአብሔር አብ ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን ፍጹምና የመጨረሻው መሥዋዕት አድርጎ ለመላክ ከዘላለም ዓለም አቅዶ ነበር። ለዚህ ነው መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቶስ «ዓለም ሳይፈጠር ጀምሮ ቀድሞ እንደተመረጠ» የሚናገረው (1ኛ ጴጥ. 1:19-20)። የብሉይ ኪዳን መሥዋዕቶች ሁሉ ወደ ክርስቶስ ፍጹም መሥዋዕትነት የሚያመለክቱ ጥላዎች ነበሩ።
ምንም ዓይነት ኃጢአት ፈጽሞ ባይገኝበትም፥ የእግዚአብሔር ዘላለማዊ ልጅ የሆነው ክርስቶስ በእኛ ምትክ በመስቀል ላይ ሞተ። በመስቀሉ ላይ ክርስቶስ የሰዎችን ሁሉ ኃጢአት በአንድነት ተሸከመ። ከአዳምና ከሔዋን ጀምሮ በታሪክ ውስጥ እስከሚኖሩት የመጨረሻዎቹ አማኞች ድረስ ይህን የማዳን ሥራ ፈጸመ (ዕብ. 9፡26-28)። ለዚህም ነው እርሱ «የእግዚአብሔር በግ» የተባለው (ዮሐ. 1፡29)፤ እንዲሁም «እኔ መንገድ፥ እውነትና ሕይወት ነኝ፤ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም» ያለው (ዮሐ. 14፡6)።
ቅዱሱ የእግዚአብሔር ልጅ ለሰዎች ሁሉ የሚሆን መሥዋዕትን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አቀረበ (ዕብ. 9፡26)። ለሰው ልጆች የራሱን መለኮታዊ ሕይወት ሰጠ። ጳውሎስ እንዳለው፥ «እኛ በእርሱ ሆነን የእግዚአብሔር ጽድቅ እንሆን ዘንድ ኃጢአት ያላወቀውን እርሱን ስለ እኛ ኃጢአት አደረገው።» (2ኛ ቆሮ. 5፡21)።
የእውነተኛ ደኅንነት መለኮታዊ “ቅመሞች”
እግዚአብሔር ሰዎች እንደገና ከእርሱ ጋር ቅዱስ ኅብረት እንዲመሠርቱ ዕድል ይሰጣቸዋል። እግዚአብሔር ሰዎች ከእርሱ ጋር የሚታረቁበትን መንገድ በጸጋ ቢያዘጋጅም፥ ማንንም በግድ አያስገድድም። ምርጫው የሰዎቹ ነው። በዓመፃችንና በኃጢአታችን ልንቀጥል ወይም ሰው ሠራሽ የሃይማኖት መንገዶቻችንን ልንከተል እንችላለን፤ ወይም ደግሞ እግዚአብሔር ያዘጋጀውን የክርስቶስን መሥዋዕት በእምነት ተቀብለን ከአምላካችን ጋር ልንታረቅ እንችላለን።
እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ከሁለቱ አንዱን መንገድ የመምረጥ ነጻነት ቢሰጥም (ማቴ. 7፡13-14)፥ እነዚህ ሁለት መንገዶች ወዴት እንደሚወስዱን መለኮታዊውን ፍጻሜ ግን ልንቀይር አንችልም። ስለሆነም የዓመፀኝነትንና ሰውን ያማከለ የሃይማኖት አምልኮ ከመረጥን፥ የዘላለምን ፍርድ እንደምንቀበል እግዚአብሔር በቃሉ ያስጠነቅቀናል (ዮሐ. 8፡24፤ 12፡46-48)። ነገር ግን የእርሱን የደኅንነት መንገድ ከተቀበልን ልጆቹ እንደምንሆን (ዮሐ. 1፡12)፥ የዘላለምን ሕይወት እንደምናገኝና (ዮሐ. 3፡16)፥ ለዘላለም በበረከቶቹ ደስ እየተሰኘን ከእርሱ ጋር በክብር እንደምንኖር ይነግረናል (ራእይ 21-22)።
ወንጌሉን በምንመሰክርበት ጊዜ በአብዛኛው ይህንን እንደ ቀላል ውሳኔ ብቻ እንመለከተዋለን፤ «በክርስቶስ እመንና ዳን» እንላለን። ምንም እንኳን ይህ ቀላል አሳብ እውነት ቢሆንም፥ እግዚአብሔርን ለመከተል በምንመረጥበት ጊዜ ልንገነዘባቸው የሚገቡንን ሌሎች ወሳኝ ጉዳዮች አንዳንድ ጊዜ ይሰውርብናል። በመልካም ወጥ ውስጥ የተለያዩ ቅመሞች እንደሚጨመሩ ሁሉ፥ እምነታችንም እውነተኛና ፍሬያማ እንዲሆን ከተፈለገ አያሌ የተለያዩ መንፈሳዊ ልምምዶችን ማካተት አለበት። የሚከተሉት ለእውነተኛ ደኅንነት ኑሮ የሚያስፈልጉ ዋና ዋና መለኮታዊ “ቅመሞች” ናቸው፦
ሀ. ትሕትና
የኃጢአት ሁሉ ማዕከል ትዕቢትና ዓመፅ ነው። ሔዋን ኃጢአትን በፈጸመች ጊዜ፥ ድርጊቷ «የራሴን መንገድ በመምረጥ የምፈልገውን አደርጋለሁ፤ ለእግዚአብሔርም አልገዛም» የሚል የትዕቢት መንፈስ ነበር። ኃጢአትን በምንሠራበት ጊዜ ሁሉ ለእግዚአብሔርና ለመንገዶቹ ከመገዛት ይልቅ፥ በራስ ወዳድነት እየተመላለስን የራሳችንን ሥጋዊ ክብርና ምቾት ለመጠበቅ እንሻለን።
የውይይት ጥያቄ፦ ባለፈው ሳምንት በሕይወትህ የተገለጡትን ድካሞችና ኃጢአቶች በልብህ አስብ። ትዕቢት፥ ዓመፅና ራስ ወዳድነት የእነዚህ ድርጊቶች ስውር ምንጭ ሊሆኑ የቻሉት እንዴት ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር ከፍ ከፍ የሚያደርገን ራሳችንን በፊቱ ስናዋርድ ብቻ እንደሆነ በተደጋጋሚ ይናገራል (ያዕ. 4፡6፥ 10፤ 1ኛ ጴጥ. 5፡5-6)። እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል፤ ትሑታንን ግን ጸጋን ይሰጣቸዋል (ኢሳ. 2፡12)። ስለሆነም ደኅንነትን ለማግኘት ወደ እግዚአብሔር በምንመጣበት ጊዜ ሊኖረን የሚገባው የመጀመሪያው “ቅመም”፥ ለራሳችን ሥጋዊ ጥቅም ሳይሆን ለእግዚአብሔር ክብር ለመኖር ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ ነው። ፍጡር ለፈጣሪው ፍጹም የመገዛትን አመለካከት ሊያሳይ ይገባል። በልባችን ውስጥ የትዕቢትና የዓመፅ ጽናት ካለ እውነተኛ የደኅንነት ደስታ ሊኖረን አይችልም።
ለ. ንስሐ
መጥምቁ ዮሐንስ «ንስሐ ግቡ» በማለት እየሰበከ ነበር የመጣው (ማቴ. 3፡2)። ጌታ ክርስቶስም አገልግሎቱን በንስሐ ጀምሯል (ማቴ. 4፡17)። ጴጥሮስም በጰንጠቆስጤ ዕለት በነበረው መጀመሪያ ስብከቱ ሰዎች ንስሐ እንዲገቡ አሳስቧቸዋል (የሐዋ. 2:38)። ስለሆነም ከእግዚአብሔር ጋር ዕርቅ ለማድረግ ከተፈለገ፥ የንስሐ ቅመም የግድ መኖር አለበት።
ነገር ግን ብዙ ክርስቲያኖች የዚህን ቃል እውነተኛ ትርጉም በትክክል አይገነዘቡም። ንስሐ ስንገባ ወይም እግዚአብሔር ኃጢአታችንን ይቅር እንዲልልን ስንጸልይ፥ አብዛኛውን ጊዜ እግዚአብሔር ለኃጢአታችን ቀለል ያለ አመለካከት እንዲኖረው የምንጠይቅ ይመስለናል፤ «እግዚአብሔር ሆይ ኃጢአትን ፈጽሜአለሁ፤ ነገር ግን እንዲሁ እርሳው» እንላለን። ነገር ግን እግዚአብሔር ፍጹም ጻድቅ አምላክ በመሆኑ ኃጢአትን በደፈናው ሊረሳ አይችልም፤ ኃጢአት ቅጣትን ያስከትላል። ክርስቶስ በመስቀል ላይ ለመሞት የተገደደው ለዚህ ነው፤ ኃጢአታችንን በጽድቅ ይቅር ለማለት እንዲችል መለኮታዊውን ዋጋ በደሙ ከፍሏል።
መጽሐፍ ቅዱሳዊ ንስሐ ሁለት ዐበይት እውነቶችን ያካትታል፦
- ዝርዝር ኑዛዜ (Specific Confession)፦ ስለ ማንነታችንና ስለፈጸምነው ተግባር እውነተኛውን ነገር ተቀብለን በእግዚአብሔር ፊት ስለ ዓመፀኛነታችን እንናዘዛለን። ለተግባራችን ምንም ዓይነት ማመኻኛ ሳናቀርብና ሌላውን ሰው ወይም ሁኔታ ሳንወቅስ ጥፋታችንን በሙሉ አምነን እንቀበላለን። የፈጸምናቸውን ኃጢአቶች በጥቅል ሳይሆን አንድ በአንድ ለይተን እንዘረዝራለን። ይህ በተለይ የእግዚአብሔር ልጆች ከሆንን በኋላ በየዕለቱ ለምንፈጽመው ድካም የሚሠራ ታላቅ መርሕ ነው። «እግዚአብሔር ሆይ ኃጢአተኛ ነኝና ይቅር በለኝ» ማለቱ ብቻ በጥቅሉ አይበቃም። ይልቁንም «እግዚአብሔር ሆይ ለእገሌ ክፉ ውሸት ተናግሬአለሁና ይቅር በለኝ» ወይም «የጥላቻና የፍላጎት ክፉ አሳብ በልቤ አስተናግጃለሁና ይቅር በለኝ» ማለት አለብን። ዛሬ ስለ ሰረቁት ገንዘብ፥ ስለ ልባቸው ጥላቻ፥ ስለ መከፋፈላቸውና ስለ ትዕቢታቸው በግልጽ ሳይናዘዙ፥ በደፈናው «ይቅር በለኝ» እያሉ የሚጸልዩ ብዙ ክርስቲያኖች አሉ። ለእግዚአብሔር ኃጢአቶቻችንን በግልጽ ዘርዝረን በመናዘዝ ይቅር እንዲለንና እነዚህን ድካሞች የምናሸንፍበትን የመንፈስ ቅዱስን ኃይል እንዲሰጠን እስካልጠየቅን ድረስ፥ ከኃጢአት የነጻ የቅድስና ሕይወት መኖር አንችልም፤ ቤተ ክርስቲያናችንም የተቀደሰች ልትሆን አትችልም። ብዙዎቻችን ዝርዝር ኃጢአቶቻችንን በጥቅል የይቅርታ ጸሎት ሥር ለመደበቅ እንሞክራለን፤ ለዚህ ነው ዛሬ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እግዚአብሔርን መፍራትና የእውነተኛ ቅድስና ሕይወት ጠፍቶ ስናይ የምንደነቀው። የውይይት ጥያቄ፦ በዚህ ሳምንት ውስጥ የፈጸምሃቸውን ድካሞች በግልጽ ለይተህ አስብና እግዚአብሔር እነዚህን ዝርዝር ኃጢአቶች በደሙ ይቅር እንዲልህ በግል ጸሎትህ ጠይቅ። ከእነዚህ መካከል በሌሎች ሰዎች ላይ የተፈጸሙና ዕርቅ የሚሹ ካሉ፥ ወደ ሰዎቹ በመሄድ ይቅርታን የመጠየቅን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሥርዓት ፈጽም።
- የአቅጣጫና የድርጊት ለውጥ (Metanoia)፦ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ንስሐ የአሳብንና የድርጊትን ሙሉ ለውጥ ያካትታል። እግዚአብሔር ይቅር እንዲለን ከጸለይን በኋላ በእርሱ ፊት ያንን መጥፎ ተግባር ሆን ብለን መፈጸማችንን ከቀጠልን ንስሐ አልገባንም ማለት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ንስሐ የሚሰጠው ማብራሪያ አንድ ሰው በተሳሳተ መንገድ ቁልቁል እየሄደ ሳለ፥ አሳቡን ሙሉ በሙሉ ቀይሮ ፊቱን ወደ እግዚአብሔር የሚያዞርበትን (የሚመለስበትን) ሁኔታ የሚያሳይ ነው። ስለሆነም ለደኅንነት ንስሐ መግባት ማለት፥ በራስ ወዳድነት፥ በኃጢአትና በዓመፅ ጎዳና ዳግመኛ አልሄድም ብሎ በልብ መወሰን ነው። ይልቁንም አቅጣጫችንን ሙሉ በሙሉ ለውጠን ለእግዚአብሔር በመገዛት የታዛዥነትን መንገድ መከተል ነው። ደኅንነትን ካገኘን በኋላም ይኸው ተመሳሳይ አመለካከት በየዕለቱ ንስሐችን ውስጥ መኖር አለበት። ያደረግነው ነገር በእግዚአብሔር ፊት ክፉ እንደሆነ በቅንነት አምነን ሳንቀበል እግዚአብሔር ይቅር እንዲለን መጠየቁ ምንም ፋይዳ የለውም። ከኃጢአት ተመልሰን እግዚአብሔርን በሚያስከብር አቅጣጫ ካልተጓዝን እውነተኛውን የኅብረት ሰላም አናገኝም።
ሐ. እምነት
በዕብራውያን 11፡6 ላይ፥ «ያለ እምነት እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት አይቻልም» የሚል ቃል እናነባለን። ይህም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከዳር እስከ ዳር ተጽፎ የምናገኘው ታላቅ መለኮታዊ ጭብጥ ነው። መጽሐፍ ቅዱሳዊ እምነት በልባችን ውስጥ የሚመላለስ ዝምተኛ ስሜት ብቻ አይደለም፤ ወይም ደግሞ «በእግዚአብሔር ማመን አለብን» እያልን ለራሳችን የምንናገረው ተጨባጭነት የሌለው ባዶ አሳብ አይደለም። ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱሳዊ እምነት፥ እግዚአብሔር በሚገልጠው ሕያው እውነት ውስጥ ለመኖርና ራስን ለቃሉ አሳልፎ ለመስጠት መወሰን ነው።
አብርሃም የእምነት አባት ነበር፤ የእርሱ እምነት ግን ስሜት ብቻ አልነበረም። እግዚአብሔር ወደ አብርሃም መጥቶ ራሱን በገለጠለት ጊዜ፥ የተስፋ ቃልንና የሚታዘዘውን ትእዛዝ አብሮ ሰጠው (ዘፍጥ. 12፡1-3)። በዚህ ጊዜ አብርሃም በእግዚአብሔር ቃል ላይ በመመሥረት ለመታዘዝ ወይም ላለመታዘዝ መምረጥ ነበረበት። በሰውኛ አመለካከት የማይቻል ቢመስልም እንኳ ሕይወቱን እግዚአብሔር በሰጠው ትእዛዝ ላይ ለመመሥረትና ለመነሳት ወሰነ።
በብሉይም ሆነ በአዲስ ኪዳን ሰዎች ከእግዚአብሔር ጋር ቅዱስ ኅብረት ለማድረግ ከፈለጉ፥ ይህንኑ የእምነት መርሕ መከተል ይኖርባቸዋል። በአዲስ ኪዳን ውስጥ ለደኅንነት የተሰጠው ትእዛዝ እጅግ ግልጽ ነው፦ «በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ እመንና ትድናለህ» (ሐዋ. 16:31)። በክርስቶስ ካመንን የዘላለምን ሕይወት እንደምናገኝ የጸጋ የተስፋ ቃል ተሰጥቶናል (ዮሐ. 3፡16)።
የሚያድን እውነተኛ እምነት ሦስት መሠረታዊ ነገሮችን በውስጡ ማካተት አለበት፦
- ትክክለኛ የእውነት መሠረት (Notitia)፦ የሚያድነን እንዲሁ በደፈናው የምናሳየው እምነት ብቻ አይደለም። የማንኛውም ባዕድ ሃይማኖት ተከታዮች በራሳቸው መንገድ እምነት አላቸው፤ ነገር ግን የብዙዎቹ እምነት እውነት ባልሆነና በሰዎች ፍልስፍና ላይ የተመሠረተ ነው። እምነታችን የሚያድን እውነተኛ እምነት እንዲሆን ከተፈለገ፥ ትክክለኛ መለኮታዊ እውቀት ሊኖረው ይገባል። ለዚህ ነው ጳውሎስ እምነት ከመስማት እንደሚመጣ፥ የምንሰማው ደግሞ የእግዚአብሔርን ቃል እንደሆነ የሚነግረን (ሮሜ 10፡17)። ለመዳን ልናውቀው የሚገባን እውነት፦ ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ ሲል በመስቀል ላይ እንደሞተ፥ የኃጢአታችንን ሙሉ ቅጣት በደሙ እንደከፈለና በእርሱ በማመን ብቻ ከቅጣት ድነን በእግዚአብሔር ፊት መጽደቅ እንደምንችል የሚያመለክተው የወንጌል እውነት ነው።
- የተስፋ ቃሉን በሙሉ ልብ መቀበል (Assensus)፦ እግዚአብሔር አብርሃምን ለመባረክ የተስፋ ቃል ሰጥቶት ነበር፤ ይህም ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን ምድሩንና ቤተሰቡን ትቶ እግዚአብሔር ወደሚያሳየው ስፍራ እንዲሄድ የሚያደርግ ትእዛዝም ሰጥቶታል። አብርሃምም በእግዚአብሔር አመነ፤ የእምነቱንም እውነተኛነት በታዛዥነት ተቀብሎ ገለጠ። በተመሳሳይ ሁኔታ እግዚአብሔር ለእያንዳንዳችን የተስፋ ቃል ሰጥቶናል። በኢየሱስ ክርስቶስ ካመንን ኃጢአታችን ሁሉ ሙሉ በሙሉ ይቅር እንደሚባልልን፥ ከእርሱ ጋር እንደምንታረቅ፥ ልጆቹ እንደምንሆንና የዘላለምን ሕይወት እንደምናገኝ ገልጿል። ይህንን መለኮታዊ በረከት ለማግኘት ግን በክርስቶስ እንድናምን የተሰጠንን የወንጌል ትእዛዝ በልብ መቀበል አለብን።
- ራስን ለቃሉ አሳልፎ መስጠት (Fiducia)፦ እውነተኛ በሆነውና ተስፋ በተሰጠው መለኮታዊ ነገር መሠረት ለመመላለስ ራስን ሙሉ በሙሉ አሳልፎ መስጠት ያስፈልጋል። ብዙ ሰዎች «ክርስቲያኖች ነን» ቢሉም እናምናለን በሚሉት የወንጌል እውነት መሠረት ግን በሕይወታቸው አይመላለሱም። አብርሃም ቤተሰቡን ትቶ ወደ ከነዓን በተግባር ባይሄድ ኖሮ የሚያድን እምነት አይኖረውም ነበር። እኛም ብንሆን በቤተሰባችን የሃይማኖት ውርስ፥ በራሳችን መልካም ተግባርና በመሳሰሉት ላይ መተማመናችንን ፈጽመን ትተን፥ በክርስቶስ ማዳን ላይ ብቻ ሙሉ በሙሉ ካልተደገፍን የሚያድን እምነት ሊኖረን አይችልም። የሚያድን እምነት ማለት ራስን ለእግዚአብሔር ጸጋ አሳልፎ እየሰጡ መታዘዝ ነው።
የውይይት ጥያቄ፦
- ሀ) በክርስቶስ አምነህ የዳነበትን የመጀመሪያውን መለኮታዊ ጥሪ ስታስብ፥ እነዚህ ሦስት የእምነት ክፍሎች በሕይወትህ ተግባራዊ ስለሆኑበት ሁኔታ አብራራ።
- ለ) ለማመን የሚፈልጉ ሰዎች ስለሚያድን እውነተኛ እምነት ትክክለኛ ግንዛቤ እንዲያገኙ ለማድረግ፥ ከወንጌል ምስክርነታችንና ከአቀራረባችን ውስጥ ልንጠነቀቅባቸው የሚገቡ ነገሮች ምንድን ናቸው?
መ. ይቅርታ
እግዚአብሔር የሚያድን እምነት በሚኖረን ጊዜ ሊሰጠን ተስፋ ከገባቸው ታላላቅ ነገሮች መካከል፥ ይቅርታን እንደምናገኝና ከእርሱ ጋር የዘላለም ኅብረት እንደምናደርግ ነው። መጽሐፍ ቅዱስን ስናጠና ከእግዚአብሔር ዘንድ ሁለት ዓይነት የይቅርታ ገጽታዎችን እንቀበላለን፦
- የመጀመሪያው ገጽታ (ህጋዊ ይቅርታ/ጽድቅ)፦ እግዚአብሔር ከዓመፀኝነት ፍርድ ሙሉ በሙሉ ነጻ አውጥቶ ወደ ልጅነት ማዕረግ ይመልሰናል። ይህም በነገረ-መለኮት ‹ጽድቅ› (Justification) ይባላል። እግዚአብሔር በክርስቶስ ሥራ ምክንያት በእኛ ላይ የነበረውን የኃጢአት ዕዳ ሰርዞ «በደለኞች አይደላችሁም» ሲል በሉዓላዊ ዙፋኑ ላይ ያውጃል። ጳውሎስ የሚያድን እምነት ያላቸው ሰዎች ከእንግዲህ ወዲህ ምንም ኩነኔ እንደሌለባቸው በግልጽ አስምሮበታል (ሮሜ 8፡1)። ድንገት በድካም ኃጢአት ልንሠራ ብንችል እንኳ፥ ያ በደል በእግዚአብሔር መለኮታዊ ቤተሰብ ውስጥ ያለንን ተቀባይነትና የዘላለም ሕይወት ተስፋ ፈጽሞ አይነጥቀንም። ይህ ለኃጢአታችን ሁሉ ስርየት የሚደረግበትና የእግዚአብሔር ልጆች የምንሆንበት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የሚፈጸም ዘላለማዊ ይቅርታ ነው።
- ሁለተኛው ገጽታ (የቤተሰብ/የኅብረት ይቅርታ)፦ በሕይወት ጉዟችን የፈረሰውን ዕለታዊ የኅብረት ደስታ ከእግዚአብሔር ጋር ለመቀጠል በየጊዜው የምንቀበለው ይቅርታ አለ። ሁላችንም ወደ ከበረው ሰማይ እስክንደርስና እግዚአብሔር የኃጢአት ተፈጥሯችንን ሙሉ በሙሉ እስኪያጠፋልን ድረስ፥ በሥጋዊ ድካም ውስጥ በየጊዜው መውደቃችን የማይቀር ነው። ይህ ድንገተኛ ኃጢአት ግን የእግዚአብሔር ቤተሰብ አባልነታችንን (ልጅነታችንን) ወይም የዘላለም ሕይወታችንን ፈጽሞ አይቀማንም። ነገር ግን ከሰማያዊው አባታችን ጋር ያለንን የቅርብ የኅብረት ደስታ ወዲያው ያቋርጠዋል። በ1ኛ ዮሐንስ 1፡9 ላይ እንደተገለጸው፥ ኃጢአታችንን ብንናዘዝ ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን ከዓመፃም ሁሉ ሊያነጻን እርሱ የታመነና ጻድቅ ነው። ክርስቶስ የእነዚህን የዕለት ተዕለት ኃጢአቶቻችንን ጭምር ቅጣት ቀደም ሲል በመስቀል ላይ ሙሉ በሙሉ ስለከፈለ፥ እግዚአብሔር ኃጢአታችንን ይቅር ብሎ የተበላሸውን የኅብረት ሰላም ወዲያው ያድሰዋል።
እውነተኛ ይቅርታ ማለት በደል ፈጽሞ እንዳልተፈጸመ ቆጥሮ እንዲሁ በደፈናው ‹መርሳት› ማለት ብቻ አይደለም። ሁልጊዜ ኃጢአትን የፈጸመው ሰው በምድር ላይ ምንም ዓይነት የኃጢአት ሥጋዊ ፍሬ (ውጤት) አይቀበልም ማለት አይደለም። አንዳንድ ጊዜ ከአንድ ሰው ገንዘብ በግፍ ከሰረቅን በኋላ፥ ግለሰቡን በቃላት ብቻ «ይቅርታ» ስለጠየቅን ገንዘቡን የመመለስ ግዴታ የሌለብን ይመስለናል። ነገር ግን የፈረሰውን ኅብረት ማደስ ብቻ ሳይሆን የተሰረቀውንም ገንዘብ በቅንነት እስካልመለስን ድረስ፥ በኃጢአታችን በእውነት ተጸጽተን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ይቅርታ አልጠየቅንም ማለት ነው (ዘሌዋ. 6፡1-7)።
በሥጋዊ ምኞት የወሲብ ኃጢአት ፈጽመን እግዚአብሔርን በንስሐ ይቅርታ ብንጠይቅና ግንኙነታችን ቢታደስም እንኳ፥ ከድርጊቱ የተነሳ ከሚመጡ ምድራዊ ፍሬዎች (ለምሳሌ ካልተፈለገ እርግዝና፥ ከተለያዩ በበሽታዎች መያዝ ወይም ከትዳር ጓደኛ እምነት ማጣትና ጥርጣሬ) በታምራት እንዲሁ ልንድን አንችልም። ኃጢአት ሁልጊዜ በምድር ላይ ጠባሳና ፍሬ አለው።
ሠ. መታዘዝ
ኃጢአት ፍጡር በፈጣሪው ላይ የሚፈጽመው ግልጽ ዓመፅ ነው። ስለሆነም ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ዕለታዊ ኅብረት በደሙ በሚስተካከልበት ጊዜ፥ እግዚአብሔር በፈጣሪና በፍጡሩ መካከል መጀመሪያ እንዲኖር ወደሚፈልገው ቅዱስ ሥርዓት እንመላለሳለን ማለት ነው። ይህም እግዚአብሔርን በደስታ የምንታዘዝበት ግንኙነት ነው። ክርስቶስ አንድ ጊዜ ለደቀ መዛሙርቱ፥ «ጌታ ሆይ፥ ጌታ ሆይ፥ ትሉኛላችሁ፥ የምለውንም አታደርጉም፤ ስለ ምን?» ብሏል (ሉቃስ 6፡46)። ከእግዚአብሔር ጋር ለምናደርገው እውነተኛ ኅብረት ትልቁ ማረጋገጫ እርሱን በመታዘዝ መመላለሳችን ነው።
በክርስቲያን ሕይወት ውስጥ ሁለት ዓይነት የመታዘዝ አመለካከቶች እንዳሉ ማወቅ ይኖርብናል፦
- የመጀመሪያው ዓይነት ታዛዥነት (የባሪያ መንፈስ)፦ አንድ አገልጋይ ወይም ባሪያ ከባድ ቅጣትን ፈርቶ የሚያደርገው መታዘዝ ነው። ወይም ደግሞ የእግዚአብሔርን ፍቅርና ምድራዊ በረከት በራሱ ጥረት ለመቀበል (ለመግዛት) ሲል የሚደረግ መታዘዝ ነው። ብዙ ክርስቲያኖች እግዚአብሔርን የሚታዘዙት እነዚህን ሁለት የተሳሳቱ አመለካከቶች ይዘው ነው፤ «ካልታዘዝን አሁን ይቀጣናል» በሚል የባሪያ ፍርሃት ይገዛሉ፥ ወይም ደግሞ በራስ ወዳድነት የእግዚአብሔርን በረከት ብቻ ለማግኘት ሲሉ ይሮጣሉ። ይህ አመለካከት አንድ ልጅ አባቱ ለትምህርት ቤት ክፍያ የሚሆን ገንዘብ እንዲሰጠው ብቻ አስቦ በግዴታ ወደ እንጨት ለቀማ ከሄደበት ሁኔታ ጋር ሙሉ በሙሉ ይመሳሰላል። እነዚህ በራስ ጥቅም ላይ የተመሠረቱ ታዛዥነቶች እግዚአብሔርን ከልብ ደስ የሚያሰኙ አይደሉም።
- ሁለተኛው ዓይነት ታዛዥነት (የልጅ መንፈስ)፦ ከታላቅ ምስጋናና ከእውነተኛ ፍቅር የሚመነጭ የልጅ ታዛዥነት ነው። ይህ ከእግዚአብሔር ዘንድ በምላሹ አንድ ምድራዊ ጥቅም ለማግኘት ሳይሆን፥ ለእግዚአብሔር የልብ ፍቅርንና አምልኮን ለመስጠት የሚደረግ ነው። በመጀመሪያ የወደደንን አባታችንን እግዚአብሔርን በቅድስና ስለምንወደው፥ እርሱን በሕይወታችን ሁልጊዜ ደስ ልናሰኘው እንፈልጋለን። ስለሆነም የማይደሰትባቸውን ክፉ ነገሮች በማድረግ ልቡን ልናሳዝን ፈጽሞ አንፈልግም። የሚያስደስቱትን ቅዱሳት ነገሮች ደግሞ ከመንፈሳዊ ልባችን በደስታ እናደርጋለን። ስለሆነም ከፈራሪ ቅጣት ፍርሃት ወይም ጥቅም ከመፈለግ የተነሳ ሳይሆን፥ ልናስደስተው ስለምንወደው ብቻ እግዚአብሔርን በነጻነት እንታዘዘዋለን። እግዚአብሔር ከመንፈሳውያን ልጆቹ ሁልጊዜ የሚፈልገው የዚህ ዓይነቱን የፍቅር ታዛዥነት ነው። ጳውሎስ በግልጽ እንዳለው፥ እኛ በክርስቶስ የጸጋ ልጆቹና ወራሾቹ እንጂ ከእንግዲህ ወዲህ የባርነት ቀንበር ያለብን ባሮች አይደለንም (ገላ. 4፡1-7)።
የውይይት ጥያቄ፦
- ሀ) አንድ አማኝ ክርስቲያን ከቅጣት ፍርሃትና ጥቅም ለማግኘት ከመፈለግ ዝንባሌ (የባሪያ መንፈስ) ወጥቶ፥ በእውነት ከፍቅር የተነሳ (የልጅ መንፈስ) እንዴት እግዚአብሔርን በዕለት ተዕለት ሕይወቱ ሊታዘዝ እንደሚችል በተግባራዊ ምሳሌ አስረዳ።
- ለ) በእነዚህ እግዚአብሔርን መታዘዝ በሚቻልባቸው የተለያዩ አመለካከቶች መካከል ያለው መሠረታዊ የመንፈስ ልዩነት ምንድን ነው?
- ሐ) አንተ በግል መንፈሳዊ ጉዞህ ብዙውን ጊዜ የምትለማመደውና በውስጥህ የሚበልጠው ታዛዥነት የትኛውን ነው?
3. እግዚአብሔር ከሕዝቡ ጋር የሚያደርገው የቃል ኪዳን ግንኙነት
እግዚአብሔር በቃል ኪዳኑ መሠረት ከሰዎች ጋር የጽኑ ግንኙነት የመመሥረቱ አሳብ፥ በብሉይና በአዲስ ኪዳን ውስጥ ትኩረት የተሰጠው ታላቅ መለኮታዊ እውነታ ነው። ለዚህም ነው መጽሐፍ ቅዱሳችን «ብሉይ ኪዳን» እና «አዲስ ኪዳን» ተብሎ በሁለት ዐበይት ክፍሎች የተከፈለው።
በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ውስጥ እግዚአብሔር ሁለት የተለያዩ የቃል ኪዳን ባህሪያትን ሲገባ እንመለከታለን፦
- በቅድመ ሁኔታ ላይ የተመሠረተ ቃል ኪዳን (ባለ ሁለት ወገን ኪዳን)፦ በሕዝቡ መታዘዝና አለመታዘዝ ላይ ሙሉ በሙሉ የተመሠረተ ቃል ኪዳን ነው። ይህ ባለ ሁለት ወገን (Conditional) ቃል ኪዳን ይባላል። ለዚህ ዋና ምሳሌ የሚሆነን እግዚአብሔር ከእስራኤላውያን ጋር በሲና ተራራ ላይ ያደረገው የሕግ ኪዳን ነው። በዚያ ስፍራ እግዚአብሔር ለእስራኤላውያን፥ «እኔ የምሰጣችሁን ትእዛዛት ፈጽማችሁ ብትቀበሉና ብትታዘዙ፥ እኔ መሪያችሁና ጠባቂያችሁ እሆናለሁ፤ እጅግም እባርካችኋለሁ» ብሏቸው ነበር (ዘዳግ. 6፡25፤ 7፡12)። ስለሆነም በእግዚአብሔርና በእስራኤል መካከል የነበረው ግንኙነት ሁለቱም ባለ ቃል ኪዳኖች ማድረግ የሚጠበቅባቸውን ድርሻ ማሟላት እንዳለባቸው የሚያመለክት ነበር። እስራኤል እግዚአብሔርን ለመታዘዝና በፊቱም በቅድስና ለመመላለስ በግልጽ ቃል ገባ፤ እግዚአብሔርም አይሁዶችን ለመባረክ ቃል ገባ። እንዲህ ዓይነቱ በቅድመ ሁኔታ ላይ የተመሠረተ ቃል ኪዳን፥ ተቀባዮቹ ወገኖች (እንደ እስራኤል ሕዝብ) ድርሻቸውን በኃጢአት ምክንያት በማይወጡበት ጊዜ ሊፈርስ ይችላል። ስለሆነም የብሉይ ኪዳን አብዛኛው የታሪክ ክፍል የሚያሳየው እስራኤል የእግዚአብሔርን ትእዛዛት ደጋግሞ ባለመታዘዙ ምክንያት መለኮታዊ ፍርዱንና ምርኮን እንዴት እንደተቀበለ ነው።
- በቅድመ ሁኔታ ላይ ያልተመሠረተ ቃል ኪዳን (የጸጋ ኪዳን)፦ በሰዎች ጥረትና ቅድመ ሁኔታ ላይ ፈጽሞ ያልተመሠረተ ቃል ኪዳን አለ። ይህ በኤርምያስ 31፡31-34 ላይ እግዚአብሔር አስቀድሞ ትንቢት የተናገረለት ታላቁ አዲስ ኪዳን ነው። ይህ ባለ ሁለት ወገን የድርድር ኪዳን ሳይሆን፥ እግዚአብሔር ራሱ በሉዓላዊ ጸጋውና በብቸኝነት ተግባራዊ የሚያደርገው የመለኮት ቃል ኪዳን (Unconditional Covenant) ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ ሁለተኛው ክፍል የ 27ቱ መጻሕፍት መጠሪያ የሆነው «አዲስ ኪዳን» የሚለው ስያሜ፥ እግዚአብሔር በኢየሱስ ክርስቶስ ደም አማካይነት ከሰው ልጆች ጋር ያደረገውን ይህንኑ የጸጋ ቃል ኪዳን ያመለክታል። እግዚአብሔር በአዲስ ኪዳን ውስጥ ሕዝቡ መለኮታዊ በረከቱን ከመቀበላቸው በፊት «ሕጉን በሙሉ ፈጽሙ» ብሎ ቅድመ ሁኔታ አይጠይቅም። ነገር ግን እግዚአብሔር ሰዎች በክርስቶስ የማዳን ሥራ ላይ በነጻ እምነት ብቻ ተደግፈው ይቅርታን አግኝተው ልጆቹ ሊሆኑ እንደሚችሉ በጸጋ አውጇል። ሰዎች ሊያደርጉ የሚገባቸው ነገር ቢኖር፥ በእምነት እጆቻቸውን ዘርግተው የእግዚአብሔርን ነጻ የደኅንነት ስጦታ በደስታ መቀበል ብቻ ነው። ከእንግዲህ ሰዎች ከእግዚአብሔር ጋር የሚያደርጉት ግንኙነት እርሱን ለመታዘዝና ቅዱሳን ለመሆን በሚያደርጉት የሰውኛ ሥጋዊ ጥረት ላይ የተመሠረተ ሳይሆን፥ እግዚአብሔር ራሱ በክርስቶስ በኩል ለቅድስናና ለይቅርታ በከፈለው ፍጹም መሠረት ላይ የሚቆም ይሆናል።
የውይይት ጥያቄ፦
- ሀ) በሕግ ኪዳን (በሲና ተራራ) እና በጸጋ ኪዳን (በቀራንዮ መስቀል) መካከል ያሉትን ታላላቅ ልዩነቶች መጽሐፍ ቅዱሳዊ በሆነ አገላለጽህ አብራራ።
- ለ) ዛሬ በአዲስ ኪዳን የጸጋ ዘመን ውስጥ የመኖር ታላቅ በረከት የተሰጠን ለምንድን ነው? ከእነዚህ መለኮታዊ በረከቶች መካከል ዋና ዋናዎቹን ዘርዝር።
4. ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ዓላማና የመጽሐፍ ቅዱስ ማዕከል ነው
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከዳር እስከ ዳር ከሚታዩ ታላላቅ ጭብጦች መካከል ዋነኛው፥ ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔር ለዓለም በወሰነው ዘላለማዊ ዕቅዱ ውስጥ ብቸኛው ማዕከል መሆኑ ነው። በብሉይ ኪዳን ታሪክ ውስጥ የክርስቶስ መኖርና መንቀሳቀስ የተረጋገጠ ቢሆንም፥ በስሙ ግን በግልጽ አልተጠቀሰም ነበር (ተሰውሮ ነበር)። ለምሳሌ በብሉይ ኪዳን ስለ ልዩው «የእግዚአብሔር መልአክ» የተጻፉ በርካታ ክፍሎችን እናነባለን። እርሱ እንዲሁ ተራ ፍጡር መልአክ ሳይሆን፥ መለኮታዊ መልእክተኛ እግዚአብሔር ራሱ ነው (ለምሳሌ ዘፍጥ. 16፡7-13፤ 22፡11-18፤ ዘፀ. 3፡2-4)። ብዙ የወንጌላውያን ሊቃውንት ይህ ልዩ መልአክ ክርስቶስ በሥጋ ከመገለጡ በፊት (Christophany) በብሉይ ኪዳን ዘመን ራሱን ለቅዱሳን የገለጠበት መለኮታዊ መንገድ እንደሆነ በጽኑ ያምናሉ።
በብሉይ ኪዳን ዘመን ለሰው ልጅ የኃጢአት ችግር እግዚአብሔር ያዘጋጀው ብቸኛ መፍትሔ፥ የሚላከው ያ ልዩ መለኮታዊ መልእክተኛ (መሢሕ) ነበር። እግዚአብሔር መጀመሪያ ስለ ክርስቶስ ድል አድራጊነት ትንቢት የተናገረው በዘፍጥረት 3፡15 ላይ ሲሆን፥ የሴቲቱ ዘር የእባቡን (የሰይጣንን) ራስ እንደሚቀጠቅጥ በግልጽ ተቀምጧል። ኢየሱስ ክርስቶስ ሰይጣንን በመስቀል ላይ በደሙ እንዳሸነፈውና አንድ ቀን ደግሞ እባብ የሆነውን ሰይጣንን ሙሉ በሙሉ ወደ እሳት ባሕር ውስጥ እንደሚወረውረው ከአዲስ ኪዳን እውነት እንረዳለን (ቆላ. 2፡13-15፤ ራእይ 20፡7-10)።
በብሉይ ኪዳን የእግዚአብሔር ዕቅድ ቀስ በቀስ እየበራ ሲመጣ (Progressive Revelation)፥ እግዚአብሔር ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ማንነትና አገልግሎት በርካታ ተጨማሪ መረጃዎችን በነቢያት በኩል ይሰጥ ጀመር፦
- ያዕቆብ በትነቢቱ «ዘንግ» (የአገዛዝ በትር) ሲል ጠርቶታል፤ ይህም ክርስቶስ የዘላለም ንጉሥ እንደሚሆን ያሳያል (ዘፍጥ. 49፡10)።
- ሙሴ ክርስቶስ ከእርሱ የሚበልጥ ታላቅ መለኮታዊ ነቢይ እንደሆነ በመግለጽ፥ ሕዝቡ ሁሉ እርሱን ብቻ እንዲሰሙት በግልጽ አዟል (ዘዳግ. 18፡15-18)።
- እግዚአብሔር ለዳዊት የሰጠው የኪዳን ተስፋ፥ ከእርሱ የሚወጣው መለኮታዊ ዘሩ (ክርስቶስ) በዙፋኑ ላይ ለዘላለም እንደሚነግሥ ያረጋግጣል (2ኛ ሳሙ. 7፡12-16)።
- በብሉይ ኪዳን መጨረሻ አካባቢ ስለ ክርስቶስ የሚሰጠው ትንቢታዊ መገለጥ ይበልጥ እያበራ መጣ። በሥጋ የሚገለጥ ታላቅ አምላክ «አማኑኤል» (እግዚአብሔር ከእኛ ጋር) እንደሚሆን ተገለጠ (ኢሳ. 7፡14)።
- መሢሕ በመሆኑ የእስራኤል ብቻ ሳይሆን የአሕዛብና የመላው ዓለም ገዥ ይሆናል (ኢሳ. 42፡1፤ 55፡3-5)።
- ለመላው ዓለም ኃጢአት መሸከሚያ ፍጹም በግና መሥዋዕት ሆኖ እንደሚሰቃይና እንደሚሞት በዝርዝር ተነገረ (ኢሳ. 53፡4-12)።
የብሉይ ኪዳን ትንቢቶች ወደ ክርስቶስ የሚያመለክቱ ብቻ ሳይሆኑ፥ የእርሱን ሰማያዊ አገልግሎት በልዩ ልዩ ታሪካዊ ተምሳሌቶች (Types) ጭምር ገልጸውታል። ስለሆነም ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጆች ሁለተኛው መሥመር መሪ የሆነው ፍጹሙ ሁለተኛው አዳም ነው (ሮሜ 5፡12-14፤ 1ኛ ቆሮ. 15፡45-49)። ክርስቶስ ከአሮን ሌዋዊ ክህነት እጅግ የሚበልጥና እንደ መልከ ጼዴቅ ሥርዓት የዘላለም ካህንና ንጉሥ የሆነ ታላቅ ሊቀ-ካህናት ነው (ዕብ. 6፡20፤ 7፡15-17)። የብሉይ ኪዳን ጊዜያዊ የእንስሳት መሥዋዕቶች ሁሉ የእግዚአብሔር ልጅ በመስቀል ላይ እንደ «እግዚአብሔር በግ» ይሞት ዘንድ ወደሚላክበት የመጨረሻው መሥዋዕት በምሳሌነት ያመለክቱ ነበር። ምንም እንኳን ክርስቶስ እንደ ሁለተኛው የሥላሴ አካል በብሉይ ኪዳን ውስጥ በስሙ በግልጽ ባይቀመጥም፥ በታሪኩና በምሳሌው ሁሉ መኖሩ ግን ፍጹም ግልጽ ነው።
ይህ በብሉይ ኪዳን በጥላና በምሳሌ «ተሰውሮ የነበረው» ኢየሱስ ክርስቶስ፥ በአዲስ ኪዳን ታሪክ ውስጥ በግልጽ በሥጋ ተገለጠ። የዕብራውያን ጸሐፊ በመንፈስ ቅዱስ ተመርቶ ይህንን ታላቅ እውነት እንዲህ ሲል ያጠቃልለዋል፦
«ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ ጎዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናግሮ፥ ሁሉን ወራሽ ባደረገው ደግሞም ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ በዚህ ዘመን መጨረሻ ለእኛ ተናገረን፤ እርሱም የክብሩ መንጸባረቅና የባሕርዩ ምሳሌ ሆኖ፥ ሁሉን በሥልጣኑ ቃል እየደገፈ፥ ኃጢአታችንን በራሱ ካነጻ በኋላ በሰማያት በግርማው ቀኝ ተቀመጠ።» (ዕብ. 1፡1-3)
በቤተልሔም በግርግም ውስጥ በትንሽነት የተወለደው ክርስቶስ፥ በሥጋ የተገለጠው ፍጹም አምላክ ነበር። እርሱ የብሉይ ኪዳንን ትንቢቶች በሙሉ በሕይወቱና በሞቱ በመፈጸም፥ ለሰው ልጆች ሁሉ የሚሆን የእግዚአብሔር ፍጹምና የመጨረሻ መሥዋዕት ሆኖ ቀረበ። በአዲስ ኪዳን አዲሱን የእግዚአብሔርን ሕዝብ (በደሙ የተዋጀችውን ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን) የመሠረተው እርሱ ነው። ይህ አዲስ መንፈሳዊ አካል ከአንድ ምድራዊ ጎሳ ብቻ ሳይሆን፥ በምድር ላይ ከሚገኝ ከሕዝብና ከነገድ ሁሉ የተውጣጣ የከበረ አካል ነው።
መጽሐፍ ቅዱስ ጠቅላላ መለኮታዊ አሳቡን የሚቋጨው፥ ክርስቶስ በምድር ሁሉ ላይ በታላቅ ክብር ለመግዛት አንድ ቀን በግልጽ እንደሚመለስ በማብሰር ነው። በዚህም ኃጢአት፥ ሰይጣን፥ መርገምና ሥጋዊ ሞት ፈጽሞ የማይኖርበትን የዘላለም ቅዱስ መንግሥት ለልጆቹ ይመሠርታል (ራእይ 19-22)።
የውይይት ጥያቄ፦
- ሀ) ክርስቶስ እንዴት በብሉይ ኪዳን ውስጥ በጥላና በምሳሌ ተሰውሮ እንደነበረና በአዲስ ኪዳን ውስጥ ደግሞ እንዴት በግልጽ እንደተገለጠ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምሳሌዎችን በመስጠት አብራራ።
- ለ) ክርስቶስ የእግዚአብሔር ዘላለማዊ ዕቅዶች ሁሉ ብቸኛ ማዕከል የመሆኑ እውነት፥ ብሉይና አዲስ ኪዳንን በትክክል እንድንተረጉም ስለምንረዳበት መለኮታዊ መንገድ ምን ያስተምረናል?
ምንጭ፦ «የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ»፣ በኤስ.አይ.ኤም (SIM) ጽሑፍ ክፍል የታተመና የተዘጋጀ መጽሐፍ ነው። ለዚህ አስደናቂና ለቤተ ክርስቲያን ዕድገት ለሚሆን ታላቅ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር አገልግሎታቸውንና ዘመናቸውን አብዝቶ ይባርክ።

ስለ ሁሉ አስቀድሜ ሁሉን የሰራና ያዘገጀ እግዚአብሔር ይክብር፤ እንግድህ ይህንን ጥበብና መስተዋልንም በዉስጥህ ያኖረዉ ጌተችንና መድሃንተችን ኢያሱስ ይበርክ፤በጠም ተበርኬዋለሁ ጌታ ዘመንህን በሙሉ ይበርክ።