ስለ እግዚአብሔር ቃል ትክክለኛ አጠቃቀም ቃሉ ሲያስተምር፡ "የእውነትን ቃል በቅንነት የሚፈታውን… ሠራተኛ ሆኖ" ይላል (2ኛ ጢሞቴዎስ 2:15)። በእውነት ቃል ማለቱ መጽሐፍ ቅዱስን ሲሆን፣ በቅንነት መፍታት ማለት ደግሞ ቃሉን በትክክል፣ ያለምንም ስህተት መተርጎምና ማስተማር ማለት ነው።
በግሪክኛው "በቅንነት መፍታት" የሚለው ቃል "ኦርቶቶሙንታ" ሲሆን፣ ቀጥተኛና ትክክለኛ መንገድን መቁረጥ ወይም ማቅናት ማለት ነው። በጥንት ዘመን ይህ ቃል ገበሬዎች ማረሻቸውን ቀጥ አድርገው ሲያርሱ ወይም ድንኳን ሰሪዎች ጨርቁን በትክክል ሲቆርጡ የሚገለፅበት ቃል ነበር።
መንፈሳዊው ትርጉሙ አንድ አገልጋይ የእግዚአብሔርን ቃል ሲያስተምር ከራሱ አሳብ፣ ከባህል ወይም ከተሳሳተ ፍልስፍና ጋር ሳይቀላቅል እውነቱን ቀጥ አድርጎ ማቅረብ አለበት ማለት ነው። ጥቅሶችን ከዐውዳቸው ውጭ በመተርጎም የራሱን ሀሳብ ለማስደገፍ መጠቀም የእውነትን ቃል ማጣመም ነው።
እንዲሁም የእውነትን ቃል በቅንነት መፍታት የብሉይና የአዲስ ኪዳንን ልዩነት፣ የተስፋ ቃላትንና ህጎችን፣ እንዲሁም ለተለያዩ ዘመናት የተሰጡትን መለኮታዊ አላማዎች ለይቶ ማወቅን ያካትታል። ይህ ካልሆነ የሀሰት ትምህርት ቤተ ክርስቲያንን ይበክላል።
ቃሉ ለእኛም የእግዚአብሔርን ቃል ስንሰማም ሆነ ስናስተምር እጅግ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለብንና ቃሉ የሚለውን ብቻ ማመን እንዳለብን ያስገነዝበናል። የእግዚአብሔር ቃል የሰውን ማሻሻያ አይፈልግም።
ስለዚህ ቃሉን ስናነብም ሆነ ስንተረጉም የመንፈስ ቅዱስን ምሪት በመጠየቅ፣ እውነትን ከተሳሳተ ትምህርት ለይተን ልናወጣና በንፁህ ልብ ልንቀበለው ይገባል (2ኛ ጴጥሮስ 1:20-21)።
