በዚህ አለም ስላለው ሀብት ሲያስተምር ቃሉ እንዲህ ይላል፡ "በአሁኑ ዘመን ባለ ጠጎች የሆኑት የትዕቢትን ነገር እንዳያስቡ፥ ደስም እንዲለን ሁሉን አትርፎ በሚሰጠን በሕያው እግዚአብሔር እንጂ በሚያልፍ ባለ ጠግነት ተስፋ እንዳያደርጉ እዘዛቸው" (1ኛ ጢሞቴዎስ 6:17)። እግዚአብሔር ለጋስ አባት ነው።
ጳውሎስ ሀብትን በራሱ አላወገዘም፣ ነገር ግን በሀብት ላይ መታመንንና መታበይን በጥብቅ ይቃወማል። የሰው ልጅ መታመን ያለበት ዛሬ ኖሮ ነገ በሚጠፋው ቁሳቁስ ላይ ሳይሆን፣ የሁሉ ፈጣሪ በሆነው ህያው እግዚአብሔር ላይ ብቻ ነው።
አንዳንዶች እግዚአብሔርን መምሰል ማለት ራስን ከምድራዊ ደስታ ሁሉ ማራቅ ነው ብለው ያስባሉ። ነገር ግን እግዚአብሔር ይህንን የተፈጥሮ አለምና በረከቶቹን የፈጠረው የሰው ልጅ በአግባቡና በምስጋና እንዲደሰትበት ነው (1ኛ ጢሞቴዎስ 4:3-4)።
እግዚአብሔር ሀብትን የሚሰጠው ለራስ ወዳድነት ሳይሆን ለመልካም ስራ ነው። ባለጠጎች በጎ ስራን እንዲያደርጉ፣ ለማካፈል የተዘጋጁና ለጋሶች እንዲሆኑ ታዘዋል። በዚህ መንገድ ሲያደርጉ እውነተኛውን የሕይወት ደስታ ያጣጥማሉ።
ቃሉ ለእኛም እግዚአብሔር የሰጠንን በረከት ጣኦት ሳናደርገው በምስጋና እንድንደሰትበትና ለሌሎችም በማካፈል የፀጋው መጋቢዎች እንድንሆን ያስገነዝበናል። ሀብት የሚያምረው ለበጎ አላማ ሲውል ነው።
በጎ ስጦታ ሁሉ ከላይ ከብርሃናት አባት ይወርዳል። ስለዚህ በተሰጠን ነገር ሁሉ እግዚአብሔርን እያመሰገንን ህይወታችንን በደስታና በቅድስና ልንመራ ይገባል (ያዕቆብ 1:17)።
