“ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው” (ዮሐ 6:54)። ይህ ንግግር በወቅቱ ለነበሩት አድማጮች እጅግ ከባድና የሚያስደነግጥ ነበረ። እዚህ ላይ "ሥጋ" እና "ደም" መንፈሳዊ ትርጉም ያላቸው ዘይቤያዊ ቃላት ናቸው እንጂ ቃል በቃል የሚወሰዱ አይደሉም።
አይሁዳውያን ደምን መብላት በህጋቸው በጥብቅ የተከለከለ ስለነበር ይህን ቃል ቃል በቃል ተረድተውት ተሰናክለዋል (ዘሌ 17:10)። ነገር ግን የክርስቶስ መልእክት ስለ ስጋዊ ምግብ አልነበረም። የዚህ ቃል እውነተኛ ትርጉም የክርስቶስን ቤዛነት ሙሉ በሙሉ መቀበልን የሚያመለክት ነው።
ክርስቶስ ይህን የተናገረው ራሱን ስለ አለም ድነት በመስቀል ላይ አሳልፎ እንደሚሰጥ ለመግለጽ ነበር። እርሱን መብላትና መጠጣት ማለት በሞቱና በትንሳኤው ማመን፣ ህይወቱን ወደ ውስጣችን መቀበልና ከእርሱ ጋር ጥልቅ ህብረት ማድረግ ማለት ነው (ዮሐ 6:56)።
ልክ ምግብ የሰውነት ክፍል እንደሚሆንና ሃይል እንደሚሰጥ፣ ክርስቶስን በእምነት መቀበል ደግሞ ለመንፈሳዊ ህይወታችን መሰረት ነው። ይህ እውነት ቆይቶ በተመሰረተው የጌታ እራት ስርአት ላይም የሚንጸባረቅ መንፈሳዊ ምስጢር ነው።
የክርስትና ሕይወት ከክርስቶስ ጋር የሚደረግ የዕለት ተዕለት ህብረት ነው። ቃሉ ለእኛም ህይወታችንን ሙሉ በሙሉ በእርሱ ላይ እንድንደገፍና በእርሱ ሕይወት እንድንኖር ያስገነዝበናል። ጌታን የህይወታችን አብይ ክፍል አድርገን ልንይዘው ይገባል።
ያለ ክርስቶስ ሕይወት ባዶ ነው። “ነፍሳችን በእግዚአብሔር ቃልና በመንፈሱ ስትመገብ ብቻ እውነተኛውን ሕይወት ታገኛለች” እንደሚባለው፣ ዘወትር ከእርሱ ጋር ህብረት ማድረግና በመንፈስ ማደግ ያስፈልገናል።
