“አንድ ሃይማኖት” ወይም በመጽሐፍ ቅዱስ አገላለጽ “አንዲት ሃይማኖት” የሚለው ቃል፣ የክርስትና እምነታችንን ማዕከል እና የክርስቶስን አካል አንድነት የሚያሳይ እጅግ ጥልቅ ሐረግ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ በመንፈስ ቅዱስ ተመርቶ ይህንን ቃል የተጠቀመው አማኞች ሁሉ በክርስቶስ ስላላቸው አንድነት እና ስለ መዳን ብቸኛ መንገድ ሲያስተምር ነው። ይህንን እውነት በሚከተሉት ነጥቦች እንመልከት፡-
1. የ”አንዲት ሃይማኖት” መሰረት
በዓለም ላይ ብዙ የሃይማኖት ተቋማት እና ፍልስፍናዎች ቢኖሩም፣ መጽሐፍ ቅዱስ ግን የሰው ልጅ መዳን የሚያገኝባት እውነተኛ እምነት (ሃይማኖት) አንዲት ብቻ መሆኗን ያስተምራል። ይህችም አንዲት ሃይማኖት የተመሰረተችው በአንድ ጌታ ላይ ነው። ቃሉ ይህንን ሲያረጋግጥ፣ አንድ ጌታ አንዲት ሃይማኖት አንዲት ጥምቀት፤ ከሁሉ በላይ የሚሆን በሁሉም የሚሠራ በሁሉም የሚኖር አንድ አምላክ የሁሉም አባት አለ (ኤፌሶን 4:5-6) ይላል። ይህ የሚያሳየው እውነተኛዋ ሃይማኖት በሰው ፈጠራ የተገኘች ሳትሆን፣ በአንዱ ጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ያለን ጽኑ እና ብቸኛ እምነት መሆኗን ነው።
2. ሕያው ግኑኝነት እንጂ ስርአት አይደለም
ብዙ ጊዜ ሰዎች “ሃይማኖት” ሲሉ የውጫዊ ስርአቶችን፣ ወጎችን እና ደንቦችን ስብስብ ያስባሉ። ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረን “አንዲት ሃይማኖት”፣ ከእግዚአብሔር ጋር በክርስቶስ በኩል የሚደረግ ህያው እና የጠበቀ ግንኙነት ነው። ይህ እምነት በልብ ውስጥ በመንፈስ ቅዱስ የሚሰራ እና ወደ ተግባር የሚለወጥ ህይወት ነው። ሐዋርያው ያዕቆብ እውነተኛውን የእግዚአብሔርን መንገድ ሲገልጽ፣ ንጹሕና ነውር የሌለባት ሃይማኖት በእግዚአብሔር አባት ዘንድ ይህች ናት፤ ወላጆች የሌላቸውን ልጆች ባልቴቶችንም በመከራቸው መጠየቅ፥ በዓለምም ከሚገኝ እድፍ ራስን መጠበቅ ነው (ያዕቆብ 1:27) በማለት ያስተምረናል።
3. የክርስቶስ አካል አንድነት
ይህች “አንዲት ሃይማኖት” የዘር፣ የቋንቋ፣ የሀገር ወይም የባህል ልዩነት ሳያግዳት፣ በክርስቶስ የሚያምኑትን ሁሉ አንድ ታደርጋለች። መንፈስ ቅዱስ ሁላችንንም በአንድ አካል እንድንሆን በክርስቶስ ደም አዋህዶናል። ቃሉ ይህንን ሲያብራራ፣ “ይሁዳዊ ወይም የግሪክ ሰው የለም፥ ባሪያ ወይም ጨዋ ሰው የለም፥ ወንድም ሴትም የለም፤ ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው ናችሁና” ይላል (ገላትያ 3:28)፡፡ ይህች አንዲት ሃይማኖት ሁላችንንም በእግዚአብሔር ቤተሰብ ውስጥ አንድ አድርጋናለች።
