የደኅንነታችንን መሠረት በተመለከተ ቃሉ ሲያብራራ፡ "የአዲስ ኪዳንም መካከለኛ ወደሚሆን ወደ ኢየሱስ፥ ከአቤልም ደም ይልቅ የሚሻለውን ወደሚናገር ወደ መርጨት ደም ደርሳችኋል" ይላል (ዕብራውያን 12:24)። መካከለኛ ማለት በሁለት የተለያዩ ወገኖች መካከል እርቅን፣ ስምምነትንና ሰላምን የሚያመጣ አስታራቂ ማለት ነው።
በብሉይ ኪዳን ሙሴ በእግዚአብሔርና በእስራኤል ሕዝብ መካከል መካከለኛ ሆኖ ሕግን አምጥቶ ነበር። ነገር ግን ያ ኪዳን በሰዎች ድካም ምክንያት ሊጸና አልቻለም። የሰው ልጅ በኃጢአቱ ምክንያት ከቅዱሱ አምላክ ጋር ተጣልቶና ርቆ ነበር። ይህንን የጥል ግድግዳ ለማፍረስ ፍጹም የሆነ፣ አምላክነትንና ሰውነትን ያስማማ ብቸኛ መካከለኛ አስፈለገ።
ኢየሱስ ክርስቶስ የአዲስ ኪዳን መካከለኛ የሆነው የሰውን ኃጢአት በራሱ ላይ ተሸክሞ በመስቀል ላይ የደም ዋጋ በመክፈል ነው። የእርሱ ኪዳን በእንስሳት ደም ሳይሆን በገዛ ራሱ ሕይወት የታተመ ነው። አሮጌው ኪዳን ሞትንና ፍርድን ሲያውጅ፣ የኢየሱስ አዲስ ኪዳን ግን ምሕረትን፣ የኃጢአት ስርየትንና የዘላለም ሕይወትን ያመጣል።
የአቤል ደም መሬት ላይ በፈሰሰ ጊዜ "ፍትሕና የበቀል ፍርድ" እንዲሰጠው ወደ እግዚአብሔር ይጮኽ ነበር። የኢየሱስ ደም ግን ከዚያ በተሻለ ቋንቋ "ምሕረትና ይቅርታ" ብሎ ይናገራል። ክርስቶስ በአብ ቀኝ ሆኖ ዘወትር ይህንን የደም ኪዳን በማቅረብ ስለ እኛ ይማልዳል፣ መካከለኛ ሆኖም ያስታርቀናል።
ቃሉ ለእኛም ወደ እግዚአብሔር አብ ለመቅረብ ከክርስቶስ ውጭ ሌላ ምንም ዓይነት አማላጅ፣ ጻድቃን ወይም መላእክት እንደማያስፈልጉንና፣ እርሱ ብቻውን ፍጹም አስታራቂያችን መሆኑን ያስገነዝበናል። ደሙ ዛሬም ስለ እኛ ይናገራል።
በእግዚአብሔርና በሰውም መካከል ያለው መካከለኛው ደግሞ አንድ አለ፤ እርሱም ሰው የሆነ ክርስቶስ ኢየሱስ ነውና፣ በእርሱ በኩል ብቻ ወደ ጸጋው ዙፋን በድፍረት መቅረብ ይገባናል (1ኛ ጢሞቴዎስ 2:5)።
