የመጨረሻውን ዘመን የመንፈሳዊ ክህደት አደጋ ቃሉ ሲገልፅ፡ "ሕይወት የሚገኝበትን ትምህርት የማይታገሡበት ዘመን ይመጣልና፤ ነገር ግን ጆሮቻቸውን የሚያሳክክ ስለ ሆነ፥ እንደ ገዛ ምኞታቸው ለራሳቸው አስተማሪዎችን ያከማቻሉ" ይላል (2ኛ ጢሞቴዎስ 4:3)። ይህ አገላለጽ እጅግ ጥልቅ የሆነ ዘይቤያዊ ትርጉም አለው።
"ጆሮቻቸውን የሚያሳክክ" የሚለው ዘይቤ፣ ልክ አንድ ሰው አካሉ ሲያሳክከው መቧጨርና ማስታገስ እንደሚፈልግ ሁሉ፣ ሰዎችም መንፈሳዊ እውነትን ከመስማት ይልቅ ስጋዊ ስሜታቸውንና ምኞታቸውን የሚያረካ ትምህርት ለመስማት ያላቸውን ጉጉት ያሳያል። የሚፈልጉት ፈውስን ሳይሆን ጊዜያዊ ማስታገሻን ነው።
በግሪክና በሮማውያን ዘመን ፈላስፎችና የንግግር አዋቂዎች ሰዎችን ለማዝናናትና ገንዘብ ለመሰብሰብ ሲሉ አድማጭ የሚፈልገውን ብቻ ይናገሩ ነበር። በመንፈሳዊውም አለም ሰዎች ሀጢያታቸውን የሚወቅስና ወደ ንስሀ የሚጠራ ትምህርት ሲከብዳቸው፣ በሀጢያታቸው እያሉ ሰላም ሰላም የሚሉ የሀሰት አስተማሪዎችን ይፈልጋሉ።
እነዚህ ሰዎች እውነትን አይፈልጉም፤ የሚፈልጉት እነርሱ ባለበት የሕይወት ዘይቤ ላይ ማረጋገጫ የሚሰጣቸውን ሰው ነው። የጆሮ ማሳከክ በሽታ መድሃኒቱ እውነት ቢሆንም፣ እነርሱ ግን እውነትን ትተው የሀሰትን ትምህርት ያቅፋሉ።
ቃሉ ለእኛም ከመድረክ የሚሰበከው ሁሉ ትክክል እንዳልሆነ እንድናስተውልና፣ ስሜታችንን ደስ የሚያሰኘውን ብቻ ለመስማት ከመፈለግ አደጋ ራሳችንን እንድንጠብቅ አጥብቆ ያስጠነቅቀናል። እውነተኛ ፍቅር አንዳንድ ጊዜ መራራ እውነትን ይናገራል።
ስለዚህ እውነትን ወድደው ከመዳን ይልቅ፣ በሀሰት የሚያምኑና በአመፃ የሚደሰቱ ሁሉ ፍርድን ይቀበላሉና ህይወታችንን በንፁሁ ቃል ላይ ልንመሰርት ይገባል (2ኛ ተሰሎንቄ 2:10-12)።
