ሐዋርያው ጳውሎስ ቤተ ክርስቲያንን እንደ ትልቅ ቤት በመመሰል ሲያስተምር፡ "እንግዲህ ማንም ራሱን ከእነዚህ ቢያነጻ፥ ለክብር የሚሆን የተቀደሰም ለጌታውም የሚጠቅም ለበጎም ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ዕቃ ይሆናል" ይላል (2ኛ ጢሞቴዎስ 2:21)። ይህ የክብር ዕቃ በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ ንፁህ የሆነውን አማኝ ያመለክታል።
በትልቅ ቤት ውስጥ ከተለያዩ ቁሳቁሶች የተሰሩ ዕቃዎች ይገኛሉ። አንዳንዶቹ ከወርቅና ከብር ሲሰሩ ሌሎቹ ደግሞ ከእንጨትና ከሸክላ የተሰሩ ናቸው። ወርቅና ብር ለክብር ሲሆኑ፣ እንጨትና ሸክላ ደግሞ ለውርደት ወይም ለተራ አገልግሎት ይውላሉ።
አንድን አማኝ "የክብር ዕቃ" የሚያደርገው ተፈጥሮው፣ ችሎታው ወይም ዝናው ሳይሆን ራሱን ከኃጢአትና ከሀሰት ትምህርት የማንፃቱ ጉዳይ ነው። አንድ ሰው ራሱን ከክፉ ነገር ሁሉ ሲለይ፣ በእግዚአብሔር እጅ የከበረ፣ የተቀደሰና ጠቃሚ መሳሪያ ይሆናል።
ጌታ የሚገለገለው ንፁህ በሆነ ዕቃ ነው። ዕቃው ምንም ያህል ውድ ከሚባል ማዕድን ቢሰራ እንኳ ውስጡ ከቆሸሸ ጌታ ሊጠጣበት አይችልም። ስለዚህ ለበጎ ስራ ሁሉ የተዘጋጀ ለመሆን፣ አስቀድሞ ንስሀ መግባትና የቅድስናን ሕይወት መምረጥ የግድ ነው።
ቃሉ ለእኛም እግዚአብሔር ሊጠቀምብን ከፈለግን ህይወታችንን በንፅህና መጠበቅና ራሳችንን ለእርሱ ፈቃድ አሳልፈን መስጠት እንዳለብን ያስገነዝበናል። ጌታ ዛሬም የሚፈልገው የተለዩትንና የነፁትን ነው።
ስለዚህ እኛም የእግዚአብሔር ማደሪያ ቤተ መቅደስ መሆናችንን አውቀን፣ ስጋንና መንፈስን ከሚያረክስ ነገር ሁሉ ራሳችንን በማንፃት ለእርሱ ክብር የሚሆን ውድ ዕቃ ሆነን መገኘት አለብን (2ኛ ቆሮንቶስ 7:1)።
