“አንቺ ሴት፥ እነዚያ ከሳሾችሽ ወዴት አሉ? የፈረደብሽ የለምን?” (ዮሐ 8:10)። ይህ ታሪክ አንድ ኃጢአተኛ ሰው በእግዚአብሔር ፊት ሲቆም የሚኖረውን ተስፋ መቁረጥና የጌታን አስደናቂ ምህረት አጉልቶ ያሳያል። የሴቲቱ ሕይወት ማለቂያው የደረሰ ቢመስልም ጌታ ግን አዲስ ምዕራፍ ከፈተላት።
ፈሪሳውያን ሴቲቱን ለኢየሱስ ያመጧት ለህጉ ተቆርቁረው ሳይሆን እርሱን ለማጥመድ ፈልገው ነበር (ዮሐ 8:6)። እርሷ በፊታቸው እንደ እቃ እንጂ እንደ ሰው አልታየችም፤ የክፋታቸውና የጥላቻቸው መጠቀሚያ አድርገዋት ነበር። ይህ ደግሞ የሰውን ልጅ ጭካኔ ያሳያል።
ከዚህ ታሪክ የምንማረው ዋናው ነገር የእግዚአብሔር ምህረት ከሰው ሃጢአት እንደሚበልጥ ነው። ህጉ ሞትን ሲፈርድ፣ የህግ ሰጭው ክርስቶስ ግን ምህረትንና አዲስ ጅማሮን ሰጣት (ሮሜ 6:23)። እግዚአብሔር በውድቀታችን ጊዜ እንኳን አይተወንም።
እንዲሁም ክርስቶስ ኃጢአትን እንዳልተቀበለ ነገር ግን ሀጢያተኛውን እንደወደደ እንመለከታለን። አዲስ ሕይወት ከሰጣት በኋላ ዳግመኛ ኃጢአት እንዳትሰራ አስጠንቅቋታል፤ ይህ እውነተኛው የጸጋ ትምህርት ነው። ጸጋ በኃጢአት እንድንቀጥል ፈቃድ አይሰጠንም።
ሁላችንም በእግዚአብሔር ፊት ምህረት የሚያስፈልገን ሰዎች ነን። ቃሉ ለእኛም በሰዎች ላይ ከመፍረድ ይልቅ የክርስቶስን ምህረት እንድናካፍል ያስተምረናል። ፍቅርና ጸጋ የሰውን ሕይወት ይቀይራሉ።
እግዚአብሔር የሰውን መጨረሻ እንጂ መጀመሪያውን አይመለከትም። “ጸጋ ሰውን ባለበት ሁኔታ ይቀበለዋል፣ ነገር ግን ባለበት ሁኔታ አይተወውም” እንደሚባለው፣ ከዚህች ሴት ታሪክ የእግዚአብሔርን አዳኝነትና የሕይወት ለውጥ እንማራለን።
