ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ ወደፊቱ የቤተ ክርስቲያን ፈተና ሲተነብይ፡ "ሕይወት የሚገኝበትን ትምህርት የማይታገሡበት ዘመን ይመጣልና" ይላል (2ኛ ጢሞቴዎስ 4:3)። ሕይወት የሚገኝበት ትምህርት (ጤናማ ትምህርት) የሚባለው ነፍስን የሚያድን፣ ባህሪን የሚቀይርና በእግዚአብሔር ቃል ላይ የተመሰረተ እውነት ነው።
በግሪክኛው "ጤናማ" የሚለው ቃል "ሂጊአይኖ" ሲሆን፣ የህክምና ቃል ሆኖ በሽታን የሚከላከልና ጤንነትን የሚጠብቅ ማለት ነው። የክርስቶስ ወንጌል ለነፍስ ጤናማ ምግብ ነው። ነገር ግን ይህ ጤናማ ምግብ የሰውን ስጋዊ ፈቃድ ስለሚቃረንና መስቀልን መሸከም ስለሚጠይቅ ብዙዎች አይወዱትም።
"አይታገሡም" የሚለው ቃል የሚያሳየው፣ እውነተኛ ትምህርት በሰው ሕይወት ላይ የሞራል ሀላፊነትንና ሸክምን ስለሚያመጣ ሰዎች ያንን መሸከም እንደሚከብዳቸው ነው። ቃሉ ኃጢአትን ሲወቅስ፣ አለማዊነትን ሲኮንንና ቅድስናን ሲያዝ፣ ስጋዊ የሆኑ ሰዎች ይህን ለመቀበል ትዕግስት ያጣሉ።
በዚህም ምክንያት ጤናማውን የእግዚአብሔርን ቃል ትተው ወደ ተረትና ወደ ሰው ፍልስፍና ዘወር ይላሉ። እውነትን መጋፈጥ ሲያቅታቸው የራሳቸውን ምኞት የሚያፀድቅላቸውን የሀሰት ትምህርት እንደ አማራጭ ይወስዳሉ።
ቃሉ ለእኛም ቃሉ ሲወቅሰንና ሲገስፀን በትዕግስትና በትህትና ልንቀበለው እንደሚገባን ያስተምረናል። የመድሃኒት መራራነት ለጤንነት ዋስትና እንደሆነ ሁሉ፣ የቃሉም ወቀሳ ለነፍሳችን ሕይወት ነው።
የእግዚአብሔር ቃል ህያው ነውና፣ የሚሰራ፣ በሁለትም በኩል ከተሳለ ሰይፍ ሁሉ ይልቅ የሚወጋ ነው። የልብንም ስሜትና አሳብ የሚመረምረውን ይህንን ቃል በፍቅር ልንታገሰውና ልንኖረው ይገባል (ዕብራውያን 4:12)።
